Administrator

Administrator

   በአፍሪካ ለሚነሱ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች የተቀናጀ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሁም የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጐች የቻይና ቪዛን የሚያስቀር አዋጅን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አዋጆች ፀድቀዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም ካፀደቃቸው አዋጆች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል አዋጅና የኪዮቶ ፕሮቶኮልን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጆች ይገኙበታል፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ሃይል ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ የተጠንቀቅ ሃይሉ ከአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በሚሰጠው ፍቃድ መሰረት በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የሚሰጡትን ግዳጆች እየተቀበለ በፍጥነት ምላሽ ይሰጣል፡፡ የተጠንቀቅ ሃይሉ ዋና መቀመጫውና የስልጠና ማዕከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሆንም አዋጅ አመልክቷል፡፡ በአምስቱ የአህጉሩ ቀጠናዎች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ካሉ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና ሲቪሎች በተውጣጡ አባላት የሚዋቀረው የተጠንቀቅ ኃይሉ የሚያከናውናቸው ተግባራት በአፍሪካ ህብረት ከለላ ውስጥ እንደሚሆንና ኢትዮጵያ ለተጠንቀቅ ሃይሉ ሰራዊቶችን የማሰልጠንና አስፈላጊ መሳሪያዎችን የማቅረብ ግዴታ እንደተጣለባት አዋጁ አመላክቷል።
ሌላው ምክር ቤቱ ያፀደቀውና በኢትዮጵያና በቻይና መንግስታት መካከል የተፈረመው ስምምነት፤ የሁለቱ አገራት ዜጐች ያለቪዛ መውጣት መግባት የሚያስችላቸው ነው፡፡ የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የኢትዮጵያና የቻይና አገራት ዜጐች ያለቪዛ ለሰላሳ ቀናት ወደየአገራቱ መውጣትና መግባት የሚያስችላቸውን ይህንኑ ስምምነትም ምክር ቤቱ አጽድቆታል፡፡ ከምክትል ሚኒስቴር በላይ የሆነ ማዕረግ ያላቸው የማዕከላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ኦፊሰሮች ወይም ከሜጀር ጀነራል በላይ ማዕረግ ያላቸው የመከላከያ ባለስልጣናት ለኦፊሴሊያዊ ሥራ ወደ ሌላኛው ተዋዋይ አገር ድንበር ከመግባታቸው በፊት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሣወቅ እንደሚገባቸው በስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የፀጥታ የደህንነትና የጤና ችግሮች በሚከሰቱባቸው ጊዜያት ተዋዋይ አገራት የስምምነቱን ተፈፃሚነት በሙሉ ወይም በከፊል መገደብ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡   

   የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በአንድ ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ መደረግ የሚችልና የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ የአልሙኒየም የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ባትሪ መስራታቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
አዲሱ የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ባትሪ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መደበኛው የሊቲየም ባትሪ ጋር ሲነጻጸር፣ በከፍተኛ ፍጥነት ቻርጅ ከመደረጉ በተጨማሪ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉም እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡
“ፈጠራችን በባትሪው ቴክኖሎጂ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡ እኛ የሰራነው ባትሪ በእሳት የማይቃጠል ነው፡፡ ለአጠቃቀምም ምቹ በሆነ መልኩ ነው የተሰራው፡፡ ሊቲየም አዮን ባትሪን ከመሳሰሉ ሌሎች ነባር የባትሪ አይነቶች ጋር ሲነጻጸር፣ ሳይደክም ለብዙ ጊዜያት ቻርጅ የመደረግ አቅሙ እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተመራጭ ያደርገዋል” ብለዋል፤ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የተመራማሪ ቡድኑ መሪ ሆንጊ ዳይ፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የአልሙኒየም ባትሪዎች፣ በሙሉ አቅማቸው መስራት የሚችሉት እስከ መቶ ጊዜ ያህል ተደጋግመው ቻርጅ እስኪደረጉ ነበር፡፡ ይሄኛው ባትሪ ግን 7ሺህ 500 ጊዜ ያህል ቻርጅ እስኪደረግ አቅሙ የማይቀንስ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡
ተመራማሪዎቹ የፈጠራ ውጤታቸውን ሰርተው ማጠናቀቃቸውን ሰሞኑን ለህትመት በበቃ መጽሄት ላይ ይፋ ቢያደርጉም፣ ባትሪው በብዛት ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብበትን ጊዜ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡

Tuesday, 14 April 2015 11:26

የየአገሩ አባባል

 የአይሁዶች አባባል
ሰው ሲያቅድ እግዚአብሔር ይስቃል፡፡
እናት፤ ልጅ ሳይናገር ይገባታል፡፡
ሃጢዓትን ሁለቴ ከፈፀምከው ወንጀል አይመስልም፡፡
ፍየልን ከፊት ለፊት፣ ፈረስን ከኋላ፣ ሞኝን በየትኛው በኩል አትጠጋቸው፡፡
ብልህነትህን በተግባር እንጂ በቃላት አታሳይ፡፡
ሻማ ለመግዛት ፀሃይን አትሽጥ፡፡
እግዚአብሔር ሸክምን ሲሰጥ ትከሻም አብሮ ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ ሊሆን ስለማይችል እናቶችን ፈጠረ፡፡
ለጎረቤቱ የሚፀልይ ለራሱ ይደርስለታል፡፡
ልዕልት ማግኘት የምትሻ ከሆነ ራስህን ልዑል አድርግ፡፡
እግር የሌለው ሰው እስከማገኝ ድረስ ጫማ የለኝም ብዬ አዝን ነበር፡፡
በዓይንህ ያላየኸውን በአፍህ አትመስክር፡፡
ሳሙና ሰውነትን እንደሚያጥበው ሁሉ እንባም ነፍስን ያጥባል፡፡
አባት ለልጁ ሲሰጥ ሁለቱም ይስቃሉ፤ ልጅ ለአባቱ ሲሰጥ ሁለቱም ያለቅሳሉ፡፡

  - “በርበሬን የመረጥነው የከፋ ጉዳት ስለማያደርስ ነው” - የአገሪቱ ፖሊስ
   በሰሜናዊ ህንድ የምትገኘው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የላክኖው ፖሊስ፣ ከአየር ላይ በርበሬ የሚረጩ አነስተኛ አድማ በታኝ ድሮኖችን በስራ ላይ ማዋል ሊጀምር ነው ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የግዛቷ ፖሊስ ህገወጥ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎችን ለመበተን የሚያስችሉና እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ግራም በርበሬ የመጫን አቅም ያላቸው አምስት አነስተኛ ድሮኖችን በስራ ላይ ለማዋል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
“ህገወጥ አመጽ የሚያካሂዱ ዜጎችን በርበሬ እየረጨን እንበትናለን፡፡ ይህን ያልተለመደ የአድማ ብተና መሳሪያ ለመጠቀም የመረጥነው፣ በአመጹ ተሳታፊዎች ላይ የከፋ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ ነው፡፡ ህገወጥ ተቃውሞዎችንና የጎዳና ላይ አመጾችን በቁጥጥር ውስጥ በማዋል ረገድ ውጤታማ እንደሚሆንም ተስፋ አለን” ብለዋል ያሻዝቪ ያዳይ የተባሉት የግዛቲቱ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን፡፡
የግዛቲቱ አስተዳደር ባለፈው አመት ባደረገው ሙከራ፤ በርበሬ የሚረጩ ድሮኖች አድማን በመበተን ረገድ ውጤታማነታቸውን በማረጋገጡ፣ ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ዶላር የከፈለባቸውን ድሮኖች በስራ ላይ ለማዋል መወሰኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ህንድ በርበሬ የሚረጩ አድማ በታኝ ድሮኖችን በመጠቀም ከዓለማችን አገራት ቀዳሚዋ እንደሆነችም ዘገባው አክሎ ገልጿል።

