
Administrator
በጆሃንስበርግ ከተማ ህንፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከሞቱት ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ተጠቆመ
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም
በደቡብ አፍሪካም ዋና ከተማ ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኝ ባለ 5 ፎቅ ህነፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከሞቱት 75 ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያም እንደሚገኙበት ምንጮች ለአዲስ አድማድስ ጠቆሙ።
በመሃል ከተማዋ የንግድ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ህንፃ ላይ በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ሳቢያ 75 የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ 50 ያህሉ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።
በአደጋው ህይወታቸውን ካጡትና ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውንም እንዳለበት የጠቆሙት ምንጮች፤ በቁጥር ምን ያህል ኢትዮጵያውያን የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ በትክክል ማወቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።
የእሳት አደጋው ህንፃውን ሙለ በሙሉ ማውደሙን የገለጹት ምንጮች፤ በአደጋው ሳቢያ የሞቱትንም ሆነ በህይወት ሊተርፉ የሚችሉትን የአደጋ ሰለባዎችን የማፈላለጉ ስራ በእሳት አደጋ ሰራተኞች እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ለሁለት ቀናት የቆየው ፍለጋ ተጠናቆ የእሳት አደጋውን መንስኤና ሌሎች ጉዳቶችን የሚያጣሩ ፖሊሶች ስፍራውን መረከባቸውንም
እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል። በአደጋው ሳቢያ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ማንነት ከተለየና አስፈላጊው መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ የአደጋ ሰለባ ኢትዮጵያውያን ቁጥርና ማንነት ገለጻል ብለው እንደሚጠብቁም ምንጮቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ብንደውልም የስልክ ጥሪ ሳይሳካ ቀርቷል።
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ሣምንታዊ ስብሰባ ተካሄደ
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (Editors Guild of Ethiopia)ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ስብሰባውን በሂልተን ሆቴል አካሂዷል ። የዕለቱ የመወያያ ርዕስ ጉዳይም ”Media and Gender“ የሚል ነበር፡፡
እንደወትሮው ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሁፍ፣ በጾታ እኩልነት ላይ ትኩረቷን አድርጋ በምትሰራው የሚዲያ፣ አድቮኬሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዋ ቤተልሔም ነጋሽ የቀረበ ሲሆን፤ የማህበሩ አባላትም በርዕሰጉዳዩ ላይ የሞቀ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከሌላው ጊዜ በተለየ በዛሬው የውይይት መርሃ ግብር ላይ በርከት ያሉ ሴቶች ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ሴቶች ውክልና 30 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቆመችው የጥናት ጽሁፍ አቅራቢያዋ፤ ሴቶች በኢትዮጵያ ሚዲያ ያላቸው ውክልና እንዲጨምር በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብላለች፡፡
በሚዲያው ላይ የሴቶች ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት የማይነሳውና የማይዳሰሰው አንድም፣ የኤዲተርነት ቦታው በአብዛኛው በሴቶች ሳይሆን፣ በወንዶች የበላይነት በመያዙ ነው የሚል ሃሳብም ተነስቷል፡፡ ሴቶች ለተወሰነ ጊዜ የኤዲቶርያሉ ቦታ ሲሰጣቸው፣ አስገራሚ የይዘት ለውጥ እንደሚስተዋልም ተጠቁሟል ፡፡
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሴት ባለሙያዎች፣ በዜና ምንጭነት ያላቸው ቦታ እጅግ አናሳ መሆኑም ተነስቷል፡፡ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት፣ ከሴቶች ይልቅ ወንድ ባለሙያዎችን እንደ መረጃና ዜና ምንጭነት የመጠቀም አዝማሚያና ልማድ እንዳላቸውም ነው በውይይቱ ላይ የተነሳው፡፡
