Administrator

Administrator

በአብዱል ፈታህ አብደላህ አዘጋጅነት በኮንሶ የባህል ህግ ላይ ጥናት ተደርጐበት የተዘጋጀው “ሤራ አታ ኾንሶ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ ትኩረት ያደረገው በኮንሶ የባህል ህግ ስርዓት ላይ ሲሆን በጥናቱ ውስጥ የኮንሶ የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን ተሳትፈውበታል፡፡ በ197 ገፆች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በኮንሶ የባህል ህግ ስርዓት ላይ ትኩረት ቢያደርግም አጠቃላይ የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና ሃይማኖታዊ ሁነቶች ይቃኛል፡፡ መጽሐፉ በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓቶች ማዕከልና በኮንሶ ወረዳ አስተዳደር ትብብር ታትሞ በነፃ ለአንባቢያን ደርሷል፡፡ በተያያዘ ዜና የቱሪዝምና እና የሙዚየም ማውጫዎችን በማሳተም የሚታወቀው ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን፤ የኮንሶ ህፃናት ስለ አካባቢያቸው የቱሪዝም መስህቦች እንዲያውቁ የሚረዳቸውን “ኮንሶን ለህፃናት” የተሰኘ የቱሪዝም መጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ሲሆን “ሴራ አታ ኾንሶ” ከተባለው መጽሐፍ ጋር በኮንሶ ካራት ከተማ ባለፈው ሳምንት ተመርቋል፡፡

መቀመጫውን አሜሪካ ሂዩስተንና ኢትዮጵያ በማድረግ በቴአትር ዘርፍ የሚንቀሳቀሰው ዮሐንስ ቴአትር ፕሮዳክሽን፤ “ደላሎቹ” የተሰኘውን ቴአትር በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ  ለእይታ ያበቃል፡፡ የምርቃት ስነስርዓቱ በዕለቱ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በሀዋላ ሴንትራል ሆቴል እንደሚካሄድም ድርጅቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በኤርሚያስ ጌታቸው ተደርሶ፣ በህይወት አራጌ በተዘጋጀው በዚህ ቴአትር ላይ ችሮታው ከልካይ፣ ህይወት አራጌ፣ ኤርሚያስ ጌታሁንና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያን እንደሚሳተፉበት ለማወቅ ተችሏል፡

በዶ/ር መልካሙ ታደሰ የተዘጋጀው “የጐጆ ድርጅት” (Home business) የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ከቀኑ በ8 ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ በዋናነት ዜጐች እውቀታቸውን፣ ችሎታቸውን እንዲሁም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ከመኖሪያ ቤታቸው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን መንገድ ያመላክታል ተብሏል፡፡ በምረቃው ላይ በመጽሐፉ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

በደራሲ ልዑል ግርማ የተዘጋጀው “ፍቅርና ትግል” የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ መፅሀፉ በፍቅር ታሪኮችና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን በ287 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡ በ45 ብር ለገበያ እንደቀረበም ታውቋል፡፡ ደራሲ ልዑል ግርማ ከዚህ ቀደም “አራት አርባ አራት” የተሰኘ አነጋጋሪ ረዥም ልብ-ወለድ የፃፈ ሲሆን “የወንድሜ ሚስት” የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል ለንባብ ማብቃቱ የሚታወስ ነው፡፡

በአርቲስትና የፎቶግራፍ ባለሙያ ወንድወሰን በየነ የተዘጋጀውና “A Glimpse of Ethiopian II” የተሰኘ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በራዲሰን ብሉ ሆቴል ይከፈታል፡፡ ኤግዚቢሽኑ የፊታችን ሐሙስ ተከፍቶ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን በኤግዚቢሽኑ መልክአምድር፣ አሮጌ ቤቶችንና ሌሎች ተፈጥሯዊ ነገሮችን የሚያስቃኙ ፎቶግራፎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

በደራሲ ደሳለኝ ስዩም የተፃፈው “የታሰረ ፍትህ” የተሰኘ ኢ-ልብወለድ መጽሐፍ ታትሞ ለገበያ ቀረበ፡፡ የመጽሐፉ ጭብጥ በህዝብና በገዢው ፓርቲ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡ በ3 ምዕራፎችና በ148 ገፆች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በ35 ብር ከ50 እየተሸጠ ነው፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ደም የተፋ ብዕር” የሚል የግጥም መድበልና “የጠረፍ ህልሞች” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወቃል፡፡

ፈጠራው በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል ተብሏል
“እነዚህ የላቀ የፈጠራ ክህሎት ከታደሉ የአሜሪካ ተማሪዎች ጥቂቶቹ ናቸው” - ባራክ ኦባማ

