Administrator

Administrator

Saturday, 11 October 2014 15:53

የፍቅር ጥግ

ሚስት ያላገባ ወንድ፣ አበባ አልባ የአበባ ማስቀመጫ እንደማለት ነው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
የሚስትህን የልደት ቀን ለማስታወስ ትክክለኛው መንገድ አንድ ጊዜ መርሳት ነው፡፡
- ኤች.ቪ. ፕሮንችኖው
ፍቅር እውር ነው፤ ትዳር ግን የብርሃን ፀጋውን መልሶ ያጐናፅፈዋል፡፡
ሳሙኤል ሊችቴንበርግ
ትዳር፤ ከጠላትህ ጋር አንድ አልጋ የምትጋራበት ብቸኛው ጦርነት ነው፡፡
ፍራንሶይስ
ብዙ ቤተሰብ ባለበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ እውነት ለመናገር ሚስት እስካገባ ድረስ ብቻዬን ተኝቼ አላውቅም፡፡
ልዊስ ግሪዛርድ
ባል ማግባቴን እወደዋለሁ፡፡ በቀሪው ህይወታችሁ ልታበሽቁት የምትፈልጉት አንድ የራሳችሁ ሰው ማግኘት ድንቅ ነው፡፡
ሪታ ሩድነር
ትዳር እስከምይዝ በፍፁም በፍቺ አምኜ አላውቅም፡፡
ዲያኔ ፎርድ
ብቸኛ ለመሆን እርግጠኛው መንገድ ትዳር መያዝ ነው፡፡
ኖራ ኢፍሮን
ማንኛውም ያገባ ወንድ ስህተቶቹን መርሳት አለበት - ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ማስታወሳቸው ምንም ፋይዳ የለውም፡፡
ዱዌኔ ዴዌል
ትዳር ሌሊት ብቻቸውን መተኛት ለሚፈሩ ሰዎች ጥሩ ነው፡፡
ሴይንት ጄሮሜ
ከፍቅር የምንወደው ትኩሳቱን ነው፤ ትዳር ደግሞ አልጋ ላይ ያስተኛውና ይፈውሰዋል፡፡
ሚኞን ማክላውግሊን


Saturday, 11 October 2014 15:48

ማራኪ አንቀፅ

           በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ፣ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረገው ግን በዚያ ጊዜ ነበር፡፡ ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣ አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለሁ፡፡ አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድንጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፤ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው  ጉብኝታችን፣ እንዴት የበኩር ልጁ የእድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡ የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩ ነው ያደግሁት፡፡ አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ “ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው” ብለውኝ አያውቁም፡፡ ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬው ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአካባቢያችን ሰው ሁሉ እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ፡፡ የእለት ተዕለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርቴ በርትቼ እንድገፋ ያበረታቱኝ ነበር፡፡

አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን (አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛ ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡
የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የህዝብ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ፣ ሥነ-ህንፃ (አርኪቴክቸር) መማር ጀመርኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የልጅነት ህልሜን አልዘነጋሁትም ነበር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመርያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ እኔም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡ የሥነ - ህንፃ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የመግቢያ ፈተናውን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡ ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ሥልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርት ገደል እንደመክተት ሆነብኝ፡፡ የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ሥልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ሥልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በህዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም በረዳት አብራሪነት ለ4ሺ475 ሰዓታት አብርሬያለሁ፡፡ ከዚም ከተለያዩ ፈተናዎች፣ ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ፣ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ሥልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመሪያ በረራዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ በ2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡ ..................
(“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ከተሰኘው አዲስ መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ፤ 2007 ዓ.ም)

