Administrator

Administrator

የትግራይ  ክልል በመላው ኢትዮጵያ እጅግ  ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለውና  በደርግ ዘመነ መንግስት ከተከሰተው የ1977ቱ ረሃብ የከፋ አደጋ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፤ 90 በመቶ የሚሆነው  የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ለከፋ ረሀብና  ለሞት ተጋላጭ መሆኑን አመልክቷል።
በትግራይ የነበረው አውዳሚ የጦርነት አሻራና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ አደገኛ ጥምረት መፍጠራቸውን የጠቆመው የጊዜያዊ አስተዳደሩ  መግለጫ፤  የፌደራል መንግስቱና አለም አቀፍ ተቋማት እያንዣበበ ያለውን  የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ መግለጫው፤በጦርነቱ ወቅት የትግራይ የኢኮኖሚ መሰረት መድቀቅ፣ የጤና ተቋማት መውደምና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የክልሉ  ህዝብ መፈናቀል፣ በትግራይ ብዙዎች ድህነትን መቋቋም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ሲል ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም   የዝናብ እጥረት፣ የአንበጣ መንጋ መከሰትና የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ በክልሉ ያለውን ችግር አባብሶታል ብሏል ።  ይህንን በክልሉ ተከስቷል የተባለውን የረሃብ  አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል  የገንዘብ አቅም  እንደሌለው የገለጸው  ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የፌደራል መንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተከሰተውን የረሀብና የሞት አደጋ ለማስቀረትና ለነዋሪው ሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት  መስራት እንደሚገባቸው ገልጿል። አያይዞም፤  ችግሩ የማይፈታ ከሆነ  ሀገራዊና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ሊያውክ እንደሚችል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ይኸው በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠውና  ክልሉ ከ1977ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ  ውስጥ  ሊገባ ጫፍ ላይ መድረሱን  የሚጠቁመው መግለጫ፤  ፈጽሞ ስህተት  መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ  ዶ/ር ለገሰ ቱሉ    በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ  እንዳስታወቁት፤ በአገር ደረጃ እንዲህ አይነት ቀውስ ሲኖር መታወጅ ያለበት በፌደራል መንግስት በኩል የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በኩል  ነው ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማእከል በማድረግ ተገምግሞ  ነው ብለዋል ። የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል አራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም፣ ከ77ቱ ድርቅና ረሃብ ጋር ይስተካከላል የሚል መረጃ እስካሁን እንዳላወጣም ሚኒስትሩ  ጨምረው ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋ አጋር አካላት እርዳታ ባቆሙበት ሰዓት  መንግስት ፕሮጄክቶቹን ሁሉ  አጥፎ ለትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያቀረበ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂዎችን በባለሙያ ስም በአንድ ቦታ ሰብስቦ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመደበ በጀት እየቀለቡ፣ በምን ሞራል ነው ስለ ትግራይ ህዝብ ረሐብና ስቃይ ማውራት የሚቻለው?” ሲሉም ጠይቀዋል። በህዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም አይነት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደማይኖረውም ገልጸዋል ።

በሽብርና በሙስና ወንጀሎች ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ በነበሩት  በእነ አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) እና በእነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው መዝገቦች ቀርበው የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡ መወሰኑን  ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቋል ።
ክሶቹ እንዲቋረጡ የተደረጉትም  ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንደሆነም ገልጿል ።
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) በ2011 ዓ.ም በክልሉ የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ፣ በቁጥጥር ስር ውለውና ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው  በ1ኛ የህገ-መንግስትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ሲታይ  መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ይኸው በፍርድ ሂደት ላይ የነበረው ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑ ተገልጿል። የክስ መቋረጡን ተከትሎም ከስድስት ዓመታት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ  ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው አስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ ኢሌ ከእስር  መለቀቃቸውም ታውቋል።የቀድሞ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢነጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት  ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከኮርፖሬሽኑ ሥራ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው  በምዕራባዊ ትግራይ በኩል ባታር በተሰኘው አካባቢ  በህዳር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ ክርክር ሲካሄድበት  የቆየ ሲሆን፤ ከራዳር እቃዎች የግዥ ሒደት ጋራ ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ3 ዓመት ከ7 ወር የእስራት ቅጣት ተወስኖባቸውም ነበር።




ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን ጥቃት የሚከታተል ድረገፅ ሥራ ጀመረ

•  የሚዲያ ነጻነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (ኢአማ)፤ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚከታተልና የሚሰንድ ድረ-ገጽ፡- sojethiopia.org  ይፋ አደረገ፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ተዘጋጅቶ ስራ ላይ የዋለው ይህ ድረ-ገጽ (ፖርታል)፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሦስት ቋንቋዎች፡- በአማርኛ ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡

ማኀበሩ ከትላንት በስቲያ በማዶ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ድረ-ገፁ በጋዜጠኞችና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ እስሮችና ግድያዎችን ለመመዝገብ፣ ለመሰነድና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ ድረገፁ በተጨማሪ፣ በማህበራዊ  ሚዲያና  በሌሎችም  መንገዶች  የሚደረጉ  ማንቋሸሽ ፣ ዘለፋ ፣ ስም  ማጥፋትና የመሳሰሉትን በመመዝገብ ፣ በማጣራትና ለቀጣይ ውትወታ ስራዎች ግብዐት በመሰብሰብ መገናኛ ብዙሃን ነፃነታቸው ተጠብቆ በኢትዮጵያ  የዴሞክራሲያዊ  ማህበረሰብ  ግንባታ ሂደት ላይ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል ነው የተባለው፡፡   

sojethiopia.org የተሰኘው ድረ-ገፅ፤ ጋዜጠኞች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሚደርስባቸውን ወከባና  የመሳሰሉ ክስተቶች  ከመከታተልና ከመመዝገብ በተጨማሪ በተለየ ሁኔታ፤ ሴት ጋዜጠኞች በስራ ቦታቸውም ሆነ በጋዜጠኝነት ጉዞአቸው ላይ የሚደርሱባቸውን ፆታዊ ጥቃቶች ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ የሚመዘግብና የመፍትሄ ሒደቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚበጅበት  ማዕቀፍ ነው፡፡


በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስርና የመብት ጥሰቶች በተመለከተ መረጃዎችን የሚያወጡት የውጭ ተቋማት መሆናቸውን የገለጸው የአርታኢያን ማህበር፤ አዲሱ ድረ-ገጽ እኒህን መረጃዎች ከውጭ ሳይሆን ከራሳችን በቀጥተኛ መንገድ ለማግኘት ያስችላል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሚያስተባብረውና ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ የሚያዘጋጀው “የመኢሶን ሰማዕታት” መጽሐፍ ላይ የሚደረግ ውይይት በነገው ዕለት ቀኑ 8፡00 ጀምሮ በጉለሌው የአካዳሚው ቅጽር ግቢ፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የኪነጥበባት ማዕከል ይካሔዳል፡፡
ከዶክተር የራስወርቅ አድማሴ ጋር የሚደረገውን የውይይት ቆይታ ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ይመሩታል፡፡

ሀገራችን በፖለቲካ፡ ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ዘርፎች የገጠሟትን ተግዳሮቶች በመንቀስና ለችግሮችም የመፍትሔ ሀሳቦችን የያዙ በርካታ መጣጥፎችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጦች በማበርከት የሚታወቁት ዶ/ር ታዬ ብርሃኑ፤ "ሕግ እና ሰብአዊነት" የተሰኘ  መጽሐፋቸውን ለሕትመት ብርሃን አብቅተዋል።
መጽሐፉ አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ምስቅልቅል የወለደውን የኢፌዲሪ ሕገመንግሥትን በብርቱ የሚሄስ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከገባንበት ፖለቲካዊ ቅርቃር ለመውጣት ፣ሥርነቀላዊ መዋቅራዊ ማሻሺያ ማምጣት የሚቻልበትን የመፍትሔ ሐሳብም ያመላክታል።
 "ሕግ እና ሰብአዊነት"  በ7 ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ234 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤ በ300 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉን ጃፋር የመጻሕፍት መደብር እንደሚያከፋፍለውም ታውቋል፡፡

