Administrator
ምህዋሩን የሳተው ፌሚኒዝም!
ዘመናዊነት የተለያዩ ሀሳቦችን ከምንም ነገር ጋር ሳያገናኙ፣ እንደያዙት ትርጉም ክብደት ማስተናገድ ነው። ይህ ማለት የትኛውንም ሀሳብ ያለምንም አጥር መመርመር ማለት ነው። ነገር ግን በተለይ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የዘመናዊነት ብሂል ከዚህ በጣም ይለያል። በደንብ መመርመር የሚገባቸውን ሀሳቦች ወቅታዊ እርግብግቢታቸውን እያዩ አብሮ የማራገብ፣ መንጋነት ይነበባል። ከነዚህ እርግብግቢቶች አንዱም ፌሚኒዝም ነው።
እ.ኤ.አ በ1848 እንደተጀመረ የሚታወቀው የፌሚኒዝም እንቅስቃሴ፣ አሁን ላይ 4ኛው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ይነገርለታል። ይህ አብዮት ቀላል የማይባሉ ማህበረሰባዊ በደሎችን የተከላከለ ቢሆንም፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምህዋሩን እየሳተ ይገኛል።
እንደ ፌሚኒዝም ያሉ ለተጎጂ ማህበረሰብ ድምፅ ለመሆን የተጠነሰሱ እንቅስቃሴዎች አንዳንዴ ግባቸውን ከመምታት አልፈው ተፈጥሯዊ ምህዋራቸውን ሊስቱ ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ይዘውት ከተነሱት ዓላማ ዘመም ማለት ሲጀምሩ ነው። ፌሚኒዝም ወንዶች በሴቶች ላይ ያደርሱት የነበረው ጭቆና የወለደው ብሶት ለበስ እንቅስቃሴ ነው። ጭቆናዎቹም በህግ፣ ሴቶችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የመቁጠር፣ እንደ ሰውም ዝቅ አድርጎ የማየት ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በተለይ 'በኋላቀር' አካባቢዎች ግቡን መምታት ባይችልም፣ እንቅስቃሴዎቹ በተካሄደባቸው ቦታዎች ግን ከታሰበለትም ርቀት በላይ በመጓዝ፣እንደውም ጭቆናውን ያደርስ የነበረውን 'ወንድ' በቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል። የአሁኑ ምዕራፍ እንቅስቃሴ ግን፣ጉዞውን እንዳይቀጥል በራሱ የአስተሳሰብ ገመድ ተጠፍሮ ይገኛል። ጠፍሮቹም፦ እኩልነት፣ፋሽንና ታሪክ አጥላይነት ናቸው።
የበፊቶቹ ፌሚኒዝም ምዕራፎች፦ እንዲመርጡ አይፈቀድላቸው የነበሩ ሴቶችን የመምረጥ መብት ማጎናጸፍ፤የትምህርት ዕድል አያገኙ የነበሩትን ማመቻቸት፤ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩትን መከላከልና የመሳሰሉትን ጭቆናዎች ማስቀረት መነሻቸው ነበር። ያሁኑ ምዕራፍስ? የአሁኑ፣ከላይ እንደተገለጸው ጭቆናዎቹ በአመዛኙ የተቀረፉ በመሆናችው፣እላይ ታች የሚባትልበት አላማ 'እኩልነትን'፣ከተቻለም የበላይነትን ማረጋገጥ ነው።
እኩልነት ከፖለቲካዊ አውድ ዉጪ ያለቦታው ሲገባ ከተፈጥሮ ጋር ይጣረሳል። ምክንያቱም፦ ተፈጥሮ ፍጥረቷን እኩል አድርጋ ስለማታውቅና፤እኩል የማድረግ አባዜም፣ ሀሳብም ኖሯት ስለማያውቅ! እኩልነት የሰው ልጅ ‘ኢጎ’ ቋንቋ ነውና!
'“ከጥላቻ በስተጀርባ ፍቅር አለ” እንዳለው ሲግማን ፍሮይድ፣ከእኩልነት በስተጀርባም የፉክክር ስሜት አለ። ፍጥረታት እኩልነት ለምን ያሻቸዋል? ሁሉም ለየቅሉ እስከተፈጠሩ ድረስ! ተፈጥሮ ውሻን ውሻ አደረገችው፣ በግንም በግ፣ ሰውንም ወንድ እና ሴት። ከዚህ ያለፈ አላማ ለፍጥረቶቿ አልሰጠችም። ነገር ግን የሰው ‘ኢጎ’ ሁሌም አርፎ ስለማይተኛ:- መጀመሪያ የሰው ልጅ የበላይ ፍጥረት ነው ብሎ አወጀ፣ ከዚያም ወንድ በሴት ላይ የበላይ ነው ብሎ ቀጠለ፣ ከዚያም ነጭ ከጥቁር ይበልጣል ብሎ አከለ፤ አሁን ደግሞ ሀብታምን ከድሃ በካፒታሊዝሙ እያበላለጠ፣ ‘ቆንጆን፣ ከአስቀያሚ በሞዴሊንጉ እየመነጠረ መኖሩን ቀጥሎበታል። ይሄ ሁሉ ከላይ የተጠቀሰችው፣ የበላይነት ስሜትን ካልተቀዳጀች ተረጋግታ መኖር የሚያቅታት ጭንቅላቱ ውስጥ ያለችው የፍርሃት ስሜቷ ንግስት ‘የኢጎ’ ስራ ውጤት ነው።
ተፈጥሮ ሴትን ሴት፣ ወንድን ወንድ ስታደርግ፣ ጾታቸውን ብቻ አለያይታ አይደለም፣ ግብራቸውንም እንጂ። ተወደደም ተጠላም ወንድ በወንዳወንድነቱ (masculine)፣ ሴት በሴታሴትነቷ (feminine) ተለያይቶ የተሰጣቸው ገጸባህሪ አለ። ይህ ልዩነት ከጾታ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ላይ ይንጸባረቃል ማለት ነው። ወቅታዊው ፌሚኒዝም ግን ይህን ልዩነት ጆሮ ዳባ በማልበስ፣ ሴትን እንደ ወንድ በማኖር እኩልነትን ለማስፈን እየጣረ ይገኛል።
በእስያ ይን እና ያንግ የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለ። አንዱ ጠንካራ፣ ፈጣንና ብሩህ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ የሱ ተቃራኒ ነው። አንዱ በአንዱ ውስጥ ያለና፣ ልዩነታቸውንም አስጠብቀው የሚኖሩ ናቸው። አንደኛው ከአንደኛው አይበልጥምም አያንስምም። እንደው በአንጻር ይኖራሉ እንጂ። ታዲያ ይህን ሃሳብ ለብዙ ነገር ሲጠቀሙበት፣ወንድና ሴትንም የሚገልጹት በዚህ መንገድ ነው።
ሌላው ፌሚኒዝም በዚህ ወቅት እንደ ፋሽን የመያዙ ጉዳይ አሳሳቢነት ነው። ፅንሰ-ሃሳቦች እንደ ፋሽን የመያዛቸውን ጉዳይ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ፋሽን በባህሪው፣አንድን ነገር ወቅታዊ ሽፋን በማልበስ፣የማይመረምሩ(shallow) ተከታይ መንጋዎችን የማፍራት ጉልበት ስላለው ነው። የፋሽን ታሪክ እንደሚያሳየው፣ነገሮች 'የሆይሆይታ'(hype) ጊዜያቸውን ጨርሰው የሚከስሙ ሲሆን፤ ፌሚኒዝምም ከፋሽናዊ ብርድልብስ ራሱን ገፎ ወደ ምክንያታዊነት እስካልመጣ ድረስ የመክሰሙ ነገር፣ የጊዜ ጉዳይ ነው።
ሌላው በወቅታዊው ፌሚኒዝም ላይ በከባዱ የሚታየው ጥራዝ ነጠቅነት፦ የኋላውን ታሪክ የበደል ጥላሸት እየቀቡ ኢ-ፍትሃዊ ጥላ የመፍጠር ነው። አባቶቻችን እናቶቻችንን ይጨቁኑ እንደነበርና፣ የኋለኛው ዘመን ታሪክ ለሴቶች የግዞት እንደነበር በማተት፣ የተጠቂነት ስሜትን (victim mentality) በመጫር አሁን ላይ የነፃነት ፍንጣቂ እንደታየ መወትወት ይስተዋላል። ይሄ ሃሳብ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ምን ያህል ሴት ነገስታት ሃገራቸውን አንቀጥቅጠው ይገዙ እንደነበር ማሰብ በቂ ነው። እንደውስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይደል እንዴ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚሉትን ሴት መሪዎች ማየት ብርቅ ያደረግነው? በሃገራችን እነ ምንትዋብ፣ ሳባ፣ ህንደኬ...፤ በአፍሪካ እነ ሞረሚ፣ ናንዲ፣ አሳንቴዋ፣ ናፈርቲቲ...፤በዓለም እንደ ሁቺ፣ ኢዛቤላ፣ ኤልሳቤጥ ወዘተ...። የማይካደው ሃቅ፣ በብዙ የዓለም ቦታዎች፣ ለሴቶች ንግስናና አስተዳደር፣ የተፈቀደና አልጋ ባልጋ የነበረ አለመሆኑ ነው። ነገር ግን አሁን ለመሳል እንደሚሞከረው፣ወንድና ሴት የሰውና የእንስሳ ያህል መናናቅ ከነበራቸው፣እንዴት በሚንቃት መመራት አስቻለው? እሷስ መምራት የሚለው ሃሳብ እንዴት ውል አለባት?