                 የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎችን አወዳድሮ የሚሸልመው የ”ለዛ” ፕሮግራም መቼና እንዴት ተጀመረ?
ፕሮግራሙ ከተጀመረ አራት አመት ሆኖታል፡፡ የ“ለዛ” ፕሮግራም በተለይ የሀሙስ የምሳ ሰዓት ዝግጅት በኢትዮጵያ ስራዎች ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ደረጃቸውን የጠበቁ የኢትዮጵያ ሙዚዎችን እየመረጥን እናስተላልፋለን፡፡ የዛሬ አራት አመት ሁሉ ነገር ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ የወጡት አልበሞች ትንሽ ነበሩ፡፡ እኛም ፕሮግራማችን ላይ የምንሰማው አዲስ ስራ አጣን፡፡ አርቲስቶቹ ከስራቸው የሚያገኙት ገቢ ባያስደስታቸውም፣ የኮፒራይት ጉዳይ ፈር ባይዝም፣ የሰሩትን ስራ አድማጩ “ጥሩ ነው” ብሎ ሲመርጠው ይበረታቱ ይሆናል በሚል ነው ሽልማቱ የተጀመረው፡፡ ሰርፀ ፍሬስብሐትና ያሬድ ሹመቴ፤ በብሄራዊ ቴያትር ከሚያዘጋጁት ፕሮግራም ጋር ለምን አይደረግም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት የመጀመርያው የሽልማት ፕሮግራም እዚያው ተደረገ፡፡ ሁለተኛውን በእምቢልታ ሲኒማ፣ ሶስተኛውን በጃዝ አምባና አራተኛውን የዛሬ ሳምንት በጣሊያን የባህል ተቋም አድርገናል፡፡
ፕሮግራሙ አላማውን አሳክቷል ትላለህ?
አዎ! የሰው ተሳትፎ በጣም ጨምሯል፤ ከመጀመሪያው በስተቀር የሌሎቹ ምርጫው የተከናወነው በኢንተርኔት ነው፡፡ በየእለቱ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ዘንድሮ በያሁ ዶት ኮምና በሸገር ዌብሳይት ላይ ነው ድምፅ የተሰጠው፡፡ በሸገር ዌብሳይት ላይ ብቻ የተሰጠው ድምፅ ከ60ሺ በላይ ነው፡፡ ማን ከየት ሀገር ማንን እንደመረጠ ማየት ይቻላል፡፡
ተወዳዳሪዎችም ምን ያህል ድምፅ እንዳገኙ ያዩታል፡፡ በዚህ በአራተኛው ዙር ከበፊቶቹ ዙሮች በተለየ ከህዝብ ድምፅ በተጨማሪ የባለሙያዎች ግምገማም እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ስራዎች ህዝብ ስለወደዳቸው ብቻ ሳይሆን ኪነ-ጥበባዊ ፋይዳቸውም እንዲታይ በማለት ለህዝብ ድምፅ 60 በመቶ፣ ለባለሙያ ድምፅ 40 በመቶ ተደርጓል፡፡
የፐርሰንት ስሌቱ እንዴት ተሰራ?
ፕሮግራሙ ሲጀመር የአድማጮች ምርጫ ስለተባለ፣ አብላጫውን ለህዝብ ለመስጠት ሲባል 60 በመቶ ለህዝብ ድምፅ ሲሆን 40 በመቶው ለባለሙያ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቁ ክርክር ምን መሰለሽ? ህዝቡን መምራት ያለበትና ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የመገምገም የመሪነቱን ሚና መጫወት ያለበት ባለሙያው ነው የሚል ነው፡፡
መስፈርቱ ምን ነበር?
 መስፈርቱ ግልፅ ነው፡፡ የሙዚቃ ስራዎችን ለመገምገም የሚችሉ ከበቂ በላይ ሙያተኞች አሉን፡፡ የፊልም ጥበብ ስራ ላይ ግን ገና ይቀረናል፡፡ ስራዎችን የሚገመግሙ በቂ ሙያተኞች የሉም፡፡ እንግዲህ በአገር ዳኛ ነው የሚዳኘው፡፡
በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ፕሮግራሙን ተረድቶት ላለፉት ዓመታት በብቸኝነት የረዳን “አኳ አዲስ” ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝ የቢራ ፋብሪካዎች አልበም ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ ስፖንሰር ያደረጓቸው አልበሞች በዚህ ውድድር ሲሳተፉ እያዩ፣ ይህን የውድድር መንፈስ ለማገዝ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ሌላው ችግር ፕሮግራሙ የሚዘጋጅበት ቦታ ማግኘት ነው፡፡ ብቸኛው ጥሩ አዳራሽ ብሔራዊ ትያትር ነው፤ ነገር ግን ነፃ የሚሆነው ሰኞ ብቻ ነው፡፡
የጣልያን የባህል ተቋም አዳራሽ ሰፊ ነው፤ ግራንድ ፒያኖና ብዙ ሰው የሚያስተናግድ ግቢ አለው፡፡ ይህንን የሚያሟላ ቦታ ለማግኘት ብዙ ምርጫ የለንም፡፡ መድረኩን እንደ አዲስ ነው የሰራነው፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ገቢ አለው?
የለውም፤ እንዲያውም ከኪስ ያስወጣል፡፡ ፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች ላይ የሚታዩ ስፖንሰሮች ገንዘብ ሳይሆን የሚሰጡት ወጪዎችን ነው የሚችሉት፡፡ አንዱ የአዳራሽ ኪራይ ሲችል ሌላው የጥሪ ካርድ፣ ሌላው ውሃ፣ ሌላኛው ምግብ ያቀርባል፡፡ በዚያ መልክ ነው የዝግጅቱ ወጪ የሚሸፈነው፡፡
በአሸናፊዎቹ ምርጫ ላይ ቅሬታ ቀርቦ ያውቃል?
በፍፁም! ተወዳዳሪ ሁሉ በእርግጥ ማሸነፍ ይፈልጋል፤ ነገር ግን የድምፅ አሰጣጡ ሂደት መቶ በመቶ ግልፅ ነው፡፡ የተገኘው ድምፅ በግልፅ ይቀመጣል፡፡ እንዲያውም “አንተ አሪፍ ነው ያልከው ስራ አሸንፏል ወይ” ብትይኝ መልሴ አይደለም ነው፤ እኔ ጥሩ ያልኳቸው ያልተሸለሙ አሉ፤ ጥሩ አይደሉም ያልኳቸው የተሸለሙ አሉ፡፡
የውድድር ዘርፎቹ እንዴት ናቸው?
በአመት ውስጥ ምን ያህል የባህል ዘፈን ይወጣል? ምን ያህል ስራዎች በሙዚቃ ስልት ለመመደብ የተመቹ ናቸው ስትይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ አልበም ውስጥ የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች አሉ፤ ስለዚህ ለምደባ አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ዜማና ግጥም የሚል ምድብ ለመጨመር እየታሰበ ነው፤ ዘንድሮ “ምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ”፣ “አዲስ ድምፃዊ” እና “የህይወት ዘመን ተሸላሚ” የሚሉ ምድቦች ተካትተዋል፡፡
 በፊልም “ምርጥ ሳውንድ ትራክ” የሚል ምድብ ለመጨመር ታስቦ ምን ያህል ናቸው ኦርጂናል ሳውንድ ትራክ የሚጠቀሙት የሚለው ተገምግሞ ውድቅ ሆኗል፡፡  

ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የእኔ ፍላጎት ኤፍቢአይ መሆን ነው፡፡ አንድ ቀን የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሆኜ እመረጥ ይሆናል፡፡ ገና ልጅ ስለሆንኩ ግን ትንሽ ይቆያል፡፡
አርተር - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የመጨረሻ ደብዳቤዬ ደርሶህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በዚያ ደብዳቤ ላይ ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ጨረቃ የምጓዝ የመጀመሪያው ሰው መሆን እንደምፈልግ ፅፌልሃለሁ፡፡ ያን ጊዜ አንተ ፕሬዚዳንት ላትሆን ትችላለህ፤ ነገር ግን ወንድምህ ቦብ ኬኔዲ የሚሆን ከሆነ፣ ይሄን ደብዳቤ ለሱ ስጥልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ስንታሊ - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
ባለቤትህ በጣም ቆንጆና በጣም ጥሩ ሴት ትመስለኛለች፡፡ በጣም ቀልደኛም ሳትሆን አትቀርም፡፡ ሁለታችሁንም እወዳችኋለሁ፡፡
ናንሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የገንዘብ ሚኒስትር እያሉህ፣ የህፃናት ሚኒስትር የሌለህ ለምንድነው? ህፃናትም እኮ ድምፅ መስጠት ይችላሉ፡፡ እነሱም መብት አላቸው፡፡
ቼሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ጎበዝ ነኝ፡፡ በትምህርቴም ጥሩ ውጤት ነው የማመጣው፡፡ እናቴ በጣም ንፁህና ጠንቃቃ እንደሆንኩ ትነግረኛለች፡፡ ስለዚህ ዋይት ሃውስን አላዝረከርክም፡፡
አቢጌል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አጎቴ ማርዮ ፀጉር አስተካካይ ነው፡፡ ዋይት ሃውስ መጥቶ ያንተን ፀጉር ማስተካከል ይፈልጋል፡፡ 50 ሳንቲም ብቻ ነው የሚያስከፍልህ፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ስለሆንክ አንተን ማስተካከል ብዙ ደንበኞች እንደሚያመጣለት ነግሮኛል፡፡
አልበርት - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
እኔ ገና መፃፍ ስለማችል ይሄን ደብዳቤ የፃፈችልኝ እናቴ ናት፡፡ አንድ ቀን ግን መፃፍ እችላለሁ፡፡ ያኔ ድምፅ መስጠት ስለምችል ድምፄን የምሰጠው ለአንተ ነው፡፡ ለደብዳቤዬ መልስ እንድትፅፍልኝ… እሺ፡፡ መፃፍ ባልችልም ማንበብ እችላለሁ፡፡
ሲድኒ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ዋይት ሃውስ ውስጥ ሃላፊው ማነው? አንተ ነህ ወይስ ቀዳማዊት እመቤት? የእኛ ቤት ሃላፊ እናቴ ናት፡፡
ካርል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አባቴ ግብር ሲከፍል ነው እንጂ ሌላ ጊዜ በጣም ነው የሚወድህ፡፡
ብሩክ - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የሴት ጓደኛዬ አሊሳ ሪፐብሊካን ስትሆን እኔ ዲሞክራት ነኝ፡፡ አንድ ቀን መጋባታችን አይቀርም፡፡ ዲሞክራት ሪፐብሊካንን ማግባትና ደስተኛ መሆን ይችላል? እኔ 12 ዓመቴ ሲሆን ጓደኛዬ 11 ዓመቷ ነው፡፡ 18 ዓመት ሳይሞላን በፊት መልስህን እንፈልጋለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ሪያን - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የአብርሃም ሊንከንን ንግግሮች ማንበብ ያለብህ ይመስለኛል፡፡ ያን ጊዜ ሰዎች ያንተን ንግግር እየሰሙ ማንቀላፋት ይተዋሉ፡፡
ጂሚ - የ10 ዓመት ህጻን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ከሚስትህ ጋር ከተጋባህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? አንተና ቀዳማዊት እመቤት ተጣልታችሁ ታውቃላችሁ? እናትና አባቴ ከተጋቡ 20 ዓመት ሲሆናቸው ሲተኙ ካልሆነ በቀር ሁልጊዜ እንደተጣሉ ነው፡፡
ካያ - የ13 ዓመት ህፃን

           የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሰባት አመታት በፊት በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአገሪቱ ከተቀሰቀሰውና ከ1ሺህ 200 በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት፣ 600 ሺህ ያህሉን ደግሞ ለመፈናቀል ከዳረገው የእርስ በርስ ግጭት ጋር በተያያዘ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት የተመሰረተባቸውን ክስ ባለፈው ረቡዕ በፍ/ቤቱ ቀርበው አደመጡ፡፡
በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን ክስ ለማድመጥ በፈቃደኝነት የተገኙ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ዘ ሄግ በሚገኘው ፍ/ቤት በተዘጋጀው የቅድመ ፍርድ ሂደት ውይይት ላይ ተገኝተው የተመሰረቱባቸውን አምስት የወንጀል ክሶች ያደመጡ ሲሆን፣ ወንጀሎቹን አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“የተመሰረቱብኝ ክሶች ከፖለቲካዊ ጥቅም ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል” ብለዋል ምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን በቦታቸው ወክለው፣ ክሱን ለማድመጥ ወደ ፍርድ ቤቱ የሄዱት ኬንያታ በሰጡት ምላሽ፡፡
በ2007 የኬንያ የምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ግጭት ውስጥ እጃቸው አለበት፣ ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥሱ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል በሚል በቀረቡባቸው አምስት ክሶች፣ የሚሊሺያ ወታደሮችን በገንዘብ በመደገፍ ለጥቃት አነሳስተዋል፤ ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ሂደት ይታይ አይታይ የሚለው  ሐሙስ የሚወሰን ይሆናል፡፡በዕለቱ አቃቤ ህግ፤ የኬንያ መንግስት በፕሬዚዳንቱ ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁልፍ ማስረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም በሚል ቢወነጅልም፣ ኬንያዊው ጠበቃ ጊቱ ሙጋይ ግን  ውንጀላውን አልተቀበሉትም፡፡ ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ ካላገኘ፣ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ወንጀሎቹ  በፕሬዚዳንቱ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ የስልክ ማስረጃዎችና ዘጠኝ ምስክሮች እንዳሉት አስታውቋል፡፡ፍርድ ቤቱ በኡሁሩ ኬንያታ ላይ የተመሰረተውን ክስ ውድቅ ማድረጉን አልያም የፍርድ ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት ሰሞኑን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሌላው መሪ፣ የሱዳኑ ኦማር አልበሽር እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፤ በዳርፉር በተከሰቱ የጦርነት ወንጀሎች ተከስሰው  ፍርድ ቤቱ ያወጣባቸውን የእስር ትዕዛዝ አልቀበልም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡በፍርድ ቤቱ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ባለፈው ሃሙስ ወደ አገራቸው የተመለሱት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ናይሮቢ በሚገኘው አየር ማረፊያ ሲደርሱ በባህላዊ ጭፈራና የወታደራዊ ማርሽ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ከአየር ማረፊያ እስከተማዋ ማዕከላዊ አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውም ለፕሬዚዳንታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
“አንድ ነን!... ኬንያ የተረጋጋች አገር ስለሆነች ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም!” ብለዋል ኬንያታ ለህዝቡ ባሰሙት አጭር ንግግር፡፡

  • ውጤት ያልቀናቸው ባሬቶ፤ በሥራቸውም ውጣ ውረድ በዝቶባቸዋል፡፡
  • ምድብ 2 ለማለፍ አልጄርያ እና ማሊ የተሻለ እድል ይዘዋል፡፡
  • ዋልያዎቹና ንስሮቹ ሲነፃፀሩ፤ የኃይል ሚዛኑ ወደ ማሊ  ያጋድላል፡፡

    ዩሱፍ ሳላህ
30 ዓመቱ ነው
ትውልዱ በስዊድን ሶላና ነው፡፡
የግራ ክንፍ መስመር ላይ ይጫወታል፡
አሁን በስዊድኑ ክለብ አይኬ ሳይረስ     ይጫወታል፡፡
ከ2012 እኤአ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 9 ጨዋታዎችን አድርጎ     1 ጎል አስመዝግቧል፡፡
በዝውውር ገበያው ያለው የዋጋ ግምት 150ሺ ዩሮ ነው፡፡


አሚን አስካር
29 ዓመቱ ነው፡፡
ትውልዱ በሃረር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
የክንፍ መስመር ላይ ይጫወታል፡፡
ከ2012 እኤአ ጀምሮ ብራነር በተባለ     የኖርዌይ ክለብ እየተጫወተ ነው፡፡
በዛሬው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሰለፍ ይሆናል፡፡
በዝውውር ገበያው ያለው የዋጋ ግምት 1 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡

ዋሊድ አታ
28 ዓመቱ ነው፡፡
ትውልዱ በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ነው፡፡
የመሃል ተከላካይ ሆኖ ይሰለፋል፡፡
በ2014 እኤአ ላይ ቢኬ ሃከን በተባለ     ክለብ እየተጫወተ ነው፡፡
ከ2008 እሰከ 2009 እኤአ በስዊድን ሀ21 ብሄራዊ ቡድን ሶስት ጨዋታዎች አድርጓል፡፡
በዝውውር ገበያው ያለው የዋጋ     


