
Administrator
ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወባ በሽታ ተይዘዋል
የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ አያይዞም፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት አንጻር፣ የዘንድሮው ዓመት በበሽታው ስርጭትም ሆነ በሞት መጠን እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በወባ በሽታ ስርጭት ዙሪያ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ከታሕሳስ 22 ቀን 2016 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ድረስ 1 ሺሕ 157 ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕብረተሰብ ጤና ተግዳሮት የሆነው የወባ በሽታ፣ 75 በመቶ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ስርጭቱ በእጅጉ እየተስፋፋ እንደሚገኝም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
“በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል፣ 69 በመቶው ያህሉ ለበሽታው ተጋላጭ ሲሆኑ፣ 20 በመቶዎቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ለሞት እየተዳረጉ ነው” ብሏል። ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፤ እ.ኤ.አ. በ2024 ከተመዘገቡት ኬዞች 81 በመቶ እና 89 በመቶ የሚሆነውን የወባ በሽታ ሞት የሚይዙት አራት ክልሎች መሆናቸውን ያመለከተ ሲሆን፤ እነሱም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ናቸው፡፡
ድርጅቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት ከመስራትም ባሻገር፣አስፈላጊ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ በዚሁ ሪፖርቱ ላይ አስታውቋል።
ሀጢያት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል
አንድ የአይሁዶች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
አንድ በጣም ኃይለኛ ውሸታም ነበር - ስመ ጥር ዋሾ እንዲሉ፡፡ የሃይማኖት መጽሀፍ ባያሌው ያነብባል፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው የፀሎት መፅሐፉን ይዞ በተመስጦ እያነበበ ሳለ፣ ከውጪ የብዙ ሰዎች የጩኸት ድምፅ ይሰማል፡፡ ወደ መስኮቱ ሄዶ ሲመለከት የሚጮሁት ትናንሽ የሰፈር ልጆች ናቸው፡፡ “እነዚህ የሰፈር ልጆች ደሞ ሌላ ተንኮል ሊሰሩ ነው! ቆይ እሰራላቸዋለሁ!” ይልና እንዲህ አላቸው፡፡
“ስሙ ልጆች፤ ወደ - ፀሎት ምኩራቡ ሂዱና እዩ፡፡ እዚያ የባህር ሰይጣን ቆሞ ታያላችሁ፡፡ ምን ዓይነት ግዙፍ ሰይጣን መሰላችሁ? 5 እግር፣ 3 ዓይኖችና እንደ ፍየል ዓይነት ጢም ያለው ነው፡፡ ደሞ አረንጓዴ ቀለም ያለው ነው!”
ልጆቹ የተባለውን ጉደኛ ፍጡር ለማየት ጓጉና እየበረሩ ሄዱ፡፡ ውሸታሙም ሰው ወደ መጽሐፉ ተመለሰ፡፡ በነዚህ ደቃቃ ልጆች እንዴት እንደቀለደባቸው እያሰበ በተንዠረገገው ረዥም ጢሙ ውስጥ ሳቀ፤
ጥቂት ቆይቶ ግን መዓት አይሁዶች ወደሱ ደጃፍ እየጮሁ ሲያልፉ ሰማና ወደ መስኮቱ ሄዶ አየ፡፡ አንገቱን ብቅ አድርጎም፤
“ወዴት እየሄዳችሁ ነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡
“ወደ ፀሎቱ- ምኩራብ!” አሉና መለሱ፡፡
“እዚያ ምን ፍለጋ ትሄዳላችሁ?”
“አልሰማህም ወዳጄ! አንድ የባህር ሰይጣን ወጥቷል አሉ፡፡ አምስት እግር፣ ሦስት ዐይን፣ የፍየል ጢም ያለው አረንጓዴ ፍጡር ነው!”
ዋሾው አይሁድ የሰራው ዘዴ አገር እንዳታለለ ገብቶት በደስታ እየሳቀ መፅሐፍ ማንበቡን ቀጠለ፡፡ ግን ብዙም ሳያነብ ሌላ ከፍተኛ ጩኸት ሰማ፡፡ ወጥቶ ቢያይ አገር ይተራመሳል፡፡ አንዳች መንጋ ህዝብ ወደ ምኩራቡ ይነጉዳል፡፡
“ሰማችሁ ወይ ጎበዝ? ወዴት ነው፣ ይሄ ሁሉ ህዝብ የሚተምመው?” አለና ጮሆ ጠየቀ፡፡
“ምን ዓይነት የጅል ጥያቄ ነው የምትጠይቀው! ከፀሎት ምኩራቡ ፊት ለፊት የባህር ሰይጣን ቆሞ እየታየ መሆኑን አልሰማህም? አምስት እግር፣ ሦስት ዐይኖች፣ የፍየል ጢምና አረንጓዴ ሰውነት እንዳለው ተረጋግጧል” አለው ከሰዉ አንዱ፡፡ ዋሾው አይሁድ በነገሩ በመገረም ቀና ብሎ ወደ ሰዎቹ አየ፡፡ ከሚጎርፈው ህዝብ መካከል ዋናውን የቤተ-አይሁድ ሰባኪ ቄስ አያቸው፡፡
“ኧረ የፈጣሪ ያለህ! ዋናው የአይሁድ ሃይማኖት አስተማሪም ወደዚያው እየሄዱ ነው ማለት ነው? ዋናው ቄስ አምነውበት ከሄዱማ በእርግጥም አንድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ እሳት ካለ ጭስ አለ!”
