Administrator

Administrator

በዳራሲ ህሩይ ሮሜል የተጻፈው “ባለዋርካው ሰጉራ”  የተሰኘ የልጆች መፅሐፍ ባለፈው እሁድ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በአክሱም ሆቴል ተመረቀ፡፡
መፅሐፉ በዋናነት መቼቱን ጅማ አድርጎ በማህበረሰቡ የሚነገሩ ተረቶችንና አፈታሪኮችን በማዘጋጀት ለልጆች በሚገባና በሚመች መልኩ ተደርጎ መሰናዳቱ ታውቋል፡፡ መፅሀፉን የፃፈው ደራሲ ህሩይ ሮሜል በህጻናትና በልጆች ላይ በስፋትና በጥልቀት የመስራት ህልም የነበረው ሲሆን ከነዚህ ህልሞቹ አንዱ የህጻናት መፅሐፍ መፃፍ በመሆኑ መፅሐፉን ፅፎ ጨርሶ የህትመት ብርሃን ሳያይ የደራሲው ህይወት ማለፉን መፅሐፉን አሳትመው ያስመረቁት የደራሲው ጓደኞች ተናግረዋል፡፡
የህሩይ ህልም እውን ለማድረግ ገንዘብ አዋጥተው ያሳተሙት ጓደኞቹ የእግዜር ድልድይ፣ ላምባ፣ የአርበኛው ልጅ በሚሉና በሌሎችም ስራዎቹ የምናውቀው የፊልም ባለሙያ አንተነህ ሀይሌን ጨምሮ ሌሎች ጓደኞቹ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መሆናቸው ታውቋል፡፡ “ባለዋርካው ሰጉራ” ሲመረቅ የመፅፍ ዳሳሳ፣ የደራሲው የህይወት ታሪክና ህልም በዕለቱ ለታዳሚ የቀረበ ሲሆን፣ መፅሐፉ ለዚህ እንደበቃ ለተረባረቡት ሁሉ የደራሲው ባለቤት ምስጋና አቅርባለች፡፡  መፅሀፉ በ66 ገፅ ተቀንብቦ በ230 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በገጣሚዋና በህክምና ባለሙያዋ ዶ/ር አበባ የሺጥላ የተሰናዳውና 66 ያህል ግጥሞችን የያዘው “እግዜር ቅኔ አማረው” የተሰኘው የግጥም ስብስብ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
በመፅሐፉ ውስጥ የተካተቱ ግጥሞች በርካታ ማህበራዊ ርዕስ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ፍሬያማ ግጥሞች ስለመሆናቸው መፅሐፉን የማንበብ ዕድል የገጠማቸው ግለሰቦች ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አበባ የሺጥላ ከውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪምነቷ ባሻገር እጅግ ጠንካራና በተለያዩ ማህራዊ ጉዳዮችም ንቁ ተሳትፎ ያላትና የተዋጣላት ገጣሚ እንደሆነችም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“እግዜር ቅኔ አማረው” የግጥም ስብስብ መፅፍ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን በ102 ገጽ ተቀንብቦ በ150 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡


            "--ጃፓንን ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ ብረት በጠነከረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ተገረሰሰ፡፡ በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት ተመሠረተ፡፡ የጃፓን አዲስ ጉዞ ተጀመረ፡፡ አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ፣ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሳይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡--"
               አያልቅበት አደም                ፈር መያዣ
ከሁለት መቶ ሃምሣ ዓመታት በላይ በመሣፍንትና በጦር አበጋዞች ስትታመስ ለነበረችው ጃፓን ቶኩጋዋ ኤያሱ የተባለ የጦር መሪ ተነሣላት፡፡ በየመንደሩና በየጎጡ  ነፍጥ አንስተው ሲተጋተጉ የነበሩ ጦረኞችን ድል ነስቶ የራሱን ወታደራዊ መንግሥት መሠረተ። የቀደመውን የንጉሥ ሥርዓት ለይስሙላም ቢኾን ወደ መንበሩ መለሰው፡፡ ይኽ ከ250 ዓመታት በላይ የዘለቀው ወታደራዊ የመንግሥት ሥርዓት ሾገን በመባል ይታወቃል፡፡
ይኽ ወታደራዊ ሥርዓት የጃፓንን በር ጠርቅሞ ከሌላው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ ነጠላት፡፡ የአገሩን ሕዝብ በመደብ ለይቶ፣ በሥራም ኾነ በማኀበራዊ ግንኙነት እንዳይተሳሰር ከፋፈለው፡፡ የእያንዳንዱ ጃፓናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንኳ በሕግ ተደነገገ፡፡ ጃፓን ውስጥ የነበሩ አውሮጳውያንን ከአገሩ አስወጣ፡፡ የአገሩም ሰው ከጃፓን ውጭ ወደየትም ውልፍት እንዳይል አዘዘ፡፡ ቀደምት መጻተኞች የሰበኩትን ክርስትና አገደ፣ አብያተ ክርስቲያን እሣት በላቸው፡፡ የወቅቱን ሁኔታ  በአጭር ለመግለጽ ከባለቅኔ ከበደ ሚካኤል “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ጥቂት እንጥቀስ፤
 “. . . ከእንግዲህ በኋላ ፀሐይ በመሬት ላይ አብርታ እስከምትኖርበት ጊዜ ማንም ሰው ቢኾን ጃፓን አገር ለመግባት አይድፈር . . . ይኽን ዐዋጅ ጥሶ ሲገባ የተገኘ የውጭ አገር ሰው ሁሉ በሞት ይቀጣል፡፡” (ገጽ፤26)
የሰው ልብ በቅጥር አይያዝም
የሰው ልብ፣ የሰው ምኞት ግን አይቀጠርም። በሥፍራ ተለይቶ አገር ድንበር ተበጅቶለት ይቀመጥ እንጂ ሰው ልቡ እግረኛ ነው፡፡ የትም መቸም፡፡ ዘራሰብ ሉላዊ ነው፡፡ ዘመነኞች ስደት በሚል ይበይኑት እንጂ ዕጣ ፈንታ እንዲህም እንዲያም ብሎ ያገናኘዋል፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው “ጉልበተኛ የፈጠራት ዓለም” የሚለው ግጥማቸው እንዲህ የሚል ሃሣብ አለው፡-
እስኪ ከዚህች ወዲህ፤ ከዚያ ወዲያ ብሎ፤
ዛቻ ከፖለቲካ ቀላቅሎ፤
ከለላት እንጂ
አሰመራት
ዓለማችን
መች ድንበር ነበራት
ከመሣፍንትና የጦር አበጋዞች ነፍጥ አስጥሎ፣ የአገሪቱን መግቢያ መውጪያ የከረቸመው የሾገኑ አስተዳደር፣ ከምዕራቡ ዓለም የዕድገት ወሬ የጃፓናውያንን ልብ በቅጥርም ኾነ በነፍጥ መከለል አልቻለም፡፡ በተለይ የባህር ዳርቻ ግዛት አስተዳዳሪዎች የወሬው ነፋስና እነርሱ ያሉበት ኹኔታ ከተራ መንፈሳዊ ቅናት አለፈ፡፡ የአገራቸው መፃዒ ዕድል ያሣስባቸው ጀመር፡፡ በአናቱ ጥቁር ጢሱን እያትጎለጎለ “ጥቁሩ መርከብ” (The Black Ship) ደረሰ፡፡  ይኽን ተከትሎ ከሁለት መቶ ሃምሣ ዓመታት በላይ ተዘግቶ የነበረው በር ተከፈተ፡፡ የመርከቡ ጢስ ለቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት መፍረክረክ፣ ለለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ግን የማንቂያ ማጠንት ኾነላቸው፡፡ ዓመጽ ማቀጣጠሉን ገፉበት፡፡ የተፍረከረከውን ነባር ሥርዓት ለማስቀጠል የቆረጡ “ታማኞች” በለውጡ እሣት አቀጣጣዮች ላይ ብረት አነሱ። ብረት ያነሱ በብረት ይጠፉ ዘንድ ተጽፏልና የሾገኑ ሥርዓትና ጭፍሮቹ ማብቂያ ኾነ፡፡
ጃፓንን ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ ብረት በጠነከረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ተገረሰሰ፡፡ በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት ተመሠረተ፡፡ የጃፓን አዲስ ጉዞ ተጀመረ፡፡ አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ፣ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሳይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡
መብሰልሰል  
ከጃፓን መንግሥት በተገኘ የባሕል፤ የቋንቋና የዲፕሎማሲ ስልጠና ለስምንት ወራት ያህል ጃፓን የቆየው ዲፕሎማቱ አሰፋ ማመጫ አርጋው፤ በጃፓን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጉዞ ያደረበትን ምሳጤ በ366 ገፆች ቀንብቦ አቅርቦልናል፤- በ“የጃፓን መንገድ”፡፡ የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚመሩት አገሮች አንዷ የኾነችውን የዚህችን ትንሽ አገር ውድቀትና አነሣስ ድርሳናት አገላብጦ፣ የዜና አውታሮችን ዘገባ ፈትሾ ቅልል ባለ ቋንቋ፣ አጠገባችን ኾኖ እንደሚተርክ ሰው እስኪሰማን ድረስ ወጉን ይቀዳልናል፡፡
እውነት እውነት እላችኋላሁ፣ በየምዕራፎቹ እንደ መስታወት የእኛን የእስካሁን የአብዮትም የነውጥም ጉዞ የሚያስታውሱ ተረኮች በርካታ ናቸው፡፡ የፀሐፊው ዋና ቁብ ይኽው ይመስለኛል፡- ቁጭትን መፍጠር፡፡
ጃፓን ላለፈችበት መከራ ሁሉ መንስኤው ልጓም ያልተበጀለት ብሔርተኝነት ይመስለኛል። መዳኛዋ ደግሞ ሽንፈትን ተቀብሎ ከመሰበር ይልቅ በአዲስ አቅጣጫ በአዲስ መንገድ፣ እንደ አገር አንድ ልብ፣ አንድ ሃሣብ ይዛ መነሣቷ ነው፡፡ ከሁለት ምዕት ዓመት በላይ አገሪቱን ዘግቶ ያቆያት ሥርወ መንግሥት እንደተቀየረ፤ አብዮተኞቹ ቀጣይ ሥራቸው አገራቸውን እንደምን አበልጽገው ከሃያላን ተርታ ማሰለፍ እንጂ በርዕዮተ ዓለም ጎራ ለይቶ መተጋተግ አልነበረም፡፡ እኒያ የጃፓንን የብርሃን ዘመን ማሾ የለኮሱ ቀደምት እንደምን በአንድ ልብ ተነስተው አገሪቱን ሃያል እንዳደረጓት አሰፋ ከሰው አውግቶ፣ ከማዕምራን ጠይቆ እና ድርሣናት ፈትሾ ነው መብሰልሰሉን የሚያካፍለን፡፡
‘. . . ለኔ ብለህ ስማ’    
የአሰፋ ትረካ ስሜትን የሚበረብር ነው። መጽሐፉ ከገጽ ገጽ በተነበበ ቁጥር፣ የእኛን የእስከዛሬ ጉዞና አሁናችንን እንድንጠይቅ፣ የት ጋ እንደጎደልን ውስጣችንን እንድንበረብር ይጎተጉታል፡፡ ለምን በመፈክርና ቃላት በማሽሞንሞን ላይ ተቸንክረን ቀረን? የጃፓን መንገድ እንዲህ ውስጥን ይሞግታል፡፡
“. . . የቀድሞው መንግሥት በአመጽ ተወግዶ የሜጂ ንጉሣዊ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ጃፓን ድሃ እና ኋላቀር አገር ነበረች፡፡ [..] እናም አገሪቱን ከኋላቀርነት ፈጥኖ ለማውጣት ለለውጡ መበዎቹ ከሌሎች የሠለጠኑ አገራት ልምድ መቅሰም ወሳኝ ጉዳይ ኾነ፡፡ [. . .] ለዚሁ ዓላማ ሥልጣን የጨበጡት ወጣቶቹ የለውጥ መሪዎች፣ በታሪክ “ኢዋኩራ ሚሽን” በመባል የሚታወቀውን የልዑካን ቡድን አዘጋጁ” (ገጽ 46-47)
በወቅቱ እንደተነገረን የኢትዮጵያ አብዮት በግብታዊነት ከፈነዳ በኋላ እና ከግማሽ ምዕት ዓመት መንበራቸው ንጉሡን ከገረሰሰ በኋላ ምን  ተፈጠረ? አንድ ጥራዝ የሶሻሊዝምን ፍልስፍና ያነበቡ ወጣት ተማሪዎች ጎራ ለይተው መተጋተግ ጀመሩ፡፡ ስልጣኑን የጨበጠው ወታደር በበኩሉ፤ "ተማሪ አርፎ ትምህርቱን ይማር፡፡ በዚህ ግርግር ይህች አገር እንደ እንቁላል ከእጃችን ወድቃ እምቦጭ ማለት የለባትም" አለና ጠብመንጃውን አቀባበለ፡፡ ያኔ የተጀመረ መናቆር አንድ ደርዝ ሳይበጅለት የትውልድ ዕድሜ እየበላ ቀጥሏል፡፡
አገር ከርዕዮት ዓለም በላይ ናት፡፡ አገር ልብ በሚያሞቅ ዘፈን፣ ነፋስ በሚነሰንሰው የሰንደቅ ዓላማ ዳንስ፣ ገድሎ በመሞት ብቻ አትበየንም፡፡ አገር በሁሉ ስምም ራዕይ የጋራ ምሰሶና ካስማ፣ ሁሉን አቅፋ የምታኖር የትናንት አደራ፣ የነገ ስም የዛሬ ማረፊያ ናት፡፡ እንጂ ለ”ከእኔ በላይ ለአሣር” በሚል የምትሰዋ በግ፣ ጭዳ የምትኾን ዶሮ አይደለችም፡፡
ጃፓን እንዲህ ነው ያደገችው፡፡ ለዘመናት ዘግቶና ጠርንፎ የያዘ የሾገኑ አገዛዝ ተገረሰሰ ብለው የተነሱ ወጣት አብዮተኞች፤ ለሌላ ትግል መነሻ እርሾ አልኾኑም፤ የተነሱበትን ዓላማ ከተነሱለት ሕዝብ ጋር ተገበሩት እንጂ፡፡
‘ሰው ጥሩ አንድ ሰው’
የሰውን ልጅ የሕይወት ትልም በአንድም በሌላ መልኩ የሚቀይረው የአንድ አሳቢ (አፈንጋጭ) ሃሣብ ነው፡፡ ሃሣቡ ግን መሬት የረገጠ፣ የሰው ልብ የሚገዛ፣ መሬት የሚወርድ፣ ውጤቱ የሚገለጥ ነው፡፡ የማኀበረሰቡ ሕይወት እና አስተሳሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሣድር አንድ ሰው አገር ያነቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናየው ፋኩዛዋ ዩኪቺ እንደዚያው ነው፡፡
መደምደሚያ
ፀሐፊው የጃፓንን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ቀለል አድርጎ በሚነበብ መልኩ አቅርቧል፡፡ ስለ ጃፓን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በቅኝ ገዢነት ያደረገችው ጦርነት ስላስከፈላት ዋጋ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ስለደረሰባት የሰውና የቁስ ውድመት፣ በሽንፈት ከመሰበር እንደምን መንቃት እንደሚቻል፤ ስለ ይቅርታ፣ እንደ አገር በአንድ ርዕይ እንደምን መነሣት እንደሚቻል፣ የሥራ ባሕልን በማኀበረሰብ ውስጥ ስለ ማስረፅ እጅግ በአስደማሚ ሁኔታ አስነብቦናል፡፡ ብቸኛዋ በአቶሚክ ቦምብ የተመታች አገር ከዚያ ውድመት እንዴት እንዳንሰራራችና ከተረጂነት ወጥታ ወደ ቁጥር አንድ የልማት ትብበርና እርዳታ ሰጪነት እንደተቀየረች ያሣያል፡፡  
በመጽሐፉ ውስጥ ከንባብ አንፃር አጽንኦት ለመስጠት በማሰብ አንዳንድ ምዕራፎች መግቢያ ላይ ቀድሞ የተነገረ ታሪክ ይደገማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “ወረድ ብለን እንደምናየው”፣ “በሌላ ቦታ በሰፊው እንደምናየው” የሚሉ አገላለፆች አንባቢውን ከንባቡ ፍሰት የሚያናጥቡ በመኾናቸው በቀጣይ ሕትመት ቢስተካከሉ ተመራጭ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ፀሐፊው የካበተ ልምድ እንዳለው ዲፕሎማት፣ የጃፓንን ጉዞ በንስር ዓይን መርምረው ይኽን ሥራ ማበርከታቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Saturday, 18 June 2022 18:18

