Administrator

Administrator

በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል
      አገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎች ከ500 ሺህ በላይ ደርሰዋል

    የቀድሞው የብሩንዲ የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከሚገኝ የጦር ካምፕ በሬዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፕሬዚደንት ኑኩሩንዚዛ አገዛዝ ማክተሙንና አገሪቱን የመምራቱን ሃላፊነት የሚረከብ ጊዜያዊ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ያስታወቁ ሲሆን አገሪቱ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሌሎች አገራት መንግስታት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ታንዛኒያ መሄዳቸውን ተከትሎ፣ ጄኔራሉ በአገሪቱ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ማስታወቃቸውንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቡጁምቡራ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን እንደገለጹ የዘገበው ቢቢሲ፤ አገዛዙን የሚቃወሙ ወታደሮችም በሁለት የጦር ታንኮች ታግዘው ወደ መዲናዋ ማዕከላዊ ክፍል ማምራታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተቃውሞው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ከትናንት በስቲያም በመንግስት ጦርና በተቃዋሚ ሃይሎች መካከል በቡጁምቡራ ግጭት እንደተከሰተ የጠቆመው ዘገባው፣ ስርዓቱ ይፍረስ የሚለውን የተቃዋሚዎች አቋም በመደገፍ ተቃውሞውን ከተቀላቀሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጋር በተደረገ ድርድር መፈንቅለ መንግስቱ መቆሙን አንድ የአገሪቱ ጦር መሪ ማስታወቃቸውንም ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤ መፈንቅለ መንግስት እንደታወጀባቸው ሲያውቁ ከታንዛኒያ ወደ ብሩንዲ ቢመለሱም፣ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ አውሮፕላን ማረፊያውና የአገሪቱ ድንበሮች እንዲዘጉ በማዘዛቸው፣ ፕሬዚዳንቱ ወደ አገራቸው መግባት እንዳልቻሉና ወደ ዳሬ ሰላም መመለሳቸውን ያስታወቀው የቢቢሲ ዘገባ፣ ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው በኩል ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልዕክት የተቃውሞ እንቅስቃሴው በቁጥጥር ስር ውሏል፣ ህገመንግስታዊ ስርአቱም ከአፍራሽ ሃይሎች ተጠብቋል ብለዋል፡፡
የመንግስት ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግስት፣ የብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያውንና አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ ቢያስታውቅም፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ግን መዲናዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ውስጥ አድርገናል ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
የመፈንቅለ መንግስቱ ቃል አቀባይ ቬኖን ንዳባንዜ በበኩላቸው፤ “መንግስት ተቃውሞውን እንዲገቱ ያሰማራቸው ወታደሮችም ከጎናችን ቆመዋል፣ ድሉ የኛ ነው” ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ከሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር በመሆን በአገሪቱ የሽግግር መንግስት መቋቋም የሚችልበትን ሁኔታ እያመቻቹ እንደሚገኙም ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ያለ አግባብ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን የተቃወሙ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ከማሰማት ባለፈ፣ አገዛዙን ከስልጣን ለማውረድ መነሳታቸውን የገለጹት ጄኔራሉ፤ ጊዜያዊ ኮሚቴው ብሄራዊ አንድነትን መልሶ በመፍጠርና ምርጫው በፍትሃዊና ሰላማዊ ሁኔታ መካሄድ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ከ20 በላይ ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አገር ጥለው የተሰደዱ ብሩንዲያውያን ዜጎች ቁጥርም ከ500 ሺህ በላይ መድረሱን አመልክቷል፡፡

