Administrator

Administrator

   የህወሓትን አሸባሪነት ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉት የኤርትራ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል ፊሊፖስ ወ/ዮሓንስ፤ እኛ ደግሞ ለቀጠናው ሰላም ስንል፣ አሸባሪዎችን አዝልቀን መቅበራችንን  እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
 “የህወሓትን አሸባሪነት ያረጋገጠው የኢትዮዽያ ህዝብ ነው። ህወሓትም አለማቀፍ የሽብርተኝነት መስፈርቶችን ከበቂ በላይ አሟልቶ አጠናክሮ ቀጠለበት እንጂ ከስህተቱ ተምሮ የኢትዮዽያን ህዝብና መንግስት ይቅርታ አልጠየቀም። ይልቁንስ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ቁልፍ ስጋት ሆኖ አረፈው።” ሲሉ መናገራቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡  የኢትዮዽያ ሰላም ለምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ኢትዮዽያ ውስጥ ሰላም የለም ከተባለ፣ ኤርትራም ሁለቱም ሱዳኖች፣ ኬንያም፣ ሱማልያም ሆነች ጅቡቲ ሰላም ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ጄነራሉ፤  በተለይ ለኤርትራ ሁሉን አቀፍ እድገትና  ሰላም የኢትዮዽያ አንድነት፣ ሰላምና እድገት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ዋጋ ያለው ነው፤ ብለዋል።
“ለአሸባሪው ህወሓት የኢትዮዽያ ጥምር የጦር ኃይል ከበቂው በላይ ነው። ይሁን እንጂ ህወሓት ጋላቢዎቹን  ግብጽ፣ አሜሪካና ምእራባውያንን ጣልቃ ለማስገባትና ቀጠናው በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆን የሰጡትን ተልእኮ ለማሳካት ሲል አስቀድሞ “በኤርትራ ልወረር ነው” ከአለ በኋላ፣ የኤርትራን ሉአላዊነት በተደጋጋሚ እየተዳፈረ በሚገባ እየተመታ ሲመለስ “የኤርትራ መንግስት ከዐቢይ ጋር ሆኖ ወረረኝ!” እያለ ያላዝናል፤ብለዋል ጄነራሉ።
“እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁልፍ ጉዳይ ግን ምንም እንኳን ህወሓት የቀጠናው የሽብር ስጋት ቢሆንም፣ ኤርትራ የራሷን ሉአላዊነት ታስከብራለች እንጂ፣ የኢትዮዽያን ሉአላዊነት በመዳፈር በኢትዮዽያ ምድር ገብታ የምታደርገው ኦፕሬሽን ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል።” ሲሉ መግለጻቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡
 “ይህ የሽብር ቡድን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ላይ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮዽያ መንግስትና ህዝብ ጋር ሆኖ መታኝ ተባበረብኝ.... ወዘተ እያለ መዘላበዱ የኢትዮዽያ ጥምር ጦር አቅሙ ውስን እንደሆነ ለውጭ ጠላቶች ማሳያ አድርጎ የተጠቀመበት ከመሆኑ ባሻገር፣ የሽብር ቡድኑ ከመሬት በታች መቀበሪያው ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን አመላካች መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።” ብለዋል፤ጄነራሉ፡፡
 “ኤርትራም ለቀጠናው ሰላም የሚበጅ እስከሆነ ድረስ ሉአላዊነቷን የሚዳፈሩ የሽብር ቡድኖችን አዝልቃ መቅበር ትቀጥላለች!” ሲሉ የኤርትራ መከላከያ ጦር አዛዥ ጄነራል ፊሊፖስ ወ/ዮሓንስ  መናገራቸውን ኤርትሪያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡


የዱባይ ቱሪዝም የምስራቅ አፍሪካ ከተሞች ኤግዚቢሽን ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ  ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ተካሂዷል።  የኤግዚቢሽኑ ዓላማ  በኢትዮጵያ ካሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት  ጋር በቅርበት በመስራት ዱባይ በውድ ዋጋ ብቻ ሳይሆን በተመጣጣኝ ክፍያ መጎብኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች ማስተዋወቅ  ነው ተብሏል፡፡
የዱባይ ቱሪዝም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ታሪቅ ቢንብሬክ ኤግዚቢሽኑን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ “ምስራቅ አፍሪካ በተለይ በዱባይ ቱሪዝም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ገበያ ሲሆን ከአፍሪካ ትልቁ የተጓዥ ቁጥር የሚመነጨው ከዚሁ ስፍራ ነው፤ ይህ ያሁኑ ኤግዚቢሽን ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የመጀመሪያው ነው፤ እኛም በመመለሳችን ደስተኞች ነን፤” ብለዋል፡፡በዚህ መርሃግብር  ከዱባይ ቱሪዝም ጋር ከ25 የማያንሱ ድርጅቶች ተወካዮቻቸውን ወደ አዲስ አበባ  የላኩ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ  ሥራቸውን በማቅረብ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአስጎብኚ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትውውቅ አድርገዋል።ባለፈው ረቡዕ በተሰጠው ሥልጠና የተሳተፉት ከ100 በላይ የሆኑ የሀገራችን የቱር እና ትራቭል ተቋማት ሲሆን ስልጠናውን የሰጡት ደግሞ የዱባይ ቱሪዝም ኢንተርናሽናል ኦፕሬሽንስ ሰብሰሀራን አፍሪካ ዳይሬክተር ስቴላ ፉባራ እና ምክትላቸው ታሬክ ቢንብሬክ ናቸው።በመዝጊያ መርሀ ግብሩ ለተሳታፊዎች ዕጣ የማውጣት ስነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ ዕድለኞቹ ወደ ዱባይ የሚጓዙ ይሆናል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ምንም የትውውቅ መድረክ ሳይኖር ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ዱባይ በሚደረግ የንግድና የቱሪዝም ጉዞ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛ ሀገር መሆኗም ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 10 September 2022 21:00

“መንኳኳት የማይለየው በር!”

 አንዳንድ በሀገራችን እንደቀልድ የሚወሩ ወጎች ውስጠ-ነገራቸው ታሪክ-አዘል ሆኖ ይገኛል።
የሚከተለው ቀልድ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት የቀድሞው የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭና አሁን በኢትዮጵያ በሌሉት  በቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ  በሊቀ መንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ዙሪያ የተቀለደ ነው።
የሩሲያ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ከዕለታት አንድ ቀን ለኢትዮጵያው መሪ ለጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የገና በዓል ሥጦታ (X-mas gift) ይልኩላቸዋል አሉ።
ሥጦታቸው አንዲት የኮርስ ብስክሌት ናት። የብስክሌቷ ልዩ ነገር፣ ምንም ዓይነት የእግር መሽከርከሪያ ወይም ፔዳል የሌላት መሆኑ ነው።
ሊቀ መንበር መንግሥቱ ፔዳል እንደሌላት ሲያዩ በጣም ተበሳጭተው፡-
