Administrator

Administrator

Saturday, 27 March 2021 14:04

የግጥም ጥግ

  ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ! የእብዶች ረሀብ

ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን ጭላንጭል ሕዝብ በድንገት ሲያይ
ጨለማውን ለምዶ በእንግዳው ብርሃን ተጨንቆ ሲወያይ
‹ውቃቢ› የሚገፋ ይሆናል ዋና ከልካይ ‹አይሆንም ! ይቅር!› ባይ፤
አዲስ ህልም የሚሸሽ ወትሮም ይቸኩላል አጉል ስም ማውጣት ላይ
 . . .
እውቀት የራበችው ዘርዐ ያዕቆብ ለኢትዮጵያ ውብ እብድ ነበረ፤
ያንቀላፋች መንፈስ ተነስታ እንድትቆም በ‹‹እንዴት?›› የቆፈረ፡፡

ዛሬ ልንኮራበት ያኔ ህዝበ ሮሀ የጉድ ዜና አወጀ፤ዠ
ኪነ-ህንፃ እርቦት ንጉስ ድንጋይ ሊወቅር ስለተዘጋጀ፤
‹‹አለቱን ፈልፍለን ቤተ መቅደስ እና´ርገው ኑ እንነሳ›› ባለ
‹‹ቅዱስ ላልይበላል እኩይ ሀሳብ ያዘ - አበደ!›› ተባለ::
           .    .    .
ሩቅ ዘመንም ሳንሄድ እዚህ ሩብ እልፍ አመት የሆነው ቢጠየቅ. . .
ጦቢያ ተከፋፍሎ  በየጎጥ ተቧድኖ  ሹመት ሲነጣጠቅ፤
ኢትዮጵያን ሊያጸና በአንድነት ሊያቆማት ሲነሳ አባ ታጠቅ፤ዠ
ጠላትን ሊመክት ቴክኖሎጂ ጠምቶት ሴባስቶፖል ሊሰራ፤ዠ
መዶሻ ጨብጦ ጋፋት ውሎ ቢያድር ከቀጥቃጮች ጋራ
ጠይባን ማፍቀሩ የጤና እንዳልሆነ
የአጤ ቴዎድሮስ ነገር ‹‹ማበዱ!›› ተወራ፡፡
.   .   .
ሰላሙ ባልጠራ ውጥንቅጥ እንቅጥቅጥ
አንቀጥቅጥ ዙፋኑ ላፍታ ነግሶ የቆየው፤
ዮሐንስ ብርቱ ባዝኗል
ከአሸንክታብ ፡ ድሪ ማተቡ የፀናን
ክቡር ያገር  ወሰን እንደ እብድ የተራበው፡፡
የፀሐይ ገበታን ትዕምርት ማህተም
በአናቱ ተነቅሶሺህ አመታት የቆየው፤
አለት ያንሳፈፉ እንደ ኑግ ለጥልጠው በእብነ አድማስ የሰፉ
ያያት ቅድማያቶቹ ጥበብ አምድ ሳለው፤
የእጹብ ድንቅ ኪን ፀጋ ቱሩፋት ጌጥ ሀውልት
አክሱም ፊቱ ቆሞዞር ብሎ እንዳይቃኘው፤
የውስጥ ትርምሱየሹመት ሁካታው
ሌቱ ያልተገታ የባእዳን ትንኮሳው ከብቦ ሲያሰቃየው
ፊት ፊቱን ሲያማትር የአገር ድንበር ጥሙ እብደቱ ሲያተከነው ፤
የአዕላፍ ጠይባን ቅርሱን
የምድሩን አንጥረኛ የጥበብ ክህሎት
አንገቱን አዙሮ ቀና ብሎ ሳያየው፤
ዋ! ያ ጀግና ቀረ የጦር ዘመን እጣው
ከክቡር አካሉ አንገቱን ቢለየው ፡፡
.ምኒልክ ተነቅፏል ለእድገት የሚበጁ
የጦቢያን ባለ እጆች መርጦ በማክበሩ፤
ስልጣኔ ተርቦ
ስልክና መኪና ወፍጮና ሲኒማ ሲያስመጣ ላገሩ
ዘመኑን ነቃፊ  ሕዝቡን አወገዙ
‹‹ሰይጣን ሥራ መጣ ! ይኼ እብደት ነው!!›› አሉ፡፡. ..

አዲስ ህልም የሚያልም በዘመኑ እብድ ነው
የህልሙ ፍቺ ሰምሮ በእውን እስከሚያየው፤
ያም ባይሆን እስኪሞት ህልሙን ነው እሚኖረው ፡፡
ስለ ረቂቅ ውበት
ከጊዜያቸው ቀድመው ‹‹እብዶች›› የተባሉ
ዘመናት ተሻግረው
በህያው ግብራቸው ገዝፈው ዛሬም አሉ፤
ያገር አድባር ሆነው
የወል ትውልድን ተስፋ እያቀጣጠሉ፡፡