ይልቅስ የድሮዎቹ ሰዎች ሴቶቹም ሴትነታቸውን፣ ወንዶቹም ወንድነታቸውን አምነውና ተቀብለው፣ ወንዱም ቤተሰቡን ማስተዳደሩ ላይ በመትጋት፣ ሴቷም ቤቷን በመምራት ድርሻቸውን የተወጡ ናቸው። ይህ ሲባል ጥፋት ያልነበረባቸው አድርጎ መውሰድ አይገባም። ነገር ግን የሚና ክፍፍላቸውን እንደ በጎ ነገር አድርጎ በመውሰድ፣እነሱንም ከጊዜያቸው አንጻር በመዳኘት፣ትሩፋታቸውንም ከአሁኑ ጊዜ ጋር በመስፋት መሄድ ያሻል።
መግቢያው ላይ እንደተገለጸው ፌሚኒዝም ጭቆናን ታግሏል። ወንድ ጡንቻውን እየተጠቀመ ይረግጣቸው የነበሩ ሴቶችን አስተንፍሷል። አሁን ላይ ላሉ ‘ስኬታማ’ ሴቶች ህልማቸውን ይኖሩ ዘንድም በር ከፍቷል። ሆኖም ግን ጭቆናን ሰበብ አድርጎ፣ ድሮም ለየቅል የነበሩትን ሰዎች፣ እኩል አደርጋለሁ ብሎ፣ ተፈጥሯቸውን እየጨቆነ ነውና ይመርመር! ይፈተሽ!
የወቅቱ ጥቅስ
“ጠመንጃችሁን አስቀምጡ። ማሽንገናችሁን እጠፉ። መድፎቻችሁን ፊታቸውን መልሱ። በመቻቻል፣ በመሸማገል፣ በሰላም እመኑ… ሀገር በታሪክ ውስጥ የምታድገው በጦር ሜዳ በጀግንነት በሚዋደቅላት ሰራዊት ብቻ አይደለም። ፊቷን ወደ ፍትህና ወደ መብት መልሳ፣ ስለእነሱ ጠቀሜታ ስትቆም እንጂ፡፡”
(አሪስቲድ ብሪያንድ፤ የፈረንሳይ መሪ)
“እኔስ ሮጬ አመልጣለሁ፤ ታሪኬ ወዴት ያመልጣል?”
የሚቀጥለው ታሪክ ዛሬ እንደ ተረት ይወራል እንጂ ዱሮ እውነት ነበር።
በአንድ የሀገራችን አሰቃቂ ዘመን፣ የአንድ ከፍተኛ፣ ሊቀመንበር ነበር። ክፉ ነው ይሉታል - ልጆቻቸውን ከጉያቸው ነጥቆ ያሰረባቸው እናቶች። ክፉ አረመኔ ነው ይሉታል - ልጆቻቸው በእስር ቤት ተሰቃይተው የተገደሉባቸው አባቶች። ነብሰ-በላ ነው ይሉታል- ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ወጣት ባልንጀሮቹ።
ይህ ሰው ድንገት በከፍተኛው ውስጥ ያልታሰረ ወጣት ካየ፤ ስራውን በሚገባ ሳይሰራ እንደኖረና “አብዮታዊ ግዴታውን እንዳልተወጣ” አድርጎ ይቆጥረዋል ይባላል። ስለዚህም፤ ወጣቱን ያስጠራውና፤
“እስከዛሬ የታባክ ተደብቀህ ከርመህ ነው፣ ገና አሁን ብቅ ያልከው?” ይላል።
ወጣቱ ግራ በመጋባትና በድንጋጤ፤
“ኧረ በጭራሽ ተደብቄ አይደለም ጓድ!” ይላል።
“ጉድጓድ ግባና ጓድ አትበለኝ! በእንዳንተ ያለ ጸረ- አብዮተኛ ‘ጓድ’ አልባልም!”
“ኧረ ጸረ አብዮተኛ አይደለሁም ጓድ!”
“ጓድ አትበለኝ!- ጓድነቴን ታረክስብኛለህ ነው የምለው! ይልቅ ና ቅደም!” ብሎ እስር ቤት አስገባው።
አንድ ቀን ደግሞ ለእስረኞች ንቃት ለመስጠት እንደተለመደው ንግግር ሲያደርግ፤ አብዮት ጥበቃው ከጎኑ ነበር። “ጓድ፤ እነዚህ የምታስተምራቸው እስረኞች እኮ ማታ ይወጣሉ (ይገደላሉ)፤ ምን አለፋህ?” ይለዋል።
ሊቀመንበሩ፤ “ቢሆንም፤ ነቅተው ይሙቱ” አለ፤ ይባል።
ጊዜው አለፈና ይህ ሊቀ መንበር ዩኒቨርሲቲ ገባ- ህግ ሊያጠና። ታዲያ እንደ ሱው ህግ ት/ቤት በዚያው ወቅት የገቡ አንድ ተረበኛ ሽማግሌ አሉ። ከሱ ጋር የአንድ ሀገር ልጆች ናቸው። እኚህ ሽማግሌ ለረዥም ጊዜ ዳኛ ሆነው የሰሩ ናቸው።”
“ለምን ህግ ይማራሉ?” ሲሏቸው፤” “ምናባቴ ላድርግ፤ ‘ያለወረቀት አይሆንም’ የሚባልበት ዘመን መጣ’ኮ! እኛ ‘የልምድ አዋላጅ’ የሚል ስም ተሰጥቶናል!” እያሉ ሰውን ያስቁታል። ታዲያ አንድ ቀን እኚህ ጨዋ አዋቂ ሽማግሌ፣ ያን ከፍተኛ ሊቀመንበር እዚያው ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያገኙትና፤
“ኦ እንዴት ነው ያገሬ ልጅ!” ብለው ሰላምታ ያቀርቡለታል።
“እንደምን ነዎ? በአገር አሉ እንዴ እርስዎ?” ይላል ሊቀመንበሩ።
“በዚያ አንተ ሞቅ ባለህ ዘመን ‘አለሁ’ አልልም ነበር እንጅ፣ መኖርስ አለሁ፤ ከአገሬ ወዴት እሄዳለሁ?” ይሉና ይመልሱለታል።
“እርስዎ ይሄን ተረብ ዛሬም አልተውትም እንዴ?”
“‘ተራቢ ቢሞት ተረብ አይሞትም’ ልበላ፤ በአንተው የትግል ቋንቋ!”
“እንደው አሁን ጊዜው አለፈ እንጂ፣ እርስዎን ነበር እዚያ እስር ቤት አስገብቶ እየገረፉ ማስለፍለፍ?”
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! ምነው ምን አደረኩህ ያገሬ ልጅ! እኔን! የገዛ ወገንህን! በአገር አማን ትጎመዠኝ!?...እሱ ይቅር ይበልህ…”
አሉና ወሬውን ለመቀየር “ለመሆኑ ወደ ግቢ ምን እግር ጣለህ?” ብለው ይጠይቁታል።
“ኦ አልነገርኩዎትም ለካ! እዚህ ዩኒቨርሲቲ ህግ እየተማርኩ‘ኮ ነው። ሁለተኛ አመቴ ነው” አላቸው ሞቅ አድርጎ።
ይሄኔ ሽማግሌው በድንጋጤ አናታቸውን ይዘው፤
“እንዴ!! ፈርደህ ጨርሰህ?!”
