Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:38

ሽፋን የሸፈናቸው የበለው ግጥሞች!!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ግጥም የማይወድ ሰው ስለ ግጥም አስተያየት መስጠት የለበትም ይላሉ- የስነጽሁፍ ምሁራን፡፡
ምክንያቱም ግጥምን ጠለቅ ብሎ ለማየት የተሳለና የተሞረደ ልብ ይፈልጋልና፡፡
ለምሳሌ ልጆች ዜማ ስለሚወድዱ ዋነኞቹ ሃያስያን ህጻናት ናቸው የሚሉት ደግሞ ቆየት ያሉት ደራሲ ኢ. ኤ. ግሪኒንግ ላምቦርን ናቸው፡፡
“Children are naturally good critics of poetry,for they are akin to the poet,who is the child of the race..” ግጥም የማይወድ ሰው ግጥም ላይ አስተያየት ይስጥ ማለት፣ ወይን የማይወድ ሰው ስለ ወይን አስተያየት ይስጥ እንደማለት ነው የሚሉት ታላቁ የሥነ ግጥም ተመራማሪ ፔሬኔ ናቸው፡፡ የመዳኘት አቅም ለማግኘት፣ጥሩና መጥፎውን አንገዋሎ ፣ ከፊል ጥሩና-ጥሩን ለመለየት ፍቅር፣ ዕውቀትና ልምምድ ይጠይቃል-ባይ ናቸው ባለሙያው፡፡እንደኛው በአገራቸው ላይ ከሚታተሙት ግጥሞች ጥቂቶቹ ብቻ ነፍስ ያላቸው እንደሆኑ የሚናገሩት ምሁሩ፤ ከመንጋው ውስጥ ጥቂቱን መዝዞ ማውጣት ጥሩ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ለመመዘንም ልክ ሬክታንግል ስፋት ጎንና ርዝመቱን ለክተን እንደምናገኝ ሁሉ የምንለካቸው ነገሮች አሉ፤ግን የሬክታንግሉን ያህል ቀላል አይደለም፡፡

…መመዘን ግን ይቻላል፡፡ በርግጥም ግጥም መለካት ቀላል አይደለም፤ግን ከዓላማው ጀምሮ፣ ማዕከላዊ ሃሳቡን ማደርጀቱንና የደረጀው ሃሳብ ደግሞ ምን ያህል ሁሉአቀፍ ነው በሚለው ማየት ይቻላል፡፡
ግጥም በስብከቱ አይለካም፤ እንዲያውም ግጥም ለመስበኪያነት ታልሞ ሲጻፍ የቀሽም ግጥም ተርታ ገባ ማለት ነው፡፡(ጥበብ ለጥበብነቱና ለማስተማሪያነቱ የሚለውን ማለት ግን አይደለም)
ሌላው የግጥም ድርሻ ሰዎችን ዘና ማድረግ ነው-ይላሉ፡፡ ዛሬ የሚያዝናና ስሜት ይሰጣል ብዬ ያሰብኩትን የአንድ ገጣሚ ስራዎችን ላስቃኛችሁ እሞክራለሁ፡፡ የዚህ ገጣሚ የግጥም መጽሃፍ ርዕሱ “የአገጭ ጢሞች” የሚል ነው፡፡ ይህ የግጥም መጽሃፍ አንባቢ ዘንድ በቅጡ ያልደረሰው በሽፋኑ ቀሽምነት ነው፡፡ እስቲ ግጥሞቹን እንይለት፡-
ወይ ቆንጅየዋ ልጅ- ውበትሽ ያማረ
ያልተማረው ልቤ-አንቺን ባፈቀረ
‹መሃይም!› ነው ብለሽ-
ትሰድቢኝ ጀመረ
አበጀሁ!
