Administrator

Administrator

ወ/ሮ ይድነቃቸው የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡ ልጆቿ በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉ ስለፈለገች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትን በቀላል አቀራረብና ቋንቋ የያዙ የልጆች መፃሕፍት ፍለጋ ብዙ ቦታዎች ጠይቃ ማጣቷን ትናገራለች፡፡ የዚህች እናት ገጠመኝ በአገራችን ያለውን የመፃሕፍት ስርጭት ችግር ያመለክት እንደሆነ እንጂ ለሕፃናት የተዘጋጁ መፃሕፍት የሉም ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም፡፡
የመፃህፍቱን ሥርጭት እንዲሁም ብዛትና ዓይነቱን ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም እንጂ ለሕፃናት የታለሙ በርካታ መፃሕፍት ተጽፈዋል፡፡ የደራሲ ማይክል ዳንኤል አምባቸው ሙት ዓመት በጣይቱ ሆቴል ሲከበር እንደተገለፀው፤ ሟቹ አብዛኛው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢሆንም  40 የልጆች መፃሕፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ 49 የልጆች መፃሕፍት አሳትመዋል የተባሉ አንድ ደራሲ የማግኘት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ የፃፏቸውን 49 የልጆች መፃሕፍት፣ በየክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች ማከፋፈላቸውን ነግረውኛል፡፡
ለልጆች ታስበው የታተሙት መፃሕፍት ቁጥር ቀላል አይደለም፤ ይዘትና አቀራረባቸው ግን ብዙ ሊያነጋግር እንደሚችል እሙን ነው፡፡ በቅርቡ “የሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” በሚል ርዕስ በደራሲ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ የተዘጋጀው የልጆች መፅሃፍ፤ ልጆች መልካም ሥነ ምግባር እንዲማሩበት ታስቦ የተሰናዳ ሲሆን ለልጆች የሚዘጋጁ መፃሕፍት እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
በ145 ገፆች ተቀንብቦ የቀረበው መጽሐፉ፤ በአራት ምዕራፎች 36 ተረቶችን ይዟል፡፡ “ከአሁን ቀደም ከጓደኛዬ ጋር ‹ናብሊስ› በሚል ርዕስ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ሊሆን የሚችል የልጆች መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ” ሲሉ በመግቢያው ላይ ያሰፈሩት ደራሲው “ይህ ጥረት በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት አጥብቄ ስላመንሁበት፣ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች የሚሆን ተነባቢና ጣፋጭ ታሪኮችን በውርስ ትርጉም መልክ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ” ብለዋል፡፡ ታሪኮቹ በ24 ስዕሎች ታጅበው ነው የቀረቡት፡፡
ደራሲ ገብረክርስቶስ፤ ለሕፃናት የሚዘጋጁ መፃሕፍትን በዕድሜና በክፍል ደረጃቸው እየለዩ ማቅረብ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ ምንም ይሁን ለአዋቂዎች እንዴት መቅረብ እንደሚችል፣ ለልጆችስ በምን መልኩ እንደሚዘጋጅ በደራሲው መፅሐፍ በተመሳሳይ ጭብጥ ከቀረብ ታሪክ ጋር ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡
በ“ሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” መጽሐፍ ውስጥ ስለ ስስትና አልጠግብ ባይነት የቀረበው ታሪክ “ቀላዋጩ ሸረሪት” የሚል ርዕስ አለው፡፡ በድሮ ዘመን ሸረሪት ወገቡ ወፍራም ነበር፡፡ በአንዱ ዕለት ጫካ ውስጥ ያሉ ሁለት እንስሳት፣ በሁለት የተለያዩ መንደሮች ድግስ መሰናዳቱን ነገሩት፡፡ በሁለቱም ድግስ መብላት የፈለገው ሸረሪት፣ የትኛው ድግስ ቀድሞ እንደሚጀመር ስላላወቀ፣ ዘዴ ማፈላለግ ያዘ፡፡
