Administrator

Administrator

ጦርነትን መሸከም የምንችልበት ትከሻ፣ የጦርነትን ውጤቶች ማስተናገድ የምንችልበት አቅም የለንም። የጦርነትን አስከፊነትና ውጤቱን ደጋግመን አይተነዋል። ምንም የተለዬ ነገር አላመጣልንም። በተለይ በእርስ በርስ ጦርነት ያተረፍነው ነገር የለም። ውጤቱ "ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ" (vicious circle) ነው። ስለሆነም፣ የውጭ ወራሪ ኃይልን ለመከላከል ካልሆነ በስተቀር፣ ጦርነት እንደዋዛ የሚገባበት አማራጭ አይደለም።
ያሉብን ችግሮችና አለመግባባቶች ይታወቃሉ። ችግሮቻችንንና/አለመግባባቶቻችንን በመነጋገርና በሠላማዊ መንገድ መፍታት ይሻላል። አሁንም አልረፈደም፤ ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ጉዳት የለውም። በአጉል እልህና ፍጥጫ የሚሆን የለም።
እባካችሁ ለህዝቡ እዘኑለት። ህዝቡ የኑሮ ውድነቱ የፈጠረበት ሸክም ትከሻውን አጉብጦታል። በዚህ ላይ ጦርነት ከተጨመረበት ችሎ መቆም ያቅተዋል። "ትግላችን ለህዝብ ነው" እያላችሁ፣ የህዝቡን መከራና ስቃይ አታብዙ። ሌላውን ተውትና፣ ለወጣችሁበት ማህበረሰብ ርህራኄ ይኑራችሁ!?
እኔ ሳስበው ስለሚዘገንነኝ ነው‼️
Mohammed Ali Mohammed-

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ስኮት ቤሴንት ለሲኤንቢሲ በሰጡት መግለጫ፣ የኢራን አየር መንገዶች ከአዲሱ ማዕቀብ ጋር ተያይዞ ከሴፕቴምበር 23 ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አስታወቁ። ሃላፊው አየር መንገዶቹ ማረፊያ፣ ነዳጅ እና የቲኬት ሽያጭ አገልግሎት እንደሚያጡ ገልጸው፣ በጠቅላላው ከዶላር ስርዓት ውጭ እንደሚሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ አዲስ ማዕቀብ የኢራንን አቪየሽን ዘርፍ የሚደግፉ ከኢራን ውጭ ያሉ አካላትንም የሚመለከት ሲሆን፤ ቀደም ሲልም በአውሮፕላን ግዢ፣ በመለዋወጫዎች እና በጥገና እጥረት ተዳክሞ በቆየው የሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በጉዳዩ ላይ የኢራን መንግሥት እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

አቢሲኒያ ስቲል በቢሾፍቱ ከተማ ለቀድሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር የማሄንድራባይ ፓቴል መታሰቢያ የሚሆንና የሚሆንና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን «ኤጂአይ» የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረክቧል። በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ፣ የኬንያ አምባሳደር እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ከውጭ ሀገር የገቡ ጥራት ያላቸው ቁሳቁሶች የተሟላለት ይህ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ትምህርት ቤትነት የሚያገለግል ሲሆን፣ ተማሪዎችም በነጻ የሚማሩበት ነው። ትምህርት ቤቱ እስከ 380 ተማሪዎችን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ ከኬጂ 1 እስከ ኬጂ 3 ያሉ 100 ህፃናትንም ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

አቢሲኒያ ስቲል ለተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚሆን ሙሉ የምግብ እና የጥበቃ አገልግሎት ወጪዎችን እንደሚሸፍን ገልጿል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደምም ለአካባቢው ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በኡጋንዳ ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

በኢትዮጵያ የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍተውና የመጀመሪያው የሆነው የዲጂታል ጭነት አስተዳደር መድረክ "ጭነት" (ChiNet Transport Management System) በሳይንስ ሙዚየም ተመረቀ።

መተግበሪያው በአስጫኞች፣ በአጓጓዦች እና በደላሎች መካከል ያለውን የመረጃ ክፍተት በመድፈን፣ አጓጓዦች ጭነት ጭነው ከሄዱ በኋላ ተመላሽ ጭነት ሳያገኙ የሚደርስባቸውን እንግልት የሚቀርፍ አጠቃላይ ዲጂታል ገበያ ይፈጥራል።

ይህ መተግበሪያ አስጫኙ ጭነቱ የት እንዳለ በክትትል እንዲያውቅ፣ አጓጓዡ ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ በቀላሉ ጭነት እንዲያገኝ እና ደላሎችም ስራቸውን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲያሰፉ ያስችላል። ከዚህም ባለፈ የስፔር ፓርት አቅራቢዎች፣ የመኪና አከራዮች እና የሁለተኛ እጅ መኪና ሻጮች የሚገናኙበት ሰፊ የንግድ መድረክን አካትቷል።

