
Administrator
ፌደራል መንግስት ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተገዢ እንዲሆን ተጠየቀ
የፌደራል መንግስት ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተገዢ እንዲሆን ተጠይቋል። ለሁለት የተሰነጠቁት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።
ከባለፈው ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በትግራይ ክልል፣ መቐለ ከተማ፣ ሮማናት አደባባይ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙ ተፈናቃዮች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ተገልጿል። በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ “ይበቃል፣ ወደ ቀድሞ ቀያችን መልሱን!” የሚለው መፈክር በዋናነት ሲስተጋባ እንደነበር ተጠቅሷል።
የተቃውሞ ሰልፉ ከቀን በተጨማሪ በምሽትም ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ ከተፈናቃዮች ባሻገር በተለያዩ የሞያ ዘርፎች የተሰማሩ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች እንደተሳተፉበት ለማወቅ ተችሏል። በርካታ የከተማዋ ጎዳናዎች ተዘግተው መታየታቸውን እንቅስቃሴውን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖች ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፣ በርካታ የክልሉ የፖሊስ ሃይል አባላትም በጎዳናዎቹ ላይ ተሰማርተው ነበር።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቃውሞ ሰልፉ በተጀመረበት ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ የተፈናቃዮችን ጥያቄ እንደሚደግፍ አስታውቋል። አስተዳደሩ፣ “’ይበቃል፣ ወደ ቀያችን መልሱን’ በሚል መሪ ቃል በተፈናቃዮች አማካይነት የተጠራው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ቀናና የሚደገፍ ነው” ብሏል።
“ተፈናቃዮቹ እየደረሰባቸው ላለው መከራ ተገቢ ምላሽ እየተሰጠ አይደለም” በማለት መግለጫውን የቀጠለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ “የፌደራል መንግስት የገባውን ውልና ቃል በመተግበር ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አለበት” ሲል አሳስቧል። “አሁንም በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ከአገር መከላከያ ሰራዊት ውጪ ያሉ ታጣቂ ሃይሎች ከትግራይ ክልል ይውጡ፤ በሕገ መንግስቱ አማካይነት፣ የትግራይ ክልል ግዛታዊ አንድነት ተከብሮ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው” ሲልም በመግለጫው አፅንኦት ሰጥቷል።
ከዚህ በተጓዳኝ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮጳ ሕብረትና የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ የትግራይ ሕዝብን ድምጽ በማዳመጥ የፕሪቶሪያ ውል በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ጫናቸው እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ።
“ጽላል ሲቪክ ማሕበር ማሕበረሰብ ምዕራብ ትግራይ” በተሰኘ ድርጅት አስተባባሪነት ሲደረግ የቆየው የተቃውሞ ሰልፍ፣ ባለፈው ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም ሲደመደም፣ ተፈናቃዮች በበኩላቸው የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። በዚህ የአቋም መግለጫ የፌደራል መንግስት ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ታማኝና ተገዢ በመሆን ስምምነቱን በሙሉነት እንዲያስፈፅም ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የፕሪቶሪያ የሰላም ውል እንዲፈረም ያሳየው ቁርጠኝነት ገቢራዊ እንዲሆን ሚናውን ማጉላት እንዳለበት ያነሱት ተፈናቃዮቹ፣ የትግራይ ክልል በሕገ መንግስቱ መሰረት ወደ “ቀድሞ ይዞታው” እስከሚመለስ ድረስ ሰላማዊ ተቃውሞ ማሰማታቸውን እንደሚቀጥሉ በአቋም መግለጫቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮች ለስልጣን ሲሯሯጡ የተፈናቃዮችን ስቃይ “ዘንግተዋል” ሲሉ ምሬታቸውን ያሰሙት እነዚሁ ሰልፈኞች፣ “ያለፈው ይበቃል፣ አሁን የተጣለባችሁን ሃላፊነት በአስቸኳይ ተወጡ!” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ እንዲሁም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና፣ በክልሉ ለሚገኙ የዕርዳታ ድርጅቶች የአቋም መግለጫቸውን ማድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚገኝ ኬላ ለዜጎች ሞት ምክንያት ሆኗል
• በሰላም ስም የሚደረጉ ሸፍጦች ይቁሙ ተባለ