በውይይቱ ማብቂያ ላይ፣ ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የመረጃ ዳይሬክቶሬት ”Women Experts Directory” ለአርታይያኑ ተሰጥቷል ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ ”Women Experts Directory” የተሰኘ ለጋዜጠኞችና ሚዲያ ተቋማት በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግል ባለ 162 ገጽ ዳይሬክቶሪ አሳትሟል፡፡ ዳይሬክቶሪው በ18 የተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ የ200 ሴት ባለሙያዎችን የትምህርትና የሥራ ልምድ መረጃ፣ ከስልክ ቁጥርና ኢሜይል አድራሻቸው ጋር አጣምሮ አቅርቧል፡፡ ዳይሬክቶሪው፤ የዜና ምንጭ የሚሆኑ የሴት ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ያግዛል፤ በሚዲያ ያለውን የጾታ ውክልናንም ያሰፋል፤ የጾታ ተመጣጣኝነትን (ሚዛናዊነትን) ያማከለ የሚዲያ ከባቢ ለመፍጠርም ያግዛል ተብሏል፡፡
በዋናነትም ሴት ባለሙያዎች ለሚዲያው የበለጠ ተደራሽ ሆነው፣ የዜና ምንጭነት ድርሻቸው እንዲጎላ በማለም ነው፣ ዳይሬክቶሪውን በህትመትና በዳታቤዝ ያዘጋጀሁት ብሏል - የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ሴቶች በመረጃ ምንጭነት ያላቸው ቦታ ባለፉት አስር ዓመታት ከተሰራ የጥናት መረጃ ጋር ሲነጻጸር ምንም መሻሻል አለማሳየቱን የጠቆመው የማርች 2021 የFOJO-IMS የጾታ ውክልና ግምገማ ሪፖርት፤ የጋዜጠኞችን የዜና ምንጮች በማስፋትና በተለያዩ መስኮች የሚሰሩ የሴት ባለሙያዎችን ዳታቤዝ በመፍጠር ሴቶች በሚዲያው ያላቸው ውክልና ሊያድግ እንደሚችል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
”Women Experts Directory” የምክረ ሃሳቡ ውጤት ነው ተብሏል ።
‹‹የነፍስ እኩያሞች›› የአጫጭር ልብወለዶች መድበል የፊታችን ማክሰኞ ይመረቃል
የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ - ጆሴፍ ፑልቲዘር
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ ጋዜጠኛ፣ መርማሪ ሪፖርተር፣ አሳታሚ፣ የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ ነበር፡፡
በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያውን የጋዜጠኝነት ት/ቤት ከፍቷል - በተጨማሪም
ለጋዜጠኝነትና ሥነጽሁፍ ዘርፎች፣ ዝነኛውን የፑልቲዘር ሽልማትም ፈጥሯል፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ የተሻለ የዕይታ ብቃት ይዞ ቢወለድ ወይም ቼዝ መጫወት ባይችል ኖሮ፣ ጋዜጦቻችን ዛሬ ከምናውቃቸው የተለዩ ይሆኑ ነበር፡፡ ጆሴፍ በ1860ዎቹ በሃንጋሪ በታዳጊነት ዕድሜው ሳለ፣ ወታደር የመሆን ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡፡ ነገር ግን ዓይኑ (ዕይታው) ደካማ በመሆኑ የተነሳ የትኛውም ሠራዊት ሊቀበለው አልቻለም፡፡ በመጨረሻ ግን የአሜሪካ ቀጣሪዎች፣ በአሜሪካው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዋጋ መለመሉት፡፡
በወታደርነት ለአንድ ዓመት ያገለገለው ጆሴፍ፤ ከእርስ በርስ ጦርነት ህይወቱ ተርፎ እዚያ አሜሪካ ተቀመጠ - ያገኘውን ሥራ እየሰራና እንግሊዝኛ ቋንቋ እየተማረ፡፡ ከዚያም በአጋጣሚ የተከሰተ ድንገተኛ ትውውቅ፣ የራሱንም ህይወት ሆነ የዓለም ጋዜጠኝነትን ታሪክ ለዝንተ-ዓለም ለወጠው፡፡
እንዲህ ነው የሆነው፡፡
ጆሴፍ በቅዱስ ሉዊስ ቤተመጻህፍት ውስጥ እያጠና ሳለ፣ ሁለት ወንዶች ቼዝ ሲጫወቱ ይመለከታል፡፡ ጠጋ ብሎም የአንደኛውን የቼዝ አጨዋወት በማድነቅ ተናገረ፡፡ ከዚያም ሦስቱ ሰዎች መጨዋወት ይጀምራሉ፡፡ ሁለቱ ሰዎች የጋዜጣ አሳታሚዎች ነበሩ፡፡ እናም የሥራ ዕድል ሰጡት - ለጆሴፍ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር ብሩህና ትጉህ ሪፖርተር መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም የጋዜጣ አሳታሚ ሆነ፡፡ ከዚያም አዋጭ ድርድሮችን ተራ በተራ ሲያካሂድ ቆይቶ፣ የከተማው ትልቁን ጋዜጣ በእጁ አስገባ - ”St. Louis Post- Dispach” የተሰኘውን ጋዜጣ ገዛው፡፡