“ወደ ቤቱ እየከነፈ ሄደና ረጃጅም ገመዶችን ያዘ፡፡ ሁለቱን ወንድና ሴት ልጆቹንም ጠራቸው፡፡ ልጆቹንና ገመዶቹን ይዞ ላይ ሰፈርንና ታች ሰፈርን በአማካይ ወደሚያዋስነው ወንዝ ሄዱ፡፡ አቶ ሸረሪት፤ በአንዱ የገመድ ጫፍ ወገቡን አሰረና ሌላኛውን ጫፍ ለሴት ልጁ ሰጣት፡፡ እርሷም የገመዱን ጫፍ እየጎተተች ወደ ታች ሰፈር ሄዳ፣ ግብዣው ሲጀመር ገመዱን በመሳብ ምልክት እንድትሰጠው ታዘዘች፡፡ በሁለተኛውም ገመድ በተመሳሳይ ወገቡን አስሮ፣ ጫፉን ለወንድ ልጁ ሰጠው፡፡ ወንድ ልጁም ወደ ላይኛው ሰፈር ሄዶ እንዲያመለክተው ታዘዘ፡፡ ሁለቱም ልጆቹ የታዘዙትን ለመፈፀም ወደየተመደቡበት ቦታ ገመድ እየጎተቱ ሄዱ፡፡ አቶ ሸረሪት ወገቡን በሁለት ገመዶች እንደታሰረ በመሀል ሆኖ ይጠባበቅ ጀመር…
“አጋጣሚ ሆኖ የሸረሪት ሀሳብ እንዳቀደው አልሆነም፡፡ የላይ ሰፈርና የታች ሰፈር የግብዣው ሰዓት ተመሳሳይ ሆነ፡፡ ሁለቱ የሸረሪት ልጆች፣ ግብዣዎቹ እንደተጀመሩ አባታቸው እንዳዘዛቸው ለመፈጸም ገመዶቻቸውን መሳብ ጀመሩ፡፡ ምስኪኑ አባት፤ ሸረሪት በሁለት አቅጣጫ በሚሳቡ ገመዶች ተወጥሮ በመሀል ተንጠለጠለ፡፡”
“ሸረሪት ወገቡ ቀጥኖ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው የሚለው ይህ ታሪክ በመቋጫ ላይ ልጆች አልጠግብ ባይና ስስታም እንዳይሆኑ የሚያስተምር ሀሳብ አቅርቧል፡፡
“በዓለም የታወቁ አጫጭር ልቦለዶች” በሚል ርዕስ በአምሳሉ አክሊሉ ተተርጉሞ፣ በ1981 ዓ.ም ለአንባብያን የቀረበው መጽሐፍም ስስትና አልጠግብ ባይነት ምን ጉዳት እንደሚያስከትል የሚያስተምር ታሪክ ይዟል፡፡ ከሩስያዊው ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ ሥራዎች ተወስዶ “ላንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” በሚል ርዕስ በቀረበው ልቦለድ ውስጥ፣ አንድ ደሀና ምንም ያልነበረው ገበሬ፣ ሀብት ማካበትን ዓላማው አድርጎ መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ የስግብግብና አልጠግብ ባይነት ስሜቱ አጉል አወዳደቅ ላይ እንደጣለው ያስቃኛል፡፡
የልቦለዱ ገፀ ባሕሪ ሚስት፣ ልጆች፣ ከሲታም ቢሆኑ የቤት እንስሳት፣ አነስተኛም ቢሆን የራሱ መሬትና ኑሮ ነበረው፡፡ ይህንን ኑሮውን ሌሎች ሲተቹበት ነበር ሀብት ለማፍራት መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ በምኞት፣ በጥረትና በድካም ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በርካታ መሬትና ሀብት አፈራ፡፡ ከእርካታ ጋር መገናኘት ግን ሳይቻለው ስለቀረ፣ የተጨማሪ መሬት ባለቤት ለመሆን ጉጉትና ፍላጎቱ እያየለ መጣ፡፡
በዚህ ወቅት ደግሞ ሊታመን በማይችል ዋጋ፣ የሰፊ መሬት ባለቤት ሊያደርገው የሚችል ዕድል አገኘ፡፡ አንድ ሺህ ሩብል ብቻ የሚከፍልበትን መሬት መርጦ፣ ለክቶና በቃኝ ብሎ የመወሰን መብት ነበረው፡፡ በዚህ መብት ውስጥ የተሰጠው ግዴታ ግን ነበር፡፡ የሚፈልገውን መሬት መርጦ ለመጨረስ፣ ፀሐይ ስትወጣ ጉዞ የጀመረበት መነሻ ላይ ጀምበር ስትጠልቅ መድረስ አለበት፡፡ የሚያየውን ለም መሬት ሁሉ ባለቤት ለመሆን ከመነሻው እየራቀ ስለሄደ፣ በመልስ ጉዞው ለብዙ ድካምና እንግልት ተዳረገ፡፡ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት መነሻ ቦታ ላይ ቢደርስም ነፍስና ስጋው በምድር መኖር የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም፡፡ አንድ ሜትር ጉድጓድ ተቆፍሮ እዚያው እንዲቀበር ሆነ፡፡
“ቀላዋጩ ሸረሪት” እና “ላንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” የሚል ርዕስ ያላቸው ታሪኮች መሰረታዊ ጭብጥ አንድ ነው፡፡ ስስታምና አልጠግብ ባይነት በስተመጨረሻ ጉዳት ማስከተላቸው እንደማይቀር ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
የሁለቱ ታሪኮች አቀራረብ ግን ተደራሻቸውን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ የደራሲ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ “የሉሲ ክዋክብትና ሌሎችም” መጽሐፍ፤ ለልጆች የሚዘጋጁ መፃሕፍት እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በያቢ ፊልም ፕሮዳክሽን የተሰራው “ከቃል በላይ” የተሰኘ አስቂኝ የፍቅር ፊልም፣ የፊታችን ሰኞ በአቤል ሲኒማ ይመረቃል፡፡ በፊልሙ ላይ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን እንደተወኑበት የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮች ገልፀዋል፡፡

