Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:12

የማንበብ ልምድን ለልጆች በተለይ ለወላጆች

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዚህ ቀደም ስለ ንባብ ጠቃሚነት ብዙ ተብሏል፡፡
ጥሩ ጥሩ መጽሐፍትን ማንበብ ከበሰሉ ሰዎች ጋር ሸንጎ እንደመቀመጥ ይቆጠራል ይባላል፡፡ የአስተሳሰብ አድማስን ስለሚያሰፋ፣ ሁለገብ እውቀት ስለሚያላብስና በራስ መተማመንን ስለሚያጎለብት ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡ ታዋቂው የአሜሪካ ፕሬዝደንት፣ አብርሃም ሊንከን የንባብን ጥቅም አስመልክቶ ሲናገር፣ ‹‹ማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች የሚገኙት መጽሐፍት ውስጥ ነው፡፡ ያላነበብኩትን መጽሐፍ የሚሰጠኝ እርሱ ከጓደኞቼ ሁሉ የተሻለው ነው›› ብሎ ነበር፡፡

እውነት ነው፣ ማወቅ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ልናገኝ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱና ዋንኛው ንባብ ነው፡፡ ከውይይትና ጠይቆ ከመረዳት ዕውቀት ሊገኝ ቢችልም፣ የተሻለውና አቋራጩ መንገድ ግን ንባብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ዘመን በተራቀቀበት በአሁኑ ወቅት፣ አለማንበብ ራስን ወደ መሃይምነት እንደመለወጥ ይቆጠራል፡፡
ኮንፊሺየስ እንዲህ ይላል “No matter how busy you may think you are, you must find time for reading, or surrender yourself to self-chosen ignorance.” (የቱንም ያህል በስራ ብትወጠር፣ ለማንበቢያ ጊዜ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ በገዛ ፈቃድህ ለመረጥከው መሃይምነት እጅህን ስጥ)
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ንባብን ልምዳቸው ያደረጉ ወጣቶች በተሻለ የስራ መስክ የመሰማራት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም በተወለዱ 17,200 ሰዎች ላይ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ የቅርብ ጊዜ ጥናት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶችን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በመገፋፋት ረገድ ንባብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተረጋግጧል፡፡ በጥናቱ መሰረት፣ በንባብና በስራ ስኬት መካከል ያለው ቁርኝት የተሻለ ክፍያ ወይም ገቢ እስከማስገኘት ይደርሳል፡፡
በዚህ ጽሁፌ ዋና ትኩረቴ ልጆቻችን የንባብን ልምድ ያዳብሩ ዘንድ እንዴት አድርገን መርዳት እንዳለብን አንዳንድ ነጥቦችን ማሳየት ይሆናል፡፡
እርግጥ ነው የዛሬ ልጆች በዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ ማለትም በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ ጨዋታዎች፣ በኢንተርኔት፣ በአይፖድ፣ በሞባይል ስልክና በመሳሰሉት ላይ ስለሚጠመዱ፣ ትኩረታቸውን ወደንባብ የማድረጉ ስራ ለእኛ ለወላጆች የሚያስቸግር ይመስላል፡፡ ሆኖም በእኛ በኩል ያላሰለሰ ጥረት ከተደረገ፣ የሚፈለገውን የንባብ ልምድ በልጆቻችን ውስጥ ማስረፁ ብዙም አይከብደንም፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት እነዚህ የቴሌቪዥን፣ የኢንተርኔትና የቪዲዮ ጨዋታዎች በአስገራሚ ሁኔታ የዕይታ ችሎታን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ናቸው ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በቪዲዮ ላይ የተጣደው ወጣት ትውልድ የዕይታ ብቃቱ ቢጨምርም፣ በአንፃሩ የተጻፉ ነገሮችን የመረዳትና የማገናዘብ ችሎታው ይቀንሳል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን እውነታዎች የተረዳን የልጆቻችን የወደፊት ዕጣ የሚያሳስበን ወላጆች እንኖር ይሆን?
