Administrator

Administrator

   የቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ በ1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በተቀመጡት አራት መስፈርቶች ድምር ውጤት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአመቱ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያ የቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ አይሲቢሲ ሆኗል፡፡
ኩባንያው በአመቱ 190.5 ቢ ዶላር ሽያጭ፣ 45.8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ፣ 4.9 ትሪሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት እና 249.5 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ በማስመዝገብ በድምር ውጤት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ነው ፎርብስ ያስታወቀው፡፡
የአሜሪካዎቹ ኩባንያዎች ጄፒሞርጋን ቼዝ እና ቤክሻየር ሃታዌይ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ የአመቱ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ አራተኛ፣ የሳዑዲው የነዳጅ ኩባንያ አራምኮ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ የቻይናው ፒንግ አን ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ የቻይና የግብርና ባንክና የአሜሪካው አማዞን እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
በአለማችን የሚገኙ ኩባንያዎችን አጠቃላይ ሃብት፣ የገበያ ዋጋ፣ ሽያጭና ትርፍ በመገምገም በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ፎርብስ መጽሄት ለ19ኛ ጊዜ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ 2000 ኩባንያዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ በድምሩ በአመቱ 39.8 ትሪሊዮን ገቢ አግኝተዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአመቱ ያስመዘገቡት ትርፍ ካለፈው አመት በ24 በመቶ በመቀነስ 2.5 ትሪሊዮን መድረሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የገበያ ዋጋቸው 79.8 ትሪሊዮን ዶላር፣ አጠቃላይ ሃብታቸው ደግሞ 223 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ በየዘርፉ በቀዳሚነት ከተቀመጡት መካከልም፣ በአየር መንገድ ዘርፍ ዴልታ ኤርላይንስ፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አፕል፣ በሪልስቴት ዘርፍ ብሩክፊልድ አሴት ማኔጅመንት፣ በባንክ ዘርፍ  ቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ፣ በመድህኒትና ፋርማሲ ዘርፍ የአሜሪካው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ፌዴክስ እንዲሁም በኢንሹራንስ ዘርፍ የቻይናው ፒንግ አን ይገኙበታል፡፡


