Saturday, 17 September 2011 10:07

የፈጣሪ ፍርድ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

ስለዚህ ሰው ለመናገር በጣም ይከብዳል፡፡ምክንያቱም እንደማንኛውም ሰው በህይወት የሚኖር ሰው ሳይሆን የሞተ
ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ሞቶም ግን በህይወት ይናገራል፡፡ በሌላ ዳይሜንሽን ወይም አውታር መጠን ውስጥ በሌላ
መንፈሳዊ አለም ወይም አፀደ ነፍስ ውስጥ ይኖራል፡፡ የሞተው በቅርቡ ነው፡፡ ቀብሩ ላይ የተገኙት ከአስር ሰዎች በላይ አይሆኑም፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎችን ታዝቧል፡፡ ምን ዋጋ አለው... ትዝብቱ ከሞተ በኋላ ሆነ እንጂ፡፡ የሞተው ከፍተኛ መጠን ባለው የደም ግፊት ሲሆን የልብ ድካምም ነበረበት፡፡

ሀኪሞቹ በሬሳው ዙሪያ ተሰብስበው ..ህይወቱ አልፏአል.. ብለው ሲናገሩ ከላይ እየተንሳፈፈ ያዳምጥ ነበር፡፡ ..አልሞትኩም፤ እሰማችኋለሁ.. ብሎ ቢናገርም የሚሰማው ሰው አጣ፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ቆርጦ ተወው፡፡
ከቀብሩ በኋላ ከተቀበረው ስጋዊ አካሉ እየራቀሄደ፡፡ በመጨረሻ በአንድ ጫጫታ የበዛበት አዙሪት ነገር ውስጥ ገባ፡፡ ይሄኔ ነው በትክክል እንደሞተ ያወቀው፡፡ በዚያ እሽክርክሪት ውስጥ ለማመን በሚያስቸግር ፍጥነት ይጓዛል፡፡ በህይወት እያለ የመጨረሻው የፍጥነት መጠን የብርሃን ፍጥነት እንደሆነ ተምሮ ነበር፡፡ በሰከንድ ሶስት መቶ ሺህ ብሎ ሜትር፡፡ አሁን ግን የሚጓዝበት የፍጥነት መጠን ከዚህ አሃዝ አንድ ሚሊዮን እጥፍ ያህል ሲሆን ባይኑ ማየት የቻለው አካል ላይ በቅጽበት ይደርሳል፡፡ ማየት የቻለው አካል አንድ ሚሊዮን የብርሃን አመት የሚርቅ እንኳን ቢሆን፡፡
ይህ ከዚህ በፊት ሰው የነበረ አሁን ምንነቱ ያልታወቀ ነገር አካል አለው ወይ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ መልሱ አዎን አለው ነው፡፡ ግን እንደስጋዊ አካሉ በጣም ጠጣር የሆነ አካል ሳይሆን የርግብግቢት መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ አካል ነው፡፡ ይህ ማለት የማይዳሰስ፣ ጠጣር ያልሆነ አካል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የርግብግቢት መጠኑ በጣም ፈጣን ስለሆነ በዚያው የርግብግቢት መጠን ላለ አካል ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ሁኔታውን ለመረዳት የአውሮፕላን ሞተር ማስተዋል በቂ ነው፡፡ በጣም በፍጥነት ሲሽከረከር የሌለ ያህል ይቆጠራል፡፡ አይታይም፡፡
የሚያጅቡት ሁለት መንፈሶች እንዳሉ ይታወቀዋል፡፡ በቀኝና በግራው እየተጓዙ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ የት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡ ሌላው ያስገረመው ነገር ደግሞ የዕድሜው ጉዳይ ነው፡፡ ሲሞት የነበረው ዕድሜ ስድሳ ሰባት አመት ሲሆን አሁን ያለው ዕድሜ ሰላሳ አምስት አመት ነው፡፡ አንድ ብልጥ ሰው በየትኛው አለም አቆጣጠር ሲል ሊጠይቅ ይችላል፡፡ መልሱ በመንፈሳዊው አለም አቆጣጠር ሲሆን ይሄ አሃዝ በኛ አቆጣጠር አንድ ሺህ አመትም ሊሆን ይችላል፡፡
ለነገሩ እኛ የምናወራው የሰማነውን ነው፡፡ የማናውቀውን አንዘባርቅም፡፡
