Administrator

Administrator

የቻይና ብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ ለመስጠት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ተልዕኮ ያለው 12ኛውን የወታደራዊ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ቡድን ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስታወቀ። ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከቻይና የተነሳውና 13 አባላት ያሉት ይህ የባለሙያዎች ቡድን፤ በአጥንት ሕክምና፣ በተላላፊ በሽታዎች፣ በዓይን ሕክምና፣ በነፍስ ወከፍና የመተንፈሻ አካላት ሕክምና፣ በሽንት ቧንቧ ሕክምና፣ በአጠቃላይ ቀዶ ጥገና እንዲሁም በባህላዊ የቻይና ሕክምና ላይ የተሰማሩ ታዋቂ ስፔሻሊስቶችን ያካተተ ነው። ቡድኑ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሆስፒታሎች ውስጥ በመገኘት ክሊኒካዊ ምርመራዎችን፣ የሰው ኃይል ሥልጠናዎችንና የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት የሕክምና አቅምን ለማጠናከርና አዳዲስ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ዝግጁ ሆኗል።
ይህ ስምሪት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ሜይ 2025 ላይ ተሰማርቶ የነበረውንና 14 ወታደራዊ ሐኪሞችን ይዞ የመጣውን 11ኛውን ቡድን የሚተካ ሲሆን፣ በወቅቱ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ የላከችው “ከፍተኛው የጦር ሕክምና ቡድን” ተብሎ ተገልጾ ነበር። ከ2015 ጀምሮ የቻይና ሕዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ከ100 በላይ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ የላከ ሲሆን፣ እነዚህ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትና ለሲቪሎች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ አጠናክረዋል። ይህ ሰፊ ፕሮግራም ቻይና በዓለም አቀፍ ሰብአዊ ትብብር ላይ ያላትን ንቁ ተሳትፎ የሚያሳይና “ለሁሉም የሚተርፍ ዓለም አቀፍ የጤና ማኅበረሰብ የመገንባት” ራዕይ አካል መሆኑ ተገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ጥሎት የነበረውን ጥብቅ የሸንገን ቪዛ ገደብ ለማንሳት መወሰኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ የንግድ ምክር ቤት አስታወቀ። ኅብረቱ ይህንን ውሳኔ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ገደቡ የተጣለው የኢትዮጵያ መንግሥት በአውሮፓ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ሰነድ የሚኖሩ ዜጎቹን መልሶ ለመቀበል በቂ ትብብር አላደረገም በሚል ምክንያት እንደነበር ይታወሳል።
ይህ የተጣለው የቪዛ ገደብ ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፓ ለመግባት ቪዛ ለማግኘት የሚፈጅባቸውን ጊዜ ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት ያራዘመ ከመሆኑም በላይ፣ የአባል አገራቱ የሸንገን ቪዛ እንዳይሰጡ አግዶ የቆየ ነበር። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ዜጎች መልሶ በመቀበል ረገድ ያሳዩትን መሻሻል ተከትሎ ኅብረቱ ውሳኔውን ለመቀየር መገደዱ ታውቋል።