     የ18 አመት ዕድሜ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተማሪ ፈለገ ገብሩ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያስችላል የተባለውን የቴክኖሎጂ ፈጠራውን ባለፈው ሳምንት በዋይት ሃውስ በተካሄደው የሳይንስ ትርዒት ላይ ማቅረቡን ኤምአይቲ ኒውስ ዘገበ፡፡
በማሳቹሴትስ የሚገኘውን ኒውተን ኖርዝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወክሎ በትርዒቱ ላይ የቀረበው ፈለገ፣ የትምህርት ቤት ጓደኛው ከሆነችው ካሬን ፋን የተባለች የ17 አመት ወጣት ጋር በመተባበር የፈጠረው አዲስ ቴክኖሎጂ፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን በማስተላለፍና እንቅስቃሴውን የተሳለጠ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታውየን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሳይንስ ትርዒቱ ላይ ተገኝተው የወጣቶችን የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች የተመለከቱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በዝግጅቱ ላይ ስራዎቻቸውን ላቀረቡ ተማሪዎች ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፣ እነዚህ በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች፣ የላቀ ፈጠራ ክህሎት ከታደሉ በርካታ የአሜሪካ ተማሪዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዴቪድ ሁድሰን በዋይት ሃውስ ድረገጽ ላይ ፈጠራውን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ “እነዚህ ወጣቶች በአለማችን እንደ ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በርካታ ቁጥር ያላቸው እግረኞች የሚሞቱበት አገር እንደሌለ በማጤን ነው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግና አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችል ፈጠራ በማመንጨት ያቀረቡት ”ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ፈጠራው አሽከርካሪዎች እግረኞችን በተመለከተ መረጃ የሚያገኙበት እንዲሁም እግረኞችም የተጨናነቁ መንገዶችን ያለ ችግር ማቋረጥ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ሁድሰን፣ ፈጠራው የጸሃይ ብርሃንን በሃይል ምንጭነት የሚጠቀምና የተሸከርካሪዎችን ፍጥነት በማስላት የተወሰነ ቦታ ላይ የሚደርሱበትን ጊዜ የሚያሰላ፣ ለእግረኞችም መንገድ ማቋረጥ የሚችሉበትን የተመረጠ ጊዜ የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 በሚማሩበት ትምህርት ቤት የተቋቋመው ኢንቬንቲም የተባለ የፈጠራ ክበብ መሪዎች የሆኑት ፈለገ እና ካረን በፈጠራ ስራ ላይ የመግፋት ዕቅድ ያላቸው ሲሆን፣ ፈለገ በአሁኑ ወቅት በብራውን ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስና የቪዡዋል አርት የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡“የፈጠራ ስራዎቻቸውን በዋይት ሃውስ የሳይንስ ትርዒት ላይ እንዲያቀርቡ መጋበዛቸው፣ ለእነዚህ ልጆች እጅግ የሚደንቅ ክብር ነው የሚያጎናጽፋቸው፡፡ ፈለገም ሆነ ሌሎቹ ተሳታፊ ተማሪዎች ለሌሎች ወጣቶች መነቃቃትን የሚፈጥር የፈጠራ ተነሳሽነትና የአላማ ጽናት የተላበሱ ናቸው።” ብለዋል ሌሊልሰን-ኤምአይቲ የተባለው የፈጠራ ፕሮግራም መምህርና የፕሮጀክቱ አማካሪ የሆኑት ሌይ ስታብሩክስ፡፡
ኤምአይቲ ኒውስ እንደዘገበው፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገብሩ፣ በአገሩ በኢትዮጵያ ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ እግረኞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ለኢንቬንቲቭ ያቀረበውን መረጃ መነሻ በማድረግ ፕሮጀክቱ ሊቀጥል ችሏል፡፡

Saturday, 07 June 2014 14:09

የፍቅር ጥግ

ፍቅር እሳት ነው፡፡ ልብህን ያሙቀው ወይም ቤትህን ያቃጥለው ግን ማወቅ አትችልም፡፡
ጆአን ክራውፎርድ
ብዙ ሰዎች ካንተ ጋር በሊሞዚን ተሳፍረው መሄድ ይሻሉ፡፡ አንተ የምትፈልገው ግን ሊሞዚኑ ሲበላሽ አብረውህ አውቶብስ የሚሳፈሩትን ነው፡፡
ኦፕራ ዊንፍሬይ
ፍቅር እርስ በእርስ መተያየት አይደለም፤ ወደ አንድ አቅጣጫ አብሮ ማየት እንጂ፡፡
አንቶይኔ ዴ ሴይንት ኢኤክዮፔሪ
ፍቅር ከባድ የአዕምሮ በሽታ ነው፡፡
ፍቅር ማብሪያ ማጥፊያው በሌላ ሰው ቁጥጥር ሥር የሆነ የኤሌክትሪክ ብርድልብስ ነው፡፡
ካቲ ካርሊሌ
ፍቅር ፒያኖ እንደመጫወት ነው፡፡ መጀመሪያ በህጎቹ መሰረት መጫወት መማር አለብህ፡፡ ከዚያ ህጎቹን ረስተህ ልብህ እንዳዘዘህ መጫወት ይኖርብሃል፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
በመጀመሪያ እይታ የሚይዝ የፍቅር ልክፍት በሁለተኛ እይታ ይድናል፡፡
የአሜሪካዊያን አባባል
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪውንም ተቀባዩንም፡፡
ዶ/ር ካርል ሚኒንገር
ፍቅር ትጋት የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከባድ ሥራ ደግሞ አንዳንዴ መጉዳቱ አይቀርም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ

Saturday, 07 June 2014 14:08

የፍቅር አቡጊዳ

አቶ መርሻ በኩራት ጨበጠው፡፡
ዕድላዊት ብሩህ ፈገግታዋን ፈነጠቀችለች፡፡
እሱም በቡናማ ዓይኖቹ አስተዋላት…
ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቧ ተሸበረ፡፡ ያኔ የአተነፋፈስ ስርዓቷ በጥቂቱ ተዛባ፡፡ ከያኔዋ ቅፅበት ጀምሮ ዕድላዊት መልስ ያላገኘችለት ጥያቄ በውስጧ ተጭሯል፡፡
የረሐብ የመሰለ፣ ያን ሰው የማግኘት፣ የራስ የማድረግ፣ በውል ይኼ ነው የማትለው፣ ነገር ግን ጠንካራ ስሜት!
ባለ ቡናማ ዓይኑ ወጣት የሸሚዙን እጅጌ እስከ ክንዱ ጠቅልሎ በውስጠኛው ዓይኗ ለውስጠቷ ይታያታል፡፡ የዳበረ ሰውነቱ፣ ወኔና ቆፍጣናነቱ፣ ማርኳታል፡፡
ሰርክ ቤታቸው እየተገኘ ከእርሷና ከመርሻ ጋር እየተጨዋወተ ያመሻል፡፡ ስለ ስራና ስለ ተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ይወያያል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በደንብ አስተውላለች ወጣትነቱ፣ ብስለቱ በዚያ ላይ ደልዳላ ሰውነቱ አስጎምጅቷታል፡፡
እርግጥ ነው አቶ መርሻም ወዶታል፡፡ በስነምግባሩ፡፡ በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ባለው ትጋትና ብቃት፣ ከሁሉም በላይ በመንፈሰ ጠንካራነቱ ሊያከብረው ተገዷል፡፡
ይሄይስ የዕድላዊት ሁኔታ አላማረውም፡፡ ድርጊቶቿ ሁሉ ሰላም አሳጥቶታል፡፡ አንጀት በሚበላ ሁኔታ እንባ ባቀረሩ አይኖቿ እየተመለከተችው፣ እየተንቆራጠጠችና ጣቶቿን እያፍተለተለች ትቀባጥራለች፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ወሬዋ ለመልስ የማይመቹ፣ እዚያው በዚያው የሚገጫጩ ፍሬ አልባ ቃላት ስለሚሆኑባት በዝምታ ሲያዳምጣት ይቆይና፡-
“በቃ ልሂድ አይደለም?” ይላታል፡፡
“እባክህ ይሄይስ ትንሽ ቆይ”
“ለምንድነው ዕድል እንዳልሰራ የምታደርጊኝ?”
“ምን አደረኩህ?”
“ይሄው ስንት ወር ሙሉ በተደጋጋሚ እያስጠራሽኝ የረባ ነገር እንኳ ሳትነግሪኝ በጊዜዬ ትጫወቻለሽ፡፡
ቀድሞውንም እኔን ብቻሽን በምትሆኚ ሰዓት መጥራትሽ አግባብነት የለውም! በጣም ነውርና ልፈቅደው የማላስበው ድርጊት ነው እያደረግሽ ያለሽው!”    ጮክ ብስጭት ብሎ፡፡
“የምታስቢው ሁሉ የማይሞከር ነው፡፡ ባለትዳር መሆንሽን፣ ባለቤትሽ ላንቺ ያለውን ፍቅር አስታውሺ እንጂ! እኔም ብሆን የዛን ጨዋ ሰው ጎጆ የማናጋ ከሐዲ አለመሆኔን ብታውቂ ደስ ይለኛል” ረጋ፣ አንገቱን ወደ ፊቷ ሰገግ እያደረገ፡፡
እሷ ፀጥ! አይኖቿን በእንባ ሞልታ ታቀረቅራለች።
የሳሎኑን በር ከፍቶ ሲወጣ ዓይኖቿ ያቆሩትን መራር ፈሳሽ፣ ከታመቀው የስሜት ትንፋሽዋ ጋር እኩል ትለቃቸዋለች…     
(“ፍቅርና ትግል” ከተሰኘው
  የደራሲ ልዑል ግርማ የአጭር ልብወለድ
  መድበል የተቀነጨበ)