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር መፈታታቸው ተሰማ፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉትና እስካሁን በእስር ላይ የቆዩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፤ ከእስር የተለቀቁት ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማንሳቱ መሆኑን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ  እስክንድር ገዛኸኝ እንደተናገሩት፤ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክሳቸው ተነስቶ የተለቀቁት በዛሬው ዕለት  መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል።

ከአቶ አብዲ በተጨማሪም በተመሳሳይ በእሳቸው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ የሌሎችም ተከሳሾች ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪው እንደሚሉት፣ ዐቃቤ ሕግ ባለው ሥልጣን መሠረት የክስ ማቋረጫውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ፣ አቶ አብዲ ከመፈታታቸው ውጪ ለጊዜው የደረሳቸው ዝርዝር ማብራሪያ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አሁን ማረጋገጥ የምችለው አቶ አብዲ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ከማረሚያ ቤት መፈታታቸውን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ስላቀረበው ጥያቄ የደረሰን ነገር የለም” ሲሉ  የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከእስር መውጣታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሲመሩ የነበሩት አቶ አብዲ፣ በክልሉ ውስጥ ከተፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ግድያዎችና የመንግሥት ሀብት ብክነት ጋር ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል።
 
በቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከልም በ2010 ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ውስጥ “በሶማሌ ክልል የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ ‘ሄጎ’ በሚል ስያሜ የሚታወቅ ወጣቶች ቡድን አደራጅተዋል” የሚል ይገኝበታል።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ እንዲሁም ንብረትና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ኢትዮ - ሮቦ ሮቦቲክስ፤ በነገው ዕለት ሐሙስ፣ የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ውድድሩን በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሚጀምር ሲሆን፤ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መርሃ ግብሩ  በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ዓመታዊ የሮቦቲክስ ወድድር መሆኑን የኢትዮ-ሮቦ ሮቦቲክስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይ መኮንን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  በነገው ዕለት የሚጀመረውን የሮቦቲክስ ውድድር አስመልክቶ ከማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ  አቶ ሰናይ መኮንን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

****

እስቲ ታዳጊዎች ባለፉት 6 ወራት በናንተ ማዕከል ውስጥ ስለወሰዱት የሮቦቲክስ ሥልጠና አብራሩልኝ?

ታዳጊዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ፕሮግራሚንግ፣ ዲዛይኒንግ እና ኢንጅነሪንግ ላይ ያተኮረ የሮቦቲክስ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ የመማር በተግባር መርህ ተከትለው በመስራት ለቬክስ ሮቦቲክስ ውድድር ተዘጋጅተዋል፡፡

ልጆቹ ከዚህ ሥልጠና በተጨባጭ የሚያተርፉት ምንድን ነው? በህይወታቸው ላይ ምን ይጨምራሉ?

በእነዚህ ጊዜያት የኢንጅነሪንግ ፣ የዲዛይኒንግ እና  የፕሮግራሚንግ ክህሎቶቻቸውን አሻሽለዋል፡፡ የራሳቸውን አዲስ ነገር የመፍጠርና የመሞከር እድል አግኝተዋል፡፡ በመጪው የዲጂታል ዘመን ውስጥ ብቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡
ባለፈው ጥር ወር በቻይና በተካሄደ ውድድር ላይ ተሳትፋችሁ ተመልሳችኋል? ውድድሩ ምን ይመስል ነበር? ውጤቱስ? በመሰል ዓለማቀፍ  ውድድሮች ላይ መሳተፍ ፋይዳው ምንድን ነው? የኛ ልጆች ከቻይናዎቹ አቻዎቻቸው ጋር ሲወዳደሩ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