ይሄኔ ነው የፑልቲዘር እውነተኛ የላቀ አዕምሮ የታየው፡፡ ጋዜጣውን የሰፊው ህዝብ ድምጽ አደረገው፡፡ ህገወጥ የቁማር ተግባራትን፣ የፖለቲካ ሙስናንና ዳጎስ ያሉ የግብር ስወራዎችን መመርመርና ሃቁን አደባባይ ላይ ማስጣት ያዘ፡፡ ሰዎች ይህን አዲስ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስታይል ወደዱለት፤የጋዜጣው ሥርጭትም በእጅጉ አሻቀበ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር ከታመመም በኋላ እንኳን ተግቶ መሥራቱን አላቋረጠም፤ እናም የዓይኑን ብርሃን ሊያጣም ደርሶ ነበር፡፡ ፑልቲዘር፤ጋዜጦች የማህበረሰቡን ዓላማ ማገዛቸው እንዲሁም ህዝቡን ከሸፍጥና ሙስና መታደጋቸው አስፈላጊ ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሌላ ጋዜጣ መግዛት ቻለ፡፡ የኒውዮርክን ጋዜጣ፡፡ የህዝበኝነት አቀራረቡንም ለብዙ ተደራሲያን ተገበረ፡፡
እ.ኤ.አ በ1909 ዓ.ም የኒውዮርክ ጋዜጣው፣ በአሜሪካ ታሪክ ታላቁ የፖለቲካ ቅሌት የተባለውን ታሪክ ሰበር ዜና አድርጎ አወጣው - የፓናማ ካናል ስምምነት፣ 40 ሚሊዮን ዶላር ህገወጥ ክፍያን አጋለጠ፡፡ ይሄን ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ፍ/ቤት ሊያቆመው ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ፑልቲዘር ”ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” አለ፡፡ በጽናት በመቆም፣ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ ድል አስመዘገበ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤በዓለም የመጀመሪያው የጋዜጠኝነት ት/ቤት፣ በኒውዮርክ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ከሃብቱ ከፊሉን መድቧል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ለጋዜጠኞችና ጸሃፍት ዓ መታዊ የሽልማት መርሃግብር የሚሆን ገንዘብም ለግሷል፤ ዛሬ ከዝነኞቹ የፑልቲዘር ሽልማቶች አንዱን ማሸነፍ፣ በጸሃፍት ዘንድ እንደ ልዕለ ኮከብ የሚያስቆጥር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ ምንም እንኳ ወደ ጋዜጠኝነት የገባው በአጋጣሚ ቢሆንም ቅሉ፣ ጋዜጦች ዛሬም ድረስ ሊያሳኩት የሚተጉበትን ስታንዳርድ አስቀምጦ ነው ያለፈው፡፡
ባነገሡት ላይ ተመልሶ ይነሣባቸዋል፤ ያፈቀሩትን ያስጨንቃቸዋል።
ሦስቱ የተባረኩና የተረገሙ ኃይሎች
እውቅና ጉልበት (ጥበብና ሥልጣን)
የሥራ ፍሬና ገንዘብ (ምርትና ሀብት)
ፍቅርና አልጋ (ሩጫና ሜዳልያ)
የማንገሥ ፍላጎት ወይም መንግሥትን የማዋቀር ሐሳብ ተገቢ የኑሮ ጉዳይ ቢሆንም፣ አደጋዎቹን ማገናዘብና መላ ማዘጋጀትም የሕልውና ጉዳይ ነው። አስቀድመው መጠንቀቅ እንደሚኖርባቸው ሙሴ ለተከታዮቹ ያስተማራቸውም በዚህ ምክንያት ነው። ለሕዝብና ለንጉሥ የሚበጁ ምክሮችን ሰጥቷቸዋል።
ንግሥና ወደ ሦስት ጠማማ መንገዶች እንዳያመራ በንጉሡ ላይ ሦስት የሥልጣን ገደቦች እንደሚያስፈልጉ ነግሯቸዋል።
ለእርሱ ፈረሶችን አያብዛ፤
ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያብዛ፤
ወርቅና ብር ለእርሱ እጅግ አያብዛ (ዘዳ 17፡ 16-17)።
ንጉሡ፣ ተወዳጅነትን ለማግኘት በውሸት ይሸነግላል። ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሌሎች ሰዎችን በውሸት እየወነጀለ ያሳድዳቸዋል። አቤቱታ የሚያቀርቡ ተበዳዮችን እንደ ከሃዲ ይቆጥራቸዋል። ከተቀናቃኞቹ ጋር ሆነው ያሤሩበት ይመስለዋል።
የሕዝብ ፍቅር እንዳያጣና ሥልጣኑን የሚነጥቅ ሌላ ጉልበተኛ እንዳይመጣበት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሐሰትን መናገር፣ ተበዳዮች ቅሬታ እንዳያቀርቡ ማሳደድ፣ የራሱን ጥፋት በሌሎች ላይ ማላካክ፣ ቀላል አቋራጭ መንገዶችን ሁሉ ይሞክራል። በዐላዋቂነትና በስንፍና ወይም በክፋትና በምቀኝነት ስሜት እየታወረ ከእውነት ጋር ይጣላል። እምነት ያጣል። ዓላማ ይደበዝዝበታል። የሥነ ምግባር መስመሮች፣ የፍትሕና የፍቅር መርሖች እንቅፋትና ጠላት ሆነው ይታዩታል።
‘እውነተኛ ሐሳብ፣ ትክክለኛ ዓላማ፣ መልካም ሥነ ምግባር’ እያለ ያነበንባል። ግን ለይስሙላ ነው። እንደ አድማጮቹ ሁኔታ ቃሉን ይለዋውጣል። ባለ ብዙ ምላስ ይሆናል።
ዳኝነት ለማግኘት ከሳሽና ተከሳሽ ለሙግት ሲመጡ ለየብቻ እየነጠለ “አንተ ትክክለኛ ነህ” እያለ ሁለቱንም እያስደሰተ ሁለቱንም ለማታለል ይሞክራል። ብልጥ መሆኑ ነው። የተቀናቃኞችን የኃይል ሚዛን እያየ ፍርዱንና አቋሙን፣ ዓላማና ተግባሩን ይገለባብጣል።
የተመልካቾችን ስሜት እያየ መልኩን ይቀያይራል። ባለ ብዙ ጭንብል አስመሳይ ሰው ይሆናል።
