Administrator

Administrator

  • በአሜሪካ፣ በፈረንሳይና ቤልጂየም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነበራቸው
  • የ25 ሚሊዮን ዶላር ባለፀጋ ነበሩ - ወደ ቢሊዬነርነት ተጠግተዋል    
  • ቤተ-መፅሃፋቸው ራሳቸው ባሰባሰቡት 10ሺ መፃህፍት የተሞላ ነበር

በሳምንቱ ማጠናቀቂያ ግድም “ጮማ” የሆነ መረጃ እጄ ገባ፡፡ አንድ ወዳጅ ነው መረጃውን ከባህር ማዶ በኢሜይል ያሻገረልን፡፡ The New York Times የዛሬ 105 ዓመት፣ አፄ ምኒልክ ሲሞቱ ነው ዘገባውን ያወጣው - ኖቨምበር 7 ቀን 1909 ዓ.ም፡፡ “ንጉስ ምኒልክ እዚህ ኢንቨስትመንት አላቸው” በሚል ርዕስ የቀረበው ፅሁፍ፤ከአቢሲኒያ የተመለሰውን የቤልጂየም አሳሽ ባሮን ዲ ጃርልስበርግ ቃለመጠይቅ በማድረግ የተጠናቀረ እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ ይገልፃል፡፡ የሚታወቁትን ታሪኮች እየዘለልኩ “ጮማ ጮማ” የሆኑትን መረጃዎች ነው የማቀብላችሁ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ከመዘጋቱ በፊት በዚህ በአዲሱ የአፄ ምኒልክ ታሪክ ላይ ትንሽ ጥናትና ምርምር ቢያካሂድ ትክክለኛው ታሪክ (ያልተጭበረበረው ማለቴ ነው!) ለትውልድ ይሸጋገራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “የለም! የአፄ ምኒልክን ጉዳይ አጥንቼ ፋይሉን ዘግቻለሁ” የሚል ከሆነም እንዳሻው፡፡ የኒውዮርክ ታይምስ መረጃ ግን የሚያወላዳ ዓይነት አደለም፡፡ ለመሆኑ እኚህ የጥቁር ህዝብ ኩራት፣የአድዋ ጀግና-----አዳዲስ ገድሎች ምን ይሆኑ? (የተጭበረበርነው ታሪክ ማለት ነው!)
ባሮን ዲ ጃርልስበርግ ለጋዜጣው እንደተናገረው፤ ምኒልክ ከሌሎች የአህጉሪቱ ነገስታት ጨርሶ የተለዩ መሪ ነበሩ፡፡ በዲፕሎማትነት፣ በኢንቨስተርነት (ፋይናንሰር)፣ በተዋጊነት የሚስተካከላቸው አልነበረም፡፡ በተዋጊነትና በዲፕሎማትነት ያላቸውን ብቃትና ዋጋ ያስመሰከሩት ጣልያን በአቢሲኒያዎች ድል በተነሳች ወቅት ነበር ይላል - ጃርልስበርግ። በመጨረሻዎቹ የንግስና ዘመናቸው ግን ምኒልክ ይበልጥ   በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው እንደታወቁ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡  
የንግስና ዘውድ ከመድፋታቸው ቀደም ብሎ በወጣትነት ዘመናቸው የኢንቨስትመንት ዝንባሌ እንደነበራቸው የሚያስታውሰው ዘገባው፤በዚያ እድሜያቸው በፈረንሳይና ቤልጂየም የማዕድን ማምረቻዎች ውስጥ ቀላል የማይባል መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው ነበር ይለናል፡፡ ከንግስናቸው በኋላ ግን አገር በማስተዳደር ሥራ በመወጠራቸው ከኢንቨስትመንቱ ተስተጓጉለው እንደነበር የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
“ዛሬ የአቢሲኒያው ገዢ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማስፋፋት በአሜሪካ የባቡር ሃዲድ ሥራ ላይ ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ አላቸው” ሲል አሳሹ የንጉሱን ወቅታዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ገልጿል፡፡
አፄ ምኒልክ በአሜሪካ እንዲሁም በፈረንሳይና ቤልጂየም ያላቸው አክስዮንና ኢንቨስትመንት ሲደማመር ከ25 ሚሊዮን ዶላር የማያንስ የግል ሃብት እንደነበራቸው ይገመታል ብሏል- አሳሹን ጠቅሶ የዘገበው ጋዜጣው፡፡   
“እኚህን ጥቁር የአቢሲኒያ ገዢ በተመለከተ በእጅጉ የሚያስደንቀው ጉዳይ ሁለ-ገብነታቸው ነው” ሲል የሚያደንቀው የቤልጂየሙ አሳሽ፤ንጉሱ የተዋጣላቸው ቋንቋ አዋቂ ነበሩ ይላል - ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛና ጣልያንኛ አቀላጥፈው ይናገሩ እንደነበር በመጥቀስ፡፡ ሁለመናቸውን ለአገራዊ ጉዳዮች ለመስጠት ቢገደዱም አዲስ የወጡ የአውሮፓ የስነጽሑፍ ስራዎችን ለመቃኘት ግን ጊዜ አያጡም የሚለው ጃርልስበርግ፤ ብዙ ጊዜ አዲስ የአውሮፓ ደራሲ ስም ሲጠቀስ እምብዛም አይደናገራቸውም ነበር ብሏል፡፡
እሳቸውን ከሁሉም በላይ የሚያኮራቸው ራሳቸው ባሰባሰቧቸው 10ሺ መፃሕፍት የተደራጀው ቤተመፅሃፋቸው ሲሆን መፃህፍትን በተመለከተ ዋነኛ ትኩረታቸው በአፍሪካና በእስያ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ላይ የሚያጠነጥኑ ሥራዎች ነበሩ ይላል - ለኒውዮርክ ታይምስ ምስክርነቱን የሰጠው ባሮን ዲ ጃርልስበርግ፡፡ ለካስ ምኒልክ ወደው አይደለም-- ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥልጣኔ፣ ዘመናዊ አስተዳደር ወዘተ----ሲሉ የኖሩት፡፡ (የንጉሱን ታሪክ ተጭበርብረናል!?)  

