Administrator

Administrator

 ኢትዮ ቴሌኮም፤ የፋይናንስ ተቋማት፣ አገልግሎቶቻቸውን በቴሌ ብር ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችላቸው  የዲጂታል የፋይናንስ ገበያና የዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ   አገልግሎቶችን  ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡
    ኩባንያው፤ ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ኢንሹራንስና ሌሎችም በዘርፉ ያሉ ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅምን ተጠቅመው፣ የፋይናንስ አገልግሎታቸውን ተደራሽና አካታች ለማድረግ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችላቸውን የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ (Digital Financial Marketplace) ሶሉሽን ማቅረቡን አመልክቷል፡፡  በተጨማሪም፣ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በርካታ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ያሏቸው እንደመሆኑ የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ ሂደታቸውን ዲጂታል በማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩበት የዲጂታል አክሲዮን ገበያ (Digital Share Sell/Buy) ሶሉሽኖችንም ማስተዋወቁን ጠቁሟል፡፡  
ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ፤ “የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ገበያ፤ የፋይናንስ ተቋማት የማይክሮ ፋይናንስ፡-የብድር፣ ቁጠባና ኢንሹራንስ አገልግሎቶቻቸውን ለደንበኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ፕላትፎርም  በዲጂታል አማራጭ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሶሉሽን ሲሆን፤ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የእጅ ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ አገልግሎቱ የደንበኞችን የብድር እንቅስቃሴና በወቅቱ የመመለስ ልምድን በማገናዘብና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን  በመጠቀም በሚሰራ የብድር ቀመር  መሰረት የሚከናወን በመሆኑ ያለምንም የንብረት መያዣ  የብድር አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል።  ከዚህ ቀደም ከዳሽን ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በቀረጸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ከ3.6 ሚሊዮን ደንበኞች በላይ በብድር አገልግሎት ተደራሽ ማድረጉን ያስታወሰው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዛሬው ዕለት የቀረበው የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ሶሉሽን፣ ባንኮች ምንም አይነት የካፒታል ኢንቨስትመንት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በገነባው ፕላትፎርም ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎቶቻቸውን ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የቴሌብር ደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበት አገልግሎት መሆኑን አመልክቷል፡፡ ”የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ አገልግሎት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ ባንኮች ይህንኑ እንዲያውቁ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ፕላትፎርሙን ለመጠቀም ከአሀዱ ባንክ፣ ከሲንቄ ባንክ፣ ከእናት ባንክና አዋሽ ባንክ ጋር ውይይት ተጠናቆ ከብሔራዊ ባንክ በሚያገኙት ይሁንታ መሰረት አገልግሎቱን በቅርቡ የሚጀምር ይሆናል፡፡” ብሏል፤ኩባንያው፡፡


  አመታዊ ምርቱን 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ለማድረስ አቅዷል


          ቢጂአይ- ኢትዮጵያ በአሰራሩ፣ በማምረት ሂደቱና በስርጭት ሞዴሉ ላይ ወሳኝ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ኢንቨስትመንቱ የኩባንያው ፋብሪካዎች የማምረት አቅም መጨመርና ታሪካዊውን  የአዲስ አበባ ፋብሪካ ሰበታና ማይጨው ወደሚገኙት ሁለቱ የቢራ ፋብሪካዎቹ ማዛወርን እንደሚያካትት   ጠቁሟል።የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚ/ር ሄርቬ ሚልሃድ ባለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህ ኢንቨስትመንት ኩባንያችንን የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቹን ለውድ ደንበኞቹ ለማቅረብ ከምንሰራቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ ነው” ብለዋል። የቢጂአይ- ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ለውጥ መተግበር ያስፈለገው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የገበያ ለውጥ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚታየው አጠቃላይ ተወዳዳሪነት ጋር እርምጃውን ለማስተካከል፣ እንዲሁም የኩባንያውን እድገት ለማፋጠንና ጠቅላላ አመለካከቱን ለማሻሻል ነው ተብሏል።
“በኢትዮጵያና በገበያዋ ከፍተኛ አቅም እንዳለ እናምናን” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ “ኢትዮጵያ እያደረገችና እየተለወጠች ስትሄድ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አሰራር ለመዘርጋት ተዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል” ብለዋል።“ራዕያችን በሚቀጥሉት ዓመታት የማምረት አቅማችንን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት ወደ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ ለማድረስ ነው” ሲሉ ሚልሃድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ይህን ትልቅ አላማ ለማሳካት በሰራተኞቻችን፣ በምርቶቻችን፣ በደንበኞቻችንና በምንኖርበት ማህበረሰብ ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን” ያሉት ሥራ አስፈጻሚው “በመካሄድ ላይ ካሉት ዋና ዋና ተግበራት አንዱ በማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት በማድረግ የድርጅታንን የማምረት አቅሙን ማሳደግ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“በውሃ አቅርቦት ውስንነትና የሎጅስቲክስ ተግዳሮቶች ምክንያት በአዲስ አበባ መሀል ከተማ የሚገኘውን ታዋቂውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካችንን ለማዛወር የተገደድን ቢሆንም፣ ይኸው ችግር ራሱ የሌሎች ፋብሪካዎቻንን የማምረት አቅም ለማሳደግ እድ ፈጥሮልናል” ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ። ቢጂአይ- ኢትዮጵያ ድርጅታዊ መዋቅሩን በማደስ ተመራጭ አሰሪ ድርጅት ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስፈፃሚ ገልጸዋል።
ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎች ለ3,500 ቋሚ ሰራተኞችና 2,000 ጊዜያዊ ሰራኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ የለውጡ ግብም በእያንዳንዱ የሥራ ክፍል ውስጥ ያሉትን አስፈላጊ ክህሎቶችና ሂደቶችን በመለየት፣ የተግባር ልህቀትን በመላ ኩባንያው ማምጣት ነው ተብሏል።
ቢጂአይ- ኢትዮጵያ አገሪቱ ከሚገኙ የግል ድርጅቶች ትልቁ ግብር ከፋይ እንደሆነና በዓመት ከ7.4 ቢሊዮን ብር በላይ ታክስ ለመንግስት እንደሚከፍል ለማወቅ ተችሏል።


ማክሰኞ ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም  በጀርመን፣ ጎተ የባህል ማዕከል በተከናወነ  እጅግ አስደሳችና አስገራሚ በሆነ ዝግጅት ተጠናቋል። ፊልሞቹን ካዩ በኋላ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት ብዛት ያላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል የስምንት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ በሀገራችንም ሆነ በአለማችን  ችግር ፈጣሪ  የሆኑ ፕላስቲኮችን ጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ የሰሯቸውን አስገራሚ ስራዎችና ስለ አፈር መሸርሸርና አካባቢ ጥበቃ ለአንድ ወር ያህል ያደረጉትን ምርምር ውጤቶች ይዘው ቀርበዋል።
በዚህ አስገራሚ የመዝጊያ ፕሮግራም ላይ፣ የመሀል ግንፍሌ፣ እየሩሳሌም፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ፣ ፎፋን/ሰላም፣ ጃካራንዳ፣ ጀርመን ቸርች ፣ ብሔረ ኢትዮጵያ እና ዋን ላቭ  አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሳተፉ፤ ሲሆን ከወዳደቁ ፕላሲኮች፣ ከቤት ማጌጫ እቃዎች ጀምሮ፣ የቤት ውስጥ ችግር መፍቻ ማሽኖች፣ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ የሚያስችሉ የኮንስትራክሽን አጋዥ እቃዎችን አክሎ፣ በራሪ ሂሊኮፕተር የመስራት ጥረቶች ታይተውባቸዋል።  ተማሪዎቹ ያቀረቧቸው ስራዎች ብዙዎቹ በአለም አቀፉ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተመርጠው ከመጡት ስራዎች እጅግ የተሻሉና ፍፁም የአዕምሮ ፈጠራ ውጤቶች ነበሩ። እነዚህን ስራዎች ተማሪዎቹ እንዲሰሩ ከፍተኛ እገዛ ላደረጉ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ከፍ ያለ ልባዊ አድናቆታችንን እናቀርባለን።
የስምንቱም ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያቀረቧቸው ስራዎችና ስለስራዎቻቸው ያቀረቡባቸው መንገዶች፣ ለሳይንስ ያላቸው ፍቅርና ለፈጠራ ያላቸው ጉጉት እጅግ አስገራሚ ነበር። በአብዛኛው ስራዎቻቸው የአካባቢያቸውን ችግር ለመፍታት ያላቸውን ልባዊ ፍላጎት በተግባር አሳይተውበታል። የህብረተሰቡን ችግሮች፣ ድክመቶች፣ ፍላጎቶች በዚህ እድሜያቸው ያስተዋሉና የተረዱ እንዲሁም ያንንም ለመቅረፍ አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩ ነበሩ። በእርግጠኝነት ትንሽ ድጋፍ ካገኘ ሀገሩን ከፍ የሚያደርግ የተሻለ ትውልድ እየመጣ እንደሆነ የታየበት ፕሮግራም ነበር።
የአለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሉን የጀርመን የባህል ማዕከል፣ ጎተ ኢንስቲቲዩት ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር በየአመቱ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ዝግጅቱን ለኢትዮጵያ ህፃናት ለማዳረስ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን መስፈርት የማይገኝለት ከፍተኛ ትብብር አድርጓል።
የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በደቡብ እስያ ፣ በአፍሪካ ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በላቲን አሜሪካ የሚካሄድ የሳይንስ ግንዛቤ ልምድ ልውውጥ በዓል ነው። የሳይንስ እውቀትን ያስተዋውቃል እና የወቅቱን ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂና የአካባቢ ጉዳዮች ግንዛቤን ለመፍጠር መንገዶችን ያመቻቻል። የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ሳይንሳዊ ጉዳዮችን ተደራሽና አዝናኝ በሆነ መልኩ ለብዙ ታዳሚዎች ያቀርባል፤ እናም ሳይንስ አስደሳችና አዝናኝ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።  ዝግጅቱ በ2005 ተጀምሮ ዛሬ በአለም ትልቁ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ለመሆን በቅቷል። በ2023፣ 2015፣ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በአለም አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 20 እስከ ህዳር 20 የተካሄደ ሲሆን፤ ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ይህ ለሶስተኛ ጊዜው ነው። የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት በሥነ ምህዳር መልሶ ማቋቋም ላይ የተባበሩት መንግስታትን የአስር ዓመት ዘመቻን የሚደግፍና በአጋርነት መቆሙን ያሳየበት ነው።  የዘንድሮ የሳይንስ ፌስቲቫል ጭብጡ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ሥነ ምህዳሮችን ከአደጋ ለመጠበቅና  እንደገና ለማደስ የተደረገ ጥሪ ነው። የፌስቲቫሉም ዋና መልዕክቶች
ዳግም ማሰላሰል
እንደገና መጀመር
እንደነበረ መመለስ
የሚሉ ነበሩ።
የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት ከ 102 አገራት ከ1700 በላይ ፊልሞችን ተቀብሎ ከ35 አገራት የተላኩ 150 ፊልሞች  መርጧል።
 ከእነዚህ ውስጥ ለሀገራችን በተለይ ለወጣቶችና ህፃናት ተስማሚ የሆኑ 26 ፊልሞች ላለፉት ሁለት ወራት ሲታዩ ቆይተዋል። የአለም የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ከእነዚህ ከተመረጡት ፊልሞች ውስጥ አሸናፊ ለሚሆኑ ስድስት ፊልሞች ሽልማቶችንም ይሰጣል። በዘንድሮው የሳይንስ ፊልም መዝጊያ ላይ እንደታዘብነው፣ ልጆቻችን ያቀረቧቸው ስራዎች ምናልባት በሚቻለው መንገድ ታግዘው ለፊልም ፌስቲቫሉ ተልከው ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ቢያንስ ከስድስቱ ሽልማቶች አንዱን የማሸነፍ ብቃት እንደነበራቸው ነው።
በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይም የጀርመን የባህል ማዕከል የፕሮግራሞች ኃላፊ አቶ አማኑኤል ፈለቀ፤ በሚቀጥሉት የአለም አቀፍ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የኢትዮጵያ የሳይንስ ፊልሞች እንደሚካተቱ ተስፋ እንዳላቸው ገልፀው፤ በተለይ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ ስራቸውን ያቀረቡ ትምህርት ቤቶች እጅግ እንዳስገረሟቸውና ትምህርት ቤቶቹ ለቀጣዩ አመት እንደ ዘንድሮው ድንቅ ስራ ለማቅረብ ቢጥሩ፣ጎተ ኢንስቲቲዩት ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።


