Administrator
ሰባራ ጥላ
ቅዳሜ ጥቅምት 30 አመሻሽ ላይ ከ( 10:00 ) ጀምሮ አብዬ በርሶማ አንጋፋ እና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች በክብር እንግድነት በተጋበዙበት መድረክ በብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት(ወመዘክር) ሥራውን ያቀርባል።
መንታ ፍቅር
መንታ ፍቅር:: አዲስ አስገራሚ: ግራ እያገባን እየሳቅን ዋሽንግተን እና እዲስ አበባ የምንመላለስበት ፊልም:: አርብ ፡ ጥቅምት 29:በ 8: በ10: በ1 ሰዓት:: ቅዳሜና እሁድ በ8: 10: 12 ሰአት ተጋብዘዋልና ይምጡ !
ሂሩት በቀለ ከ1935 - 2015 ዓ.ም.
የሮፍናን “ቢሆን” እና የይቅርታው መሓልይ!
ጥቂት ከማይባሉ፣ ከፍ ያሉ ሀሳቦችን ከያዙ ዘፈኖቹ መካከል፤ “ስድስት” ሲል በለቀቀው አልበም ውስጥ የተካተተና በጥልቅ ፍልስፍና የታሸ ስለ ይቅርታ የሚያትት አንዱ ዘፈን ነው።
ገጸ-ሰቡ በዘፈኑ ውስጥ “ቢሆን...ቦታ ብትሰጪኝ” እያለ፣ “በደልኳት” ካላት ሴት አጥብቆ ይቅርታ ይጠይቃል። ደግሞም “ሰው እምነቱን ሐይማኖቱን፣ ጸሎቱን፣ ምህላውን ቢመስል፣ ‘ቢሆን’ መልካም ነው” የሚል አንድምታም ይደመጥበታል።
“ተጸጽቶ በይቅርታ ለሚያጎነብስ ‘በዳይ’ ለተባለ ሰው፣ አንድ አማኝ እንዴት ‘ይቅር’ ለማለት ቦታ ያጣል?” በማለት ይጠይቃል። ተስፋ አንግቦ “እናውጋ...እንወቃቀስ” ይላታል።
ስሚኝ
አጠፋ በደልህ፤ ያልሽኝ ሰው
አታወሪኝ ምነው?
ዛሬም
በተስፋ እጠብቅሻለሁ
እናውጋ እላለሁ።
በድለሃል መባሉን ተቀብሎ በተማጽኖ ለይቅርታ ደጅ እየጠና ነው። “በድለኸኛል” ያለችው ሴት ፊት ብትነሳውም፣ ከነገ ዛሬ እምነቷን፣ ምህላዋን ሆና ይቅር እንደምትለው ተስፋ ሰንቋል። የተመላለሰችበት የአምልኮ ስፍራ ስለ “ይቅርታ እና በዳይን ይቅር ስለማለት” አስተምህሮ እንደማይጠፋው ተስፋ አድርጓል። ያውቃልም።
ጠዋት ማታ ማትቀሪ ደጁ
ነጠላሽ ከልብሽ ንጹህ
ምህረት ከራስ ይጀምራል (ስሚ)
ያን ጊዜ ፈጣሪ ይሰማል።
ለይቅርታ ቸለልተኛ የሆነ ልቧን፤ ቂመኛ ልቧን፣ ከምትለብሰው ነጠላ አነጻጽሮ፤ ከልቧ ነጠላዋ መንጿቱን በ”እንዴት ከጨርቅ አነስሽ” ትዝብት ይወቅሳታል። “ምህረት ስታደርጊ... ይቅር ስትዪ ነው ፈጣሪም የሚሰማው” በማለት “ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ጸሎት” ይሉትን ብሂል ያስታውሳታል።
በቂም በቆሸሸ ልብ፣ በደልን በሚያመነዥግ ህሊና፣ ከፈጣሪዋ ዘንድ መሄድ ትታ፤ ቅድሚያ ከቤቷ ይቅር እንድትል፣ ነፍሷን በምህረት፣ በመተው እንድታጸዳም እንዲህ እያለ ይወተውታታል። ይሞግታታል።
ከቤቱ መሄድ ይቅርብሽ
ይቅር በይ ቅድሚያ ከቤትሽ
ሁሌ ስትሄጂ አይሻለሁ (ዓለም)
ሰላምሽ ግን በዳይሽ ጋር ነው።
ቢሆን ቦታ ብትሰጪኝ
ለአፍታ ብታዳምጪኝ
ቢሆን ልብሽ ከልቤ
ሰላም ነበርን
አንቺና እኔ
የይቅርታን ጉልበትና ሐይል ከብርሃን እኩል እያስተካከለ፤ ይቅር አለማለት ይቅርታን መንፈግ፣ ከብርሃን እንደሚያርቅም ለማሳሰብ የተዋቡ ስንኞች ያስከትላል።
ጸሐይ ማልዳ ብትወጣም
ያለ ይቅርታ አልነጋም፤
ምህረትን ነፍጎ ያደረ
በጨለማ ዋለ።
ይቅርታዋን ለማግኘት አይፈነቅለው ድንጋይ፣ አይቧጥጠው ተራራ፣ አይወርደው ቁልቁለት የለምና፤ አንዱን ሀሳብ ከአንዱ እያስተያየ፣ እያመሳከረ መጋፈጡን ይቀጥላል።
በቶ መስቀልሽ
ግንባርሽ ላይ የተነቀሽበት
ምነው አያቅፈኝ
ከሰው አነስኩበት?
በቃል ብትረቺኝ
ብወድቅለት ያገኘ አጌጠበት
ቅኔ አማርኛሽ
ወርቅ በዝቶበት።
የእሷ ልብ ቢደነድን እንኳን፣ ለእምነቷ ምስክር አድርጋ በንቅሳት የደመቀችበት የግንባሯ “ቶ” መስቀል ሳይቀር ጨክኖበታል። እሱም ከእሷ ጋር በማበር ሲገፋው፣ “በደሉን” ሲያገዝፍበት እያስተዋለ ግራ ቢያጋባው፣ “ከሰው አነስኩበት ወይ?” ብሎ “ተበደልኩ” ባይን ይጠይቃታል።
የእሷ በደሉን ማግዘፍያና መፋለምያዋ ደግሞ “ቃል” ነው። “ሰም” የራቀው “ወርቅ” ለበስ ቃል። በእሱ ትፋለመዋለች፤ ከዛ ትረታዋለች። እሱም ይወድቃል። መረታትና መውደቁንም አይክድም። በእሱ መረታትና መውደቅ የተገኘውን “ወርቅ” ደግሞ ሌላው ይደምቅበታል።
ግን ከወደቀበት ተነስቶ፤ እሱም የአቅሙን፣ የሚችለውን የቃል ጦር ያምዘገዝጋል እንጂ በቀላሉ አይረታም...