ከአሸባሪዎች ጥቃት ጋር የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም የተወለደው ሴፕቴምበር 11 ቀን 1862 ዓ.ም ነው፡፡ ኒውዮርክን ሲወዳት ለጉድ ነው። ብዙዎቹ ታሪኮቹም ኒውዮርክ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ የጽሑፍ ሥራውን የጀመረው ወህኒ ቤት ታስሮ ሳለ ነው፡፡ ታሪኮችን እየፃፈ ኦ ሔነሪ በሚል የብዕር ስም ለጓደኞቹ ይልካል፤ ጓደኞቹ ደግሞ በኒውዮርክ በሚታተሙ መጽሔቶች ላይ ያወጡለት ነበር፡፡ እነዚያ ድንቅ ታሪኮች ከወህኒ ቤት እንደሚፃፉ ግን ማንም የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ሚስቱን በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ባጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወህኒ ቢወረወርም የሚጽፋቸው ታሪኮች ግን የሚያሳዝኑና የሚጨፈግጉ አልነበሩም፡፡ የሚያዝናኑ፣ የሚያስቁና የሚያነቃቁ እንጂ፡፡
ወጣቱ ፖርተር ቱባውን (ያላጠረውን) መዝገበ ቃላት ተሸክሞ ነበር የሚዞረው፡፡ እንደመጽሐፍም ያነበውና በቃላት ይማረክም ነበር፡፡ የቃላት ክህሎቱን ከሼክስፒር ጋር የሚያወደድሩም አልጠፉም። እንዲያም ሆኖ ፖርተር ኮሌጅ የመግባት ዕድል አላገኘም፡፡ በ15 ዓመቱ ነው ትምህርቱን አቋርጦ በአጐቱ መድሃኒት ቤት ሥራ የጀመረው፡፡ በቴክሳስ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና ስፓኒሽ ቋንቋዎችን በቅጡ የተማረ ሲሆን አስፈላጊ ሲሆን የውጭ ቋንቋ ቃላትን በታሪኩ ውስጥ ይጠቀማል፡፡
ኦ ሄነሪ አንዳንዴ “የአሜሪካው ሞፓሳ” በሚል ይታወቃል፡፡ በአጫጭር ልብወለዶች ላይ ያልተጠበቀ አስገራሚ ወይም አሳዛኝ አሊያም አስቂኝ አጨራረስን እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል፡፡ ታሪኮቹ ግን ስለተራ ተርታ ሰዎች ነው የሚተርኩት፡፡ እንዲያም ሆኖ  ዓለማቀፋዊ ጭብጦችን የሚያንፀባርቁ ናቸው - ፍቅርን፣ መስዋዕትነትን፣ ክብርንና ርህሩህነትን፡፡
ኦ ሄነሪ ዝናን የተቀዳጀው በአንድ ጊዜ አይደለም። የሚጽፋቸውን ታሪኮች በመላ አገሪቱ ለሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ቢልክም፤ በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ “ነገር ግን ይሄ ጉዳይ አሳስቦኝ አያውቅም፤ አዲስ ቴምብር ለጥፌባቸው ወደ ሌላ ቢሮ እልካቸዋለሁ፡፡ እንዲህ ሲመላለሱ ይቆዩና በአንዱ የህትመት ቢሮ ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ተቀባይነት ያላገኘ ታሪክ ግን ጽፌ አላውቅም” ብሏል፤ አፕሪል 4 ቀን 1909 ዓ.ም ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ብቸኛ ቃለምልልስ፡፡ ለምሳሌ The Emanicipation of Billy የተሰኘው ምርጥ ሥራው ከ10 ጊዜ በላይ ውድቅ እንደተደረገበት ጠቅሶ የማታ ማታ ግን እንደሌሎቹ ሥራዎቹ ሁሉ በአንዱ የህትመት ውጤት ላይ እንደታተመለት ተናግሯል፡፡
የኦ‘ሄነሪ በርካታ አጭር ልብ-ወለዶች ወደ አማርኛ የተተረጐሙ ሲሆን ከእነሱም መካከል The Last Leaf (የመጨረሻዋ ቅጠል) እና The Gift of the magi ይገኙበታል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የደራሲው ሥራዎች ተተርጉመው በዚሁ ጋዜጣ ላይም ለንባብ በቅተዋል፡፡  
የኦኼነሪ ዝነኛ ሥራዎች
Witches Loaves
A Retrieved Reformation
The pimienta Panckes
The Green Door
Let me Feel your pulse (የመጨረሻ ሥራው)
The Ransom of Red chief
Shoes
Ships (የshoes ቀጣይ ሥራው ነው)