Administrator

Administrator

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለአምስት ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መስጠቱን በዛሬው ዕለት አስታወቀ፡፡

 ብሔራዊ ባንክ፣ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ከባንክ ጋር ዝምድና ለሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሠረት፣ አምስት ድርጅቶች ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ የሥራ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ተመልክቷል፡፡  እነዚህ ድርጅቶችም፡- ዱግዳ ፊደሊቲ ኢንቨስትመንት ኃ.የተ.የግ.ማ፣ ኢትዮ ኢንዲፕንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ግሎባል ኢንዲፐንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ሮበስት ኢንዲፐንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ እና  ዮጋ ፎሬክስ ቢሮ  መሆናቸውን ባንኩ ገልጿል፡፡


የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ የሚፈጸም (spot transaction) ብቻ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም፣ ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፣ የደህንነት፣ ሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ያዘጋጀውን “ኑ፣ እንመካከር” የተሰኘ  አዲስ የሙዚቃ ክሊፕ ትናንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።

ይዘቱን በአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ባደረገው በዚህ የሙዚቃ ክሊፕ ላይ በርካታ ባለሞያዎች እንደተሳተፉ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

 የሙዚቃውን ቅንብር ካሙዙ ካሳ እንደሰራው የገለጸው አርቲስቱ፤ በሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሞያዎችና ዕገዛ ላደረጉ ወገኖች ምስጋናውን አቅርቧል።

“የመገናኛ ብዙኃን ዘፈኑን በተደጋጋሚ ሊያጫውቱት ይገባል” በማለት በአጽንዖት የተናገረው አርቲስት ዘለቀ፣ ወደፊት ሙዚቃው በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅ አስረድቷል።

በሌላ በኩል፣ የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማሕበር፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን እንዳስረከበም ተሰምቷል፡፡

-አምነስቲ ኢንተርናሽናል-

በአማራ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ በጅምላ መታገታቸውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

አምነስቲ ትላንት ማክሰኞ  መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤”ይህ የዘፈቀደ የጅምላ እገታ፣ የህግ የበላይነት መሸርሸርን የሚያባብስ ነው፡፡” ብሏል፡፡

ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ. ም. ጀምሮ በአማራ ክልል፣ ምሁራንና ሲቪል ሠራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ተይዘው መታገታቸውን ሪፖርቶች እንደደረሱት ተቋሙ  ገልጿል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃላፊ ቲጌሬ ቻጉታ፤ “የኢትዮጵያ ወታደሮችና ፖሊሶች በአማራ ክልል የከፈቱት የዘፈቀደ እገታ ዘመቻ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱን ያሳያል” ብለዋል፤ በመግለጫው፡፡

 “የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሰዎቹን ከመያዛቸው አስቀድሞ የእስር ማዘዣም ይሁን ፍተሻ ለማድረግ ፈቃድ አላሳዩም” ያሉት ቲጌሬ ቻጉታ፤ “የታገቱት ሰዎችም በህጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አልቀረቡም” ብለዋል።

የዓይን እማኞች ለአምነስቲ እንደጠቆሙት፤ በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ምሁራን በጅምላ ከታገቱት መካከል ይገኙበታል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የዘፈቀደ የጅምላ እገታ በአፋጣኝ ማቆም አለበት። በታገቱት ሰዎች ላይ ሕግን ተከትሎ ክስ መመሥረትና የሕግ ሥርዓትን መከተል ይገባዋል። አሊያም ሰዎቹን መልቀቅ አለበት። መንግሥት የዘፈቀደ እገታን ለጭቆና ማዋልን ማቆም አለበት” ሲሉም ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ማስፈራሪያ፣ ተከታታይ ጥቃትና ወከባ  ማድረጉን ያስታወሰው አምነስቲ፤በዚህም ምክንያት ብዙዎች እየተሰደዱ ነው፤ ብሏል።

ብላክ ዳይመንድ የህትመትና ማስታወቂያ ማሰልጠኛ አካዳሚ፣ ከወረቀት ህትመት ውጪ በሃገራችን የመጀመሪያውን የህትመትና ማስታወቂያ ሥልጠና በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የብላይክ ዳይመንድ አድቨርታይዚንግ መሥራቾችና አመራሮች በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ 22 ማዞሪያ ወርቁ ህንጻ ገባ ብሎ በሚገኘው የልህቀት ማዕከል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የሥልጠና አካዳሚው ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፤ ከነገ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሰልጣኞች ምዝገባ የሚጀመር ሲሆን፤ አካዳሚው የተለያዩ አጫጭር የቀንና የማታ የሥልጠና መርሃግብሮችን በመስጠት ሥልጠናውን ይጀምራል ተብሏል፡፡
ብላክ ዳይመንድ የህትመትና ማስታወቂያ ማሰልጠኛ አካዳሚ ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል፡- የባነር፣ ስቲከር ህትመት ማሽነሪ ባለሙያነት፣ ሲኤንሲ መቁረጫ ማሽነሪ ባለሙያነት፣ የህትመትና ግራፊክስ ዲዛይን ሥራዎች፣ የላይት ቦክስ ማስታወቂያ ባለሙያነት፣ የኒዮን ላይት ማስታወቂያ ባለሙያነትና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡
ተቋሙ በማስታወቂያ፣ በህትመት ማሽንና ግራፊክስ የሚታየውን የሰለጠነ ባለሙያ ክፍተት ለመሙላት ከነገ ጀምሮ ሰልጣኞችን መመዝገብ እንደሚጀምር ነው ያስታወቀው፡፡
ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ ሥልጠናዎቹ እስከ ሦስት ወር የሚደርሱ በሰርተፊኬት ደረጃ የሚሰጡ አጫጭር ኮርሶች ናቸው፡፡
በባለራዕይ ወጣቶች የተቋቋመው ብላክ ዳይመንድ አድቨርታይዚንግ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ የህትመትና ማስታወቂያ ሥራዎችን በጥራትና በብቃት በመሥራት በደንበኞቹ ዘንድ ስምና ዝናን ያተረፈ ሲሆን፤ ሥራውንም በተለያዩ ዘርፎች አስፋፍቶ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

በብልሽቱ ምክንያት ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተጠቁሟል

ከድሬዳዋ መገንጠያ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው 200 ኪሎሜትር መንገድ ብልሽት “ገጥሞታል” ተብሏል። በዚህም ሳቢያ ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ከድሬዳዋ መገንጠያ ቢኬን እስከ ጂቡቲ ወደብ መግቢያ ድረስ ለብልሽት ከተዳረገ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆነ አመልክተዋል። አክለውም፣ በዚሁ መስመር ላይ እየተሰሩ ያሉ መንገዶች ቢኖሩም ለአገልግሎት ክፍት አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“በዚህ የተነሳ እየሄድን ያለነው በተለዋጭ መንገድ ነው።” ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ ተሽከርካሪዎቹ የሚጓዙት በጋላፊ መስመር መሆኑን ገልጸዋል። “ይሁንና ይህ መንገድ የመኪና መለዋወጫን የሚያበላሽ፣ ጊዜን የሚወስድ እና ተሽከርካሪዎች እንዲወድቁ የሚዳርግ ነው” ብለዋል።

ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው የጉዞ ፈቃድ በጋላፊ መስመር በኩል በመሆኑ፣ አሽከርካሪዎቹ በደወሌ መስመር በኩል ያለፈቃድ በማሽከርከራቸው ምክንያት ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ መቀጮ እንደሚከፍሉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ነገር ግን በጋላፊ መስመር ከማሽከርከር ይልቅ መቀጮ እየከፈሉም ቢሆን ሾፌሮች በጋላፊ በኩል ማሽከርከሩን “ይመርጣሉ” በማለት የሚያስረዱት አቶ ብርሃኔ፣ “ምክንያቱም አንድ መኪና በዚያ መስመር ላይ ከወደቀ ወዲያው ከመንገድ እንዲነሳ አይደረግም። እንዲያውም ተጨማሪ መኪናዎች እስኪወድቁ ድረስ ነው የሚጠበቀው። የጂቡቲ የዕቃ ማንሻ ማሽን (ክሬን) እስኪመጣ ድረስ ይጠበቃል። ምክንያቱም የኛ ክሬን እንዲገባ አይፈቀድም። በተደጋጋሚ የራሳችንን ክሬን ለማስገባት ብዙ ጊዜ ጠይቀናል። ምላሽ ግን አልተሰጠንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ለክሬን እና ሌሎች ወጪዎች ከ400 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ድረስ ክፍያ እንደሚጠየቅ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ ክሬኖቹ አሮጌ ከመሆናቸው የተነሳ ለብልሽት ከተዳረጉ እንደገና ተጠግነው እስከሚመጡ ድረስ አንድ ወር እንደሚፈጅ ነው አቶ ብርሃኔ የሚያነሱት።

እንዲሁም በመንገዱ ብልሽት ምክንያት ሾፌሮች ለኩላሊት እና ሌሎች መሰል በሽታዎች እየተጋለጡ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ብርሃኔ፣ “ችግሩ ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የከባድ መኪና ሾፌሮች የስራ ዘርፋቸውን እየቀየሩ ወደ ራይድ ታክሲ አሽከርካሪነት ፊታቸውን እያዞሩ ነው” በማለት አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመንገዱ ብልሽት በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው የገለጹ ሲሆን፣ መንገዱ የአገሪቱ የገቢ እና ወጪ በር መሆኑን አውስተው፣ “ከተሽከርካሪ ጥገና እና ከሌሎች ወጪዎች ጋር በተያያዘ እንደአገር ዋጋ እያስከፈለን ነው። ‘ወይ መንግስት ያድሰው፣ ወይም እኛ ገንዘብ አዋጥተን እንዲታደስ እናድርገው’ እያልን ነው። እኛ ማሳሰብ የምንፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳዩን በጥልቀት እንዲያጤኑት ነው።” ብለዋል።

አቶ ብርሃኔ አያይዘውም፣ በፀጥታ ችግር ሳቢያ ሾፌሮች ለዕገታ፣ በክልሎች አለአግባብ ለሚጠየቅ ክፍያ፣ ለመንገድ መዘጋትና ሌሎችም ችግሮች ከፍተኛ አደጋ እንደሚዳረጉ አመልክተው፣ እርሳቸው የሚመሩት ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ድንጋጌዎች መሰረት ሰላማዊ ኢንዱስትሪ መስፈኑን ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን በማስታወስ፣ የአሰሪው መብት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

