Administrator

Administrator

የጣሊያኗ ቬነስ በአንደኛ ደረጃ ተቀምጣለች


ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች መካከል የሚጠቀሱት ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባት የላሊበላ ከተማ፣ ‘አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሊያያቸው የሚገባቸው 50 ምርጥ የአለማችን ከተሞች’ በማለት ታዋቂው ሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ ከጠቀሳቸው ከተሞች ተርታ ተመደበች፡፡
ጋዜጣው በቅርቡ ሚኑቢ ዶት ኔት በተባለ ድረገጽ አማካይነት የአለማችን ጎብኝዎች የሚያደንቋቸውን ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጠቁሙ በማድረግ ባሰባሰበው መረጃ፣ በጎብኝዎቹ ከተመረጡ 50 የአለማችን ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ላሊበላ 17ኛ ቦታ ላይ መቀመጧን ታዲያስ መጽሄት በሳምንቱ መጀመሪያ ዘግቧል፡፡
ላሊበላ ከኢትዮጵያ ታላላቅ ቅዱስ ከተሞች አንዷ ናት ያለው ሃፊንግተን ፖስት፣ በውስጧ የያዘቻቸው ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም በመላው አለም የሚታወቁ ድንቅ መስህቦች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ከጥንታዊ የአገራት ርዕሰ መዲናዎች፣ እስከ እስያ ዘመናዊ ከተሞች በመላው አለም የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ከተሞችን ባካተተው በዚህ ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚነትን ያገኘችው የጣሊያኗ ቬነስ ናት፡፡ የሚያማምሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ገራሚ አብያተ ክርስቲያናት፣ ማራኪ ቤቶች፣ ምቾት የሚለግሱ መጠጥ ቤቶች ብዙ ብዙ ማራኪ ነገሮች የሞሉባት ቬነስ፣ ከአለም ከተሞች አምሳያ የሌላት ምርጥ ከተማ ናት ብሏታል ጋዜጣው፡፡
የስፔን ነገስታት መናገሻ ውብ ከተማ፣ ጎብኝዎች በብርቱካናማ አበቦች የተዋቡ ጠባብ መንገዶቿን ተከትለው በመጓዝ ማራኪ ጥንታዊ ህንጻዎችን አሻግረው እየቃኙ መንፈሳቸውን የሚያድሱባት አይነግቡና ቀልብ አማላይ ከተማ በማለት ሁለተኛ ደረጃ የሰጣት ደግሞ የስፔኗን ሲቪሊ ነው፡፡
 ኒዮርክ ሲቱን ሶስተኛዋ መታየት ያለባት የአለማችን ቀልብ ገዢ ከተማ ያላት ሃፊንግተን ፖስት፤ የትም ዙሩ የትም፣ እንደ ኒዮርክ ሲቲ መንፈስን ገዝቶ በአድናቆት የሚያፈዝ የኪነጥበብ፣ የባህል፣ የምግብ አሰራርና የንግድ እንቅስቃሴ በአንድ ላይ ተዋህደው የሚገኙባት ከተማ በየትኛውም የአለም ጥግ አታገኙም ብሏል፡፡
የህንዷን ላህሳ በመንፈሳዊ ማዕከልነቷና በማራኪ የተፈጥሮ ገጽታዋ፣ የብራዚሏን ሪዮ ዲ ጄኔሮ በውበቷ፣ የእንግሊዟን ለንደን በምርጥ ሙዚየሞቿና በጎብኝዎች ተመራጭ ከሆኑ የአለማችን ቀዳሚ ከተሞች አንዷ በመሆኗ በተከታታይ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ሰጥቷቸዋል፡፡ የሞሮኮዋ ማራኬች፣ የዮርዳኖሷ ፔትራ፣ የጣሊያኗ ሮምና የህንዷ ቫራናሲም አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሳለ ሳያያቸው ማለፍ የሌለባቸው ከተሞች ናቸው ተብለዋል፡፡

Saturday, 12 July 2014 12:30

የግጥም ጥግ

ላለ - መጨቆን
ሞት ይቅር ይላሉ…
    ሞት ቢቀር አልወድም
ከድንጋይ ---ቋጥኙ---
    ከሰው ፊት አይከብድም፡፡
ማጣት ክፉ ክፉ፤
ችግር ክፉ ክፉ፤
ተብሎ ይወራል
ከባርነት ቀንበር
ከሬት መች ይመራል፡፡
***
ለ- ጅገና
ተው! ተመለስ በሉት
ተው! ተመለስ በሉት!
ያንን መጥፎ በሬ
ከጠመደ አይፈታም ያገሬ ገበሬ
* * *
ያባቴ ነው ብሎ፤
የናቴ ነው ብሎ፤
ይፋጃል በርበሬ
አባት የሌለው ልጅ፤
እናት የሌለው ልጅ፤
አይሆንም ወይ አውሬ
ለወንድ - አደር
ዓይንሽ የብር ዋጋ
ጥርስሽ የብር ዋጋ
    ወዳጆችሽ በዙ ከስንቱ ልዋጋ?
(ከክፍሌ አቦቸር (ሻምበል)
“አንድ ቀን” የግጥም መድበል፤ 1982፣ የተወሰዱ)