***
ፍትህና ርትዕ የጎደለው ስርዓት ውስጥ መኖር ክፉ መርገምት ነው። የአሜሪካ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፤ “የትም ቦታ የሚፈጠር ኢ-ፍትሃዊነት፤ በማንኛውም ቦታ ያለውን ፍትሃዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል” እንዳለው የፍትህ መጓደል እዚህ ድንበሩ፤ እዚህ ክልሉ የሚባል አይደለም። ግፍ በተፈጸመበት ቦታ ሁሉ ስለእውነት የሚጮሁ ድምጾች ይጮሃሉ-ህያዋን ቢጠፉም ከመቃብር የሚመጡ አሉ ይባላል።
በታሪክ ያየነው ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ እንዳይደገም፣ የአሁን ዘመን ዜጎች ስለ መብትና ስለ ፍትህ መቆም፣ ስለ ሰላም ስንል መንገዶችን ሁሉ ማጽዳት ይገባል። ፍትህን የሚያጎድሉ፣ ዳኝነትን የሚያዛንፉ ሰዎች ድርጊታቸው አይታወቃቸውም። ስለሆነም የተበዳዮች ቁጥር ይበረክትባቸዋል። ያም ሆኖ ራሳቸውን አይጠብቁም። ታሪክ ይጠይቀናል አይሉም። የእነሱ ሚዛን፣ የእነሱ ፍርድ ሁሌ ልክ፣ ሁሌ ፍጹም ይመስላቸዋልና ህሊናቸውን አይቆረቁራቸውም።
ፒዩ ባሮዣ የተባለ ታዋቂ ጸሃፊ፤ “እንደ እኔ ጉዳዩ ውስጥ የሌለ ማንም ተራ ሰው፤ ጅብን፣ ሸረሪትንና ዛፍን በማየት በቀላሉ መኖር እንዳለባቸው ይረዳል። የፍትህ አስተሳሰብ አለኝ የሚል እቡይ ሰው ግን ጅብን ሲገድል፣ ሸረሪትን በእግሩ ሲድጣትና ከዛፍ ጥላ ስር ሲቀመጥ፣ ደግ ስራ የሰራ ይመስለዋል” ሲል ግራሞቱን የጻፈው በተመሳሳይ አንፃር ነው። ሰውም እንደ ሀዲስ አለማየሁ ስንኝ፤ “ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” ይላል እስከ ጊዜው።
የህዝብን ምሬትና ብሶት እህ ብሎ ማስተናገድ፣ የማንኛውም መሪ፣ ሃላፊና ሹም ግዴታ ነው። ህዝብን ባልሆነ ተስፋ መሸንገልም ሆነ መዋሸት ኗሪ ትዝብት ማትረፍ ነው። አንዴ ሊሸነገል ቢችል፣ ሌላ ጊዜ በጄ አይልምና።
ኦሉፍ ፓርም የተባሉ ስዊድናዊ መሪ፤ “ስለ ማህበራዊ ፍትህ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን በሃይልና በወታደራዊ ጉልበት ምላሽ ለመስጠት መሞከር ከንቱ ቅዠት ነው። ከቶም ህዝቦች አይተውት የማያውቁትን ነጻነት እከለከልላችኋለሁ በማለት የህዝቦችን እምነት ለማግኘት መሞከር ከንቱ ድካም ነው” ያሉት እንዲህ ያለውን ሁኔታ አይተው ሳይሆን አይቀርም። በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ብንሆን የሰራነው ክፉ ስራ እንደ ጥላ ይከተለናል። ፍትሃዊ ያልሆነ እርምጃና ጠያቂ የለንም በሚል የጉልበት ስሜት የሚመነጭ መብት-ረገጣ፤ በታሪክ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ የአያሌ አገራት ታሪክ ይመሰክርልናል።
አሪስቲድ ብሪያንድ የተባሉ የፈረንሳይ መሪ፤
“ጠመንጃችሁን አስቀምጡ። ማሽንገናችሁን እጠፉ። መድፎቻችሁን ፊታቸውን መልሱ። በመቻቻል፣ በመሸማገል፣ በሰላም እመኑ… ሀገር በታሪክ ውስጥ የምታድገው በጦር ሜዳ በጀግንነት በሚዋደቁላት ሰራዊት ብቻ አይደለም። ፊቷን ወደ ፍትህና ወደ መብት መልሳ ስለእነሱ ጠቀሜታ ስትቆም እንጂ” ብለው ነበር።
ሚዛናዊ ያልሆነ የአእምሮ ፍርድ፣ ስሜታዊ የሆነ ኢ-ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ፣ የማይፈጸም ባዶ-ተስፋና ሰበካ፤ ፍትህን ሊያጨልም የሚችል የማንአለብኝ አቅጣጫ… በታሪክ አስወቃሽ እንደሚሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በጊዜ መታረም ያለባቸውን ነገሮች፣ በግትርነት አሻፈረኝ የሚል፣ የማታ ማታ እጣፋንታው፣ “እኔስ ሮጬ አመልጣለሁ፤ ታሪኬ ወዴት ያመልጣል?” ያለው ሰው አይነት እንዳይሆን፣ ከወዲሁ ማሰብ የአባት ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ
በአዲስ አበባ ከተማ የ2016 ዓ.ም. የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር መካሄዱ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
መርሃ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የምንተክለው ዛሬን አይደለም። ለነገም ጭምር ነው" ያሉ ሲሆን፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ መተባበርን እና በጋራ መስራትን በይፋ ያሳየ ስራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
አክለውም፣ በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የከተማዋ የደን ሽፋን ማደጉን በማውሳት፣ "ከባለፈው ዓመት በላቀ መጠን የመተከል እና የመከታተል ስራ መስራት አለብን" ብለዋል። እንዲሁም ችግኝ የመትከሉን ስራ ከማጠናከር ባሻገር የመንከባከብ ሂደት መከወን እንዳለበትም በአጽንዖት አመልክተዋል።
ባለፈው ዓመት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች በከተማ አቀፍ ደረጃ እንደተተከሉ ያስረዱት ክብርት ከንቲባ አዳነች፣ በዘንድሮው የታቀደው 20 ሚሊዮን ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፣ "የችግኝ ተከላ ስራው በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ደረጃ ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባል" ሲሉ ነው የተናገሩት።
"በጋራ ስንተክል የምንተክለው ችግኝን ብቻ ሳይሆን መተባበር እና አብሮ የመስራትን አሻራ ጭምር ነው።" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ልማት ከሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች ጋር አብሮ የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ፣ "ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች ያለልዩነት አገር በቀል እጽዋት፣ የውበት እጽዋት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ እጽዋት ተክለዋል" ብለዋል።
በእነዚሁ ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት ከ58 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደተተከሉ የገለጹት የቢሮ ሃላፊዋ፣ የእነዚህ ችግኞች 89 በመቶ የጽድቀት መጠን ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።
ወደፊት በአምስት ኮሪደሮች ተለይቶ የሚሰራ ስራ እንደሚኖር የገለጹ ሲሆን፣ "የተገኙ ድሎች ላይ ሳንኮራ ሌሎች ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል" ነው ያሉት።
"ለችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ ካላደረግን ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል" ሲሉ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚያስፈልግ በአንክሮ ተናግረዋል። እስከዛሬ ለተገኙ ስኬቶች ባለድርሻ አካላትን፣ በተለይም ክብርት ከንቲባ እና አስተባባሪ ኮሚቴውን አመስግነዋቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም. ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 በመቶ ከፍ እንዳለ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት አከናውነዋል።
"የምትተክል አገር፣ የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሁለተኛ ምዕራፍ፣ ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ክብር የሚታደሰው ከተረጂነት ስትላቀቅ ነው - የውጭ ጫናዎችን ስታሸንፍ።
ተረጂነት እንደ አዙሪት ነው። ከዓመት ዓመት የእርዳታ እጅ ይጠብቃሉ። ጥገኛ ይሆናሉ። የረጂዎች ታዛዥና ተጎታች የመሆን ፈተና ላይ ይወድቃሉ። ክብራቸውን ያጣሉ። እንዲህ ዐይነት ውርደት፣ በጭራሽ ለኢትዮጵያ አይመጥንም። ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የእርዳታ አዙሪት ጥሩ አይደለም። ለኢትዮጵያ ግን በጭራሽ መታሰብ አልነበረበትም።
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት። በዓለም ታሪክ ሕልውናቸውን አስጠብቀው በነጻነት መዝለቅ የቻሉ አገራት ቢበዛ ከአምስት አይበልጡም። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ውስጥ የምትጠቀስ ናት። ለአፍሪካ የነጻነት ፋና ለመሆን የበቃች አገር ናት። በሕዝብ ብዛት ከዓለም 10ኛ ናት። የተረጂነት አዙሪት በፍጹም ለኢትዮጵያ አይመጥንም።
ከተረጂነት ጋር አብሮ የሚመጣ የታዛዥነትና የተጎታችነት ውርደት ለኢትዮጵያ ባህል “አለርጂክ” ነው። ባለፉት ወራት በመላ አገሪቱ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ፣ ከሕዝብ የቀረቡ ሐሳቦች ይህን መንፈስ አጉልተው አሳይተዋል ይላሉ - የአዲስ አበባ አስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት ም.ኀላፊ ዘውዱ ከበደ።
ለነገሩ፣ “ውርደት ከኢትዮጵያ ባህል ጋር አይሄድም” የሚል የቁጭት ስሜት በሕዝብ ዘንድ መፈጠሩ አይገርምም።
የሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎልና ለማስቆም ብዙ ዘመቻ ተካሂዶብናል። በኢትዮጵያ ላይ እየተደራረበ የመጣባትን የውጭ ጫና እንዲሁ እንደዘበት የምንረሳው አይደለም። ኢትዮጵያውያንን ምንኛ እንዳስቆጣቸው እናስታውሳለን። እንዴት አናስታውስም? በኛው ዘመን በኛ ትውልድ ላይ የተካሄደ ዘመቻ ነው። የራሳችን ታሪክ፣ የእያንዳንዳችን ትዝታ ነው። ያኔ ክፉኛ አንገብግቦናል። አንገሽግሾናል። ዛሬም ይከነክነናል።
“የሕዳሴ ግድብ ግንባታን አቋርጡ፤ አለበለዚያ እርዳታ እንከለክላለን!” የሚል ማስፈራሪያ ሊዋጥልን ይቅርና መታሰቡ ራሱ ይተናነቀናል።
በተረጂነት ሰበብ የሚመጣ የውጭ ጫና እንዲህ ነው ለካ! አገራዊ ጸጋዎቻችንን እንዳናለማ፣ ሠርተንና ገንብተን እንዳናድግ አስሮ የሚይዘን ከሆነ ዘላለም “ተረጂ” ሆኖከመቅረት ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል? ተረጂነት ተረጂነትን ይወልዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። “ተረጂነት ይብቃ” ብለው በጥሰው ሰብረው ካልተላቀቁ፣ እውነትም “አዙሪት ነው” ያስብላል።
በእርዳታ ሰበብ የውጭ ጫናዎችን አሜን ብለን ከተቀበልንማ፣ ከነአካቴው ተስፋችንን ከማጨለም አይመለስም። አገራችን ታዛዥና ተጎታች እንድትሆን ከተገደደች፣ እንዴትስ “አገር አለን” ብለን በሙሉ ልብ እንናገራለን?
