Administrator

Administrator


               ዶክሌ በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ ባጋጠመው የልብ ህመም  በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ በአሜሪካ ዋሽንግተን ሜድስታር ሆስፒታል ውስጥ በ57 ዓመት ዕድሜው ማረፉ ተነግሯል፡፡
“ዶክሌ ቅንና ታዛዥ ባለሙያ ነበረ” ያለው የሙያ አጋሩ  አርቲስት ቴዎድሮስ ለገሰ፤ ኮሜዲያኑ በደረሰበት የልብ ህመም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲረዱት እንደነበር ጠቁሞ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ታሞ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እንዲያገኝ ቢደረግም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ኮሜዲያን ዶክሌ፤ በመድሐኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።
የእሱንም ሆነ የቤተሰቡን ህይወት ለመምራት በመካኒክነት ሙያ ትምህርት ቀስሞ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣በኋላ ላይ የጥበቡን ዓለም በመቀላቀል በኮሜዲ ዘርፍ ተወዳጅነትንና ከበሬታን የተቀዳጀባቸው በርካታ የተዋጣላቸው ሥራዎችን ለማቅረብ በቅቷል፡፡በስታንድ አፕ ኮሜዲ አያሌ  ቁምነገር አዘል ቀልዶችን እንዳቀረበ የሚነገርለት ኮሜዲያኑ፤ በሙሉ ጊዜ የፊልም ስራዎችም ዝናና ዕውቅናን ለማትረፍ ችሏል፡፡ ለዚህም  #የራስ አሽከር; የተሰኘው ታሪክ ቀመስ ፊልም ላይ ያሳየው ድንቅ የትወና ብቃቱ ይጠቀስለታል፡፡
ከስምንት አመት በፊት ለስራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ በማቅናት ኑሮውን በዚያው አድርጎ የቆየው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ)፤ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበር።
የኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ የቀብር ስነስርአት የሚፈጸመው በትውልድ ሀገሩ ኢትየጵያ ነው የተባለ ሲሆን ለዚህም ማስፈጸሚያ ወጪ ለማሰባሰብና ቤተሰቦቹን ለመርዳት የጎፈንድሚ አካውንት መከፈቱ ታውቋል፡፡


    በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
                                   (ጌታሁን ሔራሞ)                   አዲስ አበባ “ግራጫ ትሁን” ተብሏል። ግራጫ፣ ነጭና ብርማ “ቀለሞች” ከኪነ ሕንፃ ታሪክ አኳያ ሞደርኒዝም ከናኘበት ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት በብዙ ሀገራት ተሞክረው ቀለሞቹ በሰው ልጆች ሥነ ልቦናና አካል ላይ ከሚያስከትሉት ተፅዕኖ አንፃር በብቸኝነት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተደረጉ ናቸው። ሲጀመር እነዚህ በዘልማድ በቀለምነት ይፈረጁ እንጂ ቀለም-አልባ ዝሪያዎች(Achromatic) ናቸው።
   ከሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ አንፃር በተለይም ግራጫ ቀለም ሰፊ ቦታ ከተሰጠው ራስን የማጥፋት (Suicide commitment) ውሳኔን የሚያበረታታ “ቀለም” መሆኑ በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ግራጫ “ቀለም” ሲያይል ድባቴን (Depression) ፈጥሮ ሰዎች ከራሳቸው ወጣ ብለው እንዳይንሸራሸሩ የሚያደርገውን “Introvert” ሰብዕናን ማበረታቱ ነው። በተለይም በሌሎች የግልና ማህበረሰባዊ ችግሮች ለተወጠሩ ሰዎች(ለምሣሌ ኑሮ ውድነት፣ጦርነት) “Extrovert” እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው አካባቢ ነው መፈጠር ያለበት። ይህም መሠረታዊ የሁባሬን መርሆችን (Harmony principles) የተከተለ የቀለማት አጠቃቃም(Chromatic environment) ይተገበር ዘንድ ግድ ይላል። በተለያዩ ቀውሶች ለተከበበ ማህበረሰብ ድባቴን የሚፈጥሩ “ቀለሞችን” እንካችሁ ማለት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን እንደመጥራት ይቆጠራል።    በነገራችን ላይ የአንድ ከተማ ቀለም ከመወሰኑ በፊት በከተማው ማስተር ፕላን ውስጥ ዕቅዱ መካተት አለበት። የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ደግሞ ቀለምን በተመለከተ የሚለው አንዳች የለውም። በማስተር ፕላኑ የሌለውን መርህ ለመተግበር መሞከር በራሱ አጠያያቂ ነው። አንዳንድ የአሜሪካ፣ የካናዳ፣የአውሮፓና የእስያ ከተሞች በማስተር ፕላናቸው ውስጥ “City Color Planning” ዲፓርትመንት አላቸው። በዲፓርትመንቱ ውስጥ የከለር አማካሪዎችና ኢንቫይሮመንታል ሳይኮሎጂስቶች፣ የከተማ ፕላነርስና አርክቴክቶች፣ ሠዓሊዎች፣ ግራፊክ ዲዛይነሮችና የታሪክ ባለሙያዎች ተካትተው በይነዲስፒሊናዊ በሆነ መልኩ የቀለም ፕላኒንግ ንድፍ ያወጣሉ። አንድ ሕንፃ ከመገንባቱ በፊት ልክ እንደ ግንባታ ፈቃዱ የቀለሙም ፈቃድ በቅድሚያ ዲዛይን ውስጥ ተካትቶ ይጠናና ውሳኔው ይሰጣል። ስለዚህም የትኛውም የከተማ ቀለም ከመወሰኑ በፊት ፕላኒንጉ በማስተር ፕላኑ መታቀፍ አለበት። ይህ ባልሆነበት የከተማን ቀለም መወሰን  እንደ ሕገወጥ ግንባታ መቆጠር አለበት። አቅሙ ካለ ከሁሉም አስቀድሞ ማስተር ፕላኑ ውስጥ የከለር ፕላኒንግ መካተት አለበት። ይህ በኮሚቴ የሚወሰን ርዕሰ ጉዳይ አይደለም።  አንዳንዶቻችሁ በዚህ ሥራ ተሳታፊ ሆኜ የበኩሌን እንዳበረክት ስትጠይቁኝ ነበር። እስከ አሁን ባለው መረጃ በግልፅ ከሚመለከታቸው የከተማ ኃላፊዎች በሥራው እንድሳተፍ የተደረገ ጥሪ የለም፣ በእርግጥ አንድ ወጣት አርክቴክት (በኮሚቴው ሳይኖር አይቀርም) በግል ጠይቆኛል። በእኔ አረዳድ ጥያቄው መቅረብ ያለበት  በግለሰቦች ሳይሆን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች መሆን አለበት ባይ ነኝ። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ውሳኔዎች በችኮላ ስለሚሰጡ፣ እንደ እኛ ዓይነት ባለሙያዎች ውሳኔ አሰጣጡን ልናዘገይ ስለምንችል እንደ እንቅፋት ሳንቆጠር አንቀርም። መኪና ማርሽ፣ ነዳጅ መስጫና ፍሪሲዮን ብቻ አይደለም ያለው። ፍሬን የሚባል መቆጣጠሪያም አለው። በአብዛኛው በፖለቲከኞች ዘንድ ፕሮፌሽናልስ እንደ “ፍሬን” ብቻ ነው የሚታዩት! ፍሬኑ ተገፍቶ በማርሽና በነዳጅ መስጫ ብቻ ምን እንደሚደርስና የት እንምንደርስ አብረን የምናያው ይሆናል።


