Administrator
የአገራዊ ምክክር (ውይይት) ፋይዳ
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ብሔራዊ ምክክር ማድረግ በርካታ ፋይዳዎችን ያስገኛል፡-
1. የግጭት አፈታት፡- አገራዊ ውይይቶች ወይም ምክክሮች የረዥም ጊዜ ቅሬታዎችንና ግጭቶችን ለመፍታት መድረክ ይፈጥራሉ፤ በተለያዩ ቡድኖች መካከል እርቅን ለማውረድ ያስችላሉ፡፡
2. ሁሉን አካታች አስተዳደር፡- አገራዊ ምክክሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ ሁሉን አቀፍና ወካይ የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈጠሩ ያግዛሉ፡፡
3. ህጋዊነትና መተማመን፡- እንዲህ አይነት ውይይቶች የፖለቲካ ሂደቶችንና ተቋማትን ህጋዊነት በማጎልበት በህዝቡ መካከል መተማመንን ይፈጥራሉ፡፡
4. የፖሊሲ ቀረጻ፡- መጠነ-ሰፊ አመለካከቶችን ለመሰብሰብ እድል ይሰጣሉ፣ ይህም ሁሉን አቀፍና ውጤታማ ፖሊሲ ለመቅረጽ ያስችላል፡፡
5. ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር፡- ብሔራዊ ውይይቶች መከፋፈልን ለማስወገድና የአገር አንድነት ስሜትን ለመፍጠር እንዲሁም የጋራ ዓላማን ለማጎልበት ይረዳሉ።
የተሳኩ አገራዊ ምክክሮች - ጥቂት አብነቶች፡
1. ቱኒዝያ፡
- ዳራ፡- እ.ኤ.አ ከ2011 አብዮት በኋላ ቱኒዚያ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችና ማህበራዊ መከፋፈል ገጠማት።
- ሂደት፡- የሠራተኛ ማኅበራት፣ የአሰሪዎች ማኅበራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ያቀፈው የቱኒዚያ አገራዊ ምክክር ኳርተር ውይይቱን አመቻችቷል።
ውጤት፡- ውይይቱ አዲስ ህገ መንግስት እንዲፀድቅ፣ የቴክኖክራት መንግሥት እንዲመሰረትና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ አድርጓል። ኳርተሩ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ላበረከተው አስተዋጽኦ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸልሟል።
- የተቀሰሙ ትምህርቶች፡- አካታችነት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎና የጋራ መግባባትን መፍጠር ላይ ማተኮር ለስኬታማነቱ ወሳኝ ነበሩ፡፡
2. ደቡብ አፍሪካ፡
- ዳራ፡- እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአፓርታይድ ሥርዓት ማብቃት፣ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትሸጋገር ዘንድ ግድ አደረገው፡፡
ሂደት፡- የደቡብ አፍሪካ ዲሞክራሲያዊ ኮንቬንሽን (CODESA) በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ አሰባሰበ፡፡
- ውጤት፡- አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በአገሪቱ የመጀመሪያው የመድብለ ብሄር ምርጫ እንዲካሄድ በር የከፈተ ሲሆን፤ ይህም ኔልሰን ማንዴላን ወደ ፕሬዚዳንትነት መንበር አምጥቷል፡፡
- ቁልፍ ትምህርቶች፡- ለውይይት ቁርጠኛ መሆን፣ ስምምነት ላይ መድረስና የወደፊት የጋራ ራዕይ መፍጠር ለስኬታማነቱ ወሳኝ ጉዳዮች ነበሩ።
3. የመን (እ.ኤ.አ ከ2013-2014)
- ዳራ፡- የአረብ አብዮትን ተከትሎ የመን ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ተለመች፡፡
- ሂደት፡- ብሔራዊ የውይይት ኮንፈረንስ (ኤንዲሲ)፤ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪል ማህበረሰብን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ሌሎች ቡድኖችን ያካተተ ነበር።
- ውጤት፡- ሂደቱ በግጭት ቢቋረጥም፣ የአስተዳደርና የልማት መርሆችን የሚገልጽ ሁሉን አቀፍ ሰነድ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡
- ቁልፍ ትምህርቶች፡- ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎና ክልላዊና ሃይማኖታዊ ችግሮችን መፍታት ወሳኝ ነው፣ ምንም እንኳን ውጫዊና ውስጣዊ ግጭቶች አሁንም ከፍተኛ ፈተናዎችን ሊደቅኑ ቢችሉም፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ የምትማረው----
1. አካታችነት፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ብሔረሰቦችና የተገለሉ ማህበረሰቦችን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው ቡድኖች ውክልናና ድምጽ እንዲኖራቸው ማድረግ።
2. የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎ፡- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጽእኖና ተአማኒነት በመጠቀም ሽምግልናና ውይይትን ማመቻቸት።
3. በመግባባት ላይ ማተኮር፡- ውጤቶቹ በሰፊው ተቀባይነት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ፣ ከአብላጫ ድምጽ ይልቅ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር አልሞ መሥራት፡፡
4. ግልጽ ዓላማዎች፡- ግልጽ ዓላማዎችንና የውይይት ሂደቱን ትኩረትና አቅጣጫ ለመጠበቅ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት።
5. ግልጸኝነት፡- በተሳታፊዎችና በህብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ለመገንባት፣ በመላ የውይይት ሂደቱ ግልጸኝነትን ማስጠበቅ፡፡
6. አለም አቀፍ ድጋፍ፡- አገራዊ ውይይቶችን የማመቻቸት ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ አካላት ድጋፍና ምክር መጠየቅ፤ ሂደቱ በአገር ውስጥ የሚመራና በባለቤትነት የሚቀጥል መሆኑን በማረጋገጥ።
ከእነዚህ አብነቶች በመማር አገራችንም የግጭቶቿን መንስኤዎች የሚፈታና ለወደፊት ሰላማዊና የብልጽግና መንገድ የሚከፍት ጠንካራና ውጤታማ አገራዊ የውይይት ሂደት መፍጠር ትችላለች። በዚያ መንገድ ላይ ነው ያለነው ብለን እንገምታለን፡፡ የተጀመረው አገራዊ ምክክር ይሳካ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን፡፡
ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ነዳጅ ለማስገባት መስማማቷን የበርበራ ከተማ ከንቲባ ገለጹ
ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ፣ በርበራ ወደብ በኩል ነዳጅ ለማስገባት መስማማቷን የበርበራ ከተማ ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ሃሰን ተናግረዋል። ከንቲባው ይህንን የተናገሩት የሶማሌላንድ የነጻነት በዓል በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው።
አብዲሽኩር፤ ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርት የምታስመጣበትን ወደብ ወደ በርበራ እንደምትቀይር ያብራሩ ሲሆን፣ የገቢ ምርቶቿንም ለማስገባት ወደቡ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ንግግር ያደረጉት 33ኛው ዓመት የሶማሊላንድ የነጻነት በዓል ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው። እንደ ”በርበራ ታይምስ” ዘገባ፤ በዚህ ክብረ በዓል ላይ የኤምባሲው ባለስልጣናት፣ የሶማሌላንድ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ፖለቲከኞችና የፓርላማ አባላት ታድመዋል፡፡
ከንቲባው “ተደርጓል” ያሉት ስምምነት መቼ በትክክል ወደ ስራ እንደሚገባ የገለጹት ነገር የለም። እስካሁን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሌላንድ መንግስታት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል።
በስምምነቱ መሰረት፣ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ ወደብ ስትሰጥ፤ ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች።
ይሁንና ሶማሊያ ስምምነቱን “ሉዓላዊነቴን የሚጻረር ነው” ስትል ክፉኛ መኮነንዋ አይዘነጋም፡፡ ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ራሷን ገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም. ላይ ነበር።
በግጭት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህክምና አያገኙም
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭት በማገርሸቱ ሳቢያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን አስታውቋል። በኢትዮጵያ የኮሚቴው ቡድን መሪ ኒኮላስ ቮን አርክስ እንደተናገሩት፣ ኮሚቴው በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ ሃይሎች ጋር በመገናኘት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎችን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ እየወተወተ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ያደናቀፈ ሲሆን፤ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ማሰራጨት ፈታኝ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አለመረጋጋቱ፤ የትግራይ ክልል ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ተጽዕኖ ሕዝቡ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ተጠቁሟል።
“ችግሩን ለመፍታት በተወሰኑ አካባቢዎች እየተንቀሳቀስኩ ነው” ያለው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ከ100 በላይ የጤና ተቋማት ዕርዳታ ማሰራጨቱን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በአማራ ክልል ለ62 የጤና ተቋማት፣ በኦሮሚያ ክልል ለ17፣ በትግራይ ክልል ለ20 እና በሶማሌ ክልል ለ6 የጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ኮሚቴው በድረ ገጹ ባሰራጨው መረጃ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የጤና እንቅስቃሴዎች አስተባባሪ ሲላስ ሙካንጉ፤ “በተለያዩ አካባቢዎች በግጭትና ጥቃት የተጎዱ ዜጎች ያሉበት ችግር አሳሳቢ ነው።
የሪፈር ስርዓት በመቋረጡ፣ ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት የሚያሻቸው ዜጎች ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም።” ሲሉ ተናግረዋል።
በደቡብ ጎንደር የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ ታሰሩ
የደቡብ ጎንደር ዞን፣ ታች ጋይንት ወረዳ፣ የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ፣ በጸጥታ ሃይሎች መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል። ”የአባላቱ እስራት የፖለቲካ ስብራታችን አንድ ማሳያ ነው” ብሏል፤ እናት።
ፓርቲው ሰሞኑን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ፤ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው የታሰሩት ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር። በአሁኑ ወቅት ሰብሳቢው በላይ ጋይንት ወረዳ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ ነው ፓርቲው የጠቆመው።
አቶ ሰለሞን የታሰሩበትን ምክንያት የጸጥታ ሃይሎቹ እንዳልነገሯቸው እናት ፓርቲ በመግለጫው አትቷል። እስካሁን የተመሰረተባቸው ክስ እንደሌለም ተጠቁሟል፡፡
የአባላቱን እስራት “የፖለቲካችን ስብራት አንድ ማሳያ ነው” ያለው ፓርቲው፤ “ትግላችን ሰላማዊ በመሆኑ መንግስት አባላቶቻችንን እያሳደደ ማሰሩን ያቁም” ሲል አሳስቧል።
የፓርቲው ሕግና ሥነ ስርዓት ክፍል ሃላፊ አቶ ዋለልኝ አስፋው ባለፈው ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው፣ ግራር ሰፈር ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታስረው፣ በነጋታው ከእስር መፈታታቸው ከእናት ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ አድማስ የእናት ፓርቲ አመራሮችን በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ከሳምንታት በፊት እናት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር ባወጣው መግለጫ፤ በስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ለዚህ ውሳኔው ያቀረበው ምክንያትም፤ “ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ የለም” የሚል ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ነገ ይጀመራል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21- 27 ቀን 2016 ዓ.ም ለሰባት ተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በአዲስ አበባ ያካሂዳል፡፡