“የጉምሩክ ሰራተኞች ይሆናሉ የሰረቁኝ (የበሉኝ) እሰሩና ጠይቁልኝ!” አሉና ትዕዛዝ ሰጡ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ታሰሩ - እንደ ሕጉ። እንደ ባሕሉ። የጉምሩክ ፈታሾች በሙሉ ተከረቸሙ። በምርመራ የተገኘ ምንም ነገር አልነበረም።
በቁጣ፤ “ፓይለቶቹንም እሰሩና መርምሩልኝ” አሉ። ፓይለቶቹም ታሰሩ። ፔዳሉ ግን አልተገኘም።
ጥቂት ወራት እንዳለፈ የእስር ቤቱ መርማሪዎች፣ ምንም ፍንጭ አለመገኘቱን ሪፖርት አደረጉ።
ሊቀ መንበር መንግስቱ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው መላ ምቱ አሉ።
አማካሪዎቻቸውም፤
“ለምን ፕሬዚዳንት ጎርባቾቭ ዘንድ ተደውሎ፣ የላኳት ብስክሌት ፔዳል ያላት ይሁን፣ ፔዳል የሌላት አይጠየቁም?” ሲሉ ሀሳብ አቀረቡላቸው።
ተደውሎ የጎርባቾቭ የቅርብ ረዳት ተጠየቀ።
የቅርብ ረዳታቸው አረጋግጦ ያመጣው መልስ፣ ዕውነትም የተላከችው ብስክሌት ፔዳል የሌላት ናት።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በጣም በሽቀው፤
“እኮ ለምን? ለምንድነው ፔዳል የሌላት ብስክሌት የላካችሁት?” ብለው ጠየቁ።
ከሩሲያ ወገን ያገኙት መልስ፡-
“ጓድ ሊቀመንበር፣ እርሶ ሁልጊዜ ወደ ቁልቁለት እየወረዱ ስለሚሄዱ፣ ፔዳል መምታት (መዘውሩን ማሽከርከር) አያስፈልግዎትም!” የሚል ሆነ፤ ይባላል።
***
የአገር ኢኮኖሚ ወደ ቁልቁል በሄደ ቁጥር አገር ቁልቁል ትሄዳለች። የሕዝብ ኑሮ ከቀን ወደ ቀን እየተጎሳቆለ ይሄዳል። የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ እያሻቀበ፣ የሕዝብ ህይወት እያዘቀዘቀ ሲሄድ፤ ውጤቱ ምሬት ይሆናል። ምሬት አመፅን ይወልዳል።
ገዢ በግድ ልግዛ ካለ፣ ተገዢው ሕዝብ አልገዛም ማለቱ የማይታበል ሐቅ ነው። ይሄን የሚሸመግልና የሚያረጋጋ አካል ከሌለ፣ ህዝብና መንግሥት እሳትና ጭድ፣ አዳኝና ታዳኝ እየሆኑ ይመጣሉ። በታሪክ፣ በሀገራችን በርካታ ወደ ከፋ ሁኔታ የሚያመሩ ክስተቶች አይተናል። የሀገሪቱ ወሳኝና የነቃው ምሁር ክፍል በእሳቱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ይልቅ፤ ቆም ብሎ በጥበብ የመንቀሳቀሻ መላ መምታት ይጠበቅበታል። የማረጋጋት ሚና ለመጫወት ደግሞ አስቀድሞ ራሱን የማረጋጋት ሂደትን መወጣት አለበት። ብዙ የበሰሉና ጥሞና ያላቸው ሰዎች አሉ። አለን አለን አይሉም። በመጮህም አያምኑም። እንዲህ ያሉትን ሰዎች ፈልጎና ስራዬ ብሎ፣ “ኑ እስቲ የአገራችንን ነገር እንምከርበት” ማለት ያስፈልጋል፡፡
ነገን የተሻለ ለማድረግ ያለቀውን ዓመት መጠነኛ ግምገማ እናድርግበት፡፡  መጪውን ዘመን ከመነሻው እንቅረፀው። ዘመን ተለወጠ ማለት የሚቻለው ከትላንት የተሻለ ቅላፄና ቃና ያለው ሙዚቃ ለመፍጠር ስንችል ነው። ጦርነት እንዲያባራ በቅን ልቦና ጥረት ስናደርግ ነው። ዛቻን ትተን በክብ ጠረጴዛ መነጋገር ስንችል ነው። የ”እኔ አሸነፍኩ፣ አንተ ተሸነፍክ”ን መዝሙር መዘመርን፣ ቢያንስ በመጠኑ እየቀነስን ለመሄድ ዝግጁ ስንሆን ነው። በተራ በተራ እየሞተ ያለው የሕዝብ ልጅ ነው። ማርጋሬት ሚሼል የተባለችው ደራሲ፤ “WAR IS LIKE CHAMPAGNE, IT GOES TO THE HEADS OF FOOLS AS WELL AS BRAVE MEN AT THE SAME SPEED.” ትለናለች፡፡
(“ጦርነት ልክ እንደ ሻምፓኝ መጠጥ ነው። እጅሎችም፣ እጀግኖችም እናት ላይ በእኩል ፍጥነት ነው የሚወጣው”) እንደማለት ነው። በጦርነት ስንሰክር የሚፈስሰው ዞሮ ዞሮ የሰው ልጅ ደም መሆኑን ረስተን፣ የሚታየን ማሸነፍ ብቻ ነው። መጨረሻው ግን የአገር እጦት ነው።
