Administrator

Administrator

Saturday, 14 June 2014 12:20

የጸሐፍት ጥግ

ጭንቅላቴን ባዶ ለማድረግ መፃፍ አለብኝ፡፡ ያለዚያ አቅሌን እስታለሁ፡፡
ሎርድ ባይረን
በመፃፍ ካልተነፈስክ፣ በመፃፍ ካልጮህክ ወይም ካልዘመርክ አትፃፍ፡፡ ምክንያቱም ባህላችን ለፅሁፍ ቦታ የለውም፡፡  
አናይስ ኒን
ከሌላ ፀሃፊ ባለሁለት ቃላት ሃረግ ከምሰርቅ ሙሉ ባንክ ዘርፌ ብያዝ እመርጣለሁ፡፡
ጃክ ስሚዝ
ፅሁፍ ከዝምታ ጋር የሚደረግ ትግል ነው፡፡
ካርሎስ ፉንቴስ
ህትመት የሰውን አዕምሮ ለጨረታ ማውጣት ነው፡፡
ኤሚሊ ዲኪንሰን
የደራሲ ሁለቱ እጅግ ማራኪ ጥንካሬዎች፣ አዳዲስ ነገሮችን የተለመዱ ማድረግና የተለመዱትን አዲስ ማድረግ ናቸው፡፡
ሳሙኤል ጆንሰን
ለመፃፍ የተገደድክበትን ምክንያት እወቀው፡፡ ስሩን በልብህ ውስጥ ማሰራጨቱንም አረጋግጥ። መፃፍ ብትከለከል ብቸኛ አማራጭህ ሞት እንደሆነ ለራስህ ተናዘዝ፡፡
ሬይነር ማርያ
ጥሩ ልቦለድ የዋና ገፀ ባህሪውን እውነት ሲነግረን፣ ቀሽም ልቦለድ የደራሲውን እውነት ይነግረናል፡፡
ጂ.ኬ.ቼስቴርቶን
በአንድ ሰው አዕምሮ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃሳቦች ይኖሩታል፡፡ ያ ሰው ብዕሩን አንስቶ እስኪፅፋቸው ድረስ ግን እኒያ ሃሳቦች መኖራቸውን አያውቅም፡፡
ዊሊያም ሜክፒስ ታክሬይ
በእያንዳንዱ ጭንቅላት ውስጥ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስወግዱ መፃህፍት መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡
ጆን አፕዳይክ
ሰዎች በደምስሮቼ ውስጥ ቀለም፣ በትየባ ማሽኔ ቁልፎች ላይም ደም ማግኘታቸው አይቀርም፡፡
ቴሪ ጉይሌሜትስ
መፃህፍቱ ራሳቸው እንዲወለዱ ፈለጉ እንጂ እኔ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ወደ እኔ መጥተው “እንዲህና እንዲያ ሆነን ካልተፃፍን” ብለው ወትውተውኝ ነው፡፡
ሳሙኤል በትለር

ጀምስ ጆይስ (1882-1941)
ይሄ አየርላንዳዊ የሥነ-ፅሁፍ ሰው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ዝነኛ ደራሲያን መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1907 ዓ.ም “Chamber Music” የተሰኘ 36 ግጥሞችን ያካተተ መድበል ያሳተመ ሲሆን ከ 8 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ረዥም ልብ-ወለዱን ለህትመት አበቃ - “Dubliners” በሚል ርዕስ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ እንደወረደ ስልት (stream of consciousness) የአተራረክ ዘይቤ በመጠቀም የፃፈውን “A portrait of the Artist as a young Man” የተሰኘ ልብ-ወለዱን አሳተመ፡፡ ጆይስ ከዚህ በመቀጠል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያስገኘለትን “Ulysses” ነው ለንባብ  ያበቃው፡፡ የመጨረሻ ሥራው “Finnegan’s wake” በስነ-ፅሁፉ ዓለም ቀዝቃዛ አቀባበል በማግኘቱ ጆይስን ክፉኛ አስከፋው፡፡ አብዛኛውን ህይወቱን በገንዘብ ችግር ያሳለፈው ይሄ ዝነኛ ደራሲ፣ እስከ ዕድሜው የመጨረሻ ዓመታት ገደማ ድረስ ከስራው ምንም ገቢ አላገኘም ነበር፡፡
የጄምስ ጆይስ የአፃፃፍ ልማድ ከብዙዎቹ ደራስያን የተለየ ነበር፡፡ በቀን ምን ያህል ቃላት ወይም ገፆች እፅፋለሁ የሚለው ጉዳይ እምብዛም አሳስቦት አያውቅም፡፡ አንዲት ዓረፍተ ነገር ብቻ በመፃፍ ቀኑን  ሊያሳልፍ ይችላል፡፡ አንድ ወዳጁ “ደህና ፃፍኩ የምትለው ምን ያህል ስትፅፍ ነው?” ሲል ላቀረበለት ጥያቄ “ሦስት አረፍተ ነገሮች” በማለት መልሷል፡፡


ቭላድሚር ናቦኮቭ (1899-1977)
ትውልደ ሩሲያ አሜሪካዊ ደራሲው ቭላድሚር ናቦኮቭ፤ በረዥም ልብ-ወለድ ፀሃፊነቱ ይበልጥ ቢታወቅም ገጣሚና ሃያሲም ጭምር ነው፡፡ በከፍተኛ ፈጠራ የተሞላው አፃፃፉ እንደ 20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የሥነ-ፅሁፍ ሰውነቱ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎለታል፡፡ ናቦኮቭ እ.ኤ.አ በ1955 ለንባብ በበቃው “Lolita” የተሰኘ ረዥም ልብ-ወለዱ ይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን Pale Fire እና Ada የተሰኙ ተወዳጅነትን ያተረፉ ረዥም ልብ-ወለዶችንም ፅፏል፡፡ ሌሎች አያሌ ልብወለዶችን በእንግሊዝኛና በሩስያኛም የፃፈ ሲሆን፤ በርካታ የኢ-ልብወለድ ሥራዎችም አሉት፡፡
ቭላድሚር ናቦኮቭ የፅሁፍ ስራውን የሚያከናውነው ቁጭ ብሎ ወይም እንደ አንዳንድ ፀሃፍት ተጋድሞ ሳይሆን ቆሞ ነው፡፡ ለመፃፊያነት የሚጠቀመውም የተለመደውን ወረቀት አይደለም። በኢንዴክስ ካርዶች ነው የሚፅፈው፡፡ ይሄ ደግሞ ለትዕይንቶች ቅደም ተከተል ሳይጨነቅ እንዲፅፍ ነፃነት ይሰጠዋል፡፡ በኋላ የካርዶቹን ቅደም ተከተል እንደፈለገ ሊያስተካክል ይችላል፡፡ ደራሲው Ada የተሰኘውን ረዥም ልብ-ወለዱን ሲፅፍ ከ2ሺ በላይ ካርዶችን ተጠቅሟል፡፡


