Administrator

Administrator

Monday, 11 May 2015 09:02

የፍቅር ጥግ

ከሁሉም ጣፋጩ ድምፅ ያፈቀርናት ሴት ድምፅ ነው፡፡
ዣን ዲላ ብሩዬር
የመጀመሪያ ዕይታዬ የሚያርፈው በልብሽ ላይ ነው፡፡
ጆሃን ኤፍ ሲ ሺለር
አበባ ያለ ፀሐይ ብርሃን እንደማያብበው ሁሉ፣ ሰውም ያለ ፍቅር መኖር አይችልም፡፡
ማክስ ሙለር
ለዓለም አንድ ሰው ነሽ፤ ለእኔ ግን ዓለሜ ነሽ፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
አፍቅሪኝ፤ ያኔ ዓለም በሙሉ የእኔ ትሆናለች።
ዴቪድ ሪድ
አንድ ቃል ከህይወት ሸክምና ስቃይ ነፃ ያወጣናል፡፡ ያ ቃል “ፍቅር” ነው፡፡
ሶቅራጦስ
ህይወትን ውደዳት፤ ህይወት መልሳ ትወድሃለች፡፡ ሰዎችን ውደዳ    ቸው፤ እነሱም መልሰው

ይወዱሃል፡፡
አርተር ሩቢንስቴይን
መሳሳም ጨዋማ ውሃ እንደ መጠጣት ነው። በጠጣህ ቁጥር ጥምህ ይጨምራል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ስሞሽ (Kissing) የፍቅር ፊርማ አይደለምን?
ሔነሪ ፊንክ
ደስተኛ ትዳር ያፈቀርነውን ስናገባ ይጀምራል፤ ያገባነውን ስናፈቅር ደግሞ ያብባል፡፡
ቶም ሙሌን
የደስታን ሙሉ ጣዕም ለማግኘት፣  የምታካፍሉት ሰው ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
ማርክ ትዌይን
በጣቶቻችሁ መካከል ያሉት ክፍት ቦታዎች የተፈጠሩት በሌሎች ጣቶች እንዲሞሉ ነው፡፡
ማንነቱ ያልታወቀ ፀሐፊ
በህይወት ውስጥ አንድ ደስታ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይኸውም ማፍቀርና መፈቀር ነው፡፡
ጆርጅ ሳንድስ
መውደድን የምንማረው በመውደድ ብቻ ነው፡፡
አይሪስ ሙርዶክ
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪውንም ተቀባዩንም፡፡
ካርል ኤ. ሜኒንገር
ጥላቻ በጥላቻ አይሻርም፤ በፍቅር ብቻ እንጂ፡፡ ይሄ ዘላለማዊ ህግ ነው፡፡
ቡድሃ
በፍቅር ለሚወድቁ ሰዎች ስበት ተጠያቂ አይደለም፡፡
አልበርት አንስታይን
ፍቅር ህይወት ነው፡፡ ፍቅር ካመለጠህ፣ ህይወትም ያመልጥሃል፡፡
ሊዮ ቡስካግልያ