ከወንድወሰን ተሾመ የማህበራዊ ሳይንስና የስነ ልቦና ባለሙያ
 (ከአልታ ምርምር ሥልጠናና ካውንስሊንግ)
ጭንቀት ምንድን ነው?
ጭንቀት የሰውነትን ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚያዛባ የአካል፣የአዕምሮና የስሜት ትንኮሳ(stimulus) የሚፈጥረው  ምላሽ፣ ወይም የአንድ ሰው  ፍላጎት (demand) ሊያንቀሳቅሰው ከሚችለው የግልና የማህበራዊ ሃብቶች አቅም በላይ ሆኖ ሲታየው የሚፈጠር ስሜት፣  ወይም ነገሮች ና ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን  እንደወጡ ስናስብ የሚፈጠር ስሜት ነው፡፡
መጠኑና ጊዜው ይለያይ እንጂ ጭንቀት የማይነካው ሰው እንደሌላ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቀት በአንድ ኮሌጅ ውስጥ የሳይኮሎጂ ኮርስ ሳስተምር አንድ ተማሪ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣንን ጠቅሶ “እንዴት እሳቸው ይጨነቃሉ?” በማለት ሰውየው ከማንኛውም ጭንቀት በየትኛውም ሁኔታና  ጊዜ ነፃ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ገልጾ እንደተሟገተ ትዝ ይለኛል፡፡ ሆኖም በየትኛውም የስልጣን እርከን ወይም የሥራ ሃላፊነት ላይ ብንሆን በጥቂቱም ቢሆን በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ጭንቀት ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል፡፡ የሚወጡ ሳይንሳዊ መረጃዎች ደግሞ ሃላፊነትና ውሳኔ ሰጪነት ሲጨምር ጭንቀት እንደሚጨምር ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ነው ባለስልጣናት፣ ስራ አሰኪያጆች፣ ዲሬክተሮች፣ ሥራ ሃላፊዎች በጭንቀት መቆጣጠሪያ (stress management strategies) ስልቶች እንዲሰለጥኑ መደረግ ያለበት፡፡ በማንኛውም ደረጃ የሚሰራና ከስራ ውጪም የሆነ ሰው የጭንቀት መቆጣጠሪያ  ስልቶችን መሰልጠኑ፤ማወቁና መተግበሩ የተረጋጋ ህይወት እንዲመራ ይረዳዋል፡፡ ጭንቀት ውሳኔን የማዛባትና ትኩረትን የመቀነስ ሃይል ስላለው የጭንቀት መቆጣጠሪያ ስልቶችን ማወቅና መሰልጠን ይገባቸዋል፡፡
የጭንቀት ምንጮች ምንድን ናቸው?
የጭንቀት ምክኒያቶች በርካታ ናቸው፡፡  ሆኖም  በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ለይቶ ማየት ይቻላል፡- አካላዊና ስነ ልቦናዊ  ምንጮች፡፡ እነዚህም የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል፡-
በስራ ቦታ በሚፈጠር የሥራ ጫና
የሥራ አሰራር ግልፅነት ማጣት
ከሚወዱት ሰው ጋር የሚፈጠር ችግር
መሰረታዊ የኢኮኖሚ ግዴታዎችን መወጣት አለመቻል፡- ለምሳሌ የቤት ኪራይ፣ አስቤዛ፣ ወርሃዊ የመብራት ክፍያ ወዘተ…
ለአዳዲስ ነገሮች መዘጋጀት፡- ለምሳሌ ልጅ መወለድ፣ አዲስን ስራ መያዝ
የትራፊክ መጨናነቅ
ከፍተኛ ድምፅ
ህመም
ክፍተኛ የአየር ሁኔታ፡- ለምሳሌ ከባድ ሙቀት ወይም ከባድ ቅዝቃዜ
አካላዊ ህመም፣እንቅልፍ ማጣት፣ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ በሰውነት ላይ የሚፈጥሩት ጫና ወዘተ ናቸው
ቲምና ፔተርሰን (Timm and Peterson) የተባሉ ምሁራን  በተለይ በሥራ አካባቢ የጭንቀት ምንጮች የሚላቸውን  እንደሚከተለው ይዘረዝራሉ።
ውጤታማ ያልሆነ ተግባቦት (Communications)
አግባብነት የጎደለው የመስሪያ ቤት አሰራር
ከመጠን በላይ የሆነ የመረጃ ብዛት
ወጥ ያልሆነ የሥራ አስኪያጆች ወይም የመሪዎች ባህሪ
ከመጠን ያለፈ የስራ ብዛት ወይም ጫና
አዲስ ሥራ መግባት
የግል ችግሮች
ጭንቀትን የሚዘሩ ግለሰቦች- በንግግራቸው ሁሉ ጭንቀት የሚፈጥር ወሬን የሚያወሩ (Stress carriers ይባላሉ)
የ ድርጅቶች ደሞዝ፣ፖሊሲ እና የስራ አካባቢ(working conditions)
የሥራ ቦታዎች ከፍተኛ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ፣ ከፍተኛ ብርሃን ወይም ድንግዝታ ለጭንቀት መነሻዎች እንደሆኑ በፃፉት መፅሃፍ ላይ ይገልፃሉ፡፡
የጭንቀት ውጤቶች ምንድናቸው?
የሰውነት ድካም
ከፍተኛ የራስ ምታት
ብስጭት
የምግብ ፍላጎት መዛባት
የማስታወስ ችሎታ መቀነስ
ለራስ የሚሰጥ ዋጋ ወይም ክብር መቀነስ(low self-esteem)
ከማህበራዊ ህይወት መገለል
የ ደም ግፊት መጨመር
ትንፋሽ ማጠር
የወሲብ ፍላጎት መቀነስ
የእንቅልፍ መዛባት
የጨጓራና አንጀት ስርዓት መዛባት  ወዘተ
ከእነዚህም በተጨማሪ ጭንቀት  የልብ ህመምን፣ የቆዳ ችግርን(skin disorders) እና ሜታቦሊዝምን (በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ ኡደቶችን)የማዛባት አቅም አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም ለስነልቦናዊ ቀውሶች ለምሳሌ፡- ለፍርሃትና ለድብርት ይዳርጋል፡፡ ጭንቀት ስነልቦናዊ ችግር ነው ቢባልም አካላዊ ተፅእኖን ይፈጥራል፡፡
ጭንቀትን ለመቀነስ ምን ማድረግ አለብን ?
ከላይ የተጠቀሱት  ምሁራን ለጭንቀት መላ ይሆናሉ ያሉትን መፍትሄዎች እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፡-
ለአፍታ ዞር ይበሉ፡- ጭንቀት ከፈጠረብዎ ሁኔታ ወይም ሌላ ምንጭ ዞር ይበሉና የማሰቢያና የማሰላሰሊያ ጊዜ ይውሰዱ፡፡
ያውሩት፣ይናገሩት፡-ለቅርብና ለሚያምኑት ሰው የጭንቀትዎን ስሜት  ይናገሩ፡፡ ባወሩ ቁጥር ይቀልልዎታል፡፡
ወጣ ብለው የሚወዱትን ይጫወቱ፡- የእግር ጉዞ ያድርጉ፣ ደረጃዎችን ወደ ላይና ወደ ታች ይውጡ፡፡
አንዳንዴ እጅ ይስጡ፡- ለምሳሌ እርስዎና ባለቤትዎ ወይም አለቃዎ “ይሄ ነው ትክክል ያኛው ነው ትክክል ” እያሉ ሙግት ከገቡና ጉዳዩ ብዙ ለወጥና ተፅዕኖ የማያመጣ ከሆነ ችላ ይበሉት፤ አንዳንዴ እያወቁ ይተውት፡፡
ለሌሎች መልካም ነገር ያድርጉ፡-በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡና ሃዘን ውስጥ ሲሆኑ ችግረኞችን በመርዳትና ልገሳ በማድረግ ይሳተፉ፤ ቀለል ይልልዎታል፡፡
በአንድ ጊዜ አንድን ነገር ይስሩ፡- ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለመስራት መሞከር ጭንቀትን ስለሚያባብስ እንደ ስራዎቹ ጠቃሚነትና አስቸኳይነት ቅደም ተከተል  በማሲያዝ  በአንድ ጊዜ አንድን ነገር ይስሩ፡፡
የታላቁን ሰው ፍላጎት አድብ ግዛ ይበሉት፡-አንዳንዴ የራስዎንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ችግር በሙሉ ራስዎ መፍታት እንደሚችሉ ማሰብዎ “በውስጥዎ ያለው የሃሰተኛው ትልቅ ሰው urge of superman” ምክር ነውና አድብ ግዛ ይበሉት፡፡ እርስዎ የሁሉንም ሰው ችግር ፈቺ አይደሉም፡፡
ትችትን መቋቋም ይለማመዱ፡- አንዳንድ ሰው ትንሽ ትችት እንቅልፍ ትነሳዋለች፡፡ በተጨማሪም ሌሎችንም ከመተቸት ይቆጠቡ። ቶማስ ፍሬድማን የ “ The world is flat” ፀሃፊ በዚህ አለም አንድ መንደር በሆነችበት ግሎባላይዜሽን ዘመን ለትችት ቆዳህን አወፍር (Make your skin thick) ብሎ ይመክራል፡፡
ለሌሎች ራስህን አስገኝ፡- ሰዎች ሲፈልጉህ ተገኝላቸው፡፡ ብቸኝነት የጭንቀት ምክኒያትም ሊሆን ስለሚችል፡፡
ራስህን ለማዝናናት ጊዜ ውሰድ፡-ዘና ማለት፣መጫወት፣ አዳዲስ ነገሮችን መጎብኘት መንፈስን ያድሳል፣ ጭንቀትንም ይቀንሳል፡፡
ቆፍጣና ሁን፡- በቀን ወስጥ የምትሰራውን፣ የምትሄድበትን ሥፍራ፣ የምታገኘውን ሰው በትክክል ለይተህ በማወቅ ዝርክርክነትን አስወግድ።
ስብዕናህን ፈትሽ፡- ጭንቀት ውስጥ የሚከትህንና የማይከትህን ነገሮች ለይተህ በመረዳት ራስህን ጠብቅ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ጭንቀትን ለመቀነስ ቴክኒኮችን ማወቅና አስተሳሰብን መለወጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በሥልጠናና በባለሙያ የካውንሰሊንግ አገልግሎት  ሊገኝ ይችላል፡፡
