Administrator

Administrator

ቻርለት ኬሪች (ናይሮቢ፤ የፋይናስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኀላፊ)
ዐይን ገላጭ ልምድ ነው ያገኘነው። ከተሞችንን ለሕጻናት አመቺ ለማድረግ፣ የግድ ሰፋፊ ቦታዎች ያስፈልጋሉ ማለት እንዳልሆነ አይቻለሁ።
የከንቲባዋ ራዕይ አዲስ እይታን የሚፈጥር ነው። በተወሰኑ ቦታዎች ትልልቅ የሕጻናት መጫወቻዎችን ከመገንባት ይልቅ በየአካባቢያቸው በቅርባቸው በሺ የሚቆጠሩ የመጫወቻ ስፍራዎችን ለማዘጋጀት ነው እየሠሩ ያሉት።
የሕጻንነት ዕድሜ ለአካላዊና ለአእምሯዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በየሰፈራቸው በየአቅራቢያቸው ከቤት ውጭ ምቹ የመጫወቻ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ በጣም ትልቅ ሥራ ነው። ትምህርት ቤት ሲገቡ ዕውቀት የመጨበጥ ዐቅማቸው ጥሩ ይሆናል። ዕድሜ ልክ የሚያገለግል ኢንቨስትመንት ነው ማለት ይቻላል።
እነዚህ ሕጻናት ሲያድጉ፣ በትክክል የተገነባ አዲስ ትውልድ ይኖራችኋል ብዬ እጠብቃለሁ።
ዪቮኔ ኢኪሳውዬር - የፍሪታውን ከንቲባ፡
የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶችን አይተናል። ለትናንሽ ሕጻናት የተዘጋጁ የመጫወቻ ቦታዎችንም ጎብኝተናል። አንዲት እናት አግኝቼ እንደነገረችን፣ ቦታው አቧራማ ነበር። ሕጻናትን ለጤና ጠንቅ የሚያጋልጥ ነበር። አሁን ግን ንጹሕ ነው። በልምላሜ አረንጓዴ ለብሶ ደስ ይላል። የመጫወቻ ቁሳቁሶችም ተዘጋጅተውለታል። በዚህም የአካባቢው ሰው ደስተኛ ነው።
ከተሞችን ለሕጻናት አመቺና ተስማሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን። የፕሮጀክት ሰነድ ማዘጋጀትም ጥሩ እንደሆነ እናውቃለን። ትልቁ ቁም ነገር ግን በተግባር መሥራት ነው። እኔን ያስደሰተኝና ያስደነቀኝ፣ ሐሳቦችና ሰነዶች በተግባር መሬት ላይ ተሠርተው ማየቴ ነው።
ቺላንዶ ናካሊማ ቺታንጋላ - የሉሳካ ከንቲባ፡
ለልጆች ዕድገት የምንሠራቸው ነገሮች መጪውን ዘመን የሚቀይሩ ኢንቨስትመንቶች እንደሆኑ ይታወቃል። እዚህ አዲስ አበባ በተግባር እየተሠራ ነው። እኛንም ለሥራ አነሣሥቶናል።
ለወላጆችና ለአሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ሲመረቁ አይተናል። ያልተለመደ ነገር ነው። ገርሞኛል። የከተማው አስተዳደር ለሕጻናት አስተዳደግ በሁሉም መስክ ብዙ ኢንቨስት እያደረገ እንደሆነ ተረድቻለሁ። የአፍሪካ የከተማ ከንቲባ እንደመሆኔ፣ ጥሩ የልምድ አጋጣሚ ሆኖልኛል። አፍሪካ በፍጥነት የምታድግ አህጉር ናት። በሕፃናት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን።
ሱዛን ሌንጌዋ - የናይሮቢ የጤና ም/ሚኒስትር፡
ሁሉንም ዘርፍ ያካተተ የመንግሥት አሠራር ይደነቃል። በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፍ ሁሉ ትኩረታቸውን በመሰብሰብ ተግባራቸውን በማናበብ እንዲሠሩ የከተማው አስተዳደር  የተቀናጀ አሠራር አለው።
አዲስ አበባን ለልጆች አስተዳደግ ምቹ ለማድረግ ሁሉንም መስክ አቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈል ብቻ ሳይሆን እንደሚቻልም ነው ያየሁት። ትምህርት ቤቶችን፣ የመጫወቻ ቦታዎችን፣ የሕጻናት ማቆያ ስፍራዎችን አይተናል። ለወላጆች የምክር አገልግሎት የሚሰጠሩ ከ3ሺ በላይ ባለሙያዎች ሰልጥነው ሲመረቁም በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ። ለኛ አዲስ ነገር ነው። አዲስ ልምድ እናገኝበታለን።
ለይላ መሀመድ ሙሳ (የትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሚኒስትር)፡
ከንቲባዋንና መንግሥትን ላሞግሳቸው እወዳለሁ። የሕጻናት አስተዳደግን ለማሻሻል ያከናወኑት ሥራ፣ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ሥራ ነው። የሕጻናት ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ በአግባቡ ትምህርት እንዲያገኙ፣ የጤና አገልግሎት እንዲሟላላቸው ለማድረግ ብዙ እንደተሠራ አይቻለሁ።
ዛሬ እጃችው ውስጥ ባለ አነስተኛ ዐቅም ተጠቅመን ውጤት ለማምጣት አስተማማኝ አመራርና የተቀናጀ አሠራር አስፈላጊ እንደሆነ በተግባር ተመልክተናል።
በመጀመሪያው ዕለት ከንቲባዋ ራዕያቸውንና ዕቅዳቸውን ሲያስረዱን፣ ይሄ ሁሉ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄና ጥርጣሬ ነበር የተፈጠረብኝ። ከንቲባዋ የራዕይና የዕቅድ ብቻ ሳይሆን የተግባርም ሰው ናቸው። ሥራውንም በአካል እየሄዱ ይከታተላሉ። በሄዱበት ሁሉ ሕጻናት ከንቲባዋን በደስታ ሲቀበሉና እየሮጡ ሲያቅፉ አይቻለሁ። ከንቲባዋ ለሥራው ምን ያህል ቅርብ እንደሆኑ ታዝቤያለሁ።


የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ዋና አሰልጣኝ በትረማርያም ገዛሐኝ በኮላሮዶ አሜሪካ በሚካሄደው “ ስፓርታን ካፕ ሻምፒዮንሺፕ” ላይ ኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካን በመወከል ይሳተፋል። ዛሬ በኮሎራዶ በሚጀመረው ሻምፒዮን ሺፕ ላይ በ7 የተለያዩ ዘርፎች የውድድር መደቦች የቴኳንዶ ክለቦች፤ ማሰልጠኛዎችና አካዳሚዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።
የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ዋና አሰልጣኝ (ሳቦም) በትረማርያም ገዛኸኝ ከኮሎራዶ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በስፓርታን ካፕ ሻምፕዮናው ላይ
የኢትዮጵያን እና የቀድሞ አሰልጣኙን ኪሮስን ስም  ከፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ሳቦም በትረማርያም በአንድ ቀን ውስጥ በአራት የተለያዩ የውድድር መደቦች ተደራራቢ ተሳትፎዎችን ያደርጋል። በቴኳንዶ የፓተርን ትርዒት፤ የነጥብ ፍልሚያ ፤ ለቀበቶ የሚደረግ ስፓርታ ፋይት እና ወደ ኦሎምፒክ ሊያሳልፍ የሚችል የስፓሪንግ ውድድር ላይ ነው። በስፓርታን ካፑ ላይ የተለያዩ አገራትን የሚወክሉ የቴኳንዶ ክለቦችና ስፖርተኞች ተሳታፊ ሲሆኑ በእያንዳንዱ የውድድር መደብ ከ18-20 ተወዳዳሪዎች ይገኙበታል።ሳቦም በትረማርያም በሚሳተፍባቸው 4 የውድድር መደቦች 3 እና 4 ተጋጣሚዎችን ጥሎ ማለፍ እንዳለበት ገልፆ፤ ዋንኛ እቅዱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለከፍተኛ የቀበቶ ሽልማት ለመብቃት ነው።
ከኮሎራዶው ሻምፓዮንሺፕ በኋላ በአርጀንቲና በሚካሄደው የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በክሮሺያ በሚዘጋጀው ግዙፉ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፍ መብቃት መሆኑን ለስፖርት አድማስ ተናግሯል።
ሳቦም በትረማርያም ከኮሎራዶ ስፖርታን ካፕ በፊት በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ  99 ሜዳሊያዎችን በአገር ውስጥ፤ በአህጉር አቀፍና በዓለምአቀፍ ውድድሮች የሰበሰበ  ነው።  የቴኳንዶ ስፖርተኛ፤ አሰልጣኝና ባለሙያው  በቴኳንዶ ስፖርት ከ21 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን 5ኛ ዳን( 5ኛ ዲግሪ ጥቁር ቀበቶ) ታጥቋል።
 ከ2 ወር በፊት በአሜሪካ በተካሄደውና  14 አገራት በተሳተፉበት “ኮምባት ቴኳንዶ “ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያና አፍሪካን በመወከል ሲወዳደር አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግቦ ነበር ወደ አገሩ የተመለሰው። በኮሎራዶው ስፓርታን ካፕ ለመሳተፍ የበቃውም በዚህ ውጤቱ ነው።
ሳቦም በትረማርያም ገዛኸኝ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ውድድሮች 99   ሜዳሊያዎችን በመሠብሰብ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ 5 የተለያዩ የውድድር ዘርፎች በፍልሚያ፤ ልዮ ትርኢትና ቴክኒኮች ለ5 ተከታታይ ዓመታት የአፍሪካ ሻምፒዮን   ሲሆን በአገር አቀፍ ውድድሮችም ለ13 ዓመታት አከታትሎ በማሸነፍ ስኬታማ ሆኗል ።
በትረማርያም “ሪል ዋርየር” በሚል ስያሜ የቴኳንዶ ማሰልጠኛ  በመመስረት ያለፉትን 9 ዓመታት  እየሰራ  ቆይቷል። አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቅርንጫፎችም በሁሉም የዕድሜ ደረጃዎች ከ150 በላይ ሰልጣኞችን እያስተማረበት ነው።


ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ለሰዎች ምክር በመስጠት የታወቁ አንድ ብልህና ጨዋታ አዋቂ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንድ ጅል ዛፍ ጫፍ ላይ ሆኖ፤
“አባቴ እባክዎ ምክር ፈልጌያለሁ ይርዱኝ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“በጄ፤ ምን ልምከርህ?”
“ይቺን ቅርንጫፍ ልጥላት እዚች ጋ ልመታት ነው”
“መክረህ ጨርሰሃል ልጄ እንደውሳኔህ ቀጥል”
ይመታዋል፡፡ ቅርንጫፉ ይወድቃል፡፡
ሌላ ቅርንጫፍ ይጠቁምና፤ “ይሄኛውንም ቅርንጫፍ ለመጣል እዚህ ጋ ልሰነትር ነው” ይላል፡፡
“መክረህ ጨርሰሃል ልጄ እንደበጀህ ቀጥል” ይሉታል፡፡
ያለውን ቦታ ሲመታው ቅርንጫፉ ተገንጥሎ ይወድቃል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ቅርንጫፎቹን ሁሉ በመጥረቢያ ገነጣጥሎ ይጨርሳል፡፡ ከዚያም፤
“አባቴ፤ ቀጥዬ የቱን ልምታ?” ይልና ይጠይቃል፡፡
“እንግዲህ የቀረህ አንተኑ ይዞ የሚወድቀውን መምታት ነው”
“መውደቁን ግን ይወድቃል?”
“አሳምሮ ይወድቃል”
“እንግዲያውስ አልምረውም!”  ብሎ የተቀመጠበትን ግንድ ከበላዩ ይመታዋል፡፡ ተገንድሶ ሲወድቅ ራሱኑ ጭንቅላቱን መትቶ ይፈነክተዋል፡፡
“አባቴ፤ ግንዱ ሙሉውን አልወድቅ አለኝ ምን ይበጀኛል?”
“መፈንከቱ አልበቃህ ብሎ ነው?  ምልክት መስጠቱ እኮ ነው፤ አልገባህም?”
“ዛሬ እሱን ሳልጥል ከእዚህ ንቅንቅ አልልም!”
“እንግዲህ በጄ አላልከኝም ክፉኛ- አክርረሃል፡፡ አናቱን ብለህ እምቢ ካለህ የቀረህ ግርጌው አደል?”
ሞኙ ከእግሩ ስር ያለውን ግንድ መከትከት ይጀምራል፡፡
“ልጄ፤ እኔ ወደምሄድበት ልሂድ ስመለስ መጨረሻህን አያለሁ”
“ምነው አባቴ እስከዳር አብረውኝ ላይቆዩ ነው? እስካሁን አብረን ቆይተን?”
“ያንተ አንሶ ለኔ እንዳይተርፍ ብዬ ነዋ! ግዴለህም ከሶስታችን አንዳችን ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንቆይ፡፡ ኋላ መጨረሻህን ባይ ነው የሚሻለኝ!” ብለው ሄዱ፡፡
ሽማግሌው ሲመለሱ ግንዱም ሰውዬውም ወድቀው አገኟቸው፡፡ ሰውዬው እግሩ ተሰብሮ ወገቡ ተቀጥቅጦ ሲያቃስት ደረሱ፡፡
“ይሄውልዎት አባቴ ተሰበርኩ ግን ግንዱን ጥዬዋለሁ”
“እሱም አፍ ቢኖረው እንዳንተው ጣልኩት ነበር የሚለው፡፡ አይ የናንተ ነገር ተያይዞ መውደቅ እንጂ ተደጋግፎ መቆም አልሆነላችሁም” አሉት፡፡

