Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 September 2011 10:02

ማደግ ከፈለግህ መንገድ ሥራ የቻይናዎች ተረት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት ልጁን አስከትሎ አህያ ሊሸጥ ወደ ገበያ ይወጣል፡፡
መንገድ ላይ እየተጫወቱና እየተሳሳቁ የሚመጡ ሴቶች ያገኛሉ፡፡ ሴቶቹ አባትና ልጁን እያዩ፤
..በዚህ በኮረኮንች መንገድ አህያ እያላቸው በእግራቸው የሚሄዱ ጅሎች አይታችሁ ታውቃላችሁ?.. አሉ፡፡
አባት፤ ሴቶቹ የሚሉት ትክክል ነው አለና አሰበ፡፡ ስለዚህም ልጁን አህያ ላይ ጭኖ እሱ እየተከተለ መንገድ ቀጠለ፡፡ መንገድ ላይ ሽማግሌ ጓደኞቹን አገኘ፡፡ እነሱም ..ልጅህን እንዴት እያባለግኸው እንደሆነ ታውቆሃል? አንተ ሽማግሌው በደከመህ ሰዓት ልጅህ በአህያ አንተ በእግርህ እንዴት ትሄዳለህ?.. አሉት፡፡


አባት ምክራቸውን ተከትሎ ልጁን ..ና ውረድ እኔ ነኝ መቀመጥ ያለብኝ.. ብሎ ልጁ በእግሩ እየተከተለ አባት አህያ ላይ ሆኖ መንገድ ቀጠሉ፡፡
አሁንም እዛው መንገድ ላይ ሌሎች የሠፈር ሰዎች አገኙ፡፡ ሰዎቹም እንዲህ እያሉ ሲተርቡ አባት ይሰማል፡፡
..ምን ያለው ጨካኝና ስስታም አባት ነው? እሱ አህያ ላይ ሆኖ ልጁን በዚህ ለቋሳ እግሩ እንዲኳትን አድርጐታል..
ይሄኔ አባት፤ ..ዕውነታቸውን እኮ ነው፡፡ ለምን ልጄን አላፈናጥጠውም?.. ብሎ አሰበ፡፡
ከኋላው ልጁን አፈናጠጠውና መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደሄዱ ወደገበያ የሚሄዱ ነጋዴዎች አገኙዋቸው፡፡
ነጋዴዎቹም ሰላምታ ከሰጠ-ት በኋላ አባትዬውን እንዲህ ሲሉ ጠየቁት
..ይሄ የምትጋልቡት አህያ የራስህ ነው የሌላ ሰው?..
አባትም፤ ..አዎን የራሴ ነው፡፡ ወደገበያ ወስጄ ልሸጠው አስቤ ነው..
ነጋዴዎቹም፤
..ኧረ የሰማያቱ ÃlH! ይሄ አህያ ሁለት ሰው ተሸክሞ በፍፁም ገበያ አይደርስም፡፡ ተዝለፍልፎ ይወድቃል፤ በዚያ ሁኔታ ያለ አህያ ደሞ ማንም የሚገዛ ሰው አይኖርም፡፡ የሚሻለው ተጋግዛችሁ ተሸክማችሁ ብትወስዱት ነው.. አሏቸው፡፡
አባትዬውም ..ዕውነታችሁን ነው፡፡ ገበያዬን ከማጣ ተሸክመን ብናደርሰው ነው የሚሻለው.. አለ፡፡ ከአህያው ላይ ወርደው ሁለት እግሩን አስረው በረዥም እንጨት ተሸክመው፤ እንደምንም ገበያ ደረሱ፡፡ ገበያተኛው አባትና ልጅ፤ አህያ ተሸክመው ሲያይ ሳቅ በሳቅ ሆነ፡፡ ..እነዚህ ጅሎች ናቸው.. ..እነዚህ አብደው መሆን አለበት.. ..የለም ያገሩን ገበያ የማያውቁ የሌላ አገር ሰዎች ናቸው.. አላቸው፡፡
ተደናግጠው አህያውን እንደተሸከሙ ወደ አንድ ድልድይ ሄዱ፡፡ አህያው ከድልድዩ ሥር የሚሄደውን ወንዝ ድምጽ ሲሰማ ተረበሸና ሲንፈራገጥ ገመዱን በጠሰው፡፡ ከዚያ ከእጃቸው ተፈትልኮ ሲሮጥ ድልድዩን ስቶ ውሃው ውስጥ ሰጥሞ ሞተ፡፡
ዕድለ ቢሱ አባት አዝኖና የሐፍረት ካባ ለብሶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
በልቡም፤ ..ሁሉንም ሰው አስደስታለሁ ብዬ አንድም ሰው ሳላረካ፤ ቀረሁ፡፡ በማህል አህያዬንም አጣሁ.. አለ፡፡
*    *     *
