Administrator

Administrator

Saturday, 04 September 2021 17:39

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!
                            ጌታቸው ሽፈራው


             አሸባሪው ትህነግ ያኔ ድሮ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ሲመጣ በአደባባይ የታገለ ሰው ነው። የአዲስ አበባ ወጣት ብሶቱን የሚተነፍስለት ሲያጣ ጮህ ብሎ የተናገረለት ታማኝ ነበር። ፖለቲከኛ አልነበረም፣ አርቲስት ለመንግስት በሚያለቀልቅበት ሀገር አርቲስቱ ታማኝ ነው ድምፅ የሆነው፣ ተስፋ የሰጠው። የትህነግ አመራሮችም ባሉበት ሳይቀር ሳይፈራ የሚናገረው ታማኝ በየነ ነበር።
ለዛም ሲባል ወጣቱ “ግባ በለው! ታማኝን ግባ በለው” እያለ ጮኾለታል። ስሜቱን፣ ብሶቱን በደንብ ስለሚገልፅለት ነበር። እውነታውን ስለሚናገርለት ነበር። ታማኝን በገዳዩ በመለስ ለቅሶ ላይ ጥልመት ለብሶ ሲነፋረቅ አላገኘኸውም። ታማኝ ለሕዝብ የተገኘው መለስ ዜናዊ ገና በአፍላው በሙሉ አቅሙ ንፁሃንን ሲገድል ነው።
ታማኝ ለገዳይ አልቃሽ ሆኖ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ድምፅ ሆኖ ነው ያገኘነው። የረባ ሰው ባልነበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ተስፋ ባጣችበት ወቅት!
ያ ክፉ ትህነግ ሰሞኑን ታማኝ ሲያጋልጠው ስለኖረ፣ በታማኝ በየነ ቤተሰቦች ላይ ያደረገውን ሰምተናል። ታማኝ ያኔ በወጣትነት እድሜው ትህነግን የተቃወመው ቤተሰቤ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ አይደለም። ሀገሬ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ ነው። ለረዥም ዘመን የተቃወመው፣ ብቻውን በሚባል ሁኔታ ገመናውን ያጋለጠው ለሀገሩ እንጅ ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም። በሁለተኛው ወረራም፣ በዚህ ወቅት በፈፀመው ወረራም ታማኝ አሸባሪውን ትህነግ ያወገዘው ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም።
