Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 September 2011 10:26

..የቅጂ መብት ጥሰት መንግስትን የመገልበጥ ያክል ነው..

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በ1955 ዓ.ም በአሜሪካ ኢሊኖይስ ግዛት የተወለደው ቢል ላስዌል የታወቀ ሙዚቃ አቀናባሪ እና ፕሮዱዩሰር ነው፡፡ ለ25 ዓመታት በሙዚቃ ሙያ የዘለቀው አሜሪካዊው አርቲስት፤ ከ700 በላይ አልበሞች ፕሮዲዩስ አድርጓል፡፡ በሙዚቃ ዙሪያ በርካታ ጥናትና ምርምር በማድረግና አዳዲስ አቀራረቦችን በመፍጠር በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም ባለሞያ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የሬጌን ሙዚቃና የቦብ ማርሌን ሥራዎች ለዓለም በማስተዋወቅ ከሚታወቀው ክሪስ ብላክ ዌል ጋር በመስራት የራሱን አስተዋኦ ያበረከተ አርቲስት ነው፡፡  ይሄ ባለሙያ የታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት ድምፃዊ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ባለቤት ነው፡፡ ቢል ላስዌል በጂጂ ተወዳጅ ሙዚቃዎች ውስጥ በአቀናባሪነትና በፕሮዲዩሰርነት አሻራውን አሳርፏል፡፡ ጳጉሜ 6 ቀን 2003 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከመልቀቁ ከሁለት ሰዓት በፊት ካረፈበት የኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ውስጥ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በሙያውና በህይወቱ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡

ለምን ወደ ኢትዮጵያ መጣህ?
በዋናነት በኢትዮጵያ የሚገኙትን የአንዳንድ አርቲስቶችን ሥራ ቀርፆ ድሪም ሪከርድ (Dream Recorded) በሚባለው አሳታሚ ድርጅት የቅንብር ደረጃውን ከፍ አድርጐ በማስቀረ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በጃፓን ገበያዎች ለመልቀቅ ነው የመጣሁት፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ለስንተኛ ጊዜ መሆኑ ነው?
በኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም ጥር ወር ታስታውሽ እንደሆነ ከጂጂ ጋር የመጀመሪያውን ኮንሰርት ሰርተናል፡፡ ኮንሰርቱን ከሰራን በኋላ ወደ አራት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ መጥቻለሁ፡፡ በአሁኑ ደግሞ ከልጄ ከአማን ጋር ነው የመጣነው፡፡  ጂጂ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያቀረበችው ኮንሰርት እንዴት ነበር?  
ኢትዮጵያ ውስጥ ከጂጂም ጋር ሆነ ከሌላ ባለሞያ ጋር ስሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ኮንሰርቱ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም ከሀገር ውስጥም ከውጭም አስደሳች ምላሾችን አግኝተንበታል፡፡ ችግሮች ብዬ ስልሽ የድምጽና የሚክሲንግ ችግሮች ማለቴ ነው፡፡ ግን ያም ሆኖ ህዝቡ ደስተኛ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ህዝቡን አላስከፋም፡፡
አንዳንድ ተመልካቾች ጂጂ ያቀረበችው ሙዚቃ ከጠበቅነው በታች ነበር ይላሉ?  
ብዙ ነው ብዬ ባላስብም ትንሽ አልነበረም፡፡ በኮንሰርቱ ጂጂን ይገልታል ብለን ያሰብናቸውን ሙዚቃዎች ተጫውተናቸዋል፡፡  ዋናው ነገር ግን ጂጂ ከናፈቃት የሀገሯ አድናቂዎቿ ጋር መገናኛ መድረክ መፍጠራችን ነው፡፡  
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደምትፈልግ ተናግረህ ነበር፡፡  
እውነት ነው፡፡ እንዳሰብነውና እንዳቀድነው እያስኬድነው ነው፡፡ ከሙዚቃ አቀናባሪው አበጋዝ ሺዮታ ጋር ደረጃውን የጠበቀ ስራ ለመስራት ተስማምተናል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ስራ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ያለ ባለሞያ ስለሆነ እኛ ላሰብነው ፕሮጀክት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡  
በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑትም ካልሆኑትም፣ ወጣት ከሆኑትም ካልሆኑትም፤ ጀማሪ ከሆኑትም ካልሆኑትም የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረናል፡፡ ዋናው ከሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠራችን ነው፡፡ የሀገሪቱን ሙዚቃ ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣት መስራት ጀምረናል፡፡ በተለይ ወጣቶች ብዙ ይረዱናል ብለን እናስባለን፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ልዩነት እናመጣለን የሚል እምነት አለን፡፡  
የኢትዮጵያን የሙዚቃ ደረጃ የማሳደግ ነገር ሲነሳ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች  እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ፍራንሲስ ፋልሴቶ (የአሊያን ኢትዮ ፍራንሲስ ባለሙያ) የኢትዮጵያ የድሮ ሙዚቃዎችን በማሰባሰብ (ኢትዮፒክ) በሚል መጠሪያ በሙዚቃ መሣሪያ ተቀነባብረው ተከታታይ ስራዎች እየወጡ ነው . . .     
በመሠረቱ እኛ እንደ ኢትዮፒክ ሙዚክ ሙዚቃዎችን የማሰባሰብ አላማ አይደለም ያለን፤ በርግጥ ፍራንሲስን የመሳሰሉ ሰዎች በኢትዮጵያ ሙዚቃ በማሰባሰብና በማደራጀት ጠለቅ ያለ ስራ ሰርተዋል፤ ይህ ይደነቃል፡፡ እኛ ግን በኢትዮጵያ ሙዚቃ የወደፊት እድገት ላይ መስራት፤ ልዩነት ያለውና አለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ስራ ማውጣት ነው ዓላማችን፡፡  
በኢትዮጵያ ትኩረት አድርገህ ልትሰራበት ያሰብከው የትኛውን የሙዚቃ ዘርፍ ነው?
በበለጠ ፍላጐትና ዝንባሌው ያለኝ በባህላዊ yኢትዮጵያየሙዚቃ ቃናዎች ላይ ለመስራት ነው፡፡ ፈሩን ያልለቀቀ ሆኖ ከጃዝም ብዙ ያልተደባለቀ፣ ወደ ሮክ ያዘነበለ ስራ ለመስራት ነው በቅድሚያ ያሰብነው፡፡
በርግጥ የስራው ሂደት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጥሩ  ደረጃውን የጠበቀ የአዘፋፈን ስልቶችና የሙዚቃ ቃና ያለ በመሆኑ፣ ያለውን ስንለውጥ ነገሮችን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ አድርገን መስራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የድሮውንም እያከበርን ለመጪው ትውልድ የሚሆን ስራ ነውና ለመስራት የምንፈልገው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ደረጃውን y«bq ስቱዲዮ ከጂጂ ጋር፤ ለመስራት አስባችሁ ነበር፡፡ ምን ደረሰ?  
በኢትዮጵያ ውስጥ አበጋዝ ደረጃውን የጠበቀ ስቱዲዮ ገንብቶ ሙዚቃ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ እኛም ለጊዜው ከእርሱ ጋር ተባብረን ለመስራት ነው ያሰብነው፡፡ የሙዚቃ ገበያን በማጥናትና ሙዚቃን በማስተዋወቅ ጥልቅ እውቀት ካለው፤ ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ፤ ከቴዲ አፍሮ ጋር ከሚሠራውና አለምአቀፍ የሙዚቃ እውቀት ካለው አዲሱ ገሠሠም ጋር እንሰራለን፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስንሰራ ርምጃችን የተቀላጠፈ እንደሚሆን እምነት አለኝ፡፡  
የኢትዮጵያን ሙዚቃ አለማቀፋዊ ለማድረግ ነው ዓላማችሁ . . .   
በሚገባ! በቅርቡ የሚታይ ነው፡፡ በአውሮፓ፣ በጃፓን፣ በአሜሪካ፣ ተመሳሳይ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እድገት ላይ የሰራንባቸውና የምንሰራባቸው የሙዚቃ ስቱዲዬዎችና የፕሮሞሽን ስርዓት ስላለን በቀጣዩ አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ለአለም እናበቃለን፡፡
የሙዚቃ ጥልቅ ዕውቀት እንዳለህ ይታወቃል፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን ይጐድለዋል ብለህ ታስባለህ?
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከስር መሰረቱ ሲታይ በሙዚቃ ቃናው፣ በዜማው፣ በድምጻዊያን የአዘፋፈን ስልት ረገድ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ ሙዚቃውን በተለየ ጣዕም የማቅረብ፣ የተለየ አተያይን አይቶ የመሞከር፣ መሰረቱን ሳያበላሹ ደረጃውን ከፍ የማድረግ ጥረት አለመኖር ነው፡፡ ሙዚቃውን ስቱዲዮ ወስዶ ያለምንም የተለየ ጥረት መቅረጽ፣ ማቀናበር፣ ለሕዝብ ማቅረብ YÒ§L”” YH BÒWN GN በቂ አይደለም፡፡  ሌሎች ቃናዎችን፣ ለዛዎችን መመርመርና ማሻሻል ይቻላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ከልብ የሆነ ጊዜና ጉልበትን ይጠይቃል፡፡ ከሙዚቃው ከሀሳቡ ጀምሮ፤ ፕሮዳክሽን አልቆ፤ እስከ ማስተዋወቅና ማሻሻጥ ድረስ ያለው ሂደት ሊለፋበትና፣ ጥራቱን የጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚነሳ ክርክር አለ፤ በስቱዲዮ በኮምፒዩተርና በኪቦርድ  የሚሰሩ ሙዚቃዎች በባንድ ከሚሰሩ ሙዚቃዎች ጋር ሲነጻሩ ጣዕም የላቸውም ይባላሉ?
በተለያየ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ጎልመስ ያሉ ሰዎች በሙሉ በባንድ የተሰሩ ሙዚቃዎችን ሲያደንቁና ሲያጣጥሙ ይታያል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያየ አገር ያለ ዕውነታ ነው፡፡ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ የተለያዩ የአደጉ አገሮችን ማየት ይቻላል፤ ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ውጭም ብታይ በስቱዲዮ በአንድ ሰው ብቻ የሚቀናበሩ ሙዚቃዎች ለጆሮ በቀላሉ የሚደመጡና ጣዕም ያላቸው ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሁለቱም ቴክኒክ በሚገባ ከተሰራና የሙዚቃ ዕውቀት ከታከለበት የየራሱ ውበት አለው፡፡ በእኔ እምነት የትኛውም ቴክኒክ የትኛውንም ሊተካ አልመጣም፡፡ በሙሉ ባንድና በኮምፒዩተር የሙዚቃ ስራ ዘዴ ውስጥ ይኼኛው ፍፁም ነው፣ ያኛው እንከን የሞላው ነው ብለን ወግ አጥባቂ መሆን የለብንም፡፡ በኢትዮጵያ ብናይ በ1970 ዓ.ም. የተሰሩ ሙዚቃዎች ወደር የለሽ ናቸው ብለን መወሰን የለብንም፡፡ በሌላ አንጻር ቴክኖሎጂው ስለፈቀደ ብቻ ስቱዲዮ ውስጥ በላፕቶፕ በርካሽ፣ ድምጽና ቅንብር  ሰርቶ ለገበያ ማውጣቱ ሙያው የሚፈቅደው አሰራር አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት የቀረፃ ሂደት የተሰሩና የተበላሹ በርካታ የሙዚቃ ስራዎች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥም አይቻለሁ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተሰሩ ስራዎችን ሰው ሊወዳቸው ይችላል፡፡ ከሙያ  አንፃር ሲታይ ግን ርካሽ ነው፡፡ ይህ መሆን የለበትም፡፡
ወደ ባለቤትህ ጂጂ ስራዎች እንምጣ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ..ምስጋና.. የተባለውን አልበሟን ከኢትዮጵያ ውጭ ለገበያ አቅርባችኋል፡፡ ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ግን አልታየም?    