እዛሬም ላይ ሆነን የምንደመመው፤
‹‹ጉድ›› ተብዬዎቹ
አኑረው ባለፉት ዘመን ተሻጋሪ የ‹‹እብደት  ራዕይ›› ነው፡፡

እኛም...
ብርሃን እየናፈቅን ቆመን እየቃዠን በጨለማ የኖርነው፤
ውብ አለም መድረሻ መንገድ የሚያሳዩን እቡዶች ተርበን ነው፡፡

ሀምሌ 2003 ዓ.ም።
የፀሐይ ገበታ

Monday, 29 March 2021 00:00

አብረን እንስከን - 2

ያ! ታላቁ ባለቅኔ ሎሬቱ. . .
ያገር አድባር-የህዝብ ዋርካው «እ…!» እያለ፤
ስለጥበብ፥ ስለ ህዝበ-ዓለም እድሜ ልኩን እንደተብሰለሰለ
ቢቸግረው ”አብረን ዝም እንበል” እንዳለ፤
ከነቁጭቱ - ከነህልሙ እንደዋዛ ከንበል አለ፡፡
ግርምቴ . . .
ተፈጥሮ በነጠላና በህብር በፈጣሪ ጥበብ መዋቀሩን ላስተዋለ
የተነጣጠለ፥ የተቃረነ ቢመስልም
በፈጣሪና በተፈጥሮ ህግጋት ነው’ኮ ተገማምዶ፥ተሳስቦ  በአብሮነት የተሳለ፡፡
የሰው ልጅ ግና…!
«በህግ አምላክ!  . . .   በህገ መንግስት!” »  እየተባባለ
ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየሳለ፤
በሆነ ባልሆነው እርስ በርሱ አንገት ለአንገት ሲቀላላ ስለምን በከንቱ ዋለ?
የኛ ጉዶች፡-
በምላስና-ጠመንጃ እየተቋሰሉ¡
በዛቻ-በፉከራ ተጋግለው ሲገዳደሉ እየዋሉ
በየቤተ-ሃይማኖታቱ ደጃፎች ራሳቸውን ብፁዕ ለማስመሰል እየታገሉ፣
በየሸንጐው -በየፓርላማው እጃቸውን ሰቅለው <ፍትሐዊነት¡ እኩልነት¡> እየተባባሉ፤
በዕውንም ሆነ በህልማቸው ግን
 ለበቀል ለየጣዖታቱ-ለየአድባራቱ ሳይቀር ስለምን ስለት ተሳሳሉ፤
ስንት ሰውስ ሲሰዋ ይበቃ ይሆን? ዕርቅ ለማውረድ-ለአብሮነቱ ተባባሉ፡፡
ጡንቻ ለጡንቻ ተገጫጭተን
ትከሻ ለትከሻ ተለካክተን
በቃላት ድምቀት፥ በዲስኩር ብልጫ ተወናብደን
በባህል፥ በታሪከ ትርክት ተቀራርነን
ከእስራቱ-ግርፋቱ፥ ከደም አዙሪቱ መውጣት ቢያቅተን   
ምነው ለህዝቡ እፎይታ ብንሰክን አብረን።
ወገኖቼ . . .     
በማናውቀው፥ በማያስማማን ሚዛን ተመዛዝነን
በቃላት ጋጋታ በህግ መሰል አንቀጻት ተደናቁረን
መደማመጥ መግባባት ካልቻልን
እባካችሁ ህዝብ አናጫርስ፥ አገር አናፍርስ በደመ-ነብስ ተደናብረን፡፡
ከአልቦ በታች ቁልቁል እንዳይሆን ነጋ’ችን፤
ምናለ  ብንሰክን አብረን    
ህዝብና አገርን ለማዳን ብለን፡፡
ቃል-እምነት-መሀላ በስጋ ተበልጦ ቁልቁል ከምንወድቅ
በምድር በሰደድ፥በሰማይ በሲዖል እሳት ከምንነድ
አይሻልም እንዴ ወገኔ?
አብረን ሰክነን በአገራችን ፍቅርና ሰላምን ብናጸድቅ፡፡
ሁሉም በየጐራው እኔ ነኝ መነሻው፥ አቅኚው ካለ
ያም ይህም እርስ በርሱ ተጧጡዞ ያለልኬት «ገፋኝ-ጨቆንከኝ»  ከተባባለ
በጥላቻ . . . በንቀት አገር ምድሩ ከተበከለ
የሥነ- ሂሊና ሚዛኑ ከተከነበለ
ከዚህ በላይ ውድቀት- ድቀት- ሞትማ የታለ፡፡
ወገኖቼ . . .
ይሻል ይሆናል-ካልን እስቲ በጋራ እንሂድ
ወደ የ…ክልሎቹ አብረን  እንንጐድ…
ህገ መንግስት «ይቀደድ!...አይቀደድ!» ብለን፥ቸኩለን ሳንፈርድ
እባካችሁ! በቅድሚያ፥ የህዝባችንን ዕንባ፥ አብረን እናድርቅ፡፡
ከድምጽ ማጉያና ከእጅ መዳፍ ጭብጨባ እንገለል፡፡
ለአንድ አፍታ እንኳን-ከየአደባባዮቹና  ከየአዳራሾቹ እንነጠል፡፡
እንደጥንቱ በዛፎች ጥላ ስር እንጠለል፡፡
በጋራ ሆነን በየወጋችን-በየባህላችን  አብረን «ሰላም-እርቅ» እንበል፡፡
ከአባይ ማዶ ወደ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ወደ ህዳሴው ግድብ አብረን እንውረድ
እጅ ለእጅ ተያይዘን በፋሲል ግንብ . . .በጣና ዙሪያ እስክስታ እናውርድ፡፡
አብረን እንሂድ ጋምቤላ ከለማለሙ አገር
በባሮ ወንዝ ላይ በፍቅር መርከብ አብረን እንሸርሸር፡፡
ላሊበላ ሂደን «እግዚኦ ማረን» እንበል
የፈጣሪን ቡራኬ መለኮቱን እንቀበል፡፡
ወደጥንታዊቷ አክሱም እንዝለቅ …
ከአዴታቱ እጅ ተቋድሰን አንባሻውን
በበረከቱ እንፈወስ እርስ በእርስ ተመራርቀን፡፡
«ሆ!ያ ማሬዎ! -ማሬዎ!» አብረን እያልን
ቢሾፍቱ-ሆራ አርሰዲ ለእሬቻ እንውረድ
ሀባቦ-መርጋ ጉራቻ … እርቁን በእጃችን ጨብጠን፡፡
ወደ አርባ ምንጭ እንዝለቅ …  
ለህዝብ ክብር፥ ለወገን ፍቅር ብለን፥ ከኒያ ደጋግ ህዝቦች ጋር ሆነን
እርጥብ ሳር ይዘን፥ በመሬት ላይ  እንውደቅ አብረን፡፡
ወደ ቦረና ከአንጋፋዎቹ መገኛ አብረን እንዝለቅ
የገዳ-ዲሞክራሲ ችግኙ በሁሉም ሥፍራ እንዲጸድቅ፤
በአንደበተ ርቱዓኑ፥ በንፁሀኑ አባገዳዎቹ  እንመረቅ፡፡
ወደ ጅማ -ወደ ከፋ ሽምጥ እንጋልብ
ከቡና ረከቦት ዙሪያ እንሰብሰብ!
«አቦል ጀባ!» እየተባባልን እንዋዋብ፡፡
ሐረር ጀጐል፥ ደገሃቡር ሶማሌ፥ ድሬ ሼህ ሁሴን አብረን እንዝለቅ
«አስቶፍሩላህ!...አላሁ አክበር! »  ብለን ከፈጣሪያችን እንታረቅ፡፡
ግርምቴ . . .
እንሂድ አፋር፥ ከቅድመ ዘራችን ከእናታችን ሉሲ አገር
እንድትተርክልን በእሳተ ገሞራ የመኖርን ሚስጥር
ለሚሊዮን አመታት አጽሟ ሳይፈራርስ የመዝለቁን ቀመር፡፡
እኛው በየአምስት አመቱ «ውረድ!...አልወርድም!»  ከምንባባልበት
ለ4 ኪሎው ወንበር ከምንዶልት፥ ከምንፋጅበት
ለህዝባችን፥ ለአገራችን ብለን በቅድሚያ አብረን ብንሰክንለት፡፡
ምናለ ጐበዝ! ለዚህ ምስኪን ህዝብ በቅድሚያ ብናስብለት፤
በሰቀቀን ባይባዝንበት፥ በችጋር- በጠኔ ባይረግፍበት፣፣