ለ31 ዓመታት ያለተሳትፎ የራቀበትን አህጉራዊ ውድድር ከ1 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው  የአፍሪካ ንጫ በመሳተፍ ታሪኩን የቀየረው፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ይህን ስኬት ለመድገም አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ አንዳንድ ስፖርት ቤተሰቦች ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የምትበቃው በውድድሩ አዘጋጅነት ብቻ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በ2015 እኤአ ላይ በሞሮኮ ለሚካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በመላው አህጉሪቱ የሚደረገው የምድብ ማጣርያ በዚህ ሰሞን አጋማሹ ላይ ይደርሳል፡፡ ከትናንት ጀምሮ በሚካሄዱት የ3ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ  10 ብሄራዊ ቡድኖች በፉክክሩ ለመቆየት ይፋለማሉ፡፡ የሰባት ግዜ ሻምፒዮኗን ግብፅን ጨምሮ ኢትዮጵያ፤ ሌሶቶ፤ቦትስዋና፤ ቶጎ፤ ሴራልዮን፤ አንጎላ  እና ሱዳን በዚህ ዙር ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ብቸኛ አማራጭ ይሆንባቸዋል፡፡
ማርያኖ ባሬቶና ውጣውረዳቸውፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት የቆዩባቸው ያለፉት 6 ወራት ውጣውረዶች የበዙባቸው ነበሩ፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስንብት በኋላም የዋልያዎቹ ውጤታማነት እየወረደ መጥቷል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተከተለው ግልፅነት የጎደለው ቅጥራቸው በርካታ የስፖርት ቤተሰብ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ፌደሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያሳልፉ እና በወጣቶች ላይለማከናውናቸው ስራዎች መሰረታዊ ድጋፍ በመስጠት ያግዙኛል ያላቸውን ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በ2 ዓመት የቅጥር ኮንትራት ኃላፊነቱን ሰጥቷቸዋል፡፡ በወር 18 ሺ ዶላር የተጣራ ደሞዝ ይከፍላቸዋል፡፡ ባለፉት 6 ወራት ፌደሬሽኑ ለእኝህ አሰልጣኝ ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ውጭ እስከ 109ሺ ዶላር በደሞዝ ብቻ ከፍሏል 2.16 ሚሊዮን ብር አካባቢ ማለት ነው፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በማርያኖ ባሬቶ ሃላፊነት ከወደቀ በኋላ ውጤት ርቆታል፡፡ እስካሁንም ነጥብ ማስመዝገብ  ልተሳካለትም፡፡ ማርያኖ ባሬቶ ከማሊ ጋር የሚገናኙበት የዛሬው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድዬም ተመልካች ፊት ለሁለተኛ ጊዜ የሚያደርጉት የነጥብ ጨዋታ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሲሆን ከተሸነፈ ግን የአሰልጣኙን  ቆይታ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይከተዋል፡፡ የ57 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው

የቆዩባቸው 190 ቀናቶች ምንም ነጥብ አለማስመዝገባቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ ለዚህም የቀድሞው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሃላፊነቱ በቆዩባቸው 830 ቀናት የነበራቸው ስኬት ማስረጃ ይሆናል፡፡ በዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝነት 17 ጨዋታዎች ያደረጉት ሰውነት ቢሻው፣ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1.35 ነጥብ ይሰበስቡ ነበር፡፡ በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍም ከሜዳ ውጭ ደግሞ ነጥብ በመጋራት እና በማሸነፍ ሰውነት ቢሻው የተሻሉ ነበሩ፡፡በእርግጥ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የብሄራዊ ቡድኑን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ተሳትፎ በውጤታማ ጉዞ ለመጀመር ቢሳናቸውም በቆይታቸው አንዳንድ ምስጉን ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ የምድብ ማጣርያውን ከመጀመራቸው በፊት ከአንጎላ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲካሄድ ማስቻላቸው የመጀመርያው ውጤት ነው፡፡ ከዚያም ዋልያዎቹን ለ2 ሳምንት  ወደ ብራዚል በመውሰድ ልዩ አይነት ዝግጅት እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑን ልምድ እና ብራንድ በማሳደግ ስኬታማ ነበር፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ያሳዩት ቁርጠኛነት ተደንቆላቸዋል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ውጤታማ ተግባራት ዋና አሰልጣኙ በሃላፊነቱ በቆዩባቸው ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ጉዳዮች ከተጨዋቾች እና ከፌደሬሽኑ ያስቻላቸው ሁኔታዎች አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይህንኑ በተመለከተም ማርያኖ ባሬቶ በሁለቱ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ሽንፈቶች ከገጠማቸው በኋላ በተለይ ለሱፕር ስፖርት እና ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃናት ውጤታማ ስራ ላለማከናወን ምክንያቶች ናቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲገልፁ እና ሲተቹ ቆይተዋል፡፡ዋና አሰልጣኙ  በዝግጅታቸው የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ አላረካቸውም ነበር፡፡ በብዙዎቹ ተጨዋቾች የስራ ዲስፕሊን ላይ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ብዙዎቹ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ከስዊድን ከመጣው ዩሱፍ ሳላህ ብዙ መማር እንዳለባቸውም ሲመከሩ ሰንብተዋል፡፡ በሌላ በኩል አሰልጣኙ ከ2 ሳምንት በፊት ለሱፕር ስፖርት በሰጡት ማብራርያ ቡድናቸው በተጨዋቾች ጉዳት ክፍተት እንደበዛበት ተናግረው ነበር፡፡ በዚህም በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በአርቴፊሻል ሳር ላይ