Saturday, 28 September 2024 20:24

አጥንቱ

ሼኽ ወይም ኡስታዝ የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ለብዙ ዓመታ ዓሊሞች አሉ በተባሉበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ ቀርተዋል፡፡ የሃይማኖት አዋቂ ለመሆን ብዙ ኪታቦችን አገላብጠዋል፡፡ አሁን በተራቸው የቃረሙትን ሁሉ ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ምላሳቸው የተባረከ ነው፡፡ የሃይማኖት ዕውቀትን ማሳወቅንና ተናግረው ማሳመንን ተከነውበታል፡፡
ተማሪዎቻቸው አፋቸውን ከፍተው ነው የሚያዳምጧቸው፡፡ “የኔ አንድም አስተዋፅኦ ወይም ታላቅ ጥረት ሳይታከልበት እንዲሁ እንደዘበት ይህን ተሰጥኦ ለሰጠኝ አላህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ሚስታቸውን እንኳን ለሌላ ነገር የሚመኝ ቀርቶ መልኳንና ቁመናዋን የሚያውቅ የለም፡፡ ይህን የሚያውቁት እናትና አባትዋ፣ እህትና ወንድሞችዋ እና እስከ አጎትና አክስት ድረስ ያሉ ዘመዶችዋ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች መልኳንም ሆነ ቁመናዋን ለማወቅና ለማድነቅ አልታደሉም፡፡ ምክንያቱም በሰፊ ጥቁር አባያና ከላይ በምትደርበው ትልቅና ሰፊ ጅልባብ ሰውነትዋ ተሸፍኗል፡፡ መላው ፊትዋና ከአንገት በላይ ያለው የሰውነት ክፍልዋ በኒቃብ ኃይል ከሰው ዓይን ተጋርዷል፡፡
ይወድዋታል፡፡ የእሳቸው ብቻ ስለሆነች ደግሞ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ይኮሩባታል፡፡
ሼኽ ወይም ኡስታዝ ኡስማን ቀይ ናቸው፡፡ ፂማቸው የተንዥረገገ ነው፡፡ ይህ የሆነው ፂም ማሳደግ ሱና ስለሆነ ነው፡፡ አናታቸው ላይ ጥምጣም እንደጠመጠሙና ከላዩ ላይ ነጭ ኩፊያ እንዳጠለቁ ነው የሚውሉት፡፡ ዘውትር ሽክ የሚሉ ሰው ናቸው፡፡
“ምን ነው?” ቢሏቸው “ንጽህና የኢማን ግማሽ ነው ብለዋል ነቢያችን (ሲ.ሠ.ወ)” ይላሉ፤ ድብዳብ የመሰለውን ወፍራም ከንፈራቸውን ከጥርስ ግርዶሽነት አላቀው ፍንጭት ጥርሳቸውን እያሳዩ፡፡
ፈገግ ሲሉ ነጫጭ ጥርሶቻቸው መሀል ተሸንቁሮ ጠባብ መንገድ የመሰለው ፍንጭታቸው ለእይታ ይጋለጣል፡፡
ከልብስ ጀለቢያና ቶብ ያዘወትራሉ፡፡ በቅጥነታቸው ምክንያት እዛ ሰፊ “ድንኳን” ውስጥ ኢምንት መስለው ይታያሉ፡፡ ጥምጣም፣ ነጭ ኮፍያና፣ ነጭ ጀለብያ ወይም ቶብ መለያ ምልክቶቻቸው ናቸው፡፡ ጀለብያ ወይም ቶብ ሆነ ወይም ሱሪያቸው ከቁርጭምጭሚታቸው በላይ የሚቀሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህም ሱና ነው፡፡
“ደረሳዎቼ ስሙ!” አሉ ከስራቸው የተኮለኮሉትን ወጣች አፈራርቀው እየተመለከቱ፡፡
“ምን ጊዜም ቢሆን ነብሳችሁን ማሸነፍ አለባችሁ፡፡ ለምን? ብትሉ ነብሲያ ቆሻሻ ነች፤ የማይሆን ቦታ ላይ ትጥላለች፡፡ የማይበጅ ጉድጓድ ውስጥ ሰውን ትከታለች፡፡”
በእስልምና ሃይማኖት “ነብሲያህን አሸንፍ” የሚል አስተምህሮ አለ፡፡ ኡስታዝ ኡስማን እያስተማሩ ያሉት ይህንን ነው፡፡
“የግል ፍላጎታችንን ለሌሎች ሰዎች ስኬትና ለወል ጥቅም ስንል ማሸነፍ አለብን፡፡ ለነብሲያ ውስወሳ ቦታ መስጠት የለብንም፣ ነብሲያ እኔ እኔ ማለትዋና ለኔ ለኔ እያለች መጮህዋ መቼም አይቀርም፡፡”
የተማሪዎቻቸውን የተለያዩ ፊቶች ቃኙ፡፡
ጥቁር ፊት አለ፡፡
ጠይም ፊት አለ፡፡
ቀይ ፊት አለ፡፡
ነገር ግን ከሁሉም ፊቶች ላይ የሚነበበው ጥልቅና ረቂቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖትን የማወቅና በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ለመኖር የመመኘት ስሜት፡፡ ሁሉም የጀነት ቁልፍ እጁ ቢገባ ይወዳል፡፡ ከጀሀነም እሳት የመጠበቅና የጀነት ሰው ሆኖ ለመገኘት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የሚያስወስን ጥልቅ ፍላጎት አለ፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ትዕዛዛትን ሁሉ አክብሮ በአስተምህሮው መሰረት ህይወቱን በመምራት ለጀነት የሚበቃው ወይም ለጀነት የሚያበቃውን ስራ የሚሰራው ጥቂት ነው፡፡ ምክንያቱም ህይወት አለ፡፡ ገና ከሞት በኋላ የሚመጣውን ህይወት ማሰብ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ዘላቂውንና አዋጩን ከመምረጥ ይልቅ በእጃችን ላይ ያለውን ህይወት ማቅናትና ኑሮን ማሸነፍ ቀድሞ ይገኛል፤ ለብዙዎች፡፡
አሁንም እርግጥ ነው የማይመኝ የለም፡፡ ግን ምኞትና ተግባር፣ ፍላጎትና ኑሮ ደቡብና ሰሜን የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
“እና” አሉ ሼህ ኡስማን
“እና ፍላጎታችንን መደፍለቅ፣ ስሜታችንን መግራትና መልካም ተግባር ላይ መገኘት ይገባናል፡፡” በጥርሳቸው የነከሱትን መፋቂያ እየነቀነቁ፡፡
“ለምሳሌ አንድ የወደድነውና የራሳችን ለማድረግ ያሰብነው ነገር ይኖራል፡፡ ወንድማችን ያንኑ ነገር መፈለጉን ካወቅን ነብሲያችንን አሸንፈን ያንን ነገር ለወንድማችን ቅድሚያ  በመስጠት መተው ይኖርብናል፡፡ እስልምና መስዋዕትነትን የሚያበረታታ እምነት ነው፡፡ ለኔ ከማለት ይልቅ ለወንድሜ ማለትን ማስቀደም አለብን፡፡”
ተማሪዎች ዝም እንዳሉ ተቀምጠው የተማሩትን ትምህርት እንዴት አድርገው በህይወታቸው እንደሚተገብሩ እያሰቡ ትምህርቱን ይከታተላሉ፡፡
“ልብ በሉ ነፍስያ የዋዛ አይደለችም፡፡ ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) “ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላትን ከማሸነፍ ይልቅ መጀመሪያው እንዲሁም ትልቁና ዋናው ጀሀድ ነፍስያን ማሸነፍ ነው!” ያሉትን አትዘንጉ፡፡
“የሆነ ነገር ብንፈልግና ወንድማችን ያን ነገር የሚፈልግ ከሆነ ነፍስያችን አትስጠው አትስጠው ማለትዋ አይቀርም፡፡  እኛ ግን ነፍስያችንን በማሸነፍ ያን ነገር ለወንድማችን መተው ወይም መስጠት አለብን፡፡”
ኡስታዝ ኡስማን ማስተማሩን ከጨረሱ በኋላ ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ሰሞኑን ወደ ተጠሩበት ቦታ ሄዱ፡፡ ቦታው የአንድ ሙስሊም ባለ ሀብት ቤት ነው፡፡ የተጠሩትም ለሰደቃ ነው፡፡
ቤቱ ደረሱ፡፡
ገቡ፡፡
ምግብ በአንድ ትሪ ላይ ሆኖ ለኡስታዙና ለተማሪዎቻቸው ቀረበ፡፡
ሼሁና ደረሳዎቻቸው የቀረበላቸውን ምግብ ጠቅልለው መጉረስ ጀመሩ፡፡
ቀይና አልጫ የሆነ ስጋ ወጥ እንጀራ ላይ ፈስሶ ቀረበላቸው፡፡
እንጀራው መሀል ላይ አንድ አጥንት ወድቃለች፡፡ ኡስታዝ ኡስማን ፈጠን ብለው አጥንቷን በማንሳት መጋጥ ጀመሩ፡፡
ከተማሪዎቹ አንዱ፡-
“ምን ነው ኡስታዝ?” አለ
“ምን ነው?” አሉ አጥንት እንዳገኘ ውሻ በመስገብገብ አጥንታቸውን እየጋጡ፡፡
“ቅድም ነብሲያችንን ማሸነፍ አለብን! ብለው እያስተማሩ አልነበር?”
“እኮ!”
“ምነው ታዲያ አጥንትዋን ቀድመውን አነሱ?” አለ ተማሪው በመደነቅ፡፡
“እኮ!” አሉ ኡስታዙ በድጋሚ፡፡
“ነብሲያዬ ስጥ ስጥ ስላለችኝ እሷን አሸንፌ እየበላሁኮ ነው፡፡” አሉ ኡስታዝ ኡስማን፤ እንደዋዛ ፈገግ ብለው፡፡
ተማሪዎቹ ሁሉ በሳቅ አውካኩ፡፡ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደተባለው መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡
ተማሪዎቹ በሳቃቸው መሀል እውነትና እውቀት፣ ማስተማርና መሆን ምን ያህል እንደሚጣረሱ እያሰቡና እየተገረሙ ወደ ትሪው አጎነበሱ፡፡
(ከመሐመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ) “ጥቁር ሽታ” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ የተወሰደ፤2011 ዓ.ም)

Saturday, 28 September 2024 20:24

የግጥም ጥግ

አንዳንድ ዘመን አለ
ሳንረግጥ እንዳለፍነው እየተንሳፈፍነ
ልክ እንደ አውሮፕላን ዱካ አልባ የሆነ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
ኖረን እንዳልኖርን፣
በዕድሜ መሰላል ላይ እንዳልተሻገርን፤
ያለ አንዳች ምልክት ጥሎን መሰስ ሲል
ዞር ብለን ስናየው ህልም አለም
‘ሚመስል፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
የአመቶቹ ብዛት የሆነ ለውጥ አልባ
የሆነ ጣ’ም አልባ
ያለ እልባት ‘ሚሮጥ ጥላ ቢስ ከላባ፤
የመኸር አበባው የወራቶቹ ሰልፍ
እየመጣ እየሄደ ያለ ፍሬ ‘ሚረግፍ፤
አንዳንድ ዘመን አለ፣
እንደ አንድ ምሽት ጀምበር
ክረምትና በጋው የምናየው አልፎ
በህይወታችን ላይ ቁጥር ብቻ ፅፎ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
ትግል ‘ሚነግስበት
እድል ‘ሚነጥፍበት፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
አሻራ የሌለው የሚሄድ ቸኩሎ
ደስታችንን አዝሎ
‘ርጅናን አድሎ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
እንዳለ ‘ማንቆጥረው
እንዳለን ‘ማይቆጥረን
እየመሸ እየነጋ ቀን የሚያስቆጥረን፡፡
(አብርሀም ገነት)