 የሥልጡኑ ሰው ሥነ-ልቦና የተዋቀረውና የተቃኘው በምክንያታዊ አራዳ አስተሳሰቡ [Mindset] ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ ሥነ-ልቦናው አንድም ምክንያታዊ [realistic] ሆኖ በማሰብ የተዋቀረ አንድም አራዳ በሆነ ጠባይ - አመለካከት [attitude] የተቃኘ ነው፤ ይቃኛልም ማለት ነው፡፡ ለእርሱ አራዳነት የነቃነት ነው፤ ብልጥነት፣ ብልህነት ነው፤ ምክንያታዊነት ደግሞ እውነታ [fact] ላይ መመስረትና ተገቢ የሆነውን ተግባሪ ሰው [practical] መሆን ነው፡፡
ምክንያታዊ አራዳነቱ
1ኛ. እውነታ ላይ የባነነ - የነቃ ያደርገዋል፡፡ እውን፣ እውነት፣ ተጨባጭ ሁኔታ የሆነውን ለመገንዘብ፣ ለማገናዘብና ለመረዳት በመጣር እውነታው ላይ ይደርሳል፡፡ ያ እውነታ የአጠቃላዩ የሰው ልጅና የህይወት የሆነ፣ ግለሰባዊና ማህበራዊ ተጨባጭ እውነታ፣ ታሪካዊ እውነታ፤ ተፈጥሯዊ - ሳይንሳዊ እውነታ እይታና እምነት መሆናቸውን በተጨባጭ መከሰት አለመከሰታቸውን፣ የእውነተኛ ተፈጥሯቸውን ምንነትን በማስተዋልና በመረዳት በእውነታ የነቃ ይሆናል፡፡
2ኛ. እውነታን አያያዝ ማስተናገድ ላይ ብልጥ ብልህ ያደርገዋል፡፡ እንዴት እውነታን መጋፈጥ፣ መቀበልና ምላሽ መስጠት እንዳለበት ያውቅበታል፡፡ ለእሱ ገሃዱን እውነታ መካድ አይታሰበውም፡፡
የሚያመልጥ መስሎት ስራውን ስሙን አካባቢውን በመቀየር እውነታን ለማምለጥ አይቃጣውም። ዐይኑን በመጨፈኑ ችግሮች ይጠፉ ይመስል እውነታን ላለማየት በመሞከር ራሱን ጉዳት ላይ አይጥልም። አንገቷን ብቻ አሸዋ ውስጥ እንደ ደበቀችው ሰጎን ከእውነታው ለመደበቅ የሞኝ ነገር አያደርግም በአልኮል መጠጥና በአደንዛዥ እፅ እውነታውን ለመርሳት ብሎ ራሱን የባሰ ችግር ውስጥ አይከትም። ከልብ ባልሆነ ሳቅ ፈገግታና የደስተኝነት አኳኋን እውነታውን ለመሸፈን ብሎ ራሱን አያታልልም፤ አይሸነግልም፡፡ ፊት ለፊት ባለመናገር ከእውነታው አይሸሽም። ነገሩን ቢገልጥ ቢናገር የሚፈጠረውን በመሥጋት እውነታን አያፍንም፡፡ ፊት ለፊት በዙሪያው ያለን እውነታን ይፈቅዳል፤ በዛ እውነታን ይገዛል ወይም እውነታን ለራሱ ያስገዛል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው እውነታ በሌለው ነገር በመገዛት ወይም እውነታ ለሆነ ነገር ባለመገዛት ልክ ያልሆነ አእምሯዊ ስሜት ውስጥ ተዘፍቆ መቸገር አይፈቅድም፡፡
ሥልጡኑ ሰው አሉታዊ ነገሮች ሲያጋሙት ነገሮች በጠበቀው መንገድ ባልሄዱ ጊዜ፣ ያሰበው የተመኘው ባልተሳካ ቁጥር አንድ ነገር ምቾት በነሳው ጊዜ ሁሉ፣ ሰዎች በተናገሩት ባደረጉበት ልክ ያልሆነ ነገር ሁሉ ነገሮች በጠመሙ ጊዜ ሁሉ አራት ሥነ-ልቦናዊ መርሆች ምላሾች [responses] አሉት፡፡
1ኛ. በጣም ብዙውን ጊዜ ቀለል - ተወት የሚደርግ [easygoing]
ሥልጡኑ ሰው በችግር በፈተና በቀላሉ የማይፈታ ሰው ነው፡፡ እለት ተእለት ችግሮች መፈታተኖች ከሌሎች ሰዎች ከነገሮች፣ ከሁኔታዎች ቢገጥሙትም፣ እንደው እንደዘበት አይረበሽም፤ እጅ አይሰጥም፤ ነገሩን ቀለል አድርጎ ያየዋል፤ ይቀበለዋል፤ ያሳልፈዋል፡፡ ያለምሬት መታገስ መቻል ይቻለዋል፡፡ በቀላሉ ቅር ያለመሰኘት - ያለመቀየም፤ በቀላሉ ያለመከፋ በቀላሉ ያለመናደድና በቀላሉ ያለመጨነቅ ብልጠት አለው፡፡
2.ኛ አንዳንዴ የማይበርደው የማይሞቀው [emotionally non - reactive]
በህይወት ውስጥ ለአንዳንድ ነገሮች ደንታ የለውም፡፡ አንዳንድ የማይሞቁት የማይበርዱት ነገሮች አሉ፡፡ በውስጡ እንደ መሞቅ እንደ መብረድ ቢለው እንኳ ለውጪው አካል የሚሰጠው የስሜት ምላሽ፣ የሚያሳየው ስሜት የለውም፡፡ ቀለል አድርጎ በውስጡ ያሳልፈዋል፡፡ ያየውን እንዳላየና የሰማውን እንዳልሰማ የሚሆንበት ጊዜ የተፈጠረውን ምንም እንዳልተፈጠረ የሚቆጥርበት ጊዜ አለ፡፡ የግሉ ችግር ባልሆነ በማይመለከተው ነገር ሲቸገር አይገኝም፡፡ ዝም ብሎ ከመገንዘብ ውጪ ስንቱን አያውልም አያወጣዳጅም፡፡ የሚረብሽ ምቾት የሚነሳና የሚፈታተን ነገር ሲገጥመው እንኳ ምላሹ የሚሆነው ምላሽ አለመስጠት ነው፡፡ ምላሽ ሳይሰጥ ዝም ብሎ ያያል ወይም ያልፋል፤ አልያም የትኩረት ርእስ ይቀይራል፡፡ በአንዳንድ አሉታዊ ነገሮች ገጠመኞች ጨርሶውኑ ቅር ያለመሰኘት - ያለመቀየር፤ ጨርሶውኑ ያለመከፋት ጨርሶውኑ ያመናደድና ጨርሶውኑ ያለመጨነቅ ጠባይ አዳብሯል፡፡
3ኛ. ከስንት አንዴ ምክንያታዊ [realistic] አሉታዊ ስሜቶችን ማስተናገድ
ሥልጠኑ ሰው መቼስ ሰው ነውና ቅር የመሰኘት - የመቀየም የመከፋት የመናደድና የመጨነቅ የመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶች በምክንያት የሚፈጠሩ ድንገት ቢሰማው እንኳ በምክንያቱ የሚቆጣጠራቸው መሆናቸው ነው፡፡ ከመሬት ተነስቶ እንደው ያለ ግልፅ ምክንያት ሳይታወቀው በአሉታዊ ስሜቶች ተደጋግሞ የሚጠቃ ሥነ-ልቦና አይደለም ያለው፡፡ ከስንት አንዴ እንዲህ ያሉ አሉታዊ ስሜቶች ሲሰሙት ድብቅ - ጥልቅ ምክንያተ  ይኖራቸው ይሆን ወይም ምክንያት የለሽ ይሆኑ ይሆን ለመፈተሽ ጥቂት ጊዜ ወስዶ ያሰላስልባቸዋል፡፡ አሉታዊ ስሜቶች ምክንያት ያላቸው ከሆኑ እውቅና ለመስጠትና በየልካቸው ለማስተናገድ ይፈቅዳል፡፡ በምክንያት የሚያሳስቡት የሚያሰጉት የሚያስጨንቁት ጥቂት ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ አሉታዊ ስሜት መሰማት ሰው ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ተገቢ ቅር መሰኘቶች-መቀየም መከፋቶች መናደዶችና መጨነቆች እንዳሉ ያምናል፡፡