ዝንጀሮዎችም እንኳን ከዛፍ ላይ ይወድቃሉ፡፡
የጃፓናውያን አባባል
ሰባት ጊዜ ወድቀህ በስምንተኛው ተነስ፡፡
የጃፓናውያን አባባል
የበሰበሰ እንጨት አይቀረፅም፡፡
የቻይናውያን አባባል
አንዲት ውሸት ሺ እውነቶችን ታጠፋለች፡፡
የጋናውያን አባባል
አመድ መልሶ የሚበተነው ወደበተነው ሰው ፊት ነው፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
ለመብላት የቸኮለ አፉን ይቃጠላል፡፡
የሉሃያ አባባል
ሙቅ ውሃ የሆነ ጊዜ ላይ ቀዝቃዛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የአይቮሪኮስት አባባል
የልብን ‹ወሬ› ከፈለግህ ፊትን ጠይቀው፡፡
የጊኒያን አባባል
በአፉ አጥንት የያዘ ውሻ መጮህ አይችልም፡፡
የዛምብያውያን አባባል
ሆድ ከፊት ለመሰለፍ አይፈራም፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
የመቃብርን ስቃይ የሚያውቀው የሞተ ሰው ብቻ ነው፡፡
የስዋሂሊ አባባል
አይጥ የቱንም ያህል ብትሰክር ድመት አልጋ ላይ መተኛት የለባትም፡፡
የካሜሩናውያን አባባል
ጨለማውን ከመራገም ሻማ ማብራት ይሻላል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፡፡
የዙሉ አባባል
ትንሽም ኮከብ ብትሆን ጨለማን ትሰብራለች፡፡
የፊንላንዳውያን አባባል
ዕድል ስትጎበኝህ ሁሉም ሰው የምትኖርበትን ያውቀዋል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ጥሩ ምክር እንደሚመር መድኀኒት ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል



 የኢራቅ መከላከያ ሚኒስትር አይሲስ በመባል የሚጠራው ጽንፈኛ አራጅ የሽብር ቡድን ምክትል መሪ የሆነው አቡአላ አልአፍሪ በህብረቱ ሀይሎች በተካሄደ የአየር ጥቃት ባለፈው ማክሰኞ መገደሉ ይፋ ተደርጓል፡፡  
በዩቲውብ የተለቀቀው አጭር የቪዲዮ ፊልም እንደሚያሳየው፤ አቡ አላ አልአፍሪ የተገደለው በኢራቅ የታል አፋር ከተማ በሚገኝ አንድ መስጊድ ውስጥ ነው፡፡ አብዱራህማን ሙስጠፋ አልቃዱሊ በሚል ተለዋጭ ስም የሚታወቀውና በ1957 ሞሱል ከተማ ውስጥ የተወለደው አቡ አላ አልአፍሪ የኢራቅ የአልቃኢዳ ቡድን ምክትል መሪና የሞሱል ከተማ ክንፍ ዋና አዛዥ በመሆን አገልግሏል፡፡
የፊዚክስ መምህር የነበረው አቡ አላ አልአፍሪ፤ የኢራቅ የአልቃኢዳ ምክትል መሪ በነበረበት ወቅት በኦሳማ ቢንላደን  ዘንድ ከፍ ያለ ሞገስ ማግኘት የቻለና ለአይሲስ ከፍተኛ መሪነት በዋናነነት የታጨ ሰው ነበር፡፡ የቱርክሜን ብሔረሰብ አባላት ከሆኑ የአይሲስ ከፍተኛ መሪዎች ግንባር ቀደም የሆነው አቡአላ አልአፍሪ የአይሲስ ዋነኛ መሪ መሆን ያልቻለውና የመሪነቱ ስልጣን ለአቡበከር አልባግዳዲ የተሰጠው አቡበከር አልባግዳዲ የዘር ሀረጉ ከነብዩ ሞሀመድ የዘር ሀረግ ስለሚመዘዝ ብቻ ነው፡፡
አቡአላ አልአፍሪ ከመገደሉ በፊት በተፈፀመበት የአየር ጥቃት ክፉኛ ቆስሎ አልጋ ላይ የዋለውን የአይሲስ መሪ አቡበከር አልባግዳዲን ተክቶ ቡድኑን ሲመራ ነበር ተብሏል፡፡
አሜሪካ በቁጥጥር ስር ለማዋል በጥብቅ ከምትፈልጋቸው ዋነኛ አሸባሪዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ “ጠቁሞ ላስያዘው” የ7 ሚ. ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ ስትል የነበረ ሲሆን የአቡአላ አልአፍሪን መገደልን ገና አምና የተቀበለችው አትመስልም፡፡ የዚህን ነብሰ በላ አሸባሪ መሞት ባይኔ በብረቱ አይቼ ካላረጋገጥኩ በቀር የሰውየው መገደል ዜና ከሆዴ አይገባም ብላለች፡፡

