Administrator

Administrator

ኢትዮጵያ በኃይልና በወረራ ፍላጎቷን ማሳካት እንደማትሻና በጎረቤት አገራት ላይ ወረራ የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ ። “አገሪቱ ቃታ በመሳብ በሀይልና በወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር እንደሌላትም ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከበረው “116ኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን” በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ኢትዮጵያ ቃታ በመሳብ በኀይልና በወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር የለም፤ ይልቁንም በንግግርና በድርድር የጋራ ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማሟላት ቁርጠኛ ነን፤” ብለዋል።


የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀኑ “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል  የተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችና የሠራዊቱን አቅምና ብቃት የሚያሳዩ ደማቅ ዝግጅች በቀረቡበት ሥነ-ስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስታነሳ ወረራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ይደመጣል። ነገር ግን  ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በዚሁ በተከበረ ቀን መግለጽ የምፈልገው ኢትዮጵያ በሃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር አለመኖሩን ነው”  ብለዋል።


በሀይል ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት ወንድሞቻችን ላይ ቃታ የምንሰነዝር እንዳልሆን በአጽንኦት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ እድገት፣ ለጋራ ብልጽግና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ከወንድሞቻችን ጋር ተወያይተን የጋራ ጥቅም ለማስከበር እንጥራለን ብለዋል። “የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ከማስከበር፣ ሰላም ከመጠበቅና የሀገር ብልጽግና እንዲቀጥል ከማድረግ ውጭ ሌላ አላማ የለውም” ሲሉም ጠ/ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


የአገሪቱ ሠራዊት ሌሎችን ለማጥቃትና ለመውረር እንደማያስብ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ አገሪቱን ግን ይከለከላል ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ወይም ወደብ ያስፈልጋታል በሚል ሃሳብ ምክንያታቸውንም በዝርዝር ማቅረባቸው አይዘነጋም። አገራት ግን የጠ/ሚኒስትሩን የባህር በር ሃሳብ ወይም ጥያቄ በቀና የተመለከቱት አይመስልም። ኤርትራ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ የጠ/ሚኒስትሩን ሃሣብ የሚቃወሙና የማይቀበሉ መሆናቸውን  በመግለጽ ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።


ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ከህዝብ ቁጥሯ ብዛትና ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ወደቦች በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷን በመጥቀስና ሰጥቶ በመቀበል አግባብ የባህር በር ወይም ወደብ  የምታገኝበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት መናገራቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ምሁራን በሚዲያ እየቀረቡ የጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብ የሚደግፍና የሚያጠናክር ማብራሪያ ሲሰጡ ተደምጠዋል። ትላንት በኢቢሲ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ምሁር ኢትዮጵያ መድሃኒትና ነዳጅን ጨምሮ ወደ አገር  ውስጥ ለምታስገባቸው የተለያዩ ምርቶች ወደብ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው፣ ዓለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ወይም ጥያቄ ይደግፉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ጎረቤት አገራትም በንግግርና በውይይት ኢትዮጵያ የባህር ወደብ እንድታገኝ ትብብር ያደረጉ ዘንድ ምሁሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

Friday, 27 October 2023 07:20

አሜባ 'ኪንታሮት' ያመጣል?

አሜባ 'ኪንታሮት' ያመጣል?

ከእለት ተእለት የህክምና ስራችን ላይ ከሚያጋጥሙን እና በማህረሰባችን ዘንድ በተሳሳተ መልኩ ከሚታዩ የጤና ሁኔታዎች አንዱ በፊንጢጣ በኩል ደም መፍሰስን ወይም ፊንጢጣ አካባቢ የሚኖሩ እባጮችን  እና ተያያዥ ምልክቶችን አብዛኛውን ጊዜ ከ 'ሄሞሮይድስ' (የፊንጢጣ ኪንታሮት) ወይም  አሜባ ህመም ጋር ብቻ ማያያዝ ነው::