ባርኔጣውን አጠለቀ፣ ካፖርቱን አደረገ፤ ከዘራውን ያዘና እየሮጠ ከመንጋው ጋር ተቀላቀለ፡፡
“ማን ያውቃል? ያ ያልኩት ነገር ዕውነት ሆኖ፣ የባህሩ ሰይጣን’ኮ መጥቶ ቆሞ ይሆናል!” እያለ በሆዱ፤ ጭራሽ ከህዝቡ ቀድሞ ሩጫውን ተያያዘው፡፡
* * *
እራሱ በዋሸው ውሸት ውሎ አድሮ ተተብትቦ መውጫ መሸሻ የሚያጣ ብዙ መሪ፣ ኃላፊ፣ አስተዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪ ወዘተ ሞልቷል፡፡ በሀሰት የፈጠረው ሰይጣን ድንገት ህዝቡን ያሳምንና ማጣፊያው ያጥረዋል፡፡ ውሸት እንደ እርግዝና በትንሿ ጀምሮ፤ በኋላ የማይሸፈንበት ደረጃ ይደርስና ፍጥጥ ብሎ የመውጣት ባህሪ አለው፡፡ ለማስወረድ እንሞክርም ቢባል የተወሳሰበ ችግር ይፈጠራል፡፡ ወይ አድጎ የማስወረጃው ጊዜ ያልፋል፡፡ ወይ አስወርዳለሁ ሲሉ የመመረዝ፣ አንዳንዴም የሞት አደጋ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ውሸቱ ከርሞ ከርሞ ሲወለድ ፈጣሪውን ጭምር ማስደንገጡ ነው፡፡ ፈጣሪው የገዛ ፈጠራውን እንደ ጣዖት እንዲያመልክ የሚገደድበት ሁኔታ ሲመጣ ግን ጉዳዩ የአገርና የህዝብ ችግር እንደሚሆን ማስተዋል ይገባል፡፡
ለህዝብ የተዋሸ ውሸት ወሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርምና ህዝብን ያስቆጣል፡፡ ይህም አላስተማማኝና ያልተረጋጋ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ “ዲሞክራሲን አስፋፋለሁ፣ ሰላምን አሰፍናለሁ፤ የህግ የበላይነት ከመሬት በላይ ስለሆነ እሱን ማረጋገጥ ነው ዋናው፣ ’ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈልነው የመሬት ትርፍና ኪራን ለማስላት አይደለም፣‘ ’የህግ የበላይነት በሌለበት ወፈፍ ያደረገው ሁሉ የመሰለውን እየሰራ ጦርነት መለኮሱ ሰላምም መደፍረሱ ፍፁም የማይቀር ነው፣‘ ሉአላዊነትን አስከብራለሁ፣ ልማትን አፋጥናለሁ፣ አቅም እገነባለሁ፣” ማለት፣ ማለት፣ ማለት፡፡…. ተስፋ፣ ተስፋ፣ ተስፋ…. በየዘመኑ በየወቅቱ ተስፋ ማቆር!! ተስፋው አልጨበጥ ካለ ተዓማኒነት ይጠፋል፡፡
ይህን ሁሉ ቃል ገብተን ተዘናግተን ከተገኘን ሁሉንም መስዋዕትነት የህይወትም፣ የማቴሪያልም ዋጋ መጠየቁ ግልጽ ነውና ከተጠባቂነት ወደተጠያቂነት ያሸጋግረናል፡፡
ውለን አድረንም ’ኃይል የሌለው ታጋይ፣ ስንቅ የሌለው ጎራሽ‘ ልንሆን እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡ ይህን አውቀን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሁኑኑ ማሰብ አለብን፡፡ በመሰረቱ መቼም ቢሆን መች፤ ሰላም፤ የመንቀሳቀሻችን መሽከርክሪት የሚሆነውና ለግብም የሚያበቃን በሌሎች አቅጣጫዎች ሁሉ አቅምና ኃይላችን አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ስንችል መሆኑን በውል መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ስለ ሰላም መደረግ ያለበትን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሁሉ ጥርጊያውን ማስተካከል ተገቢ የመሆኑን ያህል፤ ራሳችንን ለወረራና ለባላንጣ አመቻችተን መስጠትም ፍፁም አደጋ ውስጥ ሊጥለን እንደሚችል በጊዜ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምነው ቢሉ “ሀይለኛ መትቶ ካልደገመ ይንጠራራል፤ ሰነፍ እንዲደገም ይለመጣል” ይሏልና፡፡
ከህዝቡ ጋር ሆኜ ስለህዝብ እሰራለሁ የሚል ወገን ሁሉ፤ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይጠበቅበታል፡፡ የህዝብ የልብ ትርታ፣ የሀገር እስትንፋስ ነውና፣ በተለይም ለስልጣን ያበቃኝ ህዝቡ ነው የሚል፣ ባለስልጣን የመቆየት አቅሙም ያው ህዝቡ መሆኑን መገንዘብ ምርጫው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው፡፡ ምንም ዓይነት የውጪ ጫና የሀገር ህልውናን ከማጣት ጋር ሊተካከል አይገባም፡፡ የህዝብንና የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ የምንተገብረውን ነገር በተመለከተ ያለመሸፋፈንና ያለማድበስበስ አቋምን ለይቶ መሄድ ኋላ ውዥንብር ውስጥ ከመግባት ያድናል፡፡ አበው “ወይ ታጥቀህ ተዋጋ፣ ወይ ርቀህ ሽሽ” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
የገዛ ውሸቱን እውነት ይሆን እንዴ? ብሎ ከህዝቡ ፊት እንደሮጠው ይሁዳ የገዛ ንግግራችንና ንድፈ - ሀሳባችን ቁራኛና ሰለባ ሆነን ተጠላልፈን መውደቅ የለብንም፡፡ ኋላ ነገር ሲከፋ፤
“…እሸሸግበት ጥግ አጣሁ”
እምፀናበት ልብ አጣሁ”
እንዳንል መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ በተደጋጋሚና አንድ ነገር እንደበቀቀን የምንለፍፍ ከሆነ፤ “ሀጢያት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል” ማለት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ታዋቂው ያገራችን ገጣሚ ያለውንም አለመርሳት ነው፡-
“ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ፤
ዕውነት ይተውኛል ብለህ፣ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
…የተወጋ በቅቶት ቢተ’ኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው፡፡
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ”
በሚኒስትሩ ንግግር ሳቢያ ኢትዮጵያ የሱዳንን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አለመግባባቶች ካልተፈቱ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ሊፈጠር “ይችላል” በማለት የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ኢትዮጵያ የሱዳንን አምባሳደር ባለፈው ረቡዕ ለማብራሪያ መጥራቷ ተነገረ።
ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ በቅርቡ በቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድሮች ፍሬ ሳያፈሩ ከቀሩ፣ አገራቸው ከግብጽ ጎን ልትሰለፍ እንደምትችልና የሦስቱንም የተፋሰስ አገራት የውሃ መብት የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የጦርነት አማራጭ ክፍት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሚኒስትሩ አስተያየት ያስቆጣው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ለሆኑት አል ዛይን ኢብራሂም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥሪ ማድረጉን፣ እንዲሁም ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለውና ከሱዳን ጋር ያለው ጠንካራ ግንኙነት በነበረበት እንደሚቀጥል መግለጹ ተዘግቧል፡፡