 ከጦርነት ያተረፈ የለም። ጊዜያዊ ድል እንጂ ዘላቂ ትርፍ አይገኝበትም! ብዙ ጊዜ ስለ ሰላም ይነገራል። ብዙ አድማጭ ግን አይገኝም። “ኧረ በገላጋይ፣ በሕግ አምላክ!” የማይባልበት ጊዜ ሆነና መጠፋፋት ብቻ እየታየን ያለበት ዘመን በመሆኑ፣ከዚህ ይገላግለን ዘንድ እግዚኦታ ያስፈልገናል። “ምህረቱን ይላክልን!” ማለት ደግ ነው።  እስከ ዛሬ ብዙ የጦር ጀግና አፍርተን ሊሆን ይችላል። የሥልጣኔ ጀግና ግን አላፈራንም። ይሄ ከእርግማን አንድ ነው። ዓለም ወደፊት ሲጓዝ እኛ ወደ ኋላ እየተመለከትን፣ ገና የታሪክ ሰበዝ ከመምዘዝ አልተላቀቅንም! መፍትሔው አንድ ብቻ ነው - የሚንኳኳውን በር አለመስማት። መንኳኳት የማይለየውን በር ነቅሎ አዲስ በር መግጠም!
ይሄንን ስናደርግ ብቻ ነው፣ አዲሱ ዓመት አዲስ የሚሆንልን! አዲስ ዓመት፤ የአዲስ ለውጥ የአዲስ ሕይወት ፀሐይ የሚፈነጥቅልን በዚህ መልኩ ነው! በአዲሱ ዘመን መንኳኳት ከማይለየው በር ይገላግለን! አሜን።


2014 ዓ.ም በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና  ሌሎች ዘርፎች በአንድ በኩል ተስፋ ሰጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የታዩበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መፈናቀል የደረሰበትና በተለይ በወለጋ በአካባቢ ዜጎች አሳዛኝ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት፣ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የህዝብ እሮሮ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰማ የሚያደርግ ቢሮክራሲ የገነነበትና ከዚያም አልፎ አንዳንድ ሰዎች “ጊዜ ሰጠን” በሚል ሁኔታ ከፍተኛ የመብት መጋፋት ተግባር ያሳዩበት ዓመት ነው ብል ማጋነን አይሆንም።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን ግዙፍ የሆኑ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበትና የተጠናቀቁበት፣ በአጠቃላይ መልካምና መጥፎ ሁኔታዎችን ጎን ለጎን ይዞ የተጓዘ ዓመት ነበር።
ከዚህ በተቃራኒው፣ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይ በወሎ ግንባርና በሁመራ  አሸባሪው፣ ተስፋፊውና አረመኔው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራንና የአፋርን አካባቢ የወረረበት እንዲሁም ብዙ ጥፋቶችን የፈጸመበት ዓመት ሆኖ አልፏል። በዓመቱ እንደ አንድ ትልቅ የከፋ ድርጊት የምቆጥረው ይህንን ነው። ይሁንና መላው ጥምር ጦራችን ማለትም መከላከያው፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ፤ በተመሳሳይም የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ በአንድ ላይ በመሆንና በመቀናጀት አሁንም በምነጋገርበት ሰዓት ወራሪውንና  አሸባሪውንን ቡድን  ድባቅ  እየመቱ ለረጅም ጊዜ በወራሪው ጭቆና ስር የነበረውን የትግራይን ህዝብ ነፃ ለማውጣት እየገሰገሱ መሆኑ አስደሳች ዜና ነው።
ሌላው ከ2014 ወደ 2015 ዓ.ም ይሸጋገራል ብዬ የማንምነው የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ ነው። ምክክር እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት በጣም ሰፊ ሚና የሚጫወት ነውና ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱና የድርጊት ቅደም ተከተል አስቀምጦ መንቀሳቀስ መጀመሩ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ምናልባትም የምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ፍሬያማ የሚሆንበት አካሄድ ካለ፣ በህገ-መንግስት ማሻሻያ ላይ ንግግር የምንጀምርበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በ2015 በጎ ጅምሮች ተጠናክረው፣ ደካማ ጎኖቹ ተሻሽለው ያለፈውን ስህተት የማንደግምበት ብሩህ ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ።
