
Administrator
“አያልቅበት” – ኤፍሬም!!
ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነው – ኤፍሬም እንዳለ። አለቀ። ከዚህ ውጪ ስለ እሱ ግላዊ ሕይወትና ማንነት፣ ጥረትና ልፋት በሕትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች ሲነገር ሰምቼ አላውቅም። የእሱም ፍላጎትም፣ ግድም አይመስለኝም፤ አደባባይ መውጣቱ። ደም ለመመለስ ቤቱን አቃጥሎ የሸፈተ ሰው፣ መልኩን አይደለም ጥላውን ሳያሳይ ጫካና ጥሻን ተከልሎ ወደ ዒላማው ጥይቱን እንደሚልከው ሁሉ፣ እሱም ካለበት ጥጋት ተሰትሮ በብዕር ከመተኮስ ውጪ በታይታ ሰውነቱ አይታወቅም።
ኤፍሬም ወደ ሰላሳ ለሚጠጉ ዓመታት – በእኔ ዕውቀት ከ”ፀደይ” መጽሔት ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ምፀት - ለበስ ወጎችንና ጨዋታዎችን ሲያስኮመኩመን አሁን ድረስ አለ። ዘወትር ቅዳሜ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት “ጨዋታዎቹን” የሚያስነብብባትን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣን ባገላበጥኩና ጽሑፎቹን ባነበብኩ ቁጥር እጅጉን የምደመምበት ነገር ቢኖር የጨዋታዎቹ ለዛቸውን ጠብቀው መቆየታቸው፣ ዕይታዎቹና የሚያነሳቸው ጉዳዮች፣ እንዲሁም የብዕሩ ከዘመን ዘመን ሳትከሽፍ የኅብረተሰባችንን ጉዳዮች በራሱ በኅብረተሰቡ ወቅታዊው አስተሳሰብና አነጋገር እነሆ ማለቱ ነው። ትናንት አራዳ፣ ዛሬም አራዳ ነገም አራዳ እንደሆነ ስለመዝለቁ ያሳብቃሉ – ለወጉ ማዋዣነት ጣል የሚያደርጋቸው አስቂኝ ቀልዶችና ገጠመኞች።
ኤፍሬም፤ በ”ፀደይ” መጽሔት “እንጨዋወት አምድ”፣ “Ethiopian Herald” ጋዜጣ “Between you and me” አምድ ላይ በአምደኝነት በ”The Sun” ጋዜጣ ከአንጋፋ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር በአዘጋጅነት፣ በ”ምዕራፍ” ጋዜጣ ከእነ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጋር በመሆን በዋና አዘጋጅነት፣ ካለፉት 17 ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ደግሞ በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ አምደኛ ነው።
መጻሕፍትን ለንባብ በማብቃቱም ረገድ፤ እጅግ ተነባቢና ተወዳጅ የነበረውን የሮበርት ሉድለምን መጽሐፍ “ፍንጭ” በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅቷል። የቱርካዊውን አዚዝ ኔሲን “እራሴን አጠፋሁ” የተሰኘ መጽሐፍም በኤፍሬም እንዳለ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃ ነው። እሱ ያዘጋጀውን “ቤርሙዳ ትርያንግል” የተባለ መጽሐፍም ከብዙ ዓመታት በፊት ማንበቤም ትዝ ይለኛል። “የዘመን ዱካ” እና “ሕይወት በክር ጫፍ” የተሰኙ ሥራዎችም አሉት። በተለያዩ መጽሔቶችና “እፍታ” መጽሐፍ ላይ የወጡ የራሱንና ትርጉም አጫጭር ልቦለዶችን ለአንባቢያን አበርክቷል። “የጉራ ሊቅ”ን ያስታውሷል። “እንግሊዘኛን በቀላሉ” የተባለች ለእንግሊዘኛ መማሪያነት የምታገለግል በኪስ የምትያዝ ታዋቂ መጽሐፍም ነበረችው። ጋዜጣና መጽሔት ላይ ወጥተው የተነበቡ ሥራዎቹንም በመጽሐፍ መልክ አሳትሟቸዋል።
በኢትዮዽያ ሬድዮ “ቅዳሜ መዝናኛ” እና በሸገር ሬድዮ “የጨዋታ” ፕሮግራም ላይ የተላለፉ ተከታታይ እና አጫጭር አዝናኝ ድራማዎችን በመድረስና በመተርጎም ለአድማጮች እንዲደርሱ አድርጓል። ተደንቆበታልም። “ስካይ ፕሮሞሽን” የሚል የማስታወቂያ ድርጅት አቋቁሞ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደ ነበር አስታውሳለሁ – አሁን ይቀጥልበት አይቀጥልበት ባላውቅም።
አንዲት ሚጢጢ መጽሐፍ አበርክቶ ሰማይ ልንካ የሚል ውርንጫ ጸሐፊ በሞላበት ሀገር፣ ይህን ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ድምፁን አጥፍቶ ትልቅ ተግባር የከወነን ሰው አለማንሳት፣ አለማውሳት ትልቅ ሀፍረት ነው – ለሁሉም። ክብር ለሚገባው ሁሉ ክብር ይሁን፤ አበቃሁ!!!
ማሳሰቢያ:– ከኤፍሬም እንዳለ ሰብዕና፣ ሥራዎችና ጥረት አንፃር ይህ ልጥፍ ጽሑፍ 1% ያህል አይሰጠውም ከመቶው። ይሁን እንጂ ከእኔ በተሻለ ስለ እሱና ስራዎቹ የምታውቁ፣ በዚህች ቅንጭብ ጽሑፍ ላይ የታያችሁን ስህተት በእርማት፣ የቀረውን ደግሞ በአስተያየት ታሟሉታላችሁ ብዬ በማመን ነው እዚህ ያሰፈርኩት። ተሳትፎአችሁ ይጠበቃል!!!
“ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ቢሰበር በአንዱ ተንጠልጠል!”
