Administrator

Administrator

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከ'ዘ ሪፖርተር' ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፣ በቅርቡ የታጠቁ ኃይሎች የመሠረቱትን "የህልውና ጥምረት" አጥብቀው ተችተዋል። አምባሳደሩ እንደተናገሩት፣ ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት ለተጨማሪ ጦርነትና ውድመት ጥሪ ከማቅረብ ያለፈ ምንም ጠቃሚ አቅጣጫ አላሳየም። አሜሪካ ይህንን አካሄድ እንደ መፍትሔ የማታየው መሆኑን ያስታወቁት አምባሳደሩ፣ በተለይም በሲቪል አየር ማረፊያዎችና በሰላማዊ ተጓዦች ላይ የሚሰነዘሩ ዛቻዎች "እጅግ ከባድ ስህተት" መሆናቸውን በመጠቆም፣ የጥምረቱ መሪዎች የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ አሜሪካ በግጭት ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል ድርድርን የማመቻቸት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። ቀደም ሲል በታንዛኒያ ዳሬሰላም በመንግሥትና በበኦ*ነግ ሸኔ (OLA) መካከል የተደረገው የሰላም ጥረት ባይሳካም፣ የውይይቱ ፍላጎት ግን አሁንም እንዳለ ተናግረዋል። ሆኖም ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በውጭ አካላት አስገዳጅነት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ራሳቸው በሚያደርጉት ስምምነት መሆኑን አስምረውበታል። ከአዲሱ የሕወሓት አመራር ጋር ቀደም ሲል ተደጋጋሚ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም፣ መስከረም 13 ቀን ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ግን በሕወሓት በኩል በተደረገ ምርጫ ምክንያት መነጋገር አለመቻሉን አብራርተዋል።
በመጨረሻም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት የኤርትራና የግብፅ ተሳትፎ እንዳለበት ከፌደራል መንግሥት የሚነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ፣ አሜሪካ በቀጠናው ሰላምና ደህንነት ላይ ያላትን የዲፕሎማሲ ሥራ አጠናክራ መቀጠሏን አምባሳደሩ ገልጸዋል። ይህም ጉዳይ በዋሽንግተን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በቅርበት ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ሁሉም ወገኖች ለጦርነት በር ከመክፈት ይልቅ ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንዲመጡ አሳስበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከትግራይ ዲያስፖራና ከኤርትራ ለውጥ ፈላጊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነት መልሶ እንዳይቀሰቀስ ከማንም በላይ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በእነ ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት አመራር ይህንን የሰላም ፍላጎት እንደ ፍርሃት በመቁጠር፣ ከሻዕቢያና ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ሀገርን ለማተራመስ ያለመ 'ፅምዶ' የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ ጦርነቱ በአማራና ዓፋር ክልሎች እንዲጀመር አቅዶ ሲሰራ እንደነበር አጋልጠዋል።
የህወሓት አመራር በትግራይ ሕዝብ ዘንድ የነበረውን ድጋፍ ማጣቱን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፣ ቡድኑ በመከላከያና በትግራይ የሰላም ኃይሎች በደረሰበት ጠንካራ ምት መቐለንና ሌሎች አካባቢዎችን ለቆ ለመውጣት መገደዱን ተናግረዋል። የቡድኑ አመራሮች የተበታተኑ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ወደ ኤርትራና ሱዳን ሲሸሹ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመቐለና አካባቢዋ በቁጥጥርና ክትትል ስር ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል። በአሁኑ ወቅት በተምቤንና አክሱም በረሃዎች የተበታተኑ ታጣቂዎች በንጹሐን ላይ ጥቃት እያደረሱ በመሆናቸው የማጥራት እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል።
የፌዴራል መንግሥት ክልሉን ከገባበት ችግር ለማውጣትና የአስተዳደር ክፍተት እንዳይፈጠር የባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙንና የማርሻል ፕላን አዘጋጅቶ ወደ ተግባር እየገባ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። ይህ ባለአደራ አስተዳደር የሕዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ተፈናቃዮችን መመለስ፣ አስቸኳይ እርዳታ ማዳረስና የወደመውን ኢኮኖሚ ማንሰራራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል። በተጨማሪም መከላከያ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሕዝቡን ያሳተፈ የአካባቢ ምርጫ እየተካሄደ እንደሚገኝና ፖሊስም ወደ ሥራው መመለሱን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ዲያስፖራ የፌዴራል መንግሥት የጀመረውን የማረጋጋት እርምጃ እንዲደግፍና ለጥፋት ተጠያቂ የሆኑትን አመራሮች እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርበዋል። ለኤርትራ ለውጥ ፈላጊዎች በሰጡት ማብራሪያም፣ አገራቸውን ለጥፋት ከዳረገው ኃይል ጋር የሚያደርጉትን ትግል አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመምከር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን ከመከላከል ባለፈ ኤርትራን የመውረር ምንም ዓይነት ዓላማ እንደሌለው አረጋግጠውላቸዋል።
Tikvah Ethiopia-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራው ገዥ ቡድን (ህግደፍ) የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሆኑን አቁሞ ለቀረበለት የሰላም እና የጋራ ልማት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ የሚከተለው መዘዝ እጅግ መራራና ከባድ እንደሚሆን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ።
ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ አገዛዙ የራሱን ሀገር እና ሕዝብ የልማት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የቀጣናው የጥፋት ኃይሎች መናኸሪያ እና መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። "የራሱን ችግር ያልፈታ ኃይል ለሌላው ሊተርፍ አይችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውጭ "አይዞህ ባዮች" ጥይት ከማቀበል ባለፈ የራሳቸውንም ችግር መፍታት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ ሥርዓቱ ከልማት እና ከትብብር ይልቅ ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳን መምረጡ ፈጽሞ እንደማያዋጣው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
በአገዛዙ ምክንያት በኤርትራ ላይ የደረሰውን ዘመናት የተሻገረ ውድቀት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት በንግድ እና በኢንዱስትሪ ደምቀው የነበሩት ከተሞቿ ሙሉ በሙሉ መደብዘዛቸውን አብራርተዋል። በአንድ ወቅት ከ300 በላይ ንቁ ፋብሪካዎች የነበሯትን ኤርትራን ወደ ባዶነት ከቀየረው እና ውቢቷን አስመራን አንሳ እንድትገኝ ካደረገው ሻዕቢያ ጋር መተባበር የጥፋት ጥግ መሆኑንም አመልክተዋል። የሕዝቦችን የወደፊት ተስፋ የሚያጨልመው ይህ የጥፋት መንገድ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባውም አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ለሰላም፣ ለትብብር እና ለጋራ ልማት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ልማትን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆንን የመረጠው የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ የልማት አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ሻዕቢያ የውጭ ኃይሎችን ተማምኖ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብሎ በጥፋት መንገዱ የሚገፋበት ከሆነ፣ በመጨረሻ የሚከተለው መዘዝ እጅግ የከፋ እንደሚሆን በድጋሚ አሳስበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