ልጆቻችን በመልካም ባህርይ እንዲታነፁ የቻልነውን እንደምናደርግ ሁሉ፣ በንባብ ልምድም በልፅገው እንዲያድጉ መርዳት ይጠበቅብናል፡፡ ይሄ እኛ ወላጆች ልንተገብረው የሚገባን አንዱና ዋንኛው ሃላፊነታችን መሆኑን ላፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡ በንባብ ልምድ ተኮትኩቶ ያደገ ልጅ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ተመስክሯል፡፡ በትምህርት ላይ ምርምር ያደረጉ አጥኚዎች እንደሚሉት፣ ንባብና ትምህርት በእጅጉ ተያያዥነት ያላቸው ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ በሌላ አባባል፣ አንድ ጥሩ አንባቢ የሆነ ተማሪ ከማያነበው ተማሪ በተሻለ መልኩ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት የማስመዝገብ ብቃት አለው፡፡
ጥሩ አንባቢ የሆኑ ተማሪዎች እያንዳንዱን ዓ. ነገር መረዳትና የአንድን ጽሁፍ ቅርፃዊ አቋም ማወቅ አይቸግራቸውም፡፡ ሃሳቦችን የመጨበጥ፣ ክርክሮችን የመከታተልና የወደፊት ድምዳሜያቸውንም የመተንበይ ችሎታ አላቸው፡፡ እነዚህ በንባብ ልምድ የሚያድጉ ተማሪዎች፣ በንባባቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን የእንግዳ ቃላት ፍቺዎች ለመረዳት ብዙም አይቸገሩም፡፡
ይህም ካልሆነ፣ በቀላሉ መዝገበ-ቃላትን በአጋዥነት መጠቀምን ይችሉበታል፡፡ ባጠቃላይ ጥሩ አንባቢ የሆኑ ተማሪዎች የተፈለገውን የአንድ ጽሑፍ ሃሳብ በፍጥነት የመገንዘብ ችሎታ አላቸው፡፡
ምርምራቸውን በትምህርት ላይ ያደረጉ ባለሞያዎች እንደሚመሰክሩት፣ በንባብና በቃላት መካከል የጠበቀ ቁርኝት አለ፡፡ ወይንም የአንዱ መኖር ለሌላው መከሰት ምክንያት ይሆናል፡፡
በቀላሉ ለመግለፅ፣ ብዙ ቃላትን የሚያውቁ ተማሪዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ የንባብ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ እሰጥ-አገባ የማያስፈልገው ትክክለኛ መረጃ ነው፡፡ በስፋት በተነበበ ቁጥር የቃላት ዕውቀትም በዚያው መጠን ማደጉ እውነት ነው፡፡
ንባብን ልምዳቸው ያደረጉ ልጆች ላቅ ያለ የፈጠራ ችሎታ አላቸው፡፡ ይሄ የሚሆነው ንባቡ እንዲያሰላስሉ ወይንም ጠልቀው እንዲመራመሩ ስለሚገፋፋቸው ነው፡፡ ንባብ ለልጆች የአእምሮ እድገት ይረዳል፤የዓይን ጡንቻዎቻቸውን ያነቃቃል፡፡ ንባብ ትልቅ ትኩረትን የሚጠይቅ ስራ በመሆኑ፣የሚያነቡትን ልጆች የንግግር ክህሎት ያዳብራል፤ በዕለት-ተዕለት ንግግሮች ላይ የሚደመጡ ቃላትንና ሐረጎችን ለመለየት ይረዳቸዋል፤ ወቅታዊ ክስተቶችን ያሳውቃቸዋል፡፡ እንዲሁም ከዘመኑ ፀሐፍት ጋር ያገናኛቸዋል፡፡