ፈረንጆች  “TO SATISFY ALL IS TO SATISFY NONE”  ይላሉ፡፡ (ሁሉን ሰው አስደስታለሁ ብለህ አንድም ሰው ሳታረካ እንዳትቀር፤ እንደማለት ነው) ሁሉም መካሪ በሆነበት አገር የሁሉንም ምክር ካልፈፀምኩ የሚል ቢያንስ የዋህ ነው፡፡ ጥሬውን ከብስሉ የማይለይ አመርቂ ሥራ አይሠራም፡፡ ለልጁ ለመጪው ትውልድ የሚያስብና እግረ መንገዱን ግን ነባሩን ትውልድ የሚያስታውስ ከሁለት የወደቀ ዛፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ልጅን ሳያሳትፍ አባት ብቻ የሚወስንበት ወይም ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት መንገድ እንደማያዋጣም መገንዘብ ደግ ነው፡፡ መንገድ ከመጀመር በፊት፤ መንገዱ ኮረኮንች ነው ምቹ? ጉልበቴ በቂ ነው አናሳ? መጓጓዣ አለኝ የለኝም? የምጓዘው ከሌሎች መንገደኞች ጋር ነው ብቻዬን? ሰው ያግዘኛል ወይስ እኔው በራሴ የምወጣው ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ከአጓጉል መካርም ያድናል፡፡ ሁሉን ምክር ለመፃረርም አስከፊውን መንገድ መጠቀም አያዋጣም፡፡
..የሀሳብህን ጥንካሬ ለማሳየት ብለህ ኃይልን አትጠቀም፡፡ ሌሎችን ማስቀየሙ አይቀርምና.. ይለናል ሮበርት ግሪን የተባለው ፀሐፊ፡፡ ስለመሪዎች ሥጋት ማዳም ማዖ ስትናገር ..አንዳንድ ጊዜ ማኦ የደህንነት ዋስትና ከማጣቱ ብዛት በትንፋሽ ውስጥ አውሎንፋስ ይፈጠራል ብሎ ይፈራል ትላለች፡፡
ቻይናዎች ..ማደግ ከፈለግህ መንገድ ሥራ.. የሚሉት ዋና ተረት አላቸው፡፡ ታላላቅ ህልሞች ታላላቅ ዕቅዶች፤ ታላላቅ መመሪያዎች ገና ጧት ሲነደፉና ሲወጡ፣ መጀመሪያ መንገድ ሊበጅላቸው፣ ጥርጊያ መንገድ ሊወጣላቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ በሌላ መንገድ ጉዞ መጀመር ወይም በማያዋጣ አቅጣጫ መሄድ ይሆናል፡፡ የዓለም አካሄድንና የአገርን አካሄድ የውጪ ፖሊሲንና ዲፕሎማሲን አሰናስሎ (የሌላም አንነካ፣ የራሳችንንም አናስነካ የሚል መፈክርም አለን) መጓዝ እንደሚያስፈልግ እንደምናውቅ ሁሉ፣ የአገር ውስጥ መመሪያዎችና ህግጋትን በጥንቃቄ መቅረጽና መተግበር ወሳኝ መሆኑንም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ዋዣቂ መመሪያዎች አመኔታን ያሳጣሉ ይባላል፡፡ ከሮ የማይበጠስ፣ ላልቶ ውሽልሽል ያልሆነ አስተሳሰብ ነው ጥሩ መንገድ እንድናይ የሚረዳን፡፡ ሚዛናዊነት እና ሆደ ሰፊነት (መቻቻል) ነው ልበ ሙሉ ዜጋ እንድንፈጥር የሚያደርገን፡፡
ዜጋ አንዱ እሰይ ባይ፣ አንዱ ወይኔ ባይ መሆን የለበትምና ወገናዊነትን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ማድረግ ያሻል፡፡ ለዚህም መንገድ መሥራት ያሻል፡፡ ለማንኛውም ልማት መንገድ መሥራት ወሳኝ የመሠረተ ልማት ግብዓት እንደመሆኑ፤ በፖለቲካ አመራርም፤ በኢኮኖሚ አገነባብም፣ በባህል አያያዝም ቀዳሚው መንገድ የመሥራት ዘዴ መከወን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ለመጪው ትውልድ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ቂምና ዕዳን አለማቆየት ነው ዋናው መንገድ፡፡ ለዚህ ቀና ልቦና ሊኖር ይገባል፡፡ ..የጀርመን ግንብ ፈርሷል ወይ?.. ተብላ የተጠየቀች አንዲት ጀርመናዊ አሮጊት ..ከቦታው የለም፡፡ ጭንቅላታችን ውስጥ ግን ግንቡ እንደቆመ ነው.. ብላለች አሉ፡፡ አሮጌና ያልተለወጡ አስተሳሰቦች እንደ ጀርመኑ ግንብ ጭንቅላታችን ውስጥ ሳይፈርሱ ቆመው ከሆነ በጋራ አገር መገንባት አዳጋች ይሆናል፡፡ አጋች አስተሳሰቦችን ለማስወገድ ዝግጁ መሆን ነው ለውጥ ፈላጊነት፡፡ ይህንን ለመተግበርም ዘዴ መዘየድ ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ እንደቻይናዎቹ ..ማደግ ከፈለግህ መንገድ ሥራ.. ማለት ነው የሚያዋጣው፡፡

Read 5166 times