Administrator
ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርቀዳጅ እና አስደናቂ ስኬት አስመዝግቧል
የኢትዮጵያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ ስምንት ምርጥ ክለቦች ተርታ የገባበት ብቃት አስደነቀ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሰው መልእክት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ማጣሪያ ያለፈ የመጀመርያ ክለብ በመሆኑ ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት ተምሳሌት መሆኑን አረጋግጧል በማለት ብሏል፡፡ ዘንድሮ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድደሮች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ አስደናቂ ተሳትፎ ያደረገው ክለቡ ስምንት ጨዋታዎች አድርጎ አራቱን ሲያሸንፍ በ3 አቻ ተለያይቶ እና 1 ጨዋታ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን 17 ግብ ተጋጣሚዎቹ ላይ ሲያስቆጠር፤ሰባት ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውበታል፡፡ የውድድር ዘመኑን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በመሳተፍ የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ ቅድመ ማጣርያ የተገናኘው ከዛንዚባሪ ጃምሁሪ ጋር የነበረ ሲሆን በሜዳው 3ለ0 ከዚያም ከሜዳው ውጭ 5ለ0 በማሸነፍ ብድምር ውጤት 8ለ0 አሸንፎ ወደ የመጀመርያው ዙር ማጣርያ ገብቷል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር ያገኘው ክለብ የማሊው ዲጆሊባ ነበር፡፡
በሜዳው 2ለ0 አሸንፎ ከሜዳው ውጭ አንድ እኩል አቻ በመለያየት በድምር ውጤት ዲጆሊባን 3ለ1 በመርታት ወደ ሁለተኛው ዙር ገብቷል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከግብፁ ክለብ ዛማሌክ ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ 1ለ1 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ2 አቻ በመለያየቱ በድምር ውጤት 3ለ3 ቢሆንም የግብፁ ክለብ ዛማሌክ ከሜዳው ውጭ ባገባቸው ጎሎች በልጦት ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል የሚገባበት እድል አምልጦት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ከተሰናበተ በኋላ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፍ የሚሳተፍበትን እድል አግኝቶ ከሌላው የግብፅ ክለብ ኤን.ፒ.ፒ.አይ ጋር ተገናኘ።
በሜዳው ኢኤንፒፒአይን 2ለ0 በማሸነፍ ለመልስ ጨዋታ ወደ ካይሮ በመጓዝ 3ለ1 ከተረታ በኋላ የደርሶ መልስ ውጤቱ 3ለ3 ቢሆንም ከሜዳው ውጭ ባስቆጠረ በሚለው ደንብ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል በመግባት ታሪክ ሰርቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ ፈርቀዳጅ የነበረ ክለብ ነው፡፡ የመድን እግር ኳስ ክለብ በኮንፌደሬሽን ካፕ ከኢትዮጵያ ክለቦች አምስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻለበትን ክብረወሰን ዘንድሮ የተጋራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምድብ ድልድል የደረሰ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ክለብ በመሆን በፈርቀዳጅነት ቀጥሏል፡፡ የ2013 ኮንፌደሬሽን ካፕ በምድብ ጨዋታዎች ከ6 ሳምንት በኋላ ሲጀምር በምድብ 1 ከአንድ የሰሜን አፍሪካ እና ከሁለት የምዕራብ አፍሪካ ክለቦች ጋር የተገናኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫ ጨዋታ ሊደርስ እንደሚችል ግምት ወስዷል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፑ የምድብ ድልድል በምድብ 1 የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ የማሊው ስታድ ደማሌይን፤ የናይጄርያው ኢኑጉ ሬንጀርስ እና የቱኒዚያ ኤትዋል ደሳህል ሲገኙ፤ በምድብ 2 የዲ ሪ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ፤ የቱኒዚያው ሲኤ ቤዛርቲን፤ የአልጄርያው ኢኤስ ሴቲፍ እና የሞሮኮው ኢፍሲ ራባት ተደልድለዋል፡፡ በምድብ ድልድሉ በመግባት ለዋንጫው ጨዋታ መድረስ እና በየምድቡ በሚገኝ የደረጃ ውጤት መሰረት ለእግር ኳስ ክለቦቹ ብቻ ሳይሆን ለወከሉት አገር የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም የገንዘብ ሽልማት ይከፋፈላል፡፡
ከሁለቱ ምድቦች መሪ ሆነው የሚጨርሱት ለኮንፈደሬሽን ካፑ ዋንጫ ሲጫወቱ አሸናፊው ክለብ 625ሺ ዶላር ሲያገኝ የወከለው ፌደሬሽን 35ሺ ዶላር እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ያገኘው ክለብ 432ሺ ዶላር ሲታሰብለት የወከለው ፈደሬሽን ደግሞ 30ሺ ዶላር ይሰጠዋል፡፡ በኮንፌደሬሽ ካፑ የምድብ ድልድል በየምድባቸው 2ኛ ደረጃ የሚያገኙት 239ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 25ሺ ዶላር፤3ኛ ደረጃ የሚያገኙት 239ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 20ሺ ዶላር እንዲሁም 4ኛ ደረጃ የሚያገኙት 150ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 15ሺ ዶላር እንደሚበረከትም ታውቋል፡፡
ለፑሽኪን በአፍሪካ ግዙፉ ሐውልት ሊቆምለት ነው
ለሩሲያዊው ባለቅኔ አሌክሳንደር ፔትሮቪች ፑሽኪን፣ ሦስት ቶን ክብደት ያለው ግዙፍ የነሐስ ሐውልት በአዲስ አበባ ሣር ቤት አካባቢ በሚገኘው “ፑሽኪን አደባባይ” ሊቆምለት እንደሆነ የሩሲያ የሳይንስ እና ባህል ማእከል አስታወቀ፡፡ ማእከሉ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፣ የነሐስ ሐውልቱ በአፍሪካ አህጉር በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን በታዋቂው ሩስያዊ ቀራፂ ዲሚትሪ ኩኮለስ ተቀርፆ በሞስኮ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉልን ነው ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር፣ የፑሽኪንን ኢትዮጵያዊ ቅድመ አያት አብርሃም ጋኒባልን ያካተተው ሃውልት፣ በጣም ያጌጠና የውጭ ጐብኝዎችን ጭምር የሚስብ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ የፑሽኪን ልደት በዚህ ሳምንት በሩስያ፣ በኢትዮጵያ እና በተቀረውም ዓለም እየተከበረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር “የጥበብ እልፍኝ” የተሰኘ የሬዲዮ ዝግጅት ጀመረ
ከተመሠረተ 53ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ “የጥበብ እልፍኝ” የተሰኘ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ባለፈው ማክሰኞ ጀመረ፡፡ በየሳምንቱ ማክሰኞ በኤፍኤም አዲስ 97.1 የሚቀርበው ዝግጅት፣የሁለት ሰዓት የአየር ቆይታ ይኖረዋል፡፡ የአየር ሰዓት በመስጠት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ቀና ትብብር እንዳደረገላቸው የገለፁት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ፣ ዝግጅቱ መጀመሩ ድርሰትን ፀሐፍትንና መፃሕፍትን ይበልጥ ለሕዝብ በማስተዋወቅ የንባብ ባህልን ያደረጃል ብለዋል፡፡ በአባላት መዋጮ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፣ ወደፊት ከማስታወቂያ ተጠቃሚ በመሆን ራሱን በገቢ እንደሚደጉም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ግጥም በጃዝ 23ኛ ያቀርባል
