Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 September 2011 10:19

..አይቻልም ወይ መኖር ሥልጣን ላይ ሳይወጡ.. ፓርቲ ያረጃል እንዴ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የዛሬ ወጋችን ከፖለቲካና ከስልጣን ጋር የተገናኘ ነው - ለነገሩ ዓምዱም ፖለቲካ በፈገግታ ይል የለ! ስለ ፖለቲካ ማውራታችን ተገቢ ነው ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ ፖለቲካን ማውራት እንጂ መተግበር አልወጣኝም፡፡ ለጊዜው እኛ አገር ፖለቲካ ሲወራ እንጂ ብዙም ደስ አይልም፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ በፈገግታችን ይቀጥላል፡፡ ለከወደ አሜሪካ በተገኘ ቁም ነገር ያዘለ ቀልድ እንጀምረው - ወጋችንን፡፡

አንድ ቀን አባት ልጁ ት/ቤት ሄዶ ሳለ  አንድ ሙከራ (Experiment) ለማድረግ ይወስናል፡፡ የአፍሪካ ፖለቲከኞች ወይም ባለሥልጣናት በህዝባቸው ላይ እንደሚያደርጉት ዓይነት ሙከራ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ ልጁ ላይ አንዳችም የጐንዮሽ ጉዳት (Side effect) የማያስከትል ነው - ኤክስፐርመንቱ፡፡ የአፍሪካ መንግስታትና ፖለቲከኞች ሙከራ እኮ ህዝብን የሚፈጅ ሁሉ ሊሆን ይችላል (እነሱ ምን ቸገራቸው!) በአፍሪካና በተቀሩት የሦስተኛው ዓለም (የድሃው ዓለም ቢባል ይሻላል!) አገራትን የእርስ በርስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የነፃነት አፈና ወዘተ... መንስኤያቸውን በቅጡ ብትመረምሩት ሁሉም የድንገተኛ ሙከራ (Experiment) ውጤት እንደሆኑ ትደርሱበታላችሁ፡፡ ይሄኛው ግን የፖለቲከኞች ሳይሆን የአንድ ልጁን የሚወድ አባት (ህዝቡን የሚወድ ፖለቲከኛ ግን ከየት እናምጣ?) ትንሽዬ ኤክስፐርመንት ናት፡፡
አባት ለሙከራ ሥራው የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ይዞ በቀጥታ ያመራው ወደ ልጁ የመኝታ ክፍል ነበር፡፡ ቁሳቁሶቹንም በልጁ የማጥኚያ ጠረጴዛ ላይ ደረደረ፡፡ መሃፍ ቅዱስ፣ ከብር የተሰራ ዶላርና አንድ ጠርሙስ ውስኪ ነበሩ - የሙከራ ቁሳቁሶቹ፡፡
ከዚያም አባትየው ከራሱ ጋር እንዲህ እያለ ያወራ ጀመር፡፡ ..ከእነዚህ ሦስት ነገሮች የትኛውን እንደሚያነሳ ከበሩ ኋላ ተደብቄ አያለሁ፡፡ መሃፍ ቅዱሱን ካነሳ ፀደቅኩ! እንደኔ ሰባኪ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ዶላሩን ካነሳም ነጋዴ ይሆናል - ይሄም ለክፉ አይሰጥም፡፡ ነገር ግን የውስኪ ጠርሙሱን ብድግ ካደረገ የመጨረሻ ቅሌት ነው - ለማንም ለምንም የማይረባ ሰካራም ይሆንልኛል! አደራህን ፈጣሪ... ከዚህ ሰውረኝ.. ብሎ የልጁን ከተማሪ ቤት መመለስ በትእግስት ይጠባበቅ ጀመር፡፡ የልጁን ኮቴና ፉጨት የሰማው አባት በር ኋላ ተሸጉጦ ነገሮችን በጥሞና ይከታተል ገባ፡፡ ልጅ እንደተለመደው ወደ ክፍሉ በመግባት ደብተሩን አልጋው ላይ ወርውሮ ሊወጣ ሲል ጠረጴዛው ላይ የተቀመጡት ነገሮች የዓይኑን ትኩረት ሳቡት፡፡ በጉጉት ተሞልቶ ወደ ጠረጴዛው ተጠጋ፡፡ በመጀመሪያ መሃፍ ቅዱሱን አነሳና ብብቱ ሥር ሸጐጠው፡፡ በመቀጠል ዶላሩን ኪሱ ውስጥ ጨመረ፡፡ በመጨረሻ ውስኪውን ከፈተና በደንብ ተጐነጨለት፡፡
አባትየውም ..እግዚአብሔር ይጠብቀው... ልጄ ፖለቲከኛ ነው የሚሆነው!.. ሲል ለራሱ አንሾካሾከ፡፡
ይታያችሁ... አባት የልጁን ፖለቲከኛ መሆን እንደመዓት የቆጠረው የዲሞክራሲ እናት ናት በምትባለዋ አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡ መአተኛ በሆነችው በአህጉረ አፍሪካ ቢሆንስ?
