Administrator

Administrator

ቤሣ ቤስቲን የሌለውና የሚልሰው የሚቀምሰው ያጣ አንድ ልብስ-ሰፊ፣ ጫካ ለጫካ ሲዞር አንድ አይሁዳዊ ነጋዴ ያገኛል፡፡ በልቡ “መቼም ይሄ አይሁድ መዓት ብር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እሺ ቢል በደግነት፣ እምቢ ቢል በጉልበት፣ ያለ የሌለውን ገንዘብ ሊሰጠኝ ይገባል” ብሎ አሰበ፡፡
ወደ አይሁዱም ዘንድ ሲደርስ፣
“ያለ የሌለህን ገንዘብ አምጣ፡፡ አለበለዚያ አሳርህን ታያለህ፡፡ ከዚያም አሻፈረኝ እላለሁ ካልክ ህይወትህን ትከፍላለህ” አለው፡፡
አይሁዱም፤
“ወዳጄ፣ እኔም እንዳንተው ገንዘብ የቸገረኝ ሰው ነኝ፡፡ ኪሴ ውስጥ ያለችኝ ሁለት ብር ብቻ ናት፡፡ ያም ሆኖ ካንተ ችግር የእኔ ይብሳል የምትል ከሆነ፤ ግዴለም አንድ አንድ ብር እንካፈል” አለው፣ በትሁት አንደበት፡፡
ልብስ - ሰፊው ግን አይሁዱ የሚለውን አላመነም፡፡
“ደሞ አይሁድ መቼ ነው ገንዘብ አጥቶ የሚያውቀው? አንተ ቀጣፊ እኔን ለማጭበርበር ፈልገህ ነው?” ብሎ፤ በያዘው በትር ይመታዋል፡፡ አይሁዱ ይወድቃል፡፡ የወደቀው አንድ ድንጋይ ላይ ኖሮ ጭንቅላቱን ከፉኛ ይጎዳዋል፡፡ ብዙ ደምም ይፈስሰዋል፡፡ ህይወቱ ጣር ላይ ትሆናለች፡፡ ነብሱ ከመውጣቷ በፊት፤
“ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች!” አለ፡፡
ከዚያም ህይወቱ አለፈች፡፡
ገዳዩ የአይሁዱን ኪስ እየፈተሸ ገንዘብ መፈለጉን ቀጠለ፡፡ ያገኘው ግን ያቺኑ አይሁዱ ያላትን ሁለት ብር ብቻ ነበር፡፡ እሷኑ ወስዶ ሲያበቃ፣ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ጫካው ሰዋራ ስፍራ ጥሎ መንገዱን ቀጠለ፡፡
ከጫካው ርቆ ሲሄድ ውሎ ወደ አንድ ከተማ ደረሰ፡፡ እዚያም ዋለ አደረና እድል ቀንቶት አንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ፡፡ ከዓመት ዓመት እድገት እያገኘም ሄደ፡፡ ሰንብቶም የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነ - ግን እጅግ ክፉ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ተንኮለኛ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ሰው ሁሉ የሚጠላው ሥራ አስኪያጅ፤ ሆነ፡፡ ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥርም ባለፈው ግፍና በደሉ ተፀፅቶ ደህና ይሆናል ሲባል፤ ጭራሽ ክፋቱ ባሰበት፡፡ ሰውነቱ ግን ከቀን ቀን እየከሳና እየመነመነ ሄደ፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው “የመክሳቷ ብዛት፤ የቸኮለ ይቀብራታል፤ እያለ ይሳለቅበት ጀመር፡፡
የኩባንያው ባለቤት አንዲት ቆንጆ ልጅ ነበረችው፡፡ ይህቺ ልጅ ይህንን ሥራ አስኪያጅ ታፈቅረዋች፡፡ እሱም ያፈቅራታል፡፡ ይጋቡና ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ይወልዳሉ፡፡
ከዚያ በኋላ የኩባንያው ባለቤትና ሚስትየው ሲሞቱ፤ ልብስ ሰፊውና ወጣቷ ባለቤቱ ኩባንያውን ይወርሳሉ፡፡
አንድ ቀን ያ ልብስ ሰፊ ቤቱ፤ መስኮቱ አጠገብ ተቀምጦ፣ ባለቤቱ ያመጣችለትን ቡና ሊጠጣ ስኒውን ወደ አፉ ሲያቀርብ፤ በመስኮቱ የምትገባዋ ፀሀይ ቡናው ላይ ስታንፀባርቅ፣ ግድግዳው ላይ የክብ ቀለበቶች ምስል ሰራች፡፡ ልብስ - ሰፊውም “አይ ፀሐይ! ሚስጥሬን ወደ ብርሃን ልታወጪ እየሞከርሽ ነው፡፡ ግን አትችይም” አለ፡፡
አጠገቡ ሆና ይህን ስትሰማ የነበረችው ባለቤቱ በጣም ደንግጣ፤
“የሰማያቱ ያለህ! ብቻህን ታወራ ጀመረ? ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ፀሀይ የምታወጣው ሚስጥርስ ምንድነው?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡


ልብስ -ሰፊውም፤ “ይሄንን ልነግርሽ አልችልም” ይላታል፡፡
እሷም፤ “እውነት ከልብህ የምታፈቅረኝ ከሆነ ንገረኝ፡፡ የምትነግረኝን ሚስጥር ከአፌ አንዲት ቃል ላላወጣ ቃል እገባልሃለሁ” አለችው፡፡ ከዚያም ካልነገርከኝ ብላ አላስወጣ አላስገባ አለችው፡፡ እረፍት ነሳችው፡፡
በመጨረሻም፣ ለማንም እንደማትነግር ቃል ከገባችለት በኋላ፤ ከዓመታት በፊት አይሁዱን እንዴት እንደገደለውና ከመሞቱ በፊትም፣ “ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች” እንዳለው ነገራት፡፡ ቀጥሎም “ታዲያ በአሁንዋ ቅጽበት ፀሀይ በመንፀባረቋ ግድግዳው ላይ ቀለበት ስትሰራ አይቼ፣ ፀሐይን ’አትልፊ ጉዱን አታወጪውም‘ ስል ሰምተሽ አንቺ ጠየቅሺኝ” አላት፡፡ “ግን ነግሬሻለሁ፣ ለማንም እንዳትናገሪ!” ሲል ደጋግሞ አስጠነቀቃት፡፡ እሷም ደጋግማ ቃል ገባች፡፡
ልብስ ሰፊው ወደ ስራው ሲሄድ ሚስቱ የምትወዳት ጓደኛዋ ጋር ሄዳ ሲጨዋወቱ፤ በጣም ስለምታምናት፤ ታሪኩን ነገረቻት፡፡ ከዚህ ወዲያ ሦስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድፍን አገር አወቀው፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ እንዲሉ፡፡
ልብስ ሰፊው ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ለዓመታት ሲመላለስ ቆይቶም በመጨረሻ ሞት ተፈረደበት፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ ብሩህዋ ፀሀይ ግን ጉዱን ወደ ብርሃን አወጣችው፡፡
*   *   *
ማናቸውም ክፉ ተግባር፣ ማናቸውም ጉድ የማታ ማታ ወደ ብርሃን ይወጣል፡፡ ብሩህዋ ፀሀይ ከማጋለጥ ወደ ኋላ አትልም፡፡ “ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን” ይሏልና፣ በሌላው ላይ የጎነጎኑት ተንኮል፣ የሸረቡት ሴራ፣ ጊዜ አመቸኝ ብሎ የዋሉት ግፍ፤ ጊዜው ይጠርም፣ ይርዘምም ሰሪውን እንደ ጥቁር ጥላ ተከትሎ መምጣቱና በአደባባይም መታየቱ፤ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታና ህብረ - ቀለም ያላቸውን ማህበረሰብ ባቀፈችው ሀገራችን እየተካሄደ ባለው የዲሞክራሲን መሰረት የመጣል ረዥም ጉዞ ውስጥ፣ ለለውጥ ስንዱ የሚያደርጉን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ተመቻችተው ሳለ፤ ለውጡ የተሸራረፈ አሊያም ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ያደረጉ አያሌ ክስተቶችን አይተናል፡፡
ከቶውንም የመሰረት ደንጊያ፣ ልስንና ማገር ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉትን እሴቶች፣ ማለትም የሰብዓዊ መብቶችን፣ ፍትህና ርትዕን፣ የዲሞክራሲያዊ መብት አላባውያንን ወዘተ ሁሉ በአግባቡ ውል ለማስያዝ እንዳይቻል፣ በየጊዜው እንቅፋት የሆኑ አያሌ ክስተቶችን አስተውለናል፡
በመንግስትነት ደረጃም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ፣ በውስጣዊ መሰነጣጠቅም ሆነ በውጫዊ ተጽእኖ፣ ለዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል ከሀገር በፊት ፓርቲንና ድርጅትን ፍጹም በሆነ መልኩ ማስቀደም፣ ስልጣንን ለማጋራት ቅንና ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለመከተልና ከእኔ ወዲያ ላሳር ማለት፤ ሙስናዊ አካሄድ ማዘውተር፣ ላልተዘጋጁበት ድልም ሆነ ሽንፈት ብስለት ያለው ምላሽ አለመስጠትና እርስበርስ ሲጠላለፉ መኖር፣ አንኳር አንኳሮቹ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየአንዳንዷ እርምጃ ውስጥ ህዝቡን አለማሰብ ዋና እንከን ነው፡፡ የህንድ መሪ የነበሩት ማህተመ ጋንዲ በትግሉ ወቅት ያሉትን መጥቀስ እዚህ ጋ ፋይዳ ይኖረዋል፡- በወቅቱ ለጨቋኞቹ ገዢዎች ያሏቸው ይህንን ነበር፡-
“እንዳሻችሁ ልትቆራርጡንና ልትበጣጥሱን ትችላላችሁ፡፡ በመድፍ አፍ ላይ እያሰራችሁ ብትንትናችንን ልታወጡንም ትችላላችሁ፡፡ ምንም አድርጉ ምን ከእኛ (ከህዝቦች) ፈቃድ ውጪ ለምታደርጉት ማናቸውም ድርጊት ቅንጣት ድጋፍና እርዳታ አናደርግላችሁም፡፡ ያለ እኛ ድጋፍና እርዳታ ደግሞ አንድም እርምጃ ወደፊት እንደማትሄዱ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እርግጥ ይሄንን ስናገር በስልጣን ሰክራችሁ ከት ብላችሁ ትስቁ ይሆናል፡፡”
የህዝቡን የልብ - ትርታ ከልብ ማድመጥና ለዲሞክራሲያዊነት ግልጽ - ተገዥነት ካሳየንና አልፎ ተርፎም “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሳንል ስህተትን ለማረምና ለመቻቻል ሆደ - ሰፊነቱን ካደለን ደረጃ በደረጃ ወደ ሰለጠነና ወደ በለፀገ ህብረተሰባዊ እርከን ለመሸጋገር እድሉ ይኖረናል፡፡ ራሳችንን ከድርጅታዊ ቅጽር ማውጣት ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ በሰፊ ግቢ ውስጥ እንዳለና ብዙ መጫወቻ እንደተገዛለት የሀብታም ልጅ፣ በወጉ እንኳ ሳንጠቀምባቸው መጫወቻዎቹ የጎረቤት ሲሳይ ይሆናሉ፡፡
የዘመኑ ጀግንነት ዲሞክራሲያዊነት እንጂ ማናቸውም የኃይል እርምጃ አይደለም፡፡ የሥልጣኔ ቆራጥነት በውይይትና በምክንያታዊ ሙግት መረታታት እንጂ እያደቡ መጠፋፋትና አንዱ ለአንዱ መቃብር መቆፈር አይደለም፡፡ ከየመንገዳችን ሁሉ በኋላ ዛሬም አገርና ህዝብ አለ፤ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡
የትላንት ታሪካችንን ለማደስ ዝግጁ አለመሆን ክፉ እርግማን ነው፡፡ ከስልጣን ውጣ - ውረድ፣ ከፓርቲ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ባሻገር የአገር አደራ መኖሩን አለመርሳት የታላላቅ ፖለቲካዊ መሪዎች ሁሉ እፁብ ዓላማ ነው፡፡ ያለፈ ስህተታችንን ለማረም ልቦናችን ውስጥ አንዲት የመፀፀቻ ጥግ ልትኖረን ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “አማራ ክልል፤ የብልጽግና መንግስት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም መንግስት አግኝቶ አያውቅም” ሲሉ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በርካታ  የልማት ሥራዎች  እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  ሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ  ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ አባላት መካከል የአማራ ክልልን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያነሱት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር አበባው ደሳለው ይገኙበታል፡፡
 “በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብሶት አለ። በተለይም በአማራ ክልል ያለው ችግር ደግሞ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ምስቅልቅል እንዲሆን ያደረገ ነው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ “አሁንም ንጹሃን ዜጎች በከባድ መሳሪያና በድሮን እየሞቱ ነው። ሲቪል ተቋማት የሚባሉ የጤና ጣቢያና ትምህርት ቤቶች እየወደሙ ነው። በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልልና በተለያዩ አካባቢዎች እስር ቤቶች የተጨናነቁት ያለፍርድ በታጎሩት አማራዎች ነው” ብለዋል።
ዶ/ር አበባው ለጥቀውም፤ “መንግሥት የሰላምና የፀጥታ ችግርን ለመፍታት እየሄደ ያለው አካሄድ ወታደራዊ ነው፡፡ ፖለቲካዊ አካሄድን ለምን አልደፈረም? ለምንድን ነው ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ መንግሥት የደከመው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ አክለውም፤ “ለእውነተኛ ድርድርና ውይይት በይፋ ጥሪ አቅርቦ ችግሩን ለምንድን ነው ለመፍታት የማይተጋው? የጅምላ እስር፣ የጅምላ ግድያስ የሚቆመው መቼ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችንም ሰንዝረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ምላሽም፤ “በአማራ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር  ንግግር አለ፤ ነገር ግን ንግግር የሚያደርጉትንና ሰላም የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት  ከዚህ መንግሥት ጋር ትነጋገራለህ  ብለው የሚወቅሱ ሰዎች አሉ” ሲሉ ለንግግር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ጠቁመዋል፡፡