በንባብ ጊዜ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ግንዛቤን የመጨበጡ ዓቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ግንዛቤን ሳይዙ ወይም ሳይረዱ ዝም ብሎ ማንበብ፣ ጊዜን በከንቱ እንደማባከን ሊቆጠር ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ንባብ በመጽሐፉ ገፅ ላይ የሰፈሩትን ቃላት ትርጉም አልባ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰዎች የሚያነቡት ጸሐፊው ለማስተላለፍ የፈለገውን ለመረዳትና በሚያገኙት መረጃዎችም ለመጠቀም ነው፡፡ እውነታን ለማግኘት፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ለማዳበርና ለመደሰት ወይም ለመዝናናትም ይሁን፣ ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡ ከንባብ የሚገኝ ግንዛቤ፣ ትንታኔና መረጃ ለትምህርት ውጤታማነት ወሳኝ ነው፡፡ ይሄንን ደሞ ተግባራዊ ለማድረግ፣ አንብቦ የመረዳት ክህሎት ያስፈልጋል፡፡
ያለበለዚያ ከንባባችን የተፈለገውን መረጃ ሳናገኝ እንቀራለን፡፡
ግንዛቤ የጎደለው ንባብ ጉዳት አለው፡፡ የተማሪውን የትምህርት ስኬት ያጨናግፈዋል፡፡ ችግሩ በመድሃኒት ብልቃጥ ላይ የተጻፉ ምክሮችን፣ አደገኛ ኬሚካል በያዙ እሽጎች ላይ የሚለጠፉ የማሳወቂያና የማስጠንቀቂያ ጽሁፎችን አንብቦ አስካለመረዳት የሚደርስ ነው፡፡ በከፋ መልኩም ሲታይ አንብቦ የመረዳት ክህሎትን ማጣት የመጨረሻ ውጤቱ፣ ከድህነትና ወንጀል ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለምሳሌ በአንድ ወቅት በተደረገ ጥናት፣ በአሜሪካ እስር ቤት ውስጥ ከነበሩት እስረኞች 60 ከመቶው የነበራቸው የንባብ ክህሎት ደረጃ ከ4ኛ ክፍል በታች ነበር፡፡ በዚያው ሃገር በእስር ላይ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ሰማንያ አምስት ከመቶ የሚሆኑት የተማሩ መሃይማን ነበሩ፡፡ የተማሩ መሃይማን የሚባሉት ማንበብ መጻፍ የሚችሉ ቢሆኑም፣ ባለባቸው አንብቦ የመረዳት ከፍተኛ ችግር ምክንያት የየዕለት ህይወታቸውን መምራት ወይም መለወጥ የተሳናቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ያለበቂ የንባብ ክህሎት 4ኛ ክፍል ከደረሱ ተማሪዎች ውስጥ 2/3 ኛዎቹ መጨረሻቸው እስር ቤትና የማገገሚያ ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ ለመገንዘብ የምንችለው አንብቦ የመረዳት ክህሎትን ማሳደግ የካበተ እውቀት አንዲኖረን፣ በስራችንና በህይወታችንም የተሳካልንና የተሻልን እንድንሆን ያስችለናል፡፡
ስለዚህም ከዚህና መሰል ችግሮች ለመዳንና በሁሉም ዘርፍ የተሻሉ ዜጎችን ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ወላጆች በልጆቻችን ውስጥ የምናሰርፀው የንባብ ልምድ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይችላል፡፡ ከት/ቤት በፊት ቀድመው ንባብ የሚጀምሩ ሕጻናት፣ ጥሩ የቋንቋ ክህሎትና ካላነበቡት ሕፃናት ይልቅ ነገሮችን በተሻለ ሁኔታ የመገንዘብ ችሎታ እንደሚኖራቸው ይነገራል፡፡ በት/ቤት ብቻ ሳይሆን በሌላውም መስክ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት ንባብ አስፈላጊ ነው፡፡ ፎርብስ መጽሔት በአንድ ዕትሙ፣ ‹‹if you want to succeed in business, read more novels,›› ብሎ ነበር፡፡ ‹‹በንግድ ስራህ ውጤታማ መሆን ከፈለግህ፣ ተጨማሪ ልቦለዶችን አንብብ›› ማለቱ ነው፡፡ ልቦለድ ማንበብ የሰዎችን ውስጣዊ ብስለት ያሳድጋል ባይ ነው - መጽሔቱ፡፡ ሰዎች ስለራሳቸውና ስለሌሎች ያላቸውን እውቀት ለማጠናከር፣ አዎንታዊ ዝምድናዎችን ለማሳደግ፣ ከሌሎች ጋር የሚፈጠር የተሻለ ግንኙነትን ለማዳበር እንዲሁም ሌሎችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ንባብ የሚያስገኛቸውን ፋይዳዎች ጽሑፉ ያትታል፡፡