በሽብር ጥቃቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀርበዋል
መንግስት 13 የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን ዘግቷል፤ 86 የባንክ ሂሳቦችን አግዷል
   አልሻባብ ባለፈው ሳምንት በኬንያዋ በጋሪሳ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከፈጸመውና 148 ያህል ተማሪዎችን ለህልፈተ ህይወት ከዳረገው የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተጎዳ እንደሚገኝና የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም እየቀነሰ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና በሚጫወተውና ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በሆነው የቱሪዝም መስክ እንቅስቃሴ ላይ መዳከም መታየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ወደ ኬንያ ለመሄድ የያዙትን ፕሮግራም ሰርዘዋል ብሏል፡፡
የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ሺልንግ የመግዛት አቅም፣ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በዚህ አመት ብቻ 2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ዘገባው ጠቁሞ፣ ቅናሹ በመጪዎቹ ቀናትም ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል፡፡
አልሻባብ በ2013 በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ላይ ጥቃት ከፈጸመ ጊዜ አንስቶ፣ የቱሪስት ፍሰቱ እየቀነሰና አገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ የመገበያያ ገንዘቡን የመግዛት አቅም ለማሻሻል ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱንም ጠቁሟል፡፡
ካለፈው ሳምንት የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦች ማክሰኞ ዕለት ናይሮቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዘገበው ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስ ነው። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለፈጸሙት አራት ግለሰቦች የጦር መሳሪያ አቅርበዋል በሚል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱም ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ ከአምስቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ አንድ ታንዛኒያዊ በሽብር ጥቃቱ ተሳትፏል በሚል በቁጥጥር ስር እንደዋለ የጠቆመው ዘገባው፤ ፖሊስ ግለሰቡ ላይ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ባለው መሰረት እንደተፈቀደለትም አክሎ አስታውቋል፡፡
የኬንያውን “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ፣ የአገሪቱ መንግስት ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ያስተላልፋሉ ብሎ የጠረጠራቸውን 13 የሶማሊያ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን የዘጋ ሲሆን በግዛቷ ውስጥ የሚፈጸሙ የሽብር እንቅስቃሴዎች በገንዘብ ይደግፋሉ ያላቸውን የ86 ግለሰቦችንና ድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል፡፡
የመንግስት ውሳኔ በኬንያ በሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል ያሉት የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ በሽር አሊ፤ ኬንያውያኑ ኑሯቸውን የሚገፉት ከተለያዩ የአለም አገራት ከዘመዶቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኬንያ መንግስት እንዲዘጉ የተወሰነባቸው የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ሃላፊዎችም ውሳኔውን በመቃወም፣ በዚህ አካሄድ ሽብርተኝነትን መዋጋት አይቻልም ብለዋ።
የኬንያ አየር ሃይልም ባለፈው እሁድ በሶማሊያ በሚገኙ ሁለት የአልሻባብ ካምፖች ላይ በፈጸመው የአየር ድብደባ ጥቃት ካምፖቹን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ቢያስታውቅም፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ጥቃቱ አልተፈጸመብኝም ሲል አስተባብሏል፡፡
አልሻባብ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በኬንያ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ከ400 በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት እንደዳረገም ቢቢሲ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስታውሷል፡፡

Tuesday, 14 April 2015 08:45

የፍቅር ጥግ

ሰውን ማፍቀር የእግዚአብሔርን ፊት ማየት ነው፡፡
(Les Miserables)
ራሴን በወደድኩበት መንገድ ሌላን ሰው ወድጄ አላውቅም፡፡
ማ ዌስት
ፍቅር፤ ሁለት ልቦችን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅረኛሞች እርስ በርስ የማይሰለቻቹት ሁሌም ስለራሳቸው ስለሚያወሩ ነው፡፡
ፍራንሶይስ ሌላ ሮቼፎካልድ
 ፍቅር ምን ይመስላል? ሌሎችን የሚረዳበት እጅ አለው፡፡ ለድሆችና ለችግረኞች ፈጥኖ የሚደርስበት እግር አለው፡፡ ችግርንና መከራን የሚያይበት ዓይን አለው፡፡ የሰዎችን ሃዘንና ጭንቀት የሚያዳምጥበት ጆሮ አለው፡፡ ፍቅር ይህንን ነው የሚመስለው፡፡
ቅዱስ አጉስቲን
ፍቅር መጠለያ ከሆነ በዝናብ ውስጥ እጓዛለሁ፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅር እውር ሊሆን ይችላል፤ ግን በእርግጠኝነት በጨለማ መንገዱን አይስትም፡፡
ያልታወቀ ምንጭ
ፍቅር ምርጫችን ሳይሆን ዕጣ ፈንታችን ነው፡፡
ጆን ድራይደን
አፍቃሪ ልብ ሁልጊዜም ወጣት ነው፡፡
የግሪኮች ምሳሌያዊ አባባል
ፍቅር፤ በጋብቻ የሚፈወስ ጊዜያዊ እብደት ነው፡፡
አምብሮሴ ቢርስ
በፍቅር ውስጥ ግንኙነቱን የሚቆጣጠሩት ብዙ ያላፈቀሩት ናቸው፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
ፍቅርን ስትከተለው ይሸሽሃል፤ ስትሸሸው ይከተልሃል
ምሳሌያዊ አባባል

Tuesday, 14 April 2015 08:44

ስብና መዘዙ!