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ የሚገኝ አንድ ኬላ ለዜጎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተገለፀ። ከግድያ በተጨማሪ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የዕገታ ተግባር እንደሚፈጽሙ ተነግሯል።
ከግልገል በለስ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘውና “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው ኬላ ላይ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ መገደላቸውን እናት ፓርቲ ባለፈው ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ “የኬላው መኖር ምክንያታዊ ያልሆነና አላስፈላጊ ነው” የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ሰሚ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ፓርቲው በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ኬላው ላይ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ታጣቂዎቹ ተሳፋሪዎችን በማንነት እየለዩ እንደሚሰውሩ፣ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገድሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን ፓርቲው የጠቀሰ ሲሆን፣ ነዋሪዎች “በአጠቃላይ የግልገል በለሱ “ቻይና ካምፕ” ኬላ የዜጎች ድብቅ ግድያ ‘ማመቻቻ ነው’ ብሎ መደምደም ይቻላል” ማለታቸውንም አክሎ አትቷል።
ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ወደ ግልገል በለስ ከተማ ይገባ የነበረውን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ቻይና ካምፕ ኬላ ላይ ታጣቂዎቹ አስቁመው ለስራ ይጓዝ የነበረን አንድ ወጣት “የዓይንህ ቀለም አላማረንም” በሚል ምክንያት ከቆመው ተሽከርካሪ አስወርደው “በአሰቃቂ ሁኔታ” መግደላችውን እናት ፓርቲ ገልጿል። የተፈጸመውን ግድያ የተመለከቱ ተሳፋሪዎች በከተማው ውስጥ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ስለሁኔታው ቢያስታውቁም፣ “ትዕዛዝ አልተሰጠንም” በሚል እርምጃ ከመውሰድ መታቀባቸውን የጠቆመው ፓርቲው፣ “’ቻይና ካምፕ’ እና ‘ኪዳነምሕረት ሰፈር’ በተባሉ አካባቢዎች ተገቢ ማጣራት ቢደረግ፣ ሌሎች የግድያ መረጃዎች ይገኛሉ። ነገር ግን መሰል ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ርብርብና ማድበስበስ አለ” በማለት አስረድቷል።
ይህንን የግድያ ድርጊት “ፈጽመዋል” የተባሉት ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ጫካ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደ ነበሩና ከክልሉ መንግስት ጋር ዕርቅ ማውረዳቸውን እናት ፓርቲ ጠቅሶ፣ እነዚሁ ታጣቂዎች ከ”ቻይና ካምፕ” ኬላ አካባቢ ወታደራዊ ካምፕ ተሰጥቷቸው ሰፍረው እንደሚገኙ አብራርቷል። በተጨማሪም ፓርቲው “በሰላም ስም ቡድኖችን እየቀለቡ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋና እገታ ይፈጽማሉ” በማለት በክልሉ መንግስት አካላት ላይ ነቀፌታውን አሰምቷል።
“በሰላም ስም የሚደረጉ ሸፍጦች ይቁሙ” ሲል ጥሪ ያቀረበው እናት ፓርቲ፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ፓርቲው አያይዞም፣ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎችን “ለከባድ ሰቆቃ እየዳረገ ነው” ሲል የጠቀሰውን ቻይና ካምፕ ኬላ “ሕዝቡን በማወያየት” በአስቸኳይ እንዲነሳ ተማጽኗል።
ተጨማሪ ድብቅ መቃብሮች “አሉባቸው” ተብለው በአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠረጠሩ እንደ ”ቻይና ካምፕ” እና “ኪዳነምሕረት ሰፈር” ዓይነት ስፍራዎች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና መሰል ተቋማት ምርመራ ተደርጎባቸው ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን እናት ፓርቲ አሳስቧል። እንዲሁም “አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ያላቸው ሚና የምርመራው አካል እንዲሆን እንጠይቃለን።” ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው።
መልዕክቶቻችሁ
ከአዲስ አድማስ ጋር እንዴት ተዋወቅን?
አዲስ አድማስን ከ13 አመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ደብረ ማርቆስ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነው የተዋወቋት። ጋዜጣዋ ቅዳሜ ከሰዓት አንዳንዴ ደግሞ እሁድ ጠዋት ትደርስ ነበር፡፡ በወቅቱ እሸት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ አባላት በተራ እየገዛን በፍቅር የምናነባት ተወዳጅ ጋዜጣ ነበረች። ለጋዜጣው አዘጋጆች ፣ አምደኞችና በትጋት ለምታነቡ የአዲስ አድማስ ወዳጆች በሙሉ እንኳን 25ኛ አመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!