 "በቤት ኪራይ ተሰቃየን:: መሄጃ አጣን:: እሺ መሬት ስጡን:: አዲሱ ትውልድ የት እንግባ" እያለች ታለቅሳለች:: ይህ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው::

1968 ላይ መሬት ላራሹ ተብሎ አዋጅ ታውጆ ትውልዱ መሬት አገኘ:: ከዚያ ወዲህ መሬት የሚባል ነገር አልተሰጠም:: መንግሥት መሬትን የሚያህል ሀብት አንቆ ይዞ ሊደባ^ደብ የሚሄደው የግለሰብ አከራዮች ጋር ነው:: መንግሥት ብር፣ መሬት፣ ቀረጥ፣ ሕግ ሁላ ይዞ ያልቻለውን መንግሥታዊ ሪል ኢስቴት ማለትም ኮንዶሚኒየም ሳይሰጥ... የግል አልሚዎች ካላሟላችሁ ይላል::

መንግሥት መሬትን በአግባቡ ማደል ሲገባው በሊዝ ያከራያል:: ትውልዱ ይሰቃያል:: ቢቸግራቸው ተሰደው ለፍተው መጥተው የወጠሩትንም ላስቲክ ያፈርሱባቸዋል:: መንግሥት መሬት ይስጥ፣ ኮንዶሚኒየም ይገንባ፣ የግሎችም የተረፈውን ይሸፍኑ::

በዋለ ባደረ ቁጥር ትውልዱ እየጨመረ የቤት ግንባታ ባለበት ቆሞ ወይም ቀንሶ እንዴት ሊጣጣም ይችላል? መጠለያ መሠረታዊ ፍላጎት ስለሆነ ወደድንም ጠላንም አብዮት ያስነሳል:: ምግብ መሠረታዊ ስለሆነ አብዮት ያስነሳል::