4ኛ. ብዙውን ጊዜ እንደ ቀልድ፣ እንደ አስቂኝ እንደ መሳቂያ ቂልነት መውሰድ
ለእርሱ የህይወት አብዛኛው ነገር አስቂኝ ቀልድ፣ መሳቂያ ቂልነት ሆኖ ይታየዋል፡፡ “መሳቂያ” “ቀልድ”፣ “ያስቃል” የሚላቸው አማርኛዎች አሉት፡፡ ከውልደት እስከ ሞት ባሉ ነገሮች በሚከሰቱ ነገሮች ውስጥ በብዛት የሚታየው አስቂኝ ነገር፣ መሳቂያ ቂልነት መራርና ጨካኝ ቀልድ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቀልድ ተፈጥሮ ስትቀልድ፣ ህይወት ስትቀልድ ማህበረሰብ ሲቀልድ መሪዎች ሲቀልዱ ይታዘባል፡፡ በሚያስቀው ነገር በጣም ይስቃል፡፡ በብዙ መፈታተኖች ችግር - ችጋሮች ላይ ፈገግ ይላል፡፡ ጉዳዩ በአንድ በኩል ጥብቅ፣ በሌላ በኩል የሚያስቅ ሲሆንበት ‘ወደው አይስቁ’ የሚለው ነገር አለው፡፡  በሰዎች በነገሮችና በሁኔታዎች ተገርሞ ፈገግ ብሎ የሚያልፍበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ አንዳንዴም በራሱ የቂል ሃሳብ ድርጊትና በመጃጃሎቹ ላይ ይስቃል፤ ያላግጣል፤ ፈገግ ይላል፡፡
የሥልጡኑ ሰው ሥነ-ልቦና የሚወሰነው እውነታ ላይ ባለው መንቃትና ብልህነት ነው። በመሆኑም አሉታዊ ፍላጎትና ስሜቶች ውስጥ ሲገባ፣ የእርሱ ዋናው ጉዳይ እውነታው ነው፡፡ አዕምሮ ውስጥ ጎላ ብሎ የሚታየውና የሚሰማው  ‘እውነታ’ ነው፡፡ ጨርሶውኑ ወይም በቀላሉ ቅር የማይሰኘው  - የማይቀየመው፣ የማይከፋው፣ የማይናደደውና የማይጨነቅ ከነገሩ እውነታ አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ- ልቦናዊ ምሾቹ እውነታን መረዳት እውነታን መቀበል ፣ እውነታን በልኩ ማየት፣ እውነታን በተለየ ማየት፣ እውነታን በገለልተኝነት ማየትና እውነታን መቀየር ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
1 እውነታን መረዳት
ሥልጡኑ ሰው መጀመሪያ ያደረገው ነገሮች በተጨባጭ መኖር አለመኖራቸውን ለመገንዘብ መሞከር ነው፡፡ በእርግጥ ህላዌ ያላቸው ናቸው ወይስ ምናልባት ቅዠቶች ይሆኑ የሚለውን ለማወቅ ጥሯል፡፡ የሰው ልጅ የአእምሮ ፈጠራ የምናቡ ውጤት፣ የገዛ ተረታተረቱ የሆኑ በተጨባጭ ኗሪነት የሌላቸው ነገሮችን ለይቶ አውቋል፡፡ በነዚህ ጨርሶውኑ በሌሉ፣ ቅዥቶች በሆኑ ነገሮች ራሱን አያስቸግርም፤ የሃሳብ የስጋት ሰበቡ እንዳይሆኑ ማድረግ ችሏል፡፡ በሌሉ ነገሮች መጃጃል ሆነ መጨነቅ አምሳያ የሌለው ቂልነት መሆኑን ተገንዝቧል፡፡
የነገሮችን እውነተኛ ተፈጥሮን ለመረዳት የራሱን ፍተሻ ያደርጋል፡፡ ሳይንሳዊ ሃቆችን ይጠቀማል፡፡ የነገሮች እውነተኛ መለያ ጠባያቸውን ውስጣዊ ይዘታቸውን ሥሪታቸውንና ምንነታቸውን ለማወቅ ይሻል፡፡ በተለምዶ ከሚታወቁበት ባሻገር ትክክለኛ ተፈጥሯቸውን ለመገንዘብ ለመረዳት ይጥራል፤ መስለው የሚታዩትን በተለምዶ የሚገለፁበትን ሳይሆን በትክክል የሆኑትን እውነተኛ ተፈጥሯቸውን ለመገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ለአብነት የዚህን ዓለም ገሃድነትን፤ እውንነት የሃሳቦቻችን ውጤት ብሎት ቅዠቶቻችን መሆን አለመሆኑ ላይ ለመድረስ አሰላስሏል፡፡
 በዙሪያችን ያለው ዓለም የምንኖርበት ዓለም እውን መሆኑን፤ ተጨባጭ እውነታ መሆኑን ከመገንዘቡና ከመረዳቱ በተጨማሪ፣ የውጪው ዓለም የሚታየው፤ ጠባዩ በእርሱ ሃሳብ በአእምሮው የሚወሰን ሳይሆን በመሰረቱ የራሱ የሆነ ነባር ጠባይ እንዳው አምኗል።  ስለ ሰው ልጅ እውነተኛ ማንነትና ምንነት ለመገንዘብ ጥሯል። የሰው ልጅ መሰረታዊ ምንነቱ ህይወት ያለው ነገር መሆኑን ሲቀጥል፣ ከእንስሳቱ እንደ አንዱ እንደሆነ ብሎም የራሱ ‘ሰው’ ወይም ‘ሰውነት’ የሚባል ምንነት - ማንነት እንዳለው ተረድቷል፡፡ ስለ ሞትም ሲያስብ፣ ሞት የሰው ልጅ የሰውነት/ የአካል ስነ-ህይወታዊ አሰራር መቼውኑም እንዳለው ዓይነት የራሱ መልክ እንዳለው ነገር እንደ የሆነ ጨለማና አስፈሪ መንፈስ ይሰማው የነበረው አስጨናቂ የሞት ሃሳብ፣ አሁን ላይ በእሱ ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጥረው አንዳች ስሜት የለም፡፡
ህይወት በመሰረቱ መልካም እንደሆነችው ሁሉ፣ የራሷ መራር እውነትም እንዳላት ተገንዝቧል፤ አስቸጋሪነትም ፈታኝነትም እንዳለባት ኖሯት እያየው ነው፡፡ በህይወቱ ውስጥ ሀዘንም ደስታም ተፈራርቆበታል፤ ተመችቶት ተጎሳቁሎም ያውቃል እናም ህይወት ትራጄዲው ኮሜዲውና ትራጄዲ ኮሜዲው የሚከወንባት መድረክ መሆኗን አስተውሏል፡፡
(ከቴዎድሮስ ሎገስ ከተሰኘው መጽሐፍ የተቀነጨበ) “ሥልጡን ሰው እና የህይወት ፍልስፍናው”