በሂንዱ የሚነገር አንድ ተረት እንዲህ ይላል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ ጫካ ውስጥ አንድ አንበሳና ሦስት ባለሟሎች ማለትም አነር፣ ዱኩላና ቁራ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
አንድ ሌሊት የሚበላ ምግብ ፍለጋ ሲዘዋወሩ ከመንገደኞቹ ተነጥሎ ብቻውን የቀረ አንድ ግመል አገኙ፡፡ አንበሳም ከዚህ ቀደም ግመል አይቶ ስለማያውቅ
“ይሄ ምን ዓይነት እንስሳ  ነው? በጣም እንግዳ አይነት ተፈጥሮ ያለው ነው!” ሲል ጠየቀ፡፡
አነሩ፣ “እንግደለውና አንብላው” አለ፡፡
“አዎ እራታችን ብናደርገው ይሻላል” አለ ድኩላው፡፡
“ኸረ ለእራትም ለቁርስም ይበቃናል፤ ብዙ ስጋ ተሸክሞ የሚዘዋወር እንስሳ’ኮ ነው፡፡”
“የለም አይሆንም!” አለ አንበሳ፤ “ብናጣራ ነው የሚሻለው፡፡ ስሙ ማን ይባላል? በዚህ በውድቅት  ሌሊት እዚህ ምን ያደርጋል? ሂዱና ጠይቁት፡፡”
ሦስቱ ባለሟሎች አንበሳው እንዳዘዘው ሄዱና ግመሉን ጠየቁት፡፡ ግመልም ስሙ ግመል  እንደሚባል፣ ከተጓዥ መንገደኞች ተለይቶ የቀረ መሆኑን ነገራቸው፡፡ ባለሟሎቹም ሄደው ለጌታቸው ለአንበሳ ይሄንኑ ገለፁለት፡፡
አንበሳም፤ “እንግዲያው በቃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ በዚህ ጫካ ውስጥ ብቻውን መኖር አይቻለውም፡፡ ምን አደጋ እንደሚያጋጥመው በምን ይታወቃል፡፡ ከእኛ ጋር ይቀላቀል፡፡ እኔ እጠብቀዋለሁ፡፡ ሂዱ አምጡት” አለ፡፡
ባለሟሎቹ ሄደው ለግመሉ የምሥራቹን ነገሩት፡፡ ያም ሆኖ ሦስቱ ባለሟሎች ግመሉ ከነሱ ጋር በመቀላቀሉ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ተጨማሪ አባል ማለት ተጨማሪ ሆድ፣ ተጨማሪ ጭንቀትና በግድ ተስማምቶ መኖር ያለበት ተጨማሪ ወዳጅ ማለት ነውና፡፡
ግመሉ መጥቶ ከተቀላቀለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በድንገት አንበሳ ከዝሆን ጋር ባደረገው የጦርነት ግጥሚያ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ ከቆሰለም በኋላ፤
“እስከሚሻለኝ ድረስ እኔ ዋሻዬ ውስጥ እቀመጣለሁ፡፡ እናንተ ሄዳችሁ የሚበላ ፈላልጉ፡፡ አሁን አደን ተስኖኛል” አለ፡፡
አነሩ ድኩላውና ቁራው እርስ በርስ ተያዩና፤ “እዚህ ትተንህ ልንሄድ አንችልም፡፡ እኛ ሄደን ማን ሊያስታምምህ ነው?” ሲሉ ሀሳቡን ተቃወሙ፡፡
አንበሳ ግን “የለም፡፡ ሄዳችሁ የሚበላ ብታመጡ ነው የሚሻለው” አለ፡፡
ባለሟሎቹ ከአንበሳው ቃል አይወጡምና፣ ጫካው ውስጥ ለአደን ተሰማሩ፡፡ ግን ምንም ምግብ አላገኙም፡፡ ጥንቸል ወይም እርግብ አሊያም ሽኮኮ እንኳን አጡ፡፡
“ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነው፡፡ ምንም አድነን የምንወስደው አልተገኘም፡፡ ይሄንኑ ሄደን    ለአያ አንበሳ ብንነግረው ይሻላል!” አለ ድኩላ፡፡
ይሄኔ ቁራው፤
“እዚህ የሚበላ የሚቀመስ በሌለበት ጫካ ውስጥ ከምንንከራተት ወደዋሻው ተመልሰን ያንን ግመል ብንበላውስ?” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡ ድኩላው ሲመልስ፣
“አያ አንበሳ እሺ አይልም፡፡ እንከባከብሃለሁ ያለውን ግመል እንብላው ብንል ፈፅሞ ፈቃደኛ አይሆንም፡፡”
“በዘዴ ካታለልነው እሺ ይለናል” አለ ቁራው፡፡ ከዚያም “ስሙኝ!” ብሎ ወደ ድኩላውና ወደ አነሩ ተጠጋና ዘዴውን በጆሮዋቸው ሹክ አላቸው፡፡
ሦስቱ አሽከሮች ወደ ዋሻው ተመለሱ፡፡ ከዚያም ድኩላው፤ “አያ አንበሶ ሆይ! በጣም እናዝናለን፡፡ የሚታደን ወፍ እንኳ ስላጣን ባዶ እጃችንን ተመለስን፡፡ እንግዲህ በረሀብ መሞታችን ነው፡፡”
“ኧረ በበለስ! በጣም አሳዛኝ ነገር’ኮ ነው!” አለ አንበሳው እያቃሰተ፡፡
ይሄኔ አነሩ፤ “እንዲህ አይናችን እያየ ስትሞትማ ዝም አንልም፡፡ ምንም ቢሆን፣ ታላቁ ጌታችን፣ ሀያሉ ጠባቂያችን፣ አዛዥ-መሪያችን ነህ’ኮ፡፡ እኔ ላድንህ እችላለሁ!” አለ፡፡
“እንዴት ልታድነኝ ትችላለህ?”
“በረሀብ ከምትሞት እኔን ብላኝ” አለ አነሩ፡፡
አንበሳም፤ “የለም አላደርገውም፡፡ ይሄን ያህል ዘመን ያገለገልከኝ ታማኝ ባለሟል ነህ’ኮ!” አለና በቁጣ ተቃወመ፡፡
ይሄኔ ድኩላው፤ “እንግዲያው እኔን ብላኝ ጌታዬ” አለ፡፡
“የለም አላደርገውም፡፡ አንተም ለብዙ ዓመታት ታማኝ ሆነህ የኖርክ ነህ!” አለ ኮስተር ብሎ፡፡
“በል እንግዲያው እኔን ብላኝ፣ የኔ ጌታ!” አለ  ቁራ፡፡
“አትጃጃል፡፡ አንተንማ ልብላህም ብል ጥቅም የለህም፡፡ በጣም ደቃቃ ነህ፡፡ ምን ትሆነኛለህ!” አለ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግመሉ አጠገባቸው ሆኖ ያዳምጥ ነበር፡፡ ለራሱ እንዲህ ሲል አሰበ፡፡
“መቼም አያ አንበሳ አንዳችንንም ለመብላት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ግልፅ አድርጎልናል፡፡ እኔንማ እንደሚጠብቀኝና  እንደሚንከባከበኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡ ስለዚህ እኔም እንደሌሎቹ “እኔን ብላኝ” ማለት ይገባኛል” አለና “አንበሳ ሆይ፤ እንግዲያው እኔን ብላኛ!” አለና ግመል ራሱን አቀረበ፡፡
“አንተን?” አለና ጠየቀ አንበሳ፡፡
“አዎ እኔን!” አለ ግመል፡፡
ይሄኔ አነሩ ቀልጠፍ ብሎ፤ “ይሄ በጣም ቅንነትና ደግነት የተሞላ ትክክለኛ ጥያቄ ነው!” አለ፡፡
“በጣም ትክክል!” አለ ድኩላ በማጠናከር፡፡
“ጥርጥር የለውም! እንደ ግመል ትክክል ሀሳብ ያቀረበ የለም!” አለ ቁራ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ አንበሳ ይሁን አይሁን ብሎ እንኳን ከመወሰኑ በፊት አነሩ ድኩላውና ቁራው ግመሉ ላይ ጉብ አሉበት፡፡ ዘዴያቸው ሰራ፡፡
*           *          *
በሀሳብ ደረጃ እንኳ ቢሆን፣ “እኔን ብላኝ ጌታዬ” ከሚልም ሆነ “ያኛውን ብላው” ከሚል ባለሟል ይሰውረን፡፡ ያገኙትን እንብላ እያሉ መስገብገብ ከንቱ አድርባይነት ነው፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት፣ ለጌታ አድሮ፣ ወዶ-ገባ ኮርማ መሆን፣ ቢሰቡ ለስለት፣ ቢከሱ ለጭነት ከመሆን አይታለፍም፡፡ ሁኔታዎችን መጠቀሚያ ለማድረግ “ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ማለትም፣ ያው ዞሮ ዞሮ ዞሮ የአድር-ባይነት ዝርያ ነው፡፡ ሁሌ አዋቂ፣ ሁሌ ዘዴኛ፣ እኔ ብቻ እያሉ፣ “እሰይ አበጀህ የእኛ ሎጋ” ተብያለሁ፣ ብሎ በግል ምኞት መሯሯጥ “የባዳ ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ” ይላል እንደሚባለው (“የባለቤቱ ልጅ” እንዲል  መፅሐፈ-አራዳ) መሆን ነው፡፡
በሰሞንኛ መፈክርና የግል-ምህዋር ዙሪያ ብቻ በመሽከርከር አርቆ አለመመልከት፣ ውሎ አድሮ አንድም፣ በአመለካከት ረገድ በውዥንብርና በዳፍንተኝነት (obscurantism) ሸረሪት ድር መተብተብን፣ ቀን ሲገፋም “እበላ ብዬ ተበላሁ….” ማለትን ግድ ይላል፡፡ ከቶውንም “እኔ ብቻ አዋቂ” ማለት በአካሄድ መወለካከፍን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ዝማሬ፣ ቅኝቱ “እኔ ብቻ ልግዛ” ወደሚል ዜማ የተሸጋገረ ዕለት ደግሞ፣ ናፖሊዮን ቦናፓርት “አገሬ እኔን የምትፈልገኝ እኔ ከምፈልጋት በላይ ነው” አለ፣ ወደተባለበት ደረጃ ያደርሳል፡፡ አይተኬ-ነኝ (indispensable) ወደ ማለትም ይነጎዳል፡፡ የዚህ የግል - ምኞት ውስጣዊ ግፊት የመጨረሻ መጠቅለያው ህዝብን መናቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ በውስጣዊ መንፈስ ግን ዝቅተኝነትን ያረግዟል፡፡
ሼክስፒር፣ በብሩተስ አንደበት በግል-ምኞት የናወዙትን የሮማን የስልጣን ጥመኞች ሲገልፅ፤
“ወትሮም ዝቅተኛ - ስሜት፣ የትኩስ ምኞት እርካብ ነው
አንዴ ሽቅብ ያንጋጠጠ፣ ከቶም መመለሻ የለው፡፡
እንዲያም ሲል ስልጣን የወጣ…
አንደዜ አናት ከረገጠ፣ ላገር ጀርባውን ይሰጣል
የበላበትንም ወጪት፣ ሰባሪ ሆኖ ይገኛል
ዳመናውን እየቃኘ፣ የታቹን ቁልቁል ይዘልፋል
መርጦ ለዚህ ያበቃውን፣ ድምሩን ህዝብ ይራገማል…” የሚለን
ይሄንኑ በቅኔ አግዝፎ ሲነግረን ነው፡፡
በሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ውስጥ በየወቅቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ የምሰጥ እኔና እኔ ብቻ ነኝ፡፡  የእኔና የእኔ መልስ ብቻ ነው ትክክለኛው፣ ብሎ በመገተር የታሪክ አይን እርሱ ላይ ብቻ የሚያተኩር አድርጎ የማየት ባህሪ፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአለቃ እስከ ምንዝር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ-ሊቃውንትን ሲተናነቅ የኖረ ክፉ ጋግርት ነበር፡፡ ነውም፡፡
የብሪታኒያ ጠ/ሚኒስትር ቤንጃሚን ዴዝሬሌ፣ ባንድ ወቅት የብሪታኒያ መሪ ስለነበሩት ስለ ሰር ሮበርት ፒል በፃፉት ደብዳቤ፡-
“ለሁሉም ታላላቅ ጥያቄዎች መልስ ፈልጎ በማግኘት በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙን ለማስፈር የመጣር ከንቱ ድካም የሚደክም ሰው ነው፡፡ ነገር ግን የፓርላማ ህገ-መንግሥት እንዲህ ላለው በግል-ምኞት ለሰከረ ግለሰብ ምቹ አይሆንም፡፡ ምነው ቢሉ፣ ሥራዎች መከናወን ያለባቸው በፓርቲዎች እንጂ ፓርቲን እንደግል መሳሪያቸው በሚጠቀሙ ግለ-ሰቦች አይደለም” ብለዋል፡፡
“እኔ የሌለሁበት ፓርቲ፣ እኔ የሌለሁበት አመራር፣ እኔ የሌለሁበት ውይይት፣ እነ እገሌ መሪ ሆነው፣ እኔ ተመሪ ሆኜ ምን ቦጣኝ….” በሚል አባዜ መጠመድ፣ ሌላው ልክፍት ነው፡፡ እሊህ ሊቃውንትና መሪዎች የባላንጣቸውን የኃይል ሚዛን የሚያይ አይን ከቶ የላቸውም፡፡
የበለጠ የከፋው መርገምት ደግሞ አዲስ ፓርቲ ተቋቋመ ሲሏቸው፣ ጠላት መጣ ያሏቸው ያህል የሚበረግጉቱና ከቶም እንቅልፍ የማይተኙቱ ናቸው፡፡ እነሱ ባለፉበት በስነ-ፓርቲ ግንባታ ሂደታቸው ላይ የደረሰውን መከራና ፍዳ ሁሉ ተከታዩ ትውልደ-ፓርቲ እንዲቀምስ የሚመኙና የእንቅፋቱን መንገድ ብቻ የሚቀይሱቱ ናቸው፡፡
ወጣም ወረደ በግል-ጥቅም የሚታወር፣ በግል-ዝና የሚጋበዝ፣ በስልጣን-ጥም የሚንሸዋረር፣ አድርባይነት የሚጠናወተው፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል የሚጥመው፣ ውሁድ ጥንካሬን ከመፍጠር ይልቅ መበታተን  የሚያረካው፣ ለእልህ እስጨራሹ የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ከቶም ካብ-አይገባ ድንጋይ ነው፤ ዲሞክራሲም ለእሱ የተከለከለች የበለስ ፍሬ ናት! ከዚህ ሁሉ በላይ ግን፣ በምንም ዓይነት መንገድ ህዝብን የሚንቅ ግለሰብም ሆነ ፓርቲ የህዝብን አደራ ተቀብሎ የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ይችላል ማለት ዘበት ነው፡፡ ይልቁንም የህዝብ ድምፅ እዳ አለበትና ዱቤ-ከልል ባርሜጣ ቢያደርግ እንኳ ከህዝብ እይታ አያመልጥምና ከሩቁ ይለያል፡፡ እንዲህ ያለው ሁሉ፤ “ዋና የማይችል ባህር አይግባ፤ ትግል የማይችል ልፊያ አይውደድ” የሚባለው ተረት ይጠቀስበታል፡፡ ልብና ልቦና ይሰጠው ዘንድ!