Monday, 11 May 2015 08:55

መርዶ ባደባባይ

በአገራችን ባህል እኛ የምናውቀው፡-
    በሌሊት ነበረ ሰው ለቅሶ ‘ሚያረዳው,
    ተረጂው ሳይሰማ፣ በምስጢር ተይዞ ጎረቤት መክሮበት
    ለዚሁ እሚመጥን አንጋፋ ተመርጦ ዕድር ያመነበት፤
    በሥርዓት ነበር፣ ሰው መርዶ እሚረዳው
    ሃዘንተኛም ሰምቶ በወጉ ነበረ እርሙን የሚያወጣው፡፡
        ዛሬ ወግ ተሸሮ፣ ባህል ተሸርሽሮ
        ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ገኖ በዕድገት ተስፈንጥሮ
        እርም ባደባባይ ኦን-ላይን አወጣን
        የሟቾችን ሲቃ በፌስ ቡክ እያየን፡፡
        በዕድገት ኋላ ቀርተን፣ በመከራ ቀድመን
        በዘመን ተሳቀን፣ ዓለም ተሳልቆብን
        እንደ ሰው ተፈጥረን፣ አጉል ሞት እየሞትን
        በጉደኛው ዘመን እንደጉድ እየኖርን
        ይሄው ለዚህ በቃን! ይኸው ለዚህ ደረስን!!
    የጉድ ቀን አይመሽም፣ ፍርጃ እቤት አይውልም
    መከራ ሲመክር አስተዋይ አዕምሮ ቀና ልብ የለውም፣
    አገር መርዶ አረዳች፣ አገር እርም አወጣች በጠራራ ፀሐይ
    ሰቆቃ ዘነበ … በረዶ ወረደ … በአገሬ ሰማይ ላይ
    ህዝቡ ደረት ጣለ፣ ሳር ቅጠሉ አዘነ በእንባ ተጥለቅልቆ
    ሀዘን ቅጡን አጣ፤ ከል ለበሰ አገር ባንዲራ አዘቅዝቆ
    ድህነት በፊናው፣ ያሰበው ሞላለት ኮራ ግዳይ ጥሎ
    በወገን ደም ግብር የሱ ቆሌ ረካ፣ የእኛ ፅዋ ጎድሎ፡፡
***
    “ድህነት ወንጀል አይደለም” ይላል አዳሜ እንደዋዛ
    ከወንጀል-ወንጀልም እንጂ ጣጣ መዘዙ የበዛ፡፡
    ማጣት የሃጢያት ሥር ነው፣ የገዛ እርምን ያበላል
    የሰው ፊት የቋያ እሳት ነው፣ ከሩቁ ይለበልባል
    “ችግር በቅቤ ያስበላል”፣ ይሉት የአበሻ ጅል ተረት
    የስላቅ የፌዝ - መርፌ ነው፣ የነፍስ ግርዛት ሸለፈት
    አጅሬ ችግር ዱር አውሬ እንኳንስ ቅቤ ሊያበላ
    አየነው ለጉድ ተፈጥረን፣ በካራ አንገት ሲያስቀላ፡፡
    የድህነትን ጅብ ሸሽቶ - ቢወጣ ካገር ተሰዶ
    ጥርሶቹን ስሎ ጠበቀው፣ አይምሬው የባህር ዘንዶ፡፡
    ምስካየ ሕዙናን ነበርን፣ ለተሰደዱት አለኝታ
    ለሰቅጣጭ “የርድ” ሞት በቃን፣ አቤቱ የማታ ማታ!
    ፅናቱን ይስጥሽ አገሬ፣ ይከብዳል መርዶው የልጅ ሞት
        በተለይ እጅሽ አጥሮበት
        ሪቅሽ እየራቀበት
        ሌማትሽ ሲራቆትበት…
        የኑሮ ሚዛን ተዛብቶ
        በቀየሽ ልጅነት ጎልቶ …
    … ቢጨንቀው ስደትን መርጦ …
    ሲኳትን በረሃ አቋርጦ …
    በባዕድ ቀላድ ቀላውጦ …
    ተስፋውን ሊወልድ አምጦ!
    ካቀደው ሳይደርስ ምኞቱ
    በሰደፍ ሲቀላ አንገቱ
        ይከብዳል ለእናት ስሱ አንጀት
        ይዳብስሽ አምላክ በምህረት!
    ፅናቱን ይስጥሽ ኢትዮጵያ! ያድንሽ ከዳግም ውርደት
    በብልፅግና ፅደቂ! ገሃነም ይውረድ ድህነት!
    ገናናነትሽ ይመለስ - አይታይ ክብርሽ ኮስሶ
        ጥቃት አንገት ያስደፋል!
        ማጣት አንገት ያስቀላል!
        ይመራል ልክ እንደ ኮሶ!
    የሐዘን ማቅሽ ይቀደድ! ያቁምሽ በፈውሱ ማማ
    ሙሾ ወረዳው አብቅቶ - ህዳሴሽ በዓለም ይስማ!!
ደመቀ ወልዴ
22/08/2007 (በሊቢያ በሥደት ሳሉ
አይኤስአይኤስ በተባለ ቡድን በግፍ ለታረዱ ወገኖቻችን)