Saturday, 16 May 2015 11:06

የፀሐፍት ጥግ

ህክምና ህጋዊ ሚስቴ ናት፤ ስነፅሁፍ ውሽማዬ ናት፡፡ አንዳቸው ሲሰለቹኝ ከአንዳቸው ጋር ሌሊቱን አሳልፋለሁ፡፡
አንቶን ቼኮቭ
የሥነፅሁፍ ማሽቆልቆል የህዝብን ማሽቆልቆል ያመለክታል፡፡
ቮን ገተ
ግጥም የሥነ ፅሑፍ ዘውድ ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
ባህልን ለማጥፋት መፃሕፍትን ማቃጠል የለብህም፡፡ ሰዎች መፃሕፍት እንዳያነቡ ማድረግ ብቻ በቂ ነው፡፡
ሬይ ብራድበሪ
ህይወት ያለ ስነፅሁፍ ገሃነም ነው፡፡
ቻርለስ ቡከውስኪ
የምታነበው ሳይንስ ከሆነ አዳዲሶቹን ሥራዎች አንብብ፡፡ ሥነፅሑፍ ከሆነ ግን የጥንቶቹን አንብብ፡፡
ኢድዋርድ ጂ. ቡልዌር - ሊቶን
ሴቶች፤ ፍቅር ረዥም ልብወለድ እንዲሆን ይሻሉ፤ ወንዶች ደግሞ አጭር ልብወለድ፡፡
ዳፍኔ ዲ ማውሪየር
ቤተ መፃህፍት ውስጥ የሚጠፋ አንድ ሰዓት፣ በቤተ ሙከራ ውስጥ ከሚጠፋ አንድ ወር ጋ እኩል ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
መፃሕፍት በሌሉበት መኖር አልችልም፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን
መፃሕፍት በሁለት መደቦች ይከፈላሉ፡፡ የወቅቱ መፃህፍትና የምንጊዜም መጻህፍት በሚል፡፡
ጆን ሩስኪን
ንባብ ሙሉ ሰው፤ ጥሞና ጥልቅ ሰው፣ ንግግር ደግሞ ግልፅ ሰው ያደርጋሉ፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
ማንበብ በራስ ጭንቅላት ከማሰብ ይልቅ በሰው ጭንቅላት ከማሰብ እኩል ነው፡፡
አርተር ስኮፊነር
በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ብልሆች መፅናኛቸውን የሚያገኙት ከመፃሕፍት ነው፡፡
ቪክቶር ሁጎ
ሳላነብ ከምቀመጥ ይልቅ የጊዜ ሰሌዳ ወይም ካታሎግ ባነብ እመርጣለሁ፡፡
ሶመርሴት ሟም
መፃህፍትን ማንበብ ያለብህ እንደ መድኀኒት በትዕዛዝ እንጂ በማስታወቂያ አይደለም፡፡
ጆን ሩስኪን