Saturday, 28 September 2024 20:13

የጃፓን ትዝታዎቼ

ካለፈው የቀጠለ

ካለፈው የቀጠለ
በ1984 ዓ.ም አስራ አንድ ወራት ያህል ለሚፈጅ ስልጠና  ጃፓን ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በጃፓን ሀገር ቆይታዬ ከማይረሱኝ ትዝታዎቼ መሀከል የተወሰኑትን ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ተርኬላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀሪውን አጫውታችኋለሁ፡፡
የቤተሰብ ጉብኝት(Family visit): በጃፓን ቆይታዬ ወቅት የማይረሳኝ ሌላው ነገር የቤተሰብ ጉብኝት ነው። የቤተሰብ ጉብኝት አብይ አላማው፣ ከተለያዩ ሀገራት ለትምህርትና ለስልጠና ጃፓን የሚገኙ የውጪ ሀገር ዜጎች፣ በሀገሪቱ ቆይታቸው ወቅት ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ከጃፓን የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ተገናኝተው እንዲጋበዙና የአብሮነት ጊዜ እንዲኖራቸው፥ የጃፓንን ህዝብ አኗኗር እንዲረዱና የቤተኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው። በአስራ አንድ ወራት የጃፓን ቆይታዬ ወቅት ሦስት ጊዜ የቤተሰብ ጉብኝት እድል ያጋጠመኝ ሲሆን፥ በአንዱ የቤተሰብ ጉብኝት ፕሮግራም ውስጥ የጃፓናዊት ሴት ጓደኛ (girlfriend) ለማግኘት በቅቻለሁ።
ጃፓናዊቷ ጓደኛዬ ያዮኢ ትባላለች። ከእሷ ጋር ከተዋወቅሁ በኋላ በእረፍት ጊዜያችን በመገናኘት ጥሩ የፍቅር ጊዜ አሳልፈናል። ሀገር ቤት ከተመለስኩም በኋላ በደብዳቤ መገናኘት ቀጠልን። በመጨረሻም በ1987 ዓ.ም. እዚህ አዲስ አበባ ድረስ ልትጠይቀኝ መጥታ የተወሰኑ ቀናቶች በአዲስ አበባ፤ በሀዋሳና በወንዶገነት ካሳለፍን በኋላ ኬንያ በመሄድ ማሳይ ማራ የተባለውንና በኬንያ የታወቀውን ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተናል። የወንዶ ገነትን አካባቢ ስታይ “Nippon mitai!”፥ ትርጉሙም “ጃፓንን ይመስላል” ማለቷ ነበር። እውነቷን ነው። ወንዶ ገነት አካባቢ ደኑ እንዴት እንደሚያምር ያየው ያውቀዋል። ሀገሩ ከዳር እስከዳር እንደ ወንዶ ገነት በደን፤ ያውም በተፈጥሮ ደን ቢሸፈን እንዴት እንደሚያምር አስቡት፡፡
ጃፓን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት በተለይ ከከተማ ውጪ በተፈጥሮ ደን የተሞላች ሀገር ናት። በሷ በኩል አቋሟ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኔ ጋር ለመኖር ነበር። እኔ ግን በወቅቱ የነበርኩበት የኢኮኖሚ ሁኔታ እሷንና እኔን ሊያኖር የሚችል አልነበረም። የኔ አቋም ደግሞ በጃፓን ሀገር ከሷ ጋር ለመኖር ነበር። ይሁን እንጂ ጃፓኖች ለጥቁር ሰው ያላቸው አመለካከት ዝቅ ያለ በመሆኑ ልጅ ወልደን ጃፓን ሀገር ብንኖር በማህበረሰቡ የመገለል ችግር ያጋጥመዋል ብላ በመፍራቷ ወደሀገሯ ከተመለሰች በኋላ ግንኙነታችን ሳይቀጥል ቀረ፡፡  የጃፓኗንና የኔን ታሪክ የሚያውቅ የቅርብ የወንድሜ ጓደኛ “እሩቅ ምስራቅ ሳለሁ ጃፓኗን ወድጄ” የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን እየዘፈነ ይቀልድብኝ ነበር።
በቤተሰብ ጉብኝት ወቅት የጃፓኖች የቤት ውስጥ አኗኗር ምን እንደሚመስል ልረዳ ችያለሁ። የሚቀመጡት ሶፋ ላይ ሳይሆን እንደ አረቢያን መጅሊስ አይነት መቀመጫ ላይ ነው። አረንጓዴ ሻይ (Japanese green tea) የመጀመሪያ ግብዣቸው ሲሆን፥ ሩዝ አትክልት፥ ቅጠላቅጠልና የባህር ውስጥ የአሳ ዝርያዎች ዋነኛ ምግባቸው መሆኑን አይቻለሁ። ቤታቸው ውስጥ ሲገባ በራፍ ላይ ጫማ ተወልቆ በተወሰነለት ቦታ ከተቀመጠ በኋላ በነጠላ ጫማ ነው ወደ ውስጥ የሚገባው። የቤታቸው ወለሉ ከንፅህናው የተነሳ ፊትን እንደ መስታወት የሚያሳይ የሚባልለት አይነት ነው። ጃፓን በእንጨት ምርት ታዋቂ ስለሆነች የቤታቸው ወለልና አብዛኛዎቹ የቤት ዕቃዎቻቸው በጣም ውብ በሆኑ የእንጨት ምርቶች የተሰሩ ናቸው። እንግዳ ሲቀበሉ በፊታቸው ላይ ትህትና የሚነበብባቸው ሲሆን፤ ልክ እንደኛ ባህል ጎንበስ ብለው ሰላምታ በመስጠት ያስተናግዱታል።                                         
አንድ ሰው የተሟላ ህይወት አለው የሚባለው የሚከተሉት አራት ነገሮች ሲሟሉለት ነው የሚል የድሮ የፈረንጆች አባባል አለ። (በእርግጥ ይህ የነሱን የኑሮ ስታንዳርድ መሰረት ተደርጎ የተነገረ ነው) “American home; British Rolce royce; French cuisine and Japanese wife”  (“የአሜሪካውያን መኖሪያ ቤት፥ የእንግሊዝ ሮልስ ሮይስ መኪና፥ የፈረንሳይ ምግብ እና ጃፓናዊት ሚስት” እንደማለት ነው፡፡) እንደምንሰማው የአሜሪካውያን ቤት ሰፊና ሁሉን ነገር የያዘ ነው፥ የእንግሊዝ ሮልስ ሮይስ መኪና ቅንጡ መሆኑ ይታወቃል፥ የፈረንሳዮች የምግብ አሰራርና የአበላል ስርዓት አርት እንደሆነ እንሰማለን፥ የጃፓን ሴቶች ለጓደኛቸው ወይም ለትዳር አጋራቸው የሚያሳዩት ፍቅር፥ አክብሮትና ታማኝነት አለም አቀፋዊ እውቅና የተቸረው ነው። ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት መሀከል ሦስቱን፥ ማለትም የቤቱን፥ የመኪናውንና የምግቡን የማየት ዕድል አላጋጠመኝም። አራተኛውን ግን፥ ማለትም የጃፓንን ሴት በሚስትነትም ባይሆን በጓደኝነት አይቻለሁ። በመሆኑም ስለነሱ ከላይ የተጠቀሰው ነገር ትክክል ስለመሆኑ እመሰክራለሁ።
ቋንቋ፡ በጃፓን ቆይታዬ የመጀመሪያ አንድ ወር ላይ የጃፓንኛ ቋንቋ ማታ ማታ ተምረናል። በዚህ የአንድ ወር የቋንቋ ስልጠና መሰረታዊ የሆኑ የዕለት ተዕለት መግባቢያ አነጋገሮችን አስተምረውን በቆይታዬ ወቅት ተጠቅሜባቸዋለሁ። እንደማንኛውም ሌላ ቋንቋ፣ ቋንቋው በየአካባቢው የራሱ የአነጋገር ዘይቤ ቢኖረውም፣ የጃፓን አጠቃላይ ህዝብ የሚናገረው አንድ የጃፓንኛ ቋንቋ ነው። ከጃፓናዊቷ የሴት ጓደኛዬ ጋር ስገናኝ የተማርኳትን ትንሽ የጃፓንኛ አባባሎችን ተጠቅሜ በጃፓንኛ ላናግራት እሞክር ነበር። ምንም እንኳን የቋንቋው ችሎታዬ በጣም ውሱን ቢሆንም፤ “ቶማስ ጃፓንኛ ስትናገር በጣም ጥርት ያለ አነጋገር ነው የምትናገረው” ትለኝ ነበር። የምችላትን የጃፓንኛ ቋንቋ እንዴት ጥርት አድርጌ ለመናገር ቻልኩ? ብዬ ሳሰላስል አንድ መልስ ላይ ደረስኩ። በጃፓንኛ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ድምዖች በሙሉ (በ”ረ” እና በ”ለ” ድምዖች መሀከል ያለ ድምፅ ካላት ፊደል በስተቀር) በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ አሉ። በመሆኑም የጃፓንኛ ቋንቋ ስናገር ጥርት አድርጌ የመናገር ምስጢሩ ይሄ ይመስለኛል።
