Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:32

ፍቅሩ ተፈራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ አምባሳደር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በሶስት አህጉራት ተዘዋውሮ እግር ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ በመጫወት ትልቅ ስም ያተረፈው ኢትዮጵያዊው ፍቅሩ ተፈራ ለሜሳ ማክሰኞ ዕለት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዟል፡፡ የ26 ዓመቱ ፍቅሩ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ክለብ ለመጫወት ወደዚያው አገር ሲሄድ የሰሞኑ ለ3ኛ ጊዜው ሲሆን ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመካተት በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ወደ አውሮፓ ክለቦች የሚዛወርበትን እድል ለማመቻቸት ነው፡፡ እግር ኳስ በክለብ ደረጃ በአዳማ ከነማ በመጫወት የጀመረው እና አሁን 26ኛ ዓመቱን የያዘው ፍቅሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከ8 ዓመታት በፊት ለሁለት የውድድር ዘመናት 55 ጨዋታዎች አድርጎ 26 ጎሎች ከማግባቱም በላይ ከክለቡ ጋር ሁለት የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫዎች እና አንድ የሱፕር ካፕ ድልን አጣጥሟል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 25 ጨዋታዎችን በማድረግ ሰባት ጎሎችን በስሙ ያስመዘገበው ፍቅሩ ተፈራ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ኢትዮጵያን በተለያየ የዓለም ክፍል ለማስጠራት መብቃቱን እንደከፍተኛ ስኬት ይቆጥረዋል፡፡ ፍቅሩ ተፈራ ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በደቡብ አፍሪካ ክለቦች ስለነበረው ቆይታ፤ በአውሮፓ በቼክ እና ፊንላንድ ክለቦች እንዲሁም በኤስያ በቬትናም ክለብ ስላሳለፈው ልምድ ይናገራል፡፡ በቅርብ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የነዋሪነት መታወቂያውን ያገኘው ፍቅሩ በጆሃንስበርግ ከተማ መኖርያውን ገዝቷል፡፡ ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና ዝግጅት እና በተያያዥ ጉዳዮች የሰጣቸው ምላሾች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የዝውውር ታሪክህን አጠቃላይ ሂደት በዝርዝር ግለጽልኝ ?
የመጀመሪያው የውጭ አገር ክለቤ የደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ፓይሬትስ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እየተጫወትኩ በመጀመሪያ የዝውውር ጥያቄ የቀረበልኝ ከሁለት የግብጽ ክለቦች ነበር፡፡ እነዚህ ክለቦች ብቃቴን ለመፈተሽ በተለያዩ ጊዜያት ሁለት ቪዛዎች እና የደርሶ መልስ ትኬቶች በመላክ ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር፡፡ በነበርኩበት ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ በጣም በመፈልጌ ግን ምላሽ አልሰጠሁም፡1 በወቅቱ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ አሰልጣኝ የነበረው ሚቾ በክለቦቹ የቀረበልኝን ጥያቄ አስመልክቶ ሲመክረኝም በጊዮርጊስ ክለብ በመቆየት ሌሎች አማራጭ ዕድሎችን መጠበቅ እንዳለብኝም ነግሮኛል፡፡ ከዚያ በኋላ በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ሆኜ ታንዛኒያ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕ ላይ ስጫወት በስፍራው የነበሩ የኦርላንዶ ፓይሬትስ ክለብ ኤጀንቶች ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ጋር በመነጋገር ለዝውውሩ እስከ 50ሺ ዶላር ከፍሎ ለ2 ዓመት የምጫወትበት ኮንትራት አስፈርሞኛል፡፡ 1 ዓመት ከተጫወትኩ በኋላ ሌላው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ፈለገኝ፡