ስለዚህ ልጆቻችን የንባብን ልምድ ያዳብሩ ዘንድ እንዴት እንርዳቸው የሚለው ዋና እና አስፈላጊ ጥያቄ ይሆናል፡፡በልጆቻችን ውስጥ የንባብ ልምድን የማስረፁ ተግባር በየትኛውም የልጅነት ዕድሜያቸው ላይ እያሉ ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን፡፡ ሆኖም፣ቢቻል ልጆቹ ት/ቤት ከመግባታቸው በፊት ስራው ቢጀመር የተሻለ እንደሚሆን በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በርግጥም ከፍ ከፍ ያሉትን ልጆች እንዲያነቡ ከመጎትጎትና ከመጫን ይቀላል፡፡
በዚህም መሰረት ልጆቻችን ገና ት/ቤት ያልገቡ ከሆነ፣ ራሳችን እያነበብንላቸው ልምዱን እያዳበሩ እንዲያድጉ ልናግዛቸው እንችላለን፡ መጽሐፍትን ለልጆቻችን የማንበቡ ልምድ ከሚኖሩት በርካታ ፋይዳዎች መካከል የሚከተሉትን ማየት እንችላለን፡፡
ጠንካራ የወላጅ-ልጆች ግንኙነት – ልጆቻችንን በእቅፋችን ሸጉጠን ስናነብላቸው ከምንሰጣቸው መንፈሳዊ ደስታ በተጨማሪ፣ በእኛና በእነሱ መካከል ያለውን ትስስር እያጠናከርን መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡ልጆቻችን በምናነብላቸው ታሪክ የራሳቸውን ደስ የሚል፣ የማይረሳ ዓለም በአእምሯቸው ይቀርፁ ዘንድ ያስቻልናቸውን ወላጆቻቸውን ያደንቃሉ፤ ይወዳሉ፡፡
የትምህርት ብቃት – ለልጆቻችን የምናነበው ታሪክ ለወደፊቱ የት/ቤት ሕይወታቸው መሰረት ነው፡፡ በርካታ ጥናቶች የሚያሳዩት ይሄንኑ ነው፡፡ በእርግጥም ከመደበኛ ት/ቤት በፊት ልጆች ከንባብ ጋር እንዲተዋወቁ ማድረግ ለወደፊቱ ትምህርታቸው ስምረት የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡
መሰረታዊ የንግግር ክህሎት – የቅድመ መደበኛ ትምህርት ንባብ የልጁን መሰረታዊ የቋንቋ ችሎታ በማዳበሩ ረገድ ላቅ ያለ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ልጆቻችን የምናነበውን ተከትለው ድምፆችን ደጋግመው ይጠራሉ፤ አስመስለው ይናገራሉ፤ ወይም ለማንበብ ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት የልጆቻችን የቋንቋ ችሎታቸው የሚሻሻልበት አጋጣሚው ይፈጠራል፡፡
የንባብ መሰረታዊ ዕውቀት – ልጆች ማንበብን ችለው አይወለዱም፡ ንባብ ከግራ ወደቀኝ ስለመነበቡም አስቀድመው የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ቃላት ከምስል የተለዩ መሆናቸውን አውቀው አይወለዱም፡፡ ስለዚህ ማንበብን ማሳየት ወይንም ማሳወቅ በእጅጉ ለልጆቻችን ይጠቅማቸዋል፡፡