ጆይስ ካሮል ኦትስ
እ.ኤ.አ በ1938 የተወለደችው አሜሪካዊቷ ደራሲ ኦትነስ፤ በተለያዩ ዘውጎች በመፃፍ ትታወቃለች፡፡ አጭር ልብ-ወለዶች፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ የሰሉ ወጎችና ረዥም ልብወለዶችን ትፅፋለች፡፡ ሶስት ተከታታይ (trilogy) ረዥም ልብ ወለዶችን የፃፈች ሲሆን በ1967 A Garden of Delights፣ በ1968 Expensive People እና በ1969 Them በሚል ለንባብ በቅተዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ የመጨረሻው (Them ማለት ነው) በ1970 ዓ.ም የናሽናል ቡክ አዋርድ ተሸላሚ ሆኖላታል፡፡ ኦትስ ሌሎች በርካታ ሽልማቶችንም አሸንፋለች፡፡
የፈጠራ ሥራዋን የምትሰራበት የተወሰነ መደበኛ ሰዓት ባይኖራትም፣ ጠዋት ከቁርስ በፊት መፃፍ እንደምትመርጥ ትናገራለች፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪዋን የሰራችው ኦትስ፤ የበዩኒቨርሲቲ ፈጠራ አፃፃፍ የምታስተምር ስትሆን ክፍል ከመግባቷ በፊት ለአንድ ሰዓት ወይም ለ45 ደቂቃ ትፅፋለች፡፡ ክፍል በሌላት ጊዜ ደግሞ ለሰዓታት ስትፅፍ ቆይታ ቁርሷን ከሰዓት በኋላ በ8 ወይም በ9 ሰዓት ትመገባለች፡፡