ዘንግተን ቃሉን
ማህተቡን ብናስረው ምንድነው
ተይ አፍሮ ይገባል
ፍቅር የሌለው፤
ማውጋት ይበጃል
በአክሱም መስቀል እምልልሻለሁ
ምህላውን ተይ
አጠገብሽ ሳለሁ።
እጅ አይሰጥም። የቃል ጉልበቷን ተቋቁሞ ሙግቱን ይቀጥላል። የተረታበትን የቃሏን ግዘፍ አትሞግትበትም ብሎ በገመተው ሌላ ቃል ነስቶ ሊረታት ይፍጨረጨራል። የአማኝነቷን ልክ ሲፈታተን የእምነት መጽሐፏ የሚነግራትን ቃል (የይቅርታን ቃል) እየገላለጠ በመጥቀስ፣ ቃል ዘንግተው፣ እምነቱን በወጉ ሳይኖሩት ማህተብ የማሰርን “ከንቱነት” ያስታውሳታል።
በዚህ መች ያበቃል...
ልቡ በቁጣ የተንቀለቀለ ጸበኛን፣ ደምን በደም ካልመለስኩኝ ባይ ተበቃይን....ተበዳይን ከበዳይ፣ ቂመኛውን ከተቄመበት አስማምቶ፣ አቀዝቅዞና የጋለ መንፈሱን አርግቦ የሚመልሰውን “አፍሮ አይገባም” መስቀልን ለአማኝ ማንነቷ በገደምዳሜ እያስታወሰ፣ “አፍሮ አይገባም ፍቅር ለሌለው አፍሮ ይገባል” እንደማለት ያለ ሙግት ያነሳል።
ስለ ቅያሜያቸው ሳያወጉ፣ በደሉን ይቅር ሳትል፣ ትርጉም የለሽ ምህላዋ ላይ የመትጋቷን ከንቱነት በእልህና በግላዊ እምነት ይፈትንባታል። ይሞግትባታል። “ቅኔ የበዛበትን ወርቅ አማርኛዋን” እያገኘ ሳይሆን አይቀርም በሚያሰኝ መልኩ ደፈርና ጠጠር ብሎ መሞገቱን በመቀጠል...
እግር ያደርሳል ከቤቱ ግምብ
ይቅርታ ግን ከልብ
መቅደስ ሰው በእጁ ከሰራው
የእርሱ ጥበብ ገላው።
ሲል ደፈር ባለ ፍልስፍና ለምህላ ጠዋት ማታ የምታቀናበትን ቦታ የእግዜሩ “ግምብ” ብሎ እየጠራ፤ በራሱ በእግዜሩ የተሰራው “ሰው” የተባለ ማንነት፣ ከማንኛውም ሰው ከሰራው ቁስ በላጭ መሆኑን አይነኬ ከተባለ ጉዳይ ጋር (ከመቅደስ) አነጻጽሮ ይገላልጣል።
በመጨረሻም ባልተሰሰተ ንጽጽራዊ ዘይቤው፣ ከላይ እንደተነሳው “የሸማዋ ከልቧ መንጻት” አሁንም ይከነክነዋልና፤ በውሃ ከሚነጻው ሸማዋ ልቧ ስለምን አንሶ ለይቅርታ እንደሰነፈ፤ ምህረትን ነፍጋ በጨርቅ፣ በሸማ መበለጧን እየነገራት፤ ፈጣሪ በጥበብ የሰው ልጅን ሰላም፣ እፎይታና በበዳይ ማንነት ውስጥ እንዳስቀመጠልን (ይቅር ስንል የሚገኘውን ሰላም ልብ ይሏል።)፣ ጥቂት የጥበብ ጠብታው ከባህር ጥልቅ እንደመሆኗ መጠን... አንድ ይቅርታም ለዓለም ማብቃቃቱን እየነገረና እያጠየቀ ዘፈኑን (ሙግቱን) ይቋጫል። እንዲህ እያለ...
ነጠላሽ የዋህ በውሃ ይነጣል
ልብሽ ግን ይቅርታ እንዴት ያጣል?
ላጠፋ ሰው ምህረት አሻፈረኝ ብለሽ
የለበሽው ሸማ በለጠሽ፤
አምላክ የሰጠውን መች ከሰው ወሰደው
ሰላምን በዳይ ጋር አስቀመጠው
ጥበቡ ጠብ ሲል ከባህር ይጠልቃል
አንድ ይቅርታ ለዓለም ይበቃል።
ነጠላችን፣ ሸማችን...የምንለብሰው ጨርቅ፤ ከልባችን፣ ከእኛነታችን የማይበልጥ ይሁን።
አጥፍቶ ይቅርታን ለሚማጸን ሰው ምህረት ነፍገን፣ ከበዳይ የምናገኘውን ሰላም በገዛ እጃችን እንዳናጣ ይሁን። የይቅርታ ሰንበት ይሁንልን!
የወቅቱ ጥቅስ
“የዘመኑ ጀግንነት ዲሞክራሲያዊነት እንጂ ማናቸውም የኃይል እርምጃ አይደለም፡፡ የሥልጣኔ ቆራጥነት በውይይትና በምክንያታዊ ሙግት መረታታት እንጂ እያደቡ መጠፋፋትና አንዱ ለአንዱ መቃብር መቆፈር አይደለም፡፡”
አዲሱ የቦሌ መንገድ - የኢትዮጵያ መግቢያ በር
“የቦሌ መንገድ” የሚለው ስያሜ ከአድናቆትና ከበጎ ስሜት ጋር የተያያዘ ነው። ለመኪኖችና ለእግረኞች፣ ለሥራና ለኑሮ፣ ለግብይትና ለመዝናናት ከሚመረጡ መንገዶች መካከል አንዱ ነው የሚል ስሜት ያስተላልፋል። የትኛው የቦሌ መንገድ? ነባሩ ወይስ አዲሱ?