ኬንያ በቢሊየነሩ ኢሎን ማስክ የሚመራው ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ቢሮ እንዲከፍት የሦስት ወር የጊዜ ገደብ እንደሰጠችው ተሰማ። ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን ማህበራዊ ሚዲያው በሀገሪቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እገዳ ሊጣልበት እንደሚችል ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያው በኬንያ ውስጥ እየሰራ የሚገኘው በጊዜያዊ ፈቃድ ሲሆን፣ የኬንያ ባለስልጣናት ግን ኩባንያው በሀገር ውስጥ ቢሮ በመክፈት የሀገሪቱን ህጎችና ደንቦች በጥብቅ እንዲያከብር ግፊት እያደረጉበት ይገኛል። ኬንያ በአለም አቀፍ ደረጃ በንቁ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነቷ የምትታወቅ ሀገር በመሆኗ፣ ለኤክስ በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ቁልፍና ትልቅ የገበያ መዳረሻ ናት።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
ዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ በናይጄሪያ ባለስልጣናት ላይ አዲስ ክስ መስረተ። ማጣሪያው የነዳጅ ምርትን በሀገር ውስጥ እያመረተ ቢሆንም፣ መንግስት የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ የማስገባት ፈቃድ መስጠቱ የሀገር ውስጥ ማጣሪያዎችን አቅም የሚጎዳና ቀደም ሲል የተሰጠውን የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚጥስ ነው ሲል ተከራክሯል።
ኩባንያው እንዳለው ከሆነ፣ ማማጣሪያው ናይጄሪያ በውጭ ነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ይቀንሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አሁንም ነዳጅ ከውጭ እንዲገባ መፈቀዱ አግባብ አይደለም ብሏል።
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ክስ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ አዲስ ክርክር በገበያ ውድድር፣ በዋጋ ተመንና በነዳጅ ገበያው ቁጥጥር ላይ የነበረውን ከፍተኛ ውጥረትና ፍጥጫ እንደገና ቀስቅሶታል።
ልክ ስራ እንደጀመርኩ ቅዳሜ ከቤቴ ወደ ሜክሲኮ በታክሲ እሄዳለሁ፤ 1.50 ብቻ ከፍዬ። ሜክሲኮ እንደደረስኩ የተቀጣጠርኩት ሰው ካለ ከሰው ጋር፣ ከሌለም ብቻዬን የምወደውን እንቁላል ፍርፍር አዛለሁ፤ በላዩ ላይ ቆንጆ ቡና እጠጣለሁ። የእለቱን ጋዜጦችና መፅሔቶች በስሙኒ ኪራይ አነባለሁ፤ የወደድኩትን ጋዜጣ ወይም መፅሔት እገዛለሁ። ጠቀም ያለ ቲፕ ለአስተናጋጆች እተዋለሁ፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
በታክሲ ወደ ፒያሳ አቀናለሁ። አራዳ ህንፃ ላይ አረፍ ብዬ ውሃ አዛለሁ፤ ለስራ የማገኛቸው ወዳጆቼ ጋር እናወራለን። «ቁርስ ካልበላችሁ ብሉ፣ ጠጡ» እላለሁ። እናም ለመክፈል ግብግብ እንገጥማለን፤ «እኔ ነኝ የምከፍለው... ስርዓት ያዝ!» እየተባባልን፤ ምክንያቱም ...ስራ አለን!
ከዳላስ ሙዚቃ ቤት አለፍ ብሎ የሚገኝ ካፌና ሬስቶራንት ነበር፤ እዛ እንሄዳለን። ማኪያቶ ቡና እንጠጣለን፣ እናወራለን፤ ፒዛቸውም አሪፍ ነበር፣ ፒያሳ በወርቅ ቤቶቹ መደዳ አልፎ ያሉት ካፌወች ውስጥ .... እንዝናናለን፤ ምክንያቱም... ስራ አለን!
ምሳ ሰዓት ይደርሳል፤ ብዙ ምርጫ ነው ያለው። ወደ አራት ኪሎ አመራለሁ፤ ሮሚና ቋንጣ ፍርፍር ወይም እዛው ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል። (ምሳ ሰዓት ፒያኖ የምትጫወት ጠይም ሴት ነበረች)፤ አጤ ሚኒሊክ ራሳቸው እዛ ሆቴል እንደ እኛ አልተዝናኑም፤ ምክንያቱም... ስራ አለን! ስራ ለራስ የሚሰጠው ንግስና አለ።
ከሰዓት ሌላ ጀመዓ ይመጣል፤ በልቶ ጠጥቶ የሚያዛጋ። «እናንተ ልጆች ይሄን ጫት ተው ብል በቃ አልሰማ አላችሁ?» እልና፣ «እግዜር ለጫት አዋጣህ እንዳይለኝ፤ እስቲ አሪፍ ራት ማታ ብሉ» ብዬ የሆነ ብር ሸጎጥ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
ስንለያይ ወደ አሮጌ ተራ ወይም ኤልያስ ጨበሬው ጋር ጎራ እልና ወይም እግር ከጣለው አዟሪ አዲስ የታተመ መፅሐፍ ካለ መፅሐፎች እሸምታለሁ። አለፍ ስል አንዱ ሱቅ ቆንጆ ቲሸርት ወይም ጫማ ካየሁ እሸምታለሁ፤ምክንያቱም.. ስራ አለኝ።
ማሳረጊያዬ ቲያትር ነው፤... ቲያትር አያለሁ። ወደ ቤት ስመለስ «ሺህ ዓመት አይኖር!» እልና 40 ወይም 50 ብር ሆጭ አድርጌ በኮንትራት ላዳ ታክሲ ነው። መግቢያዬ ላይ ካለች ፍራፍሬ መሸጫ የተወሰነ ማንሳቴም አይቀርም፤ ምክንያቱም... ስራ አለኝ!