የሚያጅቡት ሁለት መንፈሶች ናቸው፡፡ ይሄን የነገሩት መነጋገር ማለት እኛ እንደምናወራው በአፍና በጆሮ መነጋገርና መስማት ሳይሆን በአዕምሮ መግባባት ወይም በኛ ቋንቋ ቴሌፓቲ እንደምንለው ማለት ነው፡፡
የሚሄደው ወዴት እንደሆነ በአዕምሮው ሲጠይቅ መልሱ ወዲያው አዕምሮው ላይ መጣ፡፡ ወደ ፈጣሪ፡፡ ይሄኔ ነው በሽብር የተዋጠው፡፡ ምክንያቱም እሱ ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘት በጣም ይፈራል፡፡
ድንገት ወደ አንድ እጅግ በጣም ሰፊ አለም ውስጥ ገባ፡፡ ታይቶ የማይጠገብ ህብር ያለበት፣ እጅግ በጣም የተዋበና አዕምሮ የሚሰልብ ጣዕመ ሙዚቃ የሚሰማበት አለም ውስጥ፡፡ ይህ አለም ብርቱካናማና ሐምራዊ ህብር ያለው ሰማይ የሚታይበት ነው፡፡ በጣም የማያቃጥል ሳሳ ያለ ጨረር ያላቸው፣ ባለ ሰባት የተለያዩ ህብር ፀሐዮች ያሉት፣ የሚገርምና የሚያስደምም አለም ነው፡፡
ከፀሐዮቹ ህብር መካከል ውሃ ሰማያዊ፣ ቢጫና ቀይ ይጠቀሳሉ፡፡ የሚታየው ነገር ሁሉ የሚያስገርም፣ የሚወደድና የማይታመን ነው፡፡ ብርቱካናማ ሳር፣ ነጭ ሳር፣ አረንጓዴ ሳር፣ እንደ ውሃ አንፀባራቂና ብርሃን የሚያስተላልፍ ህብር ያለው ግንድ ያላቸው ዛፎች፣ እንደወርቅ የሚያንፀባርቅ ህብር ያላቸው ፏፏቴዎች፣ እንደ ብር የሚያንፀባርቁ ኩሬዎች፣ የአንድ ግዜ መአዛቸው ለዘላለም ከአዕምሮ የማይጠፉ አበቦች፣ ሰማያዊ፣ ቀይና ምንነቱ ያልታወቀ እሱ በህይወት በነበረበት ጊዜ አይቶት ቀርቶ አስቦት የማያውቀው ህብር ያላቸው የአልማዝ ቋጥኞች፣ ከሚጠቀሱት ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
..ይህ ቦታ ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ በጣም ምርጥና አንደኛ የሆነው ገነት ነው.. ሲል አሰበ፡፡ ..አይደለም ይህ ካሉት ሰባት ደረጃ ካላቸው ሰማዮች የመጨረሻው ሰማይ ሲሆን በህይወት የነበርክበት አለም እዚህ አለም ላይ ቢቀመጥ አንድ ትልቅ ሜዳ ላይ ያረፈ ቀለበት ነው የሚመስለው፡፡ የነበርክበት አለምና ይሄኛው አለም አንድ ላይ ሁለተኛው ሰማይ ላይ ቢቀመጡ አሁንም አንድ ትንሽ ቀለበት ትልቅ ሜዳ ላይ ያረፈ ነው የሚመስለው፡፡ እንዲህ እያለ ቀጥሎ ሰባቱም ሰማያት አንድ ላይ ተደምረው የፈጣሪ የእግር መረገጫ ላይ ቢያርፉ አሁንም አንድ ትንሽ ቀለበት ትልቅ ሜዳ ላይ፡፡ እንግዲህ የፈጣሪ ዙፋን ምን ቢያክል ነው? ፈጣሪስ እራሱ?.. አለው በአዕምሮው ውስጥ የሚሰማው ድምጽ፡፡ ከሁለቱ አጃቢዎቹ አንደኛው እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ሌላ የገባው ነገር ድምፁ ላይ ትዝብት እንዳለበት ነው፡፡
በዚያ ዕፁብ ድንቅ የሆነ አለም ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ስሞችና መልዕክቶች ይኖራሉ፡፡ እንደ ልዩ ፍጥረት ነው የሚያዩት፡፡ የተወሰኑት እያዩት በሀዘን ከንፈራቸውን ይመጣሉ፡፡ ብዙ ክንፎች ያሉት አንድ መልአክ እንዳየው ..እዩት ይሄን የፈጣሪ ጠላት.. ብሎ ድምፁን ጮክ አድርጐ ሲናገር ሰማው፡፡
ጉብኝቱ አላለቀም፡፡ ምክንያቱም ያ አለም እጅግ በጣም ግዙፍና ታይቶ የማያልቅ አለም ነው፡፡ አንድ ቦታ ሲደርስ ወንዶችና ሴቶች የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎች የተለያዩ ህብር ያለውና ሽታው በጣም የሚያስጐመጅ የተለያየ ምግብና ፍራፍሬ ሲመገቡ ተመለከተ፡፡
..እዚህ ዛሬ የበላኸውን ምግብ ከዛሬ ወዲያ ዕድሜ ልክህን አትበላውም፡፡ ምክንያቱም ነገ የምትበላው ከሱ የበለጠና በጣዕም እሱን የሚያስንቅ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲህ እያልክ ዕድሜ ልክህን ዳግመኛ የማትደግመው እጅግ በጣም ጣፋጭ ምግብ ትበላለህ፡፡
ከበላህ በኋላ ወደ ሽንት ቤት አትሄድም፡፡ በላብ መልክ ነው የሚወጣው፡፡ የምታልበው እጅግ በጣም ውብ ከተባለው ሽቶ በላይ የሚጣፍጥ ጠረን ያለው ነው፡፡ ደስታ እዚህ በምታገኘው ልክ ሳይሆን በምታስበው ልክ ነው፡፡ እዚህ ምግብ የምትበላው ለጣዕም ነው እንጂ ለመጥገብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እዚህ ረሃብ የለም፡፡.. አለው ያ ድምጽ፡፡ አንድ ያስተዋለው ነገር ግን አለ፡፡ ያ ከሁለቱ አጃቢዎቹ አንዱ የሚያወጣው ድምጽ ..አንተ ግን ይህንን አለም አታገኘውም፤ ቦታህ እዚህ አይደለም ገሀነም እሳት እንጂ.. የሚል ቃና ያለው እንደሆነ ገብቶታል፡፡
በህይወት እያለ ሲያደርግ የነበረውን አስታወሰ፡፡ የፈጣሪን ስም የሚያነሱ ሰዎችን አጥብቆ ይጠላ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወይም አላህ ሲሉ የሚሰማቸው ሰዎች ጠላቱ ነበሩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የፈጣሪን ስም ሲጠሩ የሚያያቸው ሰዎች በዛው ልክ አጭበርባሪዎች፣ የሰው ሃቅ የሚበሉ፣ ለሰው ክፉ የሚያሰቡ እንደነበሩ ይረዳል፡፡ አስር ጊዜ ፈጣሪ ፈጣሪ ሲሉ ደሙ ይፈላል፡፡ በዚያ ላይ ፆሞና ሰግዶ አያውቅም፡፡ እሱ በድህነት ተቆራምዶ እየኖረ ሌላው ጠግቦ እያገሳ የሚሰግድበት ምክንያት አልታየውም፡፡ ፍትህ ለሌለው አምላክ አልሰግድም ብሎ ወስኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በህይወት እያለ ሁሉም ሰው ይጠላው ነበር፡፡ እዚህም እንደማይፈለግና እንደተጠላ ከሰዎቹ ሁኔታ ገብቶታል፡፡
ድንገት አንድ የሚያስገመግም የመለከት ድምጽ ተሰማ፡፡ ህዝቡ ሁሉ እየተመመ ወደ አንድ ሰፊ ሜዳ ተሰበሰበ፡፡ የህዝቡን ቁጥር ለመገመት የሚቻል አልነበረም፡፡ የመልአክቱ ደግሞ ከዛ የባሰ ነው፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ ሰማዩን ሞልተውት ነበር፡፡ ብዛታቸው የሚያርበደብድ ፍርሃትን የሚፈጥር ነበር፡፡
|ምንድነው?.. ሲል አሰበ፡፡ ..ፈጣሪ ሊፈርድ ነው፡፡.. ሲል መለሰለት ያ ድምጽ፡፡ ..በማን ላይ.. ሲል አሰበ፡፡ ..ባንተ ላይ.. መለሰ ድምፁ፡፡ ትንሹ ቆይቶ ..ሰአቱ ደርሶአል.. አለው፡፡ ፈልጐ ሳይሆን ሳይፈልግ ወደ ሜዳው አመራ፡፡ ሜዳው መሃል ከአጃቢዎቹ ጋር ቆመ፡፡ የሁሉም አይን የተተከለው እሱ ላይ ነበር፡፡ ..አሁን ፈጣሪ ያናግርሃል.. አለ ያ ድምጽ፡፡
ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ህዝቡ እየተንጫጫ ነበር፡፡ ድንገት ሰማዩ በአንድ ታይቶ በማይታወቅ እጅግ ልዩ የሆነ ብርሃን ተደበላለቀ፡፡ ሁሉም ፀጥ እረጭ አለ፡፡ በፍርሃት ተርበድብዶ ሳይወድ በግዱ መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፋ፡፡ አይኑ ማየት አዕምሮውም ማሰብ አልቻለም፡፡ ያየው ብርሃን በሱ የማሰብ አቅም የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ..አሁን ያየኸው ፈጣሪን ሳይሆን የከበበውን ብርሃን ነው፡፡ ፈጣሪን እስከ ዛሬ ማንም አላየውም፡፡.. አለው ያ ድምጽ፡፡