የተሰራው  ልምምድ ሰበብ በመሆኑ ደስተኛ አይደለሁም በማለት ወቅሰዋል፡፡  በወቅቱ በአፍሪካ ዋንጫው 3ኛ የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ከማሊ ጋር አዲስ አበባ ላይ ከመደረጉ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ ተገኝቶ አቋም ለመፈተሽ አለመቻሉንም ክፉኛ አማርረዋል፡፡ በተያያዘ የማሊን ቡድን ለመገምገም የሚያስችል የጨዋታ ቪድዮዎችን በፌደሬሽኑም ሆነ በግል ጥረታቸው ለማግኘት ፈልገውም ስላልሆነላቸው ቅሬታ ነበራቸው፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ የመጫወቻ ቦታዎች ተጨዋቾችን ማጣታቸውን ሲነቅፉም ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ክለቦች የውጭ አገር ተጨዋቾችን በመቅጠራቸው ተተኪ ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነባቸውም በመግለፅ ነበር፡፡ለአልጄሪያና ማሊ የተሻለ ዕድል የሚያሳዩት የምድብ 2 ሁኔታዎች
ዛሬ ከማሊ ጋር በአዲስ አበባ ስታድዬም  ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሚደረገው የምድብ ማጣርያ 3ኛ ዙር ጨዋታ በፊት ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሁለት ያለምንም ነጥብ በ2 የግብ እዳ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ናት፡፡ አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያዎች መሪነቱን ስትይዝ፤ ማሊ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ ሁለተኛ እንዲሁም ማላዊ በ3 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በምድቡ የ3ኛ እና የ4ኛ ዙር ማጣርያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እና ማሊ በአዲስ አበባ እና በባማኮ፤ እንዲሁም በሌላ የምድብ 2 ጨዋታ ማላዊ እና አልጄርያ 
በብላንታየርና አልጀርስ ከተሞች የደርሶ መልስ ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ፡፡ኢትዮጵያ በምድብ ማጣርያው ሁለት ጨዋታዎች በሜዳዋ ላይ በአልጄርያ 2ለ1 ከተሸነፈች በኋላ  በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ከሜዳዋ ውጭ በማላዊ 3ለ2 ተረታለች፡፡ የዛሬ ተጋጣሚዋ የሆነችው የምእራብ አፍሪካዋ ማሊ በአንፃሩ  በመጀመርያ ጨዋታዋ ማላዊን 2ለ0 ብትረታም በሁለተኛው ጨዋታ በአልጄርያ 1ለ0 ተሸንፋ በምድብ ሁለት ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአልጄርያ እና በማላዊ ከደረሱበት ሽንፈቶች በኋላ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ከማሊ ጋር ለሚደረገው ወሳኝ የ3ኛ ዙር ማጣርያ ጨዋታቸው  23 ተጨዋቾችን በመጥራት  ከ10 ቀናት በላይ አሰርተዋል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ ብቸኛውን የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ ያደረገው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ለዋልያዎቹ ከፍተኛ ክፍተት የሆነው የሳላዲን ሰኢድ አለመኖር ነው፡፡ በግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ የመጀመርያውን የሻምፒዮናነት ክብር ለማግኘት የበቃው ሳላዲን ሰኢድ ለማሊው ጨዋታ አለመድረሱን በተመለከተ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አልሃሊ ከዛማሌክ ባደረጉት ጨዋታ ጉዳት የደረሰብት ሳላ እስከ ስድስት ሳምንት ከሜዳ መራቅ የብሄራዊ ቡድኑን አቅም ያዛባዋል፡፡  በውጭ አገር ክለቦች ይጫወቱ የነበሩት ያሉት ዩሱፍ ሳላህ፤ አሚን አስካር እና ዋሊድ አታ ብሄራዊ ቡድኑን በመቀላቀል ያለፉትን አምስት ቀናት ማርያም የሰሩት ይህን

ክፍተት ለመሸፈን ነው፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ አራት ተጫዋቾች አሰልጣኙም መቀነሳቸው አወያይቷል
የተቀነሱት አዳነ ግርማ፣ አሉላ ግርማ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና ግብ ጠባቂው ዮሃንስ በዛብህ ናቸው፡፡ እንደ ሱፐር ስፖርት ትንታኔ በዛሬው የኢትዮጵያና ማላዊ ጨዋታ በአማካይ መስመር ናትናኤል ዘለቀና ሽመልስ በቀለ ከጣሊያኑ የኤስ ሮማ ክለብ ተጨዋች ከሆነው ሰይዱ ኪዬቴ ጋር ይጋፈጣሉ፡፡ የዎልቨርሃምተኑ የክንፍ መስመር

ተጨዋች ባካሪ ሳኮ እና የፈርንሳዩ  ክለብ ቦርዶክስ አጥቂ የሆነው ቺዬክ ዲያቤቴ ለኢትዮጵያ ተከላካይ መስመር ፈተና እንደሚሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በአጥቂ መስመር ስኬታማውን ሳላዲን ሰኢድ አለማሰለፏ እንደሚጎዳት የገለፀው ሱፕር ስፖርት፤ በግብፅ ክለብ የሚጫወተው ኡመድ ኡክሪ እና በደቡብ አፍሪካ ክለብ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ የማሊ ተከላካይ መስመር ለማስከፈት ከፍተኛ ፈተና ይጠብቃቸዋል ብሏል፡፡  በሌላ በኩል የበረሃዎቹ ቀበሮዎች ከማላዊ ጋር በሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የምድብ 2 መሪነታቸከማሊ ጋር ያለውን ክፍተት ለማጥጭበብ በተለይ በሜዳቸው የሚደረገው ጨዋታ ወሳኝ ነው ዋልያዎቹ ከንስሮቹ ኢትዮጵያና ማሊ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም መገናኘታቸው ውጤቱን ለመገመት
አዳጋች አድርጎታል፡፡ ጎልዶትኮም አንባቢዎቹን በማሳተፍ በሰራው ትንበያ 67 በመቶ የማሸነፍ እድል የሰጠው ለኢትዮጵያ ሲሆን ማሊ 33 በመቶ ግምት ወስዳለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከማሊ ጋር በሚያደርጋቸው ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች  4 እና ከዚያም በላይ ነጥብ ካስመዘገበ በማጣርያው የሚኖረው ተስፋ

ያንሰራራል፡፡ በ3ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ በተለይ በዛሬው መሸነፍ ማለት ግን የሞሮኮን 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ህልም አበቃለት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያና ማሊ ሁለቱን የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን በአራት ቀናት ልዩነት ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ልምድ በሚያነስው የኢትዮጵያ ቡድን አቋም ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል፡፡የምድብ ማጣርያው ሲጀመር 23 ተጨዋቾችን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በትራንስፈር ማርኬት ድረገፅ የወጣለት የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ የዋጋ ግምቱ 725ሺ ዩሮ ነበር፡፡ ዋሊድ አታ እና አሚን አስካር ሰሞኑን ቡድኑን ከተቀላቀሉ በኋላ ግን ይህ ዋጋ ወደ 2.3 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አማካይ እድሜው 26.2 ዓመት ሲሆን በስብስቡ ያካተታቸው በውጭ አገር የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች ብዛት 9 ደርሷል፡፡ ንስሮቹ በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የማሊ ቡድን ባለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ሶስተኛ ደረጃዎችን አከታትሎ በመውሰድ በጠንካራ ልምድ እና ተሳትፎ ላይ ይገኛል፡፡ በሄነሪ ኳስፕርዧክ

የሚሰለጥነው የማሊ ብሄራዊ ቡድንን በአማካይ መስመር የሚጫወቱት አምበሉ ሰይዱ ኪዬታ እና ሞሃመድ ሲሶኮ እንዲሁም በአጥቂ መስመር የሚሰለፈውን ሞዲቦ ማይጋ መያዙና 4­-3-3 የአሰላለፍ ታክቲክ መከተሉ ወቅታዊ አቋሙን ያከብደዋል፡፡ 27 ተጨዋቾች ያሉበት የንስሮቹ ስብስብ 23 ከአገራቸው ውጭ የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን ያካትታል፡፡ በትራንስፈር ማርኬት ድረገፅ የወጣለት የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ የዋጋ ግምቱ  24.5 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን አማካይ እድሜው 25.6 አመት ነው፡፡ የማሊ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ልምድ ባለው እና የቡድኑ ዋናው አምበል በሆነው ሰይዱ ኪዬታ ብቻ ከኢትዮጵያ የላቀ ነው፡፡  በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እውቅና የተጎናፀፈው እና በርካታ ስኬቶች ያስመዘገበው የ34 ዓመቱ ሰይዱ ኪዬታ በፈረንሳይ ሊግ 1፤ በስፔን ላሊጋ፤ በቻይና ሊግና አሁን ደግሞ በጣሊያን ሴሪኤ ላለፉት 10 የውድድር ዘመናት

በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ  ነው፡፡ በመሃል አማካይ መስር የሚጫወተው ኪዬታ አሁን በጣሊያኑ ክለብ ሮማ ተዛውሮ እየተጫወተ ሲሆን በሳምንት 19ሺ ፓውንድ ይከፈለዋል፡፡ ነው፡፡ በትራንስፈር ማርኬት ድረገፅ በተገኘ መረጃ መሰረት ኪዬታ ከ5 አመት በፊት በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመኑ 16 ሚሊዮን ዩሮ ነበረ፡፡ አሁን ግን ግምቱ ወደ 1 ሚሊዮን ዩሮ ወርዷል፡፡ ከ2000 እኤአ ጀምሮ በማላዊ ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት 90

ጨዋታዎች አድርጎ 23 ጎሎች በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በባርሴሎና ስኬታማ ቆይታ የነበረው ኪዬታ ሁለት

የሻምፒዮንስ ሊግ፤ እና የላሊጋ ዋንጫዎችን ጀምሮ 14 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ታሪክ የሰራ ነው፡፡

           የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በሚገኝባት ሰሜን ኮሪያ፣ በተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን የስነ-ምግባር ጉድለት ለመቅረፍ ሲባል አዲስ የአጠቃቀም መመሪያ መውጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ ዮንሃፕ የተባለውን የሰሜን ኮሪያ የዜና ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ ከሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለቶች መካከል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ጮክ ብሎ ማውራትና መጨቃጨቅ ይገኙባቸዋል፡፡ አዲሱ የአገሪቱ የሞባይል አጠቃቀም የስነ-ምግባር መመሪያ እንደሚለው፣ ተጠቃሚዎች ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው በትህትና መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ በሞባይል ስልክ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን ለማስወገድ ሲባልም፣ የተደወለላቸው ሰዎች ጥሪያቸውን ሲመልሱ፣ ለደዋያቸው ማንነታቸውን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የደዋያቸውን ማንነት እንዳወቁ መግለጽም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ደዋዩ ራሱን ለማስተዋወቅ ጊዜ እንዳይፈጅ ያግዘዋል ተብሏል፡፡እ.ኤ.አ በ2008 የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነችው ሰሜን ኮሪያ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ አለማቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ክልክል ነው፡፡ የሞባይል ስልክ ባለቤት መሆን የሚችሉትም፣ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ (ባለፈው ሳምንት ለንባብ ባበቃነው በዚህ ዜና ላይ፣ ‘ደቡብ ኮርያ’ ተብሎ የቀረበው በስህተት በመሆኑ ከይቅርታ ጋር ዜናውን አስተካክለን አቅርበናል)

       በአሜሪካ አማካይ የህይወት ዘመን እ.ኤ.አ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መጨመር በማሳየት ወደ 78.8 ዓመት እንደደረሰ ኸልዝ ዴይ የአገሪቱ የፌደራል ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሰሞኑን ዘገበ፡፡ የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በአገሪቱ አማካይ የህይወት ዘመን ሊጨምር የቻለው ዜጎች ወደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመመለሳቸው ነው፡፡ “አሜሪካውያን ረዥም ዕድሜ እየኖሩ ሲሆን፣ ዘላቂ በሽታዎችን አስቀድሞ ስለመከላከል የተሻለ ግንዛቤ ጨብጠዋል” ብለዋል፤ የጥናት ሪፖርቱ ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ጂያኩዋን ዙ፡፡ “በህይወት የመቆያ አማካይ ዕድሜ የጨመረው ሰዎች ጤናማ ምግብ ስለሚመገቡና የአካል እንቅስቃሴ ስለሚሰሩ ነው” ብለዋል ዶክተሩ፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በህይወት የመቆየት አማካይ ዕድሜ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የተወለዱ የሴቶች በህይወት የመቆያ አማካይ እድሜ 81 ዓመት ሲሆን የወንዶች 76 እንደሆነ የሪፖርቱ አዘጋጅ ዶ/ር ዙ ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የነበሩ ሴቶች ተጨማሪ 20 ዓመት ገደማ ይኖራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ወንዶች ደግሞ 18 ዓመት ይኖራሉ ተብሏል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት፤ ከ2011 እስከ 2012 ባለው ጊዜ በአሜሪካ የሞት መጠን ከ1 በመቶ በላይ መቀነስ አሳይቷል፡፡ ለሞት የሚዳርጉ ዋና መንስኤዎች በሚል የሚታወቁት ነገሮች አሁንም አልተለወጡም ተብሏል፡፡ በ2012 ዓ.ም 75 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሞት የተከሰተው በልብ ህመም፣ በካንሰር፤ ዘላቂ በሆነ የታችኛው የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ በስትሮክ፣ በድንገተኛ ጉዳቶች፣ በመርሳት በሽታ፣ በስኳር፣ በኢንፍሉዌንዛና በሳንባ ምች፣ እንዲሁም በኩላሊት በሽታ እና ራስን በማጥፋት እንደነበር ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ከአስሩ ቀዳሚ የሞት መንስኤዎች በስምንቱ ላይ የሞት መጠን ከፍተኛ መቀነስ እንዳሳየ የሲዲሲ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ምክንያቱ ባይታወቅም ራስን ማጥፋት በ2012 ዓ.ም ከቀደመው ዓመት በ2.4 በመቶ እንደጨመረ ዶ/ር ዙ ተናግረዋል፡፡