        አንዳንድ ዕውነቶች ሲያረጁ ተረት ይመስላሉ፡፡ ትምህርትነታቸው ግን ዘመን - ተሻጋሪ ነው፡፡ ባለፈው ዘመን አንድ ሰው ጐረቤቱን በፖለቲካ ሰውነት (በመንግሥት ወጋኝነት) ይጠረጥረዋል፡፡ በጣም ስለሚፈራውም ስለሆነም ግራ ቀኙን እያጣራ ነው መንገድ የሚሄደው፡፡ ሲወጣ ሲገባ ባየው ቁጥር እየተሸማቀቀ ነው የሚያልፈው፡፡ ጐረቤትየው ኮስታራ ነው፡፡ ግን ሰው ቀና ብሎ አያይም፡፡ ልጆቹ ከልጆቹ ጋር ሊጫወቱ ሲመጡ፤ “እናንተ ልጆች አርፋችሁ ቤታችሁ ተቀመጡ፡፡
ኋላ ጣጣ ታመጡብኛላችሁ!” እያለ ይቆጣቸዋል፡፡
የልጆቹ ኳስ ጐረቤትየው ግቢ ከገባ፤ ጭንቅ ነው፡፡
“ይሄዋ እንደፈራሁት መዘዝ ልትጐትቱብኝ ነው!” ብሎ ያፈጥባቸዋል፡፡ ሚስት ትሄድና ኳሱን ታመጣለች፡፡ ጐረቤታሞቹ ሚስቶች ቡና ይጠራራሉ፡፡
ይሄኛው ባል፤ “ኋላ ነግሬሻለሁ፡፡ አፍሽን ሰብስበሽ ተቀመጪ ምን ፍለጋ ቡና እንደሚጠሩሽ አይታወቅም” እያለ ያስጠነቅቃታል፡፡
“ኧረ እኛ ምንም የፖለቲካ ነገር አናወራም፡፡ ሞኝ አደረከን እንዴ” ትለዋለች ሚስት፡፡
ባል፤  “አሄሄ አይምሰልሽ! ዛሬ ሣር - ቅጠሉ የሰው አፍ ጠባቂ ነው፡፡ ይቺ ሴትዮ እያዋዛች እንዳታወጣጣሽ!”
ሚስት፤
“ቆይ፤ መጀመሪያ ነገር፤ እኔ ምን አለኝና ነው እምታወጣጣኝ? ምን የደበኩት ፖለቲካ አለኝ?”
ባል፤
“እኔ አላውቅልሽም ወዳጄ! ብቻ ጠንቀቅ ነው!” ይላትና ይወጣል፡፡
አንድ ቀን እዚሁ ጐረቤት ጠበል ተጠሩ፡፡
ሚስት ለባሏ፤
“ጠበል ተጠርተናል ጐረቤት፡፡ እንሂድ?”
ባል፤ “አልሄድም” ይላል፡፡
ሚስት፤ “አክብረው ጠርተውሃል ምናለ ብትሄድ” ብላ ትሞግተዋለች፡፡
ባል፤ “አልሄድም ብያለሁ አልሄድም”
“እሺ፤ ለምን ቀረህ ቢሉኝ ምን እመልሳለሁ?”
“ትንሽ አሞት ተኝቷል በያቸው በቃ” አለ ቆጣ ብሎ፡፡
ሚስት ሄደች፡፡ ባል ቀረ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ አጋጣሚ ሆኖ ባል ወደ ሥራ ሊሄድ ውይይት ላይ ተሳፍሯል፡፡ ጫፍ በሩጋ ነው የተመቀመጠው፡፡
ጐረቤትየው በዛው ታክሲ ሊሳፈር ይመጣል፡፡ ሳያስበው እግሩን ረግጦት ይገባል፡፡
ይሄኔ ባል ወደሰውዬው ዞር አለና፤
“ወንድሜ የከፍተኛ ሊቀመንበር ነህ እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
“አይደለሁም” ይለዋል ጐረቤትዬው፡፡
“የቀበሌ ሊቀመንበር ነህ?”
“አይደለሁም”
“የአብዮት ጥበቃስ?”
“አይደለሁም”
“እሺ ካድሬ ነህ?”
“አይደለሁም”
“ታዲያ ምናባክ ያራግጥሃል? ና ውጣ ከፈለክ ይዋጣልን!”
“ኧረ ወዳጄ እኔ ምንም ጠብ ውስጥ የምገባ ሰው አይደለሁም፡፡ አሁን የጠየከኝን ሁሉ አንተ ነህ ብዬ ስንት ዘመን ስሰጋና ስፈራህ ኖርኩኮ!” አለው፡፡
*    *    *
ጥርጣሬ ቤቱን የሠራበት ማህበረሰብ ደስተኛና በተስፋ የተሞላ አይሆንም፡፡ መጠራጠርና መፈራራት ባለበት ቦታ ግልጽነት ድርሽ አይልም፡፡ አሜሪካዊው የንግድ ሰው ማክዳግላስ “ጭምት ነብሶችን ትናንሽ ጥርጣሬዎች ለውድቀት ይዳርጓቸዋል፡፡ ጠባብ አመለካከት ያለው፤ ፍርሃት የወረረውና አመንቺ ህብረተሰብ ሽንፈቱን ያረጋገጠ ነው” ይለናል፡፡
“ጠርጥር” የሚል ዘፈን በሚያስደስተው ህብረተሰብ ውስጥ እርግጠኝነትን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ይሄ ሥር ከሰደደ ደግሞ መድሐኒት አይገኝለትም፡፡” በሽታው ሥር-የሰደደ ከሆነ ሞቱንም መዳኑንም መተንበይ አስተማማኝ አይደለም” ይለናል የግሪኩ የህክምና አባት፤ ሒፖክ ራተስ፡፡
ጥርጣሬ የበዛበት ማህበረሰብ አገር ለመገንባት አስተማማኝ ኃይል አይሆንም፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማበልፀግ ይከብደዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ድርጊት ጀርባ አንድ ጥርጣሬ እየኖረን ወደፊት መራመድ አይቻልም፡፡ ግልፅነት ከሌለ ዴሞክራሲ ደብዛው ይጠፋል፡፡ ኢፍትሐዊነት ይነግሣል፡፡ ሙስና ያጥጣል፡፡ ሚስጥራዊነት ያይላል፡፡ በመጨረሻም፤ “በልቼ ልሙት!” መፈክር ይሆናል!! በሀገራችን ታሪክን እንኳ በጥርጣሬ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የተዘመረላቸው አሉ፡፡ ያልተዘመረላቸው አሉ፡፡ እየተዘመረላቸው የማይታወቁ አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰላሌው ጀግና አቢቹ፡፡ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደፃፈው “ይቺ አንድ ፍሬ ደጃዝማች! ከኛ በላይ ጀብዱ እየሰራች መሆኑን እንሰማለን!” አሉ አሉ ጃንሆይ፤ ስለ አቢቹ ሲናገሩ፡፡
“አቢቹ ነጋ ነጋ …. ቆሬን ሲወራኒኒ
ለቺቱ ነጋ ነጋ …… አምቱን ሲላሊኒ”
አቢቹ ሰላም ሰላም
አቢቹ እሾህ አይውጋህ
አቢቹ ክፉ አይይህ
አቢቹ ዐይን አያይህ” እንደማለት ነው፡፡
ይህ የተዘፈነው ለአቢቹ ነው፡፡ ዛሬም ይዘፈናል፡፡ ግን አቢቹን ሰው አያውቀውም “ዛሬ አዝማሪው ሳይቀር ስለራሶች ጀግንነትና ስለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅነት፤ ማንጎራጎሩን ርግፍ አድርጎ ትቶታል…” ይለናል ያው ፀሐፊ፡፡ ልብ ያለው ግን የለም፡፡ ምናልባት የነገሥታቱ
ጀግኖች እንዲወደሱ ሆን ተብሎም ታሪክ ተጋርዶ ይሆናል፡፡ ይሄም ያው ጥርጣሬ ነው፡፡
ስለመሪዎች ትተን ስለህዝብ ወይም ስለህዝባዊ ጀግኖች እንዘምር ነው ነገሩ፡፡
ያልነቃ ህብተረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዕውቀትና በትምህርት ያልዳበረ ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ የማይተማመኑ ፖለቲከኞች ያሉትና የሚመሩት ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዚህ ላይ ከፖለቲካው ሥርዓት ጋር አለመግባባት ከተጨመረበት ጨርሶ ማበድ ነው፡፡ “ማሰብም ሊገታ ይችላል” እንዳለው ነው ቲዮዶር አዶርኖ-የጀርመኑ ፈላስፋ፡፡ “አንበሳና የበግ ግልገል አብረው ሊተኙ ይችላሉ፡፡ ችግሩ የበግ ግልገሏ እንቅልፍ አይኖራትም” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ እንደተጠራጠረች መንጋቱ ነው ማለታቸው ነው፡፡
ከጥርጣሬ የምንወጣው ዕውነቱን በማወቅ ነው፡፡ መረጃዎች በቀጥታ ሲደርሱ ነው፡፡ መረጃ ሲጠራ ዕውነት ማየት ይጀመራል፡፡ ካልጠራ ጎሾ ያጎሸናል፡፡ የተማሩ ያስተምሩ፡፡ የነቁ ያንቁ፡፡ ያወቁ ያሳውቁ፡፡ “አውራ ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስም” የሚባለውን ልብ እንበል፡፡