 ማላዊ 20 ሺህ ያህል የኮሮና ክትባቶችን በይፋ አቃጥላለች

          አውስትራሊያውያንና አሜሪካውያን ሳይንቲስቶችን ያካተተ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን፣ በኮሮና ቫይረስ በተጠቁ አይጦች ላይ ተሞክሮ 99.9 በመቶ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠና ገና በምርምር ደረጃ ላይ ቢሆንም ሰዎችን በመፈወስ ረገድም ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ፍቱን የጸረ-ኮሮና ቫይረስ መድሃኒት ማግኘታቸውን ከሰሞኑ እንዳስታወቁ ዥንዋ ዘግቧል፡፡
የአውስትራሊያው ግሪፍዝ ዩኒቨርሲቲና ካሊፎርኒያ ከሚገኘው ሲቲ ኦፍ ሆፕ የካንሰር ምርምር ማዕከል የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉትን የምርምር ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ሳይንቲስቶቹ አግኝተነዋል ያሉት ጸረ-ቫይረስ መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ በተጠቁ አይጦች ላይ ተሞክሮ ቫይረሱን እንዳይባዛ በማድረግና በመግደል ረገድ ውጤታማነቱ 99.9 በመቶ ፍቱን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሲአርኤንኤ በተባለ ሳይንሳዊ መንገድ የሚሰራው መድሃኒቱ በተጠቂዎች አካል ውስጥ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ክምችት በ99.9 በመቶ ያህል እንደሚቀንስና፣ ተጠቂዎች መድሃኒቱ ከተሰጣቸው በኋላ በሳንባቸው ውስጥ ምንም የኮሮና ቫይረስ  እንደማይገኝ የምርምር ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ኒጌል ማክሚላን ጆርናል ኦፍ ሞሎኪዩላር ቴራፒ በተባለው መጽሄት ባሳተሙት የምርምር ውጤት ጽሁፍ ማስታወቃቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከዚህ ቀደም ታሚፍሉ፣ ዛናሚቪርና ሬምዲስቪርን የመሳሰሉ ጸረ-ቫይረሶች ለኮቪድ ታማሚዎች ሲሰጡ ቢቆዩም፣ በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶችን የሚያፋጥኑና ታማሚው ቀደም ብሎ እንዲያገግም የሚያግዙ እንጂ እንደዚህኛው የምርምር ውጤት ቫይረሱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱና ፈዋሽ እንዳልሆኑም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ማላዊ የአገልግሎት መስጫ ጊዜያቸው አልፏል ያለቻቸውን ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ባለፈው ረቡዕ ማለዳ በመዲናዋ በሚገኘው ካሙዙ ሴንትራል ሆስፒታል ማቃጠሏን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ከውጭ አገር ዘግይተው በመግባታቸው ሳቢያ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፏል ያላቸውን 19 ሺህ 610 የአስትራዜኒካ የኮሮና ክትባቶች በማቃጠል ማስወገዱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ህዝቡ በክትባቶቹ ላይ ያለው እምነት እንዲያድግ ያደርጋል ብሎ እንደሚያምኑ የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ቃል አቀባይ መናገራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
ማላዊ በአፍሪካ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በይፋ በማቃጠል ያስወገደች የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከአፍሪካ ህብረት ካገኘቻቸው 102,000 የአስትራዜኒካ ክትባቶች መካከል 80 በመቶ ያህሉን ለዜጎቿ መስጠቷንም አስረድቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ጋር በተያያዘ እንዲራዘም የተደረገውና በመጪው ሃምሌ ወር መጨረሻ ኮሮናን ለመከላከል በሚያስችል ጥብቅ ቁጥጥር እንዲካሄድ የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ በድጋሚ እንዲሰረዝ የአገሪቱ ዶክተሮች ለመንግስት ጥሪ ማቅረባቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ 6 ሺህ ያህል የህክምና ዶክተሮችንና የጤና ባለሙያዎችን በአባልነት የያዘው የቶክዮ ሀኪሞች ማህበር፣ ባለፈው ማክሰኞ ለአገሪቱ መንግስት አሰባስበው ባስገቡት ፊርማ #ኮሮና አሁንም ስጋት ነው፤ ወረርሽኙ ዳግም ቢያገረሽ በቂ ህክምና ልንሰጥ የምንችለበት ሁኔታ ላይ አይደለም የምንገኘው ስለሆነም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሎምፒኩ በድጋሚ እንዲራዘም በአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል; ሲሉ መጠየቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ማህበሩ ከአባላቱ በተጨማሪ ሌሎችም ሃሳቡን እንዲደግፉት በድረገጽ በጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ላይም፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፊርማቸውን በማስፈር ኦሎምፒክ እንዲራዘም መጠየቃቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

   በሰዓሊ መምህርና የፎቶግራፍ ባለሙያ ወንዶሰን በየነ የተነሱ በርካታ ፎቶዎች ከአማርኛ ግጥም ጋር የሚቀርቡበት “Ethiopia Through my Eyes” የተሰኘ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን የፊታችን አርብ ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ካዛንቺስ በሚገኘው ራዲሰን ብሉ ሆቴል ይከፈታል።
“ፎቶግራፎቼ ለኔ የጥበብ ተጋሪዎቼ ናቸው፣ በጥልቅ እይታ ያነሳኋቸው ፎቶዎች ስሜቴንና ዕይታዬን ይገልጡልኛል” የሚለው ሰዓሊ መምህርና ፎቶግራፈር ወንዶሰን በየነ፣ በዚህ ስሜት ያነሳቸው መልከአምድርን፣ የሰው መልክን፣ የኑሮ ዘይቤንና ባህልን የሚያሳዩ ፎቶዎች በኤግዚቢሽኑ ለዕይታ እንደሚቀርቡ ታውቋል። በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ሰዓሊያን የፎቶግራፍ ባለሙያዎችና የጥበብ አፍቃሪያን እንደሚታደሙ የተገለጸ ሲሆን በኤግዚቢሽኑ የአማርኛ ግጥሞች እንደሚካተቱና ኤግዚቢሽኑ እስከ ረቡዕ ግንቦት 25 ቀን ለእይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።

          ከመደናገር መነጋገር በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃች የዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ ምጥን መፅሀፍ ውስጥ ለዛሬ ርዕስ አንቀፃችን የምትሆን ቁምነገረኛ አስተማሪ ፅሁፍ አግኝተን እንደሚከተለው አቀረብናት፡፡

    ተጠያቂነትን የሚፈራ መሪ….