በጃፓን ቆይታዬ ሌላው የታዘብኩት ነገር የእንግሊዝኛ ቋንቋን ይመለከታል። በኦሳካ አለም አቀፍ የስልጠና ማዕከል ውስጥ የነበርን ሰልጣኞች ከሰሜን አሜሪካ፥ ምዕራብ አውሮፓ፥ ከራሺያ፥ ከአውስትራሊያና ከኒውዚላንድ በስተቀር ከመላው አለም የተውጣጣን ሰልጣኞች ነበርን። የቋንቋው የአነጋገር ዘይቤና ችሎታ ይለያይ እንጂ ይሄ ሁሉ የአለም ህዝብ የሚግባባበት አንድ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነበር። ከፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገር የመጡ ሰልጣኞች እንግሊዝኛ ቢከብዳቸውም እንደምንም ሰባብረውም ቢሆን መናገር ግዴታቸው ነበር፤ ለመግባባት። አንዱ የኛ ጓደኛ ሴኔጋላዊ ነበር። ሴኔጋል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ(Francophone) ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ይሄ ጓደኛችን ጃፓን መጥቶ ይህንን ሁኔታ ካየ በኋላ፤ “እኔ ሀገሬ ሴኔጋል እያለሁ እንግሊዝኛ የመማር ዕድል ነበረኝ፥ ነገር ግን ፈረንሳይኛ ስለምናገር ምን ይሰራልኛል? ሁለቱ ቋንቋዎች አቻ(እኩያ) ስለሆኑ አያስፈልገኝም ብዬ ተውኩት። ነገር ግን በተናጋሪ ብዛት እንግሊዝኛ ቋንቋ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ምን ያህል እንደሚበልጥ ያወቅሁት እዚህ ጃፓን ከመጣሁ በኋላ ነው።  እንግሊዝኛ ባለመማሬ በጣም የቆጨኝ አሁን ነው” አለኝ።
የጃፓን ህዝብ እንግሊዝኛ እምብዛም አይችልም። ሁሉን ነገር በራሳቸው ቋንቋ ስለሚሰሩ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ የተለያዩ አለም አቀፍ ግንኙነቶች በሚያደርጉበት ጊዜ እንግሊዝኛ ስለሚያስፈልጋቸው የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ማስተማራቸውን አውቃለሁ። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎቻቸውም ውስጥ ትምህርት በእንግሊዝኛ እንደሚሰጥ መረጃ አለኝ። ከዩኒቨርሲቲ በታች በሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶቻቸውም እንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት እንደሚሰጥ እገምታለሁ።
አሁን ደግሞ ስለራሴ ትንሽ ላውራ። እኛ፥ በተለይ ትንሽ ፊደል የቆጠርንና የመጀመሪያ ዲግሪ፥ ማስተርስ አለን ብለን የምንኮፈስ ሀበሾች፣ የእንግሊዝኛ  ቋንቋ ችሎታችን የሚፈተነው ከሀገር ውጪ ወጥተን የቋንቋ ችሎታችንን ከሌላው ጋር ስንመዝነው ነው። በጃፓን ከኔ ጋር የተማሩት ጓደኞቼ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆነው ከሴኔጋሉ ልጅ በስተቀር ሁሉም ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ(Anglophone) ሀገሮች የመጡ ናቸው። እኔና የሱዳኑ ልጅ በሀገራችን እንግሊዝኛ በትምህርት ቤት የተማርንና ለስራ በተወሰነ ደረጃ ብንጠቀምም ዕለት ከዕለት የምንጠቀምባቸው የራሳችን ቋንቋዎች አሉን፥ አማርኛና አረብኛ። ሌሎቹ በሙሉ ግን የራሳቸው የሆነ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ቢኖራቸውም እንግሊዝኛን በስራ ቋንቋነት የሚጠቀሙ ናቸው። በመሆኑም የቋንቋው ችሎታቸው ከፍተኛ ነው። በዚህ ምክንያት እኔና የሱዳኑ ልጅ እንግሊዝኛ ስንናገር ተብታባ፥ ገመድ አፍ የምንባል አይነት ነን። በተለይ በጨዋታ ላይ በእንግሊዝኛ ለመቀለድ፥ ወይም “Informal” ቋንቋ ለመጠቀም ስሞክር ያየሁትን ፈተና ምንጊዜም አልረሳውም። ይህም ሆኖ የጋናው ጓደኛዬ፤ “በጣሊያን ተገዝታችሁ እንዴት ይህን የመሰለ እንግሊዝኛ መናገር ቻልክ?” ይለኝ ነበር። በእንግሊዝ ስላልተገዛን  አደነቀኝ እንጂ እኔ እንኳን የቋንቋው “fluent” ተናጋሪ የምባል አይደለሁም።
የእግር ጉዞ(Hiking): በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ካምፓስ እማር በነበረበት ዘመን አብሮኝ ይማር የነበረ ጴጥሮስ አብርሀ የተባለ ጓደኛዬ ጃፓን ለስልጠና ሄዶ እዚያው እንደቀረ ጃፓን ከመሄዴ በፊት አውቅ ነበረ።  በዚሁ መሰረት ጃፓን ልሄድ ስል አድራሻውን ከት/ቤት ጓደኞቻችን ወስጄ፣ ጃፓን ሄጄ ትንሽ ከቆየሁ በኋላ ደውዬ አገኘሁት። ከዚያ በሌላ ጊዜ ደውሎልኝ እሱ ወደሚኖርበት ናጎያ ከተማ ሄጄ ለመገናኘት በቃን።
ናጎያ ከተማ በተገናኘንበት ወቅት ጴጥሮስ የጃፓን ቆይታውን እንዲህ አወጋኝ። “ጃፓን ለአጭር ጊዜ ስልጠና ከመጣሁ በኋላ ስልጠናውን እየተከታተልኩ ሳለሁ፣ እንደ አጋጣሚ ለማስተርስ ዲግሪ ትምህርቴን ሊያስቀጥሉኝ የሚችሉ የፋብሪካ ባለቤት የሆኑ ጃፓናዊ ባለሀብት እንደ ልጅ ተቀበለውኝ (adopt አድርገውኝ) ጃፓን ቀረሁኝ”።  ጴጥሮስ ባጋጠመው ጥሩ ዕድል እንደ ቅናት አይነት ነገር፥ ግን መንፈሳዊ ቅናት፥ ሸንቆጥ አደረገኝ።  ጴጥሮስ አብርሀ የሚኖርባት ናጎያ ከተማ በቶኪዮና በኦሳካ ከተማ መሀከል የምትገኝ ሲሆን፥ ለኦሳካ ከተማ የምትቀርብና የቶዮታ ካምፓኒ ዋናው የማምረቻ ፋብሪካ (Manufacturing industry) የሚገኝባት ከተማ ናት። የጃፓን ከተሞች አንዱ ከሌላው በትልቅነት ይለያያሉ እንጂ ለነዋሪው በሚሰጡት አገልግሎት እምብዛም አይለያዩም። እንኳን ከተሞቹ ይቅርና ገጠር የሚባለው አካባቢ ቢያንስ ጥሩ መንገድ፥ መብራትና ውሀ የተሟላለት ነው። በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገሮች (Industrialized countries) ዋና መለያ ባህርያቸው ይሄ ይመስለኛል።        
ታዲያ አንድ ቀን ጴጥሮስ ደወለና፤ “በሚቀጥለው አርብ ማታ ናጎያ ትመጣና እኛ ዘንድ  አድረህ በማግስቱ ቅዳሜ የእግር ጉዞ (hiking) ፕሮግራም ስላለን አብረኸን ትሄዳለህ” አለኝ። “ኦሆ ተገኝቶ ነው!” አልኩኝ በሆዴ፥ ምክንያቱም የእግር ጉዞ በጣም ነው የምወደው፡፡  ግብዣውን ተቀብዬ ዐርብ ከሰአት በ11 ሰዓት ት/ቤቴ ከሚገኝበት ኪዮቶ ከተማ በባቡር  ወደ ናጎያ ሄድኩኝ።
ኪዮቶ ከተማ በኦሳካና በናጎያ ከተሞች መሀከል የምትገኝ ጥንታዊት የጃፓን ከተማ ነች። በጥንት ዘመን የጃፓን ዋና ከተማ ስለነበረች የድሮ ቤተመንግስትና የጃፓኖች ቤተመቅደስ(Shrine) በብዛት የሚገኙባት ከተማ ነች። ታሪካዊ በመሆኗ ጃፓን ውስጥ ከሚገኙ የቱሪስት መስህብ ከተሞች መሀከል በቀደምትነት የምትጠቀስ ከተማ ናት፡፡
ናጎያ ከተማ ከኦሳካ ከተማ መቶ ኪሎሜትር፥ ከኪዮቶ ከተማ ደግሞ ሰባ ኪሎሜትር ያህል ስለምትርቅ ከኪዮቶ ናጎያ ለመድረስ ሀያ ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀብን። ወደ ናጎያ የሄድኩበት ባቡር ሺንካንሰን በሚባለው ባቡር ሲሆን፥ የዚያን ዘመኑ ሺንካንሰን ባቡር በሰዓት 200 ኪሎሜትር የሚጓዝ ነበር። ከቶኪዮ ኦሳካ 500 ኪሎሜትር ስለሚርቅ  በሺንካንሰን(Bullet train) ባቡር የሁለት ሰአት ተኩል ጉዞ ማለት ነው። ይህ ማለት ንጋት በ12፡00 ከአዲስ አበባ ተነስተን ጧት በ2፡30 ድሬዳዋ መግባት እንችላለን እንደማለት ነው። በአሁን ጊዜ የጃፓኑ ሺንካንሰን ባቡር ፍጥነቱ በሰዓት ከሁለት መቶ ኪሎ ሜትር በጣም እንደሚበልጥ ሰምቻለሁ። እኔ የተጠቀምኩበት ሺንካንሰን ባቡር የኤሌክትሪክ ባቡር ሆኖ እግር ኖሮት በሀዲድ ላይ የሚሄድ ነው። በተለይ የአሁኖቹ ማግሌቭ(Maglev) ባቡሮች(ማግሌቭ የሚባሉት ባቡሮች በሀዲዱና በባቡሩ መሀከል በሚፈጠር ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ፎርስ አማካይነት ባቡሩ ሀዲዱን ሳይነካ እንዲንሳፈፍ፥ የግራና ቀኝ ባላንሱን እንዲጠብቅና ወደፊት እንዲስፈነጠር በሚያደርግ ሀይል የሚንቀሳቀሱ ናቸው) በሰአት 500 ኪሎሜትር ፍጥነት አካባቢ ላይ እንደደረሱ ሰምቻለሁ። ይባስ ብለው አሁን ቴክኖሎጂ በደረሰበት ዕድገት የአየር ግፊት(Air resistance) ለማስቀረት በሚል በቫኪዩም ቲዩብ(አየር አልባ ቱቦ) ውስጥ ተንሳፋፊውን ባቡር ለሙከራ በነዱበት ወቅት ፍጥነቱ ከአውሮፕላን ፍጥነት እንደሚበልጥ ደርሰውበታል። አጃኢብ አያሰኝም! ይሄን ያህል ከዋናው ጉዳዬ ወጥቼ ስለቴክኖሎጂ ያወራሁት የዘመኑ በተለይም የወደፊቱ የቴክኖለጂ ፈጠራ በአለም ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ለውጥ(revolution) ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ እወቁልኝ፡፡