ነባሩ “የቦሌ መንገድ” ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ ገጽታ ተሠርቶና አካባቢውም ተሻሽሎ አምሮበታል።
አሁን ደግሞ ሌላ አስደናቂ “የቦሌ መንገድ” መጥቶለታል፤ ወይም ተጨምሮለታል። የቦሌ - መገናኛ መንገድ።
በእርግጥ በርካታ የአዲስ አበባ መንገዶችና አካባቢዎች በኮሪደር ልማት እየተስፋፉና እያማረባቸው ነው። የቦሌ - መገናኛ መንገድ ግን ይለያል። በስፋትም በውበትም።
“የመዲናችን ትልቁ ሰፊ ጎዳና” የሚል ማዕርግ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ መግቢያ በር ልንለውም እንችላለን። በልዩ ውበት ተሠርቷል።
የቦሌ መገናኛ መስመር… ርዝመቱ 4.3 ኪሎ ሜትር ነው።
አስፋልቱ ብቻ 68 ሜትር ስፋት አለው።
ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በተንጣለለው መንገድ ላይ በግራና በቀኝ 10 መኪኖች ሽር… ይሉበት ጀምረዋል። ታክሲዎችና አውቶቡሶች፣ የቤትና የንግድ መኪኖች ሳይጨናነቁ፣ ለሰዓታት ሳይጉላሉ፣ ለአደጋ ሳይጋለጡ ይመላለሱበታል።
እግረኞችም ተመችቷቸዋል።
ከግራና ከቀኝ በአምስት በአምስት ሜትር ስፋት የእግረኞች መንገድ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሠርቶለታል። ለዚያውም በኮንክሪት ነው የተሠራው። ሲያዩት ያምራል፤ ሲራመዱበት ይመቻል። ወዲህ ወዲህ ሳይል ለብዙ ዓመታት እንደሚያገለግልም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የስራና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ ይገልጻሉ።
ከእግረኛ መንገድ አጠገብ፣ በሦስት በሦስት ሜትር ስፋት የብስክሌት መስመር አለው።
ይህም ብቻ አይደለም። መንገዱ ከጫፍ እስከ ጫፍ አረንጓዴ መንፈስ ተላብሷል። ዛፎች ተተክለዋል። ሣር የለበሱና በሥርዓት የተዘጋጁት ውብ መስመሮችም፣ መኪኖችንና እግረኞችን በክብር ለማጀብ የተሰናዱ አረንጓዴ ምንጣፎች ይመስላል።
ግራና ቀኝ ፍስስ በሚሉት መኪኖች መሀል ያለው ቦታ ሣር ለብሷል። ከዳርና ከዳር ሣር አለ። የጥበብ ጥለቶች ይመስላሉ። ከእግረኞችና ከብስክሌት መንገዶች ወዲያም በሣርና በዛፎች ያጌጡ አረንጓዴ አጃቢዎች አሉ።
መብራቶቹም ልዩ ናቸው - “ስማርት ላይት” ይሏቸዋል። በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ናቸው። ምን የሌላቸው ነገር አለ? የጎደለ ነገር የለም። የማታ ድምቀታቸውና ውበታቸውም ጭምር።
ከመንገዱ መሀል እንዲሁም ከግራና ቀኝ የተተከሉት አዳዲስ መብራቶች… መሬት ላይ “የተተከሉ” አይመስሉም። የብርሃን ዐምድ ላይ የተንሣፈፉ የብርሃን ክንፎች ይመስላሉ። ወጪ ወራጁን ለመጠበቅና ለማስተናገድ የተዘረጉ ብርሃናማ ክንፎች ናቸው ብንላቸው አይበዛባቸውም።
አቶ ጥራቱም፣ በቦሌ መገናኛ መስመር የተዘረጋው የመንገድ መብራት፣ ከተማችንንና አገራችንን ከፍ የሚያደርግ ነው ይላሉ። የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚያሟላ መሆኑ አንድ ነገር ነው። ግን ደግሞ ወደ ፊትም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲራመድ ተደርጎ እንደተሠራ አቶ ጥራቱ ተናግረዋል።
ለነገሩ ዝርዝሩን ሁሉ የማያውቅ ተመልካችም መመስከር ይችላል። ከዳር እስከ ዳር መንገዱንና አካባቢውን አድምቀዋል። ለእይታ ይማርካሉ። ግን መብራት ብቻ አይደሉም።
ጥራት ያላቸው ስክሪኖች ይዘዋል። ካሜራ ተገጥሞላቸዋል።
“ዋይፋይ” የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ይጠቅማሉ። ባትሪ ቻርጅ ለማድረግ ያገለግላሉ። ለተሽከርካሪዎችም ለእግረኞም አስፈላጊ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲያስፈልግም ችግር የለም። “ስፒከር” አላቸው። ሁሉም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሳሰሩ ናቸው።
መንገደኞችና አሽከርካሪዎች የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በኢንተርኔት ለማየትና ለመከታተል የሚችሉበት ቴክኖሎጂም ተሟልቶላቸዋል።
ኢትዮቴሌኮም የአገራችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋም እንደሆነ አቶ ጥራቱ ጠቅሰው፣ የመብራትና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሥራዎችን በኀላፊነት ወስዶ በብቃት እንዳከናወነ ገልጸዋል። እናም፣ “የመንገድ መብራት” ብለን ብንጠራቸውም፣ ዓለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የዘመናችን ቴክኖሎጂዎችን ያሟሉ ነው። የመጪው ዘመን ቴክኖሎጂስ?
መቼም፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በየጊዜው እየተሻሻለና እየጨመረ ይሄዳል እንጂ፣ አሁን ባለበት አይቆምም። ለዚህም ታስቦበታል ይላሉ - አቶ ጥራቱ። አሁን የተተከሉት መብራቶች፣ ወደ ፊት የሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ እያካተቱና ደረጃቸውን እያሳደጉ እንዲቀጥሉ ተደርጎ ነው የተሠሩት። የኤሌክትሪክ ገመድ መቁረጥና መቀጠል አይኖርም። ከማዶና ከማዶ ሽቦ መተብተብ አይኖርም። እንደገና መቆፈርና ማፍረስ አይኖርም። ወደ ፊት ቴክኖሎጂዎችን ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ነው የመሠረተ ልማት ግንባታ የተካሄደው።
የቀድሞው የቀለበት መንገድና አዲሱ የቦሌ መንገድ
ከሀያ አምስት ዓመት በፊት “የቀለበት መንገድ” ሥራ ሲጀመር፣ በአገልግሎቱና በጥራት ደረጃው ከሌሎች የከተማዋ መንገዶች የተሻለ ይሆናል ተብሎ ነበር። በእርግጥም ደህና አገልግሏል።
የቀለበት መንገዱ ከችግሮች ባያመልጥም፣ ጉድለቶቹ ቀስ በቀስ እየገዘፉ ቢመጡም፣ ለጊዜው ጠቃሚ አገልግሎቶች ነበሩት ይላሉ በምክትል ከንቲባ ማዕርግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ። ነገር ግን፣ ከከተማዋ ዕድገት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።
“ቀለበት” ተብሎ ነው የተሠየመው። ግን እንደ ስሙ አልሆነም። በከተማዋ ዳርቻ ዙሪያዋን የሚቅፍ መንገድ ይመስላል - ስያሜው። ግን አይደለም። ገና ከመነሻው በከተማዋ ዳርቻ ላይ አልተሠራም። በከተማ ውስጥም ነው መንገዱ የተገነባው። ዛሬ ደግሞ የከተማ መሀል ሆኗል ማለት ይቻላል።
ሌላው ይቅርና፣ ያኔ ብዙ ነዋሪ ያልነበራቸው አካባቢዎችም ዛሬ ብዙ ሕዝብ ይኖርባቸዋል። ሰፋፊ የሥራና የንግድ ማዕከላት ሆነዋል። በመገናኛ ቦሌ መንገድ፣ ከ25 ዓመት በፊት “ገርጂ” አካባቢ ብዙ ነዋሪ አልነበረም ቢባል እንኳ፣ ዛሬ ግን የከተማ መሀል ሆኗል።
መቼም የመንገድ አገልግሎት፣ ከቦታ ቦታ በፍጥነት ለመድረስ ነው። እናም፣ “ጊዜን ይቆጥባል” ወይም ደግሞ “የተራራቁ አካባቢዎችን ያቀራርባል” ብለን ልንገልጸው እንችላለን። የቀለበት መንገዱስ?