ከሃይል እንቅስቃሴ ይልቅ ሰላም “እጅግ አዋጭ” መሆኑን  የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ከልጅነት አንስተን ክላሽ ተሸክመን ስለኖርን ጉዳቱ ይገባናል። ጦርነትን በወሬ ሳይሆን በተግባር እናውቀዋለንና አንፈልገውም። ብዙዎችን ቀጥፎብናል አንፈልገውም” ሲሉ ተናግረዋል።
“አማራ [ክልል]ን ባለፉት ሰድስት ዓመታት የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል። [ይህን] የማያምን ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባህር ዳር፣ ቡሬ ሄዶ ይቁጠር። ጨርቃ ጨርቅ፣ ሲሚንቶ፣ ማርብል፣ ግራናይት፣ የዘይት ፋብሪካ ብዙ ብር አግዘን አማራ ክልል አቋቁመናል” በማለት አስረድተዋል።
“አማራ ክልል የብልጽግና መንግስት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም መንግስት አግኝቶ አያውቅም። በወሬ ስለተደባበቀ እንዳትሸወዱ።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ጎንደር ከተማን በምሳሌነት በመጥቀስ “ያን ስልጡን ሕዝብና አገር  ከ70 እና 80 ዓመት በኋላ ዞር ብሎ የሚያየው መንግስት ያገኘው አሁን ነው።


ፋሲል ቀንና ማታ እየተገነባ ነው፣ መስቀል አደባባይ የአዲስ አበባውን መስቀል አደባባይ በሚያኽል መንገድ እየተገነባ ነው። ፒያሳ እያሸበረቀ ነው። መገጭን 18 ዓመት ከቆመ በኋላ 7 ቢሊዮን ብር መድበን ቀንና ማታ እየሰራን ነው።” ብለዋል።
የማዳበሪያ ስርጭትን በሚመለከት፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ቀበሌዎች ከፍተኛ ስርጭት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “አማራ ክልል እንዲቀየር እየሞከርን ነው።” በማለት ተናግረዋል።
የጋዜጠኞችና የማሕበራዊ ሚዲያ አንቂዎች መታሰርን በተመለከተ ለቀረበ ቅሬታ በሰጡት ምላሽ፤ “አንድ እግር ሲኦል፣ አንድ እግር ገነት አኑሮ መቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም። ወይም የገነትን ፍሬ መብላት፣ ወይም የሲኦልን እሳት መቅመስ ነው። አንዳንድ ሰዎች እዚህም ሰላም ውስጥ አሉ፣ እዛም ጦርነት ውስጥ አሉ፤ የመረጃ ችግር ያለብን እንዳይመስላችሁ።” ሲሉ አብራርተዋል፣ አስጠንቅቀዋልም፡፡
“ባለፉት ስድስት ዓመታት አማራን የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርገናታል፡፡ አማራ ክልል የብልጽግና መንግሥት የፈጠረውን ኢንዱስትሪ በየትኛውም ዘመን አግኝቶ አያውቅም፡፡ የአማራ ክልል ላይ እኛ ልማት ነው እያመጣን ያለነው፤ ልማቱን እንደልባችን እንዳንሰራ ያደናቀፉን ሰዎች ግን አሉ” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ተችተዋል፡፡  


ከጅምላ እስር ጋር በተያያዘ ከም/ቤቱ አባል ለተነሳው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ  ሲመልሱ፤ “በጅምላ የፓርላማ አባላት፣ በጅምላ የፖለቲካ ሰዎች የምናስር ቢሆን እርስዎም ይታሰሩ ነበር። በጅምላ አይደለም፤ በግብር ነው ሰው የሚታሰረው” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ አክለውም፤ ”የግል ምርጫዬን ከጠየቁኝ እኔ ‘ቢቀር’ ነው የምለው። ይቅር ተባብለን፣ ትተን፣ በደለኛ ካለ ክሰን በሰላም አገራችንን እናልማ። ከዚህም ይውጣ፣ ከዩኒቨርሲቲም ይውጣ፣ ከከተማ እስር አይጠቅምም፤ ግን መንግስት ነን፤ መኖሪያ ቤት እንገነባለን፤ ማረሚያ ቤትም እንገነባለን።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

     የጋሽ ማህሙድ አሕመድ የመጨረሻ የሙዚቃ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ የሙዚቃ መድረክ ላይ ጥቂትና የተመረጡ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተነግሯል።
ትናንት ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ላሊበላ አዳራሽ ስለ ኮንሰርቱና ስለ አንጋፋው ድምጻዊ የሙዚቃ ህይወት ስንብት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው አርቲስት  አብርሃም ወልዴ፣ የጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር መስራችና ባለቤት አቶ አጋ አባተን  ጨምሮ ሌሎች አባላትን ያካተተው የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ በመግለጫው ላይ እንዳብራራው፤ “ሰው  በሕይወት እያለ የማመስገንና የማክበር  ባህልን ለመጀመር ጋሽ ማህሙድ ትክክለኛ ሰው ነው።” ብሏል፡፡ ኮሚቴው አክሎም፤ “ታላቅን ማክበር በተዘነጋበት ዘመን ዝቅ ብሎ  ታናሹን የሚያከብር ሰው” መሆኑ ለተመሰከረለት ጋሽ ማህሙድ፤ በህይወት እያለ ማክበርና ማመስገን ተገቢ እንደሆነ የኮሚቴው አባላት   አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መግለጫ እንደተነገረው፤ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. “ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ኮንሰርት” በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን፤ 25 ሺ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኮሚቴው አባላት አንዱ የሆነው አርቲስት  አብርሃም ወልዴ ኮንሰርቱን በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ፤ “የጋሽ ማህሙድን ክብር በጠበቀ ሁኔታ፣ ጥቂት ነገር ግን ምርጥ ድምጻውያን የሚያቀነቅኑበት መድረክ ነው የሚሆነው” ሲል ተናግሯል።


የሙዚቃ ኮንሰርቱን የሚያዘጋጀው ላለፉት 10 ዓመታት ኮንሰርቶችንና ሌሎች ኹነቶችን በጥራትና በስኬት በማዘጋጀት ዕውቅናን ያተረፈው ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር

 

ኑ ታውቋል፡፡

 

በዘርፉ ስላለው ልምድና ብቃት ምስክርነቱን የሰጠው አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ዛሬ ራሱ በሸራተን አዲስ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥሩ ማሳያ ነው ብሏል፤ በአድናቆት፡፡ በእርግጥም ሌሎች እንግዶችና ጋዜጠኞችም የሸራተኑ ጋዜጣዊ መግለጫ የተዘጋጀበትን ውበትና  ድምቀት አወድሰዋል - መግለጫ ሳይሆን የኮንሰርት ዝግጅት ነው የሚመስለው በማለት፡፡   ከሙዚቃ ኮንሰርቱ በተጨማሪ፣ ለጋሽ ማህሙድ መታሰቢያ የሚሆንና በውጭ አገር የተቀረጸው ሐውልት አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚቆም ያስረዱት የኮሚቴው አባላት፣ በድምጻዊው ስም መንገድ እንደሚሰየምም አብራርተዋል። ከመንገድ እና አደባባይ ስያሜ ጋር በተገናኘ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን ገልጸው፣ እስከ ኮንሰርቱ መዳረሻ ቀን ድረስ “ጉዳዩ ውሳኔ ያገኛል ብለን እናምናለን” ሲሉ ቴስፋቸውን ገልጸዋል፡፡


ከኮሚቴው አባላት አንዷ የኾነችው እንስት በሰጠችው አስተያየት፤ ጋሽ ማህሙድ በህይወት ሳለ በስሙ መንገድ ተሰይሞለት፣ ሃውልት ቆሞለት ቢያይ፣ ለእኛ የሕይወት ዘመን ስኬታችን  ነው ብላለች፡፡
ኮንሰርቱ በሚካሄድበት ዕለት 10 ዓመት ገደማ እንደፈጀ የተነገረለት  የጋሽ ማህሙድ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ እንደሚመረቅ እንዲሁም፣ የመንገድ ስያሜውና የሃውልቱ መቆም እንደሚበሰር  የኮሚቴው አባላት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የአንጋፋው ድምጻዊ የመጨረሻ የሙዚቃ ሲዲ  ተሰርቶ መጠናቀቁን የገለጸው አብርሃም ወልዴ፤ ሥራው ሙሉ በሙሉ አዲስ እንደሆነና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ መሰራቱን ጠቁሟል፡፡
በ550 ገጾች የተቀነበበውና በጋሽ ማህሙድ አሕመድ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው መጽሐፉ፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ  በንብ  ባንክ ድጋፍ ለህትመት መበቃቱን ጋዜጠኛ ወሰንየለህ ደበበ ተናግረዋል። “የ2017 ጥር ወር ታላቅ የኪነ ጥበብ ገጸ በረከት አድርገን ለህዝቡ እናቀርበዋለን” ብለዋል፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ።
ጋሽ ማህሙድ ትውልዱን መመረቅ እንዲሁም ዕድሜ ዘመኑን ሥራዎቹን በፍቅር ሲያደምጥለት  የኖረውን  ሕዝቡን ማመስገን እንደሚፈልግ የገለጹት  የኮሚቴው አባላት፤ በመጨረሻ የሙዚቃ ኮንሰርቱ መድረክ ላይም ይህንኑ ያደርጋል   ብለዋል፡፡
የትዝታው ንጉስ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ጋሽ ማህሙድ፤ “እንግዳዬ ነሽ”፣ “አታውሩልኝ ሌላ”፣ “መላ መላ”፣ “እቴ ገላ” እና ሌሎች ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎችን ያበረከት አንጋፋና ተወዳጅ  ድምጻዊ ነው።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያቀነቀነው ጋሽ ማህሙድ፤ እ.ኤ.አ በ2007 ቢቢሲ ራዲዮ አፍሪካ በድንቅ ዘፋኝነቱ ”ቢቢሲ ራዲዮ ዎርልድ ሚዩዚክ አዋርድ“ ተሸላሚ አድርጎታል፡፡  በተጨማሪም ጋሽ ማህሙድ ለአገራችን የሙዚቃ ዕድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቶታል፡፡  

በዓመት 130ሚ. መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በኢትዮጵያ አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው በዓመት 130 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፤ በአፍሪካ ትልቁ አውሮፕላን ማረፍያ እንደሚሆንም  ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲሱን አውሮፕላን ማረፍያ ግንባታ  ይፋ ያደረጉት ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ  ላይ ነው።
አዲሱ አየር ማረፊያ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገነባ የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ሁለቱን ኤርፖርቶች የሚያገናኝ የባቡር መስመር እንደሚዘረጋም ተናግረዋል፡፡
 የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው አሁን ባለው አየር ማረፊያ ያለውን መጨናነቅ ከማቃለሉም ባሻገር  የኢትዮጵያን ዋና የአቪዬሽን ማዕከልነት ያሳድጋልም ተብሏል።


እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወደብ ለሌላቸው ሀገራት እንዲህ ያሉ ተቋማት የገበያ ብቻ ሳይሆኑ ስትራቴጂክም ስለሆኑ መጠንከርና መገንባት አለባቸው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ነው ሰፋፊ የኤርፖርት ልማቶች የተጀመሩት ብለዋል፡፡ ጠንካራ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑንም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡  አዲሱ ኤርፖርት ለአየር መንገዱ ሥራውንም ስሙን ለማስፋትና ለማሳደግ እንደሚረዳውም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን የአቪዬሽን ዘርፍ በቀዳሚነት  እየመራ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ አዲስ መሠረተ ልማት ደረጃውን የበለጠ ለማሳደግ ማለሙም ነው የተነገረው፡፡
የአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር የተገለጸ  ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአራት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሮጀክቱ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ  ኢንቨስትመንት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡  ይህ በዚህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 124 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ማዘዙን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አስታውቀዋል፡፡  


“124 አውሮፕላኖችን ማዘዝ ቀላል አይደለም፤ ይህ አስደናቂ ስኬት ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ አየር መንገዱን  አወድሰዋል፡፡ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ፣ በዓመት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያስተናግድም ተናግረዋል፡፡   
እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማስተናገድ በዓመት ከ100 እስከ 130 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል የተባለውን አዲሱን ኤርፖርት ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት መጠናቀቁም ታውቋል፡፡ ይህ  ለኢትዮጵያ  ማንሰራራት ማሳያ ነው፤ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣  ባለፈው ሩብ ዓመት፣ ከጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል  ሽያጭ  ከ31 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ  ማግኘቱን አስታውቋል፡፡  
ተቋሙ፣ ለጅቡቲ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል 10.4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል። ምንም እንኳን ሱዳን በጦርነትና ግጭት ውስጥ ብትሆንም፣ ባለፈው ሩብ ዓመት፣ ከ659,000 ዶላር በላይ ገቢ  ማግኘት ችሏል። ጦርነቱ ካቀደው ሽያጭ ውስጥ 15% ብቻ እንዲያሳካ እንዳደረገው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጠቁሟል፡፡  
ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ የተቋሙ ገቢ የተገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል ዳታ ማቀነባበር ላይ ከተሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ  በሚቀጥሉት አስር  ዓመታት ውስጥ  የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ገቢዋን ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንዳለመች የተገለጸ ሲሆን፤ መንግሥት የኃይል ኤክስፖርት አቅምን ለማሳደግና እንደ ኬንያና ታንዛኒያ ካሉ ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማሻሻል ማቀዱ ተመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ከምታደርጋቸው ምርቶች ዝርዝር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፤በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ እንደሚገኝ ገልጿል። ከህወሓት እና ብልጽግና ፓርቲ ጋር ይሰራሉ ያላቸው አመራሮች፤ የድርጅቱን እንቅስቃሴ እየገደቡ እንደሚገኙ  ፓርቲው አመልክቷል።
ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባራኺ፣ የየዞኖች አስተባባሪዎችና የቁጥጥር ኮሚሽን ሃላፊዎች በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ “ከ1 ሺሕ 500 በላይ አባላትን በማካተት አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራትና ሁሉንም የፓርቲውን መዋቅር በማሰባሰብ ወደ መደበኛ ስራው እንዲገባ ለማድረግ ስትራቴጂ ተነድፏል።” ብለዋል። አክለውም፣ የፓርቲያቸው አንዳንድ አመራሮች የትግራይ ክልልን  አገር ለማድረግ ካለመው ፕሮግራም ወደ አንድነት አስተሳሰብ ያዘነበሉት ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ዶ/ር አብርሃም በላይ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ፓርቲውን ወደ ኋላ  እንደመለሰው ገልጸዋል።


 እነዚሁ አመራሮች አዲስ አበባ ድረስ ሄደው ከሁለቱ ከፍተኛ የፌደራል መንግስት ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት “ፓርቲውን የብልጽግና መሳሪያ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱና በግልጽ ‘ብልጽግና፣ ብልጽግና’ እንደሚሸቱ” የተናገሩ ሲሆን፣ ሌላኛው አመራር ደግሞ “ከህወሓት እና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመቀናጀት ድርጅታችን በእንቅስቃሴ ሳይሆን በመፍረስ ላይ እንዲገኝ ብዙ ሰርቷል ብለዋል። በዚህም የስም ማጥፋት መረጃ በማሰራጨት ፓርቲውን ወደ መፍረስ አፋፍ ከማድረስ ባሻገር፣ በሕግ ሊያስቀጡ የሚችሉ ወንጀሎች “ስለመፈጸማቸው” በዚህ መግለጫ ተነግሯል።
የተወቀሱት የድርጅቱ አመራሮችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንነት በግልጽ ያልተነገረ ሲሆን፤ “ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ ያሉ ጉዳዮች ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚቴ አዋቅሮ እየተመለከተው ነው። በሕግም እየተመረመረ ነው” ሲል አስረድቷል።
“አጸያፊ ኋላቀርነትና አካባቢያዊነትን በማነሳሳት ከፓርቲያችን ዓላማ ጋር የሚቃረኑ ተልዕኮዎችን ያንፀባርቃሉ” በሚል ነቀፌታቸውን ያቀረቡት አመራሮቹ፤ መላው አባሎቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና ህዝቦቻችን ይህንን ተረድተው ኑሯችንን ወደ ስልጣኔ ለመመለስና ታላቋን ትግራይን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን ትግል እንዲደግፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

Friday, 01 November 2024 20:17

ጠበኛ እውነቶች

" ሁሉም ሰው በልቡ  ለማንም ማሳየት የማይፈልገው ቆሻሻ ይኖረዋል፡፡ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ግልፍተኝነት፣ ራስን መውደድ ….. ብቻ አንዱ ይኖርበታል፡፡ ልዩነቱ ብዙዎቻችን ያ ባህሪያችን በአስገዳጅ ሁኔታ ፈንቅሎን ካልተገለጠ በስተቀር ንፁህ፣ ቅን እና ፍፁም እንደሆንን እናስመስላለን፡፡ "

ጠበኛ እውነቶች
በሜሪ ፈለቀ
አምስተኛ ዕትም

ከወር በፊት ብትጠይቁኝ፣ “ይቅርብኝ፤ ከኖርኩበት ሰፈር መነሣት አልፈልግም” ብዬ እከራከር ነበር። ዛሬ ግን “ዕድለኛ ነኝ” እላለሁ። እዚህ ሰፈር ምርጥ የኮንዶሚኒዬም ቤት ውስጥ… አዲስ ኑሮ ተመችቶኛል። ቢሆንም ያደግኩበት ሰፈር ጥዋት ማታ ውል ይለኛል፤ ሆዴ ይባባል - የልማት ተነሺዋ ኑሮና ትዝታ።
ያደግንበት አካባቢ፣ እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ በእውን ተውቦ ሲደምቅ ብናይ ማን ይጠላል? የኮሪደር ልማቱ አጀማመር ታዝባችሁ ከሆነ ደግሞ፣ ያማረ ነገር ለማየት ረዥም ጊዜ የምንጠብቅ አይመስልም። ለኮሪደር ልማት የተመረጡት አካባቢዎች ላይ፣ ገና ካሁኑ በሳምንት ውስጥ ለግንባታ እየተዘጋጁ ነው።
አዲስ አበባ ለአገራችን ታሪክ የምትመጥን መዲና፣ ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ መሆን ይገባታል። የአፍሪካ መሰባሰቢያነቷን፣ የዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ መነሃሪያነቷን የምታስከብር ዘመናዊ ከተማ መሆን አለባት።
ይሄ ሁሉ እንዴት ይቻላል?
ሌላው ይቅርና፣ ለበርካታ ዓሥርት ዓመታት የተዘነጉና የተጎሳቆሉ በርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በተሻለና ባማረ ገጽታ ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። አንዳንዴም ተስፋ ያስቆርጣል። “ያ ሁሉ የተከማቸ የቤት ሥራ እንዴት እንዴት ማስተካከል ይቻላል?” የሚል ጥርጣሬ ይፈጠርብናል።

ያረጁ ቤቶች ሲፈርሱ በዕጥፍ አዲስ ቤት እየገነቡ ነው
አዎ ብዙ የቤት ሥራ ተከማችቶብናል። ነገር ግን በመተከዝ ወይም በመወቃቀስ ምንም የተሻለ ለውጥ አይመጣም።
ለውጥ ሲባል፣ አንዳንዴ የማሳመርና የማስዋብ ሥራ ብቻ ሆኖ ይታየናል።
አዎ፣ አሳምሮ መስራትና ማስዋብ ያስፈልጋል። ነገር ግን የከተማችንን የሥራ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ መሠረተ ልማቶችን በጥራት የመዘርጋትና የመገንባት ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋርም ነው፣ ማሳመርና ማስዋብ የሚኖረው።
ለውጥ ሲባል፣ አንዳንዴ የማፍረስ ጉዳይ ይመስለናል። አዎ፣ የሚፈርስ ይኖራል። በአብዛኛውም አርጅቶ ሊፈርስ የተቃረበ ነው።
ነገር ግን፣ የተጎሳቆለውን ቤት የማፍረስ ጉዳይ ሳይሆን፣ ለተሻለ አኗኗር በሚመች አዲስ ቤት የመተካት ጉዳይ ነው።
ለኑሮና ለጤና የማይመቹ፣ የተጎሳቆሉና የተፋፈጉ አካባቢዎችን እንደ አዲስ ማልማት፣ ተነሺዎችና ነዋሪዎችም ወደ ተሻለ መኖሪያ እንዲሸጋገሩ ማድረግ የኮሪደር ልማት አንድ ዓላማ ነው።
ታዲያ ለብቻው የተነጠለ ሥራ አይደለም። ከሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ጋር የተናበበ ነው። ያረጁ መኖሪያ ቤቶች ለልማት ሲፈርሱ፣ በዕጥፍ አዳዲስ ቤቶችን እየተገነቡ መሆን እንዳለበት ምን ጥያቄ አለው?
60 ሺ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት በአዲስ አበባ አስተዳደር የተጀመረውን ፕሮጀክት መጥቀስ ይቻላል። የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብቻ አይደለም። የሥራና የግብይት ማዕከላት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛና የስፖርት ሥፍራዎችም በፕሮጀክቱ ግንባታ ውስጥ ይካተታሉ።
ፕሮጀክቱ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን፣ ክብር ባለው ሁኔታ አኗኗርን ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድሎችን በብዛት ለመፍጠርም ይጠቅማል።
በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ማሻሻያና በሌሎች መስኮች፣ አዲስ አበባ የቤት ሥራዎች ብዙ ናቸው። እንደ ቤት ሥራዎቿ ብዛት ያህልም፣ ለአገራችን ትልቅነትና ለታሪክ ባለቤትነቷ የምትመጥን መዲና ለመሆን መትጋት ጀምራለች። የሥራ ባህልን፣ የሌት ተቀን ትጋትን ከአገራችን ጋር ማለማመድ ይዛለች።

የአዲስ አበባ አርአያነት ወደ 31 ከተሞች
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት፣ የከተማዋን ኑሮ ለማሻሻል፣ የነዋሪዎችን የሥራና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳደግ መጥቀሙ ብቻ አይደለም ቁምነገሩ።
አዲስ አበባ የአገራችን መዲና እንደመሆኗ፣ ለሌሎች የአገራችን ከተሞች መልካም አርአያ የመሆን ኀላፊነትም ይጠበቅባታል።
እና የአርአያነት ኀላፊነቷን እያሟላች ነው? የአዲስ አበባን ስኬት በማየትና የአሠራር ልምድ በማግኘት 31 የአገራችን ከተሞች ዘንድሮ የኮሪደር ልማት ጀምረዋል።