ትህነግ ገና ወረራ ሲፈፅም ታማኝ በየነ ተረባርበን ወረራውን መቀልበስ እንዳለብን አስረድቶናል። የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ነግሮናል። በእርግጥ ታማኝ በአሸባሪው ትህነግ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌላው ጉዳይም ከሀገሩ ጉዳይ ተነጥሎ አያውቅም።
ያም ሆኖ ግን እሱ አሸባሪውን ትህነግ ሲቃወም ፖለቲካ የሚባል የማያውቅ፣ አንዳንዱ በሕይወትም ያልነበረ ሳይቀር ሲተቸው አያለሁ። የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ፣ ትህነግ ብዙዎቹን ያኮላሸበትን የሽብር አዋጅ ያስፀደቀው ኤርሚያስ ለገሰ እንኳን ታማኝ ሳያውቅ የወጣን አንድ ባነር አንጠልጥሎ ሲተቸው አይቻለሁ። አለማፈሩ!
አንዳንዶቹ “አማራ አማራ” ካላለ ብለን እንተቸዋለን። የእኛ ሰው የትም ሆኖ እንዲጠቅም እንኳን እድል አንሰጥም። የእኔን ቅላፄ አንተም ድገመው እንላለን። ደብረፅዮን ወይንም ጃል ማሮ “ኢትዮጵያ” ቢል ፕሮፋይል ለማድረግ የምንዘጋጅ ሰዎች፣ ታማኝ ከድሮም የጮኸላትን ሀገር ስም እንዳያነሳ ከፈለግን ችግሩ ከራሳችን ነው። ፌስቡክና ዩቱዩብ ላይ ፖለቲካ የጀመረው ሁሉ ያለ አግባብ ይወቅሰዋል። ታማኝ ግን አሁንም አለ።
ከአቋሙ ሳይዋዥቅ አለ። በእርግጥ አንዳንዴ የሚደርሱ ትችቶች ካለው ተቀባይነት አንፃርና፣ ያደርገዋል ተብሎ ከሚታመነው አንፃር ሊሆን ይችላል። “ይህን ቢልልኝ” ከሚል ነው። ራሳችን ማድረግ ያቃተንን እሱ እንዲያደርግ ከመፈለግ ነው።
ታማኝ በለግላጋ እድሜው ጀምሮ አሁንም ሽበት በሽበት ሆኖ እንቅጭ እንቅጩን እንዲናገርልን እንፈልጋለን። የሳምንት አጀንዳ አስመርሮት ፌስቡኩን ሰግቶ የሚወጣ ትውልድ ታማኝን እድሜ ልክህን ተናገርልኝ ይለዋል። ታማኝ እየተናገረ ነው፣ ወገኑን እያገዘ ነው። ሁሉን እንዲያደርግ፣ ችግር ባለበት ሁሉ እንዲደርስ አትጠብቅ። አንተም የራስህን አድርግ!
ታማኝ ሰው ነው። እድሜውን ሙሉ የታገለ። ከምን መጣ የማይባል አሸን ልፍለፋም ሊያሰላቸው የሚችል ሰው ነው። ያም ሆኖ አሁንም አለ። ከእነ አቋሙ። እኛ የረባ ያልጮህነው “ጩህልን” ስላልነው ሳይሆን ለህሊናው ብሎ ይጮሃል፣ ይረዳል፣ ይታገላል። ያኔ ያወገዘውን ትህነግ፣ ሲያጋልጠው የኖረውን ትህነግ አሁንም እንታገለዋለን እያለ ነው። ይህን የመሰለ ሰው አሁንም “ታማኝን ግባ በለው!” ብለህ የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!Saturday, 04 September 2021 17:40