4 የጥንቃቄ ምክሮች - ለመንግስትና ለኢህአዴግ

       አለማችን፣ ከዳር ዳር እየተናጠች ግራ ግብት ብሏታል። የነ ግብፅ እና ሶሪያ እልባት ሳያገኝ፤ ውዥንብር የበዛበት የዩክሬን ትርምስ ተጨመረበት። የዘመናችንን ቀውስ ፍንትው አድርጎ በሚያሳየው የዩክሬን ትርምስ ውስጥ፣ ዋናዎቹ ተዋናዮች አንጋፋ ፖለቲከኞችና ትልልቅ ፓርቲዎች አይደሉም። በሃይማኖትና በቋንቋ ዩክሬንን ለሁለት መሰንጠቅ የጀመሩት ሁለት ነውጠኛ ቡድኖች፤ ከጥቂት ወራት በፊት እንኳን በአለም ደረጃ እዚያው ዩክሬንና ራሺያ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተደማጭነትና ታዋቂነት አልነበራቸውም። “ናሽናል ሶሻሊዝም” በተሰኘው የፋሺዝም ቅኝት እንደ ሞሶሎኒና እንደ ሂትለር “ከራስህ በፊት ለእናት አገርህ” እያሉ የሚዘምሩት ሁለቱ ቡድኖች፤ “አገር ትቅደም። ለአገር መስዋዕት ሁኑ፡፡ የሚል መፈክር ያስተጋባሉ። አንደኛው ቡድን፣ “ለራሺያ መስዋዕት ሁኑ” ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ “ለዩክሬን መስዋዕት ሁኑ” እያለ ዘረኝነትንና የሃይማኖት ጥላቻን በጭፍን ስሜት  እያራገቡ በርካታ አመታትን አስቆጥረዋል - ድጋፍ ባያስገኝላቸውም።
እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፣ የዩክሬንን አመፅ የመራው የ42 አመቱ ዲሚትሮ ያሮሽ፣ ከመምህራን ኮሌጅ የተመረቀ ከመሆኑ በቀር ያን ያህልም የሚታወቅ ታሪክ የለውም። ከአመታት በፊት በያሮሽ የተመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ፣ ቀኝ ዘርፍ በሚል ስያሜ ያቋቋመው ነውጠኛ ቡድን የፓርላማ ወንበር የላቸውም። ፓርቲው በምርጫ ቢወዳደርም አልተሳካለትም። አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ያሮሽ የአገሪቱ የፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ከመሆኑም በላይ፤ የቡድኑ አባላት የዩክሬን አለኝታና የቁርጥ ቀን ልጆች ስለሆኑ ትጥቅ አይፈቱም ብሏል - በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት እንደማለት ነው።
በብዛት የራሺያ ቋንቋ የሚናገሩ ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎችን የያዘችው ክሬሚያ፣ ከዩክሬን እንድትገነጠልና ወደ ራሺያ እንድትጠቃለል አመፅ ያካሄደው ሁለተኛው ቡድንም ተመሳሳይ ነው። በክሬሚያ ምክር ቤት ውስጥ ከ3 ወንበር በላይ ይዞ እንደማያውቅና ባለፈው ምርጫ ያገኘው ድምፅ አራት በመቶ ገደማ ብቻ እንደሆነ የታይም መፅሄት ዘገባ ገልጿል። የቡድኑ መሪ ሰርጌ አክስዮኖቭ ከታዋቂ የክሬሚያ ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ የሚጠቀስ አልነበረም። ታዋቂ ለመሆን ስላልሞከረ አይደለም። ክሬሚያ ከዩክሬን እንድትገነጠል የሕግ ረቂቅ ለምክርቤቱ በማቅረብ ዝና ለማትረፍ በተደጋጋሚ ሞክሯል - ለበርካታ አመታት። ግን ከቁም ነገር የቆጠረው ሰው አልነበረም። በቅርቡ ነው፤ ሌላ መላ የፈጠረው።
ካለፈው ጥር ወር ወዲህ፣ ከየቦታው ወጣቶችን እየመለመለ ማሰባሰብ የጀመረው አክስዮኖቭ፣  ወደ ጠረፍ አካባቢ እየወሰደ ታጣቂ ቡድን ሲያደረጅ ከርሟል። ብዙም አልቆየም። ከሁለት ወራት በኋላ ዩክሬን ስትቃወስ፣ አክስዮኖቭ ለታጣቂዎቹ የዘመቻ ትዕዛዝ አስተላለፈ። እናም ስራቸውን ሰሩ። የክሬሚያ ምክር ቤትን ወረሩትና ሁለት የአዋጅ ረቂቆች ቀረቡ። አዳራሹን ከሞሉት ሰዎች መካከል፣ የትኞቹ የምክር ቤት አባል እንደሆኑ፣ የትኞቹ ደግሞ የታጣቂ ቡድን አባል እንደሆኑ የሚታወቀው፤ መሳሪያ በመታጠቅና ባለመታጠቅ ብቻ ነው። አዋጅ ለማፅደቅ ድምፅ የሰጡት የትኞቹ እንደሆኑ ግን አይታወቅም። በአንደኛው አዋጅ፣ ክሬሚያ ከዩክሬን እንድትገነጠል በህዝብ ለማስወሰን ምርጫ ይካሄዳል ተባለ። በሁለተኛው አዋጅ ደግሞ፣ የ32 አመቱ አክስዮኖቭ፣ የክሬሚያ ፕሬዚዳንት ሆኖ ስልጣን ያዘ። ፓርቲው በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉት ወንበሮች ሶስት ብቻ ቢሆኑም፤ በሺ የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ስላሰማራ፣ ከፍተኛውን ስልጣን ተቆጣጠረ። በዚህ ምክንያት የሚሰነዘሩበትን ትችቶች በማጣጣል፣ “በወቅቱ ግርግር ስለነበር ምንም ማድረግ አይቻልም” የሚለው አክስዮኖቭ፤ “ሃላፊነት የሚወስድ ሰው ጠፋ። ስለዚህ ለአገሬ መስዋዕት ለመሆን ታሪካዊ ሃላፊነት ተረከብኩ” ብሏል።
የዘር እና የሃይማኖት ልዩነትን የሚያራግቡት ሁለቱ ቡድኖች፣ ከተወሸቁበት ጉራንጉር ወጥተው እንዲህ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ገናና ለመሆን የበቁት ታጣቂ ቡድን በማደራጀታቸው አይደለም። ከሌሎች ፓርቲዎች ያን ያህል የተለየ የፖለቲካ አቋም ስላላቸውም አይደለም። አንጋፋዎቹና ትልልቆቹ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ “የናሽናል ሶሻሊዝም” አስተሳሰብን የሚከተሉ ናቸው። የዩክሬን ገዢ ፓርቲ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ማየት ትችላላችሁ - “አባት አገር” ይባላል። የራሺያ ገዢ ፓርቲ ደግሞ “አንዲት ራሺያ” ይሰኛል። “ብሄረተኝነት” ወይም “አገራዊነት” የሚባለው የፋሺዝም ቅኝት፣ “እያንዳንዱ ሰው፣ ከራሱ ጥቅምና ከራሱ ሕይወት በፊት፤ ከግል መብቱና ከነፃነቱ በፊት ለአገሩ፣ ለብሔሩ፣ ለጎሳው ቅድሚያ መስጠትና መስዋዕት መሆን አለበት” የሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ የተለየ አዝማሚያ አላቸው የሚባሉት ሌሎቹ ፓርቲዎች፤ በአብዛኛው የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም እንጥፍጣፊዎች ናቸው - “እያንዳንዱ ሰው ከራሱ ሕይወትና ከግል ነፃነቱ በፊት፤ ለድሆች፣ ለጭቁኖችና ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠትና መስዋዕት መሆን አለበት” የሚለውን ሃሳብ ያዘወትራሉ።
“ናሽናሊስቶቹ” እና “ሶሻሊስቶቹ” ያን ያህልም በሃሳብና በስሜት የሚራራቁ አይደሉም። ሁለቱም በጋራ፣ “የግለሰብ ነፃነትና መብት” የሚባለውን ነገር ይጠላሉ። አንደኛው ወገን፤ “ለአገር ወይም ለብሔር ብሔረሰብ ጥቅም ቅድሚያ እሰጣለሁ” በሚል መፈክር፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ “ለጭቁን ሕዝብና ለድሆች ጥቅም ቅድሚያ እንሰጣለሁ” በሚል ሰበብ፤ የሰውን መብትና ነፃነት መርገጥ እንደሚቻል ያምናሉ። ይህ ብቻ አይደለም ተመሳሳይነታቸው። የትኛውን ሰበብና መፈክር ያዘወትራሉ ብለን ልንለያቸው ካልሞከርን በስተቀር፤ አንዱ የሌላኛውን መፈክር ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም። ዘረኝነትንና ብሔረተኝነትን በማራገብ የሚታወቁት ሂትለርና ሞሶሎኒ፣ ለሰፊው ሕዝብና ለድሆች በአለኝታነት የምንቆም ሶሻሊስቶች ነን ይሉ አልነበር? በሰፊው ሕዝብና በድሆች ስም የሚምሉ የሚገዘቱ የዩጎዝላቪያ ሶሻሊስቶችም በተራቸው፤ ዘረኝነትንና ብሄረተኝነትን በማጦዝ አገሪቱን ሰነጣጥቀው በደም አጨቅይተዋታል። የእያንዳንዱን ግለሰብ መብትና ነፃነት ለማክበር ፍላጎት የሌላቸው እነዚሁ ቅኝቶች፤ “የሕዝባዊነት አስተሳሰብ ተከታይ” (collectivist) የሚል የጋራ ስያሜ ሊሰጣቸው ይችላል። በራሺያም ሆነ በዩክሬን፣ ትልልቆቹና አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች የዚህ አስተሳሰብ ምርኮኞች ናቸው - እያንዳንዱ ሰው፤ ምንም አይነት ነፃነት የሌለው የሕዝብ ሎሌ ወይም አገልጋይ ባርያ መሆን ይገባዋል ብለው የሚያምኑ። እያንዳንዱ ሰው የሕዝብ ሎሌ መሆን አለበት ሲባል፤ በሌላ አነጋገር የመንግስት ሎሌ፤ እናም የገዢው ፓርቲ ሎሌ ይሆናል እንደማለት ነው።
እንደዚያም ሆኖ፤ በሃሳብ ደረጃ “ሕዝባዊነት”ን የሚሰብኩ የዘመናችን ብዙ ፓርቲዎች፤ በተግባር የምኞታቸውን ያህል መሄድ አይችሉም፤ እንደ ሞሶሎኒና ሂትለር ወይም እንደ ሌኒንና ስታሊን፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የፋሺዝም ወይም የሶሻሊዝም ስርዓት ለማስፈን አይደፍሩም። ለምን? ሕዝባዊነት፣ በ20ኛው ክፍለዘመን ምን ያህል እልቂትና ስቃይ፣ ምን ያህል ድህነትና ረሃብ እንዳስከተለ ስለሚታወቅ፤ አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክ ወይም የማነሳሳት ሃያልነቱ ሞቷል። ስለዚህ፤ የዩክሬን ትልልቅ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሕዝባዊነትን የሚሰብኩ አብዛኞቹ የዘመናችን ፓርቲዎች፣ በሙሉ ልብ ሃሳባቸውን ተንትነው ቢያቀርቡ ሆ ብሎ የሚከተላቸው አያገኙም፤ ሃሳባቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉትም በግማሽ ልብ ነው። የአስተሳሰባቸውን ያህል የሰውን ምርትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ ባይወርሱም፤ መንግስት እለት በእለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ እየገባ በአላስፈላጊ ቁጥጥሮችና ገደቦች የሰዎችን ኑሮ እንዲያናጋ ያደርጋሉ፡፡ በተለያዩ የቀረጥና የታክስ አይነቶች የሰውን ኪስ ያራቁታሉ። የስብከታቸውን ያህል ጭልጥ ብለው ባይገቡበትም፣ በመጠኑ ዘረኝነትን ያራግባሉ። በአጭሩ ስብከታቸውና ድርጊታቸው ይለያያል። ቆጠብ ለማለት ይሞክራሉ።
አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች ችባ ሆነዋል ቢባል የተጋነነ አይደለም። “የሕዝባዊነት” አስተሳሰባቸውን ተንትነው እንዳያቀርቡ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን የሞተ አስተሳሰብ ነው። በስሜት ደረጃ እያግለበለቡ እንዳይሰብኩም መዘዙን እየፈሩ ቆጠብ ይላሉ። ከትንታኔም ሆነ ከስሜት አንዱንም ሳይሆኑ ይቀራሉ። ሁለቱ መናኛና ነውጠኛ ቡድኖችም ወደ ትንታኔ የመግባት ዝንባሌ የላቸውም። ነገር ግን፤ ጭፍን ስሜት ከማግለብለብ ቆጠብ የማለት ፍላጎት የላቸውም። ጭልጥ ብለው ዘረኝነት ውስጥ ገብተዋል። ጉልበት ያገኙትና ዋነኛ የጥፋት ተዋናይ ለመሆን የበቁትም በዚህ ምክንያት ነው።
በእርግጥ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን “የሕዝባዊነት አስተሳሰብ” ነግሶ ከመሞቱ በፊት፣ ሁለት ዋና ዋና የአስተሳሰብ አይነቶች ነግሰው ሞተዋል። አንደኛው፤ ሊበራሊዝም የሚባለው የስልጣኔ ዘመን አስተሳሰብ ነው። “እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ሕይወትና ንብረት ላይ ብቸኛ አዛዥና ወሳኝ መሆን ስላለበት መብቱና ነፃነቱ ሙሉ ለሙሉ ሊከበርለት ይገባል፤ በሌላ ሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ደግሞ ቅንጣት ስልጣን የለውም። ስለዚህ የማንንም ሰው መብትና ነፃነት ንክች ማድረግ የለበትም። እነካለሁ፤ በሌሎች ሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ፈላጭ ቆራጭ እሆናለሁ የሚል ወንጀለኛ መኖሩ አይቀርም። መንግስት የሚያስፈልገውም በዚህ ምክንያት ነው” ይላል ሊበራሊዝም። በዚህ አስተሳሰብ፤ የመንግስት ስራ፣ ሌላ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ማስከበርና ይህንን የሚጥሱ ወንጀለኞችን ልክ ማስገባት ነው። አለመግባባት የፈጠሩ ሰዎችንም መዳኘት።
በአጭሩ፣ የመንግስት ስራ፤ የዳኝነት ወይም የግልግል እንዲሁም የዘበኝነት ወይም የጥበቃ ስራ ነው። እንግዲህ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። ሰዎች ድምፃቸውን የሚሰጡትና ውሳኔ የሚያስተላልፉት፤ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለማዘዝ አይደለም። ከራሱ ከሰውዬው በስተቀር፣ ማንም የማዘዝ ስልጣን የለውም። በቁጥር የመብለጥና የማነስ ጉዳይ አይደለም።  ለብቻዬም ብሆን አልያም ሚሊዮኖችን ባስከትል ወይም ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 99 በመቶ ያህሉ የድጋፍ ድምፅ ቢሰጠኝ ለውጥ የለውም። በሌላ ሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ቅንጣት ስልጣን አይኖረኝም። 99 በመቶም ሆነ 51 በመቶ “ሕዝብ” እና “የሕዝብ ተመራጭ”፣ እንዳሰኘው ሰውን የመግደል አልያም የሰውን ንብረት የመውረስና የመዝረፍ መብት የለውም። እና ታዲያ፣ ሕዝብ በፖለቲካ ምርጫዎች ላይ የሚሳተፈውና ድምፅ የሚሰጠው ለምንድነው? የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት የሚያስከብሩ የመንግስት አካላትን (ማለትም ገላጋዮችና ዘበኞችን) አማርጦ ለመቅጠር ነው ምርጫ የሚካሄደው። ስልጣን አገኘሁ ወይም በቁጥር እበልጣለሁ ብሎ፣ ሰዎችን መጨፍጨፍና መዝረፍ አይቻልም።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ተስፋፍቶ፣ በ18ኛው ክፍለዘመን ለአሜሪካ ምስረታ ጠንካራ መሰረት ሊሆን የበቃው የ“ሊበራሊዝም” አስተሳሰብ፣ ከሁሉም በላይ ለእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነት ከፍተኛውን ክብር ይሰጣል። ዲሞክራሲ ደግሞ፣ ይህንን መብትና ነፃነት ለማስከበር የሚያገለግል መሳሪያ ወይም አሰራር ነው። ለዚህም ነው ሊበራል ዲሞክራሲ ብለው የሚጠሩት። “ዲሞክራሲ” በጥሬው ሲሆን ግን፤ 51 በመቶው “ሕዝብ” ወይም “የሕዝብ ተመራጭ” እንዳሰኘው በሰዎች ላይ የሚፈነጭ የ“አምባገነንነት” ዝርያ ይሆናል። ለዚህም ነው፤ ታላቋን የነፃነት አገር አሜሪካን የመሰረቱ ጥበበኛና አስተዋይ ፖለቲከኞች፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ስርዓት በ“ግለሰብ ነፃነት” ላይ እንጂ በ“ዲሞክራሲ” ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ በአፅንኦት ሲናገሩ የነበሩት።  ለዚህም ነው፤ በአሜሪካ የነፃነት መግለጫ፤ ማንኛውም አይነት መንግስት፣ የተመረጠም ይሁን ያልተመረጠ፣ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ንጉሳዊ፣ አገር በቀልም ይሁን መጤ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት የማያከብር እስከሆነ ድረስ፣ ከስልጣን መወገድ የሚገባው ሕገወጥ መንግስት እንደሆነ በግልፅ የሚያውጀው። በሕገመንግስት ውስጥም እንዲሁ፣ በሕዝብ የሚመረጠው የአገሪቱ ምክር ቤት (ኮንግረስ)፣ የሰዎችን የሃሳብ ነፃነት የሚጥስ፣ በሰዎች ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ፣ ወይም ሃይማኖትን በመንግስት ጉዳይ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ሕግ የማፅደቅ ስልጣን እንደሌለው በግልፅ ተደንግጓል። በሕዝብ ተመርጬ ስልጣን ይዣለሁ ብሎ እንዳሻው የሰዎችን መብትና ነፃነት መጣስ አይችልም። ሕገመንግስት ያስፈለገውም፤ ይህንን “የሕዝብ” ወይም “የመንግስት” ስልጣን ለመገደብ ነው። በአጭሩ፤ ዋነኛው የፖለቲካ ማጠንጠኛ፣ ዲሞክራሲና ምርጫ አይደሉም - የእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነትን ማስከበር ነው አስኳሉ። ይሄው ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በአሜሪካ በስፋት ከከተገበረ በኋላ፤ በርካታ አገራት ቀስ በቀስ እንዲሻሻሉ፣ ከአምባገነንነትና ከእልቂት፣ ከድህነትና ከረሃብ እንዲላቀቁ ረድቷል። አሳዛኙ ነገር፤ እየተጠናከረ ከመሄድ ይልቅ፤ “የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ ነው” በሚል እየተንቋሸሸና እየተሸረሸረ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን የበላይነቱን አጥቶ በ“ሕዝባዊነት” አስተሳሰቦች አማካኝነት ተዳክሟል። አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክ ወይም የማነሳሳት ሃያልነቱ ተመናምኗል። እናም፤ ሊበራሊዝምን የሚሰብኩ አብዛኞቹ የዘመናችን ፓርቲዎች በግማሽ ልብ ነው ተግባራዊ የሚያደርጉት። በአብዛኛውም፣ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ሲሉ።
ሶስተኛው ርዕዮተ ዓለም፣ ከሊበራሊዝምና ከሕዝባዊነት በፊት ገናና የነበረ ጥንታዊ ርዕዮተ ዓለም ነው - ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም። ይሄኛው ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብም፤ ዛሬ እንደ ጥንቱ ሃያል አይደለም። ለሺ አመታት አለምን በጦርነትና በድህነት ውስጥ ዘፍቋት የቆየው ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የበላይነቱን በሊበራሊዝም አስተሳሰብ  ተነጥቆ የስልጣኔ ብርሃን ከደመቀ ወዲህ እንደገና ሃያልነቱን መልሶ የማግኘት እድል አላገኘም።
ከእነዚህ ሶስቱ አስተሳሰቦች ውጭ (ከሃይማኖታዊ፣ ከሊበራሊዝም፣ እና ከሕዝባዊ አስተሳሰብ ውጭ) ሌላ አይነት አስተሳሰብ የለም። ግን ደግሞ ሶስቱ አስተሳሰቦች፣ አብዛኛውን ወጣትና ምሁር የመማረክና የማነሳሳት ሃይልነታቸውን አጥተዋል። እና የአለምና የታሪክ መዘውር የሚሽከረከረው በምንድነው? መድረሻችንስ የት ነው?
ሊታረቁ የማይችሉት ሶስቱ የአስተሳሰብ አቅጣጫዎች ከተዳከሙ፤ በመላው አለም ለዘብተኛነት ሰፍኖ፣ መቻቻል ነግሶ፣ ግጭት በርዶ፣ ሰላምና ብልፅግና ይሰፍናል እያሉ በየዘመኑ ሲናገሩ የነበሩ ምሁራን ጥቂት አይደሉም። ይህንን እንደ ቂልነት የምትቆጥረው ታዋቂዋ ደራሲና ፈላስፋ አየን ራንድ፣ የለዘብተኛነት መንገድ  ስንዝር እንደማያራምድና እንደማያዛልቅ ትገልፃለች። ሊበራሊዝምና አብሮት የሚመጣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ አለምን ከጨለማ አውጥቶ፣ በበሽታና በረሃብ ሲያልቅ፣ በጦርትነትና በግጭት ሲጨፋጨፍ የነበረውን የሰው ልጅ፣ ከድሮው በሶስት እጥፍ የሚበልጥ እድሜ እንዲኖረው፣ በመቶ እጥፍ የላቀ የኑሮ ምቾት እንዲያገኝ ማድረጉን ታስረዳለች። በተቃራኒው፣ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሕዝባዊነት፤ አለምን አጨልመው፣ ምድሪቱን በደም አጨቅይተው፣ የሰውን ልጅ በረሃብ አሰቃይተዋል። ያው፤ ትክክለኛ አስተሳሰብ ወደ ስኬት ሲያደርሰን፣ የተሳሳተ አስተሳሰብ ደግሞ ወደ ጥፋት እያንደረደረ እንጦሮጦስ ያወርደናል።
ጨርሶ ጎልቶ የሚታይ አስተሳሰብ ከሌለስ? ሦስቱ አስተሳሰቦች ሲዳከሙ ውጤቱ ምን ይሆናል? ራንድ እንዲህ ትላለች - ሰዎች ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ አቅጣጫቸውን ካልቀየሩ በቀር፣ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ባለው አያያዛቸው ከቀጠሉ መጨረሻቸው ጨለማ ነው። ከእንሰሳ ባልተሻለ ጭፍን ስሜት እየተቧደኑ እርስ በርስ መናጨትና መበላላት የበዛበት ዘግናኝ የጨለማ ዘመን ይፈጠራል። ሰዎች አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ፤ የአለም አዝማሚያ ቀስ በቀስ ወደዚሁ ትርምስ እንደሚያመራ ትናገራለች ራንድ - ከ40 ዓመታት በፊት ባሳተመቻቸው መፃህፍቷ።