      የሰውነት ክብደት እንዲጨምር ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ሰውነታችን ከሚያስፈልገውና መጠቀም ከሚችለው በላይ ካሎሪ መውሰድ ዋንኛው ነው፡፡ አንድ ሰው ለዕለታዊ እንቅስቃሴ የሚበቃውን ያህል ካሎሪ ከሚመገባቸው ምግቦች ውስጥ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ወደ ሰውነቱ ውስጥ የሚያስገባው የካሎሪ መጠን በዕለታዊ እንቅስቃሴው ከሚጠቀምበት በላይ ሲሆን ግን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ውስጥ እየተጠራቀመ ይሄድና ውፍረትን ያመጣል፡፡ በእርግጥ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአስተዳደግ ሁኔታና በዘር መውረስ ለውፍረት መንስኤ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ጭንቀት፣ ድብርት፣ የመንፈስ መረበሽ፣ የሆርሞን መለዋወጥ፣ ለተለያዩ ህክምናዎች የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለውፍረት መባባስ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአመጋገብ ሥርዓት እንደዚሁ ለውፍረት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ጮማና ስብ የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ውፍረትን ከማባባሱም በላይ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርጋል፡፡
የስብና ቅባት ነክ ምግቦች ጣጣ
ከፍተኛ የክብደት መጨመርና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጡ የተለያዩ የጤና ችግሮች፤
የወገብ ህመም ፣ የአጥንት መሳሳትና ስብራት እንዲሁም የአጥንት መገጣጠሚያዎች ህመም፤
ቦርጭ ይህም ለልብና ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ይዳርጋል፤
አንዳንድ የካንሰር ህመሞች በውፍረት ሳቢያ የመከሰት /የመባባስ እድል አላቸው፤
የወር አበባ መዛባትና የሃሞት ከረጢት ጠጠር፤
የደም ግፊት፣ የስኳርና የኮሌስትሮል መብዛት ችግሮችም በቅባትና ስብ መንስኤነት የሚከሰተው የውፍረት ችግር ውጤቶች ናቸው፡፡ 