አንድ የአርሜኒያ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ የአርሜኒያ ንጉስ፣ አፍ-ጠባቂዎቹን በመላ ሀገሪቱ ልኮ “ከድፍን አርሜኒያ በመዋሸት አንደኛ ለሆነ ሰው፣ ንጉሱ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ፍሬ ሊሸልሙ ይፈልጋሉ!” እያሉ እንዲነግሩና እችላለሁ የሚል ማንኛውም ሰው እንዲመጣ እንዲደረግ ትእዛዝ ይሰጣሉ። የሀገሩ ውሸታም ሁሉ ወደ ቤተ-መንግስት መጉረፍ ይጀምራል፡፡ ግቢውን መግቢያ መውጫ አሳጣው ሰዉ፡፡ እንደእየ ማእረጉ ከየኑሮ እርከኑ ያለ ሰው መጣ፡፡ መሳፍንትና ልኡላን፣ ታላቅ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች፣ ቀሳውስት፣ ባለፀጎችና ደሆች፣ ወፍራም ቀጭን፣ አጭር እረጅም፣ ቆንጆና አስቀያሚ፡፡ በአገሩ የቀረ የሰው አይነት ያለ አይመስልም፡፡
አርሜኒያ የውሸታም እጥረት ኖሮባት አያውቅም፡፡ ሁሉ እየመጣ ለንጉሱ ውሸቱን አወራ፡፡ ወሸከተ፡፡ ንጉሱ ግን ከዚህ ቀደም የውሸት አይነት በገፍ ሰምተው ስለነበር፣ አሁን እየሰሙአቸው ያሉት ውሸቶች እንደ ድሮ ውሸት አልጥምም አላቸው፡፡ ምርጥ የሚሉት ውሸት አጡ፡፡ ማዳመጡም ደከማቸው፡፡ በጣም ከመሰልቸታቸው የተነሳ ውድድሩን ያለአሸናፊ ሊዘጉት ፈለጉ-በጨረታው አልገደድም ብለው፡፡
ሆኖም በመጨረሻ አንድ ጭርንቁሳም ደሃ መጣ፡፡
“እህስ ምን ልርዳህ አንተ ዜጋ?” ሲሉ ጠየቁ ንጉሱ፡፡
“ንጉስ ሆይ” አለ ዜጋው ትንሽ እንደመደናገጥ ብሎ “እንደሚያስታውሱት ከዚህ ቀደም፤ አንድ እንስራ ወርቅ ሊሰጡኝ ቃል ገብተውልኝ ነበር” አላቸው፡፡
“ማ? እኔ? ለአንተ?”
“አዎን ንጉስ ሆይ፤ ለአያሌ ሰው ብዙ ቃል ስለሚገቡ እረስተውት ይሆናል እንጂ፤ በእርግጥ እሰጥሃለሁ ብለውኝ ነበር!”
“ይሄ ፍፁም ውሸት ነው! አንተ ቀጣፊ ሰው ነህ! ምንም ገንዘብ ላንተ ልሰጥ ቃል አልገባሁም”
“እንግዲያው ይሄ ፍፁም ውሸት ነው ካሉ፤ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ፍሬ እሸልማለሁ ብለው አውጀው ነውና የመጣሁት፤ ሽልማቱ ለኔ ይገባኛል፡፡ የወርቁን ፍሬ ይስጡኝ” አላቸው፡፡
ንጉሱ ይሄ ዜጋ በዘዴ ሊያታልላቸው መሆኑን አሰቡና፤
“የለም የለም፤ አንተ ውሸታም አይደለህም” አሉት፡፡
“እንግዲያው ቃል የገቡልኝን አንድ እንስራ ሙሉ ወርቅ ይስጡኝ” አለ፤ ፍርጥም ብሎ፡፡
ንጉሱ አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፡፡ ከወርቅ የተሰራውን ትልቅ ፍሬ የግዳቸውን ለደሃው ሸለሙት፡፡
***
እውነተኛ ውሸት የሚዋጣለት ሰው እንኳ እንዳይጠፋ መመኘት ጥሩ ነው፡፡ ያ ሁሉ መኳንንት መሳፍንት፣ ነጋዴ ወዘተ ወሽክቶ ወሽክቶ የሚታመንና ማራኪ ውሸት መጥፋቱ ትልቅ ድክመት ነው፡፡ በአንፃሩ በገዛ አዋጁ፣ በገዛ መመሪያው፣ በገዛ ፕሮግራሙ፣ በገዛ እቅዱ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገባ መሪ፣ አለቃ፣ ሃላፊ፣ የፖለቲካ ሰው፣ የፓርቲና የማህበር የበላይ ሃላፊ ሁሉ፤ ውሎ አድሮ የሚከፍለው እዳ እንዳለ ማስተዋል ደግ ነው፡፡ የምንገባው ቃል እራሳችንን መልሶ የሚጠልፈን እናም የሚጥለን ሊሆን እንደሚችል አለመዘንጋት ነው፡፡
በታሪክ “አደገኛው ኢቫን” (Ivan the Terrible) በመባል ይታወቅ የነበረው የሩሲያ ንጉስ፤ አንዴ አስከፊ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቆ ነበር ይባላል፡፡ ይሄውም፤ በአንድ በኩል፤ ሀገሪቱ ለውጥና መሻሻል ትፈልጋለች፡፡ በሌላ በኩል፣ ወደፊት ገፍቶ ወደተሻለ አገር እንዳይለውጣት አቅም አጣ፡፡ በዙሪያው ያሉት ሁነኛ የሚላቸው ሰዎች ደግሞ ገበሬውን ሡሪ-ባንገት-አውልቅ የሚሉት ልኡላን ናቸው፡፡ በዚህ መካከል ንጉሱ ታመመና ሊሞት ተቃረበ፡፡ ለልኡላኑ፤ “ልጄ አዲሱ ዛር ነጋሲ(ንጉስ) እንዲሆን አድርጉ” አለ፡፡ ልኡላኑ ተቃወሙት፡፡ ያኔ ስልጣኑና አቅሙን እንደወሰዱበት ገባው፡፡ ወዳጅ ጠላቱን አወቀ፡፡
በዚያን ጊዜ ሩሲያ ዙሪያዋን ጠብ ተጭሮባት ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ግን እሱ ከሞት ዳነ፡፡ አንድ ጠዋት ማንንም ሳያሳውቅ የዛሩን መንግስት ሃብት ንብረት ይዞ ከቤተ-መንግስት ወጣ፡፡ አገሪቱ በድንገት ስጋት ላይ ወደቀች፡፡ ጥቂት ሰንብቶ ንጉሱ ደብዳቤ ላከ፤ “የልኡላኑንና የመሳፍንቱን ተንኮል ስላልቻልኩት ስልጣኔን ለቅቄያለሁ” አለ፡፡ ዜጋው፣ ነጋዴው፣ ሃብታሙ ግን ከጭንቀት ብዛት ዝም ብሎ ሊቀመጥ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያለበት ድረስ ሄዶ ተማጠነው፡፡ ንጉሱም ከብዙ ልመና በኋላ በመጨረሻ ሁለት ምርጫ ሰጣቸው፡፡ “ወይ ሙሉና ፍፁም ስልጣን ስጡኝ፡፡ ማንም ጣልቃ አይግባብኝ አልያ አዲስ መሪ ፈልጉ” አለ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ ከተታቸው፡፡
“አንተው ሁንልን!” አሉት፡፡ የበለጠ ስልጣን፣ የበለጠ ጉልበት አገኘና ቁጭ አለ፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ፣ ሌላውን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት እራሱን ከአጣብቂኝ ያወጣል፡፡