በኢዮብ ጌታሁን የተፃፈውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “ያልተኖረ ልጅነት” መጽሐፍ በአሜሪካዊቷ ሻርሊን ቻምበርስ ቦልድዊን ወደ እንግሊዝኛ ተተረጎመ፡፡
“ኦርፋንስ ሶንግ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይኸው የእንግሊዝኛ ትርጉም፣ ከአማርኛው ጋር እንዳይጣረስ የመፅሐፉ ደራሲ በአርታኢነት ተሳትፎበታል፡፡ መፅሐፉ 270 ገፆች ያሉት ሲሆን በዋናነት ከኢትዮጵያ ውጪ እንዲሸጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የመፅሀፉም ዋጋ 14.95 ዶላር ነው፡፡ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ውስጥ በቡክ ወርልድ የመፃህፍት መደብሮች ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡

በደራሲ መዓዛ ወርቁ “Desperate to Fight” በሚል በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተፅፎ በሱንዳንስ ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ውድድር ላይ የተመረጠው ተውኔት፤ “ከሰላምታ ጋር” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በኢትዮጵያ መታየት ሊጀምር ነው፡፡ ቲያትሩ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በኬንያ፣ በኒውዮርክ፣ በስቶክሆልም ስዊድን ለተመልካች ቀርቦ ተወዳጅነትን እንዳተረፈ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በጀርመንኛ ቋንቋ ተተርጎሞ በጀርመን እና በአውሮፓ ለሚገኙ ተመልካቾች ለማቅረብ theatralize company ከደራሲዋ ጋር ኮንትራት ተፈራርሟል፡፡ ቲያትሩ የኬኒያ፣ የዩጋንዳ፣ የአሜሪካ እና የስዊድን ዜግነት ባላቸው ተዋንያን የተሰራ ሲሆን ለሀገራችን በሚቀርበው ተውኔት ላይ በቲያትር ሙያ የዳበረ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው አርቲስት ኤልሳቤጥ መላኩ እና ፈለቀ የማርውሃ አበበ እንደሚተውኑበት ታውቋል፡፡
በኪባ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ፕሮዱዩስ የተደረገው ይኸው ቲያትር፤ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በጃዝ አምባ ላውንጅ በየሳምንቱ ለተመልካች ይቀርባል ተብሏል፡፡ ወደፊትም በሌሎች መድረኮች እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ የእያንዳንዱን ክልል የጋብቻ ስነ - ስርዓትና ትውፊታዊ ክንውን ሰንዶ ሊያስቀምጥ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ በዚህም መሰረት ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም እያንዳንዱ ክልል፣ ክልሉን ይወክላሉ ያላቸውን የጋብቻ ሥርዓቶች ይዞ በመቅረብ ለሌላው ህብረተሰብ ያስተዋውቃል ተብሏል፡፡ የጋብቻ ስነ ስርዓቱና ትውፊታዊ ክንውኑ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጭ ሲሆን ከዚያም በብሔራዊ ቴአትር ተሰንዶ ይቀመጣል ተብሏል፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ሁሉም ክልሎች ተወክለው ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በላከው መግለጫ አስታውቋል።

