Administrator

Administrator

*የወንድ ልጅ ብልት ቆርጠው “ተጫወችበት” ይላሉ--- *ቦንብ ታጥቀሽ ራስሽን አፈንጂ ተብዬ ነበር ---- *አፍሪካውያንን በኤሌክትሪክ ማቃጠል የተሰጠኝ የሥራ ኃላፊነት ነበር--- *ውሃ ስንጠይቅ ሽንታቸውን ነበር የሚሰጡን …እላያችን ላይ ይሸናሉ … ከአማርኛ ይልቅ አረብኛ መናገር ይቀናታል፡፡ የምትናገረው በቁጭት፣ በእልህና በፍርሃት ስሜት ነው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ለሥራ ወደ ሶሪያ የተጓዘችው ሃረግ (ሜሪ)፤ በሶርያ ከጦርነቱ መጀመር ጋር ተያይዞ ያሳለፈችውን መከራና ስቃይ በአንደበቷ ትናገራለች - አንዳንዴ በሰመመን፣ ሌላ ጊዜ በመንገሽገሽ፡፡ ከሶሪያ በሱዳን በኩል አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ በገባች በአምስተኛ ቀኗ ከጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡ በሶርያ በምን ሥራ ላይ ነበር የተሰማራሽው? በ2009 ዓ.ም ወደ ሶርያ የሄድኩት በአውሮፕላን ነበር፡፡ እንደሌሎች ሴት እህቶቼ የቤት ውስጥ ሥራ ሳይሆን እርሻ ላይ ነበር ሥራ ያገኘሁት፡፡ ሥራዬ የወይራ ፍሬ መልቀም እንዲሁም ሙዝ፣ ትፋህ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መኮትኮት፣ ማጨድ፣ ወዘተ ነበር፡፡ አንድ አመት ሙሉ ብቻዬን ነው የሠራሁት፡፡ ሴት ነሽ--- እንዴት የእርሻ ሥራን ልትመርጪ ቻልሽ? በመጀመሪያም ወደ ሶሪያ ስሄድ ሰው ቤት እንደምቀጠር አልነበረም የተነገረኝ፡፡ እዚያ ስደርስም ወደ ገጠር ነው የተላኩት፡፡ በእርግጥ ግብርናውን ወድጄው ነበር፡፡ ግን የምኖርበት ሰውዬ በጣም አስቸገረኝ፡፡ የተቀጠርኩበት ቤት እናትና ልጅ ነበሩ፡፡ ልጁ ትልቅ ሰው ቢሆንም የአእምሮ ዘገምተኛ ነበር፡፡ እናቱ አሮጊት ናት፡፡ ልጅዬው በተደጋጋሚ ይዝትብኝ ነበር፡፡ አብረሽኝ ካልተኛሽ እያለ ያስጨንቀኛል፡፡ ምን ልበልሽ… በጣም ያሳቅቀኝ ነበር፡፡ እና ስራዬን ሰርቼ ወደ ቤት መመለስ እንደ ጦር ነበር የምፈራው፡፡ ይመታኛል፣ ይጎትተኛል፣ ይጎነትለኛል … አንድ ዓመት ሙሉ በእነዚህ ሰዎች ቤት በስቃይ ቆየሁ ፡፡ ምን ያህል ነበር የሚከፈልሽ? ከዚህ ስሄድ 125 ዶላር እንደሚከፈለኝ ነበር የተነገረኝ፡፡ እዛ ስደርስ ግን መቶ ዶላር ሆነ፡፡ እንዲያም ሆኖ አንድ ዓመት ሙሉ የሰራሁበትን ገንዘብ ከሰዎቹ አልተቀበልኩም፡፡ በቃ ጠፍቼ ነው … የሄድኩት፡፡ በየወሩ አልነበረም ደሞዝ፡፡ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከሰራሽ በኋላ ነው የሚከፍሉሽ፡፡ እንዴት ጠፋሽ? በእርሻው ቦታ ላይ ስሰራ ጎረቤታችን የሆነ አንድ መልካም ሰው ሁልጊዜ ሁኔታዬን ያይ ነበር፡፡ አንድ ቀን አናገረኝ፡፡ እኔም የሚደርስብኝን በደል ሁሉ አጫወትኩት፡፡ እዚህ ሰውዬ ቤት ስቀጠር ህፃን ልጅ አለው ተብዬ ነበር … ይመስለኛል ለሰውዬው ማረጋጊያና ስሜት መወጫ ነው የወሰዱኝ፡፡ እኔ ከሄድኩ በኋላ እናቱን ሌላ አገር ልኳቸው እኔ ብቻ ከእርሱ ጋር ቀረሁ፤ ለሦስት ወር ሁለታችን ብቻ ነበር፡፡ በየጊዜው ይደበድበኝ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ በስለት አስፈራርቶ ደፍሮኛል፤ እ..ከዛ በጣም ታመምኩኝ፣ አርግዤ ነበር፡፡ ‹‹ፔሬዴ ቀርቷል፤ ሃኪም ቤት ውሰደኝ አሊያም ወደ አገሬ ላከኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹እገልሻለሁ›› አለኝ፡፡ ስንት ቀን እየፈራሁ ዛፍ ላይ ወጥቼ ‹‹አልወርድም›› እለው ነበር፡፡ … ይሄን ሁሉ ይመለከት ነበር - ያ ጎረቤታችን ሰውዬ፡፡ በኋላ ‹‹ከተማ ወስጄሽ የውጪ ዜጎች ቤት ትቀጠሪያለሽ›› አለኝ፡፡ ጎረቤትሽ ማርገዝሽን ያውቅ ነበር? አውቋል፡፡ ወደ ከተማ ሊወስደኝ የተነሳሳው እኮ ይህንንም ሚስጢር አጫውቼው ነው፡፡ ከዚያም ‹‹ማርሊዬስ›› የሚባል ክርስቲያን አረቦች የሚሄዱበት ቤተክርስትያን ወስዶ ጣለኝ፡፡ እዚያ ችግሬን ነገርኳቸው - ለቤ/ክርስቲያኑ ቄስ፡፡ ሀሙስ፣ አርብና ቅዳሜ ለሦስት ቀን ቤተክርስትያን ውስጥ አሳደሩኝ፡፡ “እሁድ ነው ኢትዮጵያውያኖች የሚመጡት፤ ከእነርሱ ጋር ትገናኛለሽ” አሉኝ፡፡ እሁድ ዕለት ኢትዮጵያውያኖች መጡ - ብዙ ናቸው፡፡ የደረሰብኝን በሙሉ አጫወትኳቸው፡፡ ቅዳሴ እንኳን ሳያልቅ ነው ይዘውኝ ወደ ቤታቸው የሄዱት፡፡ አንድ እንደ ትልቅ እህቴ የማያት ሴት ነበረች … ለእሷ ምስጢሬን ሁሉ አጫወትኳት፡፡፡ ‹‹ምንም ችግር የለም›› አለችና ሃኪም ቤት ሄድን፡፡ አስመረመረችኝ -----የሁለት ወር ተኩል እርጉዝ ነሽ ተባልኩ፡፡ እዛ አገር ማስወረድ ክልክል ነው፡፡ እርጉዝ ከሆንሽ ወደ አገርሽ አይልኩሽም፡፡ ከተወለደ በኋላ ልጁን ነጥቀው ነው አንቺን ወደ አገርሽ የሚሰዱሽ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ህይወት ነው፡፡ ብወልደውም ልጄን አይሰጡኝም፤ ለማስወረድ ደግሞ ገንዘብ አልነበረኝም … እስከ አምስት መቶ ዶላር ያስፈልጋል ፡፡ ያቺ እንደ ትልቅ እህቴ የማያት ልጅ የምታውቀውን ሰው አነጋግራልኝ፣ እሱ ረዳኝና ፅንሱን አቋረጥኩ፡፡ ልጆች በእስር ቤት ወልደው የሚያሳድጉ ኢትዮጵያውያኖች አሉ ይባላል … በርካታ ኢትዮጵያውያኖች፣ ኤርትራውያኖችም … አሉ፡፡ እኔ ፅንሱን ካቋረጥኩ በኋላ … ሁለት ሳምንት … እቤቷ አረፍኩ፡፡ ምናልባት ሰውዬውም የሚያፈላልገኝ ከሆነ በሚል … ሁለት ሳምንት ሙሉ ከቤት አልወጣሁም፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ጋር ተገናኘሽ … ደማስቆ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ እርስ በርስ ይተዋወቃሉ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን እሁድ እሁድ አንድ ላይ እንውላለን፣ ቡና ይፈላል፣ ተሰብስቦ እረፍት መውሰድ፣ መዝናናት የተለመደ ነው፡፡ ሴቶቹ ሰው ቤት ነው የሚሠሩት፡፡ ወንዶቹ ግን አይቀመጡም--- እዛ አገር የሚሄዱበት ምክንያት በቱርክ አድርገው ወደ ሌላ አገር ለመሻገር ነው፡፡ አንቺ ከዛ በኋላ ሌላ ሥራ አገኘሽ ወይስ----- ራሴ አማርጬ ሰው ቤት ተቀጠርኩ፡፡ ቋንቋ ስለማውቅ ችግር አልገጠመኝም፡፡ አሮጊትና ሽማግሌ ባልና ሚስቶች ቤት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ ፡፡ ይኸኛውስ ቤት ተስማማሽ? ምን ያህል ይከፈልሽ ነበር? መጀመሪያ ስገባ መቶ ሃምሳ ዶላር ነበር፡፡ በኋላ ሁለት መቶ ሃያ አምስት ዶላር ሆነልኝ፡፡ አሮጊቷ ከተኛችበት አትነሳም፡፡ 85 ዓመቷ ነበር -- እሷን አንስቼ አጥባለሁ፡፡ ፓምፐርስ (የሽንትና የሰገራ መቀበያ) እቀይርላታለሁ፡፡ … መርፌ አወጋግ ልጃቸው አሰልጥናኝ -- መርፌ እወጋቸው ነበር፡፡ እንደ ልጃቸው ነበር የሚያዩኝ፡፡ ልጆቻቸው ዩኤን ነው የሚሠሩት፡፡ የመጀመርያው ቤት ፓስፖርቴን ትቼው ስለወጣሁ እዛ ተመዝግቤ በዚያ ወረቀት ነበር የምጠቀመው፡፡ አሮጊቷ የዛሬ ዓመት ሞተች፡፡ ከዛ ሽማግሌው ልክ እንደ ሚስቱ ሆነ፡፡ እሱን ሳነሳ ስጥል … (95 ዓመቱ ነበር፡፡) ግን በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ የቤቱ ሃላፊ እኔ ነበርኩ፡፡ በጣም ሀብታሞች ናቸው፡፡ መኪና አስመጪና ላኪ ነበሩ፡፡ ሴቷ ልጅ ነበረች የቤተሰቦቿን ሀብት የምታስተዳድረው፡፡ ምን ያህል ጊዜ ሰራሽ? አራት ዓመት ከ6 ወር አብሬአቸው ነበርኩ፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ሃብታሞች ስለሆኑ ሁሉን ነገር ትተውት ወጡ፡፡ በመሃል እኔ ቀረሁ፡፡ ልጅቷ ፓስፖርት ልታወጣልኝ በጣም ደክማልኛለች፤ ግን አልተሳካም፡፡ እና ቤቱን ለእኔ ጥለው ወደ ቤሩት ተሳፈሩ፡፡ አካባቢው በጣም አስቀያሚ ነበር፡፡ አሸባሪዎች እንደፈለጉ የሚገቡበት የሚወጡበት ቦታ ነበር፡፡ እዚያ መኖር እንደማልችል አውቄዋለሁ፡፡ የነበርኩባቸዉ ሰዎች ደግሞ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ አሸባሪዎች ይፈልጓቸዉ ነበር፡፡ ያንን ትልቅ ቤት ጥለውልኝ ብቻዬን ተሸክሜው ስለቀረሁ ተጨነቅሁ … መወሰን ነበረብኝ፡፡ በርካታ ቤተክርስያኖች ተቃጥለዋል፡፡ ፈርሰዋል፡፡ የሚሸሸው ክርስቲያኑ ነው፡፡ ፓስፖርት ያለው ይሸሻል፡፡ ፓስፖርት ኖሮት ብር የሌለው ኢትዮጵያዊ አለ---ሁሉም መሸሽ ነው፡፡ እስር ቤት መግባትም አለ፡፡ እኔም እጣ ፋንታዬ ይሄው ሆነ፡፡ በእስር ቤት ውስጥ .. የነበረውን ሁኔታ ንገሪኝ? እስር ቤት አንድ ወር ተቀመጥኩ፡፡ እስር ቤት እኮ የገባሁት ልመጣ አካባቢ ነው ከዛ በፊት በአሸባሪዎች እጅ ወድቄ ስንት ነገር ደርሶብኛል..በአሁኑ ሰዓት በጣም በረዶ ነው፡፡ እስር ቤት አትበይው … ‹‹የምድር ጀሃነም›› ነው፡፡ እዚህ ካዛንቺስ ሆነሽ ፍንዳታ ከተሰማ ተነስተሽ መገናኛ ድረስ ነው የምትሮጪው፡፡ ትራንስፖርት የለም፣ ከተያዙ መያዝ ነው፤ የሚሞተውም ይሞታል፡፡ አሁን እኔ በወጣሁበት ሰዓት ከተማው ላይ ብዙም ጦርነት አልነበረም፡፡ ዳር ዳሩ ላይ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ እንደ አቃቂ ባለ ከከተማው ዳር ነበር የምኖረው፡፡ ከደማስቆ ራቅ ይላል፡፡ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት ይሠራሉ የሚባለው እውነት ነው? ወደው አይደለም ሴተኛ አዳሪ የሚሆኑት፡፡ ፓስፖርት የላቸውም፤ ሊቀጠሩ ሲሄዱ ፓስፖርት ይጠየቃሉ፡፡ ቀጣሪዋ ‹‹አልፈግሽም›› ብላ ልታባርራት ትችላለች ፡፡ መኖር፣ መብላት ስላለባቸው የግድ ለእንደዚህ ዓይነት ህይወት ይዳረጋሉ፤ እዚያ ደግሞ የኢትዮጵያ ቆንስላ የለም፤ ኤርትራውያን እንኳ ቆንስላ አላቸው፡፡ ኤርትራዊ ላይ አንድ ችግር ቢደርስበት ቆንስላው ወደተከራየው ቤቱ ይወስዳቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በጣም የሚያሳዝን ነው ኑሯቸው ፡፡ አሁን እንኳን ወደ አገራቸው መምጣት አቅቷቸው በየሜዳው ወድቀዋል፡፡ በጦርነቱ ቤቱ ሁሉ እየፈረሰ ነው፡፡ ተከራይተው የሚኖሩት ንብረታቸውን ማውጣት አልቻሉም፡፡ የሴቶች ህይወት … በቃ ይሄው ነው፡፡ ወደው አይደለም የገቡበት ---- ኢትዮጵያውያኖች ያ ባህል ኖሯቸው አይደለም፤ በችግር ነው፤ አማራጭ በማጣት፡፡ እስር ቤት ከመጣልሽ በፊት..