የተሻለ የመግባቢያ ክህሎት –በምናነብላቸው ጊዜ ልጆቻችን ስለራሳቸው የመግለፅና ለሌሎች የማውራት ዝንባሌዎችን ያሳያሉ፡ በታሪኩ ውስጥ ባሉት ገፀ-ባህርያት መካከል የሚያስተውሉት ዝምድናና ትስስር፣እንዲሁም ከእኛ ከምናነብላቸው ወላጆቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት፣ የልጆቹን መሰረታዊ የመግባቢያ ክህሎትእንዲያድግ ይረዱታል፡፡
የተሻለ የማስተዋል ክህሎት –ሌላው የቅድመ- ት/ቤት ንባብ አስፈላጊነት የሚመዘነው ልጆቻችን ረቂቅ ፅንሰ-ሐሳቦችን የመያዝና የማገናዘብ ችሎታቸውን በማዳበር ረገድ በሚኖረው ጠቀሜታ ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊነትን የማሳየት፣ ሳቢያና ውጤቶችን የማወቅና የፍርድ አደላዳይነትን ምንነት እንዲገነዘቡ ያግዛቸዋል፡፡
አዳዲስ ልምዶችን መቅሰም – ተገቢ የሆኑ (የተመረጡ) መጽሐፍትን ለልጆቻችን የማንበቡ ልምድ፣ ልጆች ወደፊት ለሚያጋጥማቸው ውስጣዊ ጭንቀት፣ ንባብ ማርከሻ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ልጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ት/ቤት የመሄድ ጭንቀት ሊኖርበት ይችላል፡፡
ት/ቤት ከመግባቱ በፊት የምናነብለት ታሪክ፣ ለልጁ የውጩውን አዲስ ልምድ በማስተዋወቅና ኋላም ላይ ሊከሰት የሚችለውን ጭንቀት በማርገብ ረገድ ጥሩ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት ልጁ ጥሩ ተሞክሮ ስለሚኖረው፣ ት/ቤት የመሄዱ ጉዳይ የተለመደ ክስተት መሆኑን እያወቀ ይመጣል፡፡
እንደውም አንዳንድ ጊዜ በንባቡ ውስጥ እንዳሉት ተማሪ ገፀ-ባህርያት፣ ልጆቻችን ወደ ት/ቤት እንዲወሰዱ ሊጠይቁን ይችላሉ፡፡
ትኩረትንና ስነ-ስርዓትን ማዳበር – ምናልባት ገና በጅምሩ ልጆቻችን ትኩረታቸው ወደ ንባቡ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በሂደት ቀልባቸውን ወደ እኛ ወይም ወደ ንባቡ መመለሳቸው አይቀርም፡፡ በቅድመ - ት/ቤት ንባብ ሳቢያ የሚዳብሩት ከአንብቦ መረዳት ጋር የሚመጡት ጥብቅ ግለ - ስነ-ስርዓቶች፣ የትኩረት መጠን ከፍ ማለትና የተሻለ የማስታወስ ችሎታ በመደበኛው የትምህርት ቆይታቸው ላይ ይጠቅማቸዋል፡፡
ንባብ አስደሳች መሆኑን ማወቅ – ቅድመ - ት/ቤት የሚዳብረው የንባብ ልምድ፣ ልጆች መጽሐፍት አስደሳች እንጂ አሰልቺ አለመሆናቸውን ለመገንዘብ ይረዳቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚያድጉ ሕፃናት መጽሐፍትን ከቪዲዮ መጫወቻዎች፣ ከቴሌቪዥንና ከሌሎች መሰል የመዝናኛ ዘዴዎች አስበልጠው የመምረጥ ዝንባሌን ያሳያሉ፡፡ለልጆቻችን ምን እናብብላቸው? በተለያዩ ርእሰ-ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን ለልጆቻችን ብናነብላቸው፣ ልጆቹ ከተለያዩ ቃላት፣ ምስሎችና ባጠቃላይ ከአዲሱ ውጫዊው ዓለም ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚው ይፈጠርላቸዋል፡፡ በሚከተሉት ርእሰ-ጉዳዮች ስር የተጻፉትን መጽሕፍት ለልጆቻችን እንድንመርጥላቸው ይመከራል፡፡