2015 ዓ.ም የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና የመተሳሰብና እርስ በእራሳችን አፍ ከልብ ሆነን ኢትዮጵያን ለማሳደግ ጥራት የጋራ የምናደርግበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ። ዓመቱ ለረጅም ጊዜ በሰቆቃ ውስጥ የቆየውንና በእንባ ለረጅም ጊዜ ተሸፍኖ ያሳለፈውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዚህ ሰቆቃ ማውጣት የምንችልበት መሆን አለበት። በተረፈ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2015 ዓ.ም አደረሳችሁ። ዓመቱ ሰቆቃ ዋይታ፣ ብጥብጥ መፈናቀልና ሞት የማይከሰትበት እንዲሆን እመኛለሁ።

የሚያሳዝነው ነገር እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ትተናል። ምክንያቱም ሁላችንም አይደለንም በሰላም እየደረስን ያለነው። እንግዲህ የተጠናቀቀውን ዓመት ፈጣሪ የሰጠን ባርኮ ነው። ዓመታትን እግዚአብሔር ባርኮ ነው የሚሰጠው። እውነት ለመናገር ዓመቱ ብዙ የተሰጋበት  ዓመት ነበር። የተሰጋለትን ያህል ባይሆንም በከፍተኛ ደረጃ የወገኖቻችን እልቂት የታየበት፣ ድርቅና ረሀብ ሀገራችን ውስጥ ተከስቶ በቦረና አካባቢ ሰውም ከብቱም ያለቀበት፣ በጦርነት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖቻችን የተሰቃዩበት፣ ጦርነቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ አገርሽቶ በርካታ ቦታዎች ላይ ብዙ ሰው ያለቀበት ብሎም ንብረት የወደመበት፣ የትግራይ ወገኖቻችን ይሙቱ ይኑሩ ሳናውቅ ከበርካታ ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር ተነጣጥለው የቆዩበት፣ በጦርነቱ ቤተሰብ ለሁለት ተከፍሎ ልጅ ከእናት፣ አባት ከሚስት የተነጣጠለበትና ይኑሩ ይሙቱ ሳይታወቅ ሁሉም ነገር ድፍን ብሎ የኖርንበት ዓመት ነው። በተለይ የትግራይ ወገኖቻችንን ማሰብ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም ምስኪን ህዝብ ነው። የትግራይም ህዝብ እንደዚሁ በጣም ምስኪን ህዝብ ነው። እነዚህ ምስኪን የትግራይ እናቶች ከልጆቻቸው ሳይሆኑ፣ ልጆቻቸውም እናቶቻቸውን ሳያዩ የቆዩበት ክፉ ዓመት ነበረ። ይህ በእርግጥ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተፈጠረ ሀቅ ነው።በእኛ በኩል ደግሞ የሚቆጠር ሀብት ከህዝብ አሰባስበን ወገኖቻችንን ለመታደግ በጣርንበት ወቅት ከኢትዮጵያውያን አጋርነትን፣ ንፁህነትን፣ ለጋሽነትን፣ ሩህሩህነትንና መልካምነትን ያየንበት ቢከሰትም እግዚአብሔርን ያየንበት ዓመት ነው።
በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ጣሪያ የነካበትና በዚህም ህዝብ የተንገሸገሸበት ዓመትም ነበረ። በግል ደረጃ የተወሰኑ ስኬቶች ሊመዘገቡ ይችላሉ። ነገር ግን 2014 ዓ.ም አብዛኛው ህዝብ በምሬት ሚያነሳው ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። 2013 ዓ.ም ላይ ሆነን 2014ን ስንቀበል ዓመቱ ከፍተኛ እልቂት የሚፈጸምበት እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ምንም እንኳን ብዙ እልቂትና መከራ ቢከሰትም፤ እግዚአብሔር በተባለው መጠን አላደረገብንምና ማመስገን አለብን።
በ2014 ሌላው የተጎዳነው ወደ አድዋ የምናደርገው ዓመታዊ ጉዞ (ጉዞ አድዋ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋረጠበት ዓመት መሆኑ ነው። አያቶቻችን አድዋ ሄደው የተዋጉት፣ አድዋ ሁሉም ድል ሆኖ እንዲቀጥልና ዓለም እስካለች የአድዋ ድል ደማቅነቱ ቀጥሎ እንዲረጋገጥ መሆኑ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን የአድዋ ልጆች የትግራይ ወገኖቻችን ከሶስተኛ ወገን  ጥቃት በደርስባቸው እንኳን ለመከላከል በማንችልበት ሁኔታ ላይ ሆነን መቆየታችን በጣም ሆድ የሚያባባና ከባድ ሀዘንን የሚያሳድር ነው።