በሀገሪቱ በጤናው መስክ የሚታየውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት፣ በዘርፉ ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጎልበትና ለጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች አመቺ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀው “ኢትዮ ሄልዝ ዳይሬክተሪ” የተሰኘ የጤና አገልግሎት ማውጫ ከትናንት በስቲያ ተመረቀ፡፡
በዘርፉ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የጤና አገልግሎት ማውጫ፣ በይዘቱ ምሉዕ እና ከሁለት አመት በላይ በፈጀ የመረጃ ስብሰባ የተዘጋጀ ሲሆን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የጤና አገልግሎት ሰጪዎችን፣ የሆስፒታሎችን፣ የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አስመጪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አድራሻ የያዘ ነው፡፡
በደብሊው ኤ ኤች አሳታሚ የተዘጋጀው የጤና አገልግሎት ማውጫው፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሲባል በመጽሃፍ መልክ ከመቅረቡ በተጨማሪ በድረ ገጽ እና በሞባይል አፕሊኬሽን አማካይነት ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን አዘጋጁ በተለይ ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡  
ማውጫው በአዲስ አበባ እና በመላ የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ የጤና ተቋማት በነጻ የሚሰራጭ ሲሆን  ለጤና ተቋማት የመረጃ ምንጭ በመሆን የርስ በርስ ግንኙነትን ከማጎልበት ባለፈ፣ ለጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎችም የማንኛውም የጤና ነክ መረጃ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡
አዘገጃጀቱ ለተጠቃሚዎች ምቹ በመሆኑና መረጃዎቹ በየጤና ዘርፉ ተከፋፍለው የቀረቡ መሆናቸው፣ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ እንደፍላጎቱና እንደችግሩ የሚበጀውን መረጃ በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችለው አዘጋጁ ገልጸዋል።
በዝግጅቱ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የመድሀኒት የምግብ እና የጤና ክብካቤ ባለስልጣንን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ መያዶች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላትና በዘርፉ ለአመታት የሰሩ አንጋፋ የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች፣ ተቋማትና የመንግስት አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት እትሞችም ተደራሽነቱን በስፋት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ተብሏል።
በዘርፉ የሚታየውን የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የተነገረለት የጤና አገልግሎት ማውጫው፣ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ልዩ ጽ/ቤት ሃላፊ ዳይሬክተር ጀነራል፣ የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ሃሙስ በኢትዮጵያ ሆቴል በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በይፋ ተመርቋል፡፡


Saturday, 16 May 2015 10:53

የሰዓሊያን ጥግ

(ስለ ፎቶግራፍ)

ብርሃን ባለበት ሁሉ ፎቶግራፍ ማንሳት ይቻላል፡፡
አና ጊዴስ
ጥሩ ፎቶግራፍ ማለት የቱ ጋ እንደምትቆም ማወቅ ነው፡፡
አንሴል አዳምስ
ፎቶግራፍ ማንሳት ከህይወት ጋር የሚደረግ የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡
ቡርክ ዩዝል
አካባቢውን እስክትለቅ ድረስ ካሜራህን አትሸክፍ፡፡
ጆ ማክናሊ
ፎቶግራፍ ማንሳት አንዴ ደም ስርህ ውስጥ ከገባ እንደ በሽታ ነው፡፡
አኖን
እጄ ላይ ካሜራ ሲኖር ፍርሃት አላውቅም፡፡
አልፍሬድ አይዞንስታዴት
የሰውን ፊት በትክክል የሚያየው ማነው? ፎቶግራፍ አንሺው ነው? መስተዋቱ ነው? ወይስ ሰዓሊው?
ፓብሎ ፒካሶ
በአሜሪካ ፎቶግራፍ አንሺ የተከሰተውን የሚቀርፅ ብቻ አይደለም፤ የሚፈጥርም ጭምር እንጂ፡፡
ሱሳን ሶንታግ
ቃላትን አላምንም፤ የማምነው ምስሎችን ነው፡፡
ጊሌስ ፔሬስ
ትኩረቴን የሚስበው ፎቶግራፍ ራሱ አይደለም፡፡ እኔ የምፈልገው የተጨባጩን ዓለም አንድ ደቂቃ ማስቀረት ብቻ ነው፡፡
ሔነሪ ካርቲየር ብሪሶን
ተመልከቱ! ምሁር አይደለሁም - ምስሎችን ብቻ ነው የማነሳው፡፡
ሔልሙት ኒውተን
ድንቅ ፎቶግራፍ የስሜት ጥልቀት እንጂ የመስክ ጥልቀት አይደለም፡፡
ፒተር አዳምስ
የእኔ ተወዳጅ ፎቶግራፎች የትኞቹ ናቸው? ነገ የማነሳቸው!!
አይሞገን ከኒንግሃም
ጥሩ ፎቶግራፍ አንዲትን ቅፅበት ከማምለጥ ይገታታል፡፡
ኢዩዶራ ዌልቲ