ለዛሬ ሁለት ቴክኒኮችን ብቻ  እንመልከት(በርካታ ቴክኒኮች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል)፡-
አንደኛው በእንግሊዝኛው ምህፃረ ቃል ABCDE ተብሎ የሚጠቀሰው ነው፡፡ ይህ ቴክኒክ አልበርት ኤሊስ (Albert Ellis) በተባሉ የስነልቦና ባለሙያ የተገኘ ዘዴ ነው፡፡ አልበርት ኤሊስ ሰዎች ወደ ጭንቀት የሚገቡት አግባብ ያልሆነ አስተሳሰቦችና እምነቶች  (Irrational beliefs and thoughts) ሲጠናወቷቸው ነው ብለው ያምናል:: ለምሳሌ ሰው ሁሉ ይጠላኛል፣ ሰው ሁሉ ይወደኛል፣ ከሰው ሁሉ ተቀባይነትን ማግኘት አለብኝ፤ በምሰራው ስራ ሁሉ መሳሳት የለብኝም ወዘተ የሚሉ እምነቶችና አስተሳሰቦች ለጭንቀት እንደሚዳርጉ ያሰምሩበታል። እኚህ ሰው እንደሚሉት አሉታዊ ነገሮችን አጋኖ ማየት(Awfulising)፤ ጥቁርና ነጭ እሳቤ(Black and White thinking) (ይህ እንግዲህ አንድን ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ መመደብና በውስጡ ሊኖር የሚችለውን የተወሰነውን ጥሩ ነገር አለማየት ነው)፣ጠቅላይ እሳቤ (Over generalizing)-ሁልጊዜ፣ሁሉም ሰው፣ በፍፁም ወዘተ የሚሉ ቃላትንና ሃሳቦችን መጠቀም፤ የማይመለከተንን ነገር ከራሳችን ጋር አቆራኝቶ ማየት (Personalizing)፤ በሁኔታዎች ውስጥ አሉታዊን ነገር ብቻ መርጦ ማየት(Filtering)፣ ይህንን አስቦ ነው ብሎ ያለምንም ማስረጃ ድምዳሜ ላይ መድረስ (Mind reading)፣ሰዎችን መተቸትና መውቀስ (Blaming)፣ለራስ ስያሜ መስጠት ለምሳሌ ደካማ ነኝ፤ዋጋ ቢስ ነኝ ወዘተ ማለት (Labeling) አግባብ ላልሆኑ አስተሳሰቦች ምክኒያት ናቸው ይሉናል፡፡
የ ABCDE ቴክኒክን ተንትነን ለማየት እንሞክር
Antecedent(Activating event, Stimulus)፡ ይህ ማለት ጭንቀትን የሚቀሰቅሰው ሁኔታ ወይም ነገር ነው(ተንኳሽ እንበለው)፡፡ ይህ ተንኳሽ  የኛን ምላሽ (Response) ይጠይቃል። ለምሳሌ ከስንት አንድ ቀን ቀጠሮ ብናረፍድ ጭንቀት ሊፈጠርብን ይችላል፡፡ በዚህ ምሳሌ መሰረት ጭንቀትን የሚፈጥርብን ጉዳይ ማርፈዳችን ነው ማለት ነው፡፡
Belief-our cognition about the situation፡- ይህ እንግዲህ ስለ ተንኳሹ ያለን ሃሳብና እምነት ነው፡፡ ለምሳሌ ማርፈዴ ያለኝን ተቀባይነት ያሳጣዋል፣ በምንም አይነት ምክኒያት ቢሆን ማርፈድ አሳማኝ አይደለም ወዘተ የሚል እምነት ማለት ነው፡፡
Consequences-the way that we feel and behave፡ ይህ ውጤት ነው - ጭንቀታችን፡፡ ይህ ምን  ባህሪ ይፈጥራል? ቶሎ ለመድረስ አላግባብ ጣልቃ እየገባን መኪናችንን መንዳትን፣ በእጃችንም በአንደበታችንም የተንቀረፈፈ የመሰለንን ሾፌር መስደብ፣መቆጣት፤ ከአስፋልት ወጥቶ በእግረኛ መንገድ መንዳት  ወዘተ ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ አልበረት ኤሊስ ይሞግታሉ “ያስጨነቀን ማርፈዳችን ነው ወይስ ስለ ማረፈድ ያለን አስተሳሰብና እምነት ነው?” አሳቸው እንደሚሉት፤ ውጤቱን የፈጠረው ማርፈዳችን(stimuls ) ሳይሆን ስለ ማርፈድ ያለን አስተሳሰብና እምነት ነው ባይ ናቸው፡፡
Dispute is the process of challenging the way we think about situations: ይኸኛው አስተሳሰባችንን የምንሞግትበት ዘዴ ነው። እሳቸው አግባብነት የሌለውን አስተሳሰብና እምነት መሞገት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስነውን ማርፈድ ብንወስድ እምነታችንን ስንሞግተው እንደሚከተለው ይሆናል፡፡ “ ብዙ ጊዜ በሰዓቱ የምገኝና ቀጠሮ አክባሪ የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡ አንድ ዛሬን ባረፍድ ተቀባይነቴን አያሳጣም”፣ “ለማርፈዴ ምክኒያት የሆነኝ የትራፊክ መጨናነቅና ያልጠበቅሁት የመንገዶች መዘጋጋት ነው፡፡ ስለዚህ በቂ ምክኒያት ሊሆን ይችላል፡፡” እነዚህን ምክኒያቶች በማሰብ ነባሩን ሃሳብ መሞገት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፤ አልበርት ኤሊስ፡፡
Effect: ይሄ አዲሱ ውጤት ነው። አስተሳሰባችንን ከሞገትነውና በአዲስ አስተሳሰብ ከተካነው በኋላ የሚፈጠር ባህሪ ነው፡፡ የላይኛውን ምሳሌ ብንከተል ተረጋግቶ መንዳት፤ ተራ መጠበቅ፤ በተፈቀደው አስፋልት መንዳት ወዘተ ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሃሳብ ስሜታችን እና ባህሪያችን ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሶቅራጠስን ቴክኒክ እንመልከት፡- የጥንቱ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጠስ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሚጠይቃቸውን  የሚከተሉትን አምስት ጥያቄዎች መጠየቅ ይጠቅማል፡፡
ተጨባጩ ነገር ምንድነው?  ስለዚህ ነገር ያለኝ የኔስ  የግል እሳቤ?
የግል እሳቤዬን  የሚደግፍ ማስረጃ አለ?
የግል እሳቤዬን የሚቃረን ማስረጃስ?
የአስተሳሰብ ስህተት ፈፅሜያለሁ?
ስለ ተፈጠረው (ስለ ተጨባጩ) ሁኔታ ምን ማሰብ አለብኝ?
ነገሩ የግል እሳቤን የሚያጠናክር ማስረጃ ካለው(ተ.ቁ 2.2) ለችግሩ መላ መፈለግ ያስፈልጋል። ከእምነቴ ተቃራኒ  ከሆነ(ተ.ቁ 2.3) መጨነቅ ለማያስፈልገው ነገር ጊዜዬን እያባከንኩ ወይም ለጭንቀት ውጤቶች ራሴን እየዳረግሁ ነው ማለት ነው፡፡ የሶቅራጠስ ቴክኒክ የነገሮችን ወይም የሁኔታዎችን ተፅእኖ የምንፈትሽበትና የእርግጠኝነት ምላሽን የምንፈልግበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዴል ካርኒጊ፤ አብዛኛው ሰው የሚጨነቀው ገና ባልደረሰብት ችግር ነው የሚል አስተሳሰብ ነበረው።
በመጨረሻም እንድ ማወቅ የሚገባን ነገር አለ፡- እንዳንድ ነገሮችንና ሁኔታዎችን መቆጣጠር እንችላለን። ይህንን ፅሁፍ ማዘጋጀትና አለማዘጋጀት በኔ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ከፈለግሁኝ አዘጋጀዋለሁ ካልፈለግሁኝ አላዘጋጀውም፡፡
ስለ ፈለግሁኝ አዘጋጀሁት፡፡ በአንዳንድ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች  ደግሞ ተፅእኖ መፍጠር እንችላለን ነገር ግን ልንቆጣጠራቸው አንችልም፡፡ ለምሳሌ በቡድን በሚሰሩ ስራዎች እርስዎ የሚያምኑበትን ነገር ተግባራዊ እንዲሆን የስራ አመራሩን ተፅኖ ሊፈጥሩበት ይችላሉ  እንጂ ውሳኔውን  በግልዎ ሊቆጣጠሩት አይችሉም። አንዳንድ ነገሮችን ደግሞ መቆጣጠርም ሆነ ተፅእኖ መፍጠር አይቻልም። ስለዚህ ሁኔታውን መቀበል ወይም በሁኔታው ውስጥ ውጤታማ ሆኖ ለመኖር መወሰን ነው የሚጠበቅብዎ፡፡ ለምሳሌ የእርስዎ የቅርብ ሰው በሞት ቢለይ ወይም ፈፅሞ እርስዎን ላለማግኘት ወስኖ ከእርስዎ መለየት  ቢቆርጥ የሚቀይሩት ጉዳይ ስላልሆነ መቀበል እንዲሁም በተፈጠረው ሁኔታ ውስጥ ራስን አዘጋጅቶ መኖር ያስፈልጋል።
 አብዛኛው ሰው መቆጣጠር የሚገባውን ነገር ለሌሎች ተፅእኖ አሳልፎ ሲሰጥ ወይም ተቀብሎ ሲኖር፣ ወይም ተፅእኖ ማሳደር የሚገባውን ነገር ለመቆጣጠር ወይም በቸልተኛነት ሲቀበለው እና ራስን አዘጋጅቶ መኖር የሚገባውን ወይም መቀበል ያለበትን ሁኔታና ነገር ለመቆጣጠር ወይም ተፅእኖ ለማሳደር ሲሞክር የጭንቀት ሰለባ የመሆኑ ዕድል የሰፋ ነው። ይህንን በአጭሩ ለማስታወስ በእንግሊዝኛው ምህፃረ ቃል CIA-Control-Influence-Accept/Adapt to ብሎ መያዝ ይጠቅማል፡፡
አንዳንዱን ነገር Control እናደርጋልን፤ አንዳንዱን influence  ነው የምናደርገውን አንዳንዱን ደግሞ Accept/Adapt to ነው ማድረግ የሚገባን፡፡
ቸር እንሰንብት
(ፀሐፊውን በሚከተለው የኢ-ሜይል አድራሻው ሊያኙት ይችላሉ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Saturday, 12 July 2014 12:21