በነገው ዕለት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የመክፈቻ ሥነስርዓቱ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
በዚህ የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ ከየወረዳው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ከ1700 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
”ይህ መድረክ ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ብዙም ባልተሄደበት ሁኔታ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እኩል የመምከር መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተሄደበት እርቀት ማሳያ ነው፡፡ የሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ መሆን አንድ ማሳያም ነው፡፡“ ብሏል- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሚያከናውነው በዚህ የምክክር ምዕራፍ፣ ከ2500 በላይ ተወካዮችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡
ለሰባት ቀናት በተከታታይ የሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ፣ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከናወኑበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡ ይኸውም፡- በዚህ እርከን ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች በውይይትና በምክክር የአጀንዳ ሃሳቦችን ያመጣሉ፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፤ በመጨረሻም የሂደቱ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ - ተብሏል፡፡
መርሃ ግብሩ፤ ኮሚሽኑ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን የያዙ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይት የሚሰበስብበት ምዕራፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይነት ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሃግብሮችን በክልሎች ከተማ አስተዳደሮች እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፈው መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የምክክር ሂደት ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት እንዲያደርጉና በንቃት እንዲሳተፉ የጠየቀ ሲሆን፤ ለሂደቱ ስኬት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡
”ባሻ አሸብር በጀርመን” የግጥም መድበል እየተሸጠ ነው
ነዋሪነቱን በባህር ማዶ ያደረገው ገጣሚ ሰሎምን ሞገስ (ፋሲል)፤ “ባሻ አሸብር በጀርመን” የተሰኘ የግጥም መድበል ባለፈው ሳምንት ለገበያ ያቀረበ ሲሆን፤ መጽሐፉ በ76 ገጾች 84 ግጥሞችን ያካተተ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በዳሽን የኪነጥበባት ሽልማት ውድድር ላይ፣ በግጥም ዘርፍ 1ኛ በመውጣት የ100 ሺህ ብር ተሸላሚ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
ገጣሚው፤ ከአብዬ መንግሥቱ ለማ “ባሻ አሸብር በአሜሪካ” የተሰኘ ተወዳጅ ግጥም፣ ባሻ አሸብር የተባሉ ገፀ ባህሪን በመውሰድ የራሱን ”ባሻ አሸብር በጀርመን” የተሰኘ የግጥሞች ስብስብ ማዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ “ባሻ አሸብር በጀርመን” ለሰለሞን ሞገስ አምስተኛ የግጥም መፅሐፉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ገጣሚው ከዚህ ቀደም “እውነትን ስቀሏት ፣ ከፀሐይ በታች ፣ ፅሞና እና ጩኸት፣ የተገለጡ ዓይኖች” የተሰኙ የግጥም መጻሕፍትን ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ለኮሜዲያን ማርቆስ “ቁራሌው” እንዲሁም ለድምጻዊ እጅጋየሁ ሽባባና ሌሎች አርቲስቶች የኮሜዲ ሙዚቃ ግጥሞችን መጻፉን ሰለሞን ሞገስ ተናግሯል፡፡
የግጥም መድበሉ ባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኙ የመፅሐፍ መሸጫ መደብሮች በ150 ብር ለሽያጭ መቅረቡ ተነግሯል፡፡
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የውዝዋዜ ጥበብ ማህበር ጉባኤ ለ6 ቀናት ተካሄደ
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የውዝዋዜ ጥበብ ማህበር ጉባኤ፣ ከግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት፣ በፈንድቃ ባህል ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል።
ጉባኤውን፤ የኢትዮጵያ የውዝዋዜ ጥበብ ማህበር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴአትርና ጥበባት ትምህርት ክፍልና የዓለም የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በትብብር እንዳዘጋጁት ታውቋል።
“ዳንስ፣ ባህልና ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ከመላው ኢትዮጵያ ለመጡ የማኅበሩ አባላት ከውጭ በመጡ ምሁራን ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበብ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ድግሪና የዶክትሬት ተመራቂዎች በዘርፉ ላይ ያደረጉትን ጥናት አቅርበዋል።