በአሸባሪዎች እጅ ወደቅሽ? በጣም አሰቃቂ ነው … በአሸባሪዎች እጅ ላይ ወደቅሁኝ፡፡ /ሰውነቷ ይንቀጠቀጣል፣ ለደቂቃዎች በዝምታ ቆየች፤ አይኖቿ እንባ አቀረሩ …) አየሽ ሰውነቴን … (ትከሻዋ አካባቢ እያሳየችኝ … የተቃጠለ ገላ …) ምንድን ነው? ሲጋራ ተርኩሰውብኝ ነው … … አሸባሪዎቹ ናቸው እንዲህ ያደረጉኝ--- የት ነው የወሰዱሽ? ቢሄዱት የማያልቅ ምድር ቤት (Underground) አላቸው፡፡ ውስጥ ለውስጥ ተቆፍሮ … የቀለጠ ከተማ ነው፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዳይመስልሽ … ወደ አምስትና ከዛም በላይ አቅጣጫ መግቢያ መውጭያ ያለው ነው … የታሰሩ ሰዎች የሚሰቃዩበት፣ የጦር መሳሪያ በየዓይነቱ በብዛት ያለበት … ኑሯቸውም እዛው ነው? አዎ፡፡ ሴቶችም ወንዶችም አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ አሸባሪዎቹ አይወልዱም፡፡ ከወለዱ ግን የልጆቻቸው አስተዳደግ አሰቃቂ ነው፡፡ በፊት ለፊታቸው አንገት በቢላዋ እየተቀላ፤ እጅና ጣት እየተቆረጠ … ያንን እያዩ ነው የሚያድጉት፡፡ ወንዶችን በፊንጢጣቸው … ኤሌክትሪክ ይልኩባቸዋል፡፡ ሴቶችን ህፃናቱ ፊት ይደፍራሉ፡፡ … የ3 እና የ5 ዓመት ህፃናት እንዲያዩ እንዲለማመዱ ይገፋፏቸዋል፡፡ የአሸባሪዎቹ ሚስቶች እዚያው አሉ፡፡ እነርሱም ሰውን ያሰቃያሉ፡፡ ሴትን ሴት፤ ወንድን ወንድ ነው የሚያሰቃየው፡፡ ሚስቱ ካሰቃየችኝ በኋላ ‹‹አምጫት›› ብሎ ይደፍረኛል፡፡ ሱዳኖች፣ ናይጄሪያዎች፣ ሴኔጋሎች … ብዙ የአፍሪካ ዜጐች ነበሩ - የሚሰቃዩ፡፡ የተለያየ አደንዛዥ ዕፅ ይሰጡናል፤ በመርፌ የሚወጋ፣ የሚጨስ፣ የሚሸተት … በግዴታ ነበር፡፡ ከዚያ መጋረፍ ነው … ወንዶቹ ብልት ላይና ምላሳቸው ጫፍ ላይ ኤሌክትሪክ ያደርጉባቸዋል፡፡ እኔን … ቦንብ ታጥቀሽ ራስሽን ታጠፊያለሽ ብለውኝ ነበር፡፡ ‹‹ላ … ላ›› አልኳቸው፡፡ ከዛ … የደረሰብኝን ስቃይ … (ረጅም ትንፋሽ) እስቲ የደረሰብሽን ንገሪኝ … … በቃ ተይው ይቅር … (ለመሄድ ተነስታ ተመልሳ በማቅማማት ተቀመጠች) አይዞሽ ንገሪኝ … ስታወሪው ይሻልሻል … ለመናገር ይከብዳል፡፡ የወንድ ልጅን ብልት ቆርጠው አምጥተው “ተጫወችበት” ይላሉ--- በጣም … አስቀያሚ ነው … ተይኝ ባክሽ … በተደጋጋሚ ስትደፈሪ እርግዝና አልተፈጠረም? ሃሃ … (ሳቅ) የሚሰጡኝ መድሃኒትስ … አምፒሲሊን ይሁን … ምን ይሁን አላውቅም ግን ይሰጡኝ ነበር … ስለዚህ እርግዝና የለም፡፡ ስቃይ ሲበዛብሽ … ምንም አትይም … ቁጣ ወይ ደግሞ … “በቃ ራሴን አፈነዳለሁ” አልኳቸው:: ውይ ሳልነግርሽ … ምግብ የለም፣ ውሃ በምንጠይቅ ሰዓት ሽንታቸውን ነበር የሚሰጡን … ሲያሰኛቸው በገላችን ላይ ይሸናሉ፡፡ ትንሽ ውሃ በተለያዩ ማደንዘዣ ዕፆች ቀላቅለው ጠጡ ይሉናል ፡፡ ያን ከሰጡኝ በኋላ የሚያደርሱብኝ ስቃይ አይታወቀኝም … እና “አፈነዳለሁ” ብዬ ተስማማሁ … ወጥቼ ልሙት … አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን እንዳዳረገች ሁሉም ይወቅ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ከእንግዲህ ምን ቀረኝ … ብሬን ንብረቴን ወስደውታል፡፡ አማርኛ የማወራው--- ችግሬን የማስረዳው ሰው እንኳን የለም፡፡ እንዲህ እናድርግ ምናምን ብላችሁ ከሌሎቹ ጋር አትማከሩም ነበር? እኔ ከሴቶች ጋር ሳይሆን ከወንዶች ጋር ነበር ይበልጥ የምቀራረበው፡፡ ናይጀሪያኖች፣ ሱዳኖች … ሱዳኖች በእኔ ስቃይ በጣም ተጐድተዋል … ስጮህ ይሳቀቁ ነበር፡፡ በእነሱ ፊት ይገናኙኝ ነበር፡፡ አፍሪካውያኖችን በኤሌክትሪክ አቃጥይ ይሉኝ ነበር፡፡ “ሂጅና አቃጥያቸው”፤ “ሽንትሽን ሽኝባቸው…” እባላለሁ፡፡ እነሱ ጋ ስደርስ በጣም አለቅስ ነበር፡፡ ጣታቸውን … እግራቸውን ይቆርጡባቸዋል፡፡ … ህክምና የለ፤ ደማቸው እየፈሰሰ ነው የሚውሉት … አቃተኝ (ረጅም ትንፋሽ) ምን ያህል ነበሩ? አስራ ሶስት፡፡ ከሞቱት ሌላ ማለቴ ነው---- (ደረትዋን ደጋግማ በእጅዋ ትይዛለች) አቤት ...ሽታው በልብሴ ...በሠራ አካላቴ ጠረኑ ሁሉ..ይመጣብኛል፡፡ ናይጀራዊው ጋ ሄጄ የታዘዝኩትን ስነግረው ..በአረብኛ ‹‹..አድርጊው..ካላደረግሽው አትወጪም፤ እኛንም አታድኝንም..አድርጊው..ለኩሽኝ..›› አለኝ፡፡ አልቻልኩም፤ የመጀመሪያ የጨካኝነት ልምምድ ነበር፡፡ አለቀስኩኝ፡፡ በብዛት ኮኬን እወስድ ነበር፡፡ ስትለኩሺያቸው ቆመው ያዩሽ ነበር? አዎ.. ደስ ይላቸዋል፡፡ .ናይጀሪያዊውን እየለኮስኩት ሳለ “ጭኔ ላይ የምታያት የበር ቁልፍ ናት፡፡ እቺን ይዘሽ መውጣት ትችያለሽ” አለኝ፡፡ እሱን እየለኮስኩ ቁልፉን ወሰድኩት፡፡ አረቡ እያየን አልነበረም፡፡ ናይጄሪያዊው ቁልፉን ከየት አገኘው? ከየት እንዳገኘው መጠየቅም አልፈለኩም፤ ጊዜውም አልነበረኝም፡፡ ማውራት አንችልም ነበር፤ ከናይጀሪያዊው ጋር ልንግባባ የምንችለው በአረብኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ በንግግርሽ ውስጥ እንግሊዝኛ ከሰሙ ...ጉድሽ ነው፡፡ የተለየ ቋንቋ እንድትናገሪ አይፈቀድልሽም፡፡ (ንግግርዋን አቋርጣ) ይቅር በለኝ--- አሰቃየኋቸው፡፡ በኤሌክትሪክ ከለኮስኳቸው በኋላ ስላለቀስኩ ..‹‹ለምን ታለቅሻለሽ›› ብለው አሰቃዩኝ፡፡ ‹‹የገነት ፓስፓርት›› የሚሉት አለ፡፡ የገነት ፓስፖርት ... ሰው ገድለው ገነት የሚገቡበት ፓስፖርት፡፡ የራሳቸው የቡድን ፓስፖርት ነው፡፡ ‹‹ነፍስ አጠፋለሁ›› ብዬ ስነሳ ፓስፖርት ተሰራልኝ፡፡ ፓስፖርቱ ምን አለው? ምንም፡፡ የእኔ ስምና የቤተሰቤ ስም ዝርዝር አለው፡፡ አረንጓዴ ነው፡፡ ፎቶ የለውም፡፡ ስትገልጪው ይሄ ብቻ ነው የያዘው መረጃ፡፡ “የገነት ፓስፖርት” ይላል ፅሁፉ፡፡ ፓስፖርቴ ተሰራልኝ፡፡ እላዬ ላይ ቦንብ ካጠመዱልኝ በኋላ የገነት መግቢያ ፓስፓርቴም፣ አብሮ ይታተምልኛል፡፡ ፓስፖርቴ ተሰራ፤ አብሬያቸው እሰግድ ነበር፤ ቁራን እንዴት እንደሚቀራ አስተማሩኝ፡፡ “የዛሬ 15 ቀን ወደ ገነት መሄጃሽ ነው ማረፍ አለብሽ” ብለው ነገሩኝ... እረፍቱ የት ነው …? ‹‹የምድር እረፍት›› ነው የሚሉት፡፡ 15 ቀኑን የሟች ሬሳ በተጠራቀመበት … (ፀጥ አለች) … ሰውነታቸው የተቆራረጠ ሰዎች በብዛት ተገድለው በተጣሉበት … ከነበርንበት ወደ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ … ሬሳ ውስጥ … ከሙታን ጋር፡፡ ጨካኝ … እንድትሆኝ ነው … እዚያ የጉድጓድ መውጫ በር አለ … ያ … ናይጄሪያዊ የሰጠኝ ቁልፍ መውጫ ነው … እሱ እኮ ከታሰረ ሁለት ዓመቱ ነው … ጦርነቱ ሲጀምር የተያዘ ነው፡፡ እረፍት እንደሚወስዱኝ ሁሉ ያውቃል፡፡ … በዚያ አሰቃቂና ዘግናኝ ቦታ በአጋጣሚ ህይወቱ ያላለፈ ትኩስ ቁስለኛ … (የገደሉት መስሏቸው ትተውት የሄዱት) አገኘሁ፡፡ ለመሞት ጥቂት ደቂቃዎች ነበር የቀረው፡፡ የእረፍቱ ቦታ..... ሱሪ እና አሮጌ ነገር አለበሱኝ፤ ሬሳው ውስጥ ተቀመጥኩ፡፡ … እፀልይ ነበር … ቁልፉን እንዴት ይዘሽው ገባሽ? በማህፀኔ ውስጥ ደብቄ … በምኔም ልደብቅ አልችልም ነበር፡፡ ስፀልይ ሰውየውም ቀና አለ … እጅግ ያሳዝናል … ሰውነቱ ሁሉ የተጠባበሰ ነው … ተበለሻሽቷል፡፡ ይህ ሰው እንደተጋደመ “ሬሳዎቹን … ገለል ገለል አድርገሽ ውጪ” ብሎ አሳየኝ … የደረጃ መወጣጫ … አለው … እሱ ሲወጣ አስፓልት ይገኛል፡፡ እየመጡ አያዩሽም ነበር? በፍፁም አያዩኝም … 15 ቀን ካረፍኩ በኋላ መጥተው ይወስዱኛል … ብቅ ብለው ግን አያዩኝም፡፡ ከዛ ሰው ጋር ተግባባሁ፤ ውሃ … ሲለኝ ሽንቴን ሸንቼ ሰጠሁት፡፡ ህይወቱን ለትንሽ አተረፍኩት፡፡ … በሌሊት በሩን ከፈትን … ተሸክሜ … አወጣሁና ጣልኩት፡፡ እነሱ ለሊት ለሊት ስራ አይሰሩም፡፡ ስራቸው ቀን ነው፡፡ በግርግር ጫጫታ ባለበት ሰዓት እንጂ … ጨለማ ተገን አድርገው እንኳን ሰውን አይደበድቡም፡፡ ቢያስተጋባ ቢሰማብን ብለው ስለሚያስቡ ይፈራሉ፡፡ ሌሊት መጠጣት ነው ሥራቸው፡፡ የቆሻሻ ቱቦ … ስር ለስር … የትና የት የሚደርስ--- ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ መንገድ መሰለሽ … እንደ ምንም ደረጃውን ተሸክሜው … እየጎተትኩት … ወጥተን ያ ናይጄሪያዊ በሰጠኝ የበለዘ ቁልፍ … ከፈትኩት … ስወጣ አስፓልት ላይ ነው የወጣሁት፡፡ ቅርብ ነው ለከተማው፡፡ ምሽት ላይ ነበር፤ ማንም ዝር አይልም፡፡ ‹‹ስምርዬ›› የሚባል ቦታ አለ፡፡ እንደ አውቶብስ ተራ ዓይነት ነው፡፡ አስፓልቱ ላይ ከወጣን በኋላ … ተሸክሜ ያወጣሁት ሰው … የተወሰነ ቦታ ድረስ እየጎተትኩት ከተማ አካባቢ ስንደርስ አደባባይ ላይ ጥዬው ሄድኩ፡፡ ከወጣሁ በኋላ ደክሞኛል … አሞኛል፡፡ ኢትዮጵያኖችን መጠጋት አልቻልኩም፡፡ ለምን? በጣም አስቀያሚ ሁኔታ ላይ ነበርኩ፡፡ ሀሺሽ ጠጥቻለሁ፣ ጠረኔ በጣም መጥፎ ነው፤ ፀባዬ ከፍቷል፡፡ በዛ ሰዓት የሄድኩት ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ፀለይኩ … አለቀስኩ … የት እንደምሄድ አላውቅም፡፡ … ሁሉ ነገር ብርቅ ሆኖብኛል፡፡ መንገድ ላይ ስዘዋወር አንድ ኢትዮጵያዊ አገኘሁ፡፡ ሳናግረው “ሰምተናል ሰምተናል” አለኝ፡፡ ምኑን? አንዲት ኢትዮጵያዊ ተይዛለች መባሉን፡፡ ማን እንደሆነች ግን አላወቅንም ነበር፡፡ በአሸባሪዎች እጅ ወደቀች ሲባል ሰምተናል - አለኝ፡፡ በአገሪቱ ላይ ስልክ የሚባል የለም … አጋጣሚ ሆኖ በነጋታው ወደ ካናዳ የሚሳፈር ልጅ ነበር፤ በጣም አዘነ፡፡ ከዛ ጉድጓድ ከወጣሁ በኋላ ግን በጣም ፈራሁ … የሚያየኝ ሰው ሁሉ የሚያውቀኝ የሚከተለኝ… የሚገለኝ ይመስለኝ ነበር፡፡ ቀን ቀን ስታያቸው ኖሮማል ሰው ስለሚመስሉ፤ ለብሰው ዘንጠው ስለሆነ የሚወጡት … አንድ ሰው አስተውሎ ካየኝ ከእነርሱ መካከል አንዱ ይመስለኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ በዛን ወቅት ደግሞ በዊግ ቁጥርጥር ተሰርቻለሁ … በፀጉሬ ይለዩኛል ብዬ እሰጋም ነበር፡፡ “እባክህ ከአንድ ሱናዳዊና ናይጄሪያዊ የተሰጠኝ መልዕክት አለ … ስማቸው እገሌ ይባላል … ሂጂና ያሉበትን ቦታ ተናገሪ ስላሉኝ እዛ ውሰደኝ” አልኩት፡፡ ናይጄሪያዎች በጣም ጎበዞች ናቸው … እንዴት እንደሚወጣ … ያውቃሉ ----ጥበበኞች ናቸው እና ይሄን ልንገር አልኩት፡፡ የተባለው ቦታ ወሰደኝ፡፡ ... ነገርኳቸው፡፡ ተላቀስን -- ቁልፍ ሰጥቶ ያስወጣኝ የናይጄርያው ወንድም “ኢሾ” ይባላል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን አወራን፡፡ ቦታው እንደዚህ ዓይነት ቦታ ነው፤ ቁልፉም ይሄው … ‹‹ስጪያቸው እነርሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ ነው ያለኝ” አልኩት፡፡ ቁልፉ ላይ … ሌላ መልዕክት አለው? እንዴ … እንዴት አወቅሽ? --- ቁልፉ ሰፋ ያለ ነው.. በላዩ ላይ በራሳቸው ቋንቋ ፅፈውበታል … ሰጠኋቸውና አወጣጤን ነገርኩት፡፡ አለቀሱ፤ በህይወት የለም ብለው ደምድመው ነበር፡፡ (እንባዋን እየጠረገች) አንድ ኢትዮጵያዊ ከአንድ ሱዳናዊ ጋር አገናኘኝ፡፡ በጣም ባለውለታዬ ነው-- እንደ ነገ ወደ ካናዳ በረራ ነበረው--- ለእኔ ሲል ቀኑን አራዘመ … በሃሺሽና በተለያዩ ሱሶች የተበከለው ደሜ … ባህሪዬን አስከፍቶት ስለነበረ መርዙ ከደሜ እስኪወጣ ድረስ ተቸገርኩ፡፡ ስለዚህ … አስመረመረኝ … ከሰው ጋር ትንሽ ትራቅና ትቀመጥ ተባለ … መድሃኒት ተሰጠኝ፡፡ ያ ያስተዋወቀኝ ያልኩሽ ሰው በሱዳን አድርጌ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጣ ነገሮችን ያመቻችልኝ ጀመር፡፡ ሌላ ዳዊት ባህሩ የሚባል ኢትዮጵያዊ (እዛ የሚኖር የአሜሪካ ዜግነት ያለው) … የቻልኩትን ሁሉ እረዳታለሁ … ፓስፖርቷንም በማውቀው ሰው አወጣላታለሁ አለ፡፡ የምንኖረው አንድ አፓርታማ ላይ ነው፡፡ እኔን ይዞ ሲወጣ ሲገባ ያየ ሰው በትኩረት ያየኝ ነበር፡፡ ስወጣ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ፀጉሬ ተከናንቤ ነበር የምወጣው፡፡ እዛ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አይከናነቡም፡፡ ‹‹አሸባሪ ናት፤ ጥቁር ናት ግን ተከናንባ ነው የምናያት ፈራናት›› ብለው አስጠቆሙኝና እስር ቤት ገባሁ፡፡ የዩኤን ወረቀት ነበረኝ፡፡ የደረሰብኝን ነገር ሁሉ አጫወትኳቸው፡፡ እስር ቤት ውስጥ ስገባ ለእኔ እረፍት ነበር፤ አልተጐዳሁም፡፡ ከእስር ቤት ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን በየሜዳውና በየመናፈሻው ወዳድቀው ተወንጫፊና፣ ተፈንጣሪ መሳሪያ እየወደቀባቸው ይሞታሉ፡፡ እኔ በቅርብ የማውቃት ልጅ የሞተች አለች፡፡ እኔ እዚህ ስመጣ … አሁንም የሚያስለቅሰኝ እዛ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ ነው … ቢያንስ መቶ ኢትዮጵያውያንን ማምጣት ቢቻል ---