በሚያሳዝን መልኩ ብዙ ታካሚዎቻች ደም መድማትን ካዩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጤና ተቋም በቶሎ ባለመቅረባቸው ወይም በእኛ በባለሙያዎች ዘንድ ምልክቱን በአግባቡ ባለመጠየቅ የህመማቸው ደረጃ ገፍቶ እናያቸዋል::

የተለመዱ በፊንጢጣ በኩል ደም እንዲፈስ የሚያደርኩ የህመም አይነቶች
1. ሄሞሮይድስ (የፊንጢጣ ኪንታሮት)
2. የፊንጢጣ ውስጠኛው ክፍል መላጥ (መሰንጠቅ)
3.የአንጀት ደም ስር ችግሮች
4. የአንጀት ላይ እባጮች (intestinal polyps)
5. የአንጀት ወይም የፊንጢጣ ካንሰር (የቀኝ የአንጀት ክፍል ካንሰር የሚታይ መድማትን ሳያመጣ ግለሰቡ የደም ማነስ ምልክት ብቻ ሊኖረው ይችላል) የግራው የአንጀት ክፍል ግን የረጋ (የጠቆረ) ደምን ሊያሳይ ይችላል

6.የተለያዩ የአንጀት ኢንፌክሽኖችና የአንጀት መቆጣት
7. የደም አለመርጋት ህመሞች ወይም ተያያዥ መድሀኒቶች

ስለሆነም በፊንጢጣ በኩል የሚኖር ደም መፍሰስ የፊንጢጣ ኪንታሮት ወይም የአሜባ ህመም ብቻ ሳይሆን ከላይ የተዘረዘሩት እና  የሌሎችም ህመሞች ምልክት ሊሆን ስለሚችል ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ይቻላል::

ሰላም!!

ዶ/ር ቢንያም ዮሐንስ: General Surgeon, Colorectal Surgery Fellow

Tuesday, 03 October 2023 00:00

ዝምተኛ ልቦች

አርቲስት ጌትነት እንየው
አምነው የወደዱ፣
ወደው የተካዱ፣
ተክደው የራዱ፣
ፍርሃት አንሸራቶ ቁልቁል የጣላቸው፣
የብቸኛ ልቦች የትነው መውደቂያቸው?
የትነው መድረካቸው?
ማነው አጃቢያቸው?
እንዴት ነው ምታቸው?
የተካዱ ልቦች አጋር የራቃቸው፣
የሚያቀነቅኑት ምንድን ነው ዜማቸው?
የተመረኮዙት እምነት ታጥፎባቸው፣
ድንገት የወደቁ ፍቅር ያዳጣቸው፣
ሚስጥር የሚያጋሩት ሰው የበረዳቸው፣
ብቸኝነት ሰርጎ ብቻ ያስቀራቸው፣
ዝምተኛ ልቦች ምን ይሆን ቋንቋቸው?
ከየት ነው ጥሪያቸው?
በየት ነው ጉዟቸው?
የት ነው መድረሻቸው?
እንደ ሰብአሰገል ጠቅሶ የሚመራቸው፣
የቃተቱ ልቦች የታል ኮከባቸው?
መቼም ከአምላክ ትንፋሽ ከውሃ ከአፈሩ፣
ከእምንት እና እውነት ከፍቅር ሲሰሩ፣
ዝምተኛ ልቦች ጥንቱን ሲፈጥሩ፣
ተገፍትረው ወድቀው፣
ደቀው እንዳይቀሩ፣
በተስፋ ጸንተው ነው ዘላለም ሊኖሩ።
አርቲስት ጌትነት እንየው ባለ ብዙ መልክ የጥበብ ስብእና ያለው ነው። ተውኔት ይፅፋል፣ ያዘጋጃል፣ ይተውናል። ግጥም ይፅፋል ።ደግሞም ደራሲ ነው። ለሃገራችን የኪነጥበብ ጉዞ ሁለገብ አስተዋፅኦ ከሚያበረክቱ የሀገራችን ከያኒዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደም ነው። ብዙዎች የቃላት ሃብት አለው ይሉታል። ቴአትርን ማዘመን ፤ ለቴአትር ህይወት መስጠትን ደግሞ ተክኖበታል። ታላቁ ባለቅኔ ጌትነት እንየው። የህይወት ታሪኩን እዝራ እጅጉ እና ዘቢባ ሁሴን ሰንደውታል፡፡
➻ ውልደት እና እድገት
ጌትነት እንየው ከጎጃም ምድር የፈለቀ ጠቢብ ነው። ወላጆቹ አርሶ አደሮች እርሱም የገበሬ ልጅ ነው። በደብረማርቆስ ከተማ አብማ ማርያም በምትባል መንደር በ 1950 ዓ.ም ተወልዷል።
ጌትነት ያደገው ከታላቅ እህቱ እና ከባለቤቷ ጋር ደብረማርቆስ ከተማ ሲሆን በ 1964 ዓ.ም የእህቱ ባል በስራ ምክንያት ወደ ጅማ ሲዘዋወር ጌትነትም ከእህቱና ከባለቤቷ ጋር ወደ አባጅፋር ሃገር ጂማ ተጓዘ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጎጃም፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጅማ ተምሯል። ገና በለጋ እድሜው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ የተጠናወተው የኪነ-ጥበብ አባዜ በጅማም አብሮት ነበር።
➻ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ጌትነት ትምህርቱን አጠናቆም በጥሩ ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ችሏል። በ 1971 ዓ.ም የመጀመሪያ ምርጫው የሆነውን የትያትር ጥበብን ማጥናት ቀጠለ።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም የግቢውን ባህል ማዕከል እንደርሱ በሚገባ የተጠቀመበት አልነበረም። ባህል ማዕከል ራሱን የሚፈትሽበት እና ራሱን የቀረፀበት ትወናን በማንያዘዋል እንዳሻው "በጠልፎ በኪሴ" ዝግጅት የጀመረበት የራሱንም የመጀመሪያ ተውኔት "ስንብትን" አዘጋጅቶ ለመድረክ ያበቃበት ባለውለታው ስፍራ ነበር።
ጌትነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲማር ዘወትር ኬኔዲ ላይብረሪ እየገባ በርካታ መፅሃፍትን ያነብ ነበር። አባኮስትር የተጠነሰሰው ያኔ ነው። አባኮስትር የካቲት መፅሄትን ሲያነብ ያገኘውና የተሳበበት ሀሳብን ያነሳበት ስራው ነበር።
ጌትነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርቱን በ 1974 ዓ.ም ተመርቆ ወጥቶ በ 1975 ዓ.ም ለተመረቁ ተማሪዎች የመመረቂያ እለት ስለ እናት ፣ ስለ ሃገር፣ ስለማገልገል የሚሰብክ መዝሙርን አዘጋጅቶ ነበር።
ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወዲያው በዝና እንጂ በውል በማያውቀው ብሄራዊ ትያትር ቤት ገብቶ ህልሙን እውን ማድረግ ጀመረ። በብሄራዊ ትያትር በነበረው ቆይታም ከተመልካች አእምሮ ውስጥ በጉልህ የተጻፉ ስራውን ማቅረብ ችሏል፡፡
ጌትነት ጎበዝ ገጣሚም ነው። ግጥምን የሚያነብበት መንገድ ከማንም ጋር የማይመሳሰል የራሱ ዜማ ያለው ፣ ወኔውና ስሜቱ ከነድምፀቱ እጅግ የሚማርክና የሚነዝር ነው።
➻ አበርክቶዎች
የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ዋርካ !ታላቁ ከያኒ ፀሐፊ ተውኔት ጌትነት እንየው በቴአትር ድርሰት ፣ በዝግጅት ፣ በትወና እና በገጣሚነት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ ጥንቅቅ ያሉ ስራዎችን ያበረከተ ፣ ሥነሥርዓት ሞልቶ የተረፈው ጨዋ ፣ ስራዎቹ በፍቅር የሚታዩለት ፣ የኪነጥበብ ታላቅ ሰው ነው። ከስራዎቹ ውስጥ ፦
➻ "ውበትን_ፍለጋ "
ይህ የጌትነት እንየው ድንቅ ተውኔት ሲሆን ግሩም አድርጎ ፅፎት ድንቅ አድርጎም አዘጋጅቶታል። ይኼ ቴአትር የመድረክ ዕይታው ሲጠናቀቅ ወደፊልም ተቀይሮም ተሰርቷል። ወደፊልም ሲቀየር ጌትነት እንየው የመሪ ተዋናዩን "ይገረሙ" የተሰኘውን ገፀ ባህሪ ወክሎ ተውኗል። ቴዎድሮስ ተስፋዬም ፊልሙን ዳይሬክት አድርጎለታል።
"ውበትን ፍለጋ" ጌትነት ከሰባት አመት በላይ የለፋበትና ውጤት ያገኘበት ተወዳጅ ተውኔት ነበር። የኔ የሚለው እምነትና ማንነቱም የተንፀባረቀበት ስራ ነበር። የአፃፃፍ ቴክኒኩ ከመምህሩ መንግስቱ ለማ ያገኘውን እውቀትም ተግባራዊ ያደረገበት ነው።
➻"በላይ_ዘለቀ" (አባኮስትር)
ይህን ቴአትር ጌትነት መድረክ ላይ ሲተውነው : በሚያስገመግም ድምፁ መድረኩ ላይ ጎብለል ጎብለል እያለ ሲምነሸነሽበትና ሲሞላው እጅግ ድንቅ ነው።
ጌትነት እንየው በላይ ዘለቀን ሲተውን ጥላሁን ገሰሰን በፍቅር ያንበረከከ በስራው ያሳመነ እና ያስጨበጨበ ሰው ነበር። ጥላሁን ገሰሰ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ መድረክ ላይ የተመለከተው ሁሉ እጅግ የተደመመበት ታላቅ ስራ ነበር።
➻ " የእግዜር_ጣት"
ጌትነት እንየው የፃፈው ትያትር ሲሆን በዚህ ተውኔት ላይ ተስፋዬ ገ/ሃና ፣ አበባየሁ ታደሰ ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ ፣ ህንፀተ ታደሰ እና ሱራፌል ወንድሙ ድንቅ ትወናቸውን አሳይተውበታል።
የድራማው ዋና ጭብጥ እግዚአብሔር ከፃፈው ውጪ ምንም ነገር ሊፈፀም አይችልም የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍና ድንቅ አስተማሪ ቴአትር ነው።
➻"የቴዎድሮስ_ራዕይ"
ጌትነት ሙዚቃን ከትያትር ጋር አዋህዶ ታሪካዊና ሙዚቃዊ ተውኔቶችን መስራት ተክኖበታል። በዚህም "የቴዎድሮስ ራዕይ" ጉልህ ማሳያ ነው። ቴዎድሮስ ታሪካዊ ትያትር ሲሆን ከ 150 በላይ ተዋንያን የተሳተፉበት ስራ ነው።
ጌትነት ቴዎድሮስን የተመለከተው ሌሎች ካዩበት የሃይለኝነትና የጀግንነት ባህሪ በዘለለ ነው። የጌትነት "ቴዎድሮስ" እጅግ ለሰው የቀረበ ሰውነት ጎልቶ የሚታይበት አፍቃሪና ለፍቅር ተረቺነት ያለው ሰው ነው። ይህንንም ያሳየበት ድንቅ ስራ ነው።
ከበላይ ዘለቀ እና የቴዎድሮስ_ራዕይ ታሪካዊ ተውኔቶች በተጨማሪ "እቴጌ ጣይቱ" ቴአትርንም ፅፏል።
➻"ወይ_አዲስ_አበባ"
ይህ በ 1996 ዓ.ም የብሄራዊ ትያትር ቤት ለእድሳት ተዘግቶ ሲከፈት በአዲስ ስራ መከፈት አለበት ተብሎ በመታሰቡ በርካታ ተዋንያን የተሳተፉበት በጌትነት የተዘጋጀ ስራ ነው ።
ተውኔቱ የአፄ ሀይለስላሴን ፣ የደርግንና የኢህአዴግን የሶስቱንም መንግስታት የአገዛዝ ዘመን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሙዚቃዊ ድራማ ሲሆን ጌትነት ፅፎና አዘጋጅቶ ከጨረሰ በኋላ ለዕይታ ሊበቃ በነበረበት ሰዓት በጊዜው መድረክ ላይ እንዳይታይ ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎ ታግዶበታል።
➻ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ለእይታ የበቁ አጫጭርና የሙሉ ግዜ ተውኔቶች:-
1, ስንብት አአዩ የባህል ማዕከል 1974
2, የግርማ ቀላቢት በብሄራዊ ትያትር ቤት ለእይታ የቀረበ 1974
3, እንቁላል በብሄራዊ ትያትር ቤት እና በአሜሪካን ሀገር ለእይታ የቀረበ 1978-81
4, (final moment) እንግሊዘኛ ሲሆን ወደ አማርኛ ሲመለስ "እውነተኛ ቅፅበት " በብሄራዊ ትያትር ቤት: ካሜሮንና ስዊዲን ሃገር ለእይታ የቀረበ
5, ዲሞቴራፒ በብሄራዊ ትያትር ቤት ለእይታ የቀረበ 1985
6, ሃምሳ አመት ስንት ነው? በአ.አ ዩኒቨርሲቲ (50ኛ ዓመት ክብረ በዓል
= ጌትነት ከተወነባቸው ቴአትሮች መካከል፦
★ ባለካባ እና ባለዳባ ፣ አሉላ አባነጋ ፣ ነፃ ወንጀለኞች ፣የቬኑሱ ነጋዴ ፣ የእጮኛው ሚዜ ፣አንድ ጡት ፣ ውጫሌ አስራሰባት ፣ እርጉም ሀዋርያ እና ሐምሌት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
= በዝግጅት ከተሳተፈባቸው ተውኔቶች ውስጥ፦
የለሊት እርግቦች ፣ የእግዜር ጣት ፣ ውበትን ፍለጋ ፣ ምስጢረኞቹ ፣ ሕንደኬ ፣የቴዎድሮስ ራዕይ ፣ አዙሪት ፣ አባትየው ( ትርጉም ተውኔት ) አዲስ ፀሐይ እና እቴጌ ጣይቱ ጀግና አዘጋጅ መሆኑን ያስመሰከረበት ስራዎቹ ሲሆኑ እነዚህንና ሌሎች ያልተካተቱ ቴአትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት በብቃት ተውኗል።
ጌትነት እንየው ከመድረክ ቲአትሮች በተጨማሪ ብዛት ያላቸው አጫጭር ልብ ወለዶችን፣ አጫጭር የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥራዎችን ለህዝብ አበርክቷል፣
★ “ላይመለስ”፣ “ዲሞቴራፒ”፣ “የቅርብ ሩቅ” እና ለ13 ተከታታይ ሳምንታት የቀረበው፣ “ጥንዶቹ” የተሰኙ የሬዲዮ ድራማዎች በብዙኃን የሬዲዮ ተደራሲያን ዘንድ እንዲታወቅ አድርጎታል::