በወጣት ገጣሚያን እየተሰናዳ የሚቀርበው “ግጥም በጃዝ” 23ኛ ወርሃዊ ዝግጅቱን እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በመጪው ረቡዕ ማምሻውን 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ግሩም ዘነበ፣ በረከት በላይነህ፣ ሜሮን ጌትነት፣ መንግስቱ ዘገየ፣ ዮሐንስ ሐብተማርያም በግጥም፤ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ብርሃነ ደሬሳ “የአፍሪካ የነፃነትና አንድነት ትግል” በሚል ርእስ ዲስኩር እንዲሁም ሀብታሙ ስዩም ወግ ያቀርባሉ፡፡
“ኤልቤት” ተከታታይ የጥበብ ዝግጅት ሊጀምር ነው
ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው “ኤልቤት ሆቴል” ወርሃዊ የኪነጥበብ ዝግጅት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዛሬ ሳምንት በሆቴሉ የሚጀመረው ዝግጅት ግጥም ላይ የሚያተኩር ነው ብሏል - ሆቴሉ፡፡ መድረክ ያላገኙ እና የራሳቸውን ግጥም የሚያቀርቡ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ሥራዎች ላይ እናተኩራለን ያሉት የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ፣ አንጋፋ ገጣሚያንም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ግጥሞች በመክፈቻው እለት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
ዊል ስሚዝ በ“አፍተር አርዝ” አልተሳካለትም
ባለፈው ሳምንት በዓለም ዙርያ በ60 አገራት መታየት የጀመረው የዊል ስሚዝ ፊልም‹አፍተር አርዝ› ገበያው እንዳልተሳካለት ተገለፀ፡፡ የፊልሙን አከፋፋይ ሶኒ ኩባንያ ለተፈጠረው የገበያ መዳከም ከዊል ስሚዝ ብቃት ይልቅ ዘንድሮ እየወጡ ያሉ ፊልሞች በገበያው የሚያሳዩት ከፍተኛ ፉክክር እንደሆነ ገልጿል፡፡‹ አፍተር አርዝ› በመጀመርያ ሳምንቱ ያስገባው 34.6 ሚሊዮን ዶላር በዊል ስሚዝ የሚሰሩ ፊልሞች አማካይ የመጀመርያ ሳምንት ገቢ በእጥፍ ያነሰ ነው፡፡ አምና ለእይታ የበቃው ‹ሜን ኢን ብላክ 3› እንዲሁም በ2008 እኤአ የታየው ‹ሃንኮክ› በመጀመርያ ሳምንታቸው 54.6 ሚሊዮን ዶላር እና 62.6 ሚሊዮን ዶላር እንደቅደምተከተላቸው አስገብተው ነበር፡፡
ከአዲሱ ፊልሙ የገበያ መቀዛቀዝ በኋላ ዊል ስሚዝ ለዲጂታል ስፓይ በሰጠው አስተያየት የደለበ ገቢ በሚያስገኙ ፊልሞች የመስራት ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ከዚሁ የዊል ስሚዝ አስተያየት በኋላ በከፍተኛ በጀት በመሰራት ጠቀም ያለ ገቢ የሚኖራቸው አይሮቦት 2፤ ሃንኮክ 2 እና ባድቦይስ 3 የተባሉት የቀድሞ ፊልሞቹ መሰራት አጠያያቂ ሆኗል፡፡ በ130 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራውን ‹ አፍተር አርዝ› የ44 ዓመቱ ዊል ስሚዝ ከ14 አመት የበኩር ልጁ ጄደን ስሚዝ ጋር የሰራው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ሲሆን በመጀመርያ ሳምንቱ ያስገባው ገቢ ዘንድሮ ከወጡ ፊልሞች ደካማው ተብሏል፡፡
ዊል ስሚዝ በሚተውንባቸው ፊልሞች የቦክስ ኦፊስ የገበያ ደረጃዎችን በመቆጣጠር፤ ለተከታታይ ክፍል ስራዎች ምክንያት በመሆን የሚታወቀውና የ100 ሚሊዮን ዶላር ተዋናይ ይባል ነበር፡፡ ከአፍተር አርዝ በፊት ዊል ስሚዝ የተወነባቸው ያለፉት 10 ፊልሞች በአማካይ በመላው ዓለም እያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር ያስገቡ ነበሩ፡፡ ዊል ስሚዝ በትወና ዘመኑ ከ20 በላይ ፊልሞች ሰርቶ ከ6.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመላው ዓለም በማስገባት የተሳካለት ነበር፡፡
ተዋናዩ በግብር እዳ ፈረንሳዊ ዜግነቱን ሊፍቅ ነው
ጄራርድ ዴፓርዲዮ በፈረንሳይ መንግስት በተጠየቀው የግብር እዳ በመማረር ፓስፖርቱን በመመለስ ዜግነቱን ለመፋቅ እንዳሰበ “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር” አስታወቀ፡፡ ‹ለስ ሚዝረብልስ› በተባለው ፊልም ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፈው ተዋናዩ፤ 1.3 ሚሊዮን ዶላር የግብር እዳ አለበት በሚል የፈረንሳይ መንግስት ክስ መስርቶበታል፡፡ ክሱ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንዴ ድጋፍ ማግኘቱ ተዋናዩን እንዳበሳጨው ታውቋል፡፡ ከትወና ሙያው ባሻገር በፊልም ሰሪነት፤ በነጋዴነት እና በወይን እርሻ ባለቤትነት የሚታወቀው የ64 ዓመቱ ዴፓርዲዮ በሙያ ዘመኑ 17 ፊልሞች ላይ ሰርቷል፡፡
ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የገባው እሰጥ አገባ ያማረረው ተዋናዩ፤ ኑሮውን በቤልጂዬም ለማድረግ ወስኗል ተብሏል፡፡ ከተመሰረተበት ክስ ጋር በተያያዘ በፓሪስ ከተማ ያለው 85 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግዙፍ ቤቱ ሐራጅ ሊወጣበት እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ ጄራርድ ጄፓርዲዬ ከሁለት ሳምንት በፊት የሩሲያ መንግስት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አማካኝነት የራሽያ ዜግነት እንደሰጠው የገለፀው “ዘ ሆሊውድ”፤ በቺቺኒያ ታሪክ ዙርያ በሚሰሩ ሁለት የራሽያ ፊልሞች ላይ እየተወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ተዋናዩ የራሽያ ዜግነቱን ካገኘ በኋላ ከሚያስገባው ገቢ እጅግ ያነሰ ግብር የሚከፍልበት እድል ማግኘቱን እንደገለፀ የዘገበው መፅሄቱ፤ በሞስኮ ከተማ ሬስቶራንት ለመክፈት ማቀዱን ይፋ እንዳደረገም አውስቷል፡፡
የማይክል ጃክሰን ልጅ ራሷን ለማጥፋት ሞከረች
የፖፕ ሙዚቃው ንጉስ የነበረው ማይክል ጃክሰን ብቸኛ ሴት ልጅ ፓሪስ ጃክሰን ከሰሞኑ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ አድርጋ በከፍተኛ የህክምና እርዳታ ህይወቷ መትረፉን ሎስአንጀለስ ታይምስ ዘገበ፡፡ የጃክሰን ቤተሰብ ጠበቃ፤ የ14 ዓመቷ ፓሪስ ህክምና ከወሰደች በኋላ እያገገመች ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋታል ተብሎ ለሦስት ቀናት በሥነአዕምሮ ሆስፒታል እንድትቆይ መደረጉን ገልጿል፡፡ ወጣቷ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ ያደረገችው ሞቶሪን የተባለ የህመም ማስታገሻ መድሃኒት አብዝታ በመውሰድ ሲሆን በአንድ ሮክ ሙዚቃ ኮንሰርት ላይ እንዳትሳተፍ በቤተሰብ መከልከሏ ራሷን የማጥፋት ሙከራ እንድታደርግ ሰበብ ሆኗታል ተብሏል፡፡ ራሷን የማጥፋት ሙከራ ከማድረጓ ከሰዓታት በፊት በትዊተር ማስታወሻዋ ላይ በህይወቷ ዙርያ ተስፋ መቁረጥ መንገሱን የሚጠቁም አሳዛኝ መልዕክቶችን ፅፋ ነበር፡፡ የ54 ዓመቷ እናቷ ዴቢ ሮው፤ ፓሪስ ራሷን ለማጥፋት ስትሞክር የመጀመርያዋ አለመሆኑን ለ“ኢንተርቴይመንት ቱናይት” ሲናገሩ፤ ባንድ ወቅት የእጇን ደምስሮች በመተልተል ለጥቂት ከሞት ተርፋለች ብለዋል፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ማይክል ጃክሰን ከመሞቱ በፊት የመጨረሻዎቹን ትእይንቶች በአጠገቡ ሆና ያሳለፈችው ፓሪስ፤ አባቷን ካጣች በኋላ በከፍተኛ ሃዘን እና የመንፈስ ጭንቀት ስትረበሽ መቆየቷን ቤተሰቧ ይናገራሉ፡፡ ፓሪስ የማይክል ጃክሰን ብቸኛዋ ሴት ልጅ ስትሆን ሁለት ወንድሞች እንዳሏት ይታወቃል፡፡
“በእጅ የሚሮጠው ወጣት” አስገራሚ ታሪክ!
ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ፤ ግን ተሳካልኝ
ስምህ ትርጉም ያለው ይመስላል--- ስወለድ አፈጣጠሬ የሚያስደንቅ ስለነበረ ፈቃዱ ዘገዬ አሉኝ፡፡ “እሱ እንደፈቀደ፣ እንደፈጠረው የሚያደርገውን ያድርገው” ለማለት ይመስለኛል፡፡ ታምሩ የሚለው ግን የቆሎ ት/ቤት እያለሁ የወጣልኝ ስም ነው፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ትርጉም አለው፡፡ አፈጣጠሬ የሚያስደንቅ ስትል--- ሁለቱም እግሮቼ ስወለድ ወደ ኋላ ተቆልምመው ነው የተወለድኩት፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ ማለት ነው። የት ነው የተወለድከው--- ከላሊበላ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች የገጠር ሰፈር (ምዢ ማርያም በምትባል ቦታ) ነው። እናቴ፤ አያቴ ቤት በቤት ሠራተኝነት ታገለግል ነበር። እኔ የተረገዝኩት አባቴ ከእናቴ ጋር በነበረው የምስጢር ግንኙነት ነው፡፡ አባቴ ሊዳር ሁለት ወር ሲቀረው እኔ ተወለድኩ።
ስትወለድ በቤት ውስጥ የነበረው ስሜት እንዴት ነበር፤ ካደግህ በኋላ ስትሰማ--- ለእናቴም ለእኔም መጥፎ እንደነበር ዛሬ ዛሬ እሰማለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ በመወለዴ የአባቴ ቤተሰቦች ‹‹ይሄ ልጅ ከእኛ ዘር አይደለም፤ ዘር አሰዳቢ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እናቴ መረራትና ጥላኝ ጠፋች፡፡ ለ3 ወር ብቻ ጡት አጥብታኝና ከተማ ገባች፡፡ ሴት አያቴ ደረቅ ጡቷን ታጠባኝ ነበር። እናቴ ካደግሁ በኋላ አልፎ አልፎ ቤተሰብ ለመጠየቅ ትመጣ ነበር፡፡ እኔን ያሳደገኝ አያቴ ነው። እስከ አምስት አመቴ ድረስ ከቤት መውጣት አልችልም ነበር፡፡ አፈና ተደርጐብኝ ሳይሆን በቃ መራመድ አልችልም፡፡ እንደ እባብ ነበር የምሳበው፤ በእጄ እየተራመድኩ፣ እጄን እንደ እግር እየተጠቀምኩ ማለት ነው፡፡ ሰው ስለሚያገለኝ ብቻዬን አወራለሁ፤ ብቻዬን እጫወታለሁ፡፡
አያቴ ቄስ ትምህርት ቤት እንድማር ይፈልግ ነበር…ያኔ በየደብሩ ቄስ ትምህርት ቤት አለ፡፡ እኔ ግን ፍላጐቴ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በእጄ እየተሳብኩ …በሩጫም እንኳን የሚቀድመኝ አልነበረም፡፡ አያቴ የትምህርት ፍላጐት እንደሌለኝ ሲረዳ ከብት ጠባቂ አደረገኝ፡፡ እንዴት? እረኝነት አልከበደህም…ከአካል ጉዳተኝነትህ አንፃር ማለቴ ነው--- አያቴ በአካባቢው አሉ ከሚባሉ ሃብታሞች አንዱ ነበር፡፡ እንደ እግር እንድጠቀምበት አንዲት ነጭ ፈረስ ሰጠኝ፡፡ ከፈረሷ ጋር የሰው ያህል የሚያግባባን ንግግርና የምልክት ቋንቋ ነበረን። እረኝነት እንደ እኔ የተዋጣለት ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ጠዋት ፈረሷ ላይ ጉብ እልና ከብቶቹን ከበረታቸው አውጥቼ መስክ እወጣለሁ። ማምሻውን ወደ ቤት እመልሳቸዋለሁ፡፡ ፈረሷን ጠዋት የተጫንኳት ማታ ነበር የምወርደው፡፡ ከእኔ ጋር በጣም ተላምዳ ነበር። ባይንቀሳቀስም ጠንካራ ነበር፡፡ ከብቶች የሰው እርሻ እየገቡ አትቸገርም? የምጠብቀው ፍየሎች፣ ላሞች፣ አህዮች… ነበር። የዘር ወቅት ሲሆን ከሰው ማሳ ይገቡብኝ ነበር። ፈረሷ እንደፈለግሁት ላትሆንልኝ ትችላለች።
አንዴ ከብቶች የሰው ማሳ ገብተው እጭድ አድርገው በሉና ለአያቴ ክስ መጣበት…አይኔ እያየ እኮ ነው ማሳውን የበሉት…ግን ፈረሷን እንዴት አድርጌ ይዤያት ልግባ… ታጥሯል፡፡ ብቻዬን ያለ ረዳት ከመስኩ መሃል ስጯጯህ አመሸሁ፡፡ ቤት ስገባ ተገረፍኩ። አምስት ዓመት ሙሉ በእረኝነት ሰርቻለሁ፤ ፈረስ ላይ ቁጭ ብዬ፡፡ ከዚያ በኋላስ-- እግሬን ተነጠቅሁ - ፈረሴን፡፡ ከፈረሷ ጋር ብዙ ነገር አሳልፌያለሁ፡፡ አብረን ወድቀን ተነስተናል፡፡ ከሞት ሁሉ የዳንኩበት ሁኔታ አለ፡፡ ይዛኝ እየሄደች ድንገት ከወደቅሁ ዞር ብላ አይታኝ ትመለሳለች፡፡ ዛሬ ሳስባት ልክ የሰው ያህል …የእናት የአባት ፍቅር የምትሰጠኝ ፈረሴ ነበረች…እሷን ሳጣ አምርሬ ነበር ያለቀስኩት፡፡ አያቴ ግን ራቅ ወደ አለ ደብር ወሰደኝ። ለምንድነው ደብር የተወሰድከው--- ወለም ዘለም ሳልል እዛው ቁጭ ብዬ የቤተክርስቲያን ትምህርት እንድማር ነበር፡፡ ግን ለስድስት ወር እንደተማርኩ ‹‹ጐርሚጥ›› የሚባል በሽታ ያዘኝ፡፡ በሽታው አጥንት ይቦረቡራል…ትል ይፈጥራል፣ በጣም ሽታ አለው…ሰው መጠጋት አይቻልም፡፡ ቤተሰቦቼም ዞር ብለው ስላላዩኝና ህመሜም ስለበረታ ክሊኒክ ሄጄ መታከም ነበረብኝ። እየተጐተትኩ ወደ ክሊኒክ ሌላ የቄስ ተማሪ ነበር፤ አካል ጉዳተኛ ነው፡፡