የዛሬ 18 ዓመት፣ “Clash of Civilizations” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ የሚታወቁት ሳሙኤል ሃቲንግተን በበኩላቸው፤ ገናናዎቹ የፖለቲካ አስተሳሰቦች መክሰማቸውን በመግለፅ፣ ሰዎች ከኢኮኖሚ ስሌት ጨርሶ ባይለያዩም በጥንታዊ የባህል፣ የቋንቋ፣ የብሄር ብሄረሰብና የሃይማኖት ውርሶች እየተሰባሰቡ መቧደን እንደሚጀምሩ ይገልፃሉ። በሌላ አነጋገር፤ ዋና ዋናዎቹ አስተሳሰቦች፣ ከሃሳብ ትንታኔ ጋር ተራርቀው ወደ ስሜት ደረጃ ይወርዳሉ። የሊበራሊዝም አስተሳሰብ፣ ዋነኛ መሰረተ ሃሳቡ ይጠፋና፣ ከተራ የፖለቲካ ምርጫ እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ብቻ የተቆራኘ የምኞት ስሜት ይሆናል። እናም፣ ሰዎች አፈና ወይም የኢኮኖሚ ችግር ሲበረታባቸው፤ እና ደግሞ የሌላው አገር ነፃነትና ብልፅግና በሳተላይት ቴሌቪዥንና በኢንተርኔት ሲያዩ፣ በቅሬታ ስሜት ተሞልተው ያምፃሉ። መፍትሄውን ግን አያውቁትም።
የግብፅና የሶሪያ፣ የሴንትራል አፍሪካና የኮንጎ ግጭቶችን ተመልከቱ። አዳሜ፣ አፈናና ችጋር እየመረረው፣ ነፃነትንና ብልፅግናን በመመኘት አደባባይ ይወጣል። መንግስት ይገለበጣል፤ ግን ተመልሶ ያው ነው። ችግር፣ በራሱ ጊዜ መፍትሄ አይወልድም። ያለ ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ በስሜት ብቻ፣ ሁነኛ መፍትሄ አይገኝም። ግብፃውያን ምን ተረፋቸው? መሃመድ ሙርሲን የመሰለ የሃይማኖት አክራሪ ወይም ጄነራል አሲሲን የመሰለ በአገርና በሕዝብ ስም የሚፎክር አምባገነን! ሶሪያውያን ምን ተረፋቸው? በአንድ በኩል፣ በአገርና በሕዝብ ስም መንደሮችን በአውሮፕላን የሚደበድብ መንግስት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሺዓ እና ሱኒ እያሉ ሰውን የሚጨፈጭፉ የሃይማኖት አክራሪዎች! ሌላ ያተረፉት ነገር የለም። ለነገሩ፤ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብም ሆነ ሕዝባዊነት፣ ከስሜት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለአገሬው ወይም ለአለም ችግሮች፤ ለኢኮኖሚና ለፖለቲካ ቀውሶች መፍትሄ ያመጣል በሚል ትንታኔ ሰዎችን መማረክ በፍፁም አይቻልም፤ መፍትሄ እንደማያመጣ ታይቷልና። ነገር ግን፣ በሃይማኖት ሰበብ የሰዎችን ስሜት ማነሳሳትና በሃይማኖት አቧድኖ ማጋጨት ይቻላል። የሕዝባዊነት አስተሳሰብም እንዲሁ፣ እንደ ሃያኛው ክፍለዘመን በየአገሩ የፋሺዝምና የሶሻሊዝም አብዮት የማካሄድ ጉልበት የለውም። ግን፣ ሰዎችን በዘርና በብሄር ብሄረሰብ፣ በቋንቋና በቀዬ ሰበብ እያነሳሱና እያቧደኑ ማጋጨት ይቻላል። ይሄው ነው እየሆነ ያለው።
21ኛው ክፍለ ዘመን ከ20ኛው ክፍለዘመን በእጅጉ እንደሚለይ የሚገልፁት ሃቲንግተን፤ የብሄር ብሄረሰብና የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ጉዳይ ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳይ ይሆናሉ በማለት ያስረዳሉ። ከዚህም በመነሳት ነው፤ በ21ኛው ክፍለዘመን የሃይማኖት አክራሪነት፣ አሸባሪነትና ግጭት እንደሚበራከት የተነበዩት። አልተበራከተም የሚል የለም። በደፈናው፣ የአለምን አዝማሚያ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ በአንድ የተለያዩ አገራት ምን አይነት ፈተና እንደሚጠብቃቸው ሃቲንግተን ተንብየዋል። ለምሳሌ፣ ሱዳን ከሰሜንና ከደቡብ ለሁለት እንደምትገነጠል ተናግረዋል። እንዳሉትም አልቀረም። ሃይማኖትና መንግስት ሊነጣጠሉ ይገባል በሚለው መርህ ለመቶ አመታት በተጓዘችው ቱርክ፣ የሃይማኖት ጉዳይ እንደገና እያቆጠቆጠ አገሪቱን እንደሚረብሻትም ሃቲንግተን ገልፀዋል። ይሄውና ሃይማኖትንና መንግስትን ለማዛመድ በሚፈልግ ፓርቲ አማካኝነት የአገሪቱ ቀውስ ተባብሷል። በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ ከሚሰነዘረው የአሸባሪዎች ጥቃት በተጨማሪ፣ “የሱኒ ተከታይ፣ የሺዓ ተከታይ” በሚል ሰበብ ግጭቶች እየተፈጠሩ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስና ሌሎች በርካታ አገራት ችግር ውስጥ እንደሚገቡም ምሁሩ ተንብየዋል። ደግሞም እየሆነ ነው። ከመካከለኛው ምስራቅ የሚወጡ የየእለቱን ዜና በመስማት ማረጋገጥ ይቻላል።
ሁሉንም ለመዘርዘር ያስቸግራል። ግን፣ አንድ ሌላ ትንበያ ልጨምርላችሁ። ዩክሬን፣ ከብሄር ብሄረሰብና ከቋንቋ፣ ከሃይማኖትና ከባህል ጋር በተያያዘ ውዝግብ ለሁለት ልትሰነጠቅ እንደምትችል ሃቲንግተን ሲገልፁ፣ ክሬሚያ እና ምስራቃዊ የዩክሬን አካባቢ ወደ ራሺያ ሊጠቃለሉ እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ። ይህንን ያሉት ከዛሬ 18 አመት በፊት ነው።
በአጠቃላይ፤ ዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተዳከሙበት የዛሬው ዘመን፣ በጭፍን ስሜቶችና በተቀጣጣይ አደጋዎች የተከበበ፤ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ዘመን ሆኗል።
መናኛ ፖለቲከኞች የሃይማኖትና የብሄር ብሄረሰብን ጉዳይ እያራገቡ ችግር ሲፈጥሩ፤ አለም የሚይዘውና የሚለቀው ጠፍቶበታል። በዩክሬን፣ እዚህ ግባ የማይባሉ ሁለት ቡድኖች አገሬውን ሲቀውጡ፣ የዩክሬን አንጋፋ ፖለቲከኞች ምን አደረጉ? ቀልባቸው የተገፈፈ አጃቢ ከመሆን የዘለለ ነገር አላደረጉም። አለምን መቶ ጊዜ የሚያጠፋ የኒኩሊዬር መሳሪያ የታጠቁት የራሺያ መሪዎችንም እዩዋቸው - በቁራሽ መሬት ነው የሚደነፉት - ቁምነገር ይመስል። መደገፍም ሆነ መቃወም አቅቷት “የሚመለከታቸው ወገኖች በውይይት ችግራቸውን ይፍቱ” ብለው ከሚንተባተቡት የቻይና ገዢዎችም የጠራ ነገር አታገኙም። ሌላው ይቅርና በስልጣኔ ደህና የተራመዱት ምዕራባዊያንስ ምን ፈየዱ? የዩክሬን ቀውስና የራሺያ ድርጊት፣ በአውሮፓ ትልቁ የ21ኛው ክፍለዘመን ቀውስ እንደሆነ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ግን፤ የአሜሪካና የአውሮፓ ባለስልጣናት ወዲህና ወዲያ ከመወራጨት ሌላ ምን አደረጉ? ቱ ራራሺያን አደብ ለማስገዛት የሚያስችል የአስተሳሰብ ፅናት ጠፍቶባቸው፤ የሚያደርጉትን ብቻ ሳይሆን የሚናገሩትን አጥተዋል። ከሁለት መልከ ጥፉ (ከራሺያና ከዩክሬን ‘ፋሺሽት’ ቡድኖች) አንዱን መምረጥ የቸገራቸው አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትም፣ ጥርት ያለ ነገር አልያዙም። በአጠቃላይ፤ ዓለም የሶሪያን እልቂት በሩቁ ከመመልከት ውጭ ምንም ማድረግ እንዳልቻለው ሁሉ፤ በዩክሬን ጉዳይ ላይም እንዲሁ መያዣና መጨበጫ አላገኘለትም። መደናበር ብቻ!
ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስትና ኢህአዴግ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ነገሩ ተደበላልቆባቸው ግራ ቢጋቡ ምን ይገርማል? እነሱን በጣም የሚያሳስባቸው፣ መንግስት በሕዝብ አመፅ ይወርዳል መባሉ ነው። ይሄ ተራ ነገር ነው። አሁን አለምን እየናጣት ያለው ቀውስ ጋር ሲነፃፀር፣ የአንድ መንግስት መውደቁና አለመውደቅ ኢምንት ነገር ነው። እጅግ አሳሳቢው ነገር፤ በየጊዜው የሚፈጠሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ አስተሳሰብ አለመኖሩ ነው። ከአመፅ አዙሪት የሚገላግልና ለዘላቂ የስልጣኔ ለውጥ የሚበጅ ጠንካራ አስተሳሰብ በአለማችን አለመኖሩ ነው። ደረጃውና መጠኑ ይለያይ እንጂ፤ በአለማችን የሰፈኑ ስርዓቶች በአብዛኛው በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ መስክ ቅሬታዎችና ችግሮች እየተደራረቡ እንዲከማቹ የሚያደርጉ ናቸው። ቅሬታና ችግር ተከማችቶ ምሬት ሲበዛ፣ አደባባይ ወጥቶ ከመጮህ ውጭ፣ ግልፅና ጤናማ መፍትሄ የለም። የአስተሳሰብ ኦና ሲፈጠር፤ በቦታው በብሄር ብሄረሰብና በቋንቋ፣ እንዲሁም በሃይማኖት ሰበብ የሚራገቡ መርዘኛ ስሜቶችን ለመከላከል የሚያስችል የስልጣኔ አስተሳሰብ የለም። መውጪያ የሌለው የትርምስ አዙሪት ነው የሚሆነው። ይሄ ነው ሊያሳስበን የሚገባው።
ያለ ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ አስተማማኝ መፍትሄ ማግኘት ባይቻልም፤ ለጊዜው ጠንቀቅ ማለት ጥሩ ነው። አንደኛ፤ በዋጋ ንረትና በታክስ ጫና፣ አልያም በአላስፈላጊ የሕግ ገደቦችና የቢሮክራሲ ቁጥጥሮች ኢኮኖሚን ላለማዳከም በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አለበለዚያ መዘዙን አንችለውም። ሁለተኛ፣ ጓዳና አደባባዩን ካልተቆጣጠርኩ ብሎ ዜጎችን መውጪያ መግቢያ ከማሳጣት፣ እንዲሁም በትንሽ በትልቁ ንትርክና ፍጥጫ ከመፍጠር ቆጠብ ብሎ፤ በፖለቲካውም ሆነ በፍትህ መስኮች ያለ ማቋረጥ የመሻሻል ምልክቶች እንዲታዩ መትጋት ያስፈልጋል። ሶስተኛ፡ የብሔር ብሔረሰብና የቋንቋ ጉዳዮችን ከማራገብ መቆጠብ ነው። አራተኛ፡ የሐይማኖት ጉዳይ ከፖለቲካ ጋር እንዳይቆራኝ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል።    


