Administrator

Administrator

ሩስያ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

     የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ትላንትና በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱ ላይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር እንደተገኙም ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሚንስትሮች በአገራቱ መካከል የተጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ውይይቶችን እንደሚቀጥሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ባድር አብደል አቲ ገልጸዋል፡፡በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፤ በሰሜናዊ ሲና አካባቢ ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ሰርዘው ወደአገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያው አቻቸው ያደረጉላቸውን ግብዣ በመቀበል ውይይቱን ለመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁሟል፡፡በሌላ በኩል ሩስያ፤ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ እንደሆነ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከግብጹ አቻቸው አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር የሃይል ማመንጫ
ግንባታ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚደረስበት ከሆነ፣ ጉዳዩ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በግብጽ አዲስ የአቶሚክ ኢንዱስትሪ ጅማሬ ይሆናል ብለዋል፡፡ግብጽ ከዚህ በፊት ባቋቋመችውና ከአሌክሳንድሪያ የወደብ ከተማ ምዕራባዊ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ዳባ ከተማ ውስጥ ባለው የኒውክሌር ምርምር ጣቢያ ላይ የሚገነባው ይህ የሃይል ማመንጫ፣ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ማብላያዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ግንባታው በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እየተስፋፋ ላለባት ግብጽ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ተብሏል፡፡ የግብጹ አሽራቅ አል አውሳት ድረገጽ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን የአገራቱ መሪዎች በይፋ ባያረጋግጡትም፣ አገራቱ ከሃይል ማመንጫ ግንባታው በተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽመዋል ሲል ኢንትራ ፋክስ የዜና ተቋምን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

       የኩዌት መንግስት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በማስገባት በቤት ሰራተኝነት ያስቀጥራሉ የተባሉ  12 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እንዳስታወቀ አረብ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሚኒስቴሩን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ 12 ሴቶችንና አንድ አሽከርካሪን በአባልነት ይዞ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ስራ ላይ እንደተሰማራ የተገለጸው ይህ ቡድን፣ በአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት መሪነት በህገወጥ መንገድ ወደ ኩዌት የሚያስገባቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለአገሪቱ ዜጎችና ለሌሎች አገራት በቤት ሰራተኝነት ሲያስቀጥር ቆይቷል፡፡
የኩዌት የነዋሪዎች ጉዳይ ምርመራ ክፍል ባለስልጣናት፤ በድኑ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ እንደተሰማራ ከታማኝ ምንጭ ያገኙትን መረጃ መሰረት በማድረግ ባካሄዱት ክትትል፣ የቡድኑን አባላት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚያከናውንበት ጀሊብ አል ሹዮክ የተባለ የአገሪቱ ክፍል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቡድኑ አባላት ከአገሪቱ የሰራተኞች ቢሮ ጋር የስራ ግንኙነት ያላቸውና በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ በማስመሰል በበርካታ የኩዌት ነዋሪዎች ላይ የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽሙ ነበር ብሏል፤ ዘገባው፡፡
በቁጥጥር ስር በዋሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  • “ሠማያዊ ፓርቲ የኔን መዋቅር ተጠቅሞ ነው እጩ ያስመዘገበው” አንድነት ፓርቲ  
  • -“እጩዎቻችንን ለማስመዝገብ ከቦርዱ አስፈፃሚዎች ተግዳሮት ገጥሞናል” ሰማያዊ ፓርቲ

      በቅርቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ እየተመራ ወደ ምርጫ እንዲገባ የወሰነለት እና በአቶ አበባው መሃሪ እንዲመራ የተወሰነው መኢአድ በምርጫው ለመወዳደር እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል፡፡
አንድት ፓርቲ ከ200 በላይ እጩዎች ማስመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን መኢአድ በበኩሉ፤ መረጃዎቹ ተጠናቅረው አልደረሱኝም ብሏል፡፡ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ፓርቲዎቹ ያስመዘገቧቸው እጩዎችን ብዛትን በተመለከተ ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም፡፡  
የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ ቦርዱ ፓርቲውን እንዲመሩ ከወሰነ ጊዜ አንስቶ ከቢሮ መረካከብ ጋር በተፈጠረው የጊዜ መጓተት ምክንያት በ5 ቀናት ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባ ሃያ ሶስቱም የምርጫ ክልሎች ጨምሮ ከሱማሌ፣ ጋምቤላና ትግራይ በስተቀር በሌሎች ክልሎች 201 እጩዎችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ለሌሎች ፓርቲዎች የተሠጠው 49 ቀን ሲሆን ለእነሱ 7 ቀን ብቻ እንደተሰጠና ፓርቲው በ5 ቀን ብቻ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መገደዱ የፈለገውን ያህል እጩ ማቅረብ እንዳላስቻለው የጠቀሱት አቶ ትዕግስቱ፤ በማስመዝገብ ሂደቱ ፓርቲው በውዝግብ ውስጥ ማለፉ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎም አባላት ወደ ሠማያዊ ፓርቲ መቀላቀላቸው፣ ሠማያዊ ፓርቲ የኛን መዋቅር ተጠቅሞ እጩዎቹን ለማበራከት አስችሎታል ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የአንድነትን አባላት ማስመዝገቡ የተገቢነት ጥያቄ ያስነሳል ነው ብለዋል፡፡ “ሠማያዊ ፓርቲ በተለይ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የአንድነት አባላትን አስመዝግቧል” ያሉት የአንድነት ሊ/መንበር፤ ይህም ፓርቲው ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ መዋቅር እንዳልነበረውና አጋጣሚውን እንደተጠቀመ ያመለክታል ብለዋል፡፡ “የኛ ሰዎች ባይኖሩ ሠማያዊ ፓርቲ ምን ያስመዘግብ ነበር?” ሲሉ አቶ ትዕግስቱ ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሠጡን የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ እንኳን ከአንድነት ወደ ሠማያዊ የተቀላቀሉትን ቀርቶ የፓርቲውን ነባር አባላት እንኳ ለማስመዝገብ ችግር ገጥማቸው እንደነበር ጠቅሰው በተለይ ጐጃም ውስጥ ለፓርላማ 10 እጩዎችን እንዳናስመዘግብ ተደርገናል ብለዋል፡፡ ደቡብ እና ኦሮሚያ ላይ በግልጽ ሠማያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉ የአንድነት አባላት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ አዲስ አበባ ላይም ከ23 ቦታዎች በ4ቱ የአንድነት አባላት የነበሩት ይወዳደራሉ ብለዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ ከመነሻው 380 መቀመጫ ለማሸነፍ አልሞ 400 እጩዎችን እንደሚያቀርብ አረጋግጦ ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ መግባቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ የአንድነት አባላት የነበሩት በፖለቲካ ትግሉ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየተመዘነ ለቦታዎቹ ታጭተው የነበሩ የሠማያዊ ፓርቲ አባላትን በመተካት እንዲገቡ ተደርጓል እንጂ ሠማያዊ የእጩ ችግር የለበትም ብለዋል፡፡ ለአንድነት የተመዘገቡ እጩዎች ሣይቀሩ ከአንድነት ለቀው ለሠማያዊ የመመዝገብ መብትም እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል አቶ ዮናታን፤ የመኢአድ የምርጫ አስተባባሪ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በተሰጠው አጭር ጊዜ ውስጥ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መሞከሩን ጠቅሰው ምን ያህል እጩዎች ተቀባይነት አግኝተው ተመዘገቡ የሚለውን ለማወቅ ገና ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል

የኢራን፣ የእስራኤልና የኩዌት ዜግነት ያላቸው ባለጸጎች፣ ቤተሰቦችና ተቋማት የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በስቅላት የተገደሉበትን ገመድ በከፍተኛ ገንዘብ በመግዛት የራሳቸው ለማድረግ የጦፈ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነውን አል አራቢ አል ጃዲድ ድረገጽ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ግለሰቦቹ በቀድሞው የኢራቅ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሞዋፋቅ አል ሩባይ እጅ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ገመድ የራሳቸው ለማድረግ እየተፎካከሩ ነው፡፡
ግለሰቡ በመኖሪያ ቤታቸው ከነሃስ በተሰራ የሳዳም ሃውልት አንገት ላይ ገመዱን አጥልቀው የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ከሁለት አመታት በፊት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ገመዱን በእጃቸው ለማስገባት ፍላጎት የሚያሳዩ ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንድ የወቅቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
ገመዱን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ከተሳተፉት መካከል፣ ሁለት የኩዌት ባለጸጎች፣ አንድ የኢራን የሃይማኖት ተቋም እና አንድ የእስራኤላውያን ሃብታሞች ቤተሰብ እንደሚገኝበት የጠቆመው ዘገባው፣ አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር ማቅረቡን አክሎ ገልጧል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ገመዱን ለማግኘት የተጀመረውን ጨረታ የተቃወሙ ሲሆን፣ ጨረታው የሚቀጥል ከሆነ ግን የሚገኘው ገንዘብ የአገሪቱን ህዝቦች ተጠቃሚ ለሚያደርግ ተግባር መዋል ይገባዋል ብለዋል፡፡

ብዙ ወጣቶች በምርጫ ድምጽ እንዲሰጡት ለማድረግ ነው
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን አባል የሆኑበት ወግ አጥባቂው ትሮይ ፓርቲ በቅርቡ በሚከናወነው ምርጫ ብዙ ድምጽ ለማግኘት በፌስቡክ ለሚያደርገው ቅስቀሳ በአመት ከ1 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ፓርቲው ባለፈው አመት መስከረም ላይ ብቻ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲወዱት ለማድረግ የከፈለውን 25 ሺህ ፓውንድ ጨምሮ፣ በወሩ በድምሩ 123ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ለፌስቡክ ኩባንያ ገቢ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው ህዳር ወር ፖለቲካዊ ይዘት ላለው ሌላ ድረገጽ 115 ሺህ ፓውንድ መክፈሉን አስታውቋል፡፡
ለፌስቡክ ይህንን ያህል ወጪ ማውጣቱን እንደ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሚቆጥረው የገለጸው ትሮይ ፓርቲ፤ ገንዘቡን የሚያወጣው ቁጥራቸው የበዛ ወጣቶች በምርጫ ድምጻቸውን እንዲሰጡት በማሰብ እንደሆነ ቢገልጽም፣ የሚሳካለት አይመስልም ብሏል ዘገባው፡፡
በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነትን በማትረፍ ረገድ፣ ብሪቴን ፈርስት የተባለው ፓርቲ ትሮይን በእጥፍ ያህል እንደሚበልጠው የጠቀሰው ዘገባው፣  ብሪቴን ፈርስት 650 ሺህ፣ ትሮይ ደግሞ 340 ሺህ ያህል የፌስቡክ ወዳጆች እንዳሏቸው ጨምሮ ገልጧል፡፡