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለሱዳን ትሪቡን እንደተናገሩት፣ ምናልባትም ራሳቸው የሱፍ ንግግራቸውን ለማብራራት በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚሁ ምንጮች፣ ኢብራሂም የሹመት ደብዳቤያቸውን በይፋ ለኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት አለማቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጠናከረና ስትራቴጂያዊ መሆኑን በመግለጽ፣ አስተያየቶቹን የማሕበራዊ ሚዲያ ወሬ ሲሉ አጣጥለውታል። ቃል አቀባዩ አክለውም፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በውይይት ለመቋጨት ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይፈጥር አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ግድቡ በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይፈጥር ባለፉት 13 ዓመታት መታየቱን ያብራሩት ቃል አቀባዩ፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የውጭ አካላት ጣልቃ መግባታቸውን ኢትዮጵያ እንደምትቃወም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የቢዝነስ አገናኞች በታሰበው ልክ ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አይደለም ተባለ
በካፒታል ገበያ ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የሚነገርላቸው የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አይደለም ተባለ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ካፒታል ገበያ መምጣቱ ሌሎች ድርጅቶችንም ሊያነቃቃ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2024 ካፒታል ገበያ ጉባኤ፣ ከባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አንስቶ መካሄድ ጀምሯል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤው፤ “ዘላቂነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ ከአፍሪካና ከዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተህክሉ፣ ጉባኤው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሲያከናውናቸው የቆዩ ስራዎችን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጪዎች ለካፒታል ገበያው በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡
“በሰዎች የተሳትፎ መጠን ጉባኤው የተሳካ ነበር” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ “ይህም ጠንክረን እንድንሰራና ተወዳዳሪ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር የሚያነሳሳን ነው” ብለዋል፡፡ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት መሆኑን በማውሳትም፣ በካፒታል ገበያ አገልግሎት ለሚሰጡ ሁለት ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ሁለቱም የኢንቨስትመንት ማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሲሆኑ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ሰነደ መዋዕለ ንዋዩን ይፋ ሲያደርግ ድጋፍ የሰጠው “deloitte” የተሰኘው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች ተቋማትም ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ሃና ተህክሉ፤ “በቅርብ ቀናት ውስጥ ፍትሕ ሚኒስቴር ይመዘግበዋል ብለን የምንጠብቀው ሰነደ መዋዕለ ንዋይን ለሕዝብ የማቅረብ መመሪያ ሲወጣ፣ ካፒታል ገበያን ወደ ስራ የሚያስገቡ የሕግ ማዕቀፎች ተሟልተዋል ተብሎ ይታሰባል” ብለዋል። ከ100 በላይ ገጾችን ይዟል የተባለው ይህ መመሪያ፣ ባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር እንደጸደቀ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ “ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ቁጥጥር መመሪያ” የጸደቀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ካልተመዘገቡ ወይም በዓዋጁና በመመሪያው ከዚህ ምዝገባ ነጻ ካልተደረጉ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ለሽያጭ መቅረብ አይችሉም ተብሏል።
ከዚህ ባሻገር፣ ማንኛውም ሰነደ መዋዕለ ነዋዮችን ለሕዝብ ማቅረብ የሚፈልግ ኩባንያ ሰነዶችን ለህዝብ ከማቅረቡ በፊት ዝርዝር መረጃዎችን ያካተተ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ለባለሥልጣኑ ማቅረብና ማጸደቅ እንደሚጠበቅበት ተብራርቷል። ይህንን ከማድረጉ በፊት ማስታወቂያ ማሰራትም ሆነ ከኢንቨስተሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም፣ በመመሪያው መሰረት።
በቀጣይ ጊዜያት በአነስተኛ የገንዘብ መጠን በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበትና ለአነስተኛ ድርጅቶች አመቺ ሁኔታ በሚፈጥረው ዓዋጅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ፣ ቡድን ተዋቅሮ እንደሚሰራበትም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሚካኤል ሃብቴ በበኩላቸው፣ የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አለመሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮም ወደ ገበያው መምጣት ሌሎችን ሊያነቃቃ እንደሚችል አመልክተዋል።
“ያለ አገናኞች የካፒታል ገበያው ሊሰራ አይችልም”ያሉት አቶ ሚካኤል፤ አገናኞቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር የካፒታል ገበያው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲፈጠር የሚያስችል ስራ ወደፊት እንደሚሰሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በአሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከመቶ በላይ ሰዎች ባለፉት 7 ወራት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ተባለ
ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከ100 በላይ ሰዎች እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡ በአሙሩ ወረዳ ኦቦራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ እነዚህ ሰዎች “ልጆቻችሁ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ተቀላቅለዋል” ተብለው መታሰራቸውን የጀርመን ሬዲዮ ድምጽ (ዶቸ ቨሌ) ያነጋገራቸው የታሳሪ ቤተሰቦች አመልክተዋል፡፡
