Administrator
“...ግልፅነት ይጎድላል... መደባበቁ ጥቅም የለውም...”
የኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደውጭው አቆጣጠር በ2020/ዓም ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚለው አንዱ ሲሆኑ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በተግባር ላይ ውለዋል ከእነዚህም መካከል፡-
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በጋራ መስራት፣
የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የPMTCT አገልግሎትን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣
አገልግሎቱን በሚመለከት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣
የሚሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል የPMTCT (Prevention of mother-to-child transmission) አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የግል እንዲሁም የመንግስት የህክምና ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተለይም ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመተባበር ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ተግባር በመከወን ላይ ያለ ሲሆን በዛሬው ፅሁፋችን የምንመለከተው ግን በደሴ ከተማ ተገኝተን አገልግሎቱ በመንግስት የህክምና ተቋማት በምን መልኩ እንደሚሰጥና ለግል የህክምና ተቋማቱ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍ የሚመለከት ነው፡፡
ሮዛ ሽፈራው በደሴ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ የአገልግሎቱ አስተባባሪ ኦፊሰር ናቸው፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግል የህክምና ተቋማት ከመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን በተወሰነ መልኩ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ቢኖርም መንግስት ከተቋማቱ ለሚደርሰው የቁሳቁስ እንዲሁም የሙያ ድጋፍ ጥያቄ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡ ምን ያህል እናቶች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...አሁን ባለው ሁኔታ በግል የህክምና ተቋማቱ አገልግሎቱን የሚጠቀሙት ታካሚዎች ከተለያየ ቦታ ነው የሚመጡት አንዳንዶቹ ምጥ ይዟቸው በመጡበት ሰአት ፖዘቲቭ የሚሆኑበት ግዜ አለ አንዳንዴ ደግሞ ፖዘቲቭ ሆነው መጥተው የሚወልዱበትም ሁኔታ አለ፣ ብዙዎቹም ከተለያየ ቦታ ይመጣሉ፣ ከአፋር ክልል ጀምሮ ከሰሜን ወሎ ከሌላም ቦታ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎቹን ቁጥር በውል ለማወቅ ያስቸግራል፡፡”
ለህክምና ተቋማቱ የምታደርጉት የቁሳቁስም ሆነ ሌሎች ድጋፎች በትክክል ለተጠቃሚዎቹ መድረሳቸውን በምን መንገድ ታረጋግጣላችሁ? ቀጥለን ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡
“...ያው ምርመራ ያደረጉትን ታካሚዎችን ለማየት እንሞክራለን ግን ምርመራን ያደረጉት ሁሉ ፖዘቲቭ ላይሆኑ ይችላሉ በዋናነት ግን ምን ያህል ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን አውቀዋል የሚለውን እናያለን፡፡ ምን ያህሉን PMTCT አገልግሎት ላይ አዋሉት የሚለውንም እንመለከታለን፡፡ አንዳንድ ግዜ እጥረት የሚፈጠረው ለሌላም ስለሚጠቀሙበት ይሆናል ብለን እንገምታለን።”
አያይዘውም በመንግስት የህክምና ተቋማት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል በሚመለከት ማንኛዋም አገልግሎቱን ፈልጋ የምትመጣ እናት የነፃ ህክምና ታገኛለች ብለዋል፡፡