Tuesday, 14 April 2015 08:40

የፖለቲካ ጥግ

በትዳራቸው ላይ
የቀበጡ የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶች

    እንኳንስ በቤተመንግስት ቀርቶ በደሳሳ ጎጆም ቢሆን በአብዛኛው በትዳር ላይ ሲማግጡ የምንሰማው ወንዶች ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች የተለወጡ ይመስላሉ። አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ እመቤቶች በትዳራቸው ላይ (ያውም የቤተመንግስት ትዳር!) እንደሚቀብጡ እየሰማን ነው። Africa Cradle የተባለው ድረገፅ፤ 5 በትዳራቸው ላይ የቀበጡ ወይም እስካሁንም የሚቀብጡ የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የስዋዚላንድ ንጉስ ሙስዋቲ 12ኛ ሚስት የሆነችው ኖታንዶ ተጠቅሳለች፡፡ (ልብ በሉ 12ኛ ልጅ አላልኩም!)
ኖታንዶ ከማን ጋር መሰላችሁ የቀበጠችው? ከአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ንዱሚሶ ማምባ ጋር ነው (ፍትህ ቀጠለች!) ሚስትየዋ በዚህም ተወንጅላ ከቤተመንግስት ተሰናብታለች (ደግ ንጉስ ስለሆኑ እኮ ነው!) ኖታንዶ ግን ብቻዋን አይደለችም፡፡ በ2004 እ.ኤ.አ የሙስዋቲ ሌሎች ሁለት ሚስቶችም በትዳራቸው ላይ ቀብጠዋል ተብለው ከቤተመንግስት የሞቀ “ጎጆአቸው” ተባርረዋል፡፡
ለነገሩ እኮ በሴቶቹም መፍረድ ያስቸግራል። እንግዲህ ንጉሱ 13 ሚስቶች ናቸው ያሏቸው፡፡ በየዓመቱም ድንግል ልጃገረድ ይበረከትላቸዋል - በባህላዊ የዳንስ ትርዒት፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ንጉሱ ለሚስቶቻቸው ጊዜ እንደሌላቸው ነው፡፡ ሴት ቤተመንግስት ውስጥ በድሎት እየኖረች ሥጋዊ ፍላጎት ቢያድርባት አይገርምም፡፡ እናም የንጉስ ሙስዋቲ ሚስቶች ቢቀብጡና ዓይናቸው ውጭ ውጭውን ቢያይ ሊወቀሱ አይገባም ይላሉ - የስነ ልቦና ተንታኞች። ጥፋተኛው ሰውየው ናቸው ሲሉ ንጉሱን ይወቅሳሉ - ተንታኞቹ፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት የጃኮብ ዙማ ሁለተኛ ሚስት ኖምፑ ሜሌሎ ንቱሊ ዙማም እንዲሁ ፊንዳ ቶሞ ከሚባለው ጠባቂዋ  ጋር ትቀብጥ ነበር ብሏል - ድረ ገፁ። (“ቦዲጋርድ” የሚለውን ፊልም አይታ ይሆን?) በእርግጥ ቦዲጋርዷ አሁን በህይወት የለም፡፡ ራሱን አጥፍቷል፡፡ ኖምፑ ሜሌሎ ንቱሊ ዙማ፤ ለፕሬዚዳንቱ 21ኛውን ልጅ አርግዛ በነበረ ወቅት ታዲያ የወላጅ አባት ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። (አይገርምም የ13 ሚስቶችና 21 ልጆች ነገር!) ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዙማ ቤተሰቦች በዙሉ ቋንቋ ለሚታተም ጋዜጣ በወቅቱ በፃፉት ደብዳቤ፤ ከሦስቱ የፕሬዚዳንቱ ሚስቶች አንደኛዋ፣ ፊንዳ ቶሞ ከተባለው ጠባቂዋ ጋር እንደምትማግጥ ገልፀው ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ማንም ወህኒ የወረደ የለም ተብሏል፡፡ “የፕሬዚዳንቱን ገፅታ ለመጠበቅ” ሲባልም ነገሩ እንዲቀዛቀዝ መደረጉ ታውቋል፡፡
ከዚያው ከደቡብ አፍሪካ ሳንወጣ ሌላ በትዳሯ የማገጠች ቀዳሚ እመቤት እናገኛለን፡፡ የኔልሰን ማንዴላ ሚስት ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ፡፡ ዊኒ በትዳሯ ላይ መማገጥ ጀመረችው ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ የፍቅር ግንኙነት የጀመረችው ደግሞ በዕድሜ ከሷ በግማሽ ከሚያንሰው ዳሊ ምፖፉ ከተባለ የህግ ባለሙያ ጋር ሲሆን የድፍረቷ ድፍረት እሷ በምትመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ፓርቲ የማህበራዊ ደህንነት ክፍል ውስጥ ምክትል ኃላፊ አድርጋ ሾማው ነበር፡፡ እናም ዊኒ፤ ማንዴላን እቤት ጎልታ ከድብቅ ፍቅረኛዋ ጋር በኮንኮርድ አውሮፕላን አሜሪካ ትንሸራሸር ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ማንዴላ ወሬ ሳይደርሳቸው ቀርቶ አልነበረም፡፡ በእሷ ላይ የሚወራውን ሁሉ ለመስማት ስለማይሹ እንጂ፡፡ ብዙም ሳትቆይ ግን ዊኒ የእጇን አገኘች፡፡ የዘራችውን አጨደች፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ዳሊ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንዳለው አወቀች፡፡
በነገሩ አንጀቷ የተቃጠለው ዊኒ ለዳሊ በፃፈችለት ደብዳቤ፤ “ለአምስት ወራት ያህል ከታታ (ኔልሰን ማንዴላ) ጋር አለመነጋገሬ ላንተ አያሳስብህም፡፡ ቤት ውስጥ ሁኔታዎች እየተበላሹ መምጣታቸውን ስነግርህ ቆይቻለሁ፡፡ አንተን ግን ምንም አላስጨነቀህም፤ ምክንያቱም በየማታው ሴት እያቀፍክ ትተኛለህ። ከአሁን በኋላ ግን ሞኝህን ፈልግ” ብላዋለች፡፡ ይሄ ደብዳቤ በኋላ ላይ በደቡብ አፍሪካው “ሰንደይ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ ታትሟል፡፡
ከወር በኋላም የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ (ANC) ከነበራት የኃላፊነት ቦታ ላይ ያነሳት ሲሆን ማንዴላም “ትዳራችን አብቅቷል” ሲሉ በአደባባይ ይፋ አደረጉ፡፡ ዊኒ በአንድ ጊዜ ሁሉ ነገሯን አጣች፡፡
African Cradle በትዳራቸው የቀበጡ ወይም አሁንም እየቀበጡ ያሉ “የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶች” በሚል ከጠቀሳቸው ውስጥ የዚምባቡዌዋ ቀዳሚ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ይገኙበታል፡፡ የ50 ዓመቷ ግሬስ፣ ከሙጋቤ ጋር የ40 ዓመት የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ሲሆን ይቀብጣሉ የተባለውም ከዚምባቡዌ ሪሰርቭ ባንክ ገዢ ጊዲዎን ጎኖ ጋር እንደሆነ ድረገፁ ይጠቁማል፡፡ ክፋቱ ደግሞ የባንኩ ገዢ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ  የቀኝ እጅ መሆናቸው ነው፡፡
ይሄ ግን ግሬስና ጎኖን በወር ሦስቴ ከመገናኘት አላገዳቸውም - አንድም በግሬስ የወተት ተዋፅኦ እርሻ ውስጥ አንድም ደግሞ በጎረቤት አገር ደቡብ አፍሪካ ሆቴሎች ውስጥ እየተገናኙ ዓለማቸውን ይቀጫሉ ተብሏል፡፡ (ሙጋቤ እንዴት አስቻላቸው? …)
ግሬስ በትዳራቸው ላይ ሲቀብጡ ይሄ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ፒተር ፓሚሬ የተባለ ፍቅረኛ የነበራቸው ሲሆን ፍቅረኛቸው አሁንም ድረስ መንስኤው ባልታወቀ የመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል። ጄምስ ማካምባ የተባለ ሌላ ፍቅረኛም ነበራቸው፡፡ እሱ ደግሞ ከአገሪቱ ወጥቶ ተሰውሯል ተብሏል፡፡
ግሬስና የባንኩ ገዢ ከድብቅ የፍቅር ግንኙነታቸው በተጨማሪ ላለፉት 15 ዓመታት የቢዝነስ ሸሪኮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ለነገሩ ሚ/ር ጎኖ ከግሬስ አጠገብ መሆናቸውን ሮበርት ሙጋቤ ይፈልጉታል፡፡ ሚስቴን እንዳትቀብጥ በዓይነ ቁራኛ ይጠብቅልኛል በሚል እዚህ ድረስ ነው ፕሬዚዳንቱ የባንክ ገዢውን የሚያምኑት። እሳቸው ግን አልታመኑላቸውም፡፡ ምክንያቱ ባይታወቅም እስካሁን ሙጋቤ የ55 ዓመቱን የባንክ ገዢ ምንም አላሏቸውም። ሰውየው ግን ምን ዓይነት የስጋት ህይወት እንደሚመሩ መገመት አያዳግትም፡፡ (ሚስትየዋ እንኳን አመላቸው እንደሆነ ይታወቃል!) በነገራችሁ ላይ ግሬስ ቀዳሚ እመቤት ከመሆናቸው በፊት የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋ ፀሐፊ ነበሩ፡፡ 