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 ጎባጣው ትዳሬ
                          በእውቀቱ ስዩም


           በየሳምንቱ ቅዳሜ አንድ መርህ አለኝ፤ ያገርቤትም ሆነ የውጭ አገር ፖለቲካ ዜና እጦማለሁ፤ ኪነጥበብና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጣድና ነፍሴን አለመልማታለሁ፤ በዚህ መሰረት፥ ቅድም ዩቲዩብ ላይ ስርመሰመስ ቆየሁ፡፡
በቀደም አንድ የሞሮኮ ዜጋ የሆነ ዘፋኝ “ሊጋባው በየነ” የሚለውን ዘፈን በራሱ ቃና ዘፍኖ አስደምሞኝ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ ሸገር ውስጥ በስደተኝነት የሚኖር ሶርያዊ ዘፋኝ “ለዚህ ለዚህማ ምናለኝ አገሬ“ የሚለውን የጌቴ አንላይን ዘፈን ዘፍኖ አስለቀሰኝ::
ወደ ፌስቡክ ተመለስኩ፤ ባለፈው አንዱ “ላጤ” የሚለውን ግሩፕ እንድቀላቀል መጥርያ ልኮልኝ ነበር፤ ያለሁበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመሰለል ፈልጎ ይመስለኛል፤ እኔም ግሩፑን ቀስ ብየ በለሆሳስ እየተራመድኩ ሰለልኩት፤ ፍቅር የተራቡ "ሆርኒ” ወጣቶች የተደራጁበት ቡድን መሆኑን ደረስኩበት፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት ወይዘሮ "በትዳራችን ጉዳይ እንመካከር" የሚል ግሩፕ ላይ እንድሳተፍ መጥርያ ሰደደችልኝ፤ ይሄ ግሩፕ የመጨረሻ ተመቸኝ፤ የመጀመርያም ተመቸኝ። አብዛኞቹ የግሩፑ አባላት፥ የፍቅር ታሪካቸውን ተርከው፤ በትዳራቸው ላይ የገጠማቸውን ችግር ዘርዝረው፥ ካንባቢ ምክርና መፍትሄ ያማትራሉ፤ እንሆ እኔም ተሞክሮየን ለማካፈል ወሰንኩ፥
በውቄ እባላለሁ፤ ከባለቤቴ ጋራ የተገናኘነው ባጋጣሚ ነው፤ በጊዜው እሷ ሚስ ኢትዯጵያ ተብላ በቁንጅና ስትመረጥ እኔ አወዳዳሪው ነበርኩ:: የመጀመርያዎቹ ሀያ አመታት የትዳር ቆይታችን ጎረቤት የሚያስቀና ነበር:: ከቢሮ ስመጣ በደስታ በፈገግታና በውዝዋዜ ትቀበለኛለች፤ ኮቴን አውልቃ ወደ ላውንደሪው አፍ እየጨመረች “ምሳ እስኪደርስ፤ ክትፎ በቆጮ እየቀማመስክ ቆይ" ትለኛለች:: ከምሳ በሁዋላ ሶፋው ሳፋ እሲከመስል ድረስ ፍቅር እንሰራለን፤
ብዙም ሳይቆይ ጸነሰች፤ ከዘጠኝ ወራት ላልበለጠ ጊዜ በርግዝና ቆየች:: ያለ ብዙ ምጥ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ልጃችንም ያለ ብዙ ለቅሶ ተገረዘ! ልጃችን በተወለደ በአንድ አመቱ ዶንኪቲዩብ ላይ እየቀረበ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ምክር መለገስ እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ጀመረ:: ሰባት አመት ሲሞላው ካሮጌ ቅጥቅጥ ሚኒባስ ሂሊኮፍተር ሰራ:: አሁን ካዲስ አበባ ብሾፍቱ ራይድ እየሰራበት ይገኛል::
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለቤቴ ጸባይዋ መቀየር ጀመረ:: የገቢ ምንጯና ለኔ ያላት ፍቅር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ ለልደቴ ፍልውሃ ያለውን ፓርክ ገዝታ በስጦታ አበረከተችልኝ::
በዚህ አይነት ሁሉን የሚያስቀና ትዳር ውስጥ እየኖርን እጅግ የሚያሳዝን ነገር ተከሰተ፤ ሄቲ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ ! ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ ተቆጣጠረ፤ ይህ ግን በፍቅራችን ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽኖ አልነበረውም::
አንባቢ ሆይ !! ትዳራችን ፈረሰ የሚለውን ለመስማት፥ ምክርና ከንፈር መጠጣ ለማዋጣት ሰፍ ብለህ እየጠበቅህ ነውን? በቃ ሼም የለህም? ለምን የሟርተኞችና የክፉ ታሪክ ናፋቂዎች ግሩፕ አታቋቁምም?