*ውሳኔው ጨረቃ የማን ናት
በሚለው ጥያቄ ላይ ተጽዕኖ አለው ተብሏል

የአሜሪካ መንግስት፤ አገራት፣ የግል የህዋ ምርምር ተቋማትና ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ የሚያከናውኗቸውን የንግድ ስራዎች በተመለከተ ቁጥጥር ማድረግ ሊጀምር እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
አሜሪካ ቁጥጥር ማድረግ እንደምትጀምር ማስታወቋ፣ ጨረቃ የማን ናት፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ጨረቃ መላክ የሚችሉትስ እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶችን አንድ እርምጃ ያራመደ ነው ተብሏል፡፡
የአገሪቱን ኩባንያዎች ጨምሮ በመስኩ የተሰማሩ የመላው አለም ኩባንያዎች መንኮራኩሮችን ወደ ጨረቃ መላክና የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን የሚችሉት ከአሜሪካ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው ያለው ዘገባው፤ ፍቃዱን የሚሰጠውም የአገሪቱ የፌዴራል አቪየሽን ባለስልጣን እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
ባለስልጣኑ ያወጣው የቁጥጥር መመሪያ ኩባንያዎችና ተቋማት ወደ ጨረቃ ለሚያደርጉት ጉዞ ፈቃድ ከመስጠት በተጨማሪ፣ በጨረቃ ላይ የሚኖራቸውን ክልል የሚወስን ነው፡፡
አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸደቀውንና ጨረቃ እና ሌሎች የህዋው አለም ቦታዎች በማንኛውም መንግስት ባለቤትነት ስር አይሆኑም የሚለውን ህግ እንደተቀበለች ያስታወሰው ዘገባው፣ ህጉ የግል ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ እንዳያስቀምጡ ባይከለክልም፣ አሜሪካ ግን ይሄን አካሄድ ለመቆጣጠር መነሳቷን አስረድቷል፡፡

በ189 ዜጎች ላይም የሞት ቅጣት ጥላለች

   የቀድሞውን የግብጽ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በአመጽ ከስልጣን ለማውረድ ከአራት አመታት በፊት በተቀሰቀሰው አመጽ ተሳትፈዋል የተባሉ 230 የአገሪቱ አብዮተኞች ባለፈው ረዕቡ በካይሮ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው  ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ታህሳስ ወር ላይ በካይሮው ታህሪር አደባባይ በተካሄደው አመጽ ከአገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፣ የተለያዩ የመንግስት ህንጻዎችንና ተቋማትን በእሳት አቃጥለዋል የተባሉት እነዚሁ ተከሳሾች፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የቅጣት ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ ከእስራቱ በተጨማሪ በድምሩ 2ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤቱ ተውስኖባቸዋል፡፡
ቅጣቱ ከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከል በችሎቱ ተገኝቶ የፍርድ ውሳኔውን ያደመጠው ብቸኛ ተከሳሽ፣ አመጹን በማቀጣጠልና በመምራት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት የ26 ዓመቱ አህመድ ዱማ፤ ዳኛው ክሱን በሚያነቡበት ወቅት በማጨብጨብና ጮክ ብሎ በመናገር፣ ተቃውሞውን ለማሰማት ሞክሯል ተብሏል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን ዳኛው በተከሳሾቹና በጠበቆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ ነበር፣ የፍርድ ሂደቱ በአግባቡ አልተከናወነም፣ ውሳኔውም በአገሪቱ ታሪክ አስደንጋጭና የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይም በአገሪቱ የሚታየው የጅምላ እስራትና ቅጣት ከዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ነው ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩ፤ ግብጽ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎችን ስትጥስ ቆይታለች፤ የግብጽ ባለስልጣናት ይህንን ግዴታ ማክበርና ፍትሃዊ የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል፡፡
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ባለፈው ሰኞም የእስላማዊ ቡድን አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ 183 ግለሰቦች ላይ ባለፈው ሰኞ የሞት ፍርድ መበየናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት  ተሟጋች ተቋማት ፍርዱን መቃወማቸውን እንደገለጹ አመልክቷል፡፡

ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ኤድስ ባጡ ህፃናት የተዘጋጁ የጥበብ ውጤቶች የሚታዩበት “ተስፋ ኪነጥበብና ሙዚቃ ጋር” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ኤግዚቢሽን ነገ በ ‹አለ› ዲዛይንና የስነ ጥበብ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ይከፈታል፡፡
የእስራኤል ኤምባሲ ከእስራኤሉ ሃዳስ ዩኒቨርሲቲ ኤንግልሃርድ፣ ከነፃ የጥበብ መንደር የአርቲስቶች ቡድንና ከአርቲስት ፎር ቻሪቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸው ወላጆቻቸውን በኤች አይቪ ኤድስ ያጡ ህፃናት ከመቶዎች በላይ ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎቻቸውን በኤግዚሽኑ ላይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡
“ተስፋ ከጥበብና ሙዚቃ ጋር የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ዝግጅት ላይ ህፃናቱ በተለያየ አይነት አቀራረብና አሳሳል የሳሏቸውን ስዕሎች እንደሚያቀርቡና ኤግዚቢሽኑም ለአንድ ሳምንት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ኤምባሲው የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡  