ሬስቶራንቶችን በክትፎ፣ ቁርጥና ጥብስ ያወዳድራል
አዋሽ ወይን ፋብሪካ ዘመናዊና ጥንታዊ የአጠማመቅ ዘዴዎችን በመጠቀም “ገበታ” የተሰኘ አዲስና ልዩ የወይን ጠጅ ምርት ለፋሲካ በዓል ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
“ገበታ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የአዋሽ ምርት ቀይና ነጭ ዘመናይ ወይኖች እንዳሉት ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የከተማዋ ሬስቶራንቶች በምርጥ ክትፎ፣ ቁርጥና ጥብስ ብቃታቸውን የሚያሳዩበት “የአዲስ ምርጥ ሥጋ ውድድር” ማዘጋጀቱን አዋሽ ወይን ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
በውድድሩ፤ የአዋሽ አዲስ ምርትን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀምበትም ጠቅሶ ሬስቶራንቶች በክትፎ፣ በቁርጥ፣ በጥብስ ወይም በአንዱ አሊያም በሁለቱም መወዳደር ይችላሉ ተብሏል፡፡
ውድድሩ፣ ደንበኞች በስልክ መልዕክት በሚያደርጉት ምርጫ (ክትፎ፣ ቁርጥ፣ ጥብስ) የሚወሰን ሲሆን ሬስቶራንቶች የመጀመሪያዎቹ 100 ውስጥ ከገቡ በየሳምንቱ እንደሚገለፅላቸው ታውቋል፡፡ ውድድሩ ከሚያዝያ 5-25 ድረስ ለሦስት ሳምንት የሚካሄድ ሲሆን በሶስተኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ 50ዎቹ ውስጥ የገቡ ሬስቶራንቶች አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት ክትፎ፣ ቁርጥና ጥብስ አቅራቢ ሬስቶራንቶች ውስጥ በደንበኞች የተመረጡና ምርጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ልዩ ሽልማት ይቀበላሉ ተብሏል፡፡ በእያንዳዱ ውድድር ከ1-5 የሚወጡ ሬስቶራንቶች አዋሽ በሚሰጣቸው ነፃ ወይን ጠጅ የቅምሻ ዝግጅት እንደሚያካሂዱ ተገልጿል፡፡  