በአፍሪካማ... ፖለቲካ እሳት ነው - ..እፉ.. ብለን ለህፃናት የምንነግራቸው ክፉ እሳት፡፡ ነገር ላልገባቸው አዋቂዎችም ..አደገኛ ስለሆነ ይጠንቀቁ!.. ብለን ቅድመ ማስጠንቀቂያ የምንሰጥበት አደገኛ ጉዳይ ነው - የአፍሪካ ፖለቲካ!!
አሜሪካኖች ግን ስለፖለቲካ እንዲህ ይላሉ ..ፖለቲካ መጥፎ ሙያ አይደለም፡፡ ከተሳካልህ በብዙ ሽልማቶች ትንበሸበሻለህ፡፡ ካልተሳካልህና ቅሌት ከተከናነብክ ደግሞ መሃፍ መፃፍ ማንም አይከለክልህም..... ወቸ gùD! እዚህ አፍሪካ ውስጥ ፖለቲካ ካልተሳካልህና ሥልጣን ካልተቆናጠጥክ መሃፍ መፃፍ አይደለም ትንፋሽ የምትወስድበት ጊዜ እንኳ የሚሰጥህ አታገኝም... ወይ ከአገር ትሰደዳለህ አሊያም አንከብክበው ወስደው ከርቸሌ ያጉሩሃል፡፡ ወዳጆቼ... የአፍሪካ ፖለቲካ የሚመኙት ሳይሆን የሚሸሹት ነው - እንደ ኤሌክትሪክ፡፡ (ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቁ ነው የተባለው እዚሁ አፍሪካ ውስጥ አይመስላችሁም?)
እኔና ፖለቲካን የሙጥኝ ያለ ወዳጄ  በአዲስ ዓመት ዋዜማ ስለ ፖለቲካ ስናወጋ ምዕራባውያኑ "Politics is a dirty game” የሚል አባባል እንዳላቸው ተነሳና እንዲህ አለ - ወዳጄ ..እነሱ እኮ መጫወቻው ሜዳ አላቸው... ስለዚህ ቢያንስ ይጫወቱታል.. አንዳችም ሙግት መግጠም አላስፈለገኝም፤ እንዳለ ተቀበልኩት፡፡ እውነት ነዋ! በኋላ ሳስበው ከፈረንጆቹ አባባል እኛ ጋ የቀረው (Politics is dirty” የሚለው ብቻ መሆኑን አጤንኩኝ፡፡ ጌሙ ሲቀነስ የሚቀረው ቆሻሻነቱ ወይም መጥፎነቱ ብቻ ነዋ!