ሀገር የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ፣ የፖለቲካ መሪዎችና ሃላፊዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፣ የአስተዳደርና የአመራር አካላት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፣ ዜጎች የኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ፤ አማራጭ መውጫ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ ከገባን አማራጭ መውጫ ያሻናል፡፡ የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ከገባን አማራጭ ያሻናል፡፡ የጦርነት አዙሪት ውስጥ ከገባን (እንዲህ እንዳሁኑ) አማራጭ ያስፈልገናል፡፡ ሆኖም መብራት አጣን ለሚል ዜጋ፤ “ለምን ጄኔሬተር አይገጠምም” የሚል አማራጭ፤ ጥሩ አማራጭ አለመሆኑን መገንዘብ ያባት ነው፡፡ “መብራት ሳይኖር በፊት እንደኖረው ይኑር”፤ የሚል አማራጭም አማራጭ አይደለም፡፡ አማራጩ አማራጭ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ አማራጭ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበረሰቡ “ዳቦ!” እያለ ይጮሃል ስትባል “ለምን ኬክ አይበሉም!” እንዳለችው እንደ ፈረንሳይዋ ንግስት እንደ ሜሪ አንቷሌት ያለ ታሪክ እንዳይደገም መጠንቀቅ ግድ ነው፡፡
ከአጣብቂኙ የሚወጡበት ሁነኛ መላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አማራጭ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ብልህ አሳቢ ሽማግሌዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሆደ-ሰፊ ምሁራን ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንንም እንደ አማራጭ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ አገርን የሚያድናት አማራጭ የመፍትሄ ሃሳብና አማራጩን ሃሳብ የሚያስፈፅም አማራጭ ሰው ነው፡፡ “ሁለት ባላ ትከል፣ አንዱ ቢሰበር በአንዱ ተንጠልጠል” የሚባለው ይሄኔ ነው!
ጎርፍ በጋምቤላ በርካታዎችን ማፈናቀሉ ተገለጸ
በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ፣ በጋምቤላ ከተማና በዘጠኝ ወረዳዎች በርካታ ሰዎችን እንዳፈናቀለ፣ የክልሉ መንግሥት ባለፈው ማክሰኞ አስታውቋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባው ተወካይ አቶ ሳይመን ቲያቺ፣ ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ ስድስት ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶችና በደረቃማ አካባቢ ላይ እንደሚገኙ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
በደረሰው የጎርፍ አደጋ ንብረት እንደወደመና በእንስሳት ላይም ጉዳት እንደደረሰ የጠቆሙት የከንቲባው ተወካይ አቶ ሳይመን፤ እስካሁን በጎርፉ የሰው ህይወት አለማለፉን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኡሞድ ኡሞድ በበኩላቸው፣ የክልሉ ህዝብ ወንዞችን እየተከተለ የሰፈረ ነው፣ በመሆኑም የባሮ፣ የአልዌሮ፣ የጊሮና የአኮቦ ወንዞች በከባድ ዝናብ ምክንያት ሞልተው በመፍሰስ፣ በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ጎርፍ ማስከተላቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኡሞድ እንዳሉት፤ በኑዌር ዞን አምስቱም ወረዳዎች፣ የክልሉን ዋና ከተማ ጨምሮ በጎርፉ እጅጉን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የ01፣ 02፣ 04 እና 05 ቀበሌዎች ነዋሪዎች በጎርፉ ከብቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ የባሮ ወንዝ መጨመር ተጨማሪ የአደጋ ስጋት መደቀኑን የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት ለችግሩ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
በጋምቤላ ከተማ የተከሰተው ጎርፍ በዚህ መጠን ህብረተሰቡን ያፈናቀለው ከ15 ዓመት በፊት በ2000 ዓ.ም እንደነበር ያስታወሱት አንድ የከተማው ነዋሪ፤ የባሮ ወንዝ በሞላ ቁጥር ዳግም ህብረተሰቡን እንዳያፈናቅል መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት፤ ባለፈው ዓመት ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ጥቅምት ወር የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ፣ በ12 ወረዳዎች እንዲሁም በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ በተከሰተው ጎርፍ 76ሺ631 ሰዎች ለጉዳት ተዳርገው ነበር፡፡
በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ የክረምቱ ዝናብ የሚያስከትለው ጎርፍ፣ ከ270ሺሕ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) ባለፈው ሳምንት አመልክቷል።
4ኛው የመላው አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን ተካሄደ
”በኢትዮጵያ የድህረ-ምርት ብክነቱ ወደ 25 ሚ. ገደማ ህዝብ የሚመግብ ነው“
ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዳራሽ የተከፈተው አራተኛው የመላው አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን፣ ”ዘላቂ የድህረ-ምርት አመራር፡ የአፍሪካን የእርስ በእርስ የግብርና ንግድ ማሳደግና የምግብና ሥነምግብ ዋስትናን ማጎልበት“ በሚል ጭብጥ፣ እስከ ትላንት አርብ ድረስ ለአራት ቀናት ተካሂዷል፡፡