      የእስራኤል ፕሬዚዳንት፣ ጠ/ሚንስትር፣ የገንዘብ ሚ/ር እና የኢኮኖሚ ሚ/ር በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ታዋቂ ድምጻዊት ኢስተር ራዳ፣ ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ጋዜጣ የአመቱ የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሁዳውያን ብሎ ከመረጣቸው 50 ታዋቂ ግለሰቦች መካከል አንዷ ሆነች፡፡
በሶል፣ በአር ኤንድ ቢ እና በፋንክ ስልቶች የተቃኙና የኢትዮ-ጃዝ ቃና ያላቸው ሙዚቃዎችን የምትጫወተውና “የእስራኤል የሶል ሙዚቃ ንግስት” በመባል የምትጠራዋ ኢስተር ራዳ፣ በእስራኤል ብቻም ሳይሆን በመላ አለም በርካታ አድናቂዎችን ማፍራት የቻለች ድምጻዊት መሆኗን ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው መረጃ መስክሮላታል፡፡
ጋዜጣው ተስፋ ከሚጣልባቸውና ከፍተኛ ስኬት ካስመዘገቡ የዘመኑ ተጠቃሽ ቤተ እስራኤላውያን አርቲስቶች ተርታ ትሰለፋለች ያላት ይህቺ ድምጻዊት፣ በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ስኬታማ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ማቅረቧንና፣ ኢትዮጵያዊ ቅኝት ያላቸውን ሙዚቃዎች እንደምትጫወትም ገልጧል፡፡
በሙዚቃው ዘርፍ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማፍራትና ለኤምቲቪ አውሮፓ የሙዚቃ ሽልማት እስከመታጨት የደረሰችው ኢስተር ራዳ፣ ‘ኪሮት’ እና ‘ስቲል ዎኪንግ’ን በመሳሰሉ ፊልሞች፣ ሙዚቃዊ ቲያትሮችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በተዋናይነት በመስራት ድንቅ የትወና ክህሎቷን አስመስክራለች፡፡
በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ ፖለቲከኞች፣ ተመራማሪዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ቢሊየነሮች፣ አርቲስቶችና በሌሎች ሙያዎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን የቻሉ ግለሰቦችን በዘንድሮው የአመቱ 50 የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሁዳውያን ዝርዝር ውስጥ ያካተተው ዘ ጀሩሳሌም ፖስት፤ ከእነዚህም ውስጥ ኢስተር ራዳን ጨምሮ 15 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ካቻምና በእስራኤል ጠ/ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፣ አምና ደግሞ በገንዘብ ሚንስትሩ የር ላፒድ ተይዞ የነበረውን የዚህ  ዝርዝር መሪነት፣ ዘንድሮ የአሜሪካ ትሬዠሪ ጸሃፊ የሆኑት ጃክ ሊው ተረክበውታል፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚናን በሚጫወተው በዚህ ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት እኒህ ሰው፣ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ውስጥ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ተሰሚ ሰው እንደሆኑ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
በተጽዕኖ ፈጣሪነት ሁለተኛውን ደረጃ የያዙት አሜሪካዊቷ ቤተ እስራኤላዊ ጃኔት የለን ሲሆኑ፣ የአሜሪካን ተቀማጭ ገንዘብ ተቋም እንዲመሩ በመመረጥ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው፡፡ እሳቸውን ተከትለው በዝርዝሩ የተካተቱት፣ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ (የእስራኤል ጠ/ሚንስትር) እና ሽሞን ፔሬዝ (የእስራኤል ፕሬዚዳንት) ናቸው፡፡
አቪግዶር ሊበርማን (የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ የር ላፒድ (የእስራኤል የገንዘብ ሚንስትር) እና ናፋታሊ ቤኔትም (የእስራኤል የኢኮኖሚ ሚንስትር)፣ በዘንድሮው ተጽዕኖ ፈጣሪ ቤተ እስራኤላውያን ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ታዋቂና በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ወላጆች ለልጆች እግር መበላሸት ተጠያቂ ናቸው ተባለ
         በቅርቡ የተካሄደ ጥናት፤ በዓለም ላይ 4ሚ. ያህል ህፃናት ልካቸው ያልሆነ በመጫማት እንደሚሰቃዩ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ ወላጆች ናቸው ይላል፡፡
የልጆቻቸውን እግሮች ልካቸው ያልሆነ ጠባብ ጫማ ውስጥ እንዲሰቃዩ የሚፈቅዱ ወላጆች፤ ለልጆቻቸው የዘላለም ችግር እያስቀመጡላቸው እንደሆነ ማወቅ አለባቸው ብሏል ጥናቱ፡፡ ጠባሳ፣ እብጠት፣ የጣት ጥፍር ወደ ውስጥ ማደግ… የአጭር ጊዜ ችግሮች ሲሆኑ የረዥም ጊዜ ችግሮች ደግሞ የእግር መንጋደድ ለምሳሌ የጣት መቆልመም እንዲሁም የጉልበትና የቅርጽ መበላሸት እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ጥርስ ብዙ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ያህል ለእግሮቻቸውም ሊያስቡላቸውና ሊጠነቀቁላቸው ይገባል ይላሉ፤ የእግር ጤናና እንክብካቤ ባለሙያዎች፡፡ ለመሆኑ 4ሚ. ህፃናት ለምንድነው ልካቸው ባልሆነ ጫማ የሚሰቃዩት? በቸልተኝነት? በገንዘብ እጥረት? በአመቺነትና ፋሽን በመሆኑ? ሁሉም ሰበብ ይሆናሉ ይላሉ ብለዋል በግላስጐው ካሌዶንያን ዩኒቨርሲቲ፣ በእግር ጤናና እንክብካቤ ዙሪያ ሌክቸር የሰጡት ዶ/ር ጐርዶን ዋት፡፡
የህፃናት እግሮች በዕድሜያቸው የመጀመያዎቹ አራት ዓመታት በፍጥነት የሚያድጉ ቢሆንም  የእግራቸው አጥንቶች፣ ጡንቻዎችና መገጣጠምያዎች እንደ አዋቂ እግር ለመጠንከር ግን እስከ 18 ዓመት ድረስ ሊወስድባቸው ይችላል የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ የታዳጊዎችም ሆነ የህፃናት እግሮች በቂ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚሹ ያሳስባሉ፡፡  በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ ከ10 ወላጆች አንዱ ልጆቹ ለእግራቸው የሚያንሳቸውን ጫማ አሁንም ድረስ እንደሚያደርጉ ሲናገር፣ ገሚሶቹ ወላጆች ደግሞ፤ ልጆቻቸው “ጫማው እግራችንን አሳመመን” ብለው እስኪጨቀጭቋቸው ድረስ አዲስ ጫማ እንደማይገዙላቸው ታውቋል፡፡
የእግር ህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ብዙ ሰዎች ለልጆቻቸው እግር ጥንቃቄ የማያደርጉት ጠባብ ጫማ መጫማት የሚያስከትለውን ችግር ስለማይረዱት ነው፡፡ ለዚህ ጥናት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወላጆች ውስጥ 40 በመቶ ብቻ ናቸው የልጆቻቸው ጫማ ልካቸው እንደሆነና ምቾት እንዳለው ለማረጋገጥ የሚተጉት ተብሏል፡፡
ልጆች ጫማ በተገዛላቸው ቁጥር እግራቸው መለካት እንዳለበት የሚያሳስቡት ባለሙያዎቹ፤ ወላጆች ጫማው ላይ የሰፈረውን ቁጥር ብቻ አይተው መግዛት እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡

Saturday, 14 June 2014 12:06

የቸኮሌት ነገር!

የደም ግፊትን ይቀንሳል
በኮኮዋ ውስጥ የሚገኙት ፍላቫኖልስ የተባሉት ንጥረ ነገሮች የደም ግፊት የሚቀንሱ መድሃኒቶችን ሥራ እንደሚሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፍላቫኖልስ ሰውነታችን ናይትረስ ኦክሳይድ እንዲያመርት በማድረግ ለደም ስሮች መከፈት እገዛ ያደርጋሉ፡፡
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች፤ ኮኮዋ ዘወትር መጠቀም የሰዎችን የደም ግፊት ዝቅ እንደሚያደርግ በጥናታቸው ያረጋገጡ ሲሆን 1 በመቶ ያህሉ ግን ቸኮሌትን ከመጠን በላይ በመመገብ ለሆድ ህመም መጋለጣቸውን በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረዋል።
የጉበት ጉዳትን ይከላከላል
ቸኮሌት ለደም ግፊት ያለው ጠቀሜታ የሚመነጨው በውስጡ ካለው ከፍተኛ የፍላቫኖል ይዘት  ነው፡፡ በጉበት ቬይኖች ከፍተኛ የደም ግፊት መከሰት ከጉበት ጉዳት ወይም ሥር ከሰደደ የጉበት በሽታ ጋር እንደሚገናኝ ይታመናል፡፡ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጥቁር ቸኮሌት መብላት በጉበት ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ያሻሽለዋል፡፡ ይኼው የቸኮሌት ዓይነት የጉበት ጉዳትን መከላከል ይችል እንደሆነ ለማረጋገጥ በአሁኑ ወቅት ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ለልብ ጤንነት ይጠቅማል
የደም ግፊትን ዝቅ በማድረግ፣ የደም ስሮችን በመክፈትና፣ ብግነትን በመቀነስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ቸኮሌት፤ የልባችንን ጤንነት በመጠበቅ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የልብ በሽታንና ስትሮክንም ይከላከላል፡፡ ከ114ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ ብዙ ቸኮሌት የሚመገቡ ሰዎች እጅግ አነስተኛ ከሚመገቡት ይልቅ በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው 37 በመቶ፣ ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድላቸው ደግሞ 29 በመቶ እንደቀነሰ ተረጋግጧል፡፡
ሸንቃጣ ያደርጋል
ከ1ሺ በሚበልጡ  ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው፤ ቸኮሌት መብላት የሚያዘወትሩ ሰዎች ሸንቃጣ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለጥናቱ የተመረጡት ሰዎች “በሳምንት ስንት ጊዜ ቸኮሌት ትመገባለህ/ትመገቢያለሽ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የጥናት ውጤታቸውን በ “አርካይቭስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን” ያሳተሙት ተመራማሪዎች፤ በሳምንት ውስጥ ደጋግመው ቸኮሌት የሚበሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ከሚበሉት የበለጠ ሸንቃጣ እንደሆኑ አረጋግጠዋል ፡፡
ብልህና ብሩህ ያደርጋል
በ”ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን” የወጣ አንድ ጥናት፤ ቸኮሌት በብዛት የሚጠቀሙ ህዝቦች ያላት አገር፣ ከሌሎች የበለጠ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች እንደሚኖራት አመልክቷል፡፡ ቸኮሌት አዘውትሮ መብላት ብልህና ብሩህ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የተጠቀሰችው ስዊዘርላንድ ናት፡፡
ስዊዘርላንዶች ቸኮሌት በብዛት በመመገብ የሚታወቁ ሲሆን ብዙ የኖቤል ተሸላሚዎች እንዳሏቸውም ተገልጿል፡፡ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በእንግሊዝ የኖቤል ተሸላሚዎችን ለማብዛት እያንዳንዱ ሰው በዓመት 2 ኪ.ግ ቸኮሌት መብላት ይኖርበታል፡፡

