Administrator

Administrator

በላዕላይ ፀለምቲ ወረዳ፣ ሰዎች  ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ምክንያት እየሞቱ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። በዚሁ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ሳቢያ  ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሕጻናት ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል።
በወረዳው “ደገርባይ” በተባለ የገጠር ቀበሌ፣ ከሁለት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ አምስት ሕጻናት፤ “ምጫራ” እና “ዲማ” በተባሉ ቀበሌያት ደግሞ ሁለት ሕጻናት ለሞት መዳረጋቸውን ቢሮው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። በዚሁ መግለጫ እንዳብራራው፤ ሕጻናቱ የሞቱት ከመስከረም 1 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች ማረጋገጡን ጠቁሟል።
ታማሚዎች ከሚያሳዩዋቸው ምልክቶች መካከል ትውከት፣ መዝለፍለፍና የሆድ ማበጥ መሆናቸውን የጠቀሰው የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ወረዳው ከጊዜያዊ ክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ውጪ በመሆኑ በቦታው ተገኝቶ በሽታውን ለመፈተሽ፣ ብሎም አስፈላጊውን የሕክምና እገዛ ለማድረግ ሁኔታዎች አልፈቀዱም ብሏል።
“አሁን የሚስተዋለውን አደገኛ ሁኔታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሊያውቁት ይገባል። አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉም እየሰራን ነው” ብሏል፣ የክልሉ ጤና ቢሮ።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ እንዲሁም ከሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች ጋር በመሆን የሕክምና ድጋፍ ለማድረስ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክቷል።
ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ዓዲያቦ ወረዳ፣ የኮሌራ በሽታ በወረርሽኝ መልኩ ተስፋፍቶ በርካቶችን ማጥቃቱን መዘገባችን አይዘነጋም።



የኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ለአልሸባብና ተመሳሳይ ሽብርተኛ ቡድኖች መጠናከር ዕድል ፈጥሯል ተባለ፡፡ በሰሜናዊ ሶማሊያ የእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ታጣቂዎች ቁጥር  በእጥፍ መጨመሩን በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) አስታወቋል፡፡
በስፍራው የአይኤስ ታጣቂዎች ቁጥር በሁለት ዕጥፍ ማደጉን የተናገሩት የዕዙ ዋና አዛዥ ማይክል ላንግሊ፤ ቡድኑ በአካባቢው አዳዲስ ታጣቂዎችን እየመለመለ ከመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ አገራት የሚገኙ አባላቱን በስፍራው እያከማቸ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አዛዡ ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በአሁኑ ወቅት በስፍራው የሚገኙ የአይኤስ ታጣቂዎች ቁጥር፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው በሁለት እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት በሰሜን ሶማሊያ እስከ 6 መቶ የሚደርሱ የቡድኑ አባላት እየተንቀሳቀሱ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፤ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር የሽብር መከላከል ስራውን እንዳዳከመው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የአፍሪኮም ዋና አዛዥ ማይክል ላንግሊ የአልሸባብ ወታደራዊ አቅም በሰው ሃይልና ጦር መሳሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ  ተናግረዋል፡፡ ከ12 እስከ 13 ሺ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚነገርለት አልሸባብ፤በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ዋና አዛዡ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ክፍተት የሽብር መከላከል ስራውን እንደጎዳው ገልጸው፣ አገራቱ በጋራ በሰሩበት ወቅት የቡድኑን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማዳከም ችለው እንደነበረ አውስተዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል መንግስት በከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ ተሸንፎ በርካታ ቦታዎችን ለቆ የነበረው አልሸባብ፣ ማዕከላዊ ሶማሊያን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች በመንግስት ጦር የተወሰዱበትን ስፍራዎች በድጋሚ እየተቆጣጠረ ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው የሚገኘው የሽብር እንቅስቃሴ ማደግ ለቀጣናው አገራት፣ ለዓለምአቀፍ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እክል ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

