Administrator
የግጥም ጥግ
መጣች
መጣች
እቴ መጣች
መጣች
ውዴ መጣች
መቼ ሄዳ ቀረች
መቼ ከእጄ ወጣች
አምቼ ሳልጨርስ
ተመልሳ መጣች!
ሄደች ብዬ ሳማት
ውል እያፈረሰች
እንባ ሆና መጣች
አይኔ ስር ፈሰሰች
ስትሄድ እያየኋት
ከአይኖቼ እየራቀች
የእንባ ጅረት ሆና
አይኔ ስር ፈለቀች!
ወለላ
የእኔ ወለላ
ሄደች ስል
ሆነች የሌላ
መጥታለች
ዙራ በመላ
ዘለላ
የእኔ ዘለላ
የራቀች መስላ
አይኔ ስር
መጣች በመላ
ሰርታብኝ
የእንባ ዘለላ
እኔው ልፈር እንጂ
አንቺ ምን በወጣሽ
ሄደች ብዬ ሳማሽ
ዞረሽ በአይኔ መጣሽ
ሄዳለች እያልኩኝ
በሩቅ ስናፍቅሽ
ዞረሽ በአይኔ መጣሽ
ከቶም ሳልጠብቅሽ
የእንባ ኩሬ ሆነሽ
ቀድቼ እማልዘልቅሽ
ሌት ተቀን ብጨልፍ
ዘለለት ብጠልቅሽ
አይንሽም ጥርስሽም
ሳቅሽም ለዛሽም
እቴ ሁለመናሽ
እያየሁ ሲርቀኝ
ምን ይውጠኝ ብዬ
ሲጠበኝ ሲንቀኝ
የገባሽልኝን
ቃልሽን አክብረሽ
እንባ ሆነሽ መጣሽ
በአይኔ ቦይ አሳብረሽ
ትታኝ ሄደች ብዬ
ከአጠገቤ ርቃ
አምቼ ሳልጨርስ
ክሴን ሳላበቃ
ስትሄድ እያየኋት
ከጐኔ እየራቀች
እምባ ሆና መጥታ
አይኔ ስር ፈለቀች
ጥላኝ ሄደች ስላት
ውድዬ ጨክና
በደም ስሬ በኩል
መጣች ቁስል ሆና
እኔም እንዳይከፋኝ
ሌላም እንዳይከፋኝ
ስውር ቁስል ሆነች
በጣቴ እማላካት
በሩቅ ስፈልጋት
ሳያት አሻግሬ
ፀፀት ሆና መጥታ
ገባች በደም ስሬ
ይሄውና ጥርስሽ
ሁሌ እሚናፍቀኝ
ይሄውና ሳቅሽ
ያየሁት ሲርቀኝ
ይሄው ሁለመናሽ
ቀርቶ እሚያስጨንቀኝ
ከደም ስሬ ገብቶ
እየተናነቀኝ
መጣች ተመልሳ
ትታኝ ሄደች ስላት
የጐን ውጋት ሆና
ዋግምት የማይነቅላት
የኔ ቃል አክባሪ
የኔ መልከመልካም
መጣች ተመልሳ
ሆናኝ ልብ ድካም!
ስለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ከተነገረው
“----አቶ ዮፍታሄ ንጉሴን የማውቃቸው ከቀኝ ጌትነታቸው በኋላ መምህር ከነበሩበት ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት እድገት ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ይባል ወደነበረው ዲሬክተር ሆነው በመጡበት ጊዜ፣ ከሰሩአቸው ትያትሮች አንዱ ላይ የሕፃን አክተር ሆኜ ስተውን ነው፡፡ “ሶረቲዮ”፣ “የኛማ ሙሽራ”፣ “ቦረናና ባሌ በጣልያን ወረራ ጊዜ” በሚሉትና በሌሎችም በአክተርነት ሰርቻለሁ፡፡
ከጣሊያን ወረራ በኋላ ጃንሆይ ሲመለሱ አቶ ዮፍታሄም ተመልሰው የድሮ ተማሪዎችን በመሰብሰብ “አፋጀሽኝ” የተባለውን ትያትር በቤተመንግሥት ለማሳየት ሐምሌ 16 ቀን 1933 ዓ.ም ትያትሩ እንዲታይ ተማሪዎች ሲሰበሰቡ እኔም ካለሁበት ተሰብስቤ “አፋጀሽኝ”ን (ሴት ገፀ ባህርይ) ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
ከዚያ ጊዜ በኋላ አልተለየሁአቸውም፡፡ በኋላም ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት በነበሩበት ጊዜ እኔም በዚያው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የመዝገብና የፐርሶኔል ሹም በነበርኩበት ጊዜ አለቃዬ ስለነበሩ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አልተለያየንም፡፡ የእሳቸውን ታሪክ በመጠኑም ቢሆን እንድገልፅ በመታደሌ እድሌን አመሰግናለሁ፡፡“ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ምን አይነት ፀባይ ነበራቸው፤ ታጋሽ ናቸው፣ ቁጡ…? ትእግስተኛ፣ አዋቂ፣ ሁሉንም በእርጋታ የሚመሩ ነበሩ፡፡ ጠባያቸው ይሄ ነው፡፡ አሁን ስለጠባያቸው ሳይሆን የምናገረው ስለ ስራቸው ነው፡፡ “አፋጀሽኝ”ን ከሰራሁ በኋላ “ዓለም አታላይ” የሚለውን የመድረክ ትያትራቸውን ራሴ ዓለም አታላይ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ከኔ ጋር የሰራው ይድነቃቸው ተሰማ ያራዳ ኮረዳ ሆኖ ሰርቷል፡፡
ዮሐንስ ወዳዘጋጀው ታሪካቸው ልምጣ፡፡ እኔ አቶ ዮፍታሔ ከሞቱ በኋላ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት “አፋጀሽኝ” ትያትር ለማዘጋጃ ቤት አክተሮች እንዳስጠናና እንዳሳይ ታዘዝኩ፡፡
እነ ተስፋዬ ሳህሉን፣ እነ… ሁሉን ላስታውስ አልችልም፡፡ እነሱ እነሱን ሰብስበው ይኼን ትያትር አስጠንቼ አሳይቻለሁ፡፡ እንግዲህ ትያትሩን አስጠንቼ ባሳየሁበት ጊዜ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አሁን ለመጀመርያ ጊዜ አደባባይ የወጣ ታሪካቸውን እኔ ለጉባኤው ገልጬ ነበር፡፡ ያ የገለጥኩት ታሪክ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተፃፈ፤ በጊዜው፡፡ ትያትሩ ተደነቀ፡፡ እንደገና እነሱም እየደጋገሙ አሳይተውታል፡፡
(የ95 ዓመቱ አዛውንት አቶ በለጠ ግርማ በባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ የተዘጋጀውና በወንድማቸው በዶ/ር ዮናስ አድማሱ የአርትኦት ሥራው የተሰራለት “የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ አጭር የህይወቱና የፅሁፉ ታሪክ” መፅሐፍ ሰሞኑን በተመረቀበት ወቅት ከተናገሩት የተወሰደ)
“ከመጠን በላይ” ፊልም ነገ ይመረቃል
ቴዲ ሊ ጽፎ ያዘጋጀውና ሊ ፔፕ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “ከመጠን በላይ” የፍቅር ፊልም ነገ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ይመረቃል፡፡ የ102 ደቂቃ ያለውን ይሄን ፊልም ለመሥራት ዘጠኝ (?) መፍጀቱን ያመለከተው ሊፔፕ ፊልም ፕሮዳክሽን፣ ፊልሙ በስድስት ዓለምአቀፍ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለመታየት መዘጋጀቱንና የተቀረፀበት ካሜራም SD Mark II canon መሆኑን ገልጿል፡፡ አጽመ ታሪኩን ባልተለመደ ውሳኔ ላይ ባደረገው የፍቅር ፊልም ላይ አማኑዔል ይልማ፣ ሄለን በድሉ፣ ሸዊት ከበደ፣ ኤልያስ ወሰንየለህ፣ ጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ፣ ቴዎድሮስ ጋሻው በዛና ሌሎችም በትወና፣ አማኑኤል ይልማና ሃይሉ አመርጋ (ጃኖ ባንድ) የማጀቢያ ሙዚቃ በመስራት፣ ቴዎድሮስ ወርቁ ፊልሙን ኤዲት በማድረግ ተሳትፈዋል፡፡
ዝንቅ
“አስራ ሁለት ሆነን አንድ ሴት ወደን
እሷ ትስቃለች እኛ ተጨንቀን”
(የአዝማሪ ግጥም፤ ከእማማ ውዴ የሰማሁት)
ተለውጫለሁ፡፡
እዚህ ግቢ በቆየሁባቸው ሦስት ከሩብ አመታት ሞዴል የሆነ ህይወት ስመራ ቆይቻለሁ፡፡ ምንም ምስጢር የለውም፡፡ እዚህ ለምን እንደመጣሁ አውቃለሁ፡፡ ለትምህርት ነው፡፡ ክፍል እየገባሁ ትምህርቴን በስነ ሥርዓት እከታተላለሁ፡፡ የማይዛነፍ የጥናት ፕሮግራም አለኝ፣ በዚያ መሰረት አጠናለሁ፡፡ በትርፍ ጊዜዬ ስለስዕል፣ አነባለሁ፡፡ (አባቴ ምርጥ ሠዓሊ ነው) አልፎ አልፎ የራሴን ስኬቾች እሰራለሁ፡፡ ፊሊፕስ ዲጂታል ሬዲዮ አለኝ፤ ሬዲዮ አዳምጣለሁ፡፡ ቁርአን እና መፅሐፍ ቅዱስ አነባለሁ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ በቀን አምስት ምዕራፍ እያነበቡ በሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት፣ ማለት በአንድ አመት ያልቃል፡፡ በቀን አምስት ምዕራፍ አነባለሁ፡፡ ኮሌጅ ከገባሁ አሁን አራተኛ ዙር እያነበብኩ ነው፡፡ ዘንድሮ የሩብ አመት፣ ማለት አራት መቶ ሃምሳ ምዕራፎች አንብቤአለሁ፡፡ ከጐበዝ ልጆች ጋር ቼዝ እጫወታለሁ፡፡
ንፅሕናዬን እጠብቃለሁ፡፡
አሁን ግን ተለውጫለሁ፡፡
ቅብጥብጥ፣ እረፍት የለሽ፣ ጭንቀታም ሆኛለሁ፡፡ አባቴ ይህን ቢሰማ ምን እንደሚል አላህ ነው የሚያውቀው፡፡
***
የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኜ ከገባሁ ጀምሮ ሁሌ እንደገረመኝ ነው፤ የተማሪው ወሬ፡፡ ሁሌም ስለሴቶች ነው፡፡ የኮሌጅ ወንዶች ስለሴቶች የሚያወሩትን ያህል የትኛውም የተፃፈ መፅሐፍ፣ የትኛውም የሴቶች ስብስብ፣ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል… ግማሹን እንኳን አይለውም፡፡
እኔ አይደለም ስለሴቶች ስለምንም ነገር አላወራም፡፡ ስለዚህ “…ድንጋይ ነው፣ ግዑዝ ነው፣ ዱዳ ነው፣ በድን ነው…” ይሉኛል፡፡ እንዳልሆንኩ ግን ያውቃሉ፡፡ እነርሱ የሚያደርጉትን ስለማላደርግ፣ አብሬአቸው ስለሴት ስለማላወራ “እርሱ ምንም አያውቅም” ይላሉ፡፡ እንደማውቅ ግን ያውቃሉ፡፡
አንድ ቀን ተሸነፍኩላቸው፡፡ ሁሉም ተሰብስቦ የየራሱን የሴት ምርጫ ሲናገር ድንገት ተመስጬ አዳምጥ ነበር፡፡ አንዳች ነገር ነው ጆሮዬን የያዘው፡፡
እኔ-አጠር ብላ ወፈር ያለች፤ ስትሄድ ፈጠን ፈጠን የምትል…
እኔ-ጥርሶቿ ነጫጭ የሆኑ፣ ጉንጮቿ የሚሰረጐድ…
እኔ-በጣም ቀይ የሆነች፣ ዳሌዋ ደልደል ያለ…
እኔ-ቀይ መልበስ የምታበዛ ሴት፣ በራሷ የምትተማመን…
እንዲህ እንዲያ ሲሉ ቆይተው ድንገት ከመሃላቸው አንዱ “አንተስ?” አለኝ፡፡
የምለውን ለመስማት ፊታቸው ላይ ታላቅ ጉጉት ይነበባል፡፡ አንዳች ነገር ፈንቅሎኝ መናገር ጀመርኩ፡፡
“…ቀጭን ሴት፣ እጅግ በጣም ቀጭን የሆነች፣ አጥነት እና ቆዳ ብቻ፣ እና ረዥም፣ አፍንጫዋ ሰልካካ፣ ጥርሶቿ ነጫጭ ሆነው ድዷን የተነቀሰች፣ አንገቷ ረዥም፣ ትከሻዋ ክብ፣ ከንፈሮቿ ስስ በጣም፤ ፀጉሯ ጥቁር፣ ብዛት ያለው እና ረዥም መሆን አለበት፤ ጣቶቿ ረዣዥም፤ ዓይኖቿ ጥቁር፣ ደግሞም መሃከለኛ፤ ድምጿ ረጋ ያለ፤ እና ቁጡ የሆነች፤ ጠይም፡፡”
ድምፄ ዝግ ብሎ ሃይል አለው፡፡ የወትሮው ቅዝቃዜ ተለይቶታል፡፡ ንግግሬም በአካላዊ ገለፃ የታገዘ ነበር፡፡ ልጆቹ አውርቼ ማብቃቴን ያወቁት ጨርሼ ረዘም ላለ አፍታ ከቆየሁ በኋላ ነበር፡፡ መጨረሴን እንዳወቁ ሁሉም በአንድ ላይ ሳቁ - ከጣራ በላይ፣ ከት ብለው፣ ከትከት ብለው ሳቁ፡፡ …ንግግሬ ውስጥ የትኛው ስህተት እንደነበረ፣ የትኛው እንደሚያስቅ አልገባህ አለኝ፡፡
“እብዶች” ብዬ ጥያቸው ወጣሁ፡፡
“የምትወዳት ልጅ እንጥሏ ምን አይነት ቢሆን ደስ ይልሃል?! ምላሷስ?!” ሲለኝ ሰማሁት አንዱ፡፡
ከዚያ በኋላ ሁሉንም ዘጋኋቸው፡፡ ማለቂያ በሌለው ዝምታዬ ዘለቅሁበት፡፡ ዝምታዬ ዋሻዬ ነው፤ መደበቂያዬ፤ የአባቴ ውርስ፤ በቁሙ እያለ ያወረሰኝ፡፡
ከዚያ በኋላ “ጓደኞቼ” ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይሳለቁብኛል፡፡
ሲበዛ ሃሳባዊ ነህ…
ለካንስ እብድ ኖረሃልና…
ነገርህ ሁሉ የጤነኛ አይደለም…
አጉል ልዩ ፍጡር ልሁን ትላለህ…
ለምን የኮሌጁን ሳይካትሪስት አታናግረውም
አንተ የኛ ሰቃይ የሆንከው እኛ ሰንፈን እንጂ አንተ ብሩህ ሆነህ እንዳልሆነ አሁን ገባኝ ወዘተ ወዘተ ይሉኛል፡፡
አሁን ይኸ ሁሉ እኔ ከተናገርኩት ጋር ምን ያገናኘዋል?!