በዚህ ሁሉ መሃል በጣም የምደሰተው ደግሞ ይሄ ሁሉ የታየው ግፍና መከራ ህዝብን ምን ያህል እንዳስመረረውና እንዳንገሸገሸው በቁርጠኝነት የሳየበትና ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ለመውጣት እንደሚፈልግ ያረጋገጠበት የተነሳበት ዓመት በመሆኑም ጭምር ነው። ህዝብ ሰላም መቀራረብና ፍቅር የሚፈልግ መሆኑን በግልጽ ያሳበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል።
በ2015 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በፍቅር የጋራ ቤቱን ለማቆምና ምሶሶውን ለማጠንከር በጋራ ሚቆምበት እንዲሆን ነው የምመኘው። ባለፈው ጦርነት ህዝብ ተጎድቷል፤  በሁለቱም ወገን ያለው ህዝብ ተክዷል። ስለዚህ ይሄ ህዝብ መካስ አለበት። መካስ ካለበት ደግሞ ወደ ሰላም፣ ወደ አንድነትና ወደ ፍቅር መምጣት አለብን። እኔ በበኩሌ 2015ን ባርኬ ነው የምጀምረው እንዲያው የምጠራጠረው ነገር እንኳን ቢኖር ከአፌ አላወጣውም፤ ዓመቱ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ።ከእስካሁኑ  መከራ አንጸር ይሄ ጦርነት መቀጠል የማይገባው ነውና ፖለቲከኞችም በጋራ ልብ ነገሩን ማስተካከል አለባቸው። የጋራ ልብ የሌለው ፖለቲከኛ ካለ ግን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ሰላም ወዳዱ ህዝብ ሰላሙን በገዛ እጁ ለመመለስ አጥፊዎችን የቀጣበት የራሱ ተዓምራዊ መንገድ ስላለው ምንም ጥርጥር የለውም ጦርነቱም ይቆማል፤ ሰላምም ይወርዳል፤ ሀገራችንም ሰላም ትሆናለች የሚል እምነት አለኝ። በድጋሚ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን።

በመጀመሪያ ለመላው ኢትዮጵያዊያን በጭንቅም ውስጥ ቢሆን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። 2014ን እንደ ፖለቲከኛ ከፖለቲካዊ ሁኔታው ነው የምመለከተው። ዓመቱ እንደ ሀገር ከፈረሱ ጋሪውን ለማስቀደም የሞከርንበት ነው። ምን ማለቴ መሰለሽ… ቅድሚያ ለችግሮቹ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳንሰጥ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ችግሮቻችን ከኋላ ወደፊት ለመፍታት የሞከርንበት ነው። 2012ም፣ 2013ም እንደዛው ነበር።
በእኔ እምነት ፖለቲካው ሲቃና ነው ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊ ህይወታችንም ሆነ ሃይማኖታዊ ጉዟችን በትክክል የሚሄደው። እኛ ለዘመናት የታገልነውን ዘውግን ወይም ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እሳቤን በቆራጥነት ካልገታነው በስተቀር እንደ ሀገር ሁሉ ነገራችንን ነው የሚያቆመው የሚል እምነት ነው ያለን። እናም 2014 ይህንን ዋናውን ችግር አልፈን፣ ሌሎች ተከትለው የሚመጡ በሽታዎችን ለመፍታት የሄድንበት ዓመት ነውና በዚህ መልኩ ነው የምገልጸው።
ስለዚህ በ2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሩን የእውነት አድርገን መጀመሪያ መፈታት ያለበትን ማለትም ሁሉ ቦታ ላይ እየገባ ችግር የሚፈጥርብንን ፖለቲካውን ፈትተን ወደ ሌሎች የምንሄድበት   ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ።  በሌላ በኩል 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብዙ ነገር ቢሞከርባትም እንኳን የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያሳየችበት  ዓመት ነው። አየሽ ኮሮና ቫይረስ ነበረ፣  ወረራ ነበረ፣ የውጪ ጣልቃገብነት ነበረ፣ አንበጣ ነበረ፣ የጎርፍ አደጋና በጣም በርካታ ፈተናዎች  ነበሩ።