  • አቶ ልደቱ ከ15 ዓመት በፊት የትጥቅ ትግል አስበው ነበር
  • ኢህአዴግ እያዳከመን ነው ማለት፣ የራስን ድክመት መናገር ነው
  • ህብረት መፍጠር የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አልጠቀመም    

የፖለቲካ ተሳትፎ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ በተፈጠሩ አሉባልታዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን “ቴአትረ ቦለቲካ፤ አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ ገመና” በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ያወጡት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በመፅሐፋቸው ጭብጥና በአጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ ከጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ ጋር አውግተዋል፡፡

ከፖለቲካው ብዙ ርቀዋል -- አሁን ምን እየሰሩ ነው?
በፖለቲካው ያለኝ ሚና ቢቀንስም አልራቅሁም። አሁን የስራ አስፈፃሚ አባል ስላልሆንኩ የእለት ተእለት ስራ ውስጥ የለሁም፡፡ በዚህ ምክንያት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አልገናኝም፡፡ የኢዴፓ የላዕላይ ምክር ቤት አባል ነኝ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ባለኝ የኃላፊነት መጠን መስራት ያለብኝን እየሰራሁ ነው፡፡ በሚዲያ ስለማልቀርብ ከፖለቲካው መራቅ ብቻ ሳይሆን የተውኩ ሁሉ የሚመስላቸው አሉ፤ እውነታው ግን ያ አይደለም፡፡ በእርግጥ ሙሉ ጊዜዬን ለፖለቲካው ስለማላውል ሌሎች ስራዎችን እሰራለሁ፡፡
“ቴአትረ ቦለቲካ” የተሰኘው አዲሱ መፅሃፍህ በዋናነት በአሉባልታ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው--
እዚህ መፅሀፍ ላይ ማስቀመጥ የፈለግሁት በአብዛኛው ሂደት ውስጥ የነበረውን ነገር ነው፤ አልፎ አልፎ የራሴን ጉዳይ ባስቀምጥም፡፡ ብዙ ጊዜ “ፖለቲካል ኮሬክትነስ” የምንለው ነገር አለ፡፡ ጉዳዩ እሱ አይደለም፤ ያለፍኩበትን ሂደት በነበረበት ሁኔታ አስቀምጬ፣ ሰዎች ሌላ ጊዜ እንደ እኔ ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ፈተና አስቀድመው እንዲያውቁት ነው፡፡ ሳያውቁት ገብተው በኋላ ላይ ችግር ከሚገጥማቸው… ምናልባትም ወደ ተስፋ መቁረጥ ከሚገቡ፣ ራሳቸውን አዘጋጅተው መቋቋም እንዲችሉ ለማድረግ ትንሽ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል ብዬ ነው የፃፍኩት። መፅሀፉ ላይ እንደገለጽኩት፤ መጀመሪያ ላይ አሉባልታ ብዙም አያስጨንቀኝም ነበር፤ “የሆነው ሆኗል፤ ያመንኩበትን አድርጌያለሁ፤ ሌላው ሰው የፈለገውን ቢል የኔ ችግር አይደለም፤ ነገሩ እየታወቀ ሲመጣ ሰዎች ሁኔታውንም እኔንም ይረዱኛል” የሚል አስተሳሰብ ስለነበረኝ፣ በጣም ጠንካራ በሆነ ሁኔታ ነው ተቋቁሜው የሄድኩት። ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ ከዚያ አስተሳሰብ የተለየ፣ ምናልባትም ሰው መሆኔን በደንብ የሚነግረኝ ስሜት ተፈጠረ፡፡
ይህ በህይወቴ ላይ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል። ሁላችንም ሰዎች እስከሆንን ድረስ የሚወጣ የሚወርድ፣ የሚፈራረቅ ስሜት አለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳታውቂው በውስጥሽ የተከማቸ ነገር እንደዚያ አይነት ሁኔታ ሲያገኝ ሊወጣ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ይህንን ማስቀመጡ ተገቢ ነው በሚል እንጂ ያለፈ ነገር ነው፡፡  በዚህ ስሜት ውስጥ ማለፍ ምን ማለት ነው የሚለውን ለመረዳት እድል የሰጠኝ አጋጣሚ ነው፡፡ በፖለቲካ ትግሉ ያለኝን ተሳትፎ እንዳቆም ወይም እንዳለዝብ አሊያም ወደ ተስፋ መቁረጥ እንድሄድ ያደረገ ነገር አይደለም፡፡ በትግሉ እቀጥላለሁ፡፡ በእርግጥ የእድሜም ጉዳይ አለ፤ ለአዲሱ ትውልድ ቦታ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ግን ይህን ምክንያት አድርጎ ከትግል መራቅ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ፖለቲካ ፈቅጄ፣ ወድጄ፣ አምኜ የገባሁበት ስለሆነ፣ ያሳለፍኩት ሂደት በጣም ከባድ ቢሆንም ወደፊትም የምርቀው ነገር አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሉባልታን በመኮትኮት ተሰሚነት እንዲያገኝ ያደረጉት ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኃን ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ በዚህ ይስማማሉ?
ለእኔ አንዱ ለሌላው ያቀበለው ባህል አይመስለኝም፡፡ ችግሩ ሁሉም ላይ የነበረና ያለ በመሆኑ ተመጋጋቢ ነው፡፡ ሁላችንም የዚህ ህብረተሰብ ውጤቶች ነን፡፡ በእኔ እምነት አሉባልታ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ወይም የፕሬሱ ብቻ አይደለም፤ በአጠቃላይ እንደ ህብረተሰብ ያለብን ችግር ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን  የአሉባልታ ሰለባ ቢሆን ወይም አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የአሉባልታ አራማጅ ቢሆን የጉዳቱ መጠን ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ህብረተሰብን ለማስተማር፣ የህብረተሰብን አስተሳሰብ ለመቅረፅ የተቋቋመ መገናኛ ብዙኃን የአሉባልታ ሰለባ ሲሆን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው የፕሬሱን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመጽሃፌ የጠቃቀስኩት። በጋዜጣ የተፃፈ፣ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የተነገረ ነገር ሁሉ እውነት መስሎ የሚታየው የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ በአፍሽ ስትነግሪው ውሸት የሚመስለው ነገር፣ በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ፣ እውነት የሚመስለው ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ችግሩ ፕሬሱ ውስጥ አለ፣ ፓርቲዎቹ ውስጥ አለ፣ ህብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ አሉባልታውን የማቀባበሉ ሚና፣ ከአንዱ ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃን ከዚህ ካልፀዱ፣ አንድ አገር ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡
 በአገሪቱ ያለውን ፕሬስ እንዴት ያዩታል?
እንግዲህ ሁሉ ነገር እኛ አገር ላይ ገና ነው፡፡ ያለን የፖለቲካ ባህል በጣም ኋላቀር ነው፡፡ በዚህ ኋላቀር ባህል ውስጥ ሆነን ሚዲያው ለብቻው ተለይቶ፣ ከችግር ነፃ ሆኖ ሊያድግ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሚዲያ ከችግር የፀዳ ሆኖ እንዲወጣ አልጠብቅም፡፡ ቁጥሩ አነሰም በዛም በሚጠበቀው ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ ይህን ስል ሁሉም ፕሬሶች ተመሳሳይ ድክመትና ችግር ነበረባቸው ማለት አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት የተሻለ የሚሰሩ ነበሩ፤አሁንም አሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዳይሸጋገር፣ የፖለቲካ ባህላችን እንዳያድግ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙኃን፣ በተለይ ነፃው ፕሬስ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፕሬሱ ሚና መረጃ ማቀበልና መቀበል ብቻ አልነበረም፤አጀንዳ ቀርፆ ለፖለቲካ ሀይሎች የማቀበልም ሚና ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁን የፕሬስ ውጤቶችን  ያነባሉ?
አልፎ አልፎ አነባለሁ፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ ወይም በፖለቲካ ፓርቲ ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንዲህ አይነት ፅሁፍ ወጥቷል አንብብ ቢሉኝ እመርጣለሁ፡፡ እንደ በፊቱ ሰፊ ጊዜ ወስጄ አላነብም፡፡ መፅሀፌ ላይ እንደገለፅኩት፣ እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን፣የፖለቲካ አስተሳሰባችን የተቀረፀው ኢህአዴግ እንደገባ በነበሩት የግል ፕሬሶች ነው፡፡ ያኔ ሁሉንም ትክክል ነው ብሎ የመውሰድ አዝማሚያ ነበረኝ፤  ትክክል እንዳልሆነ የተማርኩት በሂደት ነው፡፡
 በፖለቲካ እንቅስቃሴው ውስጥ “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” ያስባልዎት የተለየ ክስተት ምንድነው?
አሉባልታ በዚህ መጠን ችግርና ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ የተወሩብኝ ነገሮች እውነት እንዳልሆኑ እየታወቀና እየታየ እንኳን አልቆመም  ነበር፡፡ የተወራው ነገር ውሸት ለመሆኑ አንደኛ ምስክር ቅንጅት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው። አንዳቸውም ግን ምንም አላሉም፡፡ ህብረተሰቡም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል አለማለቱ ይገርመኝና ያስደነግጠኝ ነበር። አሉባልታ አገር እንደሚያፈርስ ሩዋንዳ ላይ አይተናል፡፡ አሉባልታ አሁንም  በአገር ደረጃ የሚያሳስበኝ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ፖለቲካ ሲገቡ የሚያስቡት ችግር የመታሰር፣ ከስራ የመባረር ወይ የሞት ጉዳይ ነው፤አሉባልታን እንደ ችግር ብዙም አይቆጥሩትም፡፡ እኔ 22 አመት በትግሉ አሳልፌያለሁ፤ እንደ አሉባልታ በትግሉ ውስጥ ከባድ ነገር የለም፡፡ ትግሉንም በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳው አሉባልታ ነው፡፡    
ኢዴፓ የፓርቲዎች ህብረት፣ ውህደት---- የመሳሰሉ ስብስቦችን ለምንድን ነው ላለመቀላቀል የወሰነው?
በማንኛውም ጉዳይ በተናጠል ከመሄድ መተባባር ይሻላል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ችግሩ ምንድን ነው-- ይሄ አስተሳሰብ በተለይ ወደ ፖለቲካ ስንመጣ፣ሊሰራ እንደማይችል፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጥያቄ ማንሳት አይፈለግም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ወይም ትችት ማቅረብም ከፍተኛ የፖለቲካ ስህተት ተደርጎ ነው የሚታየው። መተባበር ጥሩ ሀሳብ ነው፣ ግን በተጨባጭ ጉዳዩን እንለካው ከተባለ በተቃዋሚው ውስጥ የህብረት ጥያቄ፣ ትግሉን የጠቀመ ሳይሆን በጣም የጎዳ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ባይኖር ይሻል ነበር፡፡ የህብረት ጥያቄ ባይኖር ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ሁለት ወይ ሶስት ጠንካራ ፓርቲዎች ተፈጥረው እናይ ነበር። የህብረት ጥያቄ ትግሉን ለማጠናከር ከፈየደው በላይ በህብረት ስም አንዳንድ ግለሰቦች የራሳቸውን የፖለቲካ ተሰሚነት ወይም ተቀባይነት ለማግኘት የሚጠቀሙበት አጀንዳ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ህብረቱ ወይ የሚፈለግበትን አላሳካ ወይ በተናጠል የሚታገሉ ፓርቲዎች ራሳቸውን አጠናክረው እንዲያወጡ እድል አልሰጠም፡፡ እንዲያውም አንድ ጠንካራ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚችል ፓርቲ ሲፈጠር፣ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ነባር ፓርቲዎች፣ የዚያን ፓርቲ እንቅስቃሴ ማፈን የሚችሉበት ስልት ነው የታየው፡፡ ጉዳዩ መዘጋት የሌለበት ቢሆንም በደንብ መጤን ያለበት ነው፡፡ የእንተባበር ጥያቄ የድክመት መሸፈኛ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረት ለመፍጠር መጀመሪያ ጠንካራ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል አንድ ላይ መቆም የሚለው አስተሳሰብም የተሳሳተ ነው፡፡ ለመተባበር የሚፈልጉ ቢያንስ መሰረታዊ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው፡፡ ውህደት መፍጠር በራሱ ግብ አይደለም፡፡
ተቃዋሚዎች እርስበርሳቸው፣ እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ውዝግብ እንዴት ያዩታል?
በኔ እምነት ትግሉን በጣም የሚያዳክመው በራሱ በተቃዋሚው ጎራ ያለው ችግር ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ  ስልጣኑን መልቀቅ አይፈልግም፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሩ አመለካከት የለውም፤ስለዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲዳከሙ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ እንደዚህ አይነት ባህርይ ያለው ገዢ ፓርቲ እንዳለ እናውቃለን፡፡ የኛ ጥንካሬ የሚለካው ይህንን ተፅዕኖ ተቋቁመን በመውጣት ነው፡፡ ልንፈትነው እንዳንችል ያደረገን የውስጥ ችግራችን ነው፡፡ ክፋቱ ግን አብዛኛው ተቃዋሚ ይህንን አያምንም፤ ሁልጊዜ በውስጡ ያለውን ችግር ውጫዊ አድርጎ ነው የሚያቀርበው፡፡ ከምንሰራው ድርጅታዊ ስራ ይልቅ ትኩረት የምንሰጠው ለፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ራሳችንን የመገምገም ባህርይ የለንም፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራር ነው የምንከተለው፡፡ ገዢው ፓርቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን አላመጣም እንጂ ራሱን በደንብ የሚገመግምበት ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለው፡፡ ኢህአዴግ እያዳከመን ነው ሲባል ዞሮ ዞሮ የራስን ድክመት መናገር ነው፡፡ ችግሩ ከውጫዊው ይልቅ ውስጣዊ ነው፡፡ ራሳችንን እንገምግም ስትይ፣ ለኢህአዴግ ጥቅም እየሰራሽ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ይወዳደራሉ?
ፓርቲዬ ይወዳደራል፣እኔ አልወዳደርም፡፡
 ከግንቦቱ አገራዊ ምርጫ ምን ይጠብቃሉ?
ተቃዋሚው ያለበትን ሁኔታና የኢህአዴግን አካሄድ ሳየው፣ ካለፈው ምርጫ የተለየ ውጤት ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ምርጫውን በራሱ ቁጥጥር ስር አድሮጎ እንደቀጠለ ነው፣ ተቃዋሚው ጎራም ካለፉት ስህተቶቹና ችግሮቹ ተምሮ ራሱን አጠናክሮ የተሻለ ውጤት ለመያዝ የሚያደርገው ነገር ብዙም የለም፡፡ ድፍረት አይሁንብኝና ተቃዋሚው ጎራ ያለችውን አንድ መቀመጫ አስጠብቆ ይቀጥላል ወይ የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ሂደቱ መቀጠል ስላለበት ተሳትፎ ማድረጉ አስፈላጊ ቢሆንም በዚህ ምርጫ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ አንድ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚያደርስ ውጤት አልጠብቅም፡፡ ይህ የግል ግምቴ ነው፣ ውጤቱን እናያለን፡፡
በመጀመሪያዎቹ የትግል አመታት በጎጃምና ወሎ አዋሳኝ ቦታ ላይ ተጀምሯል የተባለ የትጥቅ ትግል ለማየት ወደ ገጠር ሄደው እንደነበር በመጽሃፉ ገልጸዋል፡፡ የትጥቅ ትግል ለመጀመር አስበው ነበር?
ብዙ ሰዎች ባለፈ ታሪካቸውና አስተሳሰባቸው ያፍሩ ይሆናል፤ እኔ በግልፅ ነው ያስቀመጥኩት። በወቅቱ ያን አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ የቀረፀኝ ሁኔታ ነበር፡፡
ትግሉን በተቀላቀልኩ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወይም አራት አመታት የነበረኝ አስተሳሰብ በጣም አውዳሚ ነበር፡፡ በስልት ደረጃ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በማንኛውም መንገድ መወገድ አለበት ብዬ ነበር የማምነው፡፡ ይህን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነበርኩ፡፡
የወጣቶች ካውንስል አባል በነበርኩበት ወቅት ራስን አቃጥሎ በስርአቱ ላይ ያለውን ብሶት በማሳየት፣ ህዝቡን ማነሳሳት ይቻላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡
ከነፍሰገዳይ ጋር የትጥቅ ትግል አለ በሚል የሄድኩትም በዚያ ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ላይ ሳየው ስህተት ቢሆንም ተምሬበት ያለፍኩበት ነው፤ እኔ ይህን ያደረግሁት ከአስራ አምስት አመት በፊት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላሳ እና አርባ አመት አሳልፈው፣እኔ ከዛሬ 15 አመት በፊት የነበረኝ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይህ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡  