Saturday, 23 December 2023 10:58

መሀል ላይ መቁለጭለጭ


          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታ አይደል፣ ግራ ግብት ያለን ነገር አለ። ‘ስልጣኔ’ ማለት… አንዳንዴ ትርጉሙ ግራ አይገባችሁም! አለመሰልጠናችንን የሚነካን በዛብና። አለ አይደል… የእኛ የእኛ የሆነውን ሁሉ የ‘ፋራነት’ … የነሱ የሆነው ሁሉ የ”ስልጣኔ” እየሆነ ተቸግረናል።
ስሙኝማ… አንዳንዶቻችሁ “በአውሮፕላን የምትመጡም…” ሰዎች! ሰላም ስጡና… ‘ዋትስ አፕ’ ‘አውችን’ ይዛችሁ መጥታችሁ… ገና ከዋሻ የወጣን አታስመስሉና! ምን መሰላችሁ… የአንዳንዶቻችን ሩጫ!... አለ አይደል… ከራስ ለማምለጥ የሚደረግ ሩጫ ሆኗል። ክፋቱ ደግሞ… ስንሮጣት እንከርማታለን እንጂ መድረሻ የለንም።
‘ፈረንጅ’… ‘አይደንቲቲ ክራይስስ’ ነው… ምናምን የሚላት ነገር አለች አይደል… አንዳንዶቻችን አውላላ ሜዳ ላይ ከተንላችኋል። አለ አይደል… ከራሳችንም ሸሽተን… ‘እነሱም’ በመጤነት እንኳን አልቀበል ብለውን… አያሳዝንም! እንዴ… ኮሚክ ነገር እኮ ነው። እንትና የ‘ቺካጎ ቡልስ’ ቲሸርት ስላደረገ… እኔ በሌጣ ከኔተራ ስለሄድኩ… እሱ ስልጡን… እኔ ‘ፋራ’ እንሁን!
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አለ አይደል ይሄ ስልጣኔና ‘ፍርንጅናን’ የማያያዝ ነገር አለ። እንግዲህ… እነሱ ‘ሲግቱን እኛ ስንጋት አይደል የተከራምነው! አንዳንዶቻችንማ… አለ አይደል… የፈረንጅ’ ‘ሞሮን’ ያለም አይመስለን። በእነሱ ባይብስ! እዚህ አዲስ አበባ ሞልቶ የለ። ምን ይደረግ… በቃ ‘ቆዳ’ ስልጣኔ ሆነላችሁና… ስንት የሀበሻ ባለሙያ ቆሎ ሲቆረጥም… የፈረንጅ ‘ማሞ ቂሎ…’ “ከፍ በል ዝቅ በል” ይለናል።
(እንትናየ… ያ ‘ፈረንጁ’… እንዴት ሆናችሁ? አይ…‘ልትፈነገይ’ ነበር ሲሉ ሰምቼ… ቂ…ቂ…ቂ… እስቲ ምናለ… እኛ ቤንች የተቀመጥነው ሞልተን… ምንድነው ፈረንጅ ላይ የሚያሻማችሁ! አሃ… አሁን እኛ  የእነሱን ያህል “አቅቶን” ነው!... “ቂ…ቂ…ቂ…!)
እናላችሁ… የእኛ የ‘አገር ቤት’ ሰው ስድስት ወር ሀምበርገር ሲገምጥ ከርሞ ይመጣና “በቃ አበሻም አልሰለጥን አለ…” ሲላችሁ… አለ አይደል ታዝናላችሁ። ኧረ ‘ባካችሁ… ሰልፍ ኮንፊደንስ’… ‘ከተደበቀበት’ ፈልጉልን! (በነገራችን ላይ… ይሄ ከኒዮርክ ምናምን የ‘ፈረንጅ’ መኪና እየተደገፉ… ፎቶ መላክ… እሱ ነገር ቀነሰሳ! አሃ… ተነቃቃና!... አሁን አሁንማ… ከዚያ ወደዚህ የሚመጣው ዶላር ቀንሶ… ከዚህ የሚሄደው ድርቆሽ እየበዛ ነውሳ! እንትና መቼም አንተም እንደ እኔ… ‘ኮምፕሌይን’ ማድረግ ትወዳለህ… “ከሀገሩ የወጣ እስኪመለስ…” ለሚለው አዝማሪ መሸለም እችላለሁ። እኔ የምለው… ከሀገሩ የወጣ ሰው በቅሎ ይሁን የሜዳ አህያ… መቼ ሄደህ ነው ያወቅከው … ወይስ በታሳቢነት ነው። እስከዚያው አለ አይደል… እኔ አንድ ትሪፕ ቢሾፍቱ እስፖንሰር አደርግሃለሁ) እኔ የምለው … አንዴ!... በቃ ሹካ አያያዝ ካልቻልን… አልሰለጠንንም ያለው ማነው! እኔ‘ኮ ስለቴክኖሎጂ ምናምን እሺ ያውሩ… መቼም በሱ በኩል ‘ይቅደሟችሁ… ይከተሉ’ የተባልን ነው የሚመስለን። ግን… ፖስታን መጠቅለል መቻልና አለመቻል የስልጣኔ መለኪያ ያደረገው ማነው? ‘ፈረንጅ’ ፓስታውን በዳቦ ስለበላ… እንጀራ በወጥ የበላውን ቅንጣት ታክል ዝቅ የሚያደርገን ነገር የለም። እናላችሁ… በቴክኖሎጂ ኋላ መቅረታችን ልክ ነው። ይሄ ነገር ሰውነታችንን የሚያሳንስ አይደለም… አለ አይደል… እዚሁ እንኳን ነገሬ ብላችሁ ስታዩ… የሚያበሽቃችሁ መአት ነገር አለ። ለጨዋታው ያህል ዛሬ ማርቲን ሉተርኪንግ… ምናን አይነት ሆንኩባችሁ አይደል! የምር ግን… አንዳንዴ ይሄ ራስ በራስ የሚደረግ ጭቆና ያበሳጫል።
አሃ ገና ለገና ቢላው ሹካው እንዴት እንደሚያዝ “አላውቅም…” የሚል የ‘ፈረንጅ’ ምግብ ንክች የማያደርግ ሞልቶላችኋል። እንዴ… ልክ አይደለም ወይ! አያያዙን ማወቅ የ‘እነሱን አበላል ማወቅ’ እንጂ… መሰልጠን ማለት አይደለም።
ሙዚቃ… ለምሳሌ… የ‘ዓለም ቋንቋ ነው’… አይደል! ግን አሬታ ፍራንክሊንን መስማት… ስልጣኔ… ሽሽግ ቸኮልን መስማት  ‘ፋራነት’ ያደረገው ማነው! የምር… ይገርማችኋል። የኬኒ ሮጀርስ ጊታር… የስልጣኔ  ‘ግሪን ካርድ’… የይርጋ ዱባለ ማሲንቆ… የፋራነት ‘ላይሰንስ’ ሲሆን… አለ አይደል… የሆነ ነገር አይሰማችሁም!
እናላችሁ… የ‘ስልጡንነትና’ የ‘ፋራነት’ መለኪያዎች… ራሳችንን ከመሬት በታች እነሱ ከመሬት በላይ!... ነገርየውማ ያው የምንሰማው የምናየውም… የምናነበውም… እነሱን አይደል… በጽሑፉም በአልበሙም በምኑም እንደማንረባ ነው የሚነግሩን! ክፋቱ ምን መሰላችሁ… ሳይታወቀን ተቀብለነዋል።
ይኸው… በፖለቲካውም በምኑም ‘ስንጣላ’ እንኳን  ሮጠን እነሱ ጋር አይደለንም! አሃ ‘ስልጣኔ’ መሆኑ ነዋ! እዚሁ… በአገር ባህል እኛ “አንተም ተው… አንተም ተው…” ወይም  “የበደለም ይቅርታ ይጠይቅ… የተበደለም ለእግዚአብሔር ብሎ ይቅር ይበል…” ማለት እያለ ‘ለ ፈረንጅ’ እየሄዱ “ልብ አድርጉልኝ… ብቻ! “ማለት ሆኗል። ምን መሰላችሁ በአገር ባህልኛ መስማማት ‘ፋራነት’ ነዋ!
እናላችሁ… ይሄ የ”ስልጡንነትና” የ “ፋራነት” መለኪያ አለ አይደል… ለ‘እኛ ሳይሆን ለእነሱ ሆኖ የተቀደደ ነው የሚመስለው። ስለ ላሊበላ ህንጻ ሲነግሩን ከእቁብ የማንከተው ሰዎች ስለ ‘ኢምፓየር እስቴት ቢልዲንግ’ ግን “አጀብ የሰው ስራ!” እንላለን። ይህ ደግሞ… እንዲያው አጉል “አገሬ ናፈቅሽኝ” ምናምን ሳይሆን… ይህ ‘የእኛ የሆነው ነገር ሁሉ’ ‘ያለመሰልጠን’ ምልክት መሆኑ ስለማይታየኝ ነው።
ብቻ… ከራስ መሸሽ የመሰለ እርግማን የለም። የምር… በአንድ በኩል እኛነታችንን በ‘ቪም’ ለማጠብ ስንሞክር… በሌላ በኩል  እነሱ… “ደግሞ አንተ ከእኔ ጋር ምን ያመሳስልህና!” ሲሉን በቃ መሃል ላይ መቁለጭለጭ ነው። እስቲ ልቦናውን ይስጠን።
ደህና ሰንብቱልኝማ!
    