ተጠያቂነት የሚፈራ መሪ፣የቤት ስራውን ሳይሰራ እንደሚቀመጥ ሰነፍ ተማሪ ነው። ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች፤ ለዜጎቻቸው የስራ ሪፖርት ማሰማትም ሆነ ለውይይት መጋበዝ አይፈልጉም፡፡ጋዜጣዊ መግለጫን እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ ምክንያቱም ይነሳሉ ብለው ለሚጠረጥሯቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ አይኖራቸውም፡፡ ይህን ካደረጉም እነሱም በጥሩ ቀለም የሚስላቸውን ድርጊት እየቀነጫጨቡ፣ትንሹን እያባዙ በማቅረብ ሳይጠየቁ በራቸውን በፍጥነት ይዘጋሉ፡፡
ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች በትናንትና ጥፋታቸው እየጸኑ የሚሄዱ እንጂ፣ከጥፋታቸው ተምረው የሚመለሱ አይደሉም፡፡ ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች ሊጠይቃቸው የሚችለውን ግለሰብ ፊት የሚነሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ የዛ ግለስብ ስምም ዝክርም እንዲወሳ የማይፈቅዱ ናቸው። ከተጠያቂነታቸው የሚሸሹ መሪዎች ተቃራኒ ወይም ተቃዋሚ ሀሳብን የሚያዳፍኑ ናቸው። የተዳፈነ እሳት ደግሞ ጊዜ ጠብቆ ምን ሊሆን እንደሚችል የሰው ልጅ የረጅም ጊዜ ታሪክ ደጋግሞ አስምሮበታል፡፡
ይህም ሲባል አሉታዊ ምላሽ ሁሉ ገንቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችም ሆኑ የማህበረሰብ አባላት፣የሚደረገው መልካም ነገር የማይታያቸው፣ ሁልጊዜ ለስሞታና ለሀሜታ የሚፈጥኑ መሆናቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ወይም የማህበረሰቡ አባሎች የራሳቸው የተደበቀ የጨለማ ምክር ያላቸው፣ እነሱ ካልመሩና አንቱ ካልተባሉ በስተቀር የመኖር ትርጉም የሚጠፋባቸው፣ስነ- ልቦና ቀውስ የተጠናወታቸው ህመምተኞች ናቸው፡፡
ሌላውን ግለሰብ ወይንም የማህበረሰብ ክፍል ድካምና ጥረት ውድቅ ባደረጉ ቁጥር፣እነሱ ታላቅነትን የተላበሱ ስለሚመስላቸው አንደበታቸውን ለሰባሪ ቃል፣አይናቸውን ደግሞ ጥፋትን ብቻ ለመመልከት የተከፈቱ ናቸው፡፡ ሲናገሩ ገንቢ ሂስ ለማስተላለፍ ሳይሆን፣ሌላውን ዜጋ ወይንም በጊዜው በመሪነት ወንበር የተቀመጠውን ሰው፣ በአደባባይ የውስጥ ልብሱን ገልበውና አውልቀው በማዋረድ ራሳቸውን ለማስከበር የሚያሴሩ ሸረኞች ናቸው፡፡
እነዚህ ቅን የሆነን ጅማሬ ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ ወደ ፍሬ እንዲደርስ ከማገዝ ይልቅ ትንሿን እንቡጥ፣ ከስር በመንቀል ወዲያው እንድትወድም የሚችሉትን ሁሉ ከመጋረጃ ጀርባ ይሁን በአደባባይ የሚፈፅሙ፣ የህዝብ ሰላም፣ምቀኞች ናቸው፡፡ ሌላው ወገናቸው ሰርቶ ሲመሰገን ማየትና መስማት እንደ ኮምጣጤ የሚመራቸው ግለኞች፣ የስኬት ደንቃራዎች ናቸው።
የአሉታ ድምፃቸው  ለግንበታ ሳይሆን ፣ ለማውደም ያነጣጠረ ስለሆነ፣ ሰሚውን የሚያንጽ ምንም የእወቀትና የጥበብ ቃል የለውም፡፡ ከራሳቸው ጋር ሰላም የሌላቸው፣የራሳቸውን የግል ኑሮ በውጤታማነት የመምራት አቅም ያጡ፣ቤታቸው፣ትዳራቸው፣የተፋታባቸው፣ በእኩይ ስነ ምግባራቸው ቤተሰብ ወዳጅ ያራቃቸው ስለሆኑ፣ለሀገር አመራር የበቃ ሰናይ ስነ ምግባር አላቸው ብሎ ማሰብ፣ በመሪነት ወንበር ድንገት ተቀምጠው ለሚያወርዱት ውርጅብኝ ተስማምቶ መፈረም ነው፡፡
ቤቱን በቅጡ ያላስተዳደረ ሰው፣ የህዝብ አለቃ ሲሆን፣ተለውጦ የመልካም አስተዳደር ሰብዕና ይጎናጸፋል ተስፋ ማድረግ፣ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ለዚህ ነው አንድ ሰው “እኔ” ብሎ እራሱን ሳያስተዋውቅ፣ ይህ ሰው ከቤተሰቡ፣ከወዳጆቹ፣ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች አንዱ ጋር የሚሆኑት፣ሌላው ጋር የሆኑትንት፣ ስለሆነ ነው፡፡