የተረት - አባት የሆነው ኤዞፕ እንዲህ ይለናል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ተኩላዎች ተመካከሩና መልዕክተኞች ወደ በጐች ላኩ፡፡
የተኩላዎቹ ልዑካን እበጐች መንደር ደረሱ፡፡ በጐች ተኩሎች መጡብን ብለው ተሸሸጉ፡፡ አድፍጠው ጋጣቸው ውስጥ አድብተው ተቀመጡ፡፡ ተኩሎቹ ግን ረጋ ብለው፣ አደብ ገዝተው፤ “በጐች አትደናገጡ” “እንደምና ዋላችሁ” አሉ፡፡
“ድርድር ነው የመጣነው” አሉ ተኩሎቹ፡፡ በጐቹ ቀስ በቀስ ከተደበቁበት ወጡ፡፡
“እኛ በድርድር እናምናለን፡፡
እህስ? ምን እግር ጥሏችሁ መጣችሁ? ምን የድርድር ሃሳብ ይዛችሁ መጣችሁ?” አሉ በጐች፡፡
“አንድ የቸገረ ነገር ገጥሞን ነበርና ልናዋያችሁ ፈልገን ነው”
“ምንድነው? ከተመካከርን የማይፈታ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ዋናው ተቀራርቦ መነጋገር ነው ንገሩን፡፡”
ተኩሎችም፤
“እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡ የቸገረን ነገር ምን መሰላችሁ? ይኸው ከተፈጠርን ጀምሮ ከውሾች ጋር ነጋ - ጠባ እንታገላለን፡፡ የችግራችን መነሻም መድረሻም ውሾች ናቸው፡፡ እርኩስ ውሾች እኛን ባዩ ቁጥር ይጮሃሉ፡፡ ይተነኩሱናል፡፡ ሠፈር ይረበሻል! ለእኛ ለእናንተ ወዳጅነትና ሰላም ዋናዎቹ እንቅፋቶች ውሾች ናቸው፡፡”
በጐችም፤
“ታዲያ ምን እናድርግ? ምን ዘዴ ብንፈጥር እንቅፋቶቹን ማስወገድ እንችላለን?”
ተኩሎችም፤
“እናንተ እሺ ካላችሁማ ዘዴ አይጠፋም ነበር”
“እኮ ዘዴ ካለ ነገሩና?”
“ለጌታችሁ ንገሩ፡፡ ውሾች እንዳልተመቿችሁ፣ ሰላምም እንደነሷችሁ አስረዱ፡፡ ይባረሩልን በሉ!”
“ይሄማ ቀላል ነው፡፡ እንነግረዋለን፡፡”
በዚህ ተስማሙና ተኩሎቹ ሄዱ፡፡
በጐቹ፤ ውሾቹ እንዲባረሩ ለጌታቸው አመለከቱ፡፡ ጌታቸውም ስንት ዘመን ቤት - ደጁን ይጠብቁ የነበሩትን ውሾች ከቤት አስወጥቶ አባረራቸው፡፡
ከዚያን ቀን በኋላ፣ የዋሆቹ በጐች የዘመናት ጠባቂዎቻቸውን አጡ፡፡ ተንኮለኞቹ ተኩሎች እየተዝናኑና በጐቹን አንድ በአንድ እየለቀሙ፤ በሏቸው፡፡
*   *   *
የድርድርን ትርጉም አለማወቅ እርግማን ነው፡፡ ከማን ጋር ነው የምደራደረው? ተደራዳሪዬስ ሊደራደረኝ ያሰበው ምን አስቦ ነው? ጠላቴ እንኳ ቢሆን ድርድሩ ያዋጣኛል ወይ? ከቅርብ ጊዜ ግቤ አንፃር ምን እጠቀማለሁ? ከዘለቄታ ግቤ አንፃርስ ምን እጠቀማለሁ? ትላንትና ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ዛሬስ? ዛሬን በዛሬው ክስተት መዳኘት እንዴት እችላለሁ? ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡
በሁለኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካው ጄኔራል ማካርተር በፊሊፒንስ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ተደርጐ ሲሾም አንድ ረዳት መኰንን አንድ መጽሐፍ ይሰጠዋል፡፡ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም የነበሩት አዛዦች የዋሉባቸውን ጦርነቶች ዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ማካርተር “የዚህ መጽሐፍ ስንት ቅጂ አለ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ረዳቱም “ስድስት አሉ” አለው፡፡ ጄኔራሉም “መልካም፡፡ በል ስድስቱንም መጽሐፍት ሰብስበህ አቃጥልልኝ፡፡ እኔ የትላንትና ውሎዎች ባሪያ መሆን አልፈልግም፡፡ ችግር ሲከሰት እዛው ወዲያውኑ መፍትሔ እሰጠዋለሁ፡፡ መጽሐፍቱን በሙሉ አቃጥልና ሁኔታዎች በተከሰቱ ሰዓት እንደ ሁኔታው ግዳጅህን ፈጽሞ” አለው፡፡ ታሪክ የራሱ ዋጋ ቢኖረውም ያንን እንደ ተመክሮ መውሰድ ተገቢም፣ ደንብም ነው፡፡ በትላንት ለመመካት ከሆነ ግን የግብዝ አመድ - አፋሽ መሆን ነው!