የሳይንስ ልቦለዶች – በእውነታው ዓለም ያልተለመዱ እንደሚናገር ውሻ፣ በራሪ ሰው፣ በመሬት ስር ስለሚገኝ በሃሳብ የተፈጠረ ዓለምና በሌሎችም መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የልጆች መጽሐፍት የልጆቻችንን ያስተሳሰብ አድማስ በማስፋት ረገድ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡
ታሪካዊ ልቦለዶች – በጥንቃቄና በጥራት የተጻፉ ታሪካዊ ልቦለዶች፣ ያለፉ ክስተቶች ህይወት ዘርተው ለልጆቹ እንዲታዩአቸው ያስችሏቸዋል፡፡
የህይወት ታሪኮች– በህይወት ታሪኮች ላይ የተፃፉ መጽሐፍት ልጆቻችንን በመቀስቀስ ወይንም በመነሸጥ በትምህርት ላይ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያግዛሉ፡፡ ስለታዋቂ የሃገር መሪዎች፣ ስለፈላስፋዎች፣ ስለፈጠራ ሰዎች፣ ስለትምህርት ባለሞያዎችና ሳይንቲስቶች የሚተርኩ መጽሐፍትን ማንበብ ይመከራል፡፡ በንባብ ወቅትም ልጆቻችን ከነዚህ ታላላቅ ሰዎች ጋር የመተዋወቁ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡
መረጃ-ሰጪ መጽሐፍት– እሳተ-ጎሞራ እንዲፈነዳ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከዓለም በጣም ረጅሙ ሰው ቁመቱ ምን ያህል ይሆናል? ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከየት ተገኘ? ዝናብ እንዴት ይመጣል?...ልጆች ብዙ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይወዳሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዓይነቶቹ መረጃ ሰጪ መጽሐፍት ለጥያቄዎቻቸው መልሶችን በመስጠት ረገድ ይረዷቸዋል፡፡ መሰል መጽሐፍትን ስንመርጥ በቅርቡ ስለመጻፋቸውና ትክክለኛውን መረጃ ስለመያዛቸው ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ግጥሞች– መነበብ ያለባቸውን ያህል ግጥሞች በሰፊው አይነበቡም፡፡ በርካታ የልጆች ግጥሞች የተሰባሰቡባቸው መጽሐፍት ልጆቻችንን በሳቅ ያስፈነድቋቸዋል፤ ፍፁም በደስታ ይሞሏቸዋል፡፡ ግጥሞች አብዛኛውን ጊዜ አጫጭሮች ናቸው፡፡ ሲነበቡ የሚሰጡት ድምፅ አስደሳች ነው፡፡ ስለዚህም ግጥሞች ንባብን ለሚርቁና ለሚሰለቹ ልጆቻችን በቀላልነታቸው ተመራጭ ናቸው፡፡ ጥንት በልጅነታችን ያነበብናቸው የአያ ጅቦ፣ የእንኮዬ ጦጢት፣ የላሜቦራ፣ የአያ አንበሴ፣ የቀበሮ፣ የተንኮለኛው ከበደና መሰል ታሪኮች ትዝ እንደሚሏችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አቤት ደስ ሲሉ! የነዚህ ዓይነት ታሪኮችንና ከላይ በተጠቀሱት ርዕሶች የተመለከቱትን መጽሐፍት ገዝተን ለልጆቻችን የምናነብበትና ከፍ ከፍ ያሉትንም በራሳቸው እንዲያነቡ የምንገፋፋበት ጊዜው አሁን ነው፡፡በአጠቃላይ የትኛውንም ንባብ ወይንም መጽሐፍ ለልጆቻችን ብንመርጥም፣ አጠቃቀሙን ወይንም አነባበቡን አስደሳች ልናደርገው ይገባል፡፡ በታሪኩ ውስጥ የተዋወቅነውን በአስማት የተገነባ ቤተ-መንግስት በሃሳብ መጎብኘት፣ ከዝነኛው ሰው ጋር መተዋወቅ፣ ለጥያቄዎቻቸው በራሳቸው ጥረት መልስ ማግኘት መቻል፣ አጭር ደስ የሚል ግጥም ማንበብ፣ በቃል አጥንቶ መልሶ ማለት… እነዚህ ሁሉ ልጆቻችንን እንዴት እንደሚያስደስቷቸው አስበን እናውቃለን?

Read 10763 times