***
…ሁለቴ ይሁን ሦስቴ እዚህ ግቢ ከሴት ተማሪዎች የፍቅር ደብዳቤዎች ደርሰውኛል፡፡ ከእነማን እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ብቻ እዚህ ግቢ ውስጥ እኔ የምፈልጋት አይነት ሴት እንደሌለች አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ሦስቱንም ወረቀቶች በቅጡ እንኳን ሳላነባቸው ነው የቀደድኳቸው፡፡ ከ”ጓደኞቼ” ለአንዱ ደርሶት ቢሆን ኖሮ ሺህ መቶ ሚሊዮን ፎቶ ኮፒ አባዝቶ ይበትነው ነበር፡፡ መጠየቄን ከእኔ በቀር ማንም አያውቅም፡፡
…ይህ ሁሉ ሊሆን እንደሚችል አባቴ ነግሮኝ ነበር፡፡
ምን እማይነግረኝ ነገር አለ እሱ?! በእኔ እና በእርሱ መሃል ያለው ግልፅነትና ቅንጅት በሦስቱ ሥላሤዎች መሃል መኖሩንም እንጃ፡፡ ውስጡን ገልብጦ ነው የሚነግረኝ፡፡ የእኔንም ህልሜን እንኳን እንድደብቀው አይፈልግም፡፡ ስለ ክህደት ይቆጥረዋል፡፡ ከሚያወራልኝ ታሪኮች መሀል ስለ እናቴ የሚነግረኝ ከምንም በላይ ይመስጠኛል፡፡ “እናትህ ነብር ነበረች” ብሎ ይጀምራል፡፡ “..ነፍሷን ይማርና” አይልም፤ አሁንም በህይወት እንዳለች ነው የሚቆጥረው መሰል፡፡ በነገራችን ላይ እኔን ስትወልድ ነው የሞተችው፤ በሃያ አመቷ፤ …አባቴ ያኔ ሃያ ሦስት ነበር፡፡ ከሞተች አንስቶ እስካሁን ድረስ ብቻውን ነው የሚኖረው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ የምንኖረው አባቴ፣ እኔ፣ አንዲት ነጭ ድመት ነን፡፡ ተመላላሽ ሠራተኛ አለችን፡፡
“…ቀጭን ነበረች ሲበዛ፤ አጥንትና ቆዳ ብቻ፡፡ …ጥርሶቿ ነጫጭ ሆነው ድዷ በሚያምር ንቅሳት የተዋበ ነበር፡፡ አፍንጫዋ እንዲህ ነው” (አመልካች ጣቱን አፍንጫው ጥግ ላይ ሰክቶ)… ይህን ታሪክ ስንቴ እንደነገረኝ አላውቅም፡፡ ግን ቢያንስ በቀን አንዴ ሳይነግረኝ አይውልም፡፡ በጣም ይወዳት ነበር፡፡ ብዙ አያወራም፤ ካወራም ስለ እርሷ ነው፡፡…
“…ሁለተኛ ደረጃ ስንማር ነበር ያፈቀርኳት፡፡ …ከስንት ጭንቀት በኋላ ደብዳቤ ፃፍኩላት፡፡ ደብዳቤውን በሰጠኋት ማግስት እሳት ለብሳ እሳት ጐርሳ መጥታ በጥፊ አናጋችኝ፡፡ (ቀኝ ጉንጩን እያሻሸ) አንድ ሳምንት ግቢው ውስጥ መጠቋቆሚያ ሆንኩኝ፡፡ ያን ሰሞን ራሴን ብሰቅል ወይ የሆነ አሲድ ብጠጣ ደስታውን አልችልም ነበር፡፡ …በኋላ እየሳቀች መጥታ ይቅርታ ጠየቀችኝ፡፡ …ቀጭን ነበረች፤ አጥንት እና ቆዳ ብቻ፤ ፀጉሯ ጥቁር፤ ከንፈሮቿ ስስ፤ አንገቷ ረዥም፤ ትከሻዋ ክብ፡፡”
ሲያወራልኝ ሁሌ ተመስጦ ስለሆነ፤ የማዳምጠው ሁሌ ተመስጨ ነው፤ በከፍተኛ ጉጉት ተይዤ፡፡ ዝምተኛ ቢሆንም ሲናገር ወሬውን ጥሩ ያስኬደዋል፡፡ ዝምታ ከጊዜ በኋላ የተጣባው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ …አባቴ ሠዓሊ ነው፡፡ ታዲያ የቀጭን የረዥም፣ የሰልካካ ሴት ምስል ነው ስቱዲዮውን የሞላው፤ ሳሎናችንንም ጭምር፤ መኝታ ቤቶች ሳይቀሩ፡፡ በተለያየ ሁኔታ ተስለው፡፡ …ገንዘብ ሲፈልግ ብቻ ነው ሌሎች አይነት ሥዕሎችን የሚሰራው፡፡
የሰሞኑን ጭንቀቴን ለአባቴ ደውዬ ልነግረው ብዬ ፈራሁ፡፡ ጤንነቴን እንዲጠራጠር፣ በእኔ ያለውን እምነት እንዲያጣ አልፈለግሁም፡፡ ሆኖ የማያውቅ ነገር ነው የሆነው፡፡ እኔም ራሴ ነገሩን ደጋግሜ ሳስበው እየቄልሁ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ስለፊልም ታሪክም የማስብ ይመስለኛል፡፡ የማክሲም ጐርኪይ ልብ-ወለድም ትውስ ይለኛል፤ ሃያ ስድስት ዳቦ ጋጋሪዎች በአንድነት አንዲት ሴት ያፈቀሩበት ታሪክ፡፡ የእኔ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ እኔ ብቻዬን ሆኜ ነው ብዙ ሴቶች ያፈቀርኩት፡፡ በራሴ ህይወት ውስጥ እየተከሰተ ያለ ነገር መሆኑን መቀበል ፍፁም አልቻልኩም፡፡ ለወሬ የማይመች ነገር ነው፤ መያዣ መጨበጫ የሌለው፡፡
ፍቅር ይዞኛል፡፡
በጉዳዩ ላይ ብዙ አስቤበታለሁ፡፡ ቡና እየጠጣሁ፤ የእግር ጉዞ እያደረኩ፤ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቼ አስቤበታለሁ፡፡ በአሰብኩት ቁጥር ግን ሁሉም ነገር ይበልጥ እየከበደ ይመጣል፤ እየተጫነኝ፡፡
ሌላው ይቅር ክፍል መግባት አቁሜያለሁ፤ አላጠናም፤ ውሎዬ ከተማ ነው፡፡ ከኮሌጅ ጠዋት የወጣሁ ማታ የግቢው ሰዓት እላፊ ሲደርስ እመለሳለሁ፡፡ ዝምታዬ በርትቷል፡፡ …ቅዠቴም ለጉድ ሆኗል፡፡
የቀረኝ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ለአባቴ መደወል፡፡
“ሄሎው… አባቴ”
“አቤት ማሙሽ…”
ሁሌም ለእርሱ ማሙሽ ነኝ፡፡ አሁን ሃያ አንድ ዓመት ሆኖኛል፡፡
“ምነው ደህና አይደለህም እንዴ!? ድምፅህ… ልክ አይደለም፡፡”
“አባቴ ሁሌ አንድ ነገር እነግርሃለሁ እልና፤ ከዚያ በቃ..” ዝም አልኩ፡፡
“…ማሙሽ እኔ ይህን መስማት አልችልም፡፡ የእኔ ልጅ ነው ለአባቱ መናገር ስላለበት ጉዳይ የሚጨነቀው?!”
“እንዴት መሰለህ አባቴ፤ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ሆኖብኝ ነው እንዴት እንደምነግርህ የጨነቀኝ፡፡”
“ማሙሽ! በእርግጥ ከልጄ ጋር ነው እያወራሁ ያለሁት?! አነተ ነህ ችግርህን ለእኔ ለመንገር የምትጨነቀው ወይ?!”
“አባቴ አትቆጣ፡፡ ቆይ ልንገርህ በቃ፡፡ ይሄውልህ፣ ምን መሰለህ፣ እ-እንትን፤ አለ አይደል… ፍቅር…” ከት ብሎ ሳቀ፤ የደስታ ሳቅ፤ የአባቴ ሳቁ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ የሳቁ ዜማ እና ግጥም ደራሲ ራሱ ነው፡፡
“ፍቅር ያዘህ? ታዲያ ይህ ምን የሚያስደንቅ ነገር አለው? ሁሌ እነግርህ አልነበር ሊከሰት እንደሚችል? ቆይ ኮሌጅ ውስጥ ከምትማር ልጅ ጋር ወይስ…?”
“ይህን ከመመለሴ በፊት ስለ እናቴ የምትነግረኝን ታስታውሳለህ? ስለ ቅጥነት፣ ስለ…”
“አዎ፤ እናትህ ቀጭን ነበረች፤ አጥንት እና ቆዳ ብቻ፤ ፀጉሯ ጥቁር፤ ረዥም እና ጫካ ነበር፤ ጥርሶቿ ነጫጭ ነበሩ፤ ድዷ…” የዘወትር ትርክቱን ከጨረሰ በኋላ ጠየቀኝ፡-
“እና እሷን የምትመስል ሴት ነው ያፈቀርኩት በለኛ!”
እሷን የምትመስል ሴት ሳትሆን ሴቶች!”
“ምን?!...” የድምፁ ቃና ተለወጠ፡፡ “…አልገባኝም ማሙሽ”
“አባቴ፣ ደብዳቤ ልፅፍልህ ብሞክር አልቻልኩም፡፡ በስልክ እንዳልነግርህ የሚሆን አይደለም፡፡ እና ምን እንደሚሻል አላውቅም”
“እባክህ ማሙሽ አስጨነከኝኮ”
“ይቅርታ አባቴ”
ሳላስበው እንባዬ መጣ፤ ድምፄ የለቅሶ ቃና ያዘ፡፡
“ቆይ ቆይ ዛሬ ምንድነው?” አለኝ አባቴ፡፡
“ሀሙስ”
“ወደ መቀሌ ሁሌ ነው መሰለኝ በረራ ያለው፡፡ በቃ ቅዳሜ ወይ እሁድ እደርሳለሁ እሺ?”
ደነገጥኩ፡፡
ምንም ከማለቴ በፊት የተለመደውን “ማሙሽ እወድሃለሁ” ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ መነጋገሪያውን አንከርፍፌ ብዙ ቆየሁ፡፡ ባለ ሱቁ የመንጠቅ ያህል ሲቀበለኝ ነው የባነንኩት፡፡ ሂሳቡን ከፍዬ ወጣሁ፡፡ ቀስ ብዬ እያዘገምኩ ወደዚያ የፅህፈት መሳሪያ መደብር አቀናሁ፡፡ በመቀሌ ትልቁ የፅህፈት መሳሪያ መደብር ነው፡፡ ሁለት እህትማማቾች ናቸው ደንበኛን የሚያስተናግዱት፤ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን፡፡ የሃያ አንድ እና የሃያ አመት ወጣት ሴቶች፡፡ አንዷ እቃ ታቀብላለች፤ ሌላኛዋ ሂሳብ ትቀበላለች፡፡ …በሆነ አጋጣሚ ድንገት እንዲያው ድንገት ወረቀት አልቆብኝ ልገዛ ገባሁ፡፡ በፊት ቢሆን ከሌላ መደብር ነበር የምገዛው፡፡
…ጭር ብሎ ነበር ቤቱ፡፡ …የሁለቱም ሴቶች አለባበስ ሆን ተብሎ አይን ለመያዝ የተደረገ ይመስላል፡፡ መጀመሪያ አንዲቷን አየሁዋት፡፡ ቀይ ናት፡፡ ፀጉሯን ለቃዋለች፤ ፍሪዝ ነው፤ ጥቁር፣ ብዛት ያለው፣ ረዥም ፀጉር፡፡ አይኖቿ ጥቋቁር ናቸው፤ መሀከለኛ፡፡ ጥርሷ ፍንጭት፣ ሰውነቷ ደልደል ያለ ነው፡፡ ቁመቷ አጭር፡፡ ትከሻዋ ክብ ነው፡፡ …ወደ ሌላይቱ ዞርኩ፡፡ ፈገግ ብላለች፤ የጥርሶቿ ንጣት ያስደነግጣል፡፡ ችምችም ያሉ ናቸው፡፡ ድዷን ተነቅሳዋለች፡፡ በጣም ያምራል፡፡ ቅጥነቷ ለጉድ ነው፡፡ አጥንት እና ቆዳ ብቻ ነች፤ ረዥም ናት፤ አፍንጫዋ ደግሞ ሰልካካ፤ አንገቷም ሰልካካ ነው፡፡ ከንፈሮቿ ስሶች ናቸው፡፡
እንደ እህቷ ከንፈሮች አይወፍሩም፡፡ …አይኖቿ ትንንሾች ናቸው፤ ገጿ ደግሞ ጠይም፡፡ ፀጉሯን ሰብስባ መሃል አናቷ ላይ አሲዛዋለች፣ አጭር ነው፡፡ በስተመጨረሻ ጐን ለጐን እንደቆሙ አንድ ላይ አየሁዋቸው፡፡ ይሄኔ ሰውነቴ መራድ ጀመረ፡፡ ትንፋሼ ፈጣን እና ቁርጥ፣ ቁርጥ የሚል ሆነ፡፡ ብብቴን፣ ውስጥ እጄን፤ አፍንጫዬን አላበኝ፡፡ ዘላለምን ለሚያህል ጊዜ ቆሜ ቀረሁ፡፡ ወይም እንደዚያ መስሎኛል፡፡
ደልደል ያለችው (ዮርዳኖስ) ተናገረች፡-
“ምን ነበር ወንድሜ?”
