Administrator

Administrator

መመኘት አልተከለከለም አይደል?

 ጊዜው በትክክል ትዝ አይለኝም። ግን የአዲስ ዓመት በዓል ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። አንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ለአንድ በሥራ ላይ ለነበረ የትራፊክ ፖሊስ ጥያቄ ያቀርብለታል። “የአዲሱ ዓመት ዕቅድህ ምንድነው?” የሚል። ትራፊክ ፖሊሱም ሲመልስ፤ “እኔ እንኳን የግል ዕቅድ የለኝም፤ መ/ቤቴ ዕቅድ ካለው ግን እሱን ለመፈጸም ዝጁ ነኝ” አለ። የእኔም ነገር እንዲሁ ነው የሆነው ዛሬ። የመጀመሪያ ሃሳቤ በራሴ የአዲስ ዓመት ዕቅድ ወይም ምኞት ዙሪያ የሚያጠነጥን ፅሁፍ መከተብ ነበር፡፡ በኋላ ግን የራሴን ትቼ  በአዲሱ ዓመት ለአገሬ የምመኘውን ብተነፍስ ወደድኩ። “በመጀመሪያ የመቀመጫየን” አለች - እንደተባለው መሆኑ ነው።
እነሆ አሮጌውን ዓመት አጠናቅቀን አዲሱን (2016) ዓመት ልንቀበል ከ72 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ነው የቀረው። እንዳለመታደል ሆኖ 2015 ዓ.ም ከቀደሙት ሁለት ዓመታት የባሰና የከፋ እንጂ የተሻለ ሆኖ አላለፈም። የተሻለ ዓመት ልናደርገው አልቻልንም ቢባል ይሻላል (ለእውነት የቀረበ ነውና!) ለምን ቢሉ? ተጠያቂው ራሳችን ነንና!!
ከሁለት ዓመቱ የህወሃትና የፌደራል መንግስቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ፣ በስንት ፀሎትና በእነ አሜሪካ ተፅዕኖና ግፊት ሳቢያ እፎይ ያልን ቢመስለንም፤ ወዲያው ግን ወደ አዲስ ጦርነት መሸጋገራችን፣ ትልቁ  የአገራችን - (የክፍለ ዘመኑ) ትራጄዲ ነው ማለት ይቻላል።
አሁንስ በአማራ ክልል እንደ ዘበት ከገባንበት ጦርነት እንዴት ነው የምንወጣው? እንዴት ነው በዘላቂነት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት የምንፈጥረው? አሁንም ለሰላም ድርድር እነ አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት መምጣት አለባቸው ማለት ነው? ምክንያቱም በራሳችን መንገድ በውይይትና በድርድር የመፍታት አዝማሚያ በፍፁም እየታየ አይደለም።
በሌላ በኩል አሜሪካ ደግሞ ስስ ብልታችንን ጠንቅቃ አውቃዋለች። (አንዴ ወደ ጦርነት ከገባን፣ በቀላሉ እንደማንወጣ ገብቶታል) ስለዚህም የፕሪቶሪያው የሰላም ድርድር ዓይነት የአጋፋሪነት ሚና ለመውሰድ የቋመጠች ትመስላለች። በእኛ በኩል በማንም አደራዳሪነት ይሁን ዜጎችን በከንቱ ከሚፈጀውና ለሰቆቃ ከሚዳርገው ዘግናኝ ጦርነት ብንወጣና ሰላምና መረጋጋት ቢሰፍን ባልጠላን ነበር። ክፋቱ ግን እነ አሜሪካ የገቡበት ነገር ጣጣው ማብቂያ የለውም፡፡ ሽምግልና ብለው የባሰ ቀውስና ብጥብጥ ፈጥረውም ሊወጡም ይችላሉ፡፡ እነ ኢራቅ… ሊቢያ… አፍጋኒስታን… ሶሪያ… ምን እንደሆኑ አይተናል፡፡
የፈረሱ አገራት ነው የሆኑት። እውነታው ይህን ቢመስልም ቅሉ፣ በራሳችን ጊዜና በራሳችን አቅም ከጦርነቱ ወጥተን ወደ ሰላም ድርድር መግባት እስካልቻልን ድረስ ሌላ አማራጭ አይኖረንም - የአሜሪካና አጋሮቿን የሰላም ድርድር ሃሳብ ከመቀበል ውጭ። (ወደን ሳይሆን ተገደን!) ያኔ ደግሞ አዲስ ወጥመድ ውስጥ ገባን ማለት ነው።
በነገራችን ላይ በአሜሪካ አጋፋሪነት የተካሄደው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት፣ ጦርነቱን በማቆሙ እፎይ ብንልም፣ የምንከፍለውን ዋጋ (ዕዳችንን) ግን ገና በቅጡ አላወቅነውም። (Free Lunch የሚባል ነገር የለማ!) እናም በጦርነት መፍትሄ እንደማይመጣ እያወቅን፣ በማያዋጣ መንገድ ከመባከን የሰላምን አማራጭ መውሰድ ብልህነት ይመስለኛል። ወደድንም ጠላንም ከጦርነትና እርስ በርስ ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥተን፤ ወደ ሰላማዊ ውይይትና ድርድር መግባት  ይኖርብናል - በእነ አሜሪካ ሳይሆን በራሳችን መንገድ።
የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባህል በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ግን በሂደት ባህል ይሆን ዘንድ ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ጨክነንና ቆርጠን ዛሬ - አሁኑኑ ልንጀምረው ይገባናል። ከዛም የሁልጊዜ ልምምዳችን ማድረግ፡፡ በትጋትና በፅናት ከቀጠልንበት፤ ያለጥርጥር በሂደት ባህል እናደርገዋለን፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ሌላ መፍትሄ የለንም። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ችግሮችና አለመግባባቶች ሁሉ ጦር እየሰበቅን፤ የጦርት ነጋሪት እየጎሰምን መቀጠል አንችልም። እውነት ለመናገር አቅሙ የለንም። የአገሪቱ ወገብ ተሰብሯል። ህዘቡ በጦርነትና ተያያዥ መከራዎች ጫንቃው ጎብጧል። ተጨማሪ ጦርነትም ሆነ ግጭት የመቋቋም አቅሙም ሆነ ችሎታው ጨርሶ የለንም!! እንደ አገር መፍረስ ካልፈለግን በስተቀር እስቲ ከሁለት ቀናት በኋላ በምንቀበለው አዲስ ዓመት ለአገሬ የምመኘውን ልነቁጥ እነሆ፡-
በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የጦርነትና ግጭት ወሬ የማንሰማበት፤
የዜጎች ግድያና መፈናቀል፤ እንግልትና ሰቆቃ በዘላቂነት የሚያከትምበት፤
ፖለቲከኞችም ይሁኑ አክቲቪስቶች ጦርነትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ተንኳሽ ቃላትን መወራወር በህግ የሚከለከሉበት፤
ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረውና ሰርተው የመኖር ህገመንግስታዊ መብታቸው የሚረጋገጥበት፤
የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበትና የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፤
የፖለቲካ ልዩነቶችን በሃይል አማራጭ ሳይሆን በውይይትና በድርድር የመፍታት ልምምድ የሚጀመርበት፤
ለኢኮኖሚ ስብራቶቻችንንና ለማህበራዊ ቀውሶቻችን ልሂቃኖቻችን ተግባራዊ መፍትሄ የሚያፈልቁበት ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በታጣቂዎች የማይታገቱበት፤  ዘመን እንዲሆን እሻለሁ።
2016 ዓ.ም የሰላምና መረጋጋት፤ የፍቅርና አንድነት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
ቅድም እንደጠቀስኩት ለአዲሱ ዓመት የራሴ ዕቅድና ምኞት ስለሌለኝ ሳይሆን አገራችንና ህዝባችን ተራራ የሚያህል ችግርና መከራ ተጋፍጠው የግል ጉዳይን ማንሳት ቅንጦት መስሎ ስለታየኝ ነው። በእርግጥም በውዱ ጋዜጣ ቦታ ላይ ያለውም በዚህ ክፉ ጊዜ ስለግል የአዲስ ዓመት ዕቅድና ምኞት ቅንጦት ነው የሚሆነው። ስለዚህም ተዘርዝሮ ከማያልቀው የአገራን አያሌ ችግሮችና መከራዎች መካከል አንገብጋቢዎቹን እያነሳሁ፤ በአዲሱ ዓመት እንዴት እንዲለወጥልን እንደምሻ ወይም እንደምመኝ የበዓል ሃሳቤን ልገልፅ እወዳለሁ።