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ብዙ እጆች ሥራን ያቀላሉ፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ሁለት ጉንዳኖች አንድ አንበጣን ለመጐተት አያንሱም
የታንዛንያውያን አባባል
አንድ አምባር ለብቻው አይንሿሿም፡፡
የኮንጐአውያን አባባል
አንድ እንጨት ይጨሳል እንጂ አይነድም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
በፍጥነት ለመጓዝ ከፈለግህ ብቻህን ሂድ፤ ሩቅ ለመጓዝ ከፈለግህ በህብረት ሂድ፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ቤተሰብ እንደዛፍ ነው፤ ይጐብጣል እንጂ አይሰበርም
የዩቴ አባባል
የቅርብ ወዳጅ የቅርብ ጠላት ይሆናል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ጓደኛ ማጣት ከመደህየት እኩል ነው፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ለከብቶችም እንኳን ወጣትነት ውበት ነው።
የግብፃውያን አባባል
ቁንጅና ተሸጦ አይበላም፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
ቡናና ፍቅር የሚጣፍጠው በትኩሱ ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ፍቅር ባለበት ጨለማ የለም፡፡
የቡሩንዲያውያን አባባል
ከአንተ የሚበልጥ እግር ያላት ሴት አታግባ።
የሞዛምቢካውያን አባባል
ትዕግስት ሁሉንም ችግሮች የሚፈታ ቁልፍ ነው፡፡
የሱዳናውያን አባባል
ስለሮጡ ብቻ ይደረሳል ማለት አይደለም፡፡
የስዋሂሊ አባባል
ትዕግስት ድንጋይ ያበስላል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል

Sunday, 10 May 2015 15:38

የነፃነት ጥግ

ነፃነት፤ ሰዎች መስማት የማይፈልጉትን የመናገር መብት ነው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
ሃላፊነት ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
መንግስት ገደብ ካልተበጀለት በቀር ሰው ነፃ አይሆንም፡፡
ሮናልድ ሬገን
ነፃነት የነፍሳችን ኦክሲጅን ነው፡፡
ሞሼ ዳያን
በመናገር ነፃነት አምናለሁ፤ ነገር ግን በመናገር ነፃነትም ላይ ሃሳባችንን የመግለጽ መብት ሊኖረን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
ስቶክዌል ዴይ
ነፃነት ካልተጠቀሙበት የሚከስም ነገር ነው፡፡
ሃንተር ኤስ.ቶምፕሰን
የመፃፍና የመናገር ነፃነት ሰዎችን የማብሸቅ ነፃነትን ይጨምራል፡፡
ብራድ ቶር