እሱ ግን ማንከስ ብቻ ነው። ከእርሱ ጋር ተያይዘን እኔ እየተጐተትኩኝ ወደ ከተማ ሄድን፡፡ መንገዱ ለጤነኛ ሰው አራት ሰዓት ይፈጅበታል፡፡ እኔ ግን እየተጐተትኩኝ ስለሆነ ሁለት ቀን ፈጀብን፡፡ በህይወቴ አስከፊ ከምላቸውና ከማልረሳቸው ቀናቶች አንዱ ነበር…እንደ ኤሊ ነበር የምጐተተው፡፡ የሚያሳድረን ሁሉ አጥተን ነበር፡፡ ሲያዩኝ ይዘገንናቸዋል፤ ቁስሉም ስለሚሸት የሚጠጋኝም አልነበረም፡፡ መልካም ሰው ገጠመንና አሳደሩን፡፡ “አስከተማ” የተባለ ቦታ ነበር የምንሄደው፡፡ እዚያ ጤና ጣቢያ እንዳለ ሰምተን ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ሲያዩኝ ግን ‹‹እዚህ ልናክምህ አንችልም፤ መቆረጥ ስላለብህ ወደ ሌላ ሆስፒታል ሂድ” አሉኝ፡፡ በዛ ጊዜ ከህመሜ የተነሳ..ተቆረጠ አልተቆረጠ አይገደኝም ነበር፡፡ በጣም እየታመምኩ ስለነበር ባለፍንበት ጫካ ሁሉ እጽዋቱን፣ ሳሩን ቅጠሉን እየሸመጠጥኩና በእጄ እየጨመቅሁ ቁስሌ ላይ አፈስስ ነበር፡፡ ያገኘሁትን ቅጥላ ቅጠል እኮ ነው… ያብሰውም፣ ያድነውም በቃ ዝም ብዬ….. ብታምኝም ባታምኝም ግን ቁስሉ ዳነ፡፡ የሚፀጽተኝ የትኛው እጽዋት እንዳዳነልኝ አለማወቄ ነው፡፡ ግን ይቆረጥ የተባለው እግሬ ዳነ። (እግሩን ገልጦ አሳየኝ፡፡ ቁስሉ ጥሎት የሄደው ጠባሳ ይታያል) ከዳንክ በኋላ ወደ ደብሩ ተመለስክ? ወደ አያቴ ቤት ነው የተመለስኩት፡፡ ሲያየኝ “ወይኔ ልጄ በድየሃለሁ” ብሎ ተፀፀተ፡፡ እናትና አባትህስ? አይተውኝ አያውቁም፡፡
ብቻዬን ነኝ፤ ማን ይፈልገኛል፡፡ አንድ “ባለእጅ” ነበር፡፡ እኛ አካባቢ “ቀጥቃጭ” ነው የሚባለው፡፡ ማታ ማታ ወደ ጅብነት ይቀየራል ይሉታል፡፡ ይሄ ሰው “ወደ ሰቆጣ ይዤህ ልሂድ” … “እዛ ትለወጣለህ፣ ትምህርትም ትማራለህ… ከአሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አናይም” ብሎ ጉዟችንን ጀመርን… ጉዞው እንዴት ነበር? የሰሜን መሬት ታውቂው እንደሆነ ወጣ ገባ ነው፤ በጣም ጠንካራ፤ ሻርክ ነው፡፡ እጄን አየሽው እሾህ ወጋግቶኝ… እጄ እንደ እግር ያገለገለች ስለነበረ እንዴት ጠንካራ እንደሆነ አልነግርሽም። አጥቢያ ላይ ዶሮ ሊጮህ ሲል ተነስተን ወደ ሰቆጣ ጉዞ ጀመርን፡፡ በእጄ ስለሆነ የምሄደው ይደክመኝና እቆማለሁ፡፡ ይሸከመኛል፡፡ ከዛ “ጉምራቅ” የተባለ ቦታ አደርን፡፡ በጣም ቀዝቃዛ ነው አገሩ፡፡ መኪና በህይወቴ አይቼ አላውቅም ተሳፍረን ስንሄድ መንገዱ ዚግዛግ ነው፤ አዋራው ይጨሳል…‹‹እመለሳለሁ ወደ አገሬ… አልፈልግም›› ብዬ አለቀስኩ…መኪናው የሚባላ ነገር ነበር የመሰለኝ፡፡ “ኧረ እባክህ ሰው ነው የሚነዳው” ቢሉኝ አሻፈረኝ አልኩ፡፡ ዕድሜህ ስንት ይሆናል ያን ጊዜ? አሥራ አንድ ዓመት ቢሆነኝ ነው፡፡ እንደምንም አሳምነውኝ ከተማ ገባን…ማታ ደግሞ ፓውዛውን መብራት ሳይ ፍርሃት ለቀቀብኝ…ጅብ እና ሌላ አውሬ እኮ አልፈራም፡፡ ይዞኝ የሄደውን ልጅ በጣም ፈራሁት፤ በረንዳ ነው ያደርነው፡፡
‹‹ባለ እጅ ነው፣ ቡዳ ስለሆነ ሌሊት ሌሊት ወደ ጅብነት ይቀየራሉ›› ስለሚባል ተጨነቅሁ፡፡ ሌሊት ከአሁን አሁን ጅብ ሆኖ ተቀይሮ በላኝ… በሚል ስጋት፡፡ ሌላ ታሪክ ለማውራት የማወራ አስመስዬ ስለ ቡዳ ማውራት ስጀምር ‹‹እናንተ እኛን ሰው ይበላሉ ትላላችሁ›› ብሎ አስደነገጠኝ፡፡ ባየው ባየው ግን አልነካኝም፡፡ ሰቆጣ ገባችሁ…ከዛስ? በጠዋት ገስግሰን ሰቆጣ መድሃኒያለም ደረስን። ለቄስ ት/ቤት ፈትነው አስገቡን፡፡ በየመንደሩ እየዞርን ‹‹በእንተ ስለማርያም›› እንላለን፡፡ ሁሉም ከንፈሩን እየመጠጠ ሳንቲም ይሰጠኛል፡፡ ‹‹ለምንድነው ሰው ሳንቲም የሚሰጠኝ›› እል ነበር፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ አልመጣም? አንቺ ደግሞ እኔንማ ማንም አይፈልገኝም። የጓደኞዬ ቤተሰቦች ግን መጥተው አዩት፡፡ ወደ አገሩ ሲሄድ…ሰልባጅ አለባብሼው ዝንጥ አድርጌ ላኩት፡፡ እኔም ሳንቲም አገኝ ስለነበረ፣ ዘንጬ … “ማንነቴን ማሳየት አለብኝ” አልኩና… ወደ ሃሙሲት ገበያ አመራሁ፡፡ እዛ ገበያ ውስጥ አባቴን አገኘሁት፤ ለሸመታ ወጥቶ ነው፡፡ አህያ ይዞ መጥቶ ስለነበር በአህያ ተጭኜ ወደ አያቴ አገር ሄድኩኝ፡፡ የተወሰነ ገንዘብ ይዤ ስለነበር፣ አያቴንና አባቴን ጠላ ጋብዤ፣ ለአያቴ ገንዘብ ሰጥቼ ተመለስኩ፡፡ በመሃል ብዙ ውጣውረድ ደረሰብኝ፡፡ ረሃብ ችግር ብዙ ነገር።