_______________________________________


                            ጌታሁን ሔራሞ ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ጋር

             ስለ ቀለም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ተፅዕኖ  በተመለከተ ከዓመታት በፊት ከወዳጄ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ጋር በ#ፍልስምና ቁ 3; መፅሐፉ ላይ መልካም ቆይታ ነበረን። ዛሬ ቴዲ ከመፅሐፉ ቀንጭቦ በመውሰድ ገፁ ላይ ያጋራውን እኔም ላካፍላችሁ ወደድኩ። ምናልባት ዘርዘር ባለ መልኩ ለመረዳት ለምትፈልጉ ምላሽ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ቴዎድሮስ:- ቀለማት በሥነ ልቡናዊና አካላዊ ማንነታችን ላይ የሚያሳድሩት የተለያዩ ተፅእኖዎች አሉ ብለናል፡፡ ባህሪያችንን እንዲለውጡ ያደረጋቸው እኛ ከቀለማቱ ጋር ያለን መለማመድ ነው ወይስ ተፈጥሯዊ ጠባይ ኖሯቸው?
ጌታሁን:- ይህ ጥያቄህ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንድ ሰው ጋር የነበረውን ቆይታ ሲያጠናቅቅ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” በማለት የተናገረውን እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ እኔም ከምታቀርብልኝ ጥያቄዎችህ ተነሥቼ እልሃለሁ፦አንተ ከቀለም ፍልስፍናና ሳይንስ የራቅህ ሰው አይደለህም፡፡ ለምሳሌ ከላይ ባነሳኻው ጥያቄህ ውስጥ የቀለማት አካላዊና ሥነልቡናዊ ተፅዕኖዎች ( psychophysiological impacts) መንስኤን በተመለከተ እንደ ፍራንክ ማሂንኬ ያሉ የዘርፉ ጠበብት ከሚያስቀምጡት ስድስት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱንና ዋናዎቹን አንስተሃል፡፡ ከተፈጥሯዊው መንስኤ እንጀምር፡፡ ተፈጥሯዊ ስንል ግን የቀለሙንም የተመልካቹንም ማካተት አለብን፡፡ የቀለማት ሥርወ ምንጭ የብርሃን ሞገድ እንደሆነ ቀደም ሲል አንስተናል፡፡ ታዲያ የዕይታ ታሪክ በዓይናችን ተጀምሮ እዚያው በዓይናችን የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ቀለም ተሸካሚው የብርሃን ሞገድ በዓይናችን መስኮት ገብቶ ውስብስብ በሆነው የነርቭ መዋቅራችን ጎዳና እስከ አንጎላችን ድረስ ይዘልቃል፡፡ ታዲያ ጉዞው የሽርሽር እንዳይመስልህ! ማዕከላዊውን የአንጎል ክፍላችንና (hypothalamic midbrain region) አንጋፋ ዕጢዎቻችንን (Pineal and pituitary glands) ቀስቅሶ ልዩ ልዩ ስሜቶችን ለመፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለም በብርሃን መልክ ወደ አይጥ አንጎል በሚላኩበት ጊዜ በአይጡ መላ አካሉ ላይ የድብርት ሆርሞኖች ተለቀው እንቅስቃሴው ሁሉ ይገታል፡፡ እንዲሁም ዶሮ ቀይ ቀለምን በብርሃን መልክ በምታይበት ጊዜ እንቁላል የመጣል አቅሟ ይጎለብታል፡፡
ቴዎድሮስ፦ ጥናቶቹ ከአይጦችና ዶሮዎች ባለፈ በሰዎች ላይስ ምን ውጤት አምጥተው ታዩ?
ጌታሁን፦ በሰዎች ላይም አያሌ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ራይካርድ ኩለር የተባለ ሳይንቲስት በ1976 (እ.ኤ.አ.)በስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ላይ ያደረገው ጥናት፤ ቀለማት በአንጎል ሞገድ ምትና በነርቭ መዋቅሮቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አካላዊም ሆነ ሥነ ልቡናዊ ተፅዕኖ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ያመላከተ ሆኗል፡፡ በጥናቱም መሠረት ግራጫ ቀለም ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል የቆዩ ሰዎች የ“አልፋ” የአንጎል ሞገድ እንቅስቃሴ (alpha brain-wave activity) በመሳሪያ በሚለካበት ወቅት በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እንደ ግራጫ ያሉ ደብዛዛ ቀለማት ትኩረትን የመሳብ አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሰዎቹ አካባቢውን በመርሳት ለራሳቸው ጉዳይ ንቁ (concisous) ለመሆን በመገደዳቸው ነው፡፡ ስለዚህም ግራጫ ቀለም በተቀባበት ክፍል የተቀመጠ ሰው ሁሌም ስለ ራሱ ሁኔታ በማጠንጠን ስለሚጠመድ ውጥረቱ ሊጨምርና ራሱን ለማጥፋት ሊነሳሳ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ሞቃት የሆኑ ቀለማት (ቀይ ፣ ቢጫ ፣ ብርቱካናማ) በተቀባበት ክፍል ለተወሰኑ ሰዓታት በምንቀመጥበት ወቅት የሚጨምረው የ“ቤታ” የአንጎል ሞገድ ምት(beta brainwave activity) ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምት በሚያይልበት ወቅት አንጎላችን ለራስ እንቅስቃሴ ዕውቅናን ይነፍግና (Unconcious state) በአካባቢያችን ሁኔታ መመሰጥ ይጀምራል፡፡ ተመስጦው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ብዙ ደም ወደ አንጎላችን ስለሚላክና ልባችንም በዚሁ ሥራ ስለሚጠመድ በቆይታ የልብ ምታችን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህም አካባቢያችንን ዲዛይን በምናደርገበት ወቅት እነዚህን ሁለቱንም ጫፎች (understimulation and Overstimulation) ማስወገድ አለብን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እስከ አሁን ያነሳሁልህ ከስድስቱ የቀለማት ተፅዕኖ መንስኤዎች ውስጥ አንዱና ተፈጥሯዊ ስለ ሆነው ስለ ሥነ ሕይወታዊው (biological reactions) ሥርዓት ነው፡፡    (አሁን #ፍልስምና ፫;  መፅሐፍ ገበያ ላይ የለም። ሆኖም ሙሉ ቃለ መጠይቁን ጃፋር መጻሕፍት ጎራ ብሎ ከ “ ፍልስምና ፩ +፪ + ፫ “ መጽሐፍ ማግኘት ይቻላል።)

