Administrator

Administrator

 በመላው አለም እስከያዝነው ሳምንት አጋማሽ ድረስ ከ5 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ለተጠቃሚዎች መሰጠታቸው ቢዘገብም፣ ብሩንዲ፣ ኤርትራና ሰሜን ኮርያ ገና አሁንም ድረስ የክትባት መርሃግብር አለመጀመራቸው ተነግሯል፡፡
እስካሁን በአለማቀፍ ደረጃ ከተዳረሰው 5 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ክትባት ውስጥ ወደ ግማሽ የሚቃረበው ወይም 1.96 ቢሊዮን ያህሉ በቻይና መሰጠቱን የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ህንድ 589 ሚሊዮን፣ አሜሪካ ደግሞ 363 ሚሊዮን የኮሮና ክትባቶች የተሰጡባቸው ተከታዮቹ የአለማችን አገራት መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
ካላቸው አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንጻር ብዛት ያላቸውን ሰዎች በመከተብ ደግሞ፣ ከአለማችን አገራት መካከል የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ኡራጓይና እስራኤል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን አመልክቷል፡፡


    በቅርቡ በተካሄደው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ቻይናን ወክለው በመወዳደር ያሸነፉ 2 አትሌቶች የተሸለምናቸው የወርቅ ሜዳልያዎቻችን ገና አንድ ወር እንኳን ሳይሞላቸው መላላጥ ጀምረዋል ሲሉ በአዘጋጅ ኮሚቴው ላይ ክስ መመስረታቸው ተነግሯል፡፡
ክሱን በማህበራዊ ድረገጽ ባስተላለፉት መልዕክት ያደረሱት በውሃ ዋና እና በጂምናስቲክ አገራቸውን ወክለው በተሳተፉበት ኦሎምፒክ አሸንፈው የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለሙ ቻይናውያን መሆናቸውን የዘገበው ግሎባል ታይምስ ድረገጽ፣ የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው ተወካዮች በበኩላቸው ምናልባት መላላጡ የተፈጠረው ሜዳሊያዎቹን ለመጠበቅ ታስቦ በተቀባው ነገር ሳቢያ ሊሆን ይችላል ሲሉ ማስተባበላቸውን ገልጧል፡፡
አትሌቶቹ በሜዳሊያዎቹ ጥራትና ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ ካደረባቸው አስፈላጊውን አቤቱታ ለሚመለከተው አካል በማቅረብና ተገቢውን ክፍያ በመፈጸም ተተኪ ሜዳሊያ ማግኘት እንደሚችሉ ኮሚቴው መግለጹንም ዘገባው አክሎ አስነብቧል፡፡

     በአፍሪካ አገራት ላይ የሚፈጸሙ የኢንተርኔት ጥቃቶች መጨመራቸውንና በአህጉሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ85 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አይነት የኢንተርኔት ቫይረስ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ካስፔርስኪ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ጥናት አመልክቷል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከአፍሪካ አገራት መካከል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢንተርኔት ቫይረሶች ጥቃት የተፈጸመባት ቀዳሚዋ አገር ደቡብ አፍሪካ መሆኗን የጠቆመው ጥናቱ፣ በአገሪቱ 32 ሚሊዮን ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ገልጧል፡፡
ኬንያ በ28.3 ሚሊዮን ጥቃቶች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ናይጀሪያ በ16.7 ሚሊዮን ጥቃቶች፣ ኢትዮጵያ በ8 ሚሊዮን ጥቃቶች ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
ከኬንያ በስተቀር በሁሉም የአፍሪካ አገራት የኢንተርኔት ቫይረስ ጥቃቶች ጭማሬ ማሳየታቸውን የሚገልጸው ጥናቱ፣ በናይጀሪያ ከፍተኛው የ23 በመቶ ጭማሬ ሲመዘገብ፣ በኢትዮጵያ የ20 በመቶ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ የ14 በመቶ ጭማሬ መታየቱን ያትታል፡፡