ኮንግረሱ በአፍሪካ አህጉር እጅግ ወሳኝ የሆነውን የምግብና ውሃ ብክነት ችግር መፍትሄ ለማበጀት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በኮንግረሱ ላይ ለውይይት ከቀረቡ ርዕሰጉዳዮች መካከል፡- ዘላቂ የድህረ-ምርት አሰራሮች፣ የምርት ብክነትን የሚቀንሱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ብክነትን ለመከላከል የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስፋት አጋርነትን ማጠናከር የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በኮንግረሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ ኮሚሽነሯ ክብርት ጆሴፋ ሊዎኔል ኮሬያ ሳኮ፤ “በዓለማቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ብናደርግም፣ የእህል ብክነት በተለይም የድህረ-ምርት ብክነት በአፍሪካ የልማት ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፤ ይሄ ደግሞ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግርን ያባብሳል፣ የገበሬዎችንና ማህበረሰቦችን ገቢ ይቀንሳል፣ ውዱን የመሬት፣ ውሃና ኢነርጂ ሃብትን በከንቱ እንዲባክን ያደርጋል..” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብና ሥነ-ምግብ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሻግሬ ዘውዱ (ዶ/ር) በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ድህረ ምርት ብክነት በእህል እስከ 30%፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ እስከ 70% እንደሚደርስ ጠቁመው፤ የምርት ብክነቱ ወደ 25 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ የሚመግብ ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን ምርታችንን እርስ በርስ ስለማንገበያይ ከፍተኛ ብክነት ይከሰታል የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ እስያውያን እስከ 60% ድረስ ሲገበያዩ፣ አፍሪካውያን ግን እስከ 20% ብቻ ነው የሚገበያዩት፤ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የምግብ ብክነት ዓለማቀፍ ክስተት እንደመሆኑ መጠን፣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ ለሰው ልጅ ፍጆታ ከሚመረተው ምግብ 30 በመቶ ገደማ የሚሆነው በከንቱ ይባክናል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እ.ኤ.አ በ2019 ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የምግብ ብክነቱ በገንዘብ ሲመነዘር፣ በበለጸጉት አገራት በየዓመቱ ወደ 680 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን፤ በታዳጊ አገራት ደግሞ 310 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያህል ተገምቷል፡፡
አራተኛውን የመላ አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከተለያዩ የልማት አጋሮች፣ የግል ዘርፉ ተዋናዮች፣ የምርምር ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ታውቋል፡፡
“እዚህ አገር ጋዜጠኝነት ድህነት ነው”
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (Editors Guild of Ethiopia) “የጋዜጠኞች የአኗኗር ሁኔታ በኢትዮጵያ፡ በዋናነት የጋዜጠኞች የተሻለ ክፍያ ወደሚያስገኙ ስራዎች መፍሰስ” በሚል ርዕስ ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ውይይቱን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጠዋት በሂልተን ሆቴል አካሄደ።
በውይይቱ ላይ በእንግድነት የታደሙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቦርድ አባል የሆኑት አምባሳደር መሃመድ ድሪር ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ሚዲያ አንድ ትልቅ ራሱን የቻለ መንግሥት ነው…. ጥሩ መንግሥት ሲያገኝ ያብባል፤ ጥሩ መንግስት ሳያገኝ ሲቀር ደግሞ ይሸሻል፤ ይሰደዳል። የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለመጎልበቱ ሣቢያ ያጣናቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡” ብለዋል፡፡
ውይይቱ ለሙያው መጎልበት ትልቅ አቅም እንደሚሰጥ የጠቆሙት አምባሳደር መሃመድ፤ መድረኩ በሙያተኞቹ ብቻ ባይወሰንና ከዩኒቨርሲቲ ወይም ከሌሎች ተቋማት የሚመጡ ምሁራንም ሃሳባቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ቢሆን ጠቃሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለዕለቱ የማህበሩ ስብሰባ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት ባቀረቡት ፅሁፍ፤ “ዛሬ በአገራችን አንጋፋ ጋዜጠኞች በብዛት አይታዩም፤ ብቃት ያለው ኤዲተር እጥረት ይስተዋላል፤ ጋዜጠኝነት የጀማሪና የወጣት ብቻ ሙያ እየሆነ መጥቷል፤ ወጣቶቹ ከአንጋፋዎቹ ልምድ እየወሰዱ አይደሉም፤” የሚሉ አንኳር ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