_________________________________________________

                         አቦሌ
                        ( በእውቀቱ ስዩም)


        ከማውቃቸው ሰዎች መሀል በነውጠኝነቱ ወደር የሌለው አቦሌ ነው፤ ከብዙ ጊዜ በሁዋላ አንድ የጫማ መሸጫ ቤት ውስጥ ሳገኘው ገረመኝ፤ በፊቱ ያለው ውስብስብ ሰንበር የቀለበት መንገድ ይመስላል፤ ግንባሩ ላይ የብረት ቦክስ ጠባሳ አለ፤ ግራ ጉንጩ ላይ የሰንጢ ጭረት ይታያል፤ ማላመጫው ግድም የኮብልስቶን ምልክት ታትሟል፡፡
የባጥ የኮርኒሱን ስናወጋ ከቆየን በሁዋላ።
“ስማ ፤ ያለፉትን አራት አመታት ብዙ መንፈሳዊ መጻህፍት በማንበብ አሳልፍያለሁ፤ ከራሴ ጋራ ተመካክርያለሁ፤ ሁሉንም አውጥቼ አውርጄ ጌታ ቡድሀን ተቀብያለሁ፤ የድሮው አቦሌ እንደሞተ ቁጠረው” አለና ትካዜ የተቀላቀለበት ፈገግታ አሳየኝ፡፡
ወዲያው አንድ ሰውዬ ገብቶ ንግግሩን አናጠበው፤
“ካልሲ አለ?” አለ ሰውየው፡፡
“ይሄ የጫማ መሸጫ ቤት ነው፤ ካልሲ እንዴት ትጠይቃለህ?; አለ አቦሌ፡፡
“ጫማ ቤት ውስጥ ካልሲ መጠየቅ ምን ነውር አለው? ኬክ ቤት ገብቼ ካልሲ የጠየቅሁ አስመሰልኸውኮ”
አቦሌ ሰውየውን ትክ ብሎ አየው፥ አስተያየቱ የዘጠኝ ቡዳ አስተያየት ድምር ነው፤ ከዚያ ቡጢውን ጨበጠ፤ ከንፈሩን ነከሰ፥ ከገዛ ሀይሉ ጋር ታገለ፤ በመጨረሻ በረጅሙ ተነፈሰና፤ “እባክህ ለግልና ላካባቢ ሰላም ሲባል ተፋታኝ” አለው፡፡
ሰውየው መሰስ ብሎ ወጣ፡፡
“እውነትም ተለውጠኻል; አልኩት፡፡
“ቀላል ተለውጫለሁ፤ ከሁለት አመት በፊት ቢሆን ይሄን ሰውዬ ጎድኑን እንደ አሮጌ ሳጠራ ጠርምሼለት ወህኒ ወርጄ ነበር፤ ወህኒ ወርጄ ሁለት እስረኛና አንድ ዘበኛ መግደሌ አይቀርም ነበር፤ “እባክህ; ከሚል ቃል ጋራ የተዋወቅሁት በቅርብ ነው! ጌታ ኢየሱስ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሁኑ ይላል፤ ይቅርታ አድርግልኝና እኔ በዚህ ህዝብ ላይ ብልህ ልሆንበት ምኞት የለኝም፤ እኔ እንደ ርግብ የዋህ እንደ ሰርከስ እባብ ገራም ነኝ”
“እንዲህ ተለውጠህ ማየት ደስ ይላል; አልኩኝ ልቤ ተነክቶ፡፡
“ክንዴ ላይ የነበረው ንቅሳት ትዝ ይልሀል?” አለኝ፡፡
“ደቁሰው” የሚለውን” አልኩ እየሳቅሁ፡፡
“አዎ ! ባለፈው ታቱ የሚሰራው ልጅ በጠባዬ አዲስነት ተገርሞ #ቁ” ን ወደ “ጉ” ቀይሮልኛል”
“ጌታ ቡድሀ የተመሰገነ ይሁን; አልኩት፡፡
“አሜን!”
አቦሌ ጫማ ቤቱን በጊዜ ዘግቶ ወደ አንድ ግሮሰሪ ሄደን ትንሽ ቀማመስን፤
“ስራ ፈልግልኝ፤ ይሄ ስራ አይመጥነኝም” አለ አቦሌ፤
ካገባደደ በሁዋላ ሁለተኛውን ቡትሌ፤
“ምንድነው ችግሩ?” ስል ጠየኩት፤
#ጫማ ሊለኩ ጫማቸውን ሲያወልቁ ከካልሲያቸው የሚያፈልቁት ጨረር አስመረረኝ፤ ሳስበው ያፍንጫ ካንሰር ሳይዘኝ አልቀረም፤ ያፍንጫ ካንሰር የሚባል ነገር ከሌለ በኔ ጀምሯል”
“ይሄን ያህል?”
“ተወኝ ባክህ! አንዳንዴ ሳስበው ፤ ላለፈው ሀጢያቴ ቅጣት ይሆን እላለሁ?; አለና ተከዘ፡፡
ትንሽ አሰብኩና ፤
“በሰኔ ስድስት ብሄራዊ ትያትር የማቀርበው ሾው አለኝ ፤ ደና ዝግ ከዘጋሁ ቦዲጋርድ አድርጌ እቀጥርሀለሁ” አልኩት፡፡
“ቦዲጋርድነት አልፈልግም፤ አንተም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚወደህ ቅጥረኛ ጠባቂ አያስፈልግህም፤ ከፊትህ ያለው ስጋት ርጅና እና በሽታ ነው፤ ደምብዛት እና ጉብጠትን ደሞ በቦዲጋርድ አትመክታቸውም” አለና ተፈላሰፈ፡፡
“ሌላ ምን ስራ ልሰጥህ እችላለሁ?”
“ለምን መኪና ገዝተህ ሾፌር አታረገኝም፤ ቀለል ያለ ቴስላ ግዛ ! እኔ እሱን እሾፍርልለሀለሁ’፤;
“መንጃ ፍቃድ አለህ?”
“መንጃ ፈቃድ ባይኖረኝም ማሽከርከር እችላለሁ”
“እንደሱማ አይሆንም፤; ገገምሁ፡፡
አቦሌ ዘጠነኛውን ቢራ ጨለጠና እንዲህ አለ፤
“የመንጃ ፍቃድ ትምህርት ቤት ያለው ጎረቤት አለኝ፤ መንጃ ፈቃዱን ዱቅ እንዲያረገው እለማመጠዋለሁ፤ እምቢ ካለ ሰላሳ አምስት ጥርሱን አራግፍለታለሁ”
_______________________________________________