በጉብዝናህ ወራት የመጦሪያህን ነገር አስብ! ከድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኞችንና ለንግድ ሥራ የሚንቀሳቀሱ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎችን የሚያመላልሰው ባቡር የዘወትር ደንበኛ ነበሩ፡፡ በድሬዳዋ ከተማም እኔ ነኝ ያሉ እውቅ የኮንትሮባንድ ነጋዴ በመሆናቸው ወ/ሮ ፋጡማ ሮብሌን የማያውቅ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ አልነበረም፡፡ በወጣትነትና በጐልማሳነት የዕድሜ ዘመናቸው ከፊናንስ ወታደሮች እየደበቁ፣ አንዳንዴም እየተሻረኩ ደህና ጥሪት ለመያዝ ችለው ነበር፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱ ከጉምሩክ ፍተሻ ሲያልፍ አትራፊ፣ በኬላ ላይ በሚደረግ ፍተሻ ሲወረስ ደግሞ እጅግ አክሣሪ መሆኑን ቀድሞውኑ ያውቁ ነበርና በየጊዜው የሚያጋጥማቸው ነገር ሣይረብሻቸው ለዓመታት በዚሁ ንግድ ዘለቁ፡፡ የኩባንያ ሠራተኛ የነበሩት ባለቤታቸው በሞት ስለተለዩዋቸውና ሰባቱን ልጆቻቸውን የማሣደጉና የማስተማሩ ኃላፊነት በእሣቸው ትከሻ ላይ ብቻ በመውደቁ፣ ቀን ከሌት ሣይሉ የሚባትሉ ትጉህ ነጋዴ ነበሩ፡፡

በኮንትሮባንድ ንግዱ ላይ የሚደረገው ፍተሻና ቁጥጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሲሄድ ሁሉም ነገር እንደቀድሞው ቀላል አልሆንላቸው አለ፡፡ በደካማ አቅማቸው እሣት ከላሱ ነጋዴዎች እየተጫረቱ የሚያመጡትን ልባሽ ጨርቆች ኬላ ላይ የፊናንስ ወታደሮች ያስቀሩባቸው ጀመር፡፡ ለምግብ እንጂ ለሥራ ያልደረሱት ልጆቻቸው ይህንን የእናታቸውን ችግር ለመረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ አልነበሩምና ችግራቸውን ለብቻቸው ለመወጣት መፍጨርጨራቸውን ቀጠሉ፡፡ ጨከን ብለው የኮንትሮባንድ ንግዱን ጥለው ወደ ሌላ ሥራ እንዳይሰማሩ አልችለውም የሚል ሥጋት ያዛቸው፡፡ ምን አድርጌ? …እኔ … ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሥሠራው የኖርኩትና የማውቀው ሥራ ይህንኑ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሥራ አላውቅ፡፡ ጭንቀቱ ፈተናቸው፡፡ እስኪ ትንሽ ቀን … ነገ ምን እንደሚመጣ ማን ያውቃል … ተስፋቸውን ሰንቀው ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ አንዴም ሲያስከፋ አንዴም ሲያስደስታቸው የኖረው የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ከቀናቶች በአንደኛው ቀን የመኖር ተስፋቸውን የሚያጨልምና ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል አጋጣሚ ፈጠረባቸው፡፡

ከድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኞችን አሣፍሮ ይጓዝ የነበረው ባቡር በመገልበጡ፣ በባቡሩ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት መንገደኞች አብዛኛዎቹ የሞትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው፡፡ እንደ ዕድል ሆነናም ወ/ሮ ፋጡማ በአደጋው ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ከሞት ከተረፉት መንገደኞች መካከል አንዷ ሆኑ፡፡ ሁኔታው እጅግ አሣዛኝ ነበር፡፡ በአደጋው በወ/ሮ ፋጡማ እግሮችና እጆች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እነዚያ ሮጠው የማይጠግቡት እግሮቻቸው ያለ ድጋፍ አልንቀሣቀስ አሏቸው፡፡ የሰው እጅ አላይም ብለው ሲታትሩ የኖሩት እናት፤ አካል ጉዳተኝነት ከቤት አዋላቸው፡፡ የወ/ሮ ፋጡማን ቤት ችግር ገባው፡፡ ልጆች ኑሮን ለመቋቋም አቅም አጡ፡፡ ህይወት ፈተና ሆነችባቸው፡፡ የወ/ሮ ፋጡማ ልጆች ይህንን የህይወት ፈተና እንደ እናታቸው ተጋፍጠው ለመቋቋም የሚያስችላቸውን አቅም አላገኙም፡፡ ቀስ እያሉ ከፈተናው እየወደቁ ቀሩ፡፡ ከወለዷቸው ሰባት ልጆቻቸው መካከል ደካማና ህመምተኛ እናትን የመጦርና የመንከባከብ፣ ታናናሽ እህትና ወንድሞችን የማስተማርና የማሣደግ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚችል ልጅ ማግኘት የማይቻል ሆነባቸው፡፡

የሚሆነውን ሁሉ አልጋ ላይ ሆነው ከማየት የዘለለ ነገር የማድረግ አቅም አጡ፡፡ እነዛ የነገን ተስፋ የሰነቁባቸው፣ ተምረውና አድገው ይጦሩኛል ያሏቸውና ያለ አባት ያሣደጓቸው ሰባት ልጆቻቸው በየተራ ይህቺን ዓለም እየተሰናበቷት ሔዱና እናታቸውን ብቸኛ አደረጓቸው፡፡ ህይወት ይብስ ጨለመች፡፡ ሰባት ልጆቻቸውን ሞት የነጠቃቸውን እናት፤ ከልጆቻቸው መካከል አንደኛዋ አያት አድርጋቸው ነበርና ከዚሁ ህፃን ጋር ኦና ቤታቸውን ታቅፈው ቀሩ፡፡ እንደ ቀድሞው እዚህም እዚያም ብለው ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ ነገር ጠፋ፡፡ ይህንን ሁኔታ የተረዱት የአካባቢያቸው ሰዎች እዛው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው “ዳዊት የአረጋውያን መጦሪያ ድርጅት” እንዲሄዱ መከሩአቸው፡፡ ወደ ድርጅቱ ሲመጡም የእሳቸው ዓይነት እጣ ፈንታ የገጠማቸውን በርካታ አረጋውያን በማየታቸው እንደገና የመኖር ተስፋቸው ለመለመ፡፡ ወ/ሮ ፋጡማ ዛሬ በማዕከሉ በየቀኑ ለቁርስ ብቻ የምትሰጣቸውን ምግብ ለመቀበል ማልደው እያነከሱ ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡

ይህቺኑ ከድርጅቱ የምትሰጣቸውን ምግብ ከሚያሣድጉት የልጃቸው ልጅ ጋር እየተቃመሱና ለነፍስ ያሉ በጐ አድራጊ ግለሰቦች በሚያደርጉላቸው የአልባሳት እርዳታ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ፡፡ እኚህን እናት ያገኘኋቸው Help age Ethiopia የተባለ ድርጅት ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሁለት የአረጋውያን መርጃ ማዕከላትን ባስጐበኘን ወቅት ሲሆን ወ/ሮ ፋጡማ በዳዊት የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ውስጥ የሚረዱ እናት ናቸው፡፡ አሰገደች አስፋው የአረጋውያን መረጃ ማዕከልም በጉብኝት ፕሮግራሙ በጋዜጠኞች የተጐበኘ የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ነው፡፡ ሁለቱም ማዕከላት በግለሰቦች የራስ ተነሳሽነት የተቋቋሙ ቢሆንም ለአረጋውያኑ የእርዳታ አገልግሎት የሚሰጡት በተለያዩ መንገዶች ነው፡፡ ወ/ሮ ፋጡማ ሮብሌን ያገኘሁበት “ዳዊት የአረጋውያን መርጃ ማዕከል” ለአረጋውያኑ እርዳታና እንክብካቤ የሚያደርገው አረጋውያኑ በመኖሪያ ቦታቸዉ ላይ ሆነው በየዕለቱ ጠዋት አንድ ጊዜ የምግብ አገልግሎት በመስጠት ሲሆን ህክምናና አልፎ አልፎ ደግሞ የአልባሣት ድጋፍም ያደርግላቸዋል፡፡ በወ/ሮ አሰገደች አስፋው መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ያየኋቸው አረጋውያን ግን ሙሉ ኑሮአቸው በዚሁ ድርጅት ውስጥ ሆኖ፣ በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ እየተመገቡ የቀንና የሌሊት ልብስ ተሰጥቶአቸው ህክምናም እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

በሁለቱም የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከላት ዘር፣ ሃይማኖትና ብሔር ቦታ የላቸውም፡፡ 950 አረጋውያን የሚረዱበት የ“ዳዊት አረጋውያን መርጃ ማዕከል” ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት በቀለ እንደነገሩን፤ ማዕከሉ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ድርጅቶች የሚያገኘውን እርዳታ ለእነዚህ አረጋውያን እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡ አረጋውያኑን ከአንድ ጊዜ በላይ ለመመገብ የማዕከሉ አቅም አለመፍቀዱን ተነግሮናል፡፡ ከማዕከሉ እርዳታ ከሚያገኙት አረጋውያን ብዙዎቹ ልጆቻቸው በህይወት የሌሉና እጅግ ከፍተኛ በሆነ የድህነት ህይወት ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማንም አግኝተናል፡፡ እነዚህ አረጋውያን ከዕድሜያቸው መግፋት በተጨማሪ በሽታው ባስከተለባቸው አዕምሮአዊና አካላዊ ህመም ሣቢያ እንደ ልባቸው ተሯሩጠው የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት አይችሉም፡፡ ማዕከሉ ደግሞ የሚሰጣቸው በቀን አንድ ጊዜ ለቁርስ የምትሆን ሩዝ፣ ዳቦ ወይም ቅንጬ ብቻ ነው፡፡

ይህ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ለሚገባው የኤች አይቪ ኤድስ ታማሚ የሚበቃ አይደለም፡፡ ሆኖም አረጋውያኑ በዚህች ብቻ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ሰዓቱን ጠብቆ መወሰድ የሚገባውን መድሃኒት ለመውሰድ አረጋውያኑ ምግብ እስኪሰጣቸው አይጠብቁም፡፡ በባዶ ሆዳቸው ይውጡታል፡፡ ይህ ደግሞ ዕድሜ፣ ረሀብና በሽታ ያደከማቸው አረጋውያን አንጀት የሚችለው አይደለም፡፡ ይህንን ሁኔታ ማዕከሉ ታሳቢ አድርጐ በተለይ ለኤች አይቪ ህሙማን የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ ሌላው በዳዊት የአረጋውን መርጃ ማዕከል ውስጥ ያገኘናቸው አዛውንቶች ትልቅ ችግር የመኖሪያ ቤት እጦት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ አረጋውያን ወደ ማዕከሉ የሚመጡት ልጆቻቸውን ወይም ቤተሰቦቻቸውን በሞት ሲነጠቁና ጧሪና ረዳት ሲያጡ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በየእምነት ተቋማቱ ደጃፍ እና በየጐዳው ላይ የወደቁ አረጋውያን ቁጥር በርካታ ነው፡፡ በዳዊት የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ውስጥ ያገኘኋቸው ተረጂ አረጋውያን እንዳጫወቱኝ፤ በቅርቡ ሁለት የዚህ ማዕከል ተረጂ የነበሩ አዛውንቶች በጅብ የመበላት ክፉ እጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ እጣ ፈንታ በሌሎችም በእድሜ በገፉና ጧሪና ቀባሪ ባጡ አረጋውያን ላይ የማይደርስበት ምክንያት የለም፡፡ ሌላው በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ አረጋውያንን ሰብስቦ እርዳታና ድጋፍ የሚያደርግላቸው ማዕከል የወ/ሮ አሰገደች አስፋው የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ነው፡፡