Saturday, 04 September 2021 17:38

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ኢትዮጵያ ስታራምደው የነበረው ፌዴራሊዝም የሕብረ-ብሔራዊ (Multinational) ፌዴራሊዝምን መስፈርትን ያሟላ አይደለም!
                           ጌታሁን ሔራሞ             መስከረም 24 መንግስት እንደሚመሠረት አፈጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ ትናንት አስታውቀዋል፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፦
አሁን ያለው ሕገመንግሥት...በተለይም ክልላዊው ኦቶኖሚው... ዜጎችን በሀገራቸው ነባርና መጤ በማለት ለሁለት የከፈለ መሆኑ ይታወቅ!
ሕገ መንግሥቱ በየክልሉ ያሉ አናሳ ብሔሮችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን የማያከብር መሆኑ ይታወቅ...ሁሉም ብሔር ከክልሉ ውጪ አናሳ መሆኑ ይሰመር (የሐረሪ ብሔር በራሱ ክልልም ጭምር አናሳ መሆኑን ሳንዘነጋ)!
ስለዚህም ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች ወረቀት ላይ የተፃፈው የብሔር ብዝሃነት ፅንሰ ሐሳብ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዲደረግ የ”Territorial Autonomy” መርህ መሻሻል እንዳለበት ከወዲሁ ይታወቅ። በሌላ አኳያ አንቀፅ 39 ለሁሉም ክልሎች በሕገ መንግሥት ደረጃ ክልላዊ ኦቶኖሚን መስጠቱ ይታወቅ ...The right for secession is meaningless without territorial autonomy! እናም አንቀፅ 39 ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ ሁኔታዎች ይመቻቹ!
ከላይ የተዘረዘሩትን ሕገ መንግሥታዊ ግድፈቶችን ጠቅለል ስናደርጋቸው፦ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተለይም በክልሎች ደረጃ ሁሌም የሚለፈፍለትን የብሔር “Diversity”ን የሚያስከብር አይደለም፣
ስለዚህም ፦
ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስታራምደው የነበረው ፌዴራላዊ አወቃቀር ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አይደለም። በየክልሉ ያሉ የአናሳ ብሔሮችን የዜግነትን መብት በሚቃረን መልኩ ከፖለቲካ ውክልና (በተለይም ከምርጫ ፖለቲካ) እና ከኢኮኖሚ (ከክልሉ ባለቤትነት) እያገለሉና እየነጠሉ “ፌዴራሊዝሙ ሕብረ-ብሔራዊ ነው” ማለት ቀልድ ነው። ይህን ማጠቃለያ የሚጠራጠር ካለ፣ በሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝምም ሆነ በ”Multiculturalism” ፅንሰሐሳቦች ዙሪያ የካናዳዊውን ዊል ኪሚልካ፣ የእንግሊዛዊዉን “Bhikhu Parekh”ን እና የሲንጋፖራዊቷን የ”Terry-Anne Teo”ን መፅሐፍት ያገላብጥ! በነገራችን ላይ ሕንድ ውስጥ ካሉት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ብሔሮች መካከል በዋናነት የሦስትና የአራት ያህል አናሳ ብሔሮች መብት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ የሕንድ ፌዴራሊዝም ሕብረ-ብሔራዊ አይደለም ብለው የሚሞግቱ ምሁራን አሉ። እኛ ሀገር በየክልሉ ያልተከበረው የሁሉም ብሔሮች (80+) የዜግነት መብቶች ናቸው።

የአየርላንድ ህዝብ ብዛት ከ170 አመታት በኋላ ከ5 ሚሊዮን አልፏል

            በአለማችን ከሚገኙ የዛፍ ዝርያዎች 33 በመቶ ያህሉ ወይም 17,500 የዛፍ ዝርያዎች ከምድረ ገጽ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት አስጠንቅቋል፡፡
ቦታኒክ ጋርደንስ ኮንሰርቬሽን ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ ዛፎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ አእዋፍት እና አጥቢዎችን ጨምሮ ህልውናቸው አደጋ ላይ የወደቁ እንስሳት ዝርያዎችን ቁጥር አሳድጎታል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው የዛፍ ዝርያዎች ለመጥፋት የተቃረቡባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ብራዚል ናት ያለው ጥናቱ፣ በአገሪቱ 1 ሺህ 788 የዛፍ ዝርያዎች ለመጥፋት መቃረባቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የአየርላንድ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ170 አመታት በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5 ሚሊዮን ማለፉን የአገሪቱ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዩፒአይ አስነብቧል፡፡
ቢሮው ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአየርላንድ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ 5.01 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የህዝብ ቁጥሩ ከ5 ሚሊዮን ሲያልፍ እ.ኤ.አ ከ1851 ወዲህ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡

 ታዋቂው የመልዕክት መላላኪያ አፕሊኬሽን ቴሌግራም በመላው አለም በተጠቃሚዎች ዳውንሎድ የተደረገበት መጠን ባለፈው ሳምንት አርብ ከ1 ቢሊዮን ማለፉ ተነግሯል፡፡
አፕሊኬሽኑ በ2021 የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 214.7 ሚሊዮን ጊዜ ዳውንሎድ መደረጉን ያስታወሰው ቴክ ክራንች ድረገጽ፣ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ61 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም አስነብቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 ለመጀመሪያ ጊዜ በአገልግሎት ላይ የዋለው ቴሌግራም እስካሁን ዳውንሎድ ከተደረገው ውስጥ 22 በመቶ ያህሉ ዳውንሎድ የተደረገው በህንድ መሆኑንና በሩስያና በኢንዶኔዥያ በብዛት ጥቅም ላይ መዋሉንም አመልክቷል፡፡
ከቴሌግራም በተጨማሪ ከ1 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ከተደረጉት ሌሎች 14 የወቅቱ የዘመናችን ተወዳጅ አፕሊኬሽኖች መካከልም ዋትሳፕ፣ ሜሴንጀር፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ስፓቲፋይና ኔትፍሊክስ ይገኙበታል፡፡ የቻይና ህጻናት የኢንተርኔት ጌሞችን አዘውትረው በመጫወት ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ለማድረግ ያቀደው የአገሪቱ መንግስት፣ ህጻናቱ በሳምንት በድምሩ ከ3 ሰዓታት በላይ መሰል ጌሞችን እንዳይጫወቱ የሚከለክል አዲስ ህግ ማውጣቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የቻይና ብሔራዊ የፕሬስና ፐብሊኬሽን አስተዳደር ይፋ ያደረገውና ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው ህግ እንደሚለው፣ ህጻናት የድረገጽ ጌሞችን መጫወት የሚችሉት አርብ፣ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በበዓል ቀናት ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ በፊት የወጣ ተመሳሳይ ህግ ህጻናቱ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ተኩል ጌም እንዲጫወቱ ይፈቅድ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱ ጥብቅ ህግ በጌም ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ የአገሪቱ ኩባንያዎችን ክፉኛ ይጎዳል ተብሎ መሰጋቱን አመልክቷል፡፡

 በያዝነው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በአፍሪካ አህጉር ከ48 ሺህ በላይ ሰዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፍቶ መቅረታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ ወደ 22 ሺህ የሚጠጉት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናት መሆናቸውን አለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
አብዛኞቹ ሰዎች ጠፍተው የቀሩት ከእርስ በእርስ ግጭት፣ ብጥብጥ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ስደት ጋር በተያያዘ መሆኑን የጠቆመው ኮሚቴው፣ ጠፍተው ከቀሩት 48 ሺህ ሰዎች መካከል 82 በመቶ የሚሆኑት ወይም 40 ሺህ ያህሉ በእርስበርስ ግጭት ውስጥ ከሚገኙ ሰባት የአፍሪካ አገራት የጠፉ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአህጉሩ ከተመዘገበው አጠቃላይ የጠፉ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ናይጀሪያውያን መሆናቸውንም ኮሚቴው አክሎ ገልጧል፡፡