“የኢትዮጵያ ህያው ሙዚየም” የተሰኘ የሙዚየም ማውጫ ታትሞ ወጣ፡፡ በሀገሬ ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን የተዘጋጀው ይሄው የሙዚየም ማውጫ፤ በሁለት ከተማ አስተዳደሮችና በሌሎችም ክልሎች የሚገኙ ሙዚየሞችን ይዟል፡፡ 80 ገፆች ያሉት ማውጫው፤ በክፍል አንድ ከያዛቸው ሙዚየሞች ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ የኢትዮጵያ ፖስታ ሙዚየም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም፤ በኦሮሚያ የሻሼ ሀውልትና ባህል ሙዚየም፣ በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ሙዚየም፣ የሆሌሎጂ ሙዚየም፣ የኮንሶ ሙዚየምና በተለያዩ ክልሎች ያሉ በርካታ ሙዚየሞችን አካትቷል፡፡ ሀገሬ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ከዚህ ቀደም የቱሪዝም ማውጫዎችን ያሳተመ ሲሆን በቱሪዝም ላይ ትኩረት አድርጐ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡

አድናቂዎች ለዕጩዎቹ ድምጽ መስጠት ይችላሉ

ኢትዮጵያውያኑ ድምጻውያን አስቴር አወቀና ጃኪ ጎሲ፣ “አፍሪካን ሚዩዚክ ማጋዚን አዋርድስ” (አፍሪማ) ለተባለው ታላቅ አህጉራዊ የሙዚቃ ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች በእጩነት ቀረቡ፡፡
አፍሪማ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ2014 ሽልማት እጩዎች ዝርዝር ላይ እንደተጠቀሰው፣ ድምጻዊት አስቴር አወቀ በ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ሴት ድምጻዊት”፣ ጃኪ ጎሲ ደግሞ በ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ወንድ ድምጻዊ” ዘርፍ በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፣ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ቡድኖች፣ ማኔጀሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ፕሮዱዩሰሮች፣ ዲጄዎች፣ የዳንስ ቡድኖችና የሙዚቃ ቪዲዮዎችም በተለያዩ 26 ዘርፎች ለሽልማት ታጭተዋል፡፡
አስቴር አወቀ በታጨችበት የ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ሴት ድምጻዊት” ዘርፍ፣ ሌሎች ሁለት የኡጋንዳ፣ ሁለት የኬኒያና አንድ የታንዛኒያ ታዋቂ ድምጻውያን በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ ጃኪ ጎሲ በቀረበበት የ“ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ወንድ ድምጻዊ” ዘርፍ ደግሞ፣ ሌሎች ሁለት የታንዛኒያ፣ ሁለት የኡጋንዳና አንድ የኬኒያ ድምጻውያን በእጩነት ቀርበዋል፡፡
አድናቂዎች http://afrimma.com/afrimma-nominees-2014/ በሚለው የድረ-ገጽ አድራሻ በመጠቀም ለሚፈልጓቸው እጩ ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ቡድኖችና ሌሎች እጩዎች ድምጻቸውን በመስጠት፣ አሸናፊ እንዲሆኑ የራሳቸውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ የሽልማቱ አዘጋጆች ተናግረዋል።
በመጪው ሃምሌ ወር አጋማሽ በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት፣ ሪቻርድሰን ውስጥ በሚከናወነው የሽልማት ስነስርዓት ላይ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፉ የተመረጡ አፍሪካውያን ድምጻውያን፣ ማኔጀሮች፣ ፕሮዲዩሰሮች፣ ዲጄዎች፣ ባህላዊ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በክብር ይሸለማሉ ተብሏል፡፡ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የተጋበዙና ከ17 የአፍሪካ አገራት በክብር እንግድነት ተጋብዘው የሚመጡ ታላላቅ ጀግኖች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካን ሙዚቃ የማስተዋወቅ አላማ ያለውና በየአመቱ በሚከናወን ደማቅ ስነስርኣት ለአሸናፊዎች የሚበረከተው ይህ ሽልማት፤ በዘርፉ ከሚሰጡ ታላላቅ አህጉራዊ ሽልማቶች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ድምጻውያንና የሙዚቃ ቡድኖች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበትና በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለእይታ የሚበቃውን የዘንድሮውን የአፍሪማ የሙዚቃ ሽልማት ስነስርዓት ስፖንሰር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ፓዎር ሃውስ ኢንተርናሽናል ኤርላይንና አክሴስ የተባለው የአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ መሆናቸውንም የሽልማት ድርጅቱ መስራች አንደርሰን ኦቢያጉ በድረ-ገጻቸው ላይ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ውድ እግዚአብሔር-
ስለአንተ ሥራ አስተማሪያችን  ነግራናለች፡፡ አንተ እረፍት ስትወጣ ግን  ማነው የሚሰራልህ?
ዴቪድ-የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ አንተስ?
ቤቢ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
ትምህርት ቤት ስንማር፣ መብራት የፈጠረው ቶማስ ኤዲሰን ነው ተብለን  ነበር፡፡ ሰንበት ት/ቤት ደግሞ አንተ እንደፈጠርከው ነገሩን፡፡ ኤዲሰን ያንተን ሃሳብ ሰርቆብህ ነው አይደል ?
ዮኒ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
ህፃን ወንድም ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ ግን የጠየኩህ የምታምር ቡችላ እንድትሰጠኝ ነበር፡፡
ቤቲ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
ስለእኔ እንዳታስብ እሺ፡፡ ሁልጊዜ መንገድ ስሻገር ግራና ቀኙን በደንብ አይቼ ነው፡፡
ዳኒ-የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
እሁድ እለት ቤተክርስትያን የምትመጣ ከሆነ አዲሱን ጫማዬን አሳይሃለሁ፡፡
ሚኪ-የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር-
በዓይን የማትታየው ሰማይ ሩቅ ስለሆነ ነው አይደል?
ሳሚ- የ4 ዓመት ህፃን