ታሪክ - ለልጆች

 ቀበጧ ቡችላ

           በጥንት ጊዜ አንዲት ውሻ ከትናንሽ ልጆቿ (ቡችሎች) ጋር በአንድ የእርሻ አካባቢ ላይ ይኖሩ ነበር። በእርሻው አካባቢ የውሃ ጉድጓድም ነበር። እናቲቱ ውሻ ልጆችዋ ወደ ውሃ ጉድጓዱ አቅራቢያ እንዳይደርሱ ወይም በዚያ አካባቢ እንዳይጫወቱ ሳትነግራቸው የቀረችበት ጊዜ የለም፡፡ ሁሌም ትመክራቸው ታስጠነቅቃቸው ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ከቡችሎቹ አንደኛዋ ቀበጥ ቡችላ በእናታቸው የተከለከሉትን የውሃ ጉድጓድ ለማየት ጥልቅ ጉጉት  አደረባት። የእናቷን ምክርና ማስጠንቀቂያ ችላ ብላ ወደ ጉድጓዱ  ለመሄድ ተነሳሳች፡፡
ቡችላዋ ብቻዋን ተደብቃ ወደ ውሃ ጉድጓዱ ሄደች። ወደ ጉድጓዱ ስትመለከትም በውሃው ውስጥ የራሷን ምስል ነጸብራቅ አየች፡፡ እሷ ግን በጉድጓዱ ውሃ ውስጥ ሌላ ውሻ ያለ ነበር የመሰላት።  ከዚያ  ውሻ ጋርም  ለጠብ ተጋበዘች፡፡
ቡችላዋ በጣም ከመናደዷ የተነሳም የውሃ ጉድጓዱ ውስጥ ዘልላ ገባች። እንዳሰበችው ግን ሌላ ውሻ አላገኘችም። ከዚያ ማን ያውጣት?! መጮህና ማልቀስ ጀመረች። ከብዙ ጩኸትና ለቅሶ በኋላ ገበሬው ደርሶ አወጣት፡፡ ከሞት አተረፋት። ከዚያ ጊዜ በኋላ ቡችላዋ ወደ ውሃ ጉድጓዱ ተመልሳ ሄዳ አታውቅም።
ውድ ልጆች፡- ከዚህ ታሪክ የምንማረው ቁም ነገር፤ የታላላቆችን ምክርና ትዕዛዝ መስማትና ማክበር ተገቢ መሆኑን ነው። ቡችላዋ የእናቷን ምክር ባለመስማቷ የገጠማትን አደጋ ከታሪኩ ተገንዝበናል፡፡

Saturday, 18 June 2022 18:16

ታሪክ - ለልጆች

ሙዚቀኛው አንበጣ
              ውድ ልጆች፡- ከዚህ ታሪክ የምንማረው ቁምነገር፣ ማንንም በቅጡ ሳናውቅ ገጽታውን ብቻ አይተን ወደ ንቀትና ማሾፍ መግባት እንደሌለብን ነው። እጃቸው ላይ ልንወድቅ እንችላለንና፡፡

                         ሙዚቀኛው አንበጣ

           በአንድ ብሩህ የመኸር ቀን፣ በሞቃቱ የፀሃይ ብርሃን፣ የጉንዳን ቤተሰብ አባላት እጅጉን በስራ ተጠምደው ነበር። ጉንዳኖቹ በበጋ ያከማቹትን እህል እያደረቁ ሳለ፣ አንድ የተራበ አንበጣ ወዳሉበት መጣ፡፡ ቫዮሊኑን በክንዱ ስር ያደረገው አንበጣ፤ ጥቂት የሚጎርሰው እህል እንዲሰጡት ጉንዳኖቹን ተማፀነ።
“እንዴት!” ጉንዳኖቹ በአንድ ላይ  ጮኹ፤ “ለክረምቱ ምንም ስንቅ አላስቀመጥክም? በጋውን በሙሉ የማንን ጎፈሬ ስታበጥር ነበር?” ሲሉ ጠየቁት።
“ከክረምቱ በፊት ስንቅ ለመያዝ ጊዜ አልነበረኝም” አለ አንበጣው እያለቃቀሰ፤ “ሙዚቃ በመስራት ተጠምጄ ነው በጋው ያለፈብኝ።”
ጉንዳኖቹ ትከሻቸውን  በግዴለሽነት እየነቀነቁ፤ “ሙዚቃ እየሰራህ ነበር? ደግ አድርገሃል፤ አሁን  ታዲያ ደንሳ!” አሉትና ጀርባቸውን ሰጥተውት ወደ ሥራቸው ተመለሱ።
ውድ ልጆች፡- ከዚህ ታሪክ የምንማረው ቁም ነገር፤ ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ነው። ለሥራም ጊዜ አለው፤ ለጨዋታና ለመዝናናትም ጊዜ አለው። ይህንን ሥርዓት ካዛባን የአንበጣው ዓይነት ችግር  ይገጥመናል።