ታዲያ ይንን ሁሉ ልንሻገር የቻነው ኢትዮጵያ የተሰራችበትና እንደ ሀገር  የተሸመነችበት ድርና ማግ የዋዛ ባለመሆኑ ነው። በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላምና የጤና ይሁንልን ለማለት እወዳለሁ። መልካም አዲስ ዓመት።

 የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
       - የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ለ10 ቀናት ይቆያሉ ተብሏ


         በኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸው ጦርነት ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ጠየቀ።
ኮሚሽኑ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዳግሞ ያገረሸው ጦርነት ወደ ሌሎች አገራት ተዛምቶ ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል።የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና ጦርነቱ ተስፋፍቶ ቀጠናውን እንዳያናጋ የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ ጉዳዩን ዋንኛው አጀንዳው እንዲያደርገውም አሳስቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ተገቢነት ያለው መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በተያያዘ ዜና፤ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የህውሃት ታጣቂ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር ለማደራደር የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ላይ ናቸው ተብሏል። ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 ቀን2014 ዓ.ም አዲስ አበባ የገቡት ልዩ መልዕክተኛው እስከ መስከረም 5 ቀን 2015 ድረስ እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው የሰላም ንግግርና ድርድር እንዲጀምሩ የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው መምጣታቸው የተነገረላቸው ልዩ መልዕክተኛው፤ በቆይታቸው ከመንግስት ባለስልጣናትና ሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የፕሬዚዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ አምባሳደር ማይክ ሀመር ባለፈው ግንቦት ወር ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሸሙወዲህ ለሁለት ጊዜያት ያህል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከአውሮፓ ህብረት አቻቸው አኔት ዌበር፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃናቴት እና ከካናዳና ጣሊያን አምባሳደሮች ጋር በመሆን ወደ መቀሌ አቅንተው ነበር። የማይክ ሐመር የመቀሌ ጉዞ በሁለቱ ወገኖች  መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፤ ህውሃት ነሐሴ 18 ቀን2014 ዓ.ም የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ዳግም ጦርነቱን በመቀስቀሱ ሳቢያ የሰላም ተስፋውን አጨልሞታል።Page 10 of 628