በ2021 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያው መንፈቅ በአፍሪካ የተፈጸሙት ጥቃቶች ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን የጠቆመው ጥናቱ፣ ለዚህም በምክንያትነት የጠቀሰው የኢንተርኔት ወንጀለኞችና መረጃ መንታፊዎች በአፍሪካ አገራት ያለውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋትና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቤታቸው ሆነው በኢንተርኔት አማካይነት ስራቸውን የሚያከናውኑ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን በማጤን በአገራቱ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ነው፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሚያሳራጯቸው ቫይረሶችና አደገኛ ሶፍትዌሮች ወደተጠቃሚዎች ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፖችና ሞባይል ስልኮች በተለያዩ መንገዶች እንደሚገቡ የጠቆመው ጥናቱ፣ ይህን ለመከላከልም ተጠቃሚዎች የማያውቋቸው ሰዎች የሚላኩላቸውን አጠራጣሪ ኢሜይሎችንና ሊንኮችን እንዳይከፍቱና ዳውንሎድ እንዳያደርጉ፣ ጸረ-ቫይረስ ፕሮግራሞችንና ሶፍትዌሮችን ዘወትር እንዲጠቀሙ፣ አፕሊኬሽኖችን ከታማኝ ድረገጾች ብቻ እንዲያወርዱ እንዲሁም ኦፐሬቲንግ ሲስተሞቻቸውንና አፕሊኬሽኖቻቸውን በየጊዜው እንዲያዘምኑ ወይም እንዲያድሱ ይመክራል፡፡

   በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ችግኙን ገዝቶ ተክሎ፣ አርሞና ኮትኩቶ፣ ውሃ አጠጥቶ ያሳደገውን የገዛ ዛፉን የከረከመ አንድ የእድሜ ባለጸጋ  ከሚመለከተው የመንግስት አካል ፈቃድ አልጠየቀም፤ የአገሪቱን የአረንጓዴ ልማት መመሪያዎች ጥሷል ተብሎ የ21 ሺህ 500 ዶላር ቅጣት እንደተላለፈበት ተዘግቧል፡፡
ሊ የተባለው የ73 አመት ጡረተኛ መምህር ከ20 አመታት በፊት በግቢው የተከለውን የገዛ ዛፉን ለማሳመርና ለመንከባከብ በማሰብ ሰራተኞችን ቀጥሮ ቅርንጫፎቹን በመቀስ አስከርክሟል በሚል የተጣለበት እጅግ የተጋነነ የገንዘብ ቅጣት ቻይናውያንን በእጅጉ እያነጋገረ እንደሚገኝ የዘገበው ሲሲቲቪ፣ ግለሰቡ ቅጣቱን ቢቃወሙትም መክፈላቸው እንዳልቀረ አመልክቷል፡፡
‹እንዴት ይሄን ያህል ገንዘብ ሊቀጡኝ እንደቻሉ አልገባኝም! አንደኛ ነገር ጭራሹን ቆርጬ አልጣልኩትም፣ ቅርንጫፉ ያለቅጥ ሲንዠረገግ ነው ያስከረከምኩት፡፡ ደግሞም በችግኙ ገንዘቤን አውጥቼ የተከተልኩትና ተንከባክቤ ያሳደግኩት ዛፍ ነው› በማለት አዛውንቱ ቅጣቱን መቃወሙም ተነግሯል፡፡

    በመላው አለም የሚገኙ ከተሞችን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም በየሁለት አመቱ የደህንነት ሁኔታ ደረጃ የሚሰጠው የኢኮኖሚስት መጽሄት የምርመራ ክፍል፣ ሰሞኑን ባወጣው የ2021 አመት ሪፖርቱ የዴንማርክ መዲና ኮፐንሃገንን በደህንነት አቻ የማይገኝላት የአለማችን ከተማ ሲል በአንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
የጤና ደህንነት፣ የመሰረተ ልማት ደህንነት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ደህንት፣ የግለሰባዊ አኗኗር ደህንነትና የአካባቢ ደህንነት በሚሉ አምስት ዋነኛ ማንጸሪያዎች በ76 መስፈርቶች ተጠቅሞ የ60 ታላላቅ የአለማችን ከተሞችን አጠቃላይ ሁኔታ ገምግሞ ደረጃ የሰጠው ተቋሙ ከሰሞኑ ባወጣው አዲስ ሪፖርቱ እንዳለው፣ ኮፐንሃገን 82.4 ነጥብ ከ100 በማምጣት ነው አንደኛ ደረጃን ለመያዝ የበቃችው፡፡
የካናዳዋ ቶሮንቶ፣ የሲንጋፖር ሪፐብሊኳ ሲንጋፖር፣ የአውስትራሊያዋ ሲድኒና የጃፓኗ ቶኪዮ እንደቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ከተሞች ሲሆኑ፣ አምስተርዳም፣ ዌሊንግተን፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሚልበርንና ስቶክሆልም እስከ አስረኛ ደረጃ ለመያዝ ችለዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በሪፖርቱ ከተካተቱ የአለማችን ከተሞች መካከል በደህንነት እጅግ አነስተኛውን ደረጃ የያዘችው የናይጀሪያዋ ሌጎስ ስትሆን፣ ካይሮ፣ ካራካስ፣ ካራቺና ያንጎን ይከተሏታል፡፡