ሩሲያ የሆነው ኢትዮጵያ ይደገማል። ወይም ሌላ አገር እንደ አዲስ ይከሰታል። ወጉ ግን ለሁሉ ይተርፋል። ሩሲያውያኑ ሲቀልዱ ይሆን አምርረው ባይታወቅም እንዲህ ይላሉ።
አትክልተኛው ሰውዬ የመስሪያ ቤቱን አትክልት በየጊዜው አላጠጣህም ተብሎ በድክመት ተገምግሞ በማስጠንቀቂያ ታልፏል። በልቡ “ይቺን ስህተት ሁለተኛ አልደግማትም” ሲል በጓዶቹ ስም ይምላል። (“ስጋ ብጽወት!” እንደ ማለት መሆኑ ነው)
በሚቀጥለው ቀን በጠዋት ይነሳና የውሃ ማጠጫ ጎማውን ከቧንቧው አገናኝቶ ሲያበቃ በረዥሙ እየረጨ አትክልቶቹን ውሃ ማጠጣት ጀመረ። በአጋጣሚ አህያ የማይችለው ዝናብ ይመጣና ዶፉን ይለቀዋል። ሰውየው ውሃውን ማጠጣቱን ይቀጥላል።
በዚያ መ/ቤት አጠገብ ዣንጥላ ይዘው የሚያልፉ ሰዎች ነገሩ ገርሟቸው፤
“ምን ሆነህ ነው ዝናብ እየዘነበ አንተ እንደገና የቧንቧ ውሃ የምታጠጣው?” ብለው ይጠይቁታል። አትክልተኛውም ስራውን እየቀጠለ፤
“መመሪያ ነው ጎበዝ! በመመሪያ ቀልድ የለም!”
***
እንደዚሁ ሌሎች ሁለት ሩስያውያን ከአለቃቸው መመሪያ ወርዶላቸዋል። መመሪያውም፡- አንደኛው ይቆፍራል፣ ሌላኛው የቧንቧውን ትቦ ይከታል የሚል ነው። ከዚያ የመጀመሪያው መልሶ ይደፍናል። እንዲህ እያሉ “በነገው እለት 200 ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ ቧንቧ አስገብተው እንዲጨርሱ” የሚል ትዕዛዝ ደርሷቸዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ በነጋታው ግን ቆፋሪ መጥቶ ቁፋሮውን መቆፈር ቢጀምርም ባለቧንቧው እክል ገጥሞት ትቦውን ይዞ ሳይመጣ ይቀራል። ያም ሆኖ ቆፋሪው ስራውን አላቋረጠም።
በሜትር እየለካ ሁለት ሜትር ያህል ርዝመት ይቆፍርና መልሶ አፈሩን እየከፈተ ይደፍነዋል። ይቀጥላል ሌላ 2 ሜትር። ደሞ ይደፍናል። እንዲህ እንዲህ እያለ 200ውን ሜትር ቆፍሮ ደፍኖ ይጨርሳል። ነገሩ ግራ የገባቸው የመ/ቤቱ ሰራተኞች፤ “ምን አይነት የሞኝ ስራ እየሰራህ ነው? ‘ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ’ አደረግከው እኮ?” ሲሉ ይጠይቁታል።
“መመሪያ እኮ ነው ጎበዝ! እኔ የተሰጠኝን ሃላፊነት ተወጥቻለሁ። መመሪያውን በሚገባ አክብሬአለሁ” አለና መለሰ።
***
በኢትዮጵያ ደግሞ እንዲህ ያለ ወግ አለ።
ጊዜው ጥቂት ዓመታት ቆየት እንደማለት ብሏል። ታጋዮች በአንድ መኪና ሞልተው ሲሄዱ የመኪናው ፍሬን ይበጠስና ሹፌሩ ሲቸገር  ቆይቶ የአንድ ትልቅ መ/ቤት ግንብ ጥሶ አስገብቶ ያቆማታል። ሹፌሩ ክፉኛ ይጎዳል። ደም በደም ይሆናል። ሌሎቹ ያልተጎዱት ታጋዮች በፍጥነት መኪና ቀይረው በአስቸኳይ ሹፌሩን ወደ አንድ ሆስፒታል ይዘውት ይበራሉ።
ሆስፒታሉ ደጃፍ ሲደርሱ መታወቂያ ይጠየቃሉ። ከደከመው በሽተኛ በስተቀር ሌሎቹ መታወቂያቸውን አውጥተው ያሳያሉ። ዘበኛው የሁሉንም የመታወቂያ ፎቶና መልካቸውን ካስተያየ በኋላ ወደተኛው በሽተኛ እያየ፤
“የሱስ መታወቂያ የታለ?” ሲል ይጠይቃል።
“ጓድ እሱማ በሽተኛ ነው። አታየውም ደም በደም ሆኖ መንቀሳቀስ እኮ አይችልም” አሉት።
“መታወቂያ ከሌለው እናንተ ግቡ እሱ ይቆያል!”
“እንዴ ምን ማለትህ ነው ጓድ…”
“መመሪያ ነው መመሪያ ነው! ከፈለጋችሁ እናንተ ግቡ አለበለዚያ በሽተኛችሁን ይዛችሁ ተመለሱ! መመሪያ ለሁሉም እኩል ነው የሚሰራው!”
***
አንዳንዱ መመሪያ ከጅማት ይጠነክራል። ያለ አንዳች ህሊናዊ ዳኝነት፣ ያላንዳች ማመዛዘን እንገልገልብህ ሲሉት ራሱን መመሪያ አውጪውን ጭምር እግር ተወርች ቀይዶ አላላውስ አላስተነፍስ ይላል። “የዝንጀሮ ንጉስ ራሱ ይከምራል ራሱ ያፈርሳል” ይሏይ ይሄ ነው። አንዱ ቦታ ስራ ሲቆም መላው ስራ በድን የሚሆንበት አይነት መ/ቤት አለ። ያ እንግዲህ አንድያውን ይሞታል ማለት ነው። የሚገርመው መመሪያውን በጥብቅ ስራ ላይ አውላለሁ ብሎ የሚውተረተረው ሰው መነሻ በመመሪያው ማመን ሳይሆን የግምገማ ስራቸው መሆኑ ነው። ይህ በፈንታው የሚያረጋግጥልን አንድ እውነት አለን። ግምገማ  ስህተትን ማረሚያ መሆኑ ቀርቶ የበታቶች በበላዮች አይን ደካማ እንዳይባሉ፣ አልፈው ተርፈው “የባህሪ ለውጥ አመጣ!”፣ “የሚታወቀው ስህተቱን በማመን ነበር ዛሬ አመሉን ለውጧል”፣ “የችግሩን ስሯን መዝዘን ስናያት መነሻዋ ሌላ ናት” ወዘተ እባላለሁ የሚል ፍርሃት በውስጡ በመንገሱ ነው። ይሄ ደግሞ በፈንታው የገዛ የስራ ባልደረቦችን መቆጣጠርን፣ ለአለቃ ማጎብደድን፣ የየአይነቱን ሙስና፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነትን ወዘተ ይወልዳል። መመሳጠር ይበረክታል።
“የልቡን የሚሰራ ለእናቱ አይነግርም” እንዲል መጽሐፉ፤ የጥቂቶች ዱለታ ያይላል። ስራ ይዳከማል። ሲከፋም ከነጭራሹ ይቆማል። ባለው የቢሮክራሲ የቆላ ቁስል ላይ የአይጥና ድመት ደፈጣ ሲጨመርበት አንድያውን ወደ ልብ ድካም ያመራል። የአቅም ግንባታው የአቅም መፍረስን ጽንስ ተሸክሞ ይጓዛል። ልማቱ ንቅዘትን አርግዞ የሚራመድና ቀኑን የሚጠብቅ በሽተኛ ይሆናል። ነጻ የሲቪክ ማህበረሰብ ይፈጠርበታል የሚባለውም እቅድ ውስጡን በግንደ-ቆርቆር የተበላ አፋዊ የፖሊሲ ዋርካ ብቻ ሆኖ ይቀራል። በዚህ ሁሉ ላይ የፖለቲካ ጫና ሲጨመርበት “የማይታጠፍን እንጨት ልለምጥህ ብሎ ማንከት” እንደተባለው ይሆናል።
የማይጠየቅ መመሪያ፣ የማይሻሻል ህግ፣ የማይለወጥ እቅድና መርሃ ግብር ጥቂት ታማኞችን እንጅ እንደ ልቡ ለማሰብ የሚችል፣ የሆዱን ለመናገር የሚደክም፣ በነጻ ውይይት የሚያምን ነጻ ህብረተሰብ ለመፍጠር አያስችልም። ይልቁንም ፈሪና ግልጽነት የጎደለው፣ በራሱም በሌሎችም የማይተማመን ዜጋ ማሳደግ ነው የሚሆነው። በመሃል ጌታው ያፈጣል፣ በጨለማ ሎሌው ያፈጣል  የሚባለው አይነት ግንኙነት እየበዛ የአጥቢያ አምባገነኖች (Local dictators) እንዲፈለፈሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ፓርቲና መንግስት መለያየት አለባቸው በሚባልበት በአሁኑ ሰዓት የመመሪያ ትርጉም በፓርቲና በመንግስት ውስጥ ይለያይ ይሆናል ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው። የተለያዩ የቲያትር መድረክ ላይ የሚተውን ተዋናይ መብራቱና መጋረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ ተዋናዩ ገጸ-ባህሪው ያው ነው። ወዲህ ፓርቲያዊ ግለሰብ፣ ወዲያ መንግስታዊ ግለሰብ ለመሆን አይቻልም። በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ከመሆን በቀር።  በሩስያ የታየውና ፓርቲውንና የመንግስትን ቢሮክራሲ ለመለየት ከማይቻልበት ደረጃ (Bureaucratization of the party) የሚባለው ማለት ነው። አስቀድሞ ነገር የፓርቲው ጤና አለመሆን ነው። ገዥው ፓርቲ ጤና ሳይሆን የሚወርዱት መመሪያዎች፣ የሚሰጡት ትዕዛዛት ጤና አይሆኑም። እንደ ኢትዮጵያ ባለው አገር ደግሞ ጭራሽ ከቢሮክራሲ ጋር ፓርቲው አንዴ ከተፈጣጠመ በኋላ እናፋታህ ቢሉት፣ ከስልጣን ናፋቂነት እስከ ጥቅም አጋባሽነት ያለውን የግለሰቦችና የድርጅቶች ህልውና ማናጋት ይሆናል።
 የውስጥ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ደረቅ ወይራ የሆኑበት ሰዓት አውራ ገዥ ለሆኑት ሃያላን መንግስታት የተሸበበ የበቅሎ ልጓም በቀላሉ እንደመሳብ ይሆንላቸዋልና ውሃውን ወደፈለጉት ቦይ የሚነዱበት ቀጫጭን መመሪያ ማድረግ የበለጠ ቀና ይሆንላቸዋል። ታዛዡ ያለችግር ይታዘዛል፡፡ መመሪያ ነዋ! ስለዚህ የወረደው መመሪያ መሬት አይወድቅም። በዚህም ሃያላኑ በሰሜን የተሳካውን ድል በምስራቅም ቤተ-ሙከራ ውስጥ ለመክተት የረጋ መደላድል ማግኘታቸው ነው ማለት ነው። ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ህብረተሰብ ውስጥ የጌቶች መዋቅር ብዙ ነው። ጌቶቹ ሰማየ ሰማያት ላይ የተቀመጡ፣ የማይታዩ  ሃያላን በሆኑ ጊዜ ደግሞ የትዕዛዙ መነሻ ጫፍ አይታይም። ውጤቱ እንጅ። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ህዝብ አልተዘጋጀበትምና በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ እሺ ወይም እንቢ ለማለት (React ለማድረግ) አቅም አይኖረውም። የቅዱስ ጊዮርጊስ ጦር ሲወጋ እንጅ ሲወረወር አይታይም እንዲል መጽሐፉ። በተጠመደለት ወጥመድ ውስጥ ዘልሎ ጥልቅ ለማለት የሚጣደፍ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የሙያ ማህበር ያልታደለ ነው። ከሚቀመርለት ቀመር፣ ከሚታጠርበት አጥር ማዶ ለማየት የማይችል ህብረተሰብ እንደተገለበጠች ኤሊ ነው። ወደ ጤናማው አቋሙ የሚመልሰው የውጭ እርዳታ ይጠብቃል።
ዝናብ ሊመጣ ሲል ጆሮዋን ለምታቆመው አህያ፣ ለውጥ ሊመጣ ዳር ዳር ሲል ጆሮውን የሚያነቃ፣ ለውጥ ወዳድ፣ ሀገር ወዳድ ምሁር ያስፈልጋል። ሀገር ወዳድ ምሁር የህዝብ አይን የህዝብ የጉዞ አቅጣጫ ጠቋሚ ቀስት ነው። በአንጻሩ ለውጥ ፈላጊ፣ ተንቀሳቃሽ ምሁር ያጣ ህዝብ ያልታደለ ነው። የኩሬ ውሃ ነው። አይፈስም። አይጠራም። አይጸዳም። አይሻሻልም።  ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ንፍቀ-ክበብ ውስጥ የማይከቱና የታዘዘውን ተቀባይ የሚያደርጉ መመሪያዎች እንደተሸነቆረ እቃ ናቸው። ምንም አይነት ቀና ነገር ቢሞሉባቸው፣ ምንም አይነት የለውጥ አስተሳሰብ ቢከቱባቸው ያፈሳሉ። ይህም ውሎ አድሮ መመሪያ አውጪዎችን፣ ፖሊሲ ቀራጮችን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ ነው። መርማሪዎች ተመርማሪዎች፣ ጠያቂዎች ተጠያቂዎች የሚሆኑበት ጊዜ እየመጣ መሆኑ ግልጽ ነው። የማረጋገጫና የማጣሪያ መንገድ ደግሞ በህዝብ እጅ አለ።  ማ ወሳኝ፣ ማ ጽዱ፣ ማ ኢዲሞክራሲያዊ፣ ማ ዲሞክራሲያዊ፣ ማ ተቻቻይ፣ ማ ገፊ፣ ማ ለአገር የቆመ፣ ማ ራሱን የሚሰዋ መሆኑ ይለያል። ጊዜው ሲደርስ “የተሰነጠቀ ቅልን ለማወቅ ውሃ ጨምርበት” ማለት ብቻ ነው።