ከእነዚህ ውስጥ “ላይመለስ” እና “የቅርብ ሩቅ” በሚል ርዕስ የሚታወቁት ድራማዎች በአገራችን ተከስቶ በነበረው ረሀብ ላይ የሚያጠነጥኑ ሥራዎች ሲሆኑ፣ በተለይ “ላይመለስ” የሚለው ሥራ በሬዲዮ ከመቅረቡ በፊት በቴሌቪዥን መታየቱ ይታወሳል፡፡
ጌትነት በሬዲዮ የመጻሕፍት ዓለም ፕሮግራም ላይ የሰርቅ ዳንኤልን፣ “ቆንጆዎቹ”ን ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ መተረኩም ይታወቃል፡፡ የአተራረክ ስልቱ እጅግ በጣም ማራኪ በመሆኑ በጊዜው ከፍተኛ እውቅናን አስገኝቶለት ነበር፡፡ በርካታ የሙዚቃ ግጥሞችን ለሙዚቀኞች እንካችሁም ብሏል።
ጌትነት ለሀገሩ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ በጥበባቸው ለህዝብ ከሚደርሱ ተዋንያን መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያን በብእሩ አሞካሽቷታል። በነጎድጎዳማ ድምፁ አነብንቦላታል። በወኔ ገልጿታል። ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ብሎ በግጥሞቹ ተንፍሶልናል። አስቆናል። ደግሞም አስለቅሶናል።
➻ ምስጋናና ሽልማት
ጸሐፌ- ተውኔት፣ ገጣሚ፣ ተዋናይ እና አዘጋጅ ጌትነት እንየው ለጥበብ ላበረከተው አስተዋጽዖ በርካታ የእውቅና ምስጋናን ተችሮበታል፡ የአማራ ክልል ባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል "ለባህልና ኪነ-ጥበብ እድገት" ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኖ የክብር የእውቅና ሽልማት ሰጥቷታል።
በ 1991 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት በቲአትር የረዥም ጊዜ አገልግሎት ተሸላሚም ነበር።
ጌትነት ከቲአትር ሙያ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት የተዟዟረ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኬንያና ካሜሮን፣ ከአውሮፓ ስዊድንን፣ ከአሜሪካ የተለያዩ ስቴቶችን ጎብኝቷል፡፡ ወደ ቻይናም አቅንቶ የቲአትር ስልጠና ወስዶ ተመልሷል።
መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ጌትነት እንየው ዛሬም የሙያ ክብሩን እንደጠበቀ ያለ ግሩም የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ በትወና ክህሎቱ ፤ በድርሰት እና በዝግጅት ብቃቱ ብዙ ባለሙያዎች መስክረውለታል፡፡ ስለ 1970ዎቹ አጋማሽ የሀገራችን የቴአትር ታሪክ ስናወሳ ጌትነት በዛን ዘመን ብቅ ካሉት አንዱ ነው፡፡ ጌትነት ከ 1975 ጀምሮ ላለፉት 40 አመታት በጽናት ሙያው ላይ የቆየ ነው፡፡ ለዚህ ጽናቱ ልናመሰግነው ግድ ይላል፡፡ የህይወት ታሪኩንም በዚህ መልኩ የሰነድነው የጽናት ተምሳሌትነቱን ለማሳየት ነው፡፡ ስለ ጌትነት ታዳሚያንም ልዩ ፍቅር እንዳላቸው አስተውለናል፡፡ በተለይ የቴዎድሮስ ራእይ ላይ ሲተውን ሙሉ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ታዲያ ጌትነት ከትወና እና ከዝግጅት ባሻገር ጎበዝ ገጣሚነቱም ተመስክሮለታል፡፡ እኛም ለአዲሱ ትውልድ አርአያ የሚሆን ስንል ታሪኩን ሰንደናል፡፡
ታሪክን_ወደኋላ
Tewedaji Media
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
Tuesday, 24 October 2023 00:00