የተረጂነት ጣጣ ብዙ ነው። ሁሉንም ነገር ይነካል ይላሉ አቶ ዘውዱ። የሕልውና ፈተና ይሆናል። በኑሮ የመሻሻል ተስፋን ያጨልማል። የኢኮኖሚ እድገትንና የአገር ብልጽግናን አሰናክሎ ያስቀራል። የአገር ሉዓላዊነትን ያሳጣል። የአገርና የሕዝብ ክብርን ያዋርዳል። በተረጂነት ሳቢያ የሚመጡ አደጋዎች ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ባሕልን ሁሉ የሚያበላሹ ናቸው።
ተረጂነት ያስጠቃል፤ ያስደፍራል፤ ያዋርዳል። ከተረጂነት የመላቀቅ ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳችን መሆን ያለበትም በእነዚህ ምክንያቶች ነው። ተስፋችን መጨለም የለበትም። ለልጆቻችን ተረጂነትንና የዕዳ ሸክም ማውረስ የለብንም። የአገራችንና የሕዝባችን ክብር መታደስ አለበት። አገራችን ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ብልጽግና መጓዝ አለባት። ደግሞም ትችላለች። እንደምትችልም ከራሳችን ልምድና ከራሳችን የስኬት ጅምሮች መማር እንደማይከብደን አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
ፈተናዎችን በራሳችን ዐቅም ተቋቁመን መሻገር እንደምንችል በኮቪድ ወረርሽ ወቅት አይተናል። ያኔ የዓለም ኢኮኖሚ እንደተናጋ ሁላችንም እናውቃለን። የብዙ አገራት ኢኮኖሚ አሽቆልቁሏል። በኢትዮጵያ ግን፣ ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቋቋም ጎን ለጎን፣ ኢኮኖሚያችንም እንዲያድግ በጥበብና በትጋት ስለጣርን ተሳክቶልናል።
በኮቪድ ምክንያት የዓለም አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ሲወድቁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በርካታ የመፍትሔ አማራጮችን በመጠቀም ውጤታማ ሆኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ወረርሽኙን ከመከላከል ባሻገር ለዘለቄታው የሚጠቅም መንገድ የጤና ተቋማትን ዐቅም ለማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ ወደ ተሻለ ከፍታ ማደግ አያቅታትም።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰባት ከባድ የውጭ ጫናም ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
በአንድ በኩል፣ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተከራክረን የማሸነፍ ዐቅም እንዳለን አሳይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተረጂነት ሳቢያ የሚመጣ የውጭ ጫና የቱን ያህል አደገኛና የቱን ያህል ቅስም ሰባሪ ሊሆን እንደሚችል በዚሁ አጋጣሚ አይተናል። የሕዳሴ ግድብን ለማስቆም የተካሄደ ዘመቻ፣ የኢትዮጵያን ቅስም ለመስበር የተደረገ ሙከራ ነው ማለት ይቻላል።
ለዚያውምኮ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በብድር ወይም በእርዳታ የሚካሄድ አይደለም። እንደዚያ ቢሆንማ፣ ከመነሻውም እርዳታና ብድሩ አይገኝም። በሆነ ተዓምር እርዳታ ተገኝቶ የግድብ ግንባታ ቢጀመርም፣ የትም አይደርስም ነበር። እርዳታው ተቋርጦ፣ የግድብ ግንባታው ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር።
ኢትዮጵያ በራሷ ዐቅም የምትገነባው ስለሆነ ነው፣ “የአገር ምኞት” በተግባር “የአገር እውነት” ወደመሆን እየተሸጋገረ የመጣው።
እንዲያም ሆኖ፣ ከብዙ ፈተና አላመለጠም። በውጭ እርዳታ የሚካሄድ ፕሮጀክት ባይሆንም፣ ከውጭ ጫና አልዳነም። ለምን? ኢትዮጵያ ተረጂ አገር ስለሆነች በውጭ ተጽዕኖ እጇን መጠምዘዝ እንችላለን ብለው ስላሰቡ ነው። “በደካማ ጎኗ እንግባባት” ብለው ነው የተረባረቡባት። “ለግድብ ግንባታ ባይሆንም ለሌላ ለሌላ ነገር እርዳታ ትፈልጋለች። እርዳታ እንቀንሳለን፤ ከፈለግንም እናቋርጣለን” ብለው የማስፈራራት ቀዳዳ አግኝተዋል።
እንዳሰቡት ቢሳካ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ይቅር የማንለው ከባድ የታሪክ ቁስል ይሆንብን ነበር። ትልቅ የታሪክ ስብራት በደረሰብን ነበር። ፊት ለፊት የመጡ ወረራዎች ሳይበግሯት አሸንፋ መልሳለች። ወረራው እጅግ ሲከፋም “አሻፈረኝ” ብላ፣ እጅ ሳትሰጥና በባርነት ሳትንበረከክ ነጻነቷን አስከብራለች። ዛሬ፣ “ያለ ጦርነት እንድትንበረከክ መጠበቃቸው” ቢያንገበግበን አይገርምም። ነገር ግን አንድ እውነት እንድንገነዘብም ያስገድደናል። ተረጂነት ያስደፍራል፤ ያስጠቃል፤ ለውርደት ያጋልጣል።
ታዲያ ምን እስኪመጣብን፣ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? እስከ መቼስ ነው የእርዳታ እጅ የምናየው? ለምንስ ነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፈው?
በእርግጥ “ተረጂነት ውርደትን ያመጣል” ሲባል፣ በአደጋ ጊዜ ያገዙንን ሰዎች ለማጣጣል አይደለም። እንዲያውም በችግር ጊዜ የደረሱልንን ለማመስገን አናመነታንም። ኢትዮጵያ ታመሰግናለች። አቶ ዘውዱ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከማመስገን ወደ ኋላ አይለም። ክብር የሚያውቅ አገር ውለታ ቢስ አይሆንም። ኢትዮጵያ ደግሞ ክብር ታውቃለች። ታሪኳ ነው። ባለውለታዎቿን ታመሰግናለች።
ነገር ግን “ተረጂ” ሆና ለመቅረት አይደለም። በጭራሽ! አዎ ተከባብሮ መተጋገዝ መተባበር መልካም ነው። ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የራሷን ድጋፍ እንዳበረከተች አቶ ዘውዱ ይናገራሉ። በቅርቡ የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያበረከቱትን የምስጋና ሽልማት በምሳሌን እንደሚጠቀስም ገልጸዋል።
በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሱና የአፍሪካዊ ወዳጅነትን የሚያስፋፋ አገልግሎት ሰጥተዋል።
አሜሪካ የሽብር ጥቃት በደረሰባት ጊዜ ኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን ደቡብ ኮሪያ ድረስ ሄደው መስዋዕት ከፍለዋል። ወደ ኮንጎም ተሰማርተዋል ። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ በስልጠና ረድታለች። በዓለም መድረክ ዋና አለኝታ ሆናላቸዋለች።
እንዲህ ዐይነት የመደጋገፍ ተግባር መልካም ነው። ከመከባበር ጋርም ይሄዳል።
አንዱ አገር የሁልጊዜ ረጂ፣ ሌላኛው አገር የሁልጊዜ ተረጂ ከሆነ ግን መከባበርን ያጠፋል።
“ተረጂነት? በጊዜ ካልተገታ፣ “ጌታና አሽከር” ለመፍጠር ይጠቀሙበታል። በወዳጅነት ምትክ የበላይነትና የበታችነት ስሜትን ያቀነቅኑበታል።
“ቁጭ ብድግ በሉልኝ” የሚል ይመጣል።
“ማን ነው አጎንብሶ ያልሰገደልኝ? ማን ነው ተንበርክኮ ያልተለማመጠኝ?” ብሎ ማስፈራራት ይጀምራል።
ኢትዮጵያ እንዲህ ዐይነቱን ውርደት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ሁነኛውና አስተማማኙ መፍትሔ ግን፣ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ በመሻገር የሚገኝ መፍትሔ ነው። ከተረጂነት በመውጣት ነው የውጭ ጫናዎችን ሙሉ ለሙሉ ማምከን የሚቻለው።
እንዲያውም ከረጂነት ውጥታ ወደ ብልጽግና ስትሸጋገር፣ ለወዳጅነት የሚፈልጓት፣ የሚያከብሯትና ከጎኗ የሚቆሙ ይበረክታሉ። በጠላትነት ስሜት ክፉ የሚያስቡባት ደግሞ ሐሳባቸውን ይለውጣሉ። ወይም ለክፉ ያሰቡትን ዋጥ አድርገው ያስቀሩታል። ለጥቃት ሊሰነዘሩ የነበሩ እጆችም ይሰበሰባሉ።
ከተረጂነት የመላቀቅ ሐሳብ ዙሪያ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንዲህ ዐይነት መሠረታዊ መግባባትና የጋራ ጽኑ ዓላማ በውይይት እንደተፈጠረና በውይይት እየዳበረ መሄድ እንዳለበት የገለጹት አቶ ዘውዱ፣ ከተረጂነት መላቀቅ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የአገር ክብር ጉዳይ ነው በሚለው የጋራ አቋም ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
የውጭ ኃይሎች የሚደፍሩት ሳይሆን የሚያከብሩት አገር፣ የሚያከብሩት ሕዝብ እንሆናለን - ለጠላትነት የሚያስቡት ሳይሆን ለወዳጅነት የሚፈልጉት።
ደካማ ጎን አይተው ጥቃት የሚሰነዝሩበት ሳይሆን፣ “ጠንካራ ነው፤ ለምንም አይበገርም፤ የሚቃጡበትን ያሳፍራል” ብለው ይጠነቀቃሉ። “ኢትዮጵያ የሚያከብራትን ታከብራለች” ብለው የሚተማመኑባት ጠንካራ አገር ትሆናለች። ክብሯም ይታደሳል። በኛ ዘመን የኢትዮጵያን ክብር ማዋረድ የለብንም።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ከዕዳ ወደ ምንዳ” እንዲሉ ነው። ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ብርሃን መሸጋገር ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። ካወቅንበትና ከሠራንበት፣ አገራችን ዕምቅ ጸጋ የበዛላት አገር ናት። በአገራችን በየአካባቢያችን የሚገኙ ጸጋዎችን ወደ ብልጽግና ልንቀይራቸው እንችላለን። በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የምንሆንበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም።
ያኔ፣ የተረጂነት ታሪክ የድሮ ትዝታ ይሆናል። በችግር ጊዜ በቀና ልቦና የረዱንን የምናመሰግንበት ትክክለኛው መንገድም፣ ከተረጂነት በመውጣትና ራሳችንን በመቻል ነው። ከራሳችን አልፈን ወደ ብልጽግና ስንጓዝና ሌሎችን የመርዳት ዐቅም ሲኖረንም ነው “ውለታ ከፋይ” የምንሆነው ይላሉ - አቶ ዘውዱ ከበደ።
ነቢይን የሚያውቁት ምን አሉ??