አንበሳና ሦስት አሽከሮቹ አነር፣ ተኩላና ቁራ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ በመዘዋወር ላይ ሳሉ አንድ ግመል አገኙ፡፡ ግመል ከዚያ ቀደም አይተው አያውቁ ስለነበር፣ ይሄ ምን ይሆን? ሲሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ፡፡ ግር ስላላቸው አነር ጠጋ ብሎ ጠየቀው፡፡ ግመል መሆኑን ነገራቸው፡፡ ነጋዴ መንገደኞች በዚህ ጫካ በኩል ይዘውት መጥተው በመካከል እንደተጠፋፉም አስረዳቸው፡፡ አነር፣ ተኩላና ቁራ ባዩትና በሰሙት እየተገረሙ ሄደው ለጌታ አንበሳ ነገሩት፡፡ አንበሳም “ይምጣና ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ እኔ እጠብቀዋለሁ፡፡ እንከባከበዋለሁ፡፡ ሂዱና ወደዚሁ አምጡት” ሲል ትዕዛዝ - አከል ሀሳብ አቀረበ፡፡
አሽከሮቹ ሄደው ለግመል ነገሩት፡፡ ግመል በጣም ተደሰተ፡፡ አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ መሆኑንንም ገለጠላቸው፡፡ አሽከሮቹ ግን በሁኔታው አልተደሰቱም፡፡ ምነው ቢሉ… ሌላ ተመጋቢ አፍ ተጨመረ ማለት ነው፡፡ ግመሉ የመጣ ሰሞን ጌታ አንበሳ ድንገተኛ ፍልሚያ ከዝሆን ጋር ገጠመ፡፡ በዚህም ፍልሚያ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ ስለዚህም ቁስሉ እስኪሽር ከዋሻ መዋል ጀመረ፡፡ አሽከሮቹም ከየትም ከየትም ብለው እሱን መመገብ ግዴታቸው ሆነ፡፡
አሳዛኙ ነገር ግን የጫካው ታዳኝ ሁሉ ቀስ በቀስ ተመናምኖ እየተሟጠጠ ሄደ፡፡ ውሎ አድሮም ከናካቴው የሚላስ የሚቀመስ ጠፋና አረፈው፡፡ ጌታ አንበሳ “እኔ ሄጄ የሚበላ ልፈልግ እንጂ እንዲህ እየተራብኩ ቁስሌ እንዴት ይድናል?” አለ። አሽከሮቹ “በጭራሽ
አይሆንም! አንተ አርፈህ መተኛት አለብህ፡፡” አሉት፡፡
አንበሳውም፤ “በሉ እንግዲያው ዘወር ዘወር ብላችሁ የሚበላ አምጡልኝ - ወደሌላም ሰፈር ሄዳችሁ ቢሆን ሞክሩ!” አላቸው፡፡
“ኧረ አንተን ብንጠብቅና ብናስታምም ይሻላል ጌታ አንበሳ”
“መጀመሪያ ምግብ ፈልጉ!”
አሽከሮቹ ምግብ ፍለጋ ወጡ፡፡ በየጫካው ሁሉ ዞሩ፡፡ ግን ምንም አጡ፡፡ ተኩላው፤ “እዚህ ምንም የለም እባካችሁ፡፡ ከንቱ ልፋት ነው!” አለ፡፡ ቁራው ቀበል አድርጎ “እውነት ነው እዚህ ምንም ነገር የለም፡፡ ቤት ግን ምን የመሰለ ግመል አለን‘ኮ” አለ፡፡ “እሱንማ እንዳንቋደስ ጌታ አንበሳ ግመሉ እንዳይነካ፤ እኔ አጠብቅልሃለሁ ብዬ ነው ያመጣችሁት ቃል - አባይ መሆን የለብንም ብሎናል‘ኮ፡፡ ስለዚህ ግመሉ በመበላቱ አይስማማም”
“ለማንኛውም ወደቤት እንሂድና ማታችንን እንንገረው፡፡ እኔ ግን ቆይ ታያላችሁ አንድ ዘዴ እዘይዳለሁ!” አለ አነር፡፡ ተያይዘው ወደ ቤት ተመለሱና የሆነውን ሁሉ ለጌታ አንበሳ ነገሩት፡፡ አቶ አንበሳ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ “ከእንግዲህ እንዴት አድርጌ ቁስሌን ላድነው ነው!” ሲል አማረረ፡፡ አነር ብድግ ብሎ “አንተ ጌታችን በረሃብ ስትሞት ዝም ብዬ አላይም፤ እኔ አድንሃለሁ፡፡” አለ፡፡
“እንዴት?” አለ ጌታ አንበሳ “እኔን ብላኝ” ሲል አነር ራሱን ለጌታው ሊሰዋ አቀረበ፡፡
“በጭራሽ አላደርገውም፡፡ ባለፉት ዓመታት ሁሉ በታማኝነት ያገለገልኩኝ ታዛዤን ንክች አላደርግም!”፡፡
ተኩላ ድንገት ብድግ ብሎ፤“ጌታዬ፤ ከተራብክ በቃ እኔን ብላኝ” ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡ አንበሳም “አንተንማ ልበላ አልችልም፡፡ ለብዙ ዓመታ በቅንነት ስታገለግለኝ የቆየህ ወዳጄ’ኮ ነህ!” አለ፡፡
ቁራም ተራውን ተነስቶ “ጌታ አንበሳ እኔን ብትበላኝ ነው የሚሻለው”አንበሳ ትንሽ ኮስተር እንደማለት ብሎ “ወዳጆቼ ጅል አትሁኑ እንጂ፡፡ አንተንም ቁራን ልበላህ አልችልም፡፡ የብዙ ጊዜ ታማኝ አገልጋዬ ነህ፡፡ በዚያ ላይ እፍኝ የማትሞላ አናሳ ፍጥረት ነህ” ብሎ ተቆጣ፡፡
ግመሉ ያደረጉትን ውይይት ሁሉ ሲያዳምጥ ቆይቶ “እንግዲህ ጌታ አንበሳ ማንኛችንንም የመብላት ፍላጎት የለውም ማለት ነው፡፡” አለ ለራሱ፡፡ “ስለዚህም እኔም እንደሌሎቹ ‘እኔን ብትበላኝስ?’ ብዬ ብጠይቀው ተገቢ ይሆናል፡፡ “ጌታ አንበሳ ሆይ ምናልባት እኔን
ብትበላኝ ሳይሻል ይቀራል?” ሲል ጠየቀ ግመል፡፡“አንተን?” አለ አንበሳ በመደነቅ፡፡


“አዎ እኔን !” አለ አቶ ግመል፡፡“ግመል የጠየቀው ትክክለኛ ጥያቄ ነው!” አለ አነር፡፡“በጣም እንጂ!” አለ ተኩላ፡፡“ከዚህ የበለጠ ልባዊና ዕውነተኛ ጥያቄ ከየትም ሲገኝ አይችልም! ከሆነ እንዲያውም አሁኑኑ መፈፀም ነው ያለበት” አለ ቁራ፡፡ ውሳኔው ፀደቀ፡፡ አንበሳው ግመሉን እንዴት እንደሚበላው ለማሰብ ቀርቶ ዐይኑን እንኳን ሳይጨፍን ሶስቱ አገልጋዮቹ ግመሉን ዘነጣጥለው መሬት ላይ ዘረጉት፡፡ የልባቸው ሞላ፡፡ግን የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ያደፈጠ ልቡን ብቻ አምኖ የሚጓዘው በርካታው ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ችግር እንፈታለን ለህዝቡም ፍትህ ርትፅ እናመጣለታለን፣ ዲሞክራሲን እንናጎናጽፈዋለን፣ ባረንጓዴው ዘመቻ አረንጓዴ ተፈጥሮን እናነጥፋለን፣ ፈጣን ልማት እናመጣለን የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫትነቷን እናረጋግጣለን፣ ከመከላከል ወደማጥቃት ተሸጋግረናል፣ (ማርሽ ያለውና ማርሽ የሌለው) መልካም አስተዳደር ከልሂቅ እስከደቂቅ እናዳርሳለን፣ አንድም ጥይት የማይተኮስባት ሰላማዊ አገር ይኖረናል፣ በቀን ሶስቴ በልተን የምናድርባት ኢትዮጵያ ትሆናለች ወዘተ ቃል - ይገባል፡፡ ማተብ ይታሰራል! በስራ ትርጓሜው የለም! ባለፈው ዘመን እንደተባለው፡፡ “የምንለውን ብለናል የምናደርገውን
እንጀምር!” ማለት ይከተላል - ቃል ይገባል ቃል ይሻራል፡፡ አደራ ያስቀምጧል መልሰው አደራ ይበሏል! የችግር ቀን አንዱ “ግመል” እዳውን በራሱ ከፍሎ ሌሎች ረሀባቸውን ያስታግሳሉ፡፡ ችግራችንን ፈትተናል ብለው ያምናሉ፡፡ ጉዳዩ ግን ዞሮ ዞሮ “በወተት አምሮት የታመመ፣ ጮጮ ሙሉ ውሃ ግጥም አደረገ!” እንደተባለው ነው፡፡ “በሌላ ወገን ደስ አይበላችሁ ምጣዶች፣ ልንጋግረው ያሰብነውን አገነፋነው!” በሚል ዓይነት ፍልሚያ አንድም ወንዝ መሻገር አይቻልም፡፡ ከቶም የእያሪኮ ጩኸት ነው፡፡ አንድን ሀገራዊ ጉዳይ እነ እገሌን ድል ለመምታት፣ እነ እገሌን “ኩም” ለማድረግ፣ እነ እገሌን “አፍ - ለማስያዝ”፣ እነ እገሌን ገና ሳያቆጠቁጡ ለማስቀረት፣ በሚል ቀመር ከተጓዝን ጊዜያዊ ደስታን ብቻ እንደሚሰጠው የወይን ትፍስህት አላፊ ጠፊ የሞቅታ ጉዞ ይሆናል፡፡

ከቶውንም በተደጋጋሚ የሚታየውን የቅርብ - ራዕይ ችግር (Myopia) በሩቅ አሳቢ ዕይታ ለመተካት ስራዬ ተብሎ ካልተደከመ ብዙ ፀፀተኛና፣ ብዙ አስተዛዛኝ ሰዎችን በዙሪያ በመሰብሰብ ከንፈርን ከመምጠጥ ያለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ አይመጣም፡፡ “እህህ እያሉ ምንቸት ሙሉ ጎመን ይጨርሳሉ” ነውና በታማኝነት በቀረቤታ፣ በ”አብሮኝ ደክሞ የት ላድርሰው” ዓይነት አንድም ሙያውን አጥቶ አንድም ቦታውን ሰቶ ዓይነት የቢሮክራሲ መዋቅር ቅንበባ ለሰው ኃይልም ፍጆታ ለመልካም አስተዳደርም ቀረፃ አመቺ ጥርጊያን አያመጣም፡፡ ከአንድ መስሪያ ቤት ወደሌላው ፕወዛም፣ ጥረዛ፣ ከፌቴ ራቅ ይበልልኝ ለማለት ያህል ካልሆነ “ከመጥበሻው ወደ እሳቴ” ከመሆን አያልፍም፡፡ ከነ ሥነ አዕምሮአዊ አሉተኝነት ከእነብሶት - ምሬቱ ፣ ከእነዳተኝነቱ፣ ከእነነገር ሰሪነቱ፣ ከነመበደል - መገፋቱ የውስጥ አፍራሽ ግብረ - ሃይል የመፍጠርን ያህል ይሆናል፡፡ ጉልቻ መቀያየሩ ቀረና ወጡን መቀያየር እንደማለት ያለ ሀገራዊ ምፀት ወይም ክፍለ - ከተማዊ ስላቅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ነበር። ሰሞኑን “ዓለም ባንክን ያመነ ብር ዘገባ” የሚለው
መፈክር እጄ አመድ አፋሽ ነው። የሚሉ ሰራተኞችን ያስዘገነ እንዳይሆን መጠንቀቅ በተገባ ነበር፡፡ የሀገራችን ሰው ተዘጋጅቶ መጠበቅን በየዘመኑ እየዘነጋው ዋናና ትርፉን እየቀላቀለ ለኪሳራ ሲዳረግ በርካታ የለውጥ ወቅቶችን ተሻግሯል፡፡ ካልታዘልኩ አላምንም በሚል
የተጠራጣሪነት መንፈስ ተሸብቦ መመካከር ሲሻው ሳይመካከር፣ መደራጀት ሲያስፈልገው ሳይደራጅ፣ መጠየቅና መሞገት ሲገባው እጁን አጣጥፎ፣ “ወቸ ጉድን”ና “ጉድ-አንድ ሰሞን ነው”ን እያዜመ ኩሬንም ባህርንም እኩል እየዋኘ፣ እየበረደውም እየለበለበውም፤ እኔ
ቀጭኑ አዳሜ ቢተራመስ አይሞቀኝ አይበርደኝ” እያለ በመጨረሻ ለውጡ እንደደራሽ - ውሃ ሲወስደው እዬዬን ባህል ሲያደርገው ይኸው አራት ለውጥ ተቆጠረ፡፡ በእንጉርጉሮው ጠባይ አንፃር የድርጅቱም የግለሰቡም፣ የፓርቲውም ማህበሩም የዜማ ቅኝቱ አንድ መሆኑ
ወይ የያሬድ አገር ያሰኛል፡፡ “ታጥቆ እንዳይጠብቅ ወይኔ ወይኔ እያለ ይኖራል” የሚለው ተረትም የዚሁ ቅኝት አንድ ምት ነው!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… በቃ ዘመኑ እንዲህ ሆነ ማለት ነው እንዴ… በቃ እኮ ሰው አየኝ አላየኝ ማለት መተፋፈር ምናምን ሁሉ ቀረ ማለት ነው? የእውነት እኮ እንደኔ ያለው በጋቢ ላይ ካፖርት መደረብ ‘ፋሺን’ የሚመስለው ‘ፕሪሚቲቭ’ ሰው.፣ ስምንተኛው ሺህ የደረሰ ቢመስለው አይገርምም፡፡ ኧረ እንደውም የእኛ ባስ ስለሚል ስምንተኛው መሆኑ ቀርቶ አስራ ስድስተኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡ስሙኝማ… ስንት ነገር አምልጦናልሳ! አንዳንዴ ለአይን ያዝ ሲያደርግ በቦሌ መንገድ ‘ዎክ’ ሳጧጡፍ [ልጄ….ለእኛ ለእኛ ቦሌም ፓሪስም አንድ ናቸው] አንዳንድ ነገር አየት አደርግና ሲገርመኝ ያመሻል፡፡ እንዴ… ሰው እንዴት እንዴት ነው የሚያደርገው!
አንድ ወዳጄ አንድ ቅዳሜ ምሽት ቦሌ አካባቢን ሲያስስ አምሽቶ ኖሮ በማግስቱ ምን አለኝ መሰላችሁ? “የቆመ መኪና ሲመጣ ብቻ እየለየ የሚወዘውዝ መሬት መንቀጥቀጥ አለ እንዴ?” እኔ… በቃ ጭጭ አልኳ፡፡ ተናግሮ ከአናጋሪ ይሰውራችሁ፡፡


እና… ይኸውላችሁ ግርም የሚል ዘመን ነው፤ድሮ ድሮ “ሎሚ ብወረውር…” ተብሎ ነበር አሉ፤ ነገርዬው የሚያልቀው፡፡ የዘንድሮ ሰው… ልጄ ሎሚ የሚያክል ድንጋይ ይወረውር እንደሁ እንጂ … ብቻ አለመያዝ ነው፡፡ አሀ…‘ፋይል ለመክፈት’ ስንት ጣጣ አለ፡፡
አለላችሁ …. አንዳንዱ ሲያምጥ ከርሞ አንድ ቡና በወተት በትልቅ ብርጭቆና ዳበስ ዳበስ አርጎ ወፈር ያለ የልጅ ምሳ ሊሆን የሚል ቦምቦሊኖ ይጋብዛል፡፡ [ነገርዬዋ ማመልከቻ ቢጤ መሆኗ ነው] ታዲያ ልክ ሻኛው የሚገላበጥ የሀረር ሰንጋ የጣለላት ይመስል (ለነገሩ ዘንድሮ አይሞከረም!) “እንዴት ነው ታዲያ… ይመችሻል!” ይልላችኋል፡፡ ኧረ!... በቦምቦሊኖ ተመቸ! የእንትን ሰፈር ልጆች ቢሆኑ ኖሮ የዚህ ዓይነቱን ስልቻ ሙሉ ቦምቦሊኖ አሸክመው “በቀረበህ መንገድ ወደ ኬንያ…ወይ ኡጋዳ ተሰደድ…” ነበር የሚሉት፡፡
በስዋሂሊኛ ‘ይመችሻል!’ ምን እንደሆነ ስለማያውቅ አርፎ ይቀመት ነበር፡፡ ደግሞ ሌላው አለላችሁ… ተንከርፍፈህ ኑር ተብሎ ርግማን የተጣለበት የሚመስል፡፡ ጧት ይጠብቅና ከኮልፌ ኮከብ ጽባህ ቢሆን እኳን ይሸኛል፡፡ የትምህርት ሰዓት ሲያቅ ደግሞ
ቤት ይመልሳል፡፡ ምን አለፋችሁ እግሩ ስር ጎማ አልተገጠመም እንጂ ሶስት ቁጥር ታርጋ ካቻማሊ በሉት፡፡

አንድ ወዳጄ “እንዲህ ዓይነቱን…. እስኩል ባስ በለው” ነው ያለኝ፡፡ስሙኝማ ደግሞ አለላችሁ… ግርም የሚል ፍጡር፡፡ ፊልም የለ ትያትር የለ ሙዚቃ
የለ… የፈረደባትን ከጎኑ አድርጎ ድፍን አዲስ አበባን በእግር ሲያካልል ይውልላችኋል፡፡ በቃ “በእግር መጓዝ ጤንነት ነው…” እያለ ፀሀይ የለ፣ ቁር የለ ብቻውን የከተማውን ማስተር ፕላን ሲከልል የሚውል ነው የሚመስለው፡፡ የምር ግን… አንዳንዴ በቃ ነጩ ባንዲራ ቀረ እንጂ የሰላምም ተጓዥ ይመስላል፡፡ ‘ዎክ’ ሌላ ‘መንክራተት’ ሌላ፡፡እኔ የምለው … ነገርዬው ሁሉ እንደ ድሮ የተመለሰባቸው ቦታዎች አሉ እንዴ!
የመሀል አራዳ ውስጥ አዋቂዎች ሲነግሩኝ እዚያ አካባቢ “ትዝ አለኝ የጥንቱ” ዓይነት ጨዋታ አለ አለ፡፡ የት መሰላችሁ? አውቶብስ ፌርማታ፡፡ አንዳንዱ ቀኑን ሙሉ አውቶብስ ፌርማታ አይጠፋም አሉ፡፡ ምን አለፋችሁ… በቃ ሽፍቱ ያደረሰ ትኬት ቆራጭ ይመስል አላፊ አግዳሚውን ሲያይ ይውላል፡፡ እኔ’ኮ ሲኒማ ኢትዮጵያ አጠገበ ያለ ሁሉ ሰው አውቶብስ ጠባቂ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካስ ሌላም ጨዋታ አለ፡፡