ላለፉት አምስት አመታት በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ልኡክ ሆነው ያገለገሉትና ከአገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች አንዱ የሆኑት አምባሳደር ሞሃመድ ኢድሪስ ጃዊ፤ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽመውን ጭቆናና የመብቶች ጥሰት በመቃወም በኢትዮጵያ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፍትህና ነጻነትን ለመጎናጸፍ ለዘመናት የታገለው የኤርትራ ህዝብ፤ በኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ስር እየማቀቀ ይገኛል ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም የኤርትራን መንግስት የጭቆና አገዛዝ በመቃወም በኢትዮጵያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ውሳኔ ላይ እንዳደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
በኤርትራ የነጻነት ትግል ዘመናት በትግል ያሳለፉት አምባሳደር ሞሃመድ፤ኤርትራ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች  በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎችና በአህጉራዊ የዲፕሎማቲክ ስራዎች ላይ ለአመታት ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡
የመብት ተሟጋች ቡድኖችና የተለያዩ ተቋማት፣ የኤርትራ መንግስት በመብቶች ጥሰትና በአስገዳጅ የወታደራዊ አገልግሎት ዜጎቹን እያሰቃየ ነው ሲሉ አገዛዙን ቢተቹም፣ የኤርትራ መንግስት ግን የሚሰነዘሩበትን መሰል የመብቶች ጥሰት ውንጀላዎች በተደጋጋሚ እንደሚያጣጥል አስታውሷል፡፡
የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት በአምባሳደሩ የጥገኝነት ጥያቄ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ሮይተርስ ገልጧል፡፡

የብሪጅስቶን ጎማ አምራች ኩባንያ ምርቱን ተረክበው ለሚያከፋፍሉና ለሚቸረችሩ ደንበኞቹ በመሰረታዊ ጎማ አመራረትና አጠቃቀም እንዲሁም በጎማው መለያ ባህርያት ላይ የግማሽ ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የብሪጅስቶን ጎማ ወኪል የሆነው ካቤ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን በመድረኩ ላይ የብሪጅስቶን ጎማ አምራች ኩባንያ የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ተጠሪዎችና ስራ አስኪያጆች እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት የኩባንያው ወኪሎች ተገኝተዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ በተካሄደው በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የኩባንያው አዲስ ምርት የሆነው “ኢኮፒያ” የተሰኘ መለያ የተሰጠው የጎማ ምርትም ተዋውቋል፡፡
መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገው ብሪጅስቶን ጎማ ነጋዴዎች ስለጎማቸው መሰረታዊ እውቀት እንዲያገኙ መሆኑን የጠቆሙት በካቤ ኃ/የተ/የግ/ኩባንያ የብሪጅስቶን ጎማ የቴክኒክ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ አህመድ፤ ኩባንያው እንዲህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀቱ ደንበኞች ስለምርቶቹ ይበልጥ እውቀት እንዲያገኙና ምርጫቸው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ብሪጅስቶን ጎማ ላለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ ገበያ የቆየ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜም የደንበኞቹ ቁጥር እየተበራከተና የገበያ ድርሻውን እያሰፋ እንደሚገኝ፣ በአለማቀፍ ደረጃም ተመራጭ ጎማ መሆኑን አቶ ካሊድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርዝመቱ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ህንፃ በአዲስ አበባ ለማስገንባት ከቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈራረሙን ባንኩ አስታወቀ፡፡
ሕንፃው በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልና በኢትዮጵያ ሆቴል መካከል ባለው ስፍራ የሚሰራ ሲሆን 198 ሜትር ርዝመትና 43 ወለሎች እንዲሁም 1,500 መኪኖች ማቆም የሚችል 4 ቤዝመንት ወለል እንደሚኖሩት የባንኩ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገልፀዋል፡፡
ከዋናው ሕንፃ ጎን ሁለት ባለ 5 ፎቅ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፤ አንዱ የኮሜርሻል ሴንተር፣ ሁለተኛው የስብሰባ ማዕከል ነው ብለዋል፡፡ ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ 2000 ሰዎች የመያዝ አቅም ሲኖረው፣ ሌሎቹ አዳራሾች 300 ሰዎች 5 አዳራሾች ደግሞ 200 ሰዎች እንደሚይዙና የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ መሳሪያዎች እንደሚገጠሙላቸው ጠቁመው ግንባታው ከሜይ 2015 ጀምሮ በ4 ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

“ጮሃ የማታውቅ ወፍ እለቁ እለቁ ትላለች” - ሀገርኛ ተረት
አንዳንድ ታሪክ ሲውል ሲያድር እንደ ተረት ይወራል፡፡ ኢሮብ ትግራይ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወረዳ ናት፡፡ ተራራማ መልክዐ - ምድር ያላት ስትሆን ኢሮብ የሚባል ብሔረሰብ ይኖርባታል፡፡ የነደጃች ሱባጋዲስ (ማሸነፍን አበልፃጊ እንደማለት ነው) አገር ናት፡፡
በዚች አገር የሚታወቀው አንድ የነዋሪው ልማዳዊና ባህላዊ ጠባይ፣ መቻል፣ መታገሥና ሁሉን እኩል ማስተናገድ ነው፡፡ ህንፃም ልጅ ቢሆን፡፡ በሠርግ ወቅት የሚታደል ማንኛውም ነገር እንኳ ለልጅም እኩል ይደርሳል፡፡ ከተማይቱ ለጦርነት አመቺ ከሆኑት እንደ አሲምባ ተራራ እና አይጋ (ሻቢያ በጣም የተመታበት ቦታ) አሊቴና (ዳውሃን) ዓይነት ቦታዎች አካባቢ በመሆንዋ የደርግ ጦር፣ የኢዲዩ ጦር፣ የኢህአፓ ጦር፣ የህወሓት ጦር፣ አንዳንዴም የህዝባዊ ግንባር ጦር ወዘተ ኃይሎች እንደመተላለፊያ በየጊዜው እየመጡ ይሰፍሩባት ነበር ይባላል፡፡
ህዝቡ እነዚህን ኃይሎች በአግባቡ፣ ሳያጋጭና ሳያጣላ፤ አንዱን በፊት ለፊት አንዱን በጀርባ/ በጓሮ አስተናግዶ ኮሽ ሳይልበት ይሸኛቸዋል፡፡ ለኢሮብ ውይይት ዋና ባህል ነው፡፡ ህዝቡ የአገር ሽማግሌ ይኖረዋል፡፡ የእድር ዳኛ፣ የማህበር መሪ፣ የጎበዝ አለቃ ወዘተ እንደሚባለው ዓይነት የበሰሉ፣ ብልህነት የተዋጣላቸውና ህዝቡ እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው አባት (አቦይ) ይኖሩታል፡፡
በአንድ ወቅት በዚሁ በኢሮብ አካባቢ ከፖለቲካ ንቅናቄ ድርጅቶች አንዱ ይመጣል፡፡ ህዝቡን ሰብስቦ እንደተለመደው ሰበካ ያደርጋል፡፡ ህዝብን ወክለው አቦይ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ጥያቄም ይጠይቃሉ፡፡
የንቅናቄ ቡድኑ አባላት በአቦይ ንቃትና አንደበተ ርቱዕነት ይደመማሉ፡፡ አቦይን በንቅናቄው ፖለቲካ ቢያጠምቋቸው የኢሮብ ህዝብ ላይ ትልቅ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገመቱ፡፡
ስለዚህም፤ አቦይን ለአሥራ አምስት ቀናት ወስደው የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ቢያስተዋውቋቸው ትልቅ ሥራ እንደሚሰሩላቸው ወሰኑ፡፡ አቦይን ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ አቦይ ውይይቱን ተካፈሉ፡፡ ግምገማውን አዳመጡ፡፡ ትምህርቱን ቀመሱ፡፡
“አቦይ እየገባዎት ነው?” ይላል አንዱ ካድሬ፡፡
“አሳምሬ” ይላሉ አቦይ፡፡
ሌላው ሰበካውንና ገለፃውን ይጨርስና፣
“እህስ አቦይ! እየተከታተሉ ነው ትምህርቱን?”
“እንዴታ!” ይላሉ አቦይ፡፡
ሌላው ይቀጥላል፡፡
“አቦይ ዓላማችን ገባዎት?”
“አዎን”
“ፕሮግራማችን በዝርዝር ፍንትው ብሎ ታየዎት?”
“እጅግ! እጅግ!” ይላሉ፡፡
የአሥራ አምስቱ ቀን የአቦይ ንቃት ፕሮግራም አለቀ፡፡ ከዚያ አለቃው ካድሬ፤
“ይበሉ እንግዲህ አቦይ፣ ወደ ኢሮብ ጎሣ ይሂዱና እስካሁን የተማሩትን ያስተምሩ” አሉ፡፡