‹‹ማኅበሩን የማዳከምና የማፍረስ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተልእኮ ነው››
/አባላትና ደጋፊዎ

   ማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀውን የአስተዳደር መዋቅር ተቆጣጥሮ ለፖለቲካ ጥቅም ሊያውል ይፈልጋል በማለት የሚቃወሙ የአዲስ አበባ የደብር አስተዳዳሪዎች ዛሬ ስብሰባ የሚያካሂዱ ሲሆን፤ የማህበረ ቅዱሳን አባላት በበኩላቸው ዘመቻ ተከፍቶብናል ይላሉ፡፡
የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ማኅበሩ ሀብቱንና ንብረቱን እንዲያስረክብ ሊያስገድዱት ተዘጋጅተዋል ይላሉ የማህበሩ አባላት፡፡
ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በመጣስ እንደሚንቀሳቀስ የሚጠቅሱት አስተዳዳሪዎቹ በበኩላቸው፤ ገንዘቡንና ንብረቱን የሚያንቀሳቅሰው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት አሰራር ውጭ ስለሆነ   የሀብቱና ንብረቱ መጠን አይታወቅም ይላሉ፡፡
‹‹ማኅበሩ አቅጣጫውን የሳተ የኦርቶዶክስ ሰለፊ ነው›› በማለት ማኅበረ ቅዱሳንን የሚፈርጁ አስተዳዳሪዎች እንዳሉ የሚናገሩት የማህበሩ አባላት፤ ዘመቻ እንደተከፈተባቸው የሚገልፁ ሲሆን፤ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው ማህበሩ በቤተክርስቲያን ላይ ዘመቻ ከፍቷል ይላሉ፡፡ ማኅበሩ ለሀገረ ስብከቱ የሠራው የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት፣ ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በመቆጣጠርና በፖለቲካ ከቤተ መንግሥቱ አጣምሮ በመያዝ ዓላማውን ለማራመድ ያዘጋጀው ነው ሲሉ የሚቃወሙ አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡  
‹‹ሕግ የሌለውና ለሕግ የማይታዘዘው ማኅበረ ቅዱሳን ለእኛ ሕግ ሊያወጣልን አይችልም›› የሚሉት አስተዳዳሪዎቹ፤ ከየአድባራቱ አምስት አምስት ሠራተኞች ይገኙበታል በተባለው በዛሬው ስብሰባቸው፤ ማኅበሩ ሕግ ወጥቶለት ወደ መዋቅር እንዲገባ በመግለጫቸው እንደሚጠይቁ የማኅበሩ አባላት በበኩላቸው፣ ማኅበሩ የሚመራው በ1994 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ለሦስተኛ ጊዜ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ ነው በማለት ‹‹ሕግ የሌለው ሕገ ወጥ ነው›› መባሉን ተቃውመዋል፡፡
ማኅበሩ በየዓመቱ ፈቃድ ባለውና ብቃቱ በተመሰከረለት የውጭ ኦዲተር፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን እያስመረመረ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርት እንደሚያቀርብ አባላቱ ተናግረዋል፡፡

            ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ማታ ላይ፤ አንድ ሰው ወደ አንድ ቡና ቤት፣ አንድ አሣማ ይዞ ይገባል። የቡና ቤቱ የመጠጥ ኃላፊ፤ በጣም ጠንቃቃና የጉጉት-ዐይን ያለው ዓይነት ሰው ነው፡፡ ሰውዬው ይዞት የመጣው አሣማ አንድ እግሩ በእንጨት የተጠገነ ነው፡፡ ይህንን የመጠጥ ኃላፊው አይቷል፡፡
ወደ እንግዳው ሄዶ እንዲህ አለው፡-
“ይህ አሣማ ምን ሆኖ ነው አንድ እግሩ እንጨት የሆነው?”
ሰውዬውም፣
“አንድ ቢራ ከሰጠኸኝ፤ ስለዚህ ልዩ ባህሪ ስላለው አሣማ ታሪክ እነግርሃለሁ!” አለው፡፡
የመጠጥ ኃላፊው፤ “መልካም፡፡ ጥሩ ታሪክ የሚወጣው ስለመሰለኝ፤ እንካ አንድ ቢራና ታሪኩን ትነግረኛለህ” አለና አንድ ቢራ አቀረበለት፡፡
“ስለዚህ ተዓምረኛ አሣማ ልንገርህ” አለና ጀመረ ያ ሰውዬ፡፡ “በጣም ልዩ አሣማ ነው፡፡ አንድ ማታ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ገደማ፣ ድንገት ቤቴ በእሳት ተያያዘ፡፡ ይሄኔ ያ አሣማ ከበረቱ በርግዶ ወጣና፣ ወደ ቤቴ መጣ፡፡ ሁለቱን ልጆቼን ተሸክሞ ይዟቸው ወጣ፡፡ እኔና ሚስቴንም ሰላም ወደሆነው ሥፍራ ይዞን ወጣ! ስለዚህ፤ ቤተሰቤንና ህይወቴን አዳነልኝ ማለት ነው!!”     
ያ የመጠጥ ክፍል ኃላፊም፤ በታሪኩ ተገርሞ፣
“በጣም የሚገርም ጉድ ነው፡፡ ግን ለምን አንድ እግሩ እንጨት ሆነ?” አለው ደገመና፡፡  ሰውዬውም፤
“አንድ ቢራ ከጋበዝከኝ የዚህን ተዓምረኛ አሣማ ታሪክ እነግርሃለሁ” ይለዋል፡፡ የመጠጥ ክፍል ኃላፊው ምሥጢሩን ለማወቅ በጣም ጓጓ፡፡ ካረግኸው ጥሩ፤ ብሎ አንድ ቢራ ጨመረለት፡፡
ሰውዬውም፤
“ከእኔ ቤት ጀርባ አንድ ሐይቅ አለ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን፤ ጀልባ ይዤ ልቀዝፍ ወጥቻለሁ፡፡ ድንገት ማዕበል መጥቶ ጀልባዋ ተገለባበጠች፡፡ እኔ እጀልባዋ ወለል ላይ ተፈጠፈጥኩ፡፡ ከዚያ ወዲያ መዋኘት አልቻልኩም፡፡ ይሄ አሣማ ያንን አውቆ፤ በረቱን በርግዶ ወጥቶ ወደ እኔ ዋኝቶ መጥቶ ወደ ሐይቁ ዳርቻ ወሰደኝ፡፡  መተንፈስ አቅቶኝ አሸዋው ላይ ተንጋለልኩኝ፡፡ ከዚያ ወደ ቤቴ ሄዶ፣ ባለቤቴን ቀስቅሶ ይዟት መጣ፡፡ እሷ ትንፋሽ መግባኝ ነብሴን ዘራሁ፡፡ ይሄ አሣማ ህይወቴን አዳነልኝ” እልሃለሁ አለው፡፡
የመጠጥ ክፍሉ ኃላፊ በጣም ተደንቆ፣ ግን በመጠኑ ትዕግሥት አጥቶ፤ “በጣም አስደናቂ ትንግርት ነው፡፡ ግን የአንድ እግሩ እንጨት መሆን ሚሥጥር ትርጉሙ ምንድን ነው?” አለና ጠየቀው፡፡
“አንድ ሌላ ቢራ ጋብዘኝና እነግርሃለሁ…” አለው፡፡ ባለ መጠጥ ቤቱ ሌላ ቢራ ከፈተለት፡፡
“ስለዚህ ተዓምረኛ አሳማ አሁን ልንገርህ፡፡ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ተነስቶ እኔ ለመሸሽ ወደ ምድር ቤት ስሮጥ አዳለጠኝና ወደቅሁኝ፡፡ አሳማ ሆይ ከበረቱ በርግዶ ወጥቶ እየጐተተ ምድር ቤት አውርዶኝ ከአውሎ-ነፋሱ ተረፍኩኝ እልሃለሁ”
ባለ መጠጥ ቤቱ ይሄ የመጨረሻው ተዓምር መሆን አለበት ብሎ፤
“ይገርማል ተዓምረኛ አሣማ ነው ባክህ! ከእሣት፣ ከውሃና ከአውሎ ነፋስ አዳነህ! ግን ይሄ የእንጨት እግሩ ከየት መጣ?”
ሰውዬውም በመጨረሻ፤     
“እንዲህ ያለውን ተዓምረኛ አሣማኮ ሁሉንም ባንድ ጊዜ አትበላውም፡፡ ቀስ ቀስ እያልክ፣ ትንሽ ትንሽ ብልቱን እየለየህ፣ ነው መብላት ያለብህ!!” አለው፡፡   
*    *    *
ለአገር ባለውለታ የሆኑን ሰዎች በምንም ዓይነት ውለታቸውን መርሳት አይገባንም፡፡ ሁሉም ዜጋ የየራሱ ድርሻ አለውና ያንን አስተዋፅዖውን አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡ የተሻለና የበለጠ ያገለገለን ዜጋ ደግሞ፤ የተሻለ እውቅና መስጠት ይገባናል፡፡ ይህ “ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው” ዓይነት መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የሀገርን የዕድገት መንፈስ የሚያፀና ነው!
አስተሳሰባችን ሙሉ ይሁን፡፡ ለእኛ የሚመች የሚመቸውን ብቻ የፖለቲካ መዘውር ነው ካልን የሚያጎድለን እንጂ የሚያሟላን ፀጋ አልጨበጥንም ማለት ነው፡፡ ጨቋኝና ተጨቋኝ  ባለበት አገር በድሮው አነጋገር Class based society ውስጥ የተበዳዩን ቁጥር ለመቀነስ ፍትሐዊ አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ “በምድር ላይ የሚራመድ አንድ ‘ባሪያ’ እስካለ ድረስ፤ ሙሉ በሙሉ ነፃ አንወጣም” ይሉናል ፀሐፍት። መልካም አስተዳደር እኛ እንደምንገምተው ቀላል አይደለም፡፡ ባህላዊ ታሳቢ እሴቶችን ሳናመዛዝን፤ የውጪውን አስገብተን እንዳለ ህዝባችን ላይ እንጫን ብንልም ዓላማው ጉዳዩን ከማወሳሰብ አያልፍም፡፡ ለዚህ ነው በሀገራችን መሻሻል የማናየው፡፡ ከመሠረታችን እንደማተባችን የማንበጥሳቸው አልበገር-ባይነት (Resistance) ውስጣችን አለ፡፡ ያንን ለማውጠንጠን ነፃ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ መንግሥትም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ህዝብም እንደዚሁ ይህ ይሆን ዘንድ መጣጣር አለበት፡፡ የረዥም ጊዜ ግልፅ ውይይት፤ ሀሜትን ያስወገደ ዕውነተኛና ልባዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ ረዥም ጉዞ ያስፈልገናል። ችግሩ እንግዲህ፤ መለወጣችንን የሚያይልን ራሱ ያልተለወጠ ሰው ከሆነ ተያይዞ ገደል መግባት ሊሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ይሄ የእገሌ፣ ያ የእገሌ ብሄረሰብ፣ ጎሣ፣ መንደር ወዘተ ሰው ነው በሚል ሌላውን አሳንሶ የማስቀመጥ አመለካከት፤ እንደቀንድ-አውጣ ውስጣችን ያደፈጠ የለውጥ እንቅፋት ነው። ለፍቅረኞች ቀን፤ የአበበ ዘንግ ሽያጭ፤ አበባ ልብን ላያመላክት ይችላል! ገቢ አለ፡፡ በገቢው የምንሠራው ምንድነው? ይሄ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምተናል፡፡ ጠጋ ብለን፣ የችግሩ ምንጭ የት ጋ ነው ብለን ግን ለማጤን አልፈቀድንም፡፡ “አንድን ጉድ፣ ሺ ጊዜ ከሰው ከመስማት አንዴ ሄዶ በዐይን አይቶ እርፍ ማለት ይሻላል” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ የታመመ ሰውን ጠይቆ የሚነግረን ሰው፤ ስለበሽተኛው የግሉን ስሜት ብቻ አጋኖ እንደሚነግረን እረስተን፤ እኛም ያንኑ ወሬ ለሌላ ጆሮ እናስተላልፋለን፡፡ ሺ ጊዜ በማጉላትም ጣር-አልጋ ላይ ያለ ሰው አድርገነው ቁጭ እንላለን፡፡ አገራችን ታማለች ካልን ቀርቦ ማየት ነው፡፡ የሚሻለውን መምከር፣ የምትታከምበትን መላ መምታት ነው ያለብን፡፡
የሀገራችን ችግሮች እጅግ በርካታ ለመሆናቸው አዋቂ መጠየቅ አያሻንም፡፡ ተራ በተራ ለመፍታት መጣጣር ነው እንጂ የለም ብሎ መካድ ግን ቢያንስ ራስን ማታለል ነው፡፡ ከራሳችን አበሳ በተጨማሪ፤ በተጋቦት እስከሚመጡት የድምበርተኛ ጎረቤቶቻችን ችግር ድረስ፤ የችግር መተላለፊያ ኮሪዶር ነን ብለናልና፤ ኮሪዶሩ መጠረግ አለመጠረጉን አለማረጋገጥ ለባሰ መዘዝ ይዳርገናል፡፡ “እንኳን አሁንና ብዙ ትጥቅ እያለን
በጦር በጎራዴ፣ ታንክ እናማርካለን”
ማለት በዘመነ-ግሎባላይዜሽን (የለየለት ቅኝ-ገዢነት) እንደማያዋጣ ማንም ሊስተው አይገባም። የሀብት ምንጮቻችንን እንጠብቅ፡፡ የሰው ኃይላችንን፣ ጦራችንን በአግባቡ እንጠብቅ! ለገዛ ጥቅሙ በስተቀር ለእኛ ብሎ እሹሩሩ የሚለን የዓለም ታላቅ አገር የለም፡፡ “አበሻም ይሁን ፈረንጅ ማንም ህዝቡ ላይ ጫና ሊጥል አይገባም” የሚለውን አባባላችንን ማጥበቅ መልካም ነገር ነው! “አነስተኛ ነን ብለን እጃችንን መጠምዘዝ የለብንም፡፡ ችግራችን የብረት በር ሆኖብናል አንበል፡፡ “እጅግ በጣም ትልቁ የብረት በር እንኳን የሚከፈተው በትንሽ ቁልፍ መሆኑን አትርሳ” ይለናል ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል ነው ነገሩ!!   