የፖለቲካ ጥግ

አመፅን የመከላከያ አስተማማኙ መንገድ ጉዳዩን ከእጃቸው ላይ መቀማት ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
(እንግሊዛዊ ፈላስፋ፣ ፖለቲከኛና የህግ ባለሙያ)
እኔና ህዝቦቼ ሁለታችንንም የሚያረካ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ እነሱም ደስ ያላቸውን ይናገራሉ፤ እኔም ደስ ያለኝን አደርጋለሁ፡፡
ዳግማዊ ፍሬድሪክ
(የፕረሽያ ንጉስ)
ማንኛውም ምግብ አብሳይ አገሪቱን መምራት መቻል አለበት፡፡
ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን
 (የሩሲያ አብዮታዊ መሪ)
በምርጫ ለተሸነፉት ሁሉ አዝናለሁ፡፡ ፈፅሞ አይቼው የማላውቀው ተመክሮ ነው፡፡
ማርጋሬት ታቸር
(የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ስለ 1997 እ.ኤ.አ አጠቃላይ ምርጫ የተናገሩት)
ዲሞክራቶቹ እዚህ የሚመጡት ድምፃችንን ሲፈልጉ ብቻ ነው፡፡ እኛን ለመደለል ጣፋጭ አምጥተውልናል፡፡ ኮሙኒስቶቹ ቮድካ ያመጡልን ነበር፡፡ እነሱ የበለጠ ስኬታማ ናቸው፡፡
ጋሊና ዴኒሶቫ
(ሩሲያዎት የሱቅ ነጋዴ ለጎረቤቷ የተናገረችው)
የኮሚኒስት ፓርቲ አመራርን ለመቃወም የሚሞክር አዲስ ፓርቲ ከተቀረፀ እንዲኖር አይፈቀድለትም፡፡
ሊ ፔንግ
(የቻይና የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር)
ኮሚቴ አራት የኋላ እግሮች ያሉት እንስሳ ማለት ነው፡፡
ጆን ሊ ካሬ
(እንግሊዛዊ ደራሲ)
ሂትለርና ሙሶሎኒ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ቢሆን ኖሮ ዓለምን መምራት እንዴት ይቀል እንደነበር ብዙ ጊዜ አስባለሁ።
ሎርድ ሃሊፋክስ
(እንግሊዛዊ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን)
የትኛውም አገዛዝ ታላላቅ ፀሃፍትን ወድዶ አያውቅም፤ አነስ አነስ ያሉት እንጅ፡፡
አሌክሳንዳር ሶልዝሄኒትሽን
(ሩሲያዊ ደራሲ)
ሞራላዊም ሆነ መንፈሳዊ አፈጣጠሬ አምባገነን እንድንሆን አይፈቅድልኝም፡፡ አምባገነን ብሆን ኖሮ ብዙ ነገሮች ይከሰቱ እንደነበር አትጠራጠሩ፡፡
አውግስቶ ፒኖቼት
(የቺሊ ወታደራዊ አምባገነን የነበሩ)

Saturday, 12 July 2014 12:16

የፍቅር ጥግ

ሳይፈልጉ ታማኝ ከመሆን ይልቅ ጨርሶ ታማኝ አለመሆን ይመረጣል፡፡
ብሪጊቴ ባርዶት
(ፈረንሳዊ የፊልም ተዋናይና የእንስሳት መብት ተሟጋች)
አዎ፤ ትዳራችን ላይጠገን እስከመጨረሻ መፍረሱ ግልፅ እስኪሆን ድረስ ታማኝ ነበርኩ፡፡
የዌልስ ልኡል ቻርልስ
(ለሚስቱ ታማኝ እንደነበር ሲጠየቅ የመለሰው)
ከወሲብ የመታቀብ መርህ ስሜትን ማፈን አይደለም፡፡ ህይወትን ሙሉ በሙሉ ወደ አንድ ግብ መቃኘት እንጂ፡፡
ዲትሪች ቦንሆፈር
(ጀርመናዊ የሥነ-መለኮት ሊቅ)
እግርሽ እንደዛለ ይገባኛል፤ ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ በአዕምሮዬ ውስጥ ስትሮጪብኝ ነው የዋልሽው፡፡
ዊል ስሚዝ
(አሜሪካዊ ተዋናይና ዘፋኝ)
አባት ለልጁ ያዝናል፡፡ እናት ልጇን ይቅር ትላለች፡፡ ወንድም የእህቱን ሃጢያት ይሸፍናል፡፡ የሚስቱን (መስረቅ) መባለግ ይቅር ያለ ግን እንዴት ዓይነቱ ባል ነው?
ማርጋሬት ኦፍ ናቫሬ
(ፈረንሳዊ ፀሃፊና የሥነፅሁፍ ደጋፊ)
ትዳር ከያዙ ወንዶች ጋር አልተኛም ስል በትዳራቸው ደስተኛ ከሆኑ ወንዶች ጋር ማለቴ ነው፡፡
ብሪት ኢክላንድ
(ስዊድናዊ የፊልም ተዋናይ)
ብዙ ሴቶችን ተመኝቻለሁ፡፡ ለበርካታ ጊዜያት በልቤ ዝሙት ፈፅሜአለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ይቅር ይበለኝ፡፡
ጂሚ ካርተር
(የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)