  • 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው በድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ
          • ሲአይኤ እና ታሊባን በድብቅ መወያየታቸው ተነግሯል


             ታሊባን ከ20 አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ዳግም ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ በነበሩት ያለፉት ሳምንታት ብቻ 2.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከአፍጋኒስታን ሸሽተው መውጣታቸውንና ሌሎች ተጨማሪ 3.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በድንበር አካባቢዎች እንደሚገኙ መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋትና መጪው ጊዜ ያሰጋቸው እጅግ በርካታ አፍጋኒስታናውያን ወደ ጎረቤት አገራት ለመሰደድ የካቡል አውሮፕላን ጣቢያን ባጨናነቁበትና በድንበር አካባቢዎች በሚንከራተቱበት የጭንቅ ሰሞን፣ የድንበር መስመሮችን በጥብቅ ቁጥጥር ስር ያዋለው ታሊባን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ጥብቅ መግለጫ አፍጋኒስታናውያን አገራቸውን ጥለው መውጣት እንደማይችሉ ማስጠንቀቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ታሊባን ወደ አፍጋኒስታን መመለሱን ተከትሎ ከአገሪቱ የተሰደዱ ሰዎችን በብዛት በመቀበል ቀዳሚነቱን በምትይዘው ጎረቤት አገር ፓኪስታን 1.5 ሚሊዮን ያህል አፍጋኒስታናውያን እንደሚገኙ ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ከሰሞኑ 780 ሺህ ያህል ስደተኞችን የተቀበለቺው ኢራንም በግዛቷ የምታስተናግዳቸው አጠቃላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ቁጥር ወደ 3.5 ሚሊዮን ማድረሷን ጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሜሪካውያን ወታደሮች እስከ መጪው ማክሰኞ ድረስ አፍጋኒስታንን ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው እንደሚወጡ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ጦሩ ጥቂት እንዲቆይ በአሜሪካ ላይ ጫና ማድረግ በጀመሩበት በዚህ ሰሞን፣ የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ ዋና ዳይሬክተር ዊሊያም በርነስ አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረው ታሊባን መሪ ሙላህ ባራዳር ጋር በመዲናዋ ካቡል ሚስጥራዊ ውይይት እንዳደረጉ እየተዘገበ ነው፡፡
ሁለቱ መሪዎች በሚስጥር እንደተወያዩ የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን አሶሼትድ ፕሬስ ቢዘግብም፣ ከሁለቱም ወገን በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለመሰጠቱ የተነገረ ሲሆን፣ ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ ምናልባትም ውይይቱ የአሜሪካ ወታደሮች ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአፍጋኒስታን ይወጣሉ በተባለው ጉዳይ ዙሪያ ያተኮረ ሊሆን እንደሚችል አስነብቧል፡፡
የታሊባን ቃል አቀባይ ባለው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተቀጥረው የሚሰሩ የአገሪቱ ሴቶች ለደህንነታቸው አስጊ ያልሆነ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ከቤታቸው እንዳይወጡ የቡድኑ ቃል አቀባይ ማስጠንቀቃቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡


Saturday, 28 August 2021 14:04