ጌትነት ተመስገን (ጌች ሐበሻ)
***
አዲስ አድማስን ማንበብ የጀመርኩት ገና ታትማ መውጣት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው። በወቅቱ Yellow journalism የተስፋፋበትና ጋዜጣ ከbroadsheet ወደ tabloid የተሸጋገረበት ጊዜ ነበር። ይልቁንም tabliod ጋዜጦች በነባር ጋዜጠኞች አሉታዊ አስተሳሰብ ሥር ነበሩ። አዲስ አድማስ ግን በ100 ከሚቆጠሩ ታብሎይድ ጋዜጦች ነጥራ ወጥታለች። ሆኖም የስፖንሰር አለመኖርና የወረቀት ዋጋ መጨመር እንዲሁም ወደፊት በሚመጣው የግብር ጫና ትቀጥል ይሆን? የሚል ስጋት አለኝ። እስካሁን ያቆዩዋትን በግሌ አመሰግናለሁ።
(ተሾመ ብርሃኑ ከድር)
***
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት አርሲ ነጌሌ ከተማ ሞኪያ የተባለ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ ከብዙ መጽሔቶች ጋር ተጀቡና በተመለከትኩበት ወቅት ነው። መኮንን በተባለ በመጻሕፍት ቤቱ ባለቤት በኩል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለከተማችን አንባብያን የመጣችው ለአጭር ጊዜ ቢኾንም፣ በኤፍሬም እንዳለ ወጎች፣ በአሰፋ ጫቦ የትዝታ ፈለጎች፣ በነቢይ መኮንን ተረቶች የታጠኑ ርዕሰ አንቀጾች፣ በዓለማየሁ አንበሴ ወቅታዊ ዜናዎች፣ በእነ ሌሊሣ ግርማ መጣጥፎች ፍቅር ለመውደቅ ግን ከበቂ በላይ ጊዜ ነበር። ይህች የቅምሻ ተጽዕኖ፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በገባሁ ወቅት የማራኪ ካምፓስ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ባለው የጋዜጣ ኮርነር ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቀበኛ እንድኾን አድርጎኛል።
እንኳን ለ25ኛ ዓመት አደረሳችሁ/ አደረሰን
(ቢንያም አቡራ)
**
ከድሮም ጀምሮ አነብ ነበር፣ ይሁንና ከዕለታት አንድ ቀን ለስራ ጉዳይ ጅማ ከተማ ሄድኩኝ፣ በከተማዋ ውስጥ ስዘዋወር ጋዜጣ የሚያዞር ልጅ አየሁኝና ጠራሁኝ፣ ከዚያ ሁለት ጋዜጣ ገዛሁኝ፣ ወደ መኖርያዬ ተመልሼ ሳነብ ግን የልበወለድ አፍቃሪ ስለነበርኩኝ በአዲስ አድማስ ተማረኩኝ፣ ከዚያ ትውውቅ ወዲህ የአዲስ አድማሰ አንባቢ ብቻ ሳይሆን ሰብሳቢ ሆንኩኝ። እዚያ ከተማ ስሄድ የሳምንቱን ብቻ ሳይሆን ያለፈውን ጭምር እየገዛሁ አስቀምጣለሁኝ።
በእርግጥ አሁን በከተማዋ ውስጥ ራስ የሚያዞር ጸሐይ እንጂ ጋዜጣ የሚያዞር የለም።
ያም ሆኖ ዕድሉ ሲገኝ በአካል ካልተገኘ በኦንላይን አነባለሁኝ። የምወደው ጥበብ የሚሰኘውን አምድ ነው፡፡ ጋዜጣውን በሙሉ ባነብም መጀመርያ ግን የኤፍሬም እንዳለን ሥራና አጭር ልበወለድ ነው የማነበው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አንብቤ የማስታውሰው አጭር ልበወለድ “ጭልፊቱ” የተሰኘው ትርጉም ልበወለድ ነው፣ አቤት አፍቃሪው ፌዴሪጎ እንዴት አሳዝኖኝ ነበር፣ እንዴት አስደስቶኝ ነበር፤ ለስንት ሰውስ ተረኩት።
ይህን አጭር ልበወለድ የያዘው ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም አሁንም ድረስ አለኝ። እና አዲስ አድማስ አንጀት የምታርስ፣ እኔን ከመሻቴ የምታደርስ ስለመሰለኝ ከተዋወቅኋት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ አነባታለሁ፡፡ እውንም በአዲስ አድማስ ተምሬአለሁኝ፣
ተዝናንቻለሁኝ፤ ተሻሽያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ድሮ ጅማ እየተገኘች እንደልብ አነባት ዘንድ እናፍቃለሁኝ።
(ከድር ነብሶ)