Saturday, 12 July 2014 12:17

የፍቅር ጥግ

ሳይፈልጉ ታማኝ ከመሆን ይልቅ ጨርሶ ታማኝ አለመሆን ይመረጣል፡፡
ብሪጊቴ ባርዶት
(ፈረንሳዊ የፊልም ተዋናይና የእንስሳት መብት ተሟጋች)
አዎ፤ ትዳራችን ላይጠገን እስከመጨረሻ መፍረሱ ግልፅ እስኪሆን ድረስ ታማኝ ነበርኩ፡፡
የዌልስ ልኡል ቻርልስ
(ለሚስቱ ታማኝ እንደነበር ሲጠየቅ የመለሰው)
ከወሲብ የመታቀብ መርህ ስሜትን ማፈን አይደለም፡፡ ህይወትን ሙሉ በሙሉ ወደ አንድ ግብ መቃኘት እንጂ፡፡
ዲትሪች ቦንሆፈር
(ጀርመናዊ የሥነ-መለኮት ሊቅ)
እግርሽ እንደዛለ ይገባኛል፤ ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ በአዕምሮዬ ውስጥ ስትሮጪብኝ ነው የዋልሽው፡፡
ዊል ስሚዝ
(አሜሪካዊ ተዋናይና ዘፋኝ)
አባት ለልጁ ያዝናል፡፡ እናት ልጇን ይቅር ትላለች፡፡ ወንድም የእህቱን ሃጢያት ይሸፍናል፡፡ የሚስቱን (መስረቅ) መባለግ ይቅር ያለ ግን እንዴት ዓይነቱ ባል ነው?
ማርጋሬት ኦፍ ናቫሬ
(ፈረንሳዊ ፀሃፊና የሥነፅሁፍ ደጋፊ)
ትዳር ከያዙ ወንዶች ጋር አልተኛም ስል በትዳራቸው ደስተኛ ከሆኑ ወንዶች ጋር ማለቴ ነው፡፡
ብሪት ኢክላንድ
(ስዊድናዊ የፊልም ተዋናይ)
ብዙ ሴቶችን ተመኝቻለሁ፡፡ ለበርካታ ጊዜያት በልቤ ዝሙት ፈፅሜአለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ይቅር ይበለኝ፡፡
ጂሚ ካርተር
(የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)

Saturday, 12 July 2014 12:11

የጸሐፍት ጥግ

ሰው አንድ መፅሃፍ ለመፃፍ ግማሽ ቤተ-መፃህፍት ያገላብጣል፡፡
ሳሙኤል ጆንሰን
(የመዝገበ ቃላት አዘጋጅና ፀሃፊ)
ግሩም ህንፃ በጠዋት ፀሃይ፣ በተሲያት ብርሃንና በማታ ጨረቃ መታየት እንዳለበት ሁሉ፣ እውነተኛ ታላቅ መፅሀፍም በወጣትነትና በብስለት እንደገናም በስተርጅና ዕድሜ መነበብ አለበት፡፡
ሮበርትሰን ዳቪስ
(ካናዳዊ ደራሲና ሃያሲ)
ሁሉም ዓይነት መፃህፍት በሁለት ይከፈላሉ። የዘመኑ መፃህፍትና የምንጊዜም መፃህፍት በሚል፡፡
ጆን ሩስኪን
(እንግሊዛዊ የሥነ ጥበብ ሃያሲ፣ ፀሃፊና ተራማጅ)
 ዘመናትና ህዝቦች መፃህፍትን እንደሚፈጥሩት ሁሉ፣ መፃህፍትም ዘመናትንና ህዝቦችን ይፈጥራሉ፡፡
ዣን ዣኩዊስ አምፔር
(ፈረንሳዊ ፀሃፊና የታሪክ ምሁር)
የሚስቴ ወንድም ያልተለመደ የነፍሰ ግድያ ታሪክ ፅፏል፡፡ ሟች የሚገደለው ሌላ መፅሃፍ ውስጥ ባለ ገፀባህርይ ነው፡፡
ሮበርት ሲልቪስተር
(አሜሪካዊ ፀሃፊ)
ሰዎች በመፃህፍት ውስጥ ማንኛውንም ነገር ያሰፍራሉ፡፡ እኔ እምብዛም አንባቢ ባልባልም ይሄን ለማወቅ የሚያስችል በቂ ንባብ ግን አለኝ፡፡
ኮምፕተን ማኬንዚ
(እንግሊዛዊ ፀሃፊ)
አዲስ መፅሃፍ ሲታተም አሮጌውን አንብብ፡፡
ሳሙኤል ሮጀርስ
(እንግሊዛዊ ገጣሚና የስዕል ሥራዎች ሰብሳቢ)
ረዥም ልብወለድ ማንበብ ሲያምረኝ ረዥም ልብወለድ እፅፋለሁ፡፡
ቤንጃሚን ዲስራኤሊ
(የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትርና ፀሃፊ)
የዘመኑ እውነተኛ ዩኒቨርሲቲዎች መፃህፍት ናቸው፡፡
ቶማስ ካርሊሌ
(ስኮትላንዳዊ የታሪክ ምሁርና ወግ ፀሃፊ)
አንዳንድ መፃህፍት ከጫፍ እስከ ጫፍ በውሸት የተሞሉ ናቸው፡፡
ሮበርት በርንስ
(ስኮትላንዳዊ ገጣሚና የዘፈን ግጥም ደራሲ)