ከካዛንችስ ወደ ገላን - የልማት ተነሺ ትዝታና አዲስ ኑሮ
ካዛንችስ አካባቢ ነበር ሰፈሯ። አሁን ገላን አካባቢ የኮንዶሚኒዬም ኑሮ ጀምራለች። ትዝታዋን ታካፍለናለች። ሐሳቧን እንዲህ ትነግረናለች።
ኑሯችን እንዲህ ክብራችንን የጠበቀ ሊሆን እንደሚችል አስቤው አላውቅም። ከወር በፊት ብትጠይቁኝ፣ “ይቅርብኝ፤ ከኖርኩበት ሰፈር መነሣት አልፈልግም” ብዬ እከራከር ነበር። ዛሬ ግን “ዕድለኛ ነኝ” እላለሁ። እዚህ ሰፈር ምርጥ የኮንዶሚኒዬም ቤት ውስጥ… አዲስ ኑሮ ተመችቶኛል ትላለች።
ቢሆንም ግን ካዛንችስንም ትወደዋለች።
በካዛንችስ ሰፈራችንና ቤታችን ለኑሮ አመቺ ባይሆንም፣ ያደግኩበት ነው። ጥዋት ማታ ውል ይለኛል። ሳይታወቀኝ ቅር ቅር የሚል ስሜት ይፈጠርብኛል፤ ሆዴ ይባባል። እውነት ለመናገር፣ ከእንቅልፌ ስነሳ ቤታችንም አካባቢያችንም ጸዳ ጸዳ ብሎ ሳየው፣ “አሪፍ” ቢሆንም ግር ይለኛል። ገና አልለመድኩትም።
ጥሩነቱ፣ የከተማው አስተዳደር የተሰጠን ድጋፍ ከጠበቅነው በላይ ነው። የውስጣችንን ስሜት ለማካካስ እያገዘን ነው። ባለፈው ሳምንት፣ 25ሺ ብር በባንክ ሂሳባችን መጥቶልናል። ቀሪው 50 ሺ ብር በቅርቡ እንደሚጨመርልንም ተነግሮናል…
አዲሱ መኖሪያ ቤታችንም ያስደስታል። የተሻለ አኗኗርን የምንጀምርበትና አዲስ የሕይወት ትዝታ የምንፈጥርበት አጋጣሚ ይሆንልናል ትላለች በተስፋ።
የልማት ተነሺዎች የቀድሞ አካባቢያቸው በጥቂት ወራት ውስጥ ገጽታው ተቀይሮ ሲስተካከል፣ የቀድሞው የተጎሳቆለ ሰፈር በጥበብ ተገንብቶ ሲያምርበት መመልከታቸው አይቀርም። የቀድሞ ትዝታ ባይጠፋም፣ ያ ያደግንበትና የምንወደው አካባቢ፣ እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ በእውን ተውቦ ሲደምቅ ብናይ ማን ይጠላል?
ደግሞም፣ የኮሪደር ልማቱ አጀማመር ታዝባችሁ ከሆነ፣ ያማረ ነገር ለማየት ረዥም ጊዜ የምንጠብቅ አይመስልም።
ዘንድሮ ለኮሪደር ልማት የተመረጡት አካባቢዎች ላይ፣ ገና ካሁኑ በሳምንት ውስጥ ለግንባታ እየተዘጋጁ ነው።
የመሠረተ ልማት መሥመሮች እንደቀድሞው በተተበተበና በተዘበራረቀ መንገድ ሳይሆን፣ ሥርዓት ይዞ ከመሬት ሥር ለመዘርጋትም ቁፋሮ ተጀምሯል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ባለ ታሪክ አገር ናት። ነገር ግን ለአገራችን ክብር የማይመጥኑና የተከማቹ በጣም ብዙ ችግሮች አሉብን። የቤት ሥራዎቻችንም የዚያኑ ያህል ብዙ ናቸው።
የባሕር በር፡
በባሕር ንግድ በዓለም ዙሪያ የምትታወቅ አገር ነበረች - ኢትዮጵያ። ዛሬ ግን የባሕር በርና የንግድ መተላለፊያ የላትም። ለአገራችን ክብር የማይመጥን ትልቅ ስብራት ነው። ይሄን የመጠገን የቤት ሥራ አለብን። ሥራው ተጀምሯል። ነገር ግን ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። ገና ብዙ ይቀራል። ወደ ፍሬ እንዲደርስ በብርቱ ጸንተን፣ በአገራዊ መንፈስ ተባብረን መሥራት የኛ ድርሻ ነው።
ለአገራችን ክብር የሚመጥ ታሪክ መሥራት የኛ ድርሻ ካልሆነ፣ ማን መጥቶ ይሠራልናል? አዎ፣ የመንግሥት ኀላፊነት ነው። ነገር ግን፣ የእያንዳንዳችንም ሥራ ነው።
አባይና ሕዳሴ
ወደ ካርቱምና ወደ ካይሮ ከሚደርሰው የአባይውኃ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉ የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ማህፀን ነው። እና በአባይ ውኃ ለመጠቀም ስንሞክር እንደ ጥፋት የሚቆጥሩብን በምን ሒሳብ ነው? አንዲት ጠብታ እንድትነኩ አንፈቅድላችሁም የሚል ዛቻ ሊደርስብንስ ይገባል? ለአገራችን ክብር የማይመጥን ውርደት ነው።
እዚህ ላይም ብዙ የቤት ሥራ አለብን። ሥራችንን ጀምረነዋል። ዓለማቀፍ ተጽዕኖዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ተከራክረን እንቅፋቶችን እያሸነፍን፣ ሕዝባችን በአንድ ልብ ቆሞ፣ እንደየ ዐቅሙ ገንዘብ እያሰባሰበ የሕዳሴ ግድብ ወደ ፍጻሜ ደርሷል።
አንዳች መዓት እንደሚፈጠር እያስመሰሉ እንዳወሩበት ሳይሆን፣ ግድቡ እስከ አፉ ውኃ ሊሞላ ምንም አልቀረውም። ይህም ብቻ አይደለም።
ኢትዮጵያና ሌሎች የአባይ ቤተሰብ አገራት ያልተሳተፉበት፣ የቀድሞ የቅኝ ግዛት ውሎችን አሜን ብለን እንድንቀበልና የአባይን ውኃ ላለመንካን እንድንገዘት ሲካሄድብን የነበረ የዲፕሎማሲ ዘመቻ እስከወዲያኛው የሚመክንበት ጊዜም እየተቃረበ ነው። በፍርደ ገምድ የቅኝ ገዢዎች ውል ምትክ አዲስ ፍትሐዊ ዓለማቀፍ የአባይ ወንዝ ውል በይፋ ጸድቋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአባይ ቤተሰብ አገራት ተስማምተው ተፈራርመውበታል።
ከሕዳሴ ግድብ ስኬት ጎን ለጎን፣ አዲሱ አለማቀፍ ውል፣ ለአገራችን ተጨማሪ የስኬት እመርታ ነው። በኢትዮጵያ መሪነትና አስተባባሪነት የተገኘ ስኬት መሆኑ ደግሞ፣ የመንፈስ ብርታት ሊሆንል ይችላል። የአገራችንን ታሪካዊ ክብር ማደስና ወደ ከፍታ ማድረስ እንደምንችል የሚመሰክር ስኬት ነውና።
እንዲህም ሆኖ ገና ብዙ የቤት ሥራ ይቀረናል። የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም።
እርዳታና የመስኖ እርሻ
ኢትዮጵያ ከቀደምት የሥልጣኔና የብልጽግና ማዕከላት መካከል አንዷ ናት ተብላ በታሪክ የምትጠቀስ አገር ነበረች። ለበርካታ ዓመታት ግን ስሟ በእርዳታ ጠባቂነት የሚነሣ አገር ሆናለች።
ብዙ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ስደት ከቤት ወጥተው፣ የበረሀ አሸዋ ሰለባ፣ የባሕር ውኃ ሲሳይ ሆነዋል እየተባለ በዓለም ዜና ይነገራል። ይሄን ስብራት የመጠገን የቤት ሥራም አለብን።
ከባድ ነው ብለን ልንተወው አንችልም። በክረምት የዝናብ እርሻን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ በበጋ የመስኖ እርሻንም ማስፋፋት እንደሚቻል በተግባር እያየን ነው። በእንስሳት እርባታም እንዲሁ ብዙ ሥራ አለብን።
የምንዛሬ ማስተካከያና የኤክስፖርት ዕድገት
የተዛባውን የገንዘብና የምንዛሬ ሥርዓት ማስተካከል ለጊዜው ሕመም ቢኖረውም፣ መንገዳችንን የሚያቃና ሌላ ዘዴ እንደሌለ ከውጤቱ ማየት ጀምረናል።
በሦስት ወራት ውስጥ የአገሪቱ ኤክስፖርት ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር ዕጥፍ ሊሆን ምንም አልቀረውም። ከ800 ሚሊዮን ዶላር ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ነገር ግን አሁንም ብዙ ይቀረናል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናትና።
የአፍሪካ እግር ኳስና የስታድየም ኪራይ
የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች የሆነች አገር፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከአፍረካ ዋንጫ አዘጋጅ መሆን አልቻለችም። የኢትዮጵያ ቡድን ለአህጉራዊ ውድድሮች፣ በሌሎች አገራት ስታዲየም ተከራይቶ መጫወት ግድ ሆኖበታል። ይሄም የስብራት ምልክት ነው። ይህን መጠገንና የአገራችንን ክብር ማደስ አለብን። ደግሞም ተጀምሯል። በዚህ ሳምንት እንደ ሰማነው፣ ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ በብቃት ማዘጋጀት ትፈልጋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለአህጉሪቱ የእግር ኳስ ፌደረሽን ተናግረዋል።
ዓለማቀፍ ደረጃቸውን ያሟሉ ስታዲዮሞች እንደሚጠናቀቁና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮችን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሚሆኑ ጠ/ሚ አብይ ገልጸዋል። የአገሪቱ ከተሞችና የመሠረተ ልማት አውታሮችም በሥርዓት እየተሻሻሉ የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በብቃት ይሰናዳሉ ብለዋል - ጠ/ሚ አብይ። ድንቅ የታሪክና የተፈጥሮ መስህቦችም ለጎብኚዎች ተመቻችተው ይዘጋጃሉ፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል መሆኗን ለማስመስከር ይረዳሉ ተብሏል።
ብሪክስ እና ፋይዳ ያለው ክብር
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደመሆኗ፣ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም መድረክም ትልቅነቷን የሚመጥን ቦታ ማግኘት አለባት። በቀላሉ የሚሳካ አይደለም። ብዙ ጥረት ይፈልጋል። እንደሚቻል ግን ሰሞኑን በራሺያ ከተካሄደው የብሪክስ አገራት መሪዎች ስብሰባ መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ የ”ብሪክስ” አገራት ውስጥ መካተቷ አንድ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ የብሪክስ አባልነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ፋይዳዎች የሚመነዘር መሆን እንዳለበት ጠ/ሚ አቢይ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
እንግዲህ…
የባሕር በርና የንግድ መተላለፊያ መሥመር…
የአባይ ውኃና የሕዳሴ ግድብ…
የምንዛሬ ማስተካከያና የኤክስፖርት ዕድገት…
የእርዳታ ጠባቂነት ስብራትና የመስኖ እርሻ…
የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራችነትና የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት…
የብሪክስ መድረክና ፋይዳ ያለው ዓለማቀፍ ክብር…
እነዚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስናቸው እንጂ፣ የቤት ሥራዎቻችን ብዙ ናቸው። ተጀምረው የሚቀሩ አይደሉም። ውጤታቸውም እንዲሁ በጅምር የሚቀር ሳይሆን እየበረከተ የሚሄድ ነው።
እዚህ ላይ፣ “ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?” ብለን እናስብ ይሆናል።
በእርግጥም፣ ለብዙ ዘመን የተከማቹ ችግሮችን መዘርዘር ለአገራችን አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን እንደተለመደው ስህተቶችንና ጥፋቶችን እየዘረዘርን ወቀሳ ለመወራወር፣ የቅሬታ ብዛት እየደረደርን ለመወዳደር፣ እያማረርን አንጀታችንን ለማሳረር አይደለም።
ከቀድሞው ስህተቶች እየተማርንና መፍትሔ እያበጀን፣ መልካም ታሪኮችን ደግሞ እያከበርንና አርአያነታቸውን እንደ መንደርደሪያ እየተጠቀምን፣ ተጨማሪ መልካም ታሪክ መሥራትና ወደ ላቀ ከፍታ መጓዝ ነው - የቤት ሥራችን።