የሎሚ ጥቅም

ሎሚ በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ ከሆኑ  የፍራፍሬ አይነቶች አንዱ ነው። ምንም እንደኳን ሎሚ ጣዕሙ ኮምጣጣ ቢሆንም በርካታ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ሎሚ ለጤና ከሚያበረክታቸው ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

1: ሎሚ ለልብ ጤናን ያገለግላል፤

ሎሚ ጥሩ የቫይታሚን ሲ እና አንቲኦክሲደንትስ ምንጭ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ  ንጥረ ነገሮች ለልብ ጤንነት ጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ ለልብ ህመም እና ስትሮክን ለመከላከል የሚያገለግሉ ሲሆን በሎሚ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ፋይበሮች ደግሞ ለልብ ሕመም የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በእጅጉ ሊቀንሱ እንደሚችሉ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የሎሚ ጭማቂ መውሰድ የደም ግፊትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

2. ሎሚ በሽታ የመከላከል አቅምን ከፍ ያደርጋል፤

ሎሚ በሽታ የመከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርግ ፍራፍሬ  በመሆኑ ለጉንፋን እና ለጉንፋን መሰል በሽታዎች  መንስኤ የሚሆኑ ጀርሞችን የመከላከል አቅምን ይገነባል። አንድ ብርጭቆ የሞቀ ውሃ በሎሚ ጭማቂ በአንድ የሾርባ ማንኪያ መውሰድ ሳልንና ጉንፋን ለመከላከል እንደሚያግዝ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

3: ሎሚ ለምግብ መፈጨት የጎላ አስተዋጽኦ አለው፤

ሎሚ ከፍተኛ መጠን ያለው የሚሟሟ ፋይበር የያዘ በመሆኑ መደበኛ የአንጀት እንቅስቃሴን ለመጠበቅ እና የምግብ መፈጨትን እንደሚያሻሽል የጤና መረጃዎች ያመላከታሉ። በሎሚ ውስጥ የሚገኘው ፖክቲን የተባለው ፋይበር የስታርች እና የስኳር የምግብ አይነቶችን በመፈጨትና በማፋጠን  የአንጀት ጤናን ለማሻሻል ይረዳል።

4.  ሎሚ  ክብደትን ለመቆጣጠር ያግዛል፤

ሙሉ በሙሉ የተጨመቀ ሎሚ በአንድ ብርጭቆ ለብ ባለ ውሃ አንድ የሾርባ ማንኪያ ማር በማድረገ መጠጣት ክብደትን ለመቀነስ እንደሚረዳ የጤና መረጃዎች ያስረዳሉ። ሎሚ  ክብደትን የሚጨምሩ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ከመመገብ የሚከለከል  ፔክቲን የተባለ ንጥረ ነገር ያለው በመሆኑ ለክብደት መቀነስ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሎሚ ውስጥ የሚገኙት አንቲኦክሲደንትስ ክብደትን ለመቆጣጠር ይጠቅማሉ፡፡

5፡ ሎሚ የካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይረዳል፤

ሎሚ እና የሎሚ ጭማቂ የበለፀጉ የቫይታሚን ሲ ምንጭ በመሆናቸው እንደ ካንሰር ያሉ ገዳይ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዱ ፀረ-አንቲኦክሲዳንቶች እንዳሏቸው የጤና መረጃዎች ያመልክታሉ፡፡

6: ሎሚ በአፍ ውስጥ የሚከሰትን ህመም ያስታግሳል፤

ቫይታሚን ሲ ለጥርስ እና ለድድ አስፈላጊ በመሆኑና ሎሚ ደግሞ  በቫይታሚን ሲ የበለፀገ በመሆኑ በአፍ ውስጥ የሚከሰቱ በሽታዎች ለመከላከል ይጠቅማል። ስኩዊቪ በቫይታሚን ሲ እጥረት የሚመጣ በሽታ ሲሆን  ለድድ እብጠት፣ መድማት ወዘተ የሚዳርግ በሽታ ሲሆን ሎሚን በመጠቀም ይህን በሽታ ለመከላከል ያግዛል እንደ ጤና ባለሙያዎች መረጃ፡፡

7: ሎሚ ለቆዳ ጠቃሚ፤

ሎሚ ከፍተኛ መጠን ያለው የቫይታሚን ሲ ይዘት ስላለው ለቆዳችን ወፍራም እና ወጣት መልክ የሚሰጠውን ኮላጅንን ያመነጫል፡፡ ኮላችን ቆዳችንን እንዲያመር ከማድረጉም ባለፈ በፊት ላይ የሚገኙ ጥቃቅን መስመሮችን ለመቀነስ እና ቆዳን ለማጥራት ያገለግላል፡፡

ሎሚ በረካታ  ንጥረ ነገሮች ያሉት በመሆኑ ከተለያዩ  ምግቦች ጋር መጠቀም መቻል የበለጠ ገንቢ እና ጤናማ ቆዳ እንዲኖር ያደርጋል፡፡