ሌሎች ክውን ጥበባት ከመጀመሪያ ድግሪ እስከ ሦስተኛ ድግሪ ትምህርት የሚሰጥባቸው ዘርፎች ያሏቸው ሲሆን እስካሁን የውዝዋዜ ጥበብ በድግሪ ደረጃ የትምህርት ዘርፍ እንደሌለው የተናገሩት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ፤ የጉባኤው አላማም በዘርፉ ሥርአተ ትምህርት ተቀርፆ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ለማድረግ ያለመ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውዝዋዜ ጥበብ ማኅበር በ2010 ዓ.ም፣ የባለሙያዎችን መብት ለማስጠበቅና ሙያዊ አቅምን ለማጎልበት ታስቦ የተመሰረተ ሲሆን፤ እስካሁንም ድረስ በመላው ኢትዮጵያ የማኅበሩን ቅርንጫፍ ቢሮዎች በማቋቋም፣ ለሙያተኞች ከውጭ ሀገር ከመጡ የዘርፉ ምሁራን ጋር የልምድ ልውውጥ መድረኮችንና ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ነሐሴ ወር መጨረሻ ይካሄዳል
የእጩዎች ጥቆማ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 መሆኑ ተነግሯል
ነሐሴ ወር መጨረሻ ለሚካሄደው 12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት፣ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የእጩ ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የሽልማት ድርጅቱ የቦርድ አመራሮች አስታወቁ። አመራሮቹ ይህን ያስታወቁት ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
“በጎ ሰዎችን በመሸለምና እውቅና በመስጠት ሌሎች በጎ ሰዎችን እናፍራ” በሚል መሪ ቃል ባለፉት 11 ዓመታት ለአገርና ለወገን አብነት የሚሆን አኩሪና በጎ ስራ የሰሩ የሀገርና የወገን ባለውለታ በጎ ሰዎችን ሲሸልምና ሲያከብር የቆየው የቆየው የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት፤ ዘንድሮም ለ12ኛ ጊዜ በ10 ዘርፎች በጎዎችን ለመሸለም በዝግጅት ላይ መሆኑን በመግለጫው ተነግሯል፡፡
በጎዎች የሚሸለሙባቸው አሥሩ ዘርፎች፡- መምህርነት፣ ኪነጥበብ፣ በጎ አድራጎት፣ ንግድ ኢንዱስትሪና ስራ ፈጠራ፣ በመንግስታዊ ተቋማት ሐላፊነት፣ ቅርስ ባህልና ቱሪዝም፣ ማህበራዊ ጥናት፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት መሆናቸውም ተብራርቷል።
የዘንድሮው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ሽልማት፣ በኪነ ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ትኩረቱን ማድረጉ ለየት ያደርገዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም ተተኪ የኪነጥበብ ትውልድ በማፍራት ረገድ ተቋማቱ ያላቸውን ጉልህ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም የቦርድ አመራሮች ጨምረው ገልፀዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የ10ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት፣ የጋዜጠኝነት ዘርፍ አሸናፊ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማ ፍሰሃ ሽልማቱ የፈጠረበትን ስሜት፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ የተቀበለውን የሃላፊነት ስሜትና የስራ ተነሳሽነት በመግለፅ፣ ልምዱን ያካፈለ ሲሆን፤ የሽልማት ድርጅቱ በቂ ድጋፍ ቢደረግለት በርካታ በጎዎችን ሊያፈራ እንደሚችል ተናግሯል፡፡
የበጎ ሰው ሽልማት ላይ ሊሸለሙ ይገባቸዋል የሚሏቸውን በጎዎች ለመጠቆም በ+251977232323 ስልክ ቁጥር ቴሌግራም፣ ቫይበርና ዋትስአፕን በመጠቀም ወይም በኢሜይል አድራሻ፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በመላክ እንዲሁም በ150035 የፖስታ ሳጥን ቁጥር በመጠቀም፣ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ለአንድ ወር ያህል ጥቆማ መላክ እንደሚቻል ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ሰዊት ጌታቸው፣ አንዱአለም አባተ (የአፀደ ልጅ) ፣ አዲሱ ሸዋ ሞልቶትና ደራሲና ጋዜጠኛ በኩረ ትጉሃን ጥበቡ በለጠ አብራርተዋል።
ነገ በአአዩ ባሕል ማዕከል እንገናኝ።
ሙጭሊት (አጭር ልብወለድ)
ምንጩን ተከትሎ የሚጓዘው አረንጓዴ ውሃ ፣ በጠፍጣፋ ቡናማ ድንጋዮች ዙሪያ ትናንሽ የኳስ አረፋዎች እየፈጠረ በጸጥታ ይፈስሳል። በወንዙ ዳርቻ የበቀሉትና ትካዜ ያጠላባቸው የሚመስሉት ዛፎች በውሃ ውስጥ ነጸብራቃቸው ይስተዋላል። ማርኒ ሳሩ ላይ ተቀምጣ ወደ ኩሬው ድንጋይ ትወረውራለች። ከዚያም እየሰፉ የሚመጡትን ክቦችና በጭቃማው የኩሬው ዳርቻ የሚፈጠሩትን ትንንሽ ሞገዶች ታስተውላለች። ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቿ (የድመት ግልገሎቿ) እያሰበች ነበር። ባለፈው አመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች ሳይሆን በዚህ ዓመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች ነበር የምታስበው። እናቲቱ ድመት - ፒንኪ የዛሬ ዓመት የወለደቻቸው ሙጭሊቶች ወደ ሰማይ ቤት መሄዳቸውን ለማርኒ የነገሯት ወላጆቿ ነበሩ፡፡ አዲስ የተወለዱትን ድመቶች ሳትጠግባቸው ነበር ያጣቻቸው፡፡ ሙጭሊቶቹን ከሦስት ቀን በላይ ለማየት አልታደለችም።
“እግዚአብሔር በገነት አብረውት እንዲኖሩ ወስዷቸዋል።” ነበር ያሏት አባቷ።
ማርኒ አባቷ ያሏትን ልትጠራጠር አትችልም፡፡ አባቷ ሃይማኖተኛ ናቸው። የእግዚአብሔር አገልጋይ፡፡ ሰንበት ት/ቤት በየሳምንቱ ያስተምራሉ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥም ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ከምእመናኑ የተሰበሰበውን ገንዘብ እየቆጠሩ በአንድ ትንሽ ቀይ መዝገብ ላይ ያሰፍራሉ። በአዘቦት ቀናትም እንዲሰብኩ ተመርጠዋል። ማታ ማታ ለቤተሰባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ምዕራፍ ያነባሉ። ማርኒ ባለፈው ምሽት ለንባብ ፕሮግራሙ በሰዓቱ ባለመድረሷ ከአባቷ ዋጋዋን አግኝታለች። አባቷ “ልጅ ካልተቀጣ መረን ይለቃል” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። እናም ማርኒ አባቷን በፍፁም ልትጠራጠር አትችልም። ለእሷ፤ስለ ሙጭሊቶቹና ስለ እግዚአብሔር የሚያውቅ ፍጡር ካለ እሳቸው ብቻ ናቸው፤ አባቷ።
ሆኖም ማርኒ ለብዙ ጊዜያት ድንገት ስለተሰወሩት ሙጭሊቶች እያሰበች መገረሟና ግራ መጋባቷ አልቀረም፡፡ በዓለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የድመት ግልገሎች እያሉ እግዚአብሔር ለምን አራቱንም የእርሷን ሙጭሊቶች ለመውሰድ መረጠ? እግዚአብሔር ይህን ያህል ራስ ወዳድ ነው እንዴ?
ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ግን ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ የሚያደርጓት በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል። ትምህርት ቤት የገባችበት የመጀመሪያ ዓመቷ ነበር። ለመጀመሪያው የትምህርት ቀን ስትሰናዳም ሆዷን ባር ባር ብሏታል - ትንሽ ተሸብራ ነበር፡፡ ደብተር፣ እርሳስና መጽሐፍት መገዛት ነበረባቸው። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ትምህርቱን ወድዳው ነበር። ከፊደላትና ቁጥሮች ጋር ያደረገችው የመጀመሪያ ትውውቅ አስደስቷታል። ውሎ አድሮ ግን ማርኒ ትምህርት እየሰለቻት ሲመጣ፣ የገና በዓል በአንፀባራቂ የበረዶ ብናኞች ታጅቦ ከተፍ አለ። የገና ስጦታ ሸመታው፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰማያዊ መብራቶቹ፣ ወዲህና ወዲያ እየተንገዳገዱ ከአንዱ ጥግ የቆሙት የገና አባት፣ እንዲሁም በዋዜማው የሚከናወነው የቤተ ክርስቲያን የሻማ ስነ-ስርዓት፡- እነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ አድርገዋት ነበር።
በመጋቢት ወር፤ ጎላ ያሉ እንቅስቃሴዎች እየተዳከሙ ሲመጡ፣ የማርኒ እናት መንታ ህፃናትን ወለደች። ማርኒ መንትዮቹ መጀመሪያ ላይ እንዴት ትንንሽ እንደነበሩና ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን እንዴት በቀስታ እያደጉ እንደመጡ አስተውላ ተገረመች። በሰኔ ወር ላይ መንትዮቹ ሦስት ወር ሆኗቸው ነበር። በዚህ ወቅት ህፃናቱ በደንብ አድገዋል። የማርኒ ትምህርት ቤት ተዘግቷል። የገና በዓልም ተመልሶ የማይመጣ በሚመስል ሁኔታ ካለፈ ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል። ሁሉም ነገር ለማርኒ አሰልቺ መሆን ጀምሯል። በዚህ ወቅት ነበር ማርኒ ድንገት ያልጠበቀችውን ዜና የሰማችው፡፡ ፒንኪ ሌሎች ትንንሽ ድመቶችን በቅርቡ ትወልዳለች ተባለ፡፡ ይህን ዜና አባቷ ለእናቷ ሲነግሩ የሰማች ዕለት ደስታዋን መቆጣጠር አልቻለችም ነበር። ወዲያው ነበር አዳዲስ ለሚወለዱት ድመቶች ቁርጥራጭ ጨርቆችና የጥጥ ልብሶች ማዘጋጀት የጀመረችው፡፡ የሚተኙበትም ሳጥን አዘጋጀችላቸው፡፡
ሁሉም ነገር ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ አንድ ምሽት ላይ ፒንኪ ወደ በረቱ ተደብቃ በመሄድ ስድስት የድመት ግልገሎችን ተገላገለች። ግልገሎቹ ግራጫና በችኮላ የተረጨ የሚመስል ጥቁር ነጠብጣ ቀለም ያለባቸው ናቸው፡፡ ማርኒ ግልገሎቹን ከመጠን በላይ ወደደቻቸው፡፡ ሆኖም እጅግ ፈርታና ስጋት ገብቷት ነበር። እግዚአብሔር እንዳለፈው ዓመት ቢወስዳቸውስ ?
“ማርኒ! ምን እየሰራሽ ነው?”
ወደ ኋላዋ ዞራ መመልከት አልነበረባትም። ማን እንደሆነ አውቃለች- አክብሮቷን ለማሳየት ግን ዞር አለች፡፡ ከአባቷ የተቆጣ ፊት ጋር ነበር የተፋጠጠችው፡፡
“ድንጋይ እየወረወርኩኝ እየተጫወትኩ ነው” ስትል ማርኒ በቀስታ መለሰች።
“ዓሳዎቹ ላይ?”
“አይደለም አባዬ። ዝም ብዬ ነው የምወረውረው”
“ከሀይማኖት ትምህርታችን የድንጋይ ውርወራ ሰለባ ማን እንደነበር እናስታውሳለን አይደል?” አሉ አባቷ የአዋቂነት ፈገግታ በፊታቸው ላይ እየተነበበ።
“ቅዱስ እስጢፋኖስ” አለች ማርኒ።
“በጣም ጥሩ” አሉ አባቷ፤ ፈገግታቸው ከፊታቸው ላይ እየጠፋ።
ወዲያው፤ “እራት ደርሷል” አሏት።
ማርኒ በአሮጌው ቡናማ ደረቅ የብረት ወንበር ላይ ተቀመጠች። አባቷ በጥቁር ቆዳ የተለበጠውን የቤተሰቡን የድሮ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ በጥሞና የምትከታተል ትመስላለች። መጽሐፍ ቅዱሱ የተላላጠና በርካታ ገጾቹም የተቀዳደዱ ናቸው፡፡ እናቷ ከአባቷ ጎን እጆቿን ጭኖቿ ላይ አደራርባ ተቀምጣለች። “አምላክ እንዴት ጥሩ ነገር ቸሮናል” የሚል ፈገግታ ተፈጥሮአዊ ውበት በተቸረው ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር።
“ህፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግስት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” ብለው ንባባቸውን ጨረሱና በዝግታ መጽሐፍ ቅዱሱን አጠፉት። ለብዙ ደቂቃዎች ማንም ምንም ነገር ሳይተነፍስ በዝምታ ቆየ።
“ማርኒ፤ የትኛውን መጽሐፍና የትኛውን ምዕራፍ ነው አሁን ያነበብነው?”
“ቅዱስ ማርቆስ፤ ምዕራፍ አስር” አለች ማርኒ፤ በቅንነት በተቃኘ ድምጸት፡፡
“ደህና!” አሉ አባቷ።
የማርኒ እናት፤ “የክርስቲያን ቤተሰብ ማድረግ ያለበትን ተግባር ነው የፈጸምነው።” የሚል ፈገግታ በፊታቸው ላይ ይስተዋላል።
“ሜሪ፤ ለእኛ ቡና፣ ለማርኒ ደግሞ አንድ ብርጭቆ ወተት ብታዘጋጂስ?” አሉ የማርኒ አባት ሚስታቸውን።
“እሺ!” አሉ እናቷ ከተቀመጡበት ተነስተው ወደ ወጥ ቤት እየተራመዱ።
የማርኒ አባት አሮጌውን መጽሐፍ ቅዱስ እያገላበጡ ይመረምሩታል። የተቀዳደደውን ገጾች በጣታቸው ይደባብሱታል። ከቢሊዮን ዓመት በፊት የኖሩት ዘር ማንዘሮቻቸው ድንገት በመጽሐፍ ቅዱሱ ገጾች ላይ ያፈሰሱትን የወይን ጠጅ በአትኩሮት እየተመለከቱ ነበር።
“አባዬ” አለች ማርኒ፤ በተጣደፈ ቅላጼ፡፡ ከመጽሐፉ ላይ ቀና ብለው ተመለከቷት። በፊታቸው ላይ ቁጣም ሆነ ፈገግታ አይስተዋልም።
“የድመቷ ልጆችስ?”
“እነርሱ?” አባቷ በሆዳቸው ነገር የያዙ ይመስላሉ።
“አሁንም እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል?” ጠየቀች ማርኒ።
“ምናልባት” አሉ አባት። ከዚህ ሌላ ምንም መናገር አልቻሉም።
“አይችልም! አይወስዳቸውም!” ማርኒ ማልቀስ ጀመረች።
“እሜቴ! እግዚአብሄር ማድረግ የሚችለውና ማድረግ የማይችለውን ነገር አለ እያልሽ ነው እንዴ?” አሉ አባቷ።
“አይደለም አባዬ” አለች ማርኒ።
“እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያደርጋል!” አሉ አባቷ።
“አዎ እሱማ ያደርጋል” አለች በተቀመጠችበት እየተቁነጠነጠች። “ግን ለምን የእኔን ትንንሽ ድመቶች በድጋሚ ይወስዳል? ሁልጊዜ ለምን የእኔን ብቻ?”
“እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ይብቃ። አሁን ፀጥ በይ ማርኒ!” አሉ አባቷ፤ በቁጣ።
“ግን ለምን የእኔን?” ማርኒ ጥያቄዋን ቀጠለች።
አባቷ ድንገት ከተቀመጡበት እመር ብለው ተነሱና ወንበሩን ተሻግረው ወደ እርሷ አለፉ። ያንን ድምቡሽቡሽ የልጅ ፊቷን በጥፊ አጮሉት!! ደም ከከንፈሯ ጠርዝ ላይ በቀጭኑ መፍሰስ ጀመረ። በእጇ መዳፍ ደሟን ጠራረገች።
“ስለ እግዚአብሔር ለመጠየቅ አንቺ ገና ልጅ ነሽ” ምራቃቸው ከንፈራቸው ላይ ተዝረክርኮ ነበር።
ክንዷን በእጃቸው አንጠልጥለው ከተቀመጠችበት አስነሷት። “አሁን ፎቁ ላይ ውጪና ቶሎ ወደ መኝታ!” አሏት በቁጣ።
ማርኒ ለመከራከር አልዳዳትም፡፡ እንደገና መፍሰስ የጀመረውን ደሟን እየጠራረገች ደረጃውን መውጣት ጀመረች። ደረጃውን ስትወጣ የእንጨት መደገፊያውን በእጆቿ እያሻሸች በእርጋታ ነበር የምትራመደው።
“ወተቱ ይኸው” ብላ እናቷ ስትናገር ማርኒ ሰማቻት።
“አያስፈልግም!” አባትየው ቁርጥ ያለ መልስ ሰጡ።
ማርኒ ከፊል ብርሃን የተላበሰው ክፍሏ ውስጥ አልጋዋ ላይ ተጋድማ ነበር። በመስኮቱ የሚገባው ብርቱካናማ ቀለም ያለው የጨረቃዋ ብርሀን፣ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ሃይማኖታዊ ሥዕሎች ላይ እያንፀባረቀ ክፍሉን ከድቅድቅ ጭለማ ነፃ አውጥቶታል። ወላጆቿ መኝታ ክፍል ውስጥ እናቷ ከመንትዮቹ ጋር የምታወራ ይመስል እያጉተመተመች፣ የሽንት ጨርቃቸውን እየቀየረችላቸው ነበር። “የእግዚአብሔር ትንንሽ መላዕክት” አለች እናቷ፡፡ አባቷ ህጻናቱን እየኮረኮሩ ያስቋቸዋል፡፡ ማርኒ፤ “መላእክቱ“ ሲስቁ እየሰማች ነው። ከወፍራም ጎሮሯቸው እየተንደቀደቀ የሚወጣውን ጥልቅ ሳቅ እያዳመጠች ነበር፡፡
በዚህ ምሽት አባቷም ሆኑ እናቷ ደህና እደሪ አላልዋትም። እንደውም ከነአካቴው ወደ መኝታ ቤቷ ድርሽ ያለ ሰው አልነበረም። ማርኒ ቅጣት ላይ ናት።
በበረቱ ውስጥ ከግልገል ድመቶቹ ጋር ጨዋታ ይዛለች፤ ማርኒ፡፡ ከአስር ደቂቃ በፊት እናቷ የላከቻትን መልዕክት ሳታደርስ እዚሁ በረት ውስጥ አንዷን ግራጫ ድመት እያጫወተች ነው፡፡ የድርቆሹ ሽታ አየሩን በሙሉ አውዶታል። አገዳዎቹ ወለሉን በሙሉ ስለሸፈኑት እግር ያደናቅፋሉ። ሁለቱ ላሞች እግራቸው በሽቦ በመቁሰሉ እንዲያገግሙ ግንቡ መጨረሻ ላይ ነው የታሰሩት፡፡ ትንንሾቹ ድመቶች ከማርኒ አገጭ ስር ያለውን አየር በፊት መዳፎቻቸው እየዳሰሱ ይጮሃሉ።
“ማርኒ የት ነች?” ከቤቱና ከበረቱ መካከል ቆመው አባቷ አምባረቁ፡፡
ቤት ውስጥ የእናቷን ጥሪ ስትሰማ ማርኒ መልስ ለመስጠት ከጅላ ነበር።
“የሄለንን የምግብ ሙያ መጽሐፍ እንድታመጣ ብራውን ጋ ልኬያታለሁ። ከሄደች ሃያ ደቂቃ ሆኗታል።” አለች እናቷ።
“ብዙ ሰዓት አለፈኮ” አሉ አባቷ። አባቷ በአቧራማው መሬት ላይ ሲራመዱ የትልቁ ጫማቸው ኮቴ ወታደራዊ ምት ያስተጋባል።
አንድ ችግር እንዳለ ማርኒ አውቃለች። ማየት የሌለባት ነገር ሊፈጸም መቃረቡን ተረድታለች። የድመት ግልገሎቹን ወደ ቀዩ ወርቃማ ሳጥናቸው ከተተቻቸውና ሁኔታውን ተደብቃ ለመመልከት ወደ አገዳው ክምር እየዳኸች ሄደች።
አባቷ ወደ በረቱ ውስጥ ገቡና ከቧንቧው ውሃ በባልዲ ሞልተው ትንንሽ ድመቶቹ ፊት ለፊት አስቀመጡ። እናትየዋ ድመት ፒንኪ “እስ” ብላ የቁጣ ድምጽ አሰማችና፣ ጀርባዋ ላይ ጉብታ ፈጠረች። አባቷ ፒንኪን በእጃቸው አንስተው ባዶ ገረወይና ውስጥ ዘጉባት። ከፒንኪ የወጣው አሰቃቂ ቁጣና ጩኸት ቦታውን የአሜሪካ የእርሻ ስፍራ ሳይሆን፣ የአፍሪካ የእንስሳት መጋለቢያ ሜዳ አስመስሎት ነበር።
ማርኒ በሁኔታው በሳቅ ፈረሰች። ሆኖም የአባቷን በሥፍራው መኖር አሰበችና ሳቋን ወዲያው ገታች።
አባቷ የድመት ግልገሎቹ ወደ ተቀመጡበት ሳጥን ዞረው ተመለከቱ። አንዷን ግልገል በጥንቃቄ ማጅራቷን ይዘው ከሳጥኑ ውስጥ አወጧት። አሸት አሸት አደረጓትና የባልዲው ውሃ ውስጥ በጭንቅላቷ ደፈቋት። ግልገሏ ድመት ባልዲው ውስጥ በስቃይ ስትንፈራፈር ይሰማ ነበር፤ የውሃ ፍንጥቅጣቂዎችም አየሩ ላይ ሲፈናጠሩ ይስተዋላል። የማርኒ አባት ፊታቸውን አጨፍግገው ግልገሏን ሙሉ በሙሉ ወደ ውሃው ውስጥ ጨመሯት። ደፈቋት! ወዲያው ግልገሏ መንፈራገጡን አቆመች። ማርኒ በፍርሃት የሲሚንቶውን ወለል በጣቶቿ እየቧጠጠች ነበር። በዚህም ሳቢያ ጣቶቿ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡
ግን ለምን? ለምን? ለምን? ለምን?
ወዲያው አባቷ ከባልዲው ውስጥ የተዝለፈለፈውን የግልገሏን በድን አወጡት፡፡ ደም የመሰለ ነገር ከድመትዋ አፍ ላይ ተዝለግልጎ ይታያል፡፡ ምላሷ ይሁን አንጀቷ፤ ማርኒ አላወቀችም።
የማርኒ አባት ስድስት በድን የፀጉር ኳሶች የመሰሉ ነገሮች ማዳበሪያ ከረጢት ውስጥ ጨመሩ። ስድስቱም ግልገሎች ከመቅጽበት ተጠናቀቁ። በመጨረሻም፣ እናትየዋን ከገረወይናው ውስጥ አወጧት። ፒንኪ እየተንቀጠቀጠች ነበር፡፡ በደከመ ድምጽ “ሚያው” ብላ እየጮኸች ሰውየውን ተከተለቻቸው። ሰውየው ዞር ብለው ሲመለከቷት “እስ!” እያለች ቁጣዋን ታሰማለች፡፡
ማርኒ ለረዥም ሰዓት ሳትንቀሳቀስ ባለችበት ተቀምጣ ቆየች፡፡ ስለሌላ ስለምንም ጉዳይ እያሰበች አልነበረም። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስለተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ፍርድ እያሰበች ነበር። በትናንሽ ድመቶቹ ላይ ተግባራዊ ስለሆነው የሞት ፍርድ!! ጠቅላላ ሁኔታውን ለመረዳት የተቻላትን ሁሉ ሙከራ አደረገች። አባቷን የላከው እግዚአብሔር ነው? ግልገሎቿን እንዲገድል የነገረውስ እርሱ ነው? ግልገሎቿን ከእሷ እንዲቀማ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው? እውነት እግዚአብሔር ከሆነ ዳግመኛ ከመንፈሳዊው ፊት ቀርባ ቁርባን አትቆርብም፡፡ ከሲሚንቶ ጋር የተቀላቀለ ደም ከጣቶቿ ላይ እየተንጠባጠቡ ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ ቤት ውስጥ ገባች።
“የምግብ አሰራር ሙያ መጽሐፉን አመጣሽ?” ጠየቀቻት እናቷ፤ ማርኒ የወጥ ቤቱን በር ዘግታ ስትገባ። “ሚስ ብራውን አላገኘችውም። ነገ እልከዋለሁ ብላለች።” ውሸቷ ራሷን ማርኒን አስገርሟታል።
“ሙጭሊቶቼን እግዚአብሔር ወሰደብኝ!” ብላ ድንገት ማርኒ ጮኸች። እናቷ የተደናገረች ትመስል ነበር። “አዎ” ብቻ ነበር መልሷ፡፡
“እግዚአብሔርን እበቀለዋለሁ!! እርሱ እንዲህ ሊያደርግ አይችልም! አይችልም!” እያለች ከወጥ ቤቱ ተስፈንጥራ ወጥታ የፎቁን ደረጃ መውጣት ጀመረች።
እናቷ ቆማ እየተመለከተቻት ቢሆንም፣ እንቅስቃሴዋን ግን መግታት አልቻለችም።
ማርኒ ኮውፊልድ ደረጃውን ስትወጣ በዝግታ እየተራመደችና ለስላሳውን የእንጨት መደገፍያ በእጇ እየታከከች ነበር።
ቀትር ላይ ዋልተር ኮውፊልድ ከእርሻ ቦታ ሲመጡ፣ የሳህንና የብርጭቆ ኳኳታ ከዋናው ቤት ሰሙ፡፡ በፍጥነት ወደ ሳሎኑ አመሩ፡፡ ደረጃው ስር ሚስታቸውን ወድቃ አገኟት። ጠረጴዛው ተገለባብጧል። እቃዎች ተበታትነዋል፡፡ ሳህኖች ተሰባብረዋል።
“ሜሪ! ሜሪ! ተጎዳሽ?” አሉ ዋልተር፤ በፍጥነት ወደ ሚስታቸው ጎንበስ ብለው።
የማርኒ እናት ዓይኖቿ በእንባ ጭጋግ ተሸፍነው “ዋልት! የፈጣሪ ያለ! ዋልት- ውድ መላዕክቶቻችን- ገንዳ ውስጥ -አዎ! ውድ መላእክቶቻችን!!!” አለች የእንባዋ ጎርፍ በፊቷ ላይ እየፈሰሰ።