        66 አጫጭር ግጥሞችን ያካተተውና በተማሪ ማንያዘዋል እሸቱ የተፃፈው “የህይወት ኮስሞቲክስ” የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
በ66 ገፆች የተቀነበበው የግጥም መድበሉ፤ ተማሪው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ያሰባሰባቸው ግጥሞች የተካተቱበት ሲሆን በማህበራዊ፣ በፍቅር፣ በአገር፣ በወጣትነት፣ በካምፓስ ህይወትና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደሆነ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ አመት የኢንቫይሮንሜንታል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ገጣሚው፤ የፊልም ስክሪፕት የመፃፍ ስራ ላይ ማተኮሩን ገልፆ የመጀመሪያ ስራው የሆነው ይህ የግጥም መድበል፤ ህይወትን የሚያስውቡና በብዙ የህይወት ጉዳዮች የሚያጠነጥኑ ግጥሞች ስለተካተቱበት “የህይወት ኮስሞቲክስ” የሚል ርዕስ እንደሰጠው ጠቁሟል፡፡ መፅሀፉ በ25 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን የሚማርበት ዩኒቨርስቲ ስፖንሰር እንዳደረገው ገጣሚው ተናግሯል፡፡

በጋዜጠኛ ግርማ ለማ የተፃፈውና በቀዳማዊ ሀ/ስላሴ የቤት ውስጥ ውሎ፣ ቤተሰባዊ ህይወትና የጓዳ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው “የንጉሱ ገመና” ለንባብ በቅቷል፡፡
መፅሀፉ እስከ ዛሬ በንጉሱ ዙሪያ ከተፃፉት መፅሀፎች የሚለየው በቤት ውስጥ ውሏቸውና ገመናቸው ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ 170 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፤ በአርጋኖ የህትመት ኢንዱስትሪ ታትሞ በጃፋር መፅሀፍ መደብር እየተከፋፈለ ሲሆን በ49 ብር ከ75 ሳንቲም ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

    ነዋሪነታቸውን በለንደን ባደረጉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ የተፃፉት “የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድን ነው?” የተሰኙ መፅሀፎች ለንባብ በቁ፡፡ እነዚህ መፅሀፎች ተከታታይ ክፍል እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በመጀመሪያው እትም ሰላም፣ ደስታና ፍቅር ስለማግኘት፣ በአላማ ስለመፅናት፣ ስሜትን ስለመቆጣጠር እና በራስ ስለመተማመን በስፋት መተንተኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ49 እና በ59 ብር ለገበያ የቀረቡት መፃህፍቱ ቀጣይ ክፍላቸው ለህትመት በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፀሀፊው ኢ/ር ወንድሙ ነጋሽ ላለፉት 15 ዓመታት በእንግሊዝ የጦር መርከቦችን ከአደጋ የመከላከል ሲስተም መሃንዲስ በመሆን ከመስራታቸው በተጨማሪ በስነ-አዕምሮና በስነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ ተከታታይነት ያላቸው ጥናታዊ መፅሀፍትን በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመፃህፍቱ ተከታይ ክፍሎች ስለ ጣፋጭ ፍቅር፣ ስለ መልካም ግንኙነት፣ ስለ ስኬታማ ትዳር ስለ ስነ-አዕምሮና ስነ-ልቦና በሳል ግንዛቤ ያስጨብጣሉ ተብሏል።

Saturday, 15 March 2014 13:19

“ስንክርተነ” የተባለ

የጉራጊኛ የግጥም መፅሀፍ ነገ-ይመረቃል
የቤተ ጉራጌ ባህል ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ተስፋዬ ጐይቴ የተፃፈው “ስንክርተነ” የተባለ የግጥም መፅሀፍ ነገ በደሳለኝ ሆቴል ይመረቃል። 135 ግጥሞችን ያካተተውና በ140 ገፆች ላይ የተመጠነው መፅሀፉ፤ በጉራጊኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን አብዛኞቹ ግጥሞች የጉራጌን ባህል፣ ወግና ትውፊት ያስቃኛሉ ተብሏል፡፡ ትልቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህይወት የተመለከተ ረጅም ግጥም እንደተካተተበትም አቶ ተስፋዬ ጐይቴ ገልፀዋል፡፡
በ33 ብር ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ በሴትኛ አዳሪነት ህይወት እና በሌሎችም ማህበራዊ ህይወት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ፀሀፊው ከዚህ በፊት “የኬርጋት” እና “ጉራጌንዶ” የተሰኙ የግጥም መፃህፍትን በጉራጊኛ ቋንቋ ፅፈው ለንባብ አብቅተዋል።
ሶስተኛውና “ስንክርተነ” የተሰኘው የግጥም መፅሀፍ ነገ ጠዋት ከ2፡30 ጀምሮ ባለስልጣናት፣ የባህልና ቱሪዝም ሀላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ይመረቃል ተብሏል፡፡

ነዋሪነታቸውን በለንደን ባደረጉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ የተፃፉት “የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድን ነው?” የተሰኙ መፅሀፎች ለንባብ በቁ፡፡ እነዚህ መፅሀፎች ተከታታይ ክፍል እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በመጀመሪያው እትም ሰላም፣ ደስታና ፍቅር ስለማግኘት፣ በአላማ ስለመፅናት፣ ስሜትን ስለመቆጣጠር እና በራስ ስለመተማመን በስፋት መተንተኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ49 እና በ59 ብር ለገበያ የቀረቡት መፃህፍቱ ቀጣይ ክፍላቸው ለህትመት በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፀሀፊው ኢ/ር ወንድሙ ነጋሽ ላለፉት 15 ዓመታት በእንግሊዝ የጦር መርከቦችን ከአደጋ የመከላከል ሲስተም መሃንዲስ በመሆን ከመስራታቸው በተጨማሪ በስነ-አዕምሮና በስነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ ተከታታይነት ያላቸው ጥናታዊ መፅሀፍትን በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመፃህፍቱ ተከታይ ክፍሎች ስለ ጣፋጭ ፍቅር፣ ስለ መልካም ግንኙነት፣ ስለ ስኬታማ ትዳር ስለ ስነ-አዕምሮና ስነ-ልቦና በሳል ግንዛቤ ያስጨብጣሉ ተብሏል።