ጤናንና ህይወትን ለመታደግ ነው ተብሏል
ሲጋራ ማጨስ ለከፍተኛ የጤና አደጋ፣ ባስ ሲልም ለህልፈት እንደሚዳርግ ማንም ሊክድ አይችልም። እንዲያም ሆኖ ከወደ አየርላንድ የተሰማው አዲስ እገዳ ክፉኛ ያስደነገጠው ከአጫሾች ይልቅ የትምባሆ ኩባንያዎችን ነው። ሰሞኑን አየርላንድ ማንኛውም ሲጋራ ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ እንዳይኖረው የሚያግድ ህግ  አውጥታለች፡፡ እገዳው ሲጋራዎች ላይ ብቻ ግን አይደለም፤ የሲጋራ ፓኮዎችም ያለምንም ፅሁፍና ምልክት ለገበያ እንዲቀርቡ ህጉ ያስገድዳል። አዲሱ ህግ የትምባሆ ኩባንያዎችን ቢያስከፋም የአየርላንድ የጤና ሚኒስትር ጄምስ ሬይሊ፤ እገዳው የብዙዎችን ህይወት ለመታደግ ያግዛል ብለዋል፡፡
የምርት ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ ያለው ሲጋራ ለሸማቶች እንዳይቀርብ የሚያግድ ህግ በማጽደቅ አየርላንድ በአውሮፓ የመጀመሪያዋ አገር ናት ተብሏል፡፡
አውስትራሊያ ተመሳሳይ እገዳ በሲጋራ ላይ በመጣል ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን ኒውዚላንዶች ደግሞ በረቂቅ ህጉ ላይ እየተከራከሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡ እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገራት እገዳው በህግ የመውጣቱን አስፈላጊነት ገና እያጤኑት ነው ተብሏል፡፡
የአየርላንድ ጤና ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ፤ “የህጉ ዓላማ የሲጋራ ፓኮዎች ለሸማቾች ያላቸውን ማራኪነት በመቀነስ፣ በጤና ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ማጉላት ነው፡፡ ፓኬቶች ሰዎችን በተለይ ህፃናትን የማሳሳት አቅማቸውን በመቀነስ የማጨስ ጐጂነትን እንዲገነዘቡ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
የትምባሆ ኩባንያዎች ግን እገዳውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ የትምባሆ ምርቶችን ስያሜና አርማ አልባ አድርጐ ማቅረብ፣ ሃሰተኛ የሲጃራ ምርቶችን የሚያመርቱ ወንጀለኞችን የሚያግዝና የሚያበረታታ ነው ብለዋል - ኩባንያዎቹ፡፡
ቤንሰን ኤንድ ሄጅስ እና ደንሂል በሚሉ ስያሜዎች የሚታወቁት ሲጋራዎች ባለቤት የሆነው የብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ (BAT) ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ የአየርላንድ ካቢኔ ረቂቅ ህጉን ማጽደቁ አሳዝኗቸዋል።
“ምንም ፅሁፍ ያልሰፈረበት ሌጣ ፓኬት፣ ታዳጊዎች ሲጋራ እንዳይጀምሩ ወይም አጫሾች ማጨስ እንዲያቆሙ ስለማድረጉ ተዓማኒ ማስረጃ የለም” ሲል ተሟግቷል  ተቋሙ፡፡
በቅርብ ዓመታት ሲጋራ ማጨስ በህብረተሰቡ ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ያደረገችው አየርላንድ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በስራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስን ሙሉ በሙሉ የሚያግድ ህግ በማውጣት በዓለም የመጀመርያው አገር ሆናለች፡፡ በሥራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስ የሚከለክለው ህግ መሸታ ቤቶችንና ክለቦችንም እንዳካተተ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ የህጉ ተፈፃሚነት 97 በመቶ እንደተሳካ ተገልጿል፡፡