“አንዲት እናት እኛ ጋር ስትመጣ ነብሰጡር ናት ተብሎ አገልግሎቱን ከጀመረችበት ግዜ አንስቶ እስከምትወልድ ግዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ አገልግሎት ታገኛለች፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ እንዲሁም ሌሎች ከእናቶችና ህፃናት ጋር ተያያዥ የሆኑ አገልግሎቶችም በአብዛኛው ነፃ ናቸው፡፡”
በመንግስት በኩል አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀና በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተመርምሮ እራስን በማወቁ እንዲሁም እራስን ካወቁም በኋላ በግልፅ ለሌሎች በማሳወቁ እረገድ በርካታ ችግሮች አሉ ያሉን ደግሞ በደሴ ከተማ የቧንቧ ውኀ ጤና ጣቢያ የነብሰጡር ክትትልና የማዋለጃ ክፍል ውስጥ ሲሰሩ ያገኘናቸው ሲስተር ካሳነሽ ግዛው ናቸው፡፡
“...ብዙዎቹ እራሳቸውን አውቀውም እንኳን ቢሆን ግልፅ መሆን አይፈልጉም እራሳቸውን አውቀው መድሀኒት እየወሰዱ እኛ ጋር መጥተው ሲመረመሩ እንደ አዲስ ነው የሚሆኑት ቀድመው እያወቁት ይደብቃሉ፡፡”
በቅርብ የገጠመጥ ብለውም የሚከተለውን አጫውተውናል፡፡
“...አንዲት እናት ...ቀደም ሲል በወለደችበት ወቅት አሁን ያለው ኦፕሽን ቢ ፕላስ ስላልተጀመረ በምጥና በወሊድ ግዜ የሚሰጠውን መድሀኒት ሰጥተው ነው ያዋለዷት፡፡ ጤና ጣቢያ ስትመጣ ኤችአይቪ መመርመር አለብሽ ብዬ የምክር አገልግሎት ስሰጣት ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ነገረችኝ፡፡ ከመቼ ጀምሮ ... ስላት ከሁለት ሺህ አመተምህረት ጀምሮ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ስለዚህ አሁን ቫይረሱ ወደ ልጅሽ እንዳይተላለፍ ጤነኛ ልጅ እንድትወልጂ መድሀኒቱን መጀመር አለብሽ ስላት ሲዲፎርሽ ዘጠኝ መቶ ነው ስላሉኝ መድሀኒት አልጀምርም ነው ያለችኝ፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህ መድሀኒቱን ለመጀመር መመሪያ ወይም ቅድመሁኔታ አይደለም፡፡ ሲዲፎር ቢወርድም ባይወርድም ኤችአይቪ በደምሽ ውስጥ እንዳለ ከታወቀና ነብሰጡር ከሆንሽ... ወዲያው ነው መድሀኒቱን መጀመር ያለብሽ ብዬ ስላት ባለቤቴን አማክሬ እመጣለሁ ብላ መድሀኒቱን ሳትይዝ ሄደች፡፡ ለእኔ ግልፅ ላለመሆን እንጂ መድሀኒቱን የምትወስድ ይመስለኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ ብዙዎቹ የመኖሪያ አድራሻቸውን ካርዳቸው ላይ እንኳን ማስመዝገብ አይፈልጉም፡፡”
ምን ቢደረግ ነው ይህን ችግር ማስቀረት የሚቻለው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲ/ር ካሳነሽ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...እንግዲህ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በየጊዜው በሚዲያ ይነገራል፡፡ በእኛም በኩል ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት በደንብ ነው የምክር አገልግሎት የምንሰጣቸው፡፡ መድሀኒቱ የእድሜ ልክ እንደሆነና ተጀምሮ መቋረጥ እንደሌለበት... ከተቋረጠ የቫይረሱ መጠን እንደሚጨምር እንዲሁም ወደ ልጁ የመተላለፍ እድሉም በዛው ልክ እንደሚጨምር እንነግራቸዋለን፤ ግን አሁንም ወደ ፊትም እኔ ለውጥ ያመጣል የምለው የmother support ቡድኑ የሚሰራው ስራ ነው ምክንያቱም እነሱ ናቸው እታች ወዳለው የህብረተሰቡ ክፍል ወርደው ብዙውን ስራ የሚሰሩት ስለዚህ ያለን አማራጭ እነሱን ማጠናከር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ከሁሉም በላይ ግን ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ባለትዳሮች በጋራ ተመርምረው ውጤታቸውን ቢያውቁ አሁን እየታየ ባለው ለውጥ ላይ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ሲ/ር ናሳነህ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
