Administrator
Monday, 12 October 2026 15:23
በቡሬ-አሰብ መስመር ምን ተከሰተ?
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚለው ስጋት እየጨመረ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ በቡሬ-አሰብ መስመር ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መታየቱን የአይን ምስክሮች ተናገሩ። በሰሜን ኢትዮጵያ በመከላከያ ሰራዊትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ያለው ጦርነት ሦስተኛ ሳምንቱን እየያዘ ሲሆን፤ የመከላከያ ሰራዊትና አጋሮቹ በርካታ ከተሞችን በመቆጣጠር ወደ ኤርትራ ድንበር መቃረባቸው ተገልጿል። በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በቡሬ አሰብ መስመር በከባድ መሳሪያዎች የተደገፈ ከፍተኛ ኃይል ማሰማራቱ ታውቋል።
ከትናንት እሁድ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሠራዊት የኤርትራን ድንበር ጥሶ መግባቱን የሚገልጹ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲዛመቱ ቢውሉም፣ የአይን ምስክሮች ግን ሠራዊቱ ከኤሊዳር እና ቡሬ ከተሞች አልፎ ወደ ኤርትራ ድንበር አለመግባቱን አረጋግጠዋል። በአካባቢው ጠንካራ የሠራዊት እንቅስቃሴ መኖሩንና ለጊዜው ምንም ዓይነት ውጊያ አለመፈጠሩን ዶቼ ቬለ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Monday, 12 October 2026 15:21
“የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ” አውደ ርዕይ ዳግም ተመለሰ
በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ጥንታዊ ጥበባት ላይ ያተኮረው “የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ” የልጆችና የቤተሰብ ልዩ አውደ ርዕይ በተመልካቾች ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት ከተጨማሪ ዝግጅትና ማሻሻያዎች በኋላ በአዲስ መልክ ዳግም ተከፍቷል።
በአዲስ አበባ ሆላንድ ፓርክ እየቀረበ የሚገኘው ይህ ልዩ አውደ ርዕይ፤ ከጎብኚዎች በተነሱ ጥያቄዎች መሠረት ለተጨማሪ ሦስት ቅዳሜና እሁዶች (መስከረም 30 እና ጥቅምት 1፣ ጥቅምት 7 እና 8፣ እንዲሁም ጥቅምት 14 እና 15) ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን አዘጋጁ ሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ተቋም አስታውቋል።
አውደ ርዕዩ ሕፃናትና ወጣቶች ስለ አገራቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ሥልጣኔና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ አሻራዎች በተጨባጭ እንዲያውቁ የተዘጋጀ ነው። ከተለመዱት መርሃ ግብሮች ለየት ባለ መልኩ ጎብኚዎች ቅርሶችን ከማየት ባለፈ በመዳሰስ፣ በመስማት፣ በማሽተትና በመቅመስ በአምስቱም የስሜት ሕዋሳት ታሪካዊ ይዘቶቹን እንዲረዱ ተደርጎ የተሠራ ሲሆን፤ አክሱም፣ ላሊበላና ደብረ ዳሞን የሚያስታውሱ የኪነ ሕንፃ ሥራዎች፣ የብራና መጻሕፍትና ጥንታዊ ጥበባት ቀርበዋል።
የካናዳ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ አውደ ርዕዩን ጎብኝተው የቤተክርስቲያንን ታሪክና ቅርስ ለትውልድ በማስተዋወቅ ረገድ ያለውን ትልቅ አስተዋጽኦ አድንቀዋል። አውደ ርዕዩ ለዝግጅት ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችና የተቋም ቡድኖች በልዩ የጉብኝት ፓኬጅና ቅናሽ እንዲጎበኙ ዕድል ተመቻችቷል። አዘጋጆቹ ሕዝቡ በተጠቀሱት ቀናት በመገኘት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ውርስ በቅርበት እንዲመለከት ጥሪ አቅርበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ህብረተሰብ
Tagged under
Monday, 12 October 2026 15:18
የሰላም ጎዳና ለብልጽግና፡ ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ተከበረ!