/ሳቅ/ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሙዚቃ ህትመትና ቅጂ ያለው አመለካከት የተዛባና ኃላፊነት የጐደለው ይመስላል፡፡ ይህ ጉዳይ የእኛም ዕገዛ ታክሎበት መቀየር የሚገባው አንገብጋቢ ችግር ነው ብለን እናምናለን፡፡ አንድ ሙዚቃ ሰርተሽ እንደማንኛውም ዕቃ አከፋፋዮች ጋር ወስደሽ ይሄን ዕቃ ይዤ መጥቻለሁ፤ እና እንዴት ታየዋለህ? ብሎ መጠየቅና አከፋፋዩም እንደማንኛውም ዕቃ ያለምንም ሙያዊ ዕውቀት ሙዚቃው ላይ የሚወስንበት አሰራር መቅረት አለበት፡፡
እሱ ሊያውቅ የሚችለው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያወጣለት፤ የት እንደሚሸጠው ብቻ ነው፡፡ አንቺ ግን ምን ያህል ኮፒ እንደተሸጠ የማወቅ መብት የለሽም፡፡ ይህ እጅግ ኋላቀርና በመንግስትም በኩልም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀየር የሚገባው ያልሠለጠነ አሰራር ነው፡፡ ሞያዊ የሆነ ግምገማና የሽያጭና የማስተዋወቅ ስርዓት ሊገነባ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንተ መሠረቱ ዘመናዊ የሆነ የመንግስት የአሰራር ሂደትን የመሠረተችና የምታውቅ አገር ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የሚታየው የአሠራር ግድፈት ግን ከዚህ ታሪክ የተለየ፣ የተበላሸና ኋላቀር ነው፡፡  
የጂጂ 3ኛ አልበሟ ..ጉራማይሌ.. በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እንደሆነ ይነገራል፡፡ አሁንስ ከዛ የተሻለ ስራ እንጠብቅ?
በርግጠኝነት ዋስትናውን እሰጥሻለሁ (ሳቅ)
የቅጂና ተዛማጅ አእምሮአዊ ንብረት ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፡፡ መፍትሄው ምን ይመስልሃል?  
አፋጣኝ እርምጃ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ የቅጂ መብት ጥሰት እኮ መንግስትን የመገልበጥ ያክል ነው፡፡ ዕውቀቱ ያላቸውና መንግስት በራሱ ይህንን የሚያሳጣ አሠራር በዘመቻ መለወጥ አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደተሻለ ደረጃ ከማሳደግ በተጨማሪ መላው ቤተሰብህን ይዘህ ኢትዮጵያ ውስጥ በቋሚነት የመኖር እቅድ አለህ?  
በአንድ ቦታ ለዘላለም መኖር አይቻልም፡፡ kኢትዮጵያêEa ባለቤቴ (ጂጂ) ቤተሰብ መስርቻለሁ፤ ልጅም ወልጃለሁ፡፡ ልጄ የመጣበትን የዘር ሀረግ፣ አገር፣ ታሪክ፣ ማንነት አውቆ እንዲያድግ እፈልጋለሁ፡፡ ቋንቋውንም እንዲማር እሻለሁ፡፡ እኔ በስራ ተጠምጄ ከአገር አገር የምዘዋወር ቢሆንም ለልጄ ጊዜ መስጠት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡   
ባለቤትህን ጂጂን ከሞያ ባሻገር በሚስትነትና በእናትነት እንዴት ትገልፃታለህ?
ጂጂ ለሙዚቃ የተሰጠች ናት፡፡ ግን ሙዚቃን ያገኘችው በትምህርት ሳይሆን በመሆን ነው፡፡ (ሳቅ) ሙዚቃን በመማር፣ በመሰልጠንና በተግባር በመለማመድ ረገድ ስንፍና ሊኖርባት ይችላል (ሳቅ) ስጦታዋ ግን ወደር የለውም፡፡ በሚስትነትም ጂጂ በሚገርም ሁኔታ እንደሙዚቃው አይነት ባህሪ ነው የሚንፀባረቅባት (በጣም እየሳቀ)
ነገ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ነው፤ (ጳጉሜ 6/2003 ዓ.ም ነበር) ከሁለት ሰዓት በኋላ አንተና ልጅህ አማን ደግሞ ወደ አሜሪካ ልትበሩ ነው... ልጅህ ..አበባየሆሽ..ን ሳያይ...?
(በመቆጨት ስሜት) በጣም ይገርምሻል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በትውልዱ ከተማ ኒውዮርክ ነገ ySep 9/11 ጥቃትን ምክንያት በማድረግ የአስረኛ ዓመት ትልቅ ክብረ በዓል አለ፡፡ መገኘት ስላለብኝ ነው የምሄደው፡፡

 

Read 5149 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:30