“...ሚስቱ ለእርግዝና ክትትል ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ባልዋ ሀላፊነት ተሰምቶት ከእሷ ጋር አብሮ ሄዶ የምክር አገልግሎት ሲደረግላት ስለ ኤችአይቪ ብቻም ሳይሆን ስለ አመጋገብ ስለ ንፅህና ሌሎችንም ነገሮች እንመክራለን፡፡ ኤችአይቪም አብሮ ይመረመራል እዚሁ አብረው ተመርምረው ሚስት እንኳን ቢገኝባት የምክር አገልግሎት አግኝቶ ከሄደ ለመድሀኒቱ እንኳን ጫና አያሳድርባትም፡፡ አንቺ ነሽ ያመጣሽብኝ ምናምን የሚለው ነገር አይኖርም፡፡ ዲስኮርዳንት ከሆኑም ወደፊት እንዴት አብረው መኖር እንዳለባቸው፣ አንዱ አንዱን እንዴት ከኤችአይቪ መጠበቅ እንዳለበት በዛው እናስተምራለን፡፡ እንደገና በእርግዝና ወቅት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም እናቲቱ ነፃ ሆናም ከሆነም ከባል ወደ እሷ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ አድርገው አንዱ ለአንዱ እንዲተሳሰቡ አብረው ስለሚመከሩ የትዳር አጋርም አብሮ ወደ ጤና ጣቢያ ቢመጣ ለኤች አይቪ ስርጭት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡”
የባልና ሚስት ውጤት መለያየት በሚገጥምበትም ወቅት ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ይቻላል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል፡-
“...ኤችአይቪ በደም ውስጥ ባይገኝ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከተገኘ መንግስት አሁን አገልግሎቱን በነፃ እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ክትትል አድርገው ጤነኛ ልጅ ወልደው እንዲያሳድጉ ይመከራል ...መደባበቁ ጥቅም የለውም... በተለይም በደሴ ከተማ ኤችአይቪን በሚመለከት ግልጽነት ይጎድላል፡፡ ለመመርመር የሚመጡ እናቶች ሳይደብቁና ሳይሳቀቁ ግልፅ ሆነው መጥተው ቢስተናገዱ ለወደፊቱ ከኤችአይቪ ነፃ ሆነ የሆነ ትውልድ ለማፍራት ይረዳል።”
የፍቅር ጥግ
በጥልቀት መፈቀር ጥንካሬ ሲሰጥህ፣ በጥልቀት ማፍቀር ፅናት ይሰጥሃል፡፡
ላኦ ትዙ
ሃዘን ለራሱ መሆን አያቅተውም፡፡ የደስታን ሙሉ ዋጋ ለማግኘት ግን አንድ የምታካፍለው ሰው ሊኖር ይገባል፡፡
ማርክ ትዌይን
ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃለህ ከተባልኩ ባንቺ የተነሳ ነው፡፡
ሔርማን ሄሲ
አንቺ ለእኔ ጣፋጭ ስቃይ ነሽ፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
ጨርሶ ሳያፈቅሩ ከመቅረት ይልቅ አፍቅሮ ማጣት ይሻላል፡፡
ሄሚንግ ዌይ
ብልህ ልጃገረድ ብትስምም አታፈቅርም፤ ብታዳምጥም አታምንም፡፡ ከዚያም ሳይተዋት በፊት ትታ ትሄዳለች፡፡
ማሪሊን ሞንሮ
እናም በመጨረሻ የወሰድከው ፍቅር ከሰራኸው ፍቅር ጋር እኩል ነው፡፡
ጆን ሌኖን እና ፓል ማእካርትኒ
የፀሃፍት ጥግ
ያልበሰሉ ገጣሚዎች ሲኮርጁ፤ የበሰሉ ገጣሚዎች ይሰርቃሉ፡፡
ቲ ኤስ ኢሊዮት
ቤት የማይመታ ግጥም መፃፍ መረቡን አውርዶ ቴኒስ እንደመጫወት ነው፡፡
ሮበርት ፎርስት
አብዛኛው ሰው አብዛኛውን ግጥም ችላ የሚለው አብዛኛው ግጥም አብዛኛውን ሰው ችላ ስለሚል ነው፡፡
አድሪያን ሚሼል
ሥነግጥም፤ በአየር ላይ መብረር የሚመኝ፣ በመሬት ላይ የሚኖር የባህር እንስሳ ዜና መዋዕል ነው፡፡
ካርል ሳንድበርግ
በመጀመሪያ ራሴን እንደገጣሚ አስባለሁ፤ ቀጥሎ በሙዚቀኛነት፡፡ እንደ ገጣሚ ኖሬ እንደገጣሚ እሞታለሁ፡፡
ቦብ ዲላን
መጨረሻውን የማውቀው ግጥም ፈጽሞ ጀምሬ አላውቅም፡፡ ግጥም መፃፍ ግኝት ነው፡፡
ሮበርት ፍሮስት
ገጣሚ የምናባዊው ዓለም ቄስ ነው፡፡
ዋላስ ስቲቨንስ
ግጥም ሲገላለጥ የህይወት ሂስ ነው፡፡
ማቲው አርኖልድ
ገጣሚ፤ ራሱን ገጣሚ ብሎ የማይጠራ ማንኛውም ሰው ይመስለኛል፡፡
ቦብ ዲላን
የንባብ ባህልን ለማዳበር ውይይት ይካሄዳል
እናት የማስታወቂያ ድርጅት፤ “ትርጉም ያለው የንባብ ባህል ለወጣቶች ስኬታማነት” በሚል መርህ ዛሬ ረፋድ ላይ ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የሚዘልቅ ውይይት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሐፍት ኤጀንሲ አዳራሽ እንደሚካሄድ አስታወቀ፡፡ደራሲ ዘነበ ወላ እና ፀጋአብ ለምለም ለውይይቱ የመነሻ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ የታወቀ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የስነ - ፅሁፍ ማህበራት ተወካዮች፣ ባለስልጣናት፣ ደራሲያን፣ የስነ ጽሑፍ ምሁራን፣ መጽሐፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