ግጭት የጥፋት ጎዳና ሰላም ደግሞ የልባሞች መንገድ መሆኑን የገለጹት የፌዴራሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ መንግሥት ለሰላም የሚያደርገውን ተደጋጋሚ ጥሪ በመቀበል ወደ ማዕቀፉ መምጣት እንደሚገባ አሳሰቡ። ፕሬዚዳንቱ «ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ቃል በተከበረው 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ላይ እንደተናገሩት፤ ሠንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት፣ የመሥዋዕትነት እና የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ምልክት ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ሆና አንድ፣ አንድ ሆናም ብዙ በመሆኗ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በአንድነት ተቋቁማ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መገንባት መቻሏን አስታውሰዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፣ ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ፍቅርና የተከፈለው መሥዋዕትነት ለትውልድ የሚተላለፍበት የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የብዝኃ ሥልጣኔ ሀገር እንደመሆኗ መጠን የዛሬው ትውልድ ዕለቱን ሲያስብ በተሰማራበት የሥራ መስክ እንደ አርበኛ ሆኖ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። ዜጎች ሀገራቸውን ወደ ተሻለ የብልጽግና ደረጃ ለማድረስና ሉዓላዊነቷን አስከብረው ለማቆየት ቃል የሚገቡበት አስፈላጊው ዕለት መሆኑም ተመላክቷል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Sunday, 11 October 2026 00:00
ጄኔራል ባጫ ደበሌ ለኤርትራ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ
"ከኢዳጋ ሐሙሱ የከፋ እርምጃ ይጠብቃቸዋል"
አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን የሚያረጋግጥ በሳተላይት እና በቪዲዮ የተደገፈ ተጨባጭ ማስረጃ መኖሩን ይፋ አድርገዋል። ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው የኤርትራ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበበትን የድንበር ጥሰት ክስ በመካድ "ኢትዮጵያ ልትወረኝ ነው" የሚል የመልስ ክስ ማቅረቡን ተከትሎ ሲሆን፣ ጄኔራሉ በኤክስ (X) ገጻቸው ባሰፈሩት መግለጫ፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መዝግቦ የያዘ በመሆኑ የኤርትራ ክስ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡
በቀረቡት ማስረጃዎች መሰረት የኤርትራ ወታደሮች ከዘመናዊ የድሮን ጥቃት ለማምለጥ የቅጠል ሽፋን በመጠቀም በአርባ ገደማ ተሽከርካሪዎች አዲግራትን አልፈው ኢዳጋ ሐሙስ ድረስ ዘልቀው መግባታቸው ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ የተጠቀሙት ስልት ከጥቃት ሊያድናቸው ባለመቻሉ በመከላከያ ሰራዊቱ ጠንካራ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የገለጹት ጄኔራል ባጫ፣ "ቅጠላ ቅጠል አያድንህም" ሲሉ አብራርተዋል።
በመጨረሻም ጄኔራሉ በቪዲዮ እና በሳተላይት ማስረጃ የተደገፈው ይህ ወረራ በአስቸኳይ ቆሞ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን መሬት ለቆ ካልወጣ፣ ከኢዳጋ ሐሙሱ የከፋ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚጠብቃቸው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Monday, 12 October 2026 15:14
በአዊ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት አለፈ