                             ኑር ባታምንም!!
                                    (ዮሐንስ ሞላ)

           “በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ሴቶች አዲስ አበባ ውስጥ ራሳቸውን ከፎቅ ወርውረው ገድለዋል።”  
ራስን መግደል ያስደነግጣል። ከፎቅ መውደቅ ያስደነግጣል። በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት (ያልተቆጠረና ለዜና ያልበቃ አይጠፋም) ሰው አንድ አይነት አሟሟት መሞቱን መስማት ያስደነግጣል።  የአሟሟትም ወረት አለው? ፋሽን አለው? በተለያዩ ጊዜያት የሰማናቸው አይነት አሟሟቶች አሉ። ፎቅ ስለበዛ የሚል ነሆለልም አይጠፋም።
ያም ሆነ ይህ የአእምሮ ጤንነት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። ወጉን፣ ባህሉን፣ ማንነቱን፣ ቀስ እያልን እየናድነው መተከዣ ጎረቤት ለማጣት እንለፋለን። ልባዊ ጓደኝነት ጥንታዊ ሆኗል። ለአስር ብር የሚሸጠን ብዙ ነው። ከቁስ ውጭ ሌላ ምንም እንዳናስብ ወላጆች (የጠቀሙን መስሏቸው ሁሉን በማሟላት) እና ባለስልጣናት እየታገሉ ነው። እምነታችንን እንድንተው፣ በመንፈስ እንዳንጽናና በስልጣኔ ስም ሊያስጥለን ደጅ የሚጠናው ብዙ ነው።
ድራግ እንደ ማስቲካ ነው አሉ። ማኅበራዊ ሚዲያም አለ። መለስ ቀለስ ብሎ ለማሰብ በምን ፋታ?
ወድቆ ለመሞት ሲታሰብ፣ ድንገት ብተርፍስ? ብሎ ማሰብ ቢቻል ጥሩ ነበር። ነበር። ነበር።
ራስ ወዳድ ሆነን ራሳችንን ለማጥፋት ስንቆርጥ፣ ለመሞት ወድቀን እምቢ ቢለን፣ ከነስብርብራችን ተቀብለው የሚያስታምሙን ቤተሰቦች አሉን እና አንጨክን። እንጠቅማለን። ጨክነን የምንተዋቸው የሚወዱን ብዙ አሉ።
ኑር ባታምንም!!