በተለያዩ ድረ-ገፆች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚያንሸራሽሩት ሃሳብ ይታወቃሉ፡፡ ስለ ኢትዮጵያኒዝም፣ ስለ ፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ምልከታዎችና ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተሰሚነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ምሁራን አንዱ ናቸው - ፕ/ር ማሞ ሙጬ፡፡ ሰሞኑን ጐንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 60ኛ አመት በዓል ሲያከብር  “Towards Innovative Africa: The Significance of Science, Technology, Engineering and Innovation for Sustainable Development” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በአሁን ሰአት በደቡብ አፍሪካ ሊዋኔ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ባለፈው ሳምንት በጐንደር ሳለ ከፕ/ር ማሞ ሙጬ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ምንድን ነው?
የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተጀመረው በአሜሪካ ነው፡፡ ከዚያ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ቅኝ ወደተያዙ የአፍሪካ ሃገሮች ተዛመተ፡፡ እነ ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ናይጄሪያ… ወደ መሳሰሉት ሃገሮች ነው የተስፋፋው። የመስፋፋት ማዕከላት የነበሩት ደግሞ ቤተ - ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ቤተ-ክርስቲያኖች የሃይማኖት አስተምህሮ ዘረኝነት ይደርስባቸው ነበር፡፡ ያንን እንዴት እንቃወመው ብለው ሲያስቡ ነው የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ የመነጨው፡፡ ነጮች ሲሰብኩ ጥቁሮችን የሠይጣን ምሳሌ፣ ነጮቹን የመላእክት አምሳል አድርገው ነበር። ነገር ግን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅስ ስታይ ነጮቹን የሚወክል ስም የለም፡፡ ኢትዮጵያ የጥቁሮች ሃገርን ብቻ ነው የሚጠቅሰው፡፡ እናም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲል እግዚአብሔር ጥቁሮችን ይሰማል ማለት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች ለተጨቆኑ የጥቁር ህዝቦች “ኢትዮጵያን ማኒፌስቶ” የሚል እ.ኤ.አ በ1820 አወጡ። እነ አሜሪካና ሌሎች የበለፀጉት ሃገራት የስጋ ምግብ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ግን የመንፈስ ምግብ ሰጠች ማለት ነው፡፡ በዚህ ከሁሉም ትበልጣለች፡፡ በአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴ የተቋቋመው በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መነሻነት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የእንቅስቃሴ አራማጆች በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የወደቁ ነበሩ፤ በዚህም ታስረዋል ተገድለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት በዘርና በቋንቋ የሚለካ አይደለም፡፡ ሰዎች የመጣባቸውን ችግር ለመቋቋም ባደረጉት ትግል፣ ባገኙት ውጤትና ስኬት ውስጥ ያለፈ ፍልስፍና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የብሄር ትርጉም ያለው አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነትን ከዘር ጋር :- ከአማራ፣ ከትግሬ ከጉራጌ ጋር ወዘተ ያያይዛሉ፤ ነገር ግን ይሄ የተሳሳተ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከትግል፣ ከስኬትና ከተገኙ የትግል ድሎች ጋር የተያያዘ ፍልስፍና ያለው ነው፡፡
ጥናትዎን ሲያቀርቡ፣ “ወደ ምዕራባውያኑ የሄደው ሁሉ የኛ ነገር ነው፤ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም” ብለው ነበር፡፡ ምን ለማለት ነው?
እኛ ሁሉም ነገር አለን፡፡ ቋንቋው፣ የስነ ህንፃ ጥበቡ፣ ስነፅሁፉ… ሁሉም አለን፡፡ ግን የራሳችንን ትተን ሌላውን ወደ መኮረጁ ገባን፣ ኩረጃ ጥሩ አይደለም፡፡ አወዛግቦናል። ሁሉንም ሚስጥራችንን የጥንት ኢትዮጵያውያን ተንትነው አስቀምጠውልናል፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ሚስጥር፣ የቀንና ሌሊት ሚስጥር የመሳሰሉት፡፡ በአቡሻከር እስከ 15 እና 22 ፕላኔቶ አሉ የሚል ተፅፏል፡፡ እኛ 9 ፕላኔቶች አሉ ተብለን ነው የተማርነው፡፡ አሁን ፈረንጆቹ 13 አድርሰዋቸዋል፡፡ እንግዲህ እኛ በመደበኛ ትምህርት ባንማረውም የቀደሙት ግን 22 ፕላኔቶች አሉ ብለው በአቡሻከር አስቀምጠዋል፡፡ አሁን እኔ ፕሮፌሰር ተብዬ በድጋሚ 13 ፕላኔቶች አሉ እየተባልኩ ልማር ነው ማለት ነው፡፡
ማንዴላ ከእስር ቤት ሲወጣ ነው ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው፡፡ ማንዴላ በወቅቱ ምን አለ አሉ? ለአቶ መለስ እና ለአቶ ኢሳያስ ስልክ ደውሎ “እንዴት አንድ ህዝብ ትከፋፍላላችሁ እኛ ከአውሮፓ የመጡ አፍሪካኖችንና ከአፍሪካ የተፈጠሩ አፍሪካኖችን አንድ እያደረግን፣ ለእናንተ አንድ የሆነውን ህዝብ እንዴት ትለያያላችሁ”? ብሏል ይባላል፡፡ በወቅቱም አቶ መለስ እና አቶ ኢሳያስ አንደኛቸው ፕሬዚዳንት አንደኛቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምክር ለግሷል፡፡ አገሪቱ ሳትገነጠል ማለት ነው፡፡  ግን አልተቀበሉትም፤ መከፋፈሉ መጣ፡፡
እኔ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስሄድ፣ አንድ ደስ ያለኝ ነገር ምርጫ ሲያደርጉ ማንም ይመረጥ ዋናው የምርጫው ሂደት ውጤታማ መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ወገን ተጠቃሁ አይልም፡፡ ለምሳሌ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መሪ ብዙዎቹ አይወዱትም ግን ምርጫው ከወገናዊነት የፀዳ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሂደት አምስት ጊዜ ሰላማዊ ምርጫ አድርገዋል፡፡ እኔ በዚህ በጣም  እኮራባቸዋለሁ፡፡ ነጮች ጥቁርን ሰይጣን ነው እንጂ ሰው አይደለም ይሉ ነበር፡፡ እነ ማንዴላ ያንን ችግር በግጭት ሳይሆን በእርቅና በሰላማዊ መንገድ ነው የፈቱት፡፡ አሁን ከአፍሪካ ሃገራት መካከል እነ ቻድ፣ ማሊ፣ ሊቢያ ሌሎችም በግጭት ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህ ሃገሮች የደቡብ አፍሪካን ፈለግ ተከትለው ችግራቸውን ቢፈቱ ህዝባቸው ምንኛ በታደለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ለግጭቶች መላ ሲፈለግ በመገዳደል ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ በመናናቅ፣ በመዘላለፍ፣ ባለመተማመንና በውይይት ቢሆን ሃገርን በማስበለጥ፣ በመረዳዳት፣ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና በመወያየት መሆን አለበት፡፡ እኛ የፈለግነው ወገን ሥልጣን ካልያዘ ሞተን እንገኛለን የሚለው አስተሳሰብ መለወጥ ይኖርበታል፡፡
በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ይካሄዳል? ከምርጫው ምን ይጠብቃል?
ምርጫው እግዚአብሄር ታክሎበትም ቢሆን ንፁህ መሆን አለበት፡፡ ንፁህ ከሆነና ያ ባህል ከተፈጠረ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካዎች ይሄን ማድረግ ችለዋል፡፡ በእነሱ እየቀናሁባቸው ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ዙማን ብዙዎች አይወዱትም፡፡ ኢኮኖሚያው ላይ ጥያቄ አለበት፤ ነገር ግን መርጠውታል፡፡ ዋናው ማን ተመረጠ የሚለው ሳይሆን ሂደቱን ሰው ማመን አለበት፡፡ ንፁህና እንከን የለሽ ነው ብሎ ከልቡ ሊቀበለው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ምርጫ አያስፈልገንም፡፡
የዳያስፖራው ፖለቲካ ለዚህች ሃገር ባለው ፋይዳ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?
ከቅንጅት በፊት እዚህ ሃገር መጥቼ ነበር፡፡ ገጠር ድረስ በበቅሎ ሄጄ አይቸዋለሁ፡፡ በወቅቱ የገጠሩ ሰው ሁሉ ስለምርጫ በሚገባ እንዳወቀ የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በጣም ደስ ይላል ብዬ ተስፋ አድርጌ ወደ መጣሁበት ተመለስኩ፡፡ ከምርጫው በኋላ ግን የሆነው አሳዛኝ ነው፡፡ በወቅቱም በፃፍኩት ፅሁፍ፤ እንዲህ ያለ እድል ተገኝቶ እንዴት እናበላሸዋለን ብዬ ተቆጭቻለሁ። ኢትዮጵያ አንዳች ነገር እንዳጣች ተናግሬያለሁ፡፡ በውጪ ሃገር የተለያዩ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ግን በጣም የተበጣጠሱ፣ በአንድነት ተቀናጅተው ሃይል መሆን ያልቻሉ ናቸው፡፡ በሃገራችን ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ማምጣት አለብን የሚለው አስተሳሰብ ቢዳብር ጥሩ ነው። እኔ ለኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ነው የምመኘው፡፡
በዳያስፖራው አካባቢ የከፋ ዘረኝነት ይራመዳል ይባላል፡፡ እርስዎም በፅሁፍዎ ይሄን ነገር በተደጋጋሚ ይገልፁታል፡፡ የዚህ የዘረኝነት አንድምታው ምንድን ነው?
አንድ ጓደኛ አለኝ፡፡ ከሱ ጋር ሆነን አንድ ጊዜ የብሄራዊ መግባባት መድረክ ፈጠርን፡፡ ሁሉንም ብሄሮች የብሄር ፖለቲከኞች ጠራን፤ ኦነግን ጨምሮ፡፡ ግን ለመወያየት ከባድ ነበር፤ ዘረኝነት አይሎ አስቸገረን። ዘረኝነታቸው የእውነት ይሁን የይስሙላ አላውቅም፡፡ እኔን “የግራዚያኒን ሃውልት ለምን ትቃወማላችሁ? የአፄ ምኒልክ እያለ” ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ ተናድጄ “እንዴት አፄ ምኒልክን እንደዚህ ትላላችሁ” ብዬአቸዋለሁ። አፄ ምኒልክ ለአፍሪካ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለአፍሪካውያን ድል የአፄ ምኒልክ እጅ አለበት፤ እሳቸውን ማጥቃት ማለት ጠቅላላ ኢትዮጵያን ማጥቃት ነው ብዬ ተቃውሜያለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ፅንፍ የያዙ አለመግባባቶች ይታያሉ፡፡ ግን ሰው ከዚህ ወጥቶ በውይይት መግባባትን ቢለምድ ጥሩ ነው፡፡ በአንድ የሆነ መላ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የዘር ፖለቲካ ብትወጣ ጥሩ ነው፡፡
ይሄ በቅርቡ እውን የሚሆን ይመስልዎታል?
አሁን እንግዲህ እዚህ የምትኖሩት ናችሁ ይሄን የምታውቁት፡፡ እኔ ውጭ ነው የምኖረው፡፡ ነገር ግን የዘር ፖለቲካ አይጠቅምም የሚለው አቋሜ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነት ብቻ ይበቃል፡፡ ወደ ታች ወርዶ በቋንቋ ምናምን መከፋፈሉ አያዋጣም፡፡ ዋናው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶቹ መጠበቃቸው ነው። ቋንቋ የሰውን ልጅ ሊከፋፍል አይገባውም፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ 11 ያህል ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት ይውላሉ፡፡ በእነሱ ዘንድ ቋንቋዎቹ ከመግባቢያነት ያለፈ ትርጉም የላቸውም፡፡ እኔ አሁን ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛ፣ አማርኛ… የሌሎች ቋንቋዎችን ሙዚቃዎችም ስሰማ ደስ ይለኛል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አማራ ብዬ ራሴን የምነጥለው፡፡ በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ማለት ምን ማለት ነው? እኔ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ መብቶች በሙሉ በህግ ጥበቃ ከተደረገላቸው በቂ ነው፡፡ እኔ አሁን ማሞ ሙጬ ነው ስሜ፡፡ አላውቅም አባቴ ኦሮሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ጎንደርን ለረጅም አመታት አስተዳድረዋል፡፡ ጎንደር ቤተ መንግስት ውስጥ ኦሮሚኛ ቋንቋ ይነገር ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍፁም የተደባለቀና የተቀላቀለ ነው፡፡
የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምን ያህል አፍሪካን ያስተሳስራል ይላሉ?
በዚህ አመት በፓን አፍሪካኒዝም ላይ መፅሃፍ ላወጣ እያዘጋጀሁ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነትም ባለፈ አፍሪካዊነት ላይ አስቀድመን ብንንቀሳቀስ ለእኛም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልድ ድል ነው፡፡ ህዝቡ የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሃሳብ ቢረዳ፣ ሌሎች አፍሪካውያን በፊት ከሚሰጡን ፍቅር የላቀ ፍቅር ይሰጡን ነበር፡፡ አሁን ያሉት ፖለቲከኞች በዚህ መንፈስ እንዲራመዱ እግዚሃር ይርዳቸው፡፡ ከዘረኝነት ወጥተው በኢትዮጵያዊነት እና በአፍሪካዊነት እንዲያስቡ እንፀልይላቸዋለን፡፡
በመንግስት በኩል ኢኮኖሚው እያደገ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ግን ዕድገቱ ህዝቡን ከድህነት አላወጣውም የሚል ትችት ይሰነዘራል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
በኢኮኖሚ እድገት ብሄራዊ ገቢን ማብዛት ብቻውን ጥቅም የለውም፡፡ ሰዎችን በማፈናቀል መሬት ለባዕድ በመስጠት የሚመጣ እድገት ጥሩ አይደለም፡፡ እድገት ማለት የህዝቡን ህይወት መቀየር ሲችል ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ካልተፈጠረ እድገት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ የህዝቡን ህይወት መቀየር መቻል አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ጥሩ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ማህበራዊ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች ይሄ ይጎድላቸዋል፡፡
ብዙውን ጊዜ በውጭ እርዳታ ላይ ስለሚንጠለጠሉ ያመኑበትን ፖሊሲያቸውን ትተው በለጋሾች ለመመራት ይገደዳሉ፡፡ ሌላው መኮረጅም ጥሩ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከቻይና መማር ያለብን እንዴት ጎበዝ እንደሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የራስን የቤት ስራ መስራት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ስንመለከት፣ አንድም ዜጋዋ መራብ አልነበረበትም፡፡   