ማራኪ አንቀፅ

       …..ቤተልሔም ባሏን በመግደል ወንጀል ተጠርጥራ እነሆ ዛሬም ለሰባተኛ ቀን በእስር ላይ ነች፡፡ የታሰረችበት ክፍል ስምንት የሚሆኑ ሴቶች ያሉበት ሲሆን፤ ክፍሉ ከሌሎች ክፍሎች በስፋቱ ትንሽ ሻል ያለ ነው፡፡ አብረዋት ያሉ ታሳሪዎች ከሦስቱ በስተቀር የተማሩና ደህና የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ከቤተልሔም ቀኝ የምትተኛው ቀጭኗ ሴትዮ ሐኪም ናት እየተባለ ይወራል። ከቤተልሔም ቀጥላ የምትተኛው ሴትዮ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣን እንደሆነች የተወራው ወሬ አብዛኛው የክፍሉ አባላት ተስማምተውበታል፡፡ ክፍሉ ከንፋስ እጥረት የተነሳ እምክ እምክ እንዳይል፣ ቀን ቀን በደንብ ስለሚከፈት ብዙም የማያጨናንቅ ነው፡፡ ማታ ላይ ግን ብርዱ፣ ጨለማው፣ የቤተልሔም ተደጋጋሚ ቅዥት አንድ ላይ ተዳምሮ ክፍሉ እጅግ እንዲያስጠላ አድርጎታል፡፡
ዛሬም ሴቶች ሲያወሩ ቆዩና ወደ አምስት ሰዓት ገደማ እንተኛ ተባብለው  ሻማቸውን አጠፉ፡፡ ሻማው እንደጠፋ ቤተልሔም ከመቼውም ማንኮራፋት እንደጀመረች ሁሉም ገርሟቸዋል፡፡ ትንሽ ሳትቆይ  ያንን የቅዠት ድምጿን ማሰማት ጀመረች፡፡
“ጥፋቱ የኔ ነው፡፡ አዎ! የኔ ነው፡፡ አንተን አስቀርቼ እኔ ግን ጥዬህ ሔድኩኝ….” እያለች ዛሬም እንደወትሮዋ ትቃዣለች፡፡
ከሳምንት በፊት፣ቤተልሔም ከአባቷ ቤት ቁጭ ብላ ወንድሟ የሚያወራላትን የጅል ወሬ እየሰማች ሳለ ነው የወንድሟ ስልኩ የጠራው፡፡
“አቶ ይሀይስ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሏል ቶሎ ድረሱ፡፡” አለ በስልኩ በዚያኛው ወዲያ የሚያወራው ሰው፡፡
የዛሬ ዓመት ጀምራ በስርዓቱ የምታናግረው ወንድሟ፣ ሊያግባባትና ያስቀየማትን ነገር ይቅር እንድትለው ከስሯ በማይጠፋ በዚህ ሰዓት፣ ስልኩ እንዴት ሲጠራ ፈጥኖ አነሳው፡፡ የመርዶ መልዕክቱን ሲቀበል እሷ እንዳትሰማና እንዳትደናገጥ ያደረገው አንዳች ጥንቃቄ አልነበረም። የሚሰማውን ነገር እሷም እንዳትሰማ የማድረጉ አስቀያሚነት ዛሬም ድረስ አልገባውም፡፡
የሰማው ነገር እንዳለ ሲነግራት መጀመሪያ አጥወለወላት፣ እግሮቿ ዛሉና መሬት ሲርቅባት ተሰማት፡፡ አስደንጋጩን መርዶ እንደ ቀልድ ተናግሮ እህቱ በድንጋጤ ስትጮኽ፣ ስትወድቅና አናቷ በጠረጴዛው ጫፍ ሲነረት ሲያይ፤ የሚያደርገው ጠፍቶት ክው ብሎ እንደደነገጠ ቆሞ ቀረ፡፡
“ልጄን…!” ብለው አባቷ ከውጭ ዘለው ሲገቡ፣ እሱ በድንጋጤ ባለበት ደንዝዟል፡፡ የሚለው ሲጠፋ በጅል ድምጹ “ወደቀችና ጠረጴዛው አናቷን መታት፡፡” አለ፡፡
ከሐዘኗ በተጨማሪ፣ ድንጋጤና የተመታው አናቷ፣ ዛሬ ለተከሰተው የአንጎል እጢ መንስኤ ነበር፡፡ ታማ የጣዕር ሆስፒታል እስከገባችበት ጊዜ ድረስ፣ የአንጎል እጢው  በመላው አካላቷ ለተሰራጨው ኢንቬክሽን ዋና ምክንያት ሆነና የሞት ጣዕር ስቃይ ማስተካከል መጀመሩን ማንም አያውቅም ነበር፡፡
የአሜሪካ ዜግነት ያለው አቶ  ይሀይስ ማን እንደገደለው ሣይታወቅ ተግድሎ ሲገኝ ፖሊስ የተጠረጠረውን ሁሉ አፍሶ እስር ቤት አጎረ፡፡ ቤተልሔምም አንድ ሳምንት ያህል ለምን ተለይታው አባቷ ቤት ታድር ነበር የሚል ጥያቄ ተነሳና ተጠርጥራ እሷም ታሰረች፡፡ የዕጢው ህመም አንዳንድ ቀላል ምልክቶች ማሳየት የጀመረው እስር ቤት በገባችበት በአንደኛው ሳምንት አካባቢ ነው።
ህመሙ ማታ ማታ ይብስባትና በእንቅልፍ ልቧ ክፉኛ ያስቃዣታል፡፡ በአብዛኘው የባሏን በድን ወለሉ ላይ ተዘርሮ ያየችበትን ሁኔታ በህልሟ ይመጣባታል፡፡ ይህን አስፈሪ ትዕይንት ሲታያት በድንጋጤ እየጮኸች ከእንቅልፏ ትባንናለች፡፡
እንደምንም ራሷን አረጋግታ እንቅልፍ ሸለብ ያረጋትና ትንሽ እንደቆየች “እኔን ጥለህ ልትሄድ?!” ብላ ከሕይወት ጉዞው ያስቆመችውን ሰው ደግሞ በህልሟ ይመጣባትና በድንጋጤ ትባንናለች። ከእንቅልፏ ባንናም ዓይኖቿን ገልጣ ከሰዎች ጋር ማውራቱ ስለሚያስጠላት ፀጥ ብላ ሰዎች ስለ እርሷ የሚያወሩትን ብቻ ትሰማለች፡፡ ዛሬም ያደረገችው ይህንኑ ነው፡፡
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ የሚሰማው ዜና ሁሉ የቅርብ አጋራቸውን በሞት ያጡ ሰዎች የሞት ወሬ ነው፡፡” ብለው ሴቶች ያወራሉ፡፡ ይህን ስትሰማ ገረማት፡፡
