Administrator
አንጎልን የሚጎዱ አጓጉል ልማዶች ቁርስ አለመመገብ
ቁርስ አለመመገብ
ቁርሳቸውን የማይመገቡ ሰዎች በደማቸው ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ይህም ለአንጎል መድረስ ያለበትን ንጥረ ነገር በማስቀረት አንጎል በተገቢው ሁኔታ እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡
ከመጠን በላይ መመገብ
ከመጠን በላይ መመገብ የአንጎል የደም መተላለፊያ ቧንቧዎችን ያደድራቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአዕምሮን ኃይል ይቀንሳል፡፡
ማጨስ
ሲጋራ ወይንም ሌሎች አደገኛ ዕፆችን ማጨስ በርካታ የአንጐል ችግሮችን ከማስከተሉም ሌላ አልዚመር ለተባለ የአዕምሮ ህመም ሊያጋልጥም ይችላል፡፡
ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ
ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ፤ አንጎል ፕሮቲኖችንና የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳያውል ያሰናክላል፡፡ ይህም አንጎል አስፈላጊ ንጥረነገሮች እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡
ጭንቅላትን ተሸፋፍኖ መተኛት
በመኝታ ሰዓት ጭንቅላትን በአንሶላ፣ በፎጣ ወይም በብርድልብስ ተሸፋፍኖ መተኛት የካርቦንዳይኦክሳይድ ክምችትን ይፈጥራል፡፡ ይህም በአንጎላችን ውስጥ ያለውን የኦክስጅን ክምችት ይቀንሳል፡፡ በዚህ ምክንያትም አንጎላችን ለአደጋ ይጋለጣል፡፡
ነፃ ገበያ ይለምልም!
ለምን መሰላችሁ ነፃ ገበያን ያወደስኩት? በእኛ አገር “ጨመረ” እንጂ “ቀነስ” የሚባል ነገር ጠፍቶ፣ “ቀነሰ” የሚለው ቃል ካልጠቀመን ምን ያደርግልናል? ከመዝገበ ቃላት ይፋቅልን! በምንልበት ጊዜ የቀነሰ ነገር በማየቴ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን፣ ዘመድ ሞቶብኝ በተለምዶ ዓለም ባንክ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነበርኩ፡፡ ከቀብር መልስ ውሃ ጥም ሲያቃጥለኝ፣ አንድ ቢራ ልጠጣ ብዬ ግሮሰሪ ቤት ገባሁ፡፡ የምመርጠውን ቢራ ስጠይቅ “አለ” ተባልኩ፡፡ አካባቢው ሩቅ በመሆኑ ዋጋው ይጨምራል በማለት ሰግቼ “ስንት ነው?” አልኩ፡፡ አስተናጋጁ “12 ብር” አለኝ፡፡ መኻል ከተማ ከ13-16 የሚሸጠው ቢራ፣ እዚያ በ12 ብር መገኘቱ እያስገረመኝ ጠጥቼ ወጣሁ፡፡ በሳልስቱም ወደለመድኩት ቤት አመራሁ፡፡ ሁሉም ሰው ፊቱ ያስቀመጠው አዲሱን ቢራ ነው፡፡ የለመድኩትን ቢራ ጠየቅሁ፡፡ የለም ተባልኩ፡፡ ሌላ ቢራ ምን እንዳለ ስጠይቅ፤ አስተናጋጁ ሰዎች ፊት ያለውን እያሳየኝ “ከዚህ በስተቀር ምንም የለም” አለኝ፡፡ ዋጋውን ጠየቅሁ፡፡ 10 ብር አለኝ፡፡ ሌላ አካባቢ 12 እና 13 ብር የሚሸጡ ስላሉ፣ እየተገረምኩ ጠጥቼ ወጣሁ፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ የረር-ጎሮ አካባቢ ነበርኩ፡፡ የምወደውን ቢራ ስጠይቅ አስተናጋጁ “እሱ የለም፤ ይኼን ይጠጡ ጥሩ ነው” አለኝ፡፡ ችግሬ ዋጋው ላይ ነውና “ስንት ነው?” አልኩት፡፡ “10 ብር ነው፡፡ ፋብሪካው‘ኮ ከዚህ አስበልጠን እንዳንሸጥ አስጠንቅቆናል” አለኝ፡፡ የቢራውን ዋጋ የቀነሰው - ፋብሪካው መሆኑን ስሰማ፣ አዲሱ ቢራ ገበያ ውስጥ ለመግባት የቀየሰው ዘዴ ነው በማለት ደስ አለኝ፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ሌላ አስገራሚ ነገር አየሁ፡፡ ቢጂአይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) አርማውን በያዘ ወረቀት ላይ የድራፍት ብርጭቆ እያሳየ ማክሰኞ፣ ሐሙስ፣ ቅዳሜ “Happy Hour” በማለት በየመጠጥ ቤቱ ለጥፎ አየሁ፡፡ እኔ ጊዮርጊስ ቢራም ሆነ ድራፍት ባልጠጣም የንግድ ውድድር የፈጠረው ነው በማለት በጣም ደስ አለኝ፡፡ ድራፍቱ፣ ከሆነ ጊዜ በፊት ዋጋ ጨምሮ ጃንቦው 11 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ አሁን ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ 3ብር ቀንሶ በ8 መሸጥ ጀምሯል፡፡
ጊዮርጊሶች በአንድ ጊዜ 3ብር የቀነሱት፣ ደንበኞቹ በ10 ብር ወዳገኙት አዲስ ቢራ ስላዘነበሉ ጭራሽ እንዳይሸሹት ለማባበል ነው የሚል ግምት አደረብኝ፡፡ ወደፊትም ወደ ገበያው አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ሲገቡ የንግድ ውድድሩ ይጦፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ የንግድ ውድድር ማን ተጠቀመ? ሸማቹ ህብረተሰብ፡፡ ለዚህ ነው ነፃ ገበያ ይለምልም ያልኩት፡፡
“…እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!”