በቅርቡ የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመው የነበሩት ዶ/ር እመቤት መለሰ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም  በፃፈው  ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው፤ ዶ/ር እመቤት መለሰ  ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ  ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።

ዶ/ር እመቤት፣ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸውም በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስትራቴጂ ፕላኒንግና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡

የፖሊሲ ባንኩን ላለፉት 4 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ዮሐንስ አያለዉ  በግል ምክንያት ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ካስታወቁ በኋላ፣ የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነዉ በቅርቡ መሾማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለአምስት ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መስጠቱን በዛሬው ዕለት አስታወቀ፡፡

 ብሔራዊ ባንክ፣ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ከባንክ ጋር ዝምድና ለሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሠረት፣ አምስት ድርጅቶች ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ የሥራ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ተመልክቷል፡፡  እነዚህ ድርጅቶችም፡- ዱግዳ ፊደሊቲ ኢንቨስትመንት ኃ.የተ.የግ.ማ፣ ኢትዮ ኢንዲፕንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ግሎባል ኢንዲፐንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ሮበስት ኢንዲፐንደንት ፎረን ኤክስቼንጅ ቢሮ እና  ዮጋ ፎሬክስ ቢሮ  መሆናቸውን ባንኩ ገልጿል፡፡


የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ የሚፈጸም (spot transaction) ብቻ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም፣ ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺ የአሜሪካን ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፣ የደህንነት፣ ሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ያዘጋጀውን “ኑ፣ እንመካከር” የተሰኘ  አዲስ የሙዚቃ ክሊፕ ትናንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።

ይዘቱን በአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ባደረገው በዚህ የሙዚቃ ክሊፕ ላይ በርካታ ባለሞያዎች እንደተሳተፉ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

 የሙዚቃውን ቅንብር ካሙዙ ካሳ እንደሰራው የገለጸው አርቲስቱ፤ በሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሞያዎችና ዕገዛ ላደረጉ ወገኖች ምስጋናውን አቅርቧል።

“የመገናኛ ብዙኃን ዘፈኑን በተደጋጋሚ ሊያጫውቱት ይገባል” በማለት በአጽንዖት የተናገረው አርቲስት ዘለቀ፣ ወደፊት ሙዚቃው በተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅ አስረድቷል።

በሌላ በኩል፣ የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማሕበር፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን እንዳስረከበም ተሰምቷል፡፡

-አምነስቲ ኢንተርናሽናል-

በአማራ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ በጅምላ መታገታቸውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

አምነስቲ ትላንት ማክሰኞ  መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤”ይህ የዘፈቀደ የጅምላ እገታ፣ የህግ የበላይነት መሸርሸርን የሚያባብስ ነው፡፡” ብሏል፡፡

ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ. ም. ጀምሮ በአማራ ክልል፣ ምሁራንና ሲቪል ሠራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ተይዘው መታገታቸውን ሪፖርቶች እንደደረሱት ተቋሙ  ገልጿል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃላፊ ቲጌሬ ቻጉታ፤ “የኢትዮጵያ ወታደሮችና ፖሊሶች በአማራ ክልል የከፈቱት የዘፈቀደ እገታ ዘመቻ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱን ያሳያል” ብለዋል፤ በመግለጫው፡፡

 “የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሰዎቹን ከመያዛቸው አስቀድሞ የእስር ማዘዣም ይሁን ፍተሻ ለማድረግ ፈቃድ አላሳዩም” ያሉት ቲጌሬ ቻጉታ፤ “የታገቱት ሰዎችም በህጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አልቀረቡም” ብለዋል።