“ይህ ዓመት የፍቅረኛሞችና የትዳር አጋሮች ሞትን ተከትሎ መሞት እየተበራከተ የመጣበት ዓመት ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ግን ማንም አያውቅም፡፡” ትላለች፤ አንዷ ስለ ሟቾቹ  ይሀይስ ከፖሊሶች ሲወራ የሰማች ሴትዮ፡፡ ይህች ሴትዮ እስረኞችን ለመሰለል የታሰረች ሰላይ እንደሆነች ማንም ሰው አያውቅም፡፡
“የሞታቸው ዋና ምክንያት የፍቅር ልብ ስብራት ነው፡፡ በዚህ የሚወራረድ ካለ ሊወራርድ ይችላል፡፡” ብላ ትመልሳለች- የሰው አናት ፈንክታ የገባችው ታሳሪ፡፡
“በፍቅር የተሰበረ ልብ ለሞት ሊዳርግ አይችልም፡፡” በማለት ሴቶቹ ሁሉ የሚያስቡት አስተሳሰብ በመናቅ፤ መመፃደቅ ጀመረች፤ የወንዳወንድ ደምጽ ያላት ሌላኛዋ ጉልቤ ሴት፡፡
“በእውነቱ ግን የተሰበረ የእውነተኛ አፍቃሪ ሰው ልብ ፣ፍቅሩ ለመሞቱ ምክንያት ለምን አይሆንም?” በማለት፤ ቤተልሔም በልቧ ራሷን ጠየቀች፡፡
“ድሮ ድሮ፣በደጉ ዘመን ማንም ቢጠይቀኝ፤ መልሴ “አዎ የፍቅረኛዬ ሞት ልብ ለሞት ይዳርጋ የሚል ነበር፡፡ ፍቅረኛን የማጣት ሐዘን ለሞት መንስኤ ተደርጎ በስፋት ሲወሰድ ኖሯል፡፡ ከሠላሳ ዓመታት ወዲህ የሳይንስ ሊቃውንት እንዲህ ዓይነቱን የሚስኪን አፍቃሪያን  ሀሳብ ነው በማለት፤  ምክንያቱንም ውድቅ አድርገውት ነበር። ዛሬ ግን እንደገና ወደ ቀድሞ አስተሳሰብ በመመለስ፣ አዎ ሐዘን ለሞት ምክንያት ነው የሚለውን የሚቀበሉ ምሁራን አልፎ አልፎም ቢሆን ታይተዋል፡፡” አለች ዘአንዷ የህክምና ባለሙያ እንደሆነች በስፋት የሚወራላት ታሳሪ፡፡ ቀጠለችና፤
“ዛሬ በስፋት በተጠናቀሩ መረጃዎች ማለትም በሰነድ በተዘረዘሩ መጥፎ  የልብ ምት መዛባት ዜናዎች፤በሐዘን ምክንያ የሚከሰቱ ውጤቶችን በሚመለከቱ ጥናቶች ወይም በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋዎችና እንዲሁም በጭንቀትና በድብርት የሚመጡ የስሜት ቀውሶች በልብ ላይ ምን ያህል ተፅኖ እንደሚያሳድሩ በተሻለ መታወቅ ተችሏል፡፡” ብላ በልበ ሙሉነት ስታብራራ፣ ሴቶች ሁሉ ብዙ የማናውቀው ነገር ይኖራል ብለው ስላሰቡ ፀጥ ብለው ማዳመጣቸውን ቀጠሉ፡፡
“ምንም እንኳን የትዳር አጋር ሞት በቀናት አሊያም በሳምንት ውስጥ በሕይወት የተረፈው ሲሞት የሚተርኩ ታሪኮች ሲነገሩ አፈታሪክ ስለሚመስሉ ባይታመንም፤ታሪኮቹ ግን ብዙውን ጊዜ እውነትነት አላቸው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች በሕይወት የተረፈው የትዳር አጋር፣ የትዳር አጋሩን የሞት ዜና ሲሰማ፤ በድንጋጤ ብዛት ሲወድቁ ታይተዋል፡፡ በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ፣ ከሞት የተረፈው ሰው ለሞት የተዘጋጀ ህሊና ሲይዝና ሞትን በፅኑ ሲመኝ  ተሰምቷል፡፡” ብላ ስታብራራ፣ አንዷ ሴት ወደ ወንዳወንዷ ሴት ጆሮ ጠጋ ብላ  “ይህች ሴት እውነትም ሐኪም ነች፡፡” አለቻት፡፡
ምንጭ፡- (ሞት በውክልና የተሰኘ መፅሐፍ  የተቀነጨበ)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ መሰንቆውን ይዞ ያንጎራጉራል። ለአንድ ባለፀጋ ሰው ነው የሚገጥመው።
“የኔማ ጌትዬ  ዘረ መኳንንት
ስጋ አልበላም አለ ትከሻው ከብዶት…”
ጌትዬውም፤
“ይበል ይበል…
ንሳ አንተ አሽከር፣አንድ ብርሌ ስጠው…” አሉ።
አዝማሪው ብርሌውን ተቀበለ።  ጎርጎጭ፣ ጎርጎጭ አደረገና፤ እንደገና አቀነቀነ፡-
“አንተ ሰው ጥርስህን አኑረው በዋንጫ የሷው ይበቃል ለእህል ማላመጫ…” አለና ገጠመ።
“ይበል ይበል…
ንሳ አንድ ብርሌ ጨምርለት” አሉ ጌትዬው።
አዝማሪው ተቀበለና ግጥም አድርጎ ጠጣና፣ ማሲንቆውን በዕጣን አዋዛ። ከዚያም ቀጠለና፤
“አንተ ሰው ጥርስህን፣ አንቆርቁረው በቅል፤
እንዘራዋለን ምናልባት ቢበቅል” አለ ሞቅ አድርጎ።
ጌትዬውም በድምፁ ማማርና በዜማው አወራርድ እጅግ አድርገው ተደሰቱና፤
“ንሣ አንተ አሽከር አንድ እጀ-ጠባብ አምጣና ስጥልኝ…” አሉና ከጠጁ እሳቸውም ደጋገሙ።
እዝማሪው ፊቱን ወደ እመቤትዬው አዙሮ፤
“እሜቴ ጥሩወርቅ ውጪ ተከስሻል
እንዲህ ያለ መኳንንት ማን ውደጅ ብሎሻል”
*   *   *
“ጫማውን አውልቆ በእግሩ አይመጣም ወይ
አንቺ ልከሽበት ሊቀር ነበር ወይ?!”
ቀጥሎ
ወደ ጌትዬው ዞረና፡-
የአገር ሁሉ አዋይ
እሜቴ ሲጠሩ ዝም ይላሉ ወይ?
መውዜርዎ ሳያንስ
ጎራዴዎ ሳያንስ
ሽጉጥዎ ሳያንስ
ሻቦላዎ ሳያንስ
ምነው መርጠው ዋሉ፣ የዝምታ ድግስ?” አላቸው። ይሄኔ ጌትዬው እልህም የንሸጣ ስሜትም ተሰማቸውና፤
“ከንግግር በፊት የአርምሞ ዝምታ
ከጦርነት በፊት የዝግጅት ፋታ
ዛሬም የልባም ልጅ ያንድ አፍታ ፀጥታ።
ነገ ግን ይዋጋል መፋለሙ አይቀርም
ታሎ ያሸንፋል ጥርጥር የለኝም” ብለው አዝማሪውን ረቱት ይባላል።
ከልቡና አንቅቶ ቅፅበታዊ ምላሽ ለመስጠት መቻል ታላቅ ተሰጥኦ ነው። ይህን ዓይነቱ ክህሎት ከባድና የረዥም ጊዜ የአዕምሮ ዝግጁነት ይጠይቃል። ይህ ማለት ግን ለሁሉም በጥድፊያ ምላሽ ካልሰጠሁ ብሎ መሯሯጥ አይደለም። “የእነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ” የሚል ድንቅ ተረትና ምሳሌ አለመዘንጋት ነው! ብዙዎች ሁሉን በፍጥነት እንሰራለን ብለው፣ “ሲሮጡ የታጠቁት፣ ሲሮጡ ሲፈታባቸው” ተስተውለዋል።”
“Rome was not built a day “ የሚለውን አባባ በጥልቀት ማጤን ነው። “ሮሜም በአንድ ቀን አልተገነባችም” እንደ ማለት ነው። የሮማ አወዳደቅን ላወቀ የተባለ ጭንቅላት ያለው ሰው ከፍርስራሽም ውስጥ ቢሆን ህንፃ ሊያም እንደሚችል ያያል። ይህ ለሀገራችን ቁልፍና አመርቂ ልህቅና የሚያበረክት ዕውቀት ነውና የሁላችንን ማህበረ-ሱታፌ (Social Participation) የሚፈልግ ነውና ልብ ሊባል ይገባዋል።


    “የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሩን ያባብሰዋል

              የተባበሩት  መንግሥታት  ድርጅት  የፀጥታው  ምክር  ቤት  በሰሜን  ኢትዮጵያ  የተከሰተውን  ግጭት  በተመለከተ  ሐሙስ ነሐሴ  20 ቀን 2013  ዓ.ም ውይይት አድርጓል።
ምክር ቤቱ የትግራይ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለበርካታ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ በዝግና በይፋ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። የአሁኑ ስብሰባም በከፊል ክፍት የነበረ ሲሆን ከመጀመሪያው ዙር ውይይት በኋላ ውይይቱ በዝግ ተደርጓል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ቀውስ አስተያየት ሰጥተዋል። ማን ምን አለ?
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ከትግራይ ተነስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ቆሞ፣ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር መምጣት አለባቸው ሲሉ ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።
ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ በተደጋጋሚ የጠየቁት ዋና ጸሐፊው፤ በትላንቱ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤም ይህንኑ አቋም አንጸባርቀዋል።
“ሁሉም ወገን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁሞ ወደ ድርድር መምጣት አለበት። ስለ ኢትዮጵያ ሲሉ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ ማድረግ አለባቸው። ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል። የውጭ ኃይሎችም ከአገሪቱ መውጣት አለባቸው” ብለዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊትም ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ የጠየቁት ጉቴሬዝ፤ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደተነጋገሩና ራሱን የትግራይ ክልል ሕጋዊ አስተዳዳሪ እያለ የሚጠራው አካል የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደብዳቤ እንደላኩላቸው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከአፍሪካ ሕብረትና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ድጋፍ እንደሚሰጥ ጨምረው ገልጸዋል።
“ወታደራዊ ግጭት መፍትሔ እንደማያመጣ ሁሉም ወገኖች መገንዘብ አለባቸው” ሲሉም ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሸን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር በመጣመር እያካሄደ ያለው ምርመራ እየተጠናቀቀ እንደሆነ ጉቴሬዝ ጠቁመዋል።
ጉቴሬዝ ያነሷቸው ሦስት ቁልፍ ነጥቦች ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ተኩስ እንዲያቆሙ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ መንገድ አመቻችተው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች መልሰው እንዲከፈቱና በኢትዮጵያ የሚመራ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር ነው።
“የኢትዮጵያ አንድነትና የቀጠናው ሰላም አደጋ ውስጥ ወድቀዋል” ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከመስፋፋቱ ባሻገር ሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎች እንደገቡበትም አክለዋል።
“ነገሮችን የሚያቀጣጥል ትርክትና ብሔርን ተመርኩዞ ሰዎችን ኢላማ ማድረግ ተባብሷል። ሴቶችና ሕፃናትም ወሲባዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ይህን እጅግ በጣም አወግዛለሁ” ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ከሰብአዊ ቀውሱ ባሻገር የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እየተሽመደመደ መምጣቱንም ተናግረዋል። የአገሪቱ እዳ እየጨመረ፣ ብድር የማግኘት እድል እየቀነሰ፣ የዋጋ ንረት እየተባባሰ፣ መሠረታዊ ምግብ አቅርበት እያለቀ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁም ህወሓት እንዲቀበል ጫና መረደግ አለበት” ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮ በገንቢ መንገድ ብቻ አገሪቱን ማገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል።
“የእኛ ግብ ሰላም ነው። ህወሓት ግን በሰላምና በኢትዮጵያ መካከል ቆሟል። ህወሓት ተጎጂ ሳይሆን አጥቂ ነው” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲወርድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህወሓት ላይ ጫና እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ሰብአዊ እርዳታ በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ያለውን ፍተሻ ለመቀነስና ፍተሻውን በዘመናዊ መሣሪያ ለማድረግ ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሰብአዊ በረራ እንደተፈቀደም አክለዋል።
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የአሜሪካው ተወካይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስተጓጎል ከተቹ በኋላ ነው።
እንደ መብራትና ስልክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን መተመለከተ “አገልግሎቱ የሚጀመረው ሰላምና ሕግ ሲሲፍን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስና ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ለመስጠት ቢሆንም፤ ህወሓት ጦርነቱን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች አስፋፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ህወሓት የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ቡድኑ በአገሪቱ አለመረጋጋት እንደፈጠረና መንግሥትም ሰላም ለማስፈን ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ አስረድተዋል።
ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን ክስ በተመለከተ “ብሔርን መሠረት ያደረገ አድልዎ የለም። መርህ አለን። ለዓመታት ማኅበረሰባዊ መስተጋብራችን የቀጠለው ልዩነትን መሠረት አድርጎ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱን ውይይት አስመልክተውም “ጉዳዩን ማግነን እና ፖለቲካዊ ቅርጽ መስጠት የኢትዮጵያን መንግሥት ውሳኔ እንደማይለውጥ” አስታውቀዋል።
አሜሪካ
ለተኩስ አቁምና ለብሔራዊ ውይይት ጥሪ ቢደረግም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት እያንቀሳቀሰ መሆኑንና ህወሓትም ጥቃቱን ወደ አፋርና አማራ ክልል በማስፋት በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህም በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁት የአሜሪካው ተወካይ ናቸው።
የኤርትራ ኃይሎች ወደ ትግራይ ተመልሰው ገብተዋል በማለት በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ወታደራዊ ትብብር ሰፊ ጦርነትን የመቀስቀስ ስጋት ይፈጥራል ብለዋል።
አሜሪካ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና የሚፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰባት ያመለከቱት ተወካዩ፤ ሁሉም ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ፤ መንግሥትና ህወሓት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲፈቅዱ፣ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም እንዲደረግና የኤርትራ ኃይሎች ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሚሊዮኖች እርዳታ በሚፈልጉበትና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሆን ብለው የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ እንዳይገባ አደንቅፈዋል ሲሉ የአሜሪካው ተወካይ የከሰሱ ሲሆን ይህም በአስቸኳይ ተስተካክሎ እርዳታ እንዲቀርብ መደረግ አለበት ብለዋል።
የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተም በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ሪፖርቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አማራ ክልል ውስጥ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ በህወሓት ኃይሎች መገደሉን እንዲሁም የእርዳታ መጋዘን በህወሓት መዘረፉን ገልጸዋል።
ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በማባባስ በኩል ያላትን ሚና አሜሪካንን በእጅጉ እንደሚያሳስባት የተናገሩት ተወካዩ፤ ይህም ተኩስ አቁም ለማድረግና በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
የኤርትራ ሠራዊትን በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የከሰሱት ተወካዩ በቅርቡ የጦሩ ኤታማዦር ሹም ላይ አሜሪካ የጣለችውን ዕቀባ በማስታወስ ተጨማሪ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የኤርትራ ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ እንደማያመጣ ተቀብለው፤ ተኩስ አቁም ለማድረግና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ በአስቸኳይ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ጠይቀዋል።
ሕንድ
ጦርነቱ በህወሓት አማካይነት ወደ አማራና አፋር ክሎች እንደተዛመተና ይህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንዲሁም ልጆችን በተዋጊነት የማሰማራት ከባድ ችግር ማስከተሉን የሕንዱ ተወካይ ገልጸዋል።
በሰኔ ወር የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለማሻሻል ወሳኝ እርምጃ እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን በሌላኛው ወገን የተኩስ አቁሙ ተቀባይነት ሳያገኝ ጦርነቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋቱ የሚደርሰው ጉዳት መጨመሩን ጠቅሰዋል።
ስብሰባውን የመሩት የሕንድ ተወካይ ጨምረውም መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና ከሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን በመግለጽ፣ ባደረገው ጥረትም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑ በመረጃ መደገፉን ጠቅሰዋል። ይህም የእርዳታ አቅርቦት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላት እንደሚገባና በተለይ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት ችግሩን ለመፍታት ድጋፍ ማድርግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማምጣት በኢትዮጵያ በእራሷ የሚመራና በሕገ መንግሥቷ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን እንዳለበት በመግለጽ፤ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መተማመን፣ እርቅና ውይይት መኖር እንዳለበት አመልክተዋል።
በማጠቃለያቸውም አገራቸው ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛቷ መከበር ህንድ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ኬንያና ሌሎች
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሐሳብ ያቀረቡት የኬንያው ተወካይ ከእራሳቸው አገር በተጨማሪ የኒጀር፣ የሴንት ቪንሰንትና ግሪናዲስን እንዲሁም የቱኒዚያን ጭምር መሆኑን አመልክተው፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።
ተወካዩ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎች በተለይ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጉዳትን እንዲያስቆሙ፣ እርዳታ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲደርስ እንዲፈቅዱ፣ ተኩስ እንዲቆም፣ ለድርድር መንገድ ለመክፈት የአገሪቱ ምክር ቤት ህወሓትን ሽብርተኛ ያለበትን ውሳኔ እንዲያነሳና ሁሉም ወገኖች ለድርድር ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
ጨምረውም፤ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ፣ ሀብታም አገራት ለሰብአዊ እርዳታ በቂ ገንዘብ እንዲያቀርቡ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ፣ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ድቀትን ሊያስከትል ከሚችል ማንኛውንም የተናጠል ማዕቀብ ከመጣል እንዲቆጠቡ እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ሰላም በማምጣት በኩል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ቻይና
የቻይናው ተወካይ በኢትዮጵያ መረጋጋት ማስፈንና የተለያዩ ብሔር ተወላጆች በሰላም እንዲኖሩ ማስቻል ከአገሪቱ ባለፈ ለቀጠናውም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
“ሁሉም ወገኖች ችግሩን በፖለቲካዊ ውይይት ይፈቱታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ ቻይና ትደግፋለች” ብለዋል።
ሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰ እንደመጣና በአማራና በአፋር ክልሎች እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተናግረው፤ ሁሉም አካሎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በትግራይና በሌሎችም ቦታዎች ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩና የተባበሩት መንግሥታት መርህን እንዲከተሉም የቻይናው ተወካይ ጠይቀዋል።
ቻይና እያደረገች እንዳለችው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ ለዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ እርቅ እንዲቆም ጠይቀዋል።
“በሰብአዊ እርዳታ ስም የውጪ ጣልቃ ገብነት መኖር የለበትም። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ይፈታ” ሲሉም ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረሩና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሱ እንደሆኑ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ሩሲያ
የሩስያዋ ተወካይ በበኩላቸው፤ ወደ ትግራይ እርዳታ ለመላክ በሰመራ የተቋቋመው መተላለፊያ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አይይዘውም፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብአዊ ሁኔታ ከፖለቲካ ጉዳይ መነጠል ያስፈልጋል። በትግራይ በሚደረገው ሰብአዊ እርዳታ መድልዎ መኖርም የለበትም። አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ለምክር ቤቱ የሩሲያን አቋም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚያስፈልግና ይህም በኢትዮጵያውያን መሪነት መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል።
“የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የፖለቲካ ነጻነት በጠበቀ መልኩ ነው መሰጠት ያለበት” ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አገሪቱን በአንድነት ወደ ሰላም የመውሰድ አቅም እንዳለው አክለዋል።
እንደ ቻይናው ተወካይ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን አውግዘው፤ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ምክረ ሐሳብ መካተት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
(ቢቢሲ አማርኛው)


   የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶኻን በድንበር ይገባኛል ውዝግብ የከፋ መቃቃር ውስጥ የገቡትን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለማሸማገል ሐሳብ አቀረቡ። ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን ለትግራይ ውጊያ በለዘብተኛ አካሄድ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኤርዶኻን ኢትዮጵያ እና ሱዳንን የማሸማገል ሐሳብ ያቀረቡት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 12 ቀን 2013 በአንካራ በሰጡት መግለጫ ነው።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ ተነስተዋል። “ኢትዮጵያ በስሱ ሒደት ውስጥ እያለፈች ነው” ያሉት ኤርዶኻን፤ በአፍሪካ አላት ያሉትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ጠቀሜታ ጠቅሰው ለሀገሪቱ ሰላም፣ ጸጥታ እና አንድነት ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
“የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት ከመጠበቅ አኳያ ለወቅታዊው ችግር በለዘብተኛ አካሄድ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን” ያሉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት፤ ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረው ውጊያ ከተባባሰ ዳፋው በአካባቢው አገራት ሊዳረስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።  
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚወዛገቡበትን የአል-ፋሽጋ አካባቢ ጉዳይን በጋዜጣዊ መግለጫው ያነሱት ኤርዶኻን፤ ሀገራቸው ሁለቱን ጎረቤታሞች ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት ጠቆም አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ “ውዝግቡ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ውይይት በመልካም ጉርብትና ላይ በመመስረት እንዲፈታ የልብ ፍላጎቴ መሆኑን ገልጪያለሁ። ቱርክ ጉዳዩ በሰላም እልባት እንዲያገኝ ሽምግልናን ጨምሮ ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ናት” ብለዋል።
ኤርዶኻን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ከመገናኘታቸው አንድ ሳምንት ገደማ በፊት፤ ወደ አንካራ ከተጓዙት የሱዳኑ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር። ከሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ ኤርዶኻን በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ “በጋራ ውይይት እና መግባባት” ሊፈታ ይገባል ብለው ነበር። ሀገራቸው በመጪዎቹ ጊዜያት ከካርቱም ጎን እንደምትቆም ማስታወቃቸውም ይታወሳል።
በጉብኝቱ፤ ቱርክ እና ኢትዮጵያ በውሃ ዘርፍ፣ በገንዘብ ዕገዛ እና ወታደራዊ የገንዘብ ትብብርን የተመለከቱ አራት ስምምነቶች መፈራረማቸው ተገልጿል። ኢትዮጵያ እና ቱርክ 125 አመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። በረጂብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግስት ላይ ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ሽብርተኛ ብላ ከፈረጀችው የሃይማኖት መምህሩ ፌቱላህ ጉለን በምታደርገው ውጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ በኢትዮጵያ ተከፍተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ለቱርኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን መተላለፋቸውንም ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን አረጋግጠዋል።
በአወዛጋቢው የፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ አማካኝነት በአዲስ አበባ ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አራት ትምህርት ቤቶች በቱርክ መንግስት ስር ላለው ማሪፍ ፋውንዴሽን ተላልፈው የተሰጡት ሰሞኑን። በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ህብረት፣ ሳር ቤት፣ ፈረንሳይ እና ሲ ኤም ሲ አካባቢዎች የሚገኙት አራቱ ትምህርት ቤቶች ለማሪፍ ፋውንዴሽን የተላለፉት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው።
 (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Page 5 of 546