እውነትና ውሸት፣ ጥሩና መጥፎ መለየት እስኪያቅተው ድረስ በራስ የመተማመን ዐቅሙ ይመነምናል። የማንነት መንፈሱ በየዕለቱና በየሰዓቱ እየተበጣጠሰ ይወናበድበታል። ስሜቱ ይዘበራረቅበታል።
እንዲህ እንዲህ እያለ፣ ንጉሡ ቀስ በቀስ የእኔነት ክብር እየጎደለው ሲመጣ፣ ውስጣዊ ባዶነት በተሰማው ጊዜ፣ የሕይወት ጣዕም ሲጠፋበትና የመንፈስ እርካታ ሲያጣ… ይህን ለማካካስ ወደ ሦስት ጠማማ መንገዶች ይገባል። ሥነ ምግባርን እንደ ጠላት ማየት ከጀመረ በኋላ…
ሕግ የማይገዛው ሥርዓት አልበኛ ይሆናል (አምባገነን፣ ወሮበላና ነውረኛ)።
አምባገነን (በሽንገላ ይጨክናል)፡
በዕውቀትና በጥበብ መንገድ የተራመደ ሰው፣ ተሰሚነትንና ክብርን ቢያገኝ ተገቢ ነው። ዕውቀት ‘ኃይል’ ነው። ጥቂት የፊዚክስ ቀመሮች ለእልፍ አእላፍ ቴክኖሎጂዎች መነሻ ይሆናል። ከአንድ ሜትር በላይ መዝለል የማይችል ሰው፣ አየር ባየር ውቅያኖሶችን እየዘለለ የመሻገር ብቃት ያገኛል።
ሰዎችን እየረገጠ አይፈነጭም። በጥበበኛ መንገድ ጨረቃን ረግጦ ይመለሳል።
ወደ ማርስ ለመምጠቅ ሌሎች ሰዎችን ወደ መቀመቅ አያወርድም።
ኃያልነቱ ሕይወትንና ንብረትን የሚያጠፋ ሳይሆን የሚያለመልምና መልካም ፍሬዎችን የሚያበዛ ነው።
የተባረከ ኃይል እንጂ የተረገመ ኃይል አይደለም - የዕውቀትና የጥበብ መንገድ።
እግረ መንገዱን ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ጸጋዎችን ያበረክታል። አርአያነቱን በማየት ገሚሶቹ ወደ ጠፈር የመብረር ዐቅም ያገኛሉ። ለዓለም ሰዎች ሁሉ በሳተላይት የመጠቀም አዲስ ዕድል ይፈጥራሉ።
የዕውቀትና የጥበብ መንገድ በሌሎች ሰዎች ላይ ጉልበቱን ለማሳየትና ገዢ ኃይል ለመሆን አይሻም። ሰዎች ፈልገውት ይመጣሉ። ዕውቀቱንና ሐሳቡን ያከብራሉ።
እርስ በርስ ተፈቃቅደው ይማማራሉ፣ ተከባብረው ይደጋገፋሉ እንጂ ባሪያና ገዢ አይሆኑም።
ጥቂት የፍልስፍና ሐሳቦችና የፖለቲካ መርሖች የእልፍ ሰዎችን ቀልብ ይገዛሉ፤ ሚሊዮን ሰዎችን ሊያነቃንቅ የሚችል ኃይል ያመነጫሉ። ከዚያም ወደ ሕገ መንግሥት አንቀጾች እየተተረጎሙ ለመላው ዓለም የነጻነት ፋና ይሆናሉ። ቢሊዮኖች በየፊናቸው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ሰፊ የነጻነት ዕድል ያገኛሉ። የዕውቀትና የጥበብ መንገድ እጅግ የተባረከ ተአምረኛ ኃይል ነው።
በአቋራጭ እሄዳለሁ ብሎ ራሱን ያጣመመ ሰውስ? ሕይወትን የሚያጠፋ የተረገመ ኃይል እንጂ ሕይወትን አክብሮ የሚያለመልም የተባረከ ኃይል አይኖረውም።
“የሥልጣን ጥመኛ፣ ጸብ ፈላጊ ወራሪ ጦረኛ ይሆናል። ሕዝብን አሰልፎ ያዘምታል። በሰበብ አስባቡ ይማግዳቸዋል። (“ዐዋቂ ስለሆንኩ ሕዝብ ይሰማኛል፤ ይከተለኛል። አቻ ያልተገኘልኝ ጥበበኛና ወደር የለሽ ጀግና ነኝ” ለማለት ነው ፍላጎቱ)።
የራሱን ሕይወት ጠብቆ የሌላውንም ሰው ሕይወት አክብሮ በሰላም መኖር አያረካውም። የሰፈር ዱርዬ ወይም የአገር መሪ ሊሆን ይችላል። የሥልጣን ጥመኛ ከሆነ፣ መከባበር አይጥመውም። በመንደርም ሆነ በአገር፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሰዎች ላይ አዛዥና አናዛዥ ለመሆን ይመኛል።
በሰዎች ሕይወትና ሰብዕና ላይ፣ በሰዎች ኑሮና ንብረት ላይ፣ በሰዎች ሐሳብና ዓላማ ላይ ዘው ብሎ እየገባ እንዳሰኘው የማዘዝ ሥልጣን ለማግኘት ይጎመጃል።
ኃያልነት ማለት ሰዎችን የማታለል ብልጠትና የመርገጥ ጉልበት ነው ብሎ ያስባል።
ትንሽ ሥልጣን አግኝቶ እልፍ ሰዎችን መኮርኮም ይጀምራል። ግን አያረካውም። ከእግሩ ስር ተደፍተው በላያቸው ላይ ካልተረማመደ የሥልጣን ትርጉም ይጠፋበታል። ይሄም አያጠግበውም። ሚሊዮኖችን መርገጥ ያምረዋል። ዐሳራቸውን ያበላቸዋል። ከአፈር ጋር ይቀላቅላቸዋል።
ገደብ በሌለው ሥልጣንና በጦር መሳሪያ ብዛት አገሬውን ከዳር እስከ ዳር ስለጨፈለቀና ስላስጨነቀ፣ ሚሊዮን ሰዎች ስለፈሩትና ስለታዘዙለት፣ እንደ ዐዋቂ ተሰሚነትን ያገኘ፣ በጥበብ የመጠቀና ታላቅ ክብር የተቀዳጀ ይመስለዋል።
ተወዳጅ ለመሆን እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። በሕዝብ ከተወደደ በኋላም ግን ይጨንቀዋል። የሚያደርገውን ያሳጣዋል።
በአንድ በኩል የሕዝብ ፍቅር ለማግኘት ይሟሟታል። ሕዝብን ዘወትር ይሸነግላል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብ ላይ እንዳሻው ሥልጣኑን ለማሳየት ይጨክናል።
ተወዳጅነቱን በየዕለቱ ለማረጋገጥ ሕዝብን ይፈታተናል። የሚያስቆጡ በደሎችን ይሰራል። የሕዝቡ ታማኝነት እንደማያወላውል ማየት አለብኝ ብሎ በየዕለቱ የባሰ ግፍ ይፈጽምባቸዋል። እንዲያጨበጭቡ፣ በጽናት እንዲደግፉት፣ ያለማመንታት እንዲታዘዙለት ያስጨንቃቸዋል።
በሁሉም ነገር ላይ ዐዋቂ ነኝ ብሎ እንደመጣለት ይናገራል። ውሸት ያወራል። እውነትን ለመናገር በነጻነት ለመተንፈስ የሚደፍር ሰው እንዳይኖር ይፈልጋል። ሁሉም ሰዎች አፋቸውን ይዘው እንዲሰሙት ብቻ ሳይሆን፣ አሜን ብለው ንግግሩን እንዲያጸድቁለት ንጉሡ ይጠብቃል።