ባለፈው ጊዜ በቻይና በነበረን ውድድር አበረታች ውጤት አይተናል፡፡ ለብዙ ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያ ስለነበር፣ ከዚህ በኋላ በሌሎች አለም አቀፍ ውድድሮች ማለትም በአሜሪካና በካናዳ ለሚጠብቃቸው መሰል ውድድር የበለጠ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ ቻይናውያን እጅግ በጣም ከፍተኛ ዝግጅት አላቸው፤ በተለይም በትምህርት ካሪኩለማቸው ሮቦቲክስ እና ፕሮግራሚንግ የተካተተ ስለሆነ፤ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ውጤት በማምጣት በውድድሩ ላይ አንደኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

እስቲ  ነገ ሐሙስ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስለሚጀመረው  የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በጥቂቱ ይንገሩኝ? በውድድሩ ሌሎች አፍሪካውያን ይሳተፋሉ እንዴ?

በነገው እለት በኢሊሌ ሆቴል የሚደረገው የአፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚዘጋጅ አመታዊ የሮቦቲክስ ውድድር ሲሆን፤ በዚህ  ውድድር የተወሰኑ እዚሁ አዲስ አበባ የሚኖሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ ውድድሩን ይበልጥ ሌሎች አፍሪካዊ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

ኢትዮ - ሮብ ሮቦቲክስ ከተከፈተ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? እስካሁን ምን ያህል ተማሪዎች አስመርቃችኋል?

አፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ያልነው፣ ሮቦቲክስ ስንጀምር በአፍሪካ የመጀመሪያዎች እኛ በመሆናችን ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ በ2011 ዓ.ም  እኛ ከብዙ አለም አቀፍ የሮቦቲክስ ኩባንያዎች  ጋር  ስንፈራረም፣ ሌሎች  የአፍሪካ አገራት  ቀድመው አልተፈራረሙም ነበር፡፡ ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አገር ከመሆንዋ አንጻር ለዚህ ውድድር ከሌላ አገር የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡

እናንተ ዘንድ  በሮቦቲክስ ሰልጥነው ትልቅ ቦታ የደረሱ ኢትዮጵያውያን  አሉ?

በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስልጠና  ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ  ወደ አሜሪካና ካናዳ ሄደው ስኮላርሺፕ ያገኙና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እየተማሩ ያሉ፣ ከ100 በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት አገራቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ ለወደፊት ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ስራ አለም ሲገቡ የምናያቸው ይሆናል፡፡ አሁን በስራ ላይ ካሉት ውስጥ  ሳሙኤል አርአያ በኦንላይን ስራ የሚጠቀስ ጎበዝ ልጅ ነው፡፡

ከሮቦቲክስ ሥልጠና ሌላ ቋንቋም ታስተምራላችሁ አይደል?

የቋንቋና የሰልፍ ዲስፕሊን ኮርስም ለህጻናት እንሰጣለን፡፡ በቋንቋ ስልጠናችን ለተማሪዎች ለየት ባለ ሪድ ኤንድ ቴል ፕሮግራማችን፣ ልዩ ልዩ በልምምድ ላይ ያተኮረ  ስልጠና እንሰጣለን፡፡

ኦቪድ ሪልእስቴት፤ “አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ ዕድል” በሚል መሪ ቃል በትላንትናው ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በስካይላይት ሆቴል፣ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ልዩ የቤቶች ሽያጭ በታላቅ ቅናሽ (40 %) ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም የሽያጭ መርሃ ግብር አብዛኞቹ ቤቶች ተሸጠው መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ኦቪድ ሪልእስቴት፤ እነዚህ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች በ4 ምድብና ሳይቶች መካተታቸውን አስታውቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ለህዝብ የቀረበው አንደኛው ፕሮጀክት ጫካ መኖሪያ ቤት ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ጫካዎች ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ 1900 የተንጣለሉ ቤቶች ባለ1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ አፓርትመንቶችን የያዘ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ 9 ሄክታር በሚሸፍን ሰፊ የከተማው አረንጓዴ መስክ ላይ የሚለማ ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ሐረር ሆራይዘን ፕሮጀክት ሲሆን፤ ባለ 2 እና 3 መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርትመንቶችን የያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ሦስተኛው ኪንግስ ታወር ሲሆን፤ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ይዟል፡፡  ኪንግስ ታወር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ያካተቱ 1740 ሰፋፊ መኖሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