***
መክሮ የጨረሰ የሌላ ምክር አይሰማም፡፡ ወይም አያስፈልገኝም ይላል፡፡ እራሱን ጭምር ይዞ የሚወድቀውን ግንድ በመጣል የሚረካ ብዙ ግብዝ አይተናል እያየንም ነው፡፡ ይህ ሂደት በፖለቲካ ፓርቲ፣ በመንግስታዊ መዋቅሮች፣ በየቢሮው ወዘተ የአዘቦት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ጉዟችን ሁሉ ደክሞ ደክሞ እንደገና ከዜሮ የመጀመር የሆነው አንድም በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ “ቀጥዬ የቱን ልምታ?” ማለት እንጂ “ቀጥዬ የቱን ላድነው” የሚል ሰው አልተዋጣልንም፡፡ በዚህም ቁልቁል ማደግን ባህል አድርገነዋል፡፡ ሌላው ፈሊጣችን ደግሞ ብንቆስልም ብንደማም ካደረስነው ጥፋትና ከደረሰብን ጉዳትም ለመማር አለመቻላችን ነው፡፡ “ተሳስቼ ይሆን?” ከማለት ይልቅ፣ “ካለመስዋዕትነት ድል የለም” ማለትን እናዘወትራለን፡፡
አንድያችን ተንኮታኩተን ካልወደቅን “ያለምኩትን ብለቅ አይማረኝ” እያልን ሙጭጭ ማለት ነው፡፡ የእርግማን ክፉ ከትንሽም ከትልቅም ስህተት ፈጽሞ አለመማር ነው፡፡
ራስን በአዲስ መላ፣ በአዲስ መርህ፣ በአዲስ ፕሮግራም ከመውለድ ይልቅ ከትላንቱ ክታቤ ጋር ልሙት ማለትን ለደጉም ለክፉውም የምንምልበት ቃለ-መሀላ አድርገነዋል፡፡
የእኛ ነገር “ተፍቆ ጥርስ አይሆን፣ ተመክሮ ልብ አይሆን” ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
የትላንት ቂም፣ የትላንት ያደረ - ሂሳብ፣ አገር ላያለማ  ነገር፣ ከእነ ግንዳችን ካልወደቅን ያሰኘናል፡፡ የቡድንና የቡድን አባቶች  ብሎ ተቧድኖ “ከቦምብ ከመትረየስ” ከማለት ይልቅ፣ ቢያንስ “ከሰማይ በራሪ-ከምድር ተሽከርካሪ” ማለት መሻሉን ካላየን እድሜ -አለማችንን ጠብ-ጠማሽ ሆነን እንደመቅረት ነው፡፡ ከበረታን በዱሮ በሬ ማረስ ይቻላል ብሎ ቢነሱ እንኳ የዱሮ እልህ፣ የዱሮ ጉልበት፣ የዱሮ መሬትና የዱሮ የእህል ዘር እንደ ልብ ስለማይገኝ አርቆ ማሰብ  ተገቢ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ በሬ በአቅልና በተገቢው ማሳ ላይ ይውላል ብሎ ማሰብም አዲስ ባዩ ቁጥር ጉሮ - ወሽባዬ ማለት ይሆናል፡፡ የወረት ውሻ ስሟ ወለተ - ጊዮርጊስ ነው እንዲሉ፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደባባይ ላይ የሚታዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ቡድኖች “ሁሉን ጥዬ እኔ ልታይበት፣” “እኔ ልዩ የክት ልብስ አለኝ” ከሚለው እምነት ይልቅ የተግባር ቅደም -ተከተላቸውን መልክ በማስያዝ፣ የፖለቲካው ስር የሰደደ ችግር በጋራስ ሆነን ሊፈታ ይችላልን? ብለው፣ አስቀድሞ የተረጋጋ ማረፊያ ህዝቡ ውስጥ፣ ቀጥሎ በየፖለቲካ መዋቅሩ ላይ፤ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የአየር ጠባይ አንፃር ሲታይ፣ ምንም ነገር ቀላል ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ጊዜ አለኝ ብሎ መዘግየትም ሞኝነት ነው፡፡ ከትላንት የምንበደረው ጊዜ እንኳ ቢገኝ መውሰድ ነው የሚባልበት ዓይነት ትግል ጠይቋል ወቅቱ፡፡ ከቶውንም ሁሉም የፖለቲካ ነገር በራስ የሚሰራ፣ የገዛ አፈርን  እያሸተቱ ከህዝቡ ጋር ተሆኖ የሚሰራ እንጂ የማናቸውም ቴክኖሎጂ የሩቅ - መቆጣጠሪያ (Remote control) የሚከናወነው አይደለም፡፡ እንደ ዱሮው “በጠባቧ ቢሮአችን  ተቀምጠን የሰፊውን ህዝብ  የልብ ትርታ እናዳምጣለን /እንቆጣጠራለን!” የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡ የየቢሮውን ቀይ - ጥብጣብ ማሸነፍን  ይጠይቃል፡፡ የህዝቡን ልብ  በመንፈስም በዐይነ-ሥጋም ማሸነፍን የግድ ይላል፡፡
ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ እንግዲህ “መቀመጫ ያገኘ እግሩን መዘርጊያ አያጣም” ለመባባል ይቻላል!!     በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፈው የሙስሊሙ ቁጥር አናሳ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት  የተሳታፊዎች ልየታ  በድጋሚ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል። በሙስሊሙ በኩል የቀረቡ አጀንዳዎች በምክክሩ ውስጥ እንዲካተቱም ጠይቋል።
“የሙስሊሞች ተሳትፎ በሕዝባችን ቁጥር ልክ መሆን አለበት” ያለው ም/ቤቱ”፤ የተሳታፊዎችና የአወያዮች ቁጥር በኮሚሽኑ የአካታችነት መርህ አማካይነት አንዲታይ አመልክቷል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የበላይ ጠባቂ፣ ለፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በፃፈው ደብዳቤ፤  የሕዝበ ሙስሊሙን የምክክር እጀንዳዎች ለጉባኤው ለማሰማትና ለማብራራት የሚችሉ ተገቢ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ተወካዮች እንዲካተቱ የሚጠይቅ ሃሳብ ከህዝቡ መምጣቱን ገልጿል። በዚህም ምክንያት “ስብጥሩ በፍትሐዊነት እንደገና ይቃኝ” ሲል ጠይቋል።


ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪና ግጭት ባለባቸው የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችን ሳያካትት፣ በ10 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታ ቢያካሂድም፣ “የሙስሊሙ ቁጥር አነስተኛ ነው” ብሏል - ጠቅላይ ምክር ቤቱ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካዮች ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ሦስት ሃላፊዎች ጋር  ውይይት ማድረጋቸውም ተነግሯል። “በባለሞያ በተሰጠ መግለጫ ላይም  በተሳታፊና በአወያይ ደረጃ የሙስሊሞችን ተሳትፎ እንዲነገረን ብንጠይቅም፣ ከምክክር ኮሚሽኑ ምላሽ አልተሰጠንም” ሲል ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው የጠየቀው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ የቀረቡ የመስሊሙ አጃንዳዎች እንዲካተቱና ህዝበ ሙስሊሙም በቁጥሩ ልክ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቀርቧል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችል የታመነበት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

      በምስራቅ ሐረርጌ ዞን “ጫት አምራች” የተባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመወሰኑ ሳቢያ፣ ጫት አምራች ገበሬዎችና ነጋዴዎች ለስደት መዳረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በጫት ምርት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ቀረጥ በጫት ንግድ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን እንኳን ለማግኘት ተፈታትኗቸዋል ነው የተባለው፡፡


ከሁለት ዓመታት ወዲህ ተወስኗል የተባለው ከፍተኛ የጫት ቀረጥ ባስከተለው ጫና፣ ገበሬዎች ለነጋዴዎች ጫት የሚያስረክቡበትን ዋጋ እንዲያረክሱ እንዳስገደዳቸው የዞኑ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። በአንድ ኪሎ ግራም ጫት ከፍ ያለ ቀረጥ መጣሉን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ይህም ከፍተኛ ቀረጥ ጫናውን አምራች ገበሬዎች ላይ ማሳረፉን አስረድተዋል።
“ቀረጡ የተወሰነው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ይህም በሕጋዊ መንገድ  ወደ ሶማሊያ (ሞቃዲሾ)፣ ሶማሊላንድና ፑንትላንድ የሚላከውን የጫት መጠን በእጅጉ እንደቀነሰው ይገልጻሉ።
አቶ አብዲሳ የተባሉ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በጫት ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ እንደ ገለፁት፣ ቀደም ሲል ለጫት የሚከፈለው ቀረጥ በአንድ ኪሎግራም 5 ዶላር ነበር።
ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ወደ ሶማሊያ የሚላከው ጫት ላይ በአንድ ኪሎግራም 10 ዶላር (570 ብር ገደማ) ቀረጥ መጣሉ፣ በነጋዴው ላይ ጫና በመፍጠሩ ጫትን ከገበሬዎች በርካሽ ዋጋ እንዲረከብ ማድረጉን  ይገልጻሉ። ቀረጡን ላለመክፈል ሲሉም በርካታ ነጋዴዎች ሕገ ወጥ አካሄድ መምረጣቸውንም ጠቁመዋል።


የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያደረገው ጥናት ለዚህ ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ አስተዋጽዖ ማድረጉን የሚናገሩት ነጋዴው፤ በተለይ ጥናቱን ባደረገው ቡድን ውስጥ የተካተቱት ባለሙያዎች “ስለጫት አመራረትና የሽያጭ ሂደት ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው መሆናቸው”  ለችግሩ ያስረዳሉ፡፡
“ቀደም ሲል ጫት ወደ ሶማሊያ ተወስዶ፣ በዶላርም፤ በሶማሊያ ሽልንግም፤ በብርም ይሸጥ ነበር። ነጋዴው ሁሉ ከዚያ ሽያጭ የተገኘውን ብር ሰብስቦ፣  ወደ ባንክ ያስገባል። ይሁንና የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ነጋዴው ሕገ ወጥ ንግድን መረጠ” ብለዋል - አቶ አብዲሳ ለአዲስ አድማስ።
በሌላ በኩል፣ መንግስት ከምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖች ወደ ሶማሊያ ክልል በቀን የሚገባው የጫት መጠን ወደ 17 ሺህ እንዲወርድ ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ የጫት ኮታው ወደ 127 ሺህ ኪሎግራም እንዲመለስ መደረጉን አቶ አብዲሳ ያወሳሉ። ግን ውሳኔው የጫት ዋጋን ከመርከስ አላዳነውም ይላሉ።