Saturday, 14 June 2014 12:04

የኢትዮጵያ ታሪክ

...በዚያም ወራት ደጃች ብሩ፤ ጭልጋ አርባ አምባ ታስሮ ሳለ፣ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ከእልፍኝ አሽከሮቿ አንዱን መልምላ ውሽማ አበጅታ ነበረ፡፡ ይህን ነገር ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ አዘነ፡፡ በበገና እንዲህ ብሎ አለቀሰ፡፡ ...
“መከራን በሰው ላይ እንዲያ ሳቀለው፣
ምንኛ ከባድ ነው እኔ ብይዘው፡፡
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣
ሲገሠግሥ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ፡፡
ዘሃው ሰለሰለ ሸማኔው ተቆጣ፣
እስተወዲያው ድረስ መጠቅለያ ታጣ፡፡
የኔታም አይመጡ እኔም አልመለስ፣
ዋ ቢቸና ቀረ እስተወዲያው ድረስ፡፡
ከእልፍኝ ሰው አይግባ ሚሽቴን ሰው አይያት አይሉም አይሉም፣
ፈረሱን ሰው አይጫነው፣ በቅዬን ሰው አይጫነው አይሉም አይሉም፣
ጠጁ ቀጠነብኝ፣ ሥጋው ጎፈየብኝ አይሉም አይሉም፣
ቀን የጣለ ለታ፣ የጨነቀ ለታ፣ ይደረጋል ሁሉም። አለ፡፡
የደጃች ብሩ ግጥም ብዙ ነው፡፡ በሰራው ክፋት ብድሩን ከፈለ፡፡ በዘመኑ ጎጃምን ሲገዛ ያደረገው ክፋት ተጽፎ አያልቅም፡፡ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ቤተክርስቲያን ልትሳለም በምትወጣበት ቀን አስቀድሞ ሰው የገባ እንደሆነ የዱላ በረዶ ይወርድበት ነበር፡፡ በደረቤ በየወረዳው ፲ ፲ (አሥር አሥር) እንስራ ጉንዳን ለምስጥ ማጥፊያ ብሎ ደሃውን አስጨንቆት ነበረ፡፡ ያንን ጊዜ ባላገር ጉንዳን በሣምባ ሥጋ እየተሰለበ በእንስራ ውስጥ እየከተተ ወደ ሶማ አምባ ሲወስድ ጆሮውንና ትክሻውን እየነከሰ አስቸገረው፡፡ የዚህ ጊዜ በለቅሶ ሲአንጎራጉር እንዲህ አለ፡፡
ከመከራው ሁሉ የጉንዳኑ ባሰ፣
የተሸካሚውን ጆሮና ትክሻ እየተናከሰ፡፡ አለ፡፡
ደግሞ የሴት ብልት ጠጉር የበቅሎ ቁርበት ይበጃል ብሎ ፭፻ ጉንዲ ጠጉር በሚዛን አምጡ ብሎ በየወረዳው ጥሎ ደኃውን አስለቀሰው፡፡ በሚዛን ሳይሞላለት ጊዜ የራሱን ጠጉር እየጨመረ ቢሰጥ እምቢ እያለ ወርቅ ተገላገለው፡፡
ያን ጊዜ የሴት ዘመድ የሌለው ተቸግሮ ነበረ፡፡ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ እንዳይሰብረው ብሎ ሶማን ሊያሰራ ፴ ጎበዝ ግንድ ተሸክሞ ሲወጣ፣ ከጠባብ ቦታ ላይ ተጨናንቆ ግንዱ ወንጥሎት ገደል ይዞት ገባና አለቀ፡፡ ይኸን ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ ገበሬ ምንኛ ተዋዳጅ ነው፡፡ አንድነት ወርዶ አለቀ ወይ ብሎ ቀለደ፡፡ አለሚገባ እጁን  እግሩን የቆረጠው ሰውም ብዙ ነው፡፡
ይህን ሁሉ ክፋት ክርስቶስ መዝኖ ጊዜው ሲደርስ፣ በአጼ ቴዎድሮስ እጅ አግብቶ ሚሽቱን ለጠብደል ማላገጫ አድርጎ ሲአስለቅሰው ኖረ። የደጃች ብሩን ልቅሶ አጼ ቴዎድሮስ በሰማ ጊዜ ሎሌዎች በድለዋል አሉና ልቅጣዎ ብሎ ላከበት። ደጃች ብሩም ለጊዜው ኀዘን አብርትቶ ነበረና መንግሥትዎን ያሰንብትልኝ፡፡ ቃሉ ደረሰኝ፡፡ ግን የጮሁለት ሰው አለና የዚያን ቁርጥ ሳውቅ ይሁን አለ፡፡
መልክተኛው ከመድረሱ ውሽማዋን መብረቅ ገደለው፡፡ ደጃች ብሩም ክርስቶስ ሰማኝ፡፡ ፍርዱን ፈረደ፡፡ ባላጋራየ ሞተ ብሎ ላከ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ሰምቶ ተደነቀ፡፡ ለካስ ደጃች ብሩ አጥብቀው አዝነዋል፡፡ ክርስቶስም ሰማቸው፤ በኔም ቢአዝኑ ያደርሱብኛል ብሎ ፈተህ አምጣልኝ አለ፡፡
ከታሰረበት ፈትቶ ወደ አጼ ቴዎድሮስ እጅ ሊነሣ ሲኸድ፣ ያው ጋኔኑ ጥንተ ትቢቱ አልለቀው ብሎ ተከናንቦ ሎሚ ታህል ደንግያ በትከሻው ይዞ ሊታረቅ መጣ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ክንንቡንና የድንጋይቱን ማነስ አይቶ ተበሳጭቶ፣ ትቢትዎ አለቀቀዎምሳ ቢለው፣ ክንብንቤን እንደሆነ የጭልጋ በረሃ  ጠጉሬን ጨርሶት ባፍር ነው አለ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ከአብራጃው አገር መቅደላ ይቆዩ፡፡ እኔ ልፈታዎ ነበረ፡፡ ነገረ ክርስቶስ ማቆያ በትቢት ምክንያት አመጣብዎ፡፡ ፈቃዱ ሲሆን ይፈታሉ አለው፡፡  
ምንጭ - (አለቃ ተክለኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሐተታ (በሥርግው ገላው (ዶ/ር))