ሊንኬጅ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ማዕከልና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች ድርጅት፣ በመጪው ህዳር ወር፣ የፊልም ፌስቲቫል በትብብር እንደሚያካሂዱ ተገለጸ።
“አጋርነት ለዘላቂ የፊልም ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫል፤ ከህዳር 23 እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ለ8 ቀናት፣ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
የፊልም ፌስቲቫሉንና በመንግስት አካላትና በግል ድርጅት የተፈጠረውን አጋርነት አስመልክቶ አዘጋጆቹ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ፣ በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሊንኬጅ የኪነጥበብ ስራዎች ማዕከልና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት፣ የፊልም ፌስቲቫል በትብብር ለማዘጋጀት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው   የተጠቀሰ ሲሆን፤ የዚህ አጋርነት ዋነኛ ዓላማው የኢትዮጵያን የፊልም ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና ለአገራዊ የገፅ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ዓላማን ያደረገ ነው ተብሏል - አጋርነቱ፡፡
“ይህ አጋርነት  ከሚኖሩት ዘርፈ ብዙ ክንውኖች አንዱ፣ በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገውን 18ኛውን የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል (ኧርዞፕያ)ንና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቱን የፊልም ፊስቲቫልን በድምር ይመለከታል፡፡” ብለዋል - አዘጋጆቹ በመግለጫቸው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ፊልም መታየት ከጀመረ 100ኛ ዓመት መሙላቱ ደግሞ ለፊልም ፌስቲቫሉ እራሱን የቻለ ድምቀትና አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡  የፊልም ፌስቲቫሉን በትብብር ለማዘጋጀት የመንግስት አካላትና የግል ድርጅት የፈጠሩት ይህ አጋርነት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን እንደማይቀር የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች፤ መሰል አጋርነቶች መቀጠላቸው ለኪነጥበቡ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡•  ድርጅቱ ለቤት ኪራይ ብቻ በወር 250ሺ ብር እያወጣ ነው ተባለ

•  ከአስተዳደሩ ቦታ ቢሰጠውም በፋይናንስ እጥረት ግንባታ አልጀመረም  

ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደወትሮው ቢሆን ኖሮ፣ ለሚደግፋቸው ከ1ሺ100 በላይ ችግረኛ ወገኖች ለዓመት በዓል ዱቄትና ዘይት እንዲሁም የበሬ ቅርጫ የመሳሰሉ የአውዳመት ፍጆታዎችን በያሉበት ያከፋፍላቸው ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ የተለመደውን ችሮታ ማድረግ አለመቻላቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ይናገራሉ፡፡