ይህም ሕገ ወጥ ንግድ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያቋቋማቸውን ኬላዎች ጥሶ በማለፍ የሚከወን እንደሆነ ነጋዴው ያብራራሉ። ንግዱን ለማቀላጠፍ ሲባል፣ ለአንድ ‘አይሱዙ’ የጭነት መኪና እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ በየኬላው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጉቦ እየተሰጠ እንደሚታለፍ ነጋዴው ጠቅሰዋል።
የጫት ቀረጡ ምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ ላይ ተጽዕኖውን ቢያሳርፍም፣ በተለይ ምስራቅ ሐረርጌ ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን አቶ አብዲሳ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። “የጫት ምርቱን ወደ ሶማሊያ በብዛት የሚልከውና፣ ሌሎች አማራጭ ምርቶችን የማያመርተው የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ስለሆነ፣ ጉዳቱ የከፋ ሆኖበታል።” ብለዋል።
በጋራ ሙለታ፣ ኦቦራ፣ ፈዲስ እና ጃርሶ አካባቢዎች የሚኖሩ ጫት አምራች ገበሬዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እያዳገታቸው መምጣቱ የጠቀሱት የዞኑ ነዋሪዎች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ሐረር፣ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባና ጅግጅጋ መሰደዳቸውንም ተናግረዋል።


እነዚሁ ጫት አምራች ገበሬዎች ከዚህ በፊት ለጫት ምርት ስራ የሚጠቀሙባቸውን የውሃ ፓምፕና ጄኔሬተሮች፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤታቸውን የብረት በር ከመሸጥ አንስቶ እስከ ማገዶ እንጨት ለቀማ ድረስ የጉልበት ስራዎችን በመስራት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እየጣሩ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አክለው ገልፀዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደርም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጡም የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ችግሩ እየሰፋና እየከፋ እንደሚመጣ ነው ያስጠነቀቁት።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ምስራቅ ሐረርጌ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ ዘንድ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም፣ ሙከራችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ስልጤ ዞን፣ ስልጢ ወረዳ የበልግ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ130 በላይ አባወራዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል። ለበልግና ለመኸር የተዘጋጀ የእርሻ መሬት በጎርፍ እንደተያዘም ተገልጿል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ከመደበኛው መጠን በላይ እየጣለ በሚገኘው የበልግ ዝናብ ሳቢያ ጎፍለላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 132 አባወራዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።
150 ቤቶች እና 235 ሄክታር የእርሻ መሬት በጎርፍ እንደተያዙም የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ አደጋው በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።
“በአሁኑ ሰዓት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ አባወራዎች በጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠለሉ አድርገናል” ያሉት ሃላፊዋ፣ ከፌደራልና ክልል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለእነዚሁ ተፈናቃዮች የምግብ ዕርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሃላባ ዞን በደረሰው የጎርፍ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር ማስታወቁ የሚታወስ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)፣ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።የአገራችንን የግማሽ ምእተ አመት የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ  እንቅስቃሴ የሚያስቃኘው  የኮሎኔል መርሻ ወዳጆ አዲስ መጽሐፍ፣ የፊታችን እሁድ ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም  ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የመጽሐፉም ርእስ  ”በሦስቱ መንግስታት ያጋጠሙኝ እድሎችና ተግዳሮቶች”  የሚል ነው፡፡

ደራሲው፣ ከፖሊስ መኮንንነት አንስቶ እስከ ሚኒስትርነት ባለው የሥራ ህይወታቸው  ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት የቻሉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ (አባዲና)  ዋና አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ኮሎኔል መርሻ፤ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ  የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል  ሳይንስና  በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፤ በአሜሪካና በህንድም  የሁለተኛ ዲግሪ  ትምህርታቸውን  ተከታትለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካደረጉት ከብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ዲቡ ጋር በቅርበት የመሥራት እድል ያገኙት  ኮሎኔል መርሻ ወዳጆ፤ ከጄነራሉ ጋር በመሆንም ሰራዊቱን የማቋቋም ሚና ተጫውተዋል፡፡

ኮሎኔል መርሻ፣ የማእከላዊ ፕላን ኢንስፔክሽን መምሪያ ኃላፊ ሆነው የሰሩ  ሲሆን፤ በ1977 ዓ.ም  የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስትር በመሆንም አገልግለዋል፡፡

በ423 ገጾች የተቀነበበው  መጽሐፋቸው 3 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ህይወት  ዳስሰውበታል፡፡ ይህንን የሥራና የህይወት ታሪካቸው የተካተተበት መጽሐፍን አዘጋጅቶ ለማሳተም 3 ዓመት ያህል እንደወሰደባቸውም ኮሎኔሉ ተናግረዋል፡፡

”በሦስቱ መንግስታት ያጋጠሙኝ እድሎችና ተግዳሮቶች” የተሰኘው የኮሎኔል መርሻ ወዳጆ መጽሐፍ በ750 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን  የመጽሐፍ ምረቃ መርሐ-ግብር የሚያዘጋጀውና የሚያስተባብረው  ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለህዝብ ባቀረበቻቸውና ከፍተኛ ተወዳጅነት ባገኘችባቸው ”ላሊበላ“ ፣ ”ገዳም“ ፣ ”በላልበልሃ“ በተሰኙ ነጠላ ዜማዎቿ  የምትታወቀው ድምጻዊት ለምለም ኃ/ሚካኤል፤ ”ማያዬ“ የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሟን የፊታችን አርብ ትለቃለች፡፡

ሰርቶ ለማጠናቀቅ ዘጠኝ ዓመት እንደፈጀ የተነገረለት አዲሱ የሙዚቃ አልበም 12 ያህል ዜማዎች የተካተቱበት ሲሆን፤ አንጋፋው ናሆም ሪከርድስ ፕሮዱዩስ አድርጎታል፡፡