Saturday, 14 June 2014 12:03

የፍቅር ጥግ

የምወድሽ ስለአንቺነትሽ ብቻ አይደለም። ካንቺ ጋር ስሆን ስለምሆነው እኔነቴም ጭምር ነው፡፡
ሮይ ክሮፍት
መፈቀርን ብቻ አይደለም የምፈልገው፤ መፈቀሬ እንዲነገረኝም እሻለሁ፡፡
ጆርጅ ኤልዮት
ሰዎችን ከፈረጅካቸው ለፍቅር ጊዜ አይኖርህም፡፡
ማዘር ቴሬዛ
አንቺ ለእኔ ጣፋጭ ስቃዬ ነሽ፡፡
                     ራልፍ ዋልዶ ኤመርሶን
ፍቅር ፈፅሞ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ሞቶ አያውቅም፡፡ የሚሞተው ምንጩን ማደስ ስለማናውቅበት ነው፡፡ የሚሞተው በጭፍንነት፣ በስህተትና በክህደት ነው። የሚሞተው በህመምና በቁስል ነው። የሚሞተው በድካም፣ በመጠውለግና በመመረዝ ነው፡፡
አናዩስ ኒን
ቤተሰብ የሚጀምረው ከየት ነው? ጉብሉ ከኮረዳዋ ጋር በፍቅር ሲወድቅ ነው፡፡ ከዚህ የላቀ አማራጭ እስካሁን አልተገኘም፡፡
ሰር ዊንስተን ቸርችል
የተወለድነው ለብቻችን ነው፡፡ የምንኖረው ለብቻችን ነው፡፡ የምንሞተውም ለብቻችንን ነው፡፡ ብቻችንን አይደለንም የሚለውን ማስመሰል መፍጠር የምንችለው በፍቅርና በጓደኝነት አማካኝነት ብቻ ነው፡፡
ኦርሶን ዌልስ
ለእውነተኛ ፍቅር ጊዜም ሆነ ቦታ የለም። የሚከሰተው እንደ አጋጣሚ ነው፡፡ በልብ ምት፣ በአንዲት ብልጭታ፣ በትርታ ቅፅበት ነው፡፡
ሳሬ ዴሴን