ይህን ችግራቸውን ያማከሩት ጋዜጠኛ ተሻለ ጣሰው፣ በመጨረሻ ሰዓት፣ በሬ ገዝቶና ሙሉ ወጪውን ችሎ፣ አዲስ ዓመትን ከ100 በላይ ከሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ጋር ምሳ እየበላን በደስታ እንድናሳልፍ አድርጎናል ሲሉ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የድርጅቱ መሥራች ይህን የተናገሩት፣ በዛሬው ዕለት፣ ኮተቤ በሚገኘው የሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ግቢ ውስጥ ተረጂ ወገኖችን ምሣ የማብላት ሥነስርዓት ከተከናወነ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡

የበጎ አድራጎት ሥራ ከጀመረ 23 ዓመታትን ያስቆጠረው ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአሁኑ ወቅት ከ1ሺ100 በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 650 ያህሉ ህጻናት መሆናቸው ታውቋል፡፡

ድርጅቱ የራሱ የሆነ ማዕከል ስለሌለው ለሚደግፋቸው ወገኖች የቤት ኪራይ ብቻ  በወር 250ሺ ብር እንደሚያወጣ መሥራቿ ይናገራሉ፡፡ ይህን ችግራቸውን የተረዳው የአዲስ አበባ አስተዳደር ታዲያ ዝም አላላቸውም፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማና በሃያት አካባቢ በአጠቃላይ  4ሺ ካሬ ቦታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ቦታውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ግንባታውንም ለማከናወን በወቅቱ ቃል መግባቱን ነው ወ/ሮ ሙዳይ የሚናገሩት፡፡ ሆኖም አስካሁን ግንባታው ባለመጀመሩ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል ብለዋል፡፡

የራሳችንን ማዕከል በፍጥነት መገንባት ብንችል ቢያንስ የቤት ኪራይ ወጪያችንን በመቀነስ ለተጨማሪ ችግረኛ ወገኖች መድረስ እንችል ነበር ያሉት ወ/ሮ ሙዳይ፤ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ምስማር ጀምሮ የአቅማቸውን በማዋጣት ግንባታውን እውን ያደርጉላቸው ዘንድ ተማጽነዋል፡፡

“ሙዳይ በጎ አድራጎት ከ1ሺ100 በላይ ተረጂ ወገኖችን ቤት ተከራይቶና ቀለብ ቆርጦ እንዴት ነው የሚያኖረው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ወ/ሮ ሙዳይ ሲመልሱ፤ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ  በማቅረብ እንዲሁም በከብት እርባታ ላይ በመሰማራት  ከሚያገኙት ገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ “ሙዳይ እንጀራ” በከተማዋ እንደሚታወቅ የጠቆሙት ወ/ሮ ሙዳይ፤ ይሄ ሥራ ከ1ሺ በላይ ለሚሆኑ እናቶችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡    

አቅሙ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በወር 500 ብር ስፖንሰር በማድረግ አንድ ልጅ ማሳደግ እንደሚችሉ የጠቆሙት የበጎ አድራጎት መሥራቿ፤ በ9923 አጭር መልዕክት ሙዳይን እንዲደግፉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በ9923 አጭር መልዕክት ድርጅቱ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረጉም ምስጋቸውን ያቀረቡት ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፤አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

• ከሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት ባገኘው ድጋፍ ለ100 ችግረኛ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ በትላንትናው ዕለት ረፋድ ላይ በአራዳ ክ/ከተማ ገዳም ሰፈር በሚገኘው ወረዳ 5 አስተዳደር ግቢ ውስጥ ያደራጀውን የህጻናት መንከባከቢያ ማዕከልና ፕሮጀክት ቢሮ የመንግሥት ሃላፊዎች፣ የድርጅቱ የህይወት ዘመን አምባሳደሮችና ባለሃብቶች በተገኙበት አስመረቀ፡፡
ድርጅቱ ያስመረቀው ይሄ የህጻናት የቀን ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል፣ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የህጻናት፣ እናቶችና ወጣቶች የጎዳና ህይወት ተጋላጭነት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ 10ሺ500 ህጻናትና 13ሺ500 አዋቂዎች፣ በድምሩ 24ሺ ሰዎች የጎዳና ህይወት እንደሚመሩ በ2010 የተደረገ ጥናት የሚያመለክት ሲሆን፤ የጎዳና ልጆች ፕሮጀክት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ተነግሯል፡፡
የህጻናት መንከባከቢያ ማዕከሉን እውን ለማድረግ ዶ/ር ኢያሱ የተባሉ ግለሰብ የራሳቸው የሆነውን ቤት ለሜሪ ጆይ በስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ዴንቨር የኢትዮጵያ ኮሙኒቲና ዓለምጸሃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የጎዳና ህጻናትን ህይወት ለመለወጥ በሚያደርገው ጥረት ኢትዮ ቴሌኮም በቀጣይነትም እንደሚያግዛቸው ቃል ገብቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሜሪ ጆይ ከሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ሃርሞን ሃጎስ በተደረገለት የ250ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ 100 ለሚደርሱ ችግረኛ ወገኖች በዛሬው ዕለት ማዕድ አጋርቷል፡፡
የመንግሥት ሃላፊዎችና ባለሃብቱ በተገኙበት ለእነዚህ ችግረኛ ወገኖች ምሳ የማብላት ሥነስርዓት ከመደረጉም በተጨማሪ ለአዲስ ዓመት መዋያ የሚሆኑ እንደ ዘይት፣ ዱቄት፣ ዶሮና የመሳሰሉት የአውዳመት መሰረታዊ ፍጆታዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት ከሜሪ ጆይ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት መሆኑን የገለጹት የሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ሄርሞን ሃጎስ፤ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ለችግረኛ ወገኖች የአቅማቸውን በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚለውን ፕሮጀክት ከጀመርን 17 ዓመት ሞልቶናል ያሉት የሜሪ ጆይ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር በበኩላቸው፤ በእነዚህ ዓመታትም ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መደጋገፍ እንደምንችል በተግባር አስመስክረናል ብለዋል፡፡
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፤ በ1986 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሊጠናቀቅ ቀናት የቀሩት 2015 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን እጅግ የከፋ ዓመት ነበር። ዓመቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭት፣ ጦርነት፣ ሞትና መፈናቀል ተባብሶ የቀጠለበት፣ በርካቶች ለብዙ መከራና ሰቆቃ የተዳረጉበት፤ ፈታኝ ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ዘገባ በ2015 ዓ.ም በአገራችን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም በኪነጥበቡ ዘርፍ የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡
በፖለቲካው ዘርፍ
የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በመከላከያ ሃይሉ ላይ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በፈፀሙት ጥቃት ሳቢያ በመንግስት የመከላከያ ሰራዊትና በህውሃት ሃይሎች መካከል የተጀመረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲያበቃና የህውሃት ሃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ሁለቱ አካላት በደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰው ስምምነት ለ2ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ቢችልም ስምምነቱ በአግባቡ ተግባራዊ የተለያዩ የተቃውሞ ድምፆች ሲሰሙ ሰንብተዋል። የስምምነቱ ዋንኛ አካል የሆነው የህውሃት ታጣቂ ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ተግባር ሲያወዛግብ ቆይቶ ከወራት በኋላ ታጣቂ ሃይሉ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግስት ማስረከቡ ተገለፀ፡፡ ከዚሁ በማስቀጠልም ክልሉን በጊዜያዊነት ሲያስተዳድር ከነበረው የፌደራል መንግስት ስልጣኑን የሚረከብ አካል ለመምረጥ የህውሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አርብ መጋቢት
8 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ምርጫ፣ አቶ ጌታችው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጣቸው። ሆኖም ክልሉን የመምራት ሃላፊነቱ ለአቶ ጌታቸው ረዳ አልጋ ባልጋ አልሆነላቸውም። ርእሰ መስተዳደሩ ከሰሞኑ በሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ክልሉን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዳይችሉ የሚያደርጉ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሟቸው ጠቁመው፤ ከህውሃት አመራሮች መካከል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ የሚታትሩ መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በወረዳዎችና በታችኛው እርከን ያሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል እንዳይሆኑ የተደራጀ ንቅናቄ እንዳለም ተናግረዋል ይህ በእንዲህ እንዳለም በትግይ ክልል የተንሰራፋውን ጭቆናና የአንድ ፓርቲ ስርዓትን እታገላለሁ የሚል “ትንሳኤ 70 እንዳርታ (ትስአፓ)” የተባለ ክልላዊ ፓርቲ መስራች ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ አካይዷል፡፡ ፓርቲው በክልሉ “ህብረ ብሔራዊ ስርዓት” እንዲፈጠር እንደሚታገልና ይህ ካልሆነ ግን የራሱን ክልላዊ መንግስትም እንደሚመሰርት አስታውቋል፡፡
ከትግራይ ክልል ሳንወጣ በክልሉ ጳጉሜ 2 ቀን 2015 ዓ.ም የተደረገውና በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ 3 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠርቶ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ተበትኗል፡፡
“የትግይ ህዝብ ስቃይ አላበቃም” በማለት ሰልፍ ወጥተው የነበሩ የትግራይ ክልል ወጣቶች፤ በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች እንዲበተኑ መደረጋቸውን ከቀናት በፊት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንደ ሰሜን ሁሉ ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍልም በፖለቲካ ውዝግብ በተቃውሞና በግጭት ነበር አመቱን ያሳለፋው፡፡ 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህገመንግስት  ከተጠቀሱት ዘጠኝ ክልሎች መካከል የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ህልውናው በይፋ ያከተመበት አመት ነው፡፡
ለሁለት አስርት አመታት በዚህ ስም ሲጠራ የኖረው ክልል፣ በአራት ክልሎች እንዲዋቀርም ጸደርጓል፡፡ ከክልሉ ቀድሞ የወጣው የሲዳማ ክልል ነበር፡፡ በመቀጠልም የደቡብ ምእራብ ህዝቦች ክልል በተመሳሳይ አዲስ ክልል ሆኖ ተቋቁሟል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ሶስተኛው ደቡቡ ኢትዮጵያ ክልል የተመሰረተ ሲሆን፤ አራተኛው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ የተመሰረቱት ክልሎች በውስጣቸው የየራሳቸውን ክልል ለማቋቋም ጥያቄ ያቀረቡ የተለያዩ ብሄሮችን የያዙ በመሆናቸው ጉዳዩ ማቆሚያ እንደሌለው የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
አገሪቱ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም እስከተከተለች ድረስ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ከግምት  ውስጥ በማስገባት የክልልነት ጥያቄው አይቀሬ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
2015 ዓ.ም በአማራ ክልልም በተከሰተው ግጭትና ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህይወት የጠፋበትና ዓመት ሆኗል። አመቱ በተለይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና በፋኖ ታጣቂ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ግጭትና ጦርነት ተቀስቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን ለሞት የዳረገ ሆኗል፡፡
በክልሎች ስር ተዋቅረው የሚገኙት ልዩ ሃይሎች እንዲፈርሱና በፌደራል የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተደረገውን ሙከራ ባልተቀበሉ ወገኖችና በመንግስት  መካከል  ላለፉት 5 ወራት ከባድ ጦርነት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ግጭቱ የተባባሰው ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ በሰሜን ሸዋ መሃል ሜዳ የተጀመረው ግጭት ተቀጣጥሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመድረሱ በሰሜን ጎንደር በደብረማርቆስ፣ በፍኖተሰላም በሰሜን ወሎና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና በታጣቂዎች መካከል ግጭት ተካሂዷል በዚህም በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ነው ያለው ግጭትና ጦርነት በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ተባብሶ በቀጠለው ጦርነት ሳቢያም የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን የመንግስት ቢሮዎችም ለአገልግሎት ዝግ ሆነው ሰንብተው ነበር። ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንደሆነ ከተወሰነበት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ አንፃራዊ መረጋጋት ቢኖርም ዛሬም ድረስ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ውጥረት መንገሱንና ዛሬም ድረስ ግጭቶች መኖራቸውን ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ክልሉን እጅግ ለበዛ ችግርና መከራ የዳረገው የሰላም እጦት በቀጣይም አመት እንዳይከተለው ይሰጋል።