በብረት የታጠረው የቀለበት መንገድ፣ ከተማ መሀል ውስጥ ተዘርግቶ ከተማውን ከማዶና ከማዶ ከፍሏል። ጎረቤት ሰፈሮችን ለያያቷል። ቅርብ ለቅርብ የሆኑትን አካባቢዎች አራርቋል። ከመንገዱ ማዶ ለመሻገር፣ አንድ ኪሎ ሜትር ሁለት ኪሎ ሜትር መጓዝ የግድ ሆኗል። ጊዜ የሚቆጥብ ሳይሆን ጊዜ የሚፈጅ ከሆነ… ችግር አለው።
በቂና አመቺ የእግረኞች መሸጋገሪያ እንዳልነበረው አቶ ጥራቱ ገልጸው፤ ተሽከርካሪዎችም ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለመሄድ የማቋረጫና የማዞሪያ አማራጭ በቅርበት የሚያገኙበት ዕድል አልነበራቸው ብለዋል።
ለነገሩ፣ የብረት አጥሩ እንዲሁ ሲታይም ለእይታ አያምርም። ነገር ግን ዋናው ችግር እሱ አይደለም። አመቺ መሸጋገሪያ ባለመኖሩ፣ አጥር ዘለው መንገድ ለመሻገር የሚሞክሩ እግረኞች ላይ ብዙ አደጋ ደርሷል።
ይህም ብቻ አይደለም።
የአዲስ አበባ የመኪኖችና የእግረኞች ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ የገለጹት አቶ ጥራቱ፣ የቦሌ መገናኛ መስመር ላይ የነበረው የቀለበት መንገድ ይህን በብቃት ማስተናገድ አልቻለም ብለዋል።
የመገናኛ መስመር ከጥዋት እስከ ምሽት የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚበዛበት መስመር ነው። መንገዱ ይጨናነቃል። መንቀሳቀሻ ይጠፋል። መኪናና እግረኛ ሲጋፋ ይውላል ማለት ይቻላል።
በፍጥነት ለመተላለፍ መንቀሳቀሻ ያጡ መኪኖች ተደረድረው ስንዝር ስንዝር ሲንፏቀቁ፣ የሥራ ሰዓት ይባክናል፤ የጉዳይ ቀጠሮ ይስተጓጎላል። አምስት ደቂቃ የማይፈጅ መንገድ፣ የአንድ ሰዓት እንግልት ይሆናል። ነዳጅ ይቃጠላል። የተሳፋሪዎችና የአሽከርካሪዎች መንፈስ ላይ የሚያሳድረው ጭንቀትም የዚያኑ ያህል ነው። ኑሮም መንፈስም ይረበሻል።
ይህን ሁሉ የሚፈታ ነው - በኮሪደር ልማት የተሠራው አዲሱ የቦሌ መንገድ።
ይህም ብቻ አይደለም።
ትልልቅ ተቋማት በመገናኛ ቦሌ መስመር ላይ ቢኖሩም፣ አካባቢው ለተጨማሪ አገልግሎት የሚያመች ቅርጽ አልያዘም ነበር። በሰፋፊ ግቢ ትልልቅ የመንግሥትና የቢዝነስ ተቋማት የሚገኙበት መስመር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጥራቱ፣ ሞኢንኮ፣ አምቼ፣ ኒያላ ማተርስና አንበሳ አውቶብስን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ነገር ግን፣ የመገናኛ ቦሌ መስመር ለሥራና ለግብይት ከፍተኛ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል መስመር ቢሆንም አገልግሎቱን ለማዘመንና ለማሻሻል ተመቻችቶ አልተሠራም። መገናኛ አደባባይ አቅራቢያ የሚገኝ አካባቢ በተለይ ትንሽ ከመሸ በኋላ፣ ጭር ማለት አልነበረበትም።
አሁን ግን ለተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት ተመቻችቷል። የካፊቴሪያና ንግድ መደብሮች፣ የመዝናኛ ቦታዎችና የመጸዳጃ ስፍራዎች ተሠርተዋል።
ይህም ብቻ አይደለም።
የአገራችንና የከተማችንን በጎ ገጽታ የሚመሰክር!
አቶ ጥራቱ እንደሚሉት፣ የቦሌ መገናኛ መስመር፣ ከመላው ዓለም የሚመጡ እንግዶችን የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት የኢትዮጵያ መግቢያ በር ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተተውና አሁን የተጠናቀቀው የመገናኛ ቦሌ መስመር፣ ዘንድሮው በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ወደ ጫካ ፕሮጀክት ከሚዘልቀው መስመር ጋር የሚገናኝ ነው።
አዲስ አበባ… የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲናም ናት። የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልም ናት። ከዚህም በተጨማሪ፣ አገራችንና ከተማችን፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቱሪዝም በዓለም ዙሪያ ተመራጭ የመሆን ትልቅ ዐቅም አላቸው።
የቦሌ መገናኛ መስመር፣ ለዚህ ሁሉ የሚመጥን የጥራት ደረጃና ውበት ሊኖረው ይገባል። የአገራችንና የከተማችንን በጎ ገጽታ የሚያሳይና የሚመሰክር መሆን አለበት።
የከተማችን አኗኗር የሚያሻሽል፣ ኢኮኖሚን የሚያሳድግ፣ ለመኪኖችና ለእግረኞች እንቅስቀሴ የሚያመች፣ የከተማችንና የአገራችንን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት ታስቦበት ዲዛይን እንደተዘጋጀ ገልጸዋል - አቶ ጥራቱ። ግንባታውም በጥራትና በፍጥነት እንደተሠራ ተናግረዋል።
አንድ የቀረ ሥራ አለ።
ለእግረኞችና ለመኪኖች ጭንቅንቅ ትልቅ እፎይታ!
በምድር ሥር ለእግረኞች ከሚዘጋጁት ሁለት መተላለፊያዎች መካከል አንዱ ተገንብቶ ተጠናቅቋል። ሁለተኛው ግን በዚህ ሳምንት ነው የተጀመረው። ለምን?