         “ሉሲ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” የሚለው መፅሀፍ ላይ የሚከተለው ታሪክ ይገኛል፡፡
በድሮ ዘመን በጣም ደስተኛ የሆነ ሰው ከሚወዳት ሚስቱና ከአራት ወንዶች ልጆቹ ጋር ይኖር ነበር። የአንጋፋው ልጅ ስም ጥልቅ ዓይን ይባላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቆቁ ተባለ፡፡ ሶስተኛው ልጅ ጡንቸኛው የሚል ስም ተሰጠው፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጅ ህፃን ስለነበር ስም አልተሰጠውም፡፡
አንድ ቀን በማለዳ እናታቸውና ልጆቹ ከመኝታቸው ሲነሱ አባታቸውን ከቤት አጡት፡፡ በሚቀጥለው ምሽትም ሳይመለስ ቀረ፡፡ በማግስቱም የአባታቸው ዱካ ጠፋ፡፡ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር ብዙ ተወያዩ፡፡ ወዴት እንደሄደ ማንም የሚያውቅ የለም፡፡
እናታቸው ራሷን በሁለት እጆቿ ደግፋ ለቅሶና ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡ ጥልቅ ዓይን “ምናልባት አጎታችንን ሊጠይቅ ሄዶ ይሆናል፡፡” አለ፡፡ “ድግስ ተጠርቶ ወደ ጎረቤት ሄዶ ይሆናል” ሲል ቆቁ የራሱን ግምት ሰጠ፡፡ “ምናልባትም ወደ ተራራ ወጥቶ ነፋስ እየተቀበለ ይሆናል” በማለት ጡንቸኛው የበኩሉን ግምት ተናገረ፡፡
ይሁንና አባታቸው እንደጠፋ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ አልፎ አልፎ ልጆቹ ወደ ጫካና ወደ ተራራ ሄደው ከፍ ባለ ድምፅ አባታቸውን ይጣራሉ፡፡ መልስ ሳያገኙ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በሁኔታቸው እየተሰላቹ ስለሄዱ መፈለጉን አቆሙ፡፡
ሕፃን ወንድማቸው ግን እንደነሱ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ አንድ ቀን ጧት እናቱ አቅፋው ሳለ፣ ህፃኑ ልጅ “አባቴ የት አለ? አባቴን እፈልጋለሁ፡፡” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገረ፡፡ ታላቅ ወንድሙ ጥልቅ ዐይን “እውነት ነው፡፡ አባባ የት አለ?” በማለት ሕፃኑን እየተመለከተ እርሱም ጠየቀ፡፡ “አሁኑኑ ተነስተን አጥብቀን ብንፈልገው ይሻላል” ሲል ጡንቸኛው አምርሮ ተናገረ፡፡
መፈለግ ቀጠሉ“ቆይ-ቆይ ከሩቅ ቦታ የለቅሶ ድምጽ ይሰማኛል፡፡ በዚህ በኩል… ጪኸት እየሰማሁ ነው! ተከተሉኝ!” በማለት ቆቁ አስገነዘበ፡፡ እንደ ጩኸቱ ቅርበትና ርቀት ቆቁ በተሰማው አቅጣጫ ተያይዘው ተጓዙ፡፡ በመጨረሻም ወደ አንድ ወንዝ ተቃረቡ፡፡ አባታቸው በወንዙ ዳርቻ በጦሩ ከወጋው አነር ጋር ተፋጦ አዩት፡፡ አነሩ የአባታቸውን እግር አቁስሎታል፡፡ “አባባን ማዳን ይገባናል!” በማለት ጡንቸኛው ጮኸ፡፡ በቅጽበት በጠንካራ ጡንቾቹ አነሩን አነቀው፡፡ የታነቀው አነር አየር አጥቶ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡
“እጅግ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ደረሳችሁልኝ! ዘነጣጥሎ ይበላኝ ነበር፡፡ በጦር ብወጋውም አስቀድሞ አቁስሎኝ ስለነበር ደከመኝ፡፡ እህል ውሃም ስላልቀመስኩ ድካሜ ተባባሰብኝ፡፡ አመጣጤ የሚታደን ነገር ለማግኘትና ለእናንተ ለማምጣት ነበር” እያለ አባታቸው አስረዳ፡፡ ሁሉም ሰው “ጀግኖች ናቸው፡፡” በማለት አደነቃቸው፡፡
ወንድማማቾቹ ይህንኑ የሕዝብ አድናቆት ሰሙ፡፡ በመካከላቸው ታላቅና ኃይለኛ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ አባታቸውን በማዳን ማን ዋነኛውን ተግባር (ሥራ) እንደሰራ ለማወቅ ይነታረኩ ጀመር፡፡ ጥልቅ ዐይን “እኔ ዱካውን (ኮቴውን) ባላየው ኖሮ አባታችን የሄደበትን አናውቀውም ነበር” አለ፡፡ ቆቁ በበኩሉ “ዱካው አንድ ቦታ ስንደርስ ጠፍቷል፡፡ እኔ የለቅሶውን ጩኸት ሰምቼ ባልመራችሁ ኖሮ አባታችንን ማግኘት አንችልም ነበር” ሲል ተከራከረ፡፡
“ሁለታችሁም ተሳስታችኋል፡፡ አባታችንን ብናገኘው ምን ዋጋ አለው፡፡ እኔ አነሩን ባልገልለት ኖሮ አባታችን እኮ በአነሩ ይበላ ነበር፡፡ ዋናው ክብር ለእኔ ይገባኛል!” እያለ ጡንቸኛው ደነፋ፡፡ ወደ አባታቸው ሄዱ፡፡ እርሱን በማዳን ረገድ ክብር የሚሰጠው ማን እንደሆነ እንዲነግራቸውም ጠየቁት፡፡
አባታቸውም “ሰማችሁ ልጆቼ እኔን በመታደጋችሁ ባለውለታዬ ናችሁ፡፡ ከሦስታችሁም እኔን አድኖ ለቤት ለማብቃት ትልቁን ክብር የሚያገኝ የለም፡፡ አንዳችሁም ትልቁን ክብር የሚያሰጥ ውለታ አልሰራችሁም፡፡ ለትልቁ ክብር የሚበቃ ሥራ የሰራው ይህ ህፃን ወንድማችሁ ነው፡፡  ክብር ለሕፃኑ ትንሽ ወንድማችሁ ይገባዋል፡፡ ጀግናችሁ ነው” በማለት አባታቸው ነገራቸው፡፡ ትንሹን ሕፃንም ታቀፈው፡፡
*         *        *
ትክክለኛው ክብርና ምሥጋና ለሚገባው ተገቢውን ክብር እንስጥ፡፡ የሌሎችን ዋጋ ለመውሰድ ጥቅማቸውንም ለመንጠቅ አንሞክር፡፡
በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስን አንመኝ! ዛሬ ሁለ-መናችንን ጠንቅቀን ለማየት ጥልቅ-ዐይን ያስፈልገናል፡፡ የምናየውንና የሚገጥመንን ሁሉ ያላግባብ እንዳንመዝንና የተሳሳተ ምላሽ እንዳንሰጥ ቆቅነት ያስፈልገናል፡፡ ይሄ ሁሉ ኖሮን ግን አቅም ማዳበር ካልቻልን ከንቱ ነው! በመጨረሻም እንደህፃን የዋህ የሆነ ልቡና ያሻናል - የምንፈልገውን ሁሉ በንፅህና ለመጠየቅ! ተስፋ የማይቆርጥ የህፃን መንፈስ ሁልጊዜም ያስፈልገናል፡፡ መሸለም ያለበትና ዘላቂው ተሸላሚ ይሄ ተስፋ የማይቆርጥ የነገ ተስፋ ነው!
ቻይናዎች ሁለት የፊደል ባህሪያትን አገጣጥመው ነው ድቀትን (Crisis)፣ የችግር ጊዜን፤ የሚተረጉሙት። ሁለቱ ባህሪያት ጣጣ (Risk) እና አጋጣሚ (Opportunity) ናቸው፡፡ አንድን ጉዳይ፣ (የችግር ጊዜ) ለማሸነፍ የሚያመጣውን ጣጣ ልንችል፣ ያሉንን አጋጣሚዎች ልንጠቀም ዝግጁ መሆን አለብን እንደማለት ነው፡፡ የሀገራችንን አያሌ ችግሮች እንዲህ ቆርጠን እንፍታቸው ካ›ልንና ዝግጁነት ካላሳየን፣ የውሃ ላይ ኩበት ነው የምንሆነው፡፡ ጣጣውን ችሎ አጋጣሚን ለመጠቀም መነጋገር,፣ መመካከር ፣ አዕምሮን ከአዕምሮ ማወዳደርና መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም ያለፈቻቸው አምስት ዘመናት አሉ፡፡ አንደኛው “ዓለም እኔን የምትሰማኝን ያህል ናት” ያልንበት ነው፡፡ ሁለተኛው “ዓለም እኔ ነች ብዬ የማስባት ናት” የምንልበት ነው፡፡ ሶስተኛው ዓለም እልቆ መሣፍርት የሌላት ማሽን ናት፡፡ እንዴት እንደምትሠራ እደርስባታለሁ” የምንልበት የሳይንስ ዘመን ነው፡፡ አራተኛው “ዓለም እኔ በፈጠርኳቸው ልዩ ልዩ ምናልባቶች የተሞላች ስትሆን ይምህ የእኔ አመለካከት ያመጣው ነው” የተባለበት ነው፡፡ በመጨረሻም፤ “የእኔ ዓለም ማናቸውም ቀመር (formulation) የማይወስነው መዋቅር ያላት ናት፡፡ እኔ ዓለምን የማያት ከሷ ጋር እንዳለኝ ጅምላ ልምድ ነው። እናም በራሴ ምልክት ስሪቶች (Symbolic constructs) ራሱን ነፃ በማውጣት መንፈስ እየተጫወትኩ፣ እየተንቀሳቀስኩ ነው” የምንልበት ዘመን ነው፡፡ የዓለምን ታሪክ ወደራሳችን ተርጉመን ፋይዳ ሰጥተን ካስተዋልነው፤ ለውጥ የማምጣትና የማሸነፍ ዕድል አለን፡፡
ቴድ ሲልቬይ የተባለ ፀሀፊ ይሄን ይላል “... ለደጋ ፍየሎች መረማመጃ የድንጋይ ደረጃ እንሰራለን። ለእንስሶች ማረፊያ ቤት እንሰራለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእባብም የሚያስደስተውን የአየር ማረጋጊያ (Air conditioning) እናደርጋለን! ለሰው ልጅ ግን ተገቢውን መጠለያ፣ ለህፃናትም በቂ መኖሪያ ሥፍራ፣ አንሰጥም” ይላል፡፡ ለዜጎቻችን ቢያንስ መሰረታዊውን የቤት ችግር ማስወገድ - በተለይ ይሄ ሁሉ የቤት ሙስና ባለበት አገር - እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አናንቀላፋ፡፡ በግሪክኛ Hypnos - እንቅልፍ ማለት ነው፡፡ Hypnos የሚለው ቃል ሥረ ቃሉ hypnosis ነው፡፡ ይህኛው ግን በመንቃትና በመተኛት መካከል ያለ ሰመመናዊ ስሜት ነው፤ ይለናል ሚካኤል ፓወል፡፡
ሁኔታዎች አጥፊያችን ሆነው ስናገኛቸው በቆቅ ዐይን ማየት እንጂ ሰመመን ውስጥ (Hypnosis) ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ መንቃት፣ ጆሮአችንን ማንቃት፣ አቅማችንን ማወቅና መስፈንጠር፤ እመርታ ማሳየት አለብን፡፡ አለበለዚያ እንደ አፈ-ታሪኩ፤ “ዕባብ ያፍዝ ያደንግዝ ያደረገባት ወፍ፤ ክንፍ እንዳላት ትረሳለች” መባል አይቀርልንም፡፡  በጥቅምት 2006 ይጠናቀቃል የተባለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ገና አልተጀመረም