አሮጌውን ዓመት በግጭትና በሰላም እጦት ያሳለፉት የአዲስ አበባና ዙሪያዋ አካባቢ ከተሞችም ከግጭትና አለመረጋጋት አላመለጡም። በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳቱ አቶ ሺመልስ አብዲሳ “በኦሮሚያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ” ነው በተባለለት የሸገር ከተማ ምስረታ ሳቢያ በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አምስት ከተሞችን በመያዝ በ12 ክፍለ ከተሞች በኦሮሚያ ክልል ስር የካቲት 19 ቀን 2015 የተመሰረተችው የሸገር ከተማ ለአመታት ጎጆ ቀልሰው ልጆች ወልደው ኑሮአቸውን የመሰረቱ በርካቶችን አፈናቅላለች። የከተማ አስተዳደሩ “ያለ ፕላንና ህጋዊነት ተሰርተዋል” ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችንና የእምነት ተቋማትን አፍርሷል። ከዚህ ከከተማው ቤት ፈረሳ ጋር በተያያዘ 100 ሺ አቤቱታዎችን መቀበሉን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ገልጿል፡፡
አስተዳደሩ ህገወጥ ናቸው እያለ ለሚያፈርሳቸው የመኖሪያ ቤቶች ምትክ ቦታ አለመስጠቱንና ለተፈናቃዮችም ጊዜያዊ መጠለያ አለማዘጋጀቱንም ተቋሙ ገልፆ ነበር፡፡ ያለፕላንና ህጋዊነት ተሰርተዋል ተብለው በከተማ አስተዳደሩ 22 መስጊዶችም መፍረሳቸውንም የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።
ሌላው የአመቱ አስገራሚ ክስተት በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ዋንኛ የሚባለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የአመራሮችና አባላቱ ከፓርቲው መልቀቅና የፓርቲው መዳከም ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ የሺዋስ አሰፋንና ለኢዜማ መሪነት ከፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተወዳድረው የነበሩትን አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ኢዜማን ለቀው መውጣታቸውን ይፋ ያደረጉት በዚህ አመት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር ይሁን እንጂ የእነዚህ ጎምቱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ከፓርቲው መልቀቅ ፓርቲውን ለመሰንጠቅ እንደማይዳርገው በቀሪዎቹ የፓርቲው አመራሮች መግለጻቸው ይታወሳል።
በማህበራዊ ጉዳዮች
አብዛኛው በአመቱ ያሳለፍናቸው ማህበራዊ ችግሮች የፖለቲካ ቀውሱን ተከትለው የመጡ ችግሮች ናቸው የሚሉት የፖለቲካ ምሁራን ህዝቡን ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች የዳረጉት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ግጭትና መፈናቀሎች እንደሆነ ይገልጻሉ።  ችግሮቹም ፖለቲካዊ መፍትሄዎች የሚሹ መሆናቸውንም ምሁራኑ ይገልጻሉ። ለዜጎች መፈናቀል፣ ስደትና ሞት መነሻ የሚሆኑ ችግሮች በጊዜው መፍትሄ ካላገኙ ማህበራዊ ቀውሶችን ማስከተላቸው አይቀሬ መሆኑን የሚገልፁት የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ታረቀኝ ደጀኔ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ህጋዊነትን የማስጠበቅ ህገወጥ ድርጊቶች ዜጎችን ለከፋ ችግር የዳረጉ ናቸው ብለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ስር በተመሰረተው አዲሱ የሸገር ከተማ አስተዳደር የተፈፀመው ቤቶችን የማፍረስና ዜጎችን በግዳጅ የማንሳት እርምጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡ የቤት ማፍረሱ ተግባር ተገቢ እይታ ያልተደረገበት ህጋዊነትን ያልተከተለ ያለበቂ ማስጠንቀቂያ የተከናወነ አድሏዊ እርምጃ መሆኑንና ይህም ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ያስከተለ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
እገታ
ባሳለፍነው አመት በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ከዘለቁ ጉዳዮች መካከል አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ የእገታ ተግባራት ይገኙበታል፡፡
ይኸው ከቤት ሰራተኞች ጀምሮ እስከ ታጣቂዎች ድረስ ለገንዘብ ሲባል የሚፈፀመው ሰዎችን ማገት በርካቶችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ዳርጓል፡፡ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከጥቂት ሺ ብሮች ጀምሮ እስከ ሚሊዮኖች ድረስ መክፈል የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከገጠር አካባቢዎች ወደ ከተሞች አድማሱን ያሰፋው የእገታ ተግባር የሁሉም አካባቢ ህዝብ ዋንኛ የስጋት ምንጭ ሆኖ ከርሟል፡፡ ይሁን እንጂ ስለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱም ሆነ ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈፀምባቸው ክልል አስተዳዳሪዎች ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡
በሃይማኖት ተቋማት ዘርፍ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና ከቤተክርስቲያኒቱ ስርዓትና ቀኖና ውጪ ጥር 14/2015 በተደረገ ህገ-ወጥ የጵጵስና ሹመት የተሾሙ 26 ጳጳሳትን ሹመት በመቃወም ቤተክርስቲያኒቱ ባወጣችው መግለጫና ለምህመናኑ ባቀረበችው ጥሪ መሰረት በአገሪቱ ከፍተኛ ተቋውሞ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ በዚህ ተቃውሞም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል ይህንኑ የቤተክርስቲያኒቱን ጥሩ የተቀበሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች የካቲት 5/2015 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ሊያደርጉ የነበረውን ታላቅ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በመንግስት ጣልቃገብነት እንዲሰረዝ የተደረገ ሲሆን ህገ-ወጡ የጳጳሳት ሹመትና የሲኖዶስ ምስረታ እንዲታገድም ተደርጓል፡፡
ይህ ችግር በቅጡ ባልተቋጨበት ሁኔታ በቅርቡ ደግሞ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ፣ የትግራይ ቤተክህነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን ግኑኝነት በማቋረጥ በመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተክህነትን መመስረቱን አስታውቆ፤ ዘጠኝ ጳጳሳትን ሾሟል፡፡ ይህንን ሹመት ተከትሎም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን “ህገ-ወጥ ነው” ያለውን የጳጳሳት ሹመት ተቃውሞ አውግዟል፡፡ በእነዚህ ተደጋጋሚ የቤተክርስቲያኒቷን ስርዓትና ቀኖና የሚጥሱ ተግባራት ሳቢያ ያሳለፈፍነው አመት የውጥረትና የግጭት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡
ከሸገር ከተማ ምስረታ ጋር በተያያዙ የፈረሱት 22 መስጊዶች ባሳለፍነው አመት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና በእምነቱ ተከታዮች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋንኛው ሆኖ ይገለፃል፡፡ ባለፈው ግንቦት ወር በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ከተከናወነው የመስጊድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ ድርጊቱን የተቃወሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በታላቁ አንዋር መስጊድ ተቃውሞአቸውን ባሰሙበት ወቅት ከመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጋር በተቀሰቀሰ ግጭት ንፁሃን መገደላቸው ይታወሳል፡፡ ተቃውሞው በየሳምንቱ ቀጥሎ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ለሞት ለእስርና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውም ተዘግቧል።
ከሁለት ቀናት በኋላ የሚጠናቀቀውን 2015 ዓ.ም ከጦርነትና ግጭት፣ ከሞትና ሰቆቃ ውጭ እንዲታወስ የሚያደርጉ ብቸኛ ምክንያቶች ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው። አገር በጦርነትና መከራ እየታመሰችም ሰንደቃችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገውልናል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ ከዚህ ቀደም  በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት ወታደራዊና ደህንነት አባላት እንዲሁም በአማራ ክልል  ሃይሎችና በህውሃት አባላት ላይ የተላለፈው ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ፣ በአንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸው ከሰሞኑ ታውቋል፡፡
 ፕሬዚዳንቱ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ያስተላለፉ  ሲሆን፤ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዙ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊ በሆኑት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደርና የህወሓት አባላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ነው።
ለኢትዮጵያ ደህንነት ስጋት የፈጠሩ፣ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረስ እንቅፋት የሆኑ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉና ሌሎች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል፤ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዙ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጷጉሜ  2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ አሁንም ያለው ሁኔታ የአገሪቱንና የመላው የአፍሪካ ቀንድን ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት ስጋት በመሆን በመቀጠሉ አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ፖሊሲ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል። በዚህም ሳቢያ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም የፈረሙትን ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ በአንድ ተጨማሪ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸው ታውቋል፡፡  
በሰሜኑ ጦርነት በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ የሆኑ ሲሆን በጦርነቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት ኃይሎች ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ነበር።
ጆ ባይደን ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ በያዘችው አቋም የተሰማውን  ቅሬታ መግለጹ ይታወሳል፡፡  


አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ፤ ለ34 ወራት የሚዘልቅ የ3.854 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ስምምነት ከየምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር መፈራረሙን አስታወቀ፡፡
 በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበሮች መሃል የሚገኙ ስደተኞችን ጨምሮ ለአደጋና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህብረተሰቦችን ለመርዳት ያስችላል የተባለው  የፕሮጀክት ስምምነቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ነው የተፈረመው፡፡
ስምምነቱን ኢጋድን በመወከል የኢጋድ ዋና ጸሃፊ የተከበሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የፈረሙ ሲሆን፤ አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያን በመወከል ደግሞ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ሳሊሁ ሱልጣን እንደፈረሙ ታውቋል፡፡
የአክሽን ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሊሁ ሱልጣንና የቦርድ ሊቀመንበሩ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም  ሳር ቤት በሚገኘው የድርጅቱ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቅርቡ ከኢጋድ ጋር በተፈራረምነው የትብብር ማዕቀፍ፣ ድርጅታችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኢጋድ አባል በሆኑ የአፍሪካ አገሮችም ለአደጋና ችግር ተጠቂ የሆኑ ዜጎችን ለመርዳት ተገቢውን ድርጅታዊና ተግባራዊ ዝግጅት በማሟላት ላይ ነን ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት በተወሰኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አክሽን ፎር ዘ ኒዲ፣ ከኢጋድ ጋር በመተባበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን መክፈቱን ጠቁመዋል - ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፡፡
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አካላት ስደተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች እንደሚሆኑ የገለጹት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የፕሮጀክቱ ወጪ ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው በክልላዊ ስደተኞች መርጃ ፈንድ በኩል በጀርመን ልማት ባንክ  መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከልም፤ በኦሮሚያ ሞያሌ አካባቢ ልዩ ስሙ ለጋ ሱሬ በተባለ ቦታ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር፣ በሶማሌ ሞያሌ አካባቢ ልዩ ስሙ ኤል ካሉ በተባለ ቦታ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር፣ በሶማሌ ሞያሌ ከተማ የእንስሳት ገበያ ማደስ፣ በኦሮሚያ ሞያሌ ከተማ የእንስሳት ገበያ ማደስ፣ በሶማሌ ሞያሌ ከተማ የቄራ ቦታ ሰፊ የተቋም ግንባታ፣ በሞያሌ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ችግረኞችን ከመርዳት ባሻገር በኢትዮጵያ ሞያሌና በኬንያ ሞያሌ ድንበሮች የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል ተብሏል፡፡
በ2022 የበጀት ዓመት የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን  ማከናወኑን የጠቆመው አክሽን ፎር ዘ ኒዲ፤ በዚሁ ወቅት 1.3 ቢሊዮን ብር በሥራ ላይ ማዋሉንና ከዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ከዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ (UNHCR) መሆኑን አመልክቷል፡፡
አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ፤ በ2004 ዓ.ም በጥቂት ለጋሾችና በጎ አድራጊዎች የተመሰረተ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ 11 ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈትና ከ700 በላይ ቋሚና  ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመቅጠር፣ በሁሉም ክልሎች ሰብአዊ አገልግሎት  በመስጠት ላይ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ ታውቋል፡፡