ኤዲተሮች የይዘት ኢንጂነሮች (Contents developers and builders) ናቸው ያሉት ጋዜጠኛ መሰለ፤ ይዘት የሚወሰነውና ተጣርቶ የሚያልፈው በእነሱ አማካኝነት ነው ሲሉ የአርታኢያንን ጠቀሜታ አመልክተዋል፡፡
አንጋፋ ኤዲተሮች በተቋማቸው ያሉባቸውን ችግሮችም ሲጠቅሱ፤ በተለያየ ሙያ ሰልጥነው ለመጡ ሃላፊዎች ፈተና መሆናቸውን እንዲሁም ራሳቸው እንደፈለጉ ለመስራት እንቅፋት እንደሚሆኑባቸው አብራርተዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት፣ “ኤዲተሮች በተቋማቸው ረዥም ዓመታት ለምን አይቆዩም?” የሚል ጥያቄም በማንሳት መልስ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ከሰጧቸው መልሶች መካከልም፡- “ሃላፊዎች ልፋታቸውን ባለመረዳትና ጥቅማቸውን ባለመገንዘብ አይንከባከቧቸውም፤ በትምህርት ደረጃ በብቃትና በችሎታ የተመረኮዘ ምደባ አለመለመድ፤ የአገልግሎት ጊዜንና አቅምን ያገናዘበ ተገቢ ክፍያና ጥቅማጥቅም አለመኖር፤ በድህነት የሚኖሩና ሲታመሙ ገንዘብ የሚዋጣላቸው መሆናቸው፣” የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ “አንጋፋ ኤዲተሮች የት ነው ያሉት?” ሲሉም በፅሁፋቸው ወሳኝ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ጋዜጠኛው እንደሚሉት፤ አንጋፋ ኤዲተሮች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም በተለያየ ሙያ ላይ ተሰማርተዋል። ከፊሎቹ ደሞ በተቋማቸው ውስጥ ከይዘት ሥራ ውጭ ተመድበው እየሰሩ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጡረታ ወጥተዋል ብለዋል።
ፅሁፍ አቅራቢው “አንጋፋ ኤዲተሮች ባለመኖራቸው ምን አጣን?” የሚል ርዕሰ ጉዳይም አንስተዋል - ለዚህም በሰጡት ምላሽ፤ “ብቃት ያለው ኤዲተር እጥረት ተስተውሏል፤ የቅብብሎሽ ድልድዩ ተሰብሯል፤ ያልበሰለ ጋዜጠኝነት እየተስፋፋ ነው፤” ብለዋል፡፡
ጋዜጠኛ መሰለ ገ/ህይወት ፅሁፋቸውን የቋጩት የመፍትሄ ሃሳቦች በማቅረብ ነው። “የጋዜጠኞች የስራ መደብ ዕድገት ቅደም ተከተሉን ይዞ መጓዝ አለበት፤ ሚዲያውን መምራት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው፤ ጋዜጠኞች የአመራር ሥልጠናም መውሰድ አለባቸው፤” ብለዋል- ባቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ፡፡
ሌላው በውይይቱ ላይ በእንግድነት የታደሙትና የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል አመራር አባል የሆኑት ጋዜጠኛ ታምራት ሃይሉ በሰጡት አስተያየት፤ “ሚዲያን ለማሻሻል መሰረቱ ያለው ኤዲተሮች ዘንድ ነው፤ በእያንዳንዱ ይዘት ላይ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ኤዲተሮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የሚዲያ ተቋምን መምራት ያለባቸው ጋዜጠኞች ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ግን በጋዜጠኛ መሰለ ሃሳብ እንደማይስማሙ ከራሳቸው ተሞክሮና መሬት ላይ ከሚታየው ተጨባጭ እውነታ በመነሳት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ሳምንታዊ ውይይት ላይ ጎልቶ የወጣው ስሜት፣ የኢትዮጵያ ኤዲተሮች ክፍያ ጅቡቲን ከመሳሰሉ ጎረቤት አገራት ጋር እንኳን ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑና በአጠቃላይ “ጋዜጠኝነት እዚህ አገር ድህነት ነው” የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ያለምንም ተጨማሪ ማስረጃና ማረጋገጫ በኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ህይወት ላይ በተጨባጭ የሚታይ እውነታ ነው።
(አለ) መታደል እና ልብ
የግጥም ጥግ
(አለ) መታደል እና ልብ
ከሕይወት ሎተሪ
በቆረጥሽው እጣ
ያሸነፍሽው ንብረት
ልቤ ሆኖ ወጣ፡፡
… መታደልሽ፡፡
****
ነው ብለው ሰጡኝ ቁልፍ
የልቧ መክፈቻ
ብሞክረው እምቢ አለኝ
ዝጎ እንደሆነ እንጃ፡፡
… አለመታደሌ፡፡
****
የጅብ ችኩል ተረት
በእሷ ደረሰና
ደረት ኪሴ ገባች
ልቤን ተወችና፡፡
… አለመታደሏ፡፡
****
ሥጋዬን እንደጮማ
ከበር አስቀምጬ
ልቧን እንደ መቅደስ
በነፍሴ ረግጬ
በእድሏ ፀናፅል
በልቤ ከበሮ
በፍቅሯ በገና
ሀሴት ተደርድሮ
በገደል ሳይሆን
ያዜምኩላት ዜማ
በሰማይ ማሚቱ
ህዋ ላይ ተሰማ
… መታደላችን!
(ሳምሶን ጌታቸው)
የግጥም ጥግ
(አለ) መታደል እና ልብ
ከሕይወት ሎተሪ
በቆረጥሽው እጣ
ያሸነፍሽው ንብረት
ልቤ ሆኖ ወጣ፡፡
… መታደልሽ፡፡
****
ነው ብለው ሰጡኝ ቁልፍ
የልቧ መክፈቻ
ብሞክረው እምቢ አለኝ
ዝጎ እንደሆነ እንጃ፡፡
… አለመታደሌ፡፡
****
የጅብ ችኩል ተረት
በእሷ ደረሰና
ደረት ኪሴ ገባች
ልቤን ተወችና፡፡
… አለመታደሏ፡፡
****
ሥጋዬን እንደጮማ
ከበር አስቀምጬ
ልቧን እንደ መቅደስ
በነፍሴ ረግጬ
በእድሏ ፀናፅል
በልቤ ከበሮ
በፍቅሯ በገና
ሀሴት ተደርድሮ
በገደል ሳይሆን
ያዜምኩላት ዜማ
በሰማይ ማሚቱ
ህዋ ላይ ተሰማ
… መታደላችን!
(ሳምሶን ጌታቸው
“የአሬራ ጥጋብ የሚመጣውን ክረምት ያስረሳል”
አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ አለ፡፡
አንድ ኃይለኛ የመርሳት ችግር የነበረበት አይሁዳዊ ነበር፡፡ ከመርሳቱ ብዛት ማታ አውልቆት የተኛውን ልብስና ጫማ የት እንዳስቀመጠ እንኳ አያስታውስም፡፡ ልብስና ጫማውን ያስቀመጠበትን ቦታ ሲፈልግ ሁልጊዜ የጸሎት ሰዓቱ ይረፍድበታል፡፡ በፀሎት ቦታ የሚሰጠውን የቶራ ትምህርትም ጠዋት ተምሮ ማታ ይረሳዋል፡፡ እሱ ግን ከሌሎች ጓደኞቹ የተሻለ የተረዳው ይመስለዋል፡፡ “የእናንተን እውቀት ማነስ ምንም ላግዘው እንደማልችል ሁሉ፤ የእኔንም አዋቂነት ምንም ላደርገው አልችልም” እያለ ጉራውን ይነዛባቸዋል፡፡
አንድ ቀን ጠዋት ሲነሳ ልብሱን፣ ጫማዉንና ባርሜጣውን የት እንዳደረገው ጨርሶ ስለጠፋው ጠዋቱን በሙሉ እሱኑ ሲፈልግ ዋለ፡፡ ትምህርትም አመለጠው፡፡ በዚህ ምክንያት “ሁለተኛ እንዳልረሳ ዘዴ መፍጠር አለብኝ” ሲል አሰበ፡፡ ይህም ሁሌ ማታ ማታ ሲተኛ የትኛውን ልብሱን የት እንዳስቀመጠ፣ ባርኔጣውን፣ ጫማውን ወዘተ የት እንደሚያደርገው በወረቀት መዝግቦ ሊያስቀምጥ ወሰነ፡፡ በዚህ መሰረት “ኮቴ ከበሩ ጀርባ ነው፣ ሱሪዬ ወንበሩ ላይ ነው” እያለ ሁሉንም ዘርዝሮ መዘገበ፡፡
በመጨረሻም አልጋው ላይ ወጣና እንደቀልድ “እኔ ደሞ አልጋው ላይ ነኝ” ብሎ ፃፈና፣ ከትራሱ ስር አስቀምጦ ተኛ፡፡
ጠዋት ሲነሳ ወረቀቷን አውጥቶ በዝርዝሩ መሰረት ሁሉንም በየቦታው አገኘው፡፡ ከፃፈው ዝርዝር ውስጥ አንድ የመጨረሻ መስመር ግን አለ፤ “እኔ ደሞ አልጋው ላይ ነኝ” ይላል፡፡
አልጋው ላይ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሄዶ አየ፡፡ እሱ የለም፡፡ መኝታ ቤቱ ውስጥ በየስርቻ ሳይቀር ዞሮ አየ፡፡ ነገር ግን ራሱን ሊያገኝ አልቻለም፡፡
“እኔ ጠፍቻለሁ ማለት ነው” አለና ከቤቱ ወጥቶ ጮኸ፡፡ “ትላንት ማታ አልጋዬ ላይ መተኛቴንስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ዛሬ ግን የለሁም!”
ይህን ሲናገር የሰሙ ጎረቤቶቹ፤ “ትክክል ነሃ፡፡ በእርግጥ አልጋህ ላይ የለህም፡፡ ምክንያቱም አንተ እዚህ ከእኛ ጋር ነው ያለኸው፡፡” አሉና ሳቁበት፡፡
“የምለው አልገባችሁም ማለት ነው፡፡ በዝርዝሬ ላይ’ኮ ተጽፌያለሁ” አለና ወረቀቷን አውጥቶ አሳያቸው፡፡
“ጅል አትሁን አንተ ሰው፡፡ አጉል ጭንቀት ውስጥም አትግባ፡፡ ይልቅ ወደ ቤትህ ግባ” አለው አንደኛው ጎረቤቱ፡፡
“ራሴን ሳላገኝማ ወደቤቴ ልገባ አልችልም”
“እያየንህ፣ እያዋራንህ እንዴት ጠፍቻለሁ ትላለህ? መኖርህን እያየን’ኮ ነው” አሉት ሁሉም፡፡ እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
በመጨረሻም አንድ ሰውዬ በጣም ተቆጥቶ፤ “አንተ ደደብ ሰውዬ፤ እዚህ መሆንህንና አለመሆንህን አሁኑኑ አረጋግጥልሀለሁ፡፡” ብሎ በመጥረጊያ ይቆነድደው ጀመር፡፡
“ኧረ በጣም አሳመምከኝ ጎበዝ!” ሲል ጮኸ፡፡
“አሁን ይሰማሀል፤ አይደል?” ሲል ጠየቀው፡፡
“በጣም ይሰማኛል እንጂ”
“የሚያምህ እዚሁ በመሆንህ ነው፡፡ የመታሁትም አንተን በመሆኑ ነው፡፡ አንተኑ ራስህኑ፡፡ አንተ እንዳልከው ግን ጠፍተህ ቢሆን ኖሮ ህመሙ ሊሰማህ አይችልም ነበር፡፡ አይደለም እንዴ?”