ሁለት የምድር ሥር መተላለፊያዎችን በአንድ ጊዜ ለመሥራት መንገዱ ሁለት ቦታ ላይ ከተዘጋ፣ ከጫፍ ጫፍ መንገዱን እንደመዝጋት ነበር የሚሆነው። በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልት ያስከትል ነበር። ለዚህም ነው፤ በየተራ ግን በፍጥነት ለመገንባት የተመረጠው።
ሰሞኑን የተጀመረው የምድር ሥር መተላለፊያ፣ 53 ሜትር ርዝመት አለው። ሰፊ ነው። በውስጡ በርካታ ሱቆችና አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይኖሩታል። ቢሆንም ግን በ45 ቀን ግንባታው እንደሚጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አቶ ጥራቱ ቃል ገብተዋል።
ለዚህም በቂ ዝግጅት ተከናውኗል። የግንባታ ማሽኖችና የግንባታ ቁሳቁሶች አዘጋጅተናል። በየቀኑ በ3 ፈረቃ፣ 24 ሰዓት እንሠራለን። በታቀደው ጊዜ ወይም ከዚያ በፊት እናጠናቅቃለን ብለዋል - አቶ ጥራቱ። በመገናኛ አካባቢ ለሚታየው የእግረኞችና የመኪኖች ጭንቅንቅ ትልቅ እፎይታ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የምንጀምርበት ዓመት ነው”
“የጀመርናቸውን የሪፎርም ስራዎችን አጠናቀን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የምንጀምርበት ዓመት ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። በዘንድሮ ዓመት 300 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በቀጣናው ከፍተኛ የስንዴ አምራች ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ወዲህ ባሉት ሦስት ወራት “ተገኝተዋል” ያሏቸውን አንኳር ድሎችን ጠቃቅሰዋል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ6 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት የግብርና ዘርፉ 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።
በዚህ ዓመት 72 ያህል የሚሆኑና ከፋብሪካ በላይ የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች ማምረት እንደሚጀምሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ከኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ከኮንስትራክሽን 12 ነጥብ 3 በመቶ፣ ከአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 7 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲን ተግባራዊ ካደረገች በኋላ ባሉት ሦስት ወራት የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ገንዘብ የ161 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የግል ባንኮች መጠባበቂያም በ29 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡
በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት የሚላክ የገንዘብ መጠን (ሬሚታንስ) ደግሞ 24 በመቶ ዕድገት አምጥቷል ነው ያሉት - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ከሪፎርሙ በኋላ ባሉት ሦስት ወራት 652 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት፣ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሸጣቸውን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል። ሀገሪቱ ባፀደቀችው የአራት አመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር፣ 27 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ሀገሪቱ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
አገሪቱ ባለፉት ሦስት ወራት ከኤክስፖርት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የገለጹት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተመሳሳይ ጊዜ ከታክስ የተሰበሰበው ገቢ 170 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከፌደራል መንግሥትና ከክልሎች ባጠቃላይ 1.5 ትሪሊዮን ብር የታክስ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ ግብር ከማይሰበስቡ አገራት አንዷ መሆኗን ጠ/ሚኒስትሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
“ላለፉት ስድስት ዓመታት የማፍታታት ስራ ስንሰራ ቆይተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዓመት የምንጀምር ይሆናል” ብለዋል፡፡
የመክሳቷ ብዛት፤ የቸኮለ ይቀብራታል
ቤሣ ቤስቲን የሌለውና የሚልሰው የሚቀምሰው ያጣ አንድ ልብስ-ሰፊ፣ ጫካ ለጫካ ሲዞር አንድ አይሁዳዊ ነጋዴ ያገኛል፡፡ በልቡ “መቼም ይሄ አይሁድ መዓት ብር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እሺ ቢል በደግነት፣ እምቢ ቢል በጉልበት፣ ያለ የሌለውን ገንዘብ ሊሰጠኝ ይገባል” ብሎ አሰበ፡፡
ወደ አይሁዱም ዘንድ ሲደርስ፣
“ያለ የሌለህን ገንዘብ አምጣ፡፡ አለበለዚያ አሳርህን ታያለህ፡፡ ከዚያም አሻፈረኝ እላለሁ ካልክ ህይወትህን ትከፍላለህ” አለው፡፡
አይሁዱም፤
“ወዳጄ፣ እኔም እንዳንተው ገንዘብ የቸገረኝ ሰው ነኝ፡፡ ኪሴ ውስጥ ያለችኝ ሁለት ብር ብቻ ናት፡፡ ያም ሆኖ ካንተ ችግር የእኔ ይብሳል የምትል ከሆነ፤ ግዴለም አንድ አንድ ብር እንካፈል” አለው፣ በትሁት አንደበት፡፡
ልብስ - ሰፊው ግን አይሁዱ የሚለውን አላመነም፡፡
“ደሞ አይሁድ መቼ ነው ገንዘብ አጥቶ የሚያውቀው? አንተ ቀጣፊ እኔን ለማጭበርበር ፈልገህ ነው?” ብሎ፤ በያዘው በትር ይመታዋል፡፡ አይሁዱ ይወድቃል፡፡ የወደቀው አንድ ድንጋይ ላይ ኖሮ ጭንቅላቱን ከፉኛ ይጎዳዋል፡፡ ብዙ ደምም ይፈስሰዋል፡፡ ህይወቱ ጣር ላይ ትሆናለች፡፡ ነብሱ ከመውጣቷ በፊት፤
“ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች!” አለ፡፡
ከዚያም ህይወቱ አለፈች፡፡
ገዳዩ የአይሁዱን ኪስ እየፈተሸ ገንዘብ መፈለጉን ቀጠለ፡፡ ያገኘው ግን ያቺኑ አይሁዱ ያላትን ሁለት ብር ብቻ ነበር፡፡ እሷኑ ወስዶ ሲያበቃ፣ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ጫካው ሰዋራ ስፍራ ጥሎ መንገዱን ቀጠለ፡፡