ሌላ መአት፡፡ የድምጿ እርጋታ ከድንዛዜዬ ከማንቃት ፈንታ ባለሁበት ውዥንብር እንድቀጥል አደረገኝ፡፡ ከስንት ትግል በኋላ ያሰብኩትን ዘንግቼ ብዕር ገብይቼ ወጣሁ፡፡ ያን ሌት አይኔ ፈጦ አደረ፡፡ ምን እንዲያ ሊያደርገኝ እንደቻለ አልገባህ አለኝ፡፡ ልጆቹ በሁኔታዬ አለቅጥ ነበር ግራ የተጋቡት፡፡ እኔም በእራሴ እንደዚያው፡፡… አስር አስር ጊዜ ሲተያዩ ነበር፡፡
ምን እንዲያ እንዳደረገኝ ለማወቅ እዚያ ቤት ተመላለስኩ፡፡ በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ እሄድ ነበር፡፡ እርሳስ፣ እስኪርብቶ፣ የብዕር ቀለም፣ ባይንደር፣ አጀንዳ፣ ሀይላይተር… መደብር ውስጥ ያሉትን እቃዎች በየተራ ገዛሁ፡፡ ከልጆቹ ጋር ተላመድን፡፡ ውሎ እያደር ችግሬ ገባኝ፡፡ ድንገት መደብሩ ውስጥ አንዲቷን ልጅ ብቻ ያየሁ እንደሆነ የሆነ ጉድለት ይሰማኛል፡፡
ያኔ ቶሎ እወጣለሁ፡፡ ያሉት ሁለቱም ካልሆኑ አንዳንዴ እንደውም ከበር እመለሳለሁ፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ የሆኑ እንደሆኑ ግን ነፍሴ በሀሴት ትዘላለች፡፡ …በተቃራኒው ደግሞ እህትማማቾቹ እኔን ሊያገኙኝ የሚፈልጉት ለየብቻ ነው፡፡ አንድ ላይ ሳገኛቸው አንዷ አንዷን ከአጠገቧ ለማራቅ የማትዘይደው የለም፡፡ ሊታረቅ የማይችል ውዥንብር ተፈጠረ፡፡ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን እስከ መኳረፍ ደረሱ፡፡ …የእኔም ጭንቀት እየበረታ መጣ፡፡
…ለእኔ አንድ ላይ ሲሆኑ ነው ያን ምስል በጥምረት የማገኘው፡፡ የሁለቱ ገፅ ድምር ነው አንድ መስል የሚሰጠኝ፡፡ የአንዲቷ ፀጉር ሲደመር፣ የሌላዋ አፍንጫ ጥንቅር… የውብ ሴት ምስል ይታየኛል ያኔ፡፡
ውስጤ ያለችውን ሴት ሁለት ሴቶች ላይ ተበታትና አገኘኋት፤ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን ላይ፡፡ እና ሁለቱንም እኩል አፈቀርኳቸው፤ በአንድ ላይ፡፡ በቃሉ ተራ ትርጉም ሁለት ሆኑ እንጂ እኔ ያፈቀርኩት አንዲት ሴት ነው፡፡
…አባቴ ስቱድዮ ውስጥ ከተለመደው የቀጭኗ ሴት (ለምን እንደሆነ እንጃ እናቴ ማለት ከበደኝ) ምስል የተለዩ ሁለት ስዕሎች አሉ፤ ጐን ለጐን የተቀመጡ፡፡ አባቴ “በሁለቱ ስዕሎች ውስጥ ያለውን ምስጢር ካገኘህ ሽልማት አለህ” ብሎ ነበር፡፡ ለቀናት ያህል አፍጥጬባቸው ብውልም ምስጢሩን ልፈታው አልቻልኩም ነበር፡፡ አባቴ እንዲነግረኝ ብለምነውም ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ “እራስህ ፈልገህ ማግኘት አለብህ፡፡” ነበር መልሱ፡፡ መልስ መስጫው ጊዜ አልፎ እንዳይሆን እንጂ አሁን መልሱን አግኝቼዋለሁ፡፡
አሁን ሁሉ ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ውስጤ እንዳትረሳ ሆና በህያው ብሩሽ የተሳለችው ሴት፣ እንዳትገረሰስ ሆና የፀናችውን ሴት መቀሌ ሰማይ ስር ሁለት ሴቶች ላይ አገኘኋት፡፡
…አንድ ነገር እፈራ ነበር፡፡ ልክ እሷን የምትመስል ሴት ካላገኘሁ ጓደኛ ሊኖረኝ እንደማይችል ጠንቅቄ አውቅ ነበር፡፡ ፍራቻም ነበረኝ፤ እንደማላገኝ፤ አሁን ግን…
መደብሩ ጋ ስደርስ አመነታሁ፡፡ ልመለስ ግን እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ገባሁ፡፡ ሁለቱም በሰፊ ፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ አንዳች ምሉዑነት ተሰማኝ፤ እርካታ፤ እድለኝነት፡፡
…በሁለቱ እህትማማቾች መሐል ያለው ቅራኔ ትዝ ሲለኝ ግን ቅዝቃዜ ወረረኝ፡፡ እነርሱን ካወቅሁ ወዲህ የተለያየ ስሜት በየደቂቃው ይፈራረቅብኛል፡፡ ሐዘን ከደስታ፣ እርጋታ ከእረፍት ማጣት ጋር፡፡ …የዮርዳኖስ እና የሙሉብርሃን ቅራኔ ከእለት እለት እየበረታ መጥቷል፡፡ አሁንም እንዲህ የጐሪጥ እየተያዩ አብሬአቸው ልቆይ አልቻልኩም፡፡ ነዶኝ ትቻቸው ወጣሁ፡፡
የወትሮው ጭንቀቴ ባሰብኝ፡፡ እግሮቼ እስኪዝሉ በመቀሌ አውራ ጐዳናዎች ላይ ተንከራተትኩ፡፡ ሀውዜን አደባባይን ለማይቆጠር ጊዜ ዞርኩት፡፡ ጐዳና አሉላ፣ ጐዳና ሠላም፣ ጐዳና አግአዚ፣ ጐዳና ሙሴ ላይ ለማይቆጠር ጊዜ ተመላለስኩ፡፡ ሲመሽ እና ስዝል ጊዜ ኮንትራት ታክሲ ይዤ ወደ ኮሌጅ አመራሁ፡፡
…የመኝታ ክፍል ተጋሪዎቼም ሆኑ ሌሎች ተማሪዎች እንደድሮው አይደሉም፡፡ ወይም እንደዚያ መስሎኛል፡፡ በሀዘኔታ ነው የሚያዩኝ፡፡ የበፊቱ ንቀት የለም፡፡
…ብዙዎቹ ችግሬን ሊካፈሉ ቀርበው ሲጠይቁኝ በጩኸት አስደንግጬአቸዋለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ ይንከባከቡኛል፡፡ አልጋዬ ተነጥፎ ነው የሚጠብቀኝ፡፡ ሎከር ስከፍትም ታጥበው የተቀመጡ ልብሶችን ነው የማገኘው፡፡ ግን ይህም ያናድደኛል፡፡ የሌሎች እርዳታ ስር መውደቄ ያበግነኛል፡፡
(…ግን፣ ግን ይህን ሁሉ እንዴት ሊሆን ቻለ) አፍጠው የሚያዩኝን ጓደኞቼን እንዴት ዋላችሁ እንኳን ሳልል ጫማዬን ብቻ አውልቄ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡
…አባቴ ቅዳሜ አምስት ሰዓት ተኩል መቀሌ ገባ፡፡ እስክንገናኝ ብዙ እንደተጨነቀ ያስታውቅበታል፡፡ ከአዲስ አበባ የሚነሳበትን ሰዓት አስታውቆኝ ስለነበር አየር ማረፊያ ድረስ ሄጄ ነው የተቀበልኩት፡፡ ተጠመጠመብኝ፡፡ ተጠመጠምኩበት፡፡ አይኑ እንባ አዘለ፡፡ ተጐሳቁዬ ነበር፡፡ በጣም ከስቻለሁ፡፡ አይኖቼ ሠርጉደዋል፡፡ ፀጉሬ ተንጨባሯል፡፡ አለቀሰ፡፡ አላለቀስኩም፡፡
ከንፈሬን በላሁት፡፡ ሁሉን ነገር ለመስማት አለመጠን ጓጉቶ ነበር፡፡ ከአየር ማረፊያው ወደ መቀሌ ከተማ እየሄድን ጀመርኩለት፤ አክሱም ሆቴል ነበር አልጋ የያዝኩለት፤ እዚያ ጨረስኩለት፡፡ እንደጠበኩት ብዙ አልተገረመም፤ መጐሳቆሌ ከፈጠረበት ሀዘን በስተቀር ምንም እንግዳ ስሜት አላየሁበትም፡፡ ሁለት ሴት በአንድ ላይ እኩል ማፍቀሬ የፈጠረበት ግልጽ ስሜት ግልጽ አልነበረም፡፡ ልጆቹን ለማየት ግን በጣም ጓጉቷል፡፡ ሰኞ እለት አስተዋወቅሁት፡፡ ሁለቱንም አንድ ላይ ሲያያቸው ከእኔ የባሰ የስሜት ማዕበል ነበር የመታው፡፡ አባቴ እንዲያ ሲሆን ሳይ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፡፡ ጉንጬን በእጁ እየዳበሰ ለረዥም ጊዜ ፈዞ ቀረ፡፡
ሰዓሊ ስለሆነ በሁለቱ ገጽ ላይ ያለውን ቅኔ ለማግኘት እና ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ የመባነን ያህል ነቅቶ የኋላ ኋላ ተዋወቃቸው፡፡ ዮርዳኖስ እና ሙሉ ብርሃን በአባት እና ልጅ አኳኋን ቅጥ አምባር ማጣት አለቅጥ ነው ግራ የተጋቡት፡፡
በእኔ ላይ የሆነው በአባቴ ተደገመ፡፡
አባቴ፤ መቀሌ ወር ያህል ቆየ፤ ያለምንም ፋይዳ፡፡ ሁሌም እምናወራው ወሬ አንድ አይነት ነው፤ ልጆቹ የሚወደዱ እንደሆነ፡፡ አንድም ቀን በመፍትሔው ላይ ተነጋግረን አናውቅም፡፡ ለዚህ፣ ለዚህ የእሱ መምጣት እንዳስፈለገ አልገባኝም፡፡ ….ያም ሆኖ ግን ባህሪዬ ተስተካክሏል፡፡
የምወደው አባቴ አጠገቤ ስላለ ይሆናል፡፡ ማጥናት ጀምሬአለሁ፡፡ ሰውነቴም መጠገን ይዟል፡፡ ከዮርዳኖስ እና ከሙሉ ብርሃን ጋር ያለን ግንኙነት ግን ምንም መሻሻል ሳያሳይ እንደነበር ቀጥሏል፡፡ …አባቴ የመጣው የዕረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ እንደሆነ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡
አባቴ፣ መቀሌ ባለበት ቀናትም የሥዕል ሥራውን አላቋረጠም፡፡
ከሸራ፣ ከቀለም ሽታ፣ ከብሩሽ፣ እና ከቅርፆች…ተነጥሎ ሊኖር አይችልም፡፡ ግን ምን እየሳለ እንደሆነ አሳይቶኝ አያውቅም፡፡ እኔም አልጠየቅሁም፡፡ ሲጨርስ መጀመያ የሚያሳየው ለእኔ እንደሆነ ግን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ በፊት ቢሆን ግን ሲጀምር፣ መሀል ላይም፣ ሲጨርስም ያሳየኝ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሀሳብ ብልጭ ሲልለት በችኮላ የወረቀት ላይ ንድፎቹን ያሳየኝ ነበር፡፡ የሆነስ ሆነና የመቀሌ ሰማይ ስር ሆኖ ምን እየሳለ ይሆን ይኼ ምርጥ ሰዓሊ እያልኩ አስባለሁ፡፡
ፈተና እየተቃረበ ስለሆነ አባቴም በስዕል ስራው ስለተጠመደ፣ በቀን በቀን መገናኘቱን ትተነዋል፡፡ ቢበዛ ከሁለት ቀን አንዴ ብንገናኝ ነው፡፡ ዛሬ ካገኘሁት አራተኛ ቀኔ ነው፡፡ ጥናቴን ስጨርስ ወደ ከተማ፣ አባቴ ወዳለበት ሄድኩ፡፡ አካሄዴ የመፍትሔውን ነገር እንዲያስብበት ለመንገር እና ቸልተኝነቱ ከምን እንደመነጨ ለመጠየቅ…ብቻ በብሶቶች ተሞልቼ ነው አባቴ ወደ አረፈበት ሆቴል ያመራሁት፡፡ ያዳፈንኩት የመሰለኝ ፍቅር ቦግ ብሎ እየተቀጣጠለ ነው፡፡
አክሱም ሆቴል ስገባ አባቴ ጉርሻ ያስለመደው አስተናጋጅ፣ በሰፊ አፉ ትልቅ ሳቅ እየሳቀ ወደ እኔ መጣ፡፡ እንደወትሮው ሆኖ እጅ ነሳኝ፡፡ እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ፤ ስብር አለ ወደፊት፡፡ ቀና ሳይል እጆቹን ብቻ አላቆ ቢጫ ፖስታ አቀበለኝ፡፡ አባቴ ነው እንዲህ አይነት ቀለም ያለው ፖስታ የሚጠቀመው፡፡
ደነገጥኩ፡፡
“ምንድነው? አባቴስ?!”
“ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በረሩ”
“ምነው? ምን ተፈጠረ? ማለቴ ሳይነግረኝ? ሳንገናኝ?”
“አይ በደህና ነው፡፡ እስኪ የተውልህን መልእክት አንብበው”
ስልት በሌለው ሁኔታ ፖስታውን ቀደድኩት፤ እጄ እየተንቀጠቀጠ ነው፡፡
“…ማሙሽ ዮርዳኖስ የእኔ ባለቤት የአንተ…ሆና አብራኝ ወደ አዲስ አበባ በራለች፡፡ ሙሉ ብርሃን ደግሞ ትምህርትህን እንደጨረስክ አብራህ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በሙሉ ፈቃደኝነት እየጠበቀችህ ነው፡፡ እንግዲህ ሁለቱንም የኛ፣ ሁለታችንም የእነሱ ሆንን ማለት አይደል? ከዚህ ውጭ መፍትሔውን ሙሉ ሊያደርግ የሚችል ምንም አማራጭ የለም፡፡ ማሙሽ በዚህ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ የተመለስኩት ነገሩን መጀመሪያ ስትሰማ ሐሳቤ ስህተት ቢመስልህ ገጽህ ላይ ሊታይ የሚችለውን ስሜት ልቋቋም እንደማልችል ስላመንኩ ነው፡፡ በደንብ አስብበት እስኪ፡፡ እኔ ብዙ አስቤበታለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የሠርጋችሁን ቀን የአንተ ምርቃት ቀን ብታደርጉት በጣም ደስ እንደሚላት ሙሉ ብርሃን ነግራኛለች፡፡ መልካም ጊዜ፡፡ ማማሽዬ እወድሃለሁ፡፡
አባትህ”
አቃሰትኩ፡፡
አስተናጋጁ ሁለት እጆቹን ወደኋላ አጣምሮ አጠገቤ አለ፤ አሁንም፡፡
“ክፍላቸው ውስጥ ዕቃ ትተውልህ ሄደዋል መሰል ቁልፍ ሰጥተውኛል፤ ይኸው” ብሎ ቁልፍ አስጨበጠኝ፡፡
በደመ ነፍስ ወደ ስድስት ቁጥር አመራሁ፡፡ ገና በር ከመክፈቴ ዓይን ከሚስቡ ሰው አከል የሁለት ሴቶች ምስል ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ የዮርዳኖስ እና የሙሉ ብርሃን ምስል…
ተንደረደርኩ፡፡ በአንድ እግር ስንዘራ የዮርዳኖስን ምስል ሸነተርኩት፡፡ ሁለት፣ አራት…በጥርሴ፣ በእግሬ፣ በእጄ…እፎይ!
ወደ ሙሉ ብርሃን ምስል ስዞር በሩ ሳይንኳኳ ተከፈተ፡
ሙሉ ብርሃን፡፡
ሙሉ ብርሃን በአካለ ሥጋ ከፊቴ ቆማለች፤ ምስሏ ከኋላዬ አለ፡፡
አየኋት፡፡
አየችኝ፡፡
አየኋት፡፡
አየችኝ፡፡
…ቀስ በቀስ ስሜቴ ሲረጋጋ ይታወቀኛል፡፡ እጆቿን ዘርግታ ተንደረደረች፡፡ አቅፋ አልጋ ላይ ጣለችኝ፡፡
ከወደቅንበት የተነሳነው ሁለታችንም ድንግልናችንን አልጋው ላይ ጥለን ነው፡፡
1992 ዓ.ም፤ መቀሌ
“የእስራኤል መንግሥት ዘረኛ አይደለም”
“በእስራኤል ቆራጥነትና በምትሰራው ጀብዱ እኮራባታለሁ”
በታዳጊነቱ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ እውቅ የእስራኤል ጋዜጠኞች ጋር በፈጠረው ትውውቅ ነው ወደ እስራኤል የተጓዘው - ከ45 ዓመት በፊት፡፡ ቤተእስራኤላዊው አላዛር ራህሚም በ1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ 14ሺ 200 ቤተእስራኤላውያን ወደ እስራኤል ያጓጓዘው “ዘመቻ ሰለሞን” ንቁ ተሳታፊ እንደነበር ይናገራል፡፡ ለ30 አመት ገደማ በእስራኤል ብሄራዊ ሬዲዮ በጋዜጠኝነት የሰራው አላዛር፤ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሚሰጡት ሹመት ተወዳድሮ አሸንፎ ነበር፤ ሆኖም በራሱ የግል ምክንያት ሹመቱን ሳይቀበለው ቀረ፡፡ ቤተእስራኤላውያን በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ “ማርና ወተት የምታፈስ” በሚል የተጠቀሰችውን እስራኤል አልመው ቢጓዙም ምድረበዳና በጦርነት የተከበበች አገር ነው ያገኙት የሚለው አላዛር፤ ቤተእስራኤላውያን የዘር ልዩነት መድልዎ ይደርስባቸዋል የሚለውን ውንጀላ ብዙም አይቀበለውም፡፡
በግለሰብና በቡድን ደረጃ ዘረኝነትን የሚያራምዱ ቢኖሩም የእስራኤል መንግሥት ግን ዘረኛ አይደለም በሚል ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ጋር የተጨዋወተው ቤተእስራኤላዊው ጋዜጠኛ አላዛር ራህሚም ስለ ቤተእስራኤላውያን የሥራ ዕድሎች፣ ስለሚያደንቃቸው የእስራኤልና የኢትዮጵያ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አውግቷል፡፡ እነሆ፡-
ራስህን በማስተዋዋቅ ጨዋታችንን ብትጀምረውስ…
አላዛር ራህሚም ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ስሜ አላዛር ምህረቱ ነው፡፡ ራህሚምን ወደ አማርኛ ስትተረጉመው ምህረቱ ማለት ነው፡፡ የእብራይስጡን ስም ወደድኩት፡፡ እብራይስጥ የኦሪት ቅዱስ ቋንቋ ስለሆነ ወድጄ ነው ያደረግሁት፡፡
ከኢትዮጵያ የት አካባቢ ነው ወደ እስራኤል የሄድከው?