   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ከት/ቤት ተመልሶ ወደ ቤቱ ይመጣል። እቤትም ሆኖ ክፉኛ ያለቅሳል።
አባት ከደጅ ሲመጡ ልጁ ሲያለቅስ ያዩትና፤
“ና አንተ አሽከር፣ ልጄ ምን ሆኖ ነው የሚያለቅሰው? እስቲ ሂድና ጠይቀኸው ና?” ይሉታል።
አሽከር እጅ ነስቶ የታዘዘውን ሊፈጽም ይሄዳል።
ልጁ ዘንድ ሄዶም፣
“ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?”
ልጁም፤
“ምንም አልሆንኩም” ይላል።
አሽከር፣
“እንዲሁማ አታለቅስም፤ ዕውነቱን ተናገር” ይለዋል።
ልጅ፣
“የኔታ መትተውኝ ነው”
አሽከርም ወደ አባትዬው ተመልሶ ሲመጣ፣ አባትዬው፡-
    “እህስ ጠየከው?”
አሽከር- “አዎን ጌታዬ”
አባት- “ምን አለ?”
አሽከር- “የኔታ መትተውኝ ነው”አለ።
አባት “ለምን መቱት?”
አሽከር- “እሱን አልነገረኝም”
አባትዬው ተነስቶ ወደ ልጁ ሄደና “ልጄ ለምን ታለቅሳለህ?”
ልጅ- “የኔታ መትተውኝ ነው!” አለ።
አባት- “ለምን መቱህ?”
ልጅ-  “”ሀ” በል ቢሉኝ እምቢ ብዬ ነው”
አባት - “የሞትክ! ሰነፍ! “ሀ” ማለት አቅደህ ትገረፋለህ!”
ልጅ- “አይ አባዬ፣ የየኔታ  ጉዳቸው መች ያልቃል- “ሀ” ስል “ሁ” በል ዠይሉኛል፡፤ “ሁ” ስል “ሂ” በል ይሉኛል። “ሂ” ስል “ሃ” በል ይሉኛል። እንዲህ እያሉ እስከ “ፐ” ድረስ ሊያስለፉኝ እኮ ነው።” አላቸው ይገባል።
*   *   *
ወጣቶች እውቀትን ከሚሸሹበት ዘመን ይሰውረን። አንድ ያገራችን ገጣሚ እንዳለው፤
“… ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ!”
ወጣቶች ለመማር ዝግጁነታቸውን እንዲያጠናክሩ
ሀ. ወላጆች
ለ. መምህራን
ሐ. ራሳቸውና ባልንጀሮቻቸው
ሊያበረታቷቸው ይገባል። አዲሱ አሮጌውን መውረሱ ከአበው ጊዜ ጀምሮ የሚነገር ሀቅ ነው። በፈረንጅኛው THE NEW IS  INVINCIBLE ይባላል። “አዲሱ አሸናፊ ነው” እንደማለት ነው። አንድ ስርዓት ተለዋዋጭ ትውልዶችን ያስተናግድ ዘንድ ግድ  ነው። አንጋፋው ለጎልማሳው፣ ጎልማሳው ለወጣቱ ማውረስ አለበት፡፡ ማውረስ ስንልም ጤናማና ያደገ ውርስ ማለታችን ነው! በትምህርት፣ በጤና፣ በመወያየት ባህል የጠነከረ ማህበረሰብ መገንባት ማለታችን ነው። ይህ ማህበረሰብ ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች ላይ የሚሰራና በትኩረት ነጋ-ጠባ የሚተጋ ኃይልን  የሚፈጥር መሆን አለበት። በዚህ ረገድ የመንግስት ሚና የማይናቅ ነው። መንግስት ቢሮክራሲ የፀዳ መሆንና የተቋማት መጠናከር ልዩ ትኩረትን ይጠይቃል። ዛሬም ከገጣሚ ገሞራው ጋር፣
    “… ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
         ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…”
እንላለን። ሁሉም ጥብቅ ህብረተሰቡን የሚገነባ ነውና  ከተተገበረ ዋና ነገር ነው። ለዚሁም ብርታቱንና ጥናቱን ይስጠን!


  የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አፍሪካ 30 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ከስራ ገበታቸው በማፈናቀል ለስራ አጥነት መዳረጉንና ወረርሽኙ በፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ሳቢያ በ2021 ብቻ 39 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታውቋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና ባለፈው ሰኞ ለሲኤንቢሲ እንደተናገሩት፤ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እስከ 190 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅናሽ የገጠማት ሲሆን፣ የበጀት እጥረቷም ከቀውሱ በፊት ከነበረው 60 በመቶ ወደ 70 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
ከ7.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት አፍሪካ ከኮሮና ተጽዕኖ ማገገም የምትችለው በቂ ክትባት ስታገኝ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአህጉሪቱ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ለመከተብ የቻለው 2.5 በመቶው ብቻ መሆኑንና ይህ መጠን ከእስያ 25 በመቶ፣ ከደቡብ አሜሪካ 27 በመቶ እንዲሁም ከ40 በመቶ በላይ ከደረሰው የአውሮፓና አሜሪካ የክትባት ሽፋን አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በሌላ የአፍሪካ ኮሮና ዜና ደግሞ፣ የደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች ራሱን በተደጋጋሚ የመቀያየር ባህሪይ ያለውና ሲ.1.2 የሚል ስያሜ ያለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ማግኘታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ የስርጭትና የገዳይነት ደረጃውን ጨምሮ በቫይረሱ የተለያዩ ተፈጥሮዎች ዙሪያ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ መነገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ታይቷል የተባለው ይህ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓና እስያ ከተሞች ሰዎችን ማጥቃቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ  ባደረበት የልብ ህመም ሳቢያ፣ በ79 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ድምጻዊ አለማየሁ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን እስከ ሦስት ዓመቱ ድረስ ከእናቱ ጋር ደሴ ነበር ያደገው።  የሦስት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ ወደ አዲስ አበባ አመጡት። ‘ክርስቲያን ትሬኒንግ ኢንስቲቲዩት’ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በትምህርት ቤቱ ቆይታውም መንፈሳዊ መዝሙሮችን  በእንግሊዝኛ ጭምር በመዘመር  ይታወቅ ነበር።
በዘመኑ ተወዳጅና እውቅ የነበሩ የምዕራባውያን ድምጻውያንን ሙዚቃ ማንጎራጎር ያዘ። በተለይ የሮክ የሙዚቃ ስልት ለአለማየሁ ነፍሱ ነበር። የአሜሪካውያኑን ድምጻዊያን ፓት ቦን፣ ቢል ሃሊይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊን የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አብዝቶ ይጫወት ነበር። የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃ አብዝቶ በመጫወቱ፣ በፀጉር አበጣጠሩና ዘመናዊ አለባበሱ ‘ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ’ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶት ነበር፡፡  
በዚህ እውቅናን እያተረፈ የመጣው አለማየሁ በጀነራል ዊንጌት፣ በዳግማዊ ምንሊክና በሌሎችም ትምህርት ቤቶች እየተጋበዘ ይዘፍን ነበር። በወቅቱ ለአማርኛ ዘፈን ብዙም ግድ አልነበረውም፡፡
ከአለማየሁ እሸቴ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል "ስቀሽ አታስቂኝ"፣ "እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ"፣ "ማን ይሆን ትልቅ ሰው"፣ "ምሽቱ ደመቀ"፣ "አዲስ አበባ ቤቴ"፣ "የወይን ሃረጊቱ"፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፤ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ"  እና "ተማር ልጄ" በዋነኝነት ይጠቀሱለታል፡፡
የድምፃዊውን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የመንግስት ባለሥልጣናትና አርቲስቶች እንዲሁም አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የሃዘን መልዕክት፤ ሃገራችን ካፈራቻቸው ታላላቅ ድምጻውያን አንዱ በሆነው በአለማየሁ እሸቴ ዜና እረፍት እጅግ አዝኛለሁ ብለዋል፡፡
‘‘የአለማየሁ ዘመን ተሻጋሪና ቁም ነገር አዘል ግጥምና ዜማዎቹ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ለዘለዓለም ይኖራሉ’’ ሲሉም  አስፍረዋል፤ በመልዕክታቸው። ለድምጻዊው ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ  ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።


Page 3 of 546