***
አዲስ አድማስን በታላቁ ወንድሜ አማካይነት ነው ማንበብ የጀመርኩት፤ አሁንም እያነበብኩ አለሁ፡፡
(ሃኒቾ ከጦር ሃይሎች)
የኮካኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ በኢትዮጵያ “ከፍተኛው ቀጣሪ” ተባለ
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በኢትዮጵያ የ2025 ከፍተኛ ቀጣሪ ኩባንያ መሆኑን “ቶፕ ኢምፕሎዮ ኢንስቲትዩት” የተሰኘ ተቋም አስታወቀ።
ተቋሙ ባካሄደው ጥናት መሰረት፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ በ2025 የከፍተኛ ቀጣሪ ደረጃ እውቅና ካገኙ ስድስት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ የገበያ ተደራሽነቱን እያሰፋ ኩባንያው፤ የሰራተኛ ቅጥርንም ገበያው በሚፈልገው ልክ እያሰፋ መሆኑ ተጠቁሟል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት በአገሪቱ የስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት አስፈላጊነት ሲገለፅ ቆይቷል።
ይሁንና የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፣ በኢትዮጵያ የፈጠረው ከፍተኛ የስራ እድልና የቅጥር አድማስ የ2025 ከፍተኛውን የዕውቅና ማእረግ ለመያዝ እንዳስቻለው ለማወቅ ተችሏል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሪል ዊልሰን ሲናገሩ፤ “ሽልማቱ ኩባንያው ከፍተኛ አቅምና አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች ለመሳብና ለማቆየት እንዲሁም፣ በሰው ሐብት አስተዳደር እድገት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን አቋም ያንፀባርቃል” ብለዋል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በአፍሪካ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከ720 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት “ቶፕ ኢምፕሎዮ ኢንስቲትዩት” ጠቁሟል።
ኩባንያው በ15 ሀገራት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን ስድስት ቁልፍ ገበያዎቹ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ናሚቢያ ናቸው። በተጨማሪም በታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ኮሞሮስ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶና ማላዊ ከፍተኛ ገበያ እንዳለው ተገልጿል።
ሁሌም ለመታረም ዝግጁ ነን!
ባለፈው ሳምንት ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም “የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎችን ጉዳይ ወደ ፍ/ቤት ወስጄዋለሁ” ከሚለው የፊት ገፅ ዜና ጋር የወጣው ኒቃም የለበሱ እንስቶች ምስል ስህተት መሆኑን ውድ አንባቢያን ደውለው ጠቁመውናል፡፡ ተማሪዎቹ የጠየቁት ሂጃብ እንጂ ኒቃም አይደለም ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለተፈፀመው የምስል ስህተት ታላቅ ይቅርታ እየጠየቅን፣ በመቆርቆር ስሜት፣ ስህተታችንን ላረሙን ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ለ25ኛ ዓመታችን የደረስነው በናንተ ፍቅርና ድጋፍ ነው ስንል፣ ይህንን ማለታችን ነው፡፡ ሁሌም ለመታረም ዝግጁ ነን፡፡
የ25 ዓመት የሃሳብና የዕውቀት ጉዞ!!
የመጀመሪያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር - የዛሬ 25 ዓመት በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለ አንድ ቅዳሜ በስተቀር ጋዜጣው ያልታተመበት ጊዜ የለም፡፡ ያም ቢሆን የተከሰተው በ97 ምርጫ ማግስት በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ነበር፡፡
የዛሬ 20 ዓመት፣ የአዲስ አድማስ ጠንሳሽ፣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ (አሴ) በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ባለፈበት ወቅት እንኳን ጋዜጣው ሳይታተም አልቀረም፡፡ ረቡዕ ከቀብር በኋላ ቢሮ ገብተን የቅዳሜውን ጋዜጣ ስናዘጋጅ ነበር፡፡ ከሃዘናችን ጋር እየታገልንም ቢሆን የቅዳሜውን ሳምንታዊ ጋዜጣ በጉጉት ለሚጠብቁን ውድ አንባቢያን አድርሰናል፡፡ በዚህም ኩራትና ክብር ይሰማናል፡፡ የጋዜጣው መሥራች አሰፋ ጎሳዬም ቢሆን፣ ከምንም በፊት ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለአንባቢያን ነበርና፡፡
እነሆ አዲስ አድማስ ከዚያም በኋላ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥራ፣ በብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች አልፍ፣ እነሆ ለ25ኛ ዓመቷ በቅታለች፡፡ ኮረኮንች በበዛበት የአገራችን የግል ፕሬስ፣ ሩብ ክፍለዘመን ቀላል ዕድሜ አይደለም፡፡ ረዥም ዕድሜ ነው፡፡ ትልቅ ስኬትም ነው ማለት ያስደፍራል፡፡
ለዚህ የደረስነው ግን በውድ አንባቢያን ገንቢ አስተያየትና ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ለአዲስ አድማስ ህልውናና በስኬት መቀጠል ከእኛ ከአዘጋጆቹ እኩል የሚጨነቁና የሚጠበቡት የረዥም ጊዜ ጽሁፍ አቅራቢዎችም ሌሎቹ ትልቅ ምስጋና የምንቸራቸው ባለውለታዎች ናቸው፡፡
ማስታወቂያቸውን በጋዜጣችን ላይ የሚያወጡ የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማትም ሁነኛ አጋሮቻችን ናቸውና ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡
መጪው ጊዜም ነጻ ሃሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት፣ ዕውቀትና ሥልጡንነት የሚያብብበት፣ የንባብ ባህል የሚዳብርበት እንዲሆን እንመኛለን፤ ለዚያም በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ በኢትዮጵያ "ከፍተኛው ቀጣሪ" ተባለ
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በኢትዮጵያ የ2025 ከፍተኛ ቀጣሪ ኩባንያ መሆኑን "ቶፕ ኢምፕሎዪ ኢንስቲትዩት" የተሰኘ ተቋም አስታወቀ። ተቋሙ ባካሄደው ጥናት መሰረት፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ የ2025 የከፍተኛ ቀጣሪ ደረጃ እውቅና ካገኙ ስድስት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ የገበያ ተደራሽነቱን እያሰፋ የሚገኘው ኩባንያው፤ የሰራተኛ ቅጥርንም ገበያው በሚፈልገው ልክ እያሳደገ መሆኑ ተጠቁሟል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት በአገሪቱ የስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የማበረታታት አስፈላጊነት ሲገለፅ ቆይቷል።
ይሁንና የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፣ በኢትዮጵያ የፈጠረው ከፍተኛ የስራ እድልና የቅጥር አድማስ፣ የ2025 ከፍተኛውን የዕውቅና ማዕረግ ለመያዝ እንዳስቻለው ለማወቅ ተችሏል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሪል ዊልሰን ሲናገሩ፤ "ሽልማቱ ኩባንያው ከፍተኛ አቅምና አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች ለመሳብና ለማቆየት እንዲሁም፣ በሰው ሐብት አስተዳደር እድገት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን አቋም ያንፀባርቃል" ብለዋል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በአፍሪካ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከ720 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት "ቶፕ ኢምፕሎዪ ኢንስቲትዩት" ጠቁሟል። ኩባንያው በ15 ሀገራት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን፤ ስድስት ቁልፍ ገበያዎቹ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ናሚቢያ ናቸው። በተጨማሪም በታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ኮሞሮስ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶና ማላዊ ከፍተኛ ገበያ እንዳለው ተገልጿል።
በተቋሙ መስፈርት መሰረት፣ ኩባንያዎች የከፍተኛ ቀጣሪነት (Top Employer) የዕውቅና ሽልማት የሚያገኙት የሥራ ከባቢያቸው፣የሠራተኞችን አቅምና ችሎታ ለማጎልበት የሚያደርጉት ጥረቶች፣ አካታችነት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የሰው ሃብታቸውን ለማበልጸግ ያላቸው ቁርጠኝነት ከተገመገመ በኋላ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