ቆም ብለው እራሳቸውን የማያዩ፣ የሚሰነዘርላቸውን ገንቢ ሀሳብ ተቀብለው የማያስተካሉ፣ ህክምናም የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ታክመው ችግራቸውን  ያልቀረፉ ሰዎች፣ያለምን ስነ ልቦናዊ እገዛ ነገ ጠዋት ሲነሱ   ሌላ ሰዎች ሆነው ይለወጣሉ ብሉ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ በመለኮታዊ ታምር ይሁን ራስን በግል  ሆነ በጋራ በማረቅ ያልተቃና ጠማማነት፣ ነገ ቀና ሆኖ ቀን ይለውጠዋል፤ ማለት የሚያከስር ተስፋ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህ በሌላ ወገን ስኬት የሚቃጠሉ፣ሌላውን በመክሰስ ራሳቸውን ነፃ የሚያደርጉ የሚመስላቸው ሰዎች፣አሉታዊ ሂስ መስጠታቸውን መቼም ስለማያቆሙ፣ማን መሆናቸውን አጥርቶ ማወቅ፣ሁልጊዜ ከሚወረውሩት ፍላፃ እራስንና የተያዘን መልካም ሀሳብ ለመጋረድ ይጠቅማል፡፡ ስለ እንደነዚህ ዓይነት እኩይ ሰብዕናዎች ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ፣ የሰላም ሰዎች አለመሆናቸውን ነው፡፡ ሆን ብለው በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና፣ በብሔረሰብና መካከል ጠብና ግጭት የሚጭሩ የሰላም ጠሮች ናቸው፡፡
ህዝብ ውጥረት ውስጥ ሲወድቅ፣የእነሱን እኩይ ስነ ምግባር ልብ ስለማይል፣ሁልጊዜ አለመረጋጋትን በመዝራት፣ራሳቸውን በዚያ ግርግር የሚደብቁ፣ በዜጋ ግራ መጋባት የሚስቁ የሚሳለቁ ከንቱ ሰዎች ናቸው፡፡ ራሳቸው የጫሩትን ጠብ፣ዞር ብለው ደግሞ ካልዳኘን ብለው የሚቀርቡ ጉበኛ ፈራጆች፣ሌባ ፖሊሶችም ናቸው፡፡ በወገን ግጭት ምክንያት በከንቱ የሚጠፋ የሰው ሕይወት፣ ጊዜ፣ የሀገር ሀብትና፣ንብረት የማይገዳቸው፤ ነገር ግን በግጭቱ ምክንያት የሚከፈትላቸውን መልካም አጋጣሚ ለዘረፋቸው የሚጠቀሙ ምንኞች ናቸው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ወይንም መሪዎች የሰላም መፍትሔ የላቸውም ኖሯቸውም አያውቅም የግጭቱ ዘመን እንዲራዘም እሳቱ ላይ ጋዝ የሚያርከፈክፉ አደጋ ጣዮችም ናቸው፡፡ የሰላም ምክርን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን፣ ምንም ዓይነት የሰላም ማመቻመች አይመቻቸውም፡፡ ለእርቅ የሚደረገውን ሀሳብ ሁሉ ውድቅ የሚያደርጉ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ባላዋቂ ሰዎች ውስጥ እየተደበቁ የራሳቸውን እኩይ ሃሳብ በማራመድ የሳር ውስጥ እባብ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ ለሰላም ሲባል ሊከፈል የሚገባውን ዋጋ መክፈል የማይፈልጉ የውጥረትና ግጭት  ዘመን እንዲረዝም የሚሹ፣ የረባ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ የሌለውን  አላዋቂ ዜጋ እየደለሉ፣ በጀርባ የሚፈናጠጡ ተጣባቂና ተለጣፊ ህዋሳት ናቸው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች እያወቁ ከሚረጩት መርዝ ህዝብም ሆነ መንግስት ሊጠነቀቅ ይገባል። ሂስ ሰጪ ሁሉ ገንቢ እንዳልሆነ መገንዘብ ከመፈራረስ ያተርፋል፡፡ መልካም መሪዎች ግን ለበጎ ምክር  ብድግ ብለው የሚሰለፉ፣ በእሺ ባዮች ሳይሆኑ፣ ከቀና ልብና ለቀና የነገ ተስፋ ሲሉ፣ እውነቱን በፍቅር በሚናገሩ ሰዎች የተከበቡ ናቸው፡፡ መሪዎች ጉድለታቸውን በዜጋቸው ብቃት በመሙላት፣ ስልጣናቸውን በማከፋፈል የተሻለ እይታ ባላቸው ሰዎች ሊከበቡ እንጂ በምሁራንና የተሻለ ያውቃሉ በሚባሉ ዜጋዎች ምክንያት ስጋት ውስጥ ሊገቡ አይገባቸውም፡፡