የመድረኩ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ላዕከ ራሳቸው የትራንስፖርት ባለቤት በመሆናቸው ችግሮቹን በቅርበት አውቀው መድረኩን እንዳዘጋጁት ተናግረዋል። አፕሊኬሽኑ በሁለቱም የሞባይል ማግኛዎች (ፕሌይስቶር እና አፕስቶር) በነጻ የሚገኝ ሲሆን፣ ለደህንነት ሲባል ተጠቃሚዎች ሕጋዊ ሰነዶቻቸውን አረጋግጠው በግልጽነት እንዲሰሩበት ተደርጎ ተዘጋጅቷል።

እኔ ጋዜጠኛ ነኝ። የሚዲያ ሰው ነኝ። ለዓመታት በሙያዬ የሰራሁ፣ የሙያውን ኃላፊነትና ጫና የምረዳ ሰው ነኝ። ዛሬ ግን “ጋዜጠኛ ነኝ”፣ “የሚዲያ ሰው ነኝ”፣ “ቲክታከር ነኝ” በሚል ስም የሌሎችን ባለሙያዎችና አገልጋዮች ሙያዊ ክብር የሚያዋርዱ፣ የሚያስፈራሩ፣ የሚያሸማቅቁ እና “ስሜን ተጠቅሜ ምን ላደርግ እችላለሁ?” የሚል አካሄድ የሚከተሉ ሰዎች መኖራቸው ያሳስበኛል።

ሚዲያ ማለት ሥልጣን አይደለም፤ ኃላፊነት ነው።ጋዜጠኝነት ማለት ሰውን ማስፈራራት አይደለም፤ ለሕዝብ የሚጠቅምእውነታን በሙያዊ መርህ መፈለግና ማቅረብ ነው።
የሚዲያ መድረክም ማንንም ሰው ለማዋረድ፣ ለማስፈራራት ወይም የራስን ጥቅም ለማስፈጸም የተሰጠ የግል መሣሪያ አይደለም።

በተለይ የጤና ባለሙያዎችን እንመልከት። ሐኪም፣ ነርስ፣ ፋርማሲስት ወይም ሌላ የጤና ባለሙያ በየቀኑ የሰው ሕይወትና ጤና ላይ ኃላፊነት ይሸከማሉ። እነሱ ላይ የሚነሳ ችግር ካለ ጥያቄ መጠየቅ፣ ቅሬታ ማቅረብ እና በሕጋዊ መንገድ መከታተል ይቻላል። ነገር ግን ሙያቸውን ማዋረድ፣ ማስፈራራት ወይም በማይገባ መንገድ ማጋለጥ የጋዜጠኝነት ሥራ አይደለም።
ሙያዊ ትችት እና ማስፈራራት ፤ መጠየቅ እና ሰውን ማሸማቀቅ ወይም የሕዝብ ድምፅ መሆን እና የግል ጥቅምን በሚዲያ መድረክ ማስፈጸም አንድ ነገር አይደሉም።

ታዋቂ መሆን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን አይተካም።ብዙ ተከታዮች መኖር ሙያዊ ብቃትን አያረጋግጥም።ማይክሮፎን መያዝም የማንንም ሰው ክብር ለመንካት ፈቃድ አይሰጥም።
ስለዚህ እንደ ጋዜጠኛ እላለሁ፦ ሙያ ክብር አለው። የሌላውን ሙያ ማክበር የራስን ሙያ ማክበር ነው።እንጠይቅ፤ እውነትን እንፈልግ፤ ስህተትን እንተች። ነገር ግን ሰውን አናስፈራራ፣ ሙያን አናዋርድ፣ የሚዲያንም ኃይል ለግል ጥቅም አንጠቀምበት።

ምክንያቱም የሚዲያ ኃይል የሚመዘነው ስንት ሰውን ማስፈራራት በቻልን ሳይሆን፣ ስንት ሰው እውነትን እንዲያይ፣ መብቱን እንዲያውቅ እና በክብር እንዲኖር ማገዝ በቻልን ነው። ሙያ ክብር አለው። እና ያንን ክብር መጠበቅ የእኛ ኃላፊነት ነው!


ግርማ ፍስሃ

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

አንድ የቻይና የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ሰዎች እስከ 150 ዓመት እንዲኖሩ የሚያስችል «ፒሲሲ1» (PCC1) የተባለ ውህድ የያዘ እንክብል አዘጋጅቻለሁ ብሏል። ከወይን ፍሬ ዘር የሚገኘው ይህ ንጥረ ነገር እድሜ እየገፋ ሲሄድ በሰውነት ውስጥ ተከማችተው በሽታዎችን የሚያስከትሉ ያረጁ ሴሎችን እንደሚያጠፋ ይነገራል።

ይህ ውህድ በአይጦች ላይ በተደረገ ሙከራ ዕድሜን በትንሹ እንደሚያራዝም ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይቷል። ሆኖም ጥናቱ እስካሁን የተደረገው በእንስሳት ላይ ብቻ በመሆኑ፣ በሰዎች ላይም ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያመጣ የተረጋገጠ ነገር የለም። የሰዎች አኗኗር እና የእርጅና ሂደት ከእንስሳት በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ውህዱ በሰው ላይ ይሰራል ማለት አያስችልም።