መሄድ የለመደ ልብ ሆነና…ስለ ላሊበላ እሰማ ስለነበር ለጉዞ ተነሳሁ፡፡ በወቅቱ የነበረው ሁኔታም ሰርቼ ስለማልበላ በቤተሰቦቼ የምሬትና የንቀት ፊት ስላየሁ …ስለሰየቹን ሌት ተቀን በእንኩትት(በእጄ እየተንፏቀቅኩ) አንድ ቀን ከተጓዝኩ በኋላ “መሪ” የሚባል ወንዝ ደረስኩ…አካባቢው በሽፍታ የታወቀ ነበር፡፡ አንድ የታወቀ ሽፍታ ከርቀት ሲያየኝ በሆዱ እየተሳበ የሚሄድ አውሬ መስዬው አነጣጥሮ ሊገለኝ ነበር፡፡ ተጠግቶ ሲያየኝ ጐስቆልቆል ብያለሁ፡፡ ‹‹ሃጢያት ውስጥ አስገብተኸኝ ነበር›› አለና አንስቶ ምግብ አበላኝና ተሸክሞ የተወሰነ ስፍራ ድረስ ከሸኘኝ በኋላ ‹‹አይዞህ በርታ›› ብሎ ተመለሰ፡፡ ምን ብትሰማ ነው ወደ ላሊበላ ለመሄድ የተነሳሳኸው? እኔ በላሊበላ አድርጌ በጌምድር ለመድረስ ነው ያሰብኩት፡፡ ዋናው ፍላጐቴ የማጂክ ትምህርት ለመማር ነበር፣ ‹‹መተት›› የሚባለውን ነገር፡፡ ለምን መሰለሽ ይህን ጥበብ ለመማር የተነሳሳሁት? ሰዎች ይበድሉኝ ነበር፡፡ ‹‹ቆማጣ፣ ጐልዳማ፣ አንካሳ›› እያሉ ይሰድቡኛል፡፡ የበደሉኝን በመተት ማጥፋት እፈልግ ነበር፡፡ እንደውም ሰዎች ሰብሰብ ብለው ቁጭ ካሉበት ሄጄ መደባደብ ነበር ስራዬ፡፡ በአፌ ዱላ ይዤ እጋጠማቸዋለሁ - ተንኮለኛ ነበርኩ፡፡ ብቻዬን ነው ቦታ እየጠየቅሁኝ የምጓዘው፡፡ “ብልባለ” የተባለ ቦታ ደረስኩ፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን ከብልባለ ላሊበላ መንገድ ይሰሩ ነበር፡፡ እነሱ ጭነው ላሊበላ ወሰዱኝ…እዚያ ግን የሚያሳድረኝ አጣሁ፤ ተንከራተትኩ፡፡ በመጨረሻ አንዲት ልጅ አሳዝኛት አስጠጋችኝ… እኔ እንግዲህ ሊቃውንት ምሁራን ወደአሉበት አካባቢ ሄጄ ጥበብ፣ ዕውቀት መቅሰም ነው ፍላጐቴ፡፡
ግን ሳላስበው ሁለት ዓመት ላሊበላ ተቀመጥኩ፡፡ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ዜማ፣ ቅኔ ተምሬ ጨረስኩ፡፡ የላሊበላ ህዝብ ደግ ህዝብ ነው። በኋላ ላይ ውስልትና መጣች፡፡ ምን ወሰለትክ? በትምህርቴ ግዴለሽነት አመጣሁ፡፡ የድብርትና ተንኮል ለመማር የመሄድ አሳቤን፣ አላማዬን አስረሳኝ የላሊበላ ቆይታዬ፡፡ በእጄ እሮጥ ነበር። ላሊበላ ላይ የምታወቀው “በእጁ የሚሮጠው›› እየተባለ ነው፡፡ ብዙ ህዝብ እያወቀኝ መጣ፡፡ አንድ ልጅ ግን መከረኝ ‹‹ፈረንጅ ስታይ በእጅህ እየሮጥክ ሂድ..›› ብሎ፡፡ ፈረንጅ ባየሁ ቁጥር በእጅ መሮጥ ሆነ፤ ፈረንጆቹ በጣም ይደነቁ ነበር፡፡ ገንዘብ በገንዘብ ሆንኩኝ… ጠላ፣ ጠጅ፣ አረቄ፣ መጠጣት ጀመርኩ፡፡ የቄስ ትምህርቱን ትውት አደረግሁት። ሊስትሮ ገዛሁና ጫማ መጥረግ ጀመርኩ፡፡ ሊስትሮዬን በትከሻዬ አዝዬ እየተንኳተትኩ መዞር ነው፡፡ ፈረንጆችን ሳይ ደግሞ ‹‹ትርዒት ላሳያችሁ›› እያልኩ በእጄ እሮጣለሁ… እንግሊዝኛ እንዴት ነው… ዘመናዊ ትምህርት አልተማርክም… አልተማርኩም፡፡ ግን ልጆች “እንደዚህ ብለህ ተናገር ይሉኝ ነበር፡፡ ከዚያ ላሊበላ የማሳየውን ትርዒትና የሊስትሮነት ስራ ትቼ ወልድያ ሄድኩ፡፡ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ሰቆጣ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ… በሊስትሮነት ሥራ አገሩን አዳረስኩት፡፡ ከዚያ ተመልሼ ወደላሊላ ሄድኩ፡፡ እዚያ የገጠመኝ ነገር ነው ለዛሬ ማንነቴ ያበቃኝ፡፡ ሁለት አሜሪካኖችን አገኘሁ፤ ባልና ሚስት፡፡ ባልየው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ስፔሻሊስት ነው፡፡
ዶ/ር ሞራስ ይባላል፡፡ ከአሜሪካ ለአጭር ጊዜ የበጐ አድራጐት ስራ የመጡ ናቸው፡፡ ላሊበላ እንዴት አገኘኻቸው? ለጉብኝት መጥተው ነው፡፡ ምርር፣ ድብር ትክዝ ብዬ ተቀምጬ አገኙኝ…እግሬን አገላብጠው ካዩት በኋላ “ይሄ ልጅ ቢታከም መዳን ይችላል…ወጪውን ሸፍኖ አዲስ አበባ ድረስ የሚያመጣው ቢገኝ” ሲሉ ለአንድ የቱርጋይድ ነገሩት፡፡ ከዚያ አንድ ብር ሰጡኝና ሄዱ፡፡ እርቦኝ ስለነበር…አምባሻ ገዝቼ በላሁበት፡፡ እድሜ ዘላለሜን እግሬን ታክሜ ይድናል የሚል ህልም ኖሮኝ አያውቅም፡፡ በጣም አሰብኩ፤ “እኔ ቆሜ ልሄድ ….. በፍፁም” አልኩ ለራሴ፡፡ የላሊበላ ህዝብ ሁሉ ያውቀኝ ስለነበር፣ ነገሩ በከተማው ተወራ፡፡ አዲስ አበባን ማለም ጀመርኩ። ገንዘብ ተዋጣ … የአውሮፕላን ትኬት ያኔ መቶ ስልሳ ብር ነበር፡፡ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፈረንጆቹ ሲያዩኝ አጨበጨቡ፡፡ ተደሰቱ። ቅዳሜ ገብቼ ማክሰኞ ኦፕሬሽኑ ተጀመረ። ኦፕሬሽኑ በጣም ከባድ ነበር፡፡ አሜሪካኖቹ ካከሙኝ በኋላ ሃላፊነቱን ዶ/ር ተመስገን ለሚባል የአጥንት ስፔሻሊስት ሰጥተው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ በአጠቃላይ አራት ጊዜ ከባድ ኦፕራሲዮን አደረግሁ። ምን ያህል ጊዜ ፈጀ? አራት ወር፤ ግን በሆስፒታሉ በትክክል የተኛሁት አንድ ወር ብቻ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ… እግርሽ፣ እጅሽ፣ አይንሽ፣ ቢታመም ምንም አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር የአእምሮ ጨዋታ ነው፡፡ ቆሜ ለመሄድ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ገና እግሬ ተሰርቶ ሳያልቅ ለመሄድ እሞክር ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በእግርህ መጓዝ ስትጀምር የተሰማህን ስሜት ታስታውሳለህ? መጀመሪያ በዊልቸር ነበር፡፡ ከዚያ ጐንና ጐን መደገፊያ ባለው ጐማ በሚመስል ነገር መንሸራተት ጀመርኩ፡፡ ቆሜ ስሄድ ዶክተሬ አላመነም፡፡ ቆሜ እየተራመድኩ የሄድኩት እሱ ቢሮ ነበር፡፡ ሲያየኝ ጭንቅላቱን ያዘ…ደስ አለውና አበረታታኝ። በጣም ይወደኝ ነበር፡፡