‘የሥልጣን ጥም’ በንጉሦች ወይም በፖለቲከኞች ላይ ብቻ የሰፈረ ልክፍት አይደለም።
አገር ምድሩ ላይ የገነነ ገዢ ንጉሠ ነገሥት ወይም አንዲት ጉብታ ላይ የመሸገ ሽፍታ ሊሆን ይችላል።
ከአባቱ ዘውድ ለመቀማት የጎመጀ የንጉሥ ልጅ አልጋ ወራሽ ሊሆን ይችላል።
የዓመፅ ጊዜ ጠብቆ በግርግር ሥልጣን ለመያዝ የሚያሤር የቤተ መንግሥት ቤተኛ፣ አልያም በሽምቅ ውጊያ ሥልጣን ላይ ለመውጣት አገርን የሚያሸብር ‘ተስፈኛ’ ሊሆን ይችላል።
የትርፍ ሰዓት አጫፋሪዎችም አሉ። ፖለቲካ እንደ ቁማርና እንደ ድራማ ሆኖ የሚታያቸው ሰዎችም በሥልጣን ሽሚያው ውስጥ ይራኮቱበታል። አንዳንዶቹ እስከ ፒኤችዲ የተማሩ ናቸው። ነገር ግን የተማሩትን አይመረምሩም። ስህተትንና ትክክልን እየለዩ አያገናዝቡም። እንደ ቁም ነገርና እንደ ዕውቀት አይቆጥሩትም። ‘መማር ለዕውቀት ሳይሆን ለብልጠት’ ይመስላቸዋል። በሌላ ወገን ደግሞ፣ ለትምህርት ቅንጣት ጊዜና ክብር የማይሰጡ ይሉኝታ ቢስ ጋጠወጦች አሉ።
አመቺ ዘመን መጣልን ብለው የሚያስቡ ብልጦችና ጋጠወጦች፣ ከመኖሪያ ቤት ሳይወጡ፣ ከተጋደሙበት ፍራሽ መነሣት ሳያስፈልጋቸው፣ ከባርሕ ማዶም ጭምር በትርፍ ሰዓታቸው የፖለቲካ ቁማር አዳማቂ ይሆናሉ። አንጋሽና አውራጅ፣ ሿሚና ሻሪ ለመሆን የሚቋምጡ ‘የኢንተርኔት አስጨፋሪዎችና አስለቃሾች’ ሞልቷል።
የሥልጣን ጥም የተጠናወታቸው ሰዎች የኑሮ ደረጃቸውና ዐቅማቸው ቢለያይም፣ በአንድ ነገር ይመሳሰላሉ።
ከንጉሥ እስከ አሰስና ገሠሥ ድረስ ነው - ልዩነታቸው።
ነገር ግን በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ የማዘዝ ረሀብ አለባቸው።
በሰው ንብረት ላይ ማዘዝ ማለት፣ በምቀኝነት የሰዎችን ቤትና ንብረት ማውደም፣ በስግብግብነት መዝረፍ ወይም ከአንዱ ነጥቆ ለሌላ መስጠት ሊሆን ይችላል።
በሰው ሕይወት ላይ ማዘዝ ማለት፣ ሰዎችን በውሸት መወንጀልና ስም ማጉደፍ፣ ማሰርና ማገት፣ መጥለፍና በባርነት ማዋረድ፣ መደብደብና መግደልን ሁሉ ይጨምራል።
ጥቃቱ የሚመጣው በቀጥታ ከፈጻሚው በአካልና በቅርበት ሊሆን ይችላል። ከሩቅ ሆኖ ሌሎች ሰዎችን በመቀስቀስ ወይም በማሰማራት ሊሆን ይችላል።
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ‘ሰጪና ከልካይ’ ቢሆን ይመኛል። እሱ እንዳሻው የሚዘውራቸው መጫወቻ እንዲሆኑለት ይፈልጋል።
ረሀቡ…
ሰዎች በገዛ ሕይወታቸውና ንብረታቸው ላይ ሥልጣን እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። ሰው የመሆን ብቃታቸውን ለማምከንና ለማኮላሸት ነው ጉጉቱ። በሌላ አነጋገር…
የሥልጣን ጥም ማለት የማጥፋት ጥም ማለት ነው።
በስብከትም ይሁን በዐዋጅ፣ በስድብም ይሁን በሚሳዬል፣ በንግሥናም ይሁን በሽፍትነት፣ በጦር ሜዳም ይሁን በኢንተርኔት… የስልጣን ጥመኛ ሁሉ እንደየዐቅሙ ሰዎችን እያቧደነ ተከታይ ሕዝብ እንዲበዛለት ይስገበገባል። አይጦችን ለማጥመድ እንደቋመጠ ቀበሮ የሕዝብን ስሜት ለማሾር ይቅለበለባል።
ንጉሥም ይሁን ሽፍታ፣ አወዳሽ አስጨፋሪም ሆነ ሙሾ አውራጅ፣… አድማጮቹና ተከታዮቹ… በስሜት እስኪጦዙ ድረስ፣ ሌሎች ዜጎችም እስኪደነዝዙ ድረስ በፕሮፓጋንዳ ወይም በአልቧልታ ዘወትር ይነዘንዛቸዋል። በአፈናና በእስር ወይም በስድብና በማስፈራሪያ ዝም ያሰኛቸዋል። ከቻለም ያዘምራቸዋል።
ወሮበላ (በመደለያ ይዘርፋል)፡
በጥበብና በትጋት ኑሮን ማሻሻል፣ ሀብት ማፍራትና ባለጸጋ መሆን ተገቢ ነው። ገበያ ይደራለታል። በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ ይሆናል። ሰዎችን መርዳትና መለገስም ይችላል።
በአቋራጭ ልሂድ ብሎ ከተጣመመ ግን…
በአንድ በኩል፣ በአቋራጭ አየር ባየር የሚመጣ ሀብት ለማግኘት ይመኛል። ገንዘብ ብቻ እየታየው ከአምራች ዜጎች እየዘረፈ ያግበሰብሳል። (ስኬታማና ፍሬያማ ነኝ ለማለት ነው ምኞቱ)። የሰዎችን ምርት ነጥቆ ሲወስድ፣ የምርታማነት ክብራቸውንም እንደወረሰ ይቆጥረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ገንዘብ የኃጢአት ሥር ናት” ብሎ የሰብካል። በትጋት የተገኘ ሀብትን በጭፍን እያወገዘ ያወድማል። የግል ንብረትንና ገንዘብን ሁሉ እያንቋሸሸ ይዘርፋል። ገንዘብ እያተመ ይከምራል።
ለጋስነት ማለት ከአምራቾች ቀምቶ ለሌሎች መስጠት ይመስለዋል። ‘ድሆችን ለማብላት አገርን ለማልማት’ እያለ ይናገራል። ተመሳሳይ የመደለያ ሰበቦችን እየፈጠረ ሁሉንም ያራቁታል፤ አገርን ያደኸያል።
ነውረኛ (በማስመሰያ ያዋርዳል)፡
ብቃቱን ያስመሰከረና በትጋት ለውጤት የደረሰ ሰው፣ መንገዱ ቀና ነው። በስራው ከብሯልና ሰዎች ቢያደንቁትና ቢያከብሩት፣ ቢያፈቅሩትና በአርአያነት ቢከተሉት ተገቢ ነው።
ጠማማ ጉራንጉር ውስጥ ልግባ ካለስ?