  ከሃያ ዓመታት በፊት የሚከተለውን ተረት ተርከነው ነበር። ሆኖም ከዚያ በባሰ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው አገራችን ደግመን እንድንለው አድርጋናለች!
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ያገር ቤት ወንድና ሴት፣ ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ተገናኝተው፣ በባልና ሚስትነት አብረው መኖር ጀመሩ። ባልየው ሁሌ የመከፋት ምልክት ይታይበት ነበርና ሚስቲቱ ሁሌ ትጨነቅ ነበር።
አንድ ቀን ግን፤
“ባሌ ወዳጄ፣ እንኳን ደስ አለን” አለችው
“ምን ተገኘ?” አላት።
“የወር አበባዬ ከቀረ ሦስት ወር አለፈ”
“እንዴት?” አለ በድንጋጤ።
“እርጉዝ ነኝ!”
“አዬ ጉድ! ሌላ መከራ!” አለና አቀረቀረ።
“ለምን ሌላ መከራ አልክ?” ብላ ጠየቀችው።
“ተይኝ ባክሽ። የደረሰብኝን መከራ ሁሌ ልነግርሽ አስብና ተመልሶ ይመጣ እየመሰለኝ ደንግጬ እተወዋለሁ።;
“ባክህ ስለመከራህ ልወቅ” ብላ ወተወተችውና አወጋት፡-
“ባገራችን በሽታ ገብቶ ብዙ ሰው አለቀና የመንደሩ ጥቂት ሰዎች ተረፍን። ከተረፍነውም ጉልበት የነበረኝ እኔ ብቻ ነበርኩኝ። ሰው ሁሉ አልቆ ቀባሪ በታጣበት ሰዓት አባትና እናቴ በአንድ ቀን ልዩነት ተከታትለው ሞቱ። ቤታችንን ዘግቼ መቃብር ስቆፍር ዋልኩና ሁለቱንም ባንድ ጉድጓድ ልቀብር በቅድሚያ ያባቴን አስክሬን ወስጄ መቃብሩን አድርሼ የናቴን ላመጣ ተመለስኩ። የእናቴን አስክሬን አውሬ በልቶት ራስ-ቅሏን ብቻ አገኘሁ። አዝኜ ወደ አባቴ ስሄድ እሱንም አውሬ በልቶታል። አንዳቸውንም ሳላድን ቀረሁ። ሌትና ቀን ይሄው ሰቀቀኑ አልለቅ ብሎኝ  አለቅሳለሁ!;
 እሷም፤
“ከኔ የባሰ መከራ የደረሰበት ያለ አይመስለኝም ነበር።; አለችው።
“ያንቺስ ምን ነበር?” ሲል ጠየቃት።
“እኔ ባሌና ሶስት ልጆቼ ረሀብ ገባና ተሰደድን። ዝናብ ዘነበ- ሀይለኛ። ባሌ ሶስቱን ልጆች ተራ በተራ አመላልሶ እኔን ሊወስድ ሲመጣ ጎርፍ በጣም ሞላና ወሰደው። ብቻዬን ቀረሁ። እንግዲህ የቀረኝ ይሄ ሆዴ ውስጥ ያለው ፅንስ ነው።;
“አይዞሽ! የባሰ አታምጣ በይ! ልጅሽን ይባርክልሽ። ያለፈውን ረስተን ለነገ እንኑር!” አላት ይባላል።
***
ረሀብ፣ ድርቅና ጦርነት ዛሬም ያልተለያት አገራችን፣ የህዝቧን ጽናትና የመንግስቷን ጥንካሬ ትማጸናለች። በሄደች ቁጥር መንገዱ ይረዝምባታል። በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿ ሁሉ ዐይናቸው በእሷ ላይ እንደቀላ ነው። ደግነቱ ዘንድሮ ቢያንስ ስፖርቱ እየካሣት ነው- ሳይደግስ አይጣላም!
የአንድ አገር ዲፕሎማሲ ከሽርሽር ባለፈ ሊታሰብ ይገባዋል። የአገር መሪ ክብር፣ የአገርና ህዝብ ክብር መሆኑን አለመዘንጋት ሀላፊነትን መወጣት ነው። መከራ ሲደራረብ ተስፋችን፣ የልብ ጽናትና ሀሞትን መራር ማድረግ ይጠይቃል።
የፖለቲካው ሁኔታ ሲጠነክር፤ መቼም ቢሆን-
“ነገሩ አልሆን  ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር።;
ማለትን እንመርጣለን - እንደ ገሞራው። ጠጣሩ እንዲላላ ግን የእኛን መጠጠር ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የንቃተ ህሊናችን መዳበር እጅግ ወሳኝ ነው። የንቃተ ህሊናችን መዳበር የሚመጣው አንድም ከዕውቀት፣ አንድም በኑሮ ከመብሰል ነው! አንድም በፊደል ´ዋ´ ብሎ፣ አንድም በኑሮው ዋ! ብሎ እንደተባለው ነው።
ገጣሚው፤
ዋ!
እግረ-ቀጭን ብጤ፣ ጭንቅላተ- ክብ
ፊደል ናት፣ ሆሄ ናት፤ እንደሌላ ራብ
መች ያጣዋል እሱ፣ ፊደል የቆጠረ
´ዋ´! ብሎ ከቀረ፣ ዋ! ብሎ የኖረ!!
ያለው ወዶ አይደለም፡፡ መጠንቀቅና ማስጠንቀቅ ደግ ነው። በምንጓዝበት የለውጥ ጎዳና ከጎረቤት አገሮች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር ዲፕሎማሲያዊ መጣጣም እንጂ በጦርነት እጅ የሚያስጠመዝዝ ሁኔታ ውስጥ የሚከትተን መሆን የለበትም። ለዚህም  የአገር ወዳዶችን ምክር ማዳመጥ በጣም ወሳኝ ነው። የአገር ውስጥ ችግራችንን ለመፍታት መትጋትን ቅድሚያ እንስጥ እንጂ ለጎረቤት አገር ድግስ ላይ-ታች የምንል ከሆነ፣” የራሷ ሲያርርባት የሰው ታማስላለች” የሚለው ተረት አስፈጻሚዎች ሆንን ማለት ነው!
ከዚህ አባዜ ይሰውረን።

  አገልግሎት ሰጪና ፈላጊን ያገናኛል ተብሏል

                አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጋር የሚያገናኝና አስተማማኝ አገልግሎት ያቀርባል የተባለ ሞባይል መተግበሪያ ተመርቆ ስራ ጀመረ።
በትናንትናው ዕለት በይፋ ስራውን የጀመረውና “ምን ልታዘዝ አዲስ” የተሰኘው ይኸው መተግበሪያ፤ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን፣ የፍሳሽ ውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና፣ የዲሽ ስራ ባለሙያዎችን ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጋር የሚያገናኝ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ቀብር ማስፈጸም ስራ፣ የምግብ  ዝግጅት ስራዎችን፣ የእንስሳት ህክምና እንዲሁም ከ30 በላይ የአገልግሎት ሰጪ ባለሙያ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጋር ይገናኛል ተብሏል።
ማንኛውም የአገልግሎቱ ፈላጊዎች በሞባይል መተግበሪያው አሊያም በ625 የስልክ መስመር ላይ በመደወል አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ጥራትና  አስተማማኝነት ያለው አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ነው ተብሏል። አገልግሎቱ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እድል ላላገኙ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል የሚከፍት መሆኑ ታውቋል።
የአገልግሎት ተጠቃሚው ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸው ቅሬታዎችን ለማስወገድ የሚቻልበት አሰራር ይዞ መምጣቱም ገልጿል።


Saturday, 11 June 2022 20:14

ራስን የመሆን ጥበብ!

 "ለመሆኑ ኢትዮጵያ ማን ናት? ምን ትመስላለች? እንደ ኅብረተ-ሰብዕ እኛ ማን ነን? ማንነታችንን ምን ያህል እናውቃለን? ምን ገጠመን? እንዴት አለፍነው? በገንቢ ጽናትስ ማንነታችንን ይዘን ቀጥለናል ወይ? ራሳችንን እንይ!"

            ይበል አዘጋጅ፡- ተንስኡ ለንባብ፡፡
ይበል አንባቢ፡- በስመ አብ…አቤቱ እውነቱን ግለጥልን፡፡ የሁሉ ፈጣሪ ማስተዋልን ስጠን፡፡
እነሆ፡- የፈጣሪ ባሪያ፣መጻፍ እና ማስነበብ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ ላነሳ የወደድሁት ፍሬ ነገርም እጅግ መሠረታዊ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ሀ/ ዓላማዎች
የመጀመሪያው ንዑስ ዓላማ ራስን መሆን ሲባል ብዙ ጊዜ ተዛብቶ ይቀርባልና እርሱን ማስተካከል ነው፡፡ በተለይ በግለሰብ ደረጃ ሲቀርብ፡፡ ራስን መሆን ሲባል ሰባቱ የማንነት መርሆዎች የምንላቸውን በሚጻረር መልኩ ሌሎችን ማዳመጥ ትቶ፣ ራሱን ብቻ እያደመጠ፣ ስሜቱን እና ሐሳቡን ተከትሎ፣ ከመንጋው ቢነጠልም ተነጥሎም፣ ለማንም ስሜት እና ጉዳት ሳይጨነቅ፣ ሥራው ያውጣው ብሎ፣ ለሌላው ግድ አጥቶ፣ በራሱ ህልም ተመስጦ፣ የራስን ኑሮ መኖር የሚመስላቸው እና እንዲህም አድርገው የሚያቀርቡ እና የሚያስተምሩ ብዙዎች ናቸው።  ያው ምዕራባዊ የግለኝነት ትርጉም ነው፡፡  ይህ በፍጹም ስህተት ነው፡፡
ራስን መሆን ማለት እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተ-ሰብዕም ሊታይ የሚችል ሲሆን ላመኑበት መኖርን ወይም ላመኑበት ነገር፣ እሺ ላላመኑበት ነገር እምቢ ማለትን የሚያሳይ ነው፡፡ ፍቅር ፍቅር እያለ በፍቅር እና መረዳዳት እንደማያምን፣ ማኅበራዊ ሆኖ እንዳልተፈጠረ የጫካ አውሬ፣ ያሻን እየሰሩ፣ ምክርን እየጣሉ፣ ትብብርን እየገፉ መኖር ማለት አይደለም፡፡
ራስን መሆን በዋናነት የሚያስፈልገው ባመኑት ለመኖርና ኃላፊነት ለመውሰድ ነው፤ ለሚሰራው ኃላፊነትን የማይወስድ ሰው ቢያጠፋ ለወቀሳ፣ ቢያለማ ለምስጋና አይመችም፤ ምክንያተኛ ይሆናልና፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ሥራ መሪዎች (ሥራ አስኪያጆች) ኃላፊነት ለማይወስድ ሰው ኀላፊነት መስጠት የማይወዱት፡፡
ዛሬ እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተሰብም ራሳችንን መሆን አለብን ስል ስለሠራነው እና ስለምንሰራው ሥራ ኃላፊነት እንውሰድ፤ ለማንነታችን ዋጋ እንስጥ፣ እያልኳችሁ ነው። ማንነትን፣ ለማጽናትም ለመለወጥም ማንነትን ከመቀበል ይጀምራልና፡፡
ራስን መቀበል እና መሆን ከሰባቱ የማንነት መርሆዎች አንዱ ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም። እነርሱም፡-
ማንነትህን ዕወቅ፣
ማንነትህን ተቀበል፣ (ራስህን ሁን፣)
ማንነትህን አጥራ፣ ገንባ፣
ማንነትህን ለአንድነት እና ለጋራ ስም ብለህ ካልሆነ በቀር አጽንተህ ያዝ ፣
በንግግርህ ማንነትህን በጨዋ ግልጥነት ግለጥ፣
ማንነትህን በሥነ-ምግባር፣ በሥራ ግለጥ፣ (ራስህን ሁን፣)
የማንነትህን ዕውቀት ለውሳኔዎችህ በግብአትነት ተጠቀምበት፤ የሚሉ ናቸው።
ማንነትን ስለማጥራት ማውራት የማይመቸው ምዕራባዊው የሥነ-ልቦና አስተምህሮና ማንነትን ስለ አንድነት ሲሉ መሰዋት የሚለው ቃል እንደ ሬት የሚመራቸው የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ በልዩ ልዩ ስልት የማንነት አጠባና የአዕምሮ አጠባ እያካሄዱብን ነው፤ አንድነታችንን እየሸረሸሩ ነው፤ ባህላችንን እያጠፉ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እና የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ ናዝራዊ በመሆን እና በመገረዝ የማንነትን ዋጋ እንደከፈሉ ወደው አያስተውሉም፡፡
ስለዚህ ወቅቱ ራሳችንን ስለመሆን እና ራሳችን ስለመቀበል አጥብቀን ልናስብ፣ አጥብቀን ልንወያይ የሚገባን ጊዜ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ኅብረተ-ሰብዕ ራሱን ሲሆን ለራሱ ያለውን ዋጋ እና ክቡርነት ይገልጣል፤ ራስን ከባዕዳን እና ከጠላት አሳንሶ ማየትን አባቶቻችን አላስተማሩንም፡፡
ነፍስን ጠልቶ፣ሕይወትን ተጠይፎም አይሆንም፡፡ ነፍስን ወዶ፣ ለሥጋ ሳስቶም አይሆንም፡፡ ወንጌል “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ይጥላት” ሲል “ይጉዳት” ማለቱ ነው፡፡ የሚጎዳውም ነፍሱን ሊያድን ነው። አብርሃም ልጁን እስከ መሰዋት የታዘዘው እግዚአብሔር እንደሚያስነሳለት እና ዳግም እንደሚያገኘው ስላመነ ነበር፡፡ የቃሉ ሐሳብ፣ ሰው መከራ መቀበል ግዴታው ከሆነ መከራን ይቀበል፤ ራሱን ይጉዳ፤ ለወንድሙ ይሙት፤ ማለቱ እንጂ፣ መከራን በገዛ እጃችን እንድንጎትተው አይደለም። ጸሎታችን ወደ ፈተና አታግባን ነው፤ ጥረታችንም ችግርን መፍታትና ማቃለል ነው፡፡ ነገር ግን ስደቱ፣ መስቀሉ ልናልፈው የማንችል ሆኖ ከመጣ ስለ ነፍሳችሁ ተጎዱ፤ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ከራሳችንም ከሰውም የምንስማማው ራሳችንን ስንሆን፣ ባመንበት ስንኖር እና ወጥ ጠባይ ሲኖረን ነው፡፡ ራስን መሆን ከጸጸት ያድናል፤ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል፤ ምነው ያመንኩትን ሠርቼ ቢሆን ከሚል ጸጸት ያድናል፡፡ የዘመናችን ምስቅልቅሎሾች ለማንነት ግጭት እንዳይዳርጉንም ይረዳናል፡፡
ሌላው ራስን መሆን እና አለመሆን መክሊትን የመጣል እና ያለመጣል ጉዳይ በመሆኑ፣ እንደሚገባ ባንይዘው እና እንደሚገባ ባንጠቀምበት፣ በአምላክም በታሪክም ተጠያቂ ያደርገናል ብዬ አምናለሁ።
ለ/ ችግሮች
ገንቢ ጽናት የሚለው ቃል ገንቢ ያልሆነ ጽናትም እንዳለ የሚጠቁም ሲሆን፣ ለለውጥ አለመቸኮልንም፣ ለለውጥ አለመለገምንም ያሳያል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ማን ናት? ምን ትመስላለች? እንደ ኅብረተ-ሰብዕ እኛ ማን ነን? ማንነታችንን ምን ያህል እናውቃለን? ምን ገጠመን? እንዴት አለፍነው? በገንቢ ጽናትስ ማንነታችንን ይዘን ቀጥለናል ወይ? ራሳችንን እንይ! ጥያቄዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ማንነታችንን ዕናውቀዋለን? (እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተ-ሰብዕም)
ካወቅነውስ ማንነታችንን ተቀብለነዋል? መልካምም ቢሆን መጥፎ ኃላፊነት ወስደናል?
ማንነታችንን አጥርተናል? ገንብተናል? ወይስ ይብስ አቆሽሸናል?
ለአንድነት እና ለጋራ ስማችን ስንልስ ማንነታችንን እና ልማዳችንን እየሰዋን ነው?
ማንነታችንን በጨዋ ግልጥነት ነው የምንገልጠው? ወይስ ይሉኝታ ቢስ ግልጥነት ያጠቃናል?
ማንነታችንስ ያለው አንደበታችን ላይ ብቻ ነው? ወይስ በሥራ እንገልጠዋለን?
“ማንነታችን፣ እንዲህ ነው፤ እናውቀዋለን።” ብለን ዘጋነው? ወይስ ለውሳኔዎቻችን እንጠቀምበታለን?
ነጻነት አምሳሉ አፈወርቅ የተባሉ ጸሐፊ ሰሞኑን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በጻፉት ጽሑፍ እንዳሉት፤ “ትውልዱ ግብረገብነት የለውም፤ እንደ ሃይማኖተኛ ሕዝብ እየኖርን አይደለም፤ እንደ ባህላችን እና ሥርዓታችን ልከኛ አልሆንም፤ ሀገር ወዳድነታችን እየቀዘቀዘ ነው፤ ማህበራዊ ትስስራችን ላልቷል፤ ወገናዊ ስሜታችን በግለኝነት ተቀይሯል፤ አጉል ባህል ተጣብቶናል፤… የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ።” ብለዋል። አዎ በሚያሳዝን ሁኔታ ባህለ ማንነታችን እየተሸረሸረ ነው፡፡ ይገርማል! ጸሐፊው የምጽፈውን አስቀድመው አውቀው ለእርዳታ የጻፉልኝ ይመስላል፤ ይህ ችግራችን ነው፡፡
ዛሬ ባማረው እና በጸናው በኢትዮጵያዊ መልካችን፣ ከአባቶቻችን በተረከብነው ማንነት እና ባህል እንዳንኖር የሚያደርጉ ብዙ ነፋሳቶች እና ግፊቶች እያስተናገድን የምንገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ከለውጡ በኋላ ብዙ ነገሮች ቢሻሻሉም እኛን የማይመስሉ መገናኛ ብዙኃን ዛሬም አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቃና ያሉ፡፡ የጠላት ፕሮፓጋንዳም ቀጥሏል፡፡ ዛሬም አለባበሳችን እና የኑሮ ዘዬአችን ባህለ- ማንነታችንን አይመስልም፡፡
በወንጌል ስም ዓለማዊ ወንጌሎች፣ በሳይንስ ስም ሐሰተኛ ሳይንሶች፣ በፍቅር ስም የጅልነት ስብከቶች፣ በእውነት ስም የድራማ እና የማኖ መረጃዎች ተጽእኖ እያደረጉብን ነው፤ ከማንነታችሁ ውጡ እያሉን ነው፡፡
ለጋሽ ሀገራት እጃችንን ለመጠምዘዝ ግፊት ያደርጋሉ፤ የተገዙ ባንዳዎች ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ፤ በመልካሙ እንዳንጸና፣ በአጉሉ እንድንቀጥል የሚፈልጉ እና ከለውጥ የሚገድቡ እንክርዳድ ባህሎች ያሰሩት የኅብረተ-ሰብዕ ክፍል እና ግፊትም አለ፤ ጭፍን ደጋፊዎችም ሳይገባቸው የሚደግፉ ክፍሎችም ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላልና ችግሮቻችን ናቸው፡፡
ሐ/ መፍትሔዎች
እስቲ በመጀመሪያ የሚከተሉትን ጽንሰ ሀሳቦች እንመልከት፡፡ በፍልስፍናው ዓለም ከሚዳሰሱ እና ምላሽ ከሚፈለግላቸው ሥነ-ማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፤ ሃይማኖትን እና ፖለቲካን አንድ ነጥብ ላይ ያገናኙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
1ኛ/ ከምንም በበለጠ ለዓለም የሚያሻት ፈዋሽ ክኒን ምንድን ነው? ሃይማኖትና መንፈሳዊነት? ብልህነትን እና ክሂልን የታጠቁ መሪዎች? አነስተኛ ህግጋት እና ደንቦች? ወይስ ምን?
2ኛ/ የአንድ ማኅበረሰብ ጥሩነት የሚመዘነው በየትኞቹ መስፈርቶች ተለክቶ ነው? በሀብት በንብረቱ? ደሀ ዜጎቹን በሚይዝበት መንገድ? በደረጀ ባህሉ እና ኪነ-ጥበቡ? በነዋሪዎች መካከል የእርስ በእርስ መስተጋብሮች በሚፋፉበት ሂደት? ወይስ በምን? የሚሉ ናቸው፡፡
ለሁለቱ ጥያቄዎች ሊሆኑ የሚገቡት ምላሾች፣ ብቁ መንፈሳዊ መሪ እና የመንፈሳዊነት ባህል የሚሉት ናቸው፡፡ የመንፈሳዊነት ባህል ያልኩት ያው ሳይንሱ ግብረገባዊ ባህል የሚለውን ነው፡፡ ማለትም ግብረገባዊነት የሚጸናው በሃይማኖትና በመንፈሳዊነት ነው በሚለው እምነት በመደገፍ ጭምር ማለት ነው፡፡
የአንድ ማኀበረሰብ ጥሩነት የሚለካው በኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው ግብረገባዊ ባህል አማካኝነት ነው፡፡ ይህን ሳይንሱም ስለተቀበለው ክርክር የሚኖር አይመስለኝም። ለዓለም የሚያሻት ፈዋሽ ክኒን ብቁ መንፈሳዊ መሪ ነው፤ የሚለው ላይ ግን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል፡፡
አስተዋይ የሆነ አንባቢ እንዲሁም የሶሻሊዝምን ሃይማኖት ጠልነት እና ዲሞክራሲ አልባነት፣ የካፒታሊዝምን ስግብግብነት እና ዓለማዊነት (ሴኩላርነት) ያስከተሏቸውን ሰብዕናዊ ውድቀቶች የተረዳ ሰው አባባሌን እንደሚረዳ እና እንደሚደግፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
የሥነ- ልቦናው ሳይንስም በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዱ ሰው ሊወስደው የሚገባው ክትባት ሥነ-ምግባራዊነት እና ግብረገብነት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ እኛስ እነዚህን መድሀኒቶች አግኝተናል ወይ?  ለነዚህ መሰረታዊ ነገሮች መፈጠር እና መዳበር ምን ማድረግ ይገባናል? ሳይንሱ ያዘዘውን መድኃኒት ማለትም ግብረገብነትን የያዘው ባህላችንን ለማስቀጠል ምን ማድረግ ይገባናል?
ባህላችን እና የግብረገብ መርሀችን መንፈሳዊ ነው፡፡ ዞር ዞር ብለን ዙሪያችንን እንመልከት። ኢትዮጵያውያን እምነት የለሽ አይደለንም፤ ራስ ወዳድም አይደለንም፤ ኢትዮጵያውያን ሥርዓተ-ወጥ አይደሉም፤ ግብዝም አይደሉም፤ ወስላታ እና ቀበጥባጣም አይደሉም፤ ልበ ጭለማም አይደሉም፣ ከጀግንነት የራቁ የፍርሃት እስረኛም አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከፈሪሃ-እግዚአብሔር አይወጡም። በምንም ልኬት የግብረገብ ባህላችን ሃይማኖተኛ እና መንፈሳዊ ነው፡፡
ስለዚህ የባህላችንን መንፈሳዊነት ይበልጥ ለመረዳት፣ የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስንልም ግብረገባዊ የጋራ ባህላችንን ነው፡፡ ግብረገባዊ የጋራ ባህላችን የፈጠረው የጋራ ሥነ-ልቦና እና የጋራ ሰብዕና ማለታችን ነው፡፡
መቼም የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያንን እና መስጊድን ገብተው ሳያጠኑ፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ቅርሶቻችንን እና እሴቶቻችንን ሳይቃኙና ሳያስተውሉ፣ ኢትዮጵያን ዐውቃታለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ሃይማኖትን የማይቀበሉ ሶሻሊስቶችን፣ ሊብራል ኑሮን እና ሴኩላሪዝምን የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞችን፣ ሌሎችም ያልተጠቀሱ አንድ አንድ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ አንድ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያን ዐለማወቃቸው ነው፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያን ዐናውቃትም፡፡
ኢትዮጵያን ዐውቀናትስ ቢሆን ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ በሀገራችን ባልተከሰተ ነበር። ዐውቀናትስ ቢሆን ‹‹ሃይማኖት ብቻ መንፈሳዊ፣ መንግስት ዓለማዊ›› ባላልን ነበር። ከባለስልጣናትም መካከል ሃይማኖተኞች እና መንፈሳዊያን ሊገኙ አይችሉምን? ሊባል የሚገባው ‹‹ሃይማኖት ሰማያዊ፣ መንግስት ምድራዊ ነው፤›› ነው። ይህም ቢሆን አብዛኛው ትኩረታቸውን ያሳያል እንጂ ሃይማኖት ምድራዊው ጉዳይ፣ መንግስትም መንፈሳዊው እና ሃይማኖታዊው ጉዳይ ፈጽሞ አይመለከታቸውም፤ ማለት አይደለም፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው የባህል ጉዳይ ይህን ያህል ወሳኝ ከሆነ፣ ለምን የባህል ጉዳይ አያሳስበንም? ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ግብረገብነት የጋራ ባህላችን ከሆነስ ለምን የግብረ ገብነት ጉዳይ አይበልጥብንም? ለምንስ ራሳችንን አንሆንም? ለምንስ ከባህላችን ለመውጣት እንወራጫለን?
በባህላችን ውስጥ እንክርዳድ ባህሎች እንዳሉ እኔም እገነዘባለሁ፡፡ ነገር ግን የጨዋ ግልጥነት ሳይሆን ይሉኝታ ቢስ ግልጥነት እንደሚያጠቃን ሁሉ ፈረንጅ ጣሉ ያለንን ለመጣል፣ ያዙ ያለንን ለመያዝ የምንሽቀዳደም አንዳንዶች አለን። ማድረግ ያለብን አንድ መፍትሄ በገንቢ ጽናት እሴታችን መቆም ነው፡፡ ገንቢ ጽናት ገንቢ ካልሆነ ጽናት የሚለየው የሚቆመው በእውነት ነው፤ ሰውን አይቶ አይደለም፡ለውጥ የሚያደርገው እውነትና መልካም መስሎት የያዘው አቋም ሐሰት እና መልካም ያልሆነ፣ መጥፎ ሆኖ ሲያገኘው ነው፡፡ በዚህ ላይ፣ ደጋግሞ መመርመር፣ ለለውጥ አለመቸኮል እና፣ ለለውጥ አለመለገምም ያስፈልጋል፡፡
እርግጥ ነው በግራኝ አህመድ ጦርነት ጊዜ እና በሁለተኛው የኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ ከገጠሙን ድንጋጤዎች የተነሳ (ማለትም ካልጠበቅናቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተነሳ) ቴክኖሎጂን ለማወቅ እና ለመጠቀም ካደረብን ጉጉት የተነሳ በራችንን ሥልጣኔ ለተባሉ ሥነ-ርዕዮቶች ሁሉ (ፍልስፍናዎች ሁሉ) በመክፈታችን፣ ባዕድ አስተሳሰቦች እና ባህሎች ሰርገው ሊገቡብን ችለዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ችግሩ ኢትዮጵያን ዐለማወቅ እና የተዛባ የበታችነት ስሜት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን “ትውልዱ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆኜ ከምኖር አሜሪካ ሀገር ኮባ ሆኜ ብፈጠር ይሻለኛል፤ የሚል ነው” የሚለው አባባል ግን በጣም የተጋነነ፣ የጠላት ፕሮፓጋንዳ እና የጥቂት ባንዳዎች ቃል ነው፡፡
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ጠላቶች ሁሉ እያሸነፈች በድል ተጉዛ፣ እዚህ የደረሰች እና በታሪክ ክብሯን ከፍ አድርገው የኖሩ ጀግኖች ልጆች የሞሏት ሀገር ናት፡፡ ንጥቂያ በተለይም የሉዐላዊነት ንጥቂያ ክፉ ኃጢአት እና ተኩላነት ስለሆነ አባቶቻችን አብረው ዘምተው ታግለውታል፤ እኛም እንታገለዋለን።
ለልዕለ ንጥቂያ ዘመቻውም ሆነ ለሌሎች አስተምህሮታዊ ችግሮች ተጠያቂው፣ አስተዳደጉ በት/ቤት የተበላሸበት እና በጥድፊያ እና በውክቢያ የሚኖረው የምዕራቡ ሀገራት ሕዝብ አይደለም፡፡ ኪነ-ጥበቡንም ድርሰቱንም ትምህርቱንም ገበያ መር ያደረጉት እና ለብዙኀኑ እና ለጉዳተኛው ሳይሆን ለጥቂት ከበርቴዎች የቆሙት፣ ገበያው የሚፈልገውን እንጂ፣ ገንዘብ እና ትርፍ ለሚያስገኘው እንጂ፣ እውነትን መናገር የሚቸግራቸው፣ እረኛ መሆን ሲገባቸው ራስ ወዳድ ተኩላ የሆኑበት የአመራሩ ክፍሎች ናቸው፡፡ ማለትም የፖሊሲ መሪዎች (ፖለቲከኞቹ)፣ የሐሳብ መሪዎች (ፈላስፎቹ)፣ የዕውቀት መሪዎች (አስተማሪዎቹ)፣የኪ-ነጥበብ ሰዎች ወዘተ… ናቸው፡፡  
ኢትዮጵያ ካወቋት እጅግ የምታኮራ ሀገር ናት፤ ራሳችንን መሆን አለብን፤ የራሳችንን ችግር በራሳችን ጸጋ ለመፍታት የምንጥር መሆን አለብን፤ ከወዳጅ ሀገራትም ጋር አብረን መሥራት አለብን፡፡ እኛን ከሚመስሉ ሀገራት ጋር በመተባበር ጭምር።  ራስን ለመሆንም ቁርጠኝነትን ማሳየት ይፈለግብናል፡፡
ሀገራችን ከጥንት አንስቶ ምድረ-ኩሽ፣ ኢትዮጵያ፣ ሀገረ-ሀበሻ፣ አቢሲኒያ ወዘተ… በሚሉ መጠሪያዎች እንደምትጠራ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ “ኢትዮጵግዮን” ወይም በሱባ “እንቅዮጳዝዮን” ከሚለው ቃል የመጣ እና “የግዮን ወርቅ” የሚል ትርጉም እንዳለው የሚናገሩ ጸሐፍት ብቅ ብለዋል። የቃሉ አመጣጥም “ኢትዮጵ” ከተባለ ንጉስ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንዳንዶች የ5 ሺህ፣ እንደ አንዳንዶች የ4 ሺህ፣ እንደ ሌሎች ደግሞ የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር ነች፡፡ ቀደምትነቷ ራሱ አንድ የኩራት ምንጭ ነው። የመጀመሪያው የምድሪቱ ነዋሪዎች የካም ነገድ ኩሻውያን ሲሆኑ ሀገሪቷንም ምድረ ኩሽ አሰኝተዋታል። በኋላም የሴም ነገዶች (አግአዛውያን)ተቀላቅለዋል፤ ማለትም እንደ ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች እምነት፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋን የሚናገሩ የብዙ ልሳነ-ህዝብ፣ የብዙ-ልሳነ ነገዶች (ብሔረሰቦች)፣ ልዩ ልዩ እምነትን ይዘው በመቻቻል እና በወንድማማችነት የሚኖሩ የበርካታ ሃይማኖቶች እና ማኅበረ-ሰቦች እናት ነች፡፡ ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ስሟ በተደጋጋሚ በክብር የተወሳ፣ በአምላክ የተመረጠች እና የተመሰገነች ሀገር ናት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡”
“ነብር ዥንጉርጉርነቱን፣ ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊለውጥ ይችላልን?”
“እናንት እስራኤላውያን እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?”
“ኢትዮጵያ የእውነት እና የፍትህ ሀገር ናት…ኢትዮጵያውያን ካልነኳችሁ አትንኳቸው።” የሚሉ ቃላቶች ይገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን የምታምን የሥልጡን ሃይማኖቶች ባለቤት ነች። የልጆቿ ገጸ መልክ፣  የአምልኮ መልኳና የቅድስናዋ መልክ ሳይለወጥ እንደምትኖር ተመስክሮላትና ከተመረጡት የአብርሃም ልጆች ከእስራኤላውያን ተካክላ እና ልቃም ስትመሰገን እናገኛታለን፡፡  ኢትዮጵያውያን በተክለ ሰውነታቸው፣ እግዚአብሔርን በመምሰላቸው እና በጽድቅ አኗኗራቸው  በታሪክ ሲደነቁ እናገኛለን፡፡
ኢትዮጵያውያን በመልካቸው ጠይም ዓሳ መሳዮች ወይም ቀይ ቡርቱካን መሳዮች ወይም ጥቁር ኑግ መሳዮች ናቸው፡፡ ከዚህም ጋር “ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ እና ትርጉሙም የተቃጠለ ፊት ማለት ነው፤ የሚለው ስህተት ነው፡፡” የሚሉ ግኝቶች እየወጡ ነው፡፡
ሌላውን የኢትዮጵያውያንን ገጽታ በሚመለከት የታሪክ ድርሳናት አጥጋቢ መረጃ እና ትንታኔ ባያቀርቡም (ብዙ ልንማርበት ስንችል ዕድሉን ባናገኝም) ገና ያልተፈተሹ እና ያልተጠኑ በርካታ የጥንታውያን መጻሕፍት (ድርሳናት) ክምችት መኖሩ እና የተመዘበሩም እንዳሉ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ የማንነቷ መገለጫዎች የሆኑ የሚያኮሩ ጥንታውያን ቅርሶች ባለቤት ነች። ከነዚህም ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያን፣ የፋሲል ግንብ፣ የጀጎል ግንብ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ እና የጥያ ትክል ድንጋዮች ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር በመሆኗ ለየትኛውም ኃይል ሳትንበረከክ እና ቀኝ ሳትገዛ ነጻነቷን ጠብቃ ለብዙ ሺህ ዘመናት የዘለቀች ታሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ዜማ እና የራሷ መንፈሳዊ ባህል ያላት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ናት። ስለዚህ ከታሪካችን እና ከባህላችን ጋር በርሷ ስም የእኛ ስም፣ በእኛ ስም የርሷ ስም እንደሚነሳ ዐውቀን፣ እጣ ፈንታ እና መክሊታችን በሆነችው ሀገራችን መደሰት እና መኩራት እንዲሁም ራሳችንን መሆን አለብን፡፡
ችግርም ካለ ኃላፊነቱን በጋራ እንውሰድ እና እንጀምር፡፡ ችግር ፈጣሪም የችግር ሰለባም መሆን ሳይሆን ችግር ፈቺ የመፍትሔ አካል ለመሆን እንጣር፡፡ ይህ ሁሉ እንደ ግለሰብም እንደ ኅብረተሰብም ራስን በመሆን መጀመርን የሚጠይቅ ነው፡፡
ይቀጥላል…
ይበል ደራሲ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡
ይበል አንባቢ፡- እንደ ቃልህ ይሁንልን፡፡Saturday, 11 June 2022 19:59

የፅጌረዳ ተክልና ቁልቋል

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ ራቅ ባለ በረሃ ላይ በውበቷ እጅጉን የምትኮራና የምትመካ አንድ የፅጌረዳ አበባ ነበረች። እሷን ክፉኛ የሚያማርራት ብቸኛ ነገር፣ ከአስቀያሚ የቁልቋል ተክል አጠገብ መብቀሏ ነበር።
ውቢቷ ፅጌረዳ በየቀኑ ቁልቋሏን በንቀት ስትሰድብና ስታሾፍበት ነው የምትውለው፡፡ ቁልቋሉ ግን ትንፍሽ ብሎ አያውቅም፡፡ ሁሌ ዝም ነው። በአቅራቢያዋ ያሉ ሌሎች ተክሎች፣ ፅጌረዳዋን ለመምከር ቢሞክሩም እሷ ግን ከመጤፍ አልቆጠረቻቸውም። በውበቷ እጅጉን ትመካ ነበር።
በአንድ የሚያቃጥል የበጋ ወቅት ታዲያ በረሃው ድርቅ አለ። ለተክሎቹ ጠብታ ውሃ እንኳን አልነበረም። ፅጌረዳዋ ሃይለኛውን በጋ መቋቋም ተሳናት፤ መጠውለግም ጀመረች። የሚያምሩ የአበባ ቅጠሎቿ ደረቁ።
በዚህ መሃል ድንገት ወደ ቁልቋሉ ስታማትር፣ አንዲት ድንቢጥ ውሃ ለመጠጣት መንቁሯን ቁልቋሉ ላይ ሰክታ ተመለከተች። ለአፍታ ድንቢጧን መሆኗን አማራት፡፡ በመጨረሻ ግን በሃፍረት ተሸማቅቃ ቁልቋሉ ጥቂት ውሃ እንዲያጠጣት  ጠየቀችው። ደጉ ቁልቋልም ከመቅፅበት ተስማማ፡፡ በዚያ አደገኛ የበጋ ሙቀት ሁለቱንም (ድንቢጧንና ፅጌረዳዋን) በውሃ ጥም ከመሞት አተረፋቸው፡፡ ጉርብትና ማለት ይኼ ነው፡፡

Saturday, 11 June 2022 20:00

ታሪክ - ለልጆች

 ውድ ልጆች፡- ከዚህ ታሪክ የምንማረው ቁምነገር፣ ማንንም በቅጡ ሳናውቅ ገጽታውን ብቻ አይተን ወደ ንቀትና ማሾፍ መግባት እንደሌለብን ነው። እጃቸው ላይ ልንወድቅ እንችላለንና፡፡

                   የወርቅ እንቁላል የምትጥለው ዶሮ

           ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ገበሬ በየቀኑ አንድ የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዶሮ ነበረችው። እንቁላሉ ለገበሬውና ሚስቱ የዕለት ፍላጎታቸውን የሚያሟላ በቂ ገንዘብ ያስገኝላቸው ነበር። በዚህም ባልና ሚስቱ ለረዥም ጊዜያት ደስታቸውን እያጣጣሙ ኖሩ፡፡
አንድ ቀን ገበሬው እንዲህ ሲል አሰበ፤ “ለምን በቀን አንድ የወርቅ እንቁላል ብቻ እናገኛለን? ሁሉንም የወርቅ እንቁላሎች በአንዴ አውጥተን ለምን ብዙ ገንዘብ አናገኝም?”
ገበሬው ይህን ሃሳቡን ለሚስቱ አማከራት። ሚስቱም ሳታቅማማ ሃሳቡን ተቀበለች፡፡
ከዚያም በነጋታው ዶሮዋ የወርቅ እንቁላሏን ስትጥል፣ ገበሬው የተሳለ ቢላዋ ይዞ እየጠበቃት ነበር። ወዲያው አረዳትና እየተጣደፈ ሆዷን ከፈተው፤ የወርቅ እንቁላሎች  በገፍ አገኛለሁ በሚል ተስፋ። ሆዷን ሲከፍተው ግን ከአንጀትና ከደም በቀር ምንም አላገኘም፡፡
ይሄኔ በጅልነቱ የፈጸመውን ስህተት ተገንዝቦ፣ ከእጁ መዳፍ ላመለጠው ሃብት ማልቀስ ጀመረ። ገበሬውና ሚስቱ ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየደኸዩ መጡ። ያጡ የነጡ ድሆችም ሆኑ።  አይ መጃጃል! ያሳዝናል!
ልጆች፡- ከዚህ ታሪክ የምንማረው ቁምነገር፣ በደንብ ሳናስብ፣ ሳናገናዝብና ሳንመክር  ምንም ድርጊት መፈጸም እንደሌለብን ነው። ስግብግብነትም ለጥፋት እንደሚዳርግ ከገበሬው ተምረናል፡፡


Page 3 of 611