Abdulkadir Hajj Nureddin

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ኢትዮጵያን ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ለማላቀቅ በተደረገው ትግል ከፍተኛ የአርበኝነት ተግባሩን የተወጣ የዚህች አገር የቁርጥ ቀን ደራሽ ነበር፡፡ ዮፍታሔ በኢትዮጵያ ቴአትር አለም ውስጥ ፋና ወጊ የሆነ ግዙፍ አስተዋጽኦ አበርክቶ ያለፈ ነው፡፡ ድንቅ ባለቅኔ ነበር፡፡

አንደበተ-ርዕቱእ የአደባባይ ዲስኩረኛም ነበር፡፡ ሐገር አስተዳደሩም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከዋክብት ልጆችሽን ጥሪ ብትባል ዮፍታሔ ንጉሴ አንድ… ብላ ትጀምር ነበር፡፡ ዮፍታሔ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓም ከዚህች አለም በሞት ተለየ፡፡ ቀብሩም ባለወልድ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ፡፡

ከ70 አመታት በኋላ አጽሙ ወጥቶ ወደ ትውልድ ሐገሩ ጎጃም ሙዛ ኤልያስ ሔዶ በክብር ተቀመጠ፡፡ በፎቶው ላይ የሚታየው ዮፍታሄ እና ልጁ ነው።