ሩቅ አይመስልም? ከአስር ዓመት ብዙ አይርቅም! እኔ የምለው... ስራ አላችሁ? እስቲ «ስራ አለኝ» ብላችሁ ጀምሩና ስራችሁ እንዴት እንደሚያኖራችሁ አካፍሉን...
(አሌክስ አብርሃም)
የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጥምረት ባወጣው ባለ 11 ነጥብ መግለጫ በቅድመ-ምርጫ ሂደት ላይ በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል። ጥምረቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 15 ዕጩዎቹ "በሲስተም ምክንያት" እንዳይመዘገቡ መደረጉንና በተለያዩ አካባቢዎችም በዕጩዎች ላይ የማወከብና የግድያ ማስፈራሪያ መፈጸሙን አመልክቷል። በተጨማሪም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች 97 በመቶ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ አለ ተብሎ የቀረበው ሪፖርት ፍጹም የተዛባና አሳሳች ነው ሲል በጽኑ ተችቷል።
በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ጥምረቱ የመራጮች መረጃ ምንተፋና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የጠየቀ ሲሆን፣ በመንግስት ላይም ጠንካራ ጥሪዎችን አስተላልፏል። በዚህም መሰረት መንግሥት የገባውን የለውጥ ቃል እንዲያከብር፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ እንዲፈታና ለዘላቂ ሀገራዊ አንድነት ሲባል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና በትብብር እንዲሠራ ጥሪ አቅርቧል።
በቅርቡ ይፋ የሆነው የሞርጋን ስታንሊ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰው መሰል (Humanoid) ሮቦቶች በፋብሪካዎች፣ በጤና ተቋማትና በቤቶቻችን ውስጥ አብረውን መስራት ይጀምራሉ። እስከ 2035 ዓ.ም ድረስ የሮቦቶቹ ቁጥር 13 ሚሊዮን ሊደርስ የሚችል ሲሆን፣ የአንዱ ዓመታዊ የኪራይ ወይም የባለቤትነት ዋጋ 10,000 ዶላር አካባቢ ስለሚሆን ልክ እንደ መኪና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ወገኖች ዘንድ በቀላሉ ሊገዛ የሚችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል።
ይህ ተመጣጣኝ ዋጋ የገበያ ፍላጎቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማናር፣ እስከ 2050 ዓ.ም ድረስ በዓለማችን ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሮቦቶች ቁጥር ወደ 1 ቢሊዮን ሊያሳድገው እንደሚችል ተተንብዮአል። በአሁኑ ወቅትም እንደ 'Digit' እና 'Figure 02' ያሉ የሮቦት ሞዴሎች በአሜሪካ የቢኤምደብሊው እና የፎክስኮን ፋብሪካዎች ውስጥ ዕቃዎችን በማንሳት፣ ደረጃ በመውጣትና የሰው ልጅ መገልገያ መሣሪያዎችን በመጠቀም በተግባር ላይ ውለዋል።
ይህ አስደናቂ እቅድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ የመጣውን የቋንቋ፣ የምስል መለያና የእጅና እግር እንቅስቃሴ ቁጥጥር ከፍተኛ ዕድገት ተከትሎ የመጣ ነው። አሁን ላይ ያሉት ሮቦቶች እንደ ፊልሞች ሁሉንም ነገር በአንድ ላይ ማድረግ የሚችሉ ባይሆኑም፣ ልክ እንደ ቻት ጂፒቲ ለተወሰኑ የተለዩ ሥራዎች ተስማሚ ሆነው ነው የሚሰሩት። ሆኖም ግን ይህ የቴክኖሎጂ አብዮት የራሱ የሆኑ ፈተናዎችን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፤ ሮቦቶቹ ለረጅም ጊዜ እንዲሰሩ ይበልጥ ቀልጣፋ ባትሪዎችንና ጠንካራ ቁሶችን መፍጠር የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን የሚፈትን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማሽኖቹ የሰውን ልጅ የሥራ ዕድል ሙሉ በሙሉ በመንጠቅ በርካታ ሠራተኞችን ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርጓቸው ስጋት ፈጥሯል። ከዚህም ባሻገር “ሮቦፎቢያ” (የሮቦት ፍርሃት) ያለባቸውን ሰዎች የስነ-ልቦና ጤንነት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይገመታል።
እስከ 2050 ዓ.ም ድረስ ሮቦቶቹ በየአካባቢያችን በስፋት የሚታዩ ሲሆን፣ ይህም ማለት በምድር ላይ ለእያንዳንዱ ስምንት ሰው አንድ ሮቦት ይኖራል ማለት ነው። ጥናቱ እንደሚጠቁመው፣ በተለይ በአሜሪካ ውስጥ 10 በመቶ ያህሉ አባወራዎች በቤታቸው ውስጥ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚያግዝ፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን የሚንከባከብ እንዲሁም ጥበቃ የሚያደርግ ሮቦት ይኖራቸዋል። በተለይም ዓመታዊ ገቢያቸው 200 ሺህ ዶላርና ከዚያ በላይ የሆኑ የአሜሪካ ዜጎች ከሮቦቶች ጋር የመኖር ዕድላቸው 33 በመቶ ይደርሳል። በሌላ በኩል ርካሽ የሆኑ የቻይና ሮቦቶችና የአቅርቦት ሰንሰለቶች መስፋፋት ቴክኖሎጂው በኤዥያ ሀገራትም በፍጥነት እንዲሰራጭ ትልቅ በር ይከፍታል።
ይህ የወደፊት የሮቦቶች ዘመን ግን በርካታ የሞራልና የሕግ ጥያቄዎችን ያስነሳል። መንግስታት ሮቦቶችን ለፖሊስነትና ለስለላ ሥራ እንዲያውሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል? የግል ኩባንያዎችስ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ አልፎ ተርፎም ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ሮቦቶቹን መልሰው እንዲያጠቁ ሊያዟቸው ይችላሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማሽኖቹ ይበልጥ ብልህ፣ ንቁ እና የራሳቸው ህሊና እና ስሜት ያላቸው ፍጡራን እየሆኑ ሲመጡ "እንደ ባሪያ ያለ ደሞዝ ማሰራት ተገቢ ነው ወይስ መብት ሊሰጣቸው ይገባል?" የሚለው ክርክር የዓለማችን ትልቁ የባህልና የማንነት መናወጥ መሆኑ አይቀሬ ነው።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
ይህ በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረው የሊቅ ቅዱስ ያሬድ ምስል የሁለገቡ የቴአትር ባለሙያ የሳሙዔል ተስፋዬ የብሩሽ ውጤት መሆኑን ስንቶቻችሁ ይሆን የምታውቁ?
ሳሚ ደራሲ፣አዘጋጅ፣ተርጓሚ፣ ተዋናይ፣የመድረክ ዲዛይነር እና ሰዓሊ ነው።
አሁን እንኳን መድረክ ላይ ሁለት ስራዎች አሉት ። "ባሎች እና ሚስቶች" ማክሰኞ በ12 ሰዓት በአለም ሲኒማ፣ "ሸምጋይ" ሐሙስ በ12 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር።
በቅርቡ ደግሞ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቴአትር ሙዚቃዊ ድራማ እንዲሁም በሀገር ፍቅር ቴአትር ሌላኛውን ቴአትር ይዞ ይከሰታል።
ውድነህ ክፍሌ-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
በአዲስ አበባ ከተማ ለጥበብ አፍቃሪያን ታላቅ የምስራች ተሰምቷል። "ወህኒ አንባ" የተሰኘው አዲስ ታሪካዊ ቴአትር በመጪው እሁድ ግንቦት 16 ቀን በድምቀት ይመረቃል። ይህ በጉጉት የሚጠበቀው ታላቅ የጥበብ ስራ ፍላሚንጎ አካባቢ በሚገኘው ዘመናዊው የህጻናት እና ወጣቶች አርት ኮምፕሌክስ መድረክ ላይ የሚቀርብ ሲሆን፤ በደራሲ መልካሙ ዘሪሁን ተፅፎ፣ በአዘጋጅ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ እና በረዳት አዘጋጅ ተስፋዬ ሲማ እጅግ ማራኪ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቷል። ታዋቂ እና አንጋፋዎቹ የራስ ቴአትር ተዋናዮች የሚሳተፉበት በመሆኑ፣ ተዋናዮቹ የተለመደ ብቃታቸውን በተለየ ደረጃ ያሳዩበታል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የቴአትር ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ መሆኑን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደርም በቅርፅም ሆነ በይዘት ደረጃቸው እጅግ ከፍ ያሉ አዳዲስ ቴአትሮችን ወደ መድረክ እያመጣ በመሆኑ ትልቅ ምስጋና የተቸረው ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማትም እነዚህን ስራዎች ለህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ላቅ ያለ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…