በአንዲት እናት በጐ ፈቃደኝነት የተቋቋመው ማዕከሉ፤ ዛሬ አንድ መቶ ሰላሳ ረዳትና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን ሰብስቦ ይጦራል፡፡ ሰማንያ የሚደርሱትን ደግሞ እዚያው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እርዳታ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ አሰገደች አስፋው፤ የሞላ ቤት ንብረታቸውን ሸጠው፣ ወርቅና ጌጣቸውን በገንዘብ ለውጠው አረጋውያኑን ወደ መጦርና መንከባከቡ ሥራ ሲገቡ “አበደች” ያላላቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ እድሜያቸው የገፉ ሰዎችን መርዳትና መንከባከብ፣ የተቸገሩን ማገዝ ደስታ ከሚሰጧቸው ተግባራት መካከል ዋንኞቹ ነበሩ፡፡ ይህ በልጅነት እድሜ የተጀመረው ያጡትን የመርዳትና የመደገፍ ፍላጐት እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ አልተዋቸውም፣ እንደውም ሀብትና ንብረትን አስንቆ ከአረጋውያንና ከደካማ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር ይበልጥ ደስታ እንዲሰጣቸው አደረጋቸዉ እንጂ፡፡ ልጆቻቸው ከአገር ውጪ ቢሆኑም በእናታቸው ሀሳብና ስራ ላይ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ ይልቁንም አቅማቸው በፈቀደ መጠን እናታቸውን ለማገዝ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ይህን የወ/ሮ አሰገደችን ብርቱ ጥረትና ቀና ተግባር የተመለከተው የአለማያ ዩኒቨርሲቲም ለወ/ሮ አሰገደች ሰባት የወተት ላሞችን በእርዳታ ሰጣቸው፡፡ እርዳታና ድጋፍ አድርጉልኝ ማለት የማይሆንላቸው እኚህ ሴት፤ ከብቶቹ ገቢ ለማስገኘት እንዲችሉና በራሳቸው ገቢ ለመተዳደር እንዲበቁ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከሉን ባቋቋሙበት የተንጣለለ ሜዳ ላይ የጓሮ አትክልቶችንና የፍራፍሬ እርሻዎችን ማልማት ጀመሩ፡፡

ከእርሻ የሚያገኙትን ፍራፍሬ ለገበያ በማቅረብ እና ከወተት ላሞቹ ከሚገኘው የወተት ምርት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የወ/ሮ አሰገደችን ሀሳብ ከግብ ለማድረስ አቅም ሆናቸው፡፡ “እኛ እርዳታና ልመና አናውቅም ሠርተን እንኖራለን፡፡ የድሬዳዋ ህዝብ ደግሞ ደግ ነው፡፡ ተለይቶንም አያውቅ፡፡ ሁሌም ከጎናችን ነው” የሚሉት ወ/ሮ አሰገደች፤ ዛሬ ለማዕከሉ ገቢ ማስገኛ የሚሆን የሚከራይ ህንፃ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ለስራ እንጂ ለወሬ እምብዛም ቦታ የማይሰጡት ወ/ሮ አሰገደች፤ ስለማዕከሉና ስለሚሰጡት እንክብካቤና ድጋፍ ብዙ መናገር አይፈልጉም፡፡ “እኔ ያደረግሁት ነገር የለም፡፡ ሁሉም በፈጣሪና በድሬዳዋ ህዝብ የሆነ ነው፡፡” የሚል ነው ምላሻቸው፡፡ እዚሁ መጦሪያ ማዕከል ውስጥ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው አቶ አድነው ሸዋረጋ የተባሉ የ78 አዛውንት ወደዚህ ማዕከል ከመጡ ሶስት አመት እንደሆናቸው አጫውተውኛል፡፡ በማዕከሉ የሚደረግላቸውን እንክብካቤና ድጋፍ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “እኔ ቃል የለኝም፡፡ በህይወቴ ሁሉ ከኖርኩባቸዉ ጊዜያት እዚህ ማዕከል ውስጥ ያሳለፍኩት ሦስት አመታት እጅግ የተለዩና አስደሳች ነበሩ፡፡ ንፁህ በልቼ ንፁህ ለብሼና ንፁህ መኝታ ላይ ተኝቼ እየኖርኩ ነው፡፡ የወጣትነትና የጉልምስና ዘመኔን የኖርኩት ወደፊት ምን ያጋጥመኛል የሚል ስጋትና ሀሳብ ሳይኖርብኝ ነው፤አስቤውም አላውቅም ነበር፤ ለካ ጌታ ይሄን አዘጋጅቶልኝ ነው፡፡ ልጆች አልወለድኩም፡፡

ግን ጧሪና ተንከባካቢ እግዚአብሔር ሰጥቶኛል” ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚኖሩት አራት ሚሊዮን አረጋውያን መካከል አብዛኛዎቹ እጅግ በከፋ ድህነትና ችግር ውስጥ እንደሚኖሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ አረጋውያን መካከል መደበኛ ወርሃዊ የጡረታ ገቢ የሚያገኙት 500ሺ ያህሉ ብቻ እንደሆኑና ቀሪዎቹ አረጋውያን ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ እንደሚተዳደሩ መረጃው ይጠቁማል፡፡ አረጋውያኑ ከተተኪው ትውልድ ክብርና እንክብካቤ የማግኘታቸው ሁኔታ በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን የጠቆመው መረጃው፤ ለዚህም ምክንያቱ አረጋውያንን የመጦር ባህልና ወግ መሸርሸሩና ቤተሰባዊ ትስስሩ እየላላ መምጣቱ ዋንኞቹ ናቸው ይላል፡፡ አረጋውያን ረዳትና ደጋፊ እንዲያጡ ከሚያደርጓቸው ሌሎች ምክንያቶች መካከል ስደትና ኤች አይ ቪ ኤድስ እንደሚገኙባቸው የጠቆመው መረጃው ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ስራና ትምህርት ፍለጋ ወደ ዋና ከተሞች የሚፈልሱ ወጣቶች አዛውንት ወላጆቻቸውን ለከፋ ድህነትና ረጂ አልባነት እንደሚዳርጓቸው አመልክቷል፡፡

ትኩስ የወጣትነት ጉልበትና ብሩህ አእምሯቸውን ለሀገራቸውና ለወገናቸው ዕድገትና መሻሻል ሲገብሩ ኖረው የዕድሜ ጀምበራቸው ስታዘቀዝቅ፣ ጉልበታቸው ሲደክም፣ ጧሪና ተንከባካቢ ሲያስፈልጋቸው፣ ጀርባችንን ልንሰጣቸው አይገባንም፡፡ እነዚህ ሁለት በግለሰቦች ተነሳሽነት የተቋቋሙት የአረጋውያን መርጃ ማዕከላት በስፋት ሊሰራባቸውና በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ መንግስትም ሆነ ዜጎች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት ያሻል፡፡ የዛሬው ወጣት የነገ አረጋዊ መሆኑ አይቀርምና በጉብዝና ወራት የመጦሪያን ነገር ማሰቡም ተገቢ ነው፡፡

በኢንተርኔት አማካኝነት የተቃዋሚዎችን መረጃ ለመሰለልና እንቅስቃሴያቸውን ለመከታተል የሚያገለግል ማጥመጃ ሶፍትዌር (Trojan horse) የሚጠቀሙ 25 አገራት እንዳሉ የገለፀ አንድ የካናዳ የጥናት ተቋም፤ ኢትዮጵያን በማካተት የበርካታ አገራትን በስም ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አስተባብሏል፡፡ ማጥመጃው ሶፍትዌር በተለያዩ መንገዶች የቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን አልፎ እየሾለከ ወደ ኮምፒዩተር መግባት የሚችል ሲሆን፤ መረጃዎችን ለመምጠጥ፣ ፓስዎርዶችን ለመስረቅ፣ የስልክና የስካይፒ ግንኙነቶችን ለመቅረጽ፣ በተለይም የኢሜይል መልእክቶችን ለመሰለል ያገለግላል ተብሏል፡፡

በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ “ስር ሲቲዘን ላብ” የተሰኘው የጥናት ተቋም ረቡዕ እለት ይፋ ባደረገው ማስጠንቀቂያ፤ ሰዎች በኮምፒዩተርና በሞባይል ስልክ ውስጥ የሚያስቀምጡት መረጃ እንዲሁም የሚለዋወጡት መልእክት ለስለላ የተጋለጠ ነው ብሏል፡፡ እንዲያውም በኮምፒዩተራችሁ ላይ የተገጠሙ ማይክሮፎኖችና ካሜራዎችን በመጠቀም ቤት ውስጥ የምታደርጉት እንቅስቃሴና የምትናገሩት ነገር ሁሉ፣ የስለላ አይንና ጆሮ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡

ለስለላ ያገለግላል የተባለውና “ፊንፊሸር” የተሰኘው ማጥመጃ ሶፍትዌር በተገኘባቸው አገራት ሁሉ፣ መንግስታት በተቃዋሚዎችና በዜጐች ላይ ስለላ ያካሂዳሉ ማለት ባይቻልም፤ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ገናና (authoritarian) መንግስታት እጅ ውስጥ መግባቱ ግን አሳሳቢ ነው ብሏል ተቋሙ፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ስለማጥመጃ ሶፍትዌሩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡

የካቲት 23 ቀን 2005 ዓ.ም “በኢንዲያን ኢንተርናሽናል ት/ቤት የተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ አቀረቡ” በሚል ርዕስ በወጣው የአዲስ አድማስ ዘገባ ላይ ት/ቤቱ ቅሬታውን በደብዳቤ ገልጿል፡፡ ት/ቤታችን ከተመሠረተበት እ.አ.አ ከ2006 ጀምሮ ከተማሪ ቤተሠቦች እና ከባለድርሻ አካላት የተመሠገነ መልካም ስም ያገኘ ሆኖ ሣለ፤ ሚዛን ያልጠበቀ ዘገባ በምናከብረው ጋዜጣችሁ ማቅረባችሁ ሃላፊነት የጐደለው ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ የት/ቤቱ ዳይሬክተር ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ በአጠቃላይ የወላጆችን ቅሬታ እንጂ የሠራተኞችን ምላሽ ሳያካትት በወጣው ዘገባ ቅሬታ ተሠምቶናል ይላል ደብዳቤው፡፡

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ፣ ውጤት እያስመዘገብኩ ነው አለ እንዴት ቢባል፤ የታክሲ ስምሪት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማካሄድ ነዋ ሌላ አዲስ አበባ ካለ ይነገረን፤ ነባሯ ከተማ ግን ታክሲ ተቸግራለች ገና ምኑን አይታችሁ? የትራንስፖርት ሚኒስትርም ያሰበው ነገር አለ ከከተማ ውጭ፣ ማታ ማታ የመኪና ጉዞ ክልክል ይሆናል ተብሏል በዚህም ውጤት ይመዘገባል - የትራንስፖርት እጥረትን የሚያባብስ ሜክሲኮ አካባቢ፣ የስራ መውጫ ሰዓት ላይ፣ ወደ ጦር ሃይሎችና ወደ አውቶቡስ ተራ ለመሄድ አዳሜ ይጋፋል።

ከወዲያ ማዶ፣ ወደ ሳሪስና ወደ ጎፋ፣ መዓት ሰው ይተራመሳል። ወዲህ ዞር ስትሉም፣ ወደ መገናኛ ለመሄድ የሚጠብቅ እልፍ ሰው ታያላችሁ። የታክሲ ስምሪት ከታወጀ በኋላ፣ የትራንስፖርት እጥረት ተባብሶ፣ ግፊያውና ግርግሩ ጨምሯል። ለዚህም ነው፤ በርካታ ፌርማታዎች ላይ ወረፋ የተጀመረው። እዚያው ሜክሲኮ አካባቢ በገሃር መስመር፤ ወደ አራት ኪሎ ታክሲ ለመሳፈር የሚፈልግ ከ150 በላይ ሰው በሁለት አቅጣጫ ተሰልፏል። ታክሲ ጠፋ! ለነገሩ “ታክሲ ጠፍቷል አልጠፋም” ለማለት ያስቸግራል።

ወረፋ ከሚጠብቁ ሰዎች አጠገብ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው ቆመዋል። ግን ወደ ቦሌ መስመር የተመደቡ ናቸው፤ ከዚያ ውጭ ቢንቀሳቀሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ከመቶ በላይ ሰዎች ታክሲ አጥተው ለወረፋ ተገትረዋል፤ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው በሰልፍ ቆመዋል። ወረፋ ጠብቀው አራት ኪሎ ሲደርሱም፣ ነገርዬው ተመሳሳይ ነው። ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳና ወደ መርካቶ ለመሄድ ብዙ ሰዎች ይሻማሉ - በታክሲ እጥረት። ዞር ብለው ሲያዩ ግን፣ ከአራት ኪሎ ወደ አምባሳደር መስመር የተመደቡ በርካታ ሚኒባሶች፣ ተሳፋሪ ጠፍቶ አፋቸውን ከፍተዋል።

ተሳፋሪ ወደሚበዛበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉማ። በደርግ ዘመን የነበረውን የታክሲ ስምሪት እንደገና ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ያስተላለፉ ባለስልጣናት፤ ገና ከጅምሩ መዘዙን ማሰብ አይችሉም ነበር? ይችሉ ነበር። ሰው ናቸው። ደግሞም፣ እነሱ ባይችሉ እንኳ፣ አስቦ የሚመክር አልጠፋም ነበር። ለምሳሌ፣ የስምሪት ቁጥጥር በግንቦት 2003 ዓ.ም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ፅሁፎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የታክሲ ስምሪት የትራንስፖርት እጥረትን በማባባስ አሁን የምናየውን አይነት ቅዠት እንደሚፈጥር በግልፅ ተንትኖ የሚያቀርብ ፅሁፍ በአዲስ አድማስ መቅረቡን አስታውሳለሁ (የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም የአዲስ አድማስ እትም)። “በየአቅጣጫውና በየመስመሩ፤ የትራንስፖርት ፈላጊዎች ብዛት እንደእለቱና እንደሰአቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው ይለያያል።

... የሰኞ፤ የአርብ፣ የቅዳሜና የእሁድ ተሳፋሪዎች ቁጥር ተመሳሳይ አይሆንም። ማለዳ 11 ሰአት፤ ጥዋት ሁለት ሰአት፤ ረፋዱ ላይ፣ ከቀኑ 11 ሰአት፤ ከምሽቱ ሶስት ሰአት በኋላ በዚያው መስመር የሚኖረው የተሳፋሪ ቁጥር… ይለያያል። በክረምት፤ በበአል ቀናት፣ በልዩ ዝግጅቶች፣ በሰርግ ወራትም እንዲሁ ለየቅል ነው። “...ታክሲዎች የራሳቸውን ገቢ ለማሳደግ ብዙ ተሳፋሪ ማግኘት ስላለባቸው፤ በእያንዳንዱ መስመር ላይ እንደሰአቱና እንደእለቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው የሚለዋወጠውን የተሳፋሪ ቁጥር በማስተዋል (መስመራቸውን እያስተካከሉ) ለመስራት ይጣጣራሉ። ... በስምሪት ቁጥጥር ከተመደቡበት መስመር ውጭ እንዳይሰሩ ከተከለከሉ ግን ገቢያቸው ይቀንሳል፣ ታክሲ ፈላጊውም ይጉላላል” “በሆነ ሰአት፤ …ተሳፋሪ ከመብዛቱ የተነሳ፤ በዚያ መስመር ከተመደቡት ታክሲዎች አቅም በላይ ይሆናል። ... ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ለሰአታት ይቆማሉ፤ ሌሎች ታክሲዎች መጥተው መስራት አይችሉም። …በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተሳፋሪ ከማነሱ የተነሳ፤ በቦታው የተመደቡ ታክሲዎች ያለስራ ቆመው ጊዜ ያባክናሉ። በትራንስፖርት እጦት ብዙ ሰው ወደተጉላላበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉም። ከጥቂት ሰአታት በኋላ፤ ሁኔታው ይቀየራል። በመጀመሪያው ቦታ ተሳፋሪ ጠፍቶ ታክሲዎች ያለ ስራ ይቆማሉ። በሁለተኛው ቦታ ደግሞ፤ በታክሲ እጥረት፤ ተሳፋሪዎች ለረዥም ሰአት ይጉላላሉ።

” “…ተሳፋሪ አጥተው ያለ ስራ የሚቆሙ ታክሲዎችን እና ታክሲ አጥተው የሚንገላቱ ተሳፋሪዎችን ማበራከት ነው የቁጥጥሩ ውጤት። ቢሮክራቶቹ… የቁጥጥር ሱስ… የመጣው ይምጣ የሚያሰኝ እጅግ ሃይለኛ ሱስ ካልሆነባቸው በቀር፤ መዘዙን ያጡታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል” እንዲህ እንደምታዩት፤ የስምሪት ቁጥጥሩ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጠቃሚ ምክር ቢቀርብም፣ የሚሰማ ባለስልጣን አልተገኘም። ለነገሩ፣ ከአንዳንድ የታክሲ ባለቤቶችና ሾፌሮች በስተቀር አብዛኛው ሰው፣ የታክሲ ስምሪት ጠቃሚ እንደሚሆን ገምቶ ነበር - የትራንስፖርት ችግር የሚቃለልለት መስሎት። ለምን መሰለው? ታስታውሱ እንደሆነ፤ አንዳንድ የታክሲ ሾፌሮችና ባለቤቶች ቅሬታቸውን ሲገልፁ፤ “ስምሪቱን የሚቃወሙት፣ ጥቅማቸው ስለሚቀርባቸው ነው” ተባለ። የዚህ ትርጉም ምን እንደሆነ አስቡት። አሃ… “ባለታክሲዎችና ሾፌሮች ከተጎዱ፣ ተሳፋሪ ይጠቀማል” ማለት ነዋ። እንዴት እንዴት? በንግድ እና በቢዝነስ ዙሪያ የብዙ ሰው አስተሳሰብ በጣም የተዛባ ከመሆኑ የተነሳ፤ ሻጮችና ሸማቾች፣ ባለታክሲዎችና ተሳፋሪዎች… ተቀናቃኝ ባላንጣ ሆነው ይታዩታል። ስለ ታክሲ ሲያስብ፣ 5 ሳንቲም አሳልፎ የማስከፈልና 5 ሳንቲም አጉድሎ የመክፈል ጉዳይ ብቻ ጎልቶ የሚታየው ሰው፤ “አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው በሌላኛው ጉዳትና መስዋእትነት ነው” ብሎ ያምናል።

እናም፣ “ስምሪቱ ባለታክሲዎችን የሚጎዳ ከሆነ፣ ተሳፋሪዎችን ይጠቅማል” ብሎ ይደመድማል። የሰዎች ኑሮ፣ ከአውሬዎች ሕይወት ብዙም የተለየ ሆኖ አይታየውም - እርስ በርስ እየተቦጫጨቁ መኖር። እውነታው ግን፣ የዚህ ተቃራኒ ነው። አንዱ የሚጠቀመው፣ ሌላኛው ሲጠቀም ነው። ባለታክሲው የሚጠቀመው መቼ ነው? በሆነ አቅጣጫ በክፍያ ለመጓዝ የሚፈልግ ተሳፋሪ ሲመጣለት። ተሳፋሪው የሚጠቀመውስ? ክፍያ ተቀብሎ ለማጓጓዝ የሚፈልግ ታክሲ ሲመጣለት። የባለታክሲው ጥቅም እየጨመረ የሚሄደው፣ ብዙ ተሳፋሪዎችን ፈልጎ ሲያገኝና ሲያስተናግድ ነው - ገቢው ያድግለታል። የተሳፋሪ ጥቅም የሚጨምረው ደግሞ፣ በርካታ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱ ታክሲዎች ሲመጡ ነው - በትራንስፖርት እጦት ተገትሮ አይውልም። አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው፣ ሌላኛውም ወገን የሚጠቀም ከሆነ ነው። መሰረታዊው የቢዝነስ ቁምነገርም ይሄው ነው - አምስት ሳንቲም የማጉደልና የማሳለፍ ሳይሆን። የስምሪት ቁጥጥሩም፣ ይህንን መሰረታዊ ቁምነገር በማደናቀፍ ነው ባለታክሲዎችንና ተሳፋሪዎችን ለጉዳት የዳረጋቸው። ጉዳቱ ግን፣ ዛሬ የምናየው ቅዠት ብቻ አይደለም። የባለታክሲዎች ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመጣ ቁጥር፤ ወደ ቢዝነሱ የሚገቡ ሰዎችም ቁጥራቸው ይቀንሳል። በተቃራኒው፣ ከቢዝነሱ የሚወጡ ሰዎች ይበራከታሉ።

ለዚህም ነው፤ በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ መደበኛ ሚኒባስ ታክሲዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣው። ከጥቂት አመታት በፊት ቁጥራቸው 12ሺ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ቢገልፁም፣ አሁን ግን በስራ ላይ የሚገኙት 9ሺ አይሞሉም። አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥር፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ ውሎ አድሮ መዘዙ የከፋ እንደሚሆን ከዚህ ቀውስ መረዳት እንችላለን። የታክሲ ወረፋ ባልነበረበት ከተማ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ… “የታክሲ ወረፋ” የኑሯችን አካል ሆኖ አረፈው። ተሳፋሪ ያጣ ታክሲ ተደርድሮ፣ ታክሲ ያጣ ተሳፋሪ ተሰልፎ የምናይበት የቅዠት ዓለም ውስጥ ገብተናል። ይህም አልበቃ ብሎ፣ ቅዠቱን የሚያጦዝ መግለጫ እንሰማለን። የአዲስ አበባ መስተዳድር የትራንስፖርት ቢሮ፣ ረቡዕ እለት በመንግስት ሚዲያዎች በኩል የሰጠውን መግለጫ አላዳመጣችሁም? በየጊዜው በምወስዳቸው እርምጃዎች መልካም ውጤቶችን እያስመዘገብኩ ነው ብሏል - የትራንስፖርት ቢሮው። ለምሳሌ ያህልም፤ የታክሲዎች ስምሪት ላይ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ እርምጃ እንደወሰደ ቢሮው ሲገልፅ፤ አሁን አሁን ከተመደበበት መስመር ውጭ ውልፍት የሚል ታክሲ የለም ብሏል። ችግሩ ምን መሰላችሁ? አላስፈላጊው ቁጥጥር በተፈጥሮው መጥፎ ወይም ጎጂ ስለሆነ፣ ቁጥጥሩ በጥብቅ ተግባራዊ ሲደረግ ጎጂነቱ ይጨምራል እንጂ መልካም ውጤት ሊመዘገብ አይችልም። መልካም ውጤት የተመዘገበባትና ባለስልጣናት ብቻ የሚያውቋት ሌላ “አዲስ አበባ” ከሌለች በቀር፤ በነባሯ ከተማ ውስጥ የታክሲ ግርግርና ወረፋ ሲበራከት ነው የምንመለከተው።

የፌደራል ባለስልጣናት ደግሞ በበኩላቸው ሌላ ቁጥጥር ተግባራዊ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል። ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በማታ የሚደረጉ ጉዞዎች እንደሚታገዱ ለኢቴቪ የተናገሩ ባለስልጣናት፤ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የታሰበ እርምጃ ነው ብለዋል። ከከተማ ውጭ፣ በማታ በሚከናወን ጉዞ ላይ የትራፊክ አደጋ ይደርሳል ወይ? አዎ ይደርሳል። ነገር ግን፣ የከተማ ውስጥ እና የቀን ጉዞ ላይም የትራፊክ አደጋ ይደርሳል። ታዲያ፣ የትራፊክ አደጋ ለመከላከል አስበን፤ በከተማ ውስጥና ከከተማ ውጭ፤ በቀን እና በማታ የሚከናወኑ የመኪና ጉዞዎችን ለምን አናግድም? ለነገሩማ፤ አይነቱና መጠኑ ይለያያል እንጂ፤ በተፈጥሮው “አደጋ” የማያሰጋው አንዳችም የሰው እንቅስቃሴ የለም። ፎቅ መስራት፣ ጉድጓድ መቆፈር፣ መንገድ መጥረግ፣ መሬት ማረስ፣ ቤት ማፅዳት… ሁሉም አይነት ስራ፣ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ መስራት ሳይቀር፣ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋ ይደርሳል።

ለምሳሌ፣ ከፍተኛ አደጋ ከሚያጋጥማቸው ነገሮች መካከል፣ እርግዝናና ወሊድ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ምን ይሄ ብቻ? እንደአረማመዱና እንደአሯሯጡ፣ እንደአጎራረሱና እንደአጠጣጡ፣ እንደአስተኛኘቱና እንደአለባበሱ ሁኔታ ለአደጋ የሚጋለጥ ሰው ጥቂት አይደለም። እና፣ አደጋዎችን ለማስቀረት አርፎ መቀመጥና ሞቱን መጠባበቅ አለበት? በጭራሽ! ሰው፣ የስራውንና የእንቅስቃሴውን ምንነት ለማገናዘብ፣ በጥረቱ የሚያገኛቸው ጥቅሞችንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለማመዛዘን የሚያስችል አቅም አለው - የአእምሮ አቅም። ጥቅሞቹን የሚያሳድጉ ዘዴዎችና አደጋዎችን የሚያስቀሩ ጥንቃቄዎች የሚፈጠሩትም፣ በሰዎች የአእምሮ አቅም ነው። ያለ ድካም በፍጥነት ከቦታ ቦታ መጓዝ እጅጉን ጠቃሚ እንደሆነ ትጠራጠራላችሁ? መኪና የተፈጠረውና የሚመረተው፣ አስፋልት የሚቀየሰውና የሚገነባው፣ ለሌላ ምክንያት አይደለም - ያለ ድካም በፍጥነት ለመጓዝ ነው። በእርግጥ አደጋዎች ያጋጥማሉ።

ግን ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር፣ አደጋው በጣም ትንሽ ነው። መኪናና አስፋልት ባልነበረበት ዘመን፣ የሰዎች አማካይ የሕይወት ዘመን 30 አመት ገደማ ብቻ ነበር። አስፋልት ላይ ፈጣን የመኪና ጉዞ፤ የሰዎችን ሕይወት አሻሽሏል። ነገር ግን፤ ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር አደጋው ትንሽ ነው በሚል፤ አደጋውን ቸል ማለት አለብን ማለት አይደለም። “አደጋ አለው” በሚል ሰበብ እርግዝናንና ወሊድን ለማስቀረት ማሰብ እብደት ቢሆንም፤ አደጋውን ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን ከመተግበር መቦዘንም “እብደት” ይሆናል። የመኪና ጉዞም ተመሳሳይ ነው። የትራፊክ አደጋ ተፈርቶ፤ የመኪና ጉዞን ማስቀረት የጤንነት አይደለም። አደጋውን በ“ፀጋ” መቀበልም እንዲሁ። ለዚህም ነው፤ የትራፊክ ደንቦችና ምልክቶች፤ የትራፊክ መብራቶችና የማሽከርከር ስልጠናዎች የተፈጠሩት። ይህም ብቻ አይደለም። አማራጮችን አመዛዝኖ፣ የመጓጓዣ አይነቱን፣ አቅጣጫውንና ጊዜውን መምረጥ ያስፈልጋል።

ለምሳሌ፤ ዋጋውንና አቅርቦቱን፣ የመጓጓዣውንና የአሽከርካሪውን ብቃት ማነፃፀር አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፤ በጥቅሉና በአመዛኙ ሲታይ፤ በብስክሌትና በሞተር ብስክሌት ከመጓዝ ይልቅ በመኪና መጓዝ የተሻለ መሆኑንም ማገናዘብ ይቻላል። በማታ ከመጓዝ ይልቅ በቀን፤ በመኪና ከመጓዝ ደግሞ በባቡር፤ በባቡር ከመጓዝ ደግሞ በአውሮፕላን ይሻላል። ለምን በጥቅሉ አማካይ የአደጋ መጠናቸው አነስተኛ ስለሆነ። እንዲህም ሆኖ፤ የአውሮፕላን ጉዞ የተሻለ ስለሆነ የመኪና ጉዞን ለማገድ፣ ወይም የመኪና ጉዞ ስለሚሻል የሞተር ብስክሌትን መከልከል፤ አልያም የቀን ጉዞ ስለሚሻል የማታ ጉዞን መከልከል… ከእብደት አይለይም። መከልከልና ማገድ ይቅርና፤ “ብስክሌት አትጠቀሙ፣ በማታ አትንቀሳቀሱ” ብሎ መምከርም ስህተት ነው።

ጥቅሙንና ጉዳቱን፣ ሰዓቱንና አቅጣጫውን፣ መጓጓዣውንና አሽከርካሪውን እያመዛዘናችሁ ተጠቀሙ ነው መባል ያለበት። “አትጠቀሙ፣ አትንቀሳቀሱ” ከሚለው የተሳሳተ ምክር አልፎ፤ ወደ ክልከላና እገዳ መግባት፤ ከመሳሳት አልፎ የሰውን ነፃነት መርገጥ ይሆናል። አለበለዚያማ፤ “የመንቀሳቀስ ነፃነት” ተብሎ በህገመንግስት የሰፈረው ፅሁፍ ምን ትርጉም አለው? ባለስልጣናት በፈቀዱት ሰዓት ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚቻለው? በደርግ ዘመን የ”ይለፍ” ወረቀት ያልያዘ ሰው ከከተማ ከተማ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ከድሮው የደርግ ዘመን የሰዓት እላፊ አዋጅ፤ በከፊል ተቀንጭቦ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ቢባል አይሻልም?

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ለሚያደርገው ሶስተኛ ጨዋታ ዝግጅቱን በውዝግቦች በመታጀብ ሊጀምር ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከቦትስዋና ጋር ከ15 ቀናት በኋላ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ይጫወታል፡፡ ይሄው የዋልያዎቹ ወሳኝ ጨዋታ ፌደሬሽኑ እና ክለቦችን ባነካኩ ውዝግቦች ገና ከዝግጅት ምእራፉ የመቃወስ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያው የሶስተኛ ዙር ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድድሮች የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለዋልያዎቹ ተጨዋቾቻውን ለመልቀቅ እንዳመነቱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገ የሊግ ጨዋታ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ፈፅመዋል በተባለው የዲስፕሊን ግድፈት የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴ በክለቦቹ ላይ ያሳለፋቸው የቅጣት ውሳኔዎች በይግባኝ ክርክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አወዛጋቢ ሁኔታዎች የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ በማቃወስ እና በክለብ ደጋፊዎች፤ በፌደሬሽኑና በብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በማካረር ለብሄራዊ ቡድኑ በሚፈልገው ትኩረት እና ሁለገብ ድጋፍ ላይ መቀዛቀዝ እንዳይፈጠር ስጋት ሆኗል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን የተጠሩ 22 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር ሰሞኑን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ እና ስምንት ተጨዋቾችን እንደቅደምተከተላቸው በማስመረጥ ከፍተኛ ውክልና አግኝተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተጨዋቾች ሲጠሩ ንግድ ባንክ ፤ መብራት ኃይልና ሰበታ ከነማ እያንዳንዳቸው 1 ተጨዋች አስመርጠዋል፡፡ የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ህልም ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በፈርቀዳጅነት በመሳተፍ ከሚጠቀሱ የአፍሪካ አገራት አንዷ ነበረች፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በ1962 እኤአ ላይ የነበረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በማጣርያው ውድድሮች በየአራት አመቱ በመደበኛነት ተሳታፊ ሆና ቆይታለች፡፡ በ2002 እኤአ ጃፓንና ኮርያ በጣምራ ላዘጋጁት የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው የቡርኪናፋሶ አቻውን 2ለ1 ቢያሸንፍም ከሜዳው ውጭ 3ለ0 ተሸንፎ ወደቀ፡፡

ከ4 ዓመታት በኋላ በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን ለምታስተናግደው 18ኛው የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ ደግሞ ኢትዮጵያ በሜዳዋ 3ለ1 በማላዊ ተሸንፋ በመልሱ ጨዋታ 0ለ0 በመለያያት ቅድመ ማጣርያውን ማለፍ ተስኗታል፡፡ ከ3 ዓመት በደግሞ ደቡብ አፍሪካ ለምታስተናግደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በቅድመ ማጣርያው ሞውሪታንያን በደርሶ መልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ 6ለ1 ብትረታም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ውድድሮች ተሳትፎ በመታደጉ ጉዞው በአጭሩ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ በአስደናቂ ስኬት የተለየ ሆኗል፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደራቀበት የአፍሪካ ዋንጫ ተመልሶ መግባት የቻለው ብሄራዊ ቡድኑ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ 1 መሪነቱን እንደያዘ ነበር፡፡

በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ጋር ተደልድሏል፡፡ በምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውተው 1 እኩል አቻ ተለያዩ፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በሜዳቸው አዲስ አበባ ላይ መካከለኛው አፍሪካን 2ለ0 አሸንፈዋል፡፡ዋልያዎቹ ከእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በሰበሰቡት አራት ነጥብ ሁለት የግብ ክፍያ የምድቡን መሪነት ጨብጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር የሚገናኝበት ግጥሚያ 3ኛው የምድብ ጨዋታ ነው፡፡ አራተኛው የምድቡን ጨዋታ ይህን ጨዋታ ካደረገ ከ10 ሳምንታት በኋላ ከሜዳው ውጭ በጋብሮኒ ቦትስዋናን መልሶ የሚገጥምበት ነው፡፡ ከዚሁ የቦትስዋና ጨዋታ በኋላ በሳምንቱ ደግሞ በምድቡ አምስተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን በሜዳው አስተናግዶ ይቀጥላል፡፡

በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ሂደት የሚያበቃው ከ6 ወራት በኋላ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር በሚያደርገው ስድስተኛው የምድብ ጨዋታ ይሆናል፡፡ የጊዮርጊስ ፤ የደደቢት እና የዋልያዎቹ የጨዋታ ጭንቅንቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለብሄራዊ ቡድን ያስመርጧቸውን ተጨዋቾች በመልቀቅ ዙርያ ከፌደሬሽኑ ጋር መወዛገብ የጀመሩት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ባለፈው ሰሞን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎቻቸው የዛንዚባር እና የመካከለኛው አፍሪካ ክለቦችን ጥለው በማለፍ ወደ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡

ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባል የመለስ ካፕ የሊግ ውድድር ለሶስት ሳምንት እንደሚቋረጥ ፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች ከየክለቡ አሰባስበው ዝግጅታቸውን በያዙት እቅድ ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጥሪ የሚቀርብላቸውን ተጨዋቾቻቸውን ላለመልቀቅ ሲያመነቱ፤ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድደሮች ከሚያደርጉት የመጀመርያ ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ በመግለፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በበኩሉ ክለቦቹ በብሄራዊ ቡድኑ እጅግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የሁለቱን ክለብ ተጨዋቾች ለመልቀቅ እንዲችሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የክለቦቹን የጨዋታ ፕሮግራም እንዲያሸገሽግላቸው እጠይቃለሁ እያለ ነው፡፡

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጭ በመጀመርያው ጨዋታ የዛንዚባሩን ጃምሁሪ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ውጤት 8ለ0 በማስመዝገብ ወደ የመጀመርያ ዙር ማጣርያው ገብቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ15 ቀናት በኋላ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ግጥሚያውን ከሜዳው ውጭ ከማሊው ክለብ ዲጆሊባ ጋር በማድረግ ይጀምራል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ደደቢት በበኩሉ የመካከለኛው አፍሪካውን ክለብ አንጌስ ዲፋቲማ ከሜዳው ውጭ 4ለ0 እንደረታ የሚታወስ ሲሆን ምንም እንኳን በመልስ ጨዋታው 2ለ1 ቢሸነፍም በደርሶ መልስ ውጤት 5ለ3 በማስመዝገቡ ሊያልፍ ችሏል፡፡

ደደቢት በኮንፌደሬሽን ካፑ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ በሜዳው ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ኤልሻንዲ ጋር በመገናኘት ይቀጥላል፡፡ የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴና የቅጣት ውሳኔዎቹ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የደረሰን መረጃ ጉዳዩ የውድድር ፕሮግራምን ለማሳወቅ፤ በብሄራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት ዙርያ ወይንም በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ በጎ እንቅስቃሴን የተመለከተ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስለተከሰተ የስርዓት አልበኛነት ተግባር እና ይህንኑ ተከትሎ በፌደሬሽኑ የዲስፒሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔ ያትታል፡፡ መለስ ካፕ ተብሎ በተጠራው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 10ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድዬም ላይ ቡና ከደደቢት ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተፈፅሟል ባለው የዲስፕሊን ግድፈት ላይ የዲስፕሊን ኮሚቴው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር እና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ ያሳለፈውን ባለ ሁለት አባሪ ገፅ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ በሁለቱ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ የጨዋታ አመራሮችን ሪፖርት መመርመሩንና ማጣራቱን ገልጿል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው የመጀመርያ ውሳኔ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ የተላለፈ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቡና ከደደቢት አድርገውት በነበረው ጨዋታ ላይ በቀኝ ጥላፎቅ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አርማና ማልያ የለበሱ ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት የሆኑትን እነ ደጉ ደበበ፤ አሉላ ግርማና አበባው ቡጣቆ የተባሉ ተጨዋቾችን ሞራል የሚነካ ቃላት በመወርወር እና አስፀያፊ ስድቦችን በመሳደብ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ዲስፕሊን ኮሚቴው ይገልፃል፡፡ የቡና ደጋፊዎች ተመሳሳይ የዲስፕሊን ግድፈት በፌደሬሽኑ ላይ መፈፀማቸውን ያሳወቀው ኮሚቴው፤ ይህ ሳይበቃቸው በእለቱ በሚያሟሙቁ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ላይ የውሃ ላስቲክና ድንጋይ በመወርወር ስርዓት መጣሳቸውን ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 9 አንቀፅ አምስት ንዑስ አንቀፅ ሁለት በፊደል ኸ በተቀመጠው መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በደጋፊዎች ለተፈጠረው የዲስፕሊን ግድፈት ተጠያቂ ተደርጓል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ በዲስፕሊን መመርያው ክፍል 6 አንቀፅ 35 በንዑስ አንቀፅ አራት መሰረት 50ሺ ብር በቅጣት እንዲከፍል እና በፕሪሚዬር ሊጉ ባለሜዳ ሆኖ የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያለተመልካች በዝግ ስታድዬም እንዲጫወት በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው ሁለተኛ የቅጣት ውሳኔ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በሆነው አበባው ቡጣቆ ላይ የተሰጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ስድብና ዘለፋ የደረሰበት አበባው የኢትዮጵያ ባህል ባልሆነ መልኩ በሰውነት ምልክት ተሳድቦ ተመልካቹን እንዳስቆጣና ረብሻው እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብላል፡፡ ስለሆነም በዲስፕሊን መመርያው ክፍል ስድስት አንቀፅ 38 መሰረት አአባው ቡጣቆ ለክለቡ በ5 ጨዋታዎች እንዳይሰለፍ እና 5ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍል በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡

የዲስፕሊን ኮሚቴው የቅጣት ውሳኔ ክፍል ሶስት የሚመለከተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን ነው፡፡ በቡና ደደቢት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በግራ ጥላ ፎቅ የጊዮርጊስን አርማና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች መሳደባቸውን የገለፀው ዲስፕሊን ኮሚቴው፤ በተጨማሪም የዚሁ ክለብ ደጋፊዎች የካቲት 15 ቀን በሴቶች የሊግ ውድድር የደደቢት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴት እግር ኳስ ቡድኖችን ባጫወቱ ዳኞች ላይ አስነዋሪ ተግባር መፈፀማቸውን ጨምሮ ለሁለቱም የደጋፊዎች የዲስፕሊን ግድፈቶች የስፖርት ማህበሩ ተጠያቂ ሆኖ እንዲቀጣ መወሰኑን አሳውቋል፡፡ ስለሆነም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 6 አንቀፅ 35 በቁጥር 4 በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር 40ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍልና በወንዶች ዋናው ቡድኑ በሜዳው የሚያደርገውን አንድ ጨዋታ በዝግ ስታድዬም እንዲያደርግ መወሰኑን ዲስፕሊን ኮሚቴው አመልክቷል፡፡

“ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ” ከትውልድህ እንጀምር የተወለድኩት ጎሬ/ኢሊባቡር ነው፤በእኛ ጊዜ ጠቅላይ ግዛት ይባል ነበር፡፡ እዛ ትንሽ ተምሬአለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ እዛ ነበሩ፡፡ ከዛም በተረፈ አዲስ አበባ ተምሬ ነው በ17 ዓመቴ ከኢትዮጵያ የወጣሁት፡፡ በምን ምክንያት ወጣህ? ዕድል፡፡ እርግጥ ቤተሰቦቼ ገንዘብ ኖሯቸው አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ቺካጎ ገባሁ፡፡ ለብዙ ዓመት እዛው ኖሬያለሁ፡፡ በኋላ እናቴንም ወንድሞቼንም ወደዛው ለመውሰድ በቃሁ፡፡ አሜሪካ የኖርኩት ለ35 ዓመት ነው፡፡ እዚያ በመቆየቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ እንዴት? ተማርኩኝ - ቢዝነስ ማኔጅመንት፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ያስገቡኝ ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ከዛ በፊት ጎበዝ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ሙዚቃ አለም ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ በጣም የተሳካ ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡

እንዴት ነው ወንድሞችህ ወደሙዚቃው ያስገቡህ? ወንድሞቼ ከሃገር የወጡት ቀይ ሽብርን ሸሽተው ነበር፡፡ ጅቡቲ እስር ቤት ከነበረ ወንድሜ ደብዳቤ ሲደርሰኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ በዛን ጊዜ ነው ወንድሞቼን ከኢትዮጵያ ያወጣሁትና ቺካጎ የመጡት፡፡ እኔ ሙዚቃ እንደሚጫወቱ አላውቅም ነበር፡፡ ሙዚቃ መቻላቸውን ሲነግሩኝ...በጣም ተገረምኩ፡፡ የኢስተርን ኢሊኖ ዩኒቨርስቲን ዲን ‹‹እነዚህ ወንድሞቼ ሙዚቀኞች ናቸው›› ስለው በየዓመቱ ፌብሪዋሪ ብላክ ሂስትሪ መንዝ (February black history month) የሚባል አለ፡፡ ያኔ ለተማሪዎች በጀት አለ ብሎ ነገረኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ለዩኒቨርስቲው ሾው እንዲያቀርቡ መሳሪያ ተከራይቼላቸው ነበር - ያን ጊዜ ነበር የወንድሞቼን ችሎታ ያየሁት፡፡

በህይወቴ ውስጥ ለለውጥ የተነሳሁበት ቀን ይሄ ነው፡፡ ምን ዓይነት ሙዚቃ ነበር ያቀረቡት? በአማርኛ፣ በአፍሪካ፣ በሬጌ ...ሙዚቃውን አቀረቡ፡፡ እነሱ በጣም ልምድ አላቸው፡፡ ሌለው ቀርቶ ጅቡቲ ከእስር ቤት ወጥተው ለትንሽ ጊዜ ቆይተው ነበር፤በዚያን ጊዜ ባንድ አቋቁመው ይጫወቱ ነበር፡፡ በጣም ጎበዞች ነበሩ፡፡ ሁሉን ነገር ትተህ ወደ ሙዚቃው አደላህ ማለት ነው? አዎ! ሙሉ በሙሉ ወንድሞቼ ቀየሩኝ፡፡ ሙዚቃ ህይወት ነው፡፡ ሙዚቃ ይለውጥሻል፡፡ እንደ አዲስ መፈጠር ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ልጅ ያደርጋል፡፡ ያን ደስ የሚል ስሜት ይዘን መከርን ከወንድሞቼ ጋር፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ መግዛት አለብን አልኳቸው፡፡ አሜሪካ ከተሰራ፣ ከተማሩ፤ ጊዜን በአግባቡ ከተጠቀሙ በጣም ጥሩ አገር ስለሆነ፤ ሰው ይኮናል፡፡ እኔ ደግሞ ቺካጎ ስኖር ዘመድ የለኝም፣ ራሴን የማስተዳድር ነኝ፣ ትጉህ ሰራተኛና መልካም ባህሪ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ወንድሞቼ የኔን ፈለግ ተከትለው በየሳምንቱ ከምንሰራው ደሞዛችን ላይ ገንዘብ አጠራቅመን መሳሪያ ገዛን፡፡ እኔ ደግሞ በክሬዲት ቫን አምጥቼ በራፋቸው ላይ አቆምኩላቸው፡፡ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡

አሜሪካን አገር...ገና በስድስት ወራቸው አዲስ መኪና..፡፡ ህልም ነው፤እኔ ግን እውን እንደሚሆን አሳየኋቸው፡፡ ዋሽንግተን ሄድን ለአበሻው የመጀመሪያ አንድ ትልቅ ሾው ስናሳይ ህዝቡ ደነገጠ፡፡ ከየት መጡ፤ እነዚህ የቺካጎ ልጆች ተባልን፡፡ ከዛ ካሊፎርኒያ ሄደን ሰራን፤ብዙ ገንዘብ፡፡ ያንን ለዓመት የትምህርት ቤት ክፍያ አዋልነው፡፡ በዓመቱ የቦብ ማርሊ ልደት ይከበራል፡፡