ያለ አጨብጫቢ በሰላም ማደር የማይችል አስመሳይ ጉረኛ ይሆናል። ወይም ደግሞ…
“ሰው ከንቱ መናኛ ፍጡር መሆኑን እመኑ” የሚል ፈሊጥ ያመጣል። ሁሉም ሰው ዐንገቱን እንዲደፋ የሚሰብክና የሚኮረኩም ምቀኛ ይሆናል።
ሁሉንም ለወሲብ የሚጎትት ክብረ ቢስ እንስሳ ወይም…
ወሲብን በጭፍን የሚያወግዝ ፍቅር አልባ ብኩን ወገኛ ሰው ይሆናል።
የፍቅርና የወሲብ በረከቶች እንደ ውጤትና እንደ ሽልማት ናቸው። ከማዕርግና ከሽልማት በፊት ‘ብቃት’ ይቀድማል። ከሜዳሊያ በፊት፣ ‘በብልኀት የተገነባ የሩጫ ብቃት’ መኖር አለበት። ብቃትም በጥረት ወደ ውጤት ይገሰግሳል፤ ማዕርግና ሜዳሊያም ይህን ተከትለው ይመጣሉ።
ለሰው ተፈጥሮ የሚመጥኑ የፍቅርና የወሲብ በረከቶችስ? የእኔነት መንፈስንና የማንነት ክብርን በመገንባት የሚገኙ አስደሳች ውጤቶችና ሽልማቶች ናቸው።
ብቃት-አልባው ክብረ-ቢሱ ሰውዬ ግን፣ የሜዳሊያ ዐይነቶችን በባዶና በአቋራጭ እየሰበሰበ ቢያንጠለጥል፣ የብቃት ባለቤት የሚሆን ይመስለዋል። በጉልበትና በብልጠት ብዙዎችን ጎትቶ ዐልጋ ላይ ሲዘርር፣ የእኔነት መንፈስና የማንነት ክብር የሚያገኝ፣ የሕይወት ጣዕም የሚሆንለት ይመስለዋል።
እንዲያ የሚቅበዘበዘው ለምን ይሆን? ነፍስ አለኝ፤ አፍቃሪ ነኝ ብሎ ራሱን ለማሳመን ነው ፍላጎቱ። የተከበርኩ አስደናቂና ተፈቃሪ ሰው ነኝ ለማለትም ነው ልፋቱ። መቅበዝበዙ ግን ይመሰክርበታል እንጂ አይመሰክርለትም።
ሌሎችን እያዋረደ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ይደክማል። ሌሎችን በመስደብ ራሱን የሚያሞግስ፣ የሌሎችን ማዕርግ በመሻር ራሱን የሚክብ፣ የሌሎችን ሜዳሊያ ስለወሰደና ሽልማታቸውን ስለነፈገ ልዕልናን የሚቀዳጅና የሚያምርበት ይመስለዋል።
በእርግጥ ሦስቱ ጠማማ መንገዶች፣ ንጉሦችን ለይተው የሚያጠቁ የሥነ ምግባር ብልሽቶች አይደሉም። በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሠቱ የሚችሉ የስህተትና የስንፍና፣ የጥፋትና የክፋት መንገዶች ናቸው።
በንጉሥ ላይ ከተከሠቱ ወይም በመንግሥት ባለሥልጣናትና በፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ከተለመዱ ግን፣ ጉዳታቸው እጅግ ይበዛል። ከሥነ ምግባር ብልሽት ባሻገር፣ የፍትሕ ፀር የባርነት ቀንበር ይሆናሉ። አደጋቸው ቀላል አይደለም። እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ሙሴ ለተከታዮቹ መናገሩም፣ ዐዋቂነቱንና ጥበበኛነቱን ያመለክታል።
የሚነጋ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ይነጋ ነበር ጭብጦዬን ስጡኝና ልብላ
አንድ የአረቦች ጥንታዊ ተረት አለ፡፡
አንድ እጅግ በጣም የናጠጠ የሀብታም ቤተሰብ ውስጥ የተወለደ ልጅ ነበር፡፡ ወላጆቹ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ አድርገው ያሞላቅቁታል፡፡ እሱ ጠይቆ እምቢ የሚባል ምንም ነገር የለም፡፡ ‘ግመሎች ግዙልኝ’ ሲል በመቶ የሚቆጠሩ ግመሎች ወዲያው ተገዝተው ይቀርቡለታል፡፡ ‘የምኖርበት ቤት ሰለቸኝ’ ሲል ሌላ ግቢ፤ ሌላ ህንፃ መገንባት ይጀመራል፡፡ ‘አጫዋች ይለወጥልኝ’ ሲል ያገሩ ድንክዬ ተሰብስቦ በል ከነዚህ መካከል ምረጥ ይባልና የፈለገው ድንክዬ ይቀጠርለታል፡፡ ት/ቤት ሄዶ አስተማሪ ካልተስማማው ያ አስተማሪ ወዲያውኑ ከዚያ ክፍል ይቀየርና ሌላ አስተማሪ ይመጣለታል፡፡
ልጁ እያደገ ሲመጣ የአውሬ አደን ያፈቅራል፡፡ አንድ ቀን አደን እንሂድ ይልና የቤቱን ባሪያዎች በሙሉ ወደ ጫካ ይዞ ይሄዳል፡፡ ከዚያም
“በየአቅጣጫው ሄዳችሁ አድኑ፡፡ ከዚያም የገደላችሁትን አውሬ ወደዚህ ይዛችሁ ኑ፡፡ ብዙ አውሬ ላመጣ ጀግና አባቴ እንዲሸልመው አደርጋለሁ፡፡” ይላል፡፡ ሁሉም ይሰማራሉ፡፡ ልጁም ማደኑን ይቀጥላል፡፡ በመካከል አንድ ዱኩላ ከሩቅ ይመለከታል፡፡ ልጁ ያነጣጥራል፡፡ እንደአጋጣሚ ግን ዱኩላው ከሌላ አቅጣጫ በተተኮሰ ጥይት ይመታና ይወድቃል፡፡ ድኩላውን የገደለው ከባሪያዎቹ አንዱ ኖሯል፡፡ ግዳዩን ተሸክሞ ይዞ ሊያስቆጥር ይመጣል፡፡ በእለቱ ብዙ አውሬዎች ከገደሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ነባር ባሪያ ነው፡፡ የሀብታሙ ልጅ ግን እጅግ ብግን ብሎ ተናዶ ከዚያ ጫካ ወጥቶ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄዷል፡፡
ሁኔታው ግር ያላቸው ባሪያዎችም የገደሏቸውን አውሬዎች ተሸክመው ወደ ቤት ተመለሱ፡፡
የልጁ አባት አራስ - ነብር ሆነው ነው የጠበቋቸው፡፡ ባሪያዎቹ ገና እንደተመለሱ፤
“ለመሆኑ ከመካከላችሁ ድኩላ የገደለ ባሪያ ማነው?”
ዱኩላውን የገደለው ባሪያ ከመቀመጫው ተነስቶ፤
“እኔ ነኝ ጌታዬ ሆይ” አለ፡፡
ጌትዬውም፤
“ለመሆኑ ምናባክ ቆርጦህ ነው ልጄ ያነጣጠረበትን ዱኩላ የገደልከው?”
ባሪያው - “አይ ጌታዬ፤ የጌታዬ ልጅ ማነጣጠሩን አላየሁም፡፡ ለዚያም ‘በጫካው በየአቅጣጫው ተሰማሩና ብዙ የገደለ ይሸለማል’ ብሎ የጌታዬ ልጅ በሰጠን ትእዛዝ መሰረት ሁላችንም እየተሻማን ግዳይ ስንጥል ነበር የቆየነው፡፡”
ጌትዬው - “ቢሆንስ ታዲያ እርስ በርሳችሁ ተሻምታችሁ ግደሉ አለ እንጂ እሱ ያነጣጠረበትን ግደል ተብለሀል? ለመቀጣጫ 60 ጅራፍ ትገረፋለህ!”
ያም ባሪያ ሰው ሁሉ በተሰበሰበበት በዚያ ሞራ በጠጣ ጅራፍ ጀርባው እስኪላጥ ተገረፈ፡፡ ከዚያ በኋላም ጌታው እንዲህ አለው፤ “በል አሁን ለባሪያ ጓደኞችህ ከዚህ የጅራፍ ግርፍ ምን ትምህርት እንዳገኘህ ንገራቸው፡፡”
ባሪያውም፤ “ወንድሞቼ ሆይ፤ ለሁለተኛው ጌታችሁ ያነጣጠረበትን ኢላማ ሳታውቁ፤ በጭራሽ አደን እንዳትጀምሩ!!”
***
እኔ ብቻ ካላደረግሁት አይጥመኝም የሚል ጌታ አያድርስ፡፡
አለቃና ምንዝር፣ መሪና ተመሪ፣ አዛዥና ታዛዥ፣ ጠርናፊና ተጠርናፊ ልብ ለልብ የማይተዋወቁበት ስርዓት ብዙ ጥፋት ያደርሳል፡፡ በተለይም ኃላፊው እንደሀብታሙ ልጅ (የባለቤቱ ልጅ እንዲሉ) የጠየቀው ሁሉ - የሚፈፀምለትና ያቀደው ዕቅድ ሁሉ ትክክል ነው ይተግበርለት የሚባልለት ከሆነ፣ ዕቅዶች፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች የበጎ ፈቃድ ውጤት እንጂ ተጨባጩንና ነባራዊውን ሁኔታ መሰረት ያደረጉ አይሆኑም፡፡ በተለይ የበላዬ ያነጣጠረውን ያላወቀ የበታች ሰው ወዮለት! መልካም ሰርቶ ምስጋናን ቢጠብቅ ጅራፍ ራቱ ነውና ጀርባውም ልቡም ይደማል፡፡ ከንቱ ምኞት ብቻ ነው ቀሪ ሃብቱ፡፡ አቅም የሌለው ሎሌ ቀና ሀሳብ ይዞ ቢነሳ ጌታህን ተጋፋህ ነው የሚባለው፡፡ መሪው ያቀደውን ሳይገነዘብ ተመሪው ኢላማ ላልም ቢል ዳር የማይደርስበት ስዓት ውስጥ የእውር የድንብሩን የሚጓዝ ነው፡፡ መደማመጥና መረዳዳት ያለበት ሥርዓት አይሆንለትም፡፡ ግንኙነቱም “የባለቤቱ ልጅ” ያለው የሚደመጥበትና የሚሰራበት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ “ከጅራፉ ግርፍ ምን እንማራለን?” ከመባባል የታሪክ ምፀት በቀር ለሀገር ፋዳ ያለው ተግባር ለማከናወን አያስችልም፡፡
ከቶውንም የራሱን አቅም በአግባብ ሳይለካ “ትላልቅ ራዕዮች አሉኝ” የሚል ኃላፊ፣ አለቃ ወይም ማንኛውም የፖለቲካ መሪ፣ “መርፌ በቂጡ ያለውን ክር የሚጎትትበት አቅም ሳይኖረው ጨርቅ ለመውጋት ወደፊት ይገሰግሳል” የተባለው ዓይነት ነው፡፡ ከራዕዩ ጋር ሙጭጭ ቢል ከነራዕዩ ይሞታታል እንጂ ግዘፍ - የነሳ ተግባር ለማየት አይበቃም፡፡
የስራ ግንኙነቶች የመርህ ሳይሆኑ የአዛዥና የታዛዥ፣ “የገምጋሚ” እና “ተገምጋሚ” በሆኑበት አሰራር የተሰናሰለና የተቀናጀ የስራ ውጤት ይኖራል ብሎ መጠበቅ ከንቱ ድካም ነው፡፡ የበላዩ ሰው በልቡ ምን እንዳሰበ ሳይናገር፣ የላዕላይ - መዋቅሩ ቡድን የሚያወርደው ትዕዛዝ የደባ ያህል በሚስጥር የሚፈበርከው ከሆነ በአፈፃፀሙ ሰፈር ላይ ሽብር እንደሚፈጥር ግልጥ ነው፡፡ የበለጠ መከፋፈል የበለጠ አንጃ ይብስ የመሰነጣጠቅ አጋር የሚፈጥረው ግልጽነት - አልባ የሆነ የደባ ዳቦ ነው፡፡ የድብቅ አስራር ለህቡዕ ፓርቲ እንጂ ፀሀይ ለሚሞቅ ግብር (over-ground activity)፣ ለቢሮክራሲያዊ ተቋም፣ ለኮሚሽን ወይም ለንግድ ድርጅት የሚፈይደው ነገር ከአፍ የወደቀችን ፍሬም አያህል፡፡ ግልጽነት የሰፈነበት ስርዓት ለመመስረትና መልካም አስተዳደርን (Good Governance) ለማምጣት የማሴርንና የማድባትን ባህል ማስወገድ ዋና ስራ ነው፡፡ የባለቤቱ ልጅ ነኝና እኔ ያልኩትና ለብቻዬ ያነጣጠርኩት ኢላማ ይበቃል ማለትን ማስወገድም ሌላኛው ዋና ስራ ነው፡፡ የተቧድኖ ምስጠራን (Group Conspiracy) ማስወገድ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ (ቢያንስ ጊዜው አልፎበታል፡፡)
“ብልት በሰራው ጥፋት ፍሬ ይቆረጣል” ይሏልና ኃላፊዎችና ዋና ዋና የተባሉ የፖለቲካ ሰዎች ባጠፉት ምንዝሮችና ዜጎች በግምገማም ሆነ በአማን-ዘራፍ መቀጥቀጥ የለባቸውም፡፡ ዝቅ ብሎ በቅርብ በሚሰራው ሥራ፣ ከፍ ብሎም በአገር ደረጃ በሚከናወነው ተግባር በዓይነተኛ ሁኔታ የሚበደሉት ጉዳዩ የማያገባቸው ከነገሩ ጦም እደሩና ጎመን በጤናን የሚያዘወትሩ ናቸው፡፡ በታሪክ የሚታየውም ይሄው ሀቅ ነበር፡፡
የማይቀርን ነገር ማወቅና የራስን አካሄድ ከመመዘን እንጂ ባላውቅ ይሻላል ብሎ መሸሽ ከቶም ግብዝነት ነው፡፡ ቢያንስ ራሷን አሸዋ ውስጥ ከደበቀችው ሰጎን የተሻለ ዘዴ ይጠበቅብናል፡፡ የምሁራን ሰፈር የእውቀት አምባ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የራሱን አገር ምሁራን የማያከብር አገር ከሌላ አገር ሊቃውንት ጋር ስለ ትምህርት ማሻሻያና ስለ አገር ብልጽግና ቢፈራረም፣ ከስር እየናደ ከላይ ይቆልላል የተባለው ዓይነት መሆኑ ነው ትርፉ፡፡ እርስ በርስ የማይተማመን አመራር በየስብሰባው ከመማማልና “ቃለ-ጉባኤ ድረሽ” ከማለት በቀር ለሀገር የበሰለ ገበታ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ ለየራስ ጎጆ መውጫ ሙስናዊ ድርጎ ከመሰብሰብ በቀር፡፡ ይልቁንም ዓለም አቀፉን ሂደት በሚገባል አለማጤን፣ “ላም የሰጠኝ ወተቱንም ይለብልኝ” ብሎ እጅን መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ “ላይቀርልሽ ታጥበሽ ታጥነሽ በጠበቅሽ” እንዲሉ ከመደረግ የማይቀሩ ነገሮችን ሲሆኑ ከመጮህና ደንበር-ገተር ከማለት ከወዲሁ የማሰብና የመምከርን ጠቀሜታ አለማስተዋል አገርና ህዝብን ያጎሳቁላል፡፡ የተሻለ ነገር ይቀጫል፡፡ በሰፊ ምኞት ባህር ከመዋዠቅ በተጨባጭ የሚዳሰስ የሚነካውን ነገር አዳምጦ አጢኖ ይዞ መገኘት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
“የሚነጋ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ይነጋ ነበር ጭብጦዬን ስጡኝና ልብላ” ብሎ እቅጩን ተናግሮ በጊዜ ተገቢው ቦታ ማደር ለሀገርና ለህዝብ ታላቅ ፋይዳ ያለው ቁም ነገር መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡
”መርካቶን በሚሊኒየም” የአውዳመት የንግድ ባዛር በይፋ ተከፈተ
• ለ500 ኢትዮጵያውያን ማዕድ የማጋራት ሥነስርዓት ተካሂዷል
በባሮክ ኤቨንት ኦርጋናይዘር የተዘጋጀው “መርካቶን በሚሊኒየም” የአዲስ ዓመት የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ዛሬ ተሲያት 9 ሰዓት ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፍቷል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ለ17 ቀናት የሚዘልቀው የንግድ ባዛር፤ ለሸማቹ ማህበረሰብ መሰረታዊና የበዓል ፍጆታዎች በስፋትና በቅናሽ የሚቀርብበት መድረክ ነው ተብሏል፡፡
“ይዝናኑ ይሸምቱ“ በሚል መርህ በሚካሄደው በዚህ የአውዳመት የንግድ ባዛር ላይ፣ የ40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
ዛሬ በተከፈተው “መርካቶን በሚሊኒየም” የአዲስ ዓመት የንግድ ባዛር ላይ፣ በርካታ የአገር ውስጥና የባህርማዶ አምራቾች፣ አስመጭና ላኪዎች እንዲሁም ጅምላ አከፋፋይና ችርቻሮ ነጋዴዎች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡
አዘጋጆቹ ባወጡት መግለጫ፤ ይሄ ታላቅ የአውዳመት የንግድ ትርኢት፤ ነጋዴዎች ለሸማቹ እጅግ ቅናሽ በሆነ ዋጋ ጥራት ያላቸው ፍጆታዎችን በሰፊ አማራጭና ዓይነት የሚሸጡበት፣ ሻጭና ገዥ በአንድ ቦታ ላይ የሚገበያዩበት፤ እንዲሁም መሰረታዊና የበዓል ፍጆታዎች በስፋት የሚቀርቡበት ይሆናል ብለዋል፡፡
እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ለተከታታይ ቀናት የሚዘልቀው የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ፣ ትርፍን ብቻ ታላሚ አድርጎ የተዘጋጀ አይደለም የተባለ ሲሆን፤ ዛሬም በይፋ የተከፈተው ባልተለመደ መልኩ 500 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ማዕድ በማጋራት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ 15 የሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሥራቸውንና ዓላማቸውን ለህብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበት ቦታ በዚሁ በሚሊኒየም አዳራሽ በነጻ እንደተሰጣቸው የባዛሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በንግድ ባዛሩ መክፈቻ ላይ በተከናወነው ማዕድ የማጋራት ሥነስርዓት፣ ከተለያዩ የከተማዋ ወረዳዎች ለተውጣጡ 500 ያህል ግለሰቦች ዘይት፣ ዱቄትና እንቁላል የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ለዝግጅቱ የወጣውን ወጪ እናት ባንክና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ተቋማት እንደሸፈኑት ተነግሯል፡፡
“መርካቶን በሚሊኒየም” የንግድ ባዛር፣ የተለያዩ ምርቶችና የበዓል ፍጆታዎች ለሽያጭ የሚቀርቡበት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ የሚዝናናበትም መድረክ ነው ያሉት አዘጋጆቹ፤ ለዚህም ታዋቂና ተወዳጅ ድምጻውያን የሚያቀነቅኑበት የሙዚቃ ድግስ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