__________________________________________


                             የአእምሮ ጂምናስቲክ የሚያሰራ የዘመኔ ድንቅ ደራሲ


             ሌሊሳ ግርማ እስካሁን ወጥ፟ ልቦለድ አልፃፈም። ስራዎቹ አጫጭር ታሪኮች፣ ወጎችና ሃሳብ ላይ ያተኮሩ ማሰላሰሎች ናቸው። የሌሊሳን መፅሐፎች አንስቼ ጭልጥ አድርጌ አልጨርስም። በጭራሽ ያን አላደርግም። የሚፅፋቸው አጫጭር ታሪኮችና ወጎች ከሚፈጥሩብኝ መደነቅና መብሰልሰል ጋር አብሬ መቆየትን እመርጣለሁ። አንዱን አጭር ታሪክ ሳላጣጥም ወደ ሌላ አልሄድም። አንዱን ወግ በደንብ ሳልጫወትበት ወደ ሌላ ፅሁፍ አልሻገርም። ታዲያ ስጫወት የምጫወተው ከሌሊሳ ጋር አይደለም። ከራሴ ጋር ነው። እርሱማ አንዴ ኳሱን ሜዳው ላይ ጥሎልኝ ሄዷል። ሌሊሳ የአእምሮ ጂምናስቲክ የሚያሰራ የዘመኔ ድንቅ ደራሲ ነው።
ብዙ ጊዜ የምናነባቸው መፅሐፎች እራሳቸው ጀምረው የሚጨርሱ ናቸው። ለአንባቢ የተተወ ክፍት ቦታ (Space) የላቸውም። ያ ከሰለቸህ ሌሊሳ አጭር ታሪክ ጀምሮ እንድትጨርሰው መንገድ ሊያመቻችልህ ይችላል፤ ያኔ በራስህ መንገድ ትጨርሰዋለህ። #የንፋስ ህልም; ላይ ያለች አንድ አጭር ታሪክን ልብ ብትል እንደዚያ ነው...
- አጫዋች ፍልስፍናዊ ወጎችን ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
- ሌላ አይን የሚፈጥርልህ ደራሲ ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
- ከተራ ነገሮች ሃሳብ ማስገር ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
ሌሊሳ በአንክሮ መነበብ ያለበት ደራሲ ነው !!
ሌሊሳን በላቀ መረዳት ውስጥ ሆነን ልናነበው የሚገባ ደራሲ ነው !!...
የፃፋቸው ስድስት መፅሐፍቶች እኒሁና፡-
1- የንፋስ ህልም አና ሌሎች የምናብ ታሪኮች
2- አፍሮጋዳ
3- መሬት አየር ሰማይ
4- የሰከረ እውነታ
5- እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎችም አጫጭር ታሪኮች
6- ነፀብራቅ
(Book for ALL)