አርብ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት አካባቢ ከጴጥሮስ ጋር በናጎያ የባቡር ጣቢያ ተገናኝተን ወደ ቤቱ ወሰደኝ፡፡ ከላይ እንደገለፅኩላችሁ አባቱ የፋብሪካ ባለቤት ናቸው። እናም የቤታቸው ደረጃ ያሉበትን የኢኮኖሚ ደረጃ(ያውም በጃፓን) የሚመጥን መሆኑን መገመት አያዳግትም። ዓርብ ማታ ጴጥሮስ(ፒተር)፥ የፒተር አባትና እናት ጥሩ መስተንግዶ አደረጉልኝ። በነጋታው ቁርስ በልተን ከጧቱ 1፡00 አካባቢ ከእነ ፒተር ቤት በመኪና ወጣን። እዚያው ከተማ ውስጥ የሚኖር የፒተር አበሻ ጓደኛ ቤት ሄደን እሱን ከያዝነው በኋላ ጉዞ ቀጠልን። ይህን ጊዜ የእግር ጉዞአችን በሚያማምሩ የከተማው መንገዶችና ፓርኮች ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ። በመቀጠል መኪናችን ከከተማው ወጥታ ትንሽ ከተጓዘች በኋላ ከዋናው መንገድ ወጥታ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ለጥቂት ጊዜ ተጓዘች። በመጨረሻም አንድ ወንዝ ዳር ባለ መስክ ላይ ስትደርስ ቆመች፥ እኛም ወረድን።
የጉዞአችን መሪ በዚያን ጊዜ ዕድሜያቸው በግምት ስልሳ አምስት ዓመት የሚሆናቸው፣ ጃፓናዊው የፒተር አባት ናቸው። በጉዞው ላይ የተሳተፍነው የፒተር አባት፤ ፒተር፤ የፒተር ጓደኛና እኔ ነበርን። ጃፓናዊው የፒተር አባት ቀጠን ያሉ፤ ቁመታቸው ልከኛ፥ ፀጉራቸው ገብስማና ፊታቸው አስተዋይነት የሚነበብበት ሸንቃጣ ሰው ነበሩ። እሳቸውም የቀኑን የጉዞአችንን ዓላማ እንደሚከተለው ገለፁልን። “የዛሬው የእግር ጉዞአችን ዓላማ የዚህን ወንዝ መነሻ ማግኘት ነው” አሉን። ያለንበት አካባቢ ወንዝ ያለበትና በደን የተሸፈነ ነው። እንዴት አድርገን ነው በዚህ ደንና ወንዝ ውስጥ የምንጓዘው? አልኩ በሆዴ። በተጨማሪም እኔ የእግር ጉዞአችን በሚያማምሩ የከተማው መንገዶችና ፓርኮች ውስጥ ሊሆን እንደሚችል የገመትኩት ቀርቶ ወንዝ ተከትለን የእግር ጉዞ ልናደርግ መሆኑ አስገረመኝ። ጃፓኖች ለተፈጥሮ ያላቸውን ፍቅርና ቅርበት የሰውዬው ምርጫ አረጋገጠልኝ። የሁላችንም አለባበስ የስፖርት ቱታና ስኒከር ስለነበረ ለእግር ጉዞ ተዘጋጅተን መውጣታችን ያስታውቃል። ከዚያ ወንዙን ተከትለን ወደ ላይ መጓዝ ጀመርን፡፡ የ “adventure” ጉዞው  ተጀመረ። አካሄዳችን ወንዝ ውስጥ ድንጋዮች ካሉ እነሱን መሸጋገሪያ በማድረግ፥ ድንጋዮች ከሌሉ ደግሞ በወንዙ በቀኝ ወይም በግራ በኩል በሚገኝ ደን ውስጥ ነበር። ፏፏቴ ሲያጋጥመን ቀጥ ያለ ዳገት ቧጥጦ መውጣት ሁሉ ነበረበት። እርምጃችን ፈጠን ያለ ነበር። እንደ ጦጣ አንዴ ወንዝ ውስጥ ከድንጋይ ወደ ድንጋይ እየተሸጋገርን፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በደን ውስጥ ነበር። እኔ፤ ፒተርና የፒተር ጓደኛ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ስለነበርን ጉዞው በጣም እንደማይከብደን መገመት ይቻላል፥ የስልሳ አምስት አመቱ ጃፓናዊ ሽማግሌ ግን ከኛ በማይተናነስ ቅልጥፍናና ፍጥነት ሲጓዙ ማየቴ በጣም ነበር ያስደነቀኝ። የደን ውስጥ ጉዞአችን ቀላል እንዳይመስላችሁ። ደኑ የተፈጥሮ ደን ስለሆነ በውስጡ የተካተቱት የዛፍ ዝርያዎች ብቻ ሳይሆኑ የሌለ የዕፅዋት አይነት አልነበረም። ሐረግ፥ ቁጥቋጦ፥ እሾክ ወዘተ ነበሩ። መንገዳችን ደግሞ ዳገታማ መሆኑን አትርሱ። ከእሾክና ከቁጥቋጦው ጋር ዳገታማው መንገድ ተጨምሮበት ጉዞአችን ከባድና ጉልበት ጨራሽ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደኑ በጣም ጥቅጥቅ ብሎ ማለፍ ያስቸግረናል፥ ወደ ወንዝ ውስጥ እንዳንገባ ደግሞ ድንጋይ የለውም። ይህ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ደኑን እንደምንም ፈልፍለን በደረታችን እንደ እባብ የምንሳብበት ሁኔታ ከአንድ ጊዜ በላይ አጋጥሞናል። በዚህ አይነት ሁኔታ እየተጓዝን ሳለ፣አንድ ቦታ ስንደርስ ደኑ አላሳልፍ ስላለን በደረታችን መሳብ ጀመርን። በደረታችን የምንሳብበት ቦታ ወደ ወንዙ ተዳፋትነት የነበረው ነበር። እንደ አጋጣሚ የወንዙ ጫፍ እኔ ካለሁበት ቦታ ቅርብ ነበር። ሳላስበው የያዝኩት ቁጥቋጦ አምልጦኝ ወደ ወንዙ ተንሸራተትኩኝ። ከዚያ እንደምንም የሆነ ነገር ይዤ መትረፍ ቻልኩ እንጂ ከላይ ተወርውሬ ውሀ ውስጥ ወይም አለት ላይ እፈጠፈጥ ነበር። ውሀ ላይ ካረፍኩ ዋና ስለምችል ችግር አልነበረውም፥ አለት ላይ ብፈጠፈጥ ኖሮ ግን ሊፈጠር የሚችለውን ነገር መገመት አልችልም።
ወንዙ ወደ ላይ በሄድን ቁጥር መጠኑ እየቀነሰ ሄደ። መነሻውን ለማግኘት ግን ፈተና ሆነብን። በዚህ አይነት ፈታኝ ጉዞ ወደ ሁለት ሰአት ያህል ከተጓዘን በኋላ ስለደከመን እረፍት አደረግን። በጉዞ ላይ በየመሀሉ የወንዙን ሁኔታ እንከታተል ነበርና በግራና በቀኝ በኩል ወደ ወንዙ የሚገቡ ብዛት ያላቸው ምንጮች አጋጥመውናል። ለዚህም ነው ወደ ላይ በሄድን ቁጥር የወንዙ መጠን እየቀነሰ የሄደው። በመጨረሻም ከሦስት ሰአት ጉዞ በኋላ የወንዙን መነሻ ሳናገኝ፥ ነገር ግን የወንዙ መጠን በጣም መቀነሱን አይተንና ለሁለተኛ ጊዜ እረፍት አድርገን ወደነበርንበት የመልስ ጉዞ ጀመርን። የወንዙን መነሻ ባናገኝም፥ የወንዙ መነሻ የምትሆነው የመጀመሪያዋ አንድ ምንጭ መሆንዋን ለመገመት አላዳገተንም፡፡
በመጨረሻም የመልስ ጉዞው ሁለት ሰአት ፈጅቶብን፥ በአጠቃላይ አምስት ሰአት ከባድ የእግር ጉዞ አድርገን መኪናችን ወደቆመችበት ቦታ ተመለስን። መኪናችን ለዚያን ያህል ጊዜ ስትቆም ያለጠባቂ መሆኑን ልብ በሉ። ከላይ እንደገለፅኩት ጉዞአችን በጣም አስቸጋሪና በ”adventure” የተሞላ ነበር። ከዚያ በፊት ሀገር ቤት በነበርኩበት ጊዜ የተለያዩ የእግር ጉዞዎችን አድርጌያለሁ። ከጃፓን ከተመለስኩ በኋላም በቡድን ጭላሎ ተራራን ወጥተን ተመልሰናል። የጭላሎው ጉዞ እንደ ጃፓኑ አምስት ሰአት ያህል የፈጀብን ሲሆን፥ ጉዞው የራሱ ፈታኝነት ነበረው። ይሁን እንጂ በሀገር ቤት ያደረግሁት የትኛውም ጉዞ ከጃፓኑ ጋር አይወዳደርም፥ ወደፊትም ከጃፓኑ ጉዞ ጋር የሚወዳደር የእግር ጉዞ አደርጋለሁ የሚል እምነቱም አቅሙም የለኝም። በዚህ ምክንያት የጃፓኑ የእግር ጉዞዬ በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚያጋጥም(ones in a life time) ክስተት ሆኖ በማለፉ የማይረሳኝ ትዝታዬ ነው።
 ጓደኝነት፡ በአንድ ፀሐያማ ቀን እኔና የጋናው ጓደኛዬ ወደ ከተማ ወጥተን ዘና እንበል፥ በዚያው “windowshop” እናደርጋለን ተባብለን ወደ ኦሳካ መሀል ከተማ ሄድን። የኦሳካ መሀል ከተማ እኛ ከምንኖርበት አካባቢ በግምት አስር ኪሎሜትር ይርቃል። ታዲያ መሀል ከተማ ደርሰን የተለያዩ ሱቆችን እየጎበኘን ሳለ፣ ሁለት ወጣት የጃፓን ሴት ልጆች ትኩር ብለው ሲያዩን እኛም አየናቸው። ከዚያ በቀጥታ ወደኛ መጥተው እንተዋወቅ ብለው ተዋወቅናቸው። ድፍረታቸው ገረመን፥ ግልፅነታቸውን ደግሞ አደነቅነው። በመቀጠል ለምን ሻይ አንገባበዝም? አሉን። ያልጠበቅነው ጥያቄ ቢሆንም፣ ግብዣውን በደስታ ተቀበልነው። ዕድሜያችን በሰላሳዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ስለሆነ ጉርምስናው ነበር። ሴቶቹም በሀያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ስለነበሩ ልባችን ሸፈተ። ከዚያ ወደ አንድ ካፌ ገብተን የሚጠጣ ነገር ካዘዝን በኋላ ጨዋታ ጀመርን። የኛ እንግሊዝኛ ከነሱ የሚሻል ቢሆንም፥ እራሳቸውን በእንግሊዝኛ ለመግለፅ የሚቸግራቸው ልጆች አልነበሩም። ጨዋታ እንደጀመርን ከሴቶቹ አንዷ ግንኙነታችን ምን አይነት እንደሚሆን(code of conduct የሚመስል ነገር) በሚከተለው መንገድ ገለፀችልን።