በኦርላንዶ ፓይሬትስ ክለብ እየተጫወትኩ በነበረኝ ምርጥ ብቃት ሳይሆን አይቀርም;; ለኦርላንዶ ፓይሬትስ 19 ጨዋታዎች አድርጌ 2 ጎሎች ብቻ በማስመዝገብ ባሳለፍኩት የውድድር ዘመን ክለቡ በሊጉ 4ኛ ደረጃ ይዞ ጨረሰ፡፡ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ በኦርላንዶ ፓይሬትስ የነበረኝን የ2 ዓመት የውል ኮንትራት በማፍረስ የወሰደኝ በአገሪቱ ደረጃ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የዝውውር ሂሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ለሱፐር ስፖርት ዩናይትድ 3 ዓመት ለመጫወት ገብቼ ከክለቡ ጋር በሁለት ተከታታይ የውድድር ዘመናት ሁለት የግል ሻምፒዮናነት ክብሮችን አገኘሁ፡፡በሁለት የውድድር ዘመናት በሁሉም ውድድሮች ላይ ለሱፐር ዩናይትድ 14 ጐሎችን አግብቻለሁ፡፡
ለሱፐር ስፖርት ዩናይትድ 2 ዓመት ከተጫወትኩ በኋላ ቀሪውን 1 ዓመት ወደ አውሮፓ የማቀናበት እድል ተፈጠረ፡፡
ወደ ቼክ ሪፖብሊክ ነበር ፡፡ ዝውውሩን የፈፀምኩት ከዚያው አገር ከሚገኙ ክለቦች በመጣ ፍላጐት ነው፡፡ የቼኩ ክለብ ምላዳ ቦሪስላቭ ይባላል፡፡ ለክለቡ የፈረምኩት በብቃት ነው፡፡ አውሮፓ ላይ በክለብ ደረጃ ለመጫወት በሚኖርህ ብቃት እንጅ በዘመድ አይደለም ፡፡ ወደ ቼኩ ክለብ የተዛወርኩት ከደቡብ አፍሪካ ክለብ የተሻለ ጥቅም ብቻ በማግኘቴም አይደለም፡ በሌላ ዓለም ክፍል በእግር ኳስ አገሬን መወከል ፍላጐት ስለነበረኝ ጭምር ነው፡፡ በዚሁ የቼክለብ እየተጫወትኩ ወደ ሮማኒያ ሊግ የመዛወርም ዕድል ተፈጥሮልኝ ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡
በምላዳ ቦሪስላቭ ለ2 ዓመት ለመጫወት በፈረምኩት ኮንትራት 1 ዓመት ስጫወት በኋላ ክለቡ በሊጉ 4ኛ ደረጃ ይዞ ሲጨርስ የገንዘብ ችግር ገጠመው፡፡ በእርግጥ በቼኩ ክለብ ሲጫወት መኖሪያ ቤት ሰጥተውኝ ጥሩ ክፍያ እያሰቡልኝ ነበር፡፡ በውላችን መሰረት ከ1 ዓመት በኋላ ይሄው ጥቅማጥቅም ማደግ ነበረበት፡፡ ክለቡ በገጠመው ችግር ጭራሽ አስቀድሞ የሚገኘው ጥቅም ሊቀነስ እንደሚችል ተገለፀልኝ፡፡ አንዳንድ የቼክ ክለቦች በአውሮፓ ውድድሮች ተሳታፊ ስለነበሩ ሊጉን ጠንካራ አድርጐታል፡፡ በምላዳ ቦሪስላቭ ያደረግኩት 9 ጨዋታዎችን ብቻ ነበር፡፡ 3 ጐል አግብቻለሁ፡፡
በወዳጅነት ጨዋታ በደረሰብኝ ጉዳት 5 ጨዋታዎች አምልጠውኛል፡፡ ቅድም እንደነገርኩህ ቦሪስላቭ በበጀት እጥረት የሚሰጠኝን ክፍያ እንደሚቀነስ ሲያሳውቀኝ ወደ ደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ለመመለስ ወሰንኩ፡፡
አውሮፓ እያለሁ ከሱፐር ስፖርት ዩናይትድ አሰልጣኝ ጋቪን ሃንት ጋር በየጊዜው እንገናኝ ስለነበር ወደ ሱፕርስፖርት ዩናይትድ በድጋሚ የምመለስበት ሁኔታ በቀላሉ ተመቻቸ፡፡ በ2010 እ.ኤ.አ ወደ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ተመልሼ ስጫወት ክለቡ በሊጉ 3ኛ ደረጃ ይዞ ጨረሰ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን ኤጀንቴ ወደ ፊንላንድ ክለብ የምዛወርበትን ዕድል አገኘ፡፡
በፊንላንድ የክለቦች ሊግ ወቅቱ የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ በአጭር የኮንትራት ቅጥር ኮፒዩ ለተባለው ክለብ ፈርሜ ለግማሽ የውድድር ዘመን በ8 ጨዋታዎች ተሰለፍኩ፡፡ ሁለት ጐሎችን አገባሁ፡፡ በዚያ አገር የነበረኝ ቆይታ ጥሩ ልምድ አግኝቼበታለሁ፡፡
ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ቬትናም ሊግ የምዛወርበት ዕድል ተፈጠረ፡፡ ታኖሃ የተባለ ክለብ ነበር፡፡ የቬይትናም ሊግ ጥሩ ፉክክር ያለበት፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወደዚያ አገር ክለብ የገባሁ ብቸኛ ሰው ሳልሆንም አልቀረም፡፡ በሊግ ውድድሩ ግን እኔ ብቻ ሳልሆን ከአፍሪካ፣ ከብራዚልና ከመላው ኤሽያ በርካታ ተጨዋቾች በሁሉም ክለቦች ይገኙ ነበር፡፡
ተመልካችም በብዛት ስታድዬም ይገባል፤ ክለቦችም በባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡ እናም ገብቶ ለመጫወት እድል ያገኘ ማንም ተጨዋች የቬይትናም ሊግ ትልቅ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ እኔ በዚያ ሊግ ለታኖሃ 21 ጨዋታዎችን በማድረግ 3 ጎሎችን በስሜ አስመዝግቢያለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊው ተብሎ ስሜ በዚያ አገር ሲጠራም ያስደስተኝ ነበር፡፡
ለሱፐር ስፖርት ዩናይትድ እየተጫወትክ አንድ ጐል አግብተህ ወደኋላ አክሮባት በመገልበጥ ደስታህን የገለፅክበት ፎቶን ተመልክቼ ስገረም ነበር፡፡ ጎሏ ምን አይነት ነበረች፡፡ ምርጥ ጐሎች ማግባት ልማድህ ነው እንዴ?
በአክሮባት ወደ ኋላ በመገልበጥ ደስታዬን የገለፅኩባት ምርጥ ጐል በሱፕርስፖርት ማልያ ተሰልፌ በመቀስ ምት በመጀመሪያው ክለቤ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ላይ ያገባኋት ነበረች፡፡ ጐሏ ለዓመቱ ምርጥ ጎል ምርጫ ተወዳድራ ከመሃል ሜዳ ባገባ ልጅ ተበልጬ ተሸንፊያለሁ፡፡ በመቀስ ምት ማግባት ያስደስተኛል፡፡ ለሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም እየተጫወትኩ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሊቢያ 3ለ1 ስንሸነፍ የማጽናኛዋን ጐል ያገባሁት በመቀስ ምት ነበር፡፡ ለቬትናሙ ክለብ ስጫወትም በተረከዝ ጐል አግብቼ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቻለሁ በጊዮርጊስም እያለሁ ምርጥ ጐሎችን አገባ ነበር፡፡
አሁን እንግዲህ ለ3ኛ ጊዜ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልትመልስ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሊግ እግር ኳስ መጫወትን ትወደዋለህ፡፡ ለምን?
የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስን ምርጫዬ የማደርገው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡
የመጀመሪያው በዚያ አገር ያለው የሊግ ውድድር በአውሮፓ ደረጃ የሚታይ በመሆኑ ነው፡
የደቡብ አፍሪካ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስብ በገንዘብ አቅም፤ በአስተዳደርና በሌሎችም መሰረተልማቶቻቸው በተሟላ እና በፕሮፌሽናል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው አገሩንም አውቃለሁ፡፡ በተጫወትኩባቸው ክለቦች በነበረኝ ብቃት እና ውጤታማነት ብዙ እውቅና አግኝቻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ነፃ አድርጐኛል፡፡ ልክ በአገሬ እንደምጫወት ያህል ይሰማኛል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የአገሬን ስም በከፍተኛ ደረጃ ማስጠራቴም ያኮራኛል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የአገሬው ሰው የተፈራ ቤተሰብ (Tefera family) እያለ ሲጠራቸው አጋጥሞኛል፡፡
ከአፍሪካ ዋንጫው በፊት ከ5 በላይ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ለዝውውርህ ጥያቄ ሲያቀርቡልህ ከውሳኔ ላይ የደረስከው ምን አወዳድረህ ነው?
ባለፉት አራት ወራት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ እንድመለስ ብዙ የዚያ አገር ክለቦች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ቀዳሚው እንደ ቤተሰብ የምመለከተው የመጀመሪያው ክለቤ ሱፐር ስፖርት ድናይትድ ነው፡፡ ሜሞሌዲ ሰንዳውንስ የተባለው ክለብ ባለቤትም ወደ እነሱ እንድዛወር ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡
ዘንድሮ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፕሪሚዬር ሊግ ያደገ ቺፓ ዩናይትድ የተባለ ክለብም ጠይቆኛል፡፡ በመጨረሻም ዝውውሬን የፈለገውና ልፈርምለት የወሰንኩለት ክለብ ደግሞ ፍሪ ስቴት ስታርስ የተባለው ሆኗል፡፡
የምዛወርበትን ክለብ ለመምረጥ የተከተልኩት መስፈርት አጭር የኮንትራት ቅጥር የሚያደርግልኝን በመፈለግ ነው፡፡
ከሁሉም ክለቦች አጭር የኮንትራት ቅጥር ለማድረግ የፈለገው ፍሪ ስቴት ስታርስ ነበር፡፡ ሌሎቹ ክለቦች በረዥም ጊዜ ኮትራት የሁለትና ሦስት ዓመት ቅጥር በመፈለጋቸው አልተቀበልኳቸውም፡፡
በእርግጥ የዝውውሩ ሂሳብ እንደ ኮንትራቱ ርዝመት የሚወሰን ነበር፡፡ እንደ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ አይነት ክለብ ለሦስት ዓመት ሲልገኝ ብዙ እንደሚከፍሉኝ አውቃለሁ፡፡ አጭር ኮንትራት ሊሰጠኝ የፈለገው ፍሪ ስቴት ስታርስ የዝውውር ሂሳቡ ቢያንስም ከእቅዴ ጋር በመጣጣሙ መርጨዋለሁ፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ፍላጐትና ዕድልም ስላለኝ ውሳኔዬ ወደዚሁ ክለብ ለማቅናት ሆኗል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ክለቦች በዚህ ወቅት በተለየ ሁኔታ ያንተ ዝውውር ለምን ፈለጉ?
በደቡብ አፍሪካ የነዋሪነት ፍቃድ ያገኘሁበትን መታወቂያ በመያዜ መሰለኝ፡፡ ይህ መታወቂያ በደቡብ አፍሪካ ሊግ በሚሳተፍ ክለብ ስገባ እንደ ውጭ አገር ዜጋ ሳይሆን እንደ ደቡብ አፍሪካዊ የመጫወት ዕድሉን ፈጥሯል፡፡ በዚያ አገር ሊግ አንድ ክለብ 5 ፕሮፌሽናል የውጭ አገር ዜጋ ተጨዋቾች ማሰለፍን ይፈቀዳል፡፡
ይሄው ደንብ ግን የነዋሪነት መታወቂያ በመያዜ ለእኔ አይሰራም፡፡ ይህም ሁኔታ የክለቦቹን ፍላጐት ፈጥሮታል፡፡
ክለቦቹ ስለዚሁ የደረስኩበት ደረጃ በወኪሌ በኩል ይሰማሉ፡፡ ከፈለጉኝም ራሳቸው ይከታተላሉ፡፡ የነዋሪነት መታወቂያው ጊዜያዊ ዜግነት የሚሰጥ እንጅ ዜግነት አይደለም፡ አገልግሎቱ የመኖሪያ ፍቃድ ብቻ ነው፡፡ እኔ በደቡብ አፍሪካ ስኖርና ስመላለስ 6 ዓመታት ሆኖኛል፡፡
የነዋሪነት መታወቂያውን እንዳገኘሁ እንደ ቤተሰብ የምመለከተው ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ለዝውውሬ ጥያቄ በማቅረብ ቅድሚያውን ወስዷል፡፡
በማንኛውም ጊዜ በተለይ ዕረፍት ባለኝ ሰዓት በተደጋጋሚ ወደ ሱፐር ዩናይትድ እየተመላለስኩ ከክለቡ ጋር ልምምድ እሠራለሁ፡፡
በሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ስጫወት ለ2 ጊዜያት የደቡብ አፍሪካ ሊግ ሻምፒዮናትን በማግኘት ስለተሳካልኝ ከክለቡ ደጋፊዎች፣ ኃላፊዎች፣ ተጨዋቾችና አሰልጣኙ ጋር በጣም የቅርብ ግንኙነት አለኝ፡፡
ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ወደ አውሮፓ ክለቦች የመዛወር ዕድሉ እንዴት ነው?