“ነቢይን የሚያውቅ ሁሉ ሳቁን ይጋራል”
‹‹እምቢልታ ማስነፋት ነበር አመላችን
ነጋሪት ማስመታት ነበር አመላችን
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን››
ብለው ነበር አሉ፣ በአንድ ቀን አዳር፣ ከንግሥትነት ወደ ወይዘሮነት የተቀየሩት እመቤት፡፡
ይህ አባባል ዛሬ ነበር ሊባል ለተገደድነው ለነቢይ ይሁን ለሕያዋን እንደሚሠራ በደንብ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ነቢይ መቶ ወዳጆች ካሉት ከሁሉም ጋር የተለያየ ትዝታ፣ የተለያየ ወግ፣ የተለየ ሣቅ፣ የተለየ ትረካ ያስቀመጠ ሰው ነው፡፡ (እንዲያውም ቢያንስ አንድ ሰው ጋ መቶ የተለያየ ታሪክ አስቀምጧል፡፡) ነቢይን የሚያውቅ ሰው ሁሉ የሚጋራው አንድ ነገር ሣቁን ነው፡፡ ሮንግ ተርን ፊልም ኮሚዲ አድርጎ እንደመተረክ ያለ፣ በሕመም ጭምር ፈገግ ብሎ ማውራት የነቢይ ወዳጆች የጋራ ትዝታ ነው፡፡
ነቢይ በራሡ አባባል ‹‹ቀለሜዋ›› የሳይንስ ተማሪ መኾኑና ኬሚስትሪን ደህና አድርጎ ማጥናቱ ጠቅሞት ይመስላል፣ ፔሬዲክ ቴብሉን ገልብጦ፣ ወደ ጥበብ አምጥቶት ተርጓሚ፣ ደራሲ፣ ጸሐፌ-ተውኔት፣ ተዋናይ፣ ሰዓሊ፣ ተራኪ፣ ገጣሚ፣ ጋዜጠኛ… በሁሉም መስክ ልክ በልጅነቱና በወጣትነቱ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪዎቹ እንደሚሠጡት ውጤት 100 ከ 100 በሚያሰጥ ብቃት ተወጥቶታል፡፡ ችግሩ ግን ነቢይ ይህ ሁሉ ማዕረግ ይጠብበዋል፡፡ ነቢይ ራሡ ማዕረግ ነው፡፡
ነቢይ መኮንንን ወደፊት ለሚመጣ ትውልድ ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ፣ (ይህም ቢኾን ያንሰዋል) ነቢይ ‹‹ጉግል›› ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ቅጠል ሆነ ስለ ሰው አንድ ቃል ብቻ ሲጠራለት ‹‹ኦ እሱኮ አሪፍ ነው፡፡›› ብሎ ይጀምራል፡፡ በቃ ከዚያ ተከትሎ የሚናገራቸው ነገሮች… ራሱ የኮምፒውተሩ ጉግልም የሚያውቃቸው አይመስለኝም፡፡ ደግሞ የሚያወራው መረጃ አይደለም - መረጃማ ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ነቢይ ግን ራሱ ሰውዬው ቢጠየቅ ስለራሱ የማይናገረውን ሁሉ ያስረዳል፡፡ ነቢይ እንደዚያ ነው፡፡
ነቢይን አግኝቶ ያናገረም ያላናገረም፣ ‹‹ይህን ጉዳይ አንስቼ ሳላወራው…›› ብለው መጸጸት አይቀርላቸውም፡፡ ምክንያቱም ነቢይን አግኝተው ለሚያወሩት ሁሉ ቅርብ ሆኖ የማናገሩን ያህል ዛሬ ሙሉ ቀን ቢያወሩት፣ ቀኑን ሙሉ የሚያወራው ነገር ካለመሰልቸቱም በላይ ያልነገረኝ የቀረ አለ ማለት ነው ያስብላል እንጂ፣ በፍጹም አናግሬዋለሁ ብሎ እፎይ አያስብልም፡፡
ነቢይ መሞቱ እጦት የሚኾነው ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ ለሚያውቁት ለሚያውቃቸው አንድ ትልቅ ወዳጅ መንጠቁ እንዳለ ኾኖ፣ እንደ ሰው ግን የሞተው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የዚህን ሰው አምሳያዎች ለማግኘት ምናልባትም ዘመናትን መጠበቅ ግድ ይላልና፣ እርሱ ለገብረክርስቶስ ደስታ የተጠቀመውን አገላለጽ ጠቅሰው፣ ወዳጁ በኃይሉ ገብረመድኀን አንተም ያው ነህ እንዳሉት፤
‹‹ነቢይን ዓይነት ሰብል ለማግኘት ሥንት ዘመን ማረስ ያስፈልጋል?››
አንድ ወዳጁ ነቢይን ሲገልጸው ምን አለ?
‹‹ነቢይን ግጥም አንብብልኝ፣ ድርሰት ተርክልኝ ማለት ሳይሆን፣ ጠዋት ሲነሳ ጀምሮ በሄደበት እየተከተለ የሚቀርጽ ካሜራ አሰናድቶ ከአካሄዱ፣ አቀማመጡ ጀምሮ ጫማ ጠራጊዎችን፣ የረዥም ዘመናት ወዳጆቹን፣ ዛሬ ያገኙት አድናቂዎቹን፣ ምግብ የሚበላበት ውኃ የሚጠጣበት ቦታ ከአስተናጋጅ፣ ከጥበቃዎች ጋር ሁሉ ሲያወራ መቅረጽ ነው የሚሻለው፡፡›› ግን እንደዚያስ ቢኾን ነቢይ ያልቅ ይሆን?
ደህና ሁን ናዝራዊው ነቢይ፡፡
ደህና ሁን የአድማሱ ሰው፡፡
ደህና ሁን ነቢይ መኮንን፡፡
ሰው ስለሆንህ አመሠግንሃለሁ፡፡
(ዮሴፍ ዳሪዮስ ሞዲ)
በሰቀቀን የፈራነው፣ ሰንሸሸው የከረምነው
እውነት ደረሰ
የቃል ኃይል፣ የኪነት ጉልበት፣ መቅኒው
ተሰብሮ ፈሰሰ፤
ትውልድን የሚያገናኘው፣ የግጥም የቅኔው
ድልድይ፣
ይኸው ዛሬ ፈረሰ፣
ዛሬን ለቀሪው ትቶ፣ ወደ ትላንት ፈለሰ
እንደ ነፋስ ሲነፍሰን ክርሞ፣ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤
የብዙ ተጠየቅ መላሽ፣ የመንፈቅ የዓመቱ
ስንክሳር፤
በወግ ያልተነበበው፣ የየአሳራችን አሳር፤
ከአትሮኑሱ ላይ ወረደ፤
ገድሉን ሰምተን ሳንጨርስ፣ ሰቀቀናችን ላይ
ረፈደ፤
የሁለት ትውልድ መስካሪው፣
መሲህ ነህ ያልነው ነቢይ፣ ላይመጣ ሄደ
ነጎደ፤
ይብላኝልን፣
ያለ ምሥክር ለቀረን።
በሰላም እረፍ ጋሽ ነቢይ !!!!