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፣ ተው ነው መጀነኑ በቅቶን
ጉራ መንዛት መዘባነን፣ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!” ይለናል ኦቴሎ የሼክስፒሩ፤
በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሣን! ስለታሪክ፣ ስለትላንት ማውራት ሳይሆን ዛሬን ማሸነፍ ነው የፖለቲካ ፋይዳው! ይሄን ያወቁ ላቁ! ይሄን የናቁ ወደቁ! እንደማለት ነው፡፡
ከ1966 ጀምሮ የተከሰቱ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አበሳዎች፤ እከሌ ከእከሌ ሳይባል በትንሹ አሥር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የተንተራሱ ይመስላሉ፡፡ ከአበሳዎቹ፤ አንደኛው/ በትንሽ በትልቁ መከፋፈል፣ ያለመስዋዕትነት ድል መመኘት፣ ውሎ አድሮ ጧት የማሉበትን ማታ መካድ፡፡ “ዕምነት ሲታመም፣ ሺ ወረቀት መፈራረም” ነው፡፡ 2ኛው/ ለባላንጣቸው ሠርጐ - ገብነት መጋለጥ ነው፡፡ 3ኛው/ እርስ በርስ አለመከባበር፣ አለመተሳሰብ 4ኛው/ የመስመር ጥራት አለመኖር ርዕዮተ - ዓለማዊ ብስለት ማጣት  5ኛው/ በትንሽ ድል መወጣጠርና በትንሽ ሽንፈት መፍረክረክ 6ኛው/ ተጋጣሚን መናቅና ወሬን/አሉባልታን እንደ አቋም ወሱድ 7ኛ/ የጊዜን ፋይዳ በትክክል መረዳት፣ ባልፈውስ? አለማለትና የኃይል ሚዛን የማን ነው አለማለት፣ ከተፈፀመም አለመመዘን፣ ይሄ ዓላማ ባይሳካ ምን ሁለተኛ ዘዴ ቀይሻለሁ? ብሎ አለመዘጋጀት፡፡
8ኛው/ ባለፈው ያረግነው የት አደረሰን? ታሪኩ ተተንትኖ ተገምግሞ ሳያልቅ በነዚያው ተዋንያን ተውኔቱ መቀጠሉ 9ኛው/ እምቢ አላረጅም ማለት ነው፡፡ አዲሱ ያሸንፈኛል አለማለት The new is invincible የሚለውን መርሳት “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለት፡፡ 10ኛው/ እኔ ባልሆንስ መፍትሔው? ሌላ ቢኖርስ ከኔ የተሻለ አለ ብሎ ፈጽሞ አለማሰብ…
ከነዚህ ሁሉ ይሰውረን፡፡ እነዚህን ሁሉ ከልብ ከመረመርን ፓርቲዎቹ ሁሉ የቆሙት በአንድ ወይም በጥቂት ቡድን ሐብለ ሠረሠር (Spinal cord) ዙሪያ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሚሆነው፤
“ከተኳሾቹም - አሉ በልዩ
ማህል - አገዳ የሚለያዩ”
በምንልበት አገር ነው፡፡ ከፖለቲካ ንቃተ - ባህሉ (ትምክህቱ ጥበቱ፣ ዕምነቱ፣ የፖለቲካ ጥንቆላው፣ ሟርቱ ወዘተ) ባለበት አገር ልማድን አለመመርመር ጦሱ ብዙ ነው፡፡ አጠቃላይ የፖለቲካ ተመክሮአችን ገና አልተፈተሸም፡፡ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይላል ያበሻ አባባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ግንዱ ሲመታ ቅርንጫፉና ቅጠሉ መርገፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቻይናዎቹ “ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” የሚሉን መሠረታዊ ነገር የሚሆነው ለዚህ ነው! “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” የሚለውም የትግሪኛ ተረት አዙረን ስናየው እንደቻይናዎቹ ነው!!