አቦይ አመስግነው ወደ ኢሮብ ተመለሱ፡፡
የኢሮብ ህዝብ ተሰብስቦ ጠበቃቸውና፤
“እሺ አቦይ ምን ተምረው መጡ?” አላቸው
አቦይም እንዲህ መለሱ፣
“ይገርማችኋል ወገኖቼ፣ የተማርኩት ስለዲሞክራሲ ነው፡፡ እናም በጣም ያስደሰተኝ ነገር በዲሞክራሲ ዝም ማለትም ይቻላል!” ብለው አጠቃለሉ፡፡
*       *      *
ብልህ ህዝብ ብልህ ዘመን ይሰራል፤ ይላሉ አበው፡፡ የተነሳበትን ቦታና ሁኔታ የማያውቅ ህዝብ የት እንድደደረሰ ለመገንዘብም ልብና ልቡና ያንሰዋል፡፡ የህዝብን ዐይን ይገልጣሉ፣ ያንቀሳቅሱታል የሚባሉ ማህበራት፣ ድርጅቶችና ፓርቲዎች፣ የነቁ፣ የተቡ፣ ሥነ - ምግባር የተላበሱና ከሁሉም በላይ አርቀው ማስተዋል የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል። ታግለው የሚያታግሉ፣ ነቅተው የሚያነቁና የተደራጀ ህዝብ የሚከተላቸው መሆንም አለባቸው፡፡ ሥርዓትን መውለድ፣ ሥርዓታዊ አስተዳደርን ማበልፀግ አለባቸው፡፡ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ያሉትን እዚህ ላይ መጥቀስ አግባብነት አለው፡-
“አዕምሮ የሌለው ህዝብ ሥርዓት የለውም፡፡ ሥርዓት የሌለው ህዝብም የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥርዓት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች፡፡”
ሥርዓታዊ አስተዳደር ሲባል፣ ከሁሉም በላይ ገዢም ተገዢም የሚዳኙበትና የሚያከብሩት ደንብ ማለት ነው፡፡
ህዝብን የማያዳምጥ ፓርቲም ሆነ መንግስት ዕድሜ አይኖረውም፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል ማለትም ብዙ መንገድ አያስኬድም፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይሉናል፡- “እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደሀና ደካማ ሀገሮች ትልቁ አደጋ እንዲህ ያለ መንግስት ዘፈኔን ካልዘፈናችሁ፣ እስክስታዬን ካልወረዳችሁ እያለ ክብራቸውን ከመንካትም አልፎ ማለቅያ ወደ ሌለው ጦርነትና ውጥረት ውስጥ እንዳያስገባቸው ነው፡፡ በአሜሪካ ዳፋ ኢትዮጵያ ከዐረቦችና ሙስሊሞች ጋር ተጣላች ማለት፤ ከውጪም ከውስጥም በእሳት ስትለበለብ ኖረች ማለት ነውን፡፡ (ምን ዓለምን? የት ደረስን? ወዴትስ እያመራን ይሆን?)
ትውልዶች ያለሙት ዒላማ በየለውጡ ኩርባ (turning point) መመርመር አለበት፡፡ ምን ምን የሰመረ ነገር ታየ? ምን አጋጣሚ ተሳተ? ምን ምን ሥተት ተሰራ? ምን ላይ ፈር ቀደድን? ምን ላይ ባቡሩ ሐዲዱን ሳተ? ማለት ይገባል፡፡
የሄድንበት መንገድ አንዱ ችግር ቃልና አፈፃፀም አለመጣጣማቸው ነው፡፡ “በተለይ መብትን በተመለከተ፡፡ በሕገ - መንግሥት የተረጋገጡ መብቶች በተግባር ሲሻሩ ይታያሉ፡፡” ይላሉ ፀሐፍት በተደጋጋሚ፤ ስለ አፈፃፀም ችግር ሲያወጉ፡፡
ማንም ይፈፅመው ማን፤ ከየትኛውም ሀረግ ጋር ይጠላለፍ፤ ሙስናን መዋጋት ሌላው ግዴታችን ነው፡፡ እነ እገሌ ካሉበት ሙስናውን ማጋለጥ አደገኛ ነው እያሉ ገሸሽ ማለት ይሄው እዚህ አድርሶናል፡፡