በኋላ ላይ ብረት ያለው ጫማ ተሰራልኝ፡፡ እሱንም በራሴ ጊዜ አውጥቼ ጥዬ ኖርማል ጫማ አደረግሁ፡፡ የብረት ጫማውን እስከአሁን ማድረግ ነበረብኝ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ግን ቁስለት ነገር ይሰማኝ አጥንቴና አጥንቴ የተያያዘበት ብረት መውጣት ነበረበት፡፡ ያ ማመርቀዝ ጀመረ፡፡ አስራ ሶስት ዓመት አብሮኝ ነበር፡፡ ይደማል ይመግላል፤ እኔ ግን አያስጨንቀኝም ነበር፡፡ ብረቱን ያወጣሁት የዛሬ ሁለት ዓመት ነው፡፡ አንደኛው እግሬ በጠቅላላ ሰላሳ አምስት ሴንቲ ሜትር ብረት አለው፡፡ እስከ አሁን ወደ ዘጠኝ ጊዜ ኦፕራሲዮን አድርጌያለሁ፡፡ እነዛ አሜሪካኖች አሁን ያለህበትን ያውቃሉ? ዶ/ር ተመስገንስ? ዶ/ር ተመስገን ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ አሜሪካ ሄደ፡፡ ለአሜሪካኖቹ “የቀለም ትምህርት መጀመር እፈልጋለሁ” ብዬ መልዕክት ልኬላቸው ነበር፡፡ በ16 ዓመቴ አንደኛ ክፍል ገባሁ፡፡ ሰዎቹ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለች አንዲት ፈረንጅ ጋር አገናኙኝ፡፡ እሷ ትረዳኝ ጀመር፡፡ 5ኛ ክፍል ሆኜ ቆሜ እንድሄድ የረዱኝ ፈረንጆች እኔን ለማየት ከአሜሪካ መጡ። ደስ አላቸው፡፡ አዝናኑኝ፡፡ ተመልሰው ሲሄዱ በየወሩ ብዙ ብር ይቆርጡልኝ ጀመር፡፡ ቤት ተከራይቼ ራሴን ማስተዳደር ጀመርኩ፡፡ ከዚያማ መጨፈር፣ ፓርቲ መውጣት ሽርሽር ሆነ፡፡ የከተማ ልጅ ሆንክ ማለት ነው… ታዲያስ! በአዲስ አበባ ያሉ ፓርቲ ቤቶችን፣ ዳንስ ቤቶችን ከጓደኞቼ ጋር ተንሸራሸርኩባቸው። ስፖርት እሰራለሁ፤ ክብደት አነሳ ነበር፡፡ በእጄ ደረጃ መውረድ ጂምናስቲክ ጀመርኩ፡፡ አንዲት ሙስሊም ወድጄ በፍቅር ልብሴን ሁሉ አስጣለችኝ።
የተዋወቅነው እንግሊዝኛ ቋንቋ በምማርበት ት/ቤት ውስጥ ነበር…እብድ አልኩላት፡፡ እሷ ደግሞ ካናዳ ሌላ ጓደኛ ነበራት፤ ጥላኝ ሄደች፡፡ አስረኛ ክፍል እያለሁ ማለት ነው፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል አንደኛ እወጣ የነበርኩት ልጅ፣ በእሷ ፍቅር አቅሌን ስቼ ከስልሳ አንድ ተማሪ ስልሳኛ ወጣሁ፡፡ ጥላኝ ስትሄድ እንደማበድ አደረገኝ፤ ራሴን ለማጥፋት ተነሳሳሁ፡፡ የፍልስፍና መጽሐፍት ማንበብ ጀመርኩ በቃአጓጉል ሆንኩ፡፡ ፀጉሬን ሁሉ አሳድጌ ነበር፡፡ በኋላ ራሴን በራሴ መክሬ አገገምኩ፡፡ እንጦጦ አጠቃላይ ቴክኒክና ሞያ ገብቼ፣ በእልህ አንደኛ ወጣሁ፡፡ በጥሩ ውጤት ዲፕሎማዬን ይዤ ወጣሁና የራሴን ቢዝነስ ለመጀመር አሰብኩ። ስድስት ኪሎ አካባቢ ኢንተርኔት ቤት ከፈትኩ፡፡ ገንዘብ አጠራቅም ነበር። አይቲዬን እያጧጧፍኩ የሜንቴናንስ ስልጠና ወስጄ ጨረስኩ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ሱዳን ይኖር ነበር፡፡ እየደወለ ‹‹ወደ አውሮፓ ልሻገር ነው ለምን አትመጣም?›› እያለ አነሳሳኝ፡፡ ሁለት ሰራተኛ ቀጥሬ እያሰራሁ ነበር፡፡ ከሞቀ የንግድ ስራዬ ተፈናቅዬ ያለኝን ሻሽጬ ሱዳን ገባሁ፡፡ በእግር ነው በአውሮፕላን? መጀመሪያ በህጋዊ መንገድ ኤምባሲ ስንጠይቅ አልተቀበሉንም፡፡ በህገወጥ መንገድ በመተማ አድርገን መሄድ አለብን ብለን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመኪና ጐንደር ደረስን፡፡ ጐንደር ላይ ተጨፈረ። አስረሽ ምችው ነበር፡፡ መተማም እንደዚሁ ጉዞ በእግር ተጀመረ፡፡ ከእኛ መካከል አንደኛው አጭበርባሪ ነበር፡፡
አረብኛ ቋንቋ ይችላል፡፡ እሱ መውጣት አይፈልግም፡፡ ሱዳን ጠረፍ ከደረስን በኋላ፣ የሱዳን ገበሬዎችን “ድንበር ጠባቂዎች በየት በኩል ናቸው” እያለ እነሱ ባሉበት ቦታ ወስዶ አስያዘን፡፡ ገንዘባችንንና የያዝነውን ሁሉ ቀምተውን ተመለሰን፡፡ አሁንም በእግራችሁ? ያውም እግሬ እየደማ፡፡ ግን ህልም አለኝ። ራሴን፤ ራዕዬን ስለማውቅ አውሮፓ በእግሬ ተጉዤ ገብቼ፣ ረጅም ፎቅ በክራንች ወጥቼ ወርጄ፣ ውጤት ማስመዝገብ ….የሆነ ሪኮርድ መስበር፣ ያለኝን ታለንት ማውጣት እፈልግ ነበር፡፡ ሱዳኖች ለኢትዮጵያ ወታደር አሳልፈው ሰጡን፡፡ ጐንደር መለሱን፡፡ እንደገና በሁመራ በኩል ሞከርን፡፡ ሁለት ሶስት ቦታ ተያዝን፡፡ አልሆነልንም፡፡ አስር ቀን ታስረን ለቀቁን። “ማይካድ ራት” የምትባል ከተማ ሄድን፡፡ ገዳሪፍ ገባን፡፡ ገዳሪፍ የተወሰነ ተሰባስበን ቀን ተጠራቅመን፤ ሱዳን ሄድን፡፡ ሱዳን ሁለት ወር ቆየሁ፡፡ ምን እየሰራህ? በሊቢያ አድርጐ ለመሻገር ወቅት ስላለው፣ ሱዳን ውስጥ ቆይተን በእግራችን ለመጓዝን ተነሳን። ግን ሊቢያ ድንበር ላይ ተያዝን፡፡ እየቀጠቀጡ እስር ቤት አስገቡን፤ ከዚያም በካርጐ መኪና አጭቀው ለሱዳን አስከረቡን፡፡ እዚያ ታሰርን፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊሴ ፓሴ ሰጠኝና ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ።