የፋብሪካ ግንባታ በመጓተቱ፤ የ100 ሚሊዮን ብር ሸንኮራ አገዳ ያለ ጥቅም ተወግዷል

የፕሮጀክቶቹ የገንዘብ ወጪ በውል አይታወቅም፤ ያለ ጥናትና ዲዛይን የተጀመሩ ናቸው

           መንግስት በመቶ ቢሊዮን ብር ወጪ የስኳር ምርትን 23 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ የሚያካሂዳቸው ከአስር በላይ አዳዲስና ነባር የስኳር ፕሮጀክቶች ያለ ውጤት ለአመታት የተጓተቱ ሲሆን፤ የመስኖና የፋብሪካ ግንባታዎቹ ለተቋራጭ ድርጅቶች የተሰጡት በህገወጥ መንገድ ያለጨረታ እንደሆነ የፌደራል ኦዲተር ገለፁ፡፡ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ህግን ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ሙሉ ለሙሉ ለብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መሰጠቱን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ የፋብሪካዎቿ ግንባታ እንደተጓተተ ገልጿል፡፡ ያለ ጨረታ የመስኖና የአገዳ ልማት ፕሮጀክቶችን ወስደው ስራ ያጓተቱ ተቋራጮች፤ በአዲስ አበባና በየክልሉ የሚገኙ የውሃ ስራ ድርጅቶች እንዲሁም የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የመንግስትን የግዢ መመሪያ ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ለተቋራጮች መሰጠታቸው፣ በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ እንዳይጠናቀቁ ያደርጋል ብሏል - የኦዲተሩ የምርመራ ሪፖርት፡፡

ፕሮጀክቶቹ ለተቋራጮቹ የተሰጡበትን አሰራር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች፣ በግዢ ክፍሉ በኩል የምናውቀው ነገር የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የኮርፖሬሽኑን የአምስት አመታት እቅድ አፈጻጸም በተመለከተ የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በጣና በለስ እና በኦሞ-ኩራዝ ፕሮጀክቶች፣ የ3 ፋብሪካዎች ግንባታ እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ እቅድ ወጥቶ እንደነበር የገለፀው የፌደራል ኦዲተር፤ እስከ አመቱ መጨረሻ የተከናወነው ስራ ግን ከ45 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው የወልቃይት የስኳር ፋብሪካ ግንባታም፣ ገና ግንባታው ሳይጀመር የእቅዱ ጊዜ ማለፉ ተገልጧል፡፡

በአገዳ ተክል ልማት፣ በመስኖ ስራና በፋብሪካ ግንባታ በኩል ኮርፖሬሽኑ የሚያዘጋጃቸው የስኳር ፕሮጀክት እቅዶች የሰው ሃይልንና የገንዘብ ምንጭን ያላገናዘቡ፣ ተግባሪ አካላትን ያላሳተፉና በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረቱ መሆናቸውን በምርመራ እንደደረሰበት ኦዲተሩ ገልፆ፤ በዚህም ምክንያት የኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ እቅዶች በአመት ከሶስት ጊዜ በላይ ይከለሳሉ ብሏል፡፡ ይህም ፕሮጀክቶቹ እንዲጓተቱ ማድረጉንና መንግስትን ተገቢ ላልሆነ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ የኦዲተሩ ሪፖርት ገልጿል፡፡ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የፋብሪካ ግንባታ ስራ በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በ5ሺህ164 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የሸንኮራ አገዳ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲወገድ መደረጉን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ በዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰ አመልክቷል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በትክክል ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገባቸው በውል ለመለየት አለመቻሉን የገለጸው የኦዲተሩ ሪፖርት፤ ከአገዳ ልማት፣ ከመስኖ ግንባታና ከፋብሪካ ግንባታ ክፍል ጋር የተቀናጀና የተጠናከረ የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት በየአመቱ ተደጋጋሚ የዕቅድ ክለሳ በማድረግ የዕቅድ አፈጻጸም መጓተትን፣ የወጪ መጨመርን፣ የጊዜ መራዘምንና የሃብት ብክነትን አስከትሏል ብሏል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለአመታት መጓተታቸው፤ የሃብት ብክነትን ከመፍጠር በተጨማሪ በአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቀመጠው ግብ እንዳይሳካ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የአገሪቱ የስኳር ምርት በየአመቱ እንደሚጨምር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ የስኳር ምርት እየቀነሰ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአምስት አመት ውስጥ የስኳር አመታዊ ምርት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 22 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ ታቅዶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ እስካሁን አራት ሚሊዮን ኩንታል አለመድረሱ ተዘግቧል፡፡