በአማራ ክልል አዊ ዞን ከእንጅባራ ወደ ቻግኒ በሚወስደው መንገድ "ቢዳ" በተባለ ቦታ በደረሰ ከባድ የትራፊክ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው ዛሬ ከቀኑ 5፡30 አካባቢ በሕዝብ ማመላለሻ ሃይሩፍ እና በሃይሉክስ መኪና መካከል በደረሰ ግጭት የተከሰተ ሲሆን፣ ሕይወታቸው ካለፉት መካከል ሁለቱ ሴቶችና የሁለቱም መኪኖች አሽከርካሪዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም በአደጋው በ20 ሰዎች ላይ ከባድ፣ በ5 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሶ ለሕክምና ወደ እንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ተወስደዋል። የአደጋው መንስኤም እየተጣራ ይገኛል ተብሏል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Monday, 12 October 2026 15:13
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስያሜ ስፖንሰር የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንፃ በደማቅ ብርሃን አሸብርቋል
Published in
ስፖርት አድማስ
Tagged under
Monday, 12 October 2026 15:08
ብሔራዊ ቴአትር ለብሪክስ የቴአትር ፌስቲቫል ልዑክ ሽኝት አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በህንድ ኒው ዴልሂ በሚካሄደው የብሪክስ ሀገራት የቴአትር ፌስቲቫል ላይ የሚሳተፈውንና 15 አባላትን ያቀፈውን የኢትዮጵያ ልዑክ ለመሸኘት የመርሐ ግብር አካሄደ። ከጥቅምት 2 እስከ 4 ቀን 2019 ዓ.ም. በሚካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚሳተፈው ልዑክ በቴአትር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ የሚመራ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የቴአትር ጥበብ፣ ባህላዊ እሴቶችና የፈጠራ ችሎታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ዋና ተልዕኮ ይዞ ነው ወደ ህንድ የሚያቀናው።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሊ ከማሎ ልዑኩ የሀገሪቱን የጥበብና የባህል ሀብት በክብር እንዲያስተዋውቅ አደራ የሰጡ ሲሆን፣ የልዑኩ መሪ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ በበኩላቸው ፌስቲቫሉ የባህል ልውውጥን ለማጠናከርና አዳዲስ የጥበብ ትብብር ዕድሎችን ለመፍጠር ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ተሳትፎ የኢትዮጵያን የቴአትር ጥበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስጠራት ባለፈ ለወደፊት የልምድ ልውውጦች አዳዲስ በሮችን እንደሚከፍት ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ዜና
Tagged under
Friday, 09 October 2026 09:10
“ስራዎቻችን ምስክሮቻችን ናቸው” — ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ
ተወዳጁ ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ የሴንቸሪ ሪልስቴት ይፋዊ የብራንድ አምባሳደር ሆኖ መሾሙ በይፋ ተበሰረ። ሴንቸሪ ሪልስቴት ያለፉትን ዓመታት የስራ ልምድና የልማት ተሳትፎ በማጠናከር፣ በአዲስ አጋርነት ወደ ቀጣዩ የስራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ባበሰረበት መርሃ ግብር ላይ ነው የድምጻዊ ዳዊት ጽጌን አምባሳደርነት ይፋ ያደረገው።
ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ በዝግጅቱ ላይ ባደረገው ንግግር፣ የሴንቸሪ ሪልስቴት ብራንድ አምባሳደር በመሆኑ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታና ኩራት ገልጻል። ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የድርጅቱን የስራ ዕንቅስቃሴዎች እስከሚደክመው ድረስ በአካል ዞሮ መመልከቱን የጠቀሰው ድምጻዊው፣ ድርጅቱ ያከናወናቸው ስራዎች “በጣም የሚያኮሩና የሚያስደስቱ” መሆናቸውን አረጋግጧል።
ዳዊት ጽጌ ከሴንቸሪ ሪልስቴት ጋር በአጋርነት ለመስራት የወሰነባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ሲያብራራ፣ ድርጅቱ ላለፉት 70 ዓመታት በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማረጋገጡ፤ ድርጅቱ ያለው የተደራጀ የሰው ሃይል፣ የፋይናንስ አቅም እንዲሁም ለደንበኞች የገባውን ቃል ጠብቆ በጥራት የመገንባትና በቶሎ የማስረከብ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ፤ ድርጅቱ ከፍተኛ ግብር ከፋይ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ተሸላሚ መሆኑ፤ በየዓመቱ የትምሕርት ቁሳቁስ መደገፍ፣ የመመገቢያ ማዕከላትን መገንባት፣ የአረጋውያን ድጋፍና የንጹህ መጠጥ ውሃ ጎድጓዶችን ማስቆፈር በመሳሰሉ ተግባራት ወገንተኝነቱን በማስመስከሩ እንደሆነ ገልጻል።