ሎሬቱ እንዳለው፡-
« . . . . . . .
ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፥ አዲስ ቀን ሳይጨልምብን
ድፍን ደመና ሳይቋጥር፥ክረምት ውርጅት ሳይወርድብን
. . . . . . . ፡፡»
ወገኖቼ . . .
በኮሮና እና በብረት መሃል ተወጥረን
ጦርነቱ ከሚፈጀን፣ በሽታና ረሃቡ ከሚያረግፈን
ምናለ ፉከራው ቀረርቶው ቢቀርብን፡፡
እናም፡-
ለአንድ አፍታ እንኳን «አሐዳዊ!...ፊዴራላዊ» ቃለ ግነቱን ገተን
ህዝባችንን-አገራችንን ብናድን አብረን ሰክነን
ለጊዜው እንኳን ባንስማማም «ሜ. . . ሃቡልቱ ዱቢን » ብለን ተስማምተን፡፡
 አሰፋ ጉያ
መታሰቢያነቱ፡-
የሥነ ጥበብ ፍቅርንና ለህዝብ የመቆርቆርን ቀናኢነት ላወረሰኝ፤
ለጋሽ ለማ፤ የክብር ዶክተር ሎሬት አርቲስት፣ ሻምበል ለማ ጉያ ይሁንልኝ፡፡