Tuesday, 14 April 2015 08:28

የትንሳኤ ስጦታ

ክርስቶስ ሊረሳን አይችልም፤ በእጆቹ መዳፍ ላይ ተቀርፀናል፡፡
ሌይስ ፒቺሎ
በምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብሆን የክርስቶስ ትንሳኤ ለህይወቴ ትርጉምና አቅጣጫ እንዲሁም እንደ  አዲስ የመጀመር ዕድል ይሰጠዋል፡፡
ሮበርት ፍላት
እኛ ኖረን እንሞታለን፤ ክርስቶስ ሞቶ ይኖራል፡፡
ጆን ስቶት
ሰዎችን ከጊዜ ቅንብብ ውስጥ አውጥቶ ዘላለማዊነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
የእኔ አምላክ ከዚህ ምድር፣ ከዚህ መቃብር፣ ከዚህ አቧራ ውስጥ እንደሚያወጣኝ አምናለሁ፡፡
ዋልተር ራሊግ
ትንሳኤ፤ እግዚአብሔር ህይወት መንፈሳዊና ዘላለማዊ መሆኑን ማሳያው ነው፡፡
ቻርልስ ኤም ክሮው
ትንሳኤ እንዲህ ይለናል፡- “እውነትን ልትቀብራት ትችላለህ፤ ግን ተቀብራ አትቀርም”
ክላረንስ ደብሊው ሆል
የክርስቶስን ስቅለት ባሰብኩ ቁጥር የቅናት ኃጢአትን እፈፅማለሁ፡፡
ሳይሞን ዌይል
ክርስቲያን ማለት በሁሉ ነገር ከክርስቶስ ጋር የሚጓዝ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ብቃት ማናችንም ጋ የለም፡፡ ክርስቲያን ማለት ትክክለኛውን መንገድ ያገኘ ነው፡፡
ቻርልስ ኤል. አለን
የኢየሱስ ክርስቶስ ደም እጅግ አያሌ ሃጢአቶችን የሚከላከል ይመስለኛል፡፡
ዴኒስ ዲድሮት
እንደ ኢየሱስ ማንም ወዶ አያውቅም፡፡ ዓይነስውርን አብርቷል፤ ዲዳን አናግሯል፡፡ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ ተቸንክሯል፡፡ አሁን እግዚአብሔር፤ “እሱ ይሄን በማድረጉ ምሬአችኋለሁ” ብሎናል፡፡
ቢሊ ግራሃም
ኢየሱስ የመጀመሪያው ሶሻሊስት ነው፤ ለሰው ልጅ ሁሉ የተሻለ ህይወት ለመፍጠር የተጋ የመጀመሪያው ሰው፡፡
ሚኻኤል ጎርባቾቭ