ሴንቸሪ ከ70 ዓመታት በላይ የዘለቀ የንግድ ልምድ እንዳለው የገለጸ ሲሆን፣ ከ30 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን ግብዓት፣ በብረታ ብረት፣ በኬሚካል፣ በማዕድንና በሪል እስቴት ዘርፎች ተሰማርቶ መቆየቱን አስታውቋል። በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት በአዲስ አበባ በርካታ የመኖሪያ፣ የንግድና የቢሮ ሕንጻዎችን ገንብቶ አስረክቧል።
በመጪው የስራ ዘመንም ትኩረት ከሚያገኙ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ውስጥ በኦሎምፒያ የሚገነባው ሴንቸሪ ኦሎምፒያ፣ በሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘው ቫልዩ ፕሮጀክት፣ ሜጋ ፒኮክ ኦፊስ ኮምፕሌክስ እንዲሁም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚገነቡ ዘመናዊ አፓርትመንቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ይህንን አዲስ የስራ ምዕራፍ ለማበሰር የተዘጋጀው “ደግሞ በእዚህ ላይ... ስራዎቻችን ምስክሮቻችን!” የተሰኘው ዘመቻ ይፋ ሲደረግ፣ ከአዲሱ ብራንድ አምባሳደር ከድምጻዊ ዳዊት ጽጌ ጋር የተደረገው አጋርነት ድርጅቱ ወደፊት ለሚያከናውናቸው ስራዎች አዲስ ጥንካሬ የሚፈጥር መሆኑ ተጠቅሷል።
Published in
ኪነ-ጥበባዊ ዜና
Tagged under
Thursday, 08 October 2026 08:35
የሉሲዎቹ ድንቅ ድል! ኢትዮጵያ ሩዋንዳን 1 ለ 0 አሸነፈች
ለ2028ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም የተጫወተው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከሜዳው ውጪ የሩዋንዳ አቻውን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በዚህ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ላይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድልን ያበረከተችው ብቸኛ ግብ የተቆጠረችው በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ (45+3') ላይ ሲሆን፤ ግቧንም የሩዋንዳዋ ተጫዋች ኡዛዬሴንጋ ሊድያ በራሷ መረብ ላይ አሳርፋለች።
ይህ ከሜዳ ውጪ የተገኘ ድል ሉሲዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጥሩ እድል የፈጠረላቸው ሲሆን፣ ሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን ጥቅምት 3 ቀን በድሬዳዋ ስታዲየም ያደርጋሉ።
Published in
ስፖርት አድማስ
Tagged under
Thursday, 08 October 2026 08:26
"የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማንም ሊያስቆመው አይችልም"
የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገው ሕዝባዊ ውይይትና ሕጋዊ ውሳኔ ሳይደረግ በጥቂት ሰዎች መሆኑን ገልጸዋል። የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች በጦርነት ማሸነፍ ሲሳናቸው የውስጥ ኃይሎችን በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈው እንዲሰጡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ከሻዕቢያ እና ህወሓት ምስረታ ጀርባ የግብጽ እጅ እንደነበረበት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን በሰላማዊ መንገድና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አቶ አባዱላ ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ከባሕር በር ነጥሎ ማቆየት እንደማይቻልና የባሕር በር ባለቤትነቷ ማንም ሊያስቆመው የማይችል አይቀሬ ጉዳይ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Published in
ህብረተሰብ
Tagged under