Saturday, 27 March 2021 12:35

አዳኞቹና ድቡ

   ከእለታት አንድ ቀን ፤ አዳኖች ጫካው ውስጥ ሁለት ወዳሉ ድቦች ያገኛሉ። አንደኛው አዳኝ ፈጥኖ ወደ አንድ ዛፍ ላይ ወጣ። ሁለተኛው ድብ መንገዱ ላይ ተዝለፍልፎ ወደቀ።
ድቡ ጠጋ ብሎ አሸተተው፡፡ አሸተተውና ትቶት ሄደ፡፡
ዛፍ ላይ የወጣው ጓደኛው ወርዶ ወደ ወደቀው ጓደኛው መጣና፤
“ለመሆኑ ድቡ ምን አለህ?” አለና ጠየቀው።”
ጓደኝየውም፤
“ድቡ ምን አለኝ መሰለህ ሁለተኛ እንደዚህ ያለ ጓደኛ መቼም እንዳይኖርህ ተጠንቅቆ” አለው። ጓደኝየውም፣
“ምነው እኔንም ይህንኑ ዓይነት ምክር በመከረኝ” ብሎ ፀፀቱን ገለፁለት።
*   *   *
የጥሩና ፅኑ ጓደኝነት ፍሬ ነገር ልባዊ! ወዳጅነት። የሁሉም ወዳጅነት ማሳኪያው ፍቅር፣ እውነትና ታማኝነት ናቸው። ማህበረሰባችን እነዚህን እሴቶች እያለማ ወደፊት እንዲጓዝ ምኞታችን ከፍ ያለ ነው። ከመመንደግ ይቀድማል ማደግ! ከማደግ በፊት የማያዳግም ህልም! ይህን ህልም መስመር ማሲያዝ ለብቻው ከባድ ትግል ነው። ሁሌም አንድን ትግል ማሸነፍ የሚቻለው በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው።
የማያቋርጠውን  እንቅስቃሴ መልክ ለማስያዝ ብርቱ የማስተባበር ጥንቃቄን ይጠይቃል።
የተገዢዎቹን መላና ትእግስት የሚቃኘው የገዢዎች ጠቢብነትና  ብስለት ነው፡፡ ያም ሆኖ መንገዱ ሁሉ ጠመዝማዛ እንጂ ሁሉም ቀጥ ያለና ሊሾ አይደለም። መንገዱን መልመድንና መጎረባበጥን ግድ ይላል!
በእርግጥ መንገዱ በሁለንተናዊ መንፈሱ ችግር በችግር ይሁን ማስታችን አይደለም።
“አልኩሃ ምን ትሆን
*   *   *
አልኩሃ ምን ትሆን
እኔም እናትህ ነኝ
“አንተም ልጄ ብትሆን” ማለታችን እንጂ።
እድላችን እራሳችን እናንብብ!!  እራሳችን  እንገንዘብ! መቼም ይሁን መቼም መማር አይቆምም! ዋናው ቁም ነገርም ይሄው ነው።
አንዳንድ ሁኔታ መቼም ላይለቀን የተማማልን ይመስላል- የሀገራችን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ   ( subjective and objective)  የግዱን የሚያስፈልገንን ያስደርገናል።
አሁን ያለን መንግስት የእጀርባ እንጂ የነፃ አስተሳሰብ ሀሳብ ላይ ያተኮረ እየሆነ እንዳልሆነ አውቀናል- ገምተናል- አስልተናል….
ባንድ ልብ ፕሮቴስታንት
ባንድ ልብ  ሚሊቴሪ ነን
ባንድ ልብ- ናሽናሊስት (ብሔርተኛ) ነን!
ባንድ ልብ  አገር ወዳድ ነን!
ኢትዮጵያ የማንኛውንም አገር አካሄድ ያለመቀበል መብት አላት፤ ሉዐላዊት አገር ናትና!
እንደምታሸንፍ እናውቃለን! ምክንያቱም ታሪኳ፤ ፖለቲካዊ፣ ጂኦግራፊዊ፣ የማይሸነፍ ጀግኖች ልጆቿ ናቸው። ነፍሳቸው ደማቸውን  ከፍለውታል- ልብ ስላላቸው ልብ  ይሰውላቱታል፡፡ ሰው ስላላቸው ሰውነታቸውን ያሳዩታል፡፡ ልጆቿን በዚሁ ፍሬ ታፈራለች ዕልፍ አዕላፍ ታመርታለች፡፡ “ይህችው ናት አገርህ! ሀገርህ ናት በቃ!አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሀት ንቃ ያልነው” ለዚህ ነው፡፡