                 ከዕለታት አንድ ቀን አራት ልጆች የነበሯቸው አንድ አባት የመሞቻቸው ጊዜ መቃረቡ ሲታወቃቸው፣ ልጆቻቸውን ጠርተው፤
“ልጆቼ፤ እንግዲህ ሰው ሆኖ፣ መሞት  አይቀርምና ያለኝን ሀብትና ንብረት ልናዘዝላችሁ። ለትልቁ ልጄ እዚህ ከተማ ማህል ያለውን ትልቁን ቤት አውርሼሃለሁ!
ለመካከለኛው ልጄ፤ ገጠር ያለኝን ቤትና የእርሻ ቦታ ሰጥቼሃለሁ።
ለሶስተኛዋ ልጄ፤ የሚታለቡና የሚረቡ፣ የሚወልዱና የሚዋለዱ ላሞቼን አውርሼሻለሁ።
ለአንተ ለትንሹ ልጄ፤ ከሁሉም በላይ የሆነውን ውርስ እሰጥሃለሁ።”
ትንሹ ልጅ በጉጉት፤
“ምንድነው የምትሰጠኝ አባባ?”
አባት፤
“ምክር። ምክር ነው የምሰጥህ። ምክር ከሁሉ ነገር በላይ ነው።;
ልጅ፡- “ምን ዓይነት ምክር ነው?”
አባት፤
“ታገሠኝ። ልነግርህ ነው።
1. ጥበበኛ ሁን። ከብልጠት ይልቅ ብልህነት ይግዛህ!
2. ጊዜህን ዕወቅ! ቃታህን አትልቀቅ!
3. መካርህን እሻ።
መካር አጨብጫቢ አይደለም። ወሬ አቀባይም አይደለም። ነገረ-ሠሪ አይደለም። አጓጉል ፖለቲከኛም አይደለም። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይዋ አህያም ዓይነት አይደለም። (apre moi le deluge እንዲል ፈረንሳይ) ጥሩ መካርህ ለአንተ አጋዥ አጋርና ወገንህ ነው!
4. መናቢ፣ ሰው አማኝ እና ተስፋ-አድራጊ ባልንጀራ ይስጥህ።
5. አዲስ አድማስ፣ አዲስ ንፍቀ-ክበብ ናፋቂ ሁን። ሀሳብህንና ትምህርትህን ይግለጽልህ፡፡
6. ከንግግርህ ቁጥብ ሁን። ለመናገር አትቸኩል። እርጋታን ተላበስ።
7. ገዢ ሁን። የአካባቢህ ተቆጣጣሪ፣ ኃላፊ የመሆን አቅሙን አይንሳህ!
8. እንደ እናት ሩህሩህ እና ለአካባቢህ አዛኝና ተንከባካቢ ያድርግህ!
9. ራዕይ ያለው ሰው ሁን! ከበጎ አድራጊና ከጥቅም-ፈላጊ የተሻለውን አስተውል! ለይና አብረህ ሁን!
10. ልብና ልቦና ይስጥህ፡፡
11. ሥርህን አውጠንጥን። ሥር የሌለው ሥርህን ከመንቀል ወደ ኋላ አይልምና መሰረትህን ጠብቅ። አጥብቅም!
12. ጀግናን ውደድ እንጂ አታምልክ!
13. አምፅ። አመጽህ ግን ለህዝብህ በጎ እንጂ ለግል ጀብድህ አይሁን!
14. ቀልድ ውደድ። ህይወት ያለቀልድ ለዛቢስና ፈዛዛ ናት! ቀልድህ ግን ቁም ነገር አዘል ይሁን!
15. ሌሎች የሰሩትን አድንቅ። አፅና!
    ለምን አልሰራሁትም ብለህ አትቅና! ይልቅ ተቆጭና ዕድሜህን አቅና!
    ገና ብዙ የምትሰራው ነገር ይጠብቅሃልና!
    በመጨረሻም፤
16. ኩሉ አመክሩ፣ ወዘሰናየ አጽንዑ!
(ሁሉንም ምከሩ፣ የተሻለውን አጽኑ) የሚለውን ቃል አጥብቀህ ያዝ!
17. የዚህ ሁሉ ማሰሪያው ፍቅር ማወቅ ነውና፤ አፍቅር! ፍቅር ስትሰጥ ፍቅር ታገኛለህ!
***
ምክሮች ምክር የሚሆኑት የሚሰማ ሲገኝ ነው! ማንም አይስማ፤ መናገር ያለበት ይናገራል። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤
#በታፈንክ ቁጥር ነው ድምጽህ ይበልጥ የሚጠራ!”
የዱሮ ታጋዮች እንዳሉትም ደግሞ ዛሬም “ምላሴን ተውልኝ!” እንላለን። ለዲሞክራሲ እንቆረቆራለንና! ማንም ምንም ቢል ውልፊት አንልም። ቁጭትም ቅጭትም አይኖርብንም። “ካፍ  ከወጣ አፋፍ;ም፣ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም”ም፣ “ባፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ;ም አንልም። ተናጋሪውን ይጭነቀው! #ከሺ ጦረኛ አንድ ወረኛ; ብለንም፣ ለወሬኞች እጅ አንሰጥም! “የተማረ ይግደለኝ!” ብለንም አንሞኝም- “ዩኒቨርስቲ ደጃፍ ተኛ!” የሚል አፈ-ጊንጥ አለና! የሆነው ሁሉ ሆኗልና ጸጸታችንን አናመነዥግም!
“አንዴ የሆነውን ነገር፣ እኮ ለምን ሆነ ማለት፤
 ለማለት ብቻ ማለት!”
(እያጎ-ኦቴሎ ሼክስፒር፣ ሎሬት ጸጋዬ እንደተረጎመው)
ኢትዮጵያ ከዘመነ-መሳፍንት ጀምሮ በርካታ መሳፍንትና ነገስታት ተፈራርቀውባታል፡፡ ከሩሲያ ነገስታትም ከአስትሮ ሐንጋሪያን ግዛት -አስፋፊያንም ወይም  ከፈረንሳዮቹ (ፕሌቢያን እና  ፓርቲሺያን ገዢዎችም) ሁሉ  የማይተናነሱ  ገዢዎች አጥታ የማታውቅ ቢሆንም፣ ድህነቷን አክብራ፣ “ታፍራና ተከብራ” የኖረች አገር ናት! ዛሬም ስለመከበሩ እንኮራባታለን! ማንነቱ የተደፈረበት የአፍሪካ አገርም ሁሉ ይኮራባታል! በቅርቡ ያከበርነው “የአድዋ በዓል” ያልደበዘዘ ልዕልናችን ነው!
አፍሪካን አንድ የሚያደርግ ታሪክ ያላት አገር፣ ልጆቿን አንድ ማድረግ ለምን አቃታት? የሚል፣ልባም ሰው መቼም አይጠፋም!
እዚህ ላይ ከቅርቡ የጣሊያን ወረራ ጊዜ እንጀምር (1928-1933 ዓ.ም) ብንል፣ ያኔ ባንዳ እና አርበኛ የሚል ስም ተከሰተ! አገር ወዳድና ከዳተኛ እንደማለት ነው! መንግስቱ ነዋይና ግርማሜ ነዋይ፣ ዋና የለውጥ ማነሳሻ  መዘውር  ሆኑ፤ የዐመፅ ጥንስሱ ሆኑ (እንደ ሪቻርድ ግሪን ፊልድ ነገረ- ታሪክ) ከዚያ ወታደሩ ተነሳሳ፡፡ ተማሪውም መንግስትን እረፍት ነሳ፡፡ ባላገሩ እዚህም እዚያም እምቢኝ- አልገዛም አለና ገሰለ! አሻፈረኝ ዘይቤው አደረገ! በዚህ መሀል “የሆድ ነገር ሆድ  ይቆርጣል; ነውና የቤንዚን ውድነት፣ የአውቶብስና  የታክሲ ዋጋ መናር የምስኪኑ ህዝብ ኑሮን ለመቋቋም አለመቻል ዋና ጉዳይ ሆነና፣ ወደ ምሬት ወደ አመፅ  ወደ ስራ ማቆም፣…. ወደ መንግስትን መገርሰሱ ተጓዘ! መንግስትስ? “ስዩመ-እግዚአብሔር ነኝ!; የሚለውን ዕምነቱን  አጠበቀ፡፡ እንዳሰበው ሳይሆን ቀረና ወደቀ! ተንኮታኮተ!
ያን ጊዜ በመንግስት ሚዲያ፣ በኢትዮጵያ አንድ ለእናቱ ቴሌቪዥን የታየው፣ በተዋናይ ዳሬክተር ተፈራ ብዙአየሁ የተዘጋጀና የተሰራው፣ “የእሳት አደጋ” የተሰኘው ድራማ፤ ሁኔታውን እጅግ ያፀኸየና ፍንትው ያደረገ ትዕይንት ነበር፡፡ ግን ማን ሰምቶ!?
“አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
 መስማት ከማይፈልግ የባሳ ደንቆሮ?!”
(ከበደ ሚካኤል)
አለመስማት ለአያሌ ነገሮች ዳርጎናል፡፡
“ፋሺስት” እና “ባንዳ” አባብሎናል!
“ኢህአፓ; እና #መኢሶን; አባብሎናል!
“ደርጊስት; እና #ፀረ- ደርግ” አሰኝቶናል!
“ፊዲስትና (የኃይሌ ፊዳ (የመኢሶን መሪ) ተከታይ አስብሎናል! ጸረ-ፊዲስት የሚል ምዳቤ አሰጥቶናል፡፡
ከሀሳብ ጦርነት ወደ ደም መፋሰስ ከትቶናል!
መደበኛ ትምህርት እንድናቆም አስገድዶናል! ሥራ ማቆም ግድ ሆኖብናል!...
ምኑ ቅጡ!
ዛሬም፤ ወደድንም ጠላንም ያ ክፉ ቀን እንዳይደገም መሆን አለበት! የቀመሰ ያውቀዋልና #አደራ!; ቢል መጪውን ትውልድ የማዳን ያህል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ “ጥረታችን ስለ ትናንት የሚባለውን የሚያዳምጥ ሁነኛ መንግስት ለመፍጠርና ለማሳደግ ነው!” ልብ ያለው መንግስት፣ ይሄን ልብ ይላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን!
“ተስፋ ባጣ ምድረ-በዳ
ያንድ ዕውነት ይሆናል ዕዳ!”  ሳንባባል እንግባባለን የሚል ዕምነት አለን፡፡
የበዓል ሰሞናችን ብዙ ነው፡-
-እንቁጣጣሽን ለምን ወደድነው? በዘመን መለወጥ  ስለምናምን!
-ደመራን ለምን ወደድነው? ከየቦታው የሠበሰብነውን ችቦ አንድ ላይ ስለምናበራ!
ትንሳኤን ለምን  ወደድነው? ዳግም ስለምንነሳ!
ፋሲካን ለምን ወደድነው? ፆመን ፆመን ስለማንቀር
ባህላችንን ለምን ወደድነው? ከአሁጉራት፤ ከአገራትና ከዓለም ህዝቦች ሁሉ፤ መለያችን ስለሆነ!
እነሆ ይሄን ሁሉ ካልን ዘንዳ፣ ማናቸውም የፓርቲ ኃላፊ፣ የድርጅት አለቃ፣ የማህበር ተመራጭ ወይም የቀበሌና የከፍተኛ ሊቀ-መንበር፤አንዳች ግንዛቤ እንዲጨብጥ እንሻለን፡-
“ብርቱ ብርቱ ሰዎችን፤ ከራሳቸው ጥቅም በላቀ ደረጃ ለአገር አሳቢ የሆኑ አገር ወዳዶችን፤ ከመንቀፍ በተሻለ ማገዝና መለወጥን የሚፈልጉ ልሂቃንን፣ የምታሳድግና የምታበረታታ ምድርን ለማለምለም፣ የሚታትሩ ዜጎችን፤ የምትወልድ ልጆች ይስጠን!; የምንል ጀግኖች ያድርገን! እጣ ፈንታችን እጃችን ላይ ነው፡፡ አገራችንን ለማሳደግ የሚችሉ አዕምሮዎችን እናማክር-አለበለዚያ፡-
“መካር የሌለው ንጉስ
አለ አንድ ዓመት አይነግስ!” የሚለው ብሂል ዕውን ይሆናል፡፡
የሚያዳምጥ ንጉስ አያሳጣን!
“እሠይ! እሠይ!” የሚሉ “የጎሽ-ጎሽ!” ኮሚቴ አባላትን ሳይሆን “ዋ!”  ብለው የሚያስጠነቅቁ አማካሪዎችን በብራ ቀን፣ በፋኖስ፣ እንደ ዲዮጋን መፈለግ ነው የሚያዋጣን!    
ትምህርታችንን ይግለጥልን!!


ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በተቀናጀ ደራሽ የክፍያ ሥርዓት አማካኝነት የውሃ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች የወርሃዊ አገልግሎት ክፍያን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት ተደርጓል፡፡
በዛሬው ዕለት ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በሐረሪ፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚገኙ የቴሌብር ደንበኞች የውሃ አገልግሎት ክፍያቸውን በተቀናጀ ደራሽ የክፍያ ሥርዓት አማካኝነት በቴሌብር ለመፈጸም ይችሉ ዘንድ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ስምምነት በመፈጸም አገልግሎቱን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡


በዚህ ስምምነት መሠረት፤ የውሃ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች በተቀናጀ ደራሽ የክፍያ ሥርዓት አማካኝነት የደንበኞቻቸውን ወርሃዊ ሂሳብ በቴሌብር ለመሰብሰብ የሚያስችላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡
#ይህ አሰራር የማህበረሰባችንን የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሳደግ፣ በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ግብይት ለመቀነስና የቢዝነስ መረጃዎችን ፍሰት በቀላሉ ለማወቅና ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ይሆናል፡፡; ብሏል፤ ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው፡፡
የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን እስካሁን 19 ሚሊዮን ደንበኞችን እንዳፈራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 40 በመቶ ያህሉ የከፋ የውሃ እጥረት ችግር ሰለባ መሆኑንና በመላው አለም በመጪዎቹ ሰባት አመታት ጊዜ ውስጥ በድርቅ ሳቢያ 700 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተነገረ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው አንድ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በየአመቱ በመላው አለም 55 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በውሃ ወይም ዝናብ እጥረት ሳቢያ በሚከሰት ድርቅ ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
የአለማችን ህዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ውሃን የመሳሰሉ ውስን የተፈጥሮ ሃብቶች በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ እየዋሉና ከፍተኛ እጥረት እየተከሰተ እንደሚገኝ የጠቆመው መረጃው፤ የአየር ንብረት ለውጥ በአለማችን የውሃ ሃብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
በመጪዎቹ 35 አመታት ከ570 በላይ በሚሆኑ የአለማችን ከተሞች የሚኖሩ 685 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የንጹህ ውሃ አቅርቦታቸው በ10 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው መረጃው፤ ይህም በበርካታ የአለማችን አገራት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያብራራል፡፡