ከጫካው ርቆ ሲሄድ ውሎ ወደ አንድ ከተማ ደረሰ፡፡ እዚያም ዋለ አደረና እድል ቀንቶት አንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ፡፡ ከዓመት ዓመት እድገት እያገኘም ሄደ፡፡ ሰንብቶም የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነ - ግን እጅግ ክፉ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ተንኮለኛ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ሰው ሁሉ የሚጠላው ሥራ አስኪያጅ፤ ሆነ፡፡ ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥርም ባለፈው ግፍና በደሉ ተፀፅቶ ደህና ይሆናል ሲባል፤ ጭራሽ ክፋቱ ባሰበት፡፡ ሰውነቱ ግን ከቀን ቀን እየከሳና እየመነመነ ሄደ፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው “የመክሳቷ ብዛት፤ የቸኮለ ይቀብራታል፤ እያለ ይሳለቅበት ጀመር፡፡
የኩባንያው ባለቤት አንዲት ቆንጆ ልጅ ነበረችው፡፡ ይህቺ ልጅ ይህንን ሥራ አስኪያጅ ታፈቅረዋች፡፡ እሱም ያፈቅራታል፡፡ ይጋቡና ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ይወልዳሉ፡፡
ከዚያ በኋላ የኩባንያው ባለቤትና ሚስትየው ሲሞቱ፤ ልብስ ሰፊውና ወጣቷ ባለቤቱ ኩባንያውን ይወርሳሉ፡፡
አንድ ቀን ያ ልብስ ሰፊ ቤቱ፤ መስኮቱ አጠገብ ተቀምጦ፣ ባለቤቱ ያመጣችለትን ቡና ሊጠጣ ስኒውን ወደ አፉ ሲያቀርብ፤ በመስኮቱ የምትገባዋ ፀሀይ ቡናው ላይ ስታንፀባርቅ፣ ግድግዳው ላይ የክብ ቀለበቶች ምስል ሰራች፡፡ ልብስ - ሰፊውም “አይ ፀሐይ! ሚስጥሬን ወደ ብርሃን ልታወጪ እየሞከርሽ ነው፡፡ ግን አትችይም” አለ፡፡
አጠገቡ ሆና ይህን ስትሰማ የነበረችው ባለቤቱ በጣም ደንግጣ፤
“የሰማያቱ ያለህ! ብቻህን ታወራ ጀመረ? ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ፀሀይ የምታወጣው ሚስጥርስ ምንድነው?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
ልብስ -ሰፊውም፤ “ይሄንን ልነግርሽ አልችልም” ይላታል፡፡
እሷም፤ “እውነት ከልብህ የምታፈቅረኝ ከሆነ ንገረኝ፡፡ የምትነግረኝን ሚስጥር ከአፌ አንዲት ቃል ላላወጣ ቃል እገባልሃለሁ” አለችው፡፡ ከዚያም ካልነገርከኝ ብላ አላስወጣ አላስገባ አለችው፡፡ እረፍት ነሳችው፡፡
በመጨረሻም፣ ለማንም እንደማትነግር ቃል ከገባችለት በኋላ፤ ከዓመታት በፊት አይሁዱን እንዴት እንደገደለውና ከመሞቱ በፊትም፣ “ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች” እንዳለው ነገራት፡፡ ቀጥሎም “ታዲያ በአሁንዋ ቅጽበት ፀሀይ በመንፀባረቋ ግድግዳው ላይ ቀለበት ስትሰራ አይቼ፣ ፀሐይን ’አትልፊ ጉዱን አታወጪውም‘ ስል ሰምተሽ አንቺ ጠየቅሺኝ” አላት፡፡ “ግን ነግሬሻለሁ፣ ለማንም እንዳትናገሪ!” ሲል ደጋግሞ አስጠነቀቃት፡፡ እሷም ደጋግማ ቃል ገባች፡፡
ልብስ ሰፊው ወደ ስራው ሲሄድ ሚስቱ የምትወዳት ጓደኛዋ ጋር ሄዳ ሲጨዋወቱ፤ በጣም ስለምታምናት፤ ታሪኩን ነገረቻት፡፡ ከዚህ ወዲያ ሦስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድፍን አገር አወቀው፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ እንዲሉ፡፡
ልብስ ሰፊው ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ለዓመታት ሲመላለስ ቆይቶም በመጨረሻ ሞት ተፈረደበት፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ ብሩህዋ ፀሀይ ግን ጉዱን ወደ ብርሃን አወጣችው፡፡
* * *
ማናቸውም ክፉ ተግባር፣ ማናቸውም ጉድ የማታ ማታ ወደ ብርሃን ይወጣል፡፡ ብሩህዋ ፀሀይ ከማጋለጥ ወደ ኋላ አትልም፡፡ “ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን” ይሏልና፣ በሌላው ላይ የጎነጎኑት ተንኮል፣ የሸረቡት ሴራ፣ ጊዜ አመቸኝ ብሎ የዋሉት ግፍ፤ ጊዜው ይጠርም፣ ይርዘምም ሰሪውን እንደ ጥቁር ጥላ ተከትሎ መምጣቱና በአደባባይም መታየቱ፤ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታና ህብረ - ቀለም ያላቸውን ማህበረሰብ ባቀፈችው ሀገራችን እየተካሄደ ባለው የዲሞክራሲን መሰረት የመጣል ረዥም ጉዞ ውስጥ፣ ለለውጥ ስንዱ የሚያደርጉን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ተመቻችተው ሳለ፤ ለውጡ የተሸራረፈ አሊያም ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ያደረጉ አያሌ ክስተቶችን አይተናል፡፡
ከቶውንም የመሰረት ደንጊያ፣ ልስንና ማገር ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉትን እሴቶች፣ ማለትም የሰብዓዊ መብቶችን፣ ፍትህና ርትዕን፣ የዲሞክራሲያዊ መብት አላባውያንን ወዘተ ሁሉ በአግባቡ ውል ለማስያዝ እንዳይቻል፣ በየጊዜው እንቅፋት የሆኑ አያሌ ክስተቶችን አስተውለናል፡
በመንግስትነት ደረጃም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ፣ በውስጣዊ መሰነጣጠቅም ሆነ በውጫዊ ተጽእኖ፣ ለዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል ከሀገር በፊት ፓርቲንና ድርጅትን ፍጹም በሆነ መልኩ ማስቀደም፣ ስልጣንን ለማጋራት ቅንና ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለመከተልና ከእኔ ወዲያ ላሳር ማለት፤ ሙስናዊ አካሄድ ማዘውተር፣ ላልተዘጋጁበት ድልም ሆነ ሽንፈት ብስለት ያለው ምላሽ አለመስጠትና እርስበርስ ሲጠላለፉ መኖር፣ አንኳር አንኳሮቹ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየአንዳንዷ እርምጃ ውስጥ ህዝቡን አለማሰብ ዋና እንከን ነው፡፡ የህንድ መሪ የነበሩት ማህተመ ጋንዲ በትግሉ ወቅት ያሉትን መጥቀስ እዚህ ጋ ፋይዳ ይኖረዋል፡- በወቅቱ ለጨቋኞቹ ገዢዎች ያሏቸው ይህንን ነበር፡-
“እንዳሻችሁ ልትቆራርጡንና ልትበጣጥሱን ትችላላችሁ፡፡ በመድፍ አፍ ላይ እያሰራችሁ ብትንትናችንን ልታወጡንም ትችላላችሁ፡፡ ምንም አድርጉ ምን ከእኛ (ከህዝቦች) ፈቃድ ውጪ ለምታደርጉት ማናቸውም ድርጊት ቅንጣት ድጋፍና እርዳታ አናደርግላችሁም፡፡ ያለ እኛ ድጋፍና እርዳታ ደግሞ አንድም እርምጃ ወደፊት እንደማትሄዱ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እርግጥ ይሄንን ስናገር በስልጣን ሰክራችሁ ከት ብላችሁ ትስቁ ይሆናል፡፡”
የህዝቡን የልብ - ትርታ ከልብ ማድመጥና ለዲሞክራሲያዊነት ግልጽ - ተገዥነት ካሳየንና አልፎ ተርፎም “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሳንል ስህተትን ለማረምና ለመቻቻል ሆደ - ሰፊነቱን ካደለን ደረጃ በደረጃ ወደ ሰለጠነና ወደ በለፀገ ህብረተሰባዊ እርከን ለመሸጋገር እድሉ ይኖረናል፡፡ ራሳችንን ከድርጅታዊ ቅጽር ማውጣት ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ በሰፊ ግቢ ውስጥ እንዳለና ብዙ መጫወቻ እንደተገዛለት የሀብታም ልጅ፣ በወጉ እንኳ ሳንጠቀምባቸው መጫወቻዎቹ የጎረቤት ሲሳይ ይሆናሉ፡፡