አራተኛው አፍሪካን ሃይትስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ጨምሮ 324 ቤቶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ኦቪድ ግሩፕ በሥሩ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ የኮርፖሬት ሆልዲንግ ነው፡፡
ኦቪድ ሪልእስቴት ለአንድ ቀን ባዘጋጀው ልዩ የቤቶች ሽያጭ
ፕሮግራም ላይ  ያቀረባቸው  ቤቶች በሙሉ መሸጣቸውን ገለፀ

ኦቪድ ሪልእስቴት፤ “አንድ ቀን፣ አንድ ህልም፣ አንድ ዕድል” በሚል መሪ ቃል በትላንትናው ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በስካይላይት ሆቴል፣ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ልዩ የቤቶች ሽያጭ በታላቅ ቅናሽ (40 %) ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም የሽያጭ መርሃ ግብር አብዛኞቹ ቤቶች ተሸጠው መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ኦቪድ ሪልእስቴት፤ እነዚህ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች በ4 ምድብና ሳይቶች መካተታቸውን አስታውቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ለህዝብ የቀረበው አንደኛው ፕሮጀክት ጫካ መኖሪያ ቤት ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ጫካዎች ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ 1900 የተንጣለሉ ቤቶች ባለ1፣ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ አፓርትመንቶችን የያዘ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ 9 ሄክታር በሚሸፍን ሰፊ የከተማው አረንጓዴ መስክ ላይ የሚለማ ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ሐረር ሆራይዘን ፕሮጀክት ሲሆን፤ ባለ 2 እና 3 መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርትመንቶችን የያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ሦስተኛው ኪንግስ ታወር ሲሆን፤ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ይዟል፡፡  ኪንግስ ታወር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ያካተቱ 1740 ሰፋፊ መኖሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

አራተኛው አፍሪካን ሃይትስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ባለ1፣ ባለ2፣ ባለ3፣ እና ባለ4 መኝታ አፓርትመንቶችን ጨምሮ 324 ቤቶችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ኦቪድ ግሩፕ በሥሩ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ የኮርፖሬት ሆልዲንግ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ሲሰሩ የነበሩ የቀድሞ ባልደረቦች ማህበራቸውን ወይም ‹‹አፊክሰን››  የመሰረቱበትን  25ኛ  ዓመት ክብረ በአል  ቅዳሜ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም  ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ በኢሲኤ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት  ሳህለወርቅ ዘውዴ  የአፊክስ የክብር አባል ሲሆኑ፤ ሌሎችም በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን ያስጠሩ ኢትዮጵያውያንም  የዚህ ማህበር አባላት ናቸው፡፡
 
አፊክስ ፣ በዋነኛነት የአባላቱን ጥቅምና መብት  ማስጠበቅን ቀዳሚ አላማው አድርጎ የተመሰረተ  ሲሆን፤ ከ586 በላይ አባላትም አሉት፡፡

 ከልዩ ልዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጡረታ በወጡ ባለሙያዎች የተመሰረተው ይህ ማህበር  25ኛ አመቱን በድምቀት ሲያከብር፤ ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ሚስተር ሪሚዝ አልካባሮቭ፣ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎችን በመወከል ንግግር አድርገዋል ።

ማህበሩን ከመሰረቱት መካከል ለረጅም አመት በፕሬዚዳንት ያገለገሉት  አቶ ተድላ ተሾመ በእለቱ የታደሙ ሲሆን፤ እርሳቸውም በዩኤንዲፒ ከ20 አመት በላይ  በከፍተኛ  ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

በዚህ ክብረ በአል ላይ ዶ/ር አፈወርቅ አየለ የኦፊክስ ፕሬዚዳንት የእለቱን መልእክት አሰምተዋል፡፡   ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ መሰናዶዎችና  የኦፊክስን የ25 አመት ጉዞ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን አማካይነት ቀርቧል፡፡