በኒውዮርክ ሲቲ ሌኖክስ ሂል ሆስፒታል ውስጥ የልብ ህመምን በመከላከል ላይ የሚሰሩት ዶ/ር ሱዛኔ ስቴይንባም፤ “ዋናዎቹ የሞት መንስኤዎች የአኗኗር ዘይቤን ተከትለው የሚመጡ ናቸው፡፡ በመከላከልና በህክምና ረገድ የተሻለ ሥራ እያከናወንን ነው” ብለዋል፡፡ የተሻለ ምግብ መመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተርና ሲጋራ ማጨስ ማቆም ጤንነትን ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃዎች እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡በህይወት የመቆያ አማካይ እድሜ እንዲሻሻል ወይም እንዲጨምር የሚያደርገው ግን የተሻለ የህክምና ክብካቤ መኖር ነው ይላሉ - ዶ/ር ሱዛኔ፡፡ “በአብዛኞቹ የተለመዱት የሞት መንስኤዎች በአኗኗር ምርጫችን የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው” የሚሉት የህክምና ባለሞያዋ፤ አመጋገባችንንም ሆነ የአካል እንቅስቃሴያችንን ከተቆጣጠርን ብዙዎቹን ዋነኛ የሞት መንስኤዎች መከላከል እንችላለን” በማለት ያስረዳሉ፡፡ “‹ህክምና - ተኮር› ከመሆን ይልቅ ‹መከላከል - ተኮር› ብንሆን የህይወት ዘመንን በእጅጉ ማርዘም ይቻላል” ብለዋል፤ ዶ/ር ሱዛኔ ስቴይንባም፡፡

         “እኛ አገር የመፃፍ ክህሎት ያላቸው በርካታ ናቸው፤ እየፃፉልን ያሉት ጥቂቶች ቢሆኑም፡፡
እነዚህ ጥቂቶችም የመፃፍ አቅማቸውን ያህል አልሰጡንም ፤ ወይ ሰንፈዋል - ወይ ያልተመቻቸው ነገር አለ፡፡ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ ሰርቅ ዳ.፣ ሌሊሳ ግርማና መሰሎች ባላቸው ልክ /በዕድሜያቸው ልክ እንደማለት/ ብዙ ለማሳተምና ያላቸውን ለመስጠት የሚታትሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእርግጥ ካላቸው ተሰጥኦና አቅም አንጻር ያሳተሟቸው ሥራዎች ማነሳቸው የሚከነክኑን እንዳሉበትም ልብ ይሏል፡፡ አዳምን ግን በተለየ ዓይን እንየው፤ በብቃትና በጥራት ያለውን ያለስስት እየሰጠን ነው፡፡
 /በዓሉና አዳም ከሚመሳሰሉባቸው ነገሮች አንዱ፣በተከታታይ በጥራት መፃፋቸውና ያንንም ለህዝብ ማድረሳቸው

ነው፤ ከአስር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ከሰባት በላይ መጻህፍት ፅፈዋል፡፡/
አዳም ወደ ራሱ አብዝቶ የሚመለከት በመሆኑ ሰቅዞ ይይዛል፡፡
ለእኔ አዕምሮ የሚያክ ደራሲ ነው፤ የትዝታ ዘመኑን /ረጅም ጊዜ ውጭ ነውና እየኖረ ያለው/ በጥፍሩ ሲቧጥጥ፣

እኛም ባልኖርንበት ዘመን ትዝታችንንና ኑሮአችንን እንድንቧጥጥ ዕድል ይሰጠናል - አገናኝ ድልድይ በመሆን፡፡ አሰላሳይ ደራሲ ስለሆነ  የቃላት ጨዋታው ሁሉ ልቡና ላይ ነው - እያነበብከው አብረኸው ታሰላስላለህ፤ ኑሮህን፣ ዘመንህን፣ አገርህን!!
አዳም <<post modernism>> አፃፃፍ የገባው ነው፡፡
ከታሪክ አወቃቀርና ከመቼት ብሎም ከሴራ በላይ በድርሰቱ ይዞት የሚመጣው ቅርፅ የሚያሳስበውና ለእሱም

አብዝቶ የሚሳሳ ይመስላል፡፡ ቅርፅና አዳም ጋብቻ ፈፅመዋል - እንደሱ ገለፃ ‹‹የእንጀራ ቅርፅን›› አስተዋውቆናል፡፡ ይህ የራሱን መንገድ ይዞ የሚፈስ ቦይ ነው እንድንል ያስችለናል፡፡ በዚያ ወንዝ ውስጥ በተለይም ከ“ግራጫ

ቃጭሎች” እስከ አሁኑ “መረቅ” ድረስ ባለው ቅርፁ እከሌን  ይመስላል ለማለት ፊት አይሰጥም - አዳም በቃ አዳምን ይመስላል፡፡
 አዳም በሰው ኮቴ ላለመራመድ ያደረገው ፣ ከ“ግራጫ ቃጭሎች” በኋላ ተሳክቶለታል - በእኔ እምነት፡፡ አዳም የሰው ዳና አላዳመጠም፣ አዳም በራሱ መንገድና በራሱ ፋና ነው የነጎደው፤ በቋንቋና በሃሳብም ቢሆን ልቀቱ

ከፍታውን ይመስክሩለታል”
          - ደመቀ ከበደ  (ገጣሚ)


“የሥነፅሁፍን ሥራ ከማንም በላይ የሚፈትሸውና  የሚያቆየው ጊዜ ባለሟሉ ነው።  የአዳም መጻህፍት  ከጊዜ ጋር ለወደፊትም በአገራችን የሥነፅሁፍ ታሪክና አፃፃፍ ዘይቤ፣ የራሳቸው  ትልቅ ድርሻና ቦታ ይኖራቸዋል።አዳም «ህጽናዊነት» የሚል ስያሜ የሰጠው የራሱ የሆነ የአፃፃፍ ዘይቤ መፍጠር የቻለ ደራሲ ነው።  ይህም ጥቃቅንንም ሆኑ ግዙፍ ነገሮችን፣ ሰዎችን (ገፀ ባህሪያት)፣ ስሜቶችን፣ ሁኔታዎችን በማያያዝና በማዛመድ አንባቢዎች አእምሮ ውስጥ ትውስታና ትዝታም የሚጭር የአፃፃፍ ዘይቤ ነው። በታሪክ ይዘታቸው በጣም መሳጭና ወደ ራሳችን ውስጥ አስገብተን፣ እራሳችንን እንድንፈትሽና እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው።   አንዳንድ  የሴት ገፀ ባህርያቱ፣ የሴቶችን አስተሳሰብና  ባህሪያት በግልፅ (ሳይሸፋፍንና ሳያድበሰበስ)

የሚያሳዩ ናቸው።  ሴት ልጅ በወጣትነት እድሜዋ የሚያጋጥማትን  ስነልቦናዊ ፈተናዎችና ከባሕላችን ጋር ለመራመድ (ለመሄድ) የምታደርገውን ነገሮች--- አስመሳይነትን በግልፅ የምናይባቸው ገፀ ባህሪያት አሉ። ለምሳሌ “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ” ውስጥ “ (ሽልንጓ) የመጨረሻዋ የቀበሌ 01 ድንግል” ውስጥ ያለችው የነፃነት ገፀ ባህሪ፣ የሴት ልጅን  ሥነልቦናዊ  ፈተና  በደንብ ያሳየናል። በእኛ ሕብረተሰብ ውስጥ ሴት ልጅ “ጨዋና ጭምት” መሆን አለባት ተብሎ ይጠበቃል። “ጨዋ” ማለት ምን ማለት ነው? ይህን እንድንጠይቅና እንድንፈትሽ የሚያደርጉ ገፀ ባህሪዎች ናቸው። በ“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ውስጥ ያሉት እትዬ ወርቄ  ደግሞ አገር ወዳድነትን፣ እናትነትን፣ እማማ ኢትዮጵያን ራሷን የሚስልበት ገፀ ባህሪ ናቸው። ለዚህም ነው ጊዜና ዘመን የማይሽራቸው መፅሐፍት የሚመስሉኝ።
እነሆ አሁን ደግሞ 600 ገጾች ያሉት  ዳጎስ ያለ አዲስ ልብወለድ፣ «መረቅ» በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አቅርቧል።”
ሮማን ተወልደ ብርሃን ገ/ እግዚያብሄር (አድናቂ፣ ከለንደን)