በዚህ መድረክ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ፍላጐት ያለው ማንኛውም ሰው እንዲታደም ተጋብዟል፡፡ እናት የማስታወቂያ ድርጅት፤ ለንባብ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ ባላቸው ስራዎች ላይ በማተኮር ላለፉት አምስት አመታት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 4፡00 ሰዓት በሚያቀርበው “ብራና” የተሰኘ ፕሮግራሙና በአዲስ አበባና በክልሎች በሚያዘጋጃቸው የመፃህፍት አውደ ርዕዮች ይታወቃል፡፡
“ቻርሊና የቸኮሌት ፋብሪካው” ገበያ ላይ ዋለ
Charlie and the Chocolate Factory” በሚል በሮዋልድ ዳህል ተፅፎ “ቻርሊና የቼኮሌት ፋብሪካው” በሚል በጌታነህ አንተነህ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የተዘጋጀው አዲስ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በቻርሊ ቸኮሌት ፋብሪካ ዙሪያ የሚያጠነጥን ወጥ ተረት ሲሆን በ157 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡
በኦላንድ አታሚዎችና አሳታሚዎች ድርጅት የታተመው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ40 ብር፣ ለውጭ አገር በ20 ዶላር ለገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡
“ፍላሎት” የግጥም መጽሐፍ ተመረቀ
በተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች ላይ የተሰማራው የዶን ፊልሞች ፕሮዳክሽን የገጣሚ በአካል ንጉሴ የግጥም ስብስቦችን ያካተተውን “ፍላሎት” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ አስመርቋል፡፡
መጽሐፉ በማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 68 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን በ91 ገፆች ተቀንብቦ በ25 ብር ለገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡ በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ተፈሪ አለሙ፣ ኪሮስ ሃ/ስላሴ፣ ምስራቅ ተረፈና እምወድሽ በቀለ ከመጽሐፉ ላይ ግጥሞችን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡
የሰዓሊ ታምራት ገዛኸኝ የስዕል አውደ ርዕይ ትናንት ተከፈተ
የነፃ አርት ቪሌጅ መስራች አባልና ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆነው የታምራት ገዛኸኝ “ፈለግ ከሀ እስከ…” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ትናንት ምሽት በጉራማይሌ የስነጥበብ ማዕከል ተከተፈ፡፡
አውደ ርዕዩ፤ ሰዓሊው ላለፉት 15 ዓመታት ያለፈበትን የስነ - ጥበብ ጉዞ የሚያስቃኝና አሁን ለደረሰበት ስነ - ጥበባዊ ከፍታ አስተዋጽኦ ያላቸውን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች የሚያስቃኝ ነው ተብሏል፡፡
የቀልድ ጥግ
ጋዜጠኛው ወደ ኢትዮጵያ ለስራ የመጣ አንድ ቻይናዊ እያነጋገረ ነው፡፡
ጋዜጠኛ - ቻይና ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት ቻይናውያን ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አንድ በቂ ነው፡፡
ጋዜጠኛ - ኢትዮጵያ ውስጥስ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት አበሾች ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አምስት፡፡ አንዱ አምፑል ለመቀየር፣ አንዱ ወንበር ለመያዝ፣ ሶስቱ ደግሞ ቆመው ለመመልከት፡፡
ጋዜጠኛ - ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት ቻይናውያን ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አምስት፡፡ አንዱ አምፑል ለመቀየር፣ አራቱ ቆመው የሚመለከቱትን አበሾች ለማባረር፡፡
ጋዜጠኛ - ቻይና ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት አበሻ ያስፈልጋል?