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ የአገሪቱ ህገ-መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ህገወጥነት እንደሆነና ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወመው የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በአገሪቱ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ እየተባባሰ መምጣቱ፣ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አመቺ አይደለም ያለው የአፍሪካ ህብረት፣ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ወደ አገሪቱ እንደማይልክም አስታውቋል፡፡ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በአሜሪካ እየተደረገባቸው ያለውን ጫና የተቃወሙት ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በበኩላቸው፤ ቀጣዩ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መከናወን እንዲችል ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥሪ አቅርበው፣ ለአራተኛ ዙር አገሪቱን ለመምራት እንደማይፈልጉና ከዚህ በኋላ በምርጫ እንደማይወዳደሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ፖሊስ የአገሪቱን ዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ ሲል በተቃውሞው የተሳተፉትን ሰዎች በማሰር ላይ እንደሚገኝና፣ ዜጎች ከመሰል ድርጊታቸው የሚታቀቡና ተቃውሞው የሚቆም ከሆነ የአገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዜጎች በሙሉ እንደሚፈቱም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡በብሩንዲ ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ ምርጫውን ለመታዘብ አንችልም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር መወዳደራቸውም አግባብነት የለውም፤ የአገሪቱ ህገመንግስት ሊከበር ይገባል ብለዋል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ንኮዛና ድላሚኒ ዙማ፤ ከቻይናው ሲሲቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፡፡አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ሲኤንዲዲ-ኤፍዲዲ ፓርቲ ከሁለት ሳምንታት በፊት የወቅቱን የአገሪቱ ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በመጪው ምርጫ በዕጩነት ማቅረቡን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተቃውሞው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡ሮይተርስ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባል ነው ያሉትን አንድ ግለሰብ በእሳት አቃጥለው መግደላቸውንና የተለያዩ ሱቆችን ማጋየታቸውን ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር ምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው የህግ ጥሰት ነው ያሉት የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ የአገሪቱ ህገመንግስት አንድ ፕሬዚዳንት በመሪነት መቆየት የሚችለው ለሁለት ዙር ብቻ እንደሆነ ቢወስንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ህገመንግስቱን በጣሰ ሁኔታ በስልጣን ላይ ለመቆየት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን የምርጫ ተሳትፎ አግባብነት በተመለከተ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የብሩንዲ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ውሳኔው፣ ፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያውን ዙር በፓርላማ እንጂ ቀጥታ በህዝቡ ተመርጠው ስልጣን ባለመያዛቸው እንደ አንድ ዙር አይቆጠርባቸውም፣ በዘንድሮው ምርጫ መወዳደር ይችላሉ ብሏል፡፡
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳላይሬ ኒምፓጋሪትሴ ግን፣ ከመንግስት በተደረገ ጫና የተላለፈ ውሳኔ ነው በሚል ተቃውመው፣ ፊርማዬን አላስቀምጥም በማለት አገር ጥለው የተሰደዱ ሲሆን የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ ግለሰቡ ውሳኔውን እንዲያስተላልፉ ምንም አይነት ጫና እንዳልተደረገባቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለአመታት የዘለቀው ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የአገሪቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እ.ኤ.አ በ2005 ከተቋጨ ወዲህ አስከፊው የተባለውንና ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና አመጽ ተከትሎ፣ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱንና 40 ሺህ የሚደርሱ የአገሪቱ ዜጎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ መሰደዳቸውንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ኦዲፋክስ ንዳቢቶሪየ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ባለፈው ረቡዕ  አመጹን አነሳስተዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ መለቀቃቸውን እንዲሁም በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከትናንት በስቲያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድን ግለሰብ ተኩሶ መግደሉንና ሶስት ዜጎችንም ማቁሰሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

መስራቾቹ ትርፋማ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ሆነዋል
ሶስቱ ሰራተኞች በሶስት ሽፍት ይሰራሉ
ታላላቅ ኩባንያዎች ምርቶቹን ለመግዛት ተመዝግበዋል


ክላውድ ዲዲኤም የተባለውና በባለሶስት አውታር ህትመት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ለመስራት ዝግጅቱን ያጠናቀቀው  የአሜሪካ ኩባንያ፣ በ3 ሰራተኞች ብቻ በሚያከናውነው የምርት እንቅስቃሴ ትርፋማ ስራ እንደሚያከናውን መስራቾቹ በእርግጠኝነት መናገራቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነውና ሙሉ ለሙሉ በማሽን አማካይነት የሚሰራው ይህ ኩባንያ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ 100 ባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹ አማካይነት በሳምንት ለ 7 ቀናት ለ24 ሰዓት የማምረት ስራውን የሚያከናውን ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው በሶስት ሽፍት ለ8 ሰዓታት የሚሰሩ 3 ሰራተኞች ብቻ እንዳሉትም ገልጽዋል፡፡
ከኩባንያው መስራች አንዱ የሆኑት ሚች ፍሪ ባለፈው ረቡዕ ለሲኤንኤን እንደገለጹት፣ ኩባንያው የምርት ስራውን በማተሚያ ማሽኖቹና በሶስቱ ሰራተኞች አማካይነት በተቀላጠፈ ሁኔታ እያከናወነ ሲሆን፣ ምርቶቹን የማሸግና ለደንበኞች የማድረስ ስራውን ደግሞ ዩፒኤስ የተባለ አጋር ድርጅት እያከናወነው ይገኛል፡፡
ኩባንያው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖች አማካይነት በማምረት ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ሲሆን አሰራሩ የተቀላጠፈ በመሆኑ ለማምረት አንድ ሳምንት ያህል ጊዜ የሚወስዱ ዕቃዎችን በ24 ሰዓታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሚች ፍሪ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውን ለማቋቋም 1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉንና በቀጣይም የባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹን ቁጥር ወደ አንድ ሺህ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ተቀማጭነቱ በኒውዮርክ የሆነው ሁማንስኬል የተባለ የቤት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ፣ ታዋቂው የቅንጦት የእጅ ሰዓቶች አምራች ኩባንያ ዴቮን ዎርክስ እንዲሁም ግዙፉ ፍሌክስትሮኒክስን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ከዚህ በአይነቱ የተለየ ኩባንያ ምርቶችን ለመግዛት ደንበኝነት መመስረታቸውንም አስታውቋል።

ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመፃሕፍት ንባብ እና ውይይት ፕሮግራም በነገው ዕለት “ዘ ማሳካር ኦፍ ደብረ ሊባኖስ ኢትዮጵያ 1937” በተሰኘው የደራሲ ኢያን ካምፔል መጽሐፍ ላይ በነገው ዕለት በብሔራዊ ቤተመፃሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት ያካሂዳል፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምሕር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሲሆኑ የሥነ ፅሁፍ ቤተሰቦች በዚህ ውይይት ላይ እንዲታደሙ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጋብዟል፡፡
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ለ6 ወራት ያህል በየ15 ቀኑ የሚያደርገውን የመፃህፍት ውይይት አቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ደራሲው ዘውዱ ደስታ የምንድስና ባለሙያ ሲሆን በዘርፋ በሃገራችን ውስጥ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ሰርቷል፡፡ እየሰራም ይገኛል፡፡ደራሲው የህይወት ልምዱን ፤የንባብ ክህሎቱን ፤የብዙ ጊዜ ገጠመኞቹን ፤ትዝብቱንም ጭምር  ሳንሱሲ ውስጥ ከትቧል፡፡
ቀድሞ ሳንሱሲን እንዲያነቡ እድሉን ያገኙ ፀሀፊያን ከሶስት  በላይ አንኳር ጉዳችን  ደራሲው በመፅሀፋ እንዳስቀመጠና እንዲህም ሆኖ ግን ቁምነገሮቹ ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ በመሆናቸው ለአንባቢያን የአይን መግለጫ ነው ብለዋል፡፡
ደራሲው ዘውዱ ደስታ ከአዲስ አበባ ምዕራብ  መዝለቂያ በሆነችው ሳናሱሲ ላይ መቼቱን አድርጎ የፈጠራቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ገጸባህርያት ፤አንዳንዶቹ በልባችን ሙቀትና ቁመት ሲጎልምሱ አንዳንዶቹ ሰንፈው ሲፈርሱ በአጠቃላይ እንድንወዳቸው እንድንጨክንባቸው እና እንድንወያይባቸው ያደርጋል፡፡
ሳንሱሲ መጽሀፍን ማግኘት ለምትሹ አንባቢያን በተለያዩ መጽሃፍት መደብሮች ቀድሞ ይሸጥ ከነበረው  136 ብር  ደራሲው ዋጋውን አስተካክሎ በ96 ብር አቅርቦታል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አውራዶሮና ሚስቱ በአንድ ቄስ የእህል መጋዘን አጠገብ ሲጓዙ አውራዶሮው አንድ ባቄላ አግኝቶ ሲውጥ፤ አነቀውና፤ ውጪ ነብስ ግቢ ነብስ ሆነ፡፡ ሚስቲቱ ዶሮ የምታደርገው ብታጣ ውሃ ፍለጋ ወደ ወንዝ ወረደች፡፡
“ወንዝ ሆይ! እባክህ ባለቤቴ ባቄላ አንቆት፣ መተንፈስ አቅቶት ሊሞትብኝ ነው፡፡ ትንሽ ውሃ ስጠኝና ነብሱን ልታደገው?” አለችው፡፡
ወንዝም፤ “ወደ ሎሚ  ዛፍ ሄደሽ አንድ የሎሚ ቅጠል ካመጣሽልኝ ውሃ እሰጥሻለሁ” አላት፡፡
ዶሮይቱ ወደ ሎሚ ዛፍ ሄደችና፤
“ሎሚ ዛፍ ሆይ! ባለቤቴ ባቄላ አንቆት መተንፈስ አቅቶት፣ ሊሞትብኝ ነው ብዬ ወንዝን ውሃ ስጠኝ ብለው፤ “የሎሚ ቅጠል ካመጣሽ እሰጥሻለሁ” አለኝ፡፡ እባክህ አንዲት ቅጠል ስጠኝ?” አለችው፡፡
የሎሚ ዛፍም፤
“ወደ ቄሱ ቤት ሠራተኛ ሄደሽ የመርፌ ክር ካመጣሽልኝ እሰጥሻለሁ” አላት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ቄሱ ቤት ሠራተኛ ሄዳ ጉዳይዋን አስረዳች፡፡
የቤት ሠራተኛዋም፤ “ወደ ላም ሄደሽ ትንሽ ወተት ካመጣሽልኝ ክሩን እሰጥሻለሁ” አለቻት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ላም ሄዳ “ትንሽ ወተት ስጪኝ ባክሽ” ብላ ጉዳይዋን ሁሉ ዘረዘረችላት፡፡
ላምም፤ “ወደ አጫጆቹ ዘንድ ሄደሽ ትንሽ ጭድ ካመጣሽልኝ እሰጥሻለሁ” አለቻት፡፡
እመት ዶሮ እንደፈረደባት ወደ አጫጆቹ ሄዳ “እባካችሁ ትንሽ ጭድ ስጡኝ” አለቻቸው፡፡
አጫጆቹም “ወደ ቀጥቃጮች ሄደሽ ትንሽ ማጭድ ከሰጡሽ ጭዱን እንሰጥሻለን” አሏት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ቀጥቃጮቹ ሄዳ ለመነቻቸው፡፡
ቀጥቃጮቹ ደግሞ “ወደ ከሰል አክሳዮቹ ጋ ሄደሽ አንድ አራት ራስ ከሰል አምጪልንና የጠየቅሽንን እንሰጥሻለን” አሏት፡፡
ወደ ከሰል አክሳዮቹ ላዕያውያን (Laians) ምርር ባለ ምስኪን ቃና አስተዛዝና፤
“ከሰል አክሳዮቹ ሆይ፤ ባለቤቴ አውራዶሮ ባቄላ አንቆት፣ መተንፈስ አቅቶት ሞት አፋፍ ቢደርስ፣ አንድ ጉንጭ ውሃ ወንዝን ብጠይቀው፣ የሎሚ ቅጠል ከሎሚ ዛፍ አምጪ፤ የሎሚ ዛፍ ጋ ብሄድ ከቄሱ ሠራተኛ የመርፌ ክር አምጪ፤ የቄሱ ሠራተኛ ከላም ወተት አምጪ፤ ላም ጋ ብሄድ ከአጫጆቹ ጭድ አምጪ፤ አጫጆቹ ጋ ብሄድ ከቀጥቃጮች ማጭድ አምጪ፤ ቀጥቃጮቹ ዘንድ ብደርስ ከላዕያውያን ከሰል ካመጣሽ እንሰጥሻለን አሉኝ፡፡ እባካችሁ እናንተ እንኳ እሺ በሉኝ፡፡”
ከሰል አክሳዮቹ ራሩላትና ከሰሉን ሰጧት፡፡
እመት ዶሮ እየከነፈች ከሰሉን ይዛ ለቀጥቃጮቹ ሰጠች፡፡ ማጭድ ተቀብላ ለአጫጆች፤ ከነሱ ጭድ ተቀብላ ለላም፤ ከላም ወተት ወስዳ ለቄሱ ሰራተኛ፤ ከሷ የመርፌ ክር ተቀብላ ለሎሚ ዛፍ፤ ከሎሚ ዛፍ ቅጠል ተቀብላ ወደ ወንዙ በረረች፡፡ ከወንዙ ውሃ ተቀብላ ወደ አውራ ዶሮ ባሏ ከነፈች፡፡
አውራ ዶሮ ባሏ ግን ለአንዴም ለሁሌም ፀጥ ብሏል፡፡ ሞት ቀድሟታል፡፡
*   *   *
ችግር ሠንሠለቱን ሲተረትር ሰው በማህል ያልቃል፡፡ አያድርስ ነው፡፡
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤ በ “አክሱም ጫፍ አቁማዳ” ግጥሙ ትግራይ ለሸዋ፣ ለአርሲ ለሲዳሞ፣ ለወለጋ፣ ለጐንደር፣ ለኤርትራ እህል ተለማምነው፤ የተላከችው አቁማዳ አንዳችም እህል ሳይገባባት ተመልሳ ለባለቤቱዋ ለትግራይ ባዶዋን ትመጣለች፡፡