ለሰባት ወራት ያህል ያለምንም ፍርድ ታስረዋል የተባሉት ሰዎች፣ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፣ በጉዳዩ ላይ ጥቆማ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ፣ 130 ሰዎች ከጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአሙሩ ወረዳ ለሰባት ወራት መታሰራቸውንና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
አንጋፋ የሚዲያ ባለሙያዎች ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር ይመሰገናሉ
በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ አገራቸውን ያገለገሉ 13 የሚደርሱ ቀደምት የሚዲያ ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በሚከናወን መርሐ- ግብር እንደሚመሰገኑና ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን አስታውቋል፡፡
በምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ይታደማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጋዜጠኞች፡- አቶ አስፋው ኢዶሳ፣ ወይዘሮ አባይነሽ ብሩ፣አቶ ሀዲስ እንግዳ፣ አቶ ዋጋዬ በቀለ፣ወይዘሮ ሚሊየን ተረፈ፣አቶ ሀይሉ ወልደፃድቅ፣አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል፣ አቶ ተክሉ ታቦር፣ አቶ ይንበርበሩ ምትኬ፣ አቶ ታዬ በላቸው ፣አቶ ግርማይ ገብረፃድቅና አቶ ኢሳያስ ሆርዶፋ ናቸው።
በዝግጅቱ ላይ እንደሚመሰገኑ ከተመረጡ በኋላ ህይወታቸው ያለፈው የሚዲያ ባለሙያ ሙሉጌታ ወልደሚካኤልም በልጆቻቸው ይወከላሉ ተብሏል፡፡
እነዚህ በዛሬው ዕለት ምስጋናና ዕውቅና የሚቸራቸው አንጋፋ የሚዲያ ሰዎች፣ ከዚህ ቀደም ተገቢውን ዕውቅና ሳያገኙ የቀሩና በሌሎች የሽልማት መርሀ ግብሮች ያልተካተቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በሁሉም ተመስጋኞች የህይወት ታሪክ ላይ በቂ ጥናትና ምርምር መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞ ጋዜጠኞችን የቆየ ድምፅና ቪድዮ የሚያሳይ አጭር ዘገባ የሚቀርብ ሲሆን፤ በዝግጅቱ ላይ የሙያ ማህበራት፣ የሚዲያ ኃላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህራንና ሌሎች እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡
የመርሀ -ግብሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የ45 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ፣የ20 ሰዎችን ታሪክ ደግሞ በመፅሐፍ ያሳተመ ነው። በተጨማሪም በርካታ የምስጋና መርሀ- ግብሮችን ያዘጋጀ ባለሙያ ነው።
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ታጣቂዎች የተወገዙበት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብና ቄለም ወለጋ፣አርሲ፣ጉጂ ዞኖችና የተለያዩ ወረዳዎች ታጣቂዎች የተወገዙበትና የሰላም ጥሪ የተላለፉባቸው ሰልፎች ባለፈው ሃሙስ መካሄዳቸው ተገለጸ፡፡ ሰልፈኞቹ በመንግሥት ኃይሎችና በአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካክል የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች ያቋረጡትን የሰላም ድርድር እንዲቀጥሉና የተኩስ አቁም በማድረግ ለሕዝቡ ሰላም እንዲሰጡም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
አንዳንዶች ሰልፉ በመንግሥት አስተባባሪነት እንደተዘጋጀ ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ “መንግሥትና ታጣቂው ቡድን ሰላም እንዲያወርዱ ለመጠየቅ በኅብረተሰቡ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ “መንግሥት ሰልፉን በማስተባበር ውስጥ እጁ የለበትም” ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
ደም ግፊትን ዝቅ ማድረግን ጨምሮ ቀይ ሥር የሚሰጣቸው አምስት ጥቅሞች
በኢትዮጵያ የደም ግፊት ያላባቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ተላላፊ ያልሆነው የጤና ችግር ከወጣት አስከ አዋቂዎች ላይ እየተከሰተ ሲሆን፣ ኣሳሳቢነቱ ከፍተኛ ሆኗል።
የአኗኗር ዘይቤ፣ አመጋገብ፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ሌሎችም ለደም ግፊት ምክንያት ከሚባሉት ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ ጤናማ አኗኗር በመከተል እራስን ከደም ግፊት ለመጠበቅ እና መቆጣጠር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከእነዚህም መካከል የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል እና ጤናማ በማድረግ ደግም ግፊትን በሚፈለገው መጠን ውስጥ ማድረግ ይቻላል። ለዚህም ከሚመከሩት የምግብ አይነቶች መካከል አንዱ ቀይ ሥር ነው።
አንዳንዶች ቀይ ሥር እንዲሁ ለቀለሙ እንጂ የሚሰጠው የምግብነት ጠቀሜታ ይህን ያህል ነው ሲሉ ቆይተዋል። ባለሙያዎች ግን ቀይ ሥር ለሰውነት ከሚሰጠው ብርታት እና ጥንካሬ ባሻገር የደም ግፊትን በመቀነስ በኩልም ጠሜታ አለው ይላሉ።
ቀይ ሥር የደም ግፊትን ዝቅ ከማድረግ እና እድሜ እየገፋ ሲሄድ የእእምሮ ጤናን ከመጠበቅ በተጨማሪ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች አሉት።
የዚህን አትክልት ለየት ያለ ጠቀሜታን በተመለከተ የሥነ ምግብ እና የጤና ባለሙያዎች መረጃዎችን እያጋሩ ሲሆን፣ በዕለት ከዕለት ምግባችን ውስጥም ቀይ ሥርን እንድናካትት እየመከሩ ነው።
አምስቱ የቀይ ሥር የጤና ጥቅሞች፡
1. ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ከሰውነት ማስወገድ
በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው ተፈጥሯዊ በጣም ደማቅ ቀለም ቤታላይን ይባላል፤ ይህም በሰውነት ውስጥ የተከማቹ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን የማስወገድ አቅም አለው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ጣልያን ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ቤታላይን በአንጀት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ የካንሰር ህዋሳትን የመግደል አቅም እንዳለው ቢያንስ በቤተ ሙከራ ደረጃ በተደረገ ጥናት ለማወቅ ተችሏል።