   "የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው"

                ኢትዮጵያ በመጭው የክረምት ወራት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የሙከራ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የገለጸ ሲሆን በመጭው ክረምት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድም ተነግሯል፡፡
ከግድቡ ሙሌትና ግንባታ ጋር ተያይዞ የአሠራር ሂደቱን “ምንም ዓይነት ኃይል አያደናቅፈውም” ብሏል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፡፡
የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል ዶ/ር  በለጠ ብርሃኑ ባለፈው ረቡዕ ለኢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና፤የታላቁ  የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል፡፡ በጎረቤት ሃገራትና ታላላቅ ሃይቆች ክልል የሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤትጋር በመተባበር፣ “የናይል ፍትሃዊ አጠቃቀም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለክልላዊ ትብብር ያለው ሚና” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በሶስቱ ሃገራት የተመራማሪዎች ብሄራዊ ቡድን በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚካሄድ ነው አቶ ደመቀ መኮንን የገለጹት፡፡  የሶስትዮሽ ድርድሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነትም አረጋግጠዋል።
ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑም አልሸሸጉም፤አቶ ደመቀ መኮንን፡፡  
በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር ደንግ ዳው ደንግ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብጽ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የግብጽ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር መግለጻቸው ጥሩ ጅማሮና የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ ገለጻ፣ ግብጽ በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ቀደም ሲል ታራምድ የነበረውን አቋም በመቀየር፣ ኢትዮጵያ የምታራምደውን አቋም ወደሚደግፍ ሃሳብ መሸጋገሯን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡


በሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት በየወሩ የሚካሄደው የኪነ-ጥበብ ምሽት የዚህ ወር መሰናዶ “ያንተም ቤት ሲንኳኳ” በሚል ርዕስ የፊታችን ማክሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል።
በዕለቱም ዲስኩር፣ ወግና ግጥም የሚቀርብ ሲሆን ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ወዳጄነህ መሃረነ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ጋዜጠኛ ወንድሙ ሀይሉ፣ መስረም ላቺሳ (ዶ/ር) እንዲሁም ገጣሚያኑ በቃሉ ሙሉ፣ ማርታ ዳዲ፣ ህሊና ሀዋዝ፣ ዳግም ደጀኔና ቶፊቅ መሃመድ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። የመግቢያ ዋጋ 100 ብር ሲሆን ትኬቶቹ በጃፋር ፣ በዮናስ፣ በዘውዱ፣ በእውቀት በርና በጦቢያ መፃህፍት መደብሮች ይገኛሉ።

 ጊዜ ባርና ሬስቶራንት ዛሬ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ልዩ የሙዚቃ ድግስ ማስናዳቱን ገለፀ። በዚህ የሚዚቃ ድግስ ድምፃዊ ታረቀኝ ሙሉ (በባይተዋር ጎጆ)፣ አዲስ ጉልሜሳ (የማህሙድ)፣ አብነት ደምሴ (የማሪቱ) እና ዋሲሁን ረታ (የሙሉቀን) ድምፃዊያኑ ከማህሌት ባንድ ጋር በመጣመር በቀጥታ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ዳዊት ፍሬው ሀይሉ ሳክስፎን እንደሚጫዎትም የጊዜ ባርና ሬስቶራንት ሃላፊዎች ገልፀዋል።
በዚህ ልዩ ምሽት ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቦሌ ማተሚያ ቤት በሚገኘው ጊዜ ጀርባ ባርና ሬስቶራንት መጥተው በመታደም አስደሳች ጊዜ  እንዲያሳልፉ ግብዣ የቀረበ ሲሆን የሙዚቃ ድግሱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድና ቀድመው የመጡ ብቻ እንደሚስተናገዱ ለማወቅ ተችሏል። በጢስ አባይ የኢኮኖሚ ልማት፣ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅት አዘጋጅነት የተሰናዳው የመጀመሪያው ዙር ሀገር አቀፍ የቢዝነስ ማሻሻያ ገበያ ትስስር መፍጠሪያ ዎርክ ሾፕ ባሳለፍነው ሳምንት በጊዮን ሆቴል ተካሄደ፡፡ አማካሪ ድርጅቱ፤ በዎርክሾቱ በሆቴልና ማኒፋክቸሪንግ ዘርፎች መነሻነት የተጠናው ቅድመ ዎርክ ሾፕ፣የኢትዮጵያ ገበያ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ አስቸኳይ ፖሊሲ ሊወጣለት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በአማካሪ ድርጅቱ የኦኮኖሚ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪና የወርክሾፑ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መንገሻ አበበ ሞሴነህ፤ የአሰራር ምልከታ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም 50 ሆቴሎችን፣50 ኢንዱስትሪዎችንና 50 ተጠቃሚዎችን በአላማ ተኮር የናሙና ዘዴ ያጠኑትን የማርኬቲንግ ጥናት በወርክሾፑ ያቀረቡ ሲሆን በምርት እጥረት፣በምርት ጥራት መጓደል፣ ኢኮኖሚያዊ ባልሆነ የምርት ዋጋ ጭማሪና መሰል ችግሮች ሳቢያ ፈተና ውስጥ የገባውን የኢትዮጵያ ገበያ፣ የህዝብ ብሶት ተከትሎ ከሚመጣ የኢንስፔክሽን እና የሬጉሌሽን የቁጥጥር ሥራ ይልቅ የሀገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት አቅም መሰረት ያደረገ፣ በአመራረትና በግብይት ሂደት የምርት ጥራትን ያመለከተ፣የምርት ስርጭት ፍትሀዊነት፣ከባቢያዊና የፍጆታ ፍላጎትን፣ ፍትሃዊ የመሸጫ ዋጋ ደረጃንና የማርኬቲንግ ማበረታቻ ሥርዓትን የሚያመለክት የማርኬቲንግ ፖሊሲ አለመኖሩ ገበያው ቅጥ እንዲያጣ ማድረጉን በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡
በተቀያያሪ የገበያ ፍሰት ውስጥ በመሆናችን ነው ከምርትና አገልግሎት የምናገኘው እርካታም በየጊዜው እየተቀያየረና በኑሮ ውድነት እየተለበለብን ሲሉ የጥናቱ አካል የሆኑ ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍሎች መናገራቸውም በጥናት ግኝቱ ተካቷል፡፡