      (መቅድም)
የዚህን መጽሐፍ ርዕስ የሚመለከቱ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞች በቀዳሚነት የደራሲውን ማንነት ለማወቅ እንደሚፈልጉ እገምታለሁ፡፡ የሙያ ማንነቴን በተመለከተ የዘመናችን በይነ-መረብ ያለብዙ ድካም በቂ መረጃ እንደሚሰጣቸው አምናለሁ። የፖለቲካ ‘የጀርባ ታሪኬን’ በሚመለከት ግን ብዙ እንዳይቸገሩ ስለ ራሴ በጥቂቱ ልግለጽ። የልጅነት ዘመኔ አስተሳሰብ የተቃኘው በአብዛኛው ባካባቢዬ ከምታዘባቸው
ማህበራዊ ጭቆናዎችና በተለያየ ወቅት ከአባቴ ከአቶ መብራቱ በላይ ጋር በማደርጋቸው ጭውውቶች ላይ የተመሰረቱ ነበሩ። ያም ሆኖ፣ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ከአጫፋሪነት የዘለለ ድርሻ አልነበረኝም። በ1966 ዓ.ም በወቅቱ ስሙ ናዝሬት፣ በአሁኑ ስሙ አዳማ በሚገኘው የአፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ይህንን ተከትሎ የመጣው የእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በወቅቱ የነበረኝን የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ አጠቃላይ የህይወት እይታ በመሰረታዊ መልኩ የቀየረ ሁነት
ነበረ። ከአስራ ሰባት እስክ ሃያ አንድ ዓመት እድሜዬ ድረስ፣ ከወጣትና የሰራተኛ ማህበር መሪነት እስከ ቀበሌ ሊቀ መንበርነትና የክፍለ ሃገር የፖለቲካ ሃላፊነት የደረሰ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ፣ በቀዳሚነት በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ተባባሪነት ሶስት ጊዜና በኋላም በማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሉዩሽናዊ ድርጅት (ማሌሪድ) አባልነት ሁለት ጊዜ፣ በአስራ አራት የተለያዩ እስር ቤቶች ቆይታ አድርጌአለሁ። በመጨረሻም፣ የአስር ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ፣ በ1975 ህዳር ወር
‘በምህረት’ እስከተፈታሁበት ጊዜ ድረስ በወህኒ ቤት ታስሬአለሁ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረኝ ንቁና ቀጥተኛ ተሳትፎ በዚሁ አብቅቷል ማለት ይቻላል።
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እኔም አንዳንድ የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞችና ተንታኞች ሊወቅሱት የሚዳዱት የዚያ ትውልድ አባል ነኝ። የዚያ ትውልድ እምነትና ጽናት ዋነኛው ምንጭ በወቅቱ የነበረውን ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ጭቆና እና አድልዎ ‘ለምን’ ብሎ መጠየቁና ሁኔታውን ለመቀየር ቆርጦ መነሳቱ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በየትኛውም ወገን ለተከፈለው መስዋእትነት ታላቅ ክብር አለኝ። በዚያው መጠን ግን፣
የየራሳችንን ፖለቲካ መሪዎች የሚገባውን ያህል ‘ለምን’ ብለን አለመጠየቃችን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለን ይሰማኛል። ምንም እንኳን ሁሉም እስራቶቼ ይህንኑ ጥያቄ ከማንሳቴ ጋር የተያያዙ ቢሆንም፣ የዚያ ትውልድ አባል የሆንን ሁላችንም በበቂ ሁኔታ ባለመጠየቃችን ለተከተለው ቀውስ የየድርሻችንን ሃላፊነት ልንወስድ ይገባል። ከአስር ዓመታት የፖለቲካና የእስር ህይወት በኋላ፣ በ1966 ወዳቆምኩት ትምህርት በመመለስ የኬሚካል፣ ኢንዱስትሪና አካባቢ ምህንድስናን በማጥናት ላለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ለተለያዩ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ስሰራ ቆይቻለሁ። እንደመታደል ሆኖ፣ የሙያ ህይወቴም በዘመናችን ገኖ ያለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት (globalization) በምድራችን የተፈጥሮ ሚዛን ላይ የሚያስከትለውን መዛባት ‘ለምን’ ብሎ በመመርመር፣ ሁሉንም አካታች የሆነ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ላይ የሚያተኩር ሆኗል። በዚህ ሂደትም ውስጥ፣
ውስብስብ ችግሮችን ባግባቡ ለመረዳትና መፍትሔ ለመሻት ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) ያለውን አበይት አስተዋጽኦ ለመገንዘብና ለመረዳት ችያለሁ።
ዛሬ በሃገራችን ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ስንመለከት፣ በቀዳሚነት በማናቸውም ወገን ለሚወሰዱ የፖለቲካ አቋሞችና እርምጃዎች ‘ለምን’ የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ከመመርመር ይልቅ አብዛኞቻችን አንድን የፖለቲካ አመለካከት በጅምላና በጭፍንነት መደገፍ ይታይብናል። ጥቂቶች የሚጠይቁ ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ውስብስብ የሆነውን የፖለቲካ መስተጋብር ወደ ጥቂት የአመክንዮ ሰበዞች የማቀናነስ አዝማሚያ
(simplification) ይታይባቸዋል። እንዲህ አይነቱ አዝማሚያዎች በተለይም ወጣቱን በስሜታዊነት በማነሳሳት አስፈላጊ ወዳልሆነ የእልቂት አዙሪት ሲመሩት ይታያሉ። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖረኝም፣ ‘ለምን’ የሚለውን ጥያቄ ባገኘሁት የተናጠል አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዜጋ ማንሳቴ አልቀረም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን እየበረታ የመጣው የፖለቲካ ምስቅልቅል እያሳሰበኝ በመምጣቱ፣ በዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ምሁራዊ ሃሳቦችን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዳጋራ አድርጎኛል። እነኝህን ጽሁፎች የተከታታሉና በጽሁፎቹ ላይ ተመርኩዞ በጥቂት ሚዲያዎች የቀረቡትን ውይይቶች ያዳመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ጽሁፎቹ በመጽሀፍ መልክ ተደራጅተውና ዳብረው ቢቀርቡ አመለካከቱ በይበልጥ ለህዝብ፣ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ተደራሽ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ይህንን መሰረት በማድረግ የምህዳራዊ አስተሳሰብ ታሪካዊ አመጣጥና ዋና ዋና እሳቤዎቹን በማቅረብና ቀደም ሲል በጋዜጣ የወጡትን ጽሁፎች ይበልጥ በማብራራት በመጽሐፍ መልክ ተደራጅቶ ቀርቧል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች በወጣትነት ዘመኔ በነበረኝ የፖለቲካ እይታና በጎልማሳነት ከኖርኩበት የአካዳሚና ዓለም አቀፍ የስራ መስክ በተቀሰሙ የሙያ ልምዶች የተቃኙ በመሆናቸው የራሳቸው ውሱንነት እንደሚኖራቸው እገምታለሁ።
ይህ ውሱንነት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ወቅቱ ለሚጠይቀው የብሔራዊ መግባባት ውይይት የራሱን ድርሻ ያበረክታል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ወጣቱን ትውልድ ዘመኑን ከሚመጥን የዕውቀት መስክ ጋር በመጠኑ በማስተዋወቅ የምክንያታዊ ጠያቂነት (critical thinking) ባህልን እንዲያዳብር ያግዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
(ከላይ የቀረበው ጽሁፍ በፕሮፌሰር ደስታ መብራቱ ተዘጋጅቶ ከታተመው ;ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ; የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተወሰደ ሲሆን የመጽሐፉ የመጀመሪያ ህትመት 1500 ቅጂዎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ቤተመጻሕፍትና የሚዲያ ተቋማት በነጻ የሚሰራጭ መሆኑን ደራሲው አስታውቋል፡፡)