Saturday, 24 May 2014 15:00

የፀሐፍት ጥግ

አንድ ፅሁፍ ያለልፋት በቀላሉ ከተነበበ፣ ሲፃፍ በእጅጉ ተለፍቶበታል ማለት ነው፡፡
ኤንሪክ ጃርዴይል ፓንሴላ
እውነተኛ ፀሐፍትን ተስፋ ማስቆረጥ አይቻልም፡፡ ምንም ብትሏቸው ደንታ  ሳይሰጣቸው ይፅፋሉ፡፡
ሲንክሌይር ልዊስ
በእጄ ላይ ብዕር ይዤ እንቅልፍ ከጣለኝ ብዕሬን አትንኩብኝ፣ በእንቅልፍ ልቤ ልፅፍ እችላለሁ፡፡
ቴሪ ጉሌሜትስ
የመፃፍ ተሰጥኦ እንደሌለኝ ለማወቅ አሥራ አምስት ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡ ፅሁፍን ማቆም ግን አልቻልኩም፡፡
 ምክንያቱም ያኔ  ዝነኛ ፀሃፊ ሆኛለሁ፡፡
ሮበርት ቤንችሌይ
የምንፅፈው አሁናችንን በኋላ ለማስታወስ ነው፡፡
 ቴሪ ጉሌሜትስ
ማንም ሰው  የፃፈውን ነገር ለሴት ሳያነብ መፅሃፍ ማሳተም የለበትም፡፡
ቫን ዊክስ ብሩክ
ሃኪሜ የምትኖረው ለስድስት ደቂቃ ብቻ ነው ቢለኝ በፍርሃት አልርድም፤ ፍጥነቴን
 ጨመር አድርጌ እፅፋለሁ እንጂ፡፡
አይሳክ አሲሞቭ