በዚህ የሙዚቃ አልበም ውስጥ ኤልያስ መልካን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

አዲሱን የሙዚቃ አልበም  አስመልክቶ ዛሬ ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ድምጻዊቷና የሙዚቃ ባለሙያዎች በማርዮት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተነገረው፤ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ኤልያስ መልካ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ታምሩ አማረ፣ አዲስ ፍቃዱና ብሩክ ተቀባ በቅንብር፤ ወንድወሰን ይሁብ፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ ጥላሁን ሰማው፣ በግጥም ሲሳተፉ፤ ኤልያስ መልካ፣ አንተነህ ወራሽ፣ እሱባለው ይታየው፣ ብስራት ሱራፌል፣ ዘርአ ብሩክ ሰማው በዜማ ተሳትፈዋል፡፡ በሚክሲንግና ማስተሪንግ ሰለሞን ኃይለማርያም የተሳተፈ ሲሆን፤ በፕሮዱዩሰርነት ወንድወሰን ይሁብ እንደተሳተፈበት ታውቋል፡፡

”ማያዬ“ የተሰኘው የድምጻዊት ለምለም ኃ/ሚካኤል አዲስ የሙዚቃ አልበም የፊታችን አርብ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በናሆም ሪኮርድስ የዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዓለማቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይለቀቃል ተብሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በባሌ አጋርፋ የተወለደችው ድምጻዊቷ፤ የሁለት ሴት ልጆች እናት ስትሆን፣ ላለፉት 10 ዓመታት በትወናና በድምጻዊነት የኪነጥበብ ዘርፍ ስታገለግል መቆየቷ ተጠቁሟል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቲያትር ጥበባት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘችው ለምለም ኃ/ሚካኤል፤ ከዚሁ የትምህርት ክፍል በቲያትር ፎር ዴቨሎፕመንት የሁለተኛ ድግሪ እጩ ተመራቂ ናት፡፡

Saturday, 11 May 2024 00:00

የተሻለ ይገባታል

    ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊና የተሟላ እድገት አስተማማኝነት፣ የስርአተ ጾታ እኩልነትን ማስፈንና በተለይም የህብረተሰብና የሀገር ተፈጥሮአዊ የህልውና መሰረት የሆኑትን ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማያወላዳ መልኩ ማረጋገጥ ለጥያቄ የማይቀርብ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡
በከተማችን ባለፉት ተከታታይ የለውጥ አመታት ለትውልድ የሚተላለፉ ትላልቅና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በመጨረስና ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በማሳየት አንጸባራቂ ውጤቶችን ያስመዘገበው መንግስትም፤ የሴቶችን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከልና ሁለንተናዊ ተሳትፎዋቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ባለፈ አስተማማኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው የተጋላጭነታቸውን ምንጭ በማድረቅና አስፈላጊውን ስራዎች በመስራት ላይ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ቆርጦ በመነሳት፣ በከተማችን አዲስ አበባ ደቡባዊ አቅጣጫ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያው ፈርቀዳጅ የሆነ የሴቶች የተሀድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በከፍተኛ ጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ሌላኛውን ታሪካዊ አሻራ አኑሯል፡፡


ይህ ማእከል በአንድ ዙር በሺዎች የሚቆጠሩ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ እና ለማህበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ሴቶችን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ምግብ፤ መኝታና አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ ፍላጎቶችን አቅርቦ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ ሞያዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍና ስልጠናዎችን በመስጠት ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ማእከሉ በውስጡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የስነ-ውበት ፤የሞግዚትነት ወይም የህጻናት ክብካቤ ፤የመስተንግዶ፤የአሌክትሪክና የሸክላ የእንጨት ስራዎች፤እንዲሁም የጋርመንት ስልጠና እና ሌሎች ዘርፈብዙ አገልግሎቶችን አካቷል፡፡ የግንባታ ጥራቱም እልፍ ሴቶችን ከአስከፊው የወሲብ ንግድ ወይም ከጨለማ ህይወት አርነት በማውጣት የአዲስ ብሩህ ተስፋ ህይወት ብርሃን እንደሚያጎናጽፍ ብሎም ለከተማችን ብቻ ሳይሆን ለክልል መስተዳድር እህት ከተሞችም አንድ ምእራፍ ወደፊት የሚያሻግር ተግባራዊ ትምህርት እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡


ይህ ማዕከል በክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሀሳብ አመንጪነት የብዙሀን ሴቶች መኖሪያ በሆነችው መዲናችን በተገቢው መንገድ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መጥቀም ያልቻሉ
ከዚህም ባለፈ ለዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን በማስተዋል፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የረጅም ጊዜ ጥናት እንዲደረግበት አቅጣጫ በማስቀመጥና ለዘርፉ ምሁራኖች የተለያዩ ገንቢ ሀሳቦችን በማቅረብ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በመከታተል አላማውን ለማሳካት በሚያስችል መልከአ ምድራዊ አቀማመጥና ምቹ የአየር ንብረት ላይ እንዲገነባ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በተለይም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሀሳቡን ከማመንጨት አንስቶ እስከ ማገባደጃው ባለው ሂደት በልዩ አይን ክትትል በማድረግ በ11 ወራት እንዲጠናቀቅ ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ ችግር ፈቺ ሀሳብ የማፍለቅና ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም አቅማቸውን በተግባር ያሳዩበት ነው፡፡ማእከሉ በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የየራሳቸው ኪነ-ህንጻዊ ውበት እንዲሁም የስፋትና የከፍታ ደረጃ ያላቸው ህንጻዎችን የያዘ፤ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን፤ግዙፍ ኤልኢዲ ስክሪን የተገጠመለት የመዝናኛ አምፊ ቴአትር፤ የአትክልት እርሻ ማሳን ብሎም ከፍተኛ መጠን ያለው ንጹህ ውሃ የሚያቀርብ የራሱ የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ከነ ግዙፍ ታንከሩ የያዘ ነው፡፡


ይህ ማዕከል የስርአተ ጾታ እኩልነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ለወደፊት አጠናክረን የምንከተለውን የፖለቲካ አቅጣጫ ከማመላከት አኳያ በመዲናችንም ሆነ በሀገራችን የመጀመሪያው ቢሆንም ተጨባጭ ውጤትና ስር ነቀል ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እንደሚያመጣ ጅማሬው ያመላክታል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ተቋም የሚገኘው ተሞክሮ ተቀምሮና ሰፍቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በእህት ክልል መስተዳድር ከተሞችና በአጎራባች ሀገራት
ትምህርት የሚወሰድበት ተምሳሌት ፕሮጀክት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡

ፕሉታርክ እንደጻፈው የሚከተለው አፈ-ታሪክ አለ።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ454 ዓመት፣ ኮሪዮሳኑስ የሚባል የሮማ ወታደራዊ መሪ ነበር። በጥንታዊ ሮም ታላቅ ወታደራዊ ጀግና ነው የተባለ ነበር። በርካታ ጦርነቶችን አሸንፏል። በዚህም አገሪቱን ከብዙ ጥፋት አድኗታል ተብሎለታል። ብዙውን ህይወቱን በጦር ሜዳ ስላሳለፈ በአካል የሚያውቁት ጥቂት ሮማውያን ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያት ከሞላ ጎደል ወደ አፈ-ታሪክነት ተለውጧል። አፈ-ታሪክ ታሪኩ እነሆ።


በ454 (ከክ.ል.በፊት) ወታደራዊ መሪ ኮሪዩሳኑስ የጦር ሜዳ ዝናዬንና ስሜን ተጠቅሜ ፖለቲካው ውስጥ ልግባ ሲል አሰበ። ከፍተኛ የምክር ቤት እንደራሴ ለመሆን ለሚያበቃው ቦታም የምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀረበ። የምርጫ ተወዳዳሪዎች ወደተወለዱበት ቦታ ሄደው፣ ለጎሳቸው ሰው ንግግር ማድረጋቸው የዚያን ጊዜ ባህላዊ ህግ ነበርና፤ ኮሪዮላኑስም ወደ ህዝቡ ቀርቦ 17 ዓመት ሙሉ ለሮም ሲታገል በጦር ሜዳ በጥይት የተመታባቸውን ከደርዘን በላይ የሆኑትን የሰውነቱን ጠባሳዎች እየገለጠ አሳየ። ከዲስኩሩ ይልቅ ህዝቡን እንባ በእንባ ያደረገው የሰውነቱን ጠባሳዎች ማየት ነበር። ኮሪዮላኑስ በምርጫው እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ መሰለ።
የምርጫው ቀን ሲደርስ ኮሪዮላኑስ በድፍን የምክር ቤት አባላትና በከተማው መኳንንት ታጅቦ ወደ ምርጫው ጣቢያ ገባ። ተራው ህዝብ ይሄ ሁሉ ጉራና እመረጣለሁ የሚል ልበ-ሙሉነት ከየት መጣ አለ በሆዱ።


ኮሪዮላኑስ አብረውት የሄዱትን አብዛኛዎቹን ወገኖቹን የሚጥም ንግግር አደረገ። ሆኖም፤ ዲስኩሩ ዕብሪትና ድፍረት የተሞላበት ከመሆኑም በላይ፤ በምርጫው ያለጥርጥር እንደሚያሸንፍ፣ የጦር ሜዳ ድሎቹን እንደሚኮራባቸው የሚያሳይ ሲሆን፤ ለሱ የገዢ መደብ ወገኖች ብቻ የሚገቡ ቀልዶችን በመጨመር እየፎከረ፤ ተቃዋሚዎቹንም በንቀት በማንገዋጠጥና በቁጣ  እየወነጀለ፤ ቢመረጥ ለሮም የበለጠ ሀብት እንደሚያስገኝ ደሰኮረ። በዚህ ንግግሩ ህዝቡ የአፈ-ታሪክ ጀግናችን ይለው የነበረው ታላቁ መሪ ተራ ጉረኛ መሆኑን ታዘበ። የሁለተኛው የጉራ ንግግሩ ይዘት በአገሩ ናኘና ህዝቡ ይሄንንማ አለመምረጥ ነው ተባባለ። እንዳለውም ህዝቡ ኮሪዮላኑስን ሳይመርጠው ቀረ።
ኮሪዮላኑስ በመሸነፉ ተናዶ ወደ ጦር ሜዳው ተመለሰ። ይሁን እንጂ ያልመረጠውን ህዝብ እንደሚበቀለውና ልክ- እንደሚያገባው በምሬት ዛተ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በትልቅ መርከብ ወደ ሮም የሚገባውን እህል ለተራበው ህዝብ በነፃ ለማደል የምክር ቤቱ አባላት አስበው በጉዳዩ ለመምከር ተሰባሰቡ። በመካከል ግን ድንገት ኮሪዮላኑስ ብቅ አለና መድረኩን ቀማቸው። ይህን እህል ማከፋፈል በአጠቃላይ ለከተማይቱ ጎጂ ነው ሲል ተከራከረ። ጥቂቶቹን አሳመነ። በዚያም አላበቃ። የዲሞክራሲን ፅንሰ-ሀሳብ ጭምር ኮነነው። የህዝብ ተወካዮቹንና አዲሶቹን ተመራጮች በማስወገድ የከተማዋን አገዛዝ ለቀድሞዎቹ ገዢዎች (ስፓትራሺያን) መስጠት ይኖርብናል ሲል ክፉኛ ተሟገተ።