ቤታላይን በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኝ ብቸኛው ጠቃሚ ንጥረ ነገር አይደለም። ቀይ ሥር የደም ዝውውር በበቂ ሁኔታ ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች እንዲደርስ በሚያደርገው ለጤና ጠቃሚ በሆነው ናይትሬ በእጅጉ የበለፀገ አትክልት ነው።
ከአስር ዓመታት በላይ ቀይ ሥር በአትሌቲክስ ስፖርተኞች ውጤት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሲያጠኑ የቆዩት በዩናይትድ ኪንግደም ኤክስተር ዩኒቨርስቲ የፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤንዲ ጆንስ አትክልቱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይመሰክራሉ።
ከቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው “ናይትሪክ ኦክሳይድ የደም ሥሮችን በማስፋት የደም ዝውውርን እንዲቀላጠፍ በማድረግ ተጨማሪ ኦክስጂን ወደ ህዋሶቻችን እንዲደርስ ያደርጋሉ” በማለት ፕሮፌሰሩ ገልጸውታል።
2. ለደም ግፊት እና ለልብ ጤና
በየለቱ የተወሰነ መጠን ያለው የቀይ ሥር ጭማቂ መውሰድ የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ የግፊት መጠናቸውን በመቀነስ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ለተወሰኑ ሳምንታት በየዕለቱ ሁለት ፍሬ ቀይ ሥር መመገብ የደም ግፊትን በአማካይ አምስት ሚሊሜትር ሜርኩሪ እንዲቀንስ ያደርጋል።
ስለዚህም አንድ የደም ግፊት ያለበት ሰው በዚህ መጠን ግፊቱን መቀነስ ከቻለ እና በዚሁ ደረጃ መቆጣጠር ከተቻለ ሊከሰት የሚችልን የልብ ድካምን እና ስትሮክን በ10 በመቶ መቀነስ ይቻላል።
ቀይ ሥር የደም ግፊትን በመቀነስ ረገድ ውጤቱ በአጭር ጊዜ የሚታይ ነው። በጥናት እንደታየውም የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ላይ ቀይ ሥር ከተመገቡ በኋላ በተወሰነ ሰዓት ውስጥ ውጤቱን ማየት ይቻላል።
ይህም የሚከሰተው በቀይ ሥር ውስጥ ያለው የናይትሪክ ኦክሳይድ ንጥረ ነገር የደም ሥሮችን እንዲሰፉ በማድረግ ደም በሰውነት ውስጥ በቀላሉ እንዲዘዋወር ማድረግ ስለሚያስችል ነው።
3. የቀይ ሥር ጥቅም ለአንጎል
ቀይ ሥር የደም ሥሮችን ለቀቅ ብለው ደም እንደ ልብ እንዲዘዋወር በማድረግ ወሳኝ የሰውነታችን ክፍሎች የሚፈልጉትን ያህል የደም ፍሰት ስለሚያገኙ ጤናማ ተግባራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ያደርጋል።
በዚህም ቀይ ሥር ወደ በአንጎላችን ውስጥ በቂ የደም ዝውውር እንዲኖር ስለሚያደርግ፣ የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት ሰዎች የማስታወስ ችሎታቸው እንዲዳብር ከማድረግ በተጨማሪ ፈጣን ውሳኔዎችን ለመስጠት ብቁ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ቀይ ሥርን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች የአንጎላቸውን ጤና ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚጠቁሙ ባለሙያዎች አሉ።
የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣትን ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር ማጣመር ከተቻለ ደግሞ የተሳካ የደም ዝውውር ስለሚኖር በአካላዊ እና በአእምሯዊ ጤና ላይ አውንታዊ ጣምራ ውጤት ይኖረዋል።
4. ቀይ ሥር ለአፍ ጤና
ለአስር ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት በአፋችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጠቃሚ ባክቴሪያዎችን ይዘት ለማሻሻል እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመልክቷል።
በጥናቱ ተሳታፊዎች ላይ ከባክቴሪያዎች ጋር በተያያዘ ከደም ሥር እና ከአንጎል ጤና ጋር የተያያዙ በጎ ለውጦች ከፍ ሲሉ፣ ከበሽታ እና ከእብጠቶች ጋር የሚያያዙ ጎጂ ባክቴሪያዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል።
ዕድሜ ሲገፋ እየቀነሰ የሚሄደውን የሰውነታችንን ናይትሪክ ኦክሳይድ የማምረት አቅምን ለመከላከል የሚያስችሉ በአፍ ውስጥ የሚገኙ የጤናማ ባክቴሪያዎች መጠንን ቀይ ሥር እንዲጨምር በማድረግ የተሻለ ጤናማ እና ረጅም ዕድሜ እንዲኖረን ያደርጋል።
5. ቀይ ሥር ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስኬት
የቀይ ሥር ሌላኛው ጠቀሜታ ደግሞ ከባድ ኃይል እና ጉልበት በሚፈልጉ ሥራዎች እና ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ሰዎች በሚሰጠው ወሳኝ ንጥረ ነገር ነው።
በተለይ በሩጫው መስክ ለተሰማሩ አትሌቶች ብቃታቸውን ከፍ በማድረግ ፈጣን እንዲሆኑ አስተዋጽ እንዳለው በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥቃት አመልክቷል።
በቀይ ሥር ምክንያት “የሰውነት ጡንቻዎች በናይትሪክ ኦክሳይድ አማካይነት የበለጠ ኦክስጂን በማግኘት በውስጣቸው በበቂ ሁኔታ እንዲሰራጭ በማድረግ ውጤታማ ያደርጋል” ይላሉ ጆንስ።
በአውሮፓውያኑ 2009 በተደረገ ጥናት የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት ከባድ ልምምድ በሚደረግበት ጊዜ አካላዊ ጽናትን በ16 ከመቶ ከፍ በማድረግ ውጤታማ ያደርጋል።
ጥናቱ እንደሚያመለክተው በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው ናይትሪክ ኦክሳይ ስፖርተኞች በልምምድ ጊዜ የሚጠቀሙትን የኦክስጂን መጠን በመቀነስ፣ ድካም ላይ የሚደርሱበትን ሂደት ያዘገየዋል።
በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ብዙም ፈላጊ ያልነበረው የቀይ ሥር ጭማቂ አሁን በበርካታ አትሌቶች ዘንድ ተፈላጊው መጠጥ ሆኗል።
ይህ አትክልት ኃይልን ከማዳበር በተጨማሪም በፍጥነትም ላይ ከፍተኛ ውጤትን አሳይቷል። በ2012 (እአአ) በተደረገ ጥናት በ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች መካከል ቀይ ሥር የተመገቡት ካልተመገቡት ይልቅ የመጨረሻውን 1.8 ኪሎ ሜትር በአምስት በመቶ ፈጣን ከመሆናቸው በተጨማሪ ያሳዩት ድካም ዝቅተኛ ሆኖ ታይቷል።
በውድድር ወቅት ውጤታማ ለመሆን ስፖርተኞች ቀይ ሥርን ከውድድሩ ጅማሬ ከሰዓታት ቀደም ብለው መመገብ ወይም ጭማቂውን መጠጣት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል ይባላል።
በዩናይትድ ኪንግደም ኤክስተር ዩኒቨርስቲ የፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰሩ ኤንዲ ጆንስ “በቀይ ሥር ውስጥ ያለውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ናይትሪን ሰውነታችን ጥቅም ላይ ለማዋል ከ2 አስከ 3 ሰዓታት ስለሚፈጅ” ቀደም ብሎ መውሰድን ይጠይቃል ይላሉ።
ምን ያህል የቀይ ሥር መመገብ ይመከራል?