“ኢትዮጵያ አንዴ በመደብ ስትመራ፣ አንዴ በብሔረሰብ ስትመራ ቆይታ፣ ወደፊት እጣ ፈንታዋ ከነዚህ ሁሉ የከፋው የሃይማኖት ጦርነት እንዳይሆን የብዙ ተመልካቾች ሥጋት ነው!” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ የሃይማኖትን አያያዝ ማወቅ ዋና ነገር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ያሉትንም ኃያላን ነቅቶ ማየት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጠንቀቅ እንበል፡፡
የሀገራችን ሌላው አስገራሚ ነገር ህዝብ ያደነቀውና ሆይ ሆይ ያለለት ታጋይ (ልክም ይሁን አይሁን) ሲገል ቆይቶ አንድ እክል ከገጠመው እንዳልነበር መረሳቱ ነው፡፡ ያላንተ ማናለን ሲባል የነበረ ታጋይ፣ መሪ ወይም ንቁ ሰው፤ ሲታሰር ወይም ካገር ሲወጣ ከአዕምሮአችን ጨርሶ ለመውጣት ሁለት ሳምንት አይፈጅበትም፤ ፈፅሞ ይረሳል፡፡ ያውም ምን አቅብጦት እዛ ነገር ውስጥ ገባ? ተብሎ ካልተተቸ ነው! ይሄ እንግዲህ ከዓመታት በፊት የተሰውለትን ሳይጨምር ነው!
ሌላው በእስከዛሬው መንገዳችን ያየነው ጉዳይ፣ የጠቅላይ ገዢነት አመለካከት ነው፡፡ በዝግ ባህላችን ላይ ይሄ ሲታከልበት “በደምባራ በቅሎ፣ ቃጭል ጨምሮ ነው!” ከዚህ ይሰውረን!
ፕሮፌሰር ባህሩ በዚያው ፅሑፋቸው፤ “ሁሉን አውቃለሁ ከማለት የሌሎችንም ሀሳብ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን፣ ሁሉንም ጠቅልዬ ልያዝ ከማለት ለመጋራት መዘጋጀት፣ ከሁሉም በላይ በስሙ የምንገዳደልበት ሰፊ ህዝብ የሚበጀውን አሳምሮ እንደሚያውቅ ተገንዝበን ከሱ መሬት የቆነጠጠ እውቀት ለመማር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡” … በኢኮኖሚውም ረገድ፡፡ “የተማረ የሰው ኃይላችንን ተንከባክቦ መያዝ፣ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሰፊ ዕድል መስጠት የዕድገታችን መሰረት ነው… ከእርሻ ኢኮኖሚ ያገኘነው ቋሚ ድህነትንና ተደጋጋሚ ረሀብን ብቻ ነው፡፡ የትም ያላደረሰንን በጥቃቅን የገበሬ ማሳዎች ላይ የተመሰረተውን የእርሻ ኢኮኖሚ ትተን ወደ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚ በፍጥነት የምንሸጋገርበትን ስልት ስናወጣ ነው የምናድገው” ይሉናል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችም ሆኑ የዲሞክራሲ መብቶች በልካችን እንዲሰፉ የታሰበ እለት “መላው ቀለጠ!” “ገደደ!” ማለት ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ የመናገርና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የምንታገልለት፣ ሳናሰልስ የምንጮህለት፣ መቼም ወደ ኋላ የማንልበት ጉዳይ ቢሆንም፣ የማይጥመን ነገር ካለ፣ የአቦይን በሳል አስተሳሰብም እንጋራለን “በዲሞክራሲ ዝም ማለትም ይቻላል!” እንላለን፡፡