ቻይናዊ - አንድ አበሻና ሶስት ቻይናውያን፡፡
አበሻው አምፑሉን ለመቀየር፣ ሶስቱ ቻይናውያን ደግሞ ሃበሻው አምፑሉን ቀይሮ ሲጨርስ አገሬ አልመለስም
እንዳይል ለመጠበቅ፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ያሰሩት ቤተ መንግስት ተቃውሞ ገጠመው
615 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል፤ ተጨማሪ 85 ሚ. ፓውንድ ለማስፋፊያ ተመድቦለታል
ለፕሬዚዳንቱ ልዩ አውሮፕላን 115 ሚ. ፓውንድ ተከፍሏል
3 ሚ. ቱርካውያን ስራ አጦች ናቸው
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሪሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ በ615 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያሰሩትና አንካራ ውስጥ በሚገኝ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስኩየር ጫማ ቦታ ላይ ያረፈው ግዙፉ ‘ነጩ ቤተ መንግስት’ በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ለ12 አመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በቅርቡ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን የያዙት ኤርዶጋን፤ ከታዋቂዎቹ ዋይት ሃውስና ቤኪንግሃም ቤተመንግስቶች እንደሚበልጥ የተነገረለትን ይህን ቤተመንግስት ማሰራታቸው፣ በአገሪቱ ግብር ከፋይ ዜጎች ዘንድ አላግባብ ወጪ የወጣበት የቅንጦት ግንባታ በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ከሳምንታት በፊት ግንባታው ተጠናቆ ስራ የጀመረውና “አክ ሳራይ” ተብሎ የሚጠራው ቤተ መንግስት፤ በከፍተኛ ወጪ ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ በአረንጓዴ ቦታነት በተከለለ ስፍራ ላይ መሰራቱ በአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እንዳስነሳ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን ጨፍጭፈው በከፍተኛ ወጪ የራሳቸውን የቅንጦት ቤት የገነቡት፣ 3 ሚሊዮን ዜጎቿ ስራ አጥ በሆኑባት አገር ላይ ነው” ብለዋል - “ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ” የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከማል ኪሊዳሮግሉ ለቴሌግራፍ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፡፡
በአገሪቱ ቤተ መንግስት ለመገንባት ከተመደበው በጀት ከሁለት እጥፍ በላይ ገንዘብ ፈሶበታል የተባለው ቤተ መንግስቱ 1 ሺህ ክፍሎች ያሉት ሲሆን እጅግ ዘመናዊ የሆነ ጥብቅ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሲስተም ተገጥሞለታል፡፡
ቤተመንግስቱ እጅግ ውድ በሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶች የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
‘ነጩን ቤተ መንግስት’ በቀጣዩ አመት የበለጠ እንዲያምርና እንዲስፋፋ ለማድረግ ተጨማሪ 85 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ለፕሬዚዳንቱ ልዩ ኤርባስ አውሮፕላን ለመግዛት 115 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡንም ገልጿል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የቡርኪናፋሶ ጦር በ2 ሳምንት ውስጥ ስልጣን እንዲያስረክብ አሳሰበ
ስልጣኑን ካላስረከበ አገሪቱን ከህብረቱ አባልነት አግዳለሁ ብሏል
ፓርቲዎች እስከ 1 አመት የመንግስት ሽግግር ለማድረግ ተስማምተዋል
ቡርኪናፋሶን ለ27 አመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ በህዝብ አመፅ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣን የያዘበት አካሄድ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የተከተለ አይደለም ሲል የተቃወመው የአፍሪካ ህብረት፤ ጦሩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሲቪል መንግስት ስልጣን እንዲያስረክብ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከንቅናቄ መሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የአገሪቱ የጦር ሃይል መሪ ሌ/ኮሎኔል አይዛክ ዚዳ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ስልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፤ ጦሩ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስልጣኑን የማያስረክብ ከሆነ፣ ቡርኪናፋሶን ከህብረቱ አባልነት ከማገድ አንስቶ በጦር መኮንኖች ላይ የጉዞ ማዕቀብ እስከመጣል የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
ድንገት የተቀሰቀሰው የቡርኪናፋሶ ህዝባዊ አመጽ ብሌስ ኮምፓዎሬን ከስልጣን ማውረዱን ተከትሎ፣ አገሪቱን የማስተዳደሩን ስልጣን የተረከበው የጦር ሃይል በአፋጣኝ ስልጣኑን ለተገቢው መሪ እንዲያስረክብ ሁኔታዎችን የማመቻቸት አላማ የያዘው የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች የልኡካን ቡድን፣ ወደ አገሪቱ በማምራት በጉዳዩ ዙሪያ መምከሩን ዘገባው ገልጿል፡፡
ጦሩ ስልጣኑን በአፋጣኝ እንዲያስረክብ ለማግባባት ወደ ቡርኪናፋሶ ያመሩት የጋና፣ የናይጀሪያና የሴኔጋል መሪዎች ከትናንት በስቲያ ከጦር ሃይሉ መኮንኖች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አካላት፣ ከጎሳ መሪዎችና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር መወያየታቸውንና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጪው አመት ህዳር ወር ላይ እስከሚካሄድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤትም በወሩ መጨረሻ በሚጠራው ስብሰባ አገሪቱን ከቀውስ ለማዳን በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ እንደሚመክርም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ ህገመንግስቱን በማሻሻል ያለ አግባብ በቀጣዩ የአገሪቱ ምርጫ ለመወዳደር መሞከራቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል፡፡