ዊሊያም ዎርድስዎርዝ (1770-1850)
እንግሊዛዊው ገጣሚ ዎርድስዎርዝ  ገና 15 ዓመት ሳይሞላው ነበር ወላጆቹን በሞት ያጣው፡፡ እንዲያም ሆኖ በእንግሊዝ የተሳካላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ገጣምያን ተርታ ከመሰለፍ ያገደው ነገር አልነበረም፡፡ ግጥሞችን መፃፍ የጀመረው ገና ተማሪ ሳለ ቢሆንም 23 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ግን አንድም የግጥም ሥራው አልታተመለትም ነበር። ዎርድስዎርዝ  የፃፋቸውን ግጥሞች የሚያነበው ለውሻው ሲሆን  ውሻው በተነበበለት ነገር ከጮኸ ወይም ከተበሳጨ፣ ዎርድስዎርዝ ግጥሙን ማሻሻልና እንደገና መፃፍ እንዳለበት ተገንዝቦ ወደ ሥራው ይገባል፡፡
ዲክ ኪንግ-ስሚዝ (1922-2011) በእንስሳት ላይ የተመሰረቱ የህፃናት መፃህፍትን በመፃፍ ይታወቅ የነበረው እንግሊዛዊው ደራሲ ዲክ ኪንግ- ስሚዝ፤በሙያ ዘመኑ ከ100 በላይ መፃህፍትን ፅፏል፡፡ ዝናን ያጎናፀፈው መፅሃፉ The Sheep Pig የተሰኘው ሲሆን ይሄ ሥራው Babe በሚል ርዕስ ወደ ፊልም ተቀይሮለታል፡፡ የመጨረሻ መፅሃፉ በ2007 እ.ኤ.አ የታተመለት ሲሆን The Mouse Family Robinson ይሰኛል፡፡ ደራሲው የፃፋቸው ታሪኮች አሁንም ድረስ በመላው ዓለም በሚገኙ ህፃናት ዘንድ በፍቅር እንደሚነበብለት ይነገራል፡፡


ከ800 ሚሊዮን በላይ መፃሕፍቶችን የቸበቸበችው የረዥም ልብወለድ ፀሐፊዋ ዳንኤላ ስቲል፤ የመጀመርያ ረቂቅ ፅሁፏን እስክታጠናቅቅ ድረስ በጥንት የትየባ ማሽን ላይ በቀን ለ20 ሰዓታት ትፅፋለች፡፡ በአንድ መፅሃፍ ላይ አተኩሮ ከመስራት ይልቅ በአንድ ጊዜ ከ4-5 የሚደርሱ መፃሕፍት ላይ በመስራትም ትታወቃለች፡፡
ጥቂት የማይባሉ የደራሲዋ ልብወለዶች ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለአገራችን አንባቢያን መቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን ወደ ፊልም የተቀየሩ ሥራዎቿም በቅዳሜ የታላቅ ፊልም ፕሮግራም ላይ ለተመልካች  ይቀርቡ ነበር፡፡


ስቲፈን ኪንግ
ከ350 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች የተሸጡለት ይሄ አሜሪካዊ ደራሲ፤ ምንም ሳያስተጓጉል በየቀኑ ስድስት ገፆች ገደማ  ይፅፋል፡፡ በቀን ከ4 እስከ 6 ሰዓታት ማንበብና መፃፍ የማይችል ሰው ታላቅ ፀሐፊ የመሆን ህልሙን ይርሳው ሲልም ደራሲው ያስጠነቅቃል፡፡  
የድርሰት ትምህርት አንድን ሰው የመፃፍ ክህሎት ያስታጥቀዋል ብሎ የማያምነው ስቲፈን ኪንግ፤ ደራሲነት ከተፈጥሮ የሚገኝ ፀጋ ነው ባይ ነው፡፡ የመጀመርያ ድርሰቱን በ7 ዓመት እድሜው የፃፈው ኪንግ፤ ይሄን ድርሰት በ18 ዓመቱ ለአንድ መፅሄት እንደሸጠው ተዘግቧል፡፡ Carrie የተሰኘውን የመጀመርያ ልብወለዱን ከፃፈ በኋላ በተወዳጅ አስፈሪ (horror) ልብወለዶቹ እየታወቀ የመጣ ሲሆን የመጀመርያ አስፈሪ መፅሃፉም The Shining ይሰኛል፡፡  

አሜሪካዊው የልብ አንጠልጣይ ረዥም ልብወለዶች ደራሲ ዳን ብራውን፤ በሳምንት ለ7 ቀናት ሳያሰልስ በመፃፍ ይታወቃል - ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ፡፡  ይሄ የቀድሞ የእንግሊዝኛ መምህር፤ ዳቪንቺ ኮድ በተባለው ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ ልቦለድ መፅሐፉ የሚታወቅ ሲሆን ይሄ ልቦለድ  በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ እየተተረጎመ ሲወጣ እንደነበር ይታወሳል፡፡