ግን ባዶ እጅህን ነው… ሱዳንም ሄድኩ ሊቢያ ብቻ ኢንተርኔት በማገኝበት ቦታ ሁሉ ከሚረዱኝ ሰዎች ጋር ግንኙነቴን አላቋረጥኩም፡፡ ኢትዮጵያ ስደርስ ወደ 15ሺ ብር አካባቢ ላኩልኝ፡፡ ላይን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ኮሌጅ በቱር ጋይድነት ተመዘገብኩና ለ2 ዓመት ተምሬ አጠናቀቅሁ፡፡ ክረምት ላይ ሰርከስ ጀመርኩ፡፡ ከማን ጋር ምን አላማ ሰንቀህ? ብቻዬን፡፡ አንድ ጓደኛዬ ነበር፤ ያየኛል፤ አብሮኝም ይሰራል፡፡ የማልሞክረው ነገር የለም። ኦፕራሲዮን አድርጌ በክራንች ነበር የምሄደው፡፡ ስለዚህ ለምን ተዘቅዝቄ በክራንች በእጄ አልሄድም ብዬ ተነሳሁ፡፡ በኢንተርኔት ላይ እንደዚህ ዓይነት ሪከርድ ያስመዘገበ የለም፡፡ በዚህ መንገድ ለምን ራሴን አላወጣም ብዬ ጀመርኩ፡፡ ወደቅሁ፣ ተነሳሁ፣ ተጋጋጥኩ፡፡ አሁን ከመቶ ሜትር በላይ እሄዳለሁ፡፡ የሚፈለገው በአንድ ደቂቃ ውስጥ ምን ያህል ሜትር ይኬዳል የሚለው ነገር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንደዚህ ዓይነት ጅምናስቲክ የሚሰራ አለ? የለም፡፡ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ቆየሁና ለምን በክራንች ላይ ሆኜ ደረጃ አልወርድም አልኩና ልምምድ ጀመርኩ፡፡
በተደጋጋሚ ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ ግን አደረግሁት፡፡ ሪኮርዱ ተሳካልህ ወይስ? በአንድ ደቂቃ ከ76 ሜትር በላይ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ ሶስት ድርጅቶች እውቅና ሰጥተውኛል፡፡ “ወርልድ ሪኮርድ አካዳሚ”፣ “ወርልድ ሪኮርድ ሴተር”፣ እና “ወርልድ ኦቶራይዝ›› ናቸው፡፡ የእነዚህ ሪከርዶች ባለቤት ነኝ፡፡ ሁለቱ ሪከርዶች ያገኘሁት በክራንች በመሄድ ነው፡፡ የራሴን ስም አስጠርቼ አገሬን ማስጠራት ነበር የምፈልገው፡፡ ይሄው ተሳካልኝ፡፡ ጊነስ ወርልድ ሪከርድ በዚህ ወር እውቅና ይሰጠኛል፡፡ ትርዒትህን ለማቅረብ ወደ ውጭ አገራት ሄደሃል? አሁን የምሰራበት “ሰርከስ ደብረብርሃን” ይባላል፡፡ አምስት ወር ይሆነኛል ከገባሁ፡፡ ነሐሴ ላይ ትርኢት ለማሳየት ወደ ስዊድን እንሄዳለን፡፡ በህይወቴ የተማርኩት ነገር ቢኖር ማንም ሰው ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ነው፡፡ በተለይ አካል ጉዳተኞች፡፡ ምስጢሩ አካል ላይ ሳይሆን አእምሮ ላይ ነው፡፡ እዚህ ለመድረስ ያበቃኝ “እችላለሁ” ብዬ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን መድፈሬ ነው፡፡ ብዙ እቅድ አለኝ፡፡ ነገን ነው የማስበው፡፡
አዞው ወደ ውሃ ሲስብ፤ ጉማሬው ወደ ሣሩ ይስባል
የምድር አውሬ ሁሉ መነገጃና መሰባሰቢያ አንድ ገበያ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አውሬ ሁሉ እገበያ ሲውል፤ አያ ጅቦ ቀርቶ ኖሯል፡፡ ማታ ሁሉም ከገበያ ሲመለስ ከጎሬው ብቅ ይልና መንገድ ዳር ይቀመጣል፡፡ ዝንጀሮ ስትመለስ ያገኛትና ገበያው እንዴት እንደዋለ ይጠይቃታል፡፡ “እቸኩላለሁ ጦጢት ከኋላ አለችልህ እሷን ጠይቃት” ብላው ሄደች፡፡ ጦጢት ስትመለስ ጠብቆ “ገበያው እንዴት ዋለ?” አላት፡፡ “መሽቶብኛል፡፡ ገና ብዙ ሥራ አለብኝ” ብላው አለፈች፡፡ ቀጥላ ሚዳቋ መጣች፡፡ ያንኑ ጥያቄ ጠየቃት፡፡ “እንኮዬ አህይት እኋላ አለች - እሷን ጠይቅ!! እኔ እነዝንጀሮ ቀድመውኛል፤ ልድረስባቸው” ብላው ሄደች፡፡ አህያ ስትንቀረደድ መጣች፡፡ ገበያው እንዴት እንደዋለ ጠየቃት፡፡ “ቆይ አረፍ ብዬ ላውራልህ” ብላ አጠገቡ ተቀመጠች፡፡
“ይሄ ተገዛ! ያ ተሸጠ!” ስትለው አመሸች፡፡ አያ ጅቦ ቀጠለና “ለመሆኑ እኔ እምዘለውን መዝለል ትችያለሽ?” አላት፡፡ “አሳምሬ” አለችው፡፡ እሱ የሞት ሞቱን ዘለለ፡፡ እሷ ግን እዘላለሁ ብላ ገደሉ ውስጥ ወደቀች፡፡ አያ ጅቦ ወርዶ ሆዷ ዘንጥሎ መብላት ጀመረ፡፡ እመት ውሻ በዛ ስታልፍ ስጋ ሸቷት መጣች፡፡ “ነይ ውረጂና እየመተርሽ አብይኝ” አላት፡፡ ወርዳ እየመተረች ስታበላው የአህያዋን ልብ አገኘችና እሱ ሳያያት ዋጥ ስልቅጥ አደረገችው፡፡ ቆይቶ “አንቺ ልቧ የታል?” ሲል ጠየቃት፡፡ ውሺትም፤ “ልብ ባይኖራት ነው እንጂ ልብ ቢኖራት መቼ ካንተ ዘንድ መጥታ ትቀመጥ ነበር?!” አለችው፡፡ “ታመጪ እንደሁ አምጪ፤ አለዛ አንቺንም እበላሻለሁ!” አለ፡፡ “አያ ጅቦ፤ ያለ ቂቤ? ያለ ድልህ? ደረቁን ልትበላኝ?” “ቅቤና ድልሁ ከየት ይመጣል?” አለ ጅቦ በመጎምጀት፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት አመጣለሁ” “ሄደሽ የጠፋሽ እንደሆን ማ ብዬ እጠራሻለሁ?” “እንኮዬ -ልብ- አጥቼ” ብለህ ጥራኝ፡፡ “በይ እንግዲያው ሄደሽ አምጪ” ብሎ ላካት፡፡ ቅርት አለች፡፡ ሲቸግረው “ኧረ እንኮዬ ልብ አጥቼ?” ሲል ጮሆ ተጣራ፡፡ ውሻም፤ “ከጌታዬና ከእመቤቴ ቤት ለምን ወጥቼ!” አለችው፡፡ ከዚያም የስድብ መዓት ታወርድበት ጀመር፡፡ ጅቦም፤ “አንቺም እጉድፍ እኔም እጉድፍ፡፡ አገኝሻለሁ ስንተላለፍ” አላት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውነትም ጉድፍ ስትለቃቅም አገኛት፡፡ ዐይኗ ፈጠጠ፡፡ “ዐይንሽ እንዴት እንዲህ አማረልሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡ “በዐሥር የአጋም እሾክ ተነቅሼ!” አለችው፡፡ “እስቲ እኔንም ንቀሺኝ?” ተስማምታ ከጌታዋ አጥር ዓሥር የአጋም እሾህ ሰብራ አምጥታ ዐይኖቹን ቸከቸከችው፡፡ “ኧረ አመመኝ” ሲል፤ “ዝም በል ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው፣ ማማር እንዲያው ይገኝ መሰለህ?” ትለዋለች፡፡ ሁለቱንም ዐይኖቹን አጥፍታ፤ “በል ና ሠንጋ ጥለው የሚሻሙ ጅቦች ጋ ልቀላቅልህ” ብላ፤ ውቂያ ላይ ያሉ ገበሬዎች ማህል ከተተችው፡፡ ወስዳ ጤፍ መውቂያ ሙጫቸውን እየመዘዙ ሊገድሉት ያራውጡት ጀመር፡፡ ውሻ ሆዬ እነሱ ሲሯሯጡ ዳቧቸውን ይዛ ወደቤቷ መጭ አለች!!
* * *
ያሰቡትን ቸል ሳይሉ ከፍፃሜ ማድረስ አስተዋይነት ነው፡፡ ያለኩያ ጓደኛ መያዝ፤ ነገርን ሳያመዛዝኑ ፈጥኖ አምኖ መቀበል ከጥቃት የሚያደርስ ቂልነት ነው፡፡ አታላይ ለጊዜው የመብለጥለጥ ምኞቱን ቢያረካም፣ የፈፀመው ደባ እንደሚደርስበት የዥቡን አወዳደቅ ማስተዋል በቂ ነው! ብልህ በዘዴ ከአደጋ ያመልጣል፡፡ ኃይለኛ የሆነ ጠላት ቢገጥመው እንኳ በጥበብ ለመርታት ይችላል፡፡ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ አንዱ ሲሠራ ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ሲታሰር ሌላው ሲተበተብ፤ የሁኔታዎች መወሳሰብ ይከሰታል፡፡ ከውስብስቡ ሁኔታ ለመውጣት እጅግ አስፈላጊው ነገር ትዕግሥትና ስክነት ነው፡፡ ባላንጣ፤ ሀገር ያልተረጋጋበትን ሰዓት መምረጡ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በብልህነት ማውጠንጠን፣ አርቆ - ማስተዋል፤ ነገሮች ተደራርበው ግራ እንዳይጋቡን ይጠቅመናል፡፡ የሙስና ላይ ዘቻው አንድ ረድፍ ነው፡፡ የቤት ችግር ሠልፍ፣ ለቤት የተመዘገበ ሰው ያገኘው ኮንዶምኒየም በሌላ ተወስዶበት ለአቤቱታ ቤት - ደጁን ማጥለቅለቅ፤ እናቱ የሞተችበትም፤ ወንዝ የወረደችበትም እኩል ማልቀሳቸው፤ መንግሥት ላይ ዕምነት ማሳደር ባንድ ወገን፣ መንግሥት በትክክል ሊቆጣጠረው ባይችልምስ የሚል ፊናንሳዊ ስጋት በሌላ ወገን፤ አፍንጫችን ሥር ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በጦርነት ድንፋታ ንፋስ ከታጀቡ ደግ አይሆንም፡፡
ስለጦርነት ከተነገሩት ድንቅ አነጋገሮች ሁሉ የሚከተለው ይገኝበታል - “ጦርነት ነፃነትህን ስለሚወስድብህ አስፈላጊ የሆነ ምርጫ ላይ ለመዋጋት ወይም ላለመዋጋት ልትወስን ትችላለህ፡፡ አንዴ ጦርነት ከገባህ ግን የምርጫ ኃይልህ አከተመ” (ጊልበርት ሙሬይ) ሁሉም ነገር ጥንቃቄንና ዝግጁነትን ይጠይቃል፡፡ የተረጋጋ ህዝብን ይጠይቃል፡፡ መንገዶች ሁሉ ወደአንድ አቅጣጫ እንዳይሄዱ፤ እመነገጃውና እመገበያያው የሚገቡትን ባለይዞታዎች በጥሞና መያዝ ይገባል፡፡ የህዝብን አመኔታ የሚያጠናክር አዎንታዊ እርምጃ ሀገራዊ ስሜትን ለማድመቅ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ቤትም አገርም አለኝ የሚል ህዝብ እንዲኖረን ያስፈልጋል! “በሰው ልጅ ላይ የወረደ ታላቅ መርገምት ጦርነት ነው፡፡
በሰላም ጊዜ የሚፈፀሙት የጭካኔ ወንጀሎች፤ በሰላም ጊዜ የሚካሄዱት ሚስጥራዊ ሙስናዎች አሊያም የሀገሮች ሃሳብ - የለሽ የገንዘብ ዝርክርክነቶች ሁሉ፤ ጦርነት ከሚያደርስብን ሠይጣናዊ ጥፋት ጋር ሲወዳደሩ እንክልካይ ነገሮች ይሆናሉ” ይለናል፤ ሲድኒ ስሚዝ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ የመንግሥት ጥንቃቄ የተሞላ እርምጃም የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን ሥራዬ ብሎ ማቀናጀት ብልህነት ነው!! ዕውነት ገና ጫማውን እያሰረ፣ ውሸት ዓለምን ዞሮ ይጨርሳል የሚለውን አባባል አንርሳ!! በመላና በጥበብ የመምራት ክህሎትን የሚጠይቅ ወቅት ነው፡፡ “አዞው ወደውሃ ሲስብ፣ ጉማሬው ወደ ሣሩ ይስባል” የሚለው የወላይታ ተረት ጉዳያችንን ያሳስበናል፡፡