 “እኛ እናንተን ስናይ ደስ ብሎን ተዋወቅናችሁ፥ ምክንያቱም የውጪ ሀገር ዜጎች ስለሆናችሁ ነው፥ ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር አልፎ አልፎ ጊዜ ማሳለፍ እንወዳለን፥ ነገር ግን አንድ በደምብ እንድታውቁት የምንፈልገው ነገር ወሲብ አንፈልግም፤ የወሲብ ነገር እንዳታነሱብን፥” አሉን። ግልፅነታቸው ያልጠበቅነው ስለነበረ ገረመን፥ ወደድናቸውም። ከዚያ ጨዋታው ቀጠለ። ብስኩት ነክ ነገርም ታዘዘ። ወደ አንድ ሰአት ያህል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስንጨዋወት ቆየን። በመጨረሻም ልንነሳ ስንል “ክፍያ በግል ነው”፥ “dutch system” አለችን አንዷ። እኛ በሀገራችን የለመድነው ግብዣ “dutch system” ከሆነ ቀደም ብለህ ትነጋገራለህ፤ ሳትነጋገር ከተገባበዝክ መጨረሻ ላይ ለመክፈል ትግደረደራለህ። እነሱ ግን መጨረሻ ላይ ነው የነገሩን። ደች ሲስተም የተለመደ “by default” የመገባበዝ ባህላቸው ይመስላል። በቂ ገንዘብ ባይኖረን ኖሮስ? አስቸጋሪ ነው። ለነገሩ በቂ ገንዘብ ባይኖረን ኖሮ የለንም ብለን መናገር ነዋ! የምን መጨነቅ ነው! የባህል ልዩነታችን ግን አስገረመን። በመጨረሻም ተመሰጋግነን ተለያየን።
ከላይ ካጋጠመን ሁለት ነገር ተማርን። የመጀመሪያው፤ የጃፓን ህዝብ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሲወዳደር ዝምተኛ፥ አይናፋርና ራሱን በደንብ መግለፅ የማይችል ህዝብ ነው የሚለው ነገር የተጋነነ መሆኑን ነው። ጃፓኖች ቀረብ ብለህ ካየሀቸው በጣም ግልፅና የሚፈልጉትን ነገር በቀጥታ የሚናገሩ መሆናቸውን ተረድተናል። ሁለተኛው ደግሞ በጃፓን ሁለት ጓደኛሞች ሲገባበዙ የኛ አይነት ባህል ሳይሆን፣ ወደ ምዕራባውያን የሚጠጋ ባህል ነው ያላቸው። ሁሉም የራሱን የሚከፍልበት ደች ሲስተምን ነው የሚመርጡት።
ቼሪ ብሉሰም(Cherry blossom): ቼሪ የሚባለው የአበባ አይነት እኔ እስከማውቀው ድረስ በጃፓን ሀገር የሚበቅል የአበባ አይነት ነው። አበባው በፀደይ(spring) ወቅት የሚያብብ አበባ ነው። በዚህ ወቅት ይህ አበባ ጃፓንን ስለሚያስውብ አበባውን መሰረት ያደረገ የባህላዊ በአል አከባበር አላቸው።
ታዲያ በአንድ ወቅት ለቼሪ አበባ አመታዊ በአል፣ እዚያው ኦሳካ ከተማ ውስጥ በአሉ የሚከበርበት ቦታ ወሰዱን። የቼሪ አበባ በዋነኛነት መልኩ ነጭ ሆኖ በግምት ሀያ በመቶ ያህል የሮዝ ቀለም የተቀላቀለበት የራሱ ውበት ያለው አበባ ነው። የበአሉ ስፍራ ስንደርስ በግምት አንድ ኳስ ሜዳ በሚያክል ቦታ ላይ ተጠጋግተው የተተከሉ የቼሪ አበባዎች የሚታዩበት ቦታ መሆኑን ተረዳን። የአበባዎቹ አተካከል ውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ እንዲኖረው ተደርጎ ስለሆነ፣ በአበባዎቹ መሀከል እየተዘዋወርን ጎብኘን። የቼሪ አበባዎቹ እንደዚያ በአንድ ላይ ተተክለው ሲታዩ እጅግ በጣም ያምራሉ። ቦታውን የምድር ገነት አስመስለውታል፡፡ እኛም የቼሪ አበባ አመታዊ አከባበርን ከጃፓኖቹ ጋር ስናከብር ውለን ወደ ቤታችን ተመለስን።
እ.ኤ.አ በ1912 ዓ.ም የቶኪዮ ከተማ ለአሜሪካዋ ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የቼሪ ዛፎች በስጦታ ማበርከቷ በታሪክ ይታወቃል። አሜሪካኖቹም ይህንን አበባ እንደ ጃፓኖቹ በአንድ ቦታ ሰፋ አድርገው ተክለው፣ በየአመቱ ፀደይ በመጣ ቁጥር የሚያከብሩት በአል እንዳላቸው አውቃለሁ። የበአሉ መሰረት ግን ጃፓን መሆኗን ልብ ይሏል።
ማጠቃለያ፡
እስካሁን  ከራሴ ተሞክሮ ተነስቼ ስለጃፓን የማውቃትንና የታዘብኩትን አጫወትኳችሁ። “ዞሮ ዞሮ ከቤት . . .” እንደሚባለው እኛስ? እንዴት ነው የምንኖረው? ለስራ፥ ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ ምን ያህል ነው? የቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድነው? ለኢኮኖሚ ዕድገት ወይስ ወንዝ ለማያሻግር የፖለቲካ ሽኩቻ? ያውም ብሔር-ተኮር የፖለቲካ ሽኩቻ? የሚሉትንና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እራሳችንን ብንጠይቅ የአሁኑ፥ የቅርቡም ሆነ የሩቁ ታሪካችን የሚያስገነዝበን አብዛኛውን ጊዜ ለሀገር በማይበጅ፥ እንደውም ሀገርን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሳትፈን ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ማሳለፋችንን ነው። ከዚህ አንጻር በሚከተሉት አንኳር ሀሳቦች ላይ ብንሰራ እነ ጃፓን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያግደን ነገር አይታየኝም።
ሀ. የፖለቲካ ባህላችንን ማዘመን ወይም መለወጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ልዩነቶቻችንን በክብ ጠረጴዛ መፍታት ግድ ይለናል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም እኩል ሀላፊነት አለብን። ታሪካችንን ዞር ብዬ ሳየው ይህን አይነት የፖለቲካ ብስለት በቀላሉ ማምጣት እንደሚከብድ ይገባኛል፥ ነገር ግን ወደድንም ጠላንም ሀገራችንን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር የግድ ማድረግ ያለብን ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
ለ. ለስራና ለጊዜ የምንሰጠው ዋጋ በጣም መሻሻል አለበት። ለዚህም ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተከትለን ስራ መፍጠር፥ የአሰራር ሥርዓታችንን ማዘመንና ሰዉ ለስራና ለጊዜ የሚሰጠውን ዋጋ በተለያዩ ስልጠናዎች ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡
ሐ. ባለብዙ ብሔር ሀገር መሆናችን ጌጣችን እንጂ መሻኮቻ ምክንያት ሊሆን በፍፁም አይገባም። ሩዋንዳ ከስህተቷ ተምራ እንዳደረገችው፥ እኛ ደግሞ ካሳለፍነው መከራ ተምረን፣ ብሔር-ተኮር ፖለቲካ ማራመድ ወንጀል መሆኑ በህግ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን አለበት እላለሁ። ምክንያቱም አነሰም በዛ በብሔር ፖለቲካ ጦስ መከራውን ያላየ ብሔረሰብ በኛ ሀገር ማግኘት ይከብዳል። የብሔር ፖለቲካ ለውጪ ጠላት መሳሪያ ከመሆን ባለፈ ስልጣንና ህገወጥ ብልፅግና የሚገኝበት አቋራጭ መንገድ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ምስጢር ከሆነ ሰንብቷል።
ቢያንስ ቢያንስ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት አንኳር ነጥቦችን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን፣ ሀገራችንን ማሳደግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ተግባራዊ ካላደረግናቸው ግን የመከራ ጊዜያችንን እናራዝማለን፥ ከታሪካችን ሳንማር ቀርተን ህዝባችን ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ በማድረግ እርባና ያለው ነገር ሳንሰራ እናልፋለን።



በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም.፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሃሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ግብጽ፣ ካይሮ ተጓዙ። በዚህ ጉብኝታቸው አልመው የሄዱትን አሳክተዋል፡፡ ከግብጽ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ ለሶማሊያ የሚደረገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ቁልፍ ነበር፡፡  
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው ዙር የጦር መሳሪያ ድጋፍ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ሞቃዲሾ ደረሰ። ይህም ድጋፍ ግብጽ በአስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሊያ ያደረገችው ወታደራዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ነው።
ሶማሊያ ከተለያዩ አገራት ወታደራዊ ድጋፍ ቢደረግላትም፣ የግብጽ ድጋፍ ግን ከሌሎች የተለየ ተደርጎ እንደሚቆጠር የአፍሪካ ቀንድን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ምክንያቱም ወታደራዊ ድጋፉ የመጣው በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል ውጥረቱ በተባባሰበት ወቅት ነው፡፡ የውጥረቱ መነሻ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ነው። ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት በኪራይ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን፤ በአንጻሩ ለሶማሊላንድ ደግሞ የአገርነት ዕውቅና ያጎናጽፋታል።
እንግዲህ ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ ዕውቅና መሰጠቱ ነው፣ ሶማሊያን ኢትዮጵያ ላይ ጥርሷን እንድትነክስ ያደረጋት፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደብ ባይኖራትም፣ ወታደራዊ አቅሟንና የንግድ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር በመሻት የባሕር በር ትፈልጋለች። ከ30 ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተነጥላ በአገርነት፣ ነገር ግን ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዕውቅና ሳታገኝ ከኖረችው ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ  የወደብ  ስምምነት መፈጸሟ ውጥረት እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ከዚያም በላይ ግን ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ  የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷ ሶማሊያን ያበገናት ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት  የአጸፋ ምላሽ በሚመስል መልኩ፣ ሶማሊያ ከግብጽ ጋር የነበራትን አጠቃላይ ግንኙነት ማጠንከሩን ያዘች።
ባለፈው እሁድ መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ሞቃዲሾ የደረሱት የግብጽ ከባድ ጦር መሳሪያዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ  ለሶማሊያ የተደረገ ወታደራዊ ድጋፍ ሲሆን፣ ያሁኑ በመጠንም በዓይነትም የላቀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የግብጽን ወታደራዊ ድጋፍ ተከትሎ፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ኒውዮርክ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ  መግለጫ እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ግብጽ ለሶማሊያ ያደረገችው የከባድ ጦር መሳሪያዎች ድጋፍ፣ ዞሮ ዞሮ ወደ አሸባሪዎች እጅ ሰተት ብሎ የሚሄድና አሸባሪዎችን የሚያጠናክር ነው ሲሉ  አምባሳደሩ በአጽንዖት ተናግረዋል። በማያያዝም፣ ወትሮም በቋፍ ላይ የሚገኘውን የቀጣናውን የሰላም ሁኔታ ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ሊመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸል፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው፤ የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ስምምነትና ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ ዓይን በጥርጣሬ የሚታይ ነው።
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከሶማሊያ ራሷን ለይታ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ግብፅ ለሶማሊያ ያስታጠቀቻቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተመለከተ ቁጣዋንና ተቃውሞዋን በመግለጽ ማንም አልቀደማትም፡፡ ሶማሊላንድ የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ በቀጣናው አሳሳቢ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስታውቃለች፡፡ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ከግብፅ ወደ ሞቃዲሾ የገቡት ከባድ የጦር መሳሪያዎች ውስብስብ የደኅንነት ፈተና ያለበትን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል ሲል ጥልቅ ስጋት መፈጠሩን ጠቁሟል።
አክሎም፤ የሞቃዲሾ አስተዳደር እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተገቢው ሁኔታ የመያዝ አቅም ስለሌለው አልሻባብን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አንጃዎች እጅ በመግባት አሳሳቢ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የቀድሞ የግብጽ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራካ አሕመድ ሐሰን ለኢምሬትሱ  ናሽናል ጋዜጣ ሲናገሩ፤ “ብዙዎች ይህ የከባድ መሳርያ ድጋፍ የተላከው ኢትዮጵያን ታሳቢ አድርጎ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ይሁንና ይህ ግምት ስህተት ነው›› ብለዋል፡፡ ንግግራቸውን ሲቀጥሉም፤ “የሶማሊያ መንግሥት ካይሮ ድረስ መጥቶ ወታደራዊ እርዳታ እፈልጋለሁ ያለው ራሱ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቅር ሊላቸው ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡
እኚህ የቀድሞ የግብጽ ሚኒስትር ለጋዜጣው በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቅርቡ የፈጠሩትን ውዝግብ ተከትሎ በስፍራው የነበሩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ለቅቀው ሊወጡ ስለሆነ፣ የፀጥታ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ሶማሊያ ይህንን ክፍተት የሚሞላ አገር ስትፈልግ ግብጽን አገኘች” ባይ ናቸው፡፡  ከጦር መሳርያ ዕርዳታ በተጨማሪ ግብጽ የሶማሊያን ወታደሮች እንደምታሰለጥንም  ገልፀዋል፡፡ የግብጽ የጦር መሳርያና ወታደሮች ወደ ሶማሊያ በመግባታቸው ኢትዮጵያ እያሰማች ያለውን ወቀሳም፤ “ከጥፋተኝነት ስሜት የሚመነጭ” ሲሉ ለማሸሞር ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምን እንዳጠፋች ግን አልጠቀሱም፡፡ “አንድ ሰው መጥፎ ነገር ከሰራ ሁሌም ጥፋተኝነት ይሰማዋል፡፡ ወይንም ላደረገው ነገር መልስ ሊሰጡኝ ነው ብሎ ይፈራል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡  
አክለውም፤ “በቅርቡ ኢትዮጵያ ራሷ ከሞሮኮ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ ግብጽ ግን ይህንን አልተቃወመችም፡፡ ወይም በስምምነቱ ላይ ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት አላሳየችም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ግብጽ ከሶማሊያ በተጨማሪ ከኤርትራ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑን አያሳይም ወይ?” በሚል ከጋዜጣው ተጠይቀው ነበር፡፡ እኚህ የቀድሞ ባለስልጣን ሲመልሱም፤ “ኤርትራን ከግብጽ ጋር በደህንነትና በወታደራዊ ጉዳዮች ያገናኛት የራሷ የሆነ ምክንያት አላት፡፡
 ወደ ግብጽም ከመጣን ከእነርሱ ጋር የምንጋራው የጋራ ፍላጎት ይኖረናል፡፡ ይሁንና ከእኛ ይልቅ በድንበርም ሆነ በብሄር የጋራ የሆነ ጉዳይ ያላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ከእኛ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ይቀርቧቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት  የሶማሊያ መንግስት ዋነኛ አጋር ነበረች። የሶማሊያ መንግሥትን በሚደግፈው፣ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ኢትዮጵያ 3 ሺህ ወታደሮችን ያሰማራች ሲሆን፣ በሌላ የሁለትዮሽ ስምምነት ከ5ሺ-7ሺ የሚደርሱ ወታደሮች አሰማርታለች፡፡ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት  የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወጡ በኋላ እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ የግብጽ ወታደሮች የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ሃይልን  ይቀላቀላሉ ተብሏል። ሌሎች 5 ሺህ ወታደሮች ደግሞ በሌላ ስምሪት ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገቡ ተገልጿል።
 የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ለቅቀው መውጣት የሶማሊያን  የጸጥታ ስጋት እንደሚያባብሰው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃዲር ሞሃመድ ኑር፣ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ግብጽ ላደረገችላቸው ወታደራዊ  ድጋፍ አመስግነዋል፣ ስለ መሳሪያዎቹ ምንም የጠቀሱት ነገር ባይኖርም፡፡ ሮይተርስ የዜና ወኪል  የወደብና የጸጥታ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለፈው እሁድ  ሞቃዲሾ የደረሱት የጦር መሳሪያዎች የአየር መቃወሚያና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ባለፈው ሳምንት ግብጽ፣ በሶማሊላንድ የሚኖሩ ዜጎቿ ከአገሪቷ ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቧ ተዘግቧል፡፡
በግብጽና ሶማሊያ መካከል  የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነቱ የተፈረመ ሰሞን፣ ኢትዮጵያ ሌሎች አካላት ቀጣናውን ለማተራመስ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት፣ በዝምታ እንደማትመለከት አሳውቃ ነበር። የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር በምላሹ “ኢትዮጵያ ጩኸቷን ታቁም፣ እያንዳንዱ ወገን የዘራው ዘር ፍሬ ማፍራቱ አይቀሬ ነውና” ብለው ነበር። እንዲህ ያለው ፍጥጫ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ካልተፈታ ለቀጣናው መተራመስ የራሱን አደፍራሽ ሚና ሊወጣ እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
በቱርክ አሸማጋይነት እንደሚደረግ ቀን የተቆረጠለት የኢትዮጵና ሶማሊያ ንግግር የራሱን ፍሬ ሊያፈራ እንደሚችል ቢገመትም፣ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሦስተኛ አገራት ጣልቃ ገብነት ውይይቱ እንዳይሰምርና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም አየር እንዳይነፍስ አደናቃፊ ሊሆን ይችላል፡፡

Page 2 of 727