“ሰዌን ሰንትዲ ጌለእዮ ኤኬቴስ” - የወላይታ ተረት

             ኒኮስ ካዛንትዛኪስ፤ “ዞርባ ዘ ግሪክ” የሚከተለውን ይላል፤ ሟቹ ዶክተር ዮናስ አድማሱ እንደተረጐመው:-  
ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት በአንድ ዛፍ ቅርፊት ሥር ሊፈለፈል የሚዘጋጅ አንድ የቢራቢሮ ሙጭ አፍጥጬ ስመለከት፣ ቢራቢሮዋ የተሸፈነችበትን ኮፈን ሰብራ ለመውጣት ቀዳዳ ስትቦረቡር አስተዋልኩ፡፡ ትንሽ ጠበቅሁ፣ ነገር ግን ጨርሳ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ስለፈጀች ትዕግስቴን ጨረስኩ፡፡ ከዚያም ትንሽ ጐንበስ ብዬ ሙቀት እንዲሆናት በማለት ተነፈስኩባት፡፡ የምችለውን ያህል በፍጥነት እየተነፈስኩ ሙቀት ዘራሁባት፡፡ ዓይኔ እያየ እዚያው አፍንጫዬ ሥር ታምር ሲሰራ ተመለከትኩ፡፡ እንደህይወት ቅጽበት፡፡
ኮፈኑ ተገለጠና ቢራቢሮዋ ቀስ እያለች መውጣት ጀመረች፡፡ ክንፎቿ ወደኋላ ታጥፈውና ጭምድድ ብለው ስመለከት መላ ሰውነቴን የወረረኝን ድንጋጤ ምን ጊዜም አልረሳውም፡፡ ምስኪኗ ቢራቢሮ ባላት ኃይል ሁሉ ሰውነቷ በሙሉ እየተንዘፈዘፈ ክንፎቿን ለመዘርጋት ሞከረች፡፡ እንደገና ጐንበስ ብዬ በትንፋሼ ልረዳት ሞከርኩ፡፡ ሙከራዬ ከንቱ ነበር፡፡ ቢራቢሮዋ መውጣት የነበረባት በዝግታ፣ ክንፎቿም መዘርጋት የነበረባቸው በፀሐይ ሙቀት በዝግመት መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ግን አልሆነም፡፡ ይረዳታል ያልኩት የኔ ትንፋሽ ቢራቢሮዋን ጊዜዋ ከመድረሱ በፊት፣ ክንፎቿም ጭምድድ ብለው የግድ ከኮፈኗ እንድትፈለፈል አድርጓት ኖሯል፡፡ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ለጥቂት ሴኮንዶች ከታገለች በኋላ መዳፌ ላይ ሕይወቷ አለፈ፡፡
ሸማ በፈርጅ እንደሚለበስ ዕውቀትም ፈርጅ ፈርጅ አለው፡፡ ከዕውቀትና ከተመክሮም በላይ ተፈጠሮ የራሱ ሂደት፣ የራሱ የላቀ የተለቀ እንዲሁም የጠለቀ መንገድ አለው፡፡ ከልኩ በላይ ሙቀት የተሰጣት ቢራቢሮ፣ ከልኩ በላይ ትንፋሽ የበዛባት ሙጭ ከተፈጥሮ ማህፀን ትላቀቅ እንጂ፤ ህይወቷን መቀጠል አልሆነላትም - ከተፈጥሮአዊ ጉዞዋ ቀድሞውኑ ተናጥባለችና ሁሉም የየራሱ ተፈጥሮአዊ ሂደት አለው - የየራሱም አቅም አለው፡፡ ስለሆነም በራሱ ሐዲድ ላይ እንጂ አንዱ በሌላው ሐዲድ ላይ አይሄድም፡፡ ዛሬ ሁሉም መንገዶች ወደ ሮማ አያመሩም፡፡ የተለያዩት መንገዶች ወደተለያዩ ከተሞች ይሄዳሉ እንጂ!
“”ቆሎ ለዘር፣ እንዶድ ለድግር አይሆንም” ይሏልና ሁሉን በቦታው ማዋል እጅግ ተገቢ ነገር ነው፡፡ በዓለም ላይ፤ በተለይም በፖለቲካ ትግል ውስጥ፣ ጊዜ የለየ፣ ቦታ የመረጠ ብቻ ነውና እግቡ የሚደርሰው፡፡
ጥበበኛ የፖለቲካ መሪ፣ ታጋይ፣ የሥራ ኃላፊ፣ የጐበዝ አለቃ ማስተዋል ካለበት ፍሬ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት የሮበርት ግሪን አስተያየቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በማናቸውም የሥልጣን ዘመን የሚያጋጥሙ “አምስት ዓይነት አደገኛ ሰዎች አሉ - በዓለም ላይ - ከእነዚህ ተጠንቀቅ” ሲል እንዲህ ይደረድራቸዋል :-
አንደኞቹ - ትዕቢተኛና ኩራተኛ ሰዎች ናቸው - ከነዚህ ዓይነቶቹ ራቅ፡፡
ሁለተኞቹ - ተስፋ - በሚያስቆርጥ ሁኔታ አደጋ ላይ ነን ብለው የሚያስቡ ስሜታቸው ስስና በቀላሉ ተሠባሪ ናቸው - ረዥም ጊዜ ራቃቸው፡፡ ሦስተኞቹ - እነ አቶ ጥርጣሬ ናቸው፡፡ እንደ ስታሊን ያሉቱ ናቸው፡፡ ሁሉ ሰው አጥፊዬ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ዒላማቸው ያደረጉህ ከመሰለህ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ አራተኞቹ - የረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታ ያላቸው እባቦች የሚባሉት ዓይነት ናቸው፡፡ አይቆጡም፣ በፊት ለፊት የሚያሳዩት የንዴት ባህሪ የለም - ያደባሉ፣ ያሰላሉ፤ ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡ ይበቀላሉ፡፡ ማሺንክ ናቸው፡፡ ከእንዲህ ያለው እባብ እጥፍ -ጥንቃቄ አድርግ፡፡ አንዴ ካቆሰልከው እስከመጨረሻው ተገላገለው - ከሱ ጋር ግማሽ መንገድ አትሂድ - ከእይታህ ውጪ አድርገው፡፡ አምስተኞቹ - ግልብ፣ የሚያደርጉትን አስበው የማያደርጉ፣ አብዛኛውን ጊዜ ዕውቀት - ጠገብ ያልሆኑ (Unintelligent) ናቸው፡፡ ከምታስበው በላይ የማይታለሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ከመጉዳቱ ወይም ከመበቀሉ ይልቅ የሚከፋው ጊዜህን፣ ጉልበትህን፣ ሀብትህን ከማባከኑም አልፎ ተርፎ ንጽህናህን ያጐድፍብሃል፡፡ በግልጽ አጥንተህ በግልጽ ፈትሸው፡፡
በሀገራችን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ችግሮች ለመላቀቅ በርካታ ጊዜ ጥያቄዎች ቢነሱም ባንዱ ችግር ላይ ሌላ እየጨመረ መፍትሔ እየራቀ መሄዱ ገሃድ ነው፡፡
ዕውቁ የሀገራችን ገጣሚና ፀሐፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በምኒልክ አንደበት “ችግሬን አላገኛችሁልኝም፡፡ ህመሜን አላወቃችሁልኝም፡፡ መድሃኒት አልኳችሁ እንጂ ለመከራዬ …አውጫጪኝ ምን ያደርግልኛል?”
እንዲሉ፤ ለችግራችን መድሃኒት ዛሬም በጋራ መፈለግ አለብን፡፡ የቃናችን፣ የልሣናችን፤ የቋንቋችን ህብር በአንድ ካልተቃኘ አገራችንን ከገባችበት አረንቋ ማውጣት ይከብደናል፡፡
“አንዱ ባለቀረርቶ፣ ሌላው ባለቄሬርሳ፣ ሦስተኛውም ያው ባለሽለላ ናችሁ፡፡ የሁላችሁም ውጤት በጠቅላላው ሲደመር፣ አንድ ባዶ ፉከራ ብቻ ነው ጩኸታችሁ፡፡ በኔ በምኒልክ ላይ ተቀያየራችሁብኝ እንጂ እናንተ ከቶም አልተቀየራችሁም፡፡ አንድ ናችሁ፡፡ ዛቻ፡፡ ማስፈራሪያ ብቻ…” ይላል፤ ያው ፀሐፌ- ተውኔት፡፡
ጩኸታችንን ቀንሰን ፍሬ የሚያፈራ ሥራ እንሥራ! በየጊዜው “በወደቀው ግንድ ላይ ምሳር ከማብዛት” የተለየ ነገር አገኘን ስንል፤ መልሰን ለጋውን ትውልድም ያላንዳች በሳል ጉዞ የምንረመርም ከሆነ፤ ሁለት ትውልድ ባንድ ጊዜ እናጣለን፡፡ ትውልድን ለማለምለም ገና ብርቱ ጥረት ይጠበቅብናል፡፡ ካለፈው እየተማርን መጪውን ካላሳመርን ውሃ - ወቀጣ ነው የሚሆነው፡፡ ከሁሉም ወገን “በፈት እየተለማመዱ ልጃገረድ ያገቧል”ን በቀና ትርጉሙ አይተን፣ “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” ካላልን ከልማታችን ጥፋታችን እንደሚበረክት ልብ እንበል!!

የኩባንያዋ ዓመታዊ ገቢ 5ሚ.ዶላር ነው

         ‘ሶል ሪበልስ’ የተባለው የጫማ አምራች ኩባንያ መስራችና ባለቤት የሆነችው ኢትጵያዊቷ የንግድ ስራ ፈጣሪ ቤተልሄም ጥላሁን፣ በታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ለአርአያነት የሚበቁ የአመቱ 10 አፍሪካውያን ወጣት ሚሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች፡፡
ፎርብስ ሰሞኑን ባወጣው ዝርዝር ከ39 አመት ዕድሜ በታች ያሉና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ቢዝነሶች ያሏቸው አፍሪካውያን በማለት ከጠቀሳቸው አስር ባለሃብቶች አንዷ የሆነችው ቤተልሄም፤ ከአስር አመታት በፊት ያቋቋመችው ‘ሶል ሪበልስ’ በአሁኑ ወቅት አምስት ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የ34 አመቷ ኢትየጵያዊት ቤተልሄም ጥላሁን ያቋቋመችው የጫማ አምራች ኩባንያ፣ ባህላዊውን የጫማ አሰራር ዘመናዊ መልክ በመስጠት በተለያዩ ዲዛይኖች የሚያመርታቸውን ምርቶቹን ወደተለያዩ የአለም አገራት በመላክ ከአመት ወደ አመት ትርፋማነቱን እያሳደገ የመጣ ሲሆን፣ ለ100 ያህል ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በአፍሪካ ውስጥ በሃያዎቹና በሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ሃብት ማፍራት መቻል፣ በእርግጥም አድናቆትና ሙገሳ የሚያስፈልገው ትልቅ ስኬት ነው ያለው የፎርብስ ዘጋቢ ሞፎኖቦንግ ኒስሄ፣ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ መሰል ስኬት ያስመዘገቡ 10 ተጠቃሽና ለአርአያነት የሚበቁ ሚሊየነሮችን በየአመቱ እየመረጠ ይፋ ማድረጉንም አስታውሷል፡፡
ፎርብስ መጽሄት ለአርአያነት የሚበቁ የአመቱ 10 አፍሪካውያን ወጣት ሚሊየነሮች በማለት ከመረጣቸው ተጠቃሽ ባለሃብቶች መካከል፣ ብቸኛዋ ሴት ቤተልሄም መሆኗን ከመጽሄቱ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በንግድ ስራ ፈጠራ መስክ ባስመዘገበችው ተጨባጭ ስኬት ፎርብስን ጨምሮ በተለያዩ ታዋቂ መጽሄቶች፣ በአህጉራዊና አለማቀፍ ድርጅቶች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና መገኛኛ ብዙሃን ስሟ በተደጋጋሚ በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሰው ቤተልሄም፣ በዘርፉ በርካታ ሽልማቶችን ለመቀበል ችላለች፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ በትራንስፖርትና በነዳጅ ምርት፣ በፋሽን ስራ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሮኒክ ንግድ፣ በቴሌኮም፣ በኮምፒውተርና በሌሎች የቴክኖሎጂ መስኮች ተሰማርተው ትርፋማ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የታንዛኒያ፣ የናይጀሪያ፣ የኬኒያና የደቡብ አፍሪካ ሚሊየነሮች ተካተዋል፡፡