እስቲ ዝም ብላችሁ ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ታዘቡልኝ... አንዴም እኮ ጨዋታ ሆኖ አያውቅም፡፡ እኔና እናንተ ወረቀት ላይ ከምንጫወተው በቀር ማለት ነው፡፡ አሁን ስመረምረው ግን ችግሩ እየገባኝ የመጣ ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ ቅድም እንዳልኩት በተለይ ለአፍሪካውያን እሳት ነው፤ ዜጐችን የሚቆላ ጥይት፡፡ ለሰለጠኑትና ለበለፀጉት ግን Politics is a dirty game ለምን ይሄ አይነት ግዙፍ ልዩነት ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ እነሱን ፖለቲካ እሳት ሆኖ የማይፈጃቸው፤ ጥይት ሆኖ የማይቆላቸው በአይነቱ ለየት ያለ መከላከያ ልብስ ስላሰሩለት ነው፡፡ ዲሞክራሲ ነው ከፖለቲካ ጥይት መከላከያቸው፡፡ ለነገሩ እነሱም ቢሆኑ ፖለቲካን አደገኛው አንጋፋ ሙያ ነው የሚሉት፡፡ እኛ ጋ ግን እንኳንስ ሙያ (Profession) ሊሆን ከጥይትነቱ (እሳትነቱ) ገና አልተላቀቀም፡፡ በየጊዜው ከፈረንጆቹ የምናስመጣው የዲሞክራሲ ጥብቆም የፖለቲካውን እሳት ሊከላከልልን አልቻለም - አንዴ እየጠበበን ሌላ ጊዜ ደግሞ እየሰፋን፡፡
እና ምን ይሻለናል? እንደኔ ከሆነ ለምን መከላከያውን እስክናገኝ ፖለቲካው አይቀርብንም፡፡ ለእኛ ለተራ ተርታው ዜጐች ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም ማለቴ ነው፡፡ እንግዲህ ተቃዋሚዎችም እንዲህ የሚማስኑት ኢህአዴግን ከሥልጣን አስወርደው በተራቸው በፖለቲካ እሳት ሊፈጁን አይደል! (ክፉ ስለሆኑ እኮ አይደለም፡፡ እኛ የፖለቲካ እሳቱን መከላከያ ስላለበጀን ነው፡፡) ቢቀርባቸውስ? (ሥልጣኑን ማለቴ ነው!) ሥልጣኑን ለማግኘት በእሳቱ መፈጀት ብቻ ሳይሆን ተለብልቦ መቃጠልም ስላለ ዝም ብለው ቢኖሩስ? ..አይቻልም ወይ መኖር ሥልጣን ላይ ሳይወጡ.. ለማለት ያህል ነው፡፡ ኧረ ይቻላል ... እንኳን ልማት ተኮሩ ኢህአዴግ ቀርቶ የትኛውም አምባገነን የአፍሪካ መንግሥት ሥልጣኑን ካልነኩበት ብዙም አይተናኮልም እኮ፡፡
ግን እስቲ የ20 ዓመት የፖለቲካ ክንውናችንን ቁጭ ብለን እንገምግመው፡፡ አተረፍን ወይስ ከሰርን? ለመለምን ወይስ ተለበለብን? ይሄን ጥያቄ አንጋፋዎቹ ፖለቲከኞች ወይም ፓርቲዎች ቢመልሱት ይሻላል፡፡ ከዚያ ፖለቲካ ይቅርብን ወይስ እንግፋበት የሚለውን ራሳቸው ይወስኑት፡፡
እኔ በበኩሌ የፖለቲካ ጥይት መከላከያ እስኪሰናዳልን ቢቀርብን እመርጣለሁ፡፡ ማነው የሚያሰናዳው? ሌላ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ የዚህንም መልስ ራሳቸው ፖለቲከኞቹ ቢመልሱት ይሻላል፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ  ... የዲሞክራሲ ጥብቆን ከማሰፋታችን በፊት ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መቧቸር ራስንና አገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ የፖለቲካ እሳት (ጥይት) ሲዘንብብን (ሲወርድብን) መግቢያ ይጠፋናል፡፡ ከዝናቡ መጠለያ ጃንጥላ አላበጀንማ! እናም ፖለቲካ ቢያንስ እንደሰለጠኑት a dirty game እስኪሆን ድረስና የጥይት መከላከያ እስክናበጅ ይቅርብን ብያለሁ! የፖለቲካውን ሂደት ወይም የዲሞክራሲን ጉዞ ያደናቅፋል የሚለኝ አይጠፋም፡፡ እኔ ግን አስመሳይ ወይም ቀጣፊ እለዋለሁ፡፡ ለምን ብትሉኝ... በፖለቲካ ሰበብ ዜጐች ሲታሰሩ፣ ነፃነታቸው ሲታፈን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፀም፤ ድህነት ሲንሰራፋበት፤ የኑሮ ዋስትና ሲያጣ፤ ሥራ አጥ ሲበረክት ወዘተ... እንዲህ አላሉማ!