እሱ ግን በግንባሩ እንደተደፋ ነው፡፡ ለዚህ ላየው ግርማ ያለው ብርሃን ለዝንተ አለም በግንባሩ ቢደፋ እንደማይጠላ በድንገት ታሰበው፡፡
ምንነቱን መግለጽ የማይቻል እጅግ በጣም ውብ ግርማ ያለውና እፎይታ የሚሰጥ ድምጽ ሰማ፤ ቃላቶቹ አይሰሙም፡፡ ግን ምን ለማለት እንደፈለገ ይገባል፡፡ ..ጉዳይህን እናያለን.. የሚል ይመስላል፡፡
አንድ ሰው ይሁን መልአክት የማይታወቅ ጮክ ብሎ ሲናገር ሰማው፡፡ ..ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ቻይና ሁሉን አዋቂ ነህ፡፡ ይህ ሰው አንተን ደፍሮአል፤ ያንተን ስም የሚጠሩ ሰዎችን አምርሮ ይጠላ ነበር፡፡ ላንተ አልፆምምና አልሰግድም ብሎ አምጿል፡፡ እሱ እንደፈለገው ስላልኖረ ብቻ አንተን ፍትህ የለህም ሲል ተሳድቧል፡፡ በህይወት ዘመኑ ያንተ ጠላት ሆኖ ኖሯል፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው የሳጥናኤልና የፈርኦን ባልደረባ ነው፡፡ ቦታውም ከነሱ ጋር ጥልቁ የገሃነም እሳት እቶን ውስጥ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ሰው ገሃነምም ቢሆን ያንሰዋል.. ሲል ተናገረ፡፡
ህዝቡ በደስታ አጨበጨበ፡፡ ከብዙ ጫጫታ በኋላ እንደገና ፀጥታ ነገሰና አንድ በቁጣ የነደደ ድምጽ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ..ብዙ ጨካኝና መጥፎ ሰዎችን አይተናል፡፡ ይህ ሰው ግን ከነሂትለርም ከነሞሶሎኒም የባሰ ነው፡፡ አቅም ስለአጣ እንጂ ከነሱ የባሰ ህዝብ ከመፍጀት አይመለስም ነበር፡፡ እነሱ እንኳን በግልጽ ያንተን ስም የሚጠሩትን ሰዎች አልጠሉም፡፡ ይህ ሰው ብርቱዎችና ሃይለኞች ነን ባዮች የሚቃጠሉበት ገሃነም ውስጥ መወርወር አለበት.. ሲል ተናገረ፡፡
አሁንም የህዝቡ ጩኸት አስተጋባ፡፡
..አንተስ ምን ትላለህ?.. አለ ያ ባለ ግርማ ያለው ድምጽ፡፡
..የአዛኞች አዛኝ የሆንከው ጌታ የምለውን አላውቅም.. አለ እየተንቀጠቀጠ፡፡
..አይዞህ.. አለ ያ ድምጽ፡፡ ድንገት ሁሉም ነገር ፀጥ አለ፡፡ ህዝቡም መላእክቱም ፀጥ እረጭ አሉ፡፡ ..በርግጥ ይህ ቦታ ያንተ ቦታ አይደለም፡፡ ያንተ ቦታ ከዚህ ቦታ ሰባት ደረጃ የሚበልጥ እፁብ ድንቅ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ከኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ የኔን ስም የሚጠሩትን ሰዎች ትጠላ የነበርከው ትቀና ስለነበር ነው፡፡ እኔ አምላክህ ያንተ የብቻህ እንድሆን ትፈልግ ስለነበር፡፡ ሌላው ሰዎቹ ከሚሰሩት ስራ አንጻር እኔን መጥራት አይገባቸውም ብለህ ስለምታስብ ነበር፡፡  አልሰግድምና አልፆምም ያልከው ደግሞ ከኔ ከአባትህ ትክክለኛውን ድርሻህን ፈልገህ ስላጣህ ነበር፡፡ እኔን እንደ አባት፣ እራስህን እንደ ልጅ አይተህ ስላኮረፍክ ነበር፡፡ እኔ ግን ፍትሃዊ አምላክ ነኝ፡፡ እዚያ ብትጐዳም እዚህ ያዘጋጀሁልህን አታውቅም፡፡.. አለ ያ ድምጽ፡፡ የሚሰማውን ማመን አቅቶት በግንባሩ እንደተደፋ በደስታ አነባ፡፡ ህዝቡም መላዕክቱም አንድ ላይ ተንጫጩ፡፡ ..ልብና ኩላሊት የምትመረምር አምላክ አንተ ብቻ ነህ፡፡ ትክክለኛ ፍርድም ያንተ ብቻ ነው.. ሲሉ ተናገሩ፡፡ ከዚያ ወዲያ ነበር ..አትፍረድ ይፈረድብሃል.. የሚለው አንቀጽ ቅድስ መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ የተወሰነው፡፡

 

Read 5073 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:11