የዓይን እማኞች ለአምነስቲ እንደጠቆሙት፤ በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ምሁራን በጅምላ ከታገቱት መካከል ይገኙበታል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የዘፈቀደ የጅምላ እገታ በአፋጣኝ ማቆም አለበት። በታገቱት ሰዎች ላይ ሕግን ተከትሎ ክስ መመሥረትና የሕግ ሥርዓትን መከተል ይገባዋል። አሊያም ሰዎቹን መልቀቅ አለበት። መንግሥት የዘፈቀደ እገታን ለጭቆና ማዋልን ማቆም አለበት” ሲሉም ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ማስፈራሪያ፣ ተከታታይ ጥቃትና ወከባ  ማድረጉን ያስታወሰው አምነስቲ፤በዚህም ምክንያት ብዙዎች እየተሰደዱ ነው፤ ብሏል።

ብላክ ዳይመንድ የህትመትና ማስታወቂያ ማሰልጠኛ አካዳሚ፣ ከወረቀት ህትመት ውጪ በሃገራችን የመጀመሪያውን የህትመትና ማስታወቂያ ሥልጠና በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የብላይክ ዳይመንድ አድቨርታይዚንግ መሥራቾችና አመራሮች በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ 22 ማዞሪያ ወርቁ ህንጻ ገባ ብሎ በሚገኘው የልህቀት ማዕከል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የሥልጠና አካዳሚው ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፤ ከነገ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሰልጣኞች ምዝገባ የሚጀመር ሲሆን፤ አካዳሚው የተለያዩ አጫጭር የቀንና የማታ የሥልጠና መርሃግብሮችን በመስጠት ሥልጠናውን ይጀምራል ተብሏል፡፡
ብላክ ዳይመንድ የህትመትና ማስታወቂያ ማሰልጠኛ አካዳሚ ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል፡- የባነር፣ ስቲከር ህትመት ማሽነሪ ባለሙያነት፣ ሲኤንሲ መቁረጫ ማሽነሪ ባለሙያነት፣ የህትመትና ግራፊክስ ዲዛይን ሥራዎች፣ የላይት ቦክስ ማስታወቂያ ባለሙያነት፣ የኒዮን ላይት ማስታወቂያ ባለሙያነትና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡
ተቋሙ በማስታወቂያ፣ በህትመት ማሽንና ግራፊክስ የሚታየውን የሰለጠነ ባለሙያ ክፍተት ለመሙላት ከነገ ጀምሮ ሰልጣኞችን መመዝገብ እንደሚጀምር ነው ያስታወቀው፡፡
ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ ሥልጠናዎቹ እስከ ሦስት ወር የሚደርሱ በሰርተፊኬት ደረጃ የሚሰጡ አጫጭር ኮርሶች ናቸው፡፡
በባለራዕይ ወጣቶች የተቋቋመው ብላክ ዳይመንድ አድቨርታይዚንግ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ የህትመትና ማስታወቂያ ሥራዎችን በጥራትና በብቃት በመሥራት በደንበኞቹ ዘንድ ስምና ዝናን ያተረፈ ሲሆን፤ ሥራውንም በተለያዩ ዘርፎች አስፋፍቶ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

በብልሽቱ ምክንያት ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተጠቁሟል

ከድሬዳዋ መገንጠያ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው 200 ኪሎሜትር መንገድ ብልሽት “ገጥሞታል” ተብሏል። በዚህም ሳቢያ ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ከድሬዳዋ መገንጠያ ቢኬን እስከ ጂቡቲ ወደብ መግቢያ ድረስ ለብልሽት ከተዳረገ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆነ አመልክተዋል። አክለውም፣ በዚሁ መስመር ላይ እየተሰሩ ያሉ መንገዶች ቢኖሩም ለአገልግሎት ክፍት አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“በዚህ የተነሳ እየሄድን ያለነው በተለዋጭ መንገድ ነው።” ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ ተሽከርካሪዎቹ የሚጓዙት በጋላፊ መስመር መሆኑን ገልጸዋል። “ይሁንና ይህ መንገድ የመኪና መለዋወጫን የሚያበላሽ፣ ጊዜን የሚወስድ እና ተሽከርካሪዎች እንዲወድቁ የሚዳርግ ነው” ብለዋል።

ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው የጉዞ ፈቃድ በጋላፊ መስመር በኩል በመሆኑ፣ አሽከርካሪዎቹ በደወሌ መስመር በኩል ያለፈቃድ በማሽከርከራቸው ምክንያት ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ መቀጮ እንደሚከፍሉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ነገር ግን በጋላፊ መስመር ከማሽከርከር ይልቅ መቀጮ እየከፈሉም ቢሆን ሾፌሮች በጋላፊ በኩል ማሽከርከሩን “ይመርጣሉ” በማለት የሚያስረዱት አቶ ብርሃኔ፣ “ምክንያቱም አንድ መኪና በዚያ መስመር ላይ ከወደቀ ወዲያው ከመንገድ እንዲነሳ አይደረግም። እንዲያውም ተጨማሪ መኪናዎች እስኪወድቁ ድረስ ነው የሚጠበቀው። የጂቡቲ የዕቃ ማንሻ ማሽን (ክሬን) እስኪመጣ ድረስ ይጠበቃል። ምክንያቱም የኛ ክሬን እንዲገባ አይፈቀድም። በተደጋጋሚ የራሳችንን ክሬን ለማስገባት ብዙ ጊዜ ጠይቀናል። ምላሽ ግን አልተሰጠንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ለክሬን እና ሌሎች ወጪዎች ከ400 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ድረስ ክፍያ እንደሚጠየቅ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ ክሬኖቹ አሮጌ ከመሆናቸው የተነሳ ለብልሽት ከተዳረጉ እንደገና ተጠግነው እስከሚመጡ ድረስ አንድ ወር እንደሚፈጅ ነው አቶ ብርሃኔ የሚያነሱት።

እንዲሁም በመንገዱ ብልሽት ምክንያት ሾፌሮች ለኩላሊት እና ሌሎች መሰል በሽታዎች እየተጋለጡ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ብርሃኔ፣ “ችግሩ ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የከባድ መኪና ሾፌሮች የስራ ዘርፋቸውን እየቀየሩ ወደ ራይድ ታክሲ አሽከርካሪነት ፊታቸውን እያዞሩ ነው” በማለት አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመንገዱ ብልሽት በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው የገለጹ ሲሆን፣ መንገዱ የአገሪቱ የገቢ እና ወጪ በር መሆኑን አውስተው፣ “ከተሽከርካሪ ጥገና እና ከሌሎች ወጪዎች ጋር በተያያዘ እንደአገር ዋጋ እያስከፈለን ነው። ‘ወይ መንግስት ያድሰው፣ ወይም እኛ ገንዘብ አዋጥተን እንዲታደስ እናድርገው’ እያልን ነው። እኛ ማሳሰብ የምንፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳዩን በጥልቀት እንዲያጤኑት ነው።” ብለዋል።

አቶ ብርሃኔ አያይዘውም፣ በፀጥታ ችግር ሳቢያ ሾፌሮች ለዕገታ፣ በክልሎች አለአግባብ ለሚጠየቅ ክፍያ፣ ለመንገድ መዘጋትና ሌሎችም ችግሮች ከፍተኛ አደጋ እንደሚዳረጉ አመልክተው፣ እርሳቸው የሚመሩት ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ድንጋጌዎች መሰረት ሰላማዊ ኢንዱስትሪ መስፈኑን ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን በማስታወስ፣ የአሰሪው መብት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