የዘመኑ ጀግንነት ዲሞክራሲያዊነት እንጂ ማናቸውም የኃይል እርምጃ አይደለም፡፡ የሥልጣኔ ቆራጥነት በውይይትና በምክንያታዊ ሙግት መረታታት እንጂ እያደቡ መጠፋፋትና አንዱ ለአንዱ መቃብር መቆፈር አይደለም፡፡ ከየመንገዳችን ሁሉ በኋላ ዛሬም አገርና ህዝብ አለ፤ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡
የትላንት ታሪካችንን ለማደስ ዝግጁ አለመሆን ክፉ እርግማን ነው፡፡ ከስልጣን ውጣ - ውረድ፣ ከፓርቲ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ባሻገር የአገር አደራ መኖሩን አለመርሳት የታላላቅ ፖለቲካዊ መሪዎች ሁሉ እፁብ ዓላማ ነው፡፡ ያለፈ ስህተታችንን ለማረም ልቦናችን ውስጥ አንዲት የመፀፀቻ ጥግ ልትኖረን ይገባል፡፡
“በአማራና በተለያዩ አካባቢዎች እስር ቤቶች የተጨናነቁት ያለፍርድ በታጎሩ አማራዎች ነው” - የም/ቤት አባል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “አማራ ክልል፤ የብልጽግና መንግስት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም መንግስት አግኝቶ አያውቅም” ሲሉ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ አባላት መካከል የአማራ ክልልን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያነሱት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር አበባው ደሳለው ይገኙበታል፡፡
“በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብሶት አለ። በተለይም በአማራ ክልል ያለው ችግር ደግሞ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ምስቅልቅል እንዲሆን ያደረገ ነው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ “አሁንም ንጹሃን ዜጎች በከባድ መሳሪያና በድሮን እየሞቱ ነው። ሲቪል ተቋማት የሚባሉ የጤና ጣቢያና ትምህርት ቤቶች እየወደሙ ነው። በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልልና በተለያዩ አካባቢዎች እስር ቤቶች የተጨናነቁት ያለፍርድ በታጎሩት አማራዎች ነው” ብለዋል።
ዶ/ር አበባው ለጥቀውም፤ “መንግሥት የሰላምና የፀጥታ ችግርን ለመፍታት እየሄደ ያለው አካሄድ ወታደራዊ ነው፡፡ ፖለቲካዊ አካሄድን ለምን አልደፈረም? ለምንድን ነው ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ መንግሥት የደከመው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ አክለውም፤ “ለእውነተኛ ድርድርና ውይይት በይፋ ጥሪ አቅርቦ ችግሩን ለምንድን ነው ለመፍታት የማይተጋው? የጅምላ እስር፣ የጅምላ ግድያስ የሚቆመው መቼ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችንም ሰንዝረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ምላሽም፤ “በአማራ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር አለ፤ ነገር ግን ንግግር የሚያደርጉትንና ሰላም የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት ከዚህ መንግሥት ጋር ትነጋገራለህ ብለው የሚወቅሱ ሰዎች አሉ” ሲሉ ለንግግር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ጠቁመዋል፡፡
ከሃይል እንቅስቃሴ ይልቅ ሰላም “እጅግ አዋጭ” መሆኑን የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ከልጅነት አንስተን ክላሽ ተሸክመን ስለኖርን ጉዳቱ ይገባናል። ጦርነትን በወሬ ሳይሆን በተግባር እናውቀዋለንና አንፈልገውም። ብዙዎችን ቀጥፎብናል አንፈልገውም” ሲሉ ተናግረዋል።
“አማራ [ክልል]ን ባለፉት ሰድስት ዓመታት የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል። [ይህን] የማያምን ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባህር ዳር፣ ቡሬ ሄዶ ይቁጠር። ጨርቃ ጨርቅ፣ ሲሚንቶ፣ ማርብል፣ ግራናይት፣ የዘይት ፋብሪካ ብዙ ብር አግዘን አማራ ክልል አቋቁመናል” በማለት አስረድተዋል።
“አማራ ክልል የብልጽግና መንግስት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም መንግስት አግኝቶ አያውቅም። በወሬ ስለተደባበቀ እንዳትሸወዱ።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ጎንደር ከተማን በምሳሌነት በመጥቀስ “ያን ስልጡን ሕዝብና አገር ከ70 እና 80 ዓመት በኋላ ዞር ብሎ የሚያየው መንግስት ያገኘው አሁን ነው።
ፋሲል ቀንና ማታ እየተገነባ ነው፣ መስቀል አደባባይ የአዲስ አበባውን መስቀል አደባባይ በሚያኽል መንገድ እየተገነባ ነው። ፒያሳ እያሸበረቀ ነው። መገጭን 18 ዓመት ከቆመ በኋላ 7 ቢሊዮን ብር መድበን ቀንና ማታ እየሰራን ነው።” ብለዋል።
የማዳበሪያ ስርጭትን በሚመለከት፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ቀበሌዎች ከፍተኛ ስርጭት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “አማራ ክልል እንዲቀየር እየሞከርን ነው።” በማለት ተናግረዋል።
የጋዜጠኞችና የማሕበራዊ ሚዲያ አንቂዎች መታሰርን በተመለከተ ለቀረበ ቅሬታ በሰጡት ምላሽ፤ “አንድ እግር ሲኦል፣ አንድ እግር ገነት አኑሮ መቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም። ወይም የገነትን ፍሬ መብላት፣ ወይም የሲኦልን እሳት መቅመስ ነው። አንዳንድ ሰዎች እዚህም ሰላም ውስጥ አሉ፣ እዛም ጦርነት ውስጥ አሉ፤ የመረጃ ችግር ያለብን እንዳይመስላችሁ።” ሲሉ አብራርተዋል፣ አስጠንቅቀዋልም፡፡
“ባለፉት ስድስት ዓመታት አማራን የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል፡፡ አማራ ክልል የብልጽግና መንግሥት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም ዘመን አግኝቶ አያውቅም፡፡ የአማራ ክልል ላይ እኛ ልማት ነው እያመጣን ያለነው፤ ልማቱን እንደልባችን እንዳንሰራ ያደናቀፉን ሰዎች ግን አሉ” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ተችተዋል፡፡
ከጅምላ እስር ጋር በተያያዘ ከም/ቤቱ አባል ለተነሳው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሲመልሱ፤ “በጅምላ የፓርላማ አባላት፣ በጅምላ የፖለቲካ ሰዎች የምናስር ቢሆን እርስዎም ይታሰሩ ነበር። በጅምላ አይደለም፤ በግብር ነው ሰው የሚታሰረው” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ አክለውም፤ ”የግል ምርጫዬን ከጠየቁኝ እኔ ‘ቢቀር’ ነው የምለው። ይቅር ተባብለን፣ ትተን፣ በደለኛ ካለ ክሰን በሰላም አገራችንን እናልማ። ከዚህም ይውጣ፣ ከዩኒቨርሲቲም ይውጣ፣ ከከተማ እስር አይጠቅምም፤ ግን መንግስት ነን፤ መኖሪያ ቤት እንገነባለን፤ ማረሚያ ቤትም እንገነባለን።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጋሽ ማህሙድ አሕመድ የግማሽ ክ/ዘመን የሙዚቃ ጉዞ፣ በታላቅ ኮንሰርት ሊቋጭ ነው
የጋሽ ማህሙድ አሕመድ የመጨረሻ የሙዚቃ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ የሙዚቃ መድረክ ላይ ጥቂትና የተመረጡ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተነግሯል።
ትናንት ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ላሊበላ አዳራሽ ስለ ኮንሰርቱና ስለ አንጋፋው ድምጻዊ የሙዚቃ ህይወት ስንብት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው አርቲስት አብርሃም ወልዴ፣ የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር መስራችና ባለቤት አቶ አጋ አባተን ጨምሮ ሌሎች አባላትን ያካተተው የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ በመግለጫው ላይ እንዳብራራው፤ “ሰው በሕይወት እያለ የማመስገንና የማክበር ባህልን ለመጀመር ጋሽ ማህሙድ ትክክለኛ ሰው ነው።” ብሏል፡፡ ኮሚቴው አክሎም፤ “ታላቅን ማክበር በተዘነጋበት ዘመን ዝቅ ብሎ ታናሹን የሚያከብር ሰው” መሆኑ ለተመሰከረለት ጋሽ ማህሙድ፤ በህይወት እያለ ማክበርና ማመስገን ተገቢ እንደሆነ የኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መግለጫ እንደተነገረው፤ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. “ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ኮንሰርት” በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን፤ 25 ሺ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኮሚቴው አባላት አንዱ የሆነው አርቲስት አብርሃም ወልዴ ኮንሰርቱን በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ፤ “የጋሽ ማህሙድን ክብር በጠበቀ ሁኔታ፣ ጥቂት ነገር ግን ምርጥ ድምጻውያን የሚያቀነቅኑበት መድረክ ነው የሚሆነው” ሲል ተናግሯል።
የሙዚቃ ኮንሰርቱን የሚያዘጋጀው ላለፉት 10 ዓመታት ኮንሰርቶችንና ሌሎች ኹነቶችን በጥራትና በስኬት በማዘጋጀት ዕውቅናን ያተረፈው ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር
መ
ኑ ታውቋል፡፡
በዘርፉ ስላለው ልምድና ብቃት ምስክርነቱን የሰጠው አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ዛሬ ራሱ በሸራተን አዲስ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥሩ ማሳያ ነው ብሏል፤ በአድናቆት፡፡ በእርግጥም ሌሎች እንግዶችና ጋዜጠኞችም የሸራተኑ ጋዜጣዊ መግለጫ የተዘጋጀበትን ውበትና ድምቀት አወድሰዋል - መግለጫ ሳይሆን የኮንሰርት ዝግጅት ነው የሚመስለው በማለት፡፡ ከሙዚቃ ኮንሰርቱ በተጨማሪ፣ ለጋሽ ማህሙድ መታሰቢያ የሚሆንና በውጭ አገር የተቀረጸው ሐውልት አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚቆም ያስረዱት የኮሚቴው አባላት፣ በድምጻዊው ስም መንገድ እንደሚሰየምም አብራርተዋል። ከመንገድ እና አደባባይ ስያሜ ጋር በተገናኘ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን ገልጸው፣ እስከ ኮንሰርቱ መዳረሻ ቀን ድረስ “ጉዳዩ ውሳኔ ያገኛል ብለን እናምናለን” ሲሉ ቴስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ከኮሚቴው አባላት አንዷ የኾነችው እንስት በሰጠችው አስተያየት፤ ጋሽ ማህሙድ በህይወት ሳለ በስሙ መንገድ ተሰይሞለት፣ ሃውልት ቆሞለት ቢያይ፣ ለእኛ የሕይወት ዘመን ስኬታችን ነው ብላለች፡፡
ኮንሰርቱ በሚካሄድበት ዕለት 10 ዓመት ገደማ እንደፈጀ የተነገረለት የጋሽ ማህሙድ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ እንደሚመረቅ እንዲሁም፣ የመንገድ ስያሜውና የሃውልቱ መቆም እንደሚበሰር የኮሚቴው አባላት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የአንጋፋው ድምጻዊ የመጨረሻ የሙዚቃ ሲዲ ተሰርቶ መጠናቀቁን የገለጸው አብርሃም ወልዴ፤ ሥራው ሙሉ በሙሉ አዲስ እንደሆነና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መሰራቱን ጠቁሟል፡፡
በ550 ገጾች የተቀነበበውና በጋሽ ማህሙድ አሕመድ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው መጽሐፉ፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ በንብ ባንክ ድጋፍ ለህትመት መበቃቱን ጋዜጠኛ ወሰንየለህ ደበበ ተናግረዋል። “የ2017 ጥር ወር ታላቅ የኪነ ጥበብ ገጸ በረከት አድርገን ለህዝቡ እናቀርበዋለን” ብለዋል፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ።
ጋሽ ማህሙድ ትውልዱን መመረቅ እንዲሁም ዕድሜ ዘመኑን ሥራዎቹን በፍቅር ሲያደምጥለት የኖረውን ሕዝቡን ማመስገን እንደሚፈልግ የገለጹት የኮሚቴው አባላት፤ በመጨረሻ የሙዚቃ ኮንሰርቱ መድረክ ላይም ይህንኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የትዝታው ንጉስ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ጋሽ ማህሙድ፤ “እንግዳዬ ነሽ”፣ “አታውሩልኝ ሌላ”፣ “መላ መላ”፣ “እቴ ገላ” እና ሌሎች ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎችን ያበረከት አንጋፋና ተወዳጅ ድምጻዊ ነው።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያቀነቀነው ጋሽ ማህሙድ፤ እ.ኤ.አ በ2007 ቢቢሲ ራዲዮ አፍሪካ በድንቅ ዘፋኝነቱ ”ቢቢሲ ራዲዮ ዎርልድ ሚዩዚክ አዋርድ“ ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ጋሽ ማህሙድ ለአገራችን የሙዚቃ ዕድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቶታል፡፡