ኦፊክስ  የአባላቱን ጥቅም ሊነካ የሚችል  የመመሪያ ለውጥ በተባበሩት መንግስታት  ድርጅት ውስጥ ቢከሰት ለውጡን  ለአባላቱ ያሳውቃል፡፡ በስራ ላይ እየተሳተፉ ያሉ አባላት  ልምድና እውቀት በሰፊው ያካበቱ በመሆኑም ይህን የተቀደሰ አላማ ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን የሚታትሩ ባለሙያዎችም  ናቸው፡፡

ማህበሩ ሲመሰረት አንስቶ፣ ከጡረታ መስሪያ ቤት ዘንድ ውሳኔ የሚጠብቅ ጉዳይ ያላቸውን አባላት  በፍጥነት ውሳኔ እንዲገኝላቸው አድርጓል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኙት ደግሞ  ጡረታ ከመውጣታቸው አስቀድሞ  ስለጡረታ ክፍያቸው እንዲሁም ስለ ጤና ጥበቃ መድን ቅድመ ዝግጅት  እንዲያደርጉ  አፊክስ እገዛውን በተሟላ መንገድ ሲሰጥ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ዓለምአቀፍ  ሠራተኞች ማህበር  ወይም አፊክስ ለጠቅላላ ጉባኤው ተጠሪ የሆኑ የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፤ የማህበሩም ጽ/ቤት በኢሲኤ ግቢ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡

ያለ ማሲያዣ ለወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች ገንዘብ ማበደር የሚያስችል አማራጭን ይዤ መጥቻለሁ ያለው ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ በትላንትናው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነፃነት ደነቀ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መስፈርቶችን በሟሟላት ሙሉ እውቅና እና ፍቃድ በመያዝ ወደ ስራ መግባቱን ያስረዱ ሲሆን፤ በዘርፉ አዲስ እንደሚቀላቀል ተቋም የተለያዩ አማራጮችን በመያዝ መምጣታቸውን ነው ያብራሩት።

ከእነዚህም መካከል ወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት እንዲቻል በሚል መርህ የስራ ፈጠራ ሃሳቦቹን አዋጭነት በማጥናት ያለ ማሲያዣ ስራ መጀመር የሚችሉበት የብድር አማራጭ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ የብድር አማራጭ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ደረጃ ያልተለመደ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፤ ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ  ወጣቶችና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም በመሆን መምጣቱን አብራርተዋል።

ከወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች በተጨማሪ በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙና የፋይናንስ ተደራሽነት በሌላቸው አካባቢዎች ላይም ማተኮር ሌላኛው የተቋሙ አገልግሎት መሆኑን አክለዋል።

የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቶ ሞገስ ታመነ በበኩላቸው፤ ተቋሙ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት በሃገሪቱ አሉ ከሚባሉ እንደ አዋሽ ባንክ፣  ዳሽን ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣  እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ከመሰሉ ተቋማት ጋር በጥምረት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አንስተዋል።

ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ሴቶችን ፣ ወጣቶችንና ስራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚያተኩር የጠቆሙት  ስራ አስፈፃሚው፤ የቁጠባ ባህልን የሚያጎለብቱ በግልና በቡድን ለሚመጡም የተለያዩ አማራጮችን ይዘን መጥተናል ነው ያሉት።

አቶ ሞገስ አክለውም፤ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አምራች  ዜጎችና ተቋማት የቁጠባና የብድር አገልግሎት ማቅረብ እንዲሁም  አካታችና ሁሉን አቀፍ የፋይናስ ስነ ምህዳር መፍጠር የሚሉት የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።

ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ በ170 አባላት አማካኝነት በ24.5 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ89.4 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ወደ ስራ የገባ ተቋም ነው።

 በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጰያ  ወደ 50 የሚጠጉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ይገኛሉ፡፡

Page 7 of 700