(ገጣሚ አበባው መላኩ)
የአዲስ አድማሱን ዋና አዘጋጅ በወፍ በረር
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ”
ኢ.ካ
አንጋፋው ገጣሚና ደራሲ፣ ተርጓሚና ጸሃፌ ተውኔት ነቢይ መኮንን የናዝሬት ልጅ ነው - ናዝሬት ተወልዶ ያደገ፡፡ ናዝሬትን ከልቡ ይወዳታል- ከእነ አቧራዋ፡፡ በልጅነቱ ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሞባታል፤ ዘመናዊ ትምህርት ቀስሞባታል፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በናዝሬት የአጼ ገላውዲዮስ ት/ቤት ነው፡፡ ስለዚህም ሁሌም ከአፉ አትጠፋም - ናዝሬት፡፡
ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድምና ከእናቱ ከወ/ሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት መምህር ተከስተ ዘንድ የቄስ ትምህርቱን ተከታትሏል - እስከ ዳዊት ድረስ፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ነው የገባው - በጉብዝናው ተመርጦ፡፡ በ1966 ዓ.ም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪ ነበር ያጠናው፡፡ ተማረበት የሙያ ዘርፍ ግን ሰርቶበት አያውቅም፡፡ መላ ህይወቱን በፍቅር የሰጠውና የተጋው ለኪነጥበብ ሥራዎች ነው፡፡
ነቢይንና ሥራዎቹን በጥልቀት የሚያውቁ ብዙዎች እንደሚመሰክሩት፣ ነቢይ መኮንን ሁለገብ ከያኒ ነበር፡፡ ያልሰራበትና አሻራውን ያላኖረበት የጥበብ ዘርፍ የለም፡፡ ከሥነግጥም እስከ ተውኔት፣ ከትርጉም ሥራዎች እስከ የፈጠራ ድርሰቶች ድረስ ተራቆበታል፡፡
የሥነጽሁፍ ረዳት ፕሮፌሰሩ የሻው ተሰማ በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ”ሙያና ጥበብ ሲመጋገብ - ከታወቁ ደራስያን ሥራዎች አኳያ“ በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሁፋቸው፣ ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ይላሉ፡፡
“--ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ግሩም ችሎታ ያለው ተርጓሚ ነው። --ነቢይ አንቱ የተባለ ገጣሚም ነው። ግጥሞቹ ልብን ይመስጣሉ። በተለይ በግጥሞቹ የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ከአዲስ እይታ የሚፈልቁና፣ ሀገራዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው። በዚያ ላይ የተነገረለት አርታኢም ነው። በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት በአዘጋጅነት ሲሠራ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ያስተዋለ ሰው፣ ጠንካራ አርታኢነቱን ለመመስከር ግንባሩን አያጥፍም።” ሲሉ የነቢይን ሁለገብ ከያኒነት አስረግጠው ይገልጻሉ፡፡
ነቢይ የትያትርና ድራማ ጸሃፊም ነበር፡፡ ከአስርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኮንንና ሌሎችም አርቲስቶች የተወኑበት፡፡ ጭብጡ ዛሬም ድረስ ተባብሶ የቀጠለው ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ ድራማው ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ፣ እንደ አዲስ በከፍተኛ አድናቆት ነው የታየለት፡፡ ነቢይ ”ናትናኤል ጠቢቡ“ የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ “ጁሊየስ ቄሳር” ሌላው ተርጉሞ ለዕይታ ያበቃው የጥበቡ በረከቱ ነው፡፡
በደርግ ዘመን እንደ እድሜ አቻዎቹ ሁሉ፣ በጸረ-አብዮተኝነት ተጠርጥሮ ወህኒ የተወረወረው ነቢይ መኮንን፤ ከዛሬ ነገ ይሙት ይትረፍ ሳያውቅ፣ Gone With The Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ ልብወለድ መጽሐፍ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ፣ በድብቅ በማስወጣት፣ ከእስር ሲፈታ ነበር፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ያሳተመው፡፡
ይህን አስገራሚ ታሪክ ሰምታ የተደመመች አንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ባህር ተሻግራ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ከነቢይ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እኔ ደግሞ አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ወደ ሃገሯ ልትመለስ አንዲት ቀን ሲቀራት አግቼያት ኢንተርቪው በማድረግ፣ ታሪኩን ለአዲስ አድማስ አንባቢያን አድርሻለሁ፡፡
“ነገም ሌላ ቀን ነው” የተሰኘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም በሳንሱር ምክንያት መግቢያውና አንዳንድ ሃሳቦቹ ተቆራርጠው መውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በቅርቡ ሦስት መጻሕፍትን በአንድ ላይ ሲያስመርቅ አብሮ የተመረቀው ህትመት ግን በፊት ያልታተመው መግቢያ፣ ታክሎበት በአዲስ መልክ ነበር ለንባብ የበቃው፡፡
በቅርቡ በአንድ ላይ ከተመረቁት ሦስት የነቢይ ሥራዎች አንዱ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከዓመት በላይ በተከታታይ ሲቀርብ የነበረውና ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ ታሪኩ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን አኗኗር ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ሦስተኛው መጽሐፍ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ The Last Lecture ከሚለው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ የተተረጎመ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አድማስ ላይ ተቀራራቢ ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ነቢይና እኔ እየተረጎምን በተከታታይ አስነብበናል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ”ቱስዴይ ዊዝ ሞሪስ” የተሰኘ ሲሆን፤ “ፕሮፌሰሩ” በሚል ርዕስ ነበር ያቀረብነው፡፡
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚያወጣቸውና በመድረክ ላይ በሚያቀርባቸው ጥልቅ ሃሳቦችን ያዘሉ ውብ የሥነግጥም ሥራዎቹ፣ ከፍተኛ አድናቆትንና ዕውቅናን ተቀዳጅቷል፡፡ “ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ በመጻሕፍት አሰባስቦ ከሰነዳቸው የሥነግጥም ሥራዎቹ ሁለት እጥፍ ያህል የሚሆኑት ግን በየቦታው ተበታትነው ነው የሚገኙት፡፡ አሰባስቦ ለህትመት የማብቃት ሥራ ይጠይቃል፡፡
ነቢይ በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ተቀናቃኝን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ማንም ሰምቶት አያውቅም፡፡ እንደ ብዙዎቹ የጦቢያ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ደሜን አፍስሼለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለ አይመጻድቅም፡፡ በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ፣ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት፣ ከመጻፍና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ማቅረብ ይወዳል - በጽሁፉም በንግግሩም፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ታዳሚን በሳቅ ያፈርሳል - አፍ ያስከፍታል፡፡ አንደበቱም ብዕሩም የተባለት የጥበብ ባለሙያ ነበር፡፡
ነቢይ ባህልና ጥበብ አገርን እንደሚለውጥ ጽኑ እምነት ነበራ፡፡ በዚህም እምነቱ ነው አዲስ አድማስ በተለይ ጥበብና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሰራ ያደረገው፡፡ የየሳምንቱን ርዕሰ አንቀጽ በተረትና ምሳሌ በመጻፍ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን ጽፏል - ለጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ፡፡ አያሌ የርዕሰ አንቀጽ አንባቢያንንም አፍርቷል፡፡