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው ሚስት ፈላጊ ነው፡፡ እናማ…አገባታለሁ ለሚላት ሚስት መስፈርቶች ያወጣል፡፡ ለጓደኛውም … “እኔ የምፈልጋት ሚስት መልካም ባህሪይ ያላት፣ ብልህና ቆንጆ መሆን አለባት…” ይለዋል፡፡
ጓድኝዬው፣ “ታዲያ አስቀድመህ እንደዚህ በግልጽ አትነግረኝም ነበር፣“ ይለዋል፡፡
ሰውየውም፣ “ይኸው ነገርኩህ እኮ…“ ሲል ይመላሳል፡፡
ጓደኝዬው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ገና አሁን ነው ግልጽ የሆነልኝ፡፡ አንተ እኮ የምትፈልገው አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ሚስት ነው፡፡ አንዲት መልካም ባህሪይ ያላት፣ አንዲት ብልህና አንዲት ቆንጆ፡ ሦስቱንም አንድ ላይ የያዘች ሴት ከፈለግህ ልብ ወለድ አንብብ!” አሪፍ አይደል! በቃ… እዚህ ላይ እኮ ይሉኝታ አያስፈልግም፡፡ እሱ ማን የማይሆን ጥያቄ ጠይቅ አለው! ልክ ነዋ… ዘንድሮ እኰ እንትናዬዎቹ በአንዱ ነገር “ክንፍ አላት…” ሲባሉ በሌላው ደግሞ “ከእነጭራዋ ብቅ አለች…” ይባላሉ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንዲህ አይነት ያለ ይሉኝታ እቅጯን የሚናገሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ነገርዬው “…ሦስቱንም አንድ ላይ የያዘች ሴት ከፈለግህ ልብ ወለድ አንብብ!”
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው…ብዙም ከሰው አይገጥምም አሉ፡፡ እናላችሁ…ሠርግ አይሄድ፣ ሀዘን ላይ አይገኝ፣ አብሮ ‘ብርጭቆ አያጋጭ’…በቃ ምን አለፋችሁ በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ምን ይሉታል…
“ያቺ ዱሮ ትወዳት የነበረችው ቆንጆዋ ገርል ፍሬንድህ ባል ሞቷል፡፡ ሁልጊዜ ሀዘን ላይ አትገኝም ስለምትባል ቀብር እንዳትቀር …” ሲሉት ምን ቢል ጥሩ ነው… “እንኳን ሞተ፣ እኔም የምፈልገው እሱን አልነበር…” ይላል፡፡
በሌላ ቀን የሚስቱ ወንድም ይሞታል፡፡ ይህን ጊዜ ቀብር ላይ ተገኝቶ ሳይሰናበት እንኳን በዛው ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ሚስቱና ሌሎች ዘመዶች ሠልስት፣ አርባ ምናምን ሲሉ እሱ አይገኝም፡፡ በዚህ የራሱ ዘመዶች ሳይቀሩ ይበሳጩበታል፡፡ “አሁንስ አበዛው! አንድ ነገር ይደረግ…” ይባባሉና ሄደው የሚያናግሩት ሦስት ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡
ታዲያላችሁ…አንደኛው ሽማግሌ “ለዚህስ ሌላ ሰው አያስፈልግም፣ እኔ ብቻዬን ሀሳቡን አስለውጬ ወደ ጥሩ ኢትዮዽያዊነት እመልሰዋለሁ…” ይላሉ፡፡
ከዛ ይሄዱና እንዲህ ይሉታል…
“አንተ ችግርህ ምንድነው? እኛስ ምን አድርገንሀል! ማንም ሰው ሀዘን ላይ አትገኝም፡፡ አሁንም የሚስትህ ወንድም ሞቶ ቀብር ላይ ብቅ ብለህ በዛው ጠፋህ፡፡ ይሄ ነገር ይብቃ፡ ሰው ቀብር ላይ መገኘት ልመድ...” ይሉታል፡፡
እሱዬው ምን ይላቸዋል… “እኔ ትልቁን በሽታ ገድዬ ቀብሬዋለሁ…” ይላቸዋል፡፡
የተላኩት ሰው ግራ ይገባቸውና… “ምን የሚሉት በሽታ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
እሱም… “ይሉኝታ የሚባል በሽታ…” ይላቸዋል፡፡
ሽማግሌ ሆነው የሄዱትም ሰው ትንሽ አሰብ አድርገው ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “አንተስ ተገላገልከው፣ እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!” ብለው ቁጭ፡፡
እሳቸውም ነገሮችን የሚያደርጉት በይሉኝታ ነዋ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እዚህ አገር ተጋፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ከሲኒማ አድዋ ጋር አብሮ ፈርሷል እንዴ! እኛ ‘ደቃቆቹ’ ግራ ገባና! (በነገራችን ላይ…በአካልም የደቀቅን፣ በፈራንካውም የደቀቅን፣ በሞራሉም የደቀቅን፣ በተስፋውም የደቀቅን… ሰብሰብ ብለን “አይዞህ ለደግ ነው…” “አይዞሽ ሊነጋ ሲል ይጨልማል…” እያልን የምንጽናናበት ማህበር ቢጤ ብኗቋቋም አሪፍ አይደል!
ደግሞላችሁ…አሁን፣ አሁን ደግሞ ክንድና ደረቱን እየተነቀሰ በ‘ቢጢሌ’ ካናቴራ ከተማዋ ውስጥ የሚንጎማለል በዝቷል፡፡ ታዲያላችሁ… በትከሻው ዘፍ ይልባችሁና…አለ አይደል… እሱ በተጋፋው እናንተ በተገፋችሁት ገላምጧችሁ ይሄዳል፡፡ (“ጡንቻ የሚያሳብጥ ኪኒን ከዱባይ እንደ ልብ ይገባል…” የሚባለው እውነት ነው እንዴ!
እናላችሁ…ሲመጡብን ‘ጥግ እንዳንይዝ’…አገሩ ሁሉ ተቆፍሮ ‘የምንለጠፍበት ጥግ’ አጣን፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ይሉኝታ የሚመስል ነገር መነሳት ካለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ ‘መድቀቃችንን’ አይቶ ገፍትሮን ከመሄድ ይቅርታ ማለት ለመንግሥተ ሰማያት ‘ሲ.ቪ.’ ማጠናከሪያ ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ…ዘንድሮ የምንገፈተረው መንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህይወታችን መስኮች ሆኗላ!
ስሙኝማ…በዛ ሰሞን አንድ ሚኒባስ ውስጥ የሆኑ ሦስት ሰዎች ጓደኛቸው ለልጁ የስም መዋጮ እንዲያደርጉ ጠይቋቸው ግራ ገብቷቸው ሲጨቃጨቁ ነበር፡፡ አስቸጋሪ ነዋ…አሁን፣ አሁን እኮ አይደለም ጓደኛ ምናምን ወላጆችም ራሳቸው ስም በማውጣቱ ግራ የተጋቡ ነው የሚመስለው፡፡
ሀሳብ አለንማ…ወይም ወላጆች “ለልጄ ስም አውጣልኝ…” ምናምን ሲሉ…አለ አይደል…አብረው ‘ቲ.ኦ.አር.’ ምናምን የሚባለውን ነገር ይላኩልን፡፡ ስሙ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ልጁ ድንገት የፊልም ተዋናይ ቢሆን ለአፍ የሚጣፍጥ ምናምን ተብሎ እቅጩ ይጻፍልን፡፡
ወይም ደግሞ…“የሚወጣው ስም የአሜሪካን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበና ልጁ በኋላ ዲጄ ሊሆን ስለሚችል ለእሱ የሚስማማ መሆን አለበት…” ተብሎ ይለይልንማ!