       8 አዳዲስ የኮሮና ክትባቶች በመጪው አመት አገልግሎት ላይ ይውላሉ

          አስትራዜኒካ የተባለው የኮሮና ቫይረስ ክትባት የደም መርጋትን ጨምሮ የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ያስከትላል የሚለው መረጃ በመላው አለም በስፋት መሰራጨቱንና አገራት ክትባቱን ለዜጎቻቸው መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ፣ የአለም የጤና ድርጅት፣ በአለማችን እስካሁን ድረስ የኮሮና ክትባት በመውሰዱ ለሞት የተዳረገ አንድም ሰው አለመኖሩን አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ሶምያ ስዋሚናታን ባለፈው ሰኞ በጄኔቫ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ እስካሁን በመላው አለም የኮሮና ክትባቶች ባስከተሉት የጎንዮሽ ጉዳት ወይም በቀጥታ በክትባቶቹ ሳቢያ ለሞት የተዳረገ ሰው እንደሌለ በመጥቀስ፣ ህዝቡ በመሰል ስጋትና ጭንቀት ውስጥ እንዳይገባ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ሳይንቲስቷ በአሁኑ ወቅት ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ በጥቅም ላይ ከዋሉት 10 የኮሮና ክትባቶች በተጨማሪ 8 ያህል አዳዲስ ክትባቶች በቤተሙከራ ምርምር ሂደት ላይ እንደሚገኙና እስከ አመቱ መጨረሻ ወይም እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2022 መጀመሪያ አገልግሎት ላይ ይውላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውንም ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ከ6 እስከ 8 ከሚደርሱት በምርምር ላይ የሚገኙ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መካከል ከመርፌ ውጭ በአፍ ወይም በአፍንጫ የሚሰጡ እንዲሁም ማቀዝቀዣ የማያስፈልጋቸው እንደሚገኙበት የጠቆሙት ሳይንቲስቷ፣ የምርምር ሂደታቸውና ህጋዊ እውቅና የመስጠት ሂደታቸው እስከ አመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለው ገልጸዋል፡፡
በመላው አለም በድምሩ ከ80 በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምሮች እየተካሄዱና በሰዎች ላይ እየተሞከሩ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ የተወሰኑት ግን ገና በክትባት ሙከራ የጅማሬ ምዕራፍ ላይ የሚገኙና ውጤታማ ላይሆኑ የሚችሉ ናቸው መባሉንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ክትባት ዜና ደግሞ፣ ከአንድ አመት በኋላ ክትባት ለወሰዱ 20 የውጭ አገራት ጎብኝዎች በሯን ክፍት እንደምታደርግ ያስታወቀቺው ቻይና፤ ያም ሆኖ ግን ወደ ግዛቷ መግባት የሚችለው “ቻይና ሰራሽ” የኮሮና ክትባት የተከተበ ሰው ብቻ መሆኑን እንዳስታወቀች ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ቻይናን ለመጎብኘት የሚፈልጉ ሰዎች በቻይና ከተመረቱ የኮሮና ክትባቶች አንዱን መውሰዳቸውን የሚያረጋገጥ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው  የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ውሳኔው አገሪቱ የራሷን ክትባቶች በአለማቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በማሰብ የተላለፈ ነው መባሉን ገልጧል፡፡
 አሜሪካ፣ ህንድ፣ ኢራቅ፣ እስራኤልና ፊሊፒንስን ጨምሮ ለ20 አገራት ቱሪስቶች በሯን ክፍት ማድረጓን ቻይና  ያስታወቀች ሲሆን 5 የተለያዩ የኮሮና ክትባቶችን አምርታ በአገልግሎት ላይ ማዋሏ ተጠቁሟል። 34 የአለማችን አገራት ቢያንስ አንዱን የቻይና ክትባት ለዜጎቻቸው ለመስጠት መፍቀዳቸውም ተዘግቧል፡፡

     ኮሮናን በአደባባይ በማናናቅ የሚታወቁትና በቫይረሱ መጠቃታቸው በስፋት ሲነገርላቸው የሰነበተው የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ባለፈው ሃሙስ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፣ በምክትልነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሳሚያ ሃሰን በአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ስልጣኑን ሊረከቡ መዘጋጀታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ለሳምንታት ከአደባባይ ጠፍተው የሰነበቱትና በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በህንድ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበር የተነገረላቸው የ61 አመቱ ማጉፉሊ፤ ከትናንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳሚያ በይፋ አስታውቀው፣ የሞታቸው ሰበብ እንደተባለው ኮሮና ሳይሆን የልብ ህመም ነው ብለዋል፡፡ የ61 አመቷ ምክትላቸው ሳሚያ በመጪው ሳምንት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣኑን እንደሚረከቡና ለቀጣዮቹ 5 አመታት አገሪቱን እንደሚያስተዳድሩ ተመልክቷል፡፡
በ2015 በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙትና ባለፈው አመት በተደረገ አወዛጋቢ ምርጫ በድጋሚ አሸንፈው ለ2ኛ የስልጣን ዘመን አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የነበሩት ማጉፉሊ፤ በአጠቃላይ አገሪቱን ላለፉት 7 አመታት የመሩ ሲሆን  በጸረ ሙስና ዘመቻ የሚወደሱትን ያህል ተቃዋሚዎችን በማፈን ይታማሉ። ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ በተወለዱ በ68 አመታቸው ማረፋቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ ህገ መንግስት በተቀመጠው መሰረት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሳሚያ፣ 6ኛዋ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሆነው መንበሩን እንደሚረከቡ ተዘግቧል፡፡
ቀጣዩዋ የአገሪቱ መሪ የፕሬዚዳንቱን ሞት በቴሌቪዥን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የ14 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን መታወጁን ያስታወቁ ሲሆን፣ ጎረቤት ኬንያም የ6 ቀናት ሃዘን ማወጇን ዘገባው አክሎ ገልጧል። የማጉፉሊን ሞት ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ፤ ታንዛኒያ ቁርጠኛ የፓን አፍሪካኒስት መሪዋን አጥታለች ያሉ ሲሆን ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችም በግለሰቡ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን መግለጻቸውን ቀጥለዋል፡፡
ከዚያው ታንዛኒያ ሳንወጣ የምናገኘው ሌላ ዜና ደግሞ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመሰረቱት መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት የታንዛኒያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ በአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሃውልት ሊቆምላቸው እንደሆነ ያመለክታል፡፡