“እውነትህን ነው፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እንዴት እንዳደረግኸው ባላውቅም እራሴን እንዳገኝ አድርገኸኛል፡፡ ምናልባት እኔ የተሻልኩ ሰው አልሆን ይሆናል፡፡” ሲል ራሱን ዝቅ ማድረግ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ የማስታወስ ችሎታውም እየተመለሰለት መጣ፡፡
***
ሁሉን ነገር የማውቅ እኔ ነኝ፤ ከማንም ሰው እኔ እሻላለሁ፤ የማለት አባዜ ክፉ እርግማን ነው፡፡ ክፉ መገበዝ ነው፡፡ የማታ ማታ ራስን ጭምር ወደ ማጣት ያመራል፡፡ ራስን ለመፈለግ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜ ከረፈደና ከመሸ በኋላ እራስን ማግኘት ዘበት ይሆናል፡፡ ይህንን መገንዘብ የጉዳዮች ሁሉ ቁልፍ ነው፡፡ ወረቀት በያዘው፣ አዋጅ በደነገገው፣ ፖሊሲ በቀረፀው፣ የትውስታ መዝገብ ቢደረደር፣ ቢገመገም ዋናው ራስ የጠፋ እስኪመስል ድረስ የግራ - መጋባትና የመወነባበድ ጣጣ ውስጥ መግባት አይቀሬ ይሆናል። ትላንት ያሉትን እንዳላሉ መሟገት፣ ትላንት ያመኑበትን በጭራሽ ዛሬ አላውቀውም ብሎ መሸምጠጥ ቀድሞውኑ ራስን ከመገበዝ የሚመነጩ ህፀፆች ናቸው፡፡ ራስን ዋርካ አሳክሎ ማየት መጨረሻው ጉቶ ማከልን መረዳት ይሆናል፡፡ ይህም የታደለና ልቡናውን የሰጠው ሰው ከተገኘ ነው፡፡ እንዲያመው እየተደረገ መኖሩን እንዲያውቅ የሚገደድ ራሱ የጠፋበት ኃላፊ፣ ባለሥልጣን ወይም መሪ ለሀገርና ለህዝብ ችግር እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ወደዚህ አሰቃቂ ሂደት መድረስም ባንድ ስር እንደተንጠለጠለ ዛፍ የሰቀቀን አፋፍ ላይ መንጠልጠል ይሆናል፡፡
“አድረህ እይ፣ አሳድረህም እይ” እንዲሉ አስቀድሞ ታላቅነትን ከመለፈፍ ይልቅ የራስን ሚዛን ለማወቅ የሚረዳው ለራስ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ መብሰል አለመብሰልን በጥሞና መለካት ነው፡፡ የ”አሜን ባይ” መብዛት የትክክልነት ማረጋገጫ አለመሆኑን ማጤን ነው፡፡ እኔ ያወጣሁት መርህ ትክክል ነውና ተቀበል ከማለት በፊት አንተስ ምን ይመስልሃል? ብሎ ለሌላው ሀሳብ እድል መስጠት ብልህነት ነው፡፡ ምናልባት ንጋት ላይ የቀናን መስሎ የታየን ነገር ረፋዱ ላይ ወይ ማምሻው ላይ መለወጥ አለመለወጡን በሚገባ አስተውሎ “ለአንድ ወቅት የሰጠሁት መፍትሄ መልካም ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ዘዴ ለዚህኛው ወቅት ላይሆን ይችላል” ብሎ መጠራጠር ያባት ነው፡፡ የትላንት ጣዕም ዛሬ ቃናው መለወጥ አለመለወጡን ማጣራት እጅግ ወሳኝነት አለው፡፡ “ነብር ሲያረጅ አነር ይወልዳል” ይሏልና ከሀሳብ ማርጀት፣ ከፖሊሲ ማርጀት፣ ከፕሮግራም መጣረስ ጋር የሚመጡትን ከሁኔታዎች ጋር የማይጣጣሙ እምነቶች አላየሁም አልሰማሁም ብሎ የዱሮውን ሃሳብ እኝኝ ብሎ መያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ አገርና ዓለም ተቀበለውም አልተቀበለውም እኔ ያሰብኩት ጋ ካልደረስኩ ፍሬን አልይዝም - አንዳች የሚያቆመኝ ኃይልም ሊኖር አይችልም ብሎ ግትርነትን ማወጅ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንጂ ሌላ ፍሬ የምናፈራበት መላ አይደለም፡፡
የተመኘነው፤ ያለምነው ያቀድነውና የተለምነው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ላይሳካ ይችላል ከሚለው እሳቤ ጀምሮ ከመሰረቱስ ሙሉ በሙሉ ስህተት ቢሆን እስከ ማለት ድረስ ለማሰላሰል ዝግጁና ደፋር መሆን ተገቢ ነው፡፡ ያማረውና የተሳካው ሁሉ የእኔ ድካም ፍሬ፣ የተሳሳተውና የተበላሸው ሁሉ የጠላቴ ሴራ ውጤት፤ ብሎ መፈረጅ የኋላ ኋላ ራሱ እንደጠፋበት ሰው መደነጋገርንና በአደባባይ “ራሴን አፋልጉኝ” ማለትን ያስከትላል፡፡
ከቶውንም የሌሎችን ድካም ለራስ ማድረግ ከአንድ ጀንበር በላይ ሊሸሸግ የሚችል ነገር አይደለም። “ያላረባ ልኳንዳ አራጅ ዐይን የሆነውን ብልት ይበላል” እንደሚባለው በሌሎች ጥናት መኩራራት፤ በሌሎች ሪፖርት ላይ ፈርሞ ብቻ መመስገን፤ በሌሎች ጫንቃ የተሰራን ስራ የእኔ ነው ማለት፤ ለሥራም፤ ለእድገትም፣ ለራስም ደግ አይደለም፡፡ አድሮ ያጋልጣልና!
በሲቪል ሰርቪስ መርሆዎች መሻሻል ብቻ መልካም አስተዳደር አይመጣም፡፡ ሰው ይፈልጋል፡፡ መርሆዎችን ከልቡ ሊተገብር የቆመ ሰው ይፈልጋል፡፡ ፍትሕ ርትዕ የሰፈነባት አገርን የሚያመላክት በርካታ አቅጣጫ ሊነደፍ ይችላል፡፡ ግን የወረቀት ስራ ብቻ ነው፡፡ ሰው ይፈልጋል፡፡ በትላንቱ አባያ በሬ አዲስ መሬት ልረስብህ ቢሉት ትርፉ ጅራፍ ማጮህ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ወደ ባህልነት ሊቀየር አንድ ሀሙስ የቀረው ሙሰኝነት ምንም ያህል የጠበቁ አናቅጽትና ህግጋት ቢጠቀሱለት፤ ተግባራዊ ትርጓሜ የሚሰጣቸው እጁን የታጠበና ልቡን ያፀዳ ሰው ብቻ ነው፡፡
አለበለዚያ “የወረት ውሻ ስሟ ትደነቂያለሽ ነው” ከሚባለው ፈሊጥ የዘለለ ነገር አይገኝም፡፡ በእርግጥም በተጎሰመው ነጋሪት፣ በተላለፈው አዋጅ፣ በብራና በተከተበው ህግና መመሪያ ጥናቱን ያስጠናውን ክፍል ለማስደሰት ይቻላል፡፡ ተግባሩ ግን ከፍተኛ የሰው ኃይልና ልባዊ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖር የማድረግን ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ተልዕኮ ነው፡፡ የሃገራችን የዘወትር ህመም፤ ያማረ እቅድና እንከን - አልባ የተባለ የወረቀት ስራ በተነደፈ ቁጥር፤ የተፃፈው ሊቀደድ እንደሚችል የታቀደው ሽባ ሆኖ ሊቀር እንደሚችል ዘንግቶ፣ ከአፍ አፍ እየተቀባበሉ በየመዋቅሩ አሸንዳ የድል ብስራት መለፈፍ፣ ነገ ያለአንዳች ተግባር በነባቤ - ቃልነት ብቻ ሊቀር እንደሚችልና ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል አለመገንዘብና ተዘናግቶ ማዘናጋት ነው፡፡ “የአሬራ ጥጋብ የሚመጣውን ክረምት ያስረሳል” እንደሚባለው መሆኑ ነው!
ኢሰመኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ መስከረም 4 ቀን 2016ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ሁኔታ የተመለከተ ዓመታዊ ባለ 29 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የዘርፍ ሪፖርት፣ ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ በማተኮር የታዩ መልካም እመርታዎች፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮችና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል።
ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራዎች፣ጥናቶች፣ የውትወታ ሥራዎች፣ በግለሰቦች ከቀረቡ አቤቱታዎች፣ ከልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በማጠናቀር የተዘጋጀ ነው።
በሪፖርት ዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ፣ በባለሦስትና አራት እግር አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ ያሳለፈውን የእገዳ ውሳኔ ተከትሎ፣ የኢሰመኮን ምክረ-ሐሳቦች በመቀበል ለጉዳዩ እልባት መሰጠቱ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ በተደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት፣ በኮሚሽኑ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ በተለይም የዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በተመለከተ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር እየተሻሻለ መምጣቱ በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተካተዋል።
በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ-ልማቶች መልሶ ለማቋቋም በፌዴራል መንግሥት ይፋ የተደረገው “የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም” እና እነዚህን ተቋማት ወደነበሩበት ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግርና እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ ሊደረስበት የሚችል ከፍተኛ አካላዊና አእምሯዊ ጤና የማግኘት፣ ትምህርትና መጠለያ የማግኘት፣የመሥራት፣ከሚኖሩበት ቦታ ያላግባብ በኃይል ያለመፈናቀልና ንብረት የማፍራት መብቶችን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው በአሳሳቢነት ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ ወቅቱ የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት የነበረ በመሆኑ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ሥራውን እንዳይሠራና መደበኛ ሕይወቱን እንዳይመራ አድርጎታል። ግጭቱ ይህ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅትም የቀጠለና እልባት ያልተበጀለት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ መባባሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች፤የቤት እንስሳትና የንብረት ዝርፊያዎች፣ ቤቶችን የማቃጠልና ነዋሪዎችን በኃይል ማፈናቀልና ቤተ-እምነቶችን ማቃጠል ምክንያት ኅብረተሰቡ በአካባቢው ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወቱን እንዳይመራ ማድረጉንና በርካታ ሰዎች ያለ መጠለያ እንዲኖሩ፤ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙና ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆነ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት በሚልና በሌሎች ምክንያቶች የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በማፍረስ ሂደት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች ሳይቀር የንግድ ቤቶቻቸው ያላግባብ እንዲፈርሱ መደረጉና ንብረታቸው መወሰዱ በገቢያቸውና በኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
በኦሮሚያ፣ በሶማሊና በተለያዩ የደቡብና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ የሕብረተሰቡ መተዳደሪያ የሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ሞተዋል፤ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።በመንግሥት በኩል ለችግሮቹ መፍትሔ ለማፈላለግ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም የቅድመ መከላከል ሥራ በበቂ ሁኔታ ባለመተግበሩ ችግሩን የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ በ2015 ዓ.ም. በኮሚሽኑ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ከመተግበር ረገድ አበረታች ተግባራት መስተዋላቸውን ገልጸው፤ የትምህርት፣ የጤና፣ ንብረት የማፍራት፣ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ የመኖር፣ የሥራና ተያያዥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁምጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአርታኢያን ማህበር በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳይ ላይ ተወያየ
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኀበር (Editors Guild of Ethiopia) 6ኛ ዙር የቁርስ ላይ የውይይት መርሐግብሩን ዛሬ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል አካኺዷል።
የዕለቱ የውይይት መርሐግብር ያተኮረው “ሰብዓዊ መብቶች እና መገናኛ ብዙሃን፤ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ የአርታኢው ሚና (Media and Human Rights: Role of Editors in Protection of Human Rights)” በሚል ርዕሰጉዳይ ላይ ነው። የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ናቸው፡፡
አቶ ፍሬው በፅሑፋቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ሰው በመኾናቸው የተጎናጸፏቸው ስለመኾኑ፣ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ህገመንግሥት መሠረታዊ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጭምር ተቀብሎ ማካተቱን በጠንካራ ጎኑ አንስተዋል።
ኾኖም በአፈፃፀም ሒደት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ቢኾንም፣ መገናኛ ብዙኃን በችግሩ ስፋት ልክ በቂ ሽፋን እየሰጡ አለመኾኑን በአሳሳቢነቱ አብነቶችን በመጥቀስ አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙኃንና አርታኢያን፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በመደበቅ ለተጠርጣሪ ወንጀለኞች ሽፋን እንዳይሰጡ በብርቱ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ፣ ዘገባዎች በሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳይጠለፉ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። በርዕሰ ጉዳዩ ላይም በማህበሩ አባላት ሰፋ ያለ ውይይት ተካኺዷል።
የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን የሚያነሱት፣ ከዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት ሲወጣ፣ ምላሽ ወይም ማስተባበያ ለመስጠት ብቻ እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በመንግሥት ባጀት የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የተሻለ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቂ ሽፋን እንደማያገኙም በማህበሩ አባላት ተነስቷል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በበላይ አለቆች “የአገር ገጽታ ያበላሻሉ” በሚል ሽፋን እንደማያገኙም ተጠቅሷል - በውይይቱ ወቅት፡፡
ሪፖርተሮችም ሆኑ አርታኢያን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በቁርጠኝነት እንዲዘግቡ ከተፈለገ ከተቋማቸው ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባም ተነስቷል፡፡