ሰቀልት የሚባል የጐንደር አካባቢ ነው የተወለድኩት፡፡ አስራ አንድ ልጆች ላሉት ቤተሰብ ስድስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ የሰፈር ረባሽ እና ተደባዳቢ ስለነበርኩ በቦታ ለውጥ ፀባዬ ይለወጣል በሚል አምቦበር የምትባል ቦታ ዘመድ ቤት ወሰዱኝ፡፡ ፈረንጆች ለመጀመርያ ጊዜ ያየሁት እዚያ ነው፡፡ ቤተሰብ አካባቢ “እብራይስጥ የተናገረ ዘመዳችን ነው” ተብያለሁ፡፡ ፈረንጆቹ እብራይስጥ ሲናገሩ ሰማሁና “ሻሎም” አልኳቸው፤ የምችለውን መጠነኛ እብራይስጥ ተጠቅሜ፡፡ ይህ የሆነው ከአርባ አመት በፊት ነው፡፡ ፈረንጅ አይቼ ስለማላውቅ “ምንድነው ነጭ ቆዳ” ብዬ እጠይቅ ነበር፡፡
ግን ጣታቸውን ሳይ እንደኔ በአንድ እጅ አምስት ጣቶች አሉ፡፡ ሁለት ጆሮዎች አሏቸው፡፡ እናም እየተከታተልኳቸው ሆቴል ገቡ፡፡ ፈረንጆቹ ምንድነህ ሲሉኝ፣ ፈላሻ ነኝ አልኳቸው፡፡ በወቅቱ ቤተእስራኤል “ፈላሻ” በሚል የስድብ ቃል ነበር የሚጠሩት፡፡
ስድብ ነው… ወይስ ከሰዎች መፍለስ ጋር ይገናኛል?
በታሪክ ወደኋላ መለስከኝ እንጂ ይሄ ስም የተሰጠው በአስራ ስድስተኛ አስራ ሰባተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ የክርስትያኑ ግዛተ አፄ ባልጠነከረበት ጊዜ የይሁዲ ግዛቶችም ነበሩ፡፡ የክርስትያኑ መንግሥት እየጠነከረ ሲሄድ፣ ይሁዳውያን ክርስትና ይነሱ፤ ካልተነሱ ይፍለሱ ተባለ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ፈላሻ ይሁኑ ተባለ፡፡ ፈላሻ ማለት መሬት የሌለው ማለት ነው፡፡
ወደ እስራኤል የሄድክበት ሁኔታስ?
እነዚያ ነጮች ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ አንዱ ለአቭየሽን መፅሔት ይፅፍ ነበር፡፡
ሌላኛው የእስራኤል ወታደራዊ ሬዲዮ ኃላፊ፣ ሦስተኛው በጋዜጠኝነት ከታች እስከ ዋና አዘጋጅነት የደረሰ ነበር፡፡
ውሰዱኝ አልኳቸው፡፡ ልጅነትም ስላለኝ አላወቅሁም፣ “ሻንጣችሁ ውስጥ ከታችሁ ውሰዱኝ” አልኳቸው፡፡ ደነገጡ፡፡
በተለይ አንዱ ሰው በሻንጣ ከቶ መሄድ እንደማይቻል አስረዳኝ፡፡ ፍተሻ ላይ ትያዛለህ አለኝ፡፡ ፍተሻ ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ፈረንጅም ለመጀመርያ ጊዜ ነው ያየሁት፡፡ ከተመለስን በኋላ እንሞክርልሃለን ብለው ቃል ገቡ፡፡
ከአንድ ስድሰት ወር በኋላ አንደኛው ተመልሶ መጣ፡፡ እኔ ወደ ቤተሰብ ተመልሻለሁ፤ ትምህርት ቤቴ አጠያይቆ አድራሻ ትቶልኝ ሄደ፡፡ ከሦስት ሳምንት በኋላ ስመለስ ሰምቼ ቆጨኝ ግን ፃፍኩለት፡፡ ከጥቂት መፃፃፍ በኋላ የአየር ትኬት መጣልኝ፡፡ ፓስፖርት ለማውጣት መከራ ነበር፡፡ በኋላ ኤምባሲ ስሄድ ቪዛ ሰጪው “ለምንድነው የምትሄደው? ማነው የሚወስድህ” ብሎ ሲጠይቀኝ፤ ሦስቱን ጋዜጠኞች ጠቀስኩለት፡፡ ሰዎቹ በእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በጣም ታዋቂ ናቸው፡፡ ጓደኞቼ ናቸው ስለው ደነገጠ፡፡ አድራሻቸውን ከሰጠሁት በኋላ፣ ቴሌግራም ተላልኮ ተፈቀደልኝ፡፡ አባቴ በሬ ሸጦ ነው ወደ እስራኤል የላከኝ፡፡
በንጉሡ ጊዜ ከሀገር መውጣት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ገና ታዳጊ ወጣት ነበርኩ፡፡
የእስራኤል መንግሥት ደግሞ ያኔ ለቤተእስራኤላውያን እውቅና ባለመስጠቱ ይሁዲ ነኝ ብልም አልተቀበሉም፡፡ እሱም አስቸጋሪ ነበር፡፡
ቤተእስራኤላዊነትን ካነሳን አይቀር የብዙ መቶ ዘመን ዘር ቆጥሮ ቤተእስራኤላዊ ነኝ ማለት አያስቸግርም?
አያስቸግርም፡፡ የምኒሊክ ዘር ነኝ፣ የካሌብ ዘር ነኝ እንደሚባለው ቤተእስኤላዊነትም በታሪክ የተመሰረተ ነው፡፡ ሐይማኖታችን በራሱ አንድ ማስረጃ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ጠብቀን ቆይተናል፡፡ ቤተእስራኤላውያን ኢትዮጵያ የገቡት ሦስት ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው በቀዳማዊ ምኒሊክ ጊዜ ነው፡፡ ሌላው ከየመን በአፄ ካሌብ ጊዜ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ሦስተኛው የሰሎሞን ቤተመቅደስ በወራሪዎች በወደመችበት ጊዜ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ይሁዲ ነገሥት መካከል ዮዲት እና ጌድዮን ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ብሉይ ኪዳን እስራኤልን “ማርና ወተት የምታፈስ” ሀገር ይላታል፡፡ እዚያ የገቡ ቤተእስራኤላውያን “ማርና ወተት የምታፈስ” እስራኤል አገኙ?
ልክ በመፅሐፍ ቅዱስ እንደተባለው ማርና ወተት የምታፈስ፣ በሽታና ችግር የሌለባት፣ የተረጋጋች፣ ሞት የሌለባት አድርገው የሚቆጥሩ የተሳሳተ እምነት የነበራቸው ቤተእስራኤላውያን ነበሩ፡፡
በሱዳን በረሃ ማንም ሳያስገድዳቸው ተጉዘው እስራኤል ሲደርሱ ዛፍ የማይበዛበት ምድረበዳ፣ በአካባቢዋና በውስጧ ጦርነት ያልተለያት ሀገር ነው ያገኙት፡፡ በዚያ ላይ የቋንቋና የባህል ችግር ይገጥማል፡፡ ያሰቡትን ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ለወጣት ቤተእስራኤላውያን ግን ቋንቋና ባህሉን ቶሎ ስለሚለምዱ ሀገሪቷ የተሻለች ነች፡፡
ቤተእስራኤላውያን የነጭ እስራኤላውያን የዘር መድልዎ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የዘረኝነቱ ምንጭ ምንድን ነው?
መሰረቱን ያጠናከረ ዘረኝነት በሀገረ እስራኤል አላየሁም፤ ያ ማለት ዘረኝነት የሚያራምዱ ቡድኖችና ግለሰቦች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የእስራኤል መንግስት ዘረኛ መንግስት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ለምሳሌ የባርያ ንግድ ሕጋዊ ሆኖ በመንግስት የሚደገፍበት ወቅት ነበር፡፡
ከዚህ የሄዱ መድልዎ እንደሚደርስባቸው እንሰማለን…
ነገርኩህ እኮ፡፡ ከዚህ ሲሄዱ ከነባህላቸው ነው የሚሄዱት፡፡ ባህላቸውን አየር ማረፊያ ወይም ጉምሩክ አያስረክቡም፡፡
እስራኤል ሄደው እንጀራ ሲጋግሩ ጠረኑ ከሩቅ ይሸታል፡፡ ነጮች ጐረቤቶቻቸው የዚያ ባህል የላቸውም፡፡
ወጡ ጨውና ቅመም የበዛበት ስለሆነ እሱም እንደ እንጀራው ነው፡፡ በድግስ፣ በሰርግ ጊዜ አሸሼ ገዳሜውን፣ አሃ ገዳሆውን ያስነኩታል፣ እልልታ ይቀልጣል፡፡
አሸበል ገዳዬ ነው፡፡ የሰአት ገደብ የለም መጨፈር ነው፡፡ ፈረንጅ የሰአት ገደብ አለው፡፡ ሁካታው ሲረብሻቸው ይበሳጫሉ፡፡ ያን ይዘን እኛ ነጮቹን ዘረኛ እንላለን፡፡ መበሳጨት የባህርይ እንጂ የዘር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የበለፀገች አገር ብትሆን ኖሮ ቤተእስራኤላውያን ወደ እስራኤል ይጓዙ ነበር ትላለህ? ምናልባት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ቢሆንስ…
ወደ እስራኤል የተጓዙት ሃይማኖቱን በደንብ የሚጠብቁበት፣ ይሁዲነታቸውን የሚያጠነክሩበት ሀገራቸው ስለሆነች ነው፡፡ በ1960ዎቹ ከኢራቅ 120ሺህ ይሁዲዎች በ”ዘመቻ እዝራ” ወደ እስራኤል ተጓጉዘዋል፡፡ በ”ዘመቻ የሂን” ከሞሮኮ፣ በ”ዘመቻ ተአምረኛ ምንጣፍ” ከየመን ይሁዲዎች እስራኤል ገብተዋል፡፡ ያለና የነበረ እንጂ እንደተአምር አይቆጠርም፡፡
እስራኤል የዛሬ ስልሳ አምስት አመት ስትመሰረት ምጣኔ ሀብቷ ደቃቃ ነበር፡፡
ያኔም ዜጐቿ ወደ ሀገሪቱ ገብተዋል፡፡ በሕገመንግስቷ ላይ፤ “እስራኤል ሀብታም ድሃ፤ ጥቁር ነጭ ሳትል ልጆቿን ትጠራለች” ይላል፡፡
በ”ዘመቻ ሰሎሞን” ቤተእስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለማውጣት ዘምተሃል፡፡ ስለዚህ የምታስታውሰውን ብትነግረን…
“ዘመቻ ሙሴ” ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1977 ተካሄደ፡፡
“ዘመቻ ሰሎሞን” ከስድስት አመት በኋላ በ1983 ተካሄደ፡፡ “ዘመቻ ሙሴ” ዓላማው ሰዎቹን ከየትኛውም የመከራ ቦታ ማውጣት ነበር፡፡
በጀርመን ናዚዎች በይሁዳውያን ላይ ከተደረገው ጭፍጨፋ አንፃር ማንኛውም ሀገር ያለ ይሁዲ መጠጊያ እንድትሆን ነው እስራኤል የተመሰረተችው፡፡ በዚህ ሀሳብ የተነሳ በ”ዘመቻ ሙሴ” በሱዳን አቋርጠው እስራኤል ለመግባት ያሰቡ ብዙ ሰዎች በረሃ ላይ ሞተዋል፡፡
ያኔ የእስራኤል መንግሥት ምን አደረገ?
ሱዳን የእስራኤል ወዳጅ አይደለችም ሆኖም እስራኤል ሱዳን የሰፈሩ ዜጐቿን ለማሸሽ ተግታለች፡፡ በሰላሳ ሁለት በረራዎች ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ሰው አውጥተናል፡፡ በግምት ሦስት ሺህ ሰዎች ሞተዋል ይባላል፡፡ ሰሞኑን ጥናታዊ ምዝገባ እየተካሄደ ነው፤ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅና ለመዘከር፡፡
“ዘመቻ ሰሎሞንስ?”
በዚያ ዘመቻ በንቃት ተሳትፌአለሁ፡፡ በግንቦት 1983 የተካሄደ ነው፡፡
ወደ ሱዳን ያልሄዱት አዲስ አበባ መጥተው ተሰባሰቡ፡፡ እስራኤልና የደርግ መንግሥት ግንኙነት አሻሽለው የእስራኤል ኤምባሲ ከተከፈተ ሁለት አመቱ ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ ካሳ ከበደ ዋነኛ ተዋናይ ነበሩ በጉዳዩ፡፡ ከመንግሥት ጋር እየተደራደርን ተቃዋሚዎች እየገሰገሱ መጡ፡፡ ዘመቻው ሊካሄድ ጫፍ ላይ ሲደርስ ነው ይኼ መንግሥት የመጣው፡፡ ሲአይኤም መጣ፤ ያኔ ወያኔ ይባሉ የነበሩት ታጋዮች “ቆዩን፣ አዲስ አበባ አትግቡ” ተባሉ፡፡ ቤተእስራኤሎች በኬንያ ወጡ፡፡
ኢትዮጵያ ለሃያ አራት ሰዓት ያለምንም መንግሥት ቆየች፡፡ ከአርብ ጠዋት እስከ ቅዳሜ ከሰአት አስራ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሰዎች ቦሌ ላይ ሲጫኑ ነበርኩ፡፡ እስራኤል ተአምር ሰራች፡፡ የዚያን ቀን ቦሌ ያለ አውሮፕላን ሁሉ የእስራኤል ነበር፡፡ የማንም የሌላ አልነበረም፡፡
ሰዎች በወቅቱ እንደ ካርጐ ተጭነው ነው የሄዱት…
አዎ፡፡
በጉዞ ወቅት ችግር አልገጠመም?
የአውሮፕላን ወንበሮች ተነስተው እንደ ባዶ አዳራሽ ነው የገቡበት፤ ባንዴ ብዙ ሰው ማሳፈር እንዲቻል፡፡ አንድም ችግር አልገጠመንም፡፡ ባይደንቅህ ሰባት ሕፃናት አውሮፕላን ላይ ተወልደዋል፡፡
ስለ ጋዜጠኝነትህ ደግሞ ንገረኝ…
በእስራኤል ብሔራዊ ሬዲዮ ለ28 አመት ሰርቻለሁ፡፡ አሁንም እሰራለሁ፡፡ በህትመት ሚዲያ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሰራሁት፡፡ ሁለት መፃህፍት ፅፌአለሁ፡፡
አንድ የአማርኛ እብራይስጥ መዝገበ ቃላትም አዘጋጅቼአለሁ፡፡ ሦስት ፊልሞች ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ተማሪ ሳለሁ “ቤተሰቦቻችን ይምጡልን” ከሚሉ አድማ መቺዎች ቅድሚያ ተሰላፊ ነበርኩ፤ የአድማ መሪም ነበርኩ፡፡
ከአዲሷ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ጋር ለመሾም እንዴት ተወዳደርክ?