የኮሪዮላኑስን የመጨረሻውን ንግግር ህዝቡ ሲሰማ ቁጣው ወሰኑን ጣሰ። የህዝቡ ተወካዮች ደግሞ ኮሪዮላኑስ ህዝቡ ፊት ይቅረብ አሉ። ኮሪዮላኑስ ግን አሻፈረኝ፣ ህዝብ ፊት አልወጣም አለ። ከተማይቱ በሁሉም አቅጣጫ በህዝብ አመጽ ተቀጣጠለ። ይሄኔ ምክር ቤቱ የህዝቡን እንቅስቃሴ በመፍራት እህሉ ይከፋፈላል በሚለው ላይ ወሰነ። ሸንጎው በዚህ ህዝቡን ያረጋጋና እፎይ ያለ መሰለው። ህዝቡ ግን ኮሪዮላኑስ ያነጋግረን! ይቅርታ ይጠይቀን! ማለቱን ቀጠለ። ከፀፀተውና ጠባዩን አሳምሮ ሀሳቡን የሚያነሳ ከሆነም ወደ ጦር ሜዳ እንዲሄድ እንደሚፈቅዱለት ተናገሩ።
በመጨረሻ ኮሪዮላኑስ ህዝቡ ፊት ቀረበና ንግግር አደረገ። በዝግታና ለስለስ ባለ ቃና ጀመረና ቀስ እያለ ወደ ይፋ ዘለፋ ተሸጋገረ። ቃናው ሁሉ የዕቡይ ሆነ። የህዝብን ክብር የናቀ ዲስኩር ሆነ። ሰውን ማዋረድ ጀመረ። እሱ የበለጠ በተሳደበ ቁጥር ደግሞ የህዝቡ ቁጣ የበለጠ ገነፈለ። በመጨረሻ በጩኸት አፉን አዘጉት።
ሸንጎው ኮሪዮላኑስን በማውገዝ የሞት ፍርድ ፈረደበት። ዳኞቹንም እንደተለመደው ከታሪፒያ ቋጥኝ ቁልቁል እንዲወረውርና የሞት ቅጣት እንዲፈፀምበት አዘዛቸው። ህዝቡንም ውሳኔውን ደገፈ። ሆኖም ፓትሪሺያንኖቹ ጣልቃ ገብተው በመደራደር የሞት ቅጣቱ ወደ “ዕድሜ ልክ ከሥራ መገለል” እንዲሻሻል ተደረገ። የሮማ ታላቅ የጦር መሪ፤ ሁለተኛ ሮማ ከተማ ድርሽ እንደማይል ተረዳው፣ ህዝብም መንገድ ላይ ወጥቶ በይፋ ጨፈረ። እንደዚህ ያለ ጭፈራና በዓል ከዚህ ቀደም በሮማ ታይቶ አይታወቅም። የሮማ ህዝቦች ወራሪ ጠላት ሲያሸንፉ እንኳን እንደዚህ ዓይነት ፌሽታ አድርገው አያውቁም።

***


ከ2000 ዓመታት በፊት የሆነን ነገር መለስ ብሎ ያስተዋለ አያሌ ትምህርት ያገኛል።
ስንቶቻችን ራሳችንን ደገምን? ስንቶቻችን ራሳችንን በአፈ-ታሪኩ ውስጥ እናያለን? ሁኔታዎችን ስናጤን ታሪክ ብቻ ሳይሆን አፈ-ታሪክም ራሱን ይደግማል ያሰኘናል። ራስንም ወደፊት ነው እየሄድኩ ያለሁት ወደኋላ? ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ከትላንት እስከዛሬ ተጠይቀው በግማሽ-ጎፈሬ ግማሽ-ልጩ መልክ ተመልሰው ወይም ከናካቴው ሳይመለሱ ቀርተው፣ እስከዛሬ የሚያጨቃጭቁን አያሌ ጥያቄዎች ነፍስ-እየዘሩ፣ በአካል እየተፋጠጡን (“ዴጃ ቩ” (deja vu) እንደሚባለው) “የት ነበር ያየናቸው?” የሚያሰኝ ድግግም ስዕሎች ነበሩ ዛሬም አሉ። የድንበር ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። ሀሳብ የመግለፅ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ጥያቄ… ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። የሰብአዊ መብት ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ፤ ወዘተ የሚገርመው ግን ታሪክ-ሰሪዎቹና የፖለቲካ መሪ ተናዋዮቹም ችግር ከሞላ ጎደል መደገማቸው ነው። መፈክሮችና መዝሙሮች ሳይቀሩ ሲደገሙ ማየት አስገራሚ ነው።
ለጉድ የጎለተው ሁሉንም ይታዘባል።
ገጣሚው እንዳለው፤
“ሲጨልም ስንነቃ፣ ሲነጋ ስንተኛ
እንቅልፍ እንኳ ካቅሙ መች ሞላልን ለእኛ።
ዘመን ተዘባርቆ ዓመት ተዟዟረ
ህልምም ወደ ኋላ፣ ማየት ተጀመረ”
ገዢው ፓርቲ በሙሉ አቅም የሚመራበት ሁኔታ ሲጠፋና፤ አዳዲሶች ፓርቲዎች በተደራጀ ሁኔታ የመምራት ሁኔታ ላይ ካልሆኑ፣ ሀገር ወደፊት መራመድ አቅቷት ወደኋላ እንዳትመለስ፣ ሀገር-ወዳዶች ሁሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት መገንዘብ አለባቸው። ምን አይነት እገዛ ያስፈልጋል? ምን አይነት አቅም መፍጠር ይገባል? ብሎ ማሰብ ወሳኝነት ይኖረዋል። መድረክ ላይ ባሉ ፓርቲዎች ላይ አቃቂር ከመሰንዘር ባሻገር የእኛ አስተዋፅኦ ምን ይሁን ማለት ደግ ነው። የወቅቱ ጥሪ ይሄው ነው።
ሶስት ታዋቂ ሰዎች ስለታሪክ እንዲህ ይሉናል።
ታሪክ ራሱን ይደግማል። የታሪክ ጸሐፊ ግን አንዱን ይደግማል። (ፊሊፕ ጉዳላ- እንግሊዛዊ ፀሐፊ)
ታሪክ ራሱን አይደግምም። የታሪክ ጸሐፊ ግን አንዱን ይደግማል። (የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር)
ታሪክ ራሱን ይደግማል። ከታሪክ ስህተቶችም አንዱ ይሄ ነው (ክላርንስ ዳሮው የፈረንሳይ ጠበቃ)
ታሪክ መልኩን እየለዋወጠ ራሱን ይደግማል። በየጊዜው ግን የሚያስከፍለን ዋጋ እየጨመረ ነው የመጣው።
(ቶማስ ቤይሌ አሜሪካዊ የታሪክ ባለሙያ)
እንግዲህ የሚሰማንን መውሰድ የእኛ ፋንታ ነው።
በ1966 ዓ.ም የነበረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣ በ1983 የነበረውን የሽግግር ሁኔታና ዛሬ በሪፎርም ማግስት ያለንበትን ወቅት በሚገባ ስናጤን፣ ወደኋላ እንድናይ የሚያመላክቱ የበዙ ሁኔታዎች ስዕል እናገኛለን። ይሄ ደግሞ አሳሳቢ ነው። “ከነገር ሁሉ ምን ትጠላለህ?” ቢለው “ወደ ትላንትና መመለስ” አለ፤ የሚባለው የዚሁ ማገናዘቢያ ነው።

Page 9 of 714