የደራሲ ይፍቱሥራ ምትኩ ሁለተኛ የልቦለድ ስራ የሆነው ”ወድቆ የተገኘ ሐገር” የተሰኘ መጽሐፍ ባለፈው  ሳምንት ለንባብ በቅቷል:: መጽሐፉ 110 ገፆች ያሉት ወጥ ልቦለድ መሆኑን ደራሲዋ ተናግራለች፡፡  
“ወድቆ የተገኘ ሐገር” መቼቱን በ1990ዎቹ መጀመሪያ በአገራችን በተካሄደው  የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት ላይ በማድረግ  የተጻፈ ልብወለድ ሲሆን፤ ታሪኩ ከአስከፊ ጦርነት  የተመለሰ ታዳጊን ህይወትና አጠቃላይ የቤተሰቡን ኑሮ  ያስቃኛል::
ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “በተለይ አስራ አንደኛው” የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቷ ይታወሳል::

የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “ኅብር ሕይወቴ፤ግለ ታሪክ” መጽሐፍ፣ ዛሬ ከ8:00 ጀምሮ  በሃይሌ ግራንድ ሆቴል እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ፕ/ር ሰብስቤ ደምሰው፣ ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድ፣ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ወግ አዋቂ በሃይሉ ገ/መድህን፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ይታደሙበታል  ተብሏል፡፡
መርሃግብሩን አርትስ ቴሌቪዥን ከፕሮፌሰሩ አክባሪና ወዳጆች ጋር ያሰናዱት ሲሆን፤ መድረኩን ጋዜጠኛ ሶዶ ለማና ገጣሚ ምሥራቅ ተፈራ እንደሚመሩት ታውቋል፡፡ የምርቃት ሥነስርዓቱን “ያለፈውን መሸኛ የሚመጣውን አዲስ አመት ደግሞ መቀበያ እናደርገዋለን!” ብለዋል፤ አዘጋጆቹ፡

መቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት፣ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው፤ በአደገኛ እጾች ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ቅድመ መከላከልና የሱስ ህክምና ዙሪያ ከ15 ዓመታት በላይ የሰራ  አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡
ራዕዩ፡- ከአደገኛ እፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት የፀዳ ባለራዕይ ትውልድ በአፍሪካ ላይ ተሰርቶና ተነስቶ ማየት! የሚል ሲሆን ፤ የራዕዩ መነሻ የሆነው የድርጅቱ ፍልስፍናም ‹‹አገር ማለት ሰው ነው፡፡ የዜጎችን አዕምሮ ስንከባከብ ለአገር ልማትና እድገት ያለው አስተዋፅ ትልቅ እንደሆነ ሁሉ፤ የሚጎዱ ነገሮች ደግሞ አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም። ስለዚህ አንጎልን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ነገሮች ትውልዱን እየጠበቅን፤ በክብካቤና ማስተማር ላይ እናተኩር..›› የሚል ነው፡፡
ባለፉት አመታት ‹‹ሱስ  የምንከላከለውና ማገገም የሚችል የአንጎል ህመም ነው!›› በሚል አዲስ ማህበረሰባዊ ንቃተ-ህሊናን ለመፍጠር፤ ከመንግስት ጋር ማለትም፤ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ድርጅት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአድቮኬሲ ስራው በትምባሆና አልኮል ላይ ተጠናክሮ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ   ከሚመለከተው መንግስታዊ ተቋምና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር፣ በምክር ቤት የህዝብ ውይይት ጊዜ የተጠናከረ የአቻ ምክረ-ሃሳቦችን  በማቅረብና አዋጁ ተጠናክሮ ከወጣ በኋላም፣ ለተፈፃሚነቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር፣ ማህበረሰባዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ የቆየ ተቋምም ነው፡፡
በግንዛቤና በቅድመ መከላከል ስራዎቻችን  በርካታ ሚሊዮኖች፣ ‹‹የሱስ ህመም የምንከላከለውና ማገገም የሚችል የአንጎል ህመም ነው!›› የሚለውን መሪ ቃል ሰምተዋል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያችን በ8 ዩኒቨርስቲዎች ከላይ ከተጠቀሱት የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር በመተባበር፣ ዩኒቨርስቲን መሰረት ያደረገ የፀረ - ሱስ ማህበረሰብ ንቅናቄ /University  Based Anti-Addiction Community Movement / መፍጠር  በሚል ዓላማ፣ ከትምባሆ ጭስ ተጋላጭነት የፀዱ ዩኒቨርስቲዎችን ለመፍጠር በስፋት  ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከሱስ የማገገም ህክምና ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴርና ከመቀለ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር፣ ከ800 መቶ በላይ ለሚሆኑ ፍቃደኛ የሱስ ህመም ታካሚዎች እገዛ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዘርፉም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ከሱስ የማገገም አማካሪና አሰልጣኞችን ለማፍራት ከጤና ሚኒስቴርና ከአሜሪካ መንግስት ጋር በመተባበር፣ በተለያዩ አገራት ስልጠናዎችን በመውሰድና የተገኘውን ልምድና ተመክሮ  አገር ውስጥ ከተገኘው ልምድ ጋር በመቀመርና ዶክመንቶችን በማዘጋጀት ትልቅ ስራዎችን ሲያከናውን  ቆይቷል፡፡
ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ ደግሞ ከኢትዮጵያ  የምግብና መድኃኒት ባለስልጣንና ከአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቢሮ ጋር በመሆን፣ አዲስ አበባን ከትንባሆ ጭስ ነጻ የማድረግ ተነሳሽነት (Addis Ababa Smoke Free Initiative) በሚል መሪ ሀሳብ በመስራት ላይ ይገኛል።
አዲስ አበባን ከትንባሆ ጭስ ተጋላጭነት ነጻ የማድረግ ተነሳሽነት ስራ በአራዳ ክ/ከተማ ውስጥ በ3 ወረዳዎች የጀመረው የፓይለት ስራ  በሂደት በማደግ፣ ሙሉ የአራዳ ክ/ከተማን፤ በኋላም ቂርቆስ ክ/ከተማን ከዚያ ልደታና ጉለሌ ክፍለ ከተሞችን በማካተት ወደ አራት ማሳደግ ተችሏል። በዚህ ስራ ውስጥ የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሚና፣ የኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒት ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ ቢሮን ማገዝ ሲሆን ፤ ይህን እገዛ እንድናደርግ በአሜሪካ አገር የሚገኘው Campaign For Tobacco Free Kids (CTFK) እያገዘን ይገኛል።
ድርጅታችን በአዲስ አበባ  ከትምባሆ ጪስ ተጋላጪነት የፀዳ አካባቢን ለመፍጠርና ከሌሎች ሱስ የመከላከልና የማገገም ስራ ጋር የተያያዙ ተግባራትን ለማከናወን  ልዩ ‹ፍኖተ ካርታ› አዘጋጅቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ፍኖተ ካርታ ”Full Package” ያለው ሲሆን፣ ይህም አካሄድ ከተማዋን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ከማድረግ  እንቅስቃሴ ጎን ለጎን፣ ትምባሆ ተጠቃሚውንና በጭሱ የሚጠቁ ሁለተኛ አጫሾችን ያካተተ ስራ መስራትን የሚከተል አካሄድ ነው ብለን እናምናለን። Full package ስንል የሚከተለውን ማለታችን ነው።
1ኛ- ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ፈጣሪ በሆነ መልኩ ሰፊ ስራ መስራት። ስለትምባሆም ሆነ ስለ ሌሎች አደገኛ እፆች ጎጂነት በማስተማርና ቅድመ መከላከል በመፍጠር ማህበረሰብን ሊታደግ የሚችል ስራ መስራት ፤
2ኛ - እስከ አሁን እየተተገበረ ያለውን የአዋጅ ቁጥር 1112/2011 ቁጥጥር የህግ ማስከበር ስራ አጠናክሮ መቀጠል። እንዲሁም የአድቮኬሲ ስራውን በተቀናጀ መንገድ ማስኬድ። እንዲሁም፤
3ኛ- በትምባሆም ይሁን በሌሎች አደገኛ እፆች ሱስ ውስጥ ያሉትን የከተማችን የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከሱሳቸው ለመውጣት ፍቃደኛ ሲሆኑ፣ ህክምና ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትና የማገገም ሂደታቸው ስኬታማ እንዲሆን የማገገሚያ ፕሮግራሞችን ማጠናከር።
በተጨማሪም ማህበረሰቡ ከትንባሆ ጭስ ተጋላጭነት የመጠበቅ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው እንዲገነዘብ ስለሚፈለግ፣ ማህበረሰቡ “ከትንባሆ ጭስ በጸዳ አካባቢ መኖር ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብቴ ነው!” በሚል መሪ ሀሳብ፣ ላለፉት ሁለት አመታትና ከዚያ በላይ ግንዛቤ ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡
በአንጻሩም፤ ትልቅ አበረታች ለውጥ ታይቶበታል። ይሁን እንጂ እየተሰራ ያለው ስራ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ተሰጥቶት ለሰፊው ማህበረሰብ ተዳርሷል ብለን አናምንም፡፡ ይህንን ለመቅረፍም ከሚዲያ ተቋማት ጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
ኤልያስ ካልአዩ
የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት
ኤክስኪዩቲቭ ዳሬክተር

Page 2 of 665