Saturday, 28 September 2024 20:24

አጥንቱ

ሼኽ ወይም ኡስታዝ የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ለብዙ ዓመታ ዓሊሞች አሉ በተባሉበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ ቀርተዋል፡፡ የሃይማኖት አዋቂ ለመሆን ብዙ ኪታቦችን አገላብጠዋል፡፡ አሁን በተራቸው የቃረሙትን ሁሉ ለሌሎች ለማካፈል ሲሉ ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ምላሳቸው የተባረከ ነው፡፡ የሃይማኖት ዕውቀትን ማሳወቅንና ተናግረው ማሳመንን ተከነውበታል፡፡
ተማሪዎቻቸው አፋቸውን ከፍተው ነው የሚያዳምጧቸው፡፡ “የኔ አንድም አስተዋፅኦ ወይም ታላቅ ጥረት ሳይታከልበት እንዲሁ እንደዘበት ይህን ተሰጥኦ ለሰጠኝ አላህ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲሉ ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ሚስታቸውን እንኳን ለሌላ ነገር የሚመኝ ቀርቶ መልኳንና ቁመናዋን የሚያውቅ የለም፡፡ ይህን የሚያውቁት እናትና አባትዋ፣ እህትና ወንድሞችዋ እና እስከ አጎትና አክስት ድረስ ያሉ ዘመዶችዋ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች መልኳንም ሆነ ቁመናዋን ለማወቅና ለማድነቅ አልታደሉም፡፡ ምክንያቱም በሰፊ ጥቁር አባያና ከላይ በምትደርበው ትልቅና ሰፊ ጅልባብ ሰውነትዋ ተሸፍኗል፡፡ መላው ፊትዋና ከአንገት በላይ ያለው የሰውነት ክፍልዋ በኒቃብ ኃይል ከሰው ዓይን ተጋርዷል፡፡
ይወድዋታል፡፡ የእሳቸው ብቻ ስለሆነች ደግሞ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ይኮሩባታል፡፡
ሼኽ ወይም ኡስታዝ ኡስማን ቀይ ናቸው፡፡ ፂማቸው የተንዥረገገ ነው፡፡ ይህ የሆነው ፂም ማሳደግ ሱና ስለሆነ ነው፡፡ አናታቸው ላይ ጥምጣም እንደጠመጠሙና ከላዩ ላይ ነጭ ኩፊያ እንዳጠለቁ ነው የሚውሉት፡፡ ዘውትር ሽክ የሚሉ ሰው ናቸው፡፡
“ምን ነው?” ቢሏቸው “ንጽህና የኢማን ግማሽ ነው ብለዋል ነቢያችን (ሲ.ሠ.ወ)” ይላሉ፤ ድብዳብ የመሰለውን ወፍራም ከንፈራቸውን ከጥርስ ግርዶሽነት አላቀው ፍንጭት ጥርሳቸውን እያሳዩ፡፡
ፈገግ ሲሉ ነጫጭ ጥርሶቻቸው መሀል ተሸንቁሮ ጠባብ መንገድ የመሰለው ፍንጭታቸው ለእይታ ይጋለጣል፡፡
ከልብስ ጀለቢያና ቶብ ያዘወትራሉ፡፡ በቅጥነታቸው ምክንያት እዛ ሰፊ “ድንኳን” ውስጥ ኢምንት መስለው ይታያሉ፡፡ ጥምጣም፣ ነጭ ኮፍያና፣ ነጭ ጀለብያ ወይም ቶብ መለያ ምልክቶቻቸው ናቸው፡፡ ጀለብያ ወይም ቶብ ሆነ ወይም ሱሪያቸው ከቁርጭምጭሚታቸው በላይ የሚቀሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህም ሱና ነው፡፡
“ደረሳዎቼ ስሙ!” አሉ ከስራቸው የተኮለኮሉትን ወጣች አፈራርቀው እየተመለከቱ፡፡
“ምን ጊዜም ቢሆን ነብሳችሁን ማሸነፍ አለባችሁ፡፡ ለምን? ብትሉ ነብሲያ ቆሻሻ ነች፤ የማይሆን ቦታ ላይ ትጥላለች፡፡ የማይበጅ ጉድጓድ ውስጥ ሰውን ትከታለች፡፡”
በእስልምና ሃይማኖት “ነብሲያህን አሸንፍ” የሚል አስተምህሮ አለ፡፡ ኡስታዝ ኡስማን እያስተማሩ ያሉት ይህንን ነው፡፡
“የግል ፍላጎታችንን ለሌሎች ሰዎች ስኬትና ለወል ጥቅም ስንል ማሸነፍ አለብን፡፡ ለነብሲያ ውስወሳ ቦታ መስጠት የለብንም፣ ነብሲያ እኔ እኔ ማለትዋና ለኔ ለኔ እያለች መጮህዋ መቼም አይቀርም፡፡”
የተማሪዎቻቸውን የተለያዩ ፊቶች ቃኙ፡፡
ጥቁር ፊት አለ፡፡
ጠይም ፊት አለ፡፡
ቀይ ፊት አለ፡፡
ነገር ግን ከሁሉም ፊቶች ላይ የሚነበበው ጥልቅና ረቂቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖትን የማወቅና በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ለመኖር የመመኘት ስሜት፡፡ ሁሉም የጀነት ቁልፍ እጁ ቢገባ ይወዳል፡፡ ከጀሀነም እሳት የመጠበቅና የጀነት ሰው ሆኖ ለመገኘት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የሚያስወስን ጥልቅ ፍላጎት አለ፡፡
እርግጥ ነው፡፡ ትዕዛዛትን ሁሉ አክብሮ በአስተምህሮው መሰረት ህይወቱን በመምራት ለጀነት የሚበቃው ወይም ለጀነት የሚያበቃውን ስራ የሚሰራው ጥቂት ነው፡፡ ምክንያቱም ህይወት አለ፡፡ ገና ከሞት በኋላ የሚመጣውን ህይወት ማሰብ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ዘላቂውንና አዋጩን ከመምረጥ ይልቅ በእጃችን ላይ ያለውን ህይወት ማቅናትና ኑሮን ማሸነፍ ቀድሞ ይገኛል፤ ለብዙዎች፡፡
አሁንም እርግጥ ነው የማይመኝ የለም፡፡ ግን ምኞትና ተግባር፣ ፍላጎትና ኑሮ ደቡብና ሰሜን የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
“እና” አሉ ሼህ ኡስማን
“እና ፍላጎታችንን መደፍለቅ፣ ስሜታችንን መግራትና መልካም ተግባር ላይ መገኘት ይገባናል፡፡” በጥርሳቸው የነከሱትን መፋቂያ እየነቀነቁ፡፡
“ለምሳሌ አንድ የወደድነውና የራሳችን ለማድረግ ያሰብነው ነገር ይኖራል፡፡ ወንድማችን ያንኑ ነገር መፈለጉን ካወቅን ነብሲያችንን አሸንፈን ያንን ነገር ለወንድማችን ቅድሚያ  በመስጠት መተው ይኖርብናል፡፡ እስልምና መስዋዕትነትን የሚያበረታታ እምነት ነው፡፡ ለኔ ከማለት ይልቅ ለወንድሜ ማለትን ማስቀደም አለብን፡፡”
ተማሪዎች ዝም እንዳሉ ተቀምጠው የተማሩትን ትምህርት እንዴት አድርገው በህይወታቸው እንደሚተገብሩ እያሰቡ ትምህርቱን ይከታተላሉ፡፡
“ልብ በሉ ነፍስያ የዋዛ አይደለችም፡፡ ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) “ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላትን ከማሸነፍ ይልቅ መጀመሪያው እንዲሁም ትልቁና ዋናው ጀሀድ ነፍስያን ማሸነፍ ነው!” ያሉትን አትዘንጉ፡፡
“የሆነ ነገር ብንፈልግና ወንድማችን ያን ነገር የሚፈልግ ከሆነ ነፍስያችን አትስጠው አትስጠው ማለትዋ አይቀርም፡፡  እኛ ግን ነፍስያችንን በማሸነፍ ያን ነገር ለወንድማችን መተው ወይም መስጠት አለብን፡፡”
ኡስታዝ ኡስማን ማስተማሩን ከጨረሱ በኋላ ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ሰሞኑን ወደ ተጠሩበት ቦታ ሄዱ፡፡ ቦታው የአንድ ሙስሊም ባለ ሀብት ቤት ነው፡፡ የተጠሩትም ለሰደቃ ነው፡፡
ቤቱ ደረሱ፡፡
ገቡ፡፡
ምግብ በአንድ ትሪ ላይ ሆኖ ለኡስታዙና ለተማሪዎቻቸው ቀረበ፡፡
ሼሁና ደረሳዎቻቸው የቀረበላቸውን ምግብ ጠቅልለው መጉረስ ጀመሩ፡፡
ቀይና አልጫ የሆነ ስጋ ወጥ እንጀራ ላይ ፈስሶ ቀረበላቸው፡፡
እንጀራው መሀል ላይ አንድ አጥንት ወድቃለች፡፡ ኡስታዝ ኡስማን ፈጠን ብለው አጥንቷን በማንሳት መጋጥ ጀመሩ፡፡
ከተማሪዎቹ አንዱ፡-
“ምን ነው ኡስታዝ?” አለ
“ምን ነው?” አሉ አጥንት እንዳገኘ ውሻ በመስገብገብ አጥንታቸውን እየጋጡ፡፡
“ቅድም ነብሲያችንን ማሸነፍ አለብን! ብለው እያስተማሩ አልነበር?”
“እኮ!”
“ምነው ታዲያ አጥንትዋን ቀድመውን አነሱ?” አለ ተማሪው በመደነቅ፡፡
“እኮ!” አሉ ኡስታዙ በድጋሚ፡፡
“ነብሲያዬ ስጥ ስጥ ስላለችኝ እሷን አሸንፌ እየበላሁኮ ነው፡፡” አሉ ኡስታዝ ኡስማን፤ እንደዋዛ ፈገግ ብለው፡፡
ተማሪዎቹ ሁሉ በሳቅ አውካኩ፡፡ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደተባለው መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡
ተማሪዎቹ በሳቃቸው መሀል እውነትና እውቀት፣ ማስተማርና መሆን ምን ያህል እንደሚጣረሱ እያሰቡና እየተገረሙ ወደ ትሪው አጎነበሱ፡፡
(ከመሐመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ) “ጥቁር ሽታ” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ የተወሰደ፤2011 ዓ.ም)