እንኳን መሃይም ሆንኩ፤
ሥራዬ ፍቅር ነው፣
ፊርማ ማይጠይቀኝ…
የተማረ ብሆን…ፊደል የቆጠረ…
ውሎዬ ታንቺ ጋር…መች ይሆን ነበረ
የበለው ገበየሁ ግጥም እንደ አብዛኞቹ የሃገራችን ግጥሞች የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ይበዛዋል ፤ወቃሽና ሰላቂ ሃሳቦችም አሉበት፡፡ በለው ግጥሞች ሲጽፍ አጫጭርም ረጅምም አድርጎ ነው፡፡ ስለ ጥበብ ፍቅር የጻፈው ግጥምም ተመችቶኛል፡፡
”ከጥበብ ሲጋቡ” እንዲህ ይላል፡፡
የስሜቴ አሞሌ ፤በቀለሟ ድምቀት እየተሞሸረ
እየተሞሸረ….
እንቅልፍ እሣቴ፤በወራጅ ውሃዋ
እየተገሸረ…
ቁርኝት ክራችን-ፈትሉ እየከረረ…
የምናቤ-ፍሬ-በኪን ማህጸኗ እየተወሸቀ…
የኔ-ኩሬ ሲነጥፍ-ምንጩ እየፈለቀ…
የኔ-አበባ ሲረግፍ-ዘሩ እየፀደቀ…
(…እንዲህ ነው ድባቡ…
በጥበብ ክህነት፣በቀለም ቀለበት …ከጥበብ ሲጋቡ…)
የኔ አካል- ቢጫጭም …
ከሷ የወለድኳቸው-ልጆች እየሰቡ…
ምላሴ ታሰር-በፍት ልሳናቸው…እያነበነቡ፤
ከ›ይወት ስኮበልል… ወደ ሕይወት ስርጸት…
ዘልቀው እየገቡ…፣
(…እንዲህ ነው ድባቡ
በቀለም ቀለበት ከጥበብ ሲጋቡ…
ይሄ ነው ምስጢሩ፤
ቀለም ተሞሽረው-ለጥበብ ሲዳሩ…)
ስለ ጥበብ ብዙ ይወራል፤በተለይ በዚህ ሸቀጥ በሆነችበት ጊዜ የዚህ ዓይነት ስንኞች መቋጠሩ የሚገርም ነው፡፡ እየጠፋ የመጣውን ሃሳብ ነው መልሶ ወደ አደባባይ የሳበው፡፡ የዚህ ዓይነት ልብ ቢኖረን ኖሮ ሰው ወልዶ ያሳደገውን ግጥምና ዜማ እየነጠቅን ሳናፍር አደባባይ ላይ አንቆምም ነበር፡፡
ገጣሚው እንዲህ ነው- እንዲያ ነው ብሎ አልሰበከንም፤የራሱን ወገን ተናገረ፣ልብ ያለው ግን ልብ ይላል፡፡ ግጥሞቹን መዘርዘርና መተንተን ሰፊ ጊዜ ፣ ሰፊ ገጽ ይጠይቃል፡፡ እኔ የማደርገው አንባቢ እንዲያጣጥማቸው ዘርግቶ ማስቀመጥ ነው፡፡
“መውደድ ማሩ” የሚለው ግጥሙ እንዲህ ትላለች፡-
ይወደኛል ብለሽ -ለሰው ብታወሪም፣
አልወደውም ብለሽ -ለሰው ብትነግሪም፣
ምንም ባትወጂኝ፤እኔን ባታፈቅሪም፤ ያንቺን መወደድ ግን ሳትወጂው አትቀሪም፡፡
የእህቶቻችንን ብብት ለመኮርኮር የተጻፈ ነው የሚመስለው፤ይህቺ ብዙ ሰው ልብ የማይላት፣ግን ውስጥ ላይ የምትደውል ቃጭል ናት፡፡ አልፎ-አልፎ በወንዶችም ልብ የምትታይ የኩራት ጉልላት ናት፡፡
ግጥምም ለስለስ ብላ በሰው ልብ ስር በዜማ እንደ ወንዝ እየፈሰሰች፣ የሰውን ውስጥ ምስጢርና ቀለም እየፈተፈተች ፤በጥፍጥና መልሳ በዜማ ማናኘት ነው፡፡
“አረፋ” - የሚለው ግጥሙም ይኸው፡-
ስትብለጨለጪ-ዘንድሮም እንዳምና፣
አልጨበጥ እንዳልሽ - አንች የኛ ሳሙና
እንደ መስክ አበባ - ውበትሽ ሲፈካ፣
አፍክቶ እያሟሟሽ -የመሙለጭለጭ ሳንካ፤
እኔም አንድ ወዳጅሽ - አንቺኑ ፍለጋ፣
ሳሙና ነሽ ብዬ - እጄን ብዘረጋ፣
እንኳን ልጨብጥሽ - ጫፍሽን ሳልነካ-
‹ብን! ትን!‹ አልሽብኝ ሳሙና ነሽ ለካ!