“…አክሱም ላይ ሠቀላት
ከባዶ አቁማዳ ነው፣ እሚዛቅ ፍቅራችን” ብሎ ይደመድማል፡፡ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ የችግሩ መጠን ይለያያል እንጂ በየሠንሠለቱ ቀለበት ላይ ችግር አለ፡፡ ቢሮክራሲያችንም እንደዚያው ነው! ሁሉም ለየግብዓቱ ጥሬ ዕቃውን ይጠይቃል፡፡ ይሄን ሠንሰለት ሙስና ብንለውም፤ ወይም የቅብብሎሽ ሂደት፤ አሊያም ዱላ ቅብብሎሽ፤ ዞሮ ዞሮ የታነቀው ህዝብ ለአንዲት ፍሬ መሞቱ አሳዛኝ ሀቅ ነው!
የችግሮቻችን ብዛት የመፍትሔዎቻችንን ውስብስብ ገፅታ ከወዲሁ ጠቋሚ ነው፡፡ የቆዩ ችግሮች መፍትሔ ሳያገኙ፤ አዳዲሶቹን ለመፍታት መጣራችን ራሱ አንድ ተጨማሪ ችግር ይሆንብናል፡፡ የሀገራችን ቁልፍ ጉዳይ ችግርን በሌላ ችግር መፍታት መሆኑ አሳሳቢ ከሆነ ቆይቷል፡፡ አብሮ መታየት ያለበት ግን ችግርን የመገንዘብ አቅማችንም አናሳ መሆን ነው፡፡
አንድ ፈላስፋ እንዳለው፡-
“The Problem is us; the Solution us” (ችግሩም እኛ፤ መፍትሔውም እኛ እንደማለት) ስለዚህ “እንዳልተመለሰው ባቡር” ያልተመለሱ ጥያቄዎች ሲደመሩ አዲስ ጥያቄ እያረግን ማሰብ ይበጃል፡፡
ሀ+1= ለ
ሀ= የዱሮ ችግር፣ “1” = አዲሱ ችግር፤ “ለ” = ያሁኑ ሁኔታ፤ እያልን ማስላት ነው፡፡ የዱሮ ችግር ብለን በመዝገብ የተያዙ ሂሳቦችን ካላወራረድን ነገ ኦዲተር አይለቀንም!
ከዲሞክራሲ ምን ጐሎ ነበር? ከፍትሕ ምን ጐሎ ነበር? ከሙስና መፍትሔ ምን ጐሎ ነበር? ከመልካም አስተዳደር ምን ጐሎ ነበር? ከሹምሽር ሥራ ምን ጐሎ ነበር? ህዳሴውስ ተመርምሯል ወይ? ከምርጫ ዝግጅት አሁን ምን ጐሎዋል? ከዱሮ ምርጫዎችስ ምን ጐሎ ነበር? በዚህ ሁሉ ድምር ሂሳብ ዛሬ ምን ላይ ነን? በአየር ጊዜ ክርክር አድማጩ ህዝብ እየረካ ነው? ምርጫው የተበላ ዕቁብ ነውን? የሚለው አስተሳሰብ መክኗል ወይስ በየልቡ ያኮበኩባል፡፡
በተፅዕኖ ከመምረጥ ጀምሮ አንዳንዱን ጠፍቶ ድንገት የመጣ ተመራጭ “አፋልጉኝ” እስከማለት የደረሰ፤ በስላቅ በሚኖር ህብረተሰብ ውስጥ ምርጫው አድሎ የሌለውና ዕውነተኛ (ነፃ) [Fair and Free] ነው ብሎ ለመኩራት፣ ለመተማመንና “አሹ!” ለማለት ከባድ ነው፡፡ “ዐባይን ጭብጦዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም!” ያለውን ባላገር ደግመን ደጋግመን እንድናስብ የሚያደርገን ፖለቲካዊም ባህላዊም ተፈጥሮ ያለን ነንና እንዴት ይሆን ወደፊት የምንገፋው ማለት አመላችን ነው!
“አይሠግሩም ተብሎ
ፈረስና በቅሎ፤
አይሮጡም ተብሎ
ፈረስና በቅሎ፤
እንዲያው በጥላቻ:-
ትመረጥ ይሆናል ኤሊ ለኮርቻ!” የሚለው አገርኛ አባባል፤ ጥቂት ቆም ብለን እንድናስብ ዐይናችሁን ክፈቱ ይለናል፡፡