የሥነጽሁፍ ረዳት ፕሮፌሰሩ የሻው ተሰማ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ”ሙያና ጥበብ ሲመጋገብ - ከታወቁ ደራስያን ሥራዎች አኳያ“ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፋቸው፤ “በርካታ የነቢይ ተደራስያን ነቢይን የሚያውቁት በተለይ በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተረቶቹ ነው። ከዶ/ር እንደለ ጌታ ከበደ ጋር ባደረገው አንድ ውይይት ላይ እንዳስተዋልነው፣ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን በጋዜጣው ላይ በርእሰ አንቀጽነት ጽፏል። ይህ ለየት ያለ የርእሰ አንቀጽ ይትበሃል፣ ለጋዜጣው የተለየ የተነባቢነት ሞገስ እንዳጎናጸፈው መናገር ይቻላል።” ብለዋል፡፡
ነቢይ፤ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአዲስ አድማስ ላይ ያለገደብ በነጻነት የሚስተናገዱት፡፡ እርሱም እንደ ጋዜጣው መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ሁሉ ሃሳብን አይፈራም፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልጹና እንዲጽፉ ሲያበረታታ ነው የኖረው፤ በዋና አዘጋጅነት ዘመኑ ሁሉ፡፡
አዲስ አድማስን ለምን እንደመሰረቱ ባስረዳበት የመጀመሪያ ርዕሰ አንቀጹ ላይ፤”የጋዜጣ ስራ እንጀምር ያልንበት አንዱ ምክንያት የልባችንን ለመናገር ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሌሎቹ ዘንድ የጎደለ የመሰለንን እኛ ልንሞላ ነው፡፡ ‘ምሉዕ በኩላሄ’ (ፍፁም የተሟላ) ያደርገዋል ባንልም፣ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው፡፡ ሁላችንም ያለንን ካልወረወርን፤ የአንባቢዎቻችን ገደል - አከል የኢንፎርሜሽን ረሃብ፣ ገርበብ ሊል አይችልምና የፕሬስ እድር ውስጥ ገብተን ጠበል እንጠጣ ብለን ነው” ብሏል፤የዛሬ 24 ዓመት ለንባብ በበቃው የመጀመሪያው የጋዜጣው ዕትም፡፡
ከጋዜጣው መሥራቾች አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ ስለ አዲስ አድማስ ዓላማ ሲያስረዳም፤ “የጋዜጣችን አላማ፤ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ፤ መሰረታዊ እውቀትን ሊያስጨብጡ፣ አስተዋይና ሀላፊነት ሊሰማቸው የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የሚያግዙና ያሉትንም ለማጠናከር የሚበጁ ዜናዎችን በወግ በወጉ ማቅረብ ነው፡፡” ሲል ገልጾታል፤ በርዕሰ አንቀጽ ፅሁፉ፡፡
ለዛሬ በሁለገቡ ከያኒና የአዲስ አድማስ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኮንን የጥበብ ህይወት ዙሪያ ያጠናቀርኩትን አጭር የግል ዳሰሳዬን በዚሁ እቋጫለሁ፤ ዳግም እንደምመለስበት ቃል በመግባት፡፡ ራሱ ነቢይ በአንደበቱ እንደተናገረው፣ ከሁሉም በላይ ግጥም ይበልጥበታል፡፡ ነፍሱ ለግጥም ታደላለች፤ ገጣሚ የሚለውን መጠሪያም ይወደዋል፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የምንለያየው በራሱ ግጥም ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ለነቢይ ለቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና አድናቂዎች መጽናናትን ከልቤ እመኛለሁ፡፡ የነቢይን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡
ለራስ የተጻፈ ወቀሳ
እንጠራራ እንጂ
እንፋለግ እንጂ
ከያለንበቱ
ሰው የለም አንበል፣ አለ በየቤቱ
ምን ቢበዛ ጫናው፣ አንገት ቢያቀረቅር
ምን አፉ ቢታፈን፣ ዝም ቢልም አገር
ምን መሄጃ እስኪያጣ፣ መንገዱ ቢታጠር
ጎበዝ እንደ ጭስ ነው፤ መተንፈሻ አያጣም
ቀን መርጦ ሰው መርጦ መነሳቱ አይቀርም፡፡
(ነቢይ መኮንን፤ አዲስ አድማስ፤
ግንቦት 9 ቀን 1995 ዓ.ም)
“አገሬ አቃቤ ጥበቧን በሞት ተነጥቃለች”
- ነቢይ ተደራራቢ የጤና እክሎች ነበሩበት
- “ነቢይ መኮንን ከሳቅ የተሰራ ሰው ነው
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ሁለገብ ከያኒ ነቢይ መኮንን፤ የጥበብ መክሊታቸውን አሟጠው ሳይጠቀሙ ህይወታቸውን በሞት ለሚነጠቁ የጥበብ ሰዎች “የዕድሜ ዕቁብ በኖረ” ሲል በግጥም ምኞቱን አስፍሯል።
….”ምነው ለጥበብ ሰው
ለበሳል ኪነት ሰው
እቁብ በኖረ፣ ወይ የእድሜ ቀይ መስቀል
የክፉ ቀን ደራሽ፣ አንድ ቀን የሚውል
አንድ የጥበብ መዓልት ለሟች የሚቀጥል
ከባካኝ ጊዜያችን፣ ደቂቃና ሰዓት እየቆነጠርን
ለልባም ፀሃፊ የምንለግስበት፣
ዋ! የዕድሜ ዕቁብ ቢኖር!...”
የአንጋፋው ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን የህልፈት ዜና ድንገተኛ ነበር - አስደንጋጭ። ምንም እንኳን ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ረቡዕ ህይወቱ ማለፉ ከቤተሰቦቹ የተነገረ ቢሆንም፣ ህመሙም ህልፈቱም ዱብ ዕዳ ነበረ - ለብዙዎች። ነቢይ በአንድ ወቅት ታምሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ የጤንነቱን ሁኔታ ይከታተል የነበረ አንድ የህክምና ባለሙያ እንደሚናገረው፤ “ነቢይ ተደራራቢ የጤና እክል ቢገጥመውም ጨዋታ አዋቂነቱን፣ ገጣሚነቱንና አገር ወዳድነቱን አላጎደለበትም።”
ግን አሁን ሳይሆን ያኔ። በቅርቡ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ራሱ እንደገለፀው፤ ወደ ህንድ አገር ተጉዞ የልብ ህክምና ያደረገ፤ ሲሆን በህንዳውያኑ የተራቀቁ የህክምና ቴክኖሎጂ መደመሙንም ተናግሯል። እንዲያም ሆኖ የ70 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ነቢይ መኮንን፤ የልብ ህመም፣ ስኳርና፣ ደም ግፊት እንደነበረበት የሆስፒታል ምንጮች ይናገራሉ።
የትኛው ህመሙ ተባብሶ ለህልፈት እንደዳረገው ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የቅርብ ወዳጆች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ያልተጨናነቀ ህይወቱ ለሚወደው ገጣሚና ደራሲ ነብይ መኮንን የመጨረሻዎች የህይወት ምዕራፎቹ ተግዳሮት የበዛባቸው ነበሩ። ህመሙን ለመንከባከብና ራሱን ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ አላገኘም የሚሉት ወዳጆቼ፣ የቅርብ ሰው በአጠገቡ እንዳልነበረም ነው የሚናገሩት፡፡
የአዲስ አድማስ ዋና ጋዜጣ አዘጋጅና የሁለገብ ጥበብ ባለቤት የነበረው ነቢይ መኮንን ህልፈትን ተከትሎ ለዓመታት ያበረከታቸውን የኪነጥበብ ስራዎች የሚያደንቁና እውቅና የሚሰጡ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል- በማህበራዊ ሚዲያው። በአንጋፋው ገጣሚ ፀሃፊ ተውኔት፣ ተርጓሚና አርታኢ - ነብይ መኮንን ህልፈት እጅጉን ማዘናቸውን የሚገልፁት የጥበብ ወዳጆች፤ ነቢይንና ሥራዎቹን እየዘረዘሩ አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት አስርት ዓመታት ተወዳጇን አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ከምስረታ አንስቶ በዋና አዘጋጅነት የመራው ነቢይ መኮንን፤ ርዕሰ አንቀጽን በተረትና ምሳሌ አዋዝቶ መጻፍን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቋል፤ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ለተቀረውም ዓለም ጭምር፡፡ ይህም የጋዜጣው አንዱ መለያ ቀለም በመሆን የዘለቀ ሲሆን፤ በአንባቢያን ዘንድም ተነባቢነትን አትርፎለታል፡፡
ነቢይ መኮንን ከዋና አዘጋጅነቱ ጎን ለጎን ግጥሞችን ይጽፍ ነበር፡፡ ተወዳጅ ታሪክ ያላቸው መጻህፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም በተከታታይ ያስነብብ ነበር፡፡ ዘ ዳ ቬንቺ ኮድ ፣ ዉመን አት ፖይንት ዚሮ፣ ቱስዴይ ዊዝ ሞሪሰን (ፕሮፌሰሩ በሚል ርዕስ) በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ቀብር ሥነ-ስርዓት ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በአዳማ ተፈጽሟል። ከዚያ በፊት ግን ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ፣ በብሔራዊ ቴአትር ዕውቅ አርቲስቶች፣ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት የነቢይ አስከሬን የሽኝት መርሃ ግብር ተከናውኗል። በመርሃ ግብር ላይ መድረኩን የመራው የማስታወቂያ ባለሙያው አርቲስት ተስፋዬ ማሞ፤ አንጀት በሚበላ የሐዘን፣ የሙዚቃ ቅንብር ታጅቦ እንዲህ ሲል መድረኩን ከፈተው፣
“የደራሲው ብዕር ታጠፈ!”
ከአርቲስት ተስፋዬ በመቀጠል፣ ዕውቁ ተዋናይና ሁለገብ የመድረክ ሰው አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ፤ የነቢይ መኮንንን የሕይወት ታሪክ በንባብ ያቀረበ ሲሆን፤ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ስለነቢይ የሚያውቁትንና የተሰማቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል።
ሌላው በመድረኩ ላይ ምስክርነታቸውን የሰጡት የነቢይ መኮንን የረዥም ዓመታት ወዳጅ ወግ አዋቂው አቶ በሃይሉ ገብረመድህን ሲሆኑ፤ ሳግ በተናነቀው አንደበታቸው፣ ምንጊዜም ሲገናኙ እርስ በርስ የሚለዋወጧትን ግጥም በማውሳት፣ “ለእኔ ዛሬ ኮረኮንቻማ ቀን ነው” ብለዋል። “ነቢይ ከሳቅ የተሰራ ሰው ነው” ያሉት አቶ በሃይሉ፣ የነቢይን ጨዋታ አዋቂነት በስፋት አንስተዋል። የነቢይ መኮንን ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ራኬብ ነቢይ በተመጠነ ንግግሯ ስለአባቷ ቤተሰባዊ ሰብዕና ተናግራለች። በልጅነታቸው ነቢይ የሚጽፋቸውን ጽሁፎች እንደሚያነብላቸው፣ በነጻነት እንዳሳደጋቸው፣ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የተለየ ቅርርብ እንደነበረው ገልፃለች። “እኔ እንደእናንተ ብዙም አላገኘሁትም፣ በጣም ነው ያስቀናችሁኝ” ስትልም ልብ የሚነካ መልእክት ልቅሶ እየተናነቃት አስተላልፋለች።
በመጨረሻም የስንብት መርሃ ግብሩ የተደመደመው በጭብጨባ ነበር፤ ነቢይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ላበረከተው የጥበብ ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት አስከሬኑ እስኪወርድ ድረስ ጭብጨባው አዳራሽ ያስተጋባ ነበር።
መርሃ ግብሩ አንጋፋና ወጣት ዕድምተኞች የተገኙበት ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ የሙዚቃ ተንታኙ ፍሬስብሃት ሰርጸ ይናገራሉ።
“የዛሬው ስንብት ብዙ ትዝብት ያለው ስንብት ነው። ብዙውን ጊዜ ለክዋኔ ጥበባት ሰዎች ሕልፈት የሚኖረው ዓይነት ታዳሚ አይደለም ዛሬ ያየነው። በጥራት ካየኸው ጥርት ያለ ሊሆን ይችላል። ትልልቅ ሰዎችን አይተናል። ግን ነቢይን የሚያውቀው ሰው ይህ ብቻ ነው ብዬ አላምንም። ከፍ ባለ ሁኔታ ሁላችንም ወጥተን አመስግነን ልንሰናበተው ይገባ ‘ነበር’ የሚል ቁጭት አለኝ ብለዋል። ለነቢይ ክብር ያለው ፕሮግራም በተከታታይ በማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም መክሯል።
ለ10 ዓመታት ያህል ከነቢይ ጋር በማዕከላዊ እስር ቤት አብረው የታሰሩት አቶ ግርማ አበራ፣ ከነቢይ ጋር እንዴት እንደተዋወቁ ሲናገሩ፤ “ድርጅት ነው ያስተዋወቀን” ይላሉ። “የቀረውን ዕድሜያችንን እስር ቤት ነው ያሳለፍነው። ነቢይ ከእኔ አንድ ዓመት ቀድሞ ወጣ እንጂ እስከመጨረሻ አብረን ነው የታሰርነው። ከወጣንም በኋላ ቅርርባችን የወንድም ያህል ቀጥሏል - ሲሉ ተናግረዋል።”
ከነቢይ መኮንን ጋር ከ30 በፊት ዓመት እንደተዋወቁ የነገረን ደግሞ፣ ተዋናይ ኩራባቸው ደነቀ ነው። “ከ30 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን በምንሰራበት ወቅት ‘ጁሊየስ ቄሳር’ን ይዞ ይመጣ ነበር። እኛ ደግሞ፣ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ን የምንሰራበት ወቅት ነበር፤ እኔ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ መንበረ ታደሰ...ወዘተ በዚያ ጊዜ እርሱ እዚያ አዘውትሮ ይመጣ ስለነበር የዚያን ጊዜ ነው የተዋወቅነው” ሲል አውግቶናል።
ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ደግሞ እንዲህ ይላል። “እኔ ነቢይን የማውቀው... በሚሰራቸው ስራዎች ነበር። ከዚያ በኋላ ነው እርሱን ለማወቅ ፍላጎት ያደረብኝ። አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ ቅዳሜ ሳነብ፣ ከአምዶቹ ውስጥ ‘የግጥም ጥግ’ የሚል አምድ ነበር። ይህ አምድ አሁን ያለነውን ገጣሚያን መንፈስ ከፍ ያደረገና ያነሳሳ ክፍል ነው። የመጀመሪያ ትውውቄ እርሱ ነው። ከዚያ በኋላ በተለያዩ መድረኮችና አጋጣሚዎች የምንገናኝባቸው ነገሮች ይፈጠሩ ነበር። ወዳጅነታችን እንደዚህ ነው የተጀመረው።” ሲል ተናግሯል።
የተወዳጁ የኪነት ሰው ነቢይ መኮንን አስከሬን በብሔራዊ ቴአትር ሽኝት ከተደረገለት በኋላ በቀጥታ ያመራው ወደሚወዳት የትውልድ ቀዬው ናዝሬት/አዳማ ነው - በኑዛዜው መሰረትም የሚወዳቸው ወላጅ እናቱ ባረፉበት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስከሬኑ አርፏል። ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በተፈፀመው የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና የሚወዳቸው አድናቂዎቹ በ70 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ነቢይ መኮንን ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበር።
በማህበራዊ ሚዲያ “የአዲስ አድማስ እንቁ ነቢይ መኮንን አለፈ” ሲል አስተያየቱን ያሰፈረው ኤልያስ የተባለ አድናቂ፣ “አገሬ ኢትዮጵያ ዛሬ ቀን ጎድሎባታል…. ወጓን ጠብቆና ሰብኮ የኖረ ዐቃቤ ጥበቧን በሞት ተነጥቃች” ሲል ሃዘኑን ገልጿል።
ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንደሚገመት ተገለጸ
በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው ሪፖርት መሰረት፣ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የሚገኙት በሶስት ክልሎች ውስጥ “ነው” ተብሏል። እነዚህም ክልሎች ሶማሊያ፣ ኦሮምያና ትግራይ እንደሆነ ተነግሯል።
አብዛኛዎቹ ቀያቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው ምክንያት፣ በአገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች መሆናቸውንም ቢሮው አመላክቷል።
ቀያቸውን ጥለው ከተፈናቀሉ የአገሪቱ ዜጎች ውስጥ 56 በመቶ የሚሆኑት ቤታቸውን ጥለው ከወጡ፣ ሶስት ዓመት “ሞልቷቸዋል” ሲል ቢሮው አመልክቷል።
ከእነዚህም ውስጥ 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከሁለት እስከ አራት ዓመት እንደሆናቸው ተጠቅሷል። 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ፣ ከቀያቸው ከተፈናቀሉ አምስት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ማስቆጠራቸውን ጠቁሟል።
ከጥር 2014 ዓ.ም. ወዲህ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያስታወቀው ማስተባበሪያ ቢሮው፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቀያቸውን ጥለው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ በአገሪቱ የተፈናቃዮች ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል።
በርካታ ተፈናቃዮች በተለይም ደግሞ ለተራዘመ ጊዜ ከቀያቸው ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎችን የተወሰነ ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲመለሱ ወይም ደግሞ አሁን ተጠልለውባቸው በሚገኙባቸው አካባቢዎች ካሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ኑሮ መስርተው እንዲኖሩ ማድረግ አለያም ደግሞ ወደ ሌላ አከባቢ እንዲዛወሩ ማድረግ እንደሚቻል ያካሄደውን ጥናት ዋቢ በማድረግ ቢሮው አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሃላፊነታቸው ተነሱ
ከግጭት ለመውጣት ሰላማዊ ውይይት
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል። ኮሚሽነሩ ከሃላፊነታቸው የተነሱት በትናንትናው ዕለት ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ ፅሕፈት ቤት ተገኝተው ይፋዊ ስንብት የተደረገላቸው ዶ/ር ዳንኤል፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ሃይሎች “ፈጽመዋቸዋል” ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመመርመር ያመለክታሉ። የተለያዩ ዘገባዎችንና መግለጫዎችን ባልተለመደ ድፍረት በማውጣት ቆይቷል። ከመንግስት ጫና እንደሚያደርስበት የሚገልጹ ዘገባዎች፤ ተደጋጋሚ ስሞታዎችን ቢያቀርብም፣ ይፋዊ ምላሽ እንዳልተሰጠው ያመለክታሉ።
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎችና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዘገበ ሲሆን፣ መራዊ እና ጅጋ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች “ተፈጸሙ” ስለተባሉ የጅምላ ግድያዎች የምርመራ ሪፖርቶችን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦ.ነ.ግ.) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ለግል ጉዳያቸው በሄዱባት፣ መቂ ከተማ መገደላቸው እንደተሰማ ምርመራ ያደረገው ኮሚሽኑ፣ የምርመራ ግኝቱን ለሕዝብ እንዳይቀርብ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጫና እንደተደረገበት አዲስ ስታንዳርድ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ላለፉት አምስት ዓመታት ኢሰመኮን የመሩት ዶ/ር ዳንኤል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የሂዩማን ራይትስ ዎች ምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የነበሩ ሲሆን 1997 ዓ.ም. የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ከሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞች ጋር ለእስር ተዳርገውም ነበር።
ኮሚሽነሩ ከሃላፊነታቸው የተነሱት የስራ ዘመናቸው ስላበቃ እንደሆነ ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአገር አቀፍ ደረጃ ከግጭት ለመውጣትና መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ሰላማዊ ውይይትና ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል። ተሰናባቹ ኮሚሽነር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፣ ትናንት በይፋ በቀረበው በ3ተኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ ነው።