በዛ ላይ ለመሳተፍ በቀጥታ ደብዳቤ ፃፍን፡፡ አክቲቭ መሆን ነው የእኔ እህት (ሳቅ) ከዚያ ሪታ ማርሊ የአውሮፕላን ትኬት ከፍላ፤ ሆቴላችንን አመቻችታ፤ ወንድሞቼ መጡ ብላ በአጀብ ተቀበለችን፡፡ የመጀመሪያውን ሾው የቦብ ማርሊ ሙት ዓመትን በማስመልከት በተወለደበት ጃማይካ ሄደን አከበርን፡፡ ያ የነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ በስንት ዓመት ምህረት ማለት ነው? እ.ኤ..አ በ1991ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ እኔም ወንድሞቼ ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እመጣለሁ የሚለውን ነገር ተውኩት፡፡ ለምን? ወንድሞቼ እንዲህ ተሰደው ከሃገር ከወጡ ትልቅ ችግር አለ የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ በዚያ መንግስት ኢትዮጵያ ለመምጣት አልፈለግሁም፡፡ በጭራሽ፡፡ አንድ ወንድሜ ሞቷል፤ ሌሎች ወንድሞቼ ተሰደዋል፡፡ “ለምን ኢትዮጵያውያን ሆነን ተፈጠርን” የሚል አይነት አስተሳሰብ ይዘው ነው የመጡት፡፡ ከኢትዮጵያ መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን እስር ቤት በነበሩ ጊዜም ብዙ ተሰቃይተዋል፡፡ ይህንን ሳይ እዚሁ አሜሪካ መኖር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ዲግሪ አለኝ ተምሬያለሁ፤ሪታ ማርሊ ጥሩ ገንዘብ ሰጥታን ወደ ቺካጎ ተመለስን፡፡

እኔን ግን በጎን ታባብለኝ ነበር፡፡ እንዴት---ምን ብላ? ከእኔ ጋር ስራ፤ጥሩ ወንድማችን ትሆናለህ በማለት፡፡ መጀመሪያ ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም፤ በኋላ ግን ደስ አለኝ፡፡ አንድ እህት አገኘሁ፤ አፍሪካዊት ጃማይካዊት፣ ኢትዮጵያዊት..የሆነች እህት፡፡ እሷ ጋ ሄጄ መኖር ጀመርኩኝ፤ለአንድ ዓመት ያህል፡፡ አንድ ዓመት ስሰራ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ እዛ መኖሩ አልታየኝም.. በጣም ከፍተኛ ደረጃ የደረስከው ሙዚቃ አብረሃቸው በመስራት ነው? የጃማይካ ባህል እንደኛው አገር ነው፡፡ የቦብ ማርሊ ልጆች ሃይስኩል እስኪጨርሱ ድረስ ነፃነት አልነበራቸውም፡፡

በአንዳንድ ካረቢያን ደሴቶች፤ትምህርት ቤት ሲዘጋ ደግሞ አሜሪካ አብረን ሄደን ሾው እንሰራለን፡፡ በኋላ ዚጊ ሃይስኩል ጨረሰ፤ሪታ ማርሊ ልጆቿዋን - ስቲቭን፣ ዚጊን፣ ሸረንና፣ ስዴላን ለእኔ ለቀቀቻቸው፡፡ ዚጊ ማርሊ “ዘ ሜሎዲ ሜከርስ” ተብሎ ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር ዳሎል ባንዱ ሆኖ ስራ ተጀመረ፡፡በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ግራሚ ከእሱ ጋ አገኙ፡፡ በከፍተኛ የአልበም ሽያጭ ጎልድና ፕላቲኒየም ሪኮርድም አገኙ፡፡ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ አንድ የድሃ ልጅ ...እኛ ምንም አልነበረንም፡፡ ቤተሰቦቼም እኔም ምንም አልነበረንም፡፡ ..ወጥተን በአለም ላይ፡፡ በጣም ትልቅ እድል ነው፡፡.

በሙዚቃ ሥራችሁ የት የት ዞራችሁ? የት አልዞራችሁም ብትይ ነው የሚቀለው የእኔ እህት...አሜሪካን ከዳር እስከዳር..አውሮፓ የቀረን አገር የለም..ወንድሞቼ ዘለቀ፣ ሙሉጌታ፣ ሩፋኤል፣ ደረጀ መኮንን (አሁን በቅርብ ጊዜ ያረፈው) በጣም ድንቅ ጊዜ ነበረን፡፡ በጣም ወጣት ነበርኩ፤እንደ አሁኑ ምርኩዝ አልያዝኩም (ረጅም ሳቅ) ህልም እውን ሲሆን ታውቂያለሽ...ትንሽ እንደሰራን ዚጊ ግፊት በዛበት.. ግፊት----ምን ዓይነት? ጃማይካ ውስጥ ሙዚቀኛ ጠፍቶ ነው ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር የሚጫወተው የሚል.. አለማቀፍ ግፊት ነው..የቦብ ማርሊ ልጅ እንዴት ከኢትዮጵያኖች ጋር ..የሚል ዓይነት ነበር፡፡ ግፊት ሲበዛ እኔን አማከረኝና የጃማይካውያን ሙዚቀኞች ባንድ መቋቋም አለበት ተባለ...ዳሎል ወደ ቺካጎ ተመለሰ፡፡

አሁን ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? አሁንም እንጠያየቃለን..አሁንም ሪታ ማርሊ እህቴ፣ እናቴ፣ ጓደኛዬ ናት፡፡ ማኔጀርዋ ነኝ.. በጣም እንገናኛለን፡፡ በቀደም እዚህ መጥታ ነበር፤ የቦብ ማርሊ ሃውልት የተሰራ አለ፤ለሱ ጉዳይ ነበር የመጣችው---.ባለፈው ፌብሪዋሪ 6 ለማስመረቅ አስበን ነበር፤ጤንነትዋ ጥሩ ስላልሆነ ተመለሰች፡፡ ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ምን አገኘህ? መውደድን የተማርኩት ከእነሱ ነው፡፡ በጣም ጥልቅ ፍቅር ነው ያሳዩኝ፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ጃማይካዎች፡፡ ጃማይካ ውስጥ ---- ጌቶ ውስጥ ብትይ፣ አፕታውን ብትይ፣ የፈለኩበት ቦታ ብሄድ ---- ንጉስ ነኝ፡፡ በቅርቡ ሎሳንጀለስ ሄጄ፤ ከዚጊ ማርሊ ጋር ትንሽ ጊዜ አጥፍቼ ነው የመጣሁት፡፡ በጣም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለን፡፡ እማልቀይረው፡፡

ዳሎል ባንድ ከቦብ ማርሊ ልጅ ጋ ከተለያየ በኋላ እጣ ፈንታው ምን ሆነ? ይሰራል፡፡ ወንድሞቼ ዘለቀና ሙሉጌታ እየሰሩ ነው፤እንደውም እኮ እዚህ አገር ናቸው አሁን፡፡ ከዛ በኋላ ግን ኒውዮርክ መጥቼ ቢሮ ከፈትኩ፡፡ ለ19 ዓመት ኒውዮርክ ነበር ቢሮዬ፤ እመላለሳለሁ በሳምንት፣ በወር ... ጃማይካ፡፡ የማኔጅመንት ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ የኒውዮርክ እምብርት ላይ..ሆኜ ማኔጅ አደርግ ነበር - እነ ዚጊን፡፡ በዚህ መሃል የዛሬ 10 ዓመት ገደማ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ብቅ አለች፡፡ እስዋን ይዟት የመጣው ቶማስ ጎበና የተባለ ቤዝ ጊታር ተጫዋች ነበር፡፡ ከቤቴ ሁለት ብሎክ ላይ ሆኖ ስልክ ደወለልኝና- ‹‹አንድ ዘፋኝ ይዤልህ መጣሁ›› “የት ነው ይዘሃት የምትመጣው?” “ይህችን ልጁ አንተ ልታገኛት ይገባል..አለበለዚያ የትም አትደርስም...አንተ እንድታግዛት ነው” ብሎ ይዟት መጣ፡፡ ያኔ ጂጂን አላውቃትም ነበር፡፡ ጥሩ ድምፅ አላት፤ በጣም ጉጉ ናት፡፡ አወራኋት፡፡

ግቢዬ ውስጥ በጓሮ በኩል የሙዚቃ ቤት አለኝ..ገባንና ዝፈኝ አልኩዋት..ለቀቀችው፡፡ በጣም ተደነቅሁ፤ ደነገጥኩ፡፡ ማመን አልቻልኩም፤ ድፍረቷ፣ተሰጥዖዋ----በጣም ጎበዝ ልጅ! በዛን ወቅት የምትኖረው ሳንፍራንሲስኮ ነበር፡፡ ሳፍራንሲስኮ የሙዚቃ ከተማ አይደለም፤ ኒውዮርክ መምጣት አለብሽ አልኳት፡፡ ‹‹ብር የለኝም›› አለች፡፡ ‹‹ግዴለም እሱን ለእኔ ተይልኝ›› አልኳት፡፡ መጣች፤በጣም ጥሩ ቤት ተከራየንላት፡፡ ከትልቅ ኩባንያ ጋር አፈራረምኳት፡፡ አንዴም ድምጿን አልሰሙዋትም፤ በእኔ እምነት ነው የፈረሙት፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ አምጥቼ ሰጠኋት፤ አላመነችም፡፡ ጂጂን የማደንቃት ነገር ቢኖር ከዛ ገንዘብ ላይ ብዙውን ወደ ባህርዳር ቤተሰቦችዋ ጋ መላኳ ነው፡፡ በጣም ገረመችኝ፡፡ ገና ሳትደራጅ..ራስዋ በእግሯ ሳትቆም፡፡ በኋላ ቤላስዌልን አስተዋወቅኋት፡፡ ባለቤቷን ማለትህ ነው? ቤልን እንደ ጥላ ያመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ አገባችው፡፡ በቃ አደገች፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ቴዲ አፍሮ መጣ፡፡ እንደ ጂጂ ሁሉ የእርሱም በጣም የሚደንቅ ነበር፡፡ አላውቀውም፡፡ አንድ ዲጄ መንጌ የሚባል ልጅ አለ፡፡ “አንድ ጎበዝ ልጁ ተፈጥሯል አዲስ አበባ፤ እሱን ማኔጅ ማድረግ አለብህ” አለኝ.. “እኔ ጊዜ የለኝም” ብዬ አባረርኩት፡፡ የባለቤቴ ቅርብ ዘመድ ነው፡፡

እኔ ቱር ሄጄ ስመለስ ባለቤቴን በደንብ አድርጎ ሞልቷት፤እኔ ስመጣ የመጀመሪያ አጀንዳ ያደረገችው ቴዲ አፍሮ ነበር፡፡ በቃ እሽ አልኩ፡፡ እዚህ መጣሁና አገኘሁት፤ወደ ቺካጎ ይዤው ሄድኩኝ..ባንድ አዘጋጀሁለት..እኔ እዛ ክለብ ነበረኝ፤ ከዘለቀ ጋር ‹‹ዋንቴር›› የሚባል የታወቀ ክለብ ውስጥ ቀን ከሌት እንዲለማመዱ አደረግሁ --- ለአንድ ወር ተኩል፡፡ ሙዚቀኞች አያውቁትም ነበር፤እሱም አያውቃቸውም.. እኔም የዚህን ልጅ ስራ ብዙ አላውቅም፤ተገናኝተው ሲሰሩ ስሰማ በጣም ተደነቅሁ-----ሶስት ሙዚቃ ሰምቼ በአራተኛው ላይ ታክሲ ይዤ ለሌላ ስራ ወደ ኤርፖርት ሄድኩ፡፡ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሾው አቀረብን፤ታሪክ ነው የተሰራው፡፡ ከሌሎች አለማቀፍ ዘፋኞችስ ጋር--- ከሎረን ሂል ጋር ትንሽ ጊዜ ሰርቻለሁ፤“አርዝ ዊንድ ኤንድ ፋየር” ከሚባሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር ለትንሽ ጊዜ ሰራሁ...፡፡ እነሱን የማውቃቸው ቺካጎ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ተም ተም ዋሽንግተን›› የሚባል በጣም ከባድ አሬንጀር አለ፡፡ በአሜሪካ ምርጥና ድንቅ የሚባል፡፡ በሱ በኩል ነው የተዋወቅኋቸው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥህን እናውራ--- ኢትዮጵያ ከመጣሁ አምስት አመቴ ነው፡፡ ላይንስ ዴይ ሆቴል የሚባል አለኝ፡፡ ባለቤቴ ነች የምታስተዳድረው፡፡

በጣም ጎበዙ ልጅ ናት፡፡ ሶስና ሽፈራው ትባላለች፡፡ ሁለት ልጆች አሉን፡፡ ሌሎችንም ስራዎች በአገሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ የማዕድን ስራ፣ እርሻውን.. ከባለሞያዎች ጋር እየሰራን ነው፡፡ አዲስ የሙዚቃ ባንድም አቋቁመሃል ----- አዎ፡፡ ብዙ ልምድ አለኝ፡፡ ያለኝን ነገር ይዤ መሄድ አልፈልግም፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ እንደመጣሁ በሙዚቃው ንፍቀክበብ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ በየክለቡ፣ አንዳንድ ቦታዎች እየዞርኩ ሙዚቀኞችን አያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ምን ወሰንኩ---በቃ የሙዚቃ ባንድ መመስረት አለብኝ አልኩኝ፡፡ የራሳቸው ሳውንድ እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ...ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ እንደ አትሌቶች..ደራርቱ፣ ጥሩነሽ፣ሃይሌ የአገራችንን ህዝቦች እንደሚወክሉ ሁሉ በሙዚቃው ደግሞ ይህን ሃላፊነት መውሰድ አለብኝ በሚል‹‹ጃኖ ባንድ›› ተጠነሰሰ፡፡ ይሄንን ሳደርግ ደግሞ ኤርምያስ አመልጋ (አክሰስ ሪል ስቴት) ባለቤት ጓደኛዬ ነው፤ ሄጄ አማከርኩት፡፡ ከመቶ መቶ ሃምሳ ከጎንህ ነኝ አለኝ፡፡ ‹‹አብረን እናድርገው›› አለ፤ከእርሱ ጋር አብረን ጀመርን፡፡ እኔ ነኝ ልጆቹን የሰበሰብኳቸው - ስምንት ሴቶች፣ አስራ አምስት ወንዶች መረጥኩኝ፡፡

ከኒውዮርክ እንዲረዳኝ ብዬ ቤላስዌልን ጠራሁት፡፡ ሴቶቹን በሙሉ አባረራቸው (ሳቅ)፡፡ ወንዶቹንም ስምንት ልጆች ብቻ ይበቃናል አለ፡፡ ፈትናችኋቸው ነው? አዎ እንዲዘፍኑ አደረግን.. ከዛ ሁለት ሴቶች ሃሌ ሎያና ሄዋንን እኔ ጨመርኩኝ፡፡ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተመሰረተ፡፡ ‹‹ተተካኩ›› ብላችሁ አይደል (ሳቅ) ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ...ትልቅ ነገር ነው የምንሰራው---- የኢትዮጵያን ስም የሚያስነሳ፡፡ ዲሲፕሊን ካላቸው ልጆች ጋር እየሰራሁ ነው፡፡ ቪዥነሪስ ናቸው፡፡ የምፈልገውን ራዕዬን (ቪዢኔን) የሚያሟላልኝ ቡድን ተፈጠረ፡፡ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ ቢላስዌል እንደ ፕሮዲዩሰር ነው የመጣው፡፡ እሱ ደግሞ አራት ኢንጂነሮች ይዞ መጣ፡፡ ስራችን ሁሉ በዓለም የሙዚቃ ደረጃ የሚሰራ ነው፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› የሚል ስያሜ የሠጠነውን የመጀመሪያ አልበማችንን እኔ ሪኮርድ አድርጌ ይዘን ሄድን፤ አሜሪካን አገር፡፡ እዚያ ተሰርቶ ተላከልን፡፡ እኛ ደግሞ ሲዲውን እዚህ ለቀናል፡፡