የሚፈለገውን ውጤት ከቀይ ሥር ለማግኘት ሁለት ወይም ሦስት መካከለኛ መጠን ያላቸውን የቀይ ሥሮችን በመፍጨት በጭማቂ መልክ መጠጣት እንደሚጠቅም ጆንስ ይመክራሉ።
“በየዕለቱ እና በየሳምነቱ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን የናይትሬት ፍጆታ ለማሻሻል የምንፈልግ ከሆነ፣ ቀይ ሥርን በመደበኛነት መመገብ ጠቃሚ ውጤት ይኖራዋል” ይላሉ ዶክተሩ።
ከቀይ ሥር ለመጠቀም እንዴት ይዘጋጃል?
ከቀይ ሥር ከሚገኘው ንጥረ ነገር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን በዝግጅት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ይመከራል።
በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኙት የናይትሬት ንጥረ ነገሮች በውሃ በቀላሉ የሚሟሙ በመሆናቸው፣ አትክልቱን በምናበስልበት ጊዜ በጣም መጠንቀቅ አለብን።
ቀይ ሥርን መቀቀል የናይትሬት ንጥረ ነገሮች ሟሙተው በውሃ ውስጥ ሊጠፉ ስለሚችሉ፣ በምንመገበው ጊዜ ጠቃሚውን ናትሬት በሚጠቅመን መጠን ላናገኘው እንችላለን።
“ቀይ ሥርን ከቀቀልን በኋላ የሚቀረውን ውሃ የምንደፋው ከሆነ፣ አብዛኛውን የናይትሬት ንጥረ ነገርን ሳንጠቀምበት እናጣዋለን” ይላሉ ዶ/ር ጆንስ።
ስለዚህም ለተለያዩ የጤና ጥቅሞቹ፣ ለጥንካሬ እና ለፍጥነት ቀይ ሥርን በመመገብ አትክልቱ የሚሰጠውን ተፈጥሯዊ ጠቀሜታን ሙሉ ለሙሉ ለማግኘት ባለበት ሁኔታ መመገብ ይመከራል።
ቀይ ሥር ተከትፎ በጥሬው፣ በተወሰነ ደረጃ ተጠብሶ ወይም ተፈጭቶ በጭማቂ መልክ ጥቅም ላይ ከዋለ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ የሚፈለገውን ንጥረ ነገር በማግኘት ሰውነታችን ተጠቃሚ ይሆን።
ተዋት ትኑርበት!
(ስለ እጅጋየሁ ሽባባው ክብር የተጻፈ)
አብርሀም ገነት
ያን ሰሞን በልቦናዬ የሚመላለሱት የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈኖች ነበሩ፡፡ ሳልሰለች ዘፈናቸውን በተደጋጋሚ ከምሰማቸው አርቲስቶች አንዷ እጅጋየሁ ናት፡፡ ዛሬም፡፡ አርቲስት ብዬ በሙሉ ልብ ከምጠራቸው በዘመኔ ከማውቃቸው ኢትዮጵያውያን አንዷ ጂጂ ናት፡፡ ለእኔ አርቲስት የሚያስተጋባ ሳይሆን የሚፈጥር ነው፡፡
ቀኔን እንዳዋዋሌ ውዬ፣ ራቴን በልቼ ወደ መኝታዬ እሄዳለሁ፡፡ ከመተኛቴ በፊት ግን አንድ ሁነኛ ነገር ይቀረኛል፡፡ እሱም ልብሴን አወላልቄ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ አንድ ሁለት የጂጂን ዘፈኖች አይኖቼን ከድኜ መስማት ነው፡፡ ያን ሰሞን፡፡ የጂጂን ለስላሳና አባባይ ዘፈኖች አይኖቼን ጨፍኜ ስስማ ነፍሴ ወደሆነ አለም ትንሳፈፋለች፡፡ ያለሁበትን እረሳለሁ፡፡ ለደቂቃዎች ከገላዬ ተነጥዬ ነፍስና ምናብ እሆናለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ አልጋዬን እያነጣጠፍሁ ቀኔን ስጀምር የማፏጨው ከጂጂ ዘፈኖች አንዱን ነው፡፡ የጂጂ ግጥሞች ውብ ናቸው፣ ዜማዎቿ ረቂቅ፡፡ ድምጿ ነፍስን ይዳብሳል፡፡ ጂጂ ጥልቅ ናት፡፡ ብርድልብስና ጨለማ ተከናንቤ አይኖቼን ከድኜ ዘፈኖቿን ስሰማ ፍፁም ፍስሃ ውስጥ እገባለሁ፤ አንዳንዴ የዘፈኑን ምት ተከትዬ በተኛሁበት ገላዬን እየሰበቅሁ በለሆሳስ እደንሳለሁ፤ አንዳንዴ እንባ ከአይኔ ኮለል እያለ በፀጥታ ላለቅስም እችላለሁ፡፡ ነፍሴ በሁሉም ትረካለች፡፡ በዚህኛው እንደዚህ በዚያኛው እንደዚያ እሆናለሁ ብዬ ዘፈኖቹን የማልጠቅስላችሁ የቱን አንስቼ የቱን እተዋለሁ ብዬ ነው፡፡ የምናውቅ እናውቃለን፣ ዝም ብሎ ማጣጣም ነው፡፡ የጂጂ ዘፈኖች ለጆሮና ለነፍስ የተሰሩ ናቸው፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሀት አንድ ጊዜ፤ “ሙዚቃ በመሰረቱ የጆሮ ነው” ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ በደንብ እስማማለሁ፡፡
የሆነ ጊዜ ስለ ጂጂ ከሙዚቃው አለም መጥፋት ሰዎች በዩቲዩብና በማህበራዊ መገናኛዎች እየተቀባበሉ ሲያወሩ ሰማሁና ስለ እሷ የበለጠ ለማወቅ ፈለግሁ፡፡ በሬዲዮና በምስል ያደረገቻቸውን ጥቂት ቃለ መጠይቆች ሰማሁ፡፡ በደንብ የሰማሁት ሸገር ሬዲዮ ላይ ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረገቺውን ቃለ መጠይቅ ነው፡፡ የጂጂን ማንነት መዘንሁ፡፡ ጂጂ ጎበዝ አርቲስት ብቻ ሳትሆን ማራኪ ሰብዕና ያላት ሴት ሆና አገኘኋት፡፡ ጂጂ ትሁት ናት፣ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ብትከይንም ራሷን ከፍ ከፍ አድርጋ አትኩራራም፡፡ ራሷን ከሌሎች ብቁ አርቲስቶች አንፃር ዝቅ አድርጋ ነው የምታቀርበው፡፡ አስቴር አወቀን ታደንቃለች፡፡ ከማሪቱ ለገሰ ጋር ብትዘፍኝስ ስትባል፤ “ውይ ድምጥማጤን ነው የምታጠፋው!” አለች፡፡ ይሄን ይሄን ስሰማ ጂጂን በዘፈኗ ብቻ ሳይሆን በሰብዕናዋም ወደድኳት፡፡
ጂጂ አሁን መዝፈን ከተወች ረጅም ጊዜ ሆኗታል፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች ሰዎች ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አሜሪካ ቤቷ ድረስ እየሄዱ እያገኟት ቆይታቸውን በምስል ቀርፀው ዩቲዩብ ላይ ሲለቁ አያለሁ፡፡ የእውነት ለጂጂ አስበውላት ይሆን ወይስ አጋጣሚውን ተጠቅመው ራሳቸውን ለማሳወቅ? ወይም ለመሸቀል? እሷስ በዚህ ደስተኛ ናት? እድሜ የማይድጠው፣ ጊዜና ሁኔታ የማያነሳውና የማይጥለው ሰው የለም፡፡ የጂጂም ነገር ከዚህ የተለየ ትንግርት የለውም፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለቺም ምናምን እያሉ፣ ጂጂን እየፈለጉ እየቀረፁ አደባባይ ላይ ማስጣት የግል ህይወቷን መጋፋት ነው፡፡ መረዳት ካስፈለጋትና ቅን ልብ ያለው ካለ፣ ያለምንም የፎቶና የምስል ጋጋታ እገዛውን በፀጥታ ማድረግ ይችላል፡፡ ምናልባት እሷ ምንም አትፈልግም፡፡ ምናልባት ጂጂ ስለ እሷ ደህና አለመሆን ከምናወራው ከብዙዎቻችን በተሻለ መረጋጋትና የአእምሮ ሰላም ውስጥ ይሆናል ያለቺው፡፡