Saturday, 28 September 2024 20:24

የግጥም ጥግ

አንዳንድ ዘመን አለ
ሳንረግጥ እንዳለፍነው እየተንሳፈፍነ
ልክ እንደ አውሮፕላን ዱካ አልባ የሆነ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
ኖረን እንዳልኖርን፣
በዕድሜ መሰላል ላይ እንዳልተሻገርን፤
ያለ አንዳች ምልክት ጥሎን መሰስ ሲል
ዞር ብለን ስናየው ህልም አለም
‘ሚመስል፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
የአመቶቹ ብዛት የሆነ ለውጥ አልባ
የሆነ ጣ’ም አልባ
ያለ እልባት ‘ሚሮጥ ጥላ ቢስ ከላባ፤
የመኸር አበባው የወራቶቹ ሰልፍ
እየመጣ እየሄደ ያለ ፍሬ ‘ሚረግፍ፤
አንዳንድ ዘመን አለ፣
እንደ አንድ ምሽት ጀምበር
ክረምትና በጋው የምናየው አልፎ
በህይወታችን ላይ ቁጥር ብቻ ፅፎ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
ትግል ‘ሚነግስበት
እድል ‘ሚነጥፍበት፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
አሻራ የሌለው የሚሄድ ቸኩሎ
ደስታችንን አዝሎ
‘ርጅናን አድሎ፡፡
አንዳንድ ዘመን አለ
እንዳለ ‘ማንቆጥረው
እንዳለን ‘ማይቆጥረን
እየመሸ እየነጋ ቀን የሚያስቆጥረን፡፡
(አብርሀም ገነት)

Page 9 of 734