አዳም ስለራሱ….
 “ስጽፍ አልለፋም!...”
 “አጣርቼ የማስወጣበት ወንፊት የለኝም!”
 (‘በስራዎችህ ከጥቃቅን ዝርዝሮች፣ የማይደፈሩ እስከሚመስሉ ነገሮች ደፍረህ ታወጣለህ፣ የገጸ ባህሪያቱን ውስጣዊ ስሜት፣ የማህበረሰቡን ህጸጾች ጨክነህ ታፍረጠርጣለህ…’ ተብሎ ሲጠየቅ፣የሰጠው ምላሽ)“ነገሮችን ማየት እወዳለሁ እንጂ አልንቀለቀልም፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮችን አልንቃቸውም፡፡ አያቸዋለሁ፡፡

እረፍት ሳገኝ ደግሞ፣ ተመልሼ በደንብ አያቸዋለሁ… የሚጻፉ መስለው ከታዩኝ፣ እጽፋቸዋለሁ!...”
 “When I want to write, I write!”
 (‘ለመጻፍ የሚያነሳሳህ ምን አይነት ሁኔታ ነው?’ ለሚል ጥያቄ የመለሰው)
“ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ውስጥ ያለችው ሰብለ ወንጌል፣ እንደ መልዓክ ናት - ከሰው ይልቅ ለመልዓክት የቀረበ

ባህሪ የተላበሰች፡፡ እኔ የሞከርኩት፣ ሰብለን ‘ሰው’ ሆና እንድትታይ ለማድረግ ነው!...”
.“Mezgebu is just living. He knows nothing about precision and the like.”
(ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደራሲ አዳም ረታ፣ ከአድናቂዎቹ ጋር በተገናኘበት የቡና ስነስርዓት ላይ ከተናገረው የተወሰደ)

          የመውለድ አቅምን ይቀንሳል ተብሏል የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ወንዶች የዘር ፍሬያቸው በመጠንና በጥራት እንደሚቀንስና በመውለድ አቅማቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ጥናት አመለከተ፡፡ “ብዙ ጥናቶች የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መውሰድ በአጠቃላይ ለጤና እንደማይበጅ አረጋግጠዋል፡፡ አልኮል በመጠኑ መውሰድ በሥነተዋልዶ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የሚያሳይ ጥናት እምብዛም የለም” ይላሉ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ማይክል ኢሰንበርግ፡፡ በሳምንት 40 ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ወንዶች የዘር ፍሬያቸው እጅግ በጣም እንደሚቀንስ ጥናቱ ቢያረጋግጥም፤ ጥናት አድራጊዎቹን ያስገረማቸው ሌላም ነገር አለ፡፡ በሳምንት አምስት ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ (ቢራ ወይም የወይን ጠጅ ሊሆን ይችላል) ብቻ የሚጠጡ ወንዶች ላይም ተመሳሳይ ችግር እንደተስተዋለ በሳውዘርን ዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ቲና ኮልድ ጄንሰን ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ አካሄድ የተነሳ በወንዶቹ የዘር ፍሬ ላይ የታየው ለውጥ በአልኮል መጠጡ ሳቢያ የመጣ ይሁን አይሁን ለማወቅ አልተቻለም ይላሉ - አጥኚዎቹ፡፡ “ለዘር ፍሬው በቁጥርም ሆነ በጥራት መቀነስ እንደ ምግብ፣ ሲጋራ፣ የሰውነት ክብደት ወዘተ… ያሉ ሌሎች ነገሮች ጋር ለማያያዝ ብንሞክርም ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር አላገኘንም፡፡ ችግሩ ከአልኮል መጠጣት ጋር በተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ሊከሰት ይችላል የሚለውን ግን ውድቅ አላደረግነውም” ብለዋል ጄንሰን፡፡ ጥናቱ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የጤና ምርመራ ያደረጉ ከ1 ሺ 200 በላይ የዴንማርክ ወጣት ወንዶችን ያካተተ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 28 የሚደርስ ነው፡፡ የአልኮል መጠጥ ልማዳቸውን የተመለከተ መጠይቅ እንዲሞሉ ከመደረጋቸውም በተጨማሪ የዘር ፈሳሽ ናሙናና ደም ሰጥተዋል፡፡

ከምርመራው በተገኘው ውጤትም በየሳምንቱ አንድ ብርጭቆ አልኮል ከሚጎነጩት ይልቅ በየሳምንቱ አምስት ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ የሚወስዱት የዘር ፍሬያቸው በመጠንም፣ በጥራትም፣ በጤነኝነትም እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በሳምንት ቢያንስ 25 ብርጭቆ አልኮል የሚጨልጡ ወንዶች፤ የዘር ፍሬያቸው በመጠንም ሆነ በጥራት በእጅጉ ያሽቆለቆለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሳምንት 40 ወይም ከዚያ በላይ በሚጠጡ ወንዶች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ በሳምንት እስከ 5 ብርጭቆ ድረስ ከሚጠጡት በ33 በመቶ ያነሰ የዘር ፍሬ ይዘት እንደነበራቸው ታውቋል፡፡ “ብዙ ወንዶች ዝምተኛ ጠጪዎች ናቸው፤ ይሄ ባህርያቸው እንደሚጎዳቸው ግን አይገነዘቡም፡፡ ዝምተኝነታቸው ከሚፈልጉት በላይ እንዲጠጡ ያደርጋቸዋል” ያሉት ደግሞ በሂዩስተን በሚገኝ ሆስፒታል የማህጸንና የወሊድ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማይክል ኸርድ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ስካር ሆርሞኖችንና በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኬሚካሎችን (ኮርቲሶል፣ ግሉኮስ፣ ኢንሱሊንና የወንድ ሆርሞን) እንዲለወጡ ያደርጋቸዋል፡፡ “እኒህ ሁሉ የዘር ፍሬ ጥራት ላይ ችግር ያስከትላሉ፤ ጥራቱ ዝቅ ያለ የዘር ፍሬ ደግሞ ፅንስ የማፍራት ሂደቱን ሊያስተጓጉለው ይችላል” ብለዋል ኸርድ፡፡