ብዙ ጊዜ ኢህአዴግን ታግለን እናሸንፈዋለን የሚል ማስፈራሪያ ከተቃዋሚዎች ጎራ ሲስተጋባ እሰማለሁ፡፡ ግን እንዴት? በምን? የሚመልስ የለም ወይም በተፈጥሮው መልስ የሌለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አባባሉ ብዙም አይደላኝም፡፡ ይልቅስ ..አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው.. የምትለዋ የመሃሙድ አህመድ ዜማ ትዝ ይለኛል፡፡ ቆይ ግን በሞቴ ኢህአዴግን እንዴት ነው ሊያሸንፉት ያሰቡት? ተቃዋሚዎችን ማለቴ ነው፡፡ የፖለቲካውን ፍልሚያ የሚመክቱበት ጋሻ ሳያዘጋጁ? እንዴት ነው 17 አመት ከደርግ ጋር ተፋልሞ ሥልጣን የያዘን ፓርቲ ታግለን እናሸንፋለን የሚሉት? በአሜሪካ በየ4 አመቱ ዲሞክራቶቹ ሪፐብሊካነን ቢያሸንፉ እኮ አይገርምም! ሁለቱም የመፋለሚያ መሳሪያቸው ተመጣጣኝ ነው - ዲሞክራሲ ይባላል፡፡ በዚያ ላይ ፖለቲካ እሳት ሳይሆን ጌም ነው - ደርቲ ጌም ቢሆንም፡፡
ስለዚህ ከትግሉ በፊት የፖለቲካ እሳት ወይም ጥይት መከላከያውን እናሰናዳ ባይ ነኝ! የዲሞክራሲ ጥብቆ በልካችን ሳናሰፋ ግጥሚያ መግባት አገርንም ዜጐችንም በእሳት ማስለብለብ ያመጣል፡፡ በ97 ምርጫ መንግስት ዜጐችን የገደለው፣ ያሰረው፣ ያዋከበው ወዶ ነው እንዴ? የፖለቲካ ጥይት መከላከያ ስለሌለን ነበር እኮ፡፡ (ምንም እንኩዋን ኢህአዴግ አድማ መበተኛ ስላልነበረኝ ነው ቢልም) እንደ ፈረንጆቹ ዲሞክራሲ የተባለው መከላከያ ቢኖረን ኖሮ ግን እሱም አይተኩስ እኛም አንሞትም ነበር፡፡
እኔ በበኩሌ በፖለቲካ ሰበብ መታሰር፣ መዋከብ፣ መሰደድ፣ መገደል እስካልቀረ ድረስ ለአቅመ ፖለቲካ አልደረስንም ባይ ነኝ፡፡ ለአቅመ ፖለቲካ የሚያበቃንን ቅድመ ዝግጅት እስክናደርግ ደሞ ፖለቲካውም ስልጣኑም ቢቆየንስ?
ኢህአዴግ እንደ ጋዳፊ 40 ዓመት ሊገዛን ... ብሎ የሚደነፋ አይጠፋም፡፡ መልሱ ግን ቀላል ነው፡፡ የራሳችንን የዲሞክራሲ ጥብቆ ካላሰናዳን ሌላም ነገር አይቀርልንም፡፡ የስልጣኑን ነገር በተመለከተ ግን ኢህአዴግም ቢሆን 40 ዓመት ሥልጣን ላይ ይቀመጣል ብዬ አላስብም - ለምን መሰላችሁ? ሥልጣን ይሰለቸዋላ! በዚያ ላይ እርጅናም አለ እኮ! (ፓርቲ ያረጃል እንዴ?)
ኢህአዴግ 40 ዓመት ገዛም አልገዛም፤ አረጀም አላረጀም ...  አገራችንን ለአቅመ ፖለቲካ እናብቃት፡፡ በአገራችን ፖለቲካ የሚለበልብ እሳት ሳይሆን ጨዋታ እንዲሆን እንትጋ - ቆንጆ ጨዋታ እንኳን ባይሆን Dirty game እናድርገው፡፡
አዲሱ ዓመት ፖለቲካን ጨዋታ የምናደርግበት እንዲሆንልን እመኛለሁ!!  
ማሳሰቢያ- ይቅርብን ያልኩት የተግባር ፖለቲካን እንጂ ፖለቲካ በፈገግታን እንዳልሆነ ይታወቅልኝ (ነገሮችን XÃ?‰N እንሂድ ብዬ ነው

 

Read 4310 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:22