ከሳቸው ጋር አይደለም የተወዳደርኩት፡፡
ወይዘሮ በላይነሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ናቸው፡፡ እኔ አይደለሁም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስራ አንድ አምባሳደር መሾም ስለሚችሉ አንድ የመ/ቤታቸው ባልደረባ የሆነ ትውልደ ሩስያዊውን በሞስኮ አምባሳደርነት ሾሙ፡፡ ይሄኔ ለአማካሪያቸው “ኢትዮጵያዊ አምባሳደር በኢትዮጵያ ቢሾሙ ታሪክ ነው” ብዬ እንደቀልድ ተናገርኩ፡፡ ቆይቶ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተወዳደርኩ፤ ተመርጠሃል ተብዬ ለሹመቱ ታጨሁ፡፡ ግን በተለያየ የግል ምክንያት አምባሳደር ሳልሆን ቀረሁ፡፡
ከዚህ የሚሄዱ ቤተእስራኤላውያን “ዝቅተኛ” ሥራ ላይ ነው የሚመደቡት ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ችግሩ አለ፡፡ አንደኛ ከመነሻው ትምህርታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዜሮ ነው በብዛት የሚጀምሩት፡፡ ሌሎች በጨረሱት ትምህርት ልክ ስራ ያላገኙም አሉ፡፡ ይኼ በነጮቹ ላይም የሚታይ ቢሆንም ከዚህ የሄዱት ሥራ አጦች ቁጥር ይበዛል፡፡ ጠንካራ ሰው ብዙ አላፈራንም፡፡ በውትድርናም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የመኖራቸውን ያህል በራሳቸው ላይ አደጋ ያደረሱም አሉ፤ ተስፋ ቆርጠው፡፡
ለምሳሌ ታሚር አላዛር የሚባል የወንድሜ ልጅ ሌተና ጀነራል ሆኗል፡፡ የታናሽ እህቴ ልጅ ሻለቃነት ደርሳለች፡፡ ሌላውም ዘመዴ ሻለቃ ነው፡፡ ብዙ ጠንካራና ታማኝ ወታደሮች አሉን፡፡ ስራ የሚያፈላልግላቸው በማጣት ነው ብዙዎቹ ዝቅተኛ ሥራ የሚሰሩት፡፡ የዘር መድልዎ የሚመስል ነገር አለ፡፡ የለየለት የዘር ጭቆና አለ ብሎ መደምደም ባይቻልም፡፡
ጋዜጠኛ ከመሆንህ በፊት ምን ሰርተሃል?
የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ማህበር ሊቀመንበር ነበርኩ፡፡ ማህበሩ ስሙን ቢቀያይርም አሁንም አለ፡፡
ከሁለቱ ትልልቅ የእስራኤል የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሌበር እና ሊኪውድ) ቤተእስራኤላውያን ለየቱ ያደላሉ?
አብዛኞቹ ለሊኪውድ ፓርቲ ያደላሉ፡፡ ሌበር ፓርቲ ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ ሰላም በእስራኤል የመጣው ግን በሊኪውድ ጊዜ ነው፡፡ ከግብፅ ጋር ተደራድሮ፤ በሜናሂም ቤጊን አማካይነት፡፡
በጋዜጠኝነትህ ያነጋገርካቸው መሪዎች አሉ?
ሚናሂም ቤጊን አነጋግሬአለሁ፡፡ ኢዛቅ ሻሚርን፣ ሺሞን ፔሬዝን አነጋግሬአለሁ፡፡ በቃለምልልስ አይሁን እንጂ ኢዛቅ ራቢንን ብዙ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡
ከመሪዎች ማንን ታደንቃለህ?
ሜናሂም ቤጊን በጣም ትሁት ናቸው፤ በዚህ አደንቃቸዋለሁ፡፡ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሳያደርጉ በትንሽ ቤት የኖሩ ናቸው፡፡ ሃብት ያላካበቱ ለደካማ ህዝብ አሳቢ ነበሩ፡፡ እስራኤልን የመሰረቱት ከአውሮፓ የሄዱ ይሁዳውያን እና በአካባቢው አረብ ሀገራት የነበሩ ዜጐች ነው፡፡ ከአውሮፓ የሄዱት እነዚያን ዝቅ አድርጐ የማየት አዝማሚያ ነበር፤ አሁንም አለ፡፡ ከኢትዮጵያ የሄድነውን በሦስተኛ ደረጃ የሚያዩን ነበሩ፡፡ ቤጊን ይሄ እንዲቀር ጥረዋል፡፡ ሌላው ሻሚር ናቸው፡፡ እሳቸውን የማደንቀው ላመኑበት ቁርጠኛ ስለሆኑ ነበር፡፡
በአቋማቸው እገሌ ምን ይለኛል አይሉም፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሆ የታይታ ሰው ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ራቢን የሰላም ሰው በመሆናቸው አደንቃቸዋለሁ፤ ለሀገራቸው መስዋእት ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ሻሚርም መስዋእት ሆነዋል፡፡ ኤርያል ሻሮንን በወታደራዊ መስክ አደንቃለሁ፤ በፖለቲከኛነታቸው አላደንታቸውም፤ ብዙ ነገር አበለሻሽተዋል፡፡ ሞሼ ዳያንን በአርበኝነቱና በወንዳወንድነቱ አደንቀዋለሁ፤ ግን ማን አለብኝነት ያጠቃው ነበር፡፡
ከኢትዮጵያስ መሪዎች?
አስቸጋሪ ጥያቄ አመጣህ፡፡ እዚህ ሀገር ተወልጄ እትብቴ ቢቀበርም የመምረጥ የመመረጥ መብት የለኝም፡፡ ለሕዝባቸው ተቆርቋሪ ስለነበሩ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን አደንቃለሁ፡፡ ልጅነታቸውንና ጐልማሳነታቸውን ያሳለፉት ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከሁለት ሦስት ሺህ አመት እንቅልፏ ያነቋት መለስ ናቸው፡፡ ሰው ሲሞት ያን ያህል አላለቅስም፤ መለስ ሞቱ ሲባል ግን እንባዬን ጠብ አድርጌ አልቅሻለሁ፡፡ ሰው በመሆኔ አልቅሼላቸዋለሁ፤ ኢትዮጵያዊ መሆን አይጠበቅብህም፡፡
ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥህ እንዴት ነው? በሥራ ነው ወይስ…
ሀገር ለማየት ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅና እንዳንተ ያለ ጓደኛ ለማፍራት ነው የመጣሁት፡፡ መሬት በሊዝ ተመርቻለሁ፤ እስራኤል ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አደራጅቶን ነው ለመኖርያ ቤት የተመራነው፡፡
እስራኤል ሲባል ፊትህ ድቅን የሚልብህ ምንድነው?
ቆራጥነቷና በምትሰራው ጀብዱ የምታስገኘው አመርቂ ውጤት!
ምረጡኝ ብዬ አላልኹም፤ ምረጡኝ ብዬ አላውቅም
- ፓትርያሪክ እንድሆን የመንግስት ባለሥልጣን አላግባባሁም
- ‹ካህናትና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያንና ለቤተ ክርስቲያን ብለው ብቻ ማሰብ፣ ይገባቸዋል›› - /ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል/
አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሞተ ሥጋ ከተለዩ ስድስት ወራት ተቆጠሩ፡፡ ከፓትርያርኩ ኅልፈት በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት ስድስተኛው ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክነት ተሠይመው ቤተ ክርስቲያኒቱን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ ለማስፈጸም ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመው የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለብዙኀን መገናኛ ይፋ ባደረገው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት፤ ከየካቲት 9 - 14 ቀን 2005 ዓ.ም አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች ሲመርጥና ሲያጣራ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚያርቀርብ ታውቋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ከዛሬ ጀምሮ በሚያካሂደው ውይይት የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚከናወነው ምርጫ በዕጩነት በሚቀርቡት አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አሳልፎ የዕጩዎቹን ዝርዝር ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
የምርጫው ሂደት በይፋ ከተጀመረ አንሥቶና ከዚያም በፊት ቀጣዩ ፓትርያሪክ እንደሚኾኑ ብዙ ከተነገረላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አንዱ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በፓትርያሪክነት ምርጫው ከሚሳተፉ ከ800 በላይ መራጮች የምርጫ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሥልጠና ስም በርካታ ገንዘብ ማውጣታቸውን፤ በሕንፃ ኪራይ፣ በሥራ ምደባ፣ በውጭ ተልእኮና በሹመት አሰጣጥ ለብዙዎች ቃል መግባታቸውን፤ ከዚህም አልፎ ቀጣዩ ፓትርያሪክ እርሳቸው እንደሚኾኑ ራሳቸውን ለመንግሥት አካላት ስለ ማስተዋወቀቸው በአንዳንድ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡
በእኒህ ጉዳዮች ላይ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን አስተያየት ከራሳቸው አንደበት ለመስማት የአዲስ አድማስ ሪፖርተር ሰላም ገረመው ከብፁዕነታቸው ጋር አጭር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡
በያዝነው ዓመት በኮሚሽኑ ድጋፍ ለአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች የተሰጡ ሥልጠናዎች፣ በአዲስ አበባ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተደረጉ የልምድ ልውውጦች ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋር በተያያዘ ለብፁዕነትዎ ድጋፍን የመሸመት ዓላማ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ የተሰጠው ሥልጠና ምን ነበር? ዓላማውና የበጀት ምንጩስ?
ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ ልኡካን ጋር የተደረገው የልምድ ልውውጥና የተሰጠው ሥልጠና፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከግብጹ ፖፕ አቡነ ሺኖዳ ጋር ቀድሞ በደረሱበት ስምምነት መሠረት የተፈጸመ፣ ነገር ግን ዘግይቶ የተፈጸመ ስለኾነ እንጂ ከፓትርያሪኩ ኅልፈት በኋላ የታቀደና ለምርጫ ድጋፍ ቅሰቀሳ የታሰበ አይደለም፤ በቀጣይም ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት ለምሳሌ ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተመሳሳይ መድረኮች የመገናኘት ዕቅድ አለን፡፡
ለአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና ሌሎች ሓላፊዎች በጥቅምት ወር ከሀገር አቀፉ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጋር ተያይዞ የተሰጠው ሥልጠና አምናም በተመሳሳይ ወቅት የነበረ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም ጥቅምት ወር ፓዝፋይንደር ኢትዮጵያ በሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በሥነ ተዋልዶና የሴት ልጅ ግርዛት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ተሰጥቷል፡፡
በዚህ ዓመት ‹‹ዳቦ ለዓለም›› በተባለ ገባሬ ሠናይ ድርጅት ድጋፍ በአቅምና የሰላም ግንባታ ጭብጥ ዙሪያ በታቀዱ በርካታ ርእሰ ጉዳዮች ላይ በመስኩ ባለሞያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ዋና ዓላማው በቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲጠናከር፣ ፍትሕ እንዲሰፍንና የልማት አቅም እንዲፈጠር ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫው ስላለ ወይም ከምርጫው ጋር ተያይዞ የታቀደ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡
ለሥልጠናው ተሳታፊዎች በአበል መልክ እንደተጨማሪ ክፍያ ወጥቷል የተባለው 500,000 ብርና የበጀት ምንጩስ?
የዚህ ዓመት ሥልጠና የበጀት ምንጩ እንደተናርኹት እኛው ቀርጸን ለ‹‹ዳቦ ለዓለም›› (Bread For the World) ገባሬ ሠናይ ድርጅት ባቀረብነው ፕሮፖዛል መሠረት የተገኘ ገንዘብ ነው ለሥልጠናው ማስፈጸሚያና ለአበል የተከፈለው፡፡ ይህም በየዓመቱ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ፕሮፖዛል እየቀረጽን፣ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችን እየጠየቅን ስንሠራው የቆየና ለወደፊቱም የሚቀጥል ነው፡፡ ለሥልጠናው ወጭ የተደረገው ገንዘብ ለአፋርና ለሶማሌ ክልሎች ለሚሠሩ የልማት ፕሮጀክቶች የተገኘ ገንዘብ ነበር ለተባለው በክልሎቹ ለምንሠራው ሥራ ድጋፍ ያገኘነው ከተመድ የስደተኞች ማእከል (UNCR) ነው፤ ገንዘቡንም የሚቆጣጠረው ራሱ ማእከሉ ነው፡፡ ስለዚህ ከሥልጠናው ወጪ ጋር አይገናኝም፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ÷ ሹመት እንደሚሰጣቸው፣ በሥራ እንደሚመደቡ፣ በሕንጻ ኪራይ፣ በውጭ ዕድል ቃል የተገባላቸው መራጮች አሉ ተብሏል…
ለመሾምም፣ ሕንጻ ለማከራየትም፣ በሥራ ለመመደብም፣ ወደ ውጭ ለመላክም ሥርዐት አለው፡፡ ከተጠቀሱት የትኛውም ነገር ከሥርዐት ውጭ እንዳይፈጸም ተከፍቶ የነበረው መንገድ ተዘግቷል፡፡
በሌላ በኩል የፓትርያሪክ ምርጫ መንፈሳዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ፕትርክናውን ለማግኘት ማሰብና መሞከር ሕግም አይፈቅድም፡፡ ይህ የሥልጣን ስግብግብነት ነው፡፡ መራጮቹስ እነማን እንደኾኑ በስም ይታወቃሉ ወይ? ይህን አሉባልታ ያመነጩትና የሚያስተጋቡት የምርጫውን ሂደት ለማወናበድ፣ ሕጋዊውን አሠራር ወደ ቤተሰባዊነት፣ ዘረኝነትና አድሏዊነት ለመውሰድ ማመኻኛ የሚሹ ሕገ ወጥ ቡድኖች ናቸው፡፡
ስድስተኛው ፓትርያሪክ ኾነው እንዲመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተ ክህነት አመራሮችንና ታዋቂ ግለሰቦችን አግባብተዋል? ስለጉዳዩ ላይ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትችት እንደሰጡ ተዘግቧል።
ምረጡኝ ብዬ አላልኹም፤ ምረጡኝ ብዬ አላውቅም፡፡ ይህን አድርገኻል የሚሉኝ ወገኖች እውነተኛ ከኾኑ መረጃውን ለምን አያቀርቡም? የቤቱን [የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን] ዕድገት፣ ልማትና መሻሻል ርምጃዎች ሲያኮላሹ የነበሩ ሰዎች ስሜት ነው፡፡
የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማግባባትዎና ‹‹መንግሥት ፓትርያሪክ ኾኜ እንድመረጥ ይፈልጋል›› እያሉ ማስወራትዎ. . .
ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል፤ በየትኛውም አቅጣጫ የተለያዩ አካላት ብዙ ሊናገሩ ይችላሉ፤ ይህንንም የሚሉት የቤታችንን የዕድገትና ልማት ርምጃ ሲያኮላሹ የነበሩ ግለሰቦችና አሁን ደግሞ በምርጫው ዙሪያ የተደራጁ ቡድኖች ናቸው፡፡
ፓትርያርክነት የአባትነት፣ የቡራኬ ሥልጣን ነው፤ ለእኔ አገልጋይነት ይሻለኛል፤ አገልጋይ መኾን ነው እንጂ፤ አገልጋይነት÷ ሃይማኖትን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ሕዝብንና እግዚአብሔርን በማእከል ኾኖ ማገናኘት እንጂ አዛዥ፣ ገዥ፣ አሳሪ፣ አሳሳሪ መኾን አይደለም፡፡
ለመኾኑ እንዴት ነው የፓትርያሪክነት ሥልጣን ይሰጠኝ ብዬ የምጠይቀው? ሹመቱ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ነው፤ ሥርዐቱ የሚፈጸመው በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ በፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንቡ መሠረት ነው፤ ሕጉን፣ ሥርዐቱን የሚፈጽመውና የሚያስፈጽመው ቅዱስ ሲኖዶሱና ሕዝቡ እንጂ መንግሥት አይደለም፤ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት ምን መኾን እንደሚገባው በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ያግባባኹትም የጠየቅኹትም የመንግሥት አካል ይኹን ባለሥልጣን የለም፡፡
በምርጫው የሚሳተፉ ካህናትና ምእመናን ለሚኖራቸው ድርሻ እርስዎ ምን ይላሉ? በምርጫው ዙሪያ ይካሄዳል ስለሚባለው የቡድኖች እንቅስቃሴስ?
በየብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ቤት፣ በእኔም ቤት ሳይቀር እየዞሩ እገሌን ካልመረጣችኹ፣ ካላስመረጣችኹ የሚሉ አካላት እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ሥልጣን ባለው አካል መንፈሳዊ ሥልጣንን ለመያዝ የሚደረገው ሽር ጉድ ሁሉ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው፤ ይህን የሚያደርጉ አካላት በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ይጠየቃሉ፡፡ እንዲህ ኾኖ የሚሾመው አባትም ቢኾን ሢመቱ ሥጋዊ ሹመት ይኾንና በነፍስም በሥጋም ያጎድለዋል፤ ያለጊዜውም ሊያሥቀስፍ ይችላል፡፡
ስለኾነም በምርጫው የሚሳተፉ ካህናትና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያንና ለቤተ ክርስቲያን ብለው ብቻ ማሰብ፣ መወሰንና መቆም ይገባቸዋል፡፡
በፍርሃትና በጩኸት እንደ እያሪኮ ግንብ የምፈርስ አይደለሁም”
(ወ/ሮ ሙሉ ሠለሞን፤ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት)
በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ኢምፖርት ኤክስፖርትና የችርቻሮ ኮርፖሬሽን ውስጥ ነው ስራ የጀመሩት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፀሐፊነት አገልግለዋል በቢዝነስ ቢኤ ዲግሪ፣ በኢንቫይሮመንትና ዴቨሎፕመንት ማስተርስ ያላቸው ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፤ አሁን ደግሞ በሊደርሺፕና ኢንተርፕሪነርሺፕ ፒኤችዲያቸውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ “ራይት ቪዥን” የተባለ ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ፤የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በንግስተ ሳባ ሆቴል በነበራቸው ቀጠሮ በሥራና ተመክሮ፣ በስኬትና ፈተና፣ በህይወትና ራዕያቸው ዙሪያ ያደረገችው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንትነት ያደረጉት ውድድሩ እንዴት ነበር?
በመሠረቱ ምክር ቤቱን ቀደም ብዬም አውቀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ቻምበርን በዳይሬክተርነት አገልግያለሁ፡፡ በበጐ ፈቃደኝነት በተለያዩ ማህበራት ውስጥም ሰርቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የራሴ ስራ ላይ ላተኩር ብዬ ባሰብኩበት ሰዓት ነው ወደዚህ ውድድር የገባሁት፡፡ አዲስ አበባ ቻምበር ዳይሬክተር የሆንኩት በከፍተኛ ድምጽ ተመርጬ ነው፡፡ እንደውም ፕሬዚዳንት እንድሆንም ብዙ ግፊቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም በግሌ የምመራቸውና የምሠራቸው በርካታ ነገሮች ስለነበሩ በወቅቱ ጥያቄውን አልተቀበልኩም፡፡
የሆነ ሆኖ እኔ የአዲስ አበባ ቻምበር ዳይሬክተር ሆኜ ከ1997 ምርጫ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ቀውስ ከሱቆች መዘጋትና ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር በተገናኘ ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ ሱቆችን ከማስከፋት ጀምሮ አጠቃላይ የንግዱ ማህበረሰብ ወደቀድሞው መረጋጋትና የንግድ ሥርዓት እንዲገባ፣ነጋዴው በራሱ ካጠፋ እንዲጠየቅ፣ነገር ግን ድርጅቶቹ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የማድረግ ፈታኝ ወቅት አሳልፈናል፡፡ ያ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የተወዳደርኩት ያለ አንዳች ተቃውሞ ሲሆን እንድወዳደር ፈርመው ነው የኔን ስም የላኩት፡፡ ነገር ግን እኔ ብዙ የራሴ ሥራ አለኝ፡፡ የአዲስ አበባውን አገልግያለሁ፡፡ ያላገለገሉ ስላሉ እነሱ ይወዳደሩ ብልም ጫናው በዛ፡፡ ምናልባት አንድም ሁለትም አመት አገልግለሽ ብትተይው ይሻላል፣ይሄ ሁሉ ሰው ያለ አንዳች ተጣባባቂ አንቺን አምኖ ሲያወዳድር እንዴት እምቢ ትያለሽ--- የሚል ጫና በረታና ተወዳደርኩኝ፡፡ በዚህ ደግሞ ሌላ ጫና ገጠመኝ፡፡
ምን ዓይነት ጫና?
ምን መሰለሽ? የበፊቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ መቀጠል ይፈልጉ ነበር መሠለኝ ከየአቅጣጫው በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያው በዛ፡፡ በአካልም መጥተው አርፈሽ ተቀመጪ፣ ቦታውን ስለሚፈልጉት ከውድድሩ ራስሽን አግልይ ያሉኝ ነበሩ፡፡ በስልክም የማላውቃቸው ሰዎች “አርፈሽ ልጆችሽን አሳድጊ” ይሉኝ ነበር፡፡ ማንነታቸውን ግን አይገልፁም፣ እኔ ደግሞ በጩኸትና በፍርሃት እንደ እያሪኮ ግንብ የምፈርስ አይነት ሰው አይደለሁም እና ጉዳዩ የበለጠ እንድፀና አደረገኝ፡፡ ለምሣሌ ሚዲያ ተቋሙንም የጋዜጠኞችንም ሥም መጥቀስ ባልፈልግም ሴት ጋዜጠኞች ማበረታታት ሲገባቸው ያቀርቡልኝ የነበረው ጥያቄ የንቀትና የማስፈራራት አይነት ነበር፡፡
እስቲ ከእርስዎ ጋር የተወዳደሩትን ሰዎች ይንገሩኝ----
ለውድድር የቀረብነው አራት ሰዎች ነን፡፡ አንደኛው ተወዳዳሪ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ናቸው፡፡ አባልነታቸው አዲስ አበባ ቢሆንም ከአዲስ አበባ አልተወከሉም፡፡
ህጉም የሚለው ካለሽበት ክልል ተወክለሽ ነው የምትወዳዳሪው፣ካለሽበት ክልል ተወክለሽ ግን የትኛውም ክልል ሊመርጥሽ ይችላል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ የተጠቆሙት ከሌላ ክልል ነበር፣ይህም የምርጫው ቀን ጭቅጭቅ አስነስቶ ነበር፡፡ ሌላው ጌታቸው አየነው ከአማራ ክልል ነበር፣ሶስተኛው የማላውቀው ሰው ነበር - ለውድድሩ አልቀረበም፣ እኔ አራተኛ ነኝ፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንትነትና ለቦርድ አባልነት የሚወዳደሩም ነበሩ፡፡ ለውድድሩ ንግግር ስናደርግ ከአማራ ክልል የመጣው ራሱን አገለለ (ሪዛይን አደረገ)፣ አንደኛው መጀመሪያውኑም አልመጣም፣ ስለዚህ እኔና አቶ ኢየሱስ ወርቅ ብቻ ቀረን፡፡ እዛ ውድድር ላይ ቀድሞ የተሠራ ሥራ እንደነበር ፍንጮች ነበሩ እናም በሻይ ሰዓት “እናንተ በቃ ሴት አትመርጡም አይደል” እያልኩ እቀላልድ ነበር፡፡
ቀደም ብሎ የተሠራው ስራ ምንድን ነው?
እሣቸውን ለመምረጥ ተማምለው የመጡ እንደነበሩ መረጃ አለኝ፣በአንደበታቸውም ይህንኑ የነገሩኝ አሉ፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ እዚህ ተወዳድሮ በመመረጥ እንጂ በሌላ ሌላው አላምንም፣ መሆንም የለበትም፣ ስለዚህ ውድድሩ ቀጠለ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ተጀምሮ 10፡00 ሰዓት ማለቅ የነበረበት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ማለቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጫናና ፍትጊያ ነበር፡፡ ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሰዎችም ነበሩበት፡፡ የሆነ ሆኖ እርሳቸው ንግግር አድርገው ሲጨርሱ እኔ በተራዬ ንግግር ካደረግኩ በኋላ አብላጫው ሰው ፊቱን ወደኔ አዞረ፡፡
ድምጽ ተቆጥሮ አሸናፊው እስከሚነገር ከአንድ የማላውቃቸው የክልል ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር ስናወራ “እኛ አንችን አናውቅሽም ስለዚህ የምናውቀውን ለመምረጥ ስምምነት ነበረን፡፡ ነገር ግን ንግግር ስታደርጉ ሁሉም ወዳንቺ ተገለበጠ” አሉኝ፡፡
ሌሎችም እንዲሁ ወንዶችም ሴቶችም ንግግሬን እስኪሰሙ አቋማቸው የእኒህ ሰውዬ አይነት እንደነበር ነግረውኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ያሸነፍኩት፡፡ እኔ 132፣ እሣቸው 62 ድምጽ ነበር ያገኘነው፡፡
ምን አይነት ንግግር ቢያደርጉ ነው መራጮችን መማረክ የቻሉት?
እኔ የተናገርኩት ብዙ ከባድ ንግግር አይደለም፡፡ ምን አልኩ መሰለሽ? “እኔ እንደ ድሮ ፓርላማ - መንገድ አሠራላችኋለሁ፣መብራት አስገባላችኋለሁ አልልም፡፡ ከአዲስ አበባም ልመረጥ ከሌላም ልወከል ለላከኝ ክልል ወይም ቻምበር ሳይሆን ለሁላችሁም የኢትዮጵያ ማህበር አባላት በቀናነት አገለግላለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ከተወከለች ለእኛ ትሠራለች ለዚህኛው ወገን በቅርበት ትሠራለች የሚል የተከፋፈለ ሃሳብ ካላችሁ አትምረጡኝ፡፡ ለእውነትና ለሃቅ ፊት ለፊት የምጋፈጥ ስለመሆኔ ታውቃላችሁ” ከዚህ በላይ ብዙ መናገር አላስፈለገኝም ነበር፡፡
የሃላፊነት ቦታው ግን እስካሁን ድረስ ከሽኩቻ እንዳልፀዳ ይነገራል------
በፊት የነበሩ ሰዎች መቀጠል ነበረብን የሚል ቁጭት አለ፣ አሁንም የሷን ስራ እናበላሻለን ይላሉ፣ የኔ ሳይሆን የመንግስትና የህዝብ ስራ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገራቸው የበለጠ እንድንሰራ ያደርገኛል እንጂ አያሰንፈኝም፡፡
የድሮ ሰው ምቀኛ አታሳጣኝ የሚለው ለምን ይመስልሻል፡፡ ሰው ሲቃወምሽ አንዳንዴ ስህተትሽንም ትመለከቻለሽ፣በጭፍን ጥላቻ የሚያወራብሽም ከሆነ ዘግተሽው ስራሽን ትቀጥያለሽ አለቀ፡፡ በወሬ ጊዜያቸውን ባያባክኑ ግን ደስ ይለኛል፡፡ እኛ በአሉባልታ ጊዜ እንድናባክን ይፈልጋሉ፣እኛ ለወሬ ጊዜ የለንም አለቀ፡፡ ሥራ ላይ ነን፡፡ ለውጥ ላይ ነን፡፡
አሸንፈው ሃላፊነቱን ሲረከቡ በቅድምያ የጠበቅዎት ስራ ምን ነበር? እስካሁንስ ምን አከናወኑ?
ብዙ ሊስተካከሉ የሚገቡ ሥራዎች ሊጠብቁሽ ይችላሉ፡፡ አንድ አገርኛ አባባል ልንገርሽ፡፡ የዱሮ ባሎች የመጀመርያ ሚስት ፈትተው ሌላ ሚስት ሲያገቡ፣ አዲስ የተገባችው ሴት የመጀመሪያዋ የሠራችውን መደብ አፍርሳ ከዛ የባሰ የተበላሸ መደብ ትሠራለች ይባላል፡፡ እሷ ያንን የምታደርገው ከጀመሪያዋ የተሻልኩ ነኝ ለማለት ነው፡፡ እኔ እንደ አዲሷ ሚስት ያለ አመለካከት የለኝም፡፡ አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላትም ጭምር፡፡ እከሌ በነበረበት ጊዜ ይህን አላደረገም ይህን አበላሽቷል ብሎ የማጣጣል ፍላጐትም ሃሳቡም የለንም፡፡ በነበረው አሠራር ጥሩ ነው ያለውን እንቀጥልበታለን፡፡
የተበላሹ ካሉ እያስተካከልን የመሄድ ሃሳብ ነው የነበረን፡፡ በጣም የሚገርምሽ የምርጫው ዕለት እኔ ሳሸንፍ ህዝቡ “ሳዳም ወረደ፤ጋዳፊ ወረደ” እያሉ ሲጨፍሩ ሊቀመንበሩ ማስቆም አልቻሉም ነበር፡፡ እኔ ድምጽ ማጉያውን ተቀብዬ “ከእኔ ጋር መስራት የምትፈልጉ ከሆነ እንዲህ አይነት ንግግር አልፈልግም፡፡ እኔ የሠላም አምባሳደር ነኝ፤ በሠላምና በፍቅር ነው መስራት የምፈልገው፡፡ የሚሠራው ሰው ይሳሳታል ያጠፋል፤ ያም ቢሆን እስከዛሬ ያገለገለ ሰው መመስገን እንጂ መሰደብ የለበትም፤አሁኑኑ ይህን አይነት ስድብና ጭፈራ ካላቆማችሁ ትቼ እሄዳለሁ” ስል ሁሉም በአንድ ጊዜ ፀጥ አሉ፡፡
ይታይሽ “ሳዳም ጋዳፊ ወረደ” የሚሉት እሳቸው ባሉበት ነው፤ የሠራ ሰው በፍፁም መሰደብ የለበትም፡፡ በእለቱ እኔ ምን አልኩኝ፤“ድግስ ደግሰን ጋብዘን ሸልመንና አመስግነን እንሸኛቸዋለን” ይህንንም አድርገናል፤ሚኒስትሮች ባሉበት ራት ጋብዘን፤ ለቦርዶቹ ደረት ላይ የሚደረግ የቻምበሩ አርማ ያለበት ወርቅ ሸልመን ነው የሸኘናቸው፡፡
ሥራውን ሲጀምሩት በጣም ፈታኝ የሆነብዎ ምን ነበር?
በጣም ፈታኝ የምለው ስራ በኢትዮጵያና በአዲስ አበባው ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች መካከል ጠብ ነበር፡፡ ጠላትነታቸው ደግሞ ለ40 ዓመታት ሥር የሰደደ ነው፡፡ እኔ ወደ ኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ስመጣ ሁኔታው በጣም የከፋ ነበር፡፡ ብቻ ምናለፋሽ ጥሩ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሰዎች የሁለቱን ቻምበሮች ጉዳይ እንዳትነኪ፤ ዝም ብለሽ ቀጥይ ይሉኝ ነበር፡፡
የጠባቸው መንስኤ ምንድን ነው?
አንዱ የሚያጣላቸው የህንፃው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የስራ መመሳሰል ነው፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ ቻምበር ይህን ይሠራል፤የኢትዮጵያ ይህን ይሠራል እየተባባሉ፡፡ ተባብረውና ተቻችለው መስራት ሲችሉ ይበጣበጡ ነበር፡፡ እኔ ለጉዳዩ እልባት ለማግኘት ስሞክር፤ሁለቱን ቻምበሮች ለማስታረቅ እንዳትሞክሪ፤የህንፃውን ጉዳይ እንዳትነኪ እባላለሁ፡፡ እኔ ደግሞ መስራት ካለብኝ ሠላምና የረጋ መንፈስ ባለው ሁኔታ ነው የምሠራው፡፡ ይህን አትንኪ ያንን አታንሺ የሚባለውን ነገር አላመንኩበትም፤እስከመቼ ነው ሳትነኪ የምትኖሪው? ችግርን ቀርበሽና ተጋፍጠሽ እንጂ በመፍራትና በመሸሽ መፍትሔ አታመጪለትም፡፡
ከቦርድ አባላት ጋር ተነጋግሬ ይህን ጭቅጭቅና ጠብ ፈትተን በሠላማዊ መንገድ መስራት አለብን በሚል ብዙ ሥራዎች ተሠሩ፡፡ መጀመሪያ ኮሚቴ አቋቋምኩኝ፤የሚጣሉበትን ነገር አጣራን፤ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ሲያቀርብ የሚበጣበጡ ሰዎችን ኮሚቴ ውስጥ በመክተት ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችንም ጨምሬ በሠላማዊ መንገድ ተነጋግረን ችግሩን ፈታን፡፡ አንድ ወር ተኩል ባልሞላ ጊዜ ነው ችግሩ የተፈታው፡፡
የህንፃውን ጉዳይ በተመለከተ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በደብዳቤ ባሳወቁት መሠረት፤ “አዲስ አበባ ቻምበር በባለቤትነት ይዞት አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የክልል ቻምበሮች እንዲገለገሉበት፤የራሳቸውን ህንፃ እያሰሩ ሲወጡ ቀሪው ለኢትዮጵያ ቻምበር እንዲሆንና እያከራየ እንዲጠቀም እንዲሁም የክልል ቻምበሮችን እንዲያጠናክርበት ይሁን” በሚል ተስማምተን አሁን በፍቅርና በሠላም ብዙ ነገሮችን በጋራ እንሠራለን፡፡ አሁን እንደውም እኛ ስራ ሲበዛበን አዲስ አበባ ቻምበሮችን አግዙን እንላለን፤ እኛም እነሱን እናግዛለን፡፡ እንደ ዱሮው መገለማመጥና የጐሪጥ መተያየት ፈጽሞ ተወግዷል፡፡ በአመት ሁለት ጊዜ የመገናኛና የመሰብሰቢያ ፕሮግራም ሁሉ አዘጋጅተው እርስ በእርስ ይገባበዛሉ ይጨዋወታሉ፡፡
ከመንግስት ቢሮዎችና ከንግዱ ጋር ከተገናኙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር ያላችሁ የስራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ከ10 እና ከ15 ዓመት በፊት ሲለፋበት የኖረን ጉዳይ ነው፤ አሁን እኛ በተሳካ ሁኔታ እየሠራን ያለነው፡፡ ለምሣሌ ከንግድ ሚኒስቴር፣ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወዘተ ስንተዋወቅና አብረን መስራት እንፈልጋለን ስንል ሁሉም እውነት አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ንግድ ምክር ቤት ከመንግስት ጋር አብሮ መስራት አይፈልግም የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ እኛ ግን ከመንግስት ጋር የመስራት ጽኑ ፍላጐት አለን፡፡ ምክንያቱም ህግና ፖሊሲ የማያወጣው መንግስት ነው፡፡ ህግና ፖሊሲ ከሚያወጣ መንግስት ጋር አብሮ አለመስራት ደግሞ መልካም አይደለም በሚል ተነጋግረን፣ ከእነርሱ ጋር ሁለትና ሶስት የምክክር መድረኮች አካሂደናል፡፡ ይህን በብሔራዊም በክልልም ደረጃ አድርገነዋል፡፡ ከተመካከርንባቸው ውስጥ የወደብ ዕቃ ማንሳት ጉዳይ፣ ህዝቡ የተጯጯኸበት የንግድ ምዝገባ ጉዳይ፣ የታክስ አከፋፈልና የመሳሰሉት ላይ ተወያይተን አሁን ህጉን ሊያሻሽሉት ነው፡፡ ለምሣሌ ከጉምሩክ ጋር ባካሄድነው ውይይት ከመንግስት ጋር ይጣላሉ ተቀባይነት አያገኙም ሲሉን፣ መንግስት 98 በመቶውን የኛን ሃሳብ ተቀብሏል፡፡ ከላይ በጠቀስኩልሽ በታክስ አከፋፈል፣ በወደብ ዕቃ አነሳስ፣ በንግድ ምዝገባና በበርካታ ጉዳዮች ለንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ለመንግስት ይጠቅማሉ ባልናቸው ሃሳቦች ላይ ነው መንግስት 98 በመቶ ሃሳባችንን የተቀበለው፡፡ “ያልተጠበቀ የመንግስት አቋም” ተብሎ ተወድሷል፡፡ በአጠቃላይ ያተኮርነው ለንግዱ ህብረተሰብ ምቹ የንግድ ከባቢን የመፍጠር ስራ ላይ ነው፡፡
አገሪቱ ውስጥ የተለያየ ፍላጐትና ባህሪ ያላቸው ነጋዴዎች አሉ፡፡ የንግዱን ማህበረሰብ የማስተዳደሩ ጉዳይ ምን ይመስላል?
እኛ የአገሪቱ የንግድ ማህበረሰብ ጥሩ ስነ - ምግባር ያለውና ታማኝ እንዲሆን የማንቃት፣ በተሳሳተ መንገድ የሚጓዙ ካሉ ወደ መስመር የመመለስ፣በሰዓቱ ግብር እንዲከፍሉና በንግድ ሥራ የሀገራቸውን መልካም ገጽታ እንዲገነቡ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እርግጥ ነው በርካታ ነጋዴዎች አሉ፣የተለያየ ባህሪ መኖሩም አይካድም፣ ነገር ግን በመልካም አቀራረብና አዎንታዊ መንፈስ በተሞላበት ሁኔታ ችግሮቻችንን እንፈታለን፡፡
የነጋዴውን ጥቅም በማስከበርና ከመንግስት ጋር ቅርርብ እንዲኖር የበኩላችንን እያደረግን ነው፡፡
አባላቱ በርካታ ቢሆኑም ነጋዴውን በመቅረብና በማነጋገር በቀላሉ ጤናማ በሆነ መንገድ መምራት ይችላል፡፡
በደርግ መንግስት ተወርሶ የነበረው ህንፃችሁ ተመልሶላችኋል፡፡ ሆኖም አዲስ ህንፃ ለማስገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የቦታ ጥያቄ ማቅረባችሁን፣ምን ያህል ቦታና የት ቦታ እንደምትፈልጉ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አሳውቁን ማለታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ያሁኑ ህንፃ እያለ ሌላ መገንባት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? ህንፃውን የምትገነቡበት ገንዘብ ከየት የሚገኝ ነው? ምን አይነት ህንፃስ ለማስገንባት አሠባችሁ?
ህንፃውን የማስመለስ ሥራ ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ ከአስራ አምስትና አስራ ስድስት ዓመት በላይ ማለት ነው፡፡ ይሄ ህንፃ የተሠራው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሳይመሠረት በፊት ነው፤ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በሚል የተሠራው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ቻምበር ይመለስልኝ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ቻምበርም ይመለስልኝ የሚል ደብዳቤ ሲያስገባ ቆይቷል፡፡ በኋላ ግን እኛ ምን አልን ---- የሚመለስ ከሆነ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአዲስ አበባ ይመለስ የሚል አቋም ላይ ደረስን፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግስት ህንፃውን ሲመልስ ኢትዮጵያ ቻምበር በባለቤትነት ይያዘውና መጠቀሙን አብረው ይጠቀሙ ሲል፤ አዲስ አበባ ደግሞ ኢትዮጵያ ቻምበር ሳይፈጠር የራሴ ነበር ይላል፡፡ ይሄው ይጠቀሙ ሲል አዲስ አበባ ደግሞ ኢትዮጵያ ቻምበር ሳይፈጠር የራሴ ነበር ይላል፡፡ ይሄ ጭቅጭቅ በነበረበት ወቅት እኛ በጭቅጭቅ ጊዜም ገንዘብም ከምናባክን ለአንዳችን ተመልሶ በጋራ ለምን አንጠቀምም፤ ከዚያስ ለምን የራሳችንን ህንፃ አንሰራም በሚል የአዲስ አበባው ንግድ ምክር ቤት ቦታ ጠይቆ ስራ ጀምሯል፡፡
እኛም ቦታ የጠየቅነው ለዚህ ነው፡፡ ህንፃው ከሁለት ዓመት በፊት ከተመለሰ በኋላ ግን ተከፋፍሎ በሠላም መጠቀም አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እኛ ተመካክረን መንግስትን የወሰነውን ተግባራዊ ወደማድረግ ሄድን፡፡
ምክንያቱም መንግስት በዚህ በዚህ መልኩ ይጠቀሙ የሚል መመሪያ አስቀምጧል፡፡
አዲሱን ህንፃ ለመገንባት የታሰበበት ዋናው ምክንያት በየሀገሩ ሄደን የንግድ ምክር ቤት ቢሮዎችን ስንጐበኝ የምናያቸው ከእኛ ጋር ፈጽሞ አይገናኙም፡፡ የእኛ በጣም ያሳፍራል፡፡ የውጭዎቹ የአብዛኛዎቹ ቢሯቸው ህንፃው ራሱ ቤተ - መንግስት ነው የሚመስለው፤የእኛ ግን ከ60 እና 70 ዓመት በፊት የተሠራ ህንፃ ነው፡፡ እንደውም ያኔ ባለራዕይ ሆነው ይሄን ሰሩ እንጂ አሁን ያለበት ሁኔታ እንኳን ከአለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤቶች ከክልል ምክር ቤቶች ጋርም መወዳደር አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን ቦታ ጠይቀናል፡፡ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ አዳራሽ፣ ቢሮዎች በአጠቃላይ የትኛውም አለምአቀፍ ሰው ቢመጣ አንገታችንን ቀና አድርገን የምናስገባበት መሆን መቻል አለበት፡፡ አሁን የአገራችን ኢኮኖሚ እያደገ ስለሆነ ብዙ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እየመጡ ነው፡፡ ሲመጡ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱን ያነጋግራሉ፡፡ ያኔ የእኛ ቢሮ እንዲህ የሚያሳፍር ከሆነ ልክ አይመጣም፤ስለዚህ ቦታውን ሊሰጡን ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ሁሉም ክልሎች ቦታ ተሰጥቷቸው ንግድ ምክር ቤት እንዲሠሩ እያልን ነው፡፡ የድሬዳዋው ንግድ ምክር ቤት ህንፃ እንዲመለስ ደብዳቤ መንግስት ጽፏል፤አፈፃፀም ነው የቀረው፡፡ በሌላ በኩል የንግዱ ማህበረሰብ ድምጽ እንዲሰማና ትኩረት እንዲያገኝ የአባላት ማብዛት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠርቷል፡፡ ለምሳሌ ትግራይ 16ሺህ ደርሷል፡፡ ደቡብም አማራም የአባላት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ ጠንካራ ስራ ሠርቶ አባላትን በከፍተኛ ሁኔታ ላበዛ ክልል ሽልማት እንሸልማለን ብለን ሁሉም በፉክክር በጥሩ ሁኔታ እየሠራ ነው፡፡ አሁን የምንጠይቀው መሬት በከተማ ውስጥ ሆኖ ስፋቱም ምክንያታዊ የሆነ ነው፡፡
መጀመሪያ ለቢሮ ነው የምንጠይቀው፡፡ ከዚያ በኋላ አለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን የምናሳይበት ከከተማ ውጭ ቦታ መጠየቃችን አይቀርም፡፡
ቻምበር አካዳሚ ለማቋቋም ሀሳብ እንዳላችሁ ሰምቻለሁ፡፡ ምንድነው የሚሰራው? ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡኝ----
ቻምበር አካዳሚ የሚለውን ስም አስጠንተናል ቻምበር አካዳሚ ከሚባል በቀላሉ “ሊደርሺፕ ኢንተርፕሪነርሺፕ ኤንድ ማኔጅመንት ሴንተር” እንዲባል ተስማምተናል፡፡ አመራርን፣ ስራ ፈጠራን እንደዚሁም ሥራ አመራርን አካትቶ ከተቋቋመ የላቁ ሰዎችን - መሪዎችን፣ የቦርድ አመራሮችን፣ የአገር መሪዎችን ወዘተ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም የሚያሰለጥን የልቀት ማዕከል ሊሆን ይችላል፡፡ ሥራ ፈጠራ ላይ በተለይ የሚያሰለጥን በቂ ተቋም የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ችግር ከመፍራት ይልቅ መፍትሔ ፈጣሪ እንዲሆኑና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያዳብሩ ማስተማር የሚችል ማዕከል ይሆናል፡፡ በማኔጅመንትም በኩል አገራችን ላይ ጉልህ የማኔጅመንት ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ሰዎች በብቃት የመምራትና የማስተባበር ችግርን አስወግደው የላቀ ብቃት የሚያገኙበት ይሆናል፡፡ ይህንን ስንልም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ነው፡፡ ለምሣሌ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከውጭ ሁሉ መጥተው የሚሠለጥኑበት ሆኗል፡፡ ራዕይ ባላቸው ሰዎች ነው አየር መንገዱ ለዚህ የደረሰው፡፡ አሁን የእኛን ሃሳብ የሚያጣጥሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን በእርግጠኝነት ዕውን እናደርገዋለን ብለን እናስባለን፡፡
በአሁን ሰዓት የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል፤ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሃሳብስ የለዎትም?
(ሣ…ቅ) እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ ፖለቲከኞች ናቸው ለስልጣን ተነሳስተው የሚሄዱት፡፡ እኔ እዛ ወጥቼ ባልመራም በየትኛውም ቦታ ላይ መሪ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሣሌ እኔ ጥሩ ሃሳብ አምጥቼ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ ላይ ካዋለው እኔ ነኝ የመራሁት ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ አንቺ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለማርያም ጥሩ ሃሳብ አቅርበሽ ሥራ ላይ ካዋሉት የመራሽው አንቺ ነሽ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያዩት ወንበር ላይ መቀመጡን ነው፤ እኔ ግን የምፈልገው ስራ መሠራቱን ነው፡፡ አንቺ ከልብሽ ከሠራሽና ከተንቀሳቀሽ አንቺ ባትፈልጊም ስራው ይፈልግሻል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ጥያቄ ገፍቶ ቢመጣስ አልፈልግም ትያለሽ?
አዎ እምቢ እላቸዋለሁ፡፡ ለምን መሠለሽ? እናንተ ምሩ፤ እኛ ከኋላ እናሠራለን እላቸዋለሁ፡፡ እኔ ፖለቲከኛ ስላልሆንኩ ነው፡፡ እዛ ቦታ ላይ መቀመጥ ያለባቸው ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ባለፈው ለምንድነው ፖለቲካ ውስጥ የማትሳተፊው ሲለኝ ነበር፡፡ እኔ ግን የፖለቲካውን ቼዝና ዳማ ጨዋታ አልችልበትም፡፡ እኔ ፊት ለፊት የምናገር ሰው በመሆኔ የፖለቲካውን ድራማ አልችልም ብዬ መልሼለታለሁ፡፡
ይሄ የብቃት ጉዳይ አይደለም፤ሞክሮ መውደቅም ይቻላል፡፡ ለአንድ ሰው ዋናው ነገር የተቀመጠበት ቦታ ሳይሆን በቀናነት ባለበት ቦታ መስራት መቻሉ ነው፡፡ ቀና ሰው ስለሆንሽ ችግር አይገጥምሽም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ችግርና እንቅፋት አለ፡፡ ያንን እንቅፋት ረግጠሽ አንቺ ወደ ላይ ከፍ ማለት ነው ያለብሽ፡፡
አንዳንዱ የአንዱን ትከሻ ረግጦ ራሱ ከፍ ማለት ይፈልጋል፡፡ እኛ እንኳን ባለንበት ቦታ ብዙ ጫና አለ፡፡
እኔ አሁን ስራውን የቀጠልኩት ለችግርና ለመከራ ስለማልበገር ነው፡፡ እንቅፋት እኮ ከኖርማሉ መሬት ከፍ ያለ ነው፤ስለዚህ እዛ እንቅፋት ላይ ስትቆሚ የባሰ ከፍ ትያለሽ፡፡ ለዚህም ነው እኔ ከመከራ በላይ ነኝ ብዬ የማምነው፡፡
የቤተሰብ ሃላፊነት አለ፣ የስራ ሃላፊነት አለ፣ አሁን ደግሞ ለፒኤችዲ እየተማርሽ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሃላፊነት በአንድ ላይ መወጣት አይከብድም? እንዴት እየተወጣሽው ነው?
ይሄ የጊዜ ጉዳይ ነው እንግዲህ፡፡ አንዳንዴ በቻምበሩ በኩል በሙያሽ ከምትሠሪው በተጨማሪ በርካታ ስራዎች ይመጣሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዛሬ ነፃ ነኝ ብለሽ ስታስቢ ያላሰብሻቸው ሥራዎች በፀሐፊዋ በኩል ይቀርቡልሻል፡፡
አለም አቀፍ ስብሰባ መምራት፣ የተለያዩ ሪሴፕሽኖች ላይ መገኘት የመሳሰሉት ለምሣሌ በአንድ ምሽት ሶስት ሪሴፕሽን ላይ እንድትገኚ ይፈለጋል፡፡ እኔ አንዱ ጋ ሄጄ ሌላው ጋ አንድ የቦርድ አባል ስልክ፣ ለምን ፕሬዚዳንቷ አልመጣችም ይላሉ፡፡ ስለዚህ አንዱ ጋ ቶሎ ግንባሬን አስመትቼ ሌላው ጋ ደግሞ እሮጣለሁ፡፡ ቻሌንጁ ብዙ ነው ግን ቁርጠኛ ከሆንሽ የማይሰራ የለም፡፡
ብዙ ጊዜ በዕቅድ እንቀሳቀሳለሁ፣ነገር ግን እቅዴን የሚያበላሹ ነገሮች ይመጣሉ፣አቻችሎ መሄድ ነው፡፡ እቤት ውስጥ እኔ ከሌለሁ የቤት ሠራተኛ አበላሽታ የምትጠብቅሽ ነገር ይኖራል፣የቤቴን መበላሸት ግን ከአገር ጉዳይ አላስቀድምም፤ ወደ መንግስት ሥራ እሄዳለሁ፤የትምህርቱም ጉዳይ በዚህ መልኩ ነው የሚሄደው፡፡ እኔ በትምህርት ልምዱ ስላለኝ ክላስ ሳልከታተል የምሠራቸው ስራዎች አሉ፡፡
ቃለምልልሱን ከማጠናቀቃችን በፊት ስኬት ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ ቢነግሩኝ----
ስኬት ማለት ሰው የፈለገውን መሆን መቻል ነው፡፡ አንድ ሰው ስኬት ብሎ የሚያስበው በ10 ደቂቃ 100 ሜትር መሮጥ ሆኖ በሳምንትም ሆነ በ10 ደቂቃ ከጨረሰ ስኬት ነው፤ ግን ያ የስኬቱ መጨረሻ ሊሆን አይገባም፡፡ ከዛ የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳት አለበት፡፡ አንድ ሰው ግቡ ጋ ሲደርስ ስኬት ነው፡፡
ግን የስኬቱ መጨረሻ መሆን የለበትም ብዬ ነው የማምነው፡፡
እኔ ሁሌም ችግርን መከራን አሸንፋለሁ፡፡ ለሌላ ስኬት እዘጋጃለሁ፡፡ በአጠቃላይ ለእኔ ስኬት ቀጣይነት ያለውና መሆን የምትፈልጊውን መሆን ማለት ነው፡፡
የዝንጀሮ ልጅ፤ ቅቤ ተቀብተህ ና ቢሉት፤ ቅቤ ቢኖር ያባቴ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ? አለ”
በኢትዮጵያ በ1920ዎቹ የነበረው ታሪክ ዛሬ ሲያስቡት ተረት ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ የጦር-ባላባቶች፤ ሰው ኃይለሥላሴ የሚባል (ራስ ተፈሪም የሚባል ስም አለው) አንድ ወጣት በአሰርታት ዓመታት ውስጥ መሪ ሊሆን ማኮብኮቡን ሰሙ፡፡ ይሄ ጭምት መሳይ ዝምተኛ ሰው አገሪቱን የመቆጣጠር አቅም እንደሚኖረው ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ሆኖም በ1927 ዓ.ም ኃ/ሥላሴ እያንዳንዱ በየተራ እንዲመጣና ታማኝነታቸውን በመግለፅ መሪያቸው መሆኑን እንዲያረጋግጡ አዘዘ፡፡
አንዳንዶች በጥድፊያ፣ አንዳንዶች ፈራ-ተባ እያሉ ትእዛዝ ሲፈፅሙ፤ የሲዳሞው ደጃዝማች ባልቻ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ኃይለሥላሴ በተለመደው የጨዋና ግትር ዘዴው፤ ባልቻ እንዲመጣ ተማፀነው፡፡ ባልቻም “እታዘዛለሁ ግን በፈለኩት ጊዜ ነው የምመጣው፡፡ በተጨማሪም 10,000 ጦር ይዤ ነው ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ እምጠብቀው” አለ፡፡
ኃ/ሥላሴም፤ “ስለክብርህ የፌሽታ ግብዣ ላደርግልህ አስቤአለሁና፤ ተጋበዝልኝ” አለ፡፡ ባልቻ ግን ታሪክን ጠንቅቆ ያውቃልና የቀደሙት የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሳፍንት ግብዣን እንደወጥመድ ሲጠቀሙበት እንደኖሩ ተገንዝቧል፡፡ ነቄ ነው፡፡ መታሰርም ሆነ መገደል የሚከተለው ከግብዣ በኋላ ነው፡፡
ደጃዝማች ባልቻ የግብዣውን ዓላማ እንደተረዳ ለመጠቆም “የምመጣው 600 ክብር ዘበኞቼን ይዤ ነው” አለ፡፡ ኃ/ሥላሴ ግን “እንዲህ ያሉትን ጀግኖችህንማ ማስተናገድ ለእኔ ክብር ነው” ሲል መለሰ፡፡
ባልቻ ክቡር ዘቦቹን ግብዣው ላይ እንዳይሰክሩና በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ አዘዘ፡፡ ግብዣው ቦታ ሲደርሱ ኃ/ሥላሴ ታይቶ የማይታወቅ አቀባበል አደገ፡፡ ባልቻ “ማምሻውን ወደ ጦር ሰፈሩ መመለስ አለብኝ፤ አለበለዚያ ጦሬ አዲስ አበባን እንዲወርር አዝዣለሁ” አለ፡፡ ኃ/ሥላሴ ባለመታመኑ እንዳዘነ በመግለፅ፤ ይልቁንም ከግብሩ በኋላ የሚዘፈነው ዘፈን የሲዳሞን ጦረኛነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን አደረገ፡፡ ባልቻም ኃ/ሥላሴ የፈራና ለማይረታው ወታደሩ እጁን የሰጠው መሰለው፡፡
ከሰዓት በኋላው ሲገባደድ ባልቻና ወታደሮቹ ነጋሪት እያስጐሰሙ ወደ ጦር ሠፈራቸው አመሩ፡፡ ከሳምንታት በኋላ አዲስ አበባን መውረር እንደሚችል አሰበና ባልቻ ኃ/ሥላሴ እንግዲህ ቦታው ወይ ዘብጥያ ወይ ሞት ነው” አለ፡፡
ሆኖም ባልቻ ወደ ጦር ሠፈሩ አካባቢ ሲደርስ አንድ የተሳሳተ ነገር መኖሩን ተገነዘበ፡፡ አንድም ድንኳን የለም፡፡ የሚታየው ጭስ ብቻ ነው፡፡ አንድ የዐይን ምስክር የሆነውን ሁሉ አስረዳው፡- የኃ/ሥላሴ ጦር ባሳቻ መንገድ መጣ፡፡
የመጣው ግን ሊዋጋ አልነበረም፡፡ ኃ/ሥላሴ በዘምቢል ወርቅና ብር አጭቆ የላከው ጦር ነው፡፡ የባልቻን ወታደሮች መሣሪያ ሁሉ በወርቅና በብር ገዛ፡፡ እምቢ ያሉ ተያዙ፡፡ በጥቂት ሰዓት ውስጥ የባልቻ ጦር መሣሪያውን አስረከበ፡፡ ባልቻ ወደ ደቡብ 600 ወታደር ይዞ ለመሸሽ ቢፈልግም ያ መሣሪያ የወሰደባቸው የኃ/ሥላሴ ወታደር መንገዱን ገትሮ ይዟል፡፡
ወደ አዲስ አበባ እንዳያቀና ሌላ ጦር መንገዱን ገድቦታል፡፡ እንደቼዝ ተጨዋች ዙሪያውን ተከበበ፡፡ ባልቻ ለመጀመሪያ ጊዜ እጁን ሰጠ፡፡ በኩራትና በአጉል ምኞት የሠራው ኃጢያት ስለፀፀተው ወደ ገዳም ሊገባ ተስማማ፡፡ ያለ አንዳች የጥይት ድምፅ ኃ/ሥላሴ ደጃዝማች ባልቻን አስወገደ፡፡
የሲዳሞው ደጃ/ባልቻም ወደ ገዳሙ ከመግባቱ በፊት፤
“የተፈሪን ጉልበት አትናቁ፡፡ እንደ አይጥ ይድሃል፡፡ ሆኖም የአንበሳ ጥርስ ነው ያለው!” አለ፡፡
***
በግብዣ ከመጠመድ ይሰውረን! የሌሎችን ጉልበት ከመናቅ አባዜ ያድነን፡፡ የራስን አቅም የዓለም መጨረሻ ነው ብሎ ከማጋነን ይሰውረን! የመስተዋት መስኮቱን ጭሳማ የማድረግ ጥበብ ያለው አለቃ ወይም የፖለቲካ መሪ፤ ጭሳማውን ቀለም የበለጠ ባጠቆረው መጠን፣ የበለጠ እንዳናየው እያደረገ መሆኑን አንርሳ፡፡ “ጦርነቱን ከማወጅህ በፊት ድልን ተቀዳጅ” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ እቅድህን አታሳውቅ፡፡ ስለእቅድህ ከመፎከር ተጠንቀቅ ነው ነገሩ፡፡ ባላንጣህ እቅድህን እንዳያውቅ ባደረግህ ቁጥር የድልህ መጠን ይበልጥ እየሰፋ ይመጣል፡፡ ስለእቅድህ በፎከርክ ቁጥር ግን ስኬትህን እያራቅህ ነው የምትሄደው፡፡ የሞቀ ከተማ እያሰብን መጨረሻችን ገዳም የሚሆነው ሥር-ባልሰደደ ድል ስንኩራራና ሌሎች ስለእኔ ምን ያስባሉ ብለን ሳንጠይቅ ስንቀር ነው፡፡
በቡድናዊ ስሜት አለመጠመድና አለመጨፈን ለአገርና ለህዝብ የሚበጅ አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰባችንን እያጠበብን የቡድናዊ ስሜት ተገዢ ስንሆን ደባንና ሴራን የሙጥኝ ወደማለት እንገባለን፡፡ ያ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡
የሦስተኛው ክፍለ - ዘመን ህንዳዊ ፈላስፋ - ካውቲላ፤
“በዓላሚ ቀስተኛ፣ የተሰደደ ቀስት
አለው አጋጣሚ፣ ወይ ሊገል ወይ ሊስት፡፡
ግን በስል-ጭንቅላት፣ ሤራ ከተሳለ
ህፃንም ይገድላል፣ እናት ሆድ ውስጥ ያለ፡፡”
የሚለን ለዚህ ነው፡፡
ሌላው የአገር ጉዳይ ግልብ - እውቀትን መከላከል ነው - ባልበሰለ አዕምሮ ዘራፍ ማለትን፡፡ ያለፖለቲካዊ ብስለት ፖለቲከኛ ነኝ ማለትን፡፡ መላው ዓለም እውቀት ሆኖ ሳለ የአዕምሮን በር ዘግቶ፣ የእኔ እውቀት ብቻ ነው ገዢ ብሎ ማሰብ ክፉ አባዜ ነው፡፡ ከሳጥኑ ውጪ (Out of the box እንዲሉ) ለማየትና ለማስተዋል አለመቻል፤ የሌሎችን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆንን ያስከትላል፡፡ ያ ደግሞ ብዙ አለመግባባቶችን ይወልዳል፡፡ “ከመርገምት ሁሉ የከፋው መርገምት ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት” ይለዋል ባለቅኔው፡፡ ወጣቱ፤ መሰረታዊ እውቀት፣ ጥልቀትና ብስለት፣ ከዚያም ስክነትና ጥበበኛነት እንዲኖረው ለማድረግ ብርቱ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ አዋቂው ራሱን እንዳያጥርና እንዳይገድብ፣ ልምዱን እንዲያጋራ መንገድ መክፈት ያሻል፡፡
ለሁሉ የህይወት ዘርፍ ፖለቲካዊ ትርጉምና አንድምታ ሰጥተን አንችለውም፡፡ መሰረታዊ እውቀት፣ ከኑሮ የምንቀስመው ልምድና ከባህል ያበለፀግነው የአእምሮ ሀብት የህይወትን ትርጉም ለማየት በዋናነት መሣሪያዎቻችን ናቸው፡፡ ይህንንም ለመቀበል እውነተኛ የህዝብ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ እውነተኛ የህዝብ ፍቅር የራስን ጥቅም መሰዋትን ይጠይቃል፡፡
“ህዝብን በመጠቀም የራስን ግብ ለመምታት ያለው ዘዴ በጉልበትና በማጭበርበር የሚደረግ ነው፡፡ ይልቁንም የህዝብ ፍቅር አንዱ መሣሪያ ነው ይላሉ ጠበብት፡፡ ያ ግን ፀሀይ እስኪወጣ መጠበቅን ይጠይቃል፡፡ ህይወት ደግሞ እያንዳንዷን ቅፅበት ትፈልጋለች” ይላል ጐይቴ፡፡
ካለፉት የወረስነው፣ ወይም የወረስን የመሰለንን ነገር ልብ ብለን እንመርምር፡፡ ለህዝብ ሰጥተነዋል ያልነውን ነፃነት፣ የኢኮኖሚ ብልፅግና፣ ፍትሕ-ርእዕ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት እንመርምር፡፡ ስትራቴጂ በነደፍን፣ መመሪያ ባወጣን፣ ሪፖርት ባቀረብን ቁጥር ምን ያህል ለህዝብ ጠቀመ? ከሚለው ማንፀሪያ አኳያ እናስተውለው፡፡ መለስ ብለን፤ ያለምነውን ነገር፣ እጅ-ካስገባነው ነገር እናወዳድር፡፡ አለበለዚያ፤ የማታ ማታ “የዝንጀሮ ልጅ ቅቤ ተቀብተህ ና ቢሉት፤ ቅቤ ቢኖር ያባቴ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ” አለ እንደሚባለው እንዳይሆን እናስብ፡፡
ቅ/ሲኖዶስ በአምስቱ ዕጩ ፓትርያሪኮች ላይ ዛሬ መወያየት ይጀምራል
ለፓትትሪያርክነት ይታጫሉ ተብለው የተጠበቁ ሊቃነጳጳሳት አልተካተቱም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ተለይተውና ተጣርተው በሚቀርቡለት አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች ላይ ዛሬ መወያየት ይጀምራል፡፡
ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ በሀገር ውስጥና በውጭ የተመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሚገኙ ሲኾን አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው የምርጫ መሪ ዕቅድ መሠረት፣ ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙ አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝቡ ይፋ የሚደረጉበት ውሳኔ የሚተላለፍበት ይኾናል፡፡
የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን የተገኙትን ጥቆማዎች እንደ ግብአት በመያዝና በፓትርያሪክ ምርጫ ሕጉ የሰፈረውን ድንጋጌ በመጠቀም እንደለያቸው የተነገሩትን ዕጩ ፓትርያሪኮች ዝርዝር ለቅ/ሲኖዶሱ የሚያስረክበው በዛሬው ዕለት እንደኾነም ታውቋል፡፡ ኮሚቴው የዕጩዎቹን ዝርዝር ለቅ/ሲኖዶሱ ከማቅረቡ ቀደም ብሎ የወጡ መረጃዎች በዕጩ ፓትርያሪክነት የተመረጡት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት÷ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ የባሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ናቸው፡፡
በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ለፓትርያርክነት ይበቃሉ ተብለው ከታሰቡት ሊቃነ ጳጳሳት÷ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ መካከል የተወሰኑት አለመካተታቸው የምርጫውን ሂደት የሚከታተሉ አካላትን አነጋግሯል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ የሚጠበቁት አባቶች በዝርዝሩ ላለመካተታቸው በምርጫው ዙሪያ ያሳስበናል የሚሉትን የቡድን እንቅስቃሴዎች በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
“ጠጠሮቹ እና ሌሎችም ወጐች” ላይ ውይይት ይካሄዳል
በዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተደረሰው ”ጠጠሮቹ እና ሌሎችም ወጐች” የተሰኘ መፅሃፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በብሔራዊ ቤተመዘክር አዳራሽ ውይይት እንደሚካሄድ ሚዩዚክ ሜይዴይ አስታወቀ፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ የሚመሩት ሃያሲና ወግ ፀሐፊ መስፍን ሃብተማርያም ናቸው፡፡