ጠ/ሚ ኃይለማርያም የግብጽን መንግስት አመስግነዋል
   በሊቢያ ታግተው የቆዩና የግብጽ መንግስት ባደረገው ድጋፍ የተለቀቁ 27 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ትናንት ማለዳ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምና ሌሎች ባለስልጣናት በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ለስደተኞቹ አቀባበል አድርገዋል፡፡በግብጽ ወታደራዊ ሃይል ድጋፍ ከእገታ ተለቀዋል የተባሉት እነዚሁ ስደተኞች ከትናንት በስቲያ ካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አቀባበል እንደተደረገላቸው  ሮይተርስ፣ ፕሬዚደንቱ፤ “ስደተኞቹ በሊቢያ የታጠቁ ሃይሎች ታግተው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የቆዩ ናቸው” ማለታቸውን የአገሪቱ የዜና ተቋም “ሜና መዘገቡ ታውቋል፡፡የዜና ተቋሙ ስለስደተኞቹ ማንነት፣ ስለተለቀቁበት ሁኔታ እና ታግተው በቆዩበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ግልጽ መረጃ ባይሰጥም፣ ሮይተርስ በበኩሉ፤ የሊቢያ ባለስልጣናት ከግብጽ የስለላ ተቋማት ያገኙትን መረጃ በመጠቀም በዴርና እና ሚስራታ ከተሞች በታጠቁ ሃይሎች ታግተው የነበሩትን እነዚህን ስደተኞች እንዳስለቀቁ መረጃ ደርሶኛል ብሏል፡፡ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ
አንድ የግብፅ ዲፕሎማት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያኑ ከሊቢያ የወጡት በወታደራዊ ሃይል ድጋፍ ሳይሆን የግብፅ መንግስት ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ከኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች አንዱ በበኩሉ፣ የሊቢያ መንግስት ከነበርንበት ቦታ ወደ አገሪቱ የጸረ ህገወጥ ስደት አካል ከወሰደን በኋላ፣ የግብጽ መንግስት ወደ ካይሮ አምጥቶናል ሲል መናገሩን ዘገባው አስረድቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የስደተኞቹን መለቀቅ ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር፣ ግብጽ ኢትዮጵያውያኑን ለማስለቀቅ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልጸው፤ መሰል ጥረቶች በግብጽ፣ በአረቡ አለምና በአፍሪካ አገራት መረጋጋትን ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባወጡት መረጃ እንዳሉት፤ በሊቢያ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል የመጀመሪያዎቹ 11 ስደተኞች ባለፈው ረቡዕ በካርቱም በኩል ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