የሎሚ ዘይት ጭንቀትን በማረጋጋት እና መንፈስን በማደስ ስሜትን ሊያሻሽል እንደሚችልም ነው የጤና ባለሙያዎች የሚያስረዱት።

8. ሎሚ የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል ይረዳል፤

በትኩስ ፍራፍሬ ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የሲትሪክ አሲድ እና የሎሚ ጭማቂ ክምችት የሽንት መጠንን ሳይቀይር የሽንት ሲትሬትን መጠን በሁለት እጥፍ ለማሻሻል ያስችላል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሎሚ ጭማቂ የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል የሽንት ሲትሬትን በመፍጠር ለክሪስታል እድገት መከላከያ ዘዴ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

9. ሎሚ ለጉሮሮ ኢንፌክሽን ጠቃሚ፤

ሰዎች ጉሮሯቸውን በሚታመምበት ጊዜ  ብዙውን ጊዜ የሎሚ ጠብታዎችን እንዲጠቀሙ እንደሚመከር የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ምክንያቱም ሎሚ በተፈጥሮ ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪያት ስላለው የባክቴሪያውን ተፅእኖ ስለሚቀንስ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሎሚ በርካታ የጤና በረከቶች እንዳሉት በጤና ባለሙያዎች ይነገራል፡፡ስለዚህ ሎሚን የምግባችን አካል በማድረግ ጤናችንን መጠበቅ ይገባል፡፡

አንጋፋው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኢጄታ የአሜሪካን ብሄራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ሽልማትን ከፕሬዚደንት ጆ ባይደን ተቀብለዋል።
ፕሮፌሰር ጋቢሳ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ብሔራዊ የክብር ሽልማት ከተሸለሙ 21 አሜሪካውያን ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።
መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ ለሽልማቱ ያበቃቸው በከፍተኛ የምርምር ስራቸው የእፅዋት ዘረመል ምህንድስና በመጠቀም በረሃማ የአየር ንብረት እና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው ነው።
ግኝታቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የምግብ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ ታምኖበታል።
ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ በምግብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ከዚህ በፊት ከዓለም የምግብ ፕሮግራሙ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ፕሬዚደንት ባይደን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ይፋ ባድረጉት የተሸላሚዎች ዝርዝር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ለሽልማት የበቁትን ተመራማሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እና ለሰላም ላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅዖ ፣ ያሳዩት በሳል እና ምሳሌያዊ አመራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ መሪዎች ምሳሌ የሚሆንና መነሳሳት የሚፈጥር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህንን Doctorate of Philosophy እንዳበረከተላቸው የትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደሪስ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶ/ር ዣክሊን ሞሀየር ገልፀዋል::
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር እና የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለሌሎች ሃገራት መሪዎች አርአያ የሚሆን ስራ በመስራታቸው የጆርጂያ ግዛት የክብር ዜግነት ሽልማት እንደተበረከተላቸው የግዛቱ ሴናተር ጋይል ዴቨንፓርት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል::
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ለዚህ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
AAU Confers full professorships on seven faculty members.
1. ፕሮፌሰር ዮናስ ጨቡዴ
በኢንኦርጋኒከ ኮሚስተሪ
2. ፕሮፌሰር አህመድ ሙስጠፋ
በኮምፒቲሽናል ኬሚስተሪ
3. ፐሮፈሰር ኑርልኝ ተፈራ
በኬሚካል ኢነጂነሪንግ
4. ፐሮፌሰር አምቢሳ ቀነዓ
በጄነራል ኢዱኬሽን
5. ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጋሻው
በፊዚክስ
6. ፐሮፌሰር አበባው ይረጋ
በሀየር ኢዱኬሽን
7. ፕሮፈሰር ታደሰ በሪሶ
በአንትሮፖሎጂ
Tuesday, 24 October 2023 19:53

https://online.fliphtml5.com/etocz/wusy/

Page 10 of 678