በዚምባቡዌ በ5 ወራት ብቻ 60 ሰዎች በዝሆን ተገድለዋል            በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገራት በየአመቱ 4.8 ሚሊዮን ያህል አህዮች በህገወጥ ንግድ እየተሸጡ ለባህላዊ መድሃኒት መስሪያ ተብለው እንደሚታረዱና በዚህም አህዮችን ጭነትን ጨምሮ በዕለት ከዕለት ኑሯቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙ በርካታ አርሶ አደሮች ተጎጂ መሆናቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ዶንኪ ሳንክቿሪ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ያወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአህዮችን ቆዳ ጨምሮ የተለያዩ አካሎቻቸው ለተለያዩ ባህላዊ መድሃኒቶች መስሪያነት ለማዋል ሲባል ፌስቡክና ዩቲዩብን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች ሳይቀር በአሻሻጮች አማካይነት በህገወጥ መንገድ እየተሸጡ በስውር እርድ የሚከናወንባቸው ሲሆን፣ ብዙ አህዮች ከሚሸጡባቸው አገራት መካከል ቻይና ቀዳሚነቱን ትይዛለች፡፡
ቻይና የአህያ ግብይት ስምምነት የፈጸመችው ድርጊቱን በህግ ካጸደቁ 20 የአለማችን አገራት ጋር ብቻ ቢሆንም፣ ከ50 በላይ ከሚሆኑ አገራት አህዮች ወደ ቻይና እንደሚገቡም የተቋሙ ጥናት ያመለክታል፡፡
በርካታ አህዮች ከሚሸጡባቸውና ከሚታረዱባቸው አገራት መካከል አብዛኞቹ ድርጊቶቹን በህግ የከለከሉ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ አገራት መካከልም ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሴኔጋልና ጋና ይገኙባቸዋል፡፡
ተቋሙ በአለማቀፍ ደረጃ አህዮችን የሚሻሽጡ 382 ያህል የግብይት ድረገጾች እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፣ አሻሻጮቹ እንደ አደንዛዥ ዕጽና የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ቡድኖች አለማቀፍ ስውር ትስስር እንዳላቸውም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በዚምባቡዌ ባለፉት 5 ወራት ብቻ 60 ያህል የአገሪቱ ዜጎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በዝሆኖች  በደረሰባቸው ጥቃት ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአለማችን በዝሆኖች ብዛት ከቦትሱዋና ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃን በያዘችውና ከ100 ሺህ በላይ ዝሆኖች ባሉባት ዚምባቡዌ፣ ዝሆኖች በየአመቱ በ5 በመቶ ያህል ብዛታቸው እንደሚጨምርና ተገቢው ጥበቃ የማይደረግላቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ወደ መኖሪያ መንደሮች እየገቡ ንብረት እንደሚያወድሙና ከሰዎች ጋር ከፍተኛ ግጭት እንደሚፈጥሩ፣ በዚህ አመት ብቻም፣ በዝሆኖችና በሰዎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች 60 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች 50 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ መንግስት ከሰሞኑ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በተመሳሳይ ሁኔታ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር 72 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በከፍተኛ መጠን ለሚያድገው የዝሆን ብዛት መፍትሄ ካልተበጀለት ጉዳዩ አገር አቀፍ የግጭት ቀውስ ሊፈጥር ይችላል መባሉንም  አክሎ ገልጧል፡፡

 የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በቅርቡ በሚካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ እንዲወዳደሩ ከአንድ የአገሪቱ ፓርቲ ደጋፊዎች ጥሪ ቢቀርብላቸውም ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡
የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ፓርቲዎች ለቀጣዩ ምርጫ የሚያቀርቡትን ዕጩ እስከ ሰኔ 3 እንዲያሳውቁ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን ያስታወሰው ዘገባው፤ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ የተባለውና ጉድላክ ጆናታን በ2015 ለድጋሚ የስልጣን ዘመን ባደረጉት ውድድር ያሸነፋቸውና በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ደጋፊዎች የሆኑ ግለሰቦች ጆናታን ፓርቲውን ወክለው በድጋሚ እንዲወዳደሩ የምርጫ መወዳደሪያ ምዝገባ ሰነዱን ከሚመለከተው አካል ገዝቶ ቢወስድላቸውም እሳቸው ግን፣ "ትልቅ ንቀት ነው" በማለት ጥሪውን አጣጥለውታል፡፡
ጉድላክ ጆናታን እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው አገሪቱን ለ5 አመታት በፕሬዚዳንትነት ማስተዳደራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን የተረከባቸውን ፓርቲ ወክለው እንዲወዳደሩ ደጋፊዎቻቸው ሰነዱን በ240 ሺህ ዶላር ያህል ገዝተው ቢያመጡላቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አመልክቷል፡፡

ዛሬ ምሽት
ከ11 ሰዓት ጀምሮ ፤ በአንጋፋው ብሔራዊ ትያትር
ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በልዩ ተሰጥኦና ጥምረት ፣ በወዳጅነት እና በሙያ አክባሪነት ላለፉት አስር ዓመታት የሚታወቁ የሀገራችን ኪነ ጥበብ ድምቀቶች ናቸው።
የተመሰረቱበትን አስረኛ ዓመት ዛሬ ምሽት ከ11 ሰዓት ጀምሮ በአንጋፋው ብሔራዊ ትያትር ቤት በድምቀት ያከብራሉ ።
ሁላችሁም ተጋብዛችኩዋል።
መግቢያ 200 ብር ብቻ ነው ።
እንዳትቀሩ !

 አዲስ አለማየሁ እና ሳምራዊት ፍቅሩ Rest of World (RoW) ዘንድሮ ባወጣው አመታዊ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ኢትዮጵያዊ ሆነዋል!
ይህ በአለም ዙርያ ያሉ እና ከካሊፎርኒያው ሲሊኮን ቫሊ ውጭ ያሉ 100 የቴክኖሎጂ ለውጥ አምጪ ሰዎች ዝርዝር በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመርጠው የሚካተቱበት ሲሆን የ Kazana Group ሊቀመንበር አዲስ እና የ Ride መስራች ሳምራዊት ዘንድሮ ተጠቅሰዋል።
አዲስ አለማየሁ በዚህ ድርጅት ስር 16 ኩባንያዎችን የሚመራ ሲሆን የ251 ኮሚኒኬሽን እና የቃና ቲቪ መስራች አባል ነው፣ የአፍሮ ኤፍኤም ሬድዮ መስራችም ነበር። በአሁኑ ወቅት የ Albright Stonebridge Group ሲኒየር አማካሪ በመሆን እያገለገለም ይገኛል። ሳምራዊት ደግሞ Ride ድርጅትን መስርታ ለስኬት የበቃች ናት።
ሰዎች እንዲህ ትልልቅ ቦታ ደርሰው ሲገኙ ደስ ይላል፣ እንኳን ደስ አላችሁ።Page 10 of 611