  ባለቤትነቱ የቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቱር ኤንድ ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሆነውና 300 ሚ.ብር እንደወጣበት የተነገረለት “ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ባለ  ኮከብ ሆቴል፣ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡
በተለምዶ አትላስ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው ሆቴሉ በ500 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሲሆን 40 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች፣ ለትልልቅና ለመለስተኛ ስብሰባ የሚሆኑ አዳራሾች፣ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ ባርና ሬስቶራንቶች እንዳሉት የተናገሩት የሆቴሉ ሀላፊዎች፤ ለ100 ሰዎች የስራ ዕድል መክፈቱንም ጠቁመዋል፡፡
ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቱር ኤንድ ትራቭል፤ በአስጎብኚነትና በጉዞ ወኪልነት፣ በአስመጪነትና በላኪነት፣በትራንስፖርት ዘርፍ፣ህንፃ በማከራየትና በመሸጥ እንዲሁም በፋብሪካ አገልግሎት ተሰማርቶ የሚገኝ አገር በቀል ድርጅት መሆኑም ታውቋል ኩባንያው በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች 10 ሪዞርቶችን የመገንባት እቀድ እንዳለውም የሆቴሉ ባለቤት ገልፀዋል፡፡ በሰበታ ከተማ ቀበሌ 04 የሚገኘው “ቱሉ መገርሳ ኢንተርናሽናል ሆቴል” ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት እንደሚመረቅ ወጣቱ ባለሃብት አቶ ጅሩ መገርሳ ገለፁ፡፡ በቅርቡ ከሌላ ባለ ሃብት በ150 ሚ.ብር የተገዛውና ለእድሳቱ 100 ሚ.ብር የተመደበለት ሆቴሉ ከ5 ሺህ ካ.ሜ በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን 54 አልጋዎች እስከ 2000 የሚደርስ ሰው የሚይዙ  የስብሰባና የሰርግ አዳራሾች፣ ስቲምና፣ሳውና ባዝ፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖች፣ የመዋኛ ገንዳ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሆቴል ሊያሟላ የሚገገባውን  ያሟላ ነው ተብሏል፡፡ አሁን በሙሉ አቅሙ ስራ ሳይጀምር 182 ሰራተኞችን ቀጥሮ  የሚያሰራው ይሄ ሆቴል፤ እድሳቱ ሲጠናቀቅና በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር፣ የሰራተኞቹን ብዛት ወደ 265 እንደሚያሳድግ ባለሃብቱ፣ የሆቴሉ ማናጀርና የባለሃብቱ አማካሪዎች ምረቃውን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ሆቴሉ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ስጋ ቤትና አዳራሽ ፣የልጆች መጫወቻ፣ ድራፍት ቤት፣የኦሮሞ የባህል ምግብ አዳራሽ እየተሟሉለት ነው ተብሏል፡፡ በቀጣይም አራት ደረጃውን የጠበቁ ሬስቶራንቶች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ በምረቃው ሳምንት ከ15-20 ሺህ ሰው ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የሆቴሉ ሃላፊዎች፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለዘጠኝ ቀናት መራዘሙን በያንዳንዱ ቀናት ከ1500-2000 ሰዎች ብቻ እንደሚያስተናግድ ተገልጿል፡፡


Page 5 of 529