Saturday, 22 December 2012 10:33

መሣሪያ የመታጠቅ መብት ያመጣው መዘዝ

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(0 votes)

የ20 ዓመቱ አዳም ፒተር ላንዛ እናቱ ከአመታት በፊት ገዝታ ያስቀመጠችውን መሣሪያ፣ደብቆና ፊቱን ጭምብል በመሸፈን ነበር ወደ ሳንዲሁክ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ያቀናው፡፡ የትምህርት ቤቱን በር በጥይት እሩምታ በመደብደብ ከከፈተ በኋላ፣በመጀመርያ በተኩሱ ድምጽ ተደናግጠው ድርጊቱን ሊከላከሉ የሞከሩትን መምህራን ህይወት ቀጠፈ፡፡ ወደተማሪዎች ክፍል በመግባትም የሃያ ንፁሀን ህፃናትን ህይወት ካጠፋ በኋላ ራሱንም አጠፋ፡፡ የእሳት አደጋ ሰራተኛ የመሆን ምኞት የነበረው የስድስት አመት ተማሪና አንዲት መምህር ከላንዛ የሚተኮሰው ጥይት ሌሎችን እንዳይመታ ከለላ ለመሆን ሲሞክሩ የራሳቸውን ህይወት እንዳጡም ተዘግቧል፡፡

የሟቾች ቀብር እስከአሁን ድረስ እየተፈፀመ ሲሆን፤ በኒውታውን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ባለፈው ማክሰኞ መደበኛ ስራቸውን ጀምረዋል፡፡ አደጋው የተፈፀመበት የሳንዲሁክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በሚቀጥለው ወር ወደሌላ ትምህርት ቤት በመዛወር ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከኒውዮርክ በሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኒውታውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተፈፀመው ግድያ፣ በአሜሪካ እስከዛሬ በመሳሪያ ከተፈፀሙ ጥቃቶች ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ተብሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም በሚኖሶታ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በተፈፀመ ተመሳሳይ ድርጊት፣ ገዳዩን ጨምሮ አስር ሰው ከሞተበት ግድያ የተረፉ ግለሰቦች ሰሞኑን በኒውታውን በመገኘት በግድያው የሚወዷቸውን ያጡ ሰዎችን አጽናንተዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲገልፁም፤ ሚኖሰታ ላይ ግድያው በተፈፀመበት ወቅት በኮሎራዶ ከሚገኝ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ግድያ የተረፉት ሰዎች ያደረጉልንን ውለታ ለመመለስ ነው ብለዋል፡፡
በአሜሪካ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተለይ በት/ቤቶች ውስጥ ግድያ ከፈፀሙ በኋላ የራስን ህይወት ማጥፋት የተለመደ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፉት ሰላሳ አመታት ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ተመሳሳይ ግድያዎች ተፈጽመዋል፡፡ የግድያ ወንጀል በተፈፀመ ቁጥር ጣት የሚቀሰርበት ብሔራዊ የጦር መሳሪያ ማህበር እና የመሳሪያ ግዢ ቁጥጥር ገደብ ሊደረግበት ይገባል የሚሉ ወገኖች ይንጫጫሉ፡፡ ከሳምንታት በኋላ ግን ነገሩ ይረሳል፡፡
ግድያውን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ “ምንም አይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም አሰቃቂ ድርጊቶችን ለመግታት አንድ መሆን አለብን” በማለት በ2004 ዓ.ም ያበቃው የመሳሪያ ክልከላ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መሳሪያ ለመግዛት በሚፈልጉ ሰዎች ማንነት ላይም ጠበቅ ያለ ምርመራ እንዲደረግና አንድ መሳሪያ በሚጐርሰው ጥይት ላይ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ገደብ እንዲቀመጥ አሳስበዋል፡፡ የኒውታውኑ ግድያ የብዙ አሜሪካውያንን ልብ የሰበረ ሲሆን ክስተቱ በተቃራኒ ጫፍ የተቀመጠውን የሁለት ወገኖች ሙግት እልባት ሊሠጠው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከግድያው በኋላ አንዳንድ በመሳሪያ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ሽያጫቸውን ለጊዜው እንዳቆሙ ታውቋል፡፡ በፒተርስርግ የሚገኘው “ዲክስ ስፓርቲንግ ጉድስ” ሽያጩን ለጊዜው ያቆመ ሲሆን በኒውታውን አቅራቢያ በሚገኙ መደብሮች ያሉ የመሳሪያ ማስታወቂያዎችን ሙሉ በሙሉ አንስቷል ተብሏል፡፡ የመሳሪያ ሽያጩ ቅድመ ሁኔታዎች ሊቀመጥለት ይገባል የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉት ሪፐብሊካኑ ጃክ ኪንግስተን፤ ምርጫ ያሸነፉት ከብሔራዊ የጦር መሳሪያ ማህበር ባገኙት ከፍተኛ ድጋፍ መሆኑ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጉዳዩ ላይ አሜሪካውያን በአንድነት እንዲቆሙ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል፡፡
የኒውታውኑ ግድያ ከተፈፀመ ከቀናት በኋላ ድምፁን ያሰማው ሃያሉ ብሔራዊ የጦር መሳሪያ ማህበር በበኩሉ፤ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ትርጉም ያለው እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገ የCBS የህዝብ አስተያየት ውጤት እንዳመለከተው፤በጦር መሳሪያ ላይ የሚደረግ ጥብቅ ቁጥጥር በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ በመሳሪያ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የመሳሪያ ቁጥጥር ላይ የቅስቀሳ ስራ የሚሠራው ብራዲ ካምፔይን፤ “እኛ ከዚህ የተሻልን ነን” በሚል መሪ ቃል የድጋፍ ፊርማዎችን ማሰባሰብ የጀመረ ሲሆን አላማውም በመሳሪያ የሚፈፀም ጥቃትን ለማስቆም የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከወገናዊነት የፀዱ እንዲሆኑ ለመጠየቅ ነው፡፡ “የሃያ ህፃናትን እና የሰባት ጐልማሶችን ህይወት የቀጠፈው ግድያ ሃላፊነት እንደሚሰማው አሜሪካዊ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ አሜሪካ ከአንድ የግድያ ድርጊት ወደ ሌላ የምትገባ እሽክርክሪት ላይ ያለች አገር ሆናለች፡፡ የጦር መሳሪያን በቀላሉ ማግኘት መቻል ተመሳሳይ የግድያ ወንጀሎች እንዲፈፀሙ እድል ሰጥቷል” ያሉት ኒኪ ስንጋስ፤ የተሻለ መንገድ መፈለግ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ከ1970ዎቹ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ በአውስትራሊያ ከፍተኛ ግድያዎች ይፈፀሙ ነበር፡፡ በ1996 ዓ.ም የብዙዎችን ህይወት ከቀጠፈ ግድያ በኋላ በጠቅላይ ሚ/ር ጆንሀዋርድ አማካኝነት “በቃ” የሚል አቋም በመያዝ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሏ ሰላም አግኝታለች፡፡ አገሪቱ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ውስጥ መሳሪያ ያላቸው ሰዎች በሚገባ እንዲታወቁ፤ የመሳሪያ ባለቤቶች ጠበቅ ያለ የማመልከቻ ሂደት እንዲያልፉና መሳሪያውን ለምን አላማ እንደፈለጉት እንዲያስመዘግቡ የሚሉ የሚጠቀሱ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ የመሳሪያ ምዝገባና ፈቃድ ለማግኘት ከአንድ አመት በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ አሁን በአውስትራሊያ ወንጀል ሙሉ በሙሉ አይፈፀምም ባይባልም ግድያዎች በጣም እንደቀነሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከ1996 ዓ.ም ወዲህ በመሳሪያ የሚፈፀም ወንጀልም አልተመዘገበም፡፡ ከለውጡ በፊት በነበሩ አስራ ስምንት አመታት ውስጥ ግን አስራ ሶስት የብዙዎችን ህይወት የቀጠፉ የግድያ ወንጀሎች ተፈጽመው ነበር፡፡ በአሜሪካ ይሄን ዓይነቱን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ “የመሳሪያ ቁጥጥር ይኑር፤ ማዕቀብ ይጣል” የሚሉ ወገኖች የሚገጥሙት እጅግ ጉልበተኛ ከሆነ ወገን ጋር ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም የኮንግረስ አባሉ ጋብሪያል ጊፎርድስ ላይ የግድያ ሙከራ ከተደረገ በኋላ ሌሎች ፖለቲከኞች ላይ ፍርሃት አንዣቧል እየተባለ ነው፡፡ በመሳሪያ ሽያጭ ላይ የተሰማሩት ሃያሎቹ ወገኖች በዋናነት ለመከራከሪያነት የሚጠቀሙት የአገሪቱ ህገመንግስት ላይ የተቀመጠውን “አገሪቱ ሚሊሽያ ያስፈልጋታል፤ ዜጐች መሳሪያ የመያዝ መብት አላቸው” የሚለውን አንቀፅ ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ የቆሙት ደግሞ “ነፃነት ማለት ቁጥጥር የሌለበት የመሳሪያ ባለቤትነት አይደለም፤ የአሜሪካ የመሳሪያ ባህል ለነፃነት ስጋት ነው” ይላሉ፡፡ ሰሞኑን በአሜሪካ ከተፈፀመው ግድያ ጋር በተገናኘ በመጪው ሳምንት የሚከበረው የፈረንጆች ገናም ሆነ ቀጣዩ የአዲስ አመት በዓል ደብዘዝ ባለ ስሜት እንደሚከበሩ ይጠበቃል፡፡

Read 5472 times