#ታሪክን_ወደኋላ

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ሉዓላዊነትና ደኅንነት ላይ አደጋ በሚደቅኑ ኃይሎች ላይ እየወሰደው ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ተገቢና ሕጋዊ መሆኑን ገለጹ። ሚኒስትሩ በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ያደረሱ ተገንጣይ ኃይሎች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ መንግሥት ሀገራዊ ሉዓላዊነቱን ለማስከበር የወሰደው የአጸፋ እርምጃ ፍጹም ትክክለኛ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል። አያይዘውም ግጭቱ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዳይዛመት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትሠራና አሸባሪነት በግልጽ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር መሆኑን አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ በሀገሯ ውስጥ የውክልና ጦርነት በከፈቱባት ቡድኖች ላይ የምትወስደውን እርምጃ አሜሪካ እንደምትደግፍ እና ለዚህም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ሂደቱን ለማጓተት መሥራቱ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ዳግም መነሳቱ እንዲሁም ለተቸገረው የትግራይ ሕዝብ የሚላከውን ሰብዓዊ እርዳታ ለታጣቂዎቹ ቀለብ ማዋሉ በምርመራ መረጋገጡ የምዕራባውያንንና የለጋሽ ሀገራትን እምነት እንዲያጣ አድርጎታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
#No_more_meat እና #Boycott በሚል ወይም ዋጋ በመተመን የሚቀንስ ሸቀጥ አለ ወይ? እኔ አይመስለኝም።
የዋጋ ጉዳይ ውስብስብ ነው። የIPhone ስልክ ከሌላው ስልክ ይልቅ ውድ የሆነው ለምን ይመስልሃል? ይህንን ቦይኮት በማለት ዋጋ የምታስቀንስ ይመስልሃል? እኔ አይመስለኝም።
ዋጋን በአብዛኛው የሚወስነው የገበያው አቅርቦትና ፍላጎት ሚዛን ነው።
የዋጋ መብዛት አንዳንዴ ፍላጎትን ይቀንሳል። እንዲህ ያሉ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ፍላጎት #Price_Elastic ነው ይባላል። ሁሉም ፍላጎት ግን እንደዚያ አይደለም።
የስጋ ዋጋ ከፍ ያለው ከፋይ ስላለ ነው። በውድ ዋጋ ስጋ የሚበሉ ወይም ውስኪ የሚጠጡ ፍላጎታቸው ከዋጋ ጋር የሚዋዥቅ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ለዋጋ ግድ የሌለው ፍላጎት #Price_inelastic_Demand ይባላል።
የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በመንግስት ቢተመንም የጭማሪ ዋጋው ከፍ ያለው የበዛ ፍላጎት ስላለ ነው። የቲማቲም ዋጋ ከፍ ዝቅ ሲል አላየህም? ለምን ይመስልሃል? አቅርቦቱ ሲበዛ ምርቱ ቶሎ ካልተነሳ ይበላሻል። ይህንን መበላሸት ቴክኖሎጂ ተጠቅመህ ከገታኸው የቲማቲም ዋጋ አይዋዥቅም።
የስጋ ዋጋ በአንዳንድ ስጋ ቤቶች በኪሎ 6000 ብር ደርሷል። አንዳንዱ ጋ በኪሎ 4400 ብር ነው። አንዳንዱ ጋ በኪሎ 2200 ብር ነው። በኪሎ 1800 ብርም ብዙ ቦታ አለ። በሸማቾች ጋ ደግሞ በኪሎ 1200 ብር ነው።
ይህ ሲታይ ሸማቾች ሱቅ ውስጥ የሚሸጠው ስጋ ቶሎ የሚያልቅ ይመስልሃል አይደል? ግን ነገሩ እንደዚያ አይደለም። በውድ ዋጋ የሚሸጡት ቶሎ ሲጨርሱ የሸማቾች ስጋ ግን ይቆያል? ለምን? ስጋው አያምርማ!
የገና ጾም እየመጣ ነው። አሁንም የጽጌ ጾም አለ። እስኪ ስጋ አንበላም ተብሎ ዋጋ ይቀንስ እንደሆን እናያለን። የስጋ ዋጋ እንዲቀንስ ገበሬው በቀላል ዋጋ በሬ ማድለብ አለበት። የበሬ መኖ ወጪው ቀላል እየሆነ አይደለም። በሬ ማድለብ እንደ ድሮው የግጦሽ ሳር ላይ በነጻ ለቅቀህ የምታደልበው አይደለም። በሬዎቹ የተመጣጠነ መኖ፣ ጤፍ፣ ምስር፣ ድርቆሽ የመሳሰሉትን በልተው ነው የሚደልቡት። በዚያ ላይ ከቤት ውስጥ አይወጡም። ይህንን ጅሩ እና አዴት የመሳሰሉት ቦታ ሄዶ ማየት ነው።
በቅርቡ በሥራው ላይ ያለ ሰውን ስለበሬ ዋጋ እና ከአንድ በሬ ስለሚገኝ የኪሎ ብዛት ጠይቄ ነበር። የአንድ ጥሩ በሬ ዋጋ እስከ 300,000 ብር ይደርሳል። ኪሎውም 120 ኪሎ አካባቢ ይሆናል። ይሄ ማለት ከምላስ ሰንበር ውጪ በኪሎ 2,500 ብር ማለት ነው። ደካማ በሬ ደግሞ በአማካይ በ120,000 ብር ይገኛል። ይህ ማለት በኪሎ 1000 ብር ማለት ነው። የስጋው ዓይነት ግን ይለያያል። እንግዲህ እንደምርጫና እንደዓቅም መወሰን ነው።
ስጋ ቤት ከፍተው ከስረው የዘጉ ብዙ አሉ። ለሀብታሞች በውድ ዋጋ ስጋ የሚሸጡ ደግሞ እንኳን ሊዘጉ ጭራሽ እያስፋፉ ነው። ከቻልክ ለሀብታም ሽጥ የሚባለው ለዚህ ነው።
ከዚህ በፊት Sell to the riches. The riches are in the niches ብለን የለ?
ስጋ መብላት ግዴታ አይደለም። ህንዶች ስጋ አይበሉም። ይኸው ግን ያለምንም ቅሬታ በሰላም ይኖራሉ።
አበላልን ሰልጠን ማድረግ ለጤና ይጠቅማል። የሚበላ ቅጠላ ቅጠልና ጥራ ጥሬ ሞልቷል። ወደዚያ ማዘንበል የስጋ ፍላጎትን ይቀንሳል። ይሄ በሂደት ምናልባት የመደበኛ ስጋ ቤቶች ውስጥ የሚሸጥ የስጋ ዋጋን ሊያስቀንስ ይችላል። የውድ ስጋ ቤት ዋጋን ግን ንክች አያደርገውም።
ይልቅ እስኪ እንቁላል ለምን አይቀንስም? ብለህ ጠይቅ። ምስር ለምን አይቀንስም? ውስኪ ለምን አይቀንስም?
በውድ ዋጋ ስጋ የሚበሉ ሰዎች ዋጋ ጨመረም አልጨመረም ስጋ መብላታቸውን ይቀጥላሉ። የውድ ስጋ ቤቶች ደንበኞች ለዋጋ የማይጨነቁ ናቸው። በዚህ ምክንያት የውድ ቤቶች ዋጋ ይቀንሳል ብዬ አልጠብቅም።
ለማንኛውም አድማ ሊመታ የሚገባበትና የሚያስጨንቀን ብዙ ጉዳይ አለ። ስጋ ልክ እንደ ምስር፣ እንደ ፓስታ፣ እንደ ሽንኩርት፣ እንደዘይት ያለ ሸቀጥ ነው። ዋጋው የሚወሰነው በገበያ እንጂ በአድማ አይደለም።
Get Toughe Zer
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን የዩክሬን ጦርነትን በራሳቸው ፍላጎት መሠረት ለማጠናቀቅ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከዶናልድ ትራምፕ እና ከቻይናው ፕሬዝዳንት ከሺ ጂንፒንግ ጋር የሶስትዮሽ ስብሰባ እንዲደረግ ሀሳብ አቀረቡ። ይህ ውይይት ከህዳር 18-19 በቻይና ሼንዘን ከተማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጎን ለጎን ሊካሄድ እንደሚችል ተነግሯል። ሆኖም በዚህ የታቀደው ስብሰባ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና የአውሮፓ መሪዎች ፈጽሞ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ተደርጓል።

ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን የቀረበውን ግብዣ መቀበላቸው የታወቀ ነገር የለም፤ ቤጂንግ በበኩሏ ዋሽንግተን ከፈቀደች ስብሰባውን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። የሩሲያ መንግሥት ውይይቶቹ አሁንም በጅማሬ ላይ ያሉ መሆናቸውን እና በስብሰባው አጀንዳ ላይ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ ተናግሯል። ይህ ሃሳብ የመጣው በአሜሪካ አደራጅነት የሚደረጉ የሰላም ጥረቶች እየደከሙ ባለበት እና በዋሽንግተንና በኪየቭ መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ ባለውበት ወቅት ነው።

ለሩሲያ ይህ ጉባኤ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን ከማጠናከሩም በላይ፣ ከዩክሬን እና ከአውሮፓ ተሳትፎ ውጭ ከአሜሪካ እና ከቻይና ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ትልቅ ዕድል ይሰጣታል። በሌላ በኩል ቻይና እንደ ሰላም አስታራቂ ራሷን ማቅረብ እና ከአውሮፓ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ማስቀጠል መካከል ስስ ሚዛን ለመጠበቅ ትሞክራለች። አጠቃላይ የቀረበው ሃሳብ አሁንም በእርግጠኛነት የታወቀ ነገር የሌለበት ሲሆን፣ መጪው ስብሰባ ራሱ ጦርነቱን ሙሉ በሙሉ ያስቆማል ተብሎ አይጠበቅም።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ውጊያና የሕክምና አቅርቦት እጥረት አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ አብዛኞቹ ሆስፒታሎች ዳግም ወደ ሥራ መመለሳቸውን ይፋ አደረገ። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምክትል ቃል አቀባይ ፋራህን ሃቅ ሐሙስ ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የጤና አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ተጨማሪ መድኃኒቶችና የሕክምና አቅርቦቶች አሁን ላይ በመጓጓዝ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ፣ በሰሜን ትግራይ፣ በአፋር እና በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም አለመረጋጋት የሚታይበት በመሆኑ በሲቪሎችና በመሠረተ ልማቶች ላይ አደጋ እንደደቀነ ተመድ ገልጿል። ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሰብአዊ እርዳታ የማድረስ ሂደቱን ውስብስብ ቢያደርገውም፣ ተመድ እና አጋሮቹ ወደ ክልሉ ተጨማሪ እርዳታዎችን ለማስገባት ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተመላክቷል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚቀጥሉትን 6 ወራት የሚቆይ የባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን አስታወቀ። በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም በሕወሐት ዕንቅፋት ምክንያት ሳይሳኩ መቅረታቸው ተገልጿል። የትግራይ ሕዝብ ከግጭት አዙሪት ወጥቶ ሰላሙን እንዲያገኝ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጸንቶ እንዲኖር ይህ አስተዳደር መቋቋሙ ተነግሯል።

ይህ አዲስ አስተዳደር በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ፣ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መጠገን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ ዋና ዋና ሥራዎቹ አድርጓል። እንዲሁም የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማስቀጠል የትኩረት አቅጣጫው ናቸው።

አስተዳደሩ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ማከናወን እና በ6 ወር ውስጥ ነጻና ግልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል። እንቅስቃሴዎቹም ሙሉ በሙሉ ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጥ መመሪያ እና ክትትል የሚመሩ ይሆናሉ።

ለዚህ የሽግግር ወቅት ሥራ የሚከተሉት ዋና አስፈጻሚዎች ተሾመዋል፦

አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ - የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ

ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወ/ሥላሴ - የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ

ብ/ጄ ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ - የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ

አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወ/ሥላሴ - የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ

ዶክተር ሽሻይ አማረ - የመቐለ ከተማ ከንቲባ

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Page 7 of 844