የገጣሚ በለው አተያይ ልብ እማይባሉ ነገሮች በማየት ላይ የተመሰረተ ነው፤ቃላቱ እሳት የጨበጡ ተዓምራት ናቸው ብለን ባንደነግጥም፣ አንዳንዴ ወረቀት ላይ እግር እየሰቀሉ ምስጢር እንደሚያሳዩት የእነጋሽ ጸጋዬ ቃላት ባንደነቅም በቂ የመግለፅ አቅም አላቸው ለማለት ግን እንችላለን፡፡ ከቃላት አጠቃቀም አንፃር ሁሉም አይሁኑ እንጂ የበድሉ ዋቅጂራና የታገል ሰይፉ ረጃጂም ግጥሞች ለዘመናችን ጌጦች ናቸው፡፡
የበለው ግጥሞች እምብዛም ሳይታወቁ መቅረታቸው፣እንደ አንድ የግጥም አፍቃሪ በቁጭት አንገብግቦኛል፡፡ ምናልባት ጥፋቱ የሽፋኑ ማስቀየም ይመስለኛል፤እንዴት የዚህ አይነት ዘግኛኝና ውበት-አልባ ሽፋን በዚህ ዘመን ይደረጋል… ለምን
የመጨረሻ ዳሰሳዬን “ክህሎት ሲረሳ” በሚለው ግጥም ላድርግ፡-
ስምዖን አሳ አጥማጁ - አሳ እያሰገረ
ባህረኛው ሆኖ - ይኖር የነበረ
በጌታው ተጠርቶ - ስራው ተቀየረ
መረቡን ጠቅልሎ - ሰው ማጥመድ ጀመረ፡፡
እናም አንድ ምሽት - በባህር ላይ ሳለ
እንደጌታው ሁላ - ባህሩ ላይ መጓዝ
መራመድ ከጀለ
“ይሁንልህ” ተብሎ ፣ጉዞ እንደ ጀመረ
ሊሰጥም ሆነና - “ጌታ አድነኝ” አለ
የድሮው አሳ አጥማጅ - በጌታው ሲመካ
የሚችለው ዋና ተረስቶታል ለካ!
በለው ግሩም አተያይ አይቷል፣ አጠቃላይ ታሪኩንና አውዱን ለሚያውቅ ሁሉ አስገራሚ ብርበራ አድርጓል፡፡
ዝም ብሎ ለሚያይ ሳይሆን ታሪኩንና ሁነቱን ለሚያስታውስ ታላቅ ፍተሻ አሳይቷል፡፡ የገጣሚው አይኖች ፈታሽና በርባሪ ናቸው፡፡ ገጣሚው ጥሩ ተመልካችና በርባሪ ብቻ ሳይሆን የግጥሞቹ ዜማም ተሰባብሮ የሚያነክስ አይደለም፡፡ ሳቢና ጣፋጭ ነው፡፡ በለውን በርታ ብዬ ቅኝቴን ቋጨሁ!!

Read 10094 times