   አቫታር ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዟል

            የዘንድሮው ታላቁ የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ባለፈው እሁድ በተለያዩ አስገራሚ ክስተቶች ታጅቦ የተከናወነ ሲሆን፣ በነጋታው ደግሞ የታላቁ ኦስካር ሽልማት የዘንድሮ ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡
በአለማችን ታላቁ የሙዚቃ ሽልማት እንደሆነ የሚነገርለትና ባለፈው እሁድ ለ63ኛ ጊዜ በሎሳንጀለስ በተከናወነው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት፣ አሜሪካዊቷ ተወዳጅ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፣ ለ28ኛ ጊዜ ግራሚን የተሸለመች የመጀመሪያዋ ሴት ሙዚቀኛ በመሆን ታሪክ የሰራች ሲሆን፣ 79 ጊዜ ለግራሚ የታጨች ቀዳሚዋ ሴት ሆናም በግራሚ ታሪክ ተመዝግባለች፡፡
በዘመነ ኮሮና የቤት ውስጥ እገታዋ በሰራችው “ፎክሎር” የተሰኘ አልበም የተሸለመችው ሌላኛዋ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት በበኩሏ፤ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት የአመቱ ምርጥ አልበም ሽልማትን የወሰደች ሴት በመሆን ሌላ ታሪክ ሰርታለች።
ሰኞ ዕለት ይፋ ወደተደረገው የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ስንዞር ደግሞ፣ በ10 ዘርፎች ለሽልማት የታጨው “ማንክ” የተሰኘው የዴቪድ ፊንቸር ፊልም፣ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዞ እናገኘዋለን፡፡
በ83 ዘርፎች የሽልማት ዕጩዎች ይፋ በተደረጉበት የ2021 ኦስካር ሽልማት፣ ጁዳስ ኤንድ ዘ ብላክ ሚሳህ፣ ሚናሪ፣ ዘ ፋዘር፣ ኖማድላንድ፣ ትሪያል ኦፍ ዘ ቺካጎ 7 እና ሳውንድ ኦፍ ሜታል በተመሳሳይ በ6 ዘርፎች በመታጨት ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል። በኦስካር ታሪክ 70 የፊልሙ ኢንዱስትሪ ሴቶች 76 ጊዜ በመታጨት ታሪክ የሰሩበት የዘንድሮው ኦስካር አሸናፊዎች፣ በመጪው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ሎሳንጀለስ በሚገኘው ዶልቢ ቲያትር በሚካሄደው ደማቅ ስነስርዓት ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በሌላ የመዝናኛው መስክ ዜና ደግሞ፣ በታዋቂው ዳይሬክተር ጄምስ ካሜሩን የተሰራውና እ.ኤ.አ በ2009 ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የበቃው “አቫታር” ፊልም ባለፈው ሳምንት በቻይና በድጋሚ ለእይታ በቅቶ በአለማቀፍ ደረጃ ያገኘውን ገቢ ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጉን ተከትሎ፣ በአለማችን ታሪክ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘ ቁጥር አንድ ፊልም ለመሆን መብቃቱ ተነግሯል፡፡ ለእይታ ከበቃበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2019 በነበሩት 10 ተከታታይ አመታት በገቢ ቀዳሚው የአለማችን ፊልም ሆኖ የቆየው “አቫታር”፤ በዚያው አመት በአቬንጀርስ ኢንድጌም ክብሩን ተነጥቆ እንደነበርም ያሁ ኒውስ አስታውሷል፡፡

     ኦስሎ በውሃ ዋጋ ውድነት ቀዳሚዋ ከተማ ሆናለች

            በመላው አለም የሚገኙ ከ1.42 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛና እጅግ ከፍተኛ የንጹህ ውሃ እጥረት ተጠቂዎች እንደሆኑና 20 በመቶ የአለማችን ህጻናት በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ውሃ እንደማያገኙ ተመድ አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በመላው አለም በሚገኙ ከ80 በላይ አገራት ህጻናት የከፍተኛ ወይም እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተጋላጭ ሲሆኑ፣ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት ከሚገኙ ህጻናት መካከል ከ58 በመቶ በላይ የሚሆኑት በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን ውሃ ለማግኘት እጅግ አዳጋች የሆነባቸው ናቸው፡፡
በሌላ ውሃ ነክ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም ከሚገኙ ከተሞች መካከል የውሃ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ የሆነባት ቀዳሚዋ ከተማ ኦስሎ መሆኗንና፣ በከተማዋ አንድ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ በአማካይ 1.85 ዶላር እንደሚሸጥ ተነግሯል፡፡
ሆሊዱ የተባለው ኩባንያ በ150 የአለማችን ከተሞች የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ ቨርጂኒያ ቢች በ1.59 ዶላር፣ ሎሳንጀለስ በ1.54 ዶላር፣ ኒው ኦርሊያንስ በ1.48 ዶላር፣ እንዲሁም ስቶክሆልም በ1.47 ዶላር በመሸጥ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ውሃን እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በመሸጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቺው ደግሞ አንድ ጠርሙስ የታሸገ ውሃ በ0.04 ዶላር የሚሸጥባት ቤሩት ስትሆን፣ የህንዷ ባንጋሎር በ0.13 ዶላር፣ የጋናዋ አክራ በ0.16 ዶላር፣ የናይጀሪያዋ ሌጎስ በ0.17 ዶላር፣ የቱርኳ ኢስታምቡል በ0.18 ዶላር በመሸጥ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡


 የአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ላለፉት 9 ተከታታይ አመታት በአንደኛነት የዘለቀው የአሜሪካው ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (ኤምአይቲ) ዘንድሮም ክብሩን ማስጠበቁ ተነግሯል፡፡
የትምህርት አሰጣጥ ጥራት፣ የምርምርና ልቀት ማዕከልነት አቅምን ጨምሮ በ6 መስፈርቶች ተጠቅሞ የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች በመገምገም የተሰራው የአመቱ ሪፖርት፣ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲን ሲሆን፣ ሃርቫርድ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ የብሪታኒያው ኦክስፎርድ፣ የስዊዘርላንዱ ስዊዝ ፌዴራል ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቶክኖሎጂ፣ የብሪታኒያው ካምብሪጅ፣ የብሪታኒያው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን፣ የአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ እና የብሪታኒያው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን በዘንድሮው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በአለም ዙሪያ በሚገኙ 5 ሺህ 500 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጥናት በማድረግ የአመቱን 1 ሺህ 29 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ይፋ ያደረገው ኪውኤስ የተባለው ተቋም፤ ከአፍሪካ ካካተታቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል 220ኛ ደረጃን የያዘው የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን፣ 403ኛ ደረጃን የያዘው ሌላኛው የአገሪቱ ተቋም ዩኒቨርሲቲ አፍ ዊትዋተርስራንድ እና 411ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የግብጹ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካይሮ ይገኙበታል።

       ከእለታት አንድ ቀን በርካታ ጅቦች  የተራቡና  የሚበላ ነገር ለማግኘት ዞር ዞር ሲሉ፣  አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን ገደል ወድቆ ገብቶ አገኙ።
እርቧቸዋልና አንደኛው፡- “እጅግ እድለኞች ነን። ልክ በሰዓቱ የተገኘ መና ነው። ከሰማይ የተላከልን ጸጋ ነው።”
ሁለተኛውን፡- “ዘለን እንግባና ዝሆኑን እንቀራመተው” አለ።
ሶስተኛው፡- መግባቱንስ  ገባን መብላቱንስ በላን፤ ከጠገብንና ሆዳችን ከሞላ በኋላ እንዴት አድርገን ነው ከዚህ አዘቅት ወደ አቀበቱ የምንወጣው። ተው አያዋጣንም” አለ።
አራተኛው፡- “ወደ ገደሉ እንግባና በኋላ እናስብበታለን” አለ።
ለተወሰነ ሰአት ከተወያዩበት በኋላ “ገብተን እናስብበታለን” በሚለው ሃሳብ ላይ ሁሉም ተስማሙ። ስለዚህ ተንደርድረው ወደ ገደሉ ገቡ።  ዝሆኑን እየተሻሙ ተቀራመቱት። ጥጋብ መጣ። ሆኖም ለመውጣት እንደተፈራው መላው መላው ጠፋው። ደሞ የመውጫ ዘዴ መመካከር ቀጠሉ። በመጨረሻም አንዱ አንዱን እሽኮኮ በማለት እየተደጋገፉ ለመውጣት ተስማሙ። እየተገፋፉ አብዛኞቹ ጫፍ ደረሱ።
የመጨረሻውን ጅብ ግን ማን ያውጣው፤ ሌላ ጅብ አልነበረም። አንደፈረደበት እዚያው በረሃብ ሞተ!
*   *   *
ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ የሚለው ተረት የዋዛ አይደለም። የሞተ ዝሆን ላይ መረባረብ ሃያልነትን አያሳይም። ቢያንስ ቢያንስ የወደቀ ዛፍ፤ ምሳር ይበዛበታል የሚለውን ከማመላከት  በስተቀር።
“አስረው ደበደቡት ያን የዝሆን ጥጃ
ዛሬም ደስ አላቸው የነገውን እንጃ”
(እንደ አጋዥ ስንኙን እንጨምር)
“ገዴ ዞራ ዞራ በእንቁላሏ ላይ
ጊዜ የሚጠብቅ ሰው ጅብ ሊባል ነው ወይ”
…የሚለውንም አለመዘንጋት ነው።
በረዥሙ የሀገራችን ጉዞ ውስጥ ከሎሬት ጸጋዬ ቴዎድሮስ ጋር፡-
“ያለፈ ተረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”… ማለትም ያባት ነው።
መንገድን አጥርቶ ማየት፣ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ከመሆን ይገላግለናል። እንዲህ ያለውን ነገር ለመተግበር ታታሪነትንና አስተውሎነትን ይጠይቃል። ይህን አስተውሎት እውን ለማድረግ ደግሞ መማር፣ ማንበብ፣ መወያየት፣ የተወያየነውን ማውጠንጠን፣ ያውጠነጠነውንም አለመርሳት መሰረታዊ ነገር ነው።  ይህ አይነት የማሰብ ባህል ካልዳበረ ትውልድ አሁን እያዘቀዘቀና እየወረደ ባለበት ቁልቁለት መገስገሱን ይቀጥላል። ትውልዱ በዚሁ ከቀጠለም የሀገርን ውድቀት ከማፋጠን ሌላ የሚፈይደው አንዳች ተስፋ እድል አይኖርም። ጉዞው የእውር የድንብር ነውና። የለዋጭ ተለዋጭ፣ የተማሪ አስተማሪ እምንፈጥረውና የምናፈራው  ነባራዊውንና ህሊናዊውን ሁኔታ እያሟላን ስንታትር ነው።
ይሄ ማሟላት ደግሞ ህብረተ ሱታፌን ይጠይቃል። እውነታን እውን ማድረግ ይጠይቃል።
እንቅፋቶችን ልብ ማለት ለአንድ መንግስት ግዴታም ጥበባዊ ክህሎትም ነው።
እነዚህን ክህሌቱ ተክህኖዎች ካቀናጀን፣ አንድ እርምጃ በእድገት አውራ መንገድ ላይ መጓዝ ነው። ያም ሆኖ  እንቅፋት ተፈርቶ እርምጃን ማቋረጥ፣ የዋህነት ነው! ውሾቹ ቢጮሁም ግመሎቹሆነን መንገድ መቀጠል አለብን።Page 5 of 523