እኔ የምለው…የስም ነገር ካነሳን አይቀር…ለልጆች የምንሰጣቸው ስሞቻችንና የቡቲኮቻችን ‘የፈረንጅ ስም’ እየተመሳሰሉብን ነው፡፡ አሀ… ምን ይደረግ… ይሄ ኢንተርኔት የሚሉት ነገር ‘ቆርጦ መለጠፍ’ አስለመደንና ስሞች ሁሉ ‘ከት ኤንድ ፔስት’ እየተደረጉ ነው፡፡
ከሀበሻ እናትና አባት እዚህቹ በግርግር ትንፋሸ ያጠራት ከተማችን ውስጥ የተወለደን ‘ፍራንክ’ ብሎ ስም መስጠት ትንሽ አያስቸግርም፡ ወዳጆቼ እንደዛ አይነት ስም መስማታቸውን ነግረውኛል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል እዚህ አገር… “እሱን እንኳን ተወው፣ እንዲህማ አይደረግም…” ብሎ ነገር እየቀረ ነው፡፡ ሌላ ቦታ ሊደረግ የማይችለው ነገር… ‘አዲስ ነገር መፍጠር’ በማይሰለቻት፣ ‘ከአፍሪካ የመጀመሪያ ከዓለም ሁለተኛ’ ማለት ዓመል የሆነባት አገራችን ውስጥ ሊሆን የማይችል ነገር በጣም ጥቂት ይመስላል፡፡
እኔ የምለው…አንድ ሰሞን ፑሽኪን ‘የእኛ ነው፣ አይደለም’ ምናምን አይነት ሙግት ነበረላችሁ! ‘ቡና አብረን መጠጣት ያቆምናቸው’ ጎረቤቶቻችን በበኩላቸው “ፑሽኪንማ የራሳችን ነው!” እያሉ በላ ልበልሃ ነገሮች ነበሩ፡፡
እኔ የምለው…የፑሽኪን ዝርያዎች ራሳቸው ለመለየት ምስክርነት ቢጠሩ እኮ… “መጀመሪያ ነገር እነኚህ አገሮች የሚገኙት እስያ ነው ደቡብ አሜሪካ?” ብለው ይጠይቁ ነበር፡፡ “አፍሪካ ውስጥ ናቸው ወይ?” ለማለት መጀመሪያ አፍሪካ አገር ሳትሆን አህጉር መሆኗን ማወቅ አለባቸው፡፡ ዓለም ይሄን ያህል ነች፡፡
ልጄ እዛ ይሉኝታ ምናምን ብሎ ነገር የለማ!
ኮሚክ እኮ ነው…በተለይ በአውሮፓ በርከት ባሉ ሀገራት… “መጤዎች ይውጡልን…” “ማንም በራፋችን ዝር እንዳይል…” አይነት ነገር የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች ጉልበታቸው እየጠነከረ ባለበትና ‘ለዓይናቸው እየተጠየፉን’ ባሉበት ዘመን የልጅን ስም አውሮፓዊ እያደረጉ ከመሰረቱ ማንነቱ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚያደርጉ ወላጆች ልብ ይግዙማ!
ሀሳብ አለን… ለአውሮፓ ህብረት የአባልነት ጥያቄ ይቅረብልንማ! ልክ ነዋ! ምድረ የአውሮፓ ከተማ ሁሉ የካፌና የሬስቱራንት መጠሪያ ሆኖ የለም እንዴ! ይህ ‘ወንድማማችነትን ለማጠናከር’ ያለንን ፍላጎት (ቂ…ቂ…ቂ…) ፍላጎታችንን የሚያሳይ አይደለም እንዴ! ቢያንስ ቢያንስ የታዛቢነት ወንበርማ ይገባናል፡፡
ለምሳሌ ‘ጆኒ’ ምናምን ድሮ ማቆላመጫ ነበር፡፡ አሁን ግን መደበኛ ስም ሆኖ ይወጣል አሉ፡፡
በ‘አብዮቱ’ ሁለት ልጆቻቸውን ‘ሆቺ ሚን’ እና ‘ቼ ጉቬራ’ ብለው የሰየሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ የ‘ቦተሊካ ነፋስ’ የነካቸው ስሞች አሉ!
ስሙኝማ… ብሰማው ደስ የሚለኝ አንድ ስም ምን መሰላችሁ… ‘ያለው ሁኔታ ነው ያለው’ የሚል ስም፡፡ ልክ ነዋ…‘ፖፑላር’ ስም ይሆናላ! ደግሞላችሁ… በየስብሰባውና በየቃለ መጠይቁ ሲደጋገም ዘመድ ወዳጅ ሁሉ… “እንዴት ቢወዱት ነው ስሙን እንዲህ የሚደጋግሙት…” ማለታቸው አይቀርማ!
እናላችሁ…ከፍ ብለን የጠቀስነው የይሉኝታ ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል በይሉኝታ ማድረግ የማንፈልጋቸውን ነገሮች እናደርጋለን፣ መቀላቀል የማንፈልጋቸውን ስብስቦች እንቀላቀላለን፣ መሄድ የማንፈልጋቸው ቦታዎች እንሄዳለን፣ በማያስቀው እንንከተከታለን…ብቻ ምን አለፋችሁ… ይሉኝታ ነገራችንን ሁሉ አርቲፊሻል ያደርገዋል፡፡እናማ… ለማግባባት የተላኩት ሰውዬ… “አንተስ ተገላገልከው፣ እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!” እንዳሉት ከልማቱ ጥፋቱ ከሚብስ ይሉኝታ የምንገላገልበትን ዘመን አንድዬ ያፋጥልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!
ከመሸ አትሩጥ ከነጋ አትተኛ
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ አባት የመሞቻው ጊዜ ደርሶ ኖሮ ልጁን ወደ አልጋው እንዲመጣ ይጠራዋል፡፡ ልጁም ይጠጋውና፤
“አባቴ ሆይ ምን ላድርግልህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አባትየውም፤
“ልጄ ሆይ! እንግዲህ የመሞቻዬ ጊዜ ደርሷል፡፡ ነገር ግን አንተን ምድር ላይ ጥዬህ ስሄድ ምንም ያጠራቀምኩልህ ጥሪት ስለሌለ ትቸገራለህ ብዬ ተጨንቄያለሁ፡፡ ሆኖም አንድ አውራ ዶሮ አለኝ፡፡ የዚህን አውራ ዶሮ አጠቃቀም ካወቅህበት ብዙ ሀብት ታፈራበታለህ” ይለዋል፡፡
ልጁም፤ “እንዴት አድርጌ?” አለው፡፡
አባቱም፤ “አውራ ዶሮ ወደማይታወቅበት አገር ሂድ፡፡ የአውራ ዶሮን ጥቅም ንገራቸው” ብሎ ሃሳቡን አስፋፍቶ ተናግሮ ሳይጨርስ ትንፋሹ ቆመ፡፡
ልጅየው አባቱን ከቀበረ በኋላ አውራ ዶሮ የማይታወቅበት አገር ለመፈለግ ከቤቱ ወጣ፡፡ ብዙ አገር ዞረ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቦታ መአት አውራ ዶሮ ስላለ ጥቅሙን ያውቁታል፡፡ በመጨረሻ ወደ አንድ ደሴት ሲገባ አንድም ዶሮ የላቸውም፡፡ ቀን መምሸት መንጋቱን እንጂ ምንም ሰዓት አይለዩም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አላቸው፡-
“ይሄ አውራ ዶሮ ይባላል፡፡ እዩ አናቱ ላይ ቀይ ዘውድ አለው፡፡ እንደ ጀግና ጦረኛም እግሩ ላይ ሹል ጫማ አለው፡፡ ሌሊት ሌሊት ሶስት ጊዜ ይጮሃል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ለእናንተው ጥቅም ነው፡፡ በየአንዳንዱ ጩኸቱ መካከል ያለው የጊዜ ርዝመት እኩል ነው፡፡ በመጨረሻ ሲጮህ ልክ ሊነጋ ሲል ነው ማለት ነው፡፡ ቀን ከጮኸ ደግሞ አየሩ ሊለወጥ መሆኑን መናገሩ ነው ማለት ነውና መዘጋጀት ይኖርባችኋል” አላቸው፡፡
ነዋሪዎቹ ሁሉ ተገረሙ፡፡ የዚያን እለት ሌሊት ማንም የተኛ ሰው የለም፡፡ አውራ ዶሮው በውብ ድምፁ አንድ ጊዜ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ፤ ጮኸ፡፡ ቀጥሎ አስር ሰዓት ላይ ጮኸ፡፡ በመጨረሻም ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ጮኸ፡፡ ህዝቡ ጉድ አለ! ስለዚሁ አውራ ዶሮ ሲያወራ ዋለ፡፡ ነገሩ ንጉሡ ጆሮ ደረሰ፡፡ ንጉሡም እንደ ህዝቡ በሚቀጥለው ሌሊት የአውራ ዶሮውን ጩኸት ሲያዳምጡ አደሩ፡፡ በጣም ተደንቀው ልጁን አስጠርተው፤
“ይሄንን አውራ ዶሮ ትሸጥልናለህ ወይ?” አሉት፡፡
ልጁም “አዎን ግን በወርቅ ነው የምትገዙኝ” ሲል መለሰ፡፡
ንጉሡም፤ “በምን ያህል ወርቅ?” አሉት፡፡
ልጁ - “አንድ አህያ ልትሸከም የምትችለውን ያህል” አለ፡፡
ንጉሡ አንድ አህያ የምትሸከመውን ኪሎ አስጭነው ሰጡትና ወደቤቱ የአባቱን ውለታ እያሰበ ሄደ፡፡ ንጉሡም አውራ ዶሮአቸውን ወሰዱ፡፡ ከዚያን እለት ጀምሮ የዚያ ደሴት ህዝብ ጊዜና ሰዓት ለየ፡፡
***
አውራ ዶሮ የሚሸጥልን አንጣ፡፡ ሰዓትና ጊዜን መለየት ለማንኛችንም ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ “የቸኮለች አፍሳ ለቀመችን”ና “የቆየ ከሚስቱ ይወልዳል”ን ዛሬም ባንረሳ መልካም ነው፡፡ ብልህ አባት ለልጁ የዘለአለም ሀብት ማውረሱን ካስተዋልን ዘላቂ ልማት፣ ዘላቂ አገር ይኖረናል፡፡ ቤትና ቀን የለየ፣ ጊዜና ሰዓት ያወቀ ወደፊት መሄድም፣ ባለበት መቆምም፤ ማፈግፈግም የሚያውቅ የነቃ የበቃ ወራሽ ካለን የነገን ጥርጊያ መንገድ አበጀን ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ቀለበት መንገድ መስራት ብቻ ሳይሆን ከቀለበት መውጪያውንም እንድንሰራ ፈር ይቀድልናል፡፡ ከተማረ የተመራመረ የሚለው ትርጉም የሚኖረው እዚህ ላይ ነው፡፡
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላል ጸሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ ጊዜን ያላወቀ እንኳን ሥልጣኑን ራሱን ያጣል፡፡ በማንኛውም ደረጃ ላይ ቢሆን “በትክክል ጊዜን መጠቀም እወቅበት፤ ይላሉ ጠበብት፡፡ አለልክ አትጣደፍ፤ ነገሮች ከቁጥጥርህ ይወጣሉና፡፡ የትክክለኛዋ ቅፅበት ሰላይ ሁን፡፡ የጊዜን መንፈስ አነፍንፈህ አሽትት፡፡ ወደ ስልጣን (ድል) የሚወስዱህን መንገዶች በዚያ ታገኛለህ፡፡ ጊዜው ካልበሰለ ማፈግፈግን እወቅበት፡፡ ሲበስል ደግሞ ፈፅሞ ወደኋላ አትበል!” የሚሉ ፀሐፍት ታላቅ ቁምነገር እየነገሩን ነው፡፡
ጊዜን በትክክል መጠቀም የሚችል ዝግጅትን ዋና ጉልበቱ ያደርጋል፡፡ ድግሱ ከመድረሱ በፊት የምግብ እህሉን፣ የጌሾ ጥንስስ ስንቁን ማደራጀትና በመልክ መልኩ መሸከፍ፣ መጥኖ መደቆስ፣ መብሰያና መፍያ ጊዜውን በቅጡ ለድግሱ ሰዓት ማብቃትን ከሸማች እስከ አብሳዩ ውል ሊያስገቡት ይጠበቃል፡፡
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሸቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ”
የሚለው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ይሄንኑ ጊዜ እንኳን ከበሰለ በኋላ እንዲሁም መዘናጋት እንደማይገባ ያስገነዘቡት ነው፡፡
ያለመላ ግጭት ጅልነት ነው፡፡ የዝግጅት ጊዜ ወስዶ አስቦ፣ ሁሉን አመቻችቶ ነው ትግል፡፡ አንዴ ከገቡ ደግሞ መስዋዕት መኖሩን ሳይረሱ ምንጊዜም ሳያቋርጡ፣ ሳይማልሉና ሳይታለሉ መቀጠል ግድ ይሆናል፡፡
በሼክስፔር ሐምሌት ቴያትር ውስጥ፤
“ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!”
የሚለን የጊዜ ዕቅጩነት (Perfect - imning) ጉዳይ ነው፡፡
“አውራ ዶሮ ጮሆ፣ መንጋቱን ነገረኝ
ዛሬ ሌሊት ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ” ያለውን ያገራችንን ወጣት ገጣሚ ረቂቅነትም አለመዘንጋት ነው!!
የሁሉ ነገር መሳሪያ ጊዜ ነው!
ዘመን የጊዜ ጥርቅምና የቅራኔና የሥምረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህም እንደታሪክ ክፉውንም ደጉንም ማጣጣሚያውና ያንን የመመርመር፣ ከስህተት የመማር፣ ነገን የመተለም ጉዳይ ነው ጊዜን ማወቅ ማለት መጪውንም ምርጫ በጊዜ ማስላት ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጊዜን ጨበጥክ ማለት ድልን ጨበጥክ ማለት ነው፤ የሚባለው እንዲያው ለወግ አይደለም! ጊዜን እንደመሳሪያ የምንቆጥረው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ አውራ ዶሯችንን በጊዜ እንግዛዛ - ሌሊትን፣ ተስፋንና ንጋትን - ይንገረን፡፡ ይህ ሚጠቅመን በማታ ሩጫ እንዳንጀምር ከነጋ በኋላም እንዳንዘናጋ ነው! “ከመሸ አትሩጥ፣ ከነጋ አትተኛ” የሚለው የወላይታ ተረት አደራ የሚለን ይሄንኑ ነው!!
ኢቢሲ የአልጀዚራን ፕሮግራሞች ማሰራጨቱ የአገሪቱን ገጽታ ይጐዳል ተባለ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን በህገወጥ መንገድ ማሰራጨታቸው የአገሪቱን ገጽታ በእጅጉ እንደሚጐዳ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለፀ፡፡ ባለስልጣኑ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዕቅድ ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ ኢቢሲና የኦሮሚያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን በህገወጥ መንገድ ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ቁጥጥር ቢደረግም ህገወጥ ስርጭቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ በአገሪቱ የውጭ ብሮድካስት ፕሮግራሞችን በክፍያ ለደንበኞች ለማድረስ የአገልግሎት ፍቃድ የወሰደው ድርጅት ከሚያቀርባቸው የዲኤስቲቪ ቻናሎች ውጪ በህገወጥ መንገድ የአልጀዚራ የስፖርት ቻናሎችን የሚቀበሉ ቢኑ ካርዶችና ዲኮደሮች ከውጪ በማስገባት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሰራጨት ላይ የሚገኙ አካላት እንዳሉም ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
የውጭ ብሮድካስት ፕሮግራሞችን በክፍያ ለደንበኞች የማድረስ አገልግሎት (subscription) ፈቃድ የተሰጠው መልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ ለተባለ ድርጅት ሲሆን ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞቹ የሚያቀርባቸው ቻናሎች ከተሰጠው ፈቃድ ጋር የሚጣጣም መሆኑ፣ የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ይዘት የህፃናትን ስነልቦናና የወጣቶችን ደህንነት እንደማይጐዱ እንዲሁም የህብረተሰቡን ባህላዊና ሞራላዊ እሴቶች የሚጠብቁና የሚዲያ ህጉን ያከበሩ ስለመሆናቸው ክትትል አለመደረጉም በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ሲፒጄ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተባባሰ ነው አለ
በወቅታዊ የመብት ጥሰቶች ዙሪያ የሰራውን ጥናት ይፋ አድርጓል
መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን አስታወቀ፡፡ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ቢሆንም የአገሪቱ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸው ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ግን እየተባባሱ ቀጥለዋል ያለው ሲፒጄ፣ ይፈጸማሉ ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ የሰራውን ጥናት በትላንትናው ዕለት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ያወጣቸውን ህጎች ከቅርብ አመታት ወዲህ ዜጎችን በሚጨቁን መልኩ ያለአግባብ እየተጠቀመበት ነው ያለው ሲፒጄ፤ መንግሥት በሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ በፕሬስ ነጻነትና በዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥሰት እየፈጸመ ነው በሏል፡፡
በጸረ-ሽብርተኝነት ህግ ሽፋን ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ቁጥር እያደገ ነው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር እንዳይችሉ ተደርገዋል ሲል ኮንኗል - ሲፒጄ፡፡
“ቶም ላንቶስ ሂውማን ራይትስ ኮሚሽን” የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በሚገኘው ሬይበርን ሃውስ አዳራሽ ባዘጋጀው የመወያያ መድረክ፣ በአገሪቱ ይፈፀማሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የሚዳስስ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሱኢ ቫለንታይን የተሰራው ጥናት፤ በኢትዮጵያ መንግስት ይፈፀማሉ የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የመገደብ፣ መገናኛ ብዙሃንን የመጨቆንና በልማት ፕሮጀክቶች ሰበብ የነዋሪዎችን ሰብዓዊ መብት የመጣስ ድርጊቶች ያብራራል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ በየዓመቱ የ800ሚ. ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ የጠቆመው ሲፒጂኤ፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመጠቀም ድጋፉ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይውልና መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር ተፅእኖ ማድረግ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩ የፓርላማ አባላት፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ተወካዮች፣ ተመራማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደተሳተፉበት ሲፒጂ ጠቁሟል፡፡
99 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬኒያ ፍርድ ቤት ተቀጡ
አፍሪካን ሰርቪስ ኮሚቴ ለ25 ችግረኛ እናቶች፤ እንጀራ ጋግረው መሸጥ እንዲችሉ ከጤፍ ጀምሮ የሚያስፈልጉትን ጠቅላላ ጥሬ እቃዎች በማሟላት ከትላንት በስቲያ ሾላ አካባቢ በሚገኘው ክሊኒኩ ውስጥ አስረከበ፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ለእነዚህ እናቶች ሁለት ኩንታል ጤፍ፣ የኤሌክትሪክ ምጣድ፣ የዱቄት ማስቀመጫ በርሜል፣ የሊጥ ማቡኪያና የውሃ ባልዲ፣ የአብሲት መጣያ ብረት ድስት፣ ጆግና ማስታጠቢያ፣ ማሰሻ ጨርቅ፣ ጎመን ዘር፣ መሶብ፣ እንቅብና የእንጀራ ማውጫ ሰፌድ በነፍስ ወከፍ ተከፋፍሏል፡፡
ተረጂዎቹ በጨረቃ ቤት፣ በዘመድ ቤትና ባስጠጓቸው በጎ ሰዎች ቤት የሚኖሩ በመሆናቸው የመጀመሪያ ወር የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ለእያንዳንዳቸው 300 ብርና የተረከቡትን እቃ የሚያጓጉዙበት የትራንስፖርት ወጪ ሁለት መቶ ብር ተሰጥቷቸዋል፡፡
አፍሪካዊ ስደተኞችን ለመርዳት ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው አቶ አስፈሃ ሃደራ በተባሉ ግለሰብ አሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ የተቋቋመው “አፍሪካን ሰርቪስ ኮሚቴ” ከ10 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ተከፍቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን ክሊኒኩ የምስጢር ኤችአይቪ ምርመራ፣ የፀረኤችአይቪ (ART) ስርጭት፣ የቲቢ እንዲሁም የአባላዘር በሽታ ምርመራና ህክምና በመስጠት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን ሲያገለግል መቆየቱን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሪት ሃና ወ/ገብርኤል ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት የክልል ከተሞች በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ በመቀሌ በዝዋይ እንዲሁም በሃሳዋ የጤናና የማህበረሰብ ልማት ማዕከል በማቋቋም፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም እናቶችና ህፃናትን በማገልገል ላይ መሆኑን ወ/ሪት ሃና አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ላለባቸው ህፃናት የወተትና የአልሚ ምግብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ18 ዓመት በታች ላሉ ህፃናትና ታዳጊዎች አሜሪካ ከሚገኝ “ቶምስ ሹ” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በዓመት ሁለት ጊዜ የጫማ የትምህርት መሳሪያዎችና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ከትላንት በስቲያ ችግረኛ እናቶች የገቢ ማስገኛ ስራ እንዲሰሩ ለተደረገው የጥሬ እቃና የገንዘብ ድጋፍ አገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው የተገለፀ ሲሆን “በፔፕፋር ስሞምል ግራንት ፕሮግራም” በኩል የአሜሪካ ኤምባሲ የ30 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ተጠቁሟል፡፡ እስከዛሬ ለድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ዲኬቲ ኢትዮጵያ፣ አይካፕ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ ኤምባሲ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማህበራት ኤጀንሲ እንዲሁም ድርጅቱ የሚንቀሳቀስባቸው የክልል መንግስታት የወረዳና የዞን ቢሮዎች በእለቱ ተመስግነዋል፡፡ በእለቱ የአንበሳ ማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ድርጅት ባለቤትና “የትውልዱ አምባሳደር” አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁና አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በክብር እንግድነት ተገኝተው ስለ ድርጅቱ እንቅስቃሴ የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥሬ እቃ ድጋፉን የተረከቡት 18 እናቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሰባት እናቶች በሌላ ድርጅት መደገፍ አለመደገፋቸው ተጣርቶ እቃቸውን መረከብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
አርቲስት ዳንኤል ተገኝና አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ ለገና በዓል ለተረጂዎቹ የተወሰነ ስጦታ ለማበርከት ቃል እንደገቡም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተባለ
ሽልማቱን ላለፉት 3 ተከታታይ አመታት ተቀብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በያዝነው ሳምንት በአልጀርስ በተካሄደው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር 46ኛ አመታዊ ጉባኤ ላይ፣ የአመቱ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተብሎ መሸለሙን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ለአመቱ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማት የበቃው በ2013 የበጀት አመት ባስመዘገባቸው ከፍተኛ ውጤቶች፣ ዘላቂነት ባለው ትርፋማነቱ እና ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ለመስራት በሚያስችለው አግባብነት ያለው ስትራቴጂው እንደሆነ ገልጾ፣ ይህንን ሽልማት ላለፉት ሶስት አመታት በተከታታይነት እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ ሽልማቱን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር አየር መንገዱ ለዚህ ሽልማት በመብቃቱ ኩራት እንደሚሰማው ገልጸው፣ ለዚህ ስኬት መሰረቱ ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑ ጠንካራ ሰራተኞቹ ትጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአንጀት ቁስለት ህመምና መዘዙ
- በሽታው በፍጥነት ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ ይችላል
- የበሽታው ምልክቶች ከአሜባ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው
- በሽታውን ለማከም ይሰጡ የነበሩት መድሃኒቶች ከባክቴሪያው ጋር ተላምደዋል
“የምግብ ፍላጐቷ እየቀነሰ፣ ሰውነቷ እየከሳና እየደከመ ሲሄድ ሃሳብ ገባኝ፡፡ በየዕለቱ ምግብ በቀመሰች ቁጥር ሽቅብ ሲተናነቃት ስመለከት ደግሞ ልቤ ሌላ ነገር ጠረጠረ፡፡ ምልክቶቹ በአብዛኛው ከእርግዝና ምልክቶች ጋር የሚመሳሰሉ በመሆናቸው ሁኔታዋ እጅግ አስደነገጠኝ፡፡
ሁለታችንም ከወላጆቻችን ጋር አብረን የምንኖርና የመሰናዶ ተማሪዎች በመሆናችን በዚህ ሁኔታና በዚህ ዕድሜዋ ማርገዟ አሳዘነኝ፡፡ ምንድነው የማደርገው? ወላጆቻችንስ እንዴት ነው የሚነገራቸው? የሚለው ሃሳብ እንቅልፍ ነሣኝ፡፡ በሁለት ዓመት የምበልጣት ታላቋ ብሆንም እንደ እኩያዬ ነበር የማያት፤ የምትደብቀኝም ሆነ የምደብቃት ሚስጢር አልነበረም፡፡ አሁን ግን ድብቅ የሆነችብኝ መሰለኝ፡፡ ነገሩን ለማውጣጣት ያላደረግሁት ሙከራ አልነበረም፡፡ ሆኖም ምንም ፍንጭ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆዷ እንደ ከበሮ እየተነፋና እየተወጠረ ሄደ፡፡ ከእንብርቷ በታችም ከፍተኛ ስቃይ ያለው ህመም እንደሚሰማትም ነገረችን፡፡ የምግብ ፍላጐቷ ጨርሶውኑ በመጥፋቱ ሚሪንዳና ጭማቂዎችን ትንሽ ትንሽ ልንሰጣት ሞከርን፡፡ የምትወስደው ምግብ ሁሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ይወጣል፡፡ ሠገራ መቀመጥ ስቃይ ሆነባት፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ ወደ ዩኒቨርሳል ክሊኒክ ይዘናት ሄድን፡፡ በክሊኒኩ በተደረገላት ምርመራም የአንጀት ቁስለት በሽታ እንዳለባትና የአንጀቷ ግድግዳዎች ክፉኛ መጐዳታቸው ተነገረን፡፡
በሽታው ያለበት ደረጃ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑም አስቸኳይ ህክምና ሊደረግላት እንደሚገባ ተነገረን፡፡ በዚህ መሰረትም ህክምናውን ማድረግ ጀመረች፡፡
“በሽታው ሥር የሰደደ በመሆኑና የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል በማጥቃቱ በቀላሉ ሊድን አልቻለም፡፡ ለሁለት ሳምንታት ህክምናው ሲደረግላት ብትቆይም አልዳነችም፡፡ ገና በ18 ዓመት ዕድሜዋ ህይወቷ አለፈ፡፡
“የእህቴን ሞት ባሰብኩ ቁጥር እጅግ የሚፀፅተኝ ችግሯን ቶሎ አውቀንላት ወደ ህክምና ልንወስዳት አለመቻላችን ነው፡፡ ስለ በሽታው ምልክቶች ቀደም ብዬ ባውቅ ኖሮ እርግዝና ነው ከሚለው ጥርጣሬዬ ተላቅቄ፣ እህቴ በወቅቱ ህክምና እንድታገኝና ህይወቷ እንዲተርፍ ልታደጋት እችል ነበር፡፡” ይህንን አሳዛኝ ታሪክ የነገረችኝ በቅርቡ ታናሽ እህቷን በሞት የተነጠቀችው ትዕግስት መንግስቴ ናት፡፡ ህክምና በወቅቱ ባለማግኘቷ የተነሳ በሽታው የአንጀቷን አብዛኛውን ክፍል ጐድቶ ለሞት እንደዳረጋት እህቷን የመረመራት ሐኪም እንደነገራቸው ገልፃልኛለች፡፡
ለመሆኑ የትልቁ አንጀት ቁስለት በሽታ ምንድነው? ምልክቶቹና መንስኤዎቹስ ምንድናቸው? ህክምናውስ የሚለውን ጉዳይ እንዲያብራሩልን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶክተር ታዲዮስ መንከርን አነጋገርናቸዋል፡፡
1.5 ሜትር ርዝመት ያለውና በትንሹ አንጀታችን ዙሪያ የሚገኘው ትልቁ አንጀት የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን በአግባቡ እንዲሆን የሚያደርግና ከጨጓራ ተፈጭቶና ልሞ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚሰራጩት ምግቦች ውስጥ በቆሻሻነት የሚወገዱትን ወደ ታች ገፍቶ በሰገራ መልክ የሚያስወግድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከቆሻሻው ውሃንና አንዳንድ ጠቃሚ ንጥረነገሮችን መጥጦ ወደ ደም እንዲገቡ ያደርጋል፡፡
ትልቁ አንጀታችን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስበትና አየርና አይነምድርን ቋጥሮ ሲይዝ፣ ድንገት ሆዳችን ይወጠርና ግሣትና እረፍት የለሽ ስቃይ ይገጥመናል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ታማሚው አስቸኳይ የቀዶ ጥገና ህክምና ካላገኘ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለ በሽታው ምንነትና መንስኤዎቹ ዶክተር ታዲዎስ ከዚህ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
ለአንጀት ጤና ችግር መነሻው
የትልቁ አንጀት መኮማተር
ይህ አይነቱ የጤና ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በወጣትነትና በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ውጥረት፣ ጭንቀትና እረፍት የለሽ ህይወት ለዚህ ዓይነቱ የጤና ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡
ኢንፌክሽን
በቫይረስ፣ በባክቴሪያና በተለያዩ ጥገኛ ህዋሳቶች አማካኝነት አንጀታችን ሲመረዝ፣ የአንጀት ቁስለት ይከተላል፡፡ ይህም አንጀት ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን በማድረግ አጣዳፊ የሆድ ውስጥ ህመም፣ ማስመለስና ማቅለሽለሽ እንዲሁም ትኩሳትና ድካም ያስከትላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር የሚከሰተው በአብዛኛው ንፅህናቸውን ባልጠበቁ ምግቦች ውሃ ሳቢያ ነው፡፡
የትልቁ አንጀት ቁስለት
በሰውነታችን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ኢንፌክሽን በሚፈጠርበት ወቅት ሰውነታችን ኢንፌክሽኖቹን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ተፈጥሮአዊ ትግል አንጀታችን ለጉዳት ሊዳርገው ይችላል፡፡ ይህም የአንጀት ጉዳት ትልቁ አንጀታችን እንዲላጥና እንዲቆስል በማድረግ ለህመም ሊዳርገን ይችላል፡፡ የአንጀት ቁስለት ህመም አልፎ አልፎ በዘር ሊከሰትም ይችላል፡፡
የአንጀት ካንሰር
ይህ አይነቱ የአንጀት ህመም እጅግ አደገኛና ከጡት፣ ከማህፀንና ከሳንባ ካንሰር ቀሎ ብዙዎችን ለስቃይና ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ዕድሜያቸው ከአርባ አመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃል፡፡
ጮማና ስብነት ያላቸውን ምግቦች መመገብ የሚያዘወትሩ፣ በሽታው በቤተሰባቸው ውስጥ ያለባቸውና በሆዳቸው አካባቢ የጨረር ህክምናን የወሰዱ ሰዎች ለዚህ ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡
የፊንጢጣ ኪንታሮት
በፊንጢጣ አካባቢ በሚገኙ የደም ስሮች ማበጥ ሳቢያ የሚከሰት ችግር ሲሆን ችግሩን ሰገራ ለመውጣት ማማጥ፣ ለረዥም ጊዜ መቆም፣ በሙቀት ውስጥ ለረዥም ሰዓት መኪና ማሽከርከርና እረፍት ማጣት ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ የሆድ ድርቀትም በሽታውን ሊያባብሱት ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የምግብ መመረዝ
በተለያዩ ለጤና ጎጂ በሆኑ ባክቴሪያዎች የተመረዙ ምግቦችን በምንመገብበትና የተበከለ ውሃን በምንጠጣበት ወቅት ተህዋስያኑ ወደ አንጀታችን ውስጥ በመግባት አጣዳፊ የሆድ ህመምን፣ ማስመለስንና ተቅማጥን ሊያመጡብን ይችላሉ፡፡ ይህ ችግርም በወቅቱ ህክምና ካላገኘ ተባብሶ አንጀታችንን በማቁሰል ለአንጀት ቁስለት ሊዳርገን ይችላል፡፡
ምልክቶቹ
የትልቁ አንጀት ህመም ውስጣዊና ውጫዊ ምልክቶች አሉት፡፡ አንድ ሰው የትልቁ አንጀት ቁስለት እንዳለበት ጠቋሚ ከሆኑት ምልክቶች መካል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው:-
ውስጣዊ ምልክቶች
ከእንብርት በታች ሃይለኛ ስቃይ ያለው የህመም ስሜት
ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና፣ የድካም ስሜት
የሆድ መነፋት፣ መጮህና የሆድ ድርቀት
የፈስ መብዛት፣ ማስማጥና በፊንጢጣ ደም መውጣት
ውጫዊ ምልክቶች
በቆዳ ላይ እጅብ ያለ ሽፍታ መውጣት
በተለያዩ የሰውነት ክፍሎችና በአጥንት መገጣጠሚያዎች ላይ እብጠት
ክብደት መቀነስ፣
የሆድ መነፋት ወይም ግልፅ ሆኖ የሚታይ የሆድ መነረት ናቸው፡፡
ትልቁ አንጀትን የሚያጠቁት በሽታዎች በርካቶች ቢሆኑም በአገራችን በብዛት የተለመዱትና ለበርካቶች ህመምና ሞት ምክንያት የሚሆኑት ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ሲሆኑ የአንጀት ካንሰር በገዳይነቱ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል፡፡
ስብና ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች አዘውትረው የሚመገቡ፣ በተፈጥሮ የአንጀት ቁስለትና አንጀት ላይ የሚፈጠሩ ትናንሽ እብጠቶች ያሉባቸው ሰዎችን በይበልጥ የሚያጠቃው ይህ በሽታ፤ ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚሰራጭና የማይሰራጭ አይነቶች አሉት፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየው በሰውነት ውስጥ የሚሰራጨው አይነቱ ካንሰር ነው፡፡ የትልቁ አንጀት ካንሰር ምልክቶች አሜባ እየተባለ ከሚጠራው በሽታ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ማስማጥ፣ ደም የተቀላቀለበት ተቅማጥ፣ የሆድ ህመምና ቁርጠት በሁለቱም በሽታዎች ላይ የሚታዩ ሲሆን አሜባ በአጭር ጊዜ ህክምና መዳን መቻሉና በሰገራ ምርመራ የበሽታው ምንነት መታወቁ ከአንጀት ካንሰር ይለየዋል፡፡
የትልቁ አንጀት ካንሰር በአገራችን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ የተደረጉ ጥናቶች አለመኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ታዲዮስ መንክር፤ ከሆስፒታሎች የሚገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጉልምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የበሽታው ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡
የተሟላና የተጠናከረ መረጃ የመያዝ ልምድ ባለመኖሩ ትክክለኛውን የአንጀት ቁስለት በሽታ ታማሚዎች ቁጥር ለይቶ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡
የሽንት ቱቦ፣ የፊኛና የማህፀን ካንሰር ምልክቶች ከትልቁ አንጀት ካንሰር በሽታ ጋር የመመሳሰል ባህርይ ስለአላቸውም አንዳንድ ጊዜ በምርመራ ወቅት የጤና ባለሙያዎችን ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ባለሙያዎች የትልቁ አንጀት ካንሰር ምርመራን በሚደርጉበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ሲሉ ዶክተሩ አሳስበዋል፡፡ አንድ ሰው የአንጀት ካንሰር በሽታ ምርመራ ተደርጎለት በሽታው መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በሽታው በሰውነቱ ውስጥ ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ሌሎች ምርመራዎች ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህም በሽታው የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹን መንካት አለመንካቱን ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ በዚህም በሽታው ያለበትን ደረጃ ማወቅና የህክምናውን ዓይነት መወሰን ይቻላል፡፡ የህመምተኛውን የመዳን እድል ለማወቅም ይረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለአንጀት ቁስለት ህመም በስፋት የሚታዘዘው መድኀኒት Amoxicillin የተባለው ሲሆን Omepazole እና Clarithromycine የተባሉት መድኀኒቶችም በሽታውን ለማከም አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ቀደም ሲል የአንጀት ቁስለት ህመም መድኀኒት የነበሩት Tetracycline እና Metronidazole (ሜዝል) እየተባሉ የሚጠሩትን መድኀኒቶች የአንጀት ቁስለት አምጪ ባክቴሪያዎች ስለተለማመዷቸውና መድኀኒቶቹ በሽታውን የማዳን ኃይላቸውን በማጣታቸው ምክንያት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እየተደረገ መሆኑን ሃኪሙ ተናግረዋል፡፡
ህክምናው
የቆሰለው የአንጀቱ ክፍል የሚደማ ከሆነ በኢንዶስኮፒ የሚደማውን ቦታ በማከም፣ ደሙን ማቆም፡፡
ህመምተኛው ደም የሚያንሰው ከሆነ፣ የደም ዓይነቱን በመለየት ደም እንዲሰጠው ማድረግ፡፡
ለቁስለቱ መነሻ ምክንያቱ ባክቴሪያ ከሆነ፣ ባክቴሪያውን የሚያጠፉ መድሃኒት መስጠት፡፡
ህመምተኛው የመጠጥ፣ የጫትና የሲጋራ ሱስ ካለበት ሱሱን እንዲያቆም ማድረግ፡፡
ሉሲ የተገኘችበት 40ኛ ዓመት በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ይከበራል
በሰው ልጆች አመጣጥ ጥናት መስክ ውስጥ አለማቀፍ ቁልፍ ግኝት እንደሆነች የሚነገርላት ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሬተ-አካል በአፋር ክልል ሃዳር የተባለ አካባቢ በቁፋሮ የተገኘበት 40ኛ ዓመት በያዝነው ወር በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ እንደሚከበር ሳይንስ ኒውስ ድረገጽ ዘገበ፡፡
ዶናልድ ጆንሰን እና ቶም ግሬይ በተባሉ አንትሮፖሎጂስቶች እ.ኤ.አ በ1974 የተገኘችውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አመታት በፊት በሁለት እግሮቿ ትራመድ የነበረችው ሉሲ፤ የሰው ልጆችን አመጣጥ በተመለከተ ቀደም ብሎ የነበረውን አስተሳሰብ የቀየረችና ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጠች ታላቅ ግኝት መሆኗን ዘገባው አስታውቋል፡፡
ሉሲ ከመገኘቷ በፊት “የሰው ልጆች መገኛ አውሮፓ ነው አፍሪካ?” የሚል ክርክር እንደነበር ያስታወሱት የግኝቱ ባለቤትና በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጆች መገኛዎች ኢንስቲቲዩት መስራችና ዳይሬክተር ዶናልድ ጆንሰን፤ የእሷ መገኘት በመስኩ የነበረውን አመለካከት በወሳኝነት እንደቀየረው ለዘ ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
ሉሲ በአንትሮፖሎጂ የጥናት መስክ ቁልፍ ሚና እንዳላት የገለፁት ዶናልድ፤ የሰው ልጆች አመጣጥ ታሪክን የቀየረችው ሉሲ የተገኘችበት 40ኛ ዓመት በዚህ ወር በዩኒቨርሲቲው በሚካሄዱ ውይይቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