በዝውውር ደላልነት አብሮኝ የሚሠራው ባለሙያ ክሮሽያዊ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሊግ ለሚጫወቱ ትላልቅ ተጨዋቾች ኤጀንት ሆኖ በመስራት የሚታወቅ ሲሆን ኢቪካ ስታንኮቪች ይባላል፡፡ ከተለያዩ የአውሮፓ ኤጀንቶች ጋር በፈጠረው ግንኙነት ስለሚኖረኝ ዕድል መረጃ አግኝቷል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ክለቦች ካለኝ ልምድ ባሻገር በአውሮፓ እና በእስያ ለሚገኙ ክለቦች በመጫወት ያካበትኩት ልምድም እንደሚያግዘኝም ገልፆልኛል፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመጫወት የተጨዋችነት ዘመኔ ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት መታወቁም ለሚያስፈልገው የዝውውር ሰነድ ጠቃሚ መረጃ ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካ ሊግ በአውሮፓ ደረጃ በቴሌቭዥን ስርጭቱ ሽፋን የሚያገኝ መሆኑም ሌላ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን እንዴት አገኘኸው? ያንተ አስተዋጽኦ ምን ነበር?
ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የአሁኑ ትውልድ ተጨዋቾች ብዙ ለፍተውበት ነው፡፡ ለዚህ ደረጃ መብቃታቸው ለቀጣዩ ትውልድ የእግር ኳስ ስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መነቃቃትና ተስፋን ይፈጥራል፡፡ በእርግጥ ባለፈው 1 ዓመት በተደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎቹ ላይ አልነበርኩም፡፡
ግን ላለፉት 8 ዓመታት ለብሔራዊ ቡድኑ በትጋት አገልግያለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በሴካፋ ውድድር የተስፋ ቡድኑ አምበል ሆኜ መጫወቴ ይታወቃል፡፡ ባለፈው 1 ዓመት ቬይትናም ሄጄ በነበረበት ወቅት ለብሔራዊ ቡድኑ ሳልሰለፍ የቀረሁት ከፌዴሬሽኑ የጥሪ ወረቀት ስላልመጣልኝ ነበር፡፡ የተሰጠው ምክንያት ስለምትጫወትበት ክለብ ብዙ መረጃ የለንም የሚል ነበር፡፡ ብዙ አያሳምንም፡፡ ግን ማንንም መውቀስ አልፈልግም፡ ፌዴሬሽኑ ያለሁበትን እንቅስቃሴ መከታተል ነበረበት፡፡
እኔ ለአገሬ አስተዋጽኦ እንዳደርግ ጥሪ ሲደርግልኝ ሁሌም ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡
ከብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ጋር መልካም ግንኙነት አለኝ፡፡ ብዙዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ መጥተው እንዲጫወቱ ስለምፈልግ በዚያ በኩል ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን የተከታተልኩት ደቡብ አፍሪካ ሆኜ ነበር፡፡ ጨዋታውን ለቴሌቭዥን እየተመለከትኩ በነበረኝ ግንኙነት አንዳንድ ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት አደርግ ነበር፡፡ አገሬን ስለምወድ ነው፡፡ የትም አገር ብሆን ከአገሬ እግር ኳስ ጋር ያለኝ ግንኙነት አይቋረጥም፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ እጠራለሁ ብለህ ታስባለህ?
አዎ፡፡ ወደዚያ የምሄደው አድራሻዬ በግልጽ ታውቆ በፌዴሬሽኑ በኩል ጥሪ እንዲቀርብልኝ ነው፡፡ ሁሉም ወገን አሁንም እንደምፈልግ እንዲያውቅ እፈልጋለሁ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ሊግ ያለሁት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ተጨዋች ነኝ፡፡በዚህ ታሪኬም የአገሬን እና የራሴን ስም አስጠርቻለሁ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ያሉ ብዙዎቹ ክለቦች ከእኔ ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ 2 የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ከወዲሁ በደቡብ አፍሪካ ክለብ ተፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ፕላቲኒየም ስታርስ የተባለ ከለብ ጌታነህ ከበደን ለማዛወር እየሞከረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በደቡብ አፍሪካ ሊግ መጫወት እንደሚፈልጉ አውቃለሁ፡፡ ይህን ፍላጐታቸውን ለማመቻቸት ለብሄራዊ ቡድን ብጠራም ባልጠራም በቅንነት እሠራበታለሁ፡፡
በእርግጥ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች በታዳጊ ተጨዋቾች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የእውነቱን ለመናገር ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ቢያንስ 6 ያህል ልጆች በደቡብ አፍሪካ ሊግ የመጫወት አቅም አላቸው፡፡ እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ በእግር ኳስ ከእኔ የተሻለ ደርሶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ ተመረጥኩም አልተመረጥኩም በደቡብ አፍሪካ የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት እና ተሳትፎ ምን አስተያየት አለህ?
ከአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት በኋላ በማለፍ የተፈጠረው ስኬት መነሻ በማድረግ የአገራችን እግር ኳስ የወደፊቱ ተስፋ እንዳይጨልም ብዙ መሰራት አለበት፡፡ ተጨዋቾች በወዳጅነት ጨዋታ እንዲጠናከሩእና አስፈላጊውን ልምድ እንዲያገኙ መሠራት ነበረበት፡፡ ከእስራኤልና ኳታር ጋር እንዲጫወቱ በግሌ ያደረግኩት ሙከራ ነበር፡፡
ብዙም አልተሳካም እንጅ፡፡ በዚህ ትውልድ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የተፈጠረ መነቃቃት እንዲቀጥል ከፍተኛ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራር የፊፋ ካላንደርን በመጠቀም መስራት እንዳለበት እመክራለሁ፡፡
በዚህ ረገድ የሚሰጥ ትኩረት አንደኛ ቀጣይነት ያለው የቡድን አቋም የሚፈጥር ሲሆን ለብሄራዊ ቡድኑ የእግር ኳስ ደረጃ መሻሻልም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት መስራት ፍላጐት ግድ ይላል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ የምድብ ጨዋታዎቹን የሚያደርጉበት ኔልስፑሪት የአየር ሁኔታው ከዚህ ከአዲስ አበባ የተለየ አይደለም፡፡ በከተማው የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውን መኖራቸውም ለቡድኑ ማራኪ ድጋፍ እንደሚፈጥር አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ጠንካራ የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ነው፡፡
ዛምቢያ ሻምፒዮን ናት፡፡ ናይጀሪያ በአውሮፓ በሚጫወቱ በርካታ ፕሮፌሽናሎች የተሞላች ናት፡፡ ቡርኪናፋሶም በፈረንሳይ ሊግ ያሉ ምርጥ ተጨዋቾች ያሰባሰበች ነች፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቡድን በተቀናቃኞቹ ብዙ አለመታወቁ ይጠቅም ይሆናል፡፡
ዋልያዎቹ ጥሩ ብቃት የማሳየት አቅም አላቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ መልካም ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡ ተጨዋቾች ልምድ ያገኛሉ፡፡ በሚገኝ ውጤታማነት ደግሞ ለተጨዋቾች ወደ አውሮፓ መዛወር አስፈላጊ የሆነው የፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃን ለማሻሻል ይቻልበታል፡፡ በዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ በህዝባችን ላይ ያመጣው መነቃቃት፤ በስፖንሰር ገቢዎች እየፈጠረ ያለው አቅም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስገኘ ያለው የሚዲያ ሽፋንና ትኩረት ብዙ ፈርቀዳጅ ነገሮች ለሚቀጥለው ትውልድ ማመቻቸቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎ በተያያዘ የአገሪቱን እግር ኳስ ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ የሚቻልባቸው አቅጣጫዎች መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች አሁን ካለው እንቅስቃሴ በመጨመር እንዲቀጥሉ ያስፈልጋል፡፡ክለቦች፣ የሊግ ውድድሮች፣ አስተዳደራዊ ሁኔታዎች በፕሮፌሽናል ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ እንዲሠራባቸው መደረግ አለበት፡፡በሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ሌላ 31 ዓመታት መጠበቅ አይገባም፡፡

Read 8929 times