ኩባንያው ሰዎችን ለረጅም ጊዜ ማኖር ብቻ ሳይሆን ከእድሜ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በሽታዎች ማዘግየት ዋናው አላማው መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን እንክብሉ ሰዎችን እስከ 150 ዓመት ማቆየቱ አሁን ላይ ከእውነት ይልቅ ግምት ብቻ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ በሰዎች ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት የሕክምና ሙከራዎችን ማካሄድ የግድ ይላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2026 የስካይትራክስ (SKYTRAX) የዓለም አየር መንገድ ሽልማት ለ9ኛዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በመባል ታላቁን ዕውቅና ተቀበለ። አየር መንገዱ ከዚህ ዋና ሽልማት በተጨማሪ በአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክላስ እና ምርጥ የኢኮኖሚ ክላስ አገልግሎት ሰጪ በመባል ተመርጦ የአህጉሪቱ ቁጥር አንድነቱን በድጋሚ አረጋግጧል።

ይህ ድል አየር መንገዱ ለጥራት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች የሰጡትን ታማኝነት የሚያሳይ ነው። እንዲሁም የሠራተኞቹን ያላሰለሰ ጥረትና የላቀ የደንበኞች እርካታ ለመስጠት የሚያስችለውን የአሠራር ደረጃ በዘላቂነት ማስቀጠሉን የሚመሰክር ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የምትታወቀው ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ፣ አራተኛውን አዲስ አልበም ልታወጣ መሆኑ ተነገረ። ቀደም ሲል "እወደሀለሁ"፣ "አታላይ" እና "ብር ብር" የመሳሰሉ ተወዳጅ ዘፈኖችን ለአድናቂዎቿ ያደረሰችው አርቲስቷ፣ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ታላላቅ ሽልማቶችን በማግኘት ቀዳሚ መሆኗ ይታወሳል።

መስከረም 16 ቀን 2019 የሚወጣው አዲሱ አልበም 10 ውብ ሙዚቃዎችን የያዘ ሲሆን፣ ከአልበሙ ውስጥ አንድ አዲስ የሙዚቃ ቪዲዮም እንደሚለቀቅ ተገልጿል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

300 የህወሓት ታጣቂዎች ህወሓት ከኤርትራ ጋር የፈጠረው ጥምረት ለትግራይ ሕዝብ የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ እጃቸውን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ምዕራብ ዕዝ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

ተዋጊዎቹ ከገቡበት ዕዝ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የህወሓት አገዛዝን በመጥላት ሠላምን በመምረጥ እጅ ለመስጠት የሚጠባበቁ በርካታ ሌሎች የትግራይ ወጣቶችም እንዳሉ አረጋግጠዋል።

የትግራይ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው በጠብመንጃ ሳይሆን በመነጋገርና በመግባባት ነው የሚል እምነት ይዘው ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሠራዊት እጅ የሠጡት የህወሃት ታጣቂዎች፣ ከሁለት መቶ ሰማንያ በላይ የነፍሰ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ በርካታ የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ የጦር ሜዳ መነፅርና ልዩ ልዩ ዶክመንቶች ይዘው መግባታቸውም ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ ለ37 ዓመታት የኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሃም፣ ለከተማዋ ከንቲባነት በምርጫ ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ዶቼቬለ ዘግቧል። ፕሮፌሰሩ በላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የከተማዋ የምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ በምርጫው ለመወዳደር የተነሳሱት ከከተማው ነዋሪዎች፣ ከማህበራትና ከንግዱ ማህበረሰብ በመጣላቸው ከፍተኛ ግፊት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምርጫው በፈረንጆች የካቲት 2027 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፣ ፕሮፌሰሩ የየትኛውም ፓርቲ አባል ባለመሆናቸው ህዝቡን በነጻነትና በእኩልነት ለማገልገል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን እያጠናቀቁ ይገኛሉ።

ከፖለቲካው በተጨማሪ ፕሮፌሰር ጌቱ በላይፕዚግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማቀራረብና ማህበር በማቋቋም ይታወቃሉ። እንዲሁም «የላይፕሲሽ ኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር» በተሰኘው ድርጅታቸው አማካኝነት በትውልድ ቦታቸው በጎጃም የትመን አካባቢ የሚገኘውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማደስና የጉድጓድ ውሃ በማውጣት ትልቅ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

ፕሮፌሰር ጌቱ ለከንቲባነት የሚወዳደሩት ገንዘብ ወይም ስልጣን ፈልገው ሳይሆን ለኖሩበት ህብረተሰብ ምስጋናቸውን ለማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል። አሸንፈው የመጀመሪያው ጥቁር የላይፕዚግ ከንቲባ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረትም ከጀርመናውያን ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያንም በሃሳብና በገንዘብ እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas