Administrator

Administrator

Sunday, 27 June 2021 18:46

“ከስክሪኑ ጀርባ”

መፅሐፍ ለንባብ በቃ
በዘመነ ኢህአዴግ (ህወሃት) ዘመን በተለይም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የነበረውን አስቸጋሪ ወቅት ከህዝብ ወገንተኝነት ይልቅ ለአንድ ፓርቲ ሲያገለግል ነበር ያለውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ይህንን ሲያስፈፅሙ የነበሩ ባለሙያዎችን የሚዘረዝረውና በዚህ ውጥረት ውስጥ ሆነው የሙያ ስነ-ምግባራቸውን በመጠበቅ በከባድ ፈተና ውስጥ የነበሩትን ታማኝ የኢትዮጵያ ልጆች ገድል የሚቃኘው “ከስክሪኑ ጀርባ” (ከኢቲቪ ጋዜጠኛው አንደበት) የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ በወቅቱ የደረሰውን አጠቃላይ ቀውስና ችግር ወደጎን በመተው ቴሌቪዥኑ ለመንግስት በማጎብደድ አገራዊ ሚናውን ባመወጣቱ ቁጭት አድሮበት ለታሪክ እንዲቀመጥ ሲል የኢቲቪ ጋዜጠኛው አለኝታ ኢዮኤል መፅሐፉን ለመጻፍ መነሳቱንና መታሰቢያቱም በኢትዮጵያ ብሮድካስንግ ኮርፖለሬሽን በታማኝነት ሲያገለግሉ ለነበሩ ተገፍተው፣ ተባረውም ሆነ በራሳቸው ጊዜ ከተቋሙ ለለቀቁ፣ በሀገርም ሆነ በውጪ ላሉና አሁንም በፅናት እያገለገሉ ላሉ ሰራተኞች መደረጉን ጋዜጠኛው በመግቢያቸው አስፍረዋል፡፡ “ግርሻው፣ “ካድሬያዊነትና የሙያ ውድቀት”፣ “ብሄራዊ ንቅዘት”፣ የ”አቶ መለሰ እረፍትና የኢህአዴግ የጭንቀት ጊዜ”፣ “ድህረ መለስ”እና “እንባና ሳቅ” በሚሉ ስድስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ179 ገጽ የተመጠነው መፅሐፉ ፣ በ120 ብር እና በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 - በቢዝነስ ፕሮጀክት የጥቁር ህዝብን ክብር ማስመለስ እንችላለን
- “ፐርፐዝ ብላክ” ፕሮጀክት በ54ቱም የአፍሪካ አገራት ይጀመራል
- “የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” አክስዮን ሽያጭ ሃምሌ 17 ይጀምራል
 
 ላለፉት 10 ዓመታት በአሜሪካ የስደት ህይወት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ፤ ከጥቂት ሳምንት በፊት አዲስ የቢዝነስ ፕሮጀክት ይዘው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የጥቁር ህዝቦችን መብትና ክብር ለማስመለስ ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ሳይሆን የጥቁሮችን የኢኮኖሚ አቅም ማጠናከር ነው የሚሉት ዶ/ር ፍስሃ፤ ይሄን ለማሳካትም #ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ;የተሰኘ አዲስ ኩባንያ በኢትዮጵያ  መመሥረታቸውን፡፡ የኩባንያው የአክስዮን ሽያጭም ሃምሌ 17 እንደሚጀምር ዶ/ር ፍስሃ አስታውቀዋል፡፡   
በአገሪቱ የመጀመሪያውን የግል ኮሌጅ-ዩኒቲ- ያቋቋሙት ዶ/ር ፍስሃ፤ የመጀመሪያውን የግል ዕለታዊ ጋዜጣ በመጀመርም ስማቸው ይነሳል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ድርጅቶቻቸውን ሁሉ ሸጠው ወደ አሜሪካ የተሰደዱት ዶ/ር ፍስሃ፤ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ አገራቸው የተመለሱት፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ዶ/ር ፍስሃ ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-  


         የዛሬ 10 ዓመት ምን ቢያጋጥሞዎ ነው ድርጅትዎን ሸጠው ወደ ባዕድ አገር የተሰደዱት?
እንደሚታወቀው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂው በሀገራችን ገና በማይሞከርበት ጊዜ፣ በኦንላይን በይው በኢ-ኮሜርስ … “ዲጂታል ኢትዮጵያ” በሚል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ነበር። የዛሬ 16 እና 17 ዓመት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ በዩኒቨርስቲው ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ ነበር፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት ስንቀሳቀስ መንገዶች ይዘጋጉብናል፡፡ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ በእኔ ላይ የደረሰው ጫና እንደ ሰው ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፡፡ አስታውሳለሁ “My Fashion” በተሰኘው መፅሔት ውዝግብ ሳቢያ ሁለት ዓመት ሙሉ ነው  ፍርድ ቤት የተመላለስኩት፡፡ ጫናው ሲበዛና በተለይ አንቺ ኢላማ መደረግሽን ስታስቢ ያለሽ ምርጫ ወይ ራስሽን መስዋዕት ማድረግ ነው ወይ ደግም ከድርጅቱ ጋር ተያይዘሽ ገደል መግባቱን ነው፡፡ በዚያን ሰዓት እኔ የመረጥኩት  ተቋማቱን አስተላልፌ መውጣት ነበር፡፡
እርስዎ የቢዝነስ ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አልነበሩም፡፡ ኢላማ የተደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው?
እንዳልሽው እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን የሚገዳደራቸው ሰው ስለማይወዱ እኔ ለእነሱ እብሪተኛ ነኝ፡፡ ይሄ የእነሱ አስተሳሰብ ነው፡፡ የምታስታውሺ ከሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በየቦታው ጭቅጭቅ ከም/ጠቅላይ ሚኒስትሩና  ከተለያዩ የመንግስት ሀላፊዎችም ጋር ውዝግብ ውስጥ ነበርኩ፡፡ በአጠቃላይ ሰዎቹ ስትገዳደሪያቸው አይወዱም ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ ገንዘብ አለሽ ብለው ካሰቡና ደጋፊ ካልሆንሽ ጠላት ነው የምትሆኚው፤ በእነሱ አስተሳሰብ፡፡ ነገር ግን ይህ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ የእነሱ ደጋፊ ካልሆንሽ፣ በየጊዜው የምትግዳደሪያቸው ከሆነና ገንዘብ አለሽ ብለው ካሰቡ አይመቻቸውም፡፡ በሁሉም ነገር መንገድ እየዘጉ እንድትማረሪ ነው የሚያደርጉሽ፡፡ ሌላው ጉቦ እየሰጠ ዝም ብሎ ዲግሪ እያተመ ሲሰጥና ዕድሉ ሲለቀቅለት፣ እኛ ትምህርት ላይ ቀልድ አናውቅም ነበርና እንዴት ያሰቃዩን እንደነበር፤ እኔ ነኝ የማውቀው። የጀመርናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሆን ተብሎ እንዲቆሙ ይደረጉ ነበር፡፡ ትታገሽ ትታገሺና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተስፋ ትቆርጫለሽ፡፡ አገርሽ ራሱ እንዲያስጠላሽ ነው የሚያደርጉት፡፡ በዚህ የተነሳ በቃኝ ብዬ አገሬን ጥዬ ወጣሁ፡፡
እንዴት ነው አዲስ አበባ አልተለወጠችብዎትም?
አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ተቀይራለች። የማውቃቸው ቦታዎች ሁሉ ጠፍተው ሌላ ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ስለመቀየሯ  እዛም ሆነን እንሰማ ነበር፡፡ ሰው ሲነግረን የተጋነነ ነበር የሚመስለን እንጂ በዚህ ደረጃ ተቀይራለች ብለን አናስብም ነበር፡፡ ወደ ዚህ ስመጣ መኪና እነዳለሁ ስላቸው “በፍፁም እንዳትነዳ ትጠፋለህ” ነበር ያሉኝ። ልክ ስገባ እንኳን መኪና ልነዳ ሁሉ ነገር ተቀያይሮ መንገዱንም መለየት አልቻልኩም፡፡ የአዲስ አበባ በዚህ መጠን መቀየር በጣም  ያስደንቃል። ሌሎቹም የሀገራችን ትልልቅ ከተሞች ተቀይረዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
እዚህ ሳሉ አቅደውት ባለማሳካትዎ የሚቆጭዎት ነገር አለ?  
የሚያሰራ ሁኔታ ቢኖርማ፣ ለእኔ 10 ዓመት ብዙ የምሰራበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ይዘን የመጣነው የኢ-ኮሜርስ ስራ እኮ የዛሬ 17 ዓመት እዚህ ጀምረነው ነበር፡፡ አስቢው አማዞን  ሥራ ከጀመረ 20 ዓመቱ ነው፤ ዛሬ የ1ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ነው። የኦንላይን ትምህርት አሁን ተስፋፍቷል፡፡ እኛ ከ16 ዓመት በፊት ስንጀምረው ማንም እዚህ አገር አያውቀውም ነበር፡፡ የኦንላይን ትምህርቱን ያን ጊዜ እንደ ጀመርነው የሚያሰራን ሁኔታ ተፈጥሮና ድጋፍ አግኝተን ቢሆን ኖር፣ አሁን ላይ ከቡና ያልተናነሰ ገቢ ያስገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኛ በዚያን ሰዓት ከዓለም ዙሪያ በሙሉ በሶስት ዲግሪ ፕሮግራሞች ማለትም በኢኖሚክስ፣ በዚዝነስ አድሚንስትሬሽንና (አንዱ በማርኬቲንግ ይመስለኛል) በኦንላይን ትምህርት ተማሪ ተቀብለን ነበር፡፡ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያለው ቢሯችን በሙሉ በአይቲ ቴክኖሎጂና በሙያተኞች የተደራጀ ነበር፡፡ ያንን ኦንላይን ትምህርት ሲከለክሉን ነው እንደገና ወደ ኖርማሉ ያዞርነው፡፡ ያንን “ዲጂታል ኢትዮጵያ” ብለን የተነሳንበትን ብንቀጥል ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡
ሌላው “ናሽናል ፔይመንት ጌትዌይ” ብለን የጀመርነውም ያን ጊዜ ነበር፡፡ የስልክ የመብራት የውሃና ሌሎች ክፍያዎችን በተቀናጀ መንገድ በኦንላይን እንዲከፈል የማድረግ ስራ የጀመርነው እኛ ነበርን። ያን ጊዜ ተፈቅዶልን ብንቀጥል ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡ “ፓን አፍሪካ ውሜን ኢጁኬሽን” በሚል የሴቶች ፕሮጀክት ጀምረን ብዙ ሂደት ታልፎ፣ 29 የአፍሪካ አገሮች ተስማምተውና ፈርመው ዲዛይኑ ተሰርቶ ወደ ትግበራ ልንገባ ስንል ነው የተከለከልነው፡፡ ያ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኢትዮጵያ ታገኝ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ብዙ ነገር ልቆጥርልሽ እችላለሁ፡፡ እዚህ ብኖር ኖሮ ዛሬ እንደ አዲስ የሚወሩት ነገሮች የዛሬ 15 ዓመት ነበር ስራ ላይ የሚውሉት። ያው ሁሉም የሚሆነው  ግን ፈጣሪ የፈቀደ ጊዜ ነው፡፡ ከሚዲያም ጋር በተገናኘ “ፓን አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ለማቋቋም ብዙ ርቀት ተጉዘን ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ የጋዜጠኛን መብት በማስከበር ቀዳሚው ዩኒቲ ነው፡፡ እነ “ዕለታዊ አዲስ” በሚታተሙበት ወቅት በጋዜጠኛ ደሞዝ ደረጃ ተሰምቶ የማይታወቅ 5 ሺ እና 6 ሺህ ብር ደሞዝ ነበር የምንከፍለው፡፡ እና እዚህ ብኖር ኖሮ፣ የዘረዘርኩልሽ ሁሉ ይተገበር ነበር፡፡ አስር ዓመት የባከነ ጊዜ ነው ለኔ፡፡ የሆኖ ሆኖ አሁንም ተስፋ አልቆረጥንም ፡፡
አሁን ይዘው ስለመጡት አዲስ ፕሮጀክት “ብላክ ፐርፐዝ” ይንገሩኝ እስቲ?  ምንድነው ሀሳቡ?
ወደ ኋላ ሄደን ስንመለከት “ብላክ ፐርፐዝ” የተባለው ፕሮጀክት ዝም ብሎ የተቋቋመ ግንጥል ቢዝነስ አይደለም፡፡ ከቢዝነስ በላይ ነው፡፡ ተልዕኮም ጭምር አለው፡ ዓላማውም ትልቅ ነው፡፡ ለምን ዓላማ ተመሰረተ ካልሽኝ፣ ቁጭት ነው የመሰረተው፤ ጥቁር የመሆን ቁጭት፡፡   እንግዲህ አንድ ሰው በአገሩ ላይ  የቢዝነስ ሰው ሆኖ ካሳለፈ በኋላ ጥሩ ህይወት ከኖረና ብዙ ነገር ካሳለፈ በኋላ አሜሪካ ሲገባ ምንም ነው፤ ያ ሰው በጥቁርነቱ ብቻ በቃ ምንም ነው ምንም!! ያን ሁሉ ትምህርት ተምረሽ ዲግሪ ተሸክመሽ፣ የካበተ የስራ ልምድሽ ሁሉ ገደል ገብቶ መልክሽ ብቻ ማተር የሚያደርግበት አገር ነው አሜሪካ፡፡ አሜሪካ የእኩልነትና የነፃነት ሃገር ነው ይባላል አንጂ ውሸት ነው፡፡ የፖሊስ መኪና ከኋላሽ ሲመጣ ገና ለገና ጥቁር ስለሆንሽ ብቻ  እታሰራለሁ ብለሽ ትፈሪያለሽ፡፡ ብቻ ብዙ ብዙ ነገር አለ። በተለይ ዘረኝነት በአሁኑ ጊዜ በጣም እየባሰ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ብትወስጂ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃው ጥቁሩ ህዝብ ነው፡፡ እንዴት እንደተገለሉ ስታይ፣ በተለይ ከትራምፕ ጋር በተያያዘ የነጮቹ ዘረኝነት ጎልቶ ሲወጣ ስትመለከቺ፣ ይሄ ነገር እስከ መቼ ነው ትያለሽ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስታይው ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጀምሮ በየሀገሩ ሲሰዱ በየባህሩ ሰጥመው ሲቀሩ፣ ሌላውንም ስንመለክት እስከ መቼ ነው አፍሪካ እንደዚህ ሆና የምትቀጥለው የሚለው ጥያቄ እረፍት ይነሳል፡፡ በተለይ እነጩ ባህር ውስጥ ገብቶ ላየውና ጥቁር ለሆነ ሰው ይታወቀዋል፡፡ እዛ አገር ውስጥ ዜግነት እንኳን ብታገኚ እኩል አይደለሽም፡፡
መዝገብ እንኳ ከጠረጴዛ በላይና ከጠረጴዛ በታች እንደሚቀመጥ ነው የሰማሁት…
እውነት ነው፡፡ ይሔ ሁሉ እስከ መቼ የሚለውን ነገር እንድታሰላስይና  እንድትብሰለሰይ ያደርግሻል፡፡ እኔ ለሁለት ዓመት በዚህ ሀሳብ ተጠምጄ ነበር፡፡ እኔ “አንድ ኢትዮጵያ” እንቅስቃሴ ላይ እያለሁ ስናገር የነበረው ከፖለቲካ ይልቅ የሰውን ልጆች ሊቀይር የሚችለው ኢኮኖሚ ነው እያልኩ ነው፡፡ ፖለቲካ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ልብ ካልነው ኢኮኖሚ ፖለቲካውንም ተፅዕኖ ያሳድርበታል፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚ ላይ መተኮር አለበት፡፡ ገንዘብ ካለ ሀይል ይኖርሻል፡፡ ከዚያም ክብርም ይኖርሻል ብዙ ጊዜ ጥቁሮች የሚሄዱበት መንገድ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ነው፡፡  አሜሪካ ውስጥ “black lives matter”  ለብዙ ዓመታት ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ስለዚህ ኢኮኖሚው ላይ ማተኮር ነው ያለብን፡፡ ይህንን ካደረግን ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው በሚል “Black Economy Excellenc” የሚባል ትልቅ ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት ሜይ 2020 ዓ.ም ላይ አቋቋምን፡፡ በኢኮኖሚ መፍትሄ የጥቁሮችን ችግር እንፍታ ጥቁሮችን እናስከብር፣ የጥቁሮችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዓለም ላይ እናረጋግጥ፤ ለውጥ እናምጣ፣ በተለይ ለልጅ ልጆቻችን የኢኮኖሚ ደህንነት ልህቀትን እናምጣ በሚል ቁጭት ነው የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ መፍትሔ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ላይ እናተኩር፤ “ተጠቅተናል እንደዚህ ተደርገናል” እያለን ሌሎችን እየወቀስን ከምንቀጥል ይልቅ በራሳችን ሰርተን ለውጥ እናምጣ፤  ባለን እንመካ የሚል ሃሳብ ነው፡፡
ተመልከቺ ከዓለም ህዝብ 1.3 ቢሊዮኑ ጥቁር ህዝብ ነው ይሄ ቀላል አይደለም። ጥቁር ህዝብ ደግሞ  ምንም የሌለው ደሃ አይደለም፡፡ አሜሪካ ውስጥ ብቻ ጥቁሮች 1.1 ትሪሊየን ዶላር በየዓመቱ ያወጣሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩ ምንድን ነው? ገንዘቡን እናወጣና ለሌላው እናስረክባለን፤ አላወቅንበትም፡፡ የጥቁር ህዝብ ገንዘብ በአንድ ላይ ቢሰባሰብ በዓለም ላይ ምርጥ 10 ከሚባሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ ይሆናል፡፡ ገንዘብ አጥተን አይደለም፤ እንደ አፍሪካ ያለ ትልቅ ሀብት ያለው አህጉርም የለም፡፡ ስለዚህ ለምንድን ነው ደሃ የምንሆነው? ከፈለግን “መብት ስጡን፤እኩል አድርጉን እያልን እየጮኽን መቀጠል እንችላለን፡፡ ከዛ ይልቅ አንደኛ ራሳችን ልንሰራቸው የምንችላቸው ነገሮች ሁሉንም ያካተተ፣ ሁለተኛ ከትንሽነት አስተሳሰብ ወጥተን ሁልጊዜ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማሰብ አለብን፡፡ ምክንያቱም የ1.3 ቢሊዮን ህዝብ እጣ ፈንታ ለመወሰን ትንሽ ፕሮጀክት የትም አያደርስም፡፡ ብልህ በመሆን ብዙ ተሞክረው የሰሩትን ለእኛ በሚመች መልኩ አድርገን መስራትና መተግበር ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ሞዴል ዘርግተናል፡፡
ምን የሚባል ሞዴል ነው የዘረጋችሁት?
“ዘ ግሎባል ብላክ  ኮሌክቲቭ ፐርፔቹዋል ዌልዝ ጀኔሬሽን” ይባላል፡፡ ይህ ማለት ስማርት በሆነ መንገድ በመሄድ የጥቁርን ሀብት ወደ አንድ ቦታ በማምጣት አቅም መገንባት ነው፤ ዋነኛው ጉዳይ፡፡ በዚህ ደግሞ አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን ለማሳካት ይውላል። ይህ በአንድ የተከማቸ ገንዘብ አንደኛ፤ በሚቀጥሉት  15 ዓመታት ውስጥ 1 ቢሊዮን ጥቁር ህዝቦችን ኢምባክት የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መዘርጋት፣ ሁለተኛ በዚህ ሂደት ውስጥ 1 ሚሊዮን ጥቁር ሚሊኒየነሮችን መፍጠር፣ ሶስተኛ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ 1.5 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያለው የጥቁር ህዝብ የጋራ ሀብት መፍጠር ሲሆን አራተኛው ለጥቁር ህዝብ ከራሱ በላይ ሊናገርለት የሚችል ማንም የለም ብለን ስለምናምን የጥቁር ህዝብ ሚዲያ ድርጅት ማቋቋም ነው፡፡ “ብላክ ናሬቲቭ ሚዲያ ኦርጋናይዜሽን” ይባላል፡፡ እነዚህን አራት ግቦች ለማሳካት የሚችል ሞዴል ነው የዘረጋነው፡፡ እኛ  ኮሌክቲቭ ሀብት የምንፈጥረውም ሆነ ሁሉን የምናሳካው ለምነን ወይም በሌላ መንገድ ሳይሆን ቢዝነስ በመስራት ነው፡፡ ማንም ላይ ጥገኛ አንሆንም፡፡ እኛ ይህንን ለሰዎች ስናስረዳ “ለምን አውሮፓ ህብረትን አትጠይቁም? ለምን የተባበሩት መንግስታትን አታናግሩም? ምናምን” ይሉናል በፍፁም! ይሄ ነው እኛን ደሀ አድርጎ ያስቀረን፡፡ ይሄ ነው የልመና አስተሳሰብ የጫነብን፡፡ ስለዚህ የራሳችን ቢዝነስ በመስራት ነው ግባችንን የምናሳካው፡፡
አሁን እኛ አባይን የገደብንበትና ከሌሎች ተፅዕኖዎች የወጣንበትን  አይነት አካሄድ ማለት ነው…..?
ኤግዛክትሊ! ትክክል ነሽ አመሰግናለሁ። የማንም እጅ ጥምዘዛና ተፅዕኖ በሌለበት መንገድ ሰርተን ነው አላማችንን የምናሳካው። በራስ ላይ መተማመን ማለት እሱ ነው፡፡ ስለዚህ ምን ዓይነት ቢዝነስ እንፍጠር ሲባል፣ አሁን ኢትዮጵያ የመጣንበት “ፐርፐዝ ብላክ” የሚባለው ተወለደ ማለት ነው፡፡ 135 ያህል ሰዎች አሉበት፤ አብረው ለዚህ ፕሮጀክት ለፍተው ደክመዋል፡፡
ከሁሉም የአፍሪካና የአሜሪካ ጥቁሮች የተወጣጡ ናቸው ወይስ ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው?
አሁን  ያሉት በአብዛኛው ኢትዮጵያን ናቸው፡፡ በዚህም በጣም  ኩራት ይሰማናል።  እኛ ይህንን ፕሮጀክት ዳግማዊ አድዋ ነው የምንለው፡፡ የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ያለመገዛት ነፃ ሆኖ የመኖር ስነ ልቦና አትሞብናል። ስለዚህ በዚህ ፕሮጀክት የጥቁር ህዝብን ታሪክ መቀየር ከቻለን፣ የጥቁር ህዝብን ክብር እናስመልሳለን ብለን ነው የምናስበው።
እቅዳችሁና ሀሳባችሁ ትልቅና አጓጊ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቁር ህዝብን ከፍ የማድረግ የማንቃት ስራ ሲሰራ ነጮቹ ደስተኛ አይሆኑም፡፡ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ሲተባበሩ፣ አንድ ሲሆኑና ጠንከር ሲሉ ምዕራባዊያን የሚበተኑበትን አጀንዳ በመፍጠር፣ እንቅፋቶችን በማበጀትና በቀጥታም ይህን በተዘዋዋሪ እጃቸውን በማስገባት ሂደቶችን ያበላሻሉ፡፡ በዚህ ፕሮጀክታችሁ መሰል ችግር ቢገጥመን ምን ማድረግ አለብን ብላችሁ አስባችኋል?
እውነትሽን ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ሳናስበው አልቀረንም፡፡ “ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” ብለን ስንነሳ ራሱ በመሃላችን ብዙ ፍትጊያ ነበር፡፡ ለምን ብላክ ብለን እንነሳለን። በውስጠ ታዋቂነት እንሂድና ለውጥ ካመጣንና ካደግን በኋላ እንቀይረዋለን የሚል ክርክር ሁሉ ነበር፡፡ ግን የለም፤ በዚሁ አቋማችን እንግፋ፤ በተቻለ መጠን እነሱ ላይ ጥገኛ የማይሆን ሲስተም እንፍጠር በሚል ነው የተስማማነው፡፡ እነሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ሲስተም ከሆነ እንዳልሽው በአንድም በሌላም መንገድ  ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። አሁን ይሄ ፕሮጀክት በማንኛውም መንገድ ሌላውን ማህበረሰብ የሚነቅፍና የሚወቅስ አይደለም፡፡ በቃ ጥቁር ህዝብ ያለውን አቅም ሀብትና እውቀት አስተባብሮ ኢኮኖሚያዊ ደህንነት መፍጠር ላይ ብቻ ነው ትኩረታችን፡፡ ሌላው ነገር የምንፈጥረው ሲስተም የሚያገልና የሚለይ አይደለም፤ ነጮችም ገብተው ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከፈለጉ የእኛን ምርት ገዝተው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ የእነሱም ምርት መጥቶ አፍሪካ ሊጠቀምበት የሚችል አሰራር ነው የሚዘረጋው፡፡
እስኪ ወደ  ኢትዮጵያ የመጣው “ብላክ ፐርፐዝ” የሚሠራውን ይንገሩኝ?
“ብላክ ፐርፐዝ” የ”ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” አንዷና ትንሿ ፕሮጀክት ናት፡፡ “ብላክ ፐርፐዝ” አሁን ያለንበትን የዲጅታል ኢኮኖሚ ዘመን በመከተል የተገለለውን ጥቁር ህዝብ ለመሳብ “ኢ-ኮሜርስ ፕላት ፎርም” መዘርጋት ነው፡፡ ለምሳሌ አማዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለነጩ ማህበረሰብ ይሰራል፡፡ አሊባባን ስትመለከቺ የኢስያ ነው፤ ቢጫውን ማህበረሰብ የሚያገለግል ነው። ለጥቁር ማህበረሰብ ማን አለው? ማንም የለውም ስለዚህ ለጥቁሩ ይህ ፕላትፎርም መፈጠር አለበት አልን፡፡ ግን ደግሞ
ቴክኖሎጂ ይዘን ብቻ እንግባ ብንል የትም አያደርሰንም፡፡ ምክንያቱም መሰረተ ልማት በአፍሪካ የተሟላ ባለመሆኑ አስቸጋሪ ነው። እንግዲህ 1 ቢ. ጥቁር ህዝብ የሚያገለግል ኢኮኖሚ እንገንባ ነው ያነው፡፡ ይሄ 1 ቢ. ህዝብ አብዛኛው የት ነው ያለው? አፍሪካ ነው፡፡
ከአፍሪካ አብዛኛው ህዝብ ያው ደግሞ ገጠር ነው፡፡ ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ያንን ህዝብ ኢምፓክት እናድርግ ካልን ከገበሬው ጋር መስራት አለብን፡፡ ከገበሬው ጋር ሰራን ማለት ገበሬው በየቀኑ የሰው ልጅ የሚበላውን የሚጠጣውን የሚያመርት ነው፡፡ ገበሬውን ስታገለግይ ተጠቃሚውንም ታገለግያለሽ፡፡ ስለዚህ ከገበሬው ጋር መስራት አለብን፡፡ N to N PTC ይባላል ሞዴሉ፡፡ ገዢና ሻጭን በማገናኘት ደላላን ከመሃል ታስወጫለሽ፡፡ ይህ ሲሆን አንደኛ ገበሬው ምርቱን በተሻለ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ሁለተኛ ተጠቃሚው ተገቢ በሆነ ዋጋ ይገዛል ማለት ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት ረገድ የምትጫወቱት ሚና ይኖራችኋል ማለት ነው?
 ትክክል ነሽ፤ ገብቶሻል፡፡ ሰው እየተማረረ ያለበት የኑሮ ውድነት ይረጋጋል፡፡ ገበሬውም ተጠቃሚ ይሆናል፤ ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ያድጋል፡፡ ለወጣቱም ብዙ የስራ ዕድል ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በፐርፐዝ ብላክ ፕሮጀክት “ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ነው ይሄ አሁን የምንነጋገርበት ቢሮ የተከፈተው፡፡ በቀጣይ  በ54ቱም የአፍሪካ አገራት ሞዴሉ ይከፈታል፡፡ እኛ ደስ የሚለን እንደ መጀመሪያ በኢትዮጵያ መከፈቱ ነው፡፡ ከገበሬው ጋር ስንሰራ 10 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ለመሰብሰብ ነው ያቀድነው፡፡ ይሄ “ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ “ለምን ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” ተባለ? የሚገኘውን ሀብት መልሰን ማህበረሰቡ ላይ ኢንቨስት ስለምናደርግ ገንዘቡ እየተሽከረከረ ለህዝብ ይሰራል ማለት ነው፤፡ ስለዚህ ካምፔይናችንም  “”ኑ በጋራ አብረን እንስራ” በሚል መሪ ቃል ነው የሚሰራው፡፡
አክሲዮን ለመሰጥ ነው ያሰባችሁት? ከሆነ መቼ ነው መሸጥ የምትጀምሩት?
ሀምሌ 17 ለህዝቡ አክስዮን መሸጥ እንጀምራለን፡፡ ገንዘቡን እንዳገኘን መንግስት መሬት እስኪሰጠን አንጠብቅም፡፡ በኪራይ  ስራ እንጀምራለን፡፡
በአሁኑ  ሰዓት ስራውን ለመስራት ከወጣቶች ፌደሬሽንና ከሌሎች ዘጠኝ ድርጅቶች ጋር ተፈራርመናል። ከወጣች ፌዴሬሽን ጋር ስልጠናም ተጀምሯል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እናስመዘግባለን፡፡ ሁሉም የዚህ ፕሮጀክት ባለቤት እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ማርጋሬት አትውድ በ1985 ያሳተመችው ልብ ወለድ መፅሐፍ; ከገሀዱ ዓለም ፓለቲካ የተቀዳ ቢሆንም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የዛሬውን ዘመንን የሚተነብይ መፅሐፍ ነው።

ባለሰፊ ክዳን ኮፈያና ቀይ ካባ በአእምሮችን የሚከሰትልን አንድ ነገር የሴቶች ጭቆና ነው። ይህንን ምስል በነፍሳችን እንዲታተም ያደረገው ማርጋሬት አትውድ እንደ አውሮፖውያኑ የዘመን ቀመር በ1985 ያሳተመችው The Handmaid’s Tale (የደንገጡርዋ ወግ) የሚለው ልብወለድ ሲሆን ሴቶች ለማህረሰቡ ልሂቃን አባወራዎች፤ ልጆች እንዲወልዱላቸው ባርነት ያደሩበትን ሁኔታና ይህንን ለማመልከት ይህ የደንብ ልብስ የሚለብሱበት በቅርብ ዘመን የሚጠበቅ ተውኔታዊ ዓለም (near-future dystopia) ስዕልን ያቀርብልናል። ከሰላሳ ዓመታት በላይ ይህ ምስል በዓለም ዙርያ በመፅሐፍ ልባስ ላይ፣ ከ 1990 ፊልም ላይ ፖስተሮች ላይ፣ በቲቪ ተከታታይ ድራማ ማስታወቂዎች በጉልህ ሲታይ የቆየ ሲሆን ለሥነ-ተዋልዶ የሚደረጉ መብቶች ትዕይንት ሕዝቦች ና ሰልፎች ላይም ሴቶች ለብሰው መታየታቸው የተለመደ ነው፡፡
ከነዚህ ምስሎች በሚበዙበት ላይ የምናያት ደንገጡር ምንም እንኳን እርግጠኞች ባንሆንም የወጉ ተራኪ የሆነችው ኦፍሬድ (Offred) ናት፡፡፡ በጊልያድ ሪፐብሊክ ደንገጡር የሆነችው ኦፍሬድ ከአለቃዋ ፍሬድ ጋር ዘወትር ወሲብ የመፈፀም ግዴታ ተጥሎባታል፡፡ የስምዋ ትርጉም የፍሬድ (“of Fred”) ይህን ያመለክታል፡፡
በርካታ የገዢው መደብ አባላት ሴቶች በአካባቢያዊ በካይ መርዞች እንዳይወልዱ ሆነው ከመከኑ በኃላ ለዚሁ ልጅ የመውለድ ሚና በመንግሥት ቁጥጥር ከዋሉ ስር ወላድ ሴቶች አንዷ ናት፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በመፈንቅለ ምንግሥት ተወግዶ ጊልያድ የተሰኘ ዙፋነ እግዜአብሔር (ሃይማኖታዊ) መንግሥት ከመቛቛሙ በፊት ሉቃስ ከተባለ ሰው ጋር ተጋብታ አንዲት ሴት ልጅ ወልዳለች፡፡
አትውድ ልብወለዱን የጻፈችው መጻኢውን የማውጠንጠኛ ልብወለድ አድርጋ ነው፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ዕድገት ከዛሬው ዘመን እምብዛም ለውጥ ሳያሳይ ሊከሰት የሚችል ሁነትን በምናብ የሚስል ትረካ ነው፡፡ በሌላ አባባል የሳይንሳዊ ልብወለድ ጭራቆችን ፣መንኩራኩሮችን ገፀ ባህሪያት ሲያደርግ አውጠንጣኝ ልብወለድ ደግሞ በእውን ሊከሰት የሚችልን ኩነት ይስላል፡፡ እያንዳንዱ የመጽሐፉ ገጽታ መጽሐፉ በተጻፈበት በ1980ዎቹ በተከሰቱ ማኅበራዊና ፖለቲላዊ ኩነቶች የተጠነሰሰ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የአትውድ ልብወለድ በመጀመሪያ ከታተመበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ በታተመባቸው ጊዜያት ሁሉ እንግዳ በሆነ ሁኔታ የወቅቱን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው ህትመት በ1985 ሲወጣ አትውድ የታሪኩን ትልም በእውነተኛ ሁነቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማሳየት በቃለ-መጠይቅ ጊዜያት የጋዜጣ ጽሑፎች ላይ ይዛ ትቀርብ ነበር፡፡ መጽሐፉ ዩናይትድስቴትስ ወግ አጥባቂነት ማቀንቀን የጀመረችበትን ሁኔታ ይህም በሮናልድ ሬገን ለፕሬዝዳንት መመረጥን የቀኝ ክንፍ ክርስቲያናዊ ቡድን እያጎለበተ የመጣውን ብርታትና የሥነምግባር ብዙሃን (The Moral Majority) ትኩረት ለቤተሰብና ክርስቲያናዊ አጋርነት (Focus on the Family and the Christian Coalition) የተሰኙ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ተፅዕኖ እንዲሁም የቴሌቪዝን ወንገላዊያን አገልግሎት ጅማሬ ያሳያል፡፡ በመጽሐፉ ላይ ሴሬና ጆይ የተባለችው ገፀባህሪያት በአንድ ወቅት የሃይማኖታዊ መንግሥት አስፈላጊነት ስታቀነቅን የነበረች የቴሌቪዥን ወንጌላዊት ስትሆን አሁን ግን በሴቶች ላይ በተጣለው ግዳጅ ሳቢያ ኑሮዋ በቤት ተወስኗል። አትውድ ስለሰሬና ጆይ እንዲህ ስትል ትጽፋለች፡፡ “አሁን ንግግር አታቀርብም፤ አንደበቷ ተሸብቧል፡፡ ውሎዋ ቤት ሆኗል፤ ሆኖም ይህ የተስማማት አትመስልም፡፡ አሁን የተሟገተችለት ርዕዮተ ዓለም በእውን ተፈፅሞ ማየቱ ምንኛ ብስጩ አድርጓት ይሆን፡፡”
አትውድ ካናዳዊት ብትሆንምና ራቅ ስላለ ጊዜ ብትጽፍም -ጆይስ ካሮል ኦትስ በኒውዮርክ ታይምስ የመጽሐፍ ቅኝት (The New York Review of Books) የመጽሐፉ መቼት 2005 ሊሆን እንደምችል ጠቁማለች- የመጽሐፉ ርዕስ ጉዳይ በ1980ዎቹ የነበረችው ዩናይትድ ስቴትስ እንደሆነችና ትኩረቶቹም ክርስቲያናዊ አክራሪነት፣ ሥነ ምህዳራ ጉዳዮችና የሴቶች የተዋልዶ ጤና መብቶች እንደሆነ ጠቁማለች። በወቅቱ በአሜሪካ ውርጃን በመቃወም ይካሄድ የነበሩ ዘመቻዎች “የአርምሞ ጩኸት” (‘The Silent Scream) የተሰኘ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ የውርጃ ክሊኒኮች በቦንብ ማውደምና ማቃጠል እንደዚሁም የሰብዓዊ መብት ዋስትና ላልተወለዱ ፅንሶች እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ሕግ መረቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡
የሬጋን አስተዳደር ለረዥም ጊዜ የቆየ ፖሊሲን በመለወጥ የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚያቀርበው ‘ተፈጥሮአዊ‘ የቤተሰብ ዕቅድን ማለትም ተአቅቦን (abstinence) ለሚያቀነቅኑ ባላደጉ ሀገራት ለሚንቀሳቀሱ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ብቻ እንደሆነ አዋጀ። ኤስሲ ኒውነማን የተሰኙ እንግሊዛዊ ፕሮፊሰር፥ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የጥናት መጽሔት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደዚህ ይላሉ “ኦፍሬድ በአጭሩ የ1970ዎቹ አንስታዊነት ወጤት ስትሆን በ1980ዎቹ ተፅዕኖው እያየለ የመጣው በሴቶች መብቶች ላይ የተነጣጠረው ዘመቻ በልብወለዳዊ ትረካ የቀረበች ሴት ናት፡፡”
በዚያን ወቅት በየአሜሪካ አስተዳደር ከነበሩ ሰዎች መካካል የደቡብ አፍሪካውን አፓርታይድ ለመቃወም የማይደፈሩ ነበሩ፡፡ ቀጣይ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡትን ዲክ ቼኒ የኔልሰን ማንዴላን ከወኅኒ መፈታት የሚቃወሙ ሲሆን ሴናተር ጆን ማክኬይን ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ማዕቀብ እንዳይጣልበት ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ አትውድ የአፓርታይድ ዘመን ባንቱስታዎኖችን በማስታወስ በደንገጡርዋ ወግ (The Handmaid’s Tale) አፍሪካ-አሜሪካውያን በመካከለኛው ምዕራብ (ሚድዌስት) በብሔራዊ መኖሪያ “National Homelands” እንዲሠፍሩ መደረጋቸውን ትገልጻለች፡፡
ማርጋሬት አትውድ
መጽሐፉ ከጥቂት አመታት በፊት ወደ  ፊልምነት ተቀይሮ በቴሌቪዥን በተከታታይ ሲታይ ነበር ዝነኛ ለመሆን የበቃው። የፊልሙ አዘጋጆች ፊልሙን ዘመናዊ ዳራ ለማልበስ፥ መፅሐፉ ላይ ከሠፈረው ውጭ፥ ብዙ ነገሮችን ጨምረዋል፡፡  እንደ ኡበር የተሰኘው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ፣ ቲንደር የተሰኘው የስልክ አፕሊኬሽን፣ ወደ ኦፍሬድ የቅድመ ባርነት ህይወት በምልሰት በማስገባት፡፡
ግን ፊልሙ እና መፅሐፉ ይበልጥ ድል ተወዳጅነትን ያተረፈው፤ የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዉ መመረጥን ተከትሎ በአሜሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ በመከሰቱ ምክንያት ነው፡፡ በድንገት፣ የመጽሐፉ እና የፊልሞቹ ዋና ዋና ነጥቦች ከመቼውም ጊዜ እውን የሚሆኑበት ጊዜ የተቃረበ መሰለ። በእስልምና አክራሪዎች ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ወታደራዊ ህግን የሚያወጅ መንግስት፣ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚያስወግድ አገዛዝ፣ የሴቶች ተግባር መውለድ ብቻ ብሎ የሚያምን ህብረተሰብ።
መጽሐፉ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ  በደንገጡርዋ ወግ መጽሐፉ ውስጥ በጣም የሚጠቀሰው አባባል፤ በክፍሏ ውስጥ ቁም ሣጥን ላይ፤ ምናልባትም በፍሬድ ቀደምት ደንገጡር ላቲን በሚመስል ሁኔታ የተፃፈው- Nolite te bastardes carborundorum (ዲቃላዎቹ እንዲፈነጩብህ አትፍቀድላቸው።) የሚል ነው። አባባሉ ለሴቶች መብት ተሟጋቾች፤ ቀስቃሽ ሆኖ በመገኘቱ ፤ በዚህ ዘመን ብዙ ሴቶች በአካላቸው ላይ ተነቅሰውታል፡፡ ገሚሶች በሃሎዊን በዐል ላይ እንደ  ደንገጡር እንዲሁም ሌሎች ተቃውሞ ሰልፎችም ይለብሱታል – እነዚህ ሁለት የልብሱ አጠቃቀሞች ለሁለት የተለያዩ መንታ አላማዎች መዋሉን ያንፀባርቃሉ በማለት ማርጋሬት አትውድ ጋርዲያን ጋዜጣ ላይ ጽፋለች፡፡ “ጨዋታ ነው ወይስ አስከፊ የፖለቲካ ትንቢት? ሁለቱንም ሊሆኑ ይችላሉን? መጽሐፉን በምጽፍበት ጊዜ ይህ ይሆናል ብየ አላሰብኩም ነበር ፡፡”

የኢዜማው  አቶ ክቡር ገና  ምርጫ ቦርድ ውጤት ሳይገልፅ ብልፅግናን “እንኳን ደስ አላችሁ! “ በማለት  ፅፈዋል ።ጠ/ሚር አብይንም  “የዚህ ምርጫ አሸናፊ “በማለት አሞግሰዋቸዋል።
ኢዜማ ምርጫ ካሸነፈ  የአዲስ አበባ ከንቲባ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት የኢዜማው አቶ  ክቡር ገና ዛሬ በፌስቡካቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ይሄን ፅፈዋል;
“ ኢትዮጵያውያን አብይ አህመድን ጠ/ ሚ  እንዲሆኑላቸው ወስነዋል። ጠ/ ሚሩም በውጭም  በውስጥም ጠላቶች   ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም ምርጫ እንዲከናወን አድርገዋል።ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል።”
“ጠ/ ሚሩ  ኢትዮጵያን አንግብው ለህዝባቸው ተስፋን በመመገባቸው  በብዙ መራጮች ልብ ገብተዋል“
“እኛ ተቃዋሚ  ፖለቲካ  ፓርቲዎች የሚጠበቅብን ስራ አልሰራንም። ይሄን ለምን ሆነ?  ብለን እራሳችን መጠየቅ፣ መፈተሽ፣ መወያየትና ለቀጣይ ስራዎች መዘጋጀት አለብን። ወጣት ፖለቲከኞችን ማምጣት አለብን። አምስት አመት  በጣም ትንሽ ግዜ ናት!።”
“ግን ሀገሪቱን ለሚገዛት ፓርቲ ምክር አለኝ ።የሰፋውን  የኑሮ ልዩነቱን ማቀራረብ ፣ድህነትን መቀነስ፣ የጤና አገልግሎትን ማስፋት፣ ስራ አጥነት ላይ ብዙ መስራት፣ ፍትህ  ላይ መስራት፣ የተሻለ የንግድ ስርአትን ፈጥሮ ስራ ፈጣሪን እና  ገቢን  ማስፋት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ አንድነት ማምጣት ......” በማለት  ፅፈዋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት በደቡብ አፍሪካ ሊመረት ነው

   ከአፍሪካ አጠቃላይ ህዝብ እስካሁን ድረስ የኮሮና ክትባት የተከተበው 0.85 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን ኦልአፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፤ በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በደቡብ አፍሪካ ሊመረት እንደሆነ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ሙሉ ለሙሉ የተከተቡት 10.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ወይም ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 0.85 በመቶው ብቻ መሆኑን ያስታወቀው ማዕከሉ፣ በአለማቀፍ ደረጃ ከተመረተው የኮሮና ቫይረስ ክትባት አፍሪካ ያገኘችው ከ2 በመቶ በታች መሆኑንም በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአለም የጤና ድርጅት በበከሉ፤ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ማዕበል ክፉኛ እየተመታች በምትገኘው አፍሪካ የክትባት እጥረት አንገብጋቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ኡጋንዳና ዚምባቡዌን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ አገራት ክትባቶቻቸውን ተጠቅመው መጨረሳቸውን ያስታወቀ ሲሆን አልአይን በበኩሉ፤ በአለም ዙሪያ የሚገኙ 40 ያህል አገራት የመጀመሪያውን ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ለወሰዱ ዜጎቻቸው ሁለተኛውን ዙር ለመስጠት የክትባት እጥረት እንዳጋጠማቸው መነገሩን ዘግቧል፡፡
ዴልታ የተባለው አደገኛ የቫይረሱ ዝርያ ወደ 14 አገራት በተሰራጨባት አፍሪካ፣ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሰኞ ከ5.2 ሚሊዮን ማለፉንና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 138 ሺህ መጠጋቱን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት በአፍሪካ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ እስከ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ ማምረት ለመጀመር ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፣ ሜሴንጀር አርኤንኤ በተባለ ቴክኖሎጂ ክትባት ለማምረት የተጀመረው ጥረት በከፍተኛ የክትባት እጥረት በርካታ ዜጎቻቸውን እያጡ ለሚገኙ የአፍሪካ አገራት ተስፋ ሰጪ ነው መባሉን አመልክቷል፡፡
ክትባቱ በአለም የጤና ድርጅት የበላይ አስተባባሪነት፣ ባዮቫክ በተባለ ኩባንያ ባለቤትነትና አፍሪጂን በተባለ ኩባንያ አምራችነት መመረት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካውያን ዩኒቨርሲቲዎችና የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መነገሩንም ገልጧል፡፡

አሽጋባት ከአለማችን ከተሞች ለመጤዎች እጅግ ውዷ ተብላለች
የአሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ኩባንያ አማዞን በአለማችን ኩባንያዎች የአመቱ የንግድ ምልክት ዋጋ ደረጃ በአንደኛነት የተቀመጠ ሲሆን፣ የኩባንያው የንግድ ምልክት ዋጋ 684 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ሰሞኑን የወጣ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡  
ካንታር ብራንድዝ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አመታዊ የ100 ምርጥ የአለማችን ኩባንያዎች የንግድ ምልክት ዋጋ ደረጃ ሪፖርት እንዳለው፤ የ100ዎቹ ኩባንያዎች ድምር ዋጋ 7.1 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን የአማዞን የንግድ ምልክት ዋጋ ባለፈው አመት ከነበረበት የ64 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ታዋቂው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል በ612 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ጎግል በ458 ቢሊዮን ዶላር፣  ማይክሮሶፍት በ410 ቢሊዮን ዶላር፣ ቴንሰንት በ240 ቢሊዮን ዶላር፣ ፌስቡክ በ226.7 ቢሊዮን ዶላር፣ አሊባባ በ196.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ቪዛ በ191.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ማክዶናልድ በ154.9 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ማስተርካርድ በ112.8 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖችን በማምረት ዘርፍ የተሰማራው የአሜሪካው ኩባንያ ቴስላ ካለፈው አመት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳየ ቀዳሚው ኩባንያ ሲሆን ካምናው የ275 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 42.6 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው ኩባንያው ከአለማችን መኪና አምራቾች በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከፍተኛ የንግድ ምልክት ዋጋ ካላቸው የአለማችን ምርጥ 100 ኩባንያዎች መካከል 74 በመቶው የአሜሪካ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣  14 በመቶው የቻይና፣ 8 በመቶው ደግሞ የአውሮፓ ኩባንያዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በሌላ አለማቀፍ ዜና ደግሞ፣ የቱርኬሚኒስታኗ ከተማ አሽጋባት ከሌሎች አገራት ለመጡ ነዋሪዎች  እጅግ ውድ የሆነች ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗንና በአንጻሩ የካይሪጊስታን መዲና ቤሽኬክ እጅግ ርካሽዋ ከተማ መሆኗን ሜርሲየር የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ጥናት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለም ዙሪያ የሚገኙ 209 ከተሞችን መኖሪያ ቤት፣ ትራንስፖርትና ምግብን ጨምሮ የ200 ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ በማጥናት የፈረንጆች አመት 2021 ሪፖርቱን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ ከሌሎች አገራት ለመጡ ሰዎች እጅግ ውድ ናቸው ብሎ ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የሰጣቸው የአለማችን ከተሞች ሆንግ ኮንግ፣ ቤሩት፣ ቶክዮ፣ ዙሪክ፣ ሻንጋይ፣ ሲንጋፖር፣ ጄኔቫ፣ ቤጂንግ፣ እና በርን ናቸው፡፡
የካይሪጊስታን መዲና ቤሽኬክ በአንጻሩ በአመቱ ለውጭ አገራት ዜጎች እጅግ ርካሽ መሆኗ የተነገረላት ቀዳሚዋ የአለማችን ከተማ ስትሆን፣ ሉሳካ (ዛምቢያ)፣ ቲብሊሲ (ጂኦርጂያ)፣ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)፣ ብራዚሊያ (ብራዚል)፣ ዊንድሆክ (ናሚቢያ)፣ ታሽኬንት (ኡስቤኪስታን)፣ ጋቦሮኔ (ቦትስዋና)፣ ካራቺ (ፓኪስታን) እና ባንጁል (ጋምቢያ) እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከ10ሩ እጅግ ውድ የአለማችን ከተሞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የእስያ ከተሞች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከአሜሪካ ከተሞች መካከል ለመጤዎች እጅግ ውዷ ኒው ዮርክ ናት ብሏል፡፡

Tuesday, 29 June 2021 00:00

9% የአለም ህዝብ በችግር

ምክንያት እራት እንደማይበላ ተነገረ
በመላው አለም 41 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል ተባለ

ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ ወደ 9 በመቶ የሚጠጋው ወይም 690 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በየዕለቱ ለራት የሚሆን ምግብ ማግኘት ባለመቻላቸው ሳይበሉ እንደሚተኙ የገለጸው የአለም የምግብ ድርጅት፣ በ43 የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 41 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡
በአራት የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ 600 ሺህ ያህል ሰዎች ከረሃብ ባልተናነሱ አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ የከፋ ኑሮን እየገፉ እንደሚገኙ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በአለም ዙሪያ የረሃብ አደጋ ያንዣበበባቸውን 41 ሚሊዮን ሰዎች ለመታደግ 6 ቢሊዮን ዶላር ያህል የአፋጣኝ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አስጠንቅቋል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ለረጅም አመታት ሲቀንስ ቢቆይም ላለፉት አምስት አመታት መጨመር ማሳየቱን ያስታወሰው ድርጅቱ፤ ጦርነቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮኖሚ ቀውሶች የሸቀጦች ዋጋ መናርንና የርሃብ አደጋዎችን የጨመሩ ምክንያቶች መሆናቸውን የጠቆመ ሲሆን፤ ባለፈው አመት ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ ሁኔታውን ክፉኛ እንዳባባሰውና የምግቦች ዋጋ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በአስር አመት ውስጥ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን አስረድቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ባወጣው አለማቀፍ መረጃ፣ በአለማችን በአስገዳጅ ሁኔታ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎች ቁጥር 82 ሚሊዮን መድረሱንና ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 1 በመቶ ያህሉ በመሰል ሁኔታ ተፈናቅሎ እንደሚገኝ ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ብቻ በመላው አለም 11.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮችን ለስደት ከዳረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ግጭት፣ አመፅና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚገኙባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በተለያዩ የአለማችን አገራት በተቀሰቀሱ ግጭቶችና ጦርነቶች ከ8ሺህ 500 በላይ ህጻናት በወታደርነት እንዲያገለግሉ መደረጉን የገለጸው ተመድ፤ ተጨማሪ 2ሺህ 700 ያህል ህጻናት መገደላቸውንና ሌሎች 5ሺህ 748 ያህል ህጻናት ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ባለፈው ሰኞ ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አካባቢዎች በተቀሰቀሱ 21 ግጭቶች በ19 ሺህ 379 ህጻናት ላይ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ጠለፋን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ጥቃቶችና በደሎች መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በመላው አለም በአመቱ በተቀሰቀሱ ግጭቶች እጅግ ከፍተኛ ጥቃቶችና በደሎች የተፈጸሙባቸው አገራት ሶማሊያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶርያና የመን መሆናቸውንም ዋና ጸሃፊው ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡

ኤርስፒደር ኢኤክስኤ የሚል ስያሜ የተሰጠውና በአለማችን ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ በራሪ መኪኖች እሽቅድድም ከወራት በኋላ በድምቀት እንደሚካሄድ ዩሮኒውስ ዘግቧል፡፡
ማቲው ፒርሰን በተባሉ ስራ ፈጣሪ ሃሳብ አመንጪነት አሉዳ ኤሮኖቲክስና ኤርስፒደር በተሰኙ እህትማማች ኩባንያዎች አዘጋጅነት ባለፈው የፈረንጆች አመት ሊካሄድ ታስቦ የነበረውና በኮሮና ወረርሽኝ ክስተት ሳቢያ ተራዝሞ በመጪዎቹ 6 ወራት ጊዜ ውስጥ ሊደረግ ቀን በተቆረጠለት በዚህ ውድድር ላይ፣ በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር ፍጥነት የመጓዝ አቅም ያላቸው በራሪ መኪኖች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡
በውድድሩ የሚካፈሉት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች አማካይ ክብደት 130 ኪሎ ግራም እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፣ በሪሞት ኮንትሮል አማካይነት ከመሬት ላይ ሆነው በሚቆጣጠሯቸው አሽከርካሪዎች አማካይነት እንደሚንቀሳቀሱም ገልጧል፡፡
ውድድሩ በ3 የተለያዩ ስፍራዎች እንደሚካሄድ እንጂ ቦታዎቹ የትኞቹ እንደሆኑ አዘጋጆቹ በግልጽ አለመናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የበራሪ መኪኖች የሙከራ በረራ ከቀናት በፊት በደቡባዊ አውስትራሊያ በሚገኝ በረሃ በስኬታማ ሁኔታ መከናወኑንና ውድድሩ እውቅና እንደተሰጠውም አክሎ ገልጧል፡፡


ለምርጫው የተመደበው አጠቃላይ  በጀት- 2.5 ቢ. ብር
ለምርጫው ከውጭ ሃገራት የተገኘ ድጋፍ - 40 ሚ. ዶላር
ለድምፅ መስጫ ካርድ ህትመት ወጪ የተደረገ - 6.7 ሚ. ዶላር
የተመዘገቡ መራጮች ብዛት - 38.2 ሚ.
የእጩ ተመራጮች (ተወዳዳሪዎች) ብዛት - 9ሺ327
የምርጫ አስፈጻሚ ሰራተኞች ብዛት - 244ሺ
አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት- 48 ሺ

Page 5 of 536