ሁለት ዓመታችን ነው፤ አንዳንድ ሾዎችን መስራት ጀምረናል፡፡ ዛሬ በ‹‹ላፍቶ ሞል›› ኮንሰርት አለን፡፡ ከዛ በኋላ አራት የኢትዮጵያ ዋና ከተማዎች ውስጥ ሰርተን ለፋሲካ ወደ አሜሪካ እንሄዳለን፡፡ ሮክ በእኛ አገር አልተለመደም---- እንደውም የሰው አቀባበል በጣም ነው ያስደነቀኝ፡፡ ከማምነው በላይ ነው የሆነብኝ..በየመኪናው፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ፣ በየክለቡ ዘፈኑ ሲለቀቅ እሰማለሁ...ከክፍለ ሃገር መልክት ይደርሰኛል፡፡ በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚመጣውን አስተያየት አያለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ነው ይህ የመጣው፡፡ የምሰራውን ነገር የሀገሬ ህዝብ ሲያደንቅልኝ አስቢ--- ምን ሊሰማኝ እንደሚችል፡፡ ትልቅ ደስታን የሚያጎናፅፍ ነገር ነው፡፡ ‹‹ጃኖ›› የሚለው የባንዱ ስያሜ እንዴት ወጣ?. በዲሞክራሲ አምናለሁ፡፡ የኖርኩበት የአሜሪካ ማህበረሰብ ያስተማረኝ ነው...በዚህ ሁኔታ ልጆቹ ስም ለማውጣት በጣም የተለያዩ አማራጮችን አቅርበው ነበር፡፡ ለሁለት ሳምንት ተከራክረንበታል፤ግን በተደጋጋሚ ይህ ስያሜ ስላሸነፈ በጃኖ ተሰየመ፡፡ ጃኖ ባንድ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ እንደ ቦብ ማርሊ.. ከሳውዝ አሜሪካ እንደወጡ የተለያዩ ሙዚቀኞች ይህችን የምንወዳትን ሃገራችንን በሰፊው ለማስተዋወቅ አልመናል፡፡ መድረሻችንን አውቀዋለሁ፡፡ ይህም በቅርብ ይሆናል፡፡

  •  “ጃኖ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው” ኪሩቤል ተስፋዬ የጃኖ ባንድ ኪቦርድ ተጫዎችና የቡድን መሪ ሲሆን ለ12 ዓመት በተለያዩ ባንዶች ውስጥ እንደሰራ ይናገራል፡፡ የ28 ዓመቱ ኪሩቤል በባንዱ ውስጥ ካሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች በዕድሜ ትልቁ ነው፡፡ ስለጃኖ ባንድ ስያሜ ንገረኝ--- ከሙዚቃችን ተነስተን ነው፡፡ ሙዚቃችን ከግማሽ በላይ አማርኛ ነው፡፡ አገርኛ ነው፤ ባህላዊ፡፡ ያንን የሚያንፀባርቅ፣ሙዚቃችንን የሚገልፅ፣ ሰዎች ሲሰሙት ለጀሮ የሚቀል በሚል ነው--- ብዙ ስሞች መጥተው መጨረሻ ላይ ‹‹ጃኖ›› ላይ ፀናን፡፡ ጃኖ በራሱ የአገር ልብስ ጥለት ነው፤ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው፤ያምርብናል፤ ደመቅ ያለ ያማረ..በባህልና በስርዓት ለየት ላለ በዓል የሚደረግ ነው...የክብር ልብስ! ሁልጊዜ የሚደረግ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን በጣም ይገልፅልናል፡፡ እኛም እያደረግን ያለነው የአገራችንን ሙዚቃ ሌላው የዓለም ክፍል በሚረዳው መልኩ ለማቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሙዚቃ እንዳላት ከዚህ በፊት ከተሰራው በተሻለ አቅም ለማስተዋወቅ ስለሆነ ጃኖ ባንድ ይገልፀዋል፡፡ የአልበማችሁን ስም ደግሞ “ኤርታሌ” ብላችሁታል---- ኤርታሌ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ የሚገኝ ድንቅ ነገር ነው፡፡ እኛም የመጀመሪያ ኮንሰርታችንን ስንሰራ አዲስ የታመቀ ሃይል ፈንድቶ ሲወጣ፤ ሃይላችንን አቅማችንን አሳየን፡፡ ጊዜያችንን ሰጥተን የለፋንበት ስራ ነው፡፡ እሳተ ጎሞራም እንዲሁ ነው፤ ካልታሰበ ቦታ ገንፍሎ የሚወጣው አንፀባራቂ የሆነ ነገር----- እሳተ ጎሞራውም ወደ አለትነት ይቀየራል፡፡ ያ ደግሞ ያለን አቅምና ሃይል ነው የሚገልፀው፡፡ የመጀመሪያ አልበማችን ይህን ይገልፀዋል፡፡ አልበሙ ውስጥ ስለሃገር፣ ስለፍቅር፣ ስለማንነት፣ተዘፍኗል፡፡ አልበሙንና እኛን የሚገልፅ ስም ይሆናል በሚል ነው ‹‹ኤርታሌ›› ያልነው፡፡ ሙዚቃ እንጂ ድምፃዊያን የላቸውም፣ ለዜማና ለግጥም አይጨነቁም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል----- እንደዚህ ዓይነት አስተያየት አለ፤ ከብዙ አቅጣጫ፡፡ አዲስ ነገር እኛ አገር ይዘሽ ስትመጪ፤ ቶሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ እኛም ፈርተነው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ እያስለመድነው ወደ ምንፈልገው ደረጃ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ደረጃ እነሱ በሚያውቁት መልኩ ለማቅረብ፣አገር ውስጥ ላለው ደግሞ ከተለመደው ከሚሰማው የተለየ ብንሰጠው ይወደዋል ብለን ነው የሰራነው፡፡ ተቀባይነቱ ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ ከአልበሙ ውስጥ ሶስትና አራት ሙዚቃዎች ሃይል ኖሯቸው መደመጥ ችለዋል፡፡ በየዘመኑ የተለያየ ሳውንድና ሙዚቃ ይመጣል፡፡ ለውጥ ይኖራል፡፡ የመጀመሪያውን የእኛን አገር ብትወስጂ ኦርኬስትራ ባንድ ነበረ፣ ዘመናዊ ሙዚቃ መጣበት፣ ከዚያ ወደ ዲጂታል እያለ ወደዚህ መጣ፡፡ በመጀመሪያው አልበማችን ሰውን ሁሉ እንቆጣጠራለን ብለን አናስብም፡፡ ቀስ በቀስ ግን እንመጣለን፡፡ በዛሬው ኮንሰርት ምን የተለየ ነገር ታቀርባላችሁ? ብዙ አዲስ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ወደ አምስት ኮንሰርቶች ሰርተናል፡፡ ትንንሽ ኮንሰርቶችን፡፡ በዛ ጊዜ ውስጥ የሰራናቸው ሙዚቃዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ አዳዲሶች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ይኼ ላያዝናና ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው የሚያውቀውን ሙዚቃ ስትጫወችለት ነው ደስ የሚለው፡፡ ሰው የማያውቃቸውን አዳዲስ ዘፈኖች አንጫወትም ብለናል፡፡ የድሮ ክላሲክ የሆኑ ሙዚቃዎችን እንጫወታለን፤የሃገራችንን ዘፈኖች፡፡ አሁን ወጣቱ የሚሰማቸውን አዳዲስ የውጪ ዘፈኖች፤ በየክለቡ የሚዝናናባቸውንም እናቀርባለን፡፡ አራት ድምፃዊያን አሉ፤ እየተፈራረቁ ያዝናናሉ፡፡ አልበሙ ላይ ያሉትንም እንጫወታለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሰላሳ ዘፈኖች ይቀርባሉ፡፡ ከምሽቱ 2፡00 ሠዓት ሲሆን በዲጄ ሲያዝናኑ ይቆይና ከ4፡00 ጀምሮ ጃኖ ባንድ በድንቅ ስራዎቹ ብቅ ይላል፡፡ ልዩ ቀን ነው፡፡ 
  •  “ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት እንፈልጋለን ሚካኤል ሃይሉ የጃኖ ባንድ ሚዩዚካል ዳይሬክተርና ሊዲ ጊታሪስት ነው፡፡ በጊታሪስትነት ከተለያዩ ባንዶች ጋር የተጫወተው ሚካኤል፤ በራሱ ስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ ያቀናብራል፡፡ እስካሁን የሚካኤል በላይነህ፣የቴዲ አፍሮ፣የአቤል ሙሉጌታና የዘሪቱ ከበደን አልበም አቀናብሯል፡፡ አንድ ህልም ነበረኝ፡፡ ወደፊት ቢሆንልኝ ብዬ የማስበው፡፡ የዚህ ባንድ ባለቤት አዲስ ገሠሠ ትግል ላይ ነበር፡፡ ልጆች ሰባስቦ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በውጭው ዓለም እንዲታወቅ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሰዓት እኔ ጋ ደውሎ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ፤ ምን ትላለህ?›› ሲለኝ ሃሳቡና ሃሳቤ ተገጣጠሙ፡፡ ህልሜን እውን ለማድረግ ጃኖን ተቀላቀልኩ፡፡ የዚህችን አሪፍ አገር ባህሏን፣ ህዝቦቿን የውጭው አለም እንዲያውቋት-----ስለዚህች አገር የተለያየ አመለካከት ነው ያለው፤ ..ብዙ ጊዜ በመጥፎ ነው የምትነሳው... ያለን ነገር ብዙም አይታወቅም፤ ለአለም በሚገባ በሙዚቃ ቋንቋ ያለንን ለማስተዋወቅ ነው ሃሳባችን፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ያላት ሀገር ናት፡፡ አለም ያላየውን ብዙ ጉድ የሚያሰኝ ሙዚቃ ለዓለም ለማሳየት ነው ዓላማችን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከሮክ የሙዚቃ ሥልት ጋር ቀላቅለን ማስተዋወቅ ነው የምንፈልገው፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ሙዚቃ በደንብ በሃላፊነት ደረጃ ተጠንቶ የተሰራበት ጊዜ የለም፡፡ ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት ነው የተነሳነው፡፡   ወጣት ሃሌሎያ ተክለፃዲቅ የባንዱ ድምፃዊት ናት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ስራ ኮሌጅ አካውንቲንግ ምሩቅ ናት፡፡ በ
  • ‹‹ኮንሰርታችንን ተጋበዙ፤ትደነቃላችሁ››‹‹ኤርታሌ አልበም›› ውስጥ አጃቢ ድምፃዊት ናት፡፡ ወደ ሙዚቃ የገባሁት ት/ቤት እያለሁ ነው - ካቴድራል ት/ቤት፡፡ ካርኒቫሎችና ፌስቲቫሎች ላይ እዘፍን ነበር፡፡ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎችን ነበር የምዘፍነው፡፡ ከአኩስቲኮች ጋር እጫወት ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነው ከአዲስ ጋር የተዋወቅሁት፡፡ አላመንኩትም ነበር፤ በጣም ትልቅ ነገር ስለሆነ፡፡ እኔንና ሄዋንን ቤላስዌል መጥቶ አየን፤ጥሩ ነው ብሎ ቀጠልን፡፡ ጥሩ ባንሆን ያስወጣን ነበር፡፡ ከጃኖ ባንድ ጋር ብዙ ኮንሰርቶችን እየሰራን ነው፤ በጣም ደስ የሚል ስብስብ ነው፡፡ አስራችንም እንደ አንድ ሰው ነው የምንጠራው፤ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተብለን፡፡ ለሃገራችን አልመን እየሰራን ስለሆነ ተመልካቾች የዛሬን የላፍቶ ሞል ኮንሰርታችንን ተጋበዙ እዩን፤ትደነቃላችሁ...

ባለፈው እሁድ በዓለ ሲመታቸውን አከናውነው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ አራት ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ተበረከተላቸው፡፡ ለፖርቱጋል መንግስት ይሰራ በነበረው ስፔናዊ ፔድሮ ፓያሽ በ1622 ዓ.ም በፖርቱጋልኛ ታትሞ በቅርቡ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን የግእዝ አንቀፆች ያሉት መጽሐፍ፤ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን ተገኝተው ለፓትርያርኩ በስጦታነት ያበረከቱት በኢትዮጵያ የፖርቱጋል አምባሳደር አንቶኒዮ ሉዊስ ኮትራም ናቸው፡፡

በሁለት ጥራዝ የተካተተውን የታሪክ መጽሐፍ ከፖርቱጋልኛ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም ስምንት አመታት የፈጀ ሲሆን በለንደን የታተመው መጽሐፍ ዋጋ 100 ፓውንድ ነው፡፡ መጽሐፉ ወደ እንግሊዝኛ ሲመለስ የፖርቱጋል ኤምባሲ የባህል አታሼና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖርቱጋሊኛ አስተማሪዎች ዶር. ኢዛቤል ቦቫዲያ፣ ማኑኤል ዣዎ ራሞስ እና ሄርቭ ፔናክ የአርትኦት ሥራውን ሠርተዋል፡፡ በሁለት ጥራዝ 900 ገፅ ያለው መጽሐፍ የወቅቱን የኢትዮጵያ አስተዳደር፣ ሃይማኖት፣ አለባበስ፣ እንስሳት … የያዘ ኢትዮግራፊክ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ ፔድሮ ፓየዝ በአፄ ሱሱንዮስ እና አፄ ፋሲል ዘመነ መንግስት የመጣ የካቶሊክ ሐይማኖት ቄስ ነው፡፡

ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዛሬ ሁለት የሕፃናት መፃሕፍት እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡ ዛሬ በጣይቱ ሆቴል የሚመረቁትን መፃሕፍት ነዋሪነቱን በሩስያ ይኖር የነበረው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ነው፡፡ ሁለቱ መፃሕፍት ሲመረቁ የደራሲው ልደትም እንደሚታሰብ ዩኒቨርሲቲው ገልጿል፡፡ እያንዳንዳቸው አርባ ገጽ የሆኑት የሕፃናት የተረት መጻሕፍት “The Giant pineapple” እና “Muna’s Monkey” ሲሆኑ የመፃሕፍቱ ሥዕሎች በጃፓናዊት አርቲስት እንደተሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሁለቱም መፃህፍት ዋጋ 33 ብር ነው፡፡ ደራሲው በሕፃናት ላይ ያተኮሩ አስራ አምስት መፃሕፍትን ጽፏል፡፡ በሌላም በኩል “የአህዛብ ጣዖታት” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ነገ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር አስታወቀ፡፡ በአቶ ዳንኤል መንገሻ የተገጠሙ ግጥሞችን የያዘው መጽሐፍ የሚመረቀው በሀገር ፍቅር ትያትር ትንሿ አዳራሽ ነው፡፡

.ወጣት እና አንጋፋ ገጣሚያን ሥራዎቻቸውን በሙዚቃ እያጀቡ የሚያቀርቡበት የግጥም በጃዝ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ነቢይ መኮንን፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ጌትነት እንየው፣ ወሠንሰገድ ገብረኪዳን እና ምህረት ከበደ ግጥሞቻቸውን በአዲስ ጣእም ባንድ ሙዚቃዎች ታጅበው ያቀርባሉ፡፡ የዝግጅቱ መግቢያ በነፍስ ወከፍ 50 ብር ነው፡፡