ስሙኝማ የአንዳንዱ አራድነት ግርም የሚል ነው፡፡ [አንድ ጊዜ በዚህ ቢለኝ በዚያ የሆነ… ጥሬ ነገር የሆንኩበት ወዳጄ “አንተ ሰውዬ… አራድነትህን ሸጠህ በላኸው እንዴ!” ብሎኛል፡፡ እኔ የምለው ‘አራድነት’ ለ‘ፕራይቬታይዜሽን’ የሚቀርበው መቼ ነው? አንተ እንትና… ላንተ አራድነት የሚወጣው ጨረታ አይደለም ሶስቴ አሥራ ሶስቴ ነበር የሚሰረዘው! የእውነት ላንተ የሆነ ኤን.ጂ.ኦ በጣሳ የአራድነት እርዳታ ቢሰፍርልህ ይሻላል፡፡]እናላችሁ አንዳንዱ ኮተቤ አካባቢ ቆሞ “ስድስት ቁጥር አለፈች እንዴ?” ይላል፡፡ [ኧረ! ብልጥ ተሁኖ ልብ ውልቅ! ‘አይ የእንትን ሊዎንቺና ነች ያመለጠችህ’ ማለት ነበር፡፡]ስሙኝማ… ሴቶች ሰብሰብ ያሉበት አካባቢ ሲደርሱ የሚሸልሉ ወንዶች አይጥሟችሁም? በቃ… እኮ አሪፍ አክተሮች ናቸው፡፡ አረማመድ እግር ስር ስፕሪንግ የተገጠመ ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንዱ ግንባሩን ከስክሶ እንዴት እንደሚኮሳተር!...
ብቻ ማን እንደሚነግራቸው እንጃ አንዳንዶች ሴቶች ኮስታራ ወንድ ይመቻቸዋል የሚል ፈሊጥ አላቸው፡፡ [ይኸው እኛ ስንት ዘመን ስንኮሳተር እንኳን ልንመቻቸው… መንገድ ተሻግረው ነው የሚያልፉት፡፡ እኔ እንደውም አንዳንዴ ኮስተር ብዬ ሸለልኩ ስል ለልጆቻቸው እየጠቆሙ “አያ ጅቦ መጣ…” ሳይሏቸው አይቀሩም፡፡]ስሙኝማ አንድ ነገሩ ሁሉ አልሆነ ያለው ወንደላጤም አለ አሉ፡፡ ምን አለ መሰላችሁ?
“ገንዘባችሁ ሁሉ አለቀ በሻይ ትዳሩን ሳናየው ዓለምን ሳናይ!”ታዲያ እኛ ከለከልን! አይ ሸጋው ወንደላጤ… አንተ ታዲያ ዘላለምክን የሰው ሆድ በስሙኒ ሻይ የምታነፍረው…የሻይ ቅጠል እርሻ የለህ፡፡ አንተ የዘጋኸውን እንጀራህን የምን “አላሳዝንም ወይ…” ነው፡፡ ገና በጠዋቱ በሻይ ላይ ሙጭጭ ያልከው በኋላ እኮ “ዋናው ነገር ፍቅሩ ነው…” እያልክ ቦምቦሊኖ አብረን እንግመጥ ከማለት አትመለስም!
ልጄ ድሮ ድሮ… ስንት ጣጣ ነበር፡፡ አንዷን እሺ ከማሰኘት የዓለም ባንክ ብድር ማስፈቀድ ይቀል ነበር - የምር፡፡ ያኔ እኮ… የወንዱም ሽለላ አሪፍ ነበር፡፡ ፀጉር ኖራቸውም ልኖራቸውም መሀል ላይ መከፈሏ አይቀርም፡፡ ካስፈለገም የሆነ ወፈር ያለ የእንግሊዝኛ ልብ ወለድ ይያዛል፡፡ አሀ… እንግሊዘኛ የሚያውቅ ‘አለመታወቂያ እንዲያልፍ’ ይፈቀድለታላ፡፡ ስሙኝማ… አንድ ወዳጄ መሀል ላይ ፀጉራቸውን የሚከፍሉ ሰዎችን ምን ትላቸው መሰላችሁ? “ሹል ቴክስ፡፡”ደግሞ አለላችሁ ብልጥነት ሞልቶ ይተርፈውና በብልጢኛ “ስምሽ መቅደላዊት
አይደለም?” ሲል ይጠይቃል፡፡ አጅሪትም “አይ አይደለም ፎዚያ ነው” ትለዋች፡፡ እሱ ምን ይላል መሰላችሁ? “አይ… ብዙም አልራቅሁም፡፡” ከዛ በብልጢኛ አሳሳቅ ይስቅና “ያው … መቼም ሞትና ትውውቅ አንድ ቀን ነው…” ይልና ብቻ ምን ለፋችሁበሴኮንድ ዘጠኝ ቃላት ይናገራል፡፡እኔ የምለው… አንዳንዶቻችሁ “እምቢ” ስትባሉ ድርቅና ነው እንዴ! በቃ ችክክ የሚል አለላችሁ፡፡ ነጋ ጠባ ከርቀት ይከተላታል፡፡ ምን አለፋችሁ ክላሺንኮቭ ቀረች እንጂ አንጋች ነው የሚመስለው፡፡በዛ ሰሞን እኔና ጓደኛዬ አንድ ሚኒ ባስ ውስጥ ሆነን… በቃ
“ፍቅር የተራበ” ዓይነት ድራማ ስናይ ነበር፡፡ አይተዋወቁም፡፡ ወንድዬው… ታዲያ በቃ የህይወት ታሪኩን ይዘረዝርላታል፡፡

እሷ ሆዬ… በተመስጦ ሳይሆን በመገረም ነበር የምታየው፡፡ አለ አይደለም… በሆዷ “ሰው እንዲህ ሞዛዛ ሆኖ ይፈጠራል?” የምትል ነው የሚመስለው፡፡እናላች…ኮሚክ ዘመን ሆኗል፡፡ አንዳንዱ የማያውቃትን “ሹራቡ ያምርብሽ…”
ይላል፡፡ “ፒንክ ቀለም እወዳለሁ፡፡” ኧረ! ታዲያ ጨርቅ ተራ አትሄድም! አይ ሽጋው ወንደላጤ… ገንዘቤ ሁሉ በሻይ አለቀ አለ! እንትን ሰፈር ብትሄድ ምን የመሰለ በሶ አለ መሰለህ፡፡ አሀ… የላጥካትን ጨጓራ ራስህ ጠግናታ! ስሙኝማ… እስቲ ቦሌ ሄጄ አስራ ዘጠኝ ቁጥርን ልጠብቅ፡፡ ማን ያውቃል…
‘ፒንክ’ ሹራብ ይመጣ ይሆናል!

Saturday, 16 December 2023 20:44

እኛማ እንቆጥራለን

እኛማ እንቆጥራለን
ዛሬም ሙሉ ሳቅክን
ያልተሸራረፈ ሙሉ ፈገግታህን
እንዳቀፍን አለን በየምላዳችን የነገ ሰብልህን..
አሴ ኩራ ኩራ፣ ባለህበት ኩራ፣
ብርሃን ያዘምራል፣ ያሳብህ ተራራ..
ዓመቱማ ያልፋል ወደ ፊት ገፍትሮን
ዘመኑ ቢሸብት፣
አይረሴ ራዕይ፣ ነጭ ፀጉር የለው
ከቶ መች ይረሳል
ህልምህ የወይን ጠጅ፣ ሲነጋ ይበስላል
የነበረህና የነበረን ሀሳብ፣ እያደር ይጠራል፡፡
ስምህ ማዘርዘሩ፣ መንፈስህ መብቀሉ
እምነት ፍልስፍና ውልና ፈትሉ
ዕውቀትና ትጋት ብርሃን ፊደሉ
ሩቅ እንዳሰብነው ሩቅ ነው ገድሉ
ዛሬም አለ ቃሉ፣
ያውም በርቶ ፈክቶ፣ እስከ ማዕዜኑ፡፡
አውቃለሁ ታውቃለህ
የመከረኛ አገር መከሯ እስኪገባ
መከራ መብዛቱ
እውን ቢሆን እንኳ
ራዕይህ አለ ምስክር ይቆማል፤ ቀኑ ለመንጋቱ
አይቆምም ጉዟችን ባይቆምም ስጋቱ....
አይደለም ራእይ ብሳና- ዛፍ ግንድ
ሽበት አይወርሰውም የዕድሜ ዘመን ግርድ
አይረሴ ራዕይ የቸገንክበትን
የፍል ዕውቀት እርሻ የዓለም አሂዶህን
ታያለህ ማሳውን፡፡
አሴ ኩራ ኩራ
ብርሃን ያዘምራል ያሳብህ ተራራ....
የራዕይ ተራራ....
ነቢይ መኮንን

በአፍሪካ ትልቁ የፓን አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ኮራ ሽልማት ላይ (KORA AWARDS, THE BIGGEST PAN AFRICAN
MUSIC AWARDS CEREMONY) አምስት ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች በአምስት ዘርፍ እጩሆነው ተመርጠዋል፡፡ አምስቱም እጩዎች ከአርባ
ሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው ጋር በሕዝብ በሚሰጥድምጽ እንደሚፎካከሩ በ KORA AWARDS የፌስቡክ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
1. በ BEST GROUP- AFRICANURBAN MUSIC ምርጥ 40ዎች ውስጥ የገቡትኢትዮጵያዊያን እጩ ጃኖ ባንዶች (JANO BAND)
ናቸው፡፡ ከታች ባለው ሊንክ በመግባት ድምጽእንድትሰጧቸው በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ VOTEHERE :HTTPS://WWW.KORAAWARDS.
COM/TOP40
2.በBEST ARTIST TRADITIONALMUSIC ምርጥ 40ዎች ውስጥ የገባውኢትዮጵያዊያዊ እጩ አስቻለው ፈጠነ(ASCHALEWU FETENE ) በእናትዋ ጎንደርእና በካሲናው ጎጃም ነው፡፡ ከታች ባለው ሊንክበመግባት ድምጽ እንድትሰጡት በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ V OTE H ERE : H TTPS://WWW.KORAAWARDS.COM/TOP403. በ BEST MALE ARTIST-RAP MUSIC ምርጥ40ዎች ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያዊ እጩ ልጅሚካኤል (LIJ MICHAEL) ነው፡፡ከታች ባለው ሊንክ በመግባት ድምጽ እንድትሰጡት በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
VOTE HERE : HTTPS://WWW.KORAAWARDS.COM/TOP404.በ BEST COLLABORATION OF THEYEAR ምርጥ 40ዎች ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያዊያንእጩ ጆሲ ሮያል (JESSE ROYAL) ናቸው፡፡ ከታችባለው ሊንክ በመግባት ድምጽ እንድትሰጧቸው በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ VOTE HERE:HT TPS://W W W.KOR AAWARDS.COM/TOP405.በ BEST FEMALE AFRICAN URBAN
MUSIC ምርጥ 40ዎች ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያዊት እጩ ሔዋን ገብረወልድ (HEWANGEBREWOLD) ናት፡፡ ከታች ባለው ሊንክ
በመግባት ድምጽ እንድትሰጧት በአክብሮትእንጠይቃለን፡፡ VOTE HERE : HTTPS://WWW.KORAAWARDS.COM/TOP40