በቅርብ ጊዜ አንድ ሰው ቤቷ ሄዶ አግኝቷት ቀርፆ የለቀቀውን ምስል አይቻለሁ፣ ጤነኛ ናት፣ ከለዛዋና ከትህትናዋ ጋር ናት፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለውን ገመናዋን ደግሞ ለራሷና ለቅርብ ቤተሰቦቿ መተው ነው ያለብን፡፡ ቀሪ ዘመኗን በሰላም ልትኖር ይገባታል፣ የግል ህይወቷን ለራሷ ልንተውላት ይገባል፡፡ ደግሞስ ጂጂ በሙዚቃ ስራዋ የግድ መመለስ አለባት? በህይወት እስካለች ድረስ ሁልጊዜም የግድ መዝፈን አለባት? የህይወት ግቧን በጊዜ አጠናቃ ከሆነስ? ከበቃትስ? ሁላችንም በየተሰማራንበት ስራ በየአመቱ ብንመነደግ እንወዳለን፡፡ ነጋዴ ሁልጊዜ ትርፍ ቢያፍስ ደስ ይለዋል፡፡ ደራሲ በየአመቱ ቢያሳትም፣ ሙዚቀኛ በየአመት በአሉ ዘፈን ቢለቅ አይጠላም፡፡ ግን ሁልጊዜ እንደምኞታችን አይሆንም፡፡ ሁኔታዎች መሻታችንንና ጥረታችንን አግዘው አብረውን የሚፈሱበት ጊዜ አለ፡፡ በዙሪያችን ያለው ሁሉ ለእኛ ስኬት የሚያደላበት ወቅት አለ፡፡ የተገላቢጦሽ የሚሆንበት ወቅትም አለ፡፡ የሚሰራበት ጊዜ አለ፣ ዝም ተብሎ የሚኖርበት ጊዜ አለ፡፡ ጂጂ ምርጥ ምርጥ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖችን አበርክታልናለች፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የራሷን መልካም አሻራ አሳርፋለች፡፡ አሁን ዝም ብላ በሰላምና በዕረፍት ኑሮዋን የምትኖርበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ይሄም ለእሷ ይገባታል፡፡ ሰላም ለጂጂ ባለችበት እመኝላታለሁ፡፡
(ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. ባህር ዳር)
የዶናልድ ትራምፕ መመረጥና የዓለም መሪዎች ምላሽ
የአፍሪካ መሪዎች ብሩህ ተስፋ
ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ከለቀቁ ከአራት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ታሪካዊ ድል ተከትሎም በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከትራምፕ ጋር በቅርበት ለመስራትና ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ተስፋና ጉጉት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የትራምፕ ዳግም መመረጥ አፍሪካን አሜሪካን ወደተሻለ ቅርርብና ትብብር ሊመራ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በማስተላለፍ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ መሪዎች የአገራችን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “በምርጫ ድልዎትና ወደ ስልጣን በመመለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ በኤክስ ገፃቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ “በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሰራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ብለዋል፡፡
የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ፈቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ “ዚምባቡዌ የተሻለች፤ የበለጠ የበለፀገችና ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት ከእርስዎና ከአሜሪካ ህዝብ ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ በመልእክታቸው፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ፣ ለተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት፤ “በአንድ ላይ የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ፤ ሰላምን ማጎልበትና ዓለማቀፍ ተግዳሮቶችን መፍታት እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ዳግም ተመረጡ መልዕክት፤ በቀጣዮቹ ዓመታት ለአገሮቻችን የጋራ ጥቅም ከእርስዎ ጋር ለመሥራት በጉጉት እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን “የጋራ ተጠቃሚነት አጋርነት” ለመቀጠል በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግብዣ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ለዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት፣ “ባለ ራዕይ፣ ደፋርና ፈጠራ የታከለበት አመራር ያላቸው” ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡
ከመሪዎች ባሻገር አፍሪካውያንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አብዛኞቹች ውጤቱ ለአሜሪካ ትልቅ ድል መሆኑን ጠቁመው፤ ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን እንደሚያስቆሙ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ደግሞ ትራምፕ ድሉን የተቀዳጁት የተሻለ ተቀናቃኝ ስላልገጠማቸው ነው ብለዋል፡፡ ለትራምፕ አሸናፊነት የአሜሪካውያንን ለሴት ፕሬዚዳንት ዝግጁ አለመሆንን በምክንያነት የጠቀሱም አልጠፉም፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ምን አሉ?
ለዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉት ቭላድሚር ፑቲን፣ ተመራጩን ፕሬዚዳንት “ደፋር” ሲሉ አሞካሽተዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት በሶቺ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበሩበት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከየአቅጣጫው ጫና በዝቶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እሠራለሁ ማለታቸው “ቢያንስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉም ፑቲን በንግግራቸው አክለዋል። ባለፈው ሐምሌ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በተመለከተም ሲናገሩ፤ “በእኔ አስተያየት በጣም ትክክለኛ በሆነ መንገድ አንድ ደፋር ሰው ማድረግ ያለበትን አድርጓል” ሲሉ ፑቲን ለትራምፕ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የተጠየቁት ፑቲን፤ “ዝግጁ ነን፣ ዝግጁ ነን” ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ለመነጋገር መዘጋጀታቸውን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ለኤንቢሲ ኒውስ በሰጡት ቃል፤ “የምንነጋገር ይመስለኛል” ብለዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ በዩክሬንና በአውሮፓ የሚገኙ በርካቶች፣ ትራምፕ ወደ ኪዬቭ የሚላከውን የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ሊገቱ ወይም ሊያዘገዩ ይችላሉ የሚል ጭንቀት እንደገባቸው ተዘግቧል።
የትራምፕን ድል “በቮድካ” እንዳከበሩ የገለጹት የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው፤ አሁን አሜሪካና አውሮፓ በንግድ መስመር ላይ ከባድ ንግግሮች ይገጥማቸዋል ብለዋል። የትራምፕ የቅርብ አጋር የሆኑት ኦርባን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው፤ “ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው የንግድ ጉዳይ ከመነሳቱም በላይ ቀላል አይሆንም” ብለዋል።
የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ምክክር
50 የሚደርሱ የአውሮፓ መሪዎች የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ በአህጉሩ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በተመለከተ መመክራቸው ተዘግቧል፡፡ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው ስብሰባ ላይ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪና የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩትን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራትና ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
መሪዎቹ በሩስያ ጉዳይ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመን እንዳለው ጠንካራ የጋራ አቋም እንዲንጸባርቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የሚሳኤልና የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን በመስጠት በምላሹ ከፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ እያገኘች ነው፤ ይህ ለአውሮፓ የኔቶ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በመጀመርያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የኔቶ አባል ሀገራት ለድርጅቱ የመከላከያ ወጪ የሚጠበቅባቸውን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ እና ከዛ በላይ እንዲያወጡ እንዲሁም ከአሜሪካ ወታደራዊ እገዛ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በጥብቅ ይገፋፉ ነበር፡፡ ይህንኑ ሀሳብ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል በስብሰባው ላይ ያነሱ ሲሆን፤ አህጉሩ በአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍና የኔቶ መዋጮ ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከአውሮፓ ጋር ከሚኖረው የንግድ ጦርነት አንስቶ ከኔቶ ለመውጣትና ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት መሰረታዊ የሆነ የድጋፍ ለውጥ እንደሚያደርጉ ዝተዋል፡፡ ይህም በመላው አውሮፓ በሚገኙ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በ2018 የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ምርቶች በአሜሪካ አጋሮች ቢመረቱም ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አስጊ ናቸው በሚል በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሚመረቱ የብረትና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ለሩስያ ሊያደሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው፡፡ የአውሮፓ አገራት መሪዎች የተሰባሰቡበትን ጉባኤ ያዘጋጀችው ሀገር ሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ትልቅ እቅድ እንዳላቸው ከስብሰባው በፊት ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በዩክሬንና በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